አትሮኖስ
277K subscribers
110 photos
3 videos
41 files
448 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#ሰመመን


#ክፍል_ሰላሳ_አምስት


#ድርሰት_በሲሳይ_ንጉሱ

...“ እንዲያው ምን ምን ይላት ይሆን?እኔ እሱ ለሴት ልጅ የሚያወራውን ነገር ለመስማት እጓጓለሁ " ግን አንተ ባል
ከው ዐይነት አገጣጥሞኝ አያውቅም ። ”

“አጅሬ ምኑ ሞኝ ነው ላንተ የሚታየው ?!እሷን ሲያገኛት ቦታው ጭር የሚልበትን ጊዜ ጠብቆ ነው ።

“ ወይ ጉድ ! መቼም ፍቅር የማያሸንፈው ልብ የለም ”አለ እስክንድር በልቡ ። ስለ ድብርት የበለጠ ለማወቅ ጓጉቶ ነበር ። ሆኖም ጨዋታው በተዘዋዋሪም ቢሆን አንዳንድ የአቤልን ድርጊቶች እንደሚንካ ስለ ገመተ አርዕስቱን ለመለወጥ ፈለገ ሳምሶንም ይህንን ሁሉ ልብ ሳይል እንደ መጣለት ነበር የሚጫወተው ። እስክንድር ግን የአቤል ስሜት
እየተለዋወጠ እንደ መጣ በሥርቆት ከገጽታው ላይ አንብቦአል ድብርት የሴት ጓደኛውን ለማግኘት ጭር ያለ ጊዜ
መጠበቁ የአቤልን ስሜት ክፉኛ ነክቶታል እሱም ትዕግሥትን ለማየት የሚጠቀምባቸውን ጊዜያቶች ያውቃል ።

ስማኝ ላምሶን ! ግን ለምንድነው አንተ ብዙ ጊዜ ድብርትን የምትለክፈው ? ” በማለት እስክንድር አርዕስቱን አሸጋገረው
“ ለተንኮል አይደለም ። ግን የሚነፋነፍ ሰው መልከፍ እንዲሁ ደስ ይለኛል ። እንዴት ብዬ ላስረዳህ ? ለምሳሌ
ቀርቦ መናከስ የማይደፍር ውሻ በሩቁ እያፈገፈገ ሲጮህብህ እልሁን ለማስጨራረስ በዱላ እንደምትተናኮለው ዐይነት ነው ። ብቻ እንዲሁ ስለክፈው ደስ ይለኛል እንጂ ለድብርት መጥፎ አመለካከት የለኝም ለየት ያለ ተፈጥሮ ስላለው ያስገርመኛል ” አለና አሳላፊዋን ለመጥራት ጠረጴዛውን ጠበጠበ።

“ አቤት ! ምን ልታዘዝ? ” እያለች አንገቷ በንቅሳት የተዥጎረጎረ ሴት ከፊታቸው መጥታ ቆመች ።

“ ቢራ ድገሚን ሦስት ቢራ ! ” አላት ሳምሶን በዚያው ቁጡ ድምፁ

“ እኔ ይብቃኝ ! ” አለ አቤል "

“ አትቀልድ እባክህ ። አንቺ እኔ የማዝሽን አምጪ!” አለና ሳምሶን አሳላፊዋ ላይ ጮኸባት ።

"ጥርስሽን እንዳያወልቅ ” አለና እስክንድር በልቡ ሳቀ ።

“ እኔኮ ያንተም ተፈጥሮ ያስገርመኛል ” አለው እስክንድር ሳምሶንን
“ እንዴት ?”
“ አሁን ሚስተር ሆርስ ከአቤል ጋር ከታረቀ በኋላ ለምን ትዝትበታለህ ?”

“ አዎ ! የማታውቀው ነገር አለ እስክንድር እየዛትክ የምትተው ከሆነ ዛቻው ሲደጋገም ሰው ይንቅሃል ።ወንድ ከሆንክ አንዴ ማቅመስ አለብህ ። እንዲያውም አንተን ብዬ ነው እንጂ እሱን ልጅ አንድቀን ብሰብረው ደስይለኛል ። ከፈለገ የገዛ ጥርሱን ከመሬት አሰለቅመዋለሁ ።

“ጡንቻህን ፈትነኝ እያለ ያስቸግሃል መሰለኝ” አለና እስክንድር እየሣቀ ከእሱ መልስ ሳይጠብቅ ፡ “ ብቻ ያለንበትንም ጊዜ አትዘንጋ : ሀያኛው ክፍለ ዘመን ላይ ነን ” አለው ።

“ እና ? ” የብሽቀት ድምፅ ነበር ።

“ እናማ ስፖርተኝነትህን እወድልሃለሁ ። ይህችን በጡንቻ መመካትህን ግን ...

“ እንግዲህ አትልከፈኝ ፡ ልጠጣበት ! ” አለና ቢራውን ተጎነጨ

ሳምሶን ሌላ ሰው እንዲህ ቢናገረውም ካልተደባደበ በዋዛ እይላቀቁም ነበር ። ለእስክንድር ያለው ክብር ግን ብዙ ዓመት ከቆየ የልጅነት የአስተሳሰብ ተጽዕኖ የመጣ ነው ። የሠፈር ልጆች እንደ መሆናቸው መጠን ሳምሶን ስለ እስክንድር ብዙ ነገር ያውቃል ። እሱ ገና ልጅነቱን ሳይጨርስ እስክንድር በሠፈራቸው ውስጥ ስመ ጥር ጎረምሳ
ነበር ። እንዲህ እንዳሁኑ ከመስከኑ በፊት እናቱ በእስክንድር ያላዩት አበሳ የለም ። ከለውጡ በፊት ጸብ አሽትቶ ነበር
የሚፈልገው ። እስር ቤትን ቤቱ አድርጎት ነበር ። አንዴ ጸበኞቹ በቡድን ሆነው ከደበደቡት በኋላ ሆዱ ላይ በጩቤ
ወግተውት ለጥቂት ነው ከምት የተረፈው ከለውጡ በኋላ ደግሞ በወቅቱ በተፈጠሩት የፖለቲካ ድርጅቶች ሳቢያ
ያልቀመሰው፡ አበሳ የለም ። ችኩል ነበር ። ሰው አይገራውም ፣ ያየሁት አይለፈኝ የሚል ስሜት ያሸንፈዋል ።
የጀብደኝነት ስሜት ያጠቃዋል ። ትኩስ ኃያልነቱ፡ መንፈሱን ያቅበጠብጠዋል ። አሁን ግን በዕድሜም በብስለትም ሰክኖ
እንኳን ለራሰ ሌሎችንም ይመክራል ። ከአፍላነት ቅብጥብጥነት ጊዜው ይዞ የመጣውና አሁንም ያልተወው ነገር ቢኖር
የሲጋራ ሱስ ብቻ ነው። ይህ ሁሉ ሁኔታ በሳምሶን ላይ የሚኖረው ተጽእኖ ቀላል አይደለም። በፀጉሩ ኪንኪነት እየለከፈው ከእስክንድር ጋር መቃለድ የጀመረው እንኳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው።

አቤል እባክህ ተጫወት ይሄንን ተወው
አለ ሳምሶን እስክንድርን በመንቀፍ አይነት

“ እየሰማኋችሁ “ኮ ነው ? ” አለ አቤል በጨዋታቸው ውስጥ የቆየ ለመምሰል ጥርሱን በውሸት ብልጭ አደረገ።

ሐሳቡ በከፌል ወደ እነ ትእግስት ዘምቶ ነበረ። ፈተና ከጨረሰች በኋሳ ወዴት ትሔድ ይሆን ? አርፎ መተኛት ወይስ
ዙረት መውጣት ? እያለ ሲያሰላስል ነው የቆየው።ሁለተኛውን ጠርሙስ ቢራ ግማሽ አድርሶታል ። ከቻቻታው ጋር
ቢራው ሞቅ አድርጎት ውስጥ ውስጡን እየሰከረ መምጣቱ ይሰማው ነበር። የመጠጣት ልምድ ስለሌለው ጭንቅላቱ ቶሎ መረታት ጀምሯል ። ድፍረትም ተሰማው ማንንም ያለመፍራት ሃይነት ስሜት !

“ ለምን ሙዚቃውን አይቀይሩልንም ? ” ሲል ድምፁን አሰማ ። የእንግሊዝኛ ሙዚቃ ነበር አዳራሹን የሚነቀንቀው፤“ ማስቀየር እንችላለን ። የማን ክር ይደረግ ? ” አሉ እስክንድርና ሳምሶን በአንድ ድምፅ አቤል ከዝምታ ወደ
ተሳትፎ መምጣቱ ደስ አሰኝቶአቸው ነበር

•የ... የመልካሙ ተበጀ ክር ቢሆን
ይሻላል” አለ አቤል በተሰባበረ ድምፅ

እስክንድርም ሆነ ሳምሶን በፍጥነት የጠረጠሩት ነገር አልነበረም ። አሳላፊዋን ጠርተው ክሩ እንዲቀየር አዘዟዋት።

ባለቤትየዋ እሷ የመረጠችው ዘፈን ካልሆን እሺ አትልም ግን ልሞክርላችሁ ” አለች አሳላፊዋ ።

“ ንገሪያት ! ለምን እሺ አትልም ? ” አለና ሳምሶን አፈጠጠበት እሷ ዘፈኑን ልታዝዝ ስትሔድ አቤል ቀድሞ በልቡ
ያንጐራጉር ጀመር።

አረ መላ ምቱ ወዳጅ ዘመዶቼ
ዐይናፋር ሆኛለሁ ፡ ዐይናፋር አይቼ
ሰሳምታ አልሰጠኋት አላነጋገርኳት
በዐይን ብቻ እያየሁ አንድ ዓመት ወደድኳት።

ልቡ ይህን እያዜመ፥ ጆሮው የሚሰማው ግን ሌላ ሙዚቃ ነበር ቢጠብቅ ፥ ቢጠብቅ የተለወጠ ነገር የለም ጥቂት
ቆይታ አሳላፊዋ ተመልሳ መጣች።

የመልካሙ ክር የለም ብላለች ባለቤትየዋ ! ”

አቤል በሽቆ “ ገደል ግቢ በያት ! ” ከማለቱ ዐይኑ እንባ አቀረረ ። የሰው ስሜት የማይጠበቅበት ዓለም ! ባለቡና ቤቶች ፍቅረኛውን የሚያስታውስበትን ዘፈን አይከፍቱለትም "መምህራን ትምህርት ምን ያህል እንዳስጠላው አይረዱለትም ። ወላጆቹ ልጃቸው ከድህነት ቀንበር እንዲያላቅቃቸው
ይመኛሉ እንጂ እሱ ያለበትን ችግር አያውቁለትም ። ጓደኞቹ ብቸኝነቱን አይፈቅዱለትም ።

“ እሷ ከሙዚቃዋ ጋር ገደል ትግባ ! አንቺ ቢራ ድግሚን ” አላት ሳምሶን በሽቆ ።

“ኧረ ይብቃን ! ሰዓቱም መሽቷል የካምፓስ ፖሊሶች አያስገቡንም ” አለ እንክንርድ ኪሱን እየዳበሰ ።

አምጪልን እባክሽ እንጠጣው ዛሬ ካምፓስ ማን ይገባል? ” አለ ሳምሶን በሞቅታ ስሜት ።

“በይ እንግዲያው አንቺንም እንጋብዝሽ የምትጠጪውን ነገር ይዘሽ ነይ ” አላትና እስክንድር ፡ ወደ ሳምሶን ዘወር ብሎ ፥ “ ከጠጣን አይቀር መሐላችን አንዲት አንስታይ ስትኖር ይሻላል” አለው ። ከሳምሶን ሁኔታ ገንዘብ እንደያዘ
ገምቶ ነበር "

እቤል ምንም አስተያየት አልሰጠም ። የያዘውን ቢራም አልጨረሰም ። ከዚያ በላይ መጠጣት አልፈለገም ። ሆኖም
አልተከላከለም ። ሕይወትን የመሰልቸት ዐይነት ነበር የሚሰማው ። ለምንም ነገር ያለመጨነቅ ። ስካር ማለት ይሄ ይሆን እንዴ?
#ሰመመን


#ክፍል_ሰላሳ_ስድስት
;
;
#ድርሰት_በሲሳይ_ንጉሱ


እስክንድር በምልክት አሳየው ። በዚያ ሁሉ ጠጪ መሐል ሁለት እጁን እኪሱ አድርጎ ፡ ሁሉንም በንቀት ዐይን እየተመለከተ ነበር ወደ ሽንት ቤቱ የሔደው ።

“ ቢራዋ ሥራዋን እየሠራች ነው ” አለ እስክንድር የአቤል አረማመድ እያየ ።

“ ግን ምን ይሻለዋል ?” አለ ሳምሶን " በአቤል ሁኔታ በማዘን ' “ አሁን በማዕረግ የሚመረቅ ይመስልሃል ? ” እስክንድር ገርሞት ሣቀ ። የሳምሶን ጥያቄ ግን ከቅን
መንፈስ የመነጨ ነበር ። አቤል የሚወደውም የሚያከብረውም በማዕረግ ተማሪነቱ ነው ። የአቤል የማዕረግ ተማሪነት በዩኒቨርስቲው ውስጥ በብዙ ተማሪዎች ዘንድ ይታወቃል
እንደ እስክንድር ጠጋ ብለው የማያውቁት አሁንም የዓመቱ የፕሬዚዳንት የከፍተኛ የማዕረግ ሽልማት ከአቤል እጅ አይወጣም የሚል ግምት አላቸው ። ሳምሶንም የመኝታ ክፍል ጓደኛው ቢሆንም ቅሉ በትምህርት ያን ያህል መድከሙን አያውቅም ነበር ።

“ እውነቴን ኮ ነው ። ምን ያሥቅሃል ?”

ማዕረጉ ቀርቶ በዚህ ዓመት መመረቁ ራሱ ነው እኔን የሚያጠራጥረኝ” አለው እስክንድር " በኀዘን ስሜት ፊቱ
ተለዋውጦ።

“ ያሳዝናል ! ግን ምን ታረገዋለህ! ” አለና ሳምሶን "ቢራውን ከጠርሙሱ ውስጥ እየጨለጠ ፥ “ በነገራችን ላይ መውደቂያችንን እናዘጋጅ እንጂ ! መቼም ዛሬ ወደ ካምፓስ አንገባም” አለው ።

እስክንድር የሳምሶን ሐሳብ ገባሁ ፤አንድ ሴሚስተር ሙሉ ታፍኖ የቆየ ስሜቴ ተነሣ ነገር ግን ኪሱ አስተ ማማኝ አልነበረም ።

“ እኔጋ በቂ ገንዘብ የለማ ! ” አለው ልመና በተቀላቀለበት ድምፅ ከልብ ተዝናንቶ ።

አቤልም እሺ የሚል አይመስለኝም ። ከአሁን በፊት ውጭ እድሮ አያውቅም ።
“ ምን ትቀልዳለህ ? ጭራሽ ? እምልህ ...”
“ አዎ ፡ ከእኔ ጋር ስንተዋወቅ ይኸው አራት ዓመት አለን አንድ ቀንም ኣድርጎት አያውቅም ።

እንግዲያው ዛሬ ድንግሉን ማስወሰድ አለብን ? ”አለ ሳምሶን ተንኮልም የፍቅር ስሜትም እየተሰማው ።

“ እዩዬ ! ተው እባክህ ! ” አለ እስክንድር ' በተዘበራረቀ ስሜት ።

“ ምናለበት ? አንተ ደሞ ! እንዲያውም ሴት ከቀመሰ የዐይኑ ፍቅር ይለቀው ይሆናል ። ገንዘብ እንደሆን እኔ ይዣለሁ ብዬሃለሁ ።

እስክንድር የሳምሶን ሁኔታ ራሱ እንግዳ ሆነበት ። ሳምሶን አብዛኛውን ጊዜ በኪሱ በርካታ ገንዘብ ይይዛል ። ወላጆቹ ደኅና ገቢ አላቸው ። አባቱ በአንድ ኢንተርናሽናል ድርጅት ውስጥ በጥሩ ደመወዝ ይሠራሉ ። በእናቱ ስም ደግሞ
መስጊድ አካባቢ የሰዓት መሸጫ ሱቅ አላቸው ። ወላጆቹ ለሳምሰን በወር ተቆራጭ ካደረጉለት ሃምሳ ብር ሌላ
ሊጠይቃቸው ብቅ ባለ ቁጥር አንድ ወይም ሁለት ባለ አሥር ኖት ሳያሽጉት አይመለስም ። ታዲያ ሳምሶን ይህን ሁሉ ገንዘብ ሲይዝ " ለመጠጥ ማጥፋት አይወድም። የሱ ገንዘብ የሚያልቀው በምግብ ነው ። መብላት ፡ ስፖርት መሥራት ግንባታ ብቻ ! በዩኒቨርስቲው አቅራቢያ ካሉት ምግብ ቤት ባለቤቶች ውስጥ እሱን የማያዉቅ የለም ። ዛሬ ገንዘቡን ለመጠጥና ለሴት ለማውጣት መዘጋጀቱ ነው እስክንድርን ያስገረመ።

“ እንዴት ነው ? ዛሬ ግንባታው ቀርቶ ለማፍረስ ነው መሰል የታጠቅከው ” አለው እስክንድር እየሣቀ ።

“አንዳንዴ ያስፈልጋል እባክህ ! ”
አሳላፊዋ አራት ጠርሙስ ቢራ ይዛ መጣች አንዱ ለራስዋ መሆኑ ነው ።

ቢራ እዚሁ ጓዳ መጥመቅ ጀመራችሁ እንዴ ? "
አላት እስክንድር ፡ ከታዘዘች መዘግየቷን ለመጠቆም ።

“ ቆየሁ እንዴ?አንድ ሰካራም ይዞ ሲነተርከኝ ነው” አለች ፥ ቢራውን እየከፈተች ።

“ አንቺው መጠጥ አቅርበሽለት አንቺው፡ሰካራም ትይዋለሽ ? በይ ነይ በይ ” አለና ሳምሶን ፡ ዳሌዋ ላይ ቸብ አደረጋት ቸብታው ጠንከር ያለ ስለ ነበር ዳሌዋን ለበለባት።

“ እንደዬ ! ታዲያ ዱላው ምንድነው ? ” አለች ተቆጥታ ዳሌዋን በእጅዋ እያሻሸች

ዝም በይና ቁጭ በይ ! ከፈለግኩ ጥርስሽን ነው የማረግፈው አላት ሳምሶን እንደ ልማዱ ።

እስክንድር ነገሩ ማየሉን ሲያይ ተደናገጠ

“ ኧረ እባክህ ! የማነህ ሒድና የሚስትህን ጥርስ አውልቅ " የእኔን የብርቅነሽን አይደለም። ስለ ቢራው እንደሆን ኬረዳሽ ! ” ብላው የከፈተችውን ቢራ ጥላ ተነሣች ብርቅነሽ አምርራ ልትሔድ ስትል'እስክንድር እጅዋን
ይዞ አባብሎ አስቀመጣት ።

“ አንቺ ደሞ እረፊ እንግዲህ ። እሱ ለጠዋታ ያህል ነው የነካሽ
እየተመናቀረች ከሳምሶን ርቃ እስክንድር ጎን ተቀምጠች ። ሳምሶንም ጥርሱን እያንቀጫቀጨባት ነበር ። በማይ
ረባ ነገር ተለካክፈው የጎሪጥ መተያየታቸው እስክንድርን
አስገረመው ።

“ ሁለታችሁም ዕረፉ ፡ ይሄ ቡና ቤት ነው በሰላም ጠጥተን መጫወት ነው የምንፈልገው ”አላቸው : ከግንባሩ ኮስተር ብሎ ፥ ግን በሆዱ እየሣቀ ።

የእስክንድር ሐሳብ እነሱጋ ረግቶ አልቆየም ። በድንገት አንድ ሐሳብ አእምሮውን ወጋው ።አቤል ወደ ሽንት
ቤት ከሔደ ቆይቷል ፤ግን አልተመለሰም ። እስክንድር ልቡ መጥፎ ነገር ጠረጠረና ድንገት ከተቀመጠበት ተነሣ ።

ምነው ?” አለው ሳምሶንም ፡ በሁኔታው ተደናግጦ ።

“ ምንም አይደለም ፥ መጣሁ ” ብሎ እስክንድር ወደ ሽንት ቤቱ ሄደ ። አቅለሽልሾት ይሆናል በሚል ግምት ሳምሶን ነገሩን ቸል አለው ።

እስክንድር ከመጸዳጃ ቤቱ አጠገብ ሲደርስ አቤል እጁን በኪሱ እንዳደረገ ግድግዳ ተደግፎ ቆሞ ነፋስ ሲቀበል አገኘው። ዐይኑ በርበሬ መስሏል ።አላፊ አግዳሚውን በንቀት ዐይን ነው የሚመለከተው።

ቴክሱ ምነው ? ”አለው እስክንድር ፥ ደህና መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ"

“ ወረፋ ሆኖብኝ ነው እባክህ ! ”

“ የሽንት ወረፋ ? በል እንግዲህ ጠብቅ ። ምን ታረገዋለህ ? ” ብሎት እስንድርን ወደ መጣበት ተመለሰ ።አቤል አንድ አደጋ ደርሶቀታል የሚል ሥጋት ስለ ነበር፡ በሰላም በማግኘቱ ልቡ ተረጋጋ ። ምንጊዜም አያምነውም አንድ ቀን በራሱ ላይ የሞት ቅጣት ይፈርዳል የሚል ፍራቻ አለው።

ወደ መቀመጫው ሲምለስ ብርቅነሽና ሳምሶን ተስማተው ጎን ለጎን ተቀምጠው ሲያወሩ አገኛቸው ።

ታረቃችሁ እንዴ ? ”

“ ዱሮስ መች ተጣላን ? አንተ ደሞ ” አለችና ብርቅነሽ ጠየቀችው፡ ፡

ቀድሞውንም ጸበኞች የሚገባበዙት መሐላቸው ገላጋይ ሲኖር ነው ። ብቻቸውን ሲሆኑ አንደኛው ዐቅሙን
ዐውቆ ወይም ጥቅሙን ከጉዳቱ አመዛዝኖ ጸባዩን ያሳምራል ? አለ እስክንድር በልቡ ።

“ ያንን ነገር “ኮ ለብርቅነሽ ነገርኳት” አለው ሳምሶን' ዓይኑን እስክንድር ላይ ተክሎ "

የቱን ነግር ? ”

የአቤልን ነዋ ! በቃ እሷ ይዛው ትደር ።

ሳምሶን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መሆናቸውን አጫውቷት ከዚያው ቡና ቤት መኝታ እንድትይዝ ገንዘብም
ሰጥቷታል ።

“ አንተ ዛሬ የልጁን ድንግል ለማስወሰድ ታጥቀህ ተነሥተሃል ማለት ነው? ” አለ እስክንድር ጉጉቱ አስገርሞት እየሣቀ ።

“መሆን አለበት ብዬሃለሁ ። አድቬንቸር ነው
“ አንቺስ ? በነገሩ ተስማማሽ ? ” አላት እስክንድር ፊቱን ወደ ብርቅነሽ መልሶ።

ውይ በደስታ ነዋ ! እንዲያም ድንግል ወንድ ደርሶኝ አያውቅም ። ዕድሌ ሆኖ የተፈተነ ብቻ ነው የሚደርሰኝ።

ስትናገር ሣቅ ሃቅ ስለምትል የቀልዷን ይመስላል እንጂ ብርቅነሽ የምትናገረው የልቧን ነበር ። ወሲብ ጀማሪ ደርሷት
አያውቅም ። የልጅነት ባሏም ቢሆን ሁለተኛ ሚስቱ ነበረች ።ቡና ቤቱ ውስጥ የሥራ ጓደኞቾ፥ “ ዛሬ የአንዱን ጀማሪ ድንግል ወሰድን ” እያሉ ሲያወሩ ትቀናለች በዚህ ወሬ የተካነችው የቡና ቤቱ ባለቤት ነች የጥንት ዝናዋን ስታወራ ይሄ አርዕስት
#ሰመመን


#ክፍል_ሰላሳ_ሰባት


#ድርሰት_በሲሳይ_ንጉሱ

....“ ምናገባህ ? ሞዛዛ ?" ስትለው ድምጿ የብሽቀት ቅላጺ ነበረው ።

“እውነት ብርቄ ፥ ምን ያህል ጊዜ ሆነሽ?” አላት ሳምሶን?

"አራት ዓመት!”

"የአራት ዓመት የሥራ ልምድ ! ከሌሎቹ አንጻር ሲታይ ትንሽ ነው ” እላት ሳምሶን "

“ መላጣ ! ” አለችው ፡ ጭንቅላቱን በዐይኗ ቂጥ እያየችው ።

“ በአራት ዓመት ውስጥ ስምሽን ለመለወጥ አልሞክርሽም ? ”አላት እስክንድር ሲቀልድባት ፡ “ እዲስ የከተማ
ስም እንደ ራሄል ኤደን ማርታ ፡ ዓለም ከተሜ ለመሆን እ ? ”

“ሒድ'ደረቅ ! ”

ሒድ፡ደረቅ !ሒድ፡ደረቅ!ደረቅ ማርታ በቅናት ቅንድቧን እያርገበገበች ከፊቱ ድቅን አለችበት ። በሐሳቡ ቁመናዋን ቃኘ በሞቅታ መንፈስ እንደገና አለማት ፡ ኪሱ ባዶ ማለም ብቻ ! ማነጣጠር ብቻ !

"ሒድ ፡ ደረቅ የሴቶች የጋራ ፈሊጽ ” አለ በልቡ ።

የብርቅነሽ ጥሬነት አስገረመው ፡ ስትጫወት የባላገር ለዛ አላት ። ንቅሳቷ ባላገርነቷን ይመሰክራል የባላገር ስሟን
አልለወጠችም " እምብዛም የከተሜ ጭምብል አላጠለቀችም ግን ከሀገርሽ ለምን ወጣሽ ? ” አላት በድንገት ።

“ ሆሆይ !ጋዜጠኛ ነህ እንዴ ?”

ባልሆን ፥ ይህን ሥራ ምን አስመረጠሽ ፡ ማለቴ ነው ። ””

“ ዋ ! ወድጄን መሰለህ ? ግድ ሆኖብኝ እንጂ ” ከማለቷ ፊቷ የኀዘን ጭጋግ ለበሰ

“ ምነው ?እንዴ? ” አላት እስክንድር ስሜቷን ተከትሎ ስሜቱ እየዳመነ።

“ ባልተቤቴ ነው ለነዚ ያበቃኝ ! በሱ ምክንያት ነው ሀገሬን ለቅቄ የወጣሁት እያለች የታሪኳ ዳር ዳር ጨረፈችው
በፍቅር ለቀረባት ሁሉ ታሪኳን ታወራለች
ልስ ልስ ሆኖ ለቀረባት የአንጀቷን ትዘከዝካለች የተማረ መስሎ ለታያት ችግሯን አፍረጥርጣ ትናገራለች ። መፍትሔ ይገኝልኛል ብላ አይደለም :: የውስጧን ተንፍሳ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የመንፈስ እረፍት ታገኛለች።

«« እባክሽ አታጓጊን ፣ በደንብ አጫውቺን" አላት እስክንድር ታሪኳን ለመስማት ተጣድፎ።

“ አያችሁ እናንተ ዕድለኞች ናችሁ : ከደኅና ቤተሰብ በመወለዳችሁ ወይም ከተማ በማደጋችሁ ለመማር በቅታችሆል እኔ የቀለም ትምህርት የለኝም ማንበብና መፃፍ እንኳ የቻልኩት አሁን የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ ከተጀመረ ወዲህ ነው።
የድሀ ገበሬ ልጅ ነኝ ። ያውም በእንጀራ
እናት ያደግኩ !ህም እቴ! ታድያ በአሥራ አራት ዓመቴ ተዳርኩ ። ባሌ ገበሬ ነበር ። እኔ ሁለተኛ ሚስቱ ነኝ ።የመጀመሪያ ሚስቱ ከተጋቡ መንፈቅ እንኳ ሳይሞላቸው ሞታበት ነበር ። ወላጆቼም ሲድሩኝ ይህን ያቃሉ በእድሜ በሰል ያለ ነው ። ጸባዩም ጥሩ ነው ለትዳሩ ታታሪ ነው ” ተባለና ተሰጠሁ ።

“ ጎጆአችንን እያሞቅን ፡ የባላባቶችን ግልምጫና ዱላ በጋራ እየተቀበልን መኖር ጀመርን ፡ ምን ይሆናል ። እግዜር ለትንኮሉ ማሕፀኔን ድፍን እደረገው። ዓመት ጠበቅን ሁለት ዓመት ጠበቅን ልጅ የለም ። በእኔና በባልተቤቴ መሐል ቅሬታ መጣ ያም ሆኖ አልተቃቃርንም ። ድህነት ያስተሳስረን ነበር ። እሱ ከገበሬዎቹ ጋር ውጭ ደክሞ ውሎ ሲመጣ ከቤት ያለሁ
ረዳቱ እኔው ነበርኩ በባላባት ጅራፍ ጀርባው ቆስሎ ሲመጣ አንጀቴ እየተንሰፈሰፈ የማለቅስላት እኔ ነበርኩ ዋ! እቴ ምን ያደርጋል!

እንዲህ እንዲህ እያልን አምስት ዓመት ያህል እንደኖርን አብዮቱ ፈነዳ ። ለውጥ መጣ ። ደክመን ለባላበት መገበሩ ቀረ። እፎይ አለን ። ቤታችን ሙሉ ሆነ እውነቴን ነው ደህና ነገር መብላት መልበስም ጀመርን ። ምን ይሆናል ። ከድህና
ኑሮ ጋር ተያይዞ ነገር መጣ ባልተቤቴ ሌላ ሴት ጋር በስርቆት መሔድ ጀምሯል የሚል ወሬ ሰማሁ ። ስውል ሳድር እኔም
ነገሩን ደረስኩበት። እንዲያውም አንድ ልጅ እንደ ወለደችለት አረጋገጥኩ ። ቀናሁ ! ቅናት አንገበገበኝ ። በሐሳብ
ተብከነከንኩ። ጨስኩ ።ቤት ውስጥ !
መቀመጥ አቃተኝ ብዙም ሳልቆይ ጓዝ ምንጓዝ ሳልል በርሬ ወጥቼ አዲስ አበባ ገበኋት !

“ እዚህ ስደርስ ደግሞ ያዘጋጀሁት ማረፊያ የለኝ ፥ እንደሁ ሜዳ ቀረሁ ። ትንሽ ቀን ሰንብቼ በደላላ አማካይነት
ግርድና ተቀጠርኩ። ስድስት ወር እንደ ሰራሁ ግርድናን እርም ብዬ ተውኩት። አባስኩ እቴ ! የሰው ቤት ሹሮ ሲያልቅ
እኔ ላይ ማፍጠጥ ። ዕቃ ሲጠፉ እኔን መወንጀል ። ምነው ከዚህ ሁሉ ሥጋዬን ሸጨ ባድር አልኩና ሽርሙጥና ጀመርኩ
እላችኋለሁ ።

ብርቅነሽ ስትናገር ታላቅ ማዕበል ተነሥቶ ባሕር ውስጥ የከታቸውን ያኸል ሥስቱም ጸጥ ብለው ነበር ። አሳዘነቻቸው። ምስኪን ጥሬ ፍጥረት ! በመጠጥ ሞቅታ ኃይል ለሁሉ ነገር ግዴለሽ ሆኖ የቆየው አቤል እንኳ፥ ከብርቅነሽ አፍ የድህነት ድምፅ ሲሰማ ቸል ማለት አልቻለም ። ሕዋሳቱ በኀዘን ስሜት ተወራጩ ::

ግን ዝዎም ብለሽ ከምትኮበልይ ፥ ሰላምን በአካባቢሽ በሚገኘው የሴቶች ወይም የገበሬ ማኅበር አመልክተሽ መፍ
ትሔ ኣትፈልጊም ነበር ? ” እላት እስክንድር ፡ ከማዘኑ የተነሣ የሚናገረው ጠፍቶት ።

ዋ እቴ ! ቤት ከፈረሰ ወዲያ ሁሉስ ምን ሊበጅ ? አየህ ፡ ቅናት ከመጣ ቤት ፈረሰ ማለት ነው። ለሁሉም እኔ ለማንም አላማከርኩ ። የሚያለቅሱ ልጆች የሉኝ ' ነጠላ ሰው ምናለበት አልኩና ብር ብዬ አዲስ አበባ ፣ ”

ታዲያ ባልሽ ሊፈልግሽ አልመጣም ” አላትአቤል በሁኔታዋ ስሜቱ ተነክቶ ።

“ ውእእይ • ሥራ አጥቶ ! እንዲያውም ከዚያ ሀገር ለንፀግድ የሚመላለሱ ሰዎች እዚሁ ቡና ቤት አግኝቼ ሲነግሩኝ' ውሽማውን ጠቅልሎ ይዟል አሉኝ • እዩዬ ! ” ብላ ሳትጨርስ ጥሬ ሰማች «

“ ብርቅነሽ ? ! አንቺን'ኮ ነው ? ” የቡና ቤት ባለቢቷ ድምፅ ነበር
“ እመት ! ወይ ጕዱ ዛሬ ! ” እያለች ብርቅነሽ ከተቀመጠችበት ተነሣች

“ እንድዩ ! ሰው ሲገባ አትታዘዥም እንዴ! ምን ይጎልትሻል ? ”

ብርቅነሽ የውስጧን ተንፍሳ ቃጠሎዎን አብርዳ ተነሣች ፡ እስክንድር ተከዘ ቃጠሉዋ ወደ እሱ ተላለፈበት ኀዘኗ ጠልቆ ወጋው ። ቅናት ተፈጥሮአዊ ነው ሀብታምና ድሀ አይልም ። የወደደ ሁሌ ለወደደው ነገር ይቀናል ። ለቀናበት ነገር ይሠዋል ። ብርቅነሽ የቅናትን እሳት ሸሽታ ኮበለለች ። ከቅናት ሸሽታ ሴትኛ አዳሪ ሆነች "

እስክንድር ሐሳቡ ከግላዊነት ወደነማኅበራዊነት መጠቀ ለእሱ ሲጋራ መግዣ መስጠት ያቃታቸው ደሀ እናቱ ላይ ሆኑ፡ሕዝቧን በሰፊው ማስተማር ' በቂ ኢንዱስትሪ ከፍታ እነብርቅነሽን ማሠማራት ያልቻለች ረሀብን ለማጥፋት
ማይምነትን ለማጥፋት ርካሽ ልምዶችን ለማስወገድ በባህል ለማደግና የቴክኖሎጂ ውጤት ተጠቃሚ ለመሆን የልጆቿን እጅ የምትማጠን እናት ሀገር፡እጆቿን ዘርግታ በሐሳቡ ታየችው
ከሐሳቡ ፋታ አግኝቶ እሱነቱን ወዳለበት ሲመልስ ምሶን ዐይኑን አፍጥጦ ተመለከተ ።አስተያየቱ አላማረውም ። በልቡ ምርምርህን እዚያው ዩኒቨርስቲው ውስጥ አድርገው ፥ ይሄ መጠጥ ቤት ነው የሚለው መሰለው "
#ሰመመን


#ክፍል_ሰላሳ_ስምንት


#ድርሰት_በሲሳይ_ንጉሱ

....በማግሥቱ ጠዋት ከቀጠሮው ሰዓት ቀድሞ ጆሊ ባር የተገኘው እስክንድር ነበር። ያደረበት ቤት ስላልተስማማው
በሌሊት ነበር ሾልኮ የወጣው ። የቤቱ አለ መስማማት ብቻ ሳይሆን የሰው ዐይን ፍራቻም ነው “ አላሁ አክብር” ሳይል ያስወጣው ። የገዛ ኅሊናው ዐይን ሲያለቅስ እንባውን አድርቆ ሲልከሰከስ እያደረ ' የሌሎችን ዐይን ለምን እንደ
ሚፈራ ሁሌም ይገርመዋል ። ባደረበት ቤት አንግቶ፡ ተዝናንቶ ቆይቶ አያውቅም ።

ይህን ልምድ ከየት ይሆን የቀዳነው ? ” ሲል አሰበ በዩኒቨርስቲው ውስጥ በትምህርት ወራት ቀለም ላይ ተደፍቶ
መክረም ፡ በዕረፍት ሳምንታት ደግሞ ኪስ እስከ ተቻለ ድረስ በአልኮል ማበድና በየበረንዳው ማደር ፈሊጥ እየሆነ መምጣቱ ነበር ያሳሰበው ። በዛሬው ዕለት እንኳ እንደ እሱው የሰው ዐይን እየፈሩ ከያደሩበት በረንዳ በሌሊት እየተሾለኩ " ጸጉራቸው እንደ ተንጨፈረረ ወደ ካምፓስ ቢሮ ያያቸው ተማሪዎች ቁጥር ትንሽ አልነበረም ።

ሁኔታው በትምህርት ተጨንቆ የከረመን አዕምሮ የማዝናናት አዝማሚያ ይመስላል” ሲል ሐሳቡን ቀጠለ
“ ታዲያ ከሰው ዐይንም ; ከዛ ኅሊናም የማይሸሹበት ሌላ መዝናኛ መፍጠር አይቻልም ወይ ? ተማሪው ከተባበረ ከፈተና በኋላ ባለው የዕረፍት ጊዜ ውስጥ እንደየዓቅሙ ገንዘብ አዋጥቶ ' የሙዚቃና ሌሎች የተለያዩ ትርኢቶችን እንዲሁም አዝናኝና አነቃቂ ውድድሮችን ማዘጋጀት፥ በቡድን ሆኖ ከከተማ ወጣ እያሉ ብርቅና ድንቅ ቦታዎችን መጐብኘትና የመሳሰሉት ልምዶች ቢዳብሩ ጤናማ መዝናኛ ይሆኑ
ነበር ። ታዲያ ይህን በጐ ተግባር ለማስተባበር የግንባሩን ቦታ ማን ይውሰድ ? ?

በራሱ ሣቀና ሲጋራ ለመፈለግ ኪሱን ይደባብስ ጀምር ትላንት ማታ ሌላ፡ ዛሬ ጠዋት ሌላ መሆኑ ነው ያሣቀውም
የአንድ ሰው ሁለት ልክ ? አለ በልቡ።

ሣቁ ከፊቱ ላይ ሳይጠፋ ሳምሶን ጉልቤው ደረሰ። ፊቱን ጭፍግግ አድርጐታል • እሱነቱ አስጠልቶት ራሱን የሚጥልበት ቦታ ያጣ ሰው ይመስላል "

“ ታድያስ ? ” አለው እስክንድር ፈገግ እያል ።

ሳምሶን አፉ መናገር እንዳቃተው ሁሉ “ መቼም አልሞትኩም ! ” በማለት ዐይነት አፍንጫውን አጣሞ አንገቱን ወደ ግራ አዘነበለ እጆቹን ኪሶቹ ውስጥ እንደ
ከተተ ሊቀመጥ ሲል ሱሪው የመተርተር ድምፅ አሰማ።

“ እናትክን ! ” አለው ሱሪውን ።

ጥርሳም እንዳትለው ሱሪው ጥርስ የለው አለና እስክንድር ቀለደበት ።

ሳምሶን ፈገግም አላለም "ቢኮረኩሩትም የሚሥቅ አይመስልም

“ ምነው ደበረህ ?” አለው እስክንድር ሣቁን እየዋጠ ።
“ ምን እባክህ ነጭ ናጫ ሴት ነች የገጠመችኝ፡እንዲሁ ስንበጣበጥ ነው ያደርነው "

አይዞህ አንድ ነን ። እኔም ቀዝቃዛ አሮጌት ይዤ ነው ያደርኩት መጠጥ ምን የማይሠራው አለ? ብቻ አትፍረድባቸው ። የእንጀራ ጉዳይ ሆኖባቸው ነው እንጂ ሰልችቶቸዋል "

“ ጥርሳሞች ! ” አላቸው ሳምሶን በልቡ ። ከእስክንድር ጋር መከራከርም መጫወትም አልፈለገም ። መላ ሰውነቱ
ደክሞአል " ለመፍታታት ያህል እንኳ የጠዋት ስፖርት አልሠራም። ሕይወትን የመሰላቸት ስሜት ተሰማው ፡ ፊቱን
በመስታወት ባያየውም በስሜቱ ጠውልጎ ታየው ። የጠጣበትን ቡና ቤት ያጠጣውን ገንዘብና አብሯት ያደረችውን ሴት በልቡ እየረገመ ጠረጴዛውን በቡጢ ደበደበ "

“አቤት!ምን ልታዘዝ?” ሲልአሳላፊው ከተፍ አለ ።
"አንድ ጠርውስ ቀዝቃዛ አምቦ ውሃ ”
“ አዎ ጎሽ ፡ የተቃጠለ አንጀት ለማራስ” አለ እስክንድር ተደርቦ ።

አምቦ ውሃው ቀርቦላቸው እየጠጡ በመጫወት ላይ ሳሉ አቤልን በውጭው መስተዋት በኩል አዩት። ከኋላው
የሚያባርሩትን ያህል በፍጥነት ነበር ወደ እነሱ የሚገሰግሰው ። የእስክንድርና የሳምሶን የተደበረ ስሜት አቤልን
ሲያዩ ተነቃቃ ። ወሬውን ለመስማት አጠገባቸው እስኪደርስ ተቻኮሉ። እሱም ከውጭ ሲያያቸው ዐይናቸውን አፍሮ
በሆዱ አቀርቅሮ ነበር የተጠጋቸው» ማታ በቅዠት መልክ የሰማውን “ ብር አምባር ሰበረልዎ ” አሁን ለቱ ሰበውን የሚሉት መሰስው ።

“ እህሳ ? ሌሊቱ እንዴት ነበር ? ” አለው ሳምሶን' ቀድሞ ሊጨብጠው እጁን እየዘረጋ።

ጥሩ ነበር” አለ አቤል ሁለቱንም ከጨበጣቸው በኋላ ጠርሙሱ ውስጥ የተረፈውን አምቦ ውሃ በብርጭቆ
እየቀዳ ። ጠጥቶ እንደ ጨረሰ በእርካታ ተንፍሶ፡ “እንሒድ እባካችሁ ” አላቸው ።

"ቁጭ በልና ተጫወት እንጂ ” አለው ሳምሶን ለወሬው ጓጉቶ ። አቤል ግን መቀመጥ አልፈለገም ። ወደ ካምፓስ ለመሔድ ቸኩሎአል ። በዩኒቨርስቲም ግቢ ውስጥ አንዳች ነገር ጥሎ ያደረ ይመስል ልቡ ተሰቅሎአል ። እስክንድርም ይህን ስሜቱን ስለ ተረዳለት ለመሔድ ተነሣ።

ወደ ስድስት ኪሎ ሲጓዙም ሳምሶን ከእቤል የመስማት “ጥማቱ እንደ ቀጠለ ነበር ። በዝምታ ትንሽ እንደ ተራመዱ "

“ ታዲያስ ፡ እንዴት ነበር ? ” ሲል ይጠይቀዋል የሴት ተግባሩን አስጐልጉሎ ለማናዘዝ በሚጥር ጥልቅ ስሜት ።

“ ደኅና ነበር ይላል አቤል ነገሩን ቸል ብሎ ለማሳጠር በሚጥር ስሜት ። ሳምሶን በዚህ መልስ አይረካም

"ብርቅነሽ እንዴት ነች ? ” ሲል ደግሞ ሊያወጣጣ ይሞክራል ።

“ ብርቅነሽ ጥሩ ሴት ነች” ሲል አቤል ነገሩን በአጭሩ ይደመድመዋል ።

አቤል ከብርቅነሽ ጋር ምን ዐይነት የመጀመሪያ ሌሊት እንዳሳለፈ ለመስማት ሳምሶን ብቻ ሳይሆን እስክንድርም
ጓጉቶ ነበር ። የብርቅነሽ ጥሬነት ፡ ግልጽነትና ጣፋጭነት ሳያስቡት በሁሉም ልብ ውስጥ ግልጽ ያልሆነ የፍቅር
ስሜት አሳድሮባቸው ነበር። ያም ሆነ ይህ፡ አቤል እንደ ጠበቁት በሰፊው የሚያወራላቸው አልሆነም ። ጓደኛሞች እንዲህ ዐይነት ሌሊት አሳልፈው ጠዋት ሲገናኙ ስለ አዳራቸው ሁኔታ ወይም አብረዋት ስላደሩት ሴት ማውራት
የተለመደ ቢሆንም ፥ ለአቤል እንግዳ ነገር ነበር ። ስለ አዳሩ እንዳይናዘዝ የፍረትና የቁጥብነት ስሜት ኅሊናውን
ጨምድዶ ያዘው ።

ብርቅነሽ የትዕግሥትን ቦታ ባትወስድም በአቤል ልብ ውስጥ የተወሰነ ዳርቻ ይዛ ነው ያደረችው ። ለወሲብ የመጀመሪያ ሴቱ በመሆንዋ ብቻም አይደለም ። እስዋም ራስዋ ሁኔታውን በማየትና ሳምሶን የነገራትን በማገናዘብ
ለአቤል ቀና ስሜት ስለ ነበራት በባነነ ቁጥር አብራው ስትባንን ነው ያደረችው ። የልቧን አጫውታው የልቡን ምስጢር ወስዳለች ። ግልጽነቷና ፍቅራዊ መስተንግዶዋ አስገድዶት አቤልም ስለ ትዕግሥት ሲያጫውታት ነው ያደረው።
የትዕግሥትን ጉዳይ ለብርቅነሽ ግልጽ ማውጣቴ የቆረቆረው ጠዋት ከተለያት በኋላ ነው ። በግትርነት ተወጥሮ የነበረው መንፈሱ እየላላ መምጣቱ ለራሱም ተሰማው ። ምስጥሬ ብሎ ደብቆ የያዘውን የትዕግሥትን ነገር በመጀመሪያ ለሐኪሙ ፡ በትላንቱ ምሽት በመጠጥ ኃይል ለእስክንድር ሌሊቱን ደግሞ ለብርቅነሽ መናዘዙን ሲያስታውስ የመንፈሱ መላላት ታወቀው ።

ሳምሶንም ሆነ እስክንድር የጓጉትን ያህል ሳያወራቸው ከዩኒቨርስቲው በር ደረሱ ። ግቢው ጭር ብሎአል ።ለወትሮው ቢሆን ይህ ሰዓት ወደ ትምህርት ክፍል መግቢያ ጊዜ በመሆኑ መራወጥ ይታይበት ነበር።ዛሬ ግን ገና ከእንቅልፉ ያልተነሣም ኘለ ። የሚነቃነቅ ተማሪ አይታይም ።

እነ አቤል ግቢ ውስጥ ከገቡ በኋላ፥ወደ መኝታ ቤታቹኑ የሚወስደውን ጠምዛዛ መንገድ ሲይዙ አራት ልጃገረዶች
ከሩቅ ተመለከቱ ። ልጃገረዶቹ ሻንጣ ሻንጣቸውን ይዘው ከግቢው በመውጣት ላይ ነበሩ ። ሦስቱ፡ ልጃገረዶች እነማን
እንደሆኑ ሦስቱም ወንዶች ከመቅጽበት ለዩኣቸው ትዕግሥት፡ ማርታና ቤተልሔም ነበሩ ። ሁሉም ያላወቋት አንዷ ልጃገረድ የቤቴልሔም የመኝታ ክፍል ጓደኛ ነበረች
አቤል ደነገጠ
#ሰመመን


#ክፍል_ሰላሳ_ዘጠኝ


#ድርሰት_በሲሳይ_ንጉሱ

ጊዜ መደፊት አይገፈትርም።ጊዜ ለሰው ጭንቀትም ሆነ ደስታ ደንታ የለውም።
የራሱን ሥርዓት ጠብቆ የሚጓዘው፤ያለፈ ጊዜ አይመለስም ፤የወደፊቱ ደግሞ እንደ
ፈለግጉት ፈጥኖ አይመጣም። ሰው በጊዜ ቁጥጥር ሥር ነው እንጂ ጊዜ በሰው ቁጥጥር ስር አይደሉም ሰዓት ሰው ሠራሽ ነገር ነው ፤ ሞላውን በማዞር ካለበት ሰዓት ወይም ደቂቃ ማስቀደም ይቻላል ። የቀን መቁጠሪያም ሰው ሠራሽ
ነገር ነው ፤አንዱን ወር አልፎ ሌላውን ወር ማየት ይቻላል ።ቀንን ገፍቶ ማስመሸት፣ ወይም ምሽት ጎፍቶ ማንጋት ግን
የማይቻል ነው ።

አቤል ቢቸግረው እንዲህ አይነት የጊዜ ምርምር ውስጥ ገባ ። ችግሩ ነው ምርምሩን የጋበዘው ቀኑ አልመሽልህ "
ሌሊቱ አልነጋልህ እያለው ተቸገረ ለሌላው ተማሪ የዕረፍት ጊዜ ለእሱ ግን የመጨረሻው ደረጃ የጭንቀት ጊዜ
ሆኖበታል ። ቀንም ይተኛል ፡ ማታም ይታኛል ። ነገር ግን እንቅልፍ አይወስደውም ። እንዲሁ አልጋው ላይ እየተገላበጠ በሐሳብ መብከንከን ሆነ ። ጊዚ ከመቼውም ይልቅ የኋሊት እየተጎተተ የሚያቃስት መስለው ።

ሳምሶን ለዕረፍቱ ወደ ቤቱ ስለ ሔደ መኝታ ክፍላቸው ውስጥ የቀሩት አቤል ፡ እስክንድርና "ድብርት ” ብቻ ነበሩ ። “ ድብርት ” ፈተና ካለቀ በኋላ ያሳየው ለውጥ ቢኖር አልጋ ማንጠፉ ብቻ ነው ። በተረፈ እንደ ጥንቱ “ድብርት ጥናቱም ቢቀር ያው አልጋውን በጋቢ ጋርዶ በራሱ ሕልም ውስጥ መኖሩን አልተወም ። ወደ ውጭ ቢወጣ ብቻውን ነው ።

እስክንድር የዕረፍት ጊዜ ጓደኛው መጽሐፍ ነው ።የአማርኛና የእንግሊዝኛ ልብወለድ መጽሐፎችን እየተዋሰ
ሲያነብ ስለሚውል፥ ቀኑ በፍጥነት ነው የሚገሰግስለት ማንበብ ስልቸት ሲለው፡ወደ መዝናኛው ክበብ እየሔደ ቼዝ
ይጫወታል ። መቼም ከሱ ቦታ ሰው ቢጠፋ ሚስተር ሆርስ አይጠፋም ።

እስክንድር በዚህ ሁኔታ የዕረፍቱን ጊዜ ቢያሳልፍም ከአቤል ጋር አብሮ መጨነቁ አልቀረለትም ። ዐቅሙ በሚፈቅደው መጠን አቤልን ለማዝናናት የማያደርገው ሙከራ የለም ። ከአነበባቸው መጽሐፎች ውስጥ ጥሩ የሚላቸውን መርጦ ይሰጠዋል ። አቤል ግን ነጻ ኣዕምሮ ስለሌለው፥ አንዱንም ከነጣዕሙ አንብቦት አያውቅም ። ጀምሮ ሳይጨርሰው ይቀራል ። ወይም በግል ሐሳቡ ውስጥ እየዋዠቀ ገጹን
በመቁጠር ብቻ ይጨርሰዋል ። እስክንድር ወደ ቼዝ መጫወቻው ቦታ ሲሔድ አቤል አብሮት እንዲሔድ ለማድረግ ቢሞክርም እሺ አላለውም ፡ ከሚስተር ሆርስ ጋር ከተጣላ ወዲህ የመዝናኛ ክበቡን ረግጦት አያውቅም ።
አቤል ወደ ውጭ ብቅ እያለ ከሰዎች ቢቀላቀል ፡ ጊዜውን መዝናኛ ቦታዎች እየሔደ ቢያሳልፍና በአንዳንድ እን
ቅስቃሴዎች ቢሳተፍ፡ ጭንቀቱ እንደሚቀልለት እስክንድር
ቢረዳም ፡ ይህን ለማድረግ ሁኔታዎች አልተመቻቹለትም አብዛኛው መዝናኛ ገንዘብ ይጠይቃል ። ይህን ማሟላት
አይችሉም ። ገንዘብ በማይጠይቅበት መዝናኛ ቦታ ለመዋል ደግሞ የአቤል ሙሉ ፈቃደኝነት አይገኝም ። ሌላ ቀርቶ
ከእስክንድር ጋር ከሚያወራበት ጊዜ ይልቅ፡ ብቻውን ተደብሮ ውስጥ ውስጡን ነገር ሲያብሰለስል የሚውልበት ጊዜ
ይበልጣል ።

ትዕግሥት በተለያየ መልክ በሕልሙ እየመጣች ትታየዋለች ። አንዴ ይጣላሉ ፤አንዴ ጥላው በመሔዷ የተሰማውን ቅሬታ ይገልጽላታል ፤ አንዳንዴ ደግሞ ደብረ ዘይት ድረስ ሔዶ ሲገናኛት ያድራል ቀን ያሰበውን ማታ በሕልሙ ይደግመዋል አንዳንዴ በቅዠት ይወራጫል ።
ከትዕግሥት ናፍቆት ጋር ተደርቦ የወላጆቹ በተለይም የእናቱ ሁኔታ ፊቱ ላይ እየተደቀነበት መጨነቁ አልቀረም ።
ያስብ ያስብና ሁሉም ነገር ፍቺ የሌለው እንቆቅልሽ ይሆንበታል ። ሆኖም እንቆቅልሽ ነው ብሎ አይተወውም ።

ተመልሶ በዚያው ሐሳብ ዙሪያ ይሽከረከራል ፡ በሐሳብ ከመብከንከኑ ጋር የምግብ ፍላጎቱም እየቀነሰ ስለመጣ
በጣም ከስቶ ነበር ። ግን ለዚህ ደንታ አልነበረውም ። አካሉ መንምኖ ነፍሱ ብቻ ከውስጥ ሚን ሚን እስክትል ይጠብቃታል

ብርቅነሽ ትዝ ስትለው የደስታ ብርሃን ትፈነጥቃለች ።ስለ እሷ ማሰብ ደስ ይለዋል። አብሯት ካደረ ጀምሮ የመውደድ ስሜት ተቀርጾበታል ። የፍቅሩን ዐይነት ግን በግል ለይቶ ማወቅ አልቻለም ። ትዕግሥትን ይወዳታል ፡ ብርቅነሽን ይወዳታል ። የመወደዱ ዐይነት ይለያያል ሲያስቡት ደስ የሚልና ሲያስቡት የሚያስቃይ ፍቅር ! ስለ ብርቅነሽ ማሰብ ያስደስተዋል ፤ አያሠቃየውም ፤ ጭንቅላቱን አይበጠብጠውም ። ስለ ትዕግሥት ማሰብ ግን ያሰቃየዋል፥
ይበጠብጠዋል ፤ ያስለቅሰዋል ። እንዲያም ሆኖ ፍቅሩ ለምታሠቃየው ለትዕግሥት ያደላል ። ሙሉ ልቡን ያሳረፈው በትዕግሥት ላይ ነው ። ቀርቦ ምስጢሩን ካካፈላት ፥ ገላዋን ካቀፈውና ትኩሳቷን ሲቀበል ካደራት ሴት ይልቅ ከዐይኑ ላላለፈች ሴት ፍቅሩ ማመዘኑ ለምን እንደያነ ሊገባው አልቻለም ። “ የፍቅር ምስጢሩ ምንድነው ? ሲል አሰበ "
ፍቅር የሚወደው ሥቃይን ይሆን እንዴ ? ?

አንድ ቀን ብርቅነሽን ሲያስታውስ ከውስጡ “ሔደህ እያት ” የሚል አንዳች ግፊት መጣበት። ለእስክንድር ሳያማክረው ተደብቆ ብቻውን ሔደ ። ለምን እንደሚሔድና ቢያገኛት ምን እንደሚላት አላሰበበትም ። ገብቶ ለመጫወትም ቢሆን ፥ የሚጠጣ! ለማዘዝ በኪሱ ገንዘብ የለም ። እናም ቡና ቤቱ አጠገብ ሲደርስ ቀጥ ብሎ ቆመ።

የቡና ቤቱ በር ክፍት ነው ። ነገር ግን ድምፅ አይሰማበትም። እንደዚያ ዕለቱ ምሽት ሙዚቃና የሰው ቻቻታ የለበትም ። ከዝንቦች እምታ በቀር ጸጥ ረጭ ብሏል ።
መግባት አልደፈረም ። እየተንጎራደደ ሰው ብቅ እስኪል ይጠብቅ ጀመር ። ጥቂት እንደ ቆየ ፥ አንዲት ሴት የከሰል
ምድጃ ይዛ ከውስጥ ብቅ አለች ። አለባበሷ ግድ የለሽ ነው ።
ሻሿን የገርዳሳ አስራለች ።

አቤል ሲያያት ክው አለ ። የዋህነቷንና ጥሬነቷን አይታ የቡና ቤቷ ባለቤት ማታ ማታ እንደ አሻሻጭ ቀን ደግሞ እንደ ገረድ ነው የምትጠቀምባት ፡ ከሰሉ እንዲቀጣጠልላት ምድጃውን ወደ ንፋስ አድርጋ ቀና ስትል አየችው ቶሎ አልለየችም። ያው እንደ መንገደኛ ነበር የተመለከተችው ። ስታየው ተደናግጦ ጀርባውን ሰጥቷት ወደ ኋላው ሊመለስ ፈልጎ ነበር ። ግን ዐይኑን ከማሸሹ በፊት የምታውቀው ወንድ መሆኑን ለይታ ጥርሷን ብልጭ አረገችለት እሷን ፍለጋ ያልመጣ ለመምሰል እጁን ኪሱ ከትቶ በግዴለሽ አረማመድ ተጠጋት ስሜቱን ለመሸፈን በከንቱ ደከመ እንጂ በድንጋጤ ፊቱ ቀልቶ ግንባሩን አልቦት ነበር።

ውይ ! አንተ ነህ እንዴ ? በሞትኩት ! ምነው ጠፋህ ? ” አለች ከልብ በሆነ አነጋግር ።

ምንም ሳይመልስላት ስሜቱን በፈግግታ ብልጭታ ለመሸፈን እየሞከረ ጨበጣት

ሙት እውነቴን እኮ ነው ጠፋህ ? ቆይ እስኪ ስንት ቀን ሆነን አዎ ሳምንት አልፎሃል ። እኔ ከዛሬ ነገ ትመጣለህህ እያልኩ በልቤ ሳስብህ ነበር አለችው።

“ እነቷን ይሆን እንዴ ? ” ሲል አሰበ ግን አሁንም ከመቅለስለስና ራሰን ከማከክ ሌላ ምንም አልመለሰም ። ድምጿ የእውነት ቅላጼ ነበረው የተናገረችው የልቧን ነው ፤ ለአቤል አንድ ጥሩ የሆነ ስሜት አድሮበታል ። ሴት ያልለመደ መሆኑና የተማረ መሆኑ ፥ በስሜቷ ውስጥ እንዲቀረጽ አድርጎታል እናም እንዳለችው አብራው ካደረችበት ሌሊት በኋላ ዐልፎ ዐልፎ በልቧ ታስበው ነበር ። የተሰማራችበት ሙያ ሆነና በወሲብ ተገናኙ እንጂ ፥ እሷ ለሱ ያደረባት ስሜት ሐሳቧንና ችግሯን እንደምታዋየው
እሱም በዕውቀቱ እንደሚረዳት የቅርብ ዘመዷ ወይም ታናሽ ወንድሟ ዐይነት ነበር

“ በል እሺ ግባ ! በር ላይ አትቁም አለችው ከእሱ አንዳችም ቃል ባለመስማቷ እያዘነች ።

“አአይ ልሒድ ፤ድንገት ሳልፍ'ኮ ነው
#ሰመመን


#ክፍል_አርባ


#ድርሰት_በሲሳይ_ንጉሱ


የዕረፍቱ ጊዜ ለአቤል ብቻ ሳይህን ለአብዛኛው ተማሪ ረዥም ነበር " በጥናት መወጠር የለምደ አእምሮ ሥራ ሲፈታ ደቂቃዋም ትረገማለች ። የአዲስ አበባም ተማሪዎች እንኳ አብዛኛዎቹ ወደየ ዘመዶቻቸው መጥተው ሰንብተዋል። ከየክፍለ ሀገሩ የመጡ ተማሪዎች ግን መሄጃም ሆነ ጊዜ ማሳለፊያ በማጣት ቦዝነው ነው የሰነበቱት ቀን ቀን ሁሌም ተደብረው ይውላሉ " ጫዋታና ቀልድ የሚኖረው ማታ ማታ በየመኝታቸው ሲሰፍሩ ነው " በአብዛኛው መኝታ ክፍል ተደጋጋሚ የጨዋታ አርዕስቶች ሆነው የሚቀርቡት የአቤልና የትዕግሥት የዐይን ፍቅር • የለማና የቤተልሔም ጉዳይ ፡ ወይም ሌሎችን የተደረሰባቸው አዲስ
ፍቅረኞችን ማጋለጥ የመሳሰሉት ናቸው ።

የግቢውን የፍቅር ታሪክ መሰለልን መዝናኛችው አድርገው የያዙ አንዳንድ ተማሪዎች አሉ ። ወሬአቸውን የሚያደምቁት የፍቅረኞቹ ጓደኛ በመምሰል ቀርበው ምስጢራቸውን እየሰረሰሩ ነው ። በዚሁ ተግባራቸው፡“ ሳተላይት”” “ ሮይተር” ፡ “ ቢቢሲ” የሚል የቅጽል ስም የወጣላቸው ተማሪዎች ነበሩ ። ወሬ አጠናቅረው መጥተው በግቢው ያሰራጫሉ ። ምሽት ላይ እነሱ ሲመጡ! ሁሉም ወሬ ለመስማት ከተኛበት ብድግ ብድግ ይላል ።

“ ያልሰማህ ስማ ! የሰማህ ላልሰማ አሰማ ! አዲስ ዜና በዚህ በዝግ ጊዜ ውስጥ አንድ መምህር ከአንዲት ተማሪው ጋር በዋቢ ሸበሌ ሆቴል የዳንስ ምሽት ላይ መታየቱ፥ ከታመኑ የዜና ምንጮች ደርሶናል።

• ደሞ ማን ይሆን ? ” እያለ ተሜ ከመኝታው ውስጥ በአንሶላው ብቻ እየወጣ ' በጆሮው ሳይሆን በመላ ሰውነቱ
የሚያዳምጥ ይመስል' ወሬው ወደ ነፈሰበት ይጠጋል ምን ጊዜም የሚሞቀው « እነ “ ሮይተር ” እነ “ ሳተላይት” ያሉበት መኝታ ክፍል ነው ። ብዙ ተማሪ ክፍሉን ትቶ እነሱ ያሉበት ድረስ እየመጣ ያመሻል ።

« ማነው እሱ በናትህ፣"

"ለማን ታውቁታላችሁ ? ሁለተኛ ዓመቶችን የሚያስተምር ራሰ በራ ሰውዬ።

“ እ" ዐወኩት ። ከማን ጋር ነው የታየው ? ” ይላል " የሚያውቀው።

ለማን የማያውቀው ደግሞ ፣ በእዝነ
ልቦናው ለማን ፍለጋ ይጓዛል።

"በተልሔም ከምትባል ቀይ ወፍራም የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ጋር ፡ ..".

“ውይ እሷንማ ሲያወጣት ቆይቶ የለም እንዴ? " ይላል ከአሁን በፊት ቀድሞ ወሬውን የሰማ።

"ሒ.....ድ?" ይላል ለወሬው እንግዳ የሆነ ሁሉ በአድናቆት

“ ኧረ እንዲያውም ሊጋቡ ነው ” ሲል ቤተልሔም ጣት ላይ የጌጥ ቀለበት ያየው ደግም ነገሩን ያጋንናል ።

“ ስጥ እንዲህ ! ” ይላሉ ፡ ውሸቱ አልዋጥ ያላቸው።

“ ተወው እስኪ ያውራ ፡ እጅሬ መቼም መስጠት ልማዱ ነው።

ውሸት ፈጥረው የወሬ ማጣፈጫ እያደረጉ በማቅረብ የተካኑ ተማሪዎች አሉ ። “ ስጥ እንግዲህ ” የጨዋታቸው»
አርዕስት ሲሆን እነሱ ደግሞ “ አባ መስጠት ” በመባል ይታወቃሉ ።

ውሸቱ ከፍ ያለ እንደህነ "ርግጫ ” ይባላል ። ዋሻዎቹ “ ረጋጮች” ሲባሉ፥ የፕሮግራማቸው ስም ደግሞ

“ረግጣ” ነው ። ማኅበራዊ ኑሮን የሚጠሉ ጥቂት መሠሪዎች ካልሆኑ በስተቀር ። የአብዛኛው ተማሪ የሮይተሩም የረጋጩም - ተግባር የዩኒቨርስቲውን የዕረፍት ጊዚ ሕይወት ለማጣፈጥ ነው። »

“ እባካችሁ ጨዋታውን ወደ ቀልድ እትቀይሩት ይላል ለወሬው የጓጓ ፥ አምርሮ ።

"በቃ " ይኸው ነው ለማ ቤተልሔምን እወጣት

“ “A” ያለምንም መጨነቅ በእጅዋ ገባ ማለት ነው ።ከቻለ ደግሞ ከራሱ ትምህርት ዐልፎ ሌሎቹም ጓደኞቹ እንዲረዷት ይለምንላታል ፡

“ እናታቸውን ! እነዚህ ሴቶች ጨረሱን ” ኮ ! ጭንቅላት ሲያጡ በወሲብ ዩኒቨርስቲን ሊወጡ ! ” ሲል ፥ ሁሉም
በብሽቀት ጥርሱን እያንቀጫቀዉ በጅምላ ሴቶቹን ይራገማል።

“ ለካ ለዚህ ነው ” ይላል " እርዕስቱ እንዳይቋረጥ የሚፈልገህ ለአርዕስቱ እንደገና ሕይወት ለመስጠት ቅመም እያዘጋጀ

“ ምኑ ? ብዙ ጆሮዎች ሰልተው ይቆማሉ "

"ሰሞኑን ለማ ከሚስተር ራህማን ጋር ግንባር ፈጥሮት የሚታየው !!

"ራህማን ? ”

"ሚስተር ራህማን እኝያ ህንዳዊው ። ”

“ እ ! እ ! ” ሞቅ ያለ ሣቅ ።

“ ለማ የቅርብ ጓደኞቸ ሆኗል ። ለሻይ ሲወጡም አንድ ላይ ነው።

“ የዓላማ አንድነት ነዋ ያስተሳሰራችው ።

“ እሳቸው”ኮ ሐኪም ሳያይዝላቸው አይቀርም ። በሴት ቀልድ አያውቁም ፤ በተለይ ወፍራም ሴት ሲወዱ ! ”

“ ብቻ አንድ ቀን ሴት ጭን ውስጥ ትንፋሻቸው ቆሞ እንዳይገኙ ” ይላል የበሸቀው ክፍል እያፈዘ »

ጨዋታው ይቀጥልና ከመምህራን ተመልሶ ወድ ግል መበሻሸቅ ያመራል ። እርስ በርስ መጋለጥ ይመጣል ። አንዱ
የሌላውን ምስጢር ለመጎልጎል በነገር ጎሸም ያረጋል "ነገሩ የሚነካው ቁስለኛ ካለ በወዲሁ ማኩረፍ ይጀምራል ።
ሆኖም እነ “ ሮይተር ” የማንም ኩርፊያ አያግዳቸውም ።

“ ነገርን ነገር ያነሣዋል ” ሲሉ ይጀምራሉ

“ ደሞ ምን ልታመጡ ነው ? ”

የቤተልሔምን ጓደኛ ሊያወጣ የሞከረም ከመሃከላችንም አይጠፋም ኮ ! ”

ማንን ? ያቺን ማርታን እንዳይሆን ? ! ”
“ እህህሳ ! ማርታ ዐይኗ ስለማያርፍ ሳይሆን አይቀርም ፤ ብዙ ተማሪዎች ዐይናቸውን ጥለውባታል ፡ በግቢው ውስጥ ከብዙ ሴቶች መሃል ተለይታ ትታወቃለች ። ጠይቀው ሊያወጧት የሞከሩ ወይም የሚፈልጓት ከእስክንድር ሌላ ብዙ ናቸው በአለባበሷ ደምቃ ከመታየቷ ሌላ ምን ጊዜም ዐይኗ አያርፍም ። ስትበላ የአዳራሹን ወንድ እየቃኘች ነው ። ስታጠናም መጻሕፍት ቤት የተቀመጠ ፍጥረት አይቀራትም ። ወንዶችን ብቻ ሳይሆን ሴቶችንም ሥራዬ ብላ ነው የምታየው ፡ ሴቶችን የምታየው ግን በጤናማ ዐይን አይደለም ። ዘወር ብላ እንደ ሽንኩርት ትልጣቸዋለች ። በተለይ ደመቅ ያለች ሴት ማርታ ዐይን ውስጥ ከገባች አለቀላት !
ውሸት ፈጥራ ስሟን ታጠፋለች ። !

“ ውይ ! ያቺን ሞጥሟጣ ነው እንዴ ?” ሲል ቁስል ያለበት ማጥላላት ይጀምራል
“ሞጥሟጣነቷን በምን ዐወቅክ ? ” በማለት ፡ ሳታላይቶቹ ያፈጣሉ "

“ደሞ ምን ልታመጡ ነው ? እዚያው በጸበላችሁ ! ”
ቁስለኞ ማኩረፍ ይጀምራል ።

“ አንተ ምን አስኮረፈህ ? አንድ ቀን ብቻ ነው የጠየቅካት እና “F” ኮመኩህ ተመለስክ ። ይሄ ደሞ አያሳፍርም ።"

ጠይቆ ሲሳካ “A” እንደማግኘት ሲቆጠር ፡ ሳይሳካ ሲቀር ደግሞ "F" መኮምኮም ይባላል ።

“ አይ አጅሬ ! መኮምኮም አይሰለቸው ! ” በማለት ከፊሉ ያደንቃል "

“ ስጡ እንግዲህ ! አባ መስጠቶች መስጠት አይሰለቻችሁ።

“ ምኑ ላይ ነው ውሸቱ ?”

“ መዋሽት ብቻ ነዉ እንዴ ደኅና አርጎ መርገጥ ነው እንጂ ። ምን ታረጉ ? ! ዝም ብለው የሚረገጡላችሁ እገኛችሁ ርግጡዋቸው !”

አስረጅ ! ” በማለት ከመሐል ነገሩን አጠናካሪ ይናገራል።

"ደም አንተ ምን ልትል ነው ? ”

“ አጅሬ አንድ ቀን" እነማርታ የሚያጠኑበት ኣካባቢ ያለ ሥራው ሲያንዣብብ አግኝቼዋለሁ ፡ ”
አጥቂ ሲበዛበት ቁስለኛው የሚያመልጥበትን ዘዴ ያሰላሰላል ኩርፊያ አያዋጣም ። ቁጣም አያዋጣም ። የዚህ
ዐይነት አዝማሚያ ከታየ ተማሪዎቹ የባሰ ያሳብዳሉ ። ያለው ምርጫ ቀስ ብሎ ቀዘዴ አርዕስት ማስለወጥ ነው ።

“ ይልቅ የሚገርመው የዚያች የእነ ማርታ ጓደኛ ነገር ነው " ያ የአራተኛ ዓመት የማዕረግ ተማሪ የሚወዳት ! ”
ሲል እንደ ምንም ወደ ሌላ አርዕስት ይሸጋገራል ።

የቤተልሔም እና የማርታ ነገር ከተነሣ የትዕግሥትም አይቀርም » ብዙ ጊዜ አብረው ስለሚታዩ ነው ። አቤል ከሚስተር ሆርስ ጋር ተጣልቶ የአዕምሮ መታከሚያ ሆስፒታል ከተወሰደ ጊዜ ጀምሮ እነ “ ሮይተር ” ስለዚህ ጉዳይ
#ሰመመን


#ክፍል_አርባ


#ድርሰት_በሲሳይ_ንጉሱ


....እስክንድር በግቢው ውስጥ በሚካሔዱት የመዝናኛ ቀልዶች ተረቦችና ጨዋታዎች በተሳተፈ ቁጥር አንድ
የሚገርመው ነገር አለ ። አብዛኛው ወሬ ስለ ሴትና ወንድ ግንኙነት ወይም ስለ ፍቅር ነው ። “ ሌላ ወሬ አጥተን ነው
ወይስ ዕድሜአችን ነው በዚህ አርዕስት ዙሪያ የሚያሽከረክረን ? ወይስ ደግሞ የጋራ ስሜታችንን የሚነካ ጉዳይ ይህ
ብቻ ሆኖ ነው ?” ሲል ያስባል ። ነገር ግን ከአቻው ጋር በተገናኘ ቁጥር ዞሮ ዞሮ አመርቂ አርዕስት ሴት ሆናለች ፤ እና
የዕድሜን ኃይል ግለት ይታዘባል ትኩስ 'አፍላ የሚያቅበጠብጥ ዕድሜ።

የዕረፍቱ የጨዋታ ምሽቶች ከፍቅር እልፍ ያሉ እንደ ሆን በግቢው ውስጥ ከሚታዩት ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ያርፋሉ የፍቅር ጉድጓድ እንደሚሰረስሩት “ሮይተሮች ” ሁሉ በዩኒቨርስቲው ውስጥ ፀረ መጤ ሃይማኖት አቋም ይዘው እያንዳንዷን እንቅስቃሴ እየተከታተሉ የሚ
ተርቡም አሉ ። በየዕለቱ በየትኛው ድርጅት ውስጥ ማን እንደ ተመለመለ ወሬው አያመልጣቸውም ሌላው ቀርቶ
የትኛው የሃይማኖት ድርጅት በግቢው ውስጥ የአባላት ብዛት እንዳለው የሚያውቁና በአሀዝ የሚያቀርቡ አሉ ።

ሰሞኑን “ ሁለተኛው አምላክ ዘ" ታላቅ ኪሳራ ደርሶበታል ” ሲል አንዱ ይጀምራል

“ እንዴት ? ”

“ በፈተና ሰሞን የመለመላቸው አባላት አብዛኛዎቹ ፈተና ካለቀ በኋላ ርግፍ አርገው ትተውታል። ከመብላታቸው በፊት መጸለይ አቁመዋል ። አስረጅ ”

“ በዩኒቨርስቲው ውስጥ በሃይማኖት አባልነት የተመለመሉት የሚታወቁት፡ምግብ ኣዳራሽ ውስጥ ከመመገባቸው
በፊት አቀርቅረው ሲጸልዩ ነው ። ጸሎቱን ሲያቆሙ ኮንትራታቸውን መጨረሳቸው ይታወቃል

“ አትለኝም ማን ማን ተወ በናትህ ? ”

የሚታወቁትን በስም የማይታወቁትን በመልክ ጥቆማ ይካሔዳል ።

“ ምነው ውጤት እስኪቀበሉ እንኳ ቢቆዩ ፈተና ላይ “ የረዳቸው ” አምላክ የአራሚውንም መምህር እጅ በማሳሳት እንዲረዳቸው ። ”

"ቸኮሉዋ ! ምን ያርጉ በዕረፍት ጊዜያቸው በሃይማኖቱ ከቀጠሉበት ሴቶቹ መደነስ ወንዶቹም መጠጣት ሊያመልጣቸው ሆነ ለማን ጀቴ ብለው !”

“ አሥቂኝ ነው ” ይላል አንዱ ቀልደኛ ከመሐል።

“ እንዴት ?” ሲል ሁሉም ጆሮውን ይቀስራል ።

“ ከአምላካቸው ጋር ድብብቆሽ ጨዋታ ነው ” ኮ የተያያዙት ። ፈተና ሲደርስ ይሰግዱለታል ። ከፈተና ከወጡ በኋላ ይዘጉታል ። ዋ ብቻ አንድ ቀን ያመረረ ዕለት !”

ቀልዱ ሲኮረኩራቸው መሣቅ እየፈለጉ በልባቸው አፍነው የሚያሳልፉ አሉ። ሲሥቁበት አምላክ እንዳያያቸው
የፈሩ ይመስላሉ ። አንዳንዱ በዚህ አርዕስት ላይ ሲያሾፍ ፡ ሲቀልድ ፥ ሲተርክ አንዳንዱ ደግሞ ገለልተኛ ሆኖ መስማቱን ይመርጣል ። ጨዋታውን ማዳመጥ ይወዳል ፤ ግን በሃይማኖታዊ ድርጅቶችም ሆነ በአምላክ ላይ አንዳችም
ተቃርኖ አያነሣም ። “ ከአፍ የወጣ እንጂ በጆሮ የገባ አያረክስም” ከሚል ግምት ላይ የደረሰ ይመስላል ።አፌን በዳቦ
ነው ነገሩ ።

እንዲህ ዐይነቶቹ የጨዋታ ምሽቶች በብዙ ተማሪዎች አእምሮ ተቀርጸው የሚቆዩ ናቸው ። በሴቶችም መኝታ ክፍል ቢሆን ሐሜቱና ተረቡ ቢበዛ እንጅ አያንስም ። ወንዶችን በማብጠልጠል አስተማሪዎችን በመቦጨቅና ራስን በመካብ ሴቶቹን የሚያህል የለም ። “ እገሌ “ኮ እንድወጣለት ጠይቆኝ ዘጋሁት ያ ባላገር ” የብዙዎቹ የጋራ ፈሊጥ ይመስላል ። የሚገርመው ደግሞ ሴቶቹ ሲዋሹ እርስ
በርሳቸው ይቻቻላሉ ። እንደ ወንዶቹ “ረገጣ” እና “ስጥ እንግዲህ ” እየተባባሉ ቅስም አይሰባበሩም ።

ቀልድ እየፈጠሩና ወሬ እያጠናቀሩ ተማሪውን የሚያዝናኑትን ያህል በየአስተማሪው ቢሮ እየተሹለከለኩ የፈተና ውጤት ከመነገሩ በፊት መርዶ የሚያረዱ አንዳንድ ተማሪዎችም አሉ ። እነዚህን ማንም አይወዳቸውም የዩኒቨርስቲ ሕይወታቸው ዕድሜ የሚኖረው ለአስተማሪዎች ወሬ በማመላለስ ነው እየተባሉ ይታማሉ ። ማርክ ቀድም የመስማት ሱስ አለባቸው ። የራሳቸውን ሳይሆን የሌሎቹንም የመስማት ሱስ ነው የያዛቸው ። እወደድ ባይ ወይም ለተራ ወሬ ጆሮውን የሰጠ መምህር የሦስት ልጆችን ማርክ ይነግራቸዋል ።እነሱ ደግሞ አባዝተውት የሃምሳ ልጆችን ውጤት እንደ ሰሙ አርገው ወሬውን ይዘራሉ መምህሩ ወደቀ ካላቸው እነሱ “ ተሰበረ ” ብለው በግቢው ውስጥ ሽብር ይፈጥራሉ ።

ዘንድሮ ይህን ያህል ፍሬሽ ይባረራል ” ብለው በአፋቸው ሙሉ ሲናገሩ የሬጂስተራሩን ቢሮ የያዙት ይመስላሉ ።

“ የእንትን አስተማሪ ከዚያ ሁሉ ተማሪ መሐል ሁለት “A” ብቻ ነው የሰጠወ” ሲሉ የመምህሩ የቅርብ ጓደኛ ይመስቀሉ

ከመልካም ዜና ይልቅ የዝቅተኛና የውድቀት ማርክ ሽብር መፍጠር ነው የሚቀናቸው ። ሌላውን አስበርግጎ ወይ
እነሱ የወሬ ሱሳቸውን ካልተወጡ አይሆንላቸውም ።

እቅጩ የሚታወቀው ግን ጊዜው ደርሶ ማንኛውም ተማሪ የራሱ ውጤት በራሱ እጅ ከደረሰው በኋላ ነው፡አቤል ከሁሉም፦ ርቋል ጥሩውንም መጥፎውንም አይሰማም ። “ ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው” እንዲሉ በሱ ላይ የሚወራበትን አያውቅም። ነገር ግን ተማሪው ሁሉ በሽታወን ያወቀበት እየመሰለው ከሁሉም ሸሽቶአል ። ጓደኛው ብቸኝነቱ ነው » አጫዋቹ የቀን ቅዠቱ ፥ የሌሊት
ሕልሙ ነው ። ሌላው ክፍል ተማሪው ተሰብስቦ እያወራ እየቀለደና እየተጫወተ ሲሣሣቅ፥ አቤል ከብቸኝነቱ ጋር
ይሟገታል ። ትዕግሥትን ያልማል ፤ በል ሲለውም ይረግማታል ። የመልካሙ ተበጀን ዘፈን ያዜማል ። ብርቅነሽን ያስባል ከራሱ ጋር ይሥቃል ። ከራሱ ጋር እየተጣላ ያለቅሳል።

በዚህ ዓይነት የሚገፉ ዐሥራ አምስት የዕረፍት ቀናት የዐሥራ አምስት ዓመት ያህል ቢረዝሙም ማለቃቸው አይቀርም ያልቃሉ ። የሚጠበቀውም ቀን መድረሱ
አይቀርም ይደርሳል ።

ትዕግሥት የፈተና ውጤት ሊሰጥ እንድ ቀን ሲቀረው ከደብረ ዘይት አዲስ አበባ ገባች ። ወደ ዩኒቨርስቲዉ መኝታ ክፍሏ ስታመራ፥ አንዳች ነገር የኋሊት ይጎትታት ነበር። ከዘመዶቿ ጋር ከርማ መለያየቷ ተጫጭኖዋታል "በዚያ ላይ ማርታና ቤተልሔምገና ስላልመጡ ብቻዋን ነበረች።

አቤልን ለማየት ቆርጣ ነበር የመጣችው ። ተለይታው በከረመችበት የዕረፍት ጊዜ ውስጥ ሲናፍቃት ነበር ። ግን ለምን ? መናፈቁን ነው እሷ ያልወደደችው ። ትዕግሥትም እንደ አቤል ለፍቅር እንግዳ ናት ። በልጅነቷ ጭቃ እያቦካች
ጎጆ ሠርታ፡ “ባልናሚስት” የተጫወተችበትን ጊዜ ወይም
ከትምህርት ቤት ጓደኞቿ ጋር የተጫወተችባቸውን ጊዜያት ታስታውስ እንደሆን ነው እንጂ ሌላ የፍቅር ትዝታ የላትም፡ አሁን ዕድሜዋ ይገፋፋታል " የወንድ ልጅ ክንድ ተደግፋ
በነፋሻማ ስፍራዎች መወዝወዝ ያምራታል አፍ ለአፍ ገጥማ ምስጢር የምታወራው አቻ ወንድ ያምራታል የወንድ ልጅ ከንፈር ጣዕም መቅመስ የሚያሰኛት ዕድሜ ላይ
ነች። ነገር ግን በዚህ ፋንታ የመጀመሪያ ፍቅሯ ከዐይን የማያልፍ ሆነ ። አቤል ቀርቦ ምስጢሯን አይካፈላትም ።የፍቅር ትኩሳቷን አይጋራትም ፡ የደረቀ ከንፈሯን አያረጥብላትም ፡ ወንዶች ላይ ለሚቅበዘበዝ ዐይኗ ገደብ አይገዛላትም። እሷነቷን ቀርቦ አያውቅላትም ። በሩቅ እየተያዩ መነፋፈቅ ብቻ

ትዕግሥት ይህን ሁሉ አመዛዝና ነበር አቤልን ቀና ብላ ለማየት የወሰነችው ። ትርጉም የሌለው ፍቅር ሆነባት ።
ከመጐዳቱና ከማንገብገቡ በቀር ጥቅሙ አልታይ አላት ።እንዳሰበችው የመጣች ዕለት ጨክና ሳታየው ዋለች። ከደብረ
ዘይት ያመጣችው የአገልግል ምግብ ስለ ነበር ወደ ምግብ አዳራሽም ብቅ ሳትል ዋለች ። ሐሳቧ ሴሚስተሩን በሙሉ
ከእርሱ ርቃ ለመቀጠል ነበር ። ግን ያን ዕለቱኑ ወደ ምሽት ላይ ከቁጥጥሯ በላይ
#ሰመመን


#ክፍል_አርባ_አንድ


#ድርሰት_በሲሳይ_ንጉሱ


ተማሪ አንዱ በአንዱ ላይ እየተንጠራራ ከሰሌዳው ላይ የመለያ ቁጥሩን መፈለግ
ጀመረ።

እነ እስክንድር ግርግሩ መሀል ሲደርሱ እነ ማርታ ውጤታቸውን ለማየት ስለ ተበታተኑ ተሰወሩባቸው ። የአንደኛና የሁለተኛ ዓመት ተማሪዎች ውጤት ብቻ ነበር የወጣው ።

የአራተኛ ዓመቶች ውጤት አልደረሰም እንዴ ? ”
አለው እስክንድር ውጤቱን የለጠፈውን ሰውዬ ሲመለስ አግኝቶት።

"ከሰዓት በኋላ ” ብሎት ሰውዬው እየተደፈ ሐደ ።

“ እስቲ እኔም ጉዴን ልመልከት ”አለ ሳምሶን አስደንጋጭ ድምፁ ስልት አጥቶ እየተንቀጠ።

“ ቆይ ምን አስቸኮለህ ? ግርግሩ ተግ ይበልልህ! ” አለው እስክንድር ።

ሳምሶን አረ ባክህ ! ” ብሎት " ተማሪውን እየገፈታተረ ወደ ልለተኛ ዓመቶች የውጤት ሰሌዳ አመራ።

እቤልና እስክንድር ከግርግሩ መሀል ወጥተው ብቻ ቸውን ቆመው ቀሩ አንዳች ነገር ተጫጭኗቸዋል አይነጋገረም።

ግርግሩን አትረው ይመለከቱ ጀመር » ማንኛውም ነገር ውስጡ ሲሆኑበትና ከውጭ ሲታዘቡት የተለያየ ገፅታ አለው የፈተና ውጤት ግዜ እንዲህ ከሩቅ ሆነው ሲያዩት አሳዛኝ ትርኢት ይታይበታል ውጤቱ የድካም ውጤት ሳይሆን የብሔራዊ ሎተሪ እጣ ይመስላል አንዳንዱ እየሳቀ ሄዶ ውጤቱን አይቶ ሲመለስ ፊቱ ኮሶ ይመስላል በፍርሃት
እየተንቀጠለጠ ሔዶ እየቦረቀ የሚመለስም አለ ውጤቱ አስደንግጦት የቆመበት ዘፍ የሚልም አይታጣም አብዛኛው ተማሪ ስለ ራሱ የነበረው ግምትና አሁን ያገኘው ውጤት እየተራራቀበት ፊቱን አጨማዶ ሲመለስ ነው የሚታየው።
እኔስ ከየትኛው ዐይነት እሆን ? ” ሲል እስክንድር ራሱን ጠየቀ ። የውጤት ጊዜን ሁኔታ እንዲህ በሩቅ ታዝቦ አያውቅም ነበር ።

አንዲት ልጃገረድ በጓደኞቿ ተደግፋ እያለቀሰች በኣጠገባቸው ስታልፍ አይተው የአቤልም የእስክንድርም ልብ
አብሮ አለቀሰ።
አይዞሽ ፡ ዩኒቨርስቲ የሕይወት መጨረሻ አይደለም ” አላት እስክንድር ቀስ ብሎ።

ቀና ብላ አላየችውም ጓደኞቿ ግን ያሾፈባት መስሏቸው ዞረው ገላመጡት ። ግልምጫ ከዐፈር የሚደባልቅ ቢሆን የማይተዋወቁት ሰው ግልጫ ኦሆሆ ! ቶሎ ብሎ ዐይኑን ከአይናቸን አሸሸ ።

ዘወር ሲል ሚስተር ሆርስ ከሶስት ልጆች ጋር ሆኖ ቅልጥሙን እጥፍ እያረገ ፌቱ ፈክቶ ሲያልፍ አየው ።

“ እንዴት ነው ውጤት? ፊትህ ሁሉ ጥርስ ሆኖአል” አለው በሩቁ ከአኳኋኑ ማለፉን ተረድቶ

“ አልሞትንም ፤ ተርፈናል ። የዩኒቨርስቲ ሕይወታችንን አራዝመናል።

« እንኳን ደስ ያለህ ! ” አለውና ፥ “ በቀላሉ የሚደሰት ተፈጥሮ ጥሩ ነው ” አለ በልቡ በድንግት የአቤል ድምፅ አስደነገጠው።

“ ያቻት ትዕግስት"

አቤል ከርቀት ትዕግሥትንና ማርታን ሲያይ ሳያስበው ነው ስሟ ያመለጠው ። በድንጋጤ ስሟን ከመጥራቱ ሌላ
የሚጨምርበት ነገር አልነበረም ።

“ እህ ?” አለው እስክንድርም ደንግጦ "

አቤል ምንም አልመለሰም ። ፊቱ በቅጽበት ተለዋውጦ ከሰል መሰለ ከንፈሩ ተጣብቆ አልላቀቅ አለው ዐይኑ
ፈዞ ቀረ።

እስክንድርም መልስ አልጠበቀም ፥ የአቤልን ዐይን ተከትሎ ትዕግሥትንና ማርታን ተመለከታቸው ውጤታቸውን
አይተው በመመለስ ላይ ነበሩ ። ፊታቸው ዳምኗል ።በኀዘን ተውጠው አንዳችም ቃል ሳይለዋወጡ መሬት መሬት እያዩ ነው የሚሔዱት ። ለእነ አቤል ደግሞ የባሰ
ዳምነውና ተክዘው ታዩአቸው ።

ትዕግሥትና ማርታ እነ አቤልን ሲያዩዋቸውመንገዱቸውን አሳብረው በሌላ በኩል ሔዱ። በማርታ ግፊት ነበር
ይህ የተደረገው። ማንም ሳያያት ወደ መኝታ ክፍሏ መሔድ ነው የፈለገችው ።

አቤል መቆም ኣልቻለም ። ወገቡ የተቀነጠሰ መሰለው። ትዕግሥት ወድቃለች ማለት ነው ? ከዩኒቨርስቲው ልትባረርና ሊያጣት? ስለ ራሱ ውጤት አንዴም አላሰበ መለየት የሞት ያህል ሆኖ ታየው ።

ቃላት መተንፈስ ፈለገ ግን ከንፈሮቹ አልላቀቅ አሉት እርዳታ በሚጠይቅ አመለካከት እስክንድርን አየው ። ከተረታ ወይም ከደከመ ልብ ብቻ ነው የዚያን
ዐይነት እይታ የሚመነጨው።

