አትሮኖስ
281K subscribers
111 photos
3 videos
41 files
481 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#ሮሚዮና_ዡልየት

እስቲ #በትያትር ደግሞ ዘና በሉ

#ክፍል_አንድ

ካፑሌና ፡ ሞንታግ ፡ ሁለት ፡ ባላባቶች ፡
ሆነው ፡ የሚኖሩ፡ ሁል ፡ ጊዜ ፡ ጠላቶች ፡
የእነሱም ፡ ወገኖች ፡ ባገረ ፡ ቬሮና ፡
ድንገት ፡ ሲገናኙ ፡ ሲያልፉ ፡ በጐዳና ፡
ጠብ ፡ እያበቀሉ ፡ በተንኰል ፡ በዘዴ ፡
ይተላለቃሉ ፡ በሰይፍ ፡ በጐራዴ ።
ሮሜዎና ዡልዬት ፡ ሁለት ፡ ልጆቻቸው ፡
በጣም ፡ ተዋደዱ ፡ ፍቅር ፡ አድሮባቸው፡
ግን ፡ አባቶቻቸው ፡ በነሱ ፡ መካከል ፡
ብርቱ ፡ ስለ ፡ ሆነ ፡ የነበረው ፡ በቀል ፡
ዕርቅን ፡ እንቢ ፡ ብለው ፡ ከቂም ፡ ስላልወጡ ፡በእነሱ ፡ ኀጢአት ፡ ልጆቹ ፡ ተቀጡ ።
ሆኖ ፡ የተገኘ ፡ ባገረ ፡ ቬሮና፡
እጅግ ፡ የሚያሳዝን ፡ የሚያስለቅስ ፡ ዜና ፡
አንባቢ፡ ተመልከት ፥ እንግዲህ፡ አስተውለው፤የምናቀርብልህ ፡ ታሪኩ ፡ ይኸ ፡ ነው ።
፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡
#በቤሮና_ከተማ_አውራ_መንገድ_ላይ

#ሶምሶንና#ጎርጎርዮስ

#ሶምሶን
ዛሬ ፡ ሣር ፡ ቅጠሉ ፡ ዐፈርና ፡ ሙጃ ፡
ደም ፡ ደም ፡ ይሸተኛል ፡ ምክንያቱን ፡ እንጃ ።

#ጎርጎርዮስ
የሞንታግ ፡ ወገኖች ፡ ሸተውህ ፡ ይሆናል

#ሶምሶን
የነሱማ ፡ ጠረን ፡ በሩቅ ፡ ይቀረናል ።

#ጎርጎርዮስ
ምን ፡ ታደርግ ፡ ኖሯል ፡ አሁን ፡ ብቅ ፡ ቢሉ ?

#ሶምሶን
ኣይዞህ ፥ በኔ ፡ በኩል ፡ አይነሣም ፡ ጥሉ ፡
ግን ፡ እኔ ፡ በሰላም ፡ ብሄድም ፡ ዐርፌ ፡
ሳይጣላ ፡ አይቀርም ፡ ዐመለኛው ፡ ሰይፌ

#ጎርጎርዮስ
አይጠረጠርም ፤ መቼም ፡ ካየናቸው ፤
እነሱም ፡ አይለቁን ፥ እኛም አንተዋቸው ።

#ሶምሶን
እኔማ ፡ እንኳንስ ፡ እነሱን ፡ አይቼ ፡
ውሻቸውን ፡ ሳየው ፡ በድንገት ፡ አግኝቼ ፡
ያንቀጠቅጠኛል ፡ ደሜ ፡ እየተቈጣ ።

#ጎርጎርዮስ
ከሞንታግ ፡ አሽከሮች ፡ ያው ፡ አንደኛው ፡ መጣ ፡አንዱም፡ተከተለ ፡ ብቅ፡አሉ፡ሁለቱ ።

#ሶምሶን
ይንቀሳቀስ ፡ ጀመር ፡ የሰይፌ፡ ስለቱ ።

#ጎርጎርዮስ
እንግዲህ ፡ ተጠንቀቅ ፡ ሶምሶን ፡ ተሰናዳ

#ሶምሶን
ብቻ ፡ እንዳያገኘን ፡ የዳኝነት ፡ ዕዳ ፡
አንድ፡ ዘዴ ፡ እናምጣ ፡ ጠቡን ፡ እንዲያነሡ ፡እዚህ ፡ ከኛ ፡ አጠገብ ፡ ጠብቄ ፡ ሲደርሱ ፡ ፊቴን ፡ ወደ ፡ እነሱ ፡ እንዲያዩኝ ፡ መልሼ ፡
አስቆጣቸዋለሁ ፡ ከንፈሬን ፡ ነክሼ ።

( #አብርሃምና #ቤልሻጥር #መጡ ) ።
👇👇

#አብርሃም
አንተ ፡ በኛ ፡ ነው ፡ ወይ ፡ ከንፈር ፡ የምትነክሰው ፤

#ሶምሶን
እኔን ፡ አይጠይቅም ፡ እንዳንተ ፡ ያለ ፡ ሰው ።

#አብርሃም
በኛ፡ ላይ ፡ እንደሆን ፡ ንገረኝ ፡ በፍጥነት ፡

#ሶምሶን
መጠየቅ ፡ አያሻም፡ ከኖረህ ፡ ወንድነት ።

#አብርሃም
ሁሉም ፡ በጃቸው ፡ ነው ፡ ሻምላ ፡ ሆነ ፡ ሰይፉም ፤
#የሞንታግ ፡ ወገኖች ፡ ተሰድበው ፡ አያልፉም ።

#ሶምሶን
የት ፡ አይተሃል ፡ ቀርተው ፡መዋጋት ፡ ሳያውቁ ፤
#የካፑሌ ፡ አሽከሮች ፡ በናንተ ፡ ሲጠቁ ?

#አብርሃም
ሊታይ ፡ ነው ፡ እኮ ፡ የናንተ ፡ ጕብዝና ፤

#ሶምሶን
መች፡ አጣህ ፡ መሆኑን ፡ የኛ ፡ ወገን ፡ ጀግና ።

( #ውግያ' #ይገጥማሉ )

#ቤንቮሊዎ ። (ይመጣል) ።

ያላንድ ፡ ምክንያት ፡ በከንቱ ፡ ሳይቸግር ፡
አሁን ፡ ምን ፡ ይባላል ፡ የናንተ ፡ ግርግር ።
ሁል ፡ ጊዜ ፡ ጧት ፡ ማታ ፡ ስታልፉ፡ በመንገድ ፡ልማድ ፡ ሆነባችሁ ፡ ደርሶ ፡ ማንገራበድ ።
ለማምጣት ፡ ነው ፡ እኮ ፡ በናንት ፡ የተነሣ
በጌቶቻችሁ ፡ ላይ ፡ የዳኛ ፡ ወቀሣ።

#ቲባልት ፡ (ሻምላውን መዞ እያወዛወዘ ' መጣ )

እየው ፡ ቤንቮሊዎ ፡ ጥላውን ፡ ዘርግቶ
ሞት ፡ የያዘ ፡ ሻሞላ ' በራስህ ፡ ላይ፡ መጥቶ ፡ ተመልከት ፡ ሲያንዣብብ ፡ እንደ ፡ ጆፌ አሞራ

#ቤንቮሊዎ
መንፋትህ ፡ ይቅርና ፡ የማይረባ ፡ ጉራ
እንገላግላቸው ፡ ይልቅ ፡ ተረዳድተን ።

#ቲባልት
ልገጥምህ ፡ ነውና ፡ የመጣሁት ፡ አንተን ፡
ይልቅ ፡ ተሰናዳ ፡ ሻምላህን ፡ ምዘዘው ፤
ሳትዋጋ ፡ እንዳትሞት ፡ ቶሎ ፡ በጅህ 'ያዘው "

ቲባልት ፡ ሻምላ ፡ መዞ ፡ እጁን ፡ ከዘረጋ ፡
ሊመለስ ፡ አይችልም ፡ ጠላቱን ፡ ሳይወጋ
ወይም ፡ ደግሞ ፡ ራሱ ፡ ቀድሞ ፡ ካልወደቀ ።
#ቤንቮሊዎ
ፉከራህ ፡ ከንቱ ፡ ነው፡ በጣም ፡ የተናቀ ።

(#ውጊያ #ይገጥማሉ) ።

#ሞንታግ ፡ (መጣ)
ወገኖቼ ፡ ሁሉ ፡ ድረሱ ፡ በፍጥነት ፤
እነሆ ፡ ሰዎቼን ፡ ፈጁዋቸው ፡ በድንገት ።

💫ይቀጥላል💫
#ሮሚዮና_ዡልየት

#ክፍል_ሁለት

#ሞንታግ ፡ (መጣ)
ወገኖቼ ሁሉ ድረሱ በፍጥነት
እንሆ ሰውቼን ፈጅዋቸው በድንገት
ሰይፌን ፡ አቀብሉኝ፡ በቶሎ፡ ፍጠኑ ።

የሞንታግ ፡ ሚስት ፡(ተከትላ ፡ መጣች) "
እስቲ፡ ባዶ ፡ እጅዎን ፡ አሁን ፡ ምን ፡ ሊሆኑ ?

#ካፑሌ ፡ (መጣ)

ሰይፌን ፡ አቀብለኝ፡ ማነህ ፡ ቶሎ ፡ ድረስ
የካፑሌ ፡ ሚስት ፡(ተከትላ ፡ መጣች) ።
ሽማግሌው ፡ አብዷል ፡ ድረሱልኝ ፡ በነፍስ

#ወታደር
ይርጋ ፡ በየቦታው ፡ ሁሉም ፡ ጠቡን ፡ ትቶ
ልዑልነታቸው ፡ መጣ ፡ ተቆጥቶ ።

#መስፍኑ ፡ (አገረ ገዥ) ።መጣ
መልካም ፡ ነው ፡ አየነው ፤ ይብቃ ፡ አሁን ፡ እርጉ፤ውጊያውን ፡ ትታችሁ ፡ ወደ ፡ እኔ ፡ ተጠጉ ፡
#ካፑሌና#ሞንታግ ፡ ልንገራችሁ ፡ ስሙ
የናንተ ፡ አምባጓሮ ፡ በመደጋገሙ ፡
አልነቀል ፡ ብሎ ፡ የቂማችሁ ፡ መርዙ ፡
ሥር ፡ ስለ ፡ ሰደደ ፡ ጠንቃችሁ ፡ መዘዙ ፡
ደከመኝ ፡ ሰለቸኝ ፤ ታከተኝ ፡ በብዙ ።
ምንድንነው ፡ በውነቱ ፡ እንዲህ ፡ ያለ ፡ ነገር፤ ሰላም 'እያወኩ' ዘለዓለም ፡ ማስቸገር ።
ሁል ፡ ጊዜ፡ ግርግር' ሁል፡ጊዜ ፡
ሁል ፡ ጊዜ ፡ አምባጓሮ 'ሁል ፡ ጊዜ ጫጫታ ።
በናንተ ፡ ምክንያት ፡ ስንት ፡ ደም ፡ ፈሰሰ፤
ስንት፡ጊዜ፡አገሩ፡ጸጥታው፡ ፈረሰ ፡
ስንት ፡ ጊዜ ፡ በጠብ ፡ ከተማው ፡ ታመሰ ?
አገሬ ፡ በናንተ ፡– ንገሩኝ ፡ በሉ ፡ እኮ ፡
እስከ ፡ መቼ ፡ ድረስ ፡ ይኖራል ፡ ታውኮ ?
እስቲ ፡ በማን ፡ አገር ፡ እስቲ ፡ በማን ፡ ዕድሜ፡ እንዲህ ፡ ያለ ፡ ጥጋብ ፡ የሌለው ፡ፍጻሜ፡
እስከ ፡ ዛሬ ፡ ድረስ ፡ ይታወቃል 'ታይቶ ፤
ማንም ፡ ሰው ፡ ይፍረደው ፡ ይህን ፡ተመልክቶ ።
እስከ ፡ መቼ፡ድረስ ሕዝቤ ፡ በሰይፍ፡ያልቃል?
ትሰሙኝ ፡ እንደሆን ፡ እንግዴህ ፡ ይበቃል
በእውነቱ ፡ ዕወቁት' ከዛሬ ፡ ጀምሮ '
በናንተ ፡ መካከል ፡ ቢሆን ፡ አምባጓሮ '
አዝዣለሁ ፡ አጥፊው ፡ በሞት ፡ እንዲቀጣ
አለዚያም ፡ ጨርሶ ፡ ካገር ፡ እንዲወጣ ።
እንግዴህ ፡ ልባችሁ ፡ የኔን ፡ ፍቅር ፡ ቢሻ ፡
የዛሬው ፡ ጠባችሁ ፡ ይሁን ፡ መጨረሻ ፡
ስታዝኑ ፡ እንዳልሰማ ፡ በኋላ ፡ በፈራጅ ፡
ይህን ' ያሁን 'ቃሌን ፡ ቁጠሩት፡ እንዳዋጅ"

#ካፑሌ#ፓሪስ ፡ አንድ ፡ #አሽከር

#ካፑሌ
የመስፍኑ'ትእዛዝ ፡ ስለ ፡ ሆነ ፡ ብርቱ ፡
ሞንታግና ፡ እኔ ፡ ሳስበው ፡ በውነቱ ፡
እንግዲህ ፡ ጠባችን ፡ እየቀዘቀዘ :
ይሄድ' ይመስለኛል ፡ ባዋጅ ፡ ከተያዘ ።

#ፓሪስ
ስማችሁ ፡ ዝናችሁ፡ በጣም ፡ የታወቀ ፡
እንዲሁም ፡ ክብራችሁ ፡ ከሁሉም ፡ የላቀ ፡
ሆኖ ይህን ፡ ያኽል ፡ ጊዜ ፡ ተጣልታችሁ ፡
በጣም ፡ ያሳዝናል ፡ በጠብ ፡ መኖራችሁ ፤
እረ ፡ እንደ ፡ ምን ፡ ሆነ ፡ ደግሞስ ፡ የኔ ፡ ነገር ?
ልጅዎን ፡ ለማግባት ፡ ጠይቄዎት ፡ ነበር ።

