ዐውደ ምሕረት
3.69K subscribers
929 photos
24 videos
271 files
192 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
አፄ ሶምሶም
እንደ ደሊላ ለወደዷት ሀገራቸው ዐይናቸውን ሰጥተው በዓይናማነት ላቆዮት ሶምሶሞች ዛሬም ምሥጋና ይገባቸዋል ::

ሶምሶም ከተወለደ ጀምሮ በእራሱ ላይ ምላጭ አርፎበት የማያውቅ የእግዚአብሔር ኃይል በጸጉሩ ላይ ያደረበት እስራኤላውያንን ይጠብቁ ዘንድ  ከተነሱ መሳፍንት መካከል ኃያሉ ናዝራዊ ሰው ነበር  :: እንደ ነፍሱ የሚወዳት  ደሊላ ግን ይህ ከሰው ሁሉ ልዮ የሚያደርግህ   የኃይል ምሥጢር ምንድን ነው ? ከወደድከኝ ንገረኝ እያለች  ዕለት ዕለት ትነዘንዘው  ነበር ። መጻሕፍ ቅዱስ እንደውም ይህን ንዝነዛዋን  እንዲ ሲል ይገልጠዋል “ዕለት ዕለትም በቃልዋ ነዘነዘችው አስቸገረችውም፥ ነፍሱም እስከ ሞት ድረስ ተጨነቀች”መሳ 16፥16
ኢትዮጵያዊው ሶምሶም ዳግማዊው አፄ ቴዎድሮስም ልክ እንደ ሶምሶም የእራስ ጸጉራቸውን ምላጭ ያልነካው ለኢትዮጵያ የተለዮ (ናዝራዊ) ጎንደራዊ ነበሩ :: ኢትዮጵያዊያንን ከድህነት ቀንበር ለማውጣት ከተላኩ የኢትዮጲያ አንድነት ጠንሳሽ  ነገሥታት መካከልም በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱ የኢትዮጵያ አንድነት አባት እየተባሉ የሚጠሩ  አንዳርጌ ናቸው :: ውልደታቸው ከጎንደር ከተማ 12 ኪ/ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው " ደዋ " በምትባለው ሥፍራ ነው ዓመተ ምህረቱም 1811 ነበር ።
አባታቸው አቶ ኃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ ሲባሉ እናታቸው ደግሞ ወ/ሮ አትጠገብ ወንደሰን ይባላሉ ምንም እንኳን አባታቸው የባለ አባትነት ዘር ያላቸው ቢሆኑም እናታቸው ግን በድህነት ምክንያት ኮሶ  ይሸጡ እንደነበር ልዮ ልዮ የታሪክ ፀአህፍት ይጠቅሳሉ :: ለምሳሌ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ ጳውሎስ ኞኞ፣ ሎሬት ፀጋዬ  ገብረ መድህን...ወዘተ  
ቢሆንም ግን አፄ ቴዎድሮስ" በእናት እና በሀገር አይታፈርም" ሲሉ  ከባለ አባት ዘር ከተከኙት ከአባታቸው ከአቶ ኃይሉ ይልቅ  " የኮሶ ሻጭ ልጅ " እየተባሉ በኮሶ ሻጭ እናታቸው ስም ያለ እፍረት መጠራትን መረጡ ::  ዛሬ ዛሬ አፄ ቴዎድሮስ በግፍ  ይህን አደረጉ አፄ ምኒልክ የሴት እንትን ቆረጡ እያሉ አፄዎቹን  ሲያብጠረጥሩ ሳይ የእውነት ይከፋኛል  ::  በኮሶ ሻጭ እናቱ  የተጠራው ቴዎድሮስ እምዬም እየተባሉ የሚጠሩት ምኒልክ እናቶችና ሴቶች ላይ ይህ የመሰለ ድርጊት አደረጉ ብሎ ማውራት ከታሪክ መጎደል ነው ::

ሶምሶም ከደሊላ ምሥጢር ከሚያስወጣ ጥያቄዋ ለማምለጥ የራሱን ጥረት አድርጓል::  በእርጥብ ጠፈር ብታስሪኝ፣ በአዲስ ገመድም ብትቋጥሪኝ፣ የእራስ ፀጉሬን በችንካር ብትቸነክሪው  ኃይሌ ከእኔ ይጠፋል እንደ ሌላም ሰው እሆናለሁ እያለ  ምሥጢርም ሳያወጣ ደሊላንም ሳያጣ እስከ ጊዜው ለመቆየት ችሎ ነበር :: “ልባም ሴት ለባልዋ ዘውድ ናት፤ አሳፋሪ ሴት ግን በአጥንቱ ውስጥ እንደ ቅንቅን ናት።” ምሳሌ 12፥4 እንዲል መጻሕፍ

