ዐውደ ምሕረት
3.69K subscribers
929 photos
24 videos
271 files
191 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
" #ካለ_ፈጣሪ_አሟጠሽ ጋግሪ"
______________________
ስስት ንፍገት ፣ሆዳምነትን፣ ኑሮዬ ይበቃኛል አለማለትን እንዲሁም አልጠግብ ባይነትን የሚገልጽ ግሥ ነው ። (የመ.ቅዱስ መዝገበ ቃላት/ ገጽ ፹ ፭ ) በዘመናች ቋንቋ "ቋጣሪነት" ልንለው እንችላለን። በንባባችን ላይ ቋጣሪነት ወይም ስስታምነት ከሰው ልጅ ውድቀት በኋላ የመጣ ነገር እንጂ በሰው ተፈጥሮ ውስጥ "ስስት" ወይም "ንፍገት" የሚባል ነገር የለም ። የስስት ተቃራኒ ቸርነት ነው ። ቸር ደግሞ #እግዚአብሔር ብቻ ነው። ሌሎች ቸር ቢሆኑ #ከእግዚአብሔር የተቀበሉን በመስጠት ነው እንጂ የእራሳቸው አንዳች የላቸውም ቸርነትን ለሌላው ቢያደርጉ በሥጋ የሕሊና ሰላም ፣በሃይማኖት ደግሞ ጽድቅን ፈልገውበት ነው ።

#እግዚአብሔር ቸር ቢሆን ግን እጸድቅበት አይል ነገር ጻድቅ ነው እከብርበት አይል ነገርም ክቡር ነው ስለዚህ ቸርነት ማንም ያልሰጠው ማንምም የማይነጥቀው የእግዚአብሔር የባሕሪው ገንዘቡ ነው:: “ #ከአንዱ_ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም።” ሉቃ ፲ ፰ ፥፲ ፱

ይህን ያልተገነዘበው ዲያቢሎስ እሩቅ ብዕሲ (ተራ ሰው) መስሎት አርባ ቀን በገዳመ ቆሮንቶስ ጾሞ ሲወጣ መራቡን ዐይቶ ቸሩ መድኃኔዓለምን በስስት ሊፈትነው ቀረበ ። በኮሮጆም ትኩስ የሚሸት ዳቦ ይዞ "የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንክ ይህን ድንጋይ ዳቦ እንዲሆን እዘዝ " አለው :: #ማቴ ፬÷፫

#ቸሩ_መድኃኔ_ዓለምም ማንነቴን ላሳየው፤ ሁሉን ቻይነቴን ይወቅልኝ ሳይል ዲያቢሎስ እንዳለው ድንጋዮን ዳቦ ሳያደርግ "ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም " ተብሎ ተጽፏል ብሎ " #በትዕግስት" ድል ነሳው። #ማቴ ፬÷፬

በበርሃ የሚኖሩ መነኮሳት ፆራቸው ስስት ነው ፤ በፈለጉ ጊዜ ምግባቸውን አያገኙምና ‹‹ ያለችን ብንመፀውት ሰውን ብናበላ ያለችን ታልቅብናለች ከዚያ ምን እንበላለን›› እያሉ በስስት ብዙውን ይፈተናሉ፡፡ ስለዚህ ቸሩ ፈጣሪያቸን ይህን የስስት ፈተና እንዴት በትዕግሥት ድል ማድረግ እንደሚችሉ ሲያስተምራቸው በመነኮሳት ቦታ በበርሃ ተገኝቶ ዲያቢሎስን በትዕግስ "ሰው በእጀራ ብቻ አይኖርም" ብሎ ድል አደረገው፡፡

#በስስት የመጣብንን ፈተና በትግሥትና በቸርነት ለንሻገረው ያስፈልጋል ያ ሲባል ግን ቁጠባንና ባህሉን ለመሸርሸር ሳይሆን የመቀበል ግልብጥ ስሌት መስጠት እንደሆነ ጭምር ለማስታወስ ነው ። ሁለት ነገር ያለው ሰው ሌላ ሦስተኛ ነገር ከፈጣሪው ከፈለገ ከያዘው ሁለት ነገር ቢያንስ አንዱን እንኳ ምንም ለሌለው መስጠት ይገባዋል :: ለመቀበልምኮ መስጠት ያስፈልጋል! ሰው ሁለት እጅ የተሰጠው በአንዱ ተቀብሎ በሌላኛው እንዲያቀብል ነው እንዲሉ አበው።


“ለድሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፥ በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል።” #ምሳሌ ፲ ፱ ፥፲ ፯ “ኀጥእ ቀኑን ሁሉ ምኞትን ይመኛል፤ ጻድቅ ግን ይሰጣል፥ አይሰስትም።” #ምሳሌ ፳ ፩ ፥ ፳ ፮ ስለዚህም በክርስቶስ እኖራለሁ የሚል ክርስቶስ ደግሞ እንደተመላለስ ይመላለስ ! ጸሎቱም ሁል ጊዜ “ልቤን ወደ ምስክርህ አዘንብል፥ ወደ ስስትም አይሁን።” የሚል ይሁን ! #መዝ ፻ ፲ ፰ (፻ ፲ ፱) ፥ ፴ ፮
......... ይቆየን..........
አ.አ ኢትዮጵያ
ተክለ ኤል ኃ/ማርያም
መጋቢት ፬ ቀን /፳ ፻ ፲ ፫ ዓ.ም
#እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል ”
________________________________
#ያዕ ፬ ፥ ፮
#፩ጴጥ ፭ ÷ ፭

ትዕቢት ከሦስቱ (አርስተ/ ርዕሰ ኃጥዐው) መካከል አንዱ ነው:: ሦስቱ ርዕሰ ኃጥዐው የሚባሉት ስስት ፣ትዕቢትና ፍቅረ ነዋይ ናቸው።

#ስስት፣ ትዕቢትና ፍቅረ ነዋይ የኃጢያት ሁሉ እራሶች ፣ አለቆች ና አውራዎች መባላቸው ኃጢያት ሁሉ ከእነዚህ ስለሚመነጭ ነው።

ዲያቢሎስ መንፈሳዊ ሰውን የሚፈትነው በሦስቱ የፈተና ዐይነቶች ነው በስስት፣ በትዕቢትና በፍቅረ ነዋይ ፤ ሌሎች የኃጢያት ዐይነቶች የነዚህ የሦስቱ ጭፍሮች ወይም ተከታዮች ናቸው።