“ ምን ልርዳህ ? ” አለው እስክንድር ' ሁኔታው ስለ ገባው።

አቤል ምንም ሳይመልስለት ፡ በሚስለመለም ዐይኖቹ እያየው ቀስ ብሎ አጠገቡ ያገኘው ነገር ላይ ቁጭ አለ።

እስክንድር በሐሳቡ አሁን ምን በወቅንና ነው ? ” አለ ። “ ምናልባት እነዚህ ልጆች ሳይወድቁ በዝቅተኛ ማርክ ብቻ እንደሆነስ የተከዙት ? ለምን ተከትዬአቸው ሔጂ አልጠይቃቸውም ? እነሱ ቢሸሹኝ ተናደው ይሆናል። እኔ
ግን ሔጄ ጠይቄአቸው ወድቀውም ከሆነ ማጽናናት አለብኝ ካለዚያ የመተዋወቅ ትርጕሙ ምንድን ነው ? ” አለና አቤልን የተቀመጠበት ትቶት ሔደ ።

ከሁለቱም ከማዘኑ ሌላ የእንድም ቀን የጫዋታ ትዝታ ቢሆን መጥፎ ነውና ከማርታ ጋር የመለያየቱ ነገር እሱንም ቅር ብሎት ነበር ።

ፈጥኖ ሔደ። ሲደርስባቸው ቀድማ ያየችው ትዕግሥት ነበረች ። በደካማ ፈገግታ ሰላምታ ሰጠችው ። ማርታም
እሷን ተከትላ ዘወር ስትል አየችው ። ሰላምታ ልትሰጠው ብትፈልግም ፈገግ ማለት አልቻለችም ።

እስክንድር አጠገባቸው ከደረሰ በኋላ ስለ ውጤታቸው መጠየቅ ፈርቶ ከንፈሩ ይንቀጠቀጥ ጀመር ።

“ እንዴት ነው ? ” አላቸው ፡ ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ፥ አንዴ ወደ ማርታ አንዴ ወደ ትዕግሥት እየተመለከተ ።

“ ዩኒቨርስቲያችሁን ለቀቅኩላችሁ እናንተው ኑሩበት!” አለችው ማርታ ቀድማ መንፈሷ ቢደክምም ምላሷ አልሞትም ነበር ።

“ ምነው ? ውጤቱ መጥፎ ነው እንዴ ? ”
ኤጭ ! ”
ከንፈሩን መጠጠና ወደ ትዕግሥት ዞሮ ' “ የአንቺስ ውጤት እንዴት ነው ? ” ሲል ጠየቃት ።

ጥሩ ነው ። በመካከለኛ ውጤት አልፌአለሁ ” አለችው በፈገግታ ።

“ እንኳን ደስ ያለሽ ! ዋናው ማለፍሽ ነው!!” አለና እሱም ፈገግ ብሎ እንደገና ጨበጣት ።

ማርታ ሁለቱንም በቅናት አስተያየት ላጠቻቸው "ዐይን የሚገድል ቢሆን ሁለቱም የቆሙበት ክው ብለው ቀርተው ነበር ።

እስክንድር ደስታና ኀዘን መሐል ገብቶ ወደ የትኛዋ 'እንደሚሆን ግራ ገባው ። “ ግማሽ ፊትን አጥቁሮ፡ ግማሽ ፊትን ማሣቅ ቢቻል እንዴት ጥሩ ነበር !” አለ በልቡ ።

ማርታን ፊት ለፊት ሊያያት አልደፈረም ። ቀስ ብሎ በስርቆሽ ተመለከታት የጠወለገች አበባ መስላለች ለካ ውበት የስሜት ነጸብራቅ ነው?” አለ በሐሳቡ ። ስሜቷ ከውስጥ ሲንድ ፡ሲቃጠል ሲብከነከን ታየው ድርብ የከንፈር ቀለሟ በመጠውለጉ ፊቷ ላይ ጎልቶ ምናምን
የላሰች አይጥ አስመስሏታል ። ቅንድቧ ብቻ እንደ ወትሮው ይርገበገባል ።

እስክንድር የቅንድቧን መርገብገብ አይቶ ወሬ እንደምትፈልግ ዐወቀ ። ግን ምን ዐይነት ወሬ ? በእሷ መውደቅ ምክንያት ተማሪውንና አስተማሪውን ማማት መቦጨቅ ? አይዞሽ ማርታ ዩኒቨርስቲ የሕይወት መጨረሻ አይደለም ” አላትና ፡ አንድ ቀን ያጫወተችውን አስታውሶ : “ ደሞም ከዚህ ወጥተሽ ስኮላርሽፕ መጠበቅ ትችያለሽ ” አላት ።

“እኔ ማርታ ጉዳዬም አይደል ! ብቻ እንኳን ዩኒቨርስቲ የምትሉትን አየሁላችሁ !
እስክንድር በልቡ “ እኛ ደሞ ምን አደረግንሽ ? " ብሎ ጭጭ።

“ የማትስ አስተማንሪኮ ነው ጉድ ያረገኝ ” አለች ትንሽ ቆየችና።

“ እሱ "F" ባይሰጠኝ ኖሮ ሌላ ትምህርት አልጎዳኝም ነበር።

“ ማነው እሱ? ” አላት ያስተዛዘናት መስሎት

“አቶ ኃይሉ የሚሉት አንድ ሽማግሌ አለ " ላውጣሽ ብሎኝ ስለ ዘጋሁት ቁጭቱን ተወጣብኝ ”

“ ያሳዝናል ! ” አለ እስክንድር ፡ ውሸቷ ኮርኩሮት በህዱ እየሳቀ።

ደሞ ከእሱ ጋር ልውጣ እንዴ? ቅሌታም ሽማግሌ ! ”፥

እስክንድር እንደገና ከንፈሩን
#ሰመመን


#ክፍል_አርባ_ሁለት


#ድርሰት_በሲሳይ_ንጉሱ

.....“እህ • ውጤት እንዴት ነው ?” አለ ገና ሲያያት "
“ ኮንግራጁሌሽን ! አልፌአለሁ” አለችው በተቀመጠበት ልታቅፈው እየተንደረደረች
“ ወዳጅ ዘመድ ይኑር በይ ” አላት እርዳታውን ለመጠቀምም ።
“ ይኑር ! ” ብላ አንገቱ ላይ ተጠመጠመችና ጉንጬን ሳመችው

"ምን ምን ደኅና አገኘሽ ? ” ሲል ጠየቃት

“ ሒሳብ “ 203 ” ጎጆ ሠርቻለሁ

በዩኒቨርስቲ ውስጥ “F ያገኙበትን ትምህርት ባንዲራ ሰቅያለሁ” ሲባል “ A ? ያገኙበትን ትምህርት ደግሞ ፡ “ ጎጆ ሠርቻለሁ” ማለት የተለመደ ቋንቋ ሆኖአል

“ እሱማ የኔው ነው ” አላት እንደገና ባለውለታነቱን ለመጠቆም

“ እኮ ! ” አለችው እየቦረቀች ።

ታዲያ ጎጆውን የሰራው ማነው ? እኔ ነኝ ወይስ አንቺ ? ”

“ አንተ!” ብላው እንደገና ልትስመው ከንፈሯን ስታስጠጋው በሩ በድንገት ብርግድ አለ ። ሁለቱም እንደ ተቃቀፉ
ክው ብለው ቀሩ የገባው ሳምሶን ጉልቤው ነበር ። አውሬ መስሎ
ታያቸው

ሁኔታቸው የፊልም ትርኢት መሰለ ። እነሱ ዱብ ዕዳ እንደ ወረደባቸው ፍቅረኞቹ በጭንቀት ተቃቅፈው ሳምሶን ቆሞ በፍቅረኞቹ ላይ ሽጉጡን የደገነ ፥ " ቴክስ” ይመስል ነበር።

“ ምን ፈለግክ ? ” አለው ለማ ድንጋጤው ከበረደለት በኋላ በትዕቢት ድምፅ ። ሳምሶን ለእሱ አልመለሰለትም ።

“ አንቺ ሸርሙጣ!” አላት ቤተልሔም ላይ አፍጥጦ። እናንተ አስተማሪ እያወረዳችሁ ትኖራላችሁ ፤ እኛ ግን እንባረራለን ! ”

“ ወይኔ ! ” ብላ ቤተልሔም ለማ ሥር ሽጉጥ አለች። ሊውጣት የመጣ ነው የመሰላት ። ዐይኖቹ ውስጥ የሚንቀ
ለቀለው የንዴት እሳት አስፈራት። ሽንቷ አምልጧት ጭርር ሲል ተሰማትና ጭንና ጭኗን አጋጠመች ።

ለማና ሳምሶን ተፋጠጡ ። የአንበሳና የነብር ፍጥጫ መሰለ ። በጉልበቱ የሚተማመነው ሳምሶን ለማ ፊት እንደ
ቆመ ጡንቻውን ለመሰንዘር ምን እንዳገደው ለማሰብ ሞከረ፡ ሕግ ! የሰዎችን የስሜት ፈረስ ለጉሞ ሲይዝ ታየው ።

“ እንዴዬ ! አሁን ምንድነው የፈለግከው ? ” አለው "ከተቀመጠበት ለመነሣት እያሰላ

“ ምን አገባህ ! ” ብሎ ሳምሶን ሌላ መናገር ፈርቶ እንዳፈጠጠ'ያላየው ሰው ከኋላ መጥቶ በድንገት ትከሻውን
ጨመደደው ።

“ምን ማድረግህ ነው ሳምሶን ? ” አለው እስክንድር ትከሻውን እንደ ጨመደደ ከቢሮው ሊያስወጣው እየታገለ ።
ከእሱና ከአቤል ተለይቶአቸው መምጣቱ ከንክኖት ነበር እስክንድር እየሮጠ የደረሰበት ።

“ ልቀቀኝ ! ” አለው ሳምሶን መጋበዙ እልሁን አግሎበት ።

እስክንድር በግድ እየጎተት ከቢሮው ካወጣው በኋላ
“ ዕረፍ ሳምሶን ” አለው ፡ “ ነገሮችን ለማመዛዘን ሞክር ።ለማ ቤተልሔምን ይጠቅማት ይሆናል እንጂ አንተን አይ
ጎዳህም ። ምክንያቱም ቀድሞ የምትዋደዱበት ወይም የምትጣሉበት ምንም ግንኙነት አልነበራችሁም

“ እንጃልህ ! ” አለና እሱም ላይ አፈጠጠበት ። “ ወቼ ጉድ ! ዛሬስ ለእኔም አይመለስ ” አለና ቀስ ብሎ እያባበለሀው ይዞት ሔደ ።

እስክንድርና አቤል ፥ ሳምሶንን እያባበሉ ወደ መኝታ ክፍሉ ከወሰዱት በኋላ ስለ ራሳቸው ለማሰብ ተገደዱ። የሌላውን የፈተና ውጤት የሰማው ጆሮአቸው የራሳቸውን ለመስማት ተጣደፈ ። መውደቅና ማለፍ ሁለቱ ተቃራኒ ነገሮች
እስካሉ ድረስ ፥ መከሠታቸው የግድ ቢሆንም ፡ የማንም አእምሮ በቀላሉ አይቀበላቸውም ። ከሰዓት በኋላው ለእነአቤል በጣም ራቀባቸው ። በተለይ አቤል የትዕግሥትን ማለፍ ከሰማ በኋላ የራሱን ውጤት ለማወቅ ለምን እንደሚጓጓ ሊገባው አልቻለም ። ምናልባት ተአምር ይወርድ ይሆን ?
ሁለቱም፥ ውጤት ከሰማው ተማሪ ጋር መቀላቀል አልፈለጉም ። ግን ጆሮአቸውን በጥጥ አይደፍነት ነገር! ባለፉ ባገደሙበት ቦታ ተማሪው በቡድን ቆሞ አንዱን ሲያነሣ አንዱን ሲጥል መስማት እሰለቻቸው ። አንዱ በአንዱ ሲቀና ወይም ደግሞ መምህሩን ሲወነጅል ነው የሚሰማው ።

በዚህ ዓለም ላይ ማን ይሆን ለኅሊናው ሐቀኛ የሆነ ፍጡር ! ሁሌም የራሱን ማንነት ደብቆ ሌላውን ሲወነጅል
ነው የሚገኘው ሁሉም ። ተማሪው አስተማሪውን በማርክ አሰጣጥ ይወነጅላል።ሠራተኛ አለቃውን ይወነጅላል።አለቃም ድክመቱን በበታች ሠራተኛ ላይ ይለጥፋል ። ለዚህ ምንጩ
ምን ይሆን ? የአስተዳደጋችንና የአኗኗራችን ኋላቀርነት የፈጠረብን ችግር ይሆን እንዴ ? ምናለበት አንዱ ሌላውን ከመወንጀሉ በፊት ፡ « ለመሆኑ እኔ ማን ነኝ ? ” ብሎ ራሱን መጠየቅ ቢችል ? አንዱ ከሌላዉ ጋር የሚኖረው የግንኙነት መሠረት ሥራና የሀገር ፅድት ሆኖ ሳለ ፥ እርስ በርስ መቦጫጨቅ ቢቀር ምናለበት ? ማንም ከምድር በላይ ወይም
ከምድር በታች ላይኖር ለመበላለጥ በምናደርገው ቅናት የበዛበት ፉክቻና ግላዊ ርኩቻ የጋራችን የሆነችውን ምድር
ባንጎዳት ምናለበት ? እስክንድር በሸቀ ።

ከቀትር በኋላ፥ከነእስክንድርና ከአቤል ቀድሞ ውጤቱን የተመለከተው "ድብርት ” ነበር ።

“ ውጤት ወጥቷል ” አላቸው ፡ የራሱን አይቶ ወደ መኝታ ክፍሉ ከተመለሰ በኋላ ደስታ አፍኖት ሲያልጎመጉም ጥርሱን አሳይቶ አልሣቀም ።

"ያንተ እንዴት ነው ? ” አሉት ።
"ግሩም ነው !
“ ስንት ጎጆ ሠራህ ? ” አለው እስክንድር
ሦስቱን ጣቶቹን አሳያቸው ።

“ የጉልበት ዋጋ ነው !” አለ እስክንድር በልቡ የድብርት ” አጠናን ምንጊዜም የጉልበት ሥራ ያህል በመታገልና
ብዙ ሰዓት በማጥናት ስለሆነ፡በጉልበቱ ዩኒቨርስቲ መቆየቱን ሁሉም ያውቅለታል "

ወዲያው እስክንድርና አቤል ተያይዘው ወደ ሰሌዳው ሔዱ። የሦስተኛና የአራተኛ ዓመት ተማሪዎች ቁጥር ያን ያህል ብዛት ስለ ሌለው በቀላሉ ወደ ሰሌዳው ተጠግተው ተመለከቱ ። እስክንድር በጥሩ ውጤት ዐልፏል ። የአቤል
ውጤት ግን አልወጣም ። አቤል ራሱን ማመን አቅቶት የመታወቂያ ወረቀቱን
ከኪሱ አውጥቶ የመለያ ቁጥሩን ተመለከተ ። ያ ቁጥር ሰሌዳው ላይ የለም ማለፍም ሆነ መውደቅ የግድ ሰሌዳ ላይ
መውጣት አለበት ። እና የአቤል ከዚህ ከሁለቱ ውጭ ምን ሊሆን ይችላል ?
የእስክንድር ማለፍ ሲያስደስታቸው፡ በሌላ በኩል ደግሞ የአቤል ጉዳይ ሁለቱንም ግራ አጋባቸው ። እስክንድር
ልቡ ፈራ ። ስሜቱ መጥፎ ነገር ጠረጠረ ። ለማንኛውም ተያይዘው ውጤቱ ወደ ተዘጋጀበት ቢሮ ሒዱ ።

“ አቤት ! ምን ነበር ? " አለቻቸው ጸሐፊዋ ፡ የምታንቀጭቅጨውን ታይፕ አቋርጣ ። “ የእሱ ውጤት አልወጣም ። እና ... ብሎ እስክንድር ወደ አቤል እያመለከተ
ንግግሩን ሳይጨርስ አቋረጠችው ።

« ስሙ ማን ነው ? ”
“ አቤል ። የፍልስፍና ትምህርት ክፍል

“አሃ ! አቤል ሙሉዬ ፡ ያንተ ውጤት አልደረሰንም እስኪ ዮናታንን ሒደህ አነጋግራቸው አለችና ሥራዎን
ቀጠለች ።

“ውጤቱ ዮናታን ጋር ምን ያደርጋል?” አለ አቤል በልቡ።ዮናታንን ማየት አልፈለገም ነበር ። በዝጉ ውስጥ ሲሸሻቸው ነው የከረመው። ምክራቸውን አለመስማቱና ሕክምናውን ያለ መቀጠሉ እያሳፈሩት ከእሳቸው ለመራቅ ምክሮ ነበር።

የግዱን ከእስክንድር ጋር ሆኖ ወደ ዮናታን ቢሮ ሔደ።ዮናታን የሉም ። ቢሮኣቸው ተቆልፎአል ።

“ ምን ይሻላል ? ” አለ የእስክንድርን ዐይን ዐይን እያየ

“ ምን ይሻላል ? ” ብሎ እስክንድርም ቃሉን በትካዜ ድምፅ ከደገመ በኋላ ፥ “ እንግዲህ ነገ መጥተን እንጠይቃቸዋለን " መቼም ከአሁን በኋላ አይገቡም ” አለው እያስተዛዘነ።

ነገ እንዴት ይነጋ ይሆን ? የጭንቅ ምሽት ፤የመከራ ሕልም ሌሊት ።

በማግሥቱ ጠዋት አቤልና እስክንድር ዮናታንን ቀድመው ነበር፡ ከቢሮአቸው የደረሱት ።አቤል ዐይናቸውን ማየት
#ሰመመን


#ክፍል_አርባ_ሶስት


#ድርሰት_በሲሳይ_ንጉሱ

.....አቤል በዮናታን መኪና የአራት ኪሎን ቁልቁለት ሲወርድ፥ ወዴት እንደሚሔድ በውል አያውቅም ነበር ዮናታን በድንገት ከመኝታ ክፍሉ አስጠርተውት ነው የወሰዱት "ዛሬ ከእኔ ጋር ነህ” ከማለት ሌላ ፡ ወዴት እንደሚወስዱት አልነገሩትም እሱም አልጠየቃቸውም ።አብዮት አደባባይ ከመድረሳቸው በፊት በሚገኝ አንድ የመኖሪያ ሕንፃ ጀርባ መኪናቸውን አቁመ የሕንፃውን ደረጃዎች ወጡ ። ሦስተኛው ፎቅ ላይ ሲደርሱ በሩ ላይ “
ቁጥር የተጻፈበትን መኖሪያ ቤት ደውል ደወሉ ። አንዲት ፈረንጅ ከውስጥ በሩን ከፍታ ብቅ አለች ።

“አቤል ማለት እሱ ነው ” አሏት ዮናታን በጀርመንኛ።

ሞቅ ካለ ፈገግታ ጋር ሰላምታ ሰጠችው "

“ ባለቤቴ ናት" አሉት ዮናታን ።

ከትውውቁ በኋላ ወደ ቤት ገብተው ተቀመጡ ። አቤል ዮናታን ወደ መኖሪያ ቤታቸው ለምን እንዳመጡት ሊገባው
አልቻለም ። በልቡ ብዙ ነገር እያሰበ በግድግዳዎቹ ላይ የተሰቀሉትን ሥዕሎች አንድ በአንድ በዐይኑ አዳረሳቸው ።
ከዮናታን ባለቤት ጋር በዐይን መሣሣቅ ካልሆነ በስተቀር ቃላት መለዋወጥ አልቻሉም ። እንግሊዝኛ ለመግባቢያ
ያህል ትችላለች ። ግን ዮናታን ጀርመንኛ ስለሚያውቁ ቤታቸው ውስጥ የሚነጋገሩት በጀርመንኛ ነው ። አንዳንዴም የምታውቃቸውን ጥቂት የአማርኛ ቃላት በመጠቀም እንግዶቻቸውን እያሣቀች ታዝናናለች "

“ይኽውልህ እዘህ ፎቅ ላይ ተሰቅለን ነው የምንኖረው ” በማለት ዮናታን ፡ ከአቤል ጋር ጨዋታ ከፈቱ።

አቤል ፈገግ አለ ።

“አንተ ወደፊት ምን ዐይነት ቤት ውስጥ መኖር ነው የምትመርጠው ? ” ሲሉ ጠየቁት ።

“ምን ዐይነት ጥያቄ ነው ?” አለ በልቡ ፥ “ አሁን ባለው የቤት ችግር ሁኔታ አንገት ማስገቢያ ይገኝ እንጂ፡ የቤት ምርጫ ይጠየቃል እንዴ ?” ዮናታን ግን እሱን ማጫወት ሲሉ አፋቸው ላይ የመጣላቸው አርዕስት ሆኖ ነው እንጂ
የሚኖሩበትን ሀገር እውነታ አጥተውት አልነበረም ።

“ በአሁኑ ጊዜ አንገት ማስገቢያ ከተገኘ ምን ምርጫ አለ ? ” አላቸው እየተቅለሰለሰ ።

የመመረቂያው ዓመት ላይ ቢሆንም ከዩኒቨርስቲዉ ሲመጣ ስለሚገባበት ቤት አስቦ አያውቅም ። ከቤት ጋር የትዳርም ሐሳብ ይኖራል ። ያንንም ቢሆን አስቦ አያውቅም ። በእርግጥም ስለ ቤት ማሰብ የሚችለው የሥራው ምድብ ቦታ ካወቀ በኋላ ነበር ።

“ አይዞህ ፡ የጊዜ ጉዳይ ነው ” አሉ ዮናታን ፡ “ አሁን ካለንበት ችግር ወጥተን የምርጫችንን የምናገኝበት ጊዜ ይመጣል ። ምን አጣን ብልህ ነው ?ለም መሬት አለን ሀገራችንን ዐልፈው ውጭ የሚፈሱ ወንዞች አሉን : ተፋቅረንና ተባብረን ጠንክረን ከሰራን ብሩህ ተስፋ ይጠብቀናል።

ባለቤታቸው ሻይ ይዛ መጣች ። እሷም ቀስ እያለች ከአቤል ጋር በእንግሊዝኛ መጨዋወት ጀመረች ። ስለ የአቤል ብዙ ነገር ታውቃለችና ሁኔታውን ሁሉ ከመጀመሪያው እስካሁን ባሏ ያጫውቷት ስለ ነበር፡ ለአቤል ደኅና አመለካከት አላት ሁሉም ለጊዜው ዝም ዝም ቢሉም ፡ እንግድነቱን ለማስታመም ካልሆነ በስተቀር ዝምታው ካለመተዋወቅ
የመነጨ አልነበረም ።

አንዳንድ ማኅበራዊ መግባቢያዎችንና ጨዋታዎችን እየተለዋጡ ሻዩ ተጠጥተው ስኒዎቹ ተነሡ «ከዚያ ዮናታን የቤቱን ክፍሎች ለአቤል ማስጎብኘት ጀመሩ ። ይህ ተግባራቸው ዓላማ ነበረው ። በመጀመሪያ መኝታ ቤቱን ፥ ወጥ ቤቱንና መታጠቢያ ቤቱን አሳዩት ።በመጨረሻም ወደ አንዲት አነስተኛ ክፍል ወሰዱት ። በክፍሏ ውስጥ ብዙ ዕቃ አልነበረም ።፡ አንድ አልጋ እና አነስተኛ ጠረጴዛ ከነወንበሩ ብቻ ይታይበታል ።

“ ይህ ደግሞ የአንተ መኝታ ክፍል ነው ” አሉት ፍርጥም ብለው ።

አቤል ግር አለው ። ድንጋጤ ይሁን ደስታ የተሰማውን ለማወቅ አልቻለም ።

“ ያሉት አልገባኝም ” አላቸው ።

“ ይህ ለአንተ ያዘጋጀሁት መኝታ ክፍል ነው ። ለተወሰነ ጊዜ ከእኔ ጋር እንድትኖር ወስኜአለሁ ። ማንኛውንም ነገር እዚሁ ሊሟላልህ ይችላል ” አሉት " በጥያቄ ሳይሆን በውሳኔ ድምፅ ።

ዮናታን አቤልን እቤታቸው አስቀምጠው ጉዳዩን ለማራአመድ የወሰኑት ሰሞኑን ከባለቤታቸውና ከቢልልኝ ጋር
ተመካክረው ነበር ። በአንድ በኩል የአካባቢ ለውጥ ለአቤል ጤና ይረዳዋል ብለው ነው ። በሌላ በኩል ደግሞ አቤል
በዚህ ዓመት ትምህርቱን ስለማይቀጥል አጠገባቸው አድርገው ሞራሉን በመጠበቅ ለማበረታታት እንዲመቻቸው
ነው ። ዮናታን ከሚስታቸው ጋር ሆነው ይህን የወሰኑት ስለ አቤል የተደረገው የሥነ ልቡና ጥናት ጥሩ ደረጃ ላይ
መድረሱን ካረጋገጡ በኋላ ፡ የመንፈስ ደስታ አግኝተው ነው ። በአቤል ጐብዝና ባሳቸው የጠነከረ እምነት በቅን፥
ልባቸው የጀመሩት ጉዳይ ከዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ አስደስቷቸው በበለጠ እንዲቀጥሉበት ገፋፍቷቸዋል ።

ዮናታን አቤልን ወደ ቤታቸው ከማምጣታቸው በፊት ይህን ውሳኔአቸውን ያልነገሩት ሆነ ብለው ነው ። ውጭ ቢነግሩት በነገሩ ያመነታ ይሆናል ። ቤት ውስጥ ገብቶ የተዘጋጀለትን ክፍል ካየ በኋላ ግን አንድም ሊወደው ይችላል !ያም ካልሆነ ድካማቸውንና የሰጡትን ክብር በማገናዘብ በእሺታ ይቀበለዋል የሚል ግምት ነበራቸው ። እንዳሰቡትም አቤል ክፍሉን ከተመለከተ በኋላ"የእምቢታ ስሜት አላየለበትም ። ነገር ግን አፉን ሞልቶ “ እሺ ይሁን ” ማለትም አልቻለም ። የተዘበራረቀ ስሜት ሰፈረበት ። ብቸኛኔቲን ይንዳል ። እናም ብቸኛነቱን ሊያስታምምበት የሚችለውን ይህን ክፍል ወድዶታል። ግን ደግሞ የዩኒቨርስቲውን ግቢ መልቀቅ ? ከትዕግሥት ዐይን መራቅ ?

“ እንዴት ነው ? ጥሩ ክፍል ነች ? ” አሉት ዮናታንበላዩ ላይ የሚያንዣብበውን የማመንታት ጥላ በሚገፍ ድምፅ ።

“ ጥሩ ነው ” ሲል ራሱን ነቀነቀ ።

“ የመጻሕፍት ክፍል ከእኔ ጋር በጋራ መጠቀም እንችላለን ” ብለው ፡ ወደ ጥናት ክፍላቸው ወሰዱት ።

መደርደሪያዎቹ በመጽሐፍ ጥቅጥቅ ያሉበት ክፍል ነበር ። መለስተኛ “ላይብራሪ !” የቀለም ትምህርት የፍልሰፍና የምርምር እና ልብ ወለድ መጽሐፎች ፥ እንዲሁም ወርኃዊ መጽሔቶች በመልክ በመልካቸው ተደርድረዋል ።አቤል ስሜቱ ለመንቃት ሲንጠራራ ተሰማው ። ባለ ሦስት ጥራዝ የማርክስ “ ካፒታል ” ከመጽሐፎቹ ሁሉ ጎልቶ ዐይኑን ሳበው ።

ይኸው ነው እንግዲህ ፡ ወደ ማታ ዕቃህን ከካምፓስ ማምጣት እንችላለን ” አሉትና ተመልሰው ወደ ሳሎኑ አመሩ ። አቤልም እግሩን በሐሳብ እየጎተተ ተከተላቸው ።

ሻንጣውን ለማምጣት ከዮናታን ጋር ወደ ዩኒቨርስቲዉ ሲሄድ፡ መንገድ ላይ ልቡ ማመንታቱ አልቀረም ። ዩኒቨርስ
ቲዉን ለቅቆ የመውጣቱን ነገር ልቡ ባይቀበለውም ሁኔታውን ሲያመዛዝን ዮናታን እሱን ለመርዳት ያደረጉለት ጥረት
ከብዶታየው ። እናም በባዶ ግትር እምነት ገደል አፋፍ ላይ የቆመች ሕይወቱ በሰው እጅ ጥበቃ ሥር እየዋለች መሔዷ ታመቀው ። የጥገኝነት ስሜት ተሰማው ። ጥገኝነትን አይወድም ነበር " ከድህነቱ ጋር ሞቶ መቀበር ከልጅነቱ ጀምሮ
ያደረበት ጸባይ ነው ። ግላዊ ነጻነቱን ይሻል ፤ግን የሌላውን እርዳታ ሳይሻ፡ብቸኛ እና ነጻ ሕይወት የኖረ ሰው በዚህ ዓለም
ላይ ማን አለ ?

ከመኝታ ቤቱ ገብቶ ሻንጣውን ሲያወጣ፡ አቤል ሆዱን ባር ባር አለው ። በዚህ መኝታ ክፍል ውስጥ የሆዱን አውጥቶ ለጓደኞቹ በደንብ ያጫወተበት ቀን ወይም በጋራ ያሳለፉዋቸው ታላላቅ ትውስቶች የሉም ። ነገር ግን ባዶ ትንፋሽም ቢሆን ከለመዱት ሲለዩ ያባባል ። ከርሱ ይበልጥ ሆጹ የባባው እስክንድር ነበር። ሆኖም የዮናታን ጥረት ለእቤል መልካም ሕይወት ስለሆነ፡ ፊቱ ላይ ምንም ዐይነት ቅሬታ እንዳይታይ ከውስጥ እየታገለ
#ሰመመን


#ክፍል_አርባ_አራት


#ድርሰት_በሲሳይ_ንጉሱ

....ለጥያቄዋ መልስ በመጠበቅ ዐይነት ሦስቱንም ተመለከተቸቻው ፡ ዐይኖቿ አንድ ቦታ እይረጐም በነጭ ቆዳዋ
ላይ ሰማያዊ መሳይ ሥራሥሮቿ ዐልፎ ዐልፎ ይታያሉ ።ገጽታዋ ላይ ፍቅርና ትሕትና ይነበባል ።

ዮናታንና እስክንድር ቡና ሲመርጡ እቤል ሻይ አለ ።ሚስታቸው ወደ ጓዳ ከመሔዷ በፊት ዮናታን ክንዷን ይዘው እጅዋ ላይ ሳም እያረጓት ። ለመልካም መስተንግዶዋ
ምስጋናቸውን የሚገልጹበት መንገድ ነበር

እስክንድር ዐይኑን ማመን አቃተው ወይም ያየው ነገር ሕልም መሰለው ። እውነት ፍቅር ይሆን ? አለ በልቡ ።የትዳር ዕድሜአቸውን ለማወቅ ጓጓ አፍላ ፍቅረኞች ካልሆኑ በስተቀር ተጋብተው በቆዩ ሰዎች መሐል አይቶ የማያውቀውን ሁኔታ ማየቱ ነው ያስደነቀው ያውም በእንግዳ ፊት !