አፄ ቴዎድሮስም ከእንግሊዞች ጋር ችግር ውስጥ እንዲገቡ ያደረጋቸው ሀገራቸውን ወደ ሥልጣኔ ማማ ለማውጣ ካላቸው ከፍተኛ ጉጉት ነበር:: አማቻቸው ደጃች ውቤን ድል ካደረጉ በኃላ የካቲት ወር 1847ዓ.ም አፄ ቴዎድሮስ ተብለው በደረስጌ ማርያም ቤተ ክርስቲያን በይፋ ነገሱ ወዳጆቼ ናቸው ከሚሏቸው ሩሲያ እና እንግሊዝ ጋርም ስለ መድፍ ሥራ መጻጻፍ ጀመሩ::
እንግሊዝ ሆዬ አሻፈረኝ ስትል የአፄውን ጥሪ በእንቢታ መለሰች ይኸኔ ሥልጣኔና ትምህርት ሳይሆን ስንዴ ለምነው ቢሆን ኖሮ እሺታቸውን ባልነፈጓቸው ነበር አፄው ግን ከአንድ አፍሪካዊ መሪ የማይጠበቅ ጥያቄ ጠየቁ ስለዚህ እንቢ ተባሉ። አፄውም ደመ ፍሉ ነበሩና በሀገር ውስጥ ያሉ እንግሊዞችን በወይኒ አጎረው ዘጉባቸው ። በጋፋትም ታሳሪዎቹን መድፍ እንዲሰሩ አስገደዷቸው እኛ ወንጌላዊያን ነን ስለ መድፍ ሥራ አናውቅም አሉ መድፍ መሥራት ካላወቃችሁበት እኔም አላውቅላችሁም ሲሉ አፄው ቆራጥ ውሳኔያቸውን ቢያሳውቋቸው ወንጌላዊ ተብዬ ሆይ የመድፉን ሥራ አጣደፉሁት ወንጌልና መስቀል ይዘው የነበሩ እጆች ብረትና ባሩድ ጨበጡ:: በዚህ ተደፈርኩ ያለችሁ እንግሊዝም በውስጥ ከፋፍሎ ለመግዛት በተዘጋጁ መሳፍንት ውጥረት ግብ ድብ ውስጥ የገቡትን ቴዎድሮስ ከውጭ ሆና ለማጥቃት ምቹ ጊዜ ያገኘች መስሏት 32 ሺህ ጦር አስከትላ መጣች እጅ እንዲሰጡም አፄውን ጠየቀች አፄ ቴዎድሮስም ይህን ሲስሙ ከት ብለው ስቀው ሲያበቁ "ሀገሬን እንኳን ለነጭ ቀኝ ገዢ ለጥቁሩም ከፋፋይ የምሰጥ አይደለውም በዓለማየሁም ቢሆን ለዚህ አማላጅ የለኝም ደግሞ እጅህን ስጥ በክብር እንዝሃለን ይሉኛል? እጄ የእሳት አሎሎ መሆኑን አያውቅም!? ወትሮንስ የት ሀገር ነው ጠላት በክብር የሚያዘው!?

ንዝነዛዋ የበዛበት ሶምሶም የልቡን ሁሉ ገለጠላት  የኃይሉ ምንጭ ጸጉሩ እንደሆነና ጸጎሩን ቢላጭ ኃይሉ ከእርሱ እደሚርቅ ነገራት ደሊላም የልቡን ሁሉ እንደገለጠላት ባየች ጊዜ በጕልበትዋ ላይ አስተኛችው በተኛበትም፤ አንድ ሰውም ጠራች፥ እርሱም ሰባቱን የራሱን ጕንጕን (ቁንድላ) ላጨው። ልታዋርደውም ጀመረች፥ ኃይሉም ከእርሱ ሄደ።” ከተኛበት ቀስቅሳም ሶምሶም ሆይ ፍልስጤማውያን መጡብህ አለችው ተነስቼ እንደ ቀድሞ እሆናለው ቢል ኃይል ከእርሱ እርