ዐውደ ምሕረት
3.68K subscribers
930 photos
24 videos
271 files
193 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
"የእግዚአብሔር መልአክ"

#በስሙ ስመ እግዚአብሔርን የተሸከመ መልአክ ማለት ነው።ሚካኤል፣ገብርኤል፣ሩፋኤል ወ.ዘ.ተ የሚሉት ስሞች ውስጥ "ኤል" የሚለው ቃል አምላክ ማለት ነውና።“ስሜም በእርሱ ስለ ሆነ።”ዘጸ 23፥21
እንዲል።

#በልቡ ስብሐተ እግዚአብሔርን የያዘ በአንደበቱም
እግዚአብሔርን የሚያመሰግን መልአክ ነው።“አንዱም ለአንዱ፦ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኽ ነበር።”(ኢሳ 6፥3) እንዳለ ነቢዩ።

#ፈቃደ እግዚአብሔርን የሚፈጽም ማለት ነው።ማር ያለውን ይምራል ፤ ቅሰፍ ያለውን ይቀስፋልና።

“የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል።”(መዝ33፥7)

“ለእግዚአብሔርም ክብር ስላልሰጠ ያን ጊዜ የጌታ መልአክ መታው በትልም ተበልቶ ሞተ።”ሐዋ12፥23
ተብሎ እንደተጻፈ።

#የእግዚአብሔርን ክብር የሚገልጥ መልአክ ነው።“ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል።” (መዝ 18፥1) በሚለው ኃይለ ቃል ውስጥ "ሰማያት" የሚለው ቃል በምሥጢር መላእክት ማለት ነው።ይኸውም “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ።”
(ሉቃ2፥14) ባለው ኃይለ ቃል ውስጥ ካለው "አርያም" ከሚለው ቃል ጋር አንድ ነው።

#የእግዚአብሔርን ሕዝብ መርቶ ወደ ተዘጋጀላቸው ስፍራ የሚያገባ መልአክ ነው።“በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ።”
( ዘጸ 23፥20) እንዲል።

#በእግዚአብሔር የሚታመነውን ሰው እግሩ በድንጋይ እንዳይሰናከል በእጆቹ የሚያነሣ መልአክ ነው።"በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል።
(መዝ 90:11-12)

#ሰዎች ሁሉ መዳንን (መንግሥተ እግዚአብሔርን) እንዲወርሱ ለማገዝ የሚላክ፤የሚያገለግልም መልአክ ነው።“ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?”(ዕብ 1፥14) እንዳለ ሐዋርያው።

#በኃጢአተኞች መዳንም የሚደሰት መልአክ ማለት ነው።“ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል።”ሉቃ15፥10

ይኸውም ሰውን እጅግ እጅግ እጅግ የሚወድድ መልአከ ምሕረት፣መልአከ ፍስሐ፣መልአከ ሰላም ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ነው!!!በረከቱ ይደርብን!!!

#ኢዮብ ክንፈ
#ኅዳር ሚካኤል/2017 ዓ.ም
ሁሉ አንተን ተስፋ ያደርጋሉ (መዝ103፥27)

#ፍጥረት ሁሉ የፈጠረው እግዚአብሔርን ተስፋ ያደርጋል።ምርጫ አይደለም የህልውና ጉዳይ እንጂ።በደመነፍስ ሕያዋን ሆነው የሚኖሩት እንስሳት፣አራዊት፣አዋዕፍ፣ዓሦችና አንበሪዎች እርሱ እግዚአብሔር ባወቀ ተስፋ ያደርጉታል።እርሱም ምግባቸውን በየጊዜው ይሰጣቸዋል።ከቸር እጆቹ ጠግበው ያመሰግኑታል።

#ሰውም እንደ መላእክት ሁሉ "ተስፋ" የተሰጠው ታላቅ ፍጡር ነው።ተስፋውም በሕግ ቃልኪዳን ላይ የተመሠረተ ነው።“ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።”(ዘፍ 2፥17) ሲል ጌታ ለሰው ማዘዙ የሰው የሕይወት ተስፋው ሕጉን በመጠበቅ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያስረዳል።

#ኋላም በቅዱስ ሙሴ አማካኝነት የተሰጠው “ለሚወድዱኝ፥ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝ።” (ዘጸ 20፥6) የሚለው ቃል ከላይ ያነሣነውን ሐሳብ ያጠናክረዋል።

#በእግዚአብሔር ታላቅ ፍቅር የተወደደ ሰው የሚባል ፍጡር ለሕይወቱ የተሰጠውን ሕግ አፍርሶ ቢበድል እንኳን ይቅር የመባል ተስፋ አለው። ስለዚህ የሚተማመነው "በእግዚአብሔር ምሕረት" ላይ እንጂ በራሱ ሕግ የመጠበቅ ብቃት ላይ አይሆንም።

#ተስፋ ቆርጫለሁ

#የሚለው ድምፅ እዚህና እዚያ ይሰማል።ተስፋ ማለት እግዚአብሔር ከሆነ ተስፋ ቆርጫለሁ ማለት እግዚአብሔርን ትቼአለሁ ማለት ይሆናል።ተስፋ ለመቁረጥ ተስፋ ማድረግ ያስፈልጋል።ሰው ተስፋ የሚያደርጋቸው ጊዜአዊ ነገሮች ከእውነተኛ ተስፋው ከእግዚአብሔር ጋር ይምታቱበትና፤ያልተሳኩ እንደሆነ
ተስፋ ቆረጥሁ ይላል።መማርን፣አንድ ቦታ ተቀጥሮ መሥራትን፣እገሌን ወይ እገሊትን ማግባትን፣ልጆች መውለድን፣ባህር ማዶ ተሻግሮ መኖርን ወ.ዘ.ተ።

#አሁንስ ደከመኝ፣ታከትኩ፣ከዚህ በላይስ አልሄድም፣
በቃኝ ... የሚሉ ንግግሮች ከላይ በተጠቀሱት ጉዳዮች አለመሳካት የሚነገሩ ናቸው።"እናንተ ስለፈለጋችሁ የሚሆን ነገር የለም፤ሆኑ አልሆኑ የእግረ መንገድ ጉዳዮች ናቸው።እነዚህ ጉዳዮች እንደ ሕፃናት ማቆያዎች (Day cares) ናቸው።የተፈጠራችሁላቸው ዓላማዎች አይደሉም።" እያለ ሕፃንነታችንን እየነገረን ከሆነስ!? "ፈቃድህ ይሁን" ብለን በፈቃዱ ሲከለክለን ማዘን አይገባም።

#ኑሮው!!! ኧረ ውድነቱ!!! "እግዚአብሔር ሆይ ወዴት ነህ???" "አንተን በማኖር ግብር ነኝ" ይልሃላ።ወይ ግሩም እስከዛሬ ታዲያ በኑሮ ርካሽነት ነበር እንዴ የኖርነው!?በእኔ ዕድሜ ሳውቅ በየጊዜው "ኑሮ ተወደደ" ነው የሚባለው።ሲወደድ እንጂ ሲረክስ ያየሁት ነገር የለም (ከሰው(ከእኔ) በቀር 😭)።ግን በቸርነቱ አለን!!!ግሩም ነው መቼስ!!!

#ለነፍሳችን ለማደር ከኃጢአት ጋር በምናደርገው ትግልም ተመሳሳዩ ነገር ይገጥመናል።"ከዚህ በኋላ ይህንን ያህል በድለህ እግዚአብሔር ይቅር የሚልህ መሰለህ" የሚል ሐሳብ በኅሊናህ ሲመጣ "አዎን ይቅር ይለኛል" በለው።ገድለህ "አዎን"፤አመንዝረህ "አዎን"፤ዘሙተህ "አዎን"፤ሰርቀህ "አዎን"፤"ዋሽተህ" አዎን!!!

#ታዲያ የእግዚአብሔር ፍርድ ወዴት አለ?

#ቅዱስ ዳዊት “መንገድህ በባህር ውስጥ ነው፥ ፍለጋህም በብዙ ውኆች ነው፥ አረማመድህም አልታወቀም።”(መዝ 76፥19) ሲል የእግዚአብሔር አሠረ ፍትሑ (የፍርዱ መንገድ) እንደማይታወቅ ተናግሯል።ቅዱስ ጳውሎስም “የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም።”(ሮሜ 11 ፥ 33) በማለት የእግዚአብሔርን ፍርድ አይመረመሬነት ገልጧል።ስለዚህ "የእግዚአብሔር ፍርድ ወዴት አለ?" ለሚለው ጥያቄ መልሱ "በራሱ ዘንድ ነው" የሚል ነው።

#ይህንን ሁሉ አጥፈተህማ እግዚአብሔር ሳይቀጣህ አይቀርም" የሚል ድምፅ ኅሊናህ ውስጥ ሲመላለስ፤"እግዚአብሔር ደግ አባቴ ነውና በደንብ ይቅጣኝ፤አንዴ አይደለም መቶ ጊዜ ይቅጣኝ።ብቻ ለአንተ ለከይሲው አሳልፎ አይሰጠኝ።እንኳን የእኔ የአንዱ በደል ከአዳም ጀምሮ እስከ ኅልፈተ ዓለም የሚሠራው ኃጢአት የደጉ አባቴን የእግዚአብሔርን አንዲቱን የምሕረት ጠብታ አያህልም!!!" በለው። እንዲህ ብለን በንስሐ ወደ እግዚአብሔር ስንቀርብ እግዚአብሔር ደስ ይለዋል።ቁጣውን ሁሉ ይተወዋል።ሰው ራሱ ላይ ከልቡ ሲፈርድ እግዚአብሔር ፍርዱን ይተውለታል!!!
እግዚአብሔር ጻድቅ ነውና፥ ጽድቅንም ይወድዳል፤ ቅንነት ግን ፊቱን ታየዋለች።”(መዝ 11፥7) እንዳለ መዝሙረኛው በጽድቅ ራሳችን ላይ ፈርደን፤በልብ ቅንነት ራሳችንን ጻድቅ ለሆነ እግዚአብሔር ስንሰጥ፤እግዚአብሔር ደግሞ የምሕረት ፊቱን ያሳየናል።ይህንንም በልባችን በሚመላብን ፍጹም ሰላምና ደስታ እናውቃለን!!!

"#ሳለ #መድኃኔዓለም" የምወዳት የእናቶቼ ብሂል ናት።እውነትም "#ሳለ #መድኃኔዓለም" #አምላከ #ተክለሃይማኖት!!!

#ኢዮብ ክንፈ
#ኅዳር 13/2017 ዓ.ም
#ተስፋ ነቢያት ክርስቶስ

#ከአዳም ጀምሮ የነበሩ ነቢያት ሁሉ ተስፋቸው
#ክርስቶስ ነው።#ክርስቶስም ዓለሙን ሁሉ ያዳነው መሲሕ ነው።ከድንግሊቱ እመቤታችን ማርያም ሲወለድም #ኢየሱስ" ተብሎ ተጠራ።በመሆኑም ነቢያት የተነበዩለት ክርስቶስ (መሲሑ) ከእመቤታችን የተወለደው #ኢየሱስ" ነው ለማለት "ኢየሱስ ክርስቶስ" ብለን እንጠራዋለን።"ኢየሱስ ክርስቶስ" ማለት "መድኃኒት ወንጉሥ" ማለትም ነው።

#የነቢያቱ ጾም ተስፋ ነው።ልደተ ክርስቶስ ኢየሱስ ደግሞ የተስፋው ፍጻሜ።ከቅዱስ አዳም ጀምሮ 5,500 ዓመት ያህል የጌታ ልደቱ ተጠብቋል።"
“የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ”(ገላ 4፥4) እንዳለ ሐዋርያው እግዚአብሔር በአዳም ሥጋ ተገለጠ።

#ልዑል ክንዱን ሰደደልን" እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም ልዑል አብ ክንዱን ወልድን ላከልን።በዚህም ተስፋችን
ተፈጸመ።እውነተኛ ተስፋ እንዲህ ደጅ ያስጠናል።በ ቀላሉም አይገኝም።በረጅሙ ጾመ ነቢያት “ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን አምላካችንን የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ”(ቲቶ 2፥12-13) አየን።

#በሺዎች ዓመታት ተስፋን የሚፈጽም እውነተኛ ተስፋ እግዚአብሔርን ይዘን ተስፋ እንዳንቆርጥ እንጠንቀቅ።ተስፋችን ግን "የእግዚአብሔር ፈቃድ" ይሁን እንጂ የእኛ አይሁን።ከቅዱሳን ነቢያቱ ጋር በአንድ መንፈስ ተሠርተን ልደቱን ለማየት ያብቃን።
#ጾመ ነቢያት ተስፋ ፤ #የጌታ ልደት የተስፋቸው ፍጻሜ ነውና!!!

#መልካም ጾመ ነቢያት

#ኢዮብ ክንፈ
#ኅዳር 15/2017 ዓ.ም
#ተስፋ ነቢያት ክርስቶስ

#ከአዳም ጀምሮ የነበሩ ነቢያት ሁሉ ተስፋቸው
#ክርስቶስ ነው።#ክርስቶስም ዓለሙን ሁሉ ያዳነው መሲሕ ነው።ከድንግሊቱ እመቤታችን ማርያም ሲወለድም #ኢየሱስ" ተብሎ ተጠራ።በመሆኑም ነቢያት የተነበዩለት ክርስቶስ (መሲሑ) ከእመቤታችን የተወለደው #ኢየሱስ" ነው ለማለት "ኢየሱስ ክርስቶስ" ብለን እንጠራዋለን።"ኢየሱስ ክርስቶስ" ማለት "መድኃኒት ወንጉሥ" ማለትም ነው።

#የነቢያቱ ጾም ተስፋ ነው።ልደተ ክርስቶስ ኢየሱስ ደግሞ የተስፋው ፍጻሜ።ከቅዱስ አዳም ጀምሮ 5,500 ዓመት ያህል የጌታ ልደቱ ተጠብቋል።"
“የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ”(ገላ 4፥4) እንዳለ ሐዋርያው እግዚአብሔር በአዳም ሥጋ ተገለጠ።

#ልዑል ክንዱን ሰደደልን" እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም ልዑል አብ ክንዱን ወልድን ላከልን።በዚህም ተስፋችን
ተፈጸመ።እውነተኛ ተስፋ እንዲህ ደጅ ያስጠናል።በ ቀላሉም አይገኝም።በረጅሙ ጾመ ነቢያት “ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን አምላካችንን የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ”(ቲቶ 2፥12-13) አየን።

#በሺዎች ዓመታት ተስፋን የሚፈጽም እውነተኛ ተስፋ እግዚአብሔርን ይዘን ተስፋ እንዳንቆርጥ እንጠንቀቅ።ተስፋችን ግን "የእግዚአብሔር ፈቃድ" ይሁን እንጂ የእኛ አይሁን።ከቅዱሳን ነቢያቱ ጋር በአንድ መንፈስ ተሠርተን ልደቱን ለማየት ያብቃን።
#ጾመ ነቢያት ተስፋ ፤ #የጌታ ልደት የተስፋቸው ፍጻሜ ነውና!!!

#መልካም ጾመ ነቢያት

#ኢዮብ ክንፈ
#ኅዳር 15/2017 ዓ.ም
ከዕለቱ #መዝሙር

#መዝሙረ ዳዊት 69

አቤቱ፥ እኔን ለማዳን ተመልከት፤ አቤቱ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን።
ነፍሴን የሚሹአት ይፈሩ ይጐስቍሉም፥ ክፉንም የሚመክሩብኝ ወደ ኋላቸው ይመለሱ ይፈሩም።
እንኳ እንኳ የሚሉኝ አፍረው ወዲያው ወደ ኋላቸው ይመለሱ።
የሚሹህ ሁሉ በአንተ ሐሤት ያድርጉ ደስ ይበላቸው፤ ማዳንህን የሚወድዱ ሁልጊዜ፦ እግዚአብሔር ታላቅ ነው ይበሉ።
እኔ ችግረኛና ምስኪን ነኝ፤ አቤቱ፥ እርዳኝ፤ ረዳቴ ታዳጊዬም አንተ ነህ፤ አቤቱ፥ አትዘግይ።

እንኳን ለጻድቁ፣ለየዋሁ፣ለደጉ፣ለብእሴ #እግዚአብሔር ለቅዱስ #ዳዊት በዓለ ዕረፍት በሰላም አደረሳችሁ!!!የቅዱስ #ዳዊት በረከቱ ይደርብን!!!

#ታኅሣሥ 23/2017 ዓ.ም
#ኢዮብ ክንፈ
" #ደስታ_ተክለ_ሃይማኖት_ተወለደ"

#የሚገቡት
እንኳን ማርያም ማረችሽ ፣
አሜን!
እንኳን ማርያም ሁለት አረገችሽ
አሜን!
#የሚወጡት
ማርያም ጭንሽን ታሙቀው
አሜን!
ማርያም በሽልም ታውጣሽ.......ይሏታል
የእመጫቷ መልስ አሜን !አሜን! የሚል ብቻ ነው። ይህ የእግዚእኃረያ ቤት ነው። ባሏ ፀጋ ዘአብ ደስታውን መቋቋም አቅቶታል ቤቷ በወዳጆቻቸው እና በጠያቂዎቻቸው እንዲሁም ባለ መውለዳቸው እንደ ኃጢያተኛ ቆጥሮ ይጠቋቆሙባቸው በነበሩ ሰዎች ተጨናንቃለች መካን ሚስቱ ወንድ ልጅን ወልዳለችና ። ለሁሉም እንደ ማዕረጋቸው ምሳ አደረጉላቸው ማጋረጃ ገልጠው እናቲቱንና ልጇን ቅቤ እስኪቀቡ የቸኮሉ ሳይኖሩ አይቀሩም ሌላው ግን ስለ አወላለዷ ለመረዳት ሰሀናቸውን ይዘው የወላዲቱ አልጋ አጠገብ ጠጋ ብለው የተቀመጡም አልጠፋም ።

#እርሷም_የእግዚአብሔርን ቸርነት የቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት እየመሰከረች ከሞተለሚ ምርኮ እንዴት ባለ ተአምር እደዳነች እያወራች ከባሏ ከፀጋ ዘአብም ጋርም ወንድ ልጅ ስለ መውለዷ አስቀድመው ዕራይን እንዳዮ እየነገረቻቸው ቀኑን በደስታ አሳለፈች ደስታ የሆነ ልጅ ወልዳለችና ።

*ስሙንስ ማን አላችሁት ?
ፍስሐ ጽዮን ( የጽዮን ደስታዋ) ብለነዋል ። ነገር ግን መላእኩ እንደነገረን ስሙ ሌላ ነው ከእናንተም የተሰወረ በልበ ሥላሴ የተጻፈ አዲስ ስም ይወጣለታል ብሎናል። "ተክለ ሃይማኖት"! ሕጻናት እንደሚያለቅሱም አያለቅስም ነበር "ቅኖች ሰዎች ሁል ጊዜ ደስ ይላቸዋል" እንደሚል

"ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን ለእራስህ አዘጋጀህ " አንደተባለም ሕጻኑ ፍስሐ ጽዮን በተወለደ ገና በሦስተኛው ቀን ከእናቱ እቅፍ ወርዶ "አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ" ብሎ ሥላሴን በአንድነት በሦስትነት አመስግነ:: መዝ 9÷2

#ልጆች_የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው የእግዚአብሔር ስጦታ ሁሉ ደግሞ ደስ ያሰኛል ። ይልቁኑ እግዚአብሔር በእነርሱ አድሮ ድንቅ ሥራውን ይሰራባቸው ዘንድ ያዘጋጃቸው የቅዱሳን ሰዎች ልደታቸው ብቻ ሳይሆን እነርሱ እራሳቸው ደስታ ናቸው :: " በመወለዱ ብዙዎች ደስ ይላቸዋል ተድላና ደስታም ይሆንልሃል" ዮሐ1፥14 ተብሎ እንደተጻፈ እውነት ነው በመወለዱ ብዙዎች ደስ ብሎናል በሉቃስ ወንጌል ላይ መላእኩ ቅዱስ ገብርኤል በመጥምቀ መለኮት በቅዱስ ዮሐንስ መወለድ ብዙዎች ደስ እንደሚሰኙ አስረግጦ ነግሮናል።

እነሆ ዛሬ ደግሞ እንደ ዮሐንስ በድንግልና የኖረ እንደ መጥምቁ ካህን ያውም ሰማያዊ የሆነ እንደ አዋጅ ነጋሪው በምድረ ኢትየጵያን ሁሉ እየዞረ ወንጌልን የሰበከ ለእናትና ለአባቱ እንዲሁም ለብዝዎቻችን የደስታ ምንጭ የሆነ የጽዮን ደስታዋ የተባለ ፍስሐ ጽዮን ተወለደ እነሆ እኛም እንደ ተስፋው ቃል ዳግማዊው ዮሐንስ ተወልዶልናልና ደስ አለን::
#መፍቀሬ ጥበብ ቅዱስ ሰለሞን" ጻድቃን በበዙ ቁጥር ሕዝብ ደስ ይለዋል" እንዳለ አባታችን ተክለ ሃይማኖት በተወለዱ ሰዓት ክርስቲያኖች ደስ ብሏቸዋል ምክንያቱም ጻድቁ ሕሙማነ ነፍስን በትምህርታቸው ሕሙማነ ሥጋን በተአምራታቸው እያዳኑና እየፈወሱ ለሕዝብ ደስታ ምንጭ ሆነዋል ያን ጊዜ ብቻም ሳይሆን ዛሬም በአፀደ ነፍስ ሳሉ ለኛ ለክርስቲያኖች የደስታችን ምንጭ ናቸው " የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለችና " ስለኛ የጽድቅ ሕይወት የሰላም እጦት የሃይማኖት ጉለት የምግባር ዝቅጠት ዕለት ዕለት ወደ ፈጣሪ እየጸለዮ ያማልዱናልና ነው #ያዕቆ 5÷16

በጻድቃን መወለድ ሕዝብ ደስ የሚለው በተወለዱበት ዘመን እና ወር ብቻ አይደለም አንዴ ጻድቃን ከተወለዱ በኃላ ሕዝብ ለዘለአለሙ ደስ ይለዋል ጻድቃን በአፀደ ሥጋም በአፀደ ነፍስም በምልጃቸው ደስ ያሰኛሉና ..... .. ልክ እንደዛሬው......

" #እኔ ግን ለዘለዓለሙ ደስ ይለኛል
ለያዕቆብ( #ለተክለ_ሃይማኖት )
አምላክም ዝማሬን አቀርባለው" #መዝ76÷9
...........ይቆየን........

የጻድቁ አባታችን የተክለ ሃይማኖት እረድኤትና በረከት በሀገራችን ኢትዮጵያ እና በሕዝበ ክርስቲያኖች ላይ ሁሉ ለዘለዓለሙ ቀንቶ ይኑር ....!!!

ኃ/ማርያም አ.አ ኢትዮጵያ
በድጋሚ የተለጠፈ ጥንተ ጽሕፈቱ
ታህሳስ 22/2013ዓ/ም
#ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ ስለ ጠላትህ፥ ጠላትንና ቂመኛን ለማጥፋት።”(መዝ 8፥2)

#ፍስሐ #ጽዮን የተባለ #ተክለሃይማኖት በተወለደ በሦስተኛው ቀን "አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ" ብሎ እግዚአብሔርን አመሰገነ።

#ነቢየ #እግዚአብሔር #ኤርምያስ “በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፥ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ።” (ኤር 1፥5)እንደተባለ ቅዱስ #ተክለሃይማኖት ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ነቢይ ሆኖ ለእግዚአብሔር ተለየ።


#መልአከ #ብርሃን ቅዱስ #ገብርኤል ስለ ቅዱስ #ዮሐንስ መጥምቅ“በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፥ የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል፤”( ሉቃስ 1፥15) እንዳለ #ተክለሃይማኖት ጻድቅ ከዓለምና ከምኞቷ ሁሉ የተለየ ፤ በጌታም ፊት ታላቅ የተባለ ፤ መንፈስ ቅዱስም የሞላበት ነው።ዳግመኛም መልአክ “ደስታና ተድላም ይሆንልሃል፥ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል።”(ሉቃ 1፥14) እንዳለ በፍስሐ ጽዮን (በጽዮን ደስታ) በ #ተክለሃይማኖት መወለድ ለጊዜው አባቱ ቅዱስ #ጸጋ ዘአብና እናቱ ቅድስት #እግዚእ ኃረያ ተደስተዋል ፤ ለፍጻሜው ግን ጽዮን የተባለች ቅድስት #ቤተክርስቲያን ተደስታለች።

#ቅዱስ #ጳውሎስም ስለ ራሱ “ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም”(ገላ1፥15-16) እንዳለ አባታችን #ተክለሃይማኖት በጸጋ #መንፈስ #ቅዱስ ለስብከተ ወንጌል ገና በማኅፀን ተጠራ።

#ጌታም በወንጌል ስለ እነ #ተክለሃይማኖት እንዲህ አለ “በእናት ማኅፀን ጃንደረቦች ሆነው የተወለዱ አሉ”(ማቴ 19፥12)

#እንኳን አደረሳችሁ!!!

#ታኅሣሥ 26 /2017 ዓ.ም
#ኢዮብ ክንፈ
#ሁለተኛውን_ልደቱን_አስደናቂ_አደረገው!

📍እግዚአብሔር እልፍ ድንቅ ነገሮችን ትላንት አድርጓል፣ ዛሬም እያደረገ ነው ለወደፊትም ያደርጋል። ከድንቆች በላይ ግን ምንድነው ከተባለ ይህ ነው።

 አምላክ ሰው የሆነበት፣ ሰውም አምላክን የሆነበት፣ ረቂቁ
ግዙፍ የሆነበት፣ ልዑሉ ትሑት የሆነበት ይህ ሁለተኛው ልደቱ
እጅግ ይደንቃል።

 ታላቅነቱን በታናሽነት፣ ኃያልነቱን በደካማ ሥጋ ሰውሮ
መምጣቱ በጣሙን ይገርማል።

 ሰማይና ምድር የማይችሉት አምላክ በማኅፀነ ማርያም መወሰኑ
እጅግ ያስደንቃል።

 ሰማይ ዙፋኑ ምድር የእግሩ መረገጫ የሆነችለት አምላክ የዕለት
ጽንስ ሆኖ በማኅፀነ ማርያም ማደሩ በጣሙን ያስደንቃል።

 የአስራ አምስት ዓመት ብላቴና እንድትሸከመው መፍቀዱ እጅግ ያስደንቃል።

 የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ተብሎ መጠራቱ እጅግ
ያስደንቃል።

 እኛን ወደሰማይ ሊያወጣ እርሱ ወደመሬት መውረዱ በጣም
ያስደንቃል።

 እኛን ከክብር ዙፋን ላይ ሊያስቀምጥ እርሱ በውርደት በረት
መጣሉ እጅጉን ያስደንቃል።

 እኛ ከመላእክት ጋራ እንድንዘምር እርሱ ከእንስሳት ጋራ በበረት
ማደሩ ያስደንቃል።

 ባለዙፋን ባለበረት ሲሆን ማየት እጅግ ያስደንቃል።

 ኃያል አምላክ ሕጻን ሆኖ መወለዱ ያስደንቃል። (ኢሳይያስ ሕጻን ተወለደልን አለ ማቴዎስ ደግሞ የተወለደው ንጉሥ ነው ይለናል። ሰብአ ሰገል ለዚህ ዘውዳቸውን አንሥተው ለሕጻኑ ሰግደዋል። በሚታይ ዕድሜ ቢሆን ኖሮ አይታሰብም አይሞከርም ነበር።)

#በሚታይ ሕጻንነቱ ግን ዘለዓለማዊ አባትነት አለው፣
#በሚታይ ሕጻንነት ዘለዓለማዊ ንግሥና አለው፣
#በሚታይ ሕጻንነት ዘለዓለማዊ አምላክነት ስላለው ዘውዳቸውን አንሥተው ለሕጻኑ ሰገዱለት።

 ኃያል አምላክ ሕጻን ሆኖ መወለዱ እጅግ ያስደንቃል።

 የዘለዓለም አባት "አንድ" ተብሎ ዘመን ሲቆጠርለት አረ
በጣሙን ያስደንቃል።

 ከአንዲት ታናሽ ብላቴና ምግብ ሲለምን ማየት በጣም
ያስደንቃል።

 ከአንዲት ታናሽ ብላቴና ምግብን ፈልጎ ማልቀሱ እጅግ
ያስደንቃል። እግዚአብሔርም አለቀሰ ሲባል እጅግ ያስደንቃል።

 የእርሱ ማልቀስ የእርሷ እሹሩሩ ብሎ ማባበል እጅግ በጣም
ያስደንቃል።
.
.
.
.

አባ ጊዮርጊስ "የመጀመሪያውን ልደቱን (ከአብ ያለ እናት) ረቂቅ አደረገው። ሁለተኛውን ልደቱን (ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አባት) አስደናቂ አደረገው።" ብሎ እንደተናገረ በእውነት ይህ ሁለተኛ ልደቱ እጅጉን ድንቅ ነው!!

ምድር እስከ ተዘረጋችበት ውኃም እስከፈሰሰበት ድረስ ያላችሁ በክርስቶስ ክርስቶሳውያን የሆናችሁ ሁሉ እንኳን ለልደቱ ለእግዚእነ አደረሳችሁ።
መልካም በዓል!!🤲🤲



©️ከ ስምዓ ጽድቅ አርአያ የፌስ ቡክ ገጽ የተወሰደ
#ኖላዊ ወበግዕ#(እረኛም በግም)

#ትጉህ #እረኛችን #አማኑኤል ከድንግል #ማርያም ተወልዶ በበረት ተኛ።ቅዱስ ዳዊት “እነሆ፥ እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኛም አያንቀላፋምም።”(መዝ 121፥4) ሰው ሆኖ በሕፃናት ልማድ በበረት ውስጥ ተኛ።(ሉቃ 2:7)

#እረኛ ሲሆን በግ ፣ በግ ሲሆን እረኛ ነው።መልአኩም በጎቹን (ምዕመናንን) ተግቶ የሚጠብቅ የጌታን ልደት ያበሠረው መንጎቻቸውን ተግተው ይጠብቁ ለነበሩ እረኞች ነው።በእረኛነቱ ይጠብቀናል ፤ በበግነቱም በመስቀል ላይ ተሠውቶልናል (ዮሐ 1:29)።

#የጌታችን እረኛነት ግን ልዩ ነው።እረኛ በጎቹን አስብቶ ኋላ ይበላቸዋል ወይም ሽጧቸው ጥቅም ያገኛል።ይህ እረኛችን ግን ስለ ራሱ “መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል።”
(ዮሐ 10፥11) ሲል ተናግሯል።

#እርሱ ከሚገኝባት የበጎች በረት (ከቤተክርስቲያን) ያልሆኑ ሌሎች በጎችን አስመልክቶ ሩኅሩኅ እረኛ #መድኃኔዓለም እንዲህ ይላል “ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፥ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ።”(ዮሐ 10፥16)

#በዓሉን አከባበራችን ሁሉ የተዘክሮተ #እግዚአብሔር ሊሆን ይገባዋል።ስንበላ እውነተኛ መብላችን ክርስቶስ መወለዱን ፤ ስንጠጣም እውነተኛ መጠጣችን አምላካችን መወለዱን ፤ ስንለብስ ስናጌጥም እውነተኛ ልብሳችን ክርሰቶስ መወለዱን ልናስብ ይገባናል።ይህ ካልሆነ ግን ጌታ ለእኛ ያደረገውን ውለታ የዘነጋን ውለተ ቢሶች እንሆናለን።
በዓሉን በዓል የሚያደርገውም የጌታን የፈቃድ ተዋርዶውንና ውለታውን እያሰብን ካመሰገንን ብቻ ነው ፤ እንጂ የምግብና መጠጡ ጉዳይ አይደለም።ይህን #የጌታችን ውለታ ከሚያረሳሱ የቴሌቪዥን መርኃግብሮችን ሁሉ ልንጠነቀቅም ይገባናል!!!

#በዓለ #ልደቱን በተዘክሮ እግዚአብሔር እንድናከብር አምላካችን ቅዱስ እግዚአብሔር ይርዳን!!!

#በጎል ሰከበ በአጽርቅት ተጠብለለ
#ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ!!!

ልደተ #እግዚእ / 2017 ዓ.ም
#ዛሬ #እግዚአብሔር “ኑ፥ እንውረድ፤ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው።” (ዘፍ 11፥7) ብሎ ለራሱ በብዙ ቁጥር ተናግሮ ሦስትነቱን ገልጧል።ስለዚህም ቅድስት #ሥላሴ ብለን እናከብራለን።ቅድስት #ሥላሴ ማለትም ልዩ ሦስትነት ማለት ነው።

#እግዚአብሔር ያንጻል #እግዚአብሔር ያፈርሳል

#“በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።”( ዘፍ1፥1) በሚለው ቃል የእግዚአብሔርን አናፂነቱን ተረዳን ፤“እግዚአብሔርም ከዚያ በምድር ሁሉ ላይ በተናቸው፤ ከተማይቱንም መሥራት ተው።"ዘፍ 11፥8) በሚለው ቃልም የእግዚአብሔር አፍራሽነቱን ዐወቅን።የሰናዖርን ግንብ የገነቡ ሰዎች ዓላማቸው እግዚአብሔርን ከንግሥና ዙፋኑ አውርዶ ለመንገሥ ነበር።

#እነዚህም ቅዱስ #ዳዊት"የምድር ነገሥታት ተነሡ፥ አለቆችም በእግዚአብሔርና በመሢሑ ላይ እንዲህ ሲሉ ተማከሩ። ማሰርያቸውን እንበጥስ፥ ገመዳቸውንም ከእኛ እንጣል። በሰማይ የሚኖር እርሱ ይሥቃል፥ ጌታም ይሣለቅባቸዋል። በዚያን ጊዜ በቍጣው ይናገራቸዋል፥ በመዓቱም ያውካቸዋል።"(መዝ 2:2-5) ብሎ የተናገረላቸው ዓይነት ሰዎች ናቸው።ዓላማቸውም #የእግዚአብሔር አምላክነቱን (ገዢነቱን) ከላያቸው ላይ መጣል ነው።ነገሩ ግን አስቂኝ ነው።ሰው የማይሆንለትን ነገር ሲሞክር ቂልነቱ ያስቃል።