#ለምሳሌ የትዕቢት መንፈስ የተጠናወተው አንድ ሰው እኔ ከማን አንሳለሁ የሚል የበታችነት ስሜት ውስጥ በመግባት ለግድያ ፣ለስርቆት፣ ብሎም ለዝሙት ኃጢያቶች ተጋላጭ ይሆናል።
ትዕቢት የዲያቢሎስ ልዮ መገለጫው ነው ስለሆነም ዲያቢሎስ ስለ ግብሩ ( ስለ ሥራው) ትዕቢተኛ ብቻ ሳይሆን እራሱ ትዕቢት እየተባለ ይጠራል። ለዚህ ነው ሐዋርያው እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል" ካለ በኋላ " እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፤ " ሲል ትዕቢተኞች ብሎ በተውላጠ ስም የጠራቸውን ዲያቢሎስና ጭፍሮቹን አስከትሎ ደግሞ "ዲያቢሎስን" ብሎ በግልጥ የተናገረው #ያዕ ፬÷፮ - ፯
#ለዚህ ትልቁ ማሳያ የገዳመ ቆሮንቶስ ሁለተኛ ፈተና ትዕቢት የተሞላበት መሆኑ ነው "ዲያብሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወሰደውና (ወሰደው ሲል በፍቃዱ ሄደለት ለማለት እንጂ ለዲያቢሎስስ ታዛዢ ሆኖ አይደለም) እርሱን በመቅደስ ጫፍ ላይ አቁሞ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ወደ ታች ራስህን ወርውር አለው። “ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል" ብሎ የትዕቢትን ፈተና በትሕትና ድል ነሳው ። የካህናት ፆራቸው ትዕቢት ነው ፤‹ ‹ እኛ አእምሮአችን ረቂቅ ማዕረጋችን ምጡቅ ›› እያሉ በትዕቢት ይፈተናሉ፡፡ ዲያብሎስ በካህናት ቦታ በቤተመቅደስ በትዕቢት ቢመጣበት በትህትና ድል አድርጎላቸዋል፡፡ #የትዕቢትን ፈተና ማሸነፍ የሚቻለው በትሕትና ብቻ ነው! #ማቴ ፬÷ ፭- ፰ .