“ ሊብሊንግ ሚስቴም እናቴም ናት ። የሕይወት ጣእም የሚታወቀኝ እሷን አጠገቤ ሳገኛት ነው አሉ ዮናታን ፥
ሚስታቸው ወደ ጓዳ ከገባች በኋላ ። “ ሰውን ማስደሰት መቻል ቀላል ነገር አይደለም ። ሊብሊንግ ይህን ችሎታ በተፈጥሮዋ ታድላዋለች ። ሁል ጊዜ ደስተኛ ነች እንደሚገባኝ ፡ ደስታዋን የምታገኘው ሰዎችን በማስደሰት ነው ።
አቤል ሁኔታዎች እስኪመቻቹለት ከእኛ ጋር እንዲኖር ሐሳቡን ቀድማ ያቀረበችልኝ እሷ ናት ።

አቤል በጥያቄ መልክ ዐይኑን እቁለጨለጨ ።

ከአሁን በፊት የት ታውቀኛለች ?ብሎ ነበር ራሱን የጠየቀው ። ማንኛውም ነገር በዮናታን ሊደርሳት እንደሚችል ወዲያው ገመተ። ወደዚህ ቤት የመምጣቱ ሐሳብ ከእሷ መመንጨቱን ሲሰማ በልቡ ውስጥ ለሴትዮዋ ልዩ ስሜት ተፈጠረበት

“ ከተጋባችሁ ? ” ሲል እስክንድር ፈራ ተባ በሚል ድምፅ ጠየቀ ።

“ ኦ! ስድስት ዓመት ያህል ሆኖአል ። በርሊን በነበርኩበት ጊዜ፡አንዴ ታምሜ ተኝቼ ሐኪም ቤት ውስጥ አስታማሚዬ ሆና ነው ያገኘኋት ። ”

ዮናታን ይህን ሲናገሩ ድምፃቸው የተለየ ቃና ነበረው ።የፍቅረኞች የመጀመሪያ ትውውቅ በልባቸው ታላቅ ትውስት
ጥሎ ያልፋል ። ዮናታንም ለእስክንድር በሰጡት መልስ ሳቢያ ከስድስት ዓመት በፊት የተፈጸመ ትውስት ውስጥ ገቡ .....
ዮናታን በምሥራቅ ጀርመን ውስጥ በሚገኘው ትልቅ ዩኒቨርስቲ የድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ለተወሰኑ ዓመታት በምቦልት ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር ሆነው አገልግለው ነበር ። እዚያ ሳሉ አንድ ጊዜ የሆድ ውስጥ ሕመም ያድርባቸውና በርሊን ቤክ እሚባለው
ሆስፒታል ይገባሉ ።

በርሊን ቤክ ፣ ከመሃል ከተማው ሀያ ኪሎ ሜትር ያህል ይርቃል ። ውስጡ በአምስት ግቢዎች ተከፍሎ ፡ በጠቅላላ
ዐሥር ሺህ አልጋዎች ያሉት ሰፊ ሆስፒታል ነው ። ዮናታን የተኙት፡“ታይል አይንስ” በሚባለው ግቢ፡ “ እስታስዩን አይን ሁንደርት ሲ ” ክፍል ውስጥ ነበር ።
በማገገም ላይ እንዳሉ አንዲት ነርስ ሲያዩ ልባቸው ይደነግጣል ። ይህች ነርስ ፊቷ ላይ ፈገግታ የተሳለ እንጂ እንደ ሌላው ሰው አንዳንድ ጊዜ ብቻ የምትሥቅ አትመስልም ። ሕሙማንን ለመጎብኘት ስትገባ በሕመም የደከመ ስሜታቸውን በፈገግታ ታነቃቃዋለች ። በውስጥ ቁስል
የዳመነ ፊታቸውን ፈገግታዋ ብርሃን ሆኖ ያፈካዋል ። መስተንግዶዋ ፍቅር የሞላበት በመሆኑ'በክፍሏ ሕሙማን ዘንድ ተወዳጅ ነበረች ። ወደ በሽተኞቹ ክፍል ለመግባት የጉብኝት ወይም የመድኃኒት ዕደላ ሰዓት እስኪደርስ ወይም እነሱ በደወል እስኪጠሩዋት አትጠብቅም ። ብቅ ጥልቅ እንዳለች
ነው የምትውለው ። ልማድ ሆኖባት ሁሌ ትቸኩላለች ።እናም አንድ ቦታ ቆማ አትቆይም ።

ዮናታን ልባቸው ከደነገጠላት ጊዜ ጀምሮ ይህን ችኮላዋን አልወደዱላትም ። ክፍላቸው ገብታ ስትወጣ ፀሐይ
ብልጭ ብላ ድርግም ያለች ያህል ስሜታቸው ይከፋ ጀመር ።

ሥራዋን ጨርሳ ወደ ቤትዋ ልትሔድ በሽተኞቹን ስትሰናበታቸው። የዮናታን ልብ ይረበሽ ነበር ።ሌሊት አልመዋት አድረው ጠዋት ዐይኗን የሚያዩበትን ጊዜ መናፈቅ ሲጀምሩ ልባቸው ፍቅር ፍለጋ ዳዴ እያለ መሆኑን ገመቱ ። ሞኒካ የሚለው ስም አሁንም አሁንም ጆሮአቸው፡ ውስጥ ይደውል ጀመር ።

አንድ ቀን ከሥራ በኋላ እንደ ልማዷ ልትሰናበታቸው ወደ ክፍላቸው ስትግባ ዮናታን እጅዋን ያዝ አድርገው ቅሬታቸውን ተነፈሱላት ።

"ቆይ እንጂ አትቸኩዪ ። ትንሽ አጫውችኝ ሁሌ መቸኮል ምንድነው ?” አሏት ።

ሞኒካ ፈገግ ብላ ፍቃዳቸውን ለመፈጸም አልጋቸው አጠገብ ትንሽ ቆመች ።

“ እውነት ለምንድነው እንዲህ የምትቸኩዬው ” ሲሉ ጠየቋት ።

“ ልማድ ሆኖብኝ ነው ። በምሰራበት ጊዜ ፍጥነቴ አይታወቀኝም ” አለችና : ትንሽ አሰብ አድርጋ ! “ በዚህ በአራት ዓመት ውስጥ ያፈራሁት ጸባይ ነው” አለቻቸው ።

“ ግን ምነው ! ለምን ? ” አሏት ።

“ለአፍላ ፍቅሬ ያገኘሁት ማካካሻ ራሴን ከይዲያ ወዲህ በማራወጥ ዕረፍት መንሣት ነበር ” አለቻችው ሰሜቷን
ግልጽ አድርጋ።

ከዚህ ንግግሯ ጋር ፊቷ ፍም ሲመስል ተመለከቱት ። ስሜቷ መጨፍገጉን አገጽታዋ ላይ አጠኑ ሰው ሠራሽ
የሚመስሉት ዐይኖችዋ፡በቅርቧ ያለውን ነገር ለማየት የተከለከሉ ይመስል በመስኮቱ ማዶ ከሚታየወው ባዶ ሰማይ ላይ ዐረፉ ።

“ ነገሩ እንዲህ ነው ” ስትል ቀጠለች ። “ ከአራት ዓመት በፊት አፈቅረው የነበረው ወጣት የመጀመርያዬ ነበር ። በመሆንም እጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ ልቤንና ፍቅሬን ሰጥቼው ነበር ለማለት እደፍራለሁ ። ነገር ግን ሁለት ዓመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ጥሎኝ ጠፋ” አለችና ዝም !

“ የት ነው የጠፋው ?” አሏት ዮናታን ፥ ተመስጠው ።

“ ወደ ምዕራብ ጀርመን። እኔ የሰማሁት ጠፍቶ ከሔደ በኋላ ነው እንጂ ምንም ያማከረኝ ነገር አልነበረም ። በእርግጥ
ልቡ መሸፈቱን በአንዳንድ ንግግሮቹ ገምቼ ነበር ። አብዛኛውን ጊዜ በአስተሳሰብ እንጋጫለን ። እኔ በፋሽስቶች ላይ ከፍተኛ ጥላቻ አለኝ ። በሂትለር ዘመን በናዚዎች ታስሮ የማቀቀው አባቴ ቆስሎ በእኔም ላይ ከባድ ተጽዕኖ ነበረው ።ፍቅረኛዬ ግን ያለፈው ትውልድ በፋሺዝም ምን ያህል
እንደ ተሠቃየ ለማጤን ደንታ አልነበረውም በኣፍላ ስሜት ግፊት እኔደሚነቃነቅ እገምት በር ። እናም መጨረሻውን እንደዚያ አደረገወ ። ”

ዮናታን በኀዘን ከንፈራቸውን መጠጡ።

“አያሳዝነኝም ። ልቤን አሳዝኖት ነው የሔደው ”አለች ሞኒካ ፥ ራሷን እየነቀነቀች “ ነገር ግን እሱን ብጠላውም ልቤ ውስጥ የተተከለውን ፍቅር በቀላሉ መንቀል
አልቻልኩም ነበር። ስለዚህ ራሴን በሥራ በማዋከብ ልረሳው ሞከርኩ ። በሚረባውም ፥ በማይረባውም ነገር ነበር ራሴን የማደክመው ። በማያሰፈልግበት ቦታ እፈጥን ነበር ። እየቆየ ሲሔድ ይህ ልማድ እውስጤ ሥር እየሰደያ መጣ። አሁን ያለ ሥራ ለአጭር ጊዜም ቢሆን መቀመጥ አልችልም ። መንፈሴም የሚረካው ፈጠን ፈጠን እያልኩ ከሠራሁ ነው ”አለቻቸውና ፥ ደመናውን ከፊቷ አባርራ ፈገግ አለች ።

ታሪኳ ዮናታንን አጥንታቸውን ሰርስሮ ገብቶ ወደ ፍቅር መዳህ የጀመረ ልባቸውን እደፋፍረው። ነገር ግን ፥
በአፍላነቱ የተጎዳወን የሞኒካን ልብ ለማዳን መቻላቸውን እርግጠኛ አልነበሩም እድሜአቸውን ለማመዛዘን ሞከሩ ።
በዐሥር ዓመት ያህል ይበልጧታል ። ይህ ሁሉ የእንምሮ ማመንታት ነው እንጂ ፥ ፍቅሩ ያለ ምንም ፍርሃት በልባቻው ውስጥ እያደገ መጥቷል ።

ሞኒካም ዮናታን ታሪኳን በተመስጦና በትካዜ ካዳመጡዋት ጊዜ ጀምሮ ስሜታቸውን በማጤን ልቧ ውስጥ ለየት
ያለ አዲስ ስሜት ሲያብብ ተሰማት እና የእሷም ልብ እንደ እሳቸው ልብ ወደ ፍቅር በመዳህ ላይ ሳለ መንገድ ላይ ተገናኙ።

የዘመን መለወጫ በዓል ሲከበር፡ ዮናታን እዚያው ሐኪም ቤት ውስጥ
#ሰመመን


#ክፍል_አርባ_አምስት


#ድርሰት_በሲሳይ_ንጉሱ

አቤል ካምፓሱን በለቀቀ ማግሥት ሳምሶንም ጓዙን ይዞ ስለ ወጣ እስክንድር ፊቱን ወደ ዩኒቨርስቲው ማዞር አስጠልቶት ሦስት ቀን ያህል መኖሪያ ቤቱ ነበር የሰነበተው ። እዚያም ሆኖ የአቤልን ጉዳይ ለማስፈጸም ወዲያ ወዲህ
ማለቱ አልቀረም ። ብርቅነሽን አነጋግሮአት አቤል ያካፈላትን ምስጢር ለቢልልኝ እንድትነግራቸው አድርጓል ። መጀመሪያ ብርቅነሽ ፍርድ ቤት የመቅረብ ያህል ቆጥራው እምቢ ብላ አስቸግራው ነበር ። በብዙ ውትወታና ማሳመን ነው ወደ ቢልልኝ የወሰዳት ። ከእሷም ሌላ አቤል ቀድሞ በርቀት ካስተዋወቀው ሰዎች መሐል ለሥነ ልቡናው ምርምር ጥቂት
ይረዳሉ ብሎ የገመታቸውን ከቢልልኝ ጋር በመመካከር አነጋግሮአቸዋል ። እሱም እንደ ዮናታን በጓደኛው በአቤል ጉዳይ ውስጥ እጁን ማስገባቱና አንዳንድ ጠቃሚ ውጤቶች ማስገኘቱ አስደስቶት የበለጠ እንዲገፋበት እያደረገው
ነበር ።

በአራተኛው ቀን ወደ ካምፓስ ሲገባ ሁለት ሴቶች በጥብቅ ሲፈልጉት እንደ ሰነበቱ ድብርት ነገረው ። ቶሎ ሐሳቡ ውስጥ የመጣችበት ማርታ ነበረች ።

” ምን ዐይነት ሴቶች ? ” አለው ፡ ለማወቅ ቸኩሎ።

“ አንዷ ወፍራም ቀይ ፡ አንዷ መጠነኛ ወይም ሁለቱም አጭሮች ” ካለው በኋላ ፥ የነገሩትን ስም አስታውሶ ።ድብርት“ ቤተልሔምና ትዕግሥት የሚባሉ” አለው
“ አሃ ! ” አለ እስክንድር ። የተፈለገበት ምክንያት ምን እንደሆነ ለመገመት ጊዜ አልወሰደበትም ። ነገር ግን በጣም የጓጓው ስለ አቤል የሚቀርብለት ጥያቄ ከትዕግሥት ከራሷ አፍ ይወጣ እንደሆን ለመስማት ነበር ።
ሁለቱም በምሳ ሰዓት ወደ መመገቢያው አዳራሽ ሊገቡ ሲሉ አገኛቸው ።
በእግር በፈረስ ስትፈለግ የት ነው እንዲህ የጠፋኸው ? ” አለችው ቤተልሔም ።

በመኪና ብትፈልጉ ፡ ታገኙኝ ነበር ! ” ሁለቱም ሴቶች በቀልዱ ሣቁ ።

“ ማርታኮ ፡ ሔደች ! ” አለችው ቤተልሔም ሣቋን ገታ አድርጋ

“ የት?” አላት የደመ ነፍሱን ።

“ ወድቃ ፡ ትላንት ሻንጣዋን ይዛ ግቢውን ለቀቀች ። ”

"እና? እና እኔ ታዲያ እኔ ምኗ መሰልኳት የማርታን መርዶ የጨዋታ መክፈቻ የምታደርግልኝ ”አለ እስክንድር በልቡ ።

“ በራሷ ጥፋት ነው ” አለች ቤተልሔም ፡ ከእስክንድር መልስ ስታጣ ።

“ እንዴት ? ”

"ጸባይ የላትም ። ጸባይ ቢኖራት ኖሮ ህእ ! ” አለችው ፥ እንደ ሕፃን ልጅ ለምቦጭዋን ጥላ ።

“ ጸባይ ወይስ ጭንቅላት ?” እለ እስክንድር በሐሳቡ ።ምን ለማለት እንደ ፈለገች ገብቶታል ። ወዲያው ትዝ ያለው
ማርታ ለማን አጥላልታ ያወራችለት ነገር ነበር ።

“ ያንተስ ጓደኞች ?” አለችው ትዕግሥት በድንገት ።ስለ አቤል ለማወቅ ካላት ጉጉት የተነሣ፥ ሌላውን ጨዋታ
ለስማት ትዕግሥት አጥታ ነበር ።

“ ሳምሶን ወድቆ ተባረረ” አላትና አቋረጠ
ቤተልሔም የሳምሶንን ስም ሲጠራ እሱ ራሱ አጠገቧ የቆመ ያህል ሽምቅቅ አለች ከፍርሀቷ ብዛት ተደብቃው ከርማ ግቢውን ለቅቆ መሔዱን ካረጋገጠች በኋላ ነበር
ከመኝታ ክፍሏ መውጣት የጀመረችው ።

እስክንድር የሳምሶንን መባረር ብቻ ተናግሮ ስለ አቤል ምንም ነገር ሳያነሣ ያቋረጠው ሆነ ብሎ ነበር ። ትዕግሥት
ደፍራ ትጠይቀው እንደሆን ሊፈትናት ፈልጎ ነበር ትዕግሥት ዐይን ዐይኑን አየችው የምትፈልገውን እንዲነግራት በዐይኗ ለመነችው ። ነገር ግን ከእስክንድር አፍ ጠብ ያለ ነገር ኣልነበረም ።

“አቤልስ ? ” አለችው ደፍራ ። ድምጿ ግን ድክምክም ብሎ ነበር።

እስክንድር ደስ አለው ። ትዕግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ የአቤልን ስም በጓደኛው ፊት መጥራቷ በእርግጥም ትልቅ ለውጥ ነበር ። ደስታዊው ስላስደነገጠው ቶሎ መልስ አልሰጣትም ። እሱም ድምፅ እንደ እሷው እንዳይደካክም መጠ ንቀቅ ነበረበት ።

“ አበል እንኳ አልወደቀም ። ግን እሱም ካምፓሱን ለቅቆ ወጥቶአል ” አላት ።

እስክንድር ይህን ሲናገር ከትዕግሥት ፊት ላይ የጠበቀውን ለውጥ አልተመለከተም አቤል ግቢውን መልቀቁ ያስደነግጣታል ብሎ ነበር ። ነገር ግን ትዕግሥትም ሆነች
ቤተልሔም ለነዚህ ዜና እንግዳ አልነበሩም ። አቤል በዮናታን መኪና ሻንጣውን ጭኖ የወጣ ዕለት ነበር ያዩት ተማሪዎች ወሬውን ቀምመው ሲያራቡ ነው የሰነበቱት ። እና አሁን የትዕግሥት ጉጉት የአቤል መውደቅ ትክክለኛ መሆኑን
ማረጋገጥ ብቻ ነበር ።

“ ታዲያ ካልወደቀ ለምን ካምፓሱን ለቅቆ ወጣ ? " አለችወ ትዕግሥት በጥርጣሬ ።

“ በሌላ ምክንያት ነው ”አላትና እስክንድር ለአመላለስ ተቸግሮ ፡ “ ሰፊ ነው ነገሩ ፣ በቁም ጨዋታ የሚያልቅ አይደለም ” አለ።
አላመነችውም ፊቷ ላይ ጥርጣሬ አነበበ የተከፋው ገጽታዋ አቤል ወድቋል ብላ እንደ ደመደመች ይናገራል ።ይህ እስክንድርን ብዙ አላስጨነቀውም ጊዜውን ጠብቆ ሁሉን ነገር እንድታውቀው ይደረጋል ። ዋናው ነገር በሩ መከፈቱ ነውጅ የአቤልን ስም እንስታ በግልጽ መጫወት ጀምራለች።

"ግን ምን ይሆን ' ወይስ ማን ይህን ያደፋፈራት ?? ሲል አሰበ ።

ከደስታው የተነሣ ምሳውን በሚበላበት ጊዜ ጉዳይ እንዳለበት ሰው እየተጣደፈ ቶሎ ቶሎ ነበር የጎረሰው ምግቡን ቶሎ ጨርሶ ያንን ሰው የበዛበት አዳራሽ ለቅቆ ወጥቶ ብቻውን ከሐሳቡ ጋር እየተሣሣቀ ለመፈንደቅ ካልሆነ በስተቀር ፡ ሌላ የሚሔድበት ቦታ አልነበረውም ።

መኝታ ክፍሉ ገብቶ እንደ ወትሮው አጭር የቀን እንቅልፍ ለመተኛት ቢሞክርም አልሆነለትም ከውጭ ይዞት የገባው ደስታ ጠፍቶ ትካዜ ተጫጫነው ። ከክፍሉ ውስጥ አቤልንና ሳምሶንን ማጣቱ ቅር ቅር አሰኘው ወና ቤት ውስጥ የገባ ይመስል ሰውነቱን ቀፈፈው ። ለሚቀጥሉት አራት ወራት በዚህ ክፍል ውስጥ የሚያሳልፈው ሕይወት
በጣም ብቸኛ ሆኖ ታየው ። በእርግጥ አጠንቡ ድብርት አለ ግን ድምፁ ከማይሰማ ሰው ጋር እንዴት ይኖራል ?

ሳምሶን "ጉልቤው" መኝታ ክፍሉን ምን ያህል ያደምቀው እንደ ነበር የገባው አሁን ነው » እየፈሳም ሆነ እየዘለለ ወይም ድብርትን እያበሽቀ ክፍሉን ሕይወት ይሰጠው ነበር ። መቼም መለያየት ክፉ ነው» ፤ እንደዚያ የሚያበሽቀው ድብርት እንኳ ሳምሶን ሲባረር ተገላገልኩ አላለም
ከልቡ ነበር ያዘነላት እስክንድር እንደ ተጋደመ ስለ ሳምሶን ሲያስብ የተለያዩበት ቀን ትዝ አለው ። በሰላም አልነበረም የተለያዩት ።

ሳምሶን ሰው ሳያየው ተደብቆ ካምፓሱን ለመልቀቅ ከለሊቱ አስራ አንድ ሰዓት አካባቢ ዕቃውን ሲያሰነዳዳ እስክንድር ድንገት ከእንቅልፉ ባነነ ። ሆኖም አዝማሚያው ስለገባው እስከ መጨረሻው ልመልከት ብሎ ፊቱን ከአንሶላው ውስጥ ሳያወጣ ጭጭ ብሎ ያዳምጥ ጀመር። ሻንጣውን አዘገጃጅቶ ጨርሶ ሲወጣ በሩጋ ሲደርስ ከአንሶላው ውስጥ አሾልቆ ተመለከተውና ፡ “ ሳምሶን ! ” ብሎ በኃይለ ቃል ጠራው።

"ምነው ? ! ”አለ ሳምሶን ዘወር ብሎ ከቁጣ ባልተናነሰ ድምፅ ስለተነቃበት ተናዶ ነበር።

"ምን ሆነሃል ? ”

"መሄዴ ነው"

“ ታዲያ እንዲህ ነው እንዴ የሚኬደው ? ምነው ሳምሶን ? የተወሰነ ጊዜም ቢሆን በጓደኝነት አሳልፈናል ። ቻው ብለኸን በሰላም ሸኝተንህ ፥ ብንለያይ ምናለበት ? መውደቅ በአንተ አልተጀመረ ! ” አለው እስክንድር ፥ ሆድ ብሶት ።

“ ሸኝ አልፈልግም ! ያው ሰፈር እንገናኛለን” ! ብሉ ጥሎት ሔደ ።

ሰው ለምን ድክመቱን ለመሸፈን ሲል እውሬ ይሆናል?” አለ እስክንድር በልቡ ። በሳምሶን አልበሸቀበትም " እንዲያውም ፡ “ በዚህ በንዴቱ ሰዓት ምግብ ቢቀርብለት
እንደ ቀድሞው ይበላ ይሆን ? ” ብሎ አስቦ ሣቅ አለ ። “ ጥርሳሞች ! ” ሲል በሐሳቡ ታየው ።ሰው
#ሰመመን


#ክፍል_አርባ_ስድስት


#ድርሰት_በሲሳይ_ንጉሱ

....ቢልልኝና ረዳቶቻቸው በስብሰባው አዳራሽ ቀድሞው ቦታቸውን ይዘዋል ። ከዩኒቨርስቲው አስተዳደርና ትምህርት
ክፍል በአቤል ላይ የተካሔዶውን የሳይኮሉጄ ጥናት እንዲያዳምጡ
የተጋብዙ፥ እንግዶች እየተንጠባጠቡ ገቡ

ዮናታን ፈገግታ በፈገግታ ሆነው አዳራሹ መግቢያ በር ላይ ከእስክንድር ጋር ቆመው ለእንግዶቻቸው ሞቅ ያለ ሰላምታ በመስጠት ላይ ይገኛሉ። እስክንድር ከዮናታ ግዙፍ ቁመና ስር ግብቶ አንድ ፍሬ ልጅ ይመስላል። እንግዶቻቸውን
አስገብተው ከጨረሱ በኋላ እነሱም ገብተው ተቀመጡ።

ቢልልኝ ንግግሩን ለመክፈት ተነስተው ጎሮሮአቸውን ሲሰሉ አዳራሹ ጸጥ አለ ።

“ እንግዶቻችን ፡ እንኳን ደኅና መጣችሁ የዛሬው አርዕስታችን በዐይን ፍቅር የተለከፈ ወይም የተጠመደ አንድ ወጣት ነው ። የሥነ ልቦና ጥናት ክፍላችን በዚህ
ወጣት ችግር ላይ አቅሙ በፈቀደ መጠን ጥናት አድርጎ ውጤቱን ይዞ ቀርቧል ። ”

እንግዶቹ መሐል ጥናቱ የተካደበት ወጣት ማን እንደሆነ የሚያቁ ስለነበሩ፥ በስሜታቸው ውስጥ ወጣቱን የማወቅ ጉጉት ያዛቸው ። አቶ መአምርና ዶክተር አጥናፉ እንዲሁም ሌሎች ከአሁን በፊት ዮናታን የአቤልን ጐዳይ ያናገሯቸው ሰዎች ቸል ያሉት ጉዳይ አድጎ እዚህ መድረሱ ሳያስደንቃቸውም ሳያሳፍራቸዉም አልቃረም የአንድ
ተማሪ የዓይን ፍቅር ችግር፡ ክብደት ተሰጥቶት ይህን ያህል መጠናቱ አስገርሞአቸው አዳራሹ ወስጥ እንዲያው ለትዝብት የተቀመጡም አልጠፉም

በመጀመሪያ ለዚህ ተማሪ ግላዊ ችግር አትክሮትና ክብደት ሰጥተውት ሳይታክቱ ጥረት በማድረግ ለደከመለት
ለፍልስፍና መምህር ዮናታን ምስጋና እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ ። ”

”ሞቅ ያለም” ባይሆን ድጋፉን የሚገልጽ መጠነኛ ጭባ ጨባ ሲሰማ ፥ ዮናታንም ሳያስቡት ለራሳቸው እያጨበጨቡ
ነበር ።

ዮናታን በዕውቀቱ የሚተማመኑበት ጎበዝ ተማርያቸው ሲደክም ወይም ሲሰንፍ እያዩ ቸል ቢሉት ኖሮ የአቤል ውስጣዊ ችግር ተዳፍኖ ውጤቱ ከዩኒቨርስቲው መባረር ነበር በዚህም ሆነ በሌላ ተመሳሳይ ችግር ከአሁን በፊት በርካተታ ጎበዝ ተማሪዎች በአጭር እንደ ቀሩ ጥርጥር የለውም።

በመደበኛ ተማሪነት ወደ ዩኒቨርስቲያችን ከሚገቡት መሐል አብዛኛዎቹ ወጣቶች ናቸው ። ጥሩውንና ገንቢውን ነገር በፍጥነት እንደሚቀበሉ ሁሉ ፥ ለአደጋና ለአፍራሽ ነገሮችም በቀላሉ ይጋለጣሉ። ቀዩኒቨርስቲያችን በተካሔው የሳይኮሎጂ ጥናት ወሠረት የተማሪዎች ዋነኛ ችግር፥
ሦስት ናቸው ። አንደኛ ፡ ወላጆቻቸው ችግረኞች በሆኑ ተማሪዎች ላይ የሚታየው የኢኮኖሚ ችግር ነው ። ይኸው ችግራቸው እያስገደዳቸው የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን እያቋረጡ የወጡ ተማሪዎች አልጠፉም ። ሁለተኛ ፡ የማርክ ወይም የደረጃ ችግር ነው ። ማንኛውም ተማሪ አነስተኛ ውጤት ማግኘት አይፈልግም ። ነገር ግን ፉክክር እስካለ ድረስ መበላለጥ አለ ። ይህን ሐቅ መቀበል አቅቷቸው ፥ ወይም ለጥናት
የሚያደርጉት ጥረትና የሚያገኙት ውጤት አልገጣጠም እያላቸው ከራሳቸው ጋር የሚጣሉም ሞልተዋል ። ሦስተኛ
በሁለቱ ትርጉም ጾታዎች ግንኙነት ላይ የሚታየው ችግር ወይም በድፍን ፍቅር ” እየተባለ የሚጠራው ነው ።

ዛሬ ይዘን የቀረብነው በዚ በሦስተኛው ችግር የተጠመደ ወጣት አርዕስት ነው። ወደ ወጣቱ ጉዳይ ከመግባታችን በፊት ፍቅር የሚለውን ቃል ለማተት እንገደዳለን
እዚህ ላይ የማተኩረው በሁለቱ፡ ጾታዎች መካከል ዕድሜን ተከትሎ የሚመጣው ፍቅር ላይ ነው ።

“ ፍቅር በልባችን ውስጥ ታላቅ ቦታና ክብደት ያለው :ከልባችን ወጭ ግን የሚገባውን ክብደትትና አትኩሮት የነፈግነው ጉዳይ ነው ብል ማጋነን አይመስለኝም » አንድ ፈላስፋ እንዳለው ፥ ዓለምን የሚያንቀሳቅሷት ፍቅርና ረሃብ
ናቸው አንጋፋው ሳይኮሎጂስት ፎሮይድ የፍቅርን ክብደት ሲገልጽ ጥሳቻ ማለት ሞት ነው ፍቅር ደግሞ ከጥላቻ የጠነከረ ነው እናም ፍቅር ከሞት ይጠነክራል ማለት ነው” ይለዋል ። በመሠረቱ ጤናማ የሆነና ጤናማ ያልሆነ የፍቅር ዐይነት አለ ሌላው የሥነ ልቡና ጥናት ሊቅ ሆርኒ
እንደሚለው ጤናማ ያልሆነው የፍቅር ፍላጎት ጠንክሮ ሊገለጽ የሚችለው ለፍቅር ባለን ከመጠን ያለፈ ግምት ነው ።