#የሰው ፍላጎት በአጭሩ #እግዚአብሔርን መሆን ነው።የአዳም ምኞት ፣ የባቢሎን ሰዎች ፍላጎት፣ የአላውያን ነገሥታት ጉጉት ፣ አሁን ያለን ሰዎች ፍላጎትም አምላክ መሆን ነው።አምላክ የመሆን ፍላጎታችን ማሳያዎችም አሉ።መውሰድ #የእግዚአብሔር ነው እኛ እንሰርቃለን ፤ መግደል #የእግዚአብሔር ነው እኛ እንገድላለን ፤ መፍረድ #የእግዚአብሔር ነው እኛ እንፈርዳለን።

#ቅድስት #ሥላሴ በዛሬው ዕለት የባቢሎንን ግንብ እንዳፈረሰ የእኛንም የትዕቢትና የኃጢአት ግንብ በቸርነቱ አፍርሶ ፤ ሰውነታችንን ለእርሱ ማደሪያነት ያንጽልን።

#ጥር #ሥላሴ / 2017 ዓ.ም
ኢዮብ ክንፈ
#ዛሬ የኪዳናት ሁሉ ፍጻሜ #ኪዳነ #ምሕረት ናት።ለቅዱሳኑ ለአዳም፣ለኖኅ፣ለመልከጼዲቅ፣ለአብር
ሃም፣ለዳዊት የተገባው ቃልኪዳን ሁሉ በእግዝእትነ ድንግል ማርያም ፍጻሜውን አገኘ።ይህ ኪዳነ እግዚአብሔር ምንድነው? ቢሉ የእግዚአብሔር ወልድ ሰው መሆን ነው።ሰው ሆኖም መዳናችንን መፈጸም ነው።

#ቅዱስ ዳዊት “ማዳን የእግዚአብሔር ነው፥ በረከትህም በሕዝብህ ላይ ነው።” መዝ 3፥8
ብሎ እንደተናገረው ሰውን ከተፈረደበት የሞት ፍርድ ማዳን የሚቻለው የፈረደበት እግዚአብሔር ነው።

#“ጽድቅንና ፍርድን ይወድዳል፤ የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች።”(መዝ 33፥5) በሚለው ቃልም ምን እግዚአብሔር ሰውን ማዳን(ጽድቅ) ቢችልም ፍርድንም ይወድዳል።ሰውን በቸርነቱ የማዳን ፈቃዱ ጽድቅ ሲሆን፤የበደለ ሰው ነውና ሊክስ የሚገባውም ሰው ነው፦ይህ ፍርድ ይባላል።
ሰው ደግሞ ራሱ የሞት ፍርድ ስላለበት ሰውን ማዳን የማይቻለው ነው።ታዲያ ምን ተሻለ? የሞት ፍርድ የሌለበት፤የባሕርይ ጉስቁልና (fallen nature)፤መርገመ አዳም መርገመ ሔዋን ያላገኘው ንጹሕና ቅዱስ ሰው ነዋ !!! ይህንን ነቢዩ ኢሳይያስ
“የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፥ እንደ ሰዶም በሆንነ እንደ ገሞራም በመሰልነ ነበር።”
(ኢሳ1፥9) በማለት የገለጸው ከላይ ካነሣናቸው ጉዳዮች የቀረች ንጹሕ ዘር ታስፈልግ ነበር።ከዚህች ንጹሕ ዘር ነው ራሱ እግዚአብሔር የነሣውን ሥጋዋን ነፍሷን ተዋሕዶ የሚያድነን።

#ይህቺ አዳምና ሔዋን በበደሉት በደል ከመጣው ጣጣ ሁሉ ከአዳም ልጆች በተለየ መልኩ ያስቀራት ዘር እመቤታችን ናት።ልብ በሉ "ዘርን ባያስቀርልን" አለ እንጂ "ዘሮችን" አላለም።ዘርዪቱ አንዲት ናት።ልዩ ናት!!!አትደገምም፤አትነገርም።ይህቺ ሰዎች ሁሉ ላይ ከመጣው የሞት ዕዳ የቀረች (የተረፈች) ዘር እመቤታችን ለመሆኗ ሰማያውያን መላእክትን ምድራውያን ጻድቃንን ምስክር እናቆማለን።“እግዚአብሔር ተናግሮአልና ሰማያት ስሙ፥ ምድርም አድምጪ።”(ኢሳ 1፥2)

1.“በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ።”
(ዘፍ 3፥15) የሰማዮች ሰማይ እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ነው።ይህቺ ከእባቡ (ከሰይጣን) ጋር ጠላትነት ውስጥ የምትገባ ዘር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት።ሔዋን ከመሰለችህ ተሳስተሃል።ስለ እርሷማ ቅዱስ ኤፍሬም "ከይሲ ዲያቢሎስ ያሳታት ሔዋንን እግዚአብሔር ምጥሽንና ፃዕርሽን አበዛዋለሁ ብሎ ፈረደባት"ብሎ ተናገረ ።በምክረ ሰይጣን የተስማማ ሰው ከሰይጣን ጋር ጠላትነት ውስጥ ሊገባም አይችልም።ይህ የእመቤታችንና የሰይጣን ጠላትነት “ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ”
(ራእይ 12፥17) ተብሎ ተጽፎለታል።ዘንዶው ማንነው? ካልክ “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።”(ራእይ 12፥9) በማለት የቀደመው እባብ (ሰይጣን) መሆኑን ቅዱስ ዮሐንስ ይነግርሃል።ሴቲቱስ?“ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች።”ራእይ 12፥1
የተባላለት ድንግል ማርያም ናት።በዘፍጥረት በሴቲቱና በእባቡ ጠላትነት እንደሚደረግ እግዚአብሔር ነገረን።ቅዱስ ዮሐንስ ይህን ጠላትነት በተግባራዊ መልኩ በራእዩ አስረዳን።

2. “ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ።”(መዝ 45፥4) ልዑል እግዚአብሔር ማደሪያውን ለየ፤አመሰገነ፤አከበረ።
ቅዱስ እግዚአብሔር ማደሪያው የምትሆን ድንግል ማርያምን ከመርገመ አዳም ከመርገመ ሔዋን ጠበቀ ፤ በመጠበቁም አከበረ።

3.“ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፥ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ።”ሉቃ1፥27
ቅዱስ ገብርኤል የተላከው "ከደናግል ወደ አንዲቱ" አይደለም፤ወደ "አንዲት ድንግል" እንጂ!!!በሥጋ ደናግል የሆኑ ሴቶች ሊኖሩ ይችላሉ።እነዚህ ግን እንደ ማንኛውም የሰው ዘር መርገመ አዳም ወሔዋን ደርሶባቸዋል።እመቤታችን ግን ከዚህ ሁሉ ንጽሕት ናትና "አንዲት ድንግል" አላት።"አንዲት ድንግል" ማለትም "ብቸኛዪቱ ድንግል" ማለት ነው።ይህ ዓይነቱ ድንግልና ነው "የድንግልናሽ ምስጋናና ክብር ታላቅ ነው" ተብሎ የተመሰገነ።

4. “መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ፦ ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት።”(ሉቃ 1፥28)
ሰው ሁሉ ኃዘን አግኝቶት "ደስ ይበልሽ" የተባለች፤ሰው ሁሉ ከጸጋ እግዚአብሔር ጎድሎ "ጸጋ የሞላብሽ ሆይ" ተብላ የተመሰገነች፤በበደል በደሉንም ተከትሎ በደረሰብን መርገም ከእግዚአብሔር ተለይተን በነበርን ጊዜ መርገምም ሆነ በደል ካላገኛት ከእመቤታችን ጋር ጌታ እግዚአብሔር ነበር።ከሌሎች ሴቶች መካከል የተባረከች ናት እመቤታችን።መባረክ የመረገም ተቃራኒ መሆኑ ግልጥ ነው።ሌሎች ሴቶች ላይ “በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፥ እርሱም ገዥሽ ይሆናል።” (ዘፍ 3፥16) የተባለው መርገም ሲደርስባቸው በእመቤታችን ግን ይህ ሁሉ የለባትም።

#በእውኑ #የእመቤታችን ሥጋ የወደቀው የአዳም ሥጋ እንዳልሆነ፤አዳም ሳይበድል የነበረው ሥጋ እንደሆነ ዐወቅን ተረዳን!!!ይህንን የገለጠልን ለእመቤታችን የምሕረት ቃል ኪዳን የሰጠ ቅዱስ እግዚአብሔር ስሙ ይክበር ይመስገን!!!

#የካቲት #ኪዳነ #ምሕረት /2017 ዓ.ም

#ኢዮብ ክንፈ
ወንድም እህቶቼ መንፈሳዊ አገልግሎት ለሁላችን ጠቃሚ ነውና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ወንድም እህቶቼ ሁላችሁ ይህንን ዝማሬዎቼን የምለጥፍበትን የዩትዩብ ገጼን በመቀላቀልና በመከታተል ሌሎች እንዲቀላቀሉኝ በማድረግና በማስደረግ ለአገልግሎቱ ኀይል ይሁኑኝ ድጋፍ ያድርጉልኝ እግዚአብሔር ያክብርልኝ!🙏🙏🙏

https://youtube.com/@zemaridawitkibru2405?si=XABE7A5j_OybqfK5

#subscribe
#share
#like
#forfriends
#forfamily

@zdk24_5_21_official
መኑ ውእቱ ገብር ኄር ወምእመን ዘይረክቦ እግዚኦ በምግባረ ሠናይ ወይሰይሞ ዲበኲሉ"


"ጌታው በበጎ ሥራ የሚያገኘውና በገንዘቡ ሁሉ ላይ የሚሾመው ቸርና ታማኝ አገልጋይ ማነው ?"
ማቴ ፳፭ ÷ ፲፬-፴፩

እህት ወንድሞቼ እግዚአብሔር ቢፈቅድ በዕለተ ቅዳሜ በገብር ኄር ዋዜማ ለሳምንቱ በሚስማማ ዝማሬ ስለምንገናኝ እንዲጠብቁኝ ስንል በእግዚአብሔር ስም እጠይቃለው !

     "በጥቂት ልታመን"
       ዘማሪ ዳዊት ክብሩ

             ግጥም
       ዘማሪ ዳዊት ክብሩ

                ዜማ
       ዘማሪ ዲ/ን ዘላለም ታከለ

       ድምጽ  ቀረጻና ማስተሪንግ
              ዘጎላ ሬከርድስ


እስከምንገናኝ ቻናሉን  ሰብስክራይብ በማድረግና በማስደረግ ያግዙኝ !🙏
            👇👇👇
https://youtube.com/@zemaridawitkibru2405?si=XABE7A5j_OybqfK5
#​​በግብረ ሕማማት ውስጥ የሚገኙ እንግዳ ቃላት እና ትርጉማቸው ፡-

በግብረ ሕማማት ውስጥ ወደ ግዕዝም ሆነ በኋላ ወደ አማርኛ ሳይተረጎሙ የተቀመጡ የዕብራይስጥ፣ የቅብጥ እና የግሪክ ቃላት ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ ቃላት ትርጉም የሚከተለው ነው፡፡

#ኪርያላይሶን
ቃሉ የግሪክ ሲሆን አጠራሩ «ኪርዬ ኤሌይሶን»ነው፡፡ «ኪርያ» ማለት «እግዝእትነ» ማለት ሲሆን «ኪርዬ» ማለት ደግሞ «እግዚኦ» ማለት ነው፡፡ ሲጠራም «ኪርዬ ኤሌይሶን» መባል አለበት፡፡ ትርጉሙ «አቤቱ ማረን» ማለት ነው፡፡ «ኪርያላይሶን» የምንለው በተለምዶ ነው፡፡ ይኼውም ኪርዬ ከሚለው «ዬ» ኤላይሶን ከሚለው ደግሞ«ኤ» በመሳሳባቸው በአማርኛ «ያ»ን ፈጥረው ነው፡፡

#ናይናን
የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙ «መሐረነ፣ ማረን» ማለት ነው፡፡

#እብኖዲ
የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙ «አምላክ» ማለት ነው፡፡ «እብኖዲ ናይናን» ሲልም «አምላክ ሆይ ማረን» ማለቱ ነው

#ታኦስ
የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙ «ጌታ፣ አምላክ» ማለት ነው፡፡ «ታኦስ ናይናን» ማለትም «ጌታ ሆይ ማረን» ማለት ነው፡፡

#ማስያስ
የዕብራይስጥ ቃል ሲሆነ ትርጉሙ «መሲሕ» ማለት ነው፡፡ «ማስያስ ናይናን» ሲልም «መሲሕ ሆይ ማረን» ማለት ነው

#ትስቡጣ
«ዴስፓታ» ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም ደግ ገዥ ማለት ነው

አምነስቲቲ ሙኪርያቱ አንቲ ፋሲልያሱ፦
የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙም «ተዘከረነ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ- አቤቱ በመንግሥትህ አስበኝ» ማለት ነው፡፡

አምንስቲቲ ሙዓግያ አንቲ ፋሲልያሱ፦
የቅብጥ ቃል ሲሆን «ተዘከረነ ኦ ቅዱስ በውስተ መንግሥትከ -ቅዱስ ሆይ በመንግሥትህ አስበን» ማለት ነው፡፡

#አምንስቲቲ ሙዳሱጣ አንቲ ፋሲልያሱ፦
የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙም «ተዘከረነ እግዚአ ኩሉ በውስተ መንግሥትከ- የሁሉ የበላይ የሆንክ ወይ በመንግሥትህ አስበን» ማለት ነው፡፡

እንበለ ደዌ ወሕማም እንበለ ጻማ ወድካም ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ ለብርሃነ ትንሳኤሁ እግዚአብሔር በፍስሐ ወበሰላም።
++ ለክርስቶስ ልደት መንገድ የጠረገ ልደት ++

እንኳን አደረሳችሁ!!

☞ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ ጥንተ አብሶ ካመጣው ፍዳና መርገም ጠብቋታል:: የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ዓለም በጥንተ አብሶ በነበረበት ዘመን በክርስቶስ ማዳን ዋዜማ ሲያበሥራት፤ ቅድስት ኤልሳቤትም በፅንሰቷ ጊዜ ስታመሰግናት ደጋግመው "ጸጋን የሞላብሽ ሆይ" "አንቺ ከሴቶች መካከል ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ።" እያሉ ይህን እውነት መስክረዋል። (ሉቃ፩:፳፮-፵)

☞ በጥንተ አብሶና ውጤቱ (origional sin and its effects) ምክንያት ሰዎች "የእግዚአብሔር ክብር ጎድሏቸዋል በተባሉበት ዘመን ጸጋን የተመላች ብቸኛ ልዩ እርሷ ነበረች::" (ሮሜ ፫:፳፫) እግዚአብሔር እርሷ የዓለም መድኃኒት ክርስቶስን ለመውለድ ፈቃደኛ እንደምትሆን ስለሚያውቅ አስቀድሞ በአካል የሚመስለው በባሕርይ ከእርሱ ጋር አንድ የሆነ አንድያ ልጁን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንድትወልድ ቅድመ ዓለም መርጧታልና የእመቤታችን ልደት (ልደታ ለማርያም) የዓለም መዳን የማይቀር መሆኑ ለታወቀበት ለጌታችን ለአምላካችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ልደት መንገድ የጠረገ ልደት ነው እንላለን። (The nativity of the blessed virgin Mary prepares the way for the birth of Jesus Christ) እንዳለ ሊቁ። (The book of the nativity of Virgin Mary)

☞ የጌታችን ሰው መሆን "ከዘላለምና (ቅድመ ዓለም) ከትውልዶች ጀምሮ (ከፍጥረተ ዓለም ጀምሮ) ተሰውሮ የነበረ ምሥጢር ነው።" መባሉም የአምላክ ሰው መሆን እንዲሁም የእርሷ እርሱን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና መውለድ ዓለም ሳይፈጠር በአምላክ ሕሊና የሚታወቅ መሆኑን ያስረዳናል። (ቆላ፩:፳፮፣ኢሳ ፯:፲፬ ፱:፮)

☞ እርሱ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የነገሥታት ንጉሥ፣ የጌቶች ጌታ፣ የአማልክት አምላክ ነው። (መዝ ፻፴፭:፩ ራእ፲፱:፲፮)

☞ እርሱ ፍጥረትን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ ፈጣሪ ነው:: "ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳች ያለ እርሱ አልሆነም።" (ዮሐ ፩:፫)፤ "መልካሙን ነገር ለማድረግ በክርስቶስ ተፈጠርን።"፤ "የሚታዩትና የማይታዩትም ዙፋናት ቢሁኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና።" እንደተባለ:: (ቆላ ፩:፲፭-፲፮፣ ኤፌ ፪:፲)

☞ እርሱ ለቅዱሳን የጸጋ አምላክነትን ክብር የሰጠ ሁሉን ፈጥሮ የሚገዛ የባሕርይ አምላክ ነው:: (ዘጸ ፯:፩፣ መዝ ፹፩:፩፣ ዮሐ፲÷፴፬፣ ሮሜ ፱:፭፣ ፩ተሰ ፫:፲፩፣ ቲቶ ፪:፲፩፣ ፩ዮሐ ፭:፳)

☞ እርሱ ቸር ከሆነ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በአገዛዝ በሥልጣን በሕልውና በመለኮት አንድ ነው:: (ዮሐ ፲:፴፣ ፲፯:፲፣ ማቴ ፲፩:፳፯-፳፱፣ ዮሐ ፲፬:፮-፰)

☞ እርሱ ፀሐይ እናቱ ምሥራቅ ናት:: (ሕዝ ፵፬:፩፣ ዮሐ ፰:፲፪፣ ሚል ፬:፪) ምሥራቅ እናቱን ዘወትር መሻታችን የፀሐይ ክርስቶስን በረከት ፍቅርና ቸርነት ለማግኘት ነው:: እንኳንስ እናቱን ነቢዩ ዳዊት ስለ ወዳጆቹ "ምስክሮችህ ድንቆች ናቸው ስለዚህም ነፍሴ ፈለገቻቸው።" ብሎ ዘምሯል:: (መዝ ፻፲፰:፻፳፭)

☞ እርሱ የባሕርይ አምላክ እርሷ ደግሞ ወላዲተ አምላክ ( Theotokos) ናት:: ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ከተፈጠረም በኋላ መቸም መች አምላክን "ልጄ ወዳጄ" ማለት ከቶ ለማን ተችሏል? እርሱ ፈጣሪ እርሷ ደግሞ ወላዲተ ፈጣሪ ኩሉ ዓለም ናት::

☞ እርሱ እውነተኛ ደስታ እርሷ የደስታ መፍሰሻ ናት። (መዝ ፵፭:፭)

☞ እርሱ ሕይወት እርሷ ነቅዐ ሕይወት (የሕይወት ምንጭ) ናት። ይህች ብርሃን ሙዳየ መድኃኒት ቤዛዊተ ኩሉ ብርሃንን ትሰጠን ሕይወት ክርስቶስን ትወልድልን ዘንድ ከተቀደሱ ተራሮች ከአብርሃም ከዳዊት ቤት ተወለደች። (መዝ ፹፰(፹፱):፩)

+++ የልደቷ ቀን +++

አንተ የራስህን እንዲሁም የምትወዳቸውን ሰዎች ልደት ሻማ አብርተህ፣ ኬክ አስጋግረህ፣ ወዳጅ ዘመዶችህን ጠርተህ፣ በዳንስ በጭፈራና እስክስታ በመውረግረግ ታከብራለህ የአምላክ እናት ድንግል ማርያም የተወለደችበትን ቀን በማሰብ በዓለ ልደቷን የሚያከብሩ ሰዎችን ግን ለምን ያከብራሉ? ብለህ ትተቻለህ::

የእናቱን ልደት እርሱን እያመሰገንን፣ እያወደስን እናቱ "ትውልድ ሁሉ ያመሰግኑኛል።" (ሉቃ ፩:፵፱) እንዳለችም እርሷንም እያመሰገንን "ብርቱ የሆን እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጓልና።" ብላ እንደመሠከረችም በእርሷ ለሰው ዘር የተደረገውን ታላቅ ሥራ እያሰብን ብናከብር የሚያዝንብን ይመስላሃልን? ከማዳኑስ በላይ ምን ታላቅ ሥራ አለ? ዓለም:- የኤድስ ቀን፣ የጉበት ቀን፣ የኩላሊት ቀን፣ የላብ አደር ቀን፣ የውሃ ቀን፣ የአፈር ቀን፣ የእናቶች ቀን፣ የአባቶች ቀን እያለ በልዩ ልዩ መንገድ ሲያከብር ቅር አይለውም የእናቱ የእመቤታችንን ልደት ለማክበር ግን ያመዋል::
ልደታ ለማርያምን ስናከብር

☞ ቤተ ክርስቲያንን በሚያስነቅፍ አብዝቶ በመብላትና በመጠጣት በዳንኪራና በአስረሽ ምስናከብር
ሆን በመንፈሳዊ ሥርዓት እናክብረው ያኔ የልጇ በረከት እጥፍ ድርብ ይሆንልናል። (ምሳ ፲:፯፣ ፩ጴጥ ፪:፲፪)

☞ የቤተክርስቲያን ባልሆነ የልደቷን ነገር በማይገልጥ በማይወክል መንገድ በአምልኮ ባዕድ፣ በየዛፉ ዙርያ አረቄና ቡና በማፍሰስ የሚያከብሩትን ሰዎች በማስተማርና ትክክለኛውንና የክርስትናውን መንገድ በተከተለ መንገድ እንዲያከብሩት በማድረግ ድርሻችንን በመወጣት እናክብር ::

☞ ልደቷ "በመወለዱ ብዙዎች ደስ ይላቸዋል።" ከተባለለት ከዮሐንስ ልደት የሚልቅ መሆኑን እንወቅ። እርሷ የዮሐንስ ፈጣሪ የክርስቶስ እናቱ ናትና። ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም " ድንግል ፈጣሪዋን ወለደችው እርሱም እናቱን ፈጠረ።" እንዳለ:: እርሱ ክርስቶስ "ሁሉን በስሜ አድርጉት" እንዳለን እርሷን በእርሱ ስም ወላዲተ አምላክ እመ ብርሃን ብለን ተቀብለን ልደቷን እንደምናከብር እንረዳ:: (ሉቃ ፩:፲፬)

+++ አድባር +++

አድባር የሚለው ቃል የግእዝ ሲሆን ትርጉሙም ተራሮች ማለት ነው:: እመቤታችን በሊባኖስ ተራሮች መሐል ተወልዳለችና የልደቷን ወቅት አድባር እንላለን። (መኃ ፬:፰)

🚹የእናቱን በዓለ ልደት ማክበር ማኅበራዊ ፋይዳ 🚹

በዚህ ቀን የአንድ ቀዬ ሰዎች በአንድነት ተሰብስበው ጸሎት በማድረግ እግዚአብሔርን በማመስገን እናቱንም በማወደስ ማክበራቸው ከሃይማኖታዊው ፋይዳ ባለፈ በልዩ ልዩ ምክንያት እየደበዘዘና እንደ ዳይኖሰርና ዶዶ ድራሹ እየጠፋ የመጣውን አብሮነት ማኅበራዊ ትስስር የሚያጠነክር መልካም ባሕላችንም ጭምር ነውና አጥብቀን ልንይዘው ይገባናል:: የድንግል ልጅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ የልደት ቀን በረከት ያሳትፈን!!!

ቢትወደድ ወርቁ
ሚያዝያ ፴ ቀን ፳፲፯ ዓ ም
የዘማሪ ዳዊት ክብሩ Zemari Dawit Kibru Official Telegram Channel
Photo
“ስለ እናንተ ሲያማልዱ፥ በእናንተ ላይ ከሚሆነው ከሚበልጠው ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣ ይናፍቁአችኋል።” (ቅዱስ ጳውሎስ 2ኛ ቆሮ 9፥14)
--------------------------------

☞ ጻድቃን "አያማልዱም" የሚለውን ክርክር ተወውና የዘፍጥረትን መጽሐፍ ገልጠህ ፈጣሪህን ጠይቅ። ደጋጎች አይደለም ማልደው ለጥፋት በተዘጋጀች ከተማ ቢኖሩ እንኳን በከተማይቱ ስለመኖራቸው ብሎ ምሕረትን ያወርዳል።

እግዚአብሔር ሰዶምና ገሞራን በኃጢአታቸው ምክንያት በእሳትና በዲን አቃጥሎ ከመቅጣቱ አስቀድሞ ለወዳጁ ለአብርሃም "እኔ የማደርገውን ከአብርሃም እሰውራለሁን? አብርሃም በእውነት ታላቅና ብርቱ ሕዝብ ይሆናልና፥ የምድር አሕዛብም ሁሉ በእርሱ ይባረካሉና። ጽድቅንና ፍርድን በማድረግ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከእርሱ በኋላ ቤቱን እንዲያዝዝ አውቃለሁና፤ ይህም እግዚአብሔር በአብርሃም ላይ የተናገረውን ነገር ሁሉ ያመጣ ዘንድ ነው።" ካለ በኋላ "የሰዶምና የገሞራ ጩኸት እጅግ በዝቶአልና፥ ኃጢአታቸውም እጅግ ከብዳለችና፥ እንግዲህስ ወደ እኔ እንደ መጣች እንደ ጩኸትዋ አድርገው እንደ ሆነ ወርጄ አያለሁ፤ እንዲሁም ባይሆን አውቃለሁ።" በማለት ነገረው። ይህ ነገር በእግዚአብሔር የተነገረው አብርሃም ደጋግሞ ምን ብሎ እንደጸለየ ታስተውላለህን? "አምሳ ጻድቃን በከተማይቱ ውስጥ ቢገኙ በውኑ ሁሉን ታጠፋለህን? ከተማይቱንስ በእርስዋ ስለሚገኙ አምሳ ጻድቃን አትምርምን?"….... ዳግመኛም "ከአምሳው ጻድቃን አምስት ቢጐድሉ ከተማይቱን ሁሉ በአምስቱ ምክንያት ታጠፋለህን? "… ሦስተኛም "ጌታዬ አይቆጣ እኔም እናገራለሁ፤ ምናልባት ከዚያ ሠላሳ ቢገኙሳ?… አራተኛም፦ "እኔ ደግሞ አንድ ጊዜ ብቻ ብናገር ጌታዬ አይቆጣ፤ ምናልባት ከዚያ አሥር ቢገኙሳ?" አለ።" ቅዱሱ ሰው አብርሃም በመጨረሻ የጸለየውን ጸሎት ልብ በል "በእነዚህ በሁለት ታላላቅ ከተሞች አሥር ጻድቃንን ብታገኝ አትምርምን?" የሚል ነው። እግዚአብሔር ምን ብሎ የመለሰ ይመስልሃል? "አምሳ ሳይሆን አሥርም ጻድቃን ባገኝ እምራለሁ!!!" (ዘፍ 18:17-25)