“ከእኔም_ተማሩ_እኔ_የዋህ_በልቤም_ትሑት_ነኝና"
#ማቴ ፲ ፩ ፥ ፳ ፱

አ.አ ኢትዮጵያ
ተክለ ኤል ኃ/ማርያም
መጋቢት ፬ ቀን /፳ ፻ ፲ ፫ ዓ.ም
" #ዕለት_ሳበችው_ምሕረትም_ጠቀሰችው"
_______________________________
#አባታችን_ሁልጊዜ እንዲህ ይሉ ነበር። ‹‹የሚጣፍጥ ምግብን መውደድ ኃጢአትን
ያመጣል፣ሞትን ያስከትላል፡፡ ክንፍ ያላቸው የሰማይ ወፎች እንኳን በመብል ምክንያት
ይጠመዳሉ፣ ምግብ በመሻት ከምድር ላይ ይወድቃሉ በወጥመድም ይያዛሉ፡፡የሰው ልጅም
ምግብን በመውደድ በኃጢአት ይወድቃልና እኔስ ለሰውነቴ ምግብ መጠጥን
አልፈልግም፤ልብስም አልሻም ዕራቁቴን ከእናቴ ማኅፀን እንደወጣሁ እንዲሁ ዕረቁቴን ወደ
መቃብር እመለሳለሁ እንጂ፡፡ከዚህ ከኃላፊው ዓለም በሞት በተለየሁ ጊዜ መብል
መጠጥንና ልብስን ማን ያስከትልልኛል?›› አሉ። ዳግመኛም‹‹ሰው:ሊደርስበ
ማይችልበት:በረሃ:እኖራለሁ፣ ነጣቂ ተኩላዎችና አራዊቶች ባሉበት እነርሱ እንዲበሉኝ
ሥጋዬን እጥላለሁ፤ ዳዊት በመዝሙር ‹የጻድቃን ሥጋቸው ለዱር አራዊት ነው› እንዳለ እኔ
ክፉ አውሬዎች፣ ተናዳፊ እባቦችና ዘንዶዎች ወዳሉበት እገባለሁ ምግብም እሆናቸው ዘንድ
እወዳለሁ››በማለት አባታችን ራሳቸውን ለሞት አሳልፈው ይሰጡ ነበር ነገር ግን አራዊቱ
ሁሉ እየሰገዱላቸው ይገዙላቸው ከእግራቸውም በታች ይተኙ ነበር፡፡ እንደሚታዘዝ ደቀ
መዝሙርም ይታዙላቸው ነበር፤ለጸሎትም በሚቆሙበት ጊዜ አብረዋቸው ይቆማሉ፡፡
በፊታቸውም ይጫወታሉ፡፡
#በመጨረሻም ዕለት ሳበችሁ ምሕረትም ጠቀሰችሁ ለሞትም የሚያበቃ ጽኑ ሕማም
ታመመ የሚጠጋበት የዛፍ ጥላ በሌለበት እንደ አንበሳ በበርሃ ወደቀ ለጸሎት ከቆመበት
ጊዜ አንስቶ እስከ ሞተበት ቀን ድረስ እጆቹን በትምህርተ መስቀል እንዳማተበ ነበር ። ብዙ
ግሁሳንም ወደ እርሱ መጡ #እግዚአብሔር አምላክም ብዙ የብዙ ብዙ መላእክትን
አስከትሎ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምን አስቀድሞ ዳዊትንም በገና አስይዞ ተገለጠና
ነብሱን አክብሮ ተቀበላት፣ሳማት፣ ደስታውንም መላት መላእክትም ከዳዊት ጋር "ክቡር ሞቱ
ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር " የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው" እያሉ
በአንድነት ዘመሩለት #መዝ ፻ ፲ ፭ {፻ ፲ ፮ }÷፲ ፭
#እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ
እናውቃለን።”
#ሮሜ ፰ ፥፳ ፰
አ.አ ኢትዮጵያ
ተክለ ኤል ኃ/ማርያም
መጋቢት ፭ ቀን ፳ ፻ ፲ ፫ ዓ.ም
" ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ !"
________________________________
#ማቴ ፬÷፱
#ንግግሩ_ብዙ_ጊዜ ዲያቢሎስና የግብር ልጆቹ ሰዎችን በፍቅረ ነዋይ ሊጥሉ
ከሃይማኖትም መንገድ ሊያስወጡ ሲፈልጉ የሚናገሩት የተንኮል ንግግር ነው። የሚሰጥ
መስፈርት ወይም ቅድመ ሆኔታ አያስቀምጥም ዝም ብሎ በፍቅር ይሰጣል ተንኮለኞች ግን
ለተንኮል ይሰጣሉ ። #እግዚአብሔር ቸር ሰጪ ነው ሲሰጥም የሰገደልኝ ያልሰገደልኝ
ያመነኝ ያላመነኝ አይልም ያመነው ይበልጡኑ ያተርፍበታል ያላመነው በሥራው ይከሥርበታል
እንጂ አያስገድደውም ።“ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና
በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና።” #ማቴ ፭ ፥ ፵፬-፵ ፭
ከፍቅረ ነዋይ የተነሳ ብዙዎች " ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ" ለሚላቸው አካል ልቡናቸው ክፍት
ነው። ዲያቢሎስም ይህን ስለሚያውቅ በብዙ ይፈትናቸዋል ስለዚህ እግሮቻቸውን " ይህን
ሁሉ እሰጥሃለሁ " ወደሚል ወደ ጠንቋይ ቤት ያነሳሉ በእውነቱ ግን ጠንቋይ ሁሉን
ሊሰጣቸው ቀርቶ ያላቸውንም አራቁቶ ባዶ ያስቀራቸዋል። ጠንቋይ ማለት ጠንቀ ነዋይ
ማለት ነውና። የንጽሕ ገንዘብ ምንጭ አይደለም ሰርቶ ባለ ፀጋ መሆን ይቻላል!
አያስኮንንም። ሰርቆ መክበር ግን ያዋርዳል።
ብዙ ጊዜ ባለ ጸጎች # ከእግዚአብሔር መንግሥ የራቁ ናቸው። ለዚህም ነው " ለባለ ጸጋ
መንግሥተ ሰማያት መግባት ጭንቅ ይሆንበታል፤ ባለ ጸጋ መንግሥተ ሰማያት ከሚገባ
ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብትሾልክ ይቀላል "ተብሎ የተነገረው #ማቴ ፲ ፱÷፳ ፫
ዲያቢሎስ በጠንቋይ እያደረ " ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ" ያለንን ሁሉ ያሳጣናል በዚህ የፍቅረ
ነዋይ ፈተና #እግዚአብሔር ሁሉ ሳይቀር ይህን "ሁሉ እሰጥሀለሁ " ብሎ ለመፈተን
ሞክሯል። ግን አልተሳካለትም # እግዚአብሔር ሰጪ እንጂ ተቀባይ አይደለምና በዚህም
ፈተና ተፈተነ ሲባል ሰይጣን የእግዚአብሔር የሚፈትነው ሆኖ አይደለም ወደ ፊት ለሚነሱ
ጾሚ ተአራሚዎች እንዴት ድል እንደሚያደርጉት ድል ማድረጌያውን ሊያስተምራቸው ወዶ
ነው እንጂ።
# እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፥ የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም
አሳይቶ ብትሰግድልኝ እጅ ብትነሣኝም ይህን ሁሉ እሰጥሀለሁ " አለው፡፡” #ማቴ ፬ ÷ ፰
ወሰደው ”ሲባል፡- ሰይጣን ጌታችንን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚወስድ
የሚያመጣው ሆኖ ሳይሆን ‹‹ ነገሥታቱን ድል በምንነሣበት በተራራ ቢሆን መች ድል ይነሳኝ
ነበር›› ብሎ አስቧልና ነው ፡፡ (ነገሥታት በተራራ ቤተ መንግስታቸውን ይሠራሉና) አሁንም
ምክንያት ለማሳጣት ከረጅም ተራራ በራሱ ፍቃድ ወጥቷልና “ወሰደው ” ተባለ፡፡ ሰይጣን
ሳያፍርና ሳይፈራ “ብትሰግድልኝ እጅም ብትነሣኝ ይህን ሁሉ እሰጥሀለሁ” ብሎ ብዙዎችን
ድል ባረገበት በፍቅረ ነዋይ የመጨረሻ ፈተናውን አቀረበ፡፡
በእውነቱ ከሆነ ዛሬ በዚህ ፈተና ያልተሸነፈ የለም፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ሁሉም ጦርነቶች
ሌላምክንያት ቢሰጣቸውም ዋናው ምክንያታቸው የኢኮኖሚ ፉክክር ፣የከበርቴነት ውድድር