#ካፑሌ
ችላ ፡ ብዬ ፡አይደለም ፡ ጥቂት ፡ ጊዜ ፡ ታገሥ ፤
ዡልዬት ፡ ከፍ ፡ ትበል ፤ ለመታጨት ፡ ትድረስ ፡
አሁን ፡ አእምሮዋ ፡ ዕውቀቷም ፡ አልጠና
ከልጅነት ፡ ዕድሜ ፡ አልወጣችም ፡ ገና ፡
እስከዚያ ድረስ ፡ ግን 'አንተ ፡ ተላመዳት ፤
ትወቅህ ፡ ዕወቃት ፡ትውደድህ ውደዳት
አሁን ፡ ለምሳሌ ፡ ይኸው ፡ ዛሬ ፡ ማታ ፡
ትልቅ ፡ ግብዣ ፡ አድርጌ ፡ በቤቴ ፡ ጨዋታ፡
ደስታም ፡ ይሆናል ፡ አንተም ፡ እንዳትቀር ፤
ናና፡ ከሷ ፡ ጋራ ፡ ቀርበህ ፡ ተነጋገር ።
በጣም ፡ ተዋወቁ፤

ና፡ እባክህ ፡ አንተ ፡ #አሽከር

በዚህ ፡ ወረቀት፡ ላይ ፡ ተጽፎ ፡ ስማቸው ፡
የሚነበበውን ፡ ቶሎ ፡ ፈልጋቸው ፤
ውጣ ፡ ከከተማ ፡ ዙር ፡ በየመንገዱ ፤
ታገኛቸዋለህ ፡ በድንገት ፡ ሲሄዱ ።
አደራ ፡ በላቸው ፡ ማታ ፡ እንዲመጡ ፤
ከግብዣዬ ፡ ቀርበው ፡ በልተው ፡ እንዲጠጡ ፡
እንዲጫወቱልኝ ፡ ፈቃዴ ፡ መሆኑን ፡
ፈጥነህ ፡ ንገራቸው ፤ ቶሎ ፡ ሂድ ፡ አሁኑን

#አሽከር ፡(ወረቀት ፡ ተቀብሎ ፡ ሄዴ) ።

(#ሮሜዎና#ቤንሾሊዎ) "

#ሮሜዎ
የነካፑሌ ፡ አሽከር ፡ አንድ ፡ ወረቀት ፡ ይዞ ፡
መንገድ ፡ አገኘሁት ፡ ሲመለከት ፡ ፈዞ ፡ .
እሱስ ፡ ለካ ፡ ማንበብ ፡ የማያውቅ ፡ ኖሮ ፡
የሚያነብለት ፡ ሰው ፡ በጣም ፡ ተቸግሮ ፡
እኔን ፡ ቢለምነኝ፡ እኔም ፡ የነሱ፡አሽከር ፡
ሳላውቅ ፡ መሆኑን ፡ ባለመጠራጠር፡
ምንም ፡ ሳልተረጒም ፡ በደግም ፡ በመጥፎ ፡
የብዙ ፡ ሰዎች ፡ ስም ፡ አየሁኝ ፡ ተጽፎ ።
አንብቤ ፡ ስጨርስ ፡ ከሰማ ፡ በኋላ ፡
በወረቀቱ ፡ ላይ ፡ ስማቸው ፡ የሞላ፡
ምንድናቸው ፡ ብዬ ፡ እኔ ፡ ብጠይቀው ፡
ዛሬ ፡ ካፑሌ ፡ ቤት ፡ ማታ ፡ራት፡ተጋብዘው ፡
የሚመጡ ፡ ናቸው ፡ አለና ፡ ነገረኝ ።

#ቤንቮሊዎ
- እኔም ፡ ሰምቻለሁ ፡ እንኳን ፡ አስታወስከኝ ፡
እርግጥ፡በነሱ ፡ ቤት ፡ ይኸው ፡ ዛሬ ፡ ማታ
ትልቅ ፡ ግብዣ ፡ ሆኖ ፡ የዳንስም ፡ ጨዋታ ፡ብዙ፡ሰው፡ተጠርቷል፤ሰውም፡ የሚሄደው!
ፊቱን ፡ በመሰውር ፡ እየሸፈነ ፡ ነው ።
ስለዚህ ፡ አያውቅም ፡ አንዱን፡አንዱን ፡ ለይቶ ፤
አንተና፡እኔ ፡ብንሄድ ፡ ማንም ፡ ቢሆን ፡ ከቶ
አያውቀንምና ፡ እንሂድ ፡ ሳንፈራ ፤
እዚያም ፡ ከሮዛሊን ፡ ካንተ ፡ እጮኛ፡ጋራ ፡
እንገናኛለን ፡ ተጠርታለችና።

#ሮሜዎ
እውነት ፡ ቤንቮሊዎ ፡ አስበሃል ፡ ደኅና ፡
በል'እንግዴህ ፡ ፍጠን ፡ ቶሎ ፡ እንሰናዳ
እውነትም ፡ ባስበው ፡ የኔን ፡ ጽጌ ፡ ረዳ ፡
ካየኋት ፡ ቈይቷል ፡ ወር ፡ ሆኖኛል ፡ ይኸው ፤
በጣም ፡ ጥሩ'አሳብ' ነው፡አሁን'ያመጣኸው ።

(#ሮሜዎና' #ሜርኮቲዎ)

#ሜርኩቲዎ
ወዴት ፡ ትሄዳለህ ፡ እንዲህ ፡ በጨለማ ?

#ሮሜዎ
ዐይንህ፡እንዳላየ ፡ ጆሮህ'እንዳልሰማ ፡
ሆነህ ፡ ዝም ፡ ብለህ ፡ እለፍ ፡ በጐዳና ፤
ማንም ፡ ሰው ፡ እንዲያውቀኝ ፡ አልፈልግምና ።

#ሜርኩቲዎ
ባሁን ፡ ሰዓት ፡ ስትሄድ ፡ ብቻህን ፡ አይቼ ፡
ለመቅረት ፡ አልችልም ፡ ካንተ ፡ ተለይቼ ።

#ሮሜዎ
ልብህ 'እንዳይሠጋ፡ ሆድህ ፡ እንዳይፈራ ፡
ምስጢሬን ፡ ልንገርህ ፡ የኔ ፡ ባልንጀራ ፤
ዛሬ ፡ ካፑሌ ፡ ቤት፡ ትልቅ ፡ ግብዣ ፡ ሆኖ ፡
ሰዉ ፡ በመሰውር ፡ ፊቱን ፡ ተሸፍኖ ፡
ዳንስ ፡ ይጫወት፡ ነበር፡ ከቤንቮሊዎ፡ጋራ፡
ማንም ፡ ሰው ፡ ሳያየን ፡ ገባን ፡ ሳንፈራ ፡
የቀድሞ ፡ እጮኛዬን ፡ ሮዛሊንን' ልሻ '
ሄጄልህ ፡ ነበረ ፤ ኋላም ፡ መጨረሻ ፡
በጣም ያስገርማል ፡ ይደንቃል ፡ ወዳጄ፤
አልማዝ አገኘሁኝ ፡ ወርቅ ፡ ልሻ 'ሄጄ
የነካፑሌን ፡ ልጅ ፡ ዡልዬትን ፡ አይቼ ፡
በውበቷ ፡ ብርሃን ፡ መጣሁ ፡ ተረትቼ ፡
ግብዣው ፡ ስላለቀ ፡ ሰዉ ፡ ተበትኖ ፡
ብቅ ፡ ብትልልኝ ፡ ምናልባት ፡ ልቧ ፡ አዝኖ
ይኸው ፡ መሄዴ ፡ ነው ፡ ደግሞ ፡ ተመልሼ
እመጣለሁ ፡ አሁን ፡ በፍጥነት ፡ ደርሼ ።

#ሜርኩቲዎ
እንዴት ፡ ትሄዳለህ፡ደፍረህ ፡ ከነሱ ፡ቤት ?
አንድ ፡ ሰው ፡ ከነሱ ፡ ቢያገኝህ ፡ በድንገት
ዕወቅ ፡ ይገድልሃል ፡ አብደሃል ፡ ፈጽሞ ፤
በራቸው ፡ ይዘጋል ፡ ለመግባትስ ፡ ደግሞ
እንዴት ፡ ትችላለህ ? ይቅርብህ ፡ ተመለስ

#ሮሜዎ
ማ ፡ ሊያየው ፡ ይችላል ፡ ሰው ፡ ጨለማ ፡ ሲለብስ ?
አጥሩ ፡ ቢረዝም ፡ በሩ፡ ቢጠነክር ፡
ጠላትም ፡ አድፍጦ ፡ ሊገድለው ፡ ቢሞክር
ሰው ፡መውደድ፡አድሮበት፡ፍቅር ካሰከረው
ምንም ፡ አያግደው ፤ምንም አይበግረው
ባገኛት ፡ ቢቀናኝ ፡ ቶሎ ፡ ልምጣ ፡ ሄጄ ፤
ሜርኩቲዎ ፡ደኅና ፡ እደር ፡ አትሥጋ ፡ ወዳጄ።

💫ይቀጥላል💫
#ሮሜዎና_ዡልዬት


#ክፍል_ሰባት

#ቤንቮሊዎ
ጠቡን ፡ የጀመረው ፡ ክፉ ፡ ቃል ፡ ተናግሮ
ይኸው ፡ ቲባልት ፡ ነው ፡ ሌላ ፡ ሰው ፡ አይደለም ፤
ከሱ ፡ በቀር ፡ ዛሬ ፡ ጠብ ፡ ያነሣ ፡ የለም ።
እኔና ፡ ሜርኩቲዎን ፡ ሰደበን ፡ ሳንሰድበው
ሮሜዎ ፡ ደረሰ ፡ ድንገት ፡ ሳናስበው ።
እሱም ፡ በደግነት ፡ ቃሉን ፡ አለስልሶ ፡
ልዑል ፡ የሰጡትን ያዋጅ ፡ ቃል ፡ ኣስታውሶ ፡
ቲባልትን ፡ ለመነው ፡ ጠብ ፡ እንዳያነሣ ፤
መቼም ፡ መጥቷልና ፡ እሱ ፡ ግን ፡ ላበሳ ፡
በእልህ ፡ እንቢ ፡ ብሎ ስድቡን ፡ ሲቀጥል
ከሜርኩቲዎ ፡ ጋራ ፡ ተማረሩ ፡ በጥል ፤
ሻምላ ፡ ቢማዘዙ ፡ ቶሎ ፡ መገላገል ፡
አሰብንና ፡ ገባን ፡ ከነሱ ፡ መካከል ።
እኔና ፡ ሮሜዎ ፡ ስንገላግላቸው ፡
ሜርኩቲዎን ለመውጋት ቲባልት ተመቸው
እኛም ፡ አላየንም ሜርኩቲዎን ፡ ሲወጋው
ኋላ ፡ ግን ፡ አየነው ፡ ቁስሉን ፡ ከነ አደጋው
ከሽሸ ፡ በኋላ ፡ ቲባልት ፡ እንደ ፡ ገና ፡
ቢመጣ ፡ ሮሜዎ ፡ ነዶት ፡ ነበርና ፤
ደሙን ፡ ለመበቀል ፡ በንዴት ፡ ተነሥቶ ፡
ከቲባልት ፡ ጋራ ፡ በቅጽበት ፡ ተዋግቶ ፡
ወዲያው በደቂቃ ውጊያው በጣም ሲግል
እኔም ፡ ሳያደርሰኝ ፡ ችዬ ፡ ሳልገላግል ፡
ቲባልት ፡ ቆሰለና ፡ በፍጥነት ፡ ወደቀ ፥
ሮሜዎም ፡ ሸሸና ፡ በዚሁ ፡ አለቀ ፤
ከተናገርኩትም ፡ ከውነቱ ፡ የራቀ ፡
ውሸት ፡ ቢገኝብኝ ፡ ተደርጎ ፡ ምርመራ ፡
ይድረስብኝ ፡ በኔ ፡ የቅጣት ፡ መከራ ።

የካፑሌ ፡ ሚስት (መጣች)

መሠረት ፡ የለውም ፡ ምስክርነቱ ፤
ከእውነተኛው ፡ ነገር ፡ ይበልጣል ፡ ሐሰቱ '
ይህንን ፡ ቢናገር ፡ እያስመሰለ ፡ እሱ ፡
የሞንታግ ወገን ነው ልዑል ሆይ አይርሱ!
በፍርድ ሮሜዎ ፡ ይሙት ፡ ነው ፡ የምለው

#መስፍን
ሮሜዎ ፡ ቲባልትን ፡ ወግቶ ፡ ከገደለው ፡
እናንተ ፡ ስለሱ ፡ ፍርድ ፡ ስጥ ፡ ስትሉ ፡
የሜርኩቲዎን ፡ ደም ፡ ማን ይክፈለኝ ፡ለኔ
ዘመዴ ፡ ነው ፡ እኮ ፥ ሥጋዬ ፡ወገኔ ።

#ሞንታግ
ልዑል ፡ሆይ ሜርኩቲዎን ቲባልት ገደለው
ዐዋጁ 'ቲባልትን ፡ ይሙት' ነው ' የሚለው
ስለዚህ ፡ ቢያስቡት ፡ አሁን ፡ የኔ ፡ ልጅ ፤
ቲባልትን ሲገድለው ፡ዐዋጅ ፈጸመ ፡ እንጅ
ሌላ ፡ ምን ፡ ጨመረ ፡ እስቲ ምን አጠፋ ?