“ ለመሆኑ ፍቅር ምንድን ነው ? ከባድ ጥያቄ ነው። አብዛኛዎቻችን ፡ፍቅር ዕውር ነው” እንላለን ። ነገር ግን ፍቅር ዕውር አይደለም። ፍቅርን በግድ ዕውር የምናደርገው እኛው ነን ። ወይም በፍቅር ላይ ዕውራኑ እኛ ነን ለማለት እደፍራለሁ ። ይህም ራሱን የቻለ ምክንያት አለን ። የባህል ኋላ ቀርነታችን ፍቅርና ወሲብን ውስጥ ውስጡን እንድናደርጋቸው እንጂ በአደባባይ እንዳንወያይባቸውም። ስለሚያፍነን ?ወይም ከልጅነታችንና ከዝቅተኛ ክፍል ጀምሮ በትምህርት
መልክ ስለማይሰጥ ይመስለኛል ዕውር የሚሆንብን ። አሁንም ሌላው ሳይኮሎጂስት አንግያል እንዲህ ይላል ። “እውነተኛ ፍቅር ዕውር አይደለም ፤ እንዲያውም ዐይናማ ነው ሌሎች የማያዩትን ያያል ። ”

“በርካታ የሥነ ልቡና ጥናት ሊቃውንት ለፍቅር በቅርጽ የተለያየ በይዘቱ ግን የተቀራረበ ትርጓሜ ሰጥተውታል ።
ይሁንና አብዛኛዎቹ “ ፍቅር መተሳሰር ነው በሚለው የተስማሙ ይመስላል ። ሆርኒ እንደሚለው ፍቅር ራስን በግብታዊነት ለሌላው የመስጠት ችሎታ ነው ። ከአብዛኛው የቀን ተቀን ገጠመኛችን እንደምንረዳው ፍቅር የመላማመድም
ውጤት ነው ።

ይህ እንግዲህ በጥቅሉ ለፍቅር ያለን ግምት ነው ።ወደ ዋናው አርዕስተ
ነገራችን ስንመጣ ፥ አቤል የተጠመደው
በዐይን ፍቅር ሆኖ እናገኘዋለን ።

ከተሳታፊዎቹ መሐል አንድ ሰው እጁን ሲያወጣ አይተው ቢልልኝ ንግግራቸውን አቋረጡ ሰውየው ይቅርታ ጠይቆ ጥያቄውን ቀጠለ “ የዐይን ፍቅር የሚለው አርዕስት እንግዳ ነው የሆነብኝ ። ደሞም ለፍቅር ከተሰጠው ሐተታ ጋር የሚጋጭ መስለኝ ። እና በመጀመሪያ ይህንን ሊያብራሪልኝ ቢችሉ።

ጠያቂዉ እጅ ነሥቶ ተቀመጠ ቢልልኝ ቀጠሉ "

“ወደያዚያ ልመጣ ነበር ። በእርግጥም የዓይን ፍቅር ለብዝዎቻችን እንግዳ አርዕስት እንደሚሆን እገምታለሁ ።
በሌላ ስያሜ ፤አስቸጋሪ በመሆኑ ነው በዚሁ ሰም መጥራት የተገደድነው። ወይነቱ የደመ ነፍስ ፍቅር ነው ። አንድን
ነገር አይቶ መወደድ ስሜት ልብ ሲደንግጥ ማንኛውም ዐይነት ፍቅር የሚጀምረው ከዐይንኮ ነው ያላዩት
ሀገር አይናፍቅም ” ይባል የለ ! አይተው ሳያልሙ መላመድ ሆነ መተባበር አይኖርም የሚወዱት ነገር ዓይን ውስጥ ከተቀረጸ በኋላ ነው መተሳሰሩ የሚቀጥለው ። ነገር ግን አይቶ በመውደድ ስሜት ልብ የደነገለጠለት ሰው ተቀራርቦ በአካልና በመንፈስ መተሳሰሩ ቀርቶ በዐይን ልማድ ላይ
ብቻ ሲወሰን ፥ ከዐይን ፍቅር የተሻለ ስያሜ እናገኝለትም።

ይህ ዐይነቱ ሁኔታ” ነው በአቤልና በወደዳት ኮረዳ መሐል የታየው በጥናታችን እንደደረስንበት
አቤል ትዕግሥት አዳነ የምትባለዋን የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ አይቶ ልቡ ውስጥ ከቀረጻት ጀምሮ እነሆ ለአራት ወራት ያህል ያለ አንዳች የተቀራረበ ግንኙነት በዐይኑ ብቻ ወዶአታል ።
በቅርቡ ለውጡን ከተከታተሉት ሰዎች መረዳት እንደቻልነው አቤል ትዕግስትን ቀርቦ ባያነጋግራትም ፥ ቀጥተኛ
የአፍቃሪ ስሜት ይታይበት ነበረ ። በቂ ያለመብላት እንቅልፍ ማጣት ትምህርቱን መጥላትና ብቸኛ መሆን በዐይን ፍቅር ከተጠመደ ወዲህ ያሳያቸው የጸባይ ለውጦች ናቸወ፡፡ ልጅቷን ሳያያት ውሎ መደር፤ አይችልም ። ነገር ግን ይህን እይታውንም ሆነ ውስጣዊ መውደዱን ሰው እንዳያውቅበት በመጠንቀቅ ብቻውን ተሰቃያቷል ። ደረጃው ይለይ እንጂ ትዕግሥት ራሷም ከቀን በኋላ የዐይን
#ሰመመን


#ክፍል_አርባ_ሰባት


#ድርሰት_በሲሳይ_ንጉሱ

“ሕመሙ በአቤል ላይ ሊጠነክርበት የቻለው ፍቅሩ ከዐይን ባለማለፉ ነው የሚል ግምት አለን ። የዐይን ፍቅር
የሚጠነክርበት ምክንያት የወጭውን ወይም ያጓጓውን ክፍል ብቻ ስለሚወድ ነው ። ተቀራርቦ ውስጣዊ ገጽታዎችን የሚተያዩበት አፍላ ፍቅር የሕመም ኃይሉ ሊቀንስ ይችላል ፤ ምክንያቱም በሰዎች መልክም ሆነ ባህርይ ፍጹምነት የለምና ነው ። ለዐይን ፍቅር አቤል የመጀመሪያ ሰው ኣይደለም ። ችግራቸው አድጎ እንዲህ አደባባይ ባይወጣም የዚህ
በሽታ ምርኮኞች ጥቂት አይደሉም ። መልካሙ ተበጀ
“ ሰላምታ ኣልሰጠኋት # አላነጋገርኳት ፥ በዐይን ብቻ እያየሁ አንድ ዓመት ወደድኳት ”” እያለ የሚጫወተው ዘፈን
በብዙ ሰዎች መወደዱና በዘፈን ምርጫ ፕሮግራም በተደጋጋ መቅረቡ ችግሩ በጥቂት ሰዎች ብቻ ያልተወሰነ መሆኑን
ያስገነዝበናል ።

ቢልልኝ ንግግራቸውን አቋርጠው ለጥያቄ ፋታ ሰጡ ።ነገር ግን ሁሉም በተመሳሳይ ከማዳመጥ በቀር ለጥያቄ እጁን
ያወጣ አልተገኘም ።

“ መልካም ! ” ሲሉ ቀጠሉ ቢልልኝ ፣ “ የእቤል ፍቅር ከዐይን ያላለፈበትንና ስሜቱን ደብቆ በግሉ የሚሰቃይባቸውን ምክንያቶች በመጠኑ አይተናል ። እስቲ ደግሞ የትዕግሥት መልክ ወይም ቁመና አቤልን እንዴት ሳበው ?ወይም ትዕግሥት አቤል ዓይን ወሰጥ እንዴት ልትገባ
ቻለች ? የሚለውን ነጥብ እናያለን ። ለዚህ ጥናት እንዲረዳን የትዕግሥትን ፎቶግራፍ ወስደን ከአቤል የሕይወት ታሪክ ጋር ለማስተያየት ሞክረን ነበር ። ሆኖም ፥ በአገራችን የሥነ ልቡና ጥናት አሁን ካለበት ዝቅተኛ ደረጃና የኢኮኖሚ
ችግር አንጻር አቤል ከጎንደር ሕይወቱ ጀምሮ የተቀራረባቸው ዋና ዋና የሴት ምስሎች ማግኘት አስቸጋሪ ሆኖብናል ። በጎንደር ዉስጥ አንድ ዋርካ ሥር አዘውትረው ን ይገናኙ የነበሩ ሁለት ፍቅረኞች በአቤል የልጅነት ጭንቅላት
ውስጥ ከፍተኛውን ቦታ ይዘው ይገኛሉ ። ምናልባትም የልጅቷ መልክ ወይም ቁመና ከአሁኗ ትዕግሥት ጋር የሚመሳ
ሰልበት አለ የሚል ግምት አለን ።
አቤል አንድ ቀን አብሯት ላደረው ሴትኛ አዳሪ እንዳጫወቻት

(ይህን ስታነቡ የተሰማቹ ስሜት እኔንም ተሰምቶኛል ግን በጊዜው ችግር አልነበረውም መሰለኝ)

ከሆኔ ፥ ትዕግሥትን ከዱሮ ጀምሮ የሚያውቃት ይመስለዋል ። ነገር ግን አቤልና ትዕግሥት በተለያየ ክፍለ ሀገር ስላደጉ፡የቆየ ትውውቅ ሊኖራቸው አይችልም ።ቁም ነገሩ፡የእሷን የመሰለ መልክ ከልጅነቱ ጀምሮ ሳያስበው
ጭንቅላቱ ውስጥ ተቀርጾበታል ማስት ነው ። ፎሮይድ እንደሚለው ፍቅር የሚጀምረው በልጅነት ነው ። በልጅነታ
ችን የምናፈቅረውና የምንፈልገው ሰው በጭንቅላታችን ውስጥ ተደብቆ እድጎ ነው- በጉልምስናችን ጊዜ ምርጫችን
የሚሆነው ። የመልክ ወይም የውበት ማነጻጸሪያችንም የሚመሠረተው ባደግንበት አካባቢ ዓይን ነው ። በሀገራችን በተዘዋዋሪም ቢሆን ይህን ሐቅ የሚያንጸባርቁ አንዳንድ አባባሎች አሉ ። ለምሳሌም ፥ ባልና ሚስት ከአንድ ዉሃ ይቀዳሉ ” ሲባል በሁለቱም ውስጥ ተቀርጾ ያደገና ተግናኙ በኋላ የዳበረ ተመሳሳይ ስሜትና ምርጫ መኖሩን ያሳያል ። ሌላው ደግሞ ፡ የ እናትህን የመሰለች እስክታገኝ ሚስት አታገባም ” የሚለውም አነጋገር የሚያሳየን የውበት ማነጻጸሪያዎቻችን ከልጅነት ጀምሮ ጭንቅላታችን ውስጥ የሚቀረጹት ወላጆቻችን ወይም ሌሎች በአካባቢው
በቅርብ የምናገኛቸው ሰዎች መሆናቸውን ነው ።

“ ጀርመናዊው ፈላስፋ ሾፐንሀወር የፍቅረኛ ምርጫን በሚመለከት እንዲህ ብሎ ነበር “ ለፍቅር ምክንያት ከሚሆነው ነገር ዘጠኝ አሥረኛው በአፍቃሪው ወስጥ ያለ ነው። አንድ አሥረኛው ምናልባት በተፈቃሪው ላይ ይኖር ይህናል ። ” ይህም የሚያሳየን አንድ ሰው አፍቅሮ የሚመርጠው ራሱኑ ወይም በውስጡ ያለውን ስሜት እንጂ ከውጭ
አለመሆኑን ነው ። ለማንኛውም ይህ የአፈቃቀር ሁኔታ ለእኛ እንጂ ለአቤል ችግር የለውም ።

ዐይን አይከለከልም : አቤል አይቷል ። መውደድ አይከለከልም ፡ ያያትን ወዷል ። ነገር ግን ፥ ፍቅሩ በዐይን በመወሰኑ ማስደሰቱ ቀርቶ ትርፉ ሕመም ሆኖበታል
እና አሁን እንዴት እንርዳው ነው ጥያቄው ዮናታን አቤልን ለመርዳት በግላቸው ብዙ ጥረዋል ። ከትዕግሥት ጋር አሁን ያለበት ሁኔታ ጤናማ መልክ እንዲይዝ ለማድረግ
ከተቻለ እኛም ከመርዳት ወደኋላ አንልም ሆኖም በትምህርቱ ረገድ ለሚኖረው ችግር የአካዳሚክ ኮሚሽኑን ርዳታ
እንጠብቃለን አቤል በልጅቷ ፍቅር ከተጠመደበት ጊዜ ጀምሮ ፡ “ ትምህርቱ ላይ በጤናማ አዕምሮ ላለመቀመጡ
በርካታ ማስረጃዎች አሉ ምግብ አዳራሽ ውስጥ ከተማሪው መሐል ወድቆ ታሟል፤ በአእምሮ ንክነት ሳይኪያትሪስት ድረስ ተወስዶ ታክሟል " እኚህንና የመሳሰሉትን ማስረጃዎች በመደገፍ አቤል በዚህ ሴሚስተር የተከታትላቸው ኮርሶች ተሰርዘውለት በሚቀጥለው ዓመት እንደገና እንዲጀምራቸው የአካዳሚክ፦ ኮሚሽኑን ፈቃድ እንጠይቃለን ።

“ በእኛ በኩል ያለው ዝግጅት ይኸው ነው አስተያየትም ሆነ ጥያቄ ካለ መድረኩን ለሌሉች እለቃለሁ ። ”

ቢልልኝ ጨርሰው ከተቀመጡ በኋላ ፡ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ያህል ከጎን ለጎን መወያየት ያለፈ ጥያቄ አልነበረም
ዮናታን ተነሥተው አሁን አቤል ያለበትን ሁኔታና ከእሳቸው ጋር ለተወሰነ ጊዜ እንዲኖር መወሰናቸውን ለስብሰባው
ገለጹ " ይህ ሁኔታ የብዙዎቹን ስሜት ለእርዳታ ገፋፍቶ ነበር ዮናታንን ተከትሎ አንድ ሌላ ሰው ለመናገር ተነሣ ።

“ ትንሽ ነገር እንድናገር ይፈቀድልኝ " በእውነት ይህ ጉዳይ አትኩሮት ተሰጥቶት ለዚህ መድረክ መቅረቡ ደስ ያሰኛል እኔ እስከማውቀው ድረስ ጎበዝ ተማሪዎቻችን
በፍቅርም ሆነ በሌላ ማኅበራዊ ችግር እየተደናቀፉ ትምህርታቸውን ሲያቋርጡ እስካሁን ዩኒቨርስቲያችን ብዙም
ትኩረት አልሰጣቸውም ። አንድ ተማሪ ያፈቀራት ልጅ ገድሎ ጓደኛውንም ለመግደል ሲፈልግ ሌላው ሲያብድ
የሥነ ልቡና ጥናት መሰሉችም ሆኑ ዩኒቨርስቲው በቸልታ ነው የተመለከቱት ። ወይም ድርጊቶች ከተከናወኑ በኋላ
ዜናውን ከማድነቁ ላይ ነው የተተኮረው ። ለመሆኑ ፡ ጎበዝ ተማሪያችን በትምህርቱ ሲደክምና ደረጃው ሲቀንስ ያገኘውን ሰጥተን ባወጣ ያውጣህ ከማለት በቀር ተማሪውን በግል ጠርተን ለማጤን ወይም ችግሩን ለማማከር የሞከርን ስንቶቻችን ነን ? ይህ ለማንም መምህር የሚከብድ ርዳታ አይደለም ። ! የሚያሳዝን ቸልተኝነት ያለብን ይመስለኛል አሁን ግን መልካም አጀማመር ነው የታየው ። እንግፋበት እላለሁ ። እኔም ማንኛውንም ዐቅሜ የሚፈቅደውን ርዳታ ለማድረግ ከጎናችሁ እቆማለሁ ። ”

ሰውየው ከኋላ ስለነበር፡ ዮናታን ዘወር ብለው በአድናቆት ተመለከቱት ። እንግዳ አልነበረም ። እዚያው ግቢ የታሪክ መምህር ነው ። “ ወይ ልብ ለልብ አለመተዋወቅ ! አሉ ዮናታን በሐሳባቸው

ቢልልኝ የሰውየው ሐሳብ የግድ እንዲናገሩ ገፋፋቸው ። መልካም ነው ። ድጋፍህን ተቀብለናል ። ሆኖም እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት የእኛ ዓላማ የሚያተኩረው ግለሰቦችን በማስታመም ላይ ሳይሆን ችግራቸውን ወስደን አጠቃላይ መፍትሔ ከመፈለጉ ላይ ነው ። ይህ ደግሞ በዩኒቨርስቲያችን ውስጥ ብቻ ሳይሆን ፥ ከዚህ ውጭም መጠናትና መታሰብ ያለበት ነገር ነው ። የዩኒቨርስቲው አባላት ከማኅበረሰቡ የወጡ ናቸው ። ችግሩንም ይዘው የሚመጡት ከማኅበረሰቡ ነው ። ለምሳሌ ፥ በየአካባቢውና በየትምህርት ቤቱ ፍቅር በማኅበራዊ ኑሮ ክፍልነቱ ግልጽ ተደርጎ ትምህርት ቢሰጥበት ፡ ሁለቱም ጾታዎች መፋቀሪያ ጊዜያቸው ላይ ሲደርሱ እንዲህ ዐይነት ችግር አይገጥማቸውም ግልጽና ጤናማ ዜጋ ለማፍራት ከአካባቢው ከሥር ከመሠረቱ ነው
#ሰመመን


#ክፍል_አርባ_ስምንት


#ድርሰት_በሲሳይ_ንጉሱ

...ዮናታን ቤታችው ሲደርሱ፥ ሞኒካ የስብሰባውን ሁኔታ ለመስማት ጓጉታ በሕንፃው መናፈሻ በኩል ቁልቁል እየተመለከተች መምጫቸውን በመጠባበቅ ላይ ነበረች ።

“ እንዴት ነው ? ” አለቻቸው ፡ ከፊቷ ላይ የማይጠፋ ፈገግታዋን ብልጭ አድርጋ "

“ ደስ የሚያሰኝ ስብሰባ ነበር " በብዙ ሰዎች ላይ ቀና ስሜት አሳድረናል” አሏት፡እጅዋን ይዘው ወደ ውስጥ እየገቡ ጥናቱንም ቢልልኝ በጥሩ መልክ አቅርበውታል የጥናቱን ጽሑፍ ከእሳቸው ተውሼ ሰሞኑን አመጣልሻለሁ”

ሞኒካ ስብሰባው ላይ ለመገኘትና በአቤል ላይ የተካሔደውን ጥናት ለማዳመጥ ከፍተኛ ጉጉት ነበራት ጥናቱ የቀረበው በአማርኛ ስለ ነበር በደንብ የማትሰማው ቋንቋ ሆኖባት ነው የቀረችው።

“ አካዳሚክ ኮሚሽኑስ ምን አለ ? ” ስትል ጠየቀቻቸው "

“ የእነሱ መደበኛ ስብሰባ ገና ከአራት ቀን በኋላ ነው ።ሆኖም ስብሰባችን ላይ የነበሩት የኮሚሽኑ አባላት በግል ተስፋ ሰጥተውኛል ። እና ጥሩ ውጤት እጠብቃለሁ ።

ዮናታን ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ልባቸው አቤልን ለማየት ጓጉቶ ነበር • ሳሎን ውስጥ ሲያጡት የት እንዳላ
ለማወቅ ሞኒካን መጠየቅ አላስፈለጋቸው? በቀጥታ ወደ መጻሕፍት ክፍላቸው ሔዱ ። በሩን በዝግታ ከፍተው
ሲገቡ'አቤል በሚያነበው መጽሐፍ ክፉኛ ተመስጦ አገኙት ።
ሊረብሹት አልፈለጉም ። በሩን በዝግታ ዘግተው ለመመለስ ቢያስቡም እጃቸው የበሩን እጀታ መጎተት አልቻለም ለአቤል አንዳች ነገር ሊነግሩት ፈለጉ ። ቀን ምን እንደሚነግሩት ወይም ደስታቸውን እንዴት እንደሚገልጹለት አያውቁም ነበር። አቤል በእሱ ጉዳይ ስብሰባ መካሔዱን አያ
ውቅም ። ጉዳዩ ክብደት ተሰጥቶት አደባባይ መቅረቡ በአንድ በኩል ሊያስደስተው ቢችልም በሌላ በኩል ደግሞ የሚደብቀው የዐይን ፍቅር መጋለጡ ስሜቱን ሊጎዳው ስለሚችል፥ ይህን በማመዛዘን ዮናታን ሆነ ብለው ነበር ያልነገሩት አሁንም ይህን ሊነግሩት አልፈለጉም። እንዲሁ ብቻ በፈገግታ የደስታ ስሜታቸውን ሊያስተላልፉለት አሰቡ ።

ወደ ውስጥ የጫማቸው ድምፅ አቤልን ከተመሰጠበት አባነነውና ካቀረቀረበት መጽሐፍ ቀና አለ ። ፈገግታቸውን
ሲያይ ፡ ምን አገኙ ይሆን ? ብሎ አልተደነቀም ። ንባብ ላይ ተቀምጦ በማግኘታቸው የተደሰቱበት መሰለው ።
“ እንደምን ውለሃል ? ” አሉት ፡ እንዲህ የሳበው መጽሐፍ ምን እንደሆነ ለማወቅ ዐይናቸውን ወደ ርዕሱ እየወረወሩ
ደኅና ፡ ሲገቡ አልሰማሁዎትምኮ ” አላቸው ፡ የደረሰበት ገጽ እንዳይጠፋው ማዕዘኑ ላይ እያጠፈ ።

የሚያነበው “ ማን አገንስት ሄምሰልፍ ! ” “ ሰው ራሱን ሲጻረር ! የሚለው የዶክተር ሜኔንገር መጽሐፍ ነበር " ዮናታን ይህን አርዕስት ሲያዩ ደነገጡ ። ካልጠፋ
መጽሐፍ ይኽን ለምን መረጠው ? የሚል ጥርጣሬ አደረባቸው፤ፈገግታቸው በአንድ አፍታ ጠፋ ። ፈጥነው ሊጠይቁት ግን አልደፈሩም ። ከውጭ ይዘውት የመጡት የደስታ ስሜት ከውስጥ ጥቀርሻ ሲለብስ ተሰማቸው ።

“ ወደ ውጭ ወጣ ብለን እንናፈስ ? ዛሬ ንባብ ላይ ብዙ የቆየህ ይመስለኛል ” አሉት ' ስሜቱ በመጥፎ ነገር ተወጥሮ ከሆነም ወጣ ብሎ መናፈሱ ይሻለዋል በሚል ግምት ።

“ በደስታ!” አላቸው ከተቀመጠበት እየተንጠራራ ።

አመላለሱም ሆነ የፊቱ ብርሃን ከውስጡ መጥፎ ስሜት የወጠረው ሰው አይመስልም ። ዮናታን በግምታቸው ግራ
ተጋቡ ።

ሊብሊንግ ፡ ሽርጥሽን አውልቂና ወጣ እንበል ”አሏት ሚስታቸውን ወደ ሳሎኑ ተመልሰው ።

ሞኒካ ቤት ውስጥ ከሆነች ከወገቧ ነጭ ሽርጥ አይጠፋም።

“ አቤልስ ይመጣል ? ”አለቻቸው ፈቃደኛነቱን ለማረጋግጥ ።

“ አዎ ፡ እወጣለሁ ብሏል ” አሏትና " ወደ ጆሮዋ ጠጋ ብለው ፥ የዛሬ ውሎው እንዴት ነው ? ” አሏት ፡

የመጽሐፉ አርዕስት እየከነከናቸው ነበር
“ ደኅና ነው የዋለው ። እንዲያውም ንባብ ከመጀመሩ በፊት እሱ ባደገበት አካባቢ ያለውን የጋብቻ ሥነ-ሥርዓት ሲያጫውተኝ ነበር ” አለቻቸው ሽርጧን እየፈታች ።

ዮናታን ውጭ ወለው ቤት ሲገቡ ስለ አቤል ሁኔታ መጠየቅ ልማዳቸው ነበር ። አቤልም ዮናታን ቤት መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ ያሳየው ለውጥ ቀላል አልነበረም » እብሯቸው ሲኖር ሳምንት ሆኖታል ። ከእራሱ ጋር መታረቅ ጀምሯል ለውጡ የሞኒካ የድካም ውጤት ነው
ማለት ይቻላል ።

ለመጀመሪያው ሁለት ቀን አቤል ራሱን ገዝቶ ቤት ውስጥ መቀመጡ በጣም አስቸግሮት ነበር " ትዕግሥት በሐሳቡ
እየመጣችበት ብረር ብረር ይለው ነበር ። ሲጠላው የነበረው ዩኒቨርስቲ ይናፍቀዋል ትንሽም ቀለል የሚለው እስክንድር መጥቶ አጫውቶት ሲሔድ ነበር ።

ዮናታንና ሚስታቸውም ይህን ችግሩን ሳይረዱለት አልቀሩም ። ሐሳቡን ከትዕግሥትም ሆነ ከሌላ መጥፎ
ስሜት ለማዘናጋት የተጠቀሙበት ዘዴ መንፈሱ ለሥራ መወጠር ነበር ለቀን ተቀን እንቅስቃሴው ፕሮግራም
አውጥተውለታል ። ሞኒካ ምግብ በምታበስልበት ሰዓት አብሯት ሆኖ የምግብ አሠራሯን እያጠና በአንዳንድ
ማኅበራዊ አርዕስቶች ላይ ይወያያሉ በቀን የተወሰነ ሰዓት እሷ ጀርመንኛ ታስተምረዋሶች ። እሱም በፈንታው
ለተወሰነ ሰዓት አማርኛ ያስተምራታል ። ይህ አቤል ከመምጣቱ በፊት የዮናታን ሥራ ነበር ። ስለዚህ ማታ ማታ ሞኒካ ቀን የተማረቻቸውን አንዳንድ አዳዲስ የአማርኛ ቃላት ስትናገር፥ ዮናታን ወደ አቤል እየመተለከቱ ፥ ጥሩ ረዳት አገኘሁ እንዲያው ከኔ የተሻለ ዘዴ ሳይኖርህ አይቀርም ” በማለት ይክቡታል ። በመጀመሪያ ለንባብ የተመደበለት የተወሰነ ሰዓት ነበረው ውሎ ሲያድር ወደ ንባቡ ፍቅር ሲመለስ ግን፡ለንባብ ከተቀመጠበት ስፍራ የሚነሣው .
በቀስቃሽ ሆነ ። ከንባብ ውጭ ለመዝናናት ያህል በቤት ውስጥ የሚያገኛቸውን የጀርመን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ሥዕላዊ መግለጌ የያዙ መጻሕፍት ማገላበጠት በመንፈስ
ውስጥ የጥሩ ሕይወት ስሜት ያሳድርበት ነበር ። የሀገር ውስጥና የውጭ ሙዚቃ በሙሉ ጆሮው ሰምቶ ለማድነቅ
የቻለው በዚህ ሳምንት ውስጥ ነው ። ትርጉሙም ሆነ ጣዕሙ ሲገባው ያልቻለውና ዮናታን የሚያደንቁትና በተመስጦ ያሚያዳምጡት፡የእነ ቫግነርና ቤትሆቭን ክላሲካል ሙዚቃ ነው "
ቤት ውስጥ ሙዚቃ ማዳመጡ ቢያስደሰተውም አንዳንዴ ትካዜ ስለሚጫነው ፥ ለመቆጠብ ወይም ብቸኝነት በማያጠቃው ሰዓት ብቻ ለማዳመጥ ተግዶ ነበር ።

ቀን በዚህ ዐይነት ውሎ ወደ ማታ ላይ ሦስቱም ነፋስ ለመቀበል ወደ ከተማው ጸጥታማ ቦታዎች ብቅ ይላሉ ።
አሰልሠው ሲኒማ ይገባሉ ። ይህን የመሰለው የሕይወት እንቅስቃሴ አቤልን ከብቸኝነት ስሜቱ በማዘናጋት ሐሳቡ
አንድ ነገር ላይ ብቻ በማተኮር እንዳይሠቃይ ከፋፍሎታል ። ያም ሆኖ ትዕግሥትን እያሰበ ሳይጨነቅ አያድርም
ግን ጭንቀቱ እንደ ቀድሞው አልነበረም ፡ በሥራ በተወጠረ አእምሮ ወይም ደክሞ እንቅልፍ በፈለገ ጭንቅላት ስለሆነ የሚያስባት ፥ ያን ያህል አይረበሽም ።

አቤል ከብርቅነሽ ቀጥሎ በሕይወቱ የገጠመችው ግልጽ ሴት ሞኒካ ነች ። በአንድ ምሽት ዕድሜም ቢሆን
የብርቅነሽ ትሑትና ግልጽ ተፈጥሮ በልቡ ተቀርጿል ። ምናልባትም የብርቅነሽ ግልጽነት ከማይምነቷ ጋር የተያያዘ
የልብ ክፍትነትና የጥሬነት ውጤት ሊሆን ይችላል ። የሞኒካ ግልጽነት ግን ምሁራዊ ጥልቅ ትርጉምና ድምቀት አለው ። ከአኳኋኗ መረዳት እንደሚቻለው “የምንፈጽመው ጥሩም ሆነ መጥፎ ነገር የህልውናችን ነጸብራቅ ነው ፤ ስለሆነም
እኛነታችንን ደብቀን መሠቃየት የለብንም ፤ መጥፎ የምንለውን አምቀን ጥሩ የምንለውን ብቻ የምንተነፍስ ከሆነ
ውስጣችን ገምቶ ደማችን ይደፈርሳል የምትል ትመስላለች አቤል በቀላሉ ነው የተግባባት
#ሰመመን


#ክፍል_አርባ_ዘጠኝ


#ድርሰት_በሲሳይ_ንጉሱ

ከገና ማዕበል ያመለጠው ተማሪ፥ የዩኒቨርስቲ ውስጥ ዕድሜው መራዘሙን ካረጋገጠ በኋላ መረጋጋት ይታይበታል ። የሁለተኛው ሴሚስተር ትምህርት ቢጀመርም ገና ሞቅ ሞቅ ባለማለቱ አንገቱን መልሶ ቀለም ላይ የደፋ ተማሪ
እምብዛ!” ነው ። ሆኖም ፋታ ፈጥሮአቸው የነበሩት ቀልድ ፥ትችት።ውንጀላና ተረብ ተግ ብለዋል ።

ትዕግሥት ማጥናት አልጀመረችም ። የወረቀት ዘር ማየት ያስጠላት ትመስላለች ትምህርት ክፍሉ ውስጥ እንኳ ከመምህራኑ ገለጻ ሙሉ በሙሉ ማስታወሻ መውሰዷን ትጠራጠራለች ። ምክንያቱ አንዳንዴ ሐሳቧ እያመለጣት
ወደ ወጭ መብረር ጀምሯል ፤ በግልጽ ያልተከተላት ስሜት ሲፈታተናት ይሰማታል ከውስጧ አንዳች ነገር የጎደለ ይመስላታል። ምናልባት በቢልልኝ አገላለጽ ለፍቅር የተዘጋጀው ሥፍራ ሳይሆን አይቀርም የሚረብሻት ።

እቤል ሕመሙን አጋብቶባት እንደ ሄደ ለመገመት ብዙ ጊዜ አልወሰደባትም ። መኝታ ክፍሏ መግባት መውጣትም አስጠልቷታል ። ጸባይዋ ቢንቋሸሽም ፡ በመጠኑ ለምዳት የነበረችው ጓደኛዋ ማርታ ነበረች ። እሷ ከተባረረች ወዲህ በደንብ ቀርባ የምትጫወተውን የሴት ጓደኛ አላገኘችም ። ከቤተልሔም ጋር ዐልፎ ህልፎ ይገናኛሉ ። ሆኖም በግቢው ውስጥ የቤተልሔም ስም እየቆሸሽ ስለ መጣ ትዕግሥት አብራ እንዳትታማ በመፍራት ቀስ በቀስ እየራቀቻት
ነበር ። አቤል ግቢውን ለቅቆ ከወጣ ወዲህ ለዐይኗ ማሳረፊያ ያገኘችው ሰው እስክንድር ነው ፡ ሳታየዉ ወይም
አግኝታው የተለመደውን “ ታዲያስ ፥ ታዲያስ ” ሰላምታ ሳትለዋወጥ ውላ
አታውቅም ።

እስክንድርም ቢሆን፥የትዕግሥትን መግቢያና መውጪያ ሰዓት ጠብቆ ነው የሚገኛት ፥ ከመኝታ ክፍሉ ጠዋት
ሲወጣ ስለ አቤል ሁኔታ ፍርጥርጥ አርጎ አጫውቷት መፍትሔውን እንዲወያዩበት ሊለምናት ያስብና ፡ በሚያገኛት ጊዜ ልቡ ይከዳዋል ። በዮናታን ፊት የፎከረውንና እሷን ሲያገኛት ምላሱ መተሳስሩን ሲያመዛዝን ራሱን ታዘበው ።
“ አቤልስ ቢደነግጥላትም ቢፈራትም ወዷት ነው ፤እኔ ደግሞ ያሰብኩትን ልነግራት መፍራቴ ለምንድን ነው ? ” እያለ
ከራሱ ጋር መሟገቱ አልቀረም ። ግን ለእስክንድር አልታወቀውም እንጂ፥ ስለ አቤል ጠልቆ ሳያነሳባት ከትዕግሥት ጋር
ግንኙነቱን ማጠናከሩ ለዓላማው ጥሩ መንገድ አመቻችቶለት ነበር ። በአንዴ ነጥቡ ላይ ደርሶ ዱብ ዕዳ ከማውረድ ፥ ቀስ በቀስ አለማምዶ ከነጥቡ ላይ መድረሱን መልሱ የእሽታ እንዲሆን ይበልጥ ይረዳል ።

ትዕግሥትን ከአቤል ጋር ለማገናኘት አማራጭ መንገዶችን ዮናታንና ቢልልኝ ተነጋግረው ነበር ። ትዕግሥትን ድንገት ወስዶ አቤል ፊት ማቅረቡን ቢልልኝ አልደገፉትም ምናልባትም ካለፈው ልምዳቸው በመነሣት ሊሆን ይችላል።
አንዴ እንዲሁ ተመሳሳይ ችግር የገጠመው ተማሪ የሚፈልጋትን ልጅ አቅርበው እናስተዋውቅህ ሲሉት፡ ካልገደልኳት ብሎ የተጋበዘው ነገር ምንጊዜም አይረሳቸውም ። እና አሁን ያቀረቡት ሐሳብ በመጀመሪያ አቤል ስለ ትዕግሥት ቀና አመለካከት እንዲኖረው መኮትኮትና አጠገቡ ከመድረሷ በፊት በስልክ እንድታነጋግረው ወይም ደብዳቤ እንድትጽፍለት ማድረግ ነበር ። ደብዳቤ መጻፍዋ የተሻለ መንገድ ሆኖ ተመረጠ ። ይህን ለማስፈጸም በሙሉ ልብ ኃላፊነቱን
የወሰደው እስክንድር ነበር ። ታዲያ አሁን ተግባሩ ላይ ሲዲርስ የምን ወገቤን ያዙኝ ነው ?