ፍቅረ ነዋይ ነው፡፡ዘፈኑ፤ዝሙቱ፤ሥርቆቱም ምንጫቸው ፍቅረ ነዋይ ነው፡፡
ባለ ሽቶዋ ማርያም የአልባስጥሮሽ ሽቶ ይዛ መታ የጌታዋን እግር በትቀባ ገንዘብ ወዳዱ
ይሁዳ አልተዋጠለትም "ይህ ሦስት መቶ ዲናር የሚያወጣ ውድ ሽቶ ነው ተሽጦ ለድሆች
በተሰጠ ይሻል ነበር ብሎ ተናገረ፤ ሽቶው ከተሸጠ ከሦስቱ አስር አስር እጅ ማለትም ሰላሳ
የሚጠዱ ዲናሮችን በቀረጥ መልክ ይሰበስብ ነበርና ነው እንጂ ለድሆችሽ ተጨንቆላቸው
አልነበረም እንዲያውም መጻሕፍ " ሌባ "ስለ ነበር ነው ብሎ ይገልጠዋል። ጌታችን
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቀጥሎ ሽቶ ስለቀባችኝ ይህችን ሴት ስለምን
ታደክሟታላችሁ? ድሆችስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው ባሻችሁ ጊዜ መልካም
ልታደርጉላቸው ትችላላችሁ አለ።
# ይሁዳ ሠላሳዋን ብር ስላጣ ተቆጨ በዚህም ሰይጣን በልቡ ገባበት ሠላሳውንም ብር
ጌታውን ሽጦ ያገኛት ዘንድ ሰይጣን ልቡን አጸናው ። በመጨረሻም በገንዘብ ፍቅር ታውሮ
ነበርና ወደር ስለማይገኝለት ፍቅሩ ክህደትን ከፈለው ። የሚገርመው ይሁዳን ገንዘብ
መውደደ የሚያውቅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እሱ ሌባ ነው ሳይል የሐዋርያት ገንዘብ ያዢ
አድርጎ ሁሉ ሾሞት ነበር ። ይህ ሁሉ ግን የይሁዳን ድንጋይ ልብ ሊሰብረው አልቻለም።
ፍቅረ ነዋይ እንዲህ ነው!
ብዙዎቻች በዚህ ፈተና ውስጥ እንገኛለን ገንዘብ ከመውደዳችን የተነሳ አስራቱን በአግባቡ
ባለማውጣት ከእግዚአብሔር እንኳን ሳይቀር ሰርቀናል “ሰው # እግዚአብሔርን ይሰርቃልን?
እናንተ ግን እኔን ሰርቃችኋል። እናንተም፦ የሰረቅንህ በምንድር ነው? ብላችኋል።
በአሥራትና በበኵራት ነው።” # ሚልክያስ ፫፥፰
# ጌታችን_አምላካችን_መድኀኒታችን_ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ይሄን ሁሉን ተንኮሉን
ያውቃልና “ብትሰግድልኝ ይሄን ሁሉ እሰጥሃለሁ” ብሎ በፍቅረ ነዋይ የፈተነውን ሰይጣን
“አንተ ሰይጣን ከአጠገቤ ሒድ ፤ ለጌታ ለእግዚአብሔር ስገድ እርሱን ብቻ አምልክ ተብሎ
ተፅፏልና ” ብሎ በጸሊአ ነዋይድል አድርጎታል፡፡
.“አንተ ሠይጣን ከአጠገቤ ሒድ”፡- ሲለው እግዚአብሔር አምላክ የሌለበት ቦታ ኖሮ
ወደዚያ ሂድ ያለው አይደለም፡፡ይልቁንም “ ከእኔ በኃላ ከሚነሱ ከኦርቶዶክሳዊያን ልቦና
ሒድ ሲለው” እንጂ # ማቴ. ፲፮፥፳፫፡፡ በእውነት በፍቅረ ነዋይ የሚፈታተነንን ሰይጣን
ዲያቢሎስን ከልቦናችን አርቆ ያስቀርልን “ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ባርያ ማንም
የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላልና ሁለተኛውንም ይወዳል፥ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል
ሁለተኛውንም ይንቃል። # ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።” ተብሏልና
ገዘብን ከመውደድ እግዚአብሔር መውደድን አብዝቶ ያድለን ገንዘብን መውደድ (ፍቅረ
ነዋይን) እንዴት መተው እንችላለን ቢሉ አላፊነቱን፣ ከእግዚአብሔር መንግስት መለየቱንና
የጥፋት ሁሉ ሥር መሆኑን ዕለት ዕለት በማሰብ ጸላሄ ነዋይ መሆን ይቻላል ይህ ለመንፈሳዊ
ሰው ቀላል ነው በገዳመ ቆሮንቶስ ያስተማረን ይህንኑ ነው!
ለሀገራችንና ለዓለማችንም ሠላሙን ይስጥልን # ሉቃስ ፲ ፮ ፥ ፲ ፫
.......ይቆየን.......
ግብሐት:- መጻሕፍ ቅዱስ
ወንጌል ትርጓሜ
መቅረዘ ተዋሕዶ
አ.አ ኢትዮጵያ
ተክለ ኤል ኃ/ማርያም
መጋቢት ፯ ቀን /፳ ፻ ፲ ፫ ዓ.ም
#ዛቲ_ዕለት_ቅድስት_ይዕቲ
(ይህቺ ቀን የተቀደሰች ናት)
*****************************
#ቅድስት_ማለት የተለየች የጸናች ክብርት ማለት ነው:: ቤተ ክርስቲያንም በዚህ በዐብይ ጾም ሁለተኛውን ሳምንት ቅድስ ብላ በመሰየም የሰንበትን ቅድስና ታስባለች ::
ሰንበትን ቅድስት ያሰኛት ምንድነው?
_________________________
ፈጣሪ ዓለማት ልዑል እግዚአብሔር በሰድስቱ ዕለታት ፍጥረታትን ከፈጠረ በኃላ በሰባተኛው ዕለት ከሰራው ሥራ ሁሉ አረፈ "ለሙሴም የሰንበትን ቀን ትቀድሳት ዘንድ አሰብ "የምትለውን ትዕዛዝ ሰጠ ስለዚህ ሰንበትን ቅድስት ያሰኛት ከስራ ሁሉ የሚታረፍባት ሕመምተኛ የሚጠየቅባት ወደ ቤተ እግዚአብሔር የሚገሰገስባት ቀን በመሆኗ ነው ::
በግብራቸው የተነሳ ዕረፍት እየተባሉ የሚጠሩ
***********************************
1) (ሰንበት ክርስቲያን )ዕለት እሁድ :- ዕረፍት ተብላ ትጠራለች: ዕለተ እሁድ በሌላ ስሟ ሰንበተ ክርስቲያንም ተብላ ትጠራለች :: አንዳንድ ጊዜ ሰንበት እሁድ ከሆነች ቅዳሜ ታድያ ምንድነች??? ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል :: አስቀድሞ ዕለተ ቅዳሜ የአይሁድ ሰንበት ነበረች ጌታችንም እንደተናገረው ሕግ ና ነቢያትን ልፈጽም እንጂ ልሽራቸው አልመጣውም እንዳለ የአይሁድ ሰንበት ቅዳሜም አልተሻረችም ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ቀዳዊት ሰንበት የቀደመች ሰንበት ብላ ታስባታለችች :: ማቴ5÷17 አንድም ደግሞ የኦሪት ሥርዓቶች ሁሉ ለአዲስ ኪዳን ሥርዓቶች ምሳሌ ጥላ መርገፍ ናቸውና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ቅዳሜን እንደ ምሳሌ አድርጋ እሁድን አማናዊት ሰንበት አድርጋ ታስባቸዋለች ::
ዕለተ እሁድ( ሰንበተ ክርስቲያን)
*ጥንተ ዕለት ናት :- ፍጥረታት መፈጠር የጀመሩባት ዕለት ናትና "ይህቺ ዕለት ከ7ቱ ዕለታት ቀድማ የተገኘች ናት እንጂ በኃላ የተገኘች አይደለችም " እንዳለ ቅዱስ አትናቲዮስ በኩረ በዓላት ናት :-
* #የበዓላት ሁሉ መጀመሪያ ናትና ዓለም የተገኘባት
* #ወልድ ሰው የሆነባት
* # ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተነሳባት
* #ዳግመኛ ለፍርድ የሚመጣበት ዕለት ጭምር ናት::
2) #እመቤታችን ዕረፍት ተብላ ትጠራለች
____________________________

ከ5500 ዘመን የድካም የመከራ ጊዜ ሁሉ በእርሷ እረፍትን አግኝተናልና :: እንዴት ቢሉ መላእኩ ቅዱስ ገብርኤል መጥቶ ባበሰራት ጊዜ ለዓለም መዳን ምክንያት ትሆኚ ዘንድ መርጦሻል ብሎ ፍቃዷን በጠየቀ ጊዜ "ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ "እነሆኝ የጌታ ባርያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ" በማለት ለድኅነተ ዓለም ምክንያት እረፍት ሆናለች:: #ሉቃ 1÷26
3) #ቅዱሳን :- እረፍት ተብለው ይጠራሉ::ቅዱሳን በሳኦል መንፈስ ለተያዘችው ደካማዋ ዓለም እረፍት ናቸው " እንዲህም ሆነ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ መንፈስ በሳኦል ላይ በሆነ ጊዜ ዳዊት በገና ይዞ በእጁ ይመታ ነበር፤ ሳኦልንም ደስ ያሰኘው ያሳርፈውም ነበር፥ ክፉ መንፈስም ከእርሱ ይርቅ ነበር። (መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 16÷23) አንድም ጻድቃን በጸሎታቸው ሕዝብ የሚያሳርፉሁ ናቸው ጻድቃንም በበዙ ጊዜ ሕዝብ ደስ ይለዋልና በመወለዳቸውም ብዙዎች ደስ ተሰኝተዋልና ምሳ 29÷2 ሉቃ 1÷14 ያዕ 5÷16
4) #ቅድስት_ቤተ ክርስቲያን እረፍት ትባላለች :-
__________________________________
ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት እግዚአብሔር እረኛዬ ነው የሚያሳጣኝም የለም በለመለመ መስክ ያሰማራኛል በእረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል " ብሎ ቤተ እግዚአብሔርን እንደ እረፍት ሥፍራ በውስጧ የሚፈሰውን ቃለ እግዚአብሔርን ደግሞ እንደ መብል እንደ መጠጥ አድርጎ ተናግሯል:: መዝ 22(23)÷1 አንድም የእረፍት ቦታ የሆነችው የመንግስተ ሰማያት የሰማያዊት ኢየሩሳሌም ምሳሌ ናትና ዕረፍት ተብላ ትጠራለች ::
5) #መንግሥተ ሰማያት ራሷ እረፍት ትባላለች
_______________________________
እስራኤል ዘሥጋ ድካም ከበዛባት ከምድረ ግብጽ ወተው እረፍት የሆነችውን ምድረ ከንዓንን ወረሰዋል እኛም እስራኤል ዘነፍሶች ከዚህች ድካም ከበዛባት ዓለም እረፍት የምናገኘው በመንግስተ ሰማያት ነውና መንግስተ ሰማያት እረፍት ትባላለች :: " ነገር ግን። ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንድተጻፈ፥ እንዲህ እንናገራለን።" (1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2:9)
6) #ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ዕረፍት ይባላል :-
___________________________________
" እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።" ብሏልና ዕረፍታችን ነው (የማቴዎስ ወንጌል 11:28) አንድም የእግዚአብሔር መንግስት(የዕረፍት ሥፍራ) ከወድየት አለች ብለው በጠየቁት ጊዜ " ደግሞም። እንኋት በዚህ ወይም። እንኋት በዚያ አይሉአትም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና አላቸው።" (የሉቃስ ወንጌል 17:21) ይህን ያለው በመካከላቸው የነበረው እርሱ መንግስተ ሰማያት የእረፍት ሥፍራ ወይም እረፍታችን በመሆኑ ነው ::
ስለዚህ እኛ ክርስቲያኖች የሰንበትን ቅድስና ስናስብ እግዚአብሔርን እመቤታችንን ቅዱሳንን መንግስተ ሰማያትን ሁሉ ታሳቢ ማድረግ ይገባናል ማለት ነው::
#የግርጌ_ማስታወሻ
++++++++++++++
እረፍትን ለማግኘት አስቀድሞ ሥራ ሊኖር ይገባል ሥራ በሌለበት እረፍት የለም:: እንድ ሰው አረፈ ለማለት አስቀድሞ ሥራ ሰራ ሊባል ይገባዋል:: እግዚአብሔርም ከሰራው ሥራ ሁለ አረፈ ተብሎ ተጻፈ እንጂ አረፈ ተብሎ ብቻ አልተጻፈልንም በመሆኑም እኛ ክርስቲያኖች እረፍተ መንግስተ ሰማያትን እረፍት እግዚአብሔርን እረፍት እመቤታችንን እረፍት ቅዱሳንን ለማግኘት በጎ ሥራን ሁሉ ልንሰራ ያስፈልጋል :: አንድ ሊቅ በሰንበት አንድ ሥራ ሲሰሩ የኔ ቢጤ ጨዋ መቶ ምነው አባ እግዚአብሔር እንኳን ባረፈበት ቀን በሰንበት ለምን ሥራ ይሰራሉ አላቸው ሊቁም ፈገግ ብለው አዮትና ልጄ እርሱ ኮ ያረፈው ሥራውን ሁሉ ጨርሶ ነው እኔ ምን ሰርቼ ነው የማርፈው አሉት ይባላል :: በሰንበት ለሰንበት የሚገባ ሥራ ልንሰራበት ይገባል እንጂ ሥራ ፈተን መቀመጥ አይገባንም ሥራ የፈታ አህምሮ የሰይጣን ቢሮ ነውና ያለ ሥራ የተቀመጠ ሰው ሊስት ሊሳሳት ይችላል::
በሰንበት ዝም ብሎ ከመቀመጥ ወደ ቤተ እግዚአብሔር መሄድ የታመመ ካለ መጠየቅ መጸለይ ሌላም ሌላም የትሩፋት ሥራ ልንሰራ ይገባል :: ይህን ካደረግን ቅድስት ከሆነችው ከሰንበት ረድኤትና በረከትን እናገኛለን::
.........ይቆየን...........
አ.አ ኢትዮጵያ
ተክለ ኤል ኃ /ማርያም
የካቲት 12/2010 ዓም
#እንደ_ልማዱም_በሰንበት_ቀን_ወደ_ምኵራብ_ገባ__ሊያነብም_ተነሣ
#ሉቃ ፬ ÷ ፲ ፮

ምኩራብ የአይሁድ የጸሎት ሥፍራ መጠሪያ ነው። የአይሁድ አምልኮ በኢየሩሳሌም ባለ ቤተ መቅደስ ሥርዓት የሚፈጸም ነበር ናቡ ከደነጹር ቤተ መቅደሱን ካፈረሰ እና ሕዝቡንም ካፈለሰ በኃላ ግን አይሁድ በየደረሱበት " #ምኩራብ" እየሰሩ ጸሎትና ትምህርት እንዲሁም ሌሎች የአምልኮ ሥርዓቶችን ያስቀጥሉ ጀምረዋል። አሥር የጎለመሱ ወንዶች ሲገኙ ምኩራብ መሥራት ይፈቀድላቸዋል ቤቱም ወይም ምኩራቡም ትንሽ ወይም ትልቅ ሊሆን ይችላል።/የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃል ገጽ ፷ /

#ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመንፈስ ኃይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ስለ እርሱም በዙሪያው ባለችው አገር ሁሉ ዝና ወጣ። እርሱም በምኵራባቸው ሲያስተምር፥ ሁሉም ያመሰግኑት ነበር።

ይህ ምኩራብ እየተባለ የሚጠራው የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት በነብዩ በኢሳይያስ እንደተጻፈ ጌታ በአይሁድ ምኩራብ ገብቶ መጽሐፍ እንዲሰጡት ጠይቆ የሚሰሙት ቃል ዛሬ በጆሯቸው እንደተፈጸመ እንዲህ ሲል እንደ ነገራቸው ይዘከርበታል፦

ወዳደገበትም ወደ ናዝሬት መጣ፤ #እንደ_ልማዱም_በሰንበት_ቀን_ወደ_ምኵራብ_ገባ__ሊያነብም_ተነሣ። የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሰጡት፥ መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ። የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ። መጽሐፉንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ ሰጠውና
ተቀመጠ፤ በምኵራብም የነበሩት ሁሉ ትኵር ብለው ይመለከቱት ነበር። እርሱም። ዛሬ ይህ መጽሐፍ በጆሮአችሁ ተፈጸመ ይላቸው ጀመር።

#ሁሉም_ይመሰክሩለት ነበር ከአፉም ከሚወጣው ቃል የተነሣ እየተደነቁም ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን? ይሉ ነበር። እርሱም፦ ያለ ጥርጥር ይህን ምሳሌ። ባለ መድኃኒት ሆይ፥ ራስህን ፈውስ፤ በቅፍርናሆም እንዳደረግኸው የሰማነውን ሁሉ በዚህ በገዛ አገርህ ደግሞ አድርግ ትሉኛላችሁ አላቸው። #ሉቃ.፬÷፲ ፬ -፳ ፫

ሳምንቱ ምኩራብ ተብሎ የተሰየመበት ሌላው ምክንያት በዚሁ ዕለት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ከዋዜማው ጀምሮ እስከ ሰላሙ ድረስ በዕለተ ሰንበት « #ቦአ_ኢየሱስ_ምኩራበ_አይሁድ » «ኢየሱስ በሰንበት ቀን ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ» እያለ ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ ምኩራብ ማስተማሩን እየጠቃቀሰና እያነሣሣ ስለሚዘምር ይህን ሰንበት ለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኩራብ እየገባ ለማስተማሩና በምኩራብ የሚሸጡ የሚለውጡ ነጋዴዎችን ጅራፍ ጀርፎ አንድም ከሐዋርያቱም ተቀብሎ ይላል ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች እናንተ ግን የወንበዴዎች መናህሪያ አደረጋችኋት" ብሎ እየገረፈ ከመቅደስ እዳባረራቸው ገበቴያቸውምን እንደ ገለበጠ ገብያቸውንም እንደፈታባቸው የሚሰበክበት የሚተረክበት ሳምንት ጭምር በመሆኑ ነው ፡፡ #ማቴ ፳ ፩ ፥ ፲ ፪-፲ ፫ ተጠቅሷል፡፡ “ሰንበታቴን ጠብቁ፥ መቅደሴንም ፍሩ፤ #እኔ_እግዚአብሔር ነኝ።” እንዳለ መጻሕፍ #ኦ.ዘሌ ፳ ፮ ፥ ፪.
#ጌታችን_መድኃኔታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በምድር ሲመላለስ ከዚህ ቀደም በምኩራቦቻቸው ተሰምቶ የማይታወቅ የወንጌል ትምህርት እንዳስተማራቸውና ዕውራን እንዲያዩ፤ ደንቆሮዎች እንዲሰሙ፤ ዲዳዎች እንዲናገሩ በማድረግ እንዲሁም ደግሞ ሙታንን በማሥነሳት የተለያዩ ድንቅ ተአምራቶችን በማድረግ የወንጌልን ኃይል ስለማሳየቱ ይተረክበታል።

"እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ (የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና) #መዝ ፷ ፰ ( ፷ ፱ )፥ ፱ ተብሎ እንደተጻፈ ሕገ እግዚአብሔር እንዲፈጸም፤ ሕገ ቤተ ክርስቲያን እንዳይፈርስ፤ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንዳይበላሽ በአይሁድ ምኩራብ በመግባትእንዳስተማረ ሁሉ ዛሬም እያንዳንዳችን የቤተ ክርስቲያንን ነገር ለቤተ ክርስቲያን በማድረግ በቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ነገርን ብቻ በመሥራት ለቤተክርስቲያ የሚገባትን ቦታ መስጠት እንደሚገባ ይስበክበታል። ይልቁኑ በአርያ ሥላሴ የተፈጠረ ሰውነታችን ምኩራብ እየተባለ ይጠራል በዚህ ሰውነት ኃጢያትን መሸጥ መለውጥ ማርከስ እንደማይገባም ልብ ሊባል ይገባል። ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው። ስለዚህ አይሁድ፦ ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፥አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን?አሉት። #እርሱ_ግን_ስለ_ሰውነቱ_ቤተ_መቅደስ ይል ነበር። #ዮሐ ፪÷፲ ፱-፳ ፩ “ #የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ #የእግዚአብሔርም_መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ” ማንም #የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ #እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ #የእግዚአብሔር_ቤተ_መቅደስ_ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ።” #፩ኛ_ቆሮንቶስ ፫ ፥ ፲ ፯

አ.አ ኢትዮጵያ
ተክለ ኤል ኃ/ማርያም
መጋቢት ፲ ፩/ ፳ ፻ ፲ ፫.ዓ.ም
" #እነሆ_መንገድህ_በፊቴ_ጠማማ_ነውና እቋቋምህ ዘንድ ወጥቼአለሁ፤ "
_____________________________________________
#ዘኍ ፳ ፪ ÷፴ ፪

ይህን ኃይለ ቃል የተናገረው #ሊቀ_መላእኩ_ቅዱስ_ሚካኤል ነው ። የተናገረውም ለተራጋሚው በልዓም ስለተባለ ሰው ነው:: ቃሉን ጽፎ ያስቀመጠልን ሊቀ ነብያት ቅዱስ ሙሴ ነው::