#መስፍን
ሞንታግ ምሕረት አለ ብለህ ፡ እንዳትለፋ፡
ሮሜዎ ፡ በፍጥነት ፡ ዛሬ ፡ ካገር ፡ ይውጣ
ጠባችሁ ፡ በኔ ፡ ላይ ፡ ይኸው ዞሮ ፡ መጣ
በናንተ ፡ ምክንያት ፡ የሞተው ፡ ደጉ ፡ ሰው
ሥጋዬ ፡ ነው ፡ ዛሬ ፡ ደሙ ፡ የፈሰሰው ፡
በሰጠሁት ፡ ዐዋጅ ፡ ራሴ ፡ ወስኜ ፡
እገኛለሁ ፡ እኔ ፡ ጨካኝ ፡ ቀጭ ፡ ሆኜ፡
የፍርዴንም ፡ ሥራ ፡ በቅጣት ፡ ስሠራ ፡
ይቅርታ ፡ የለኝም ፡ ለማንም ፡ አልራራ ።
አማላጅ ፡ ልመና ፡ ጸጸትና ፡ ለቅሶ ፡
ፍርዴን ፡ ሊመልሱት ፡ አይችሉም ፡ ጨርሶ
ስማ ፡ ልጅህ ፡ ዛሬ ፡ የኔን ፡ ትእዛዝ ፡ ሽሮ ፡
የተገኘ ፡ እንደሆን ፡ በከተማው ፡ አድሮ ፡
ዛሬ ፡ ከቬሮና ፡ በፍጥነት ፡ ካልወጣ '
ዕወቀው ' ያለፍርድ' በሞት እንዲቀጣ ።

#ዡልዬትና#ሞግዚቷ ፡ (በቤታቸው) "

#ዡልዬት
እኔና ፡ ሮሜዎ ፡ ዕድላችን ፡ ክፉ ፤
ይደንቃል ፡ ሰርጋችን ፡ እንደዚህ ፡ ማለፉ፡
ሰርጉ አልነበረም ወይ የሰው ፡ልጅ ደስታ
እኛ ፡ ግን ፡ምስኪኖች በዚህ ፡ ሁሉ ፈንታ፡
መሥጋትና ፡ መፍራት ፡ ያባት የናት ፡ ቁጣ
ሆነና ፡ ተገኘ ፡ የተሰጠን ፡ ዕጣ ።
አልገሠግሥ ፡ አለ ፡ ጊዜና ፡ ሰዓቱ ፤
ምነው ፡ የዛሬ ፡ ቀን ፡ ደከመ ፡ ፍጥነቱ ?
ሰዓቱም ፡ ለገመ ፡ ዳተኛ ፡ መሆኑ ፡
ሮሜዎን ፡ ስጠብቅ ፡ አልመሽ ፡አለኝ ፡ ቀኑ
ደግሞ ፡ ሞግዚቴ ፡ ነች ፡ ዋና ፡ ጥፋተኛ ፤
ምነው ፡ ሆነችብኝ ፡ እንደዚህ ፡ ዳተኛ ?
በፊት ፡ ደኅንነቱን ፡ ነግራኝ ፡ ተመልሳ ፡
መሄድ ፡ ትችል ፡ ነበር ዳግም ፡ በግሥገሣ
ሌሊቱ ፡ ሲጨልም ፡ ጨረቃ ፡ ሳትወጣ ፡
ንገሪው ፡ አልኩና ፡ ሮሜዎ ፡ እንዲመጣ '
ብልካት ፡ እንሆ ፡ ቀረች ፡ እዚያው ፡ ቀልጣ
እባክህ ፡ ጨለማ ፡ ፍጠን ፡ በቶሎ ፡ ና ፤
ካልመሸ ፡ ሮሜዎ ፡ ደፍሮ ፡ አይመጣምና
ሌሊቱ' ይተካ ፡ የቀን ፡ ብርሃን ፡ ሄዶ፤
ሮሜዎን ወደ እኔ እንዲያስገባው ፡ ጋርዶ።
ቀኑ ፡ እየደከመ ፡ ብርሃን ፡ እየሸሸ ፡
ፀሓይ ፡ እየጠፋች ፡ ሰዓቱ ፡ እየመሸ ፡
አንተ ፡ ከባድ ፡ ጽልመት፡የሌሊት ፡ ጨለማ
ፈጥነህ ፡ ቶሎ ፡ ድረስ ፡ አትሁን ፡ ደካማ ።
ገሥግሠህ ፡ ሸፍናት ፡ ዓለምን ፡ በጥላ ፤
ጥላህ ፡ ለሮሜዎ ፡ ይሁነው ፡ ከለላ '
ፀሓይም ፡ ጥለቂ ፤ ብርሃንን ፡ አትስጪ ፤
ኮከብ ፡ ተሰወሪ ፡ ጨረቃም ፡ አትውጪ'
ካለም ፡ ገለል ፡ በሉ ፡ ብርሃንና ፡ ፋና ፡
ብርሃን ፡ እሱ፡ ራሱ ፡ ሮሜዎ ፡ ነውና ፡
ያቻት ወዲህ መጣች ብቅ አለች ሞግዚቴ
ደርሳ እስክትነግረኝ ፡ ወሬውን ፡ ከፊቴ ፡
ቸኩያለሁ ፡ በጣም ፡ እንዴት ፡ ያለ ፡ ወሬ ፡
ይዘሽልኝ ፡ መጣሽ ፡ ሞግዚቴ ፡ ሆይ ፡ ዛሬ ?
ምነው ፡ ምን ፡ ሆነሻል ፡ ፊትሽ ፡ ተለወጠ ?

#ሞግዚት
አዬ 'ከንቱ ፡ ነገር ፡ በቃ ፡ ተቈረጠ'
ባጭር ፡ ተቀጠፈ ' ያን ፡ መሳይ ፡ መኰንን
አዬ ፡ጉድ አዬ ፡ ጉድ! ጠላሁ ሰው መሆንን

#ዡልዬት
አሁን ፡ ባሁን 'ሄደሽ ፡ ከኔ ዘንድ ፡ ከወጣሽ'
ምን ፡ዐይነት ፡ኀዘን ነው ይዘሽው የመጣሽ

#ሞግዚት
አወይ 'ሮሜዎ 'ቲባልት ፡ መልካሙ ፡ ሰው፡
እንደ ፡ፋሲካ ፡ በግ ፡ ደሙ ፡ የፈሰሰው ።

#ዡልዬት
ሐዘኑን ' ሰምቼ ፡ ልቤ ፡ ሳይመታ፡
መናገር' አቃተሽ ፡ አፍሽ ፡ አመነታ '
ሮሜዎ ፡ ሞተ፡ ወይ ? ሞቶም ፡እንደ ፡ ሆነ
ንገሪኝ ፡ ምላስሽ ፡ እየሸፋፈነ ፡
ሳይደብቅ ፡ ገልጦልኝ ፡ መርዶውን ፡ ልረዳ
ልቤም ፡ ተሠንጥቆ ፡ በሐዘን ፡ ይፈንዳ ።

#ሞግዚት
ቍስሉንም ፡ አየሁት ፡ በጣም ፡ ያሳዝናል ፤
ሐኪም 'አይጠሩለት ፡ ሞቶ፡ ምን ፡ ይሆናል
ምንም' ትንፋሽ የለው አልፋለች ፡ ሕይወቱ፡
ደሙ ፡ ይመነጫል ፡ ቆስሎ ' ከደረቱ ፤
ከሞተ 'ቁይቷል ደርቋል ፡ ሰውነቱ "
እንዲህ ፡ ያለ ፡ ሥራ መቼም ፡ አልተሠራም
ዥልዬት ፡ የዛሬ ፡ ጉድ ፡ ይቅር ፡ አይወራም
ቲባልት ! ሮሜዎ ! አየሁ ፡ ደሙ ፡ ፈሶ :
ልብሱ ፡ ተበክሎ ፡ መሬቱም ፡ ርሶ ።

#ዡልዬት
ቲባልት ! ሮሜዎ ! ሁለቱንም ፡ ጠርተሽ ፡
ከምታስጨንቂኝ ፡ ንገሪኝ ፡ ለይተሽ '
ሮሜዎ ፡ ባሌ ፡ ነው ፡ ቲባልት ፡ ዘመዴ ፤
የቱ ፡ ነው ፡ የሞተው ፡ ተጨነቀ ፡ ሆዴ
ባለም ፡ ላይ ፡ ከሌሉ ፡ እነዚህ ፡ ሁለቱ ፡
መታከት ፡ ነውና ፡ ሁሉ ፡ ነገር ፡ ከንቱ ፡
የምጽኣት ፡ ቀን ፡ ይሁን ፡ መለከት ፡ ይነፋ ፤
አሁን ፡ ተደምስሶ ፍጥረተ ዓለም ፡ ይጥፋ፡
ባሕር ፡ ጫካ ፥ ገደል ፥ ጅረትም ፡ ተራራ ፡
ፍጡር ፡ እዬዬ ፥ በል ፡ አልቅስ ፡ ከኔ ፡ ጋራ

#ሞግዚት
ሟቹ ፡ ቲባልት ፡ ነው ፡ ካለም ፡ ላይ ፡ የሄደ
ገዳዩ ፡ ሮሜዎ ፡ ካገር ፡ተሰደደ ።

#ዡልዬት
ሮሜዎ ፡ ቲባልትን ፡ ብትዪኝ ፡ ገደለው ፡
አይችልም ፡ መንፈሴ ፡ አምኖ ፡ ሊቀበለው

💫ይቀጥላል💫
#ሮሜዎና_ዡልዬት


#ክፍል_አስራ_አምስት(የመጨረሻ
ክፍል)

#ሁለተኛ_ዘበኛ
ይኸው ፡ አገኘነው ፡ የሮሜዎን ፡ አሽከር ።

#የመጀመሪያ_ዘበኛ
መስፍኑ ፡ እስቲመጡ፡ እንዳይመረመር ።
(ሦስተኛ ፡ ዘበኛ ፡ ከአባ ' ሎራ፡ጋራ፡ መጣ)

#ሦስተኛ_ዘበኛ
እያንቀጠቀጠው ፡ ጥግ ፡ ይዞ ፡ ሲያለቅስ
ይኸውና ፡ ደግሞ ፡ አገኘሁ ፡ አንድ ፡ ቄስ ፡
ለምን ፡ እንደ ፡ ያዘው ፡ አልታወቀም፡ ከቶ ፡
ጕጠቱን ፡ ቀማነው ፡ በእጁ ፡ ላይ ፡ተገኝቶ

#የመጀመሪያ_ዘበኛ
መስፍኑ ፡ እስቲመጡ ፡ እሱን ፡ አትልቀቁ ፤
የሚጠረጠር ፡ ነው ፡ ይዛችሁ ፡ ጠብቁ ።
(መስፍኑ ፡ ታጅቦ ፡ መጣ) ።

#መስፍን
እኔን ፡ የሚያስጠራ ፡ ሳይነጋ ፡ ሌሊቱ ፤
ምንድነው ፡ንገሩኝ ፡ እስቲ ፡ ምክንያቱ ? ..
(ካፑሌ ' ፤ ሚስቱና ሌሎች ሰዎች መጡ)

#ካፑሌ
ምስጢሩ ፡ ምንድነው ፡ የሰዉ ጫጫታ ?

#የካፑሌ_ሚስት
እረ ፡ እንዲህ ፡ አይደለም ፡ የሕዝቡ ጋጋታ ፡
ግማሹ ፡ ሮሜዎ ፡ ግማሹ ፡ ዡልዬት ፡
ግማሾቹም ፡ ፓሪስ ፡ እያሉ ፡ በጩኸት ፡
ወደ ፡ እኛ ፡ መቃብር ፡ ገቡ ፡ እየተጋፉ ።

#መስፍን
ነገሩን ፡ ንገሩኝ፡ ደግም ፡ ሆነ፡ ክፉ ።

#የመጀመሪያ_ዘበኛ
ልዑል ፡ ሆይ ፡ ያስተውሉ'ፓሪስን ፡ተገድሎ
እዩት ፡ ሮሜዎ ፡ መሬት ፡ ላይ ፡ ተንጋሎ ፡
ቀድሞ ፡ የሞተችው ፡ ዡልዬት ፡ ተመልሳ፣
እይዋት ፡ እሷ ፡ ደግሞ ፡ በደም ተለውሳ ።

#መስፍን
ይህ ፡ ዐመፅ ፡ እንደ፡ምን ፡ ሆኖ ፡ እንደ ፡ ተሠራ ፍጠኑ ፡ በቶሎ ፡ይደረግ ፡ ምርመራ

#የመጀመሪያ_ዘበኛ
የሮሜዎ ፡ ሎሌ ፥ ካንድ ፡ ካህን ፡ ጋራ ፡
እነሆ ፡ ተገኝቷል ፡ አሁን ፡ በዚህ ፡ ስፍራ ።

#ካፑሌ
ሚስቴ ፡ ተመልከቺ ፡ ልጃችን ፡ ተኝታ ፥
እዪው ፡ ደሟ ፡ ሲፈስ ሆዷ ላይ ፡ ተወግታ
አስተውዪው ይህ ጩቤ ከመጣበት ፡ ቦታ
ከሞንታግ ልጅ ላይ ነው ተመልከች አፎቱ
ባዶውን ፡ ይታያል ፡ ይግባሽ ፡ ምክንያቱ ።

#የካፑሌ_ሚስት
እባክህን ፡ ተወኝ ፡ እኔ ፡ አልችልም ፡ ማየት
ወይ፡ልጄ ፡ ወይ ልጄ ፡ ወይ፡ ልጄ ፡ ዝልዬት
ሐዘን ፡ ጨፈለቀኝ ፡ ውሃ ፡ ሆንኩኝ ፡ እኔ ፤
ይህንን ፡ ትልቅ ፡ ጕድ ፡ ይህንን ፡ ጭካኔ፡
ኣይችልም ፡ አይችልም። ሊመለከት ዐይኔ
(ሞንታግና ፡ ሌሎች ፡ ሰዎች ፡ መጡ) "

#መስፍን
ሞንታግ ፡ ወዲህ ፡ ቅረብ ፡ ተመልከተው ፡ አንተ ፡ልጅህን ፡ አስተውለው ፥ እየው ፡ እንደ ፡ ሞተ ።

#ሞንታግ
የልጅዋ ፡ መሰደድ ፡ ሆኖባት ፡ በሽታ ፡
ሚስቴ ፡ ሌሊት ፡ ሞተች በሐዘን ተጐድታ
ያሁን ፡ ሐዘኔ ፡ ግን በጣም ፡ ትልቅ መዓት
የባሰ ፡ ጐዳት፡ ነው ፡ የመጣ ፡ ለቅጣት ።

#መስፍን
እንባህን ፡ አግደው ፡ አትቸኵል ፡ ለማልቀስ
በፊት ፡ ምርመራውን ፡ ይገባል ፡ መጨረስ
ያመፁን ፡ ምክንያት፡ ምንጩን ፡ እንወቀው
ምርመራው ይጀመር አብረን ፡ እንዝለቀው
የተያዙት ፡ ሰዎች ፡ በፍጥነት ፡ ይቅረቡ ።