ሲያምጥ ከርሞ፡አንድ ቀን እንደ ምንም ደፍሮ ሔደ ። ከመኝታ ክፍሏ አስጠራትና ፡ “ ለጥብቅ ጉዳይ እፈልግሻለሁ ” አላት ። በቆይታ የሚያወሩበት ቦታም ችግር ነበር
እነትዕግሥት ቀድሞ ያጠኑበት የነበረው ከዋናው ቤተ መጹሕፍት ጀርባ ያለው ዋርካ አካባቢ ታየው ። ግን ሁለታችንን
ብቻ እዚያ ዋርካ ሥር ሲያዩን ተማሪዎች ምን ይሉናል ? የሚል ሥጋት እደረበት በመጨረሻም ካወጣ ካወረደ በኋላ ሌላ ቦታ በማጣቱ “ ያሉትን ይበሉ ወደ
ዋርካው ሥር ይዟት ሔደ
እንዴት እንደሚጀምርላት ግራ ገብቶት ትንሽ ተጨነቀ። ግን ዝም ማለትም አልቻለም ። ዐይኖችዋ ውስጥ የጥያቄ
ምልክቶች ተደርድረው ያየ መሰለው ።

“ ሁለታችንም ሳንጠላው የምንሸሸው አርዕስት ነው አላት በድንገት ።

“ ምን ? ” አለችው ፥ ነገሩ ቢገባትም ከእሱው ይምጣ በሚል ስሜት ።

የእቤልን ነገር ሁለቱ በተገናኙ ቁጥር ዳር ዳር ሳይሉ ስለማይለያዩ አሁን ስለእሱ ሊያወራት መሆኑን ትዕግሥት አላጣቸውም ። ስሜቷን ደብቃ ነው እንጂ ወሬውን ለመስ ማት ቸኩላለች

ስለ አቤል በደንብ ላጫውትሽ ብዬ ነው ?” አላት ።

ፈቃደኛነቷን በአፏ ሳይሆን በዐይኖቿ ነው የግለጸችለት ።

አጫወታት ነው ረበሻት የሚባለው ? የለም ! ማጫወት ላይ ላዩን ሲሆን ነው ። ከሥር ከመሠረቱ ጀምሮ ልብን እያናጉ
መንፈስን እያወራጩ ፥ ቁስልን እየቀሰቀሱ ስሜትን እያንገላቱ የሚናገሩት ነገር፡ “ መረበሽ ” የሚለውን ቃል ቢይዝ ይሻላል ። እስክንድር እንደዚያ ነው ያደረገው ። ሳያስበው የእሱም ስሜት አርዕስተ ነገሩ ውስጥ ሰምጦ እየተንገላታ ስለ አቤል የሚያውቀውን ሁሉ ነገራት። እሷን ካየበት
ዕለት ጀምሮ በግሉ የተቀበለውን ሥቃይ አሁን የት እና በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ዘረዘረላት እያወራላት ገጽታዋን ገመገመ ከንፈሯ በቅጽበት ሲከስል ታየው ። ፊቷ በአንዴ ጠወለገ ። አዲስ ነገር ተናግሮ
አልረበሻትም ። አብዛኛው የምታውቀው ነገር ነው ። አብዛኛው ከአቤል ጋር አንድ ሴሚስተር ሙሉ በዐይናቸው የተለዋወጡት የጥናት ፥ የቁጣ ፥ የሥቃይና የእልህ ድምፅ አልባ
ግንኙነት ነው።

“ ታዲያ ጥፋተኛው ማነው ? ” አለችው ንግግሩን መጨረሱን ካረጋገጠች በኋላ
ዐይኖችዋ ያቀረሩትን ዕንባ ሲያይ ስሜትዋ ተጋባበት።ግን እሱ የማልቀስ ችግር አለበት ፤ዕንባው ቶሎ አይመጣለትም ።

ለፍርድ አስቸጋሪ ነው ። ሁለታችሁም ጥፋተኛች አይደላችሁም ። እየተፈላለጉ መራራቅን ፡ “ የፍቅር እንቆቅልሽ ” ብንለው ይሻላል ” አላት ።ዝም አለችው ። እሱም ዝም ብሎ ተመልከታት ። የአቤልን ስሜት ያደነዘዘውን የመልኳን ውበት ማጥናት ፈለገ ።ግን ከዳመነ ፊቷ ላይ ውበት ለማጥናት መሞከሩ አስቸጋሪ
ሆነበት ።

በረዥሙ ተነፈሰች የጭንቅ አተነፋፈስ ። የታባቱ !በሥቃይ የታመቀው አየር ወጣ ።

“ አሁን አንገብጋቢው “ ጥያቄ ጥፋተኛው ማነው?”ሳይሆን ፥ “ መፍትሔው ምንድነው ?” ይመስለኛል” አላት እስክንድር ።

“ ምን መፍትሔ አለው ? ” አለችው ፡ ተስፋ በቆረጠ ድምፅ።

“ አለው እንጂ ።አቤል ይወድሻል ፥ ይፈልግሻል ማወቅ የሚፈልገው ያንቺ ምላሽ ምን እንደሆን ነው ። ካንቺ
መረዳት እንደ ቻልኩት ደግሞ አንቺም ትፈልጊዋለሽ ፤ትወጂዋለሽ ። ይህን ስሜትሽን በደብዳቤ ብትገልጪለት
ችግሩ ይቃለላል ። ”

ደብዳቤ ”አለችው ; ሳይተዋወቁ የምትጽፍለት ደብዳቤ ምን እንደሚሆን ግር ብሏት ።

"አዎ ደብዳቤ !"

"ምን ብዬ ?"
“ በቃ ለእሱ ያለሽን ስሜት ነዋ ! ”

አሰበች ፤ደብዳቤ ። አዎ ጥሩ መንገድ ነው ስትጽፍ አጠገቧ የምታፍረው ወይም የምትፈራው አቤል አይኖርም ወረቀቱ ሳይ የምታሰፍራቸው ቃላት ፈንቅለዋት ማልቀስ ቢዳዳትም ማልቀስ ትችላለች ። ታዛቢ አይኖርባትም ። የምትጽፈው ነገር ከጭንቅላቷ ውስጥ እየፈለቀ ኣሁን አሁን
አሰኛት ።

“ ካልሆነም ረቂቁን እኔ ልጻፍልሽ ” አላት እስክንድር፡ ዝም ስትልበት ጊዜ የቸገራት መስሎት ።

ግድ የለም ፤ እኔው እሞክራለሁ ” አለችው ፥ በሐሳቧ የምትጽፍበትን ቦታ እየመረጠች ምቹ ቦታ የለም ።
የመኝታ ክፍል ጓደኞቿ ከተኙ በኋላ፥ ሌሊት ተነሥታ የመጻፍ ሐሳብ መጣላት ።

“ ጥሩ እንግዲህ ፥ ጸፊና ሰጪኝ ። እኔ አደርስልሻ
#ሰመመን


#ክፍል_ሃምሳ


#ድርሰት_በሲሳይ_ንጉሱ

....ለማንኛውም አሁን ከለማ ጋር ግንኙነታችን ተቋርጧል።

"በቃ?"

" አዎ " ከእንግዲህ በዚህ አይነት የምንቀጥል አይመስለኝም ። በእሱ የተነሣ ነው ፡ እንዲህ ስሜ የጠፋው ። ”

ሁለቱም ዝም አሉ። እስክንድር ለሁኔታው ያልተዘጋጀበት ሆኖ ነው ለአፋጣኝ ጥያቄም ሆና መልስ የተቸገረው።
ቤተልሄም ግን በዝምታው መርከብ ተሳፍራ ወደ ኋላዋ ከለማ ጋር የተጣሉበት ቀን ደርሳ ነበር።

የሁለተኛ ሴሚስተር ትምህርት ተጀምሮ ልማ ምንም ኮርስ እንደማያስተምራት ካረጋግጠች በኋላ ፥ ቤተልሔም ሸርተት ለማለት ትጀምራለች ። ጭራሹን ለአንድ ሳምንት ያህል ትሰወርበታለች።ለማ ልቡ ይጠረጥርና በዚያው ሳምንት ግቢ ውስጥ ፈልጎ ካገኛት በኋላ ፥ ቤቱ ድረስ እንድትመጣ ነብር ሆኖ ይቀጥራታል ።

"ምን ሆነሽ ነው እንዲህ የጠፋሽው!" እንደ ብራቅ ጮህባት።
"ስላልተመቸኝ ነው"
"ይህው ነው መልስሽ?" አላት በሽቆ።
ዐይኗን ሰብራ ዝም አለች ። አኳኋኑ አስፈራት ። ገላጋይ በሌለበት ባዶ ቤት ውስጥ የያዛት እንደሆን ማን ይደርስላታል ? ሽንቷ ወጠራት ።
"ምን መሰለህ ለማ" አለችው እንባ በተናነቀው ድምፅ ዬኒቨርስቲዉ ውስጥ ስሜን እያጠፉ ነው ። ከአንተ ጋር ባለኝ ግንኙነት ክፉኛ ታምቻለሁ ። ሰላም ይሉኝ የነበሩ ተማሪዎች ሁሉ ዘግተውኛል !
"እና ? ”
“ እና ለአንተም ስም ሆነ ለእኔ ይህን ግንኙነታችንን ብናቋርጠው ይሻላል ብዬ ነው። እኔ እዚያ ግቢ ውስጥ መኖር
እልቻልኩም ፡ ሰውነቴ አለቀ” አለችው ፡ ለቅሶ እየቃጣት
እንዲሁ ነች ። እስክንድርን ጠርታ ፥ “ ጓደኛዬ ሁን ” እንዳለችው መሆኑ ነው ። ብልጠቷ ስልት የለውም ። ይህ ስልት ያጣው ብልጠቷ ለማን አብከነከነው ።

“ ስሚ ! ” አላት ። መቀጠል አልቻለም ። ጉሮሮው ላይ የሆነ ነገር ተናነቀው ። ከወጣትነት ባለፈ ዕድሜው የእልህ ዕንባ እንዳያነባ ፈራ ። እናም ከምላሱ ይልቅ እጁን ማንቀሳቀስ መረጠ ። የራስጌ ኮመዲኖውን ከፍቶ አንድ ወረቀት አወጣና ሰጣት ።

ምንድነው ? አለችው ።
አንብቢው ! አላት ፡ ዐይኑን አፍጥጦ ።

በዚሁ ሳምንት ውስጥ ቢሮው ወስጥ በድብቅ ተጥሎ ያገኘው ወረቀት ነበር ። ቤተልሔም ተቀብው ማንበብ ጀመረች።

ጽሑፉ በቅጡ አልተቀነባበረም ። በግጥም ይጀምርና
ምሁር ሰማ ዘቀጠ ...

ኅሊናውን ለሴት ሽጠ ...

ካለ በኋላ ፥ በስድ ንባብ ይቀጥላል ። ቃላቱ ተስፋ መቁረጥን ያመለክታሉ ። በለማ ላይ የተደረደሩ ተራ ስድቦች ነበሩ ።
በመሐል ደግሞ

... ወሲብ አንጎል ሆኖ ሲያስመርቅ እያየሁ ፡ የእኔ ጥናት ከንቱ እንዲያው ተሠቃየሁ አወይ እኔ ፡ አወይ እኔ ! ሴት አለ መሆኔ !...” ይልና፡ ተመልሶ ስድቡን ይቀጥላል ።

አንብባ ጨርሳ ቀና ስትል፥ የምትናገረውን ለመስማት ዐይን ዐይኗን ተመለከታት ። ለእሷ ሲል የተጋፈጣቸው ችግሮች በውስጧ ኅዘን እንዲፈጥሩባት ነበር ሃሳቡ ። እንዲህ ዐይነት ነገሮችን ሥራዬ ብሎ ነው የሚነግራት ። አንዴም በመጀመሪያው ሴሚስተር አንድ ጓደኛው መቼም የቅርቤ ነው ብሎ ሊመክረው ፥ “ ለማ እዚህ ግቢ ውስጥ በአንዲት
ልጅ ምክንያት ስምህ እየተበከለ ነው ” ብሎ ሲጀምር' ለማ በሽቆ ፡ “ ስለዚህ ጉዳይ ምንም አታንሣብኝ ። ተፈጥሮን
ተመክሮ አይመልሰውም ! ማንም የፈለገውን ሊል ይችላል” ብሎ ዘግቶታል ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ መምህራንም
እየታዘቡት መሆናቸውን ሊነግረው ነበር ጓደኛዉ የፈለገው ነገር ግን ለማ የሚበገር ሰው አልሆነም።

በወቅቱ ይህንንም ለቤተልሔም አጯውቷታል ።በአንቺ የተነሳ ያየሁት አበሳ" አይነት መሆኑ ነው። ታዲያ ያኔ ቤተልሄም አዝና ከንፈሯን መጥጣለት
ነበር ።

"አበሻ ነገር መፈትፈት ልማዱ ነው ! አትጨነቅ ” በማለትም አበረታታዋለች ። አሁን ግን ግጥሙን አንብባ የዚያን ዐይነት መልስ አልሰጠችውም ፡፡ እንዲያውም ለአፍራሽ ሐሳቧ መንገድ የጠረገላት ነው የመሰላት......

እና ፥ ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ ወዴት ነው። ሸርተት የምትይው ? አላት አፍጥጦ።

“ እኔስ የፈራሁት ይህንኑ አይደል ? ” አለችና ጽሑፉ ክፉኛ እንደ ቆረቆራት ሁሉ ዐይኗን አሸች ። ዕንባው ደግሞ ራሱ ካልፈቀደ እንደ ፈለጉት አይመጣ ! ዐይኗን ምራቅ እንዳትቀባ ለማ አጠገቧ ቆሟል።

መጀመሪያ ለምን ነበር የቀረብሽው ? ” አላት እስክንድር።

" ፈራሁኛ ! ”
"ምን ? "
"ማትስ እንዳልወድቅ ። እኔ የቁጥር ዘር ጠላቴ ነው ።

ፍቅር ብቻ ሳይሆን እልህ ጭምር ነበር የያዘው ። አስተያየቱ አላማራትም ጡንቻው ላይ አባብጠው የተጋደሙት
ሥሮች አሰፈሯት ። ከተቀመጠችበት ቀስ ብላ ተነችና ወደ በሩ አምራች ።

የት ልትሔጂ ነው ? ” አለና ፥ አጠገቡ የነበረውን አምቦ ውሃ ጠርሙስ አንስቶ ግንባሯ ላይ አነጣጠረ።
“ውይ ለማ ! ” ብላ ጮሃ ጣውላው ላይ ቁጭ አለች ።
“ ሸርሙጣ ! ” አላት አጠገቧ ደርሶ ቁልቁል እየተመለከታት
የሚለማመጡና የተቆጡ ዐይኖች ሽቅብና ቁልቁል ተፋጠጡ ። ለማ ደፍሮ እጁን ሊያሳርፍባት አልቻለም ። አቅፎ
ለማባበልም ልቡ ያን ያህል አላላም ።

"ስሚ ፤ በሦስት ቀን ውስጥ አስበሽበት መልሱን ንገሪኝ። የሦስት ቀን ዕድሜ ሰጥቼሻለሁ ! ” አላት እንዳፈጠጠ ።

ቤተልሄም ከጣውላው ላይ ቶሎ አልተነሳችም” በድንጋጤ ከጭኗ ሥር ሽንት ጠብ ያለ ስለ መስላት እንዳይታይባት ፈራች ። ነገር ግን ሰውነቷን ዐልፎ ጣውላው ላይ
የደረሰ አልነበረም...

ያን ዕለት እንደ ምንም ከክፍሉ ከወጣች በኋላ መንገድ ላይ በጕዳዩ እሰበችበት ። የይህሆን ጨዋታ ነው ። የለማ ኮንትራት አልቋል ። አብራው ከቀጠለች ለሚቀጥሉት ዓላማዎቿ ዕንቅፋት ይሆንባታል ። ከአንድ ወንድ ጋር ብዙ መታየት ሴሎች የጥቅም መንገድን ወመዝጋት ነው ። ጥቅሙን የሚያሳድድ ሰው በአንድ ነገር ላይ መርጋት አይችልም ትርፉን ከኪሳራው እያሰላ በሚያዋጣው መንገድ መንቀሳቀስ አለበት ... እና ለማ እስኪረሳት ድረስ ከዐይኑ ለመሰወር ወሰነች። ከዚህ ውሳኔ በኋላ ስሟን ለማደስ በግቢው ውስጥ አብራው
የምትታይ ተማሪ ስታስብ ፥ እስክንድር በሐሳብዋ ብቅ አለ ። ብዙ ተማሪዎች ከዘጓት በኋላ እሱ ሳይለወጥ እንደ
ወትሮ ሰላም ይላት ስለ ነበር ነው የታሰባት......

እስክንድር በሆዱ ሣቀ። የግልጽ ሰው ሳይሆን የብልጥ አንበሳ ምስል ከፊቱ የቆመ መሰለው ለጥቅም የቆመች
አንበሳ ! ሣር ባየችበት ሁሉ የምታጎነብስ በግ ፤ ግን ደግሞ እንስሳ ለማዳ ነው ያበላውን ያጠጣውን ፥ የቀረበውን ቶሎ
ያፈቅራል ።

«ግን ታዲያ አብራችሁ ስትቆዩ ከለማ ጋር ፍቅር አልያዘሽም ? ” ሲል ጠየቃት ።

“ ኤጭ ! ” አለች በንቀት
"እሺ ፤ እሱስ ፍቅር ቢይዘው ኖሮ ? ”

“ እእይ እኔ አስቀድሜ ነግሬዋለሁ" አለች ግንባሯን አኮማትራ
"ምን ብለሽ ?
“ አሜሪካ የመሔድ ሐሳብ እንዳለኝ እጮኛዬ እየጠበቀኝ ነው።
ሣቁ እንዳያመልጠው እየሞከረ ፥ ዋና ይዘሽ በትርፍ እየተጫወትሽ ነዋ ! ” አላት
ፈገግ ብላ ዝም አለች ።

“የእኔም ጓደኝነትስ ምሽን እስካሳደርስሽ ድረስ ነዋ!”አላት ድንገት ግልፍ ብሎት ።

ወይኔ ! ካንተ ጋር እኮ እንዲሁ ጓደኝነት ነው ” አለችው ፥ ድንገተኛ ቁጣው አስደንግጧት ።

“ እንዲሁ ጓደኝነት ብሎ ነገር ምንድነው?” ሲል አሰበ። ሐሳቡ ከውስጥ ጥቀርሻ እየለበሰ ሲመጣ ተሰማው ። የአሁኗ
ቤተልሔም ሳትሆን ነገ የምትይዘው ቦታና የምትፈጽመው ተግባር ነው የታየው በዚህ ዐይነት ብላሽ ጥበብ ከዩኒቨርስቲ የምትረቅ ሴት ፥ በሥራ ዓለም ስትሠማራም መሰሎቿን ታፈራና ትመለምል እንደሆን እንጂ ያስተማራትን ሕዝብ
#ሰመመን


#ክፍል_ሃምሳ_አንድ


#ድርሰት_በሲሳይ_ንጉሱ


...ማሰብና መጀመር የተለያዩ ሆነውበት ተቸግሯል አቤል ። ሐሳቡ በጣም ይመጥቅበታል ።ሊጽፍ ያሰበው ነገር መጽሐፍ ይሆንበታል ። ለሐሳቡ ወግ የሚያግኝለትም አይመስለው ። ወረቀቱን ይዞ ቁጭ ሲል ግን ከብዕሩ ጠብ የሚል ነገር ይጠፋል ። ባዶ ወረቀት ላይ ማን ፎር ሂምሰልፍ” ከሚል አርዕስት ጋር መፋጠጥ ብቻ !

“ችግሩ ከቋንቋው ይሆን ? ” ሲል አሰበ ። በሰው ቋንቋ ከምቸገር ሓሳቤን እንደ ልቤ ላንቆረቁርበት በምችለው በራሴ ቋንቋ ለምን አልፅፍም?።

ባዶውን ወረቀት ከአጠገቡ አገለለና መጽሐፍ ገለጠ ለጽሑፉ የሚጠቅመውትን መጽሐፎች መርጦ አውጥቶ ጠረጴዛው ላይ ከምሯል ። መጻፍ ከመጀመሩ በፊት በዚህ አርዕስት
ጐዳይ ላይ የተጻፉ ብዙ መጽሐፎች ማንበብ እንዳለበት ስለ ተረዳ፡ ሰሞኑን እያነበበ ነበር። ችግሩ ግን አለ ከሚያነበው መጽሐፍ ላይ ብዙ ሰዓት መቆየት አለ መቻሉ ነው ከመጽሐፉ ውስጥ ጠቃሚ ሐሳብ ሲያገኝ የእሱ ሐሳብ ቀድሞ ይሐጥቅና ጻፍ ጻፍ ይለዋል

አሁንም ከተቀመጠበት ተነሥቶ ትንሽ ተንጎራደደ ። ከመንጐራደዱ ጋርም የሚጽፈው ነገር ብልጭ አለለት
ሰው ከራሱ ጋር የሚጣላው ለምንድነው ? በግል ምኞትና ግብ አእምሮው ተወጥሮ ሲጨነቅ ነው ። ነገር ግን የሰው ልጅ የመጨረሻ ግቡ እኛ እንጂ እኔ መሆን የለበትም ከራሱ ጋር ሊታረቅ የሚችለው በዚህ እምነት ተጠምቆ ከግሉ ይልቅ ለማኅበራዊ ችግር ክብደት ሲሰጥና ደስታውን ከኅብረተሰቡ ጣፋጭ ሕይወት ውስጥ ለማግኘት ሲሞክር ነው ። ሰው በመጀመሪያ ለሕያውነቱ ከፍተኛ ግምት መስጠትና ማድነቅ አለበት ። ይህን ካመነ ደግም ማናቸውም በውስጡ የሚከሠቱ ነገሮች የሕያውነቱ ነጸብራቆች ስለሆኑ
እንዳመጣጣቸው ተቀብሎ መፍታት እንጂ ለችግሮች ምረታት የለበትም ። ሰው በትግሉ በተጸጥሮ ላይ ፍጹም የበላይነቱን መቀዳጀት አለበት ።

እቤል መጻፍ የፈለገውን መቋጠሪያ ሐሳብ ያገኝ መሰለው ደስ ደስ አለው። በአንጻሩ ግን ከውስጡ አዘናጊ ስሜት ይታግለው ነበር ። " አይ አቤል ፤ አሁንስ ጅል ሆንክ አዲስ ሐሳብ ያፈለቅክ መስሎህ ነው ? ስንት ፈላስፋዎች ብለውት ብለውት የበቃውን ነገር እንዴት እንደ አዲስ ታነሳዋለህ ? እባክህ ይልቅ ያልተሳበ አዲስ ነገር ፈልግ ።ለዚያውስ በዚህ ዓለም ላይ ምን ያልተባለ ነገር አለ ?”