#በልዓም ሃብተ መርገም ያለው የረገመው በቶሎ የሚደርስለት ሰው ነበር :: በዚህም ጸጋው ተጠቅሞ እስራኤልን ይረግም ዘንድ እጅ መንሻ ገንዘብን እንዲሰጡት ባላቅ ሰዎች ላከበት "፤ የሞዓብ ሽማግሌዎችና የምድያም ሽማግሌዎችም የምዋርቱን ዋጋ በእጃቸው ይዘው ሄዱ፤ ወደ በለዓምም መጡ፥ የባላቅንም ቃል ነገሩት። " #ዘኍ ፳ ፪÷ ፯
በልዓምም የተሰጠውን ሃብተ መርገም በገንዘብ ቀይሮ ሕዝበ #እግዚአብሔርን እስራኤልን ለመርገም በአህያው ላይ ተቀምጦ ሽማግሌዎቹንም ከዋላው አስከትሎ ጉዞ ጀመረ ::ጥቂት እንደሄደ ግን አህያው አንድ ባታ ላይ ቆማ አልንቀሳቀስም አለችሁ:: #የእግዚአብሔር_መላእክ የተመዘዘ ሰይፍ ይዞ ከፊቷ ቆሞ አይታዋለችና:: በልዓም ግን አህያይቱን አብዝቶ ደበደባት አህያይቱም ወደፊት ላለመሄድ ወደጉን ወደ እርሻው ተጠጋች

"፤ አህያይቱም #የእግዚአብሔርን መልአክ አይታ ወደ ቅጥሩ ተጠጋች፥ የበለዓምንም እግር ከቅጥሩ ጋር አጣበቀች፤ እርሱም ደግሞ መታት። " #ዘኍ ፳ ፪÷፳ ፭

#እግዚአብሔር አምላክ የሚረግሙህን እረግማለው የሚባእኩህንም እባርካለው ብሎ ቃል የገባላቸው የነ አብርሃም የነ ይስሐቅ የነ ያዕቆብ ዘር ናቸውና ሕዝበ እስራኤል እንዲረገሙ አልፈቀደም::ዘፍ 12÷3

የበላዓም ዓይኖች አሁንም አልተከፈቱም ልቦናውም ከአህያይቱ ልብ አልተሻለም አሁንም አብዝቶ ደበደባት ይህን ጊዜ በሰው አንደበት እንዲ ብላ ተናገረችው ሦስት ጊዜ የመታኸኝ ምን አድርጌብህ ነው? አለችው። "፤ በለዓምም አህያይቱን። #ስላላገጥሽብኝ_ነው_በእጄስ_ሰይፍ_ቢኖር አሁን በገደልሁሽ ነበር አላት።

"፤ አህያይቱም በለዓምን። ከብዙ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የምትቀመጥብኝ አህያህ አይደለሁምን? በውኑ እንዲህ አደርግ ዘንድ ልማዴ ነበረን? አለችው። እርሱም ። እንዲህ አላደረግሽብኝም አላት። እግዚአብሔርም የበለዓምን ዓይኖች ከፈተ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየ፤ ሰገደም፥ በግምባሩም ወደቀ።
#የእግዚአብሔርም_መልአክ። አህያህን ሦስት ጊዜ ለምን መታህ? እነሆ፥ መንገድህ በፊቴ ጠማማ ነውና እቋቋምህ ዘንድ ወጥቼአለሁ፤ አህያህ አይታኝ ከፊቴ ፈቀቅ ባትል ኖሮ በገደልኩ ነበር አለው ደግሞም በለዓምን ከሰዎቹ ጋር ሂድ፥ ነገር ግን የምናገርህን ቃል ብቻ ትናገራለህ አለው። በለዓምም ከባላቅ አለቆች ጋር ሄደ መልአኩ እየነገረው እስራኤልን ሊረግም ሄዶ መርቆ ተመለሰ::

#የእግዚአብሔር ሥራ ይገርማል ። የበልዓም አህያ የመላእኩን ክብር በማወቋና በመገንዘቧ የበላህምን ሕይወት ታድጋለች ዛሬ የቅዱሳን መላእክትን ክብር የማያውቁ የጸጋ ስግደት የማይሰግዱ አማላጅነታቸውን የማይቀበሉ ከአህያ ያነሱ ሰዎች በዝተዋል እግዚአብሔር አምላክ እንደ በልዓም ዓይነ ልቦናቸውን ከፍቶ ክብረ መላእክትን አውቀው ቅዱሳንን መርገም ትተው አንገታቸውን ደፍተው እንዲሰግዱ ያድርጋቸው ... .....ሌላ ምን እንላለን ከጌታችን የተማርነው ይህን ነውና

"፤ #የሚረግሙአችሁንም_መርቁ፥ ስለሚበድሉአችሁም ጸልዩ። "
(ሉቃ ፮÷ ፳ ፰ )
....#ይቆየን......
በዛሬው ዕለት ለበልዓምና ለአህያው የተገለጠበት ዓመታዊ ክብረ በዓሉ የሚከበርለት የሊቀ መላእኩ የቅዱስ ሚካኤል ረድኤትና ምልጃው አይለየን!