#አባ_ሎራ
እዚህ ፡ ያላችሁት ፡ አሁን ፡ ስታስቡ ፡
እኔ ፡ መገኘቴ ፡ በዚህ ፡ ዐመፅ ፡ ቦታ ፡
ያስጠረጥረኛል ፡ ገፍቶ ፡ በግዴታ ፡
ዳሩ ፡ ግን ፡ ነገሩን ፡ ልናገረውና ፡
ተረዱት ፡ ዕወቁት ፡ የኔን ፡ ንጽሕና ።

#መስፍን
ታሪኩን ፡ እንስማ ፡ በሉ ፡ ይናገሩ ።

#አባ_ሎራ
ሐተታ ፡ አላበዛም ፡ ልናገር ፡ ባጭሩ ፤
ረዥም ፡ አይደለም ፡ቀላል፡ ነው ምስጢሩ
መልካሙ ፡ ሮሜዎ ፡ ይህ አሁን ፡ የሞተው ለዡልዬት ፡ባሏ ነው በተክሊል ተጋብተው
ቃል ኪዳን ሞልተዋል ቈርበው እንደ ሕጉ
በሃይማኖት ሥራት ቃል፡ ኪዳን ሲያደርጉ
የተክሊሉን ፡ ሥራት ፡ ባርኮ ፡ የቀደሰው ፡
እኔው ፡ ራሴ ፡ ነኝ፤ አይደለም ፡ ሌላ ፡ ሰው
በዚያው ቀን ቲባልትን ቢገድለው ፡ ተፈርዶ
ከዚህ ፡ አገር ፡ ወጣ ፡ ሮሜዎ ፡ ተሰዶ፡
ዡልዬት ፡ ዘመዶቿ ፡ ይህንን ፡ ሳያውቁ ፡
ለፓሪስ ፡ ሊድሯት ፡ እሷን ፡ ቢያስጨንቁ ፡
በሐዘን ፡ አልቅሳ ፡ ነገረችኝ ፡ መጥታ ፤
ዘዴ ፡ ካልተገኘ ፡ በገዛ ፡ እጅዋ ፡ ሞታ ፡
ልትድን ፡ አሰበች ፡ ካገኛት ፡ ፈተና ፤
እኔም ፡ በዚህ ፡ ነገር ፡ በጣም ፡ አዘንኩና ፡
መድኀኒት ፡ ሰጠኋት ሕይወት ፡ አጠውልጎ
እንቅልፍ ፡ የሚያስተኛ እንደ ሞት ፡ አድርጎ
ከዚያም ፡ ለሮሜዎ ፡ ወረቀት ፡ ጽፌለት ፡
እንዲመጣ ፡አዘዝኩት ገሥግሦ በፍጥነት
ከእንቅልፋ፡ ስትነቃ የመርዙ ኃይል ፡ አልቆ
እንዲወስዳት ፡ ነበረ ውጭ ፡ አገር ፡ ደብቆ
የኔንም ፡ ወረቀት ፡ የወሰደልኝ ፡ ሰው ፡
የኛ ፡ ካህን ፡ ነበር ፤ እሱም ፡ ሳያደርሰው ፡
እክል፡ ስላገኘው ፡ በሄደበት ፡ ቦታ ፡
መልሶ ፡ አመጣልኝ ፡ ትናንትና ፡ ማታ ።
የዡልየት ፡ መነሻ ፡ ሌሊት ፡ ስለ ፡ ነበር ፡
እኔም ፡ በጨለማ ፡ መጣሁ ፡ ስደናበር ፡
አሳቤ ፡ ነበረ ፡ ሮሜዎ ፡እስቲመጣ ፡
ደብቄ ፡ ላቆያት ፡ ከቤት ፡ ሳላስወጣ ፡
ዳሩ፡ግን ፡ ገሥግሼ ፡ እኔ ፡ ከዚህ ፡ ስደርስ
ወድቀው ፡ አየኋቸው ፡ ሮሜዎና፡ ፓሪስ ።
እሷም ፡ ነቃችና ፡ ወዲያው ፡ ስትነሣ ፡
እግዜር ፡ ያመጣውን ፡ ብትቀበል ፡ ታግሣ
የሚሻል ፡ መሆኑን ፡ ላስረዳት ፡ ሞክሬ ፡
ከደጅ ፡ ድምፅ ሰማሁ ሳጥናናት በምክሬ
ለመንኳት ፡ እንድትሄድ ፡ እኔን ፡ ተከትላ ፥
ምክሬን ፡ አልሰማችም ቀረች እንቢ ፡ ብላ
እኔም ፡ የመጣውን ፡ ለማየት ፡ በኋላ ፤
ወጥቼ ፡ መጣሁኝ ፡ ይኸው ፡ እዚህ ፡ ቦታ
ያስረዳ፡ ነበረ ፡ የዡልዬት ፡ ሁኔታ ፡
ሐዘኗ ፡ መሆኑን ፡ በጣም ፡ የበረታ ።
ከዚያ በኋላ ፡ ግን ፡ የሆነውን ፡ ነገር ፡
አላየሁምና ፡ አልችልም ፡ መናገር ፡
ዡልዬት ፡ ሮሜዎን በተክሊል ፡ ማግባቷን
ታውቀዋለችና ፡ ጠይቁ ፡ ሞግዚቷን ፡
እንግዴህ ፡ ልቀጣ ፡ ቃሌ ፡ ቢገኝበት ፡
በውስጡ ፡ የገባ ፡ ሐሰትና፡ ውሸት

#መስፍን
ጻድቅ ፡ሰው ኣድርገን ፡እርስዎን ከማክበር
አቋርጠን ፡ አናውቅም የሮሜዎን ፡ አሽከር
በፍጥነት ፡ አቅርቡት ፡ ያየውን ፡ ይናገር ።

#ቤልሻጥር
የዡልዬትን ፡ መሞት ፡ ጌታዬ ፡ ብነግረው ፡
መርዶውን ፡ ሲሰማ ፡ ሐዘን ፡ አሰከረው ፡
ወዲያው ፡ ተነሣና ፡ እየገሠገሠ ፡
ሌሊት ፡ እዚህ ፡ ቦታ ፡ ከኔ ፡ ጋር ፡ ደረሰ ።
ይህንን ፡ ደብዳቤ ፡ ላባቴ ፡ ስጥ ፡ ብሎ ፡
እኔን ፡ እንዳልገባ ፡ በብርቱ ፡ ከልክሎ ፡
ትእዛዙን ፡ ባልፈጽም ፡ በሞት ፡ አስፈራርቶ
አየሁት ፡ ሲገባ ፡ እኔን ፡ እዚህ ፡ ትቶ ።

#መስፍን
ደብዳቤውን ፡ ስጠኝ እስቲ ፡ ልመልከተው
የፓሪስም ፡ አሽከር ፡ ይጠራ ወዴት ፡ ነው ?
(የፓሪስ • አሽከር ፡ ቀረበ) ።
ሌሊት ፡ በጨለማ ፡ ደግሞ ፡ ያንተ ፡ ጌታ ፡
እዚህ ፡ ለምን ፡ መጣ ፡ እመቃብር ፡ ቦታ ?