አቤል የራሱ ስሜት አስጠላው ለምንድነው ስሜቱን ገንቢውን ትቶ አፍራሹ ላይ የሚሮጠው? አዲሱ ሰው ሁሉን ነገር “ ተብሏል” እያለ ራሱን የሚያዘናጋ ከሆነና እጁን አጣምሮ ከተቀመጠ ነገር ተበላሸ ከአሁን በፊትም ማንም ቢሆን ፍጹም አዲስ ነግር ይዞ አልተሄዶም ። ሁሉም እውቀቱን የቀመረው በተከሠረት ወይም በተባለ ነገር ላይ እየቆመ ነው።እና አቤል አቤልሽ ! ይልቅ ደፍረህ ጀምር የአቅምህን ሞክር ፤ ጫር ! ” አለና እንደገና ቁጭ አለ።

እንዴት እንደሚጀምረው ቁልጭ ብሎ ታየው " ሰፊ አርዕስት ነው የያዘው ፤ስለዚህ በንዑስ ርዕስ ከፋፍሎ እያንዳንዷን ንዑስ ክፍል በጽሑፍ ማስረጃና በሕይወት ገጠመኝ
አስደግፎ ማስኬድ ! ሰውነቱን አንዳች የደስታ ስሜት ወረረው ። ሐሳቡ ካለበት መጥቆ ሲሮጥ ንዑስ ርዕሱ ልጓም ሆኖ
ያዘለት ። ሰው የራሱ ወዳጅ የሚሆንበትን ሐሳብ ከመደርደሩ በፊት ከራሱ ጋር የሚጣላባቸውን ሁኔታዎች ለመደርደር ተገደደ ። እዚህ ላይ ለመድረስ ደግሞ፥ ሰው በተፈጥሮ ይዟቸው የሚወጣውንና ከአካባቢው የሚቀስማቸውን ዐብይት ጸባያት ይዞ መነሣት ነበረበት ። የጅማሬ ሐሳቡን በዚህ ንዑስ ርዕስ ሥር አጠቃልሎ ፥ “ በዚህ ዓለም ላይ ታላቅና
ክቡር ፍጡር ነው” ሲል ጀመረ ።

በተመስጦ እየጻፈና ደጋፊ ሐሳቦች ፍለጋ መጽሐፎች እያገላበጠ ትንሽ እንደ ቆየ ፡ ሞኒካ ሻይ ይዛለት መጣች።

የአምስት ሰዓት ሻይ ነበር ። ጊዜው ከምኔው እንደ ሮጠ ገረመው
“ ጽሑፉን ጀመርኩት “ ኮ ” አላት ፡ ገና እየገባች ሳለች ።

“ ዳስ ኢስት ሸን ” አለችው ሞኒካ • ፈገግ ብላ ደስታዋን በመግለጽ ።

አቤል ይህንኑ “ ጀመርኩት ” የሚለውን ቃል ለዮናታንም ለመንገር ተቻኮለ ። እንዲያመጡለት የጠየቃቸውን የቀድሞ የተበላሹ የጥናት ጽሑፎቹን ባመጡለት ጊዜ ፥ የገባላቸው ቃል ትዝ አለው ። ወረቀቶቹን ተቀብሎ ፊታቸው በክ
ብሪት ካቃጠለ በኋላ ፥ አሁን ከፊትዎ የቆመው አዲሱ አቤል ነው ። አዲስ ጽሑፍ አዘጋጅቶ ያሳይዎታል ” ብሏ
ቸው ነበር ። አሁን ዮናታን የሚመጡበት የምሳ ሰዓት ራቀበት።

ሞኒካ አሁን እቤል ያለበትን ጥሩ ስሜት ካረጋገጠች በኋላ፥ ወደ መኝታ ክፍሏ ሔዳ አንድ ጉርድ ፎቶግራፍና የታሸገ
ኢንቬሎፕ ይዛ ተመለሰች ።

“ ይህችን ልጅ ታውቃታለህ ? ” አለችው ፥ ፎቶውን ዐይኑ ሥር አቅርባ ።ፉት ብሎ የነበረውን ሻይ ቶሎ መዋጥ አቃተው
የልብ ትርታ የሚቀሰቅስ ምስል ! አስደንግጦ የሚያስደስት ምስል ! “ ማወቅ ብቻ ነው!? አምልኬባታለሁ እንጂ!” ሊላት ፈለገ። የሞኒካ ቶሎ መልስ መፈለግ ግን፥ አቤል ነገሩን አመዛዝኖ እንዲናገር ጊዜ አልሰጠውም ።

አዎ ! አላት ፥ ሌላውን ስሜቱን ዋጥ አድርጎ
“ የት ? ”
“ ዩኒቨርስቲ ውስጥ አንድ ሴሚስተር ሙሉ በዐይን ፍቅር የማቀቅኩላት ናት” አላት ቃናው በተለወጠ ድምፅ ።

“ ከዚህ ፎቶዋ ጋር ደብዳቤ ልካልሃለች ” አለችና የታሸገውን ፖስታ ሰጠችው። ፈጥኖ ተቀበላት ። ነገር ግን ፈጥኖ መቅደድ አልቻለም ። አንዳች ነገር እጁን የያዘው ይመስል ተንቀጠቀጠ ።

በሚያነብበት ጊዜ ነጻ እንዲሆን በማሰብ ሞኒካ ክፍሉን ለቅቃለት ወጣች ። ደብዳቤዉንና ፎቶዉን ከእስክንድር
ከተቀበሰች ሁለት ቀን አልፎአል ።ለአቤል ወድያውኑ ያልሰጠችው እንዲህ ጥሩ ስሜት እስኪታይበት በመጠበቅ ነበር።

አቤል ደብዳቤዉን ግልጾ ማንበብ ጀመረ፡-

አቤል፥ ስምህን ደብዳቤ ላይ ለመጀሪያ ጊዜ ስጽፈው የተሰማኝን ስሜት ልገልጽልህ አልችልም ። የምወደውንና
የምፈልጎውን ቃል መጥራት ለምን እንደሚያስፈራኝ ሊገባኝ አልቻለም ። የዚህን ደብዳቤ ረቂቅ ብታየው ትግረማለህ ። ስርዝ፤ ድልዝዝ ብቻ ነው። ከስሜቴ ጋር ክፉኛ መታገሌን በዚህ መገመት ትችላለህ ።

ይህን ደብዳቤ እንድጽፍልህ ያደፋፈረኝ እስክንድር ነው ። ጥሩ ጓደኛ ነው ያለህ እሱ ባይገፋፋኝ ኖሮ እንዲሁ ስሜቴን አምቄ ውስጥ ውስጤን እሠቃያለሁ እንጂ ከቶም አልሞክረውም ነበር ። አንተ በእኔ የተነሣ የተቀበልከውን ስቃይ ስሰማ ለብቻዬ ተደብቄ ስቅስቅ ብዬ ነው ያለቀስኩት ፤ግን ጥፋተኛው ማን ነው ? አየህ አቤል ! እኔ መቼም ሴት ነኝ ፤ደፍሬ መጥቼ እንዳነጋግርህ የአካባቢ ተጽዕኖ
አለብኝ ። አንተ ግን በሩቅ ከምትሠቃይ ቀርበህ ! ብታነጋረኝና እወድሻለሁ ብትለኝ ምን ነበረበት ።

“ሕመምህ ጠልቆ የተሰማኝ አሁን ነው ። ለካስ ፍቅር ተገጣጥሞ ካልሰመረ ሥቃይ ነው። በካምፓስ ውስጥ አንተን በዐይኔ ካጣሁበት ጊዜ ጀምሮ ያለሁበትን ሁኔታ ልገልጽልህ አልችልም ። አንተን ለማየት እናፍቃለሁ ፣ ብቸኝነት ያሰቃየኛል ፥ አካባቢዩ ያስጠላኛል ፤ጥናት ያንገሸግሸኛል ፣ሁሉ ነገር ከብዶና መርሮ ይታየኛል ። እውነቴን ነው የምልህ
የተፈጥሮ ክሥተት ባይሆን ኖሮ፡ አፍላ ፍቅር ፈጽሞ እያስመኝም
“ በመጀመሪያው ሴሚስተር ከትምህርቴ እንዳልሰናከል እፈራ ስለ ነበር፡ ፍቅርህን ክፉኛ ተቃውሜዋለሁ›
አሁን የተረዳሁት ነገር ቢኖር ግን ፥ ፍቅር ታግለው የሚጥሉት ነገር አለመሆኑን ነው ። ገና መጀመሪያ የዩኒቨርስቲውን ግቢ ስረግጥ ካየኸኝ ጀምሮ በዐይን እንደምትከተለኝ ያልተረዳሁልህ እንዳይመስልህ እያንዳንዷ እይታ ከንግግር የበለጠ ተሰምታኛለች። እንዲያውም አንዳንዴ ቃላት
#ሰመመን


#ክፍል_ሃምሳ_ሁለቴ


#ድርሰት_በሲሳይ_ንጉሱ


...የጠዋት ፀሐይ የማንንም ፈቃድ ሳትጠይቅ ፈገግ ብላ በዝግታ ወደ ጥናት ክፍሉ ገባች ። ፈገግታዋ ሙቀት እንጂ
ድምፅ ስለ ሌለው ፥ አቤል ቶሎ አላያትም እያዘገመች የተቀመጠበት ወንበር ላይ ደርሳ ግራ ጐኑን ስትሞቀው ነቃ ከእንቅልፉ ሳይሆን በተመስጦ ይሠራው ከነበረው ጽሑፍ ላይ እና ብዕሩን ወረቀቱ ላይ ወርውሮ በተቀመጠበት ተንጠራራ ። ሰውነቱን አፍታታ ።

እጁ ላይ ሰዓት የለም ። ነገር ግን፥ከንጋቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ መሆኑን ለመገመት አልተቸገረም” ። ከተቀመጠበት
ሳይነቃነቅ ሦስት ሰዓት ያህል መቆየቱ አላስገረመውም ። ከሌሊቱ ዐሥር ሰዓት ከእንቅልፉ እየነቃ እስከ ንጋት ድረስ
መሥራት፡ሰሞኑን ልማድ እያደረገው መጥቷል ። በንጹሕ አእምሮ ስለሚሠራ፥ ፍሬያማ ውጤትም አግኝቶበታል ።
ዮናታን ይህንኑ በመመልከት ለማንቃት እንዲረዳው የሳሎ ኑን ባለደወል የጠረጴዛ ሰዓት መኝታ ክፍሉ ውስጥ አድርገውለታል ። ቀን ቀን ለጥናት ጽሑፉ የሚረዱትን መጽሐፎች ሲያገላብጥ ውሎ በዚች በለሊቷ ሰአት መጻፉ ጥሩ መንገድ
ሆኖለታል።

ተንጠራርቶ ሲያበቃ ከተቀመጠበት ተነሣ ወደ በረንዳ መናፈሻ ብቅ ብሎ ፀሐይዋን ሙሉ በሙሉ ሊሞቃት ፈለግ ። የሰንበት ፀሐይ ! ጭለማው ገልጦ የእሑድ ፀሐይ ብቅ ካለች ከውጭ የሚመጣ ሰው አለ ስለዚህ የእሑድ እንግዳውን ለመቀበል ጸጉሩን ማበጣጠር ልብሱን መቀየር ነበረበት።

ጸጉሩን ሲያበጥር ልቡ ድቤ መምታት ጀመረ ። ዕረፍ ብለው አያሳርፉት ነገር ! የልብን ከበሮ አይቆጠሩት ነገር !
የገዛ ልቡ አናደደው ። ድንገት የበሩን ደወል የሰማ መሰለው ተሳስቷል ። ናፍቆት የፈጠረ ደውል ካልሆነ በስተቀር ፡ በክፍሉ ውስጥ የተሰማ ድምፅ የለም ። የሹካ ማንከያና የስሐን ድምፅ ግን በርግጥ ከሌላኛዉ ክፍል ይሰማል ።
ያቺ ሞኒካ ስትንደፋደፍ ነው ። መቼም እሷ ጠዋት መተኛት አትወድ።

ወደ በረንዳው መናፈሻ ወጥቶ ከፎቁ ቁልቁል ተመለከተ ። የዮናታን መኪና እቦታዋ የለችም ። ጠዋት ሲነሡ
ስለሰማ፡የት እንደሔዱ አላጣውም። በአስፋልቱ ሳይ ከሚሠሩ መኪናዎች መሐል ነጥሎ የሚለያት ይመስል ዐይኑን ወደ ሩቅ ወረወረ ። የቤት መኪናዎች እምብዛም የሉም ። ታክሲዎች ናቸው ሽቅብ ቁልቁል ውር ውር የሚሉት ።

ቆሞ መጠበቁ ሰለቸው ። የቆመበት ጊዜ ከዐሥራ አምስት ደቂቃ ባይበልጥም ለእሱ የዓመት ያህል ረዘመበት
“ምን ሆነው እንዲህ ቆዩ ? ” አለ በሐሳቡ፡ አልሔድም ብላቸው ይሆን ? ወይስ የሙሽራ ልብስ አልብሰው ሊያመጧት
ይሆን ? ?

ትዕግሥቱ አልቆ ወደ ውስጥ ተመለሰና ሞኒካ ጋ ሔደ።ወጥ ቤት ውስጥ ምግብ እያበሰለች ነበር ። የቡታ ጋዙን ሦስቱም ምድጃ ድስት ተጥዶበታል ። ሰርግ ሰርግ ሸተተው ፤ የወጡ ሽታ ራብ ለቀቀበት ። ቁሌቱ ገና ይንተሸተሻል ። የበሰለው ደግሞ ክዳኑን ሽቅብ እየገፈተረ ይንተከ
ተካል ። ሞኒካ ፊት ላይ ክፉኛ መቻኮል አነበበ ።

“ ምን ልርዳሽ ? ” አላት ። እሷም ፈገግ ብላ " ከምድጃው ላይ አንዱን ድስት አውርዳ ፥ ቡና በማንቆርቆሪያ
እንዲጥድላት ነገረችው ፡ሁለቱም የሥራ ድርሻቸው ላይ አትኩረው እግረ መንግዳቸውን ስለ ጽሑፍ ሥራው ሁኔታ መጨዋወት ላይ እንዳሉ ድንገት ደወሉ ተንቃጨለ።

አቤል ሲሰማው በላብ ተጠምቀ ፣ጭንቅ አለው ፤የልቡ ትርታ ፍጥነቱን ጨመረ ። ምን ሰው ያስደነግጣሉ ! ቀስ ብለው አይደውሉም እንዴ ? ” የቡና ማንቆርቆሪያ ክዳን እንደ ወደቀበት ያስተዋለው ቆየት ብሎ ትንሽ ከተረጋጋ በኋላ ነው።

ሞነካ ዋናውን በር ከፍታ እንግዶቿን ስትቀበል አቤል ወጥ ቤት ውስጥ እንደ ቆመ ጆሮውን ላከ። የተነባበረ የጫማ ድምፅ ። የማን የማን ይሆን ? የዮናታን ፡ የእስክንድር ፡ የሚሰማው የወንዶች ድምፅ ብቻ ሆነበት ። የልቡ ምት ስላስፈራው ደረቱን በእጁ ደገፈ ። ወዲያው ግን ሞኒካ ራሷን በእንግሊዝኛ ስታስተዋውቅ ስለ ሰማ አዲስ ሰው
መምጣቱን ገመት ።

ያላበውን እጁን አጠገቡ ያገኘው ነገር ላይ ጠራረገ ።ግንባሩን ፡ ጉንጩን ዐይኑን በእጁ አሻሸ እንደ ቆመ ጸጉሩን አበጣጠረ ። የሸሚዝ ኮሌታውን እያስተካከለ በረዥሙ ተነፈሰ ጭንቀት የሚያባርር፥ ፍርሐት የሚያስወግድ አተነፋፈስ : እና ርምጃውን በልቡ እየቆጠረ ወደ ሳሎን ገባ ።

ከአጭር ጠይም ሴት ልጅ ጋር ዐይን ለዐይን ተገጣጠሙ ። የሁሉም ፊት በፈገግታ ደምቆአል " ፈገግታው ሁሉ ለአቤል ጐልቶ የታየው የትዕግሥት ነው " በጉንጭ መሰርጐድ የታጀበ ፈገግታ ! ይህን ፈገግታዋን ለመጀመሪያ ጊዜ ካየው አንሥቶ ከአምስት ወር ራብ በኋላ ማየቱ ነው ። የሚወደውን የጉንጯን ስርጉድ ቀርቦ ሲያይ የመጀመሪያው ጊዜው መሆኑ ነው ። ማንን ቀድሞ መጨበጥ እንዳለበት ግራ ገብቶት ሲርበተበት አብራው የቆየችውን
ሞኒካንም እንደ አዲስ ጨበጣት ።

ለእስክንድር ያለዉን ስሜት ቆንጥጦ መያዝ አልቻለም ። ስሜቱ ፈንቅሎት ጉንጩን ጥብቅ አድርጐ ሳመውና
ይህ ሁሉ የአንተ ጥረት ያስገኘው ፍሬ ነው አስው ። ፊቱን በቅጽበት ወዶ ዮናታን መል። እና ደግሞ የርስዎ ? ” አላቸው ። ፍቅሩን በዓይኑ ከመግለጽ ቀቀር ተንጠራርቶ ሊስማቸው አልደፈረም ። ሦስተኛ ባለውለታውን ሲያመሰግን ዘወር ሲል ከአጠገቡ አጣት ። ሞኒካ ድስት ሲገነፍል ሰምታ እየሮጠች ወደ ወጥ ቤቱ ተመልሳ ነበር ።

ትዕግሥት በነጭ የሀገር ልብስ ነው የመጣችው።አቤል ይህንኑ ለብሳ የተመለከተቀትን እሑድ ወዲያው አላስታወሰም " ቆይቶ ቆይቶ ነው ከእነ ማርታ ጋር ሰርግ ቤት ስትሄድ ልብሳው እንደ ነበር ያስታወሰው። ሰላምታውንና ምስጋናውን ጨርሶ ሲቀመጥም ልቡ እልተረጋጋም ነበር ።ይበልጥ የትርታውን ፍጥነትና አስጭናቂነት ጨመረ
ዘሎ ዘሎ አንዴ ቀጥ እንዳይል ፈራ።

ትዕግሥት ማለት እሷ ነች ። ታዲያ የተመኙትን ሲያገኙ መንቀጥቀጥ ነው ? ደብዳቤዉ ያሳደረበት ስሜትና ሲገናኙ የደረሰው ሁኔታ ባለመገጣጠሙ በልቡ በሸቀ። ያ ሁሉ የፍቅር ቃላት ጋጋታ ምን ዋጠው ? ይኖራል ! ጸጥታውን የሚሰብርለት ድምፅ አጥቶ ነው እንጄ በሁለቱም ውስጥ አለ ።

አቤል ኤቼዳች ቃል መተንፈስ ፈልጎ ምላሱን ተጠራጠረው " ምናልባት የተሳሰረበት እንደሆንስ ? ከፍቅር
እመቤቱ ፊት የተቀመጠው ገላው የሚንቀጠቀጥ ጀርክ የሚመታ መሠለው።

በድንገት ዐይኑ የእጁ ጠባሳ ላይ ዐረፈ ምግብ አዳራሹ ውስጥ የወደቀ ጊዜ የወጡ ፍንጣቂ ያተረፈለት ጠባሳ ።
መጥፎ ስሜት አልተናነቀውም መጥፎ የልብ ጠባሳ ነበር እንጂ የእጅ ጠባሰ ምንም አይደለም ። የልቡን ቁስል ደብዳቤዋ ባመነጨበት እንባ ካጠበው ሰንብቷል ።

ተጫወቺ የሚል ቃል እንደ ምንም ከአፉ
ገፍትሮ አወጣ ።

ትዕግት በእሺታ ፈገግ አለች ፈገግታዋ ጠዋት ከሥራው ላይ ካባነነችው ፀሐይ ይበልጥ ደምቆ ታየው።

ሳያስቡት የዝምታው ባሕር ዮናታን እስክንድርም ውጧቸው ነበር ። ከተቀመጡ ጀምሮ ቃል አልተነፈሱም
ታዛቢ ባይሆኑም ታዛቢ መሰለዋል ። ወጥ ቤት ውስጥ የሚንተሽተሽው ምግብ ሽታ የእስክንድርን አንጀት እያላወሰው ነበር። በአፉ ምራቅ ሲሞላ ተሰማው።

"በመጀመሪያ የመኝታና የጥናት ክፍሎችህን ለትእግስት አሰጎብኛት ! አሉ ዮናታን በቤቱ ውስጥ እንቅስቃሴና ድምፅ ለመፍጠር በማሰብ።

አቤል ከትዕግሥት ጋር ተነሣ" ዮናታንና እስክንድርን በዝግታ ከኋላቸው ተከተሏቸው ።

“ ፍቅራቸው በጥሩ መልክ ይቀጥል ይሆን ? ” አለ እስክንድር በሹክሹክታ ድምፅ ፥ ወደ ዮናታን ጆሮ ጠጋ ብሎ ።
ቢቀጥል መልካም ነው ። ባይቀጥልም አቤልን እንዳለፈው አይጐዳውም ። ተቀራርበው ቃላት ከተለዋወጡ
ዐይኑን መግለጥ ይችላል አሉ ዮናታንም በሹክሹክታ በአቤልና
ሊቀበላቸው መዘጋጀቱን ፧እንዴት ይጠርጥሩት? እነሱ የሚያውቁት በወዳጃቸው፡ በባለውለታቸውና
በድሮ ጐረቤታቸው በአባባ ብራቱ ቤት ተገኝተው ጸበል፤ ጸዲቅ ሊቀምሱ፤ ሊጨዋወቱ ነው፡፡ ተዘገጃጅተው ለመሄድ ተነሱ......
ጠዋት ላይ መቶ አለቃ ድንበሩ እንዲጽናና፡ እንዲረጋጋ ተደርጐ፤ እህል ውሃ ከቀመሰ በኋላ፤ ልጆቹ ወደሱ እየመጡ እንደሆነ ተነገረው፡፡ ከዚያም በእድርተኞቹና በወዳጅ ዘመዶቹ ተከቦ አይኖቹን በበሩ አጥር ለይ እያንከራተተ በናፍቀት ይጠባበቅ ጀመር። ልጆቹ ከአሁን አሁን መጥተውለት እስከሚስማቸው፣ እስከሚያቅፋቸው፡ አንገታቸው ላይ ተጠምጥሞ እስከሚያነባ ድረስ ተጣድፎና፤ በጉጉት ተውጦ፤ ከአጥሩ በር ላይ አይኖቹን ሳይነቅል መጠባበቁን ቀጠለ፡፡ ትህትና ትህትና...ትንሿ ትህትና... ቆንጅዬዋ ትህትና፣ የሚወዳት ልጁ እንዴት ሆና
ይሆን? ማንን አክላ ይሆን? እንደዚያ የሚንሰፈሰፍላት ትህትና...
አንዱዓለም ትንሹ የአካሉ ክፋይ ጋሻዬ የሚለው ወንድ ልጁ ፣ እንደ አህያ ጡት ሁለት ብቸኛ ልጆቹ፡፡ በድንገት እንደተለያቸው ሲቀር ለዘመናት ናፍቆታቸው ውስጡን ሲቦረቡረው የኖረው፣ ዐይኖቹ ደም እስከሚያለቅሱ ድረስ ያለቀሰላቸው ልጆቹ ተያይዘው ይመጡልሃል ተብሎ ከተነገረው በኋላ፤ እሰከሚያያቸው፤ እስከሚያገኛቸው ፤ ድረስ አላምን አለ፡፡ እንደ ባለቤቱ እንደ አመልማል እነሱም ከድተውት እንዳይሆን ልቡ ፈርቶና በጥርጣሬ ተውጦ መጠባበቁን ቀጠለ... በንግግራቸው መሰረት እነ ሻለቃ ልክ ቤት መድረሳቸውን ሲያውቁ አባባ ብራቱ ከደጅ
ተቀበሏቸውና....
ዛሬ ጸበል ጻዲቁ የተዘጋጀው ከኔ ቤት ሳይሆን እዚህ ከናንተ ቤት ነው!" አሉና የጐረቤታቸውን የእነትህትናን አጥር በር ብርግድ አድርገው ከፈቱት፡፡ የአብራኩን ክፋዮች ዓይናቸውን ለማየት የአስራ
አንድ አመታት ናፍቆቱን ሊወጣ የሚጠባበቀው እንግዳ እዚያ ከሰዎች
መካከል ሆኖ ደጅ ደጁን ሲናፍቅ በሩ ብርግድ ብሎ ተከፈተ፡፡ የሱም ልብ
ከበሩ ጋር አብሮ ተበረገደ..አባባ ቢራቱ ቀድመው ገቡ፡፡ ከዚያም ሻለቃ
ብሩክ ተከተለ፡፡ እንግዳው ልቡ ከቦታዋ ተነቃነቀች፡፡ቀጥሎ...ቀጥሎ አዎን! ! እሷ ናት! እሷ ናት! ! ትህትና ናት!! ትንሿ ልጄ ናት! የኔ ፍቅር ናት!! እናቴ ናት!! አዎን ! አዎን! ደርባባዬ ናት!! እንደ እብድ
አይነት ሆኖ፤ እጆቹን በሰፊው ዘርግቶ፤ እያለቀሰ፤ እየጮኽ፤ ተነሳ... ምን ያደርጋል? ውስጡ በሃዘንና በመከራ ተደቁሶ አቅም አነሰውና ድንቅፍቅፍ ብሎ ሊወድቅ ሲል ሰዎች ተረባርበው ደገፉት፡፡ ከዚያም ራሱን ከደጋፊዎቹ እጅ አላቀቀና “ትህትናዬ... ትሁቴ ልጄ... ህይወቴ
አካሌ... እንዱዓለሜ..! የኔ ጌታ! ጌታዬ! እናታችሁስ የታለች?
አመልማልዬስ የታለች? የታለች? እናታችሁ?! ጥሯትና ተቀበሉኝ!
ልጆቼ! ኑ ሳሙኝ ልጆቼ ኑ ሳሙኝ ...ኑ! ...ኑ! ...ኑ! ወደዚህ” እንባውን
እንደ ጉድ እያጉረፈ እጆቹን እያርገበገበ በሁለመናው ሊያቅፋቸው እያለቀሰ፤ እየሳቀም፣ እየሳቀ ፧ እያለቀሰም፣ እንደ እብድ ዓይነት ሆኖ፤ እየተደነቃቀፈ፧ ወደ ልጆቹ ተንደረደረ... ትህትናም አንዱዓለምም ከፊት ለፊት ወደ እነሱ የሚመጣው ሰው ሞትን ድል ነስቶ የተነሳ፣ በአካል የሚያዩት ሰው፤ እሱ የሚወዱት፤ የሚያፈቅሩት፤ ገና በልጅነታቸው የተለያቸው አባታቸው፣ አለኝታቸው መቶ አለቃ ድንበሩ
መሆኑን፤ ያ እንደ ነፍሱ የሚወዳቸው አባታቸው መሆኑን፤ ያ ገና ናፍቆቱን የተነጠቁትና ትንሿ ልባቸው በሀዘን
የተሰበረችለት፤መመኪያ ፤አለኝታቸው፤ እሱ ራሱ መቶ አለቃ ድንበሩ
ለማወቅ ጊዜ አልወሰደባቸውም ነበር፡፡ ሥጋ ለሥጋ የሚነጋገርበት የራሱ ቋንቋ ስላለው እሱነቱን ለማወቅ እንዴት ሊሳናቸው ይችላል ? ስጋ የራሱ ቋንቋ እንጂ ምን ሌላ ቋንቋ ያስፈልገዋል እግዚኦ! በዚያን አባታቸው መሆኑን ባውቁ ጊዜ ስሜት? የማይታመን ታሪክ! ሊሆን የማይችል አንደሀውልት ደርቀው ከቀሩበት ሳይንቀሳቀሱ፤ እንደምስሶ ከተገተሩበት ቦታ ንቅንቅ ሳይሉ፤ እሱ በሰዎች ተደግፎ እያለቀሰ፣ እየሳቀ ፣እየሳቀ እያለቀሰም ሄዶ እላያቸው ላይ
ተጠመጠመ...
የተፈጥሮ ህግ አቅጣጫዋን ለወጠች? የቀንና የሌሊት መፈራረቅ ህግ ቀረ? ወንዞች ሽቅብ ይፈስ ጀመረ? ፀሐይዋስ በምስራቅ ወጥታ በምዕራብ መጥለቋን አቆመች? መሬት በፀሐይ ዙሪያ መሽከርከሯ ታበቃና ወንዞች ሽቅብ መፍሰስ ከጀመሩ ብቻ ነው የሞተ ሰው ሊነሳ የሚችለው፡፡
ሁለቱም በጭንቅላታቸው ውስጥ የነጐድጓድ ድምፅ ያስተጋባ መሰላቸው፡፡
ዓይኖቻቸውን ጨፈኑ፡፡ ገለጡ፡፡ ጨፈኑ፡፡ ገለጡ፡፡ ህያው ነው፡፡ ነገሩ ህልም አይደለም፡፡ ከረጅም ዓመታት በፊት ወጥቶ የቀረውና ሞቷል ብለው ተስፋ
የቆረጡበት አባታቸውን በህይወት ማግኘት ማለት ሊቋቋሙት ከሚገባው
በላይ የሚያስደነግጥ ደስታ ነውና፤ ደንግጠው ያለ እንቅስቃሴ እንደ
ሀውልት በቆሙበት ቦታ ላይ፤ እሱ ደርሶ እላያቸው ላይ ሲጠመጠም፣
ከገቡበት ሰመመናዊ የህልም ዓለም ወጥተው፣ ገሀዳዊውን እውነታ ሲረዱ፣ አባታቸውን በአካል ዳብሰው ሲያስተውሉት፣ በተለይ የትህትና
ሁኔታ እጅግ የሚያሳዝን አንጀት የሚበላ ነበር፡፡ በሰመመን ውስጥ ሆነው፤ በሚንቀጠቀጡ እጆቻቸው ይደባብሱት
ጀመር... ህልም ያለመሆኑን፣ ሥጋ የለበሰ አባታቸው መቶ አለቃ ድንበሩ መሆኑን፣
ሲያረጋግጡ፤ አስተቃቀፋቸው፣ አሳሳማቸው፤ በአጠቃላይ ሁኔታቸው
ሁሉ እጅግ ልብ የሚነካና እዚያ የነበሩትን ሁሉ በእንባ ያራጨ ነበር።
ከዚያም አባትና ልጆች ተቃቅፈው እንደ ስስት እንጀራ እርስ በርስ እየተሻሙ፤ አንገት ለአንገት ተቃቅፈው ሲሳሳሙ ከቆዩ በኋላ፤ ሻለቃ የፈራው ነገር ሁሉ ሆነ :: በዚያች ግቢ ውስጥ ተፈጥሮ እንቅስቃሴዋን ለየት አደረገች፡፡ ፀሃይዋ ጥቁር ግርዶሿን ጣለችና ብርሀንዋን ከለከለች፡፡
ነፋሱም አስገመገመና በዚያች ትንሽ ግቢ ውስጥ አዋራውን ወደ ሰማይ አስነሳ!! ለዚህች አስገራሚና ውብ ቀን ላልታደለችው ሚስኪን የሰማይ አሞራ ጭምር በድጋሜ ዋይ! ዋይ! እያለ አለቀሰላት፡፡ አንገት ለአንገት ተቃቅፈው፤ ለዚያች ይህንን የመሰለውን አስደሳች ቀን ለአንድ ቀን እንኳ ለማየት ላልታደለችው ከርታታ፤ እዬዬ ብለው በእንባ ተራጩላት።
ሁለቱ የትህትና ልጆች በቤተሰቡ ለቅሶ ተደናግጠውና በእናታቸው እግር ላይ የሙጥኝ ብለው ተጠምጥመው የለቅሶው ተካፋዮች ሆኑ፡፡ ሳያውቁት
እነሱም የደስታውና የሀዘኑ ተካፋይነታቸውን አሳዩ :: ድንቅ! ነው ፀሐይዋ እንደጠለቀች አልቀረችም! በሌላ በኩል በተራራው አናት ላይ ብርሀኗን ፈንጥቃለች.. አዲስ ህይወት ይመጣል... አዲስ ህይወት ይቀጥላል...ህዝቡ በዋይታና በደስታው መሃል እየዋዠቀ አብሯቸው ወዲያና ወዲህ ሲሯሯጥ፣ ሻለቃ ብሩክ በደስታ ተሞልቶ፤ እንባውን ከፊቱ ላይ አየጠራረገና ካሜራውን ደጋግሞ እየተጫነ ለነገው ትዝታ የዛሬውን እጅግ አስደናቂውንና አስገራሚውን እውነታ መቅረጹን ቀጠለ.........!!!

ተፈጸመ

ታሪኩ ይህን ይመስላል አስተያያታችሁ ለሰጣችሁኝ እንዲሁም በንባብ አብራችሁኝ ለነበራችሁ ሁሉ በጣም አመሰግናለው ዛሬም አንብባችሁ ስትጨርሱ የተለመደውን አስተያየት እጠብቃለው በ @atronosebot አድርሱኝ። ሌላው #ሰመመን ድርሰት በቅርቡ መጠናቀቁን ታውቃላቹ በተቻለኝ መጠን ለመመለስ ሞክሪአለሁ ያልመለስኩት ካለም ምስጋናዬ አሁን ይድረሳቹ በጣም አመሰግናለው ከቡዙዎቸለ ግን ልቤን የነካኝ አንድ አስተያየት አለ በድምፅ የተላከልኝ ስለሆነ ሁላችሁም ብትሰሙት ደስ ይለኛል 👇