አ.አ ኢትዮጵያ
ተክለ ኤል ኃይለ ማርያም
መጋቢት ፲ ፪ ቀን ፳ ፻ ፲ ዓ.ም የተጻፈ
#ልትድን ትወዳለህን?"
#ዮሐ ፭÷፮
የዐቢይ ጾም አራተኛው ሰንበት “መጻጉዕ” ይባላል፡፡ መጻጉዕ ማለት “በሽተኛ” ማለት ነው፡
በዚህ ዕለት ጌታችን በቤተ ስዳ መጻጉዕን ማዳኑን ቤተክርስቲያን ትሰብካለች፡፡ ለ ፴ ፰
ዓመታት ያህል የፈውስ ተስፈኛ ሆኖ በመጠመቂያው አጠገብ የኖረ መጻጉዕን በአልጋው
ተኝቶ ሳለ ደዌው እንደጠናበት ፈውስ እንደዘገየበት አይቶ ‹‹አዎን›› እንደሚለው እያወቀ
መጻጉዕን ‹‹ልትድን ትወዳለህን?” አለው።
#መጻጉዕም ‹‹ሰው የለኝም›› በማለት የመዳን ጉጉቱን ከወዳጅ አልባነቱ ጋር ገለጠ።
ጌታም ‹‹ተንስና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” አለው፡፡ ወዲያው አፈፍ ብሎ በፍጥነት ያን ሁሉ
ዘመን የተሸከመችውን ጠንካራ አልጋ ተሸክሟት ሄደ (ዮሐ ፭÷፩ -፭)።
ጌታችን መጻጉዕን ‹‹ ተነስተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ›› ያለው ስለ ሁለት ነገር ነው፡፡
አንደኛው ቅዱስ ኤስድሮስ እንዳለው አልጋው ጠንካራ የብረት አልጋ ነበረና ጽንዓ
ተአምራቱን ለማሳየት ነው፡፡ ሁለተኛው ‹‹ታዲያ ቢያድነኝ በከንቱ መች ሆነና የገዛ አልጋዬን
ትቼለት የመጣሁ ለመዳኔ ዋጋ የከፈልኩበት አይደለምን?›› እንዳይል መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ‹‹ያለህን ይዘህ ሂድ እኔ ከአንተ አንዳች አልሻም›› ባሰኘ ቃል ‹‹አልጋህን
ተሸክመህ ሂድ›› ብሎታል።
# ይህ_ሰንበት የሕሙማን ፈውስ መታሰቢያ ዕለት ነው። የሰንበቱም ስያሜ በዕለቱ
የሚነበቡትን የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢርና የጾመ ድጓውን ይትበሀል ተከትሎ የተሰየመ
ነው፡፡ በመልእክታቱ የሚነበቡት (ገላ ፭÷፩ እና ያዕ ፭÷፡፲ ፬) ስለ ድውያን መፈወስ
የሚያወሱ ናቸው፡፡ ከሐዋርያት ሥራ የሚነበውም እንዲሁ (ሐዋ ፫÷፩)፡፡ የዕለቱ ምስባክ
እንዲሁ የድውያንን መፈወስ የሚሰብክ ሲሆን “እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ላይ ሳለ
ይረዳዋል፤ መኝታውንም ሁሉ ከበሽታው የተነሳ ይለውጥለታል፡፡ እኔስ “አቤቱ ይቅር በለኝ፤
አንተን በድያለሁና ለነፍሴ አስተስርይላት” አልሁ፡፡” ይላል (መዝ ፴ ፱(፵)÷፫)
መጻጉዕ ማለት ድዊ፣ ሕመምተኛ፣በሽተኛ ማለት ነውና በቤተ ሳይዳ ፴ ፰ ዓመት በአልጋ
ቁራኛ በደዌ ዳኛ ተይዞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ የፈወሰው ሰው ስም ብቻ
አይደለም የዚያ ሰው ስም "ስምዖን" ነው። ሕመምተኞች ሁሉ መጻጉዕ ተብለው ሊጠሩ
ይችላሉ ።ስለሆነም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህን የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት መጻጉዕ
ብላ ስታስብ ሕሙማነ ነፍስን እሙማነ ሥጋን ሁሉ ፈውሰ ነፍስ ፈውሰ ሥጋ እንዲያገኙ
ታስባቸዋለች ማለት ነው ። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመዋለ ስብከቱ
እሙማነ ነፍሳትን በትምህርቱ እሙማነ ሥጋን በተአምራቱ እንደፈወሳቸውም
ታዘክርበታለች።
#ሕማማ ወይም ደዌ በ ፭ ዓይነት መንገድ ሊመጣ ይችላል። እነርሱም
፩, ደዌ ዘንጽሕ(በንጽሕና የሚመጣ በሽታ) ለአብነትም እንደ ጢሞቲዎስ በአገልግሎት
ምክንያት የሚመጡ ::እንደ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት።
፪, ደዌ ዘእሴት (ለዋጋ የሚመጣ በሽታ) እንደ ጻድቁ ኢዮብ
፫, ደዌ ዘተአምራት( የእግዚአብሔር ተአምራት እንዲገለጥ የሚመጡ በሽታዎች) እንደ
ዘውር ተወልደ
፬, ደዌ ዘመቅሰፍት(በቅጣት የሚመጣ በሽታ)
እንደ ፈርዖን ዘመን ያሉ በሽታዎችና አባር ቸነፈሮች በዘመናችን ኮረና
፭,ደዌ ዘኃጢያት (በኃጢያት ምክንያት የሚመጣ) አንደ መጻጉዕ ፣ እንደ ባለ ሽቶዋ
ማርያም፣ በድንጋይ ልትወገር እንደነበረችው አመንዝራ ሴት
#ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ድኅነትን በ፭ መንገድ ይፈጽምላቸው
ነበር።ይህውም
፩,በኃልዮ (በሀሳቡ) ማር ፩፥፳ ፭
፪,በነቢብ(በንግሩ) ማቴ፲ ፭፥፳ ፰፣ ዮሐ ፭÷፰
፫,በገሲስ(በመዳሰስ) ማቴ፰፥፫ ፣ማቴ ፰፥፩ ፭
፬,በዘፈራ ልብስ (በልሱ ዘርፍ) ሉቃስ ፰፥፵ ፬
፭,በወሪቀ ምሪቅ (ምራቅን እንትፍ በማለት)“ ዮሐ ፱፥፮
ለድኅነት የሰው በጎ ፍቃድና ፍላጎት እጅግ አስፈላጊ ነው።መጻጉን ልትድን ትወዳለህን ብሎ
የመጠየቁም ምጢር ይህ ነበር ሰው ነጻ ፍቃዱ ሊነፍገው አይሻምና ። ሰው ለመዳን ወይም
ሌላውንም ለማዳን ብርቱ ጥረትን ሊያደርግ ይገባዋል
መጽሐፍ ቅዱስ አራት ሰዎች አንድ ሕመምተኛ ለማዳን የተጠቀሙትን ብርቱ ጥረት እንዲ
በግሩም ተርኮልን እናነባለን።
" #አራት_ሰዎችም የተሸከሙትን ሽባ አመጡለት። ስለ ሕዝቡም ብዛት ወደ እርሱ ማቅረብ
ቢያቅታቸው እርሱ ያለበትን የቤቱን ጣራ አነሡ፥ ነድለውም ሽባው የተኛበትን አልጋ
አወረዱ። # ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን፦ አንተ ልጅ፥
ኃጢአትህ ተሰረየችልህ አለው። ማር ፪ ÷፫-፭
.............ይቆየን.......
ግብሐት :-የዮሐንስ ወንጌል ም፭ ትርጓሜው
አ.አ ኢትዮጵያ
ተክለ ኤል ኃ/ማርያም
መጋቢት ፲ ፱ ቀን/፳ ፻ ፲ ፫ ዓ.ም
Audio