#የፓሪስ_አሽከር
አበባ ፡ ሊያስቀምጥ ፡ እመቃብሯ ፡ ላይ ፡
መጣና ፡ እኔንም ፡ እዚሁ ፡ ሁኜ ፡ እንዳይ ፡
አዞኝ ፡ እንድጠብቅ ፡ እዚህ ፡ እንድቀመጥ
ሰው ፡የመጣ እንደሆን ምልክት እንድሰጥ
ስጠብቅ አንድ፡ ሰው፡ መብራት ይዞ መጣ
አፍጨሁ ፡ ጌታዬም ፡ ከመቃብር ፡ ወጣ ።
ሁለቱ ፡ ሲዋጉ ፡ ይኸው ፡ እዚህ ፡ ስፍራ ፡
ቶሎ ፡ ሮጬ ፡ ወጣሁ ፡ ዘበኛ ፡ ልጠራ ።

#መስፍን
አምነን ፡ ለመቀበል ፡ እኛ ፡ የቄሱን ፡ ቃል ፡
ተመልክቼዋለሁ ፥ ደብዳቤው ፡ ይበቃል ።
የፍቅራቸው ፡ ነገር ፡ የዡልዬትም ፡ መሞት
ይኸው ፡ ይነበባል ፡ በደብዳቤው ፡ ጽፎት
ሁሉንም ፡ ገልጦታል ፤ ከዡልዬትም ፡ ጋራ
ለመሞት መምጣቱን ይኸው እዚህ ስፍራ
መድኀኒት የሚሸጥ ድኻ ሰው ፡ አግኝቶ
መርዝ
👎1
፡ ይዞ ፡ እንደ መጣ በገንዘቡ ገዝቶ
ይኸው ፡ ተናግሮታል ፡ የሠራውን ፡ ሥራ ፤
ማስረጃው ፡ በቂ ፡ ነው ፡ ትክክል ፡ የጠራ
ካፑሌና ፡ ሞንታግ ፡ የት ናችሁ? አስተውሉ
የበቀልን ፡ ፍሬ ፡ ዛሬ ፡ ተቀበሉ ፡
እንሆ ፡ ይኸ ፡ ነው ፡ የቂማችሁ ፡ ዋጋ ፤
እዩት ፡ ይህን ፡ መዓት ፡ ይህንን ፡ አደጋ ፡
እግዚአብሔር ፡ አስቦ ፡ እናንተን ፡ ሊቀጣ ፡
እንዴት ፡ ያለ መቅሠፍት በኛ ላይ አመጣ
በኛ ፡ ላይ ፡ እላለሁ ፤ ምክንያቱም ፡ ዛሬ ፡
ይኸው ፡ ሁለተኛ ፡ ዘመዴን ፡ ቀብሬ ፡
እኔም ፡ ከናንተ ፡ ጋር ፡ ተቀጣሁ ፡ አብሬ ።
ዘላለም ፡ ቂመኞች ፡ የማትመከሩ ፡
ደም ፡ ለማፍሰስ ፡ ብቻ ፡ የምትጣጣሩ ፡
ፍቅርን ፡ የጠላችሁ ፡ ሆናችሁ ፡ ስትኖሩ ፡
ትልቅ ፡ ትምህርት ፡ ነው ፡ ብትመለከቱ ፡ .
ዛሬ ፡ ልጆቻችሁ ፡ ለፍቅር ፡ ሲሞቱ ።
ሌላ ፡ ልጅ ፡ የላችሁ ፡ አለነሱ ፡ በቀር ፤
ከዚህ ፡ በላይ ፡ ቅጣት ፡ መቼም ፡ አይፈጠር ።

#ካፑሌ
ይህ ፡ የወደቀብኝ ፡ የዛሬው ፡ ቅጣቴ ፡
ከሥጋዬ ፡ ዘልቆ ፡ ተሰማኝ ፡ ላጥንቴ ፡
ለኔ ፡ ሆኖ ፡ ሳለ ፡ የሚገባኝ ፡ ሞቱ ፡
ንጹኋ ፡ የኔ ፡ ልጅ ፡እንደዚህ ፡ በከንቱ ፡
ደሟን ፡ በኔ ፡ ክፋት መሬት ፡ ላይ ፡ አፍስሳ
መሥዋዕት ፡ ሆና ፡ ሞተች ፡ ለክፋቴ ፡ ካሳ
ሞንታግ ወንድሜ ሆይ በል እጅህን ስጠኝ፤
ይብቃን ' እንታረቅ ፡ በፍቅር ፡ ጨብጠኝ ።
(እጅ ፡ ለጅ ፡ ይጨባበጣሉ) ።
ደኅና ፡ አድርገን ከፈልን የኀጢአትን ዋጋ
እየው ሲያንገበግብ የእግዚአብሔር አለንጋ ፡
ክፉዎች ፡ ብንሆንበት እሱም ፡ ክፉ ፡ ሆኖ
ድብን፡ አደረገን ፡ ሳይራራ ፡ ጨክኖ ፡
በውነት ፡ ሆንኩ ዛሬ ፡ ዕርቅን የምሻ ፡ ሰው
በልጄ ፡ ንጹሕ ፡ ደም ፡ መሬት ፡ በፈሰሰው

#ሞንታግ
እኔም ፡ ለዡልዬት ፡ ይኸው ፡ በዚህ ፡ ስፍራ
ሐውልት ፡ አቆማለሁ ፡ በወርቅ ፡ የተሠራ :
ዜናዋ ፡ እንደ ፡ ወርቅ ፡ ያማረ ፡ ነውና ፤
ዘለዓለም ፡ እንዲኖር ፡ ስሟ' በቬሮና ፡
ከልብ ፡ ለሆነ ፡ ለእውነተኛ ፡ ፍቅር ፡
ምሳሌ ፡ ይሆናል ፡ አብነት ፡ ምስክር ።

#መስፍኑ
ተመልከቱት ፡ ፊቷን ፡ የዛሬ ፡ ጧት ፡ ፀሓይ
ደመና ፡ ለብሳለች ፡ ውበቷ ፡ እንዳይታይ ፤
ሆናለች ፡ ከሰው ፡ ጋር ፡ ሐዘኑን ፡ ተካፋይ ።
በሉ ፡ ሁላችሁም ፡ ሥራችሁን ፡ ሥሩ ፤
ሐዘን ፡ ያለው ፡ ያልቅስ ፡ ሙታን ፡ ይቀብሩ፡
እንደ ፡ ሙታን ፡ ሁሉ ፡ እኛን ፡ በሙቅጣቱ ፡
ነፍሳቸውን ፡ ያድን ፡ እግዜር ፡ በምሕረቱ ፡
መቼም ፡ መቼም ፡ቢሆን ታይቶ ፡ አያውቅና
እንደ ፡ እነዚህ ፡ ልጆች ፡ የሚያሳዝን ፡ ዜና

💫ተፈፀመ💫

ለደራሲው ዊሊያም ሼክስፒር ለትርጉሙ ከበደ ሚካኤል አመሰግናለው።

እንደተለመደው አስተያየታችሁን በ @atronosebot አድርሱን ትላንት በተጠናቀቀው #ህመም_ያዘለ_ፍቅር ላይ የሰጣችሁት አስተያየት ደርሶኛል በጣም ብዙ ነው ለሁሉም መመለስ አዳጋች ሆኖብኛል ግን ለሁላችሁም። እጅግ እጅግ አመሰግናለው 🙏