☞ እስቲ ልጠይቅህ ዛሬ ግብረ ሰዶማዊነት የት ደርሶዋል? በደጅህ አልደረሰምን? ለቀደሙት ስለገባው ቃልኪዳን ታግሦዋል እንጂ ሰዶማውያኑ በጠፉበት ግብረ ሰዶም ዓለሙ ይጠፋ እንደነበር የታወቀ ነው። ጠቢቡ ሰሎሞን “ጻድቃን በበዙ ጊዜ ሕዝብ ደስ ይለዋል።” (ምሳ 29፥2) ብሎ ለምን ተናገረ? በጻድቃን ብዛት ሀገር እንደምትድን በተረዳ ነገር ስላወቀ አይደለምን?

☞ የጻድቃን ልመና ብቻ ሳይሆን መኖር እንኳን ከጥፋት ይታደግሃል። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ።” ብሎ በምሥጢረ ምጽዓት ትምህርቱ እንዳስተማረ። (ማቴ 24፥22) እግዚአብሔር ለወዳጆቹ በሚገባው ቃልኪዳን ቁጣውን በምሕረት በትእግሥት እንደሚለውጥ መከራውን እንደሚያሳጥር ይህ የጌታ ቃል ምስክር ነው። ዓለም አልገባውም እንጂ ሐሳዊ መሲሕ የሚሠለጥንባቸው እነዚያ አስጨናቂ ወራት እንኳን የሚያጥሩት በጽኑ እምነታቸው በቀና ምግባራቸው እርሱን ላስደሰቱት ወዳጆቹ በገባው ቃልኪዳን ነው።

መድኅን ዓለም ክርስቶስ ሕያዋን ቅዱሳኑን "ሙታን" ለሚሉ ሰዱቃውያን “እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም።” ብሎ የተናገረውን ቃል ልብ በልና ሙታን እንደሌሉን አውቀህ ወደ ሕይወት የተሻገሩበትን የዕረፍታቸውን ቀን እንደ ዳዊት “የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።” (መዝ116፥15) እያልክ እየዘመርክ አክብር። (ማቴ 22፥31-32)

እባክዎን ቃለ እግዚአብሔርን በማጋራት ለወዳጆችዎ ያድርሱ።

ቢትወደድ ወርቁ
ሠኔ 24 ቀን 2017 ዓ ም
(ሥዕለ ተክለ ሃይማኖት በ Coptic ቤተ ክርስቲያን ሠዐሊ ዐይን)
በዚህ ዕለት ሐምሌ 7 ቀን #ቅድስት_ሥላሴ በአብርሃም ቤት የገቡበት እና ሣራ ይስሐቅን እንደምትወልድ የተናገረበት ዕለት ነው፡፡

ዳግመኛም በዚህ ዕለት ልደቱ እና ዕረፍቱ በአንድ ቀን የገጠመለት የእመቤታችን ወዳጅ ፣ ኢትዮጲያዊው ቄርሎስ የተባለ የሃይማኖት ጠበቃ ፣ ቅዱስ እና ሊቅ #አባ_ጊዮርግስ_ዘጋስጫ ዓመታዊ ክብረ በዓል ነው።

#ቅድስት_ሥላሴ

አባታችን አብርሃም ከተመሳቀለ ጐዳና ላይ ድንኳን ሠርቶ መንገደኞችን ዅሉ በእንግድነት እየተቀበለ ሲያስተናግድ ይኖር ነበር፡፡ ጥንተ ጠላታችን ሰይጣን ለተንኮል አያርፍምና ይህንን መልካም ግብሩን ለማሰናክል አሰበ፡፡ አስቦም አልቀረ፤ የተጐዳ ሰው መስሎ ከጐዳና ቆሞ አብርሃም እንግዳ መቀበል እንደ ተወ፤ እርሱ ሊበላ ሊጠጣ ከቤቱ ቢሔድ ራሱን ፈንክቶ፣ ደሙን አፍሶ፣ አጥንቱን ከስክሶ፣ ልብሱን ገፎ እንደ መለሰው ወደ አብርሃም ቤት ለሚሔዱ ሰዎች ይናገር ጀመር፡፡ በዚህ የተነሣም እንግዳ ወደ አብርሃም ቤት አልመጣ አለ፡፡ በዚህ ጊዜ አብርሃምም ማዕደ እግዚአብሔርን ያለ ምስክር (ያለ እንግዳ) አልመገብም ብሎ ሦስት ቀን ሳይመገብ ጾሙን አደረ፡፡ በሦስተኛው ቀን ይህን ደግነቱን እግዚአብሔር ተመልክቶ በሦስት ሰዎች አምሳል አንድም በሥላሴው (በሦስትነቱ) ከአብርሃም ቤት ገብቷል (ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ፣ 4 ፥32 )፡፡

በኦሪት ዘፍጥረት 18 ፥ 1 -19 ተጽፎ እንደምናገኘው በቀትር ጊዜ አብርሃም በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በሦስት ሰዎች አምሳል በመምሬ አድባር ዛፍ ተገልጦለታል፡፡ አብርሃምም ሦስት ሰዎች ቆመው ባየ ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ወደ እነርሱ ሮጠ፡፡ ወደ ምድርም ሰገደና ‹‹አቤቱ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ኾነ ባርያህን አትለፈኝ?›› ብሎ ተማጸነ፡፡ በመቀጠል አብርሃም ‹‹ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ፤ እግራችሁን ታጠቡ፤ ከዚህችም ዛፍ በታች ዕረፉ፡፡ ቍራሽ እንጀራም ላምጣላችሁ፤ ልባችሁንም ደግፉ፡፡ ከዚያም በኋላ ትሔዳላችሁ፡፡ ስለዚህ ወደ ባርያችሁ መጥታችኋልና›› ሲላቸው እነርሱም ‹‹እንዳልህ አድርግ›› ብለውታል፡፡

ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ጠርቶ ‹‹ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?›› አለው፡፡ አብርሃምም ከድንኳኑ ውስጥ እንዳለች ነገረው፡፡ እግዚአብሔርም ‹‹የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች›› ብሎ ለአብርሃም አበሠረው፡፡ ሣራ ይህንን ቃል በሰማች ጊዜ ባለቤቷም አርጅቶ፤ እርሷም የሴቶች ግዳጅ ትቷት ነበርና ‹‹‹ሲያረጁ አምባር ይዋጁ› እንዲሉ ‹‹እስከ ዛሬ ድረስ ቆንጆ ነኝን? ጌታዬ አብርሃምስ ገና ጐረምሳ ነውን?›› ብላ በማሰቧና መውለዷን በመጠራጠሯ ሳቀች፡፡ እግዚአብሔርም ምሥጢሩን በአጽንዖት ለማስረዳትና አስረግጦ ለመንገር አብርሃምን ‹‹ሣራ ለምን ትስቃለች? በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?›› አለው፡፡ ሣራም ስለፈራች ‹‹አልሳቅሁም›› አለች፡፡ እግዚአብሔርም መሳቋን እንዳወቀባት ከነገራት በኋላ በድጋሜ በዓመቱ ወደ አብርሃም ቤት እንደሚመጣና ሣራ ወንድ ልጅ (ይስሐቅን) እንደምትወልድ አብሥሯቸዋል፡፡

የቅድስት ሥላሴ ረድኤታቸው አይየን!
የቅዱስ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ አማላጅነቱ አትለየን ። ሀገራችንን ቅድስት ኢትዮጺያን ሊለያይ የሚሽቀዳደመውን ዲያብሎስን በመስቀሉ ይምታልን።

©️ ዮቶር ደሳለኝ
#መልካም_በዓል
#ጸልዩ_በእንተ_ቤተክርስቲያን_ቅድስት@zdk24_5_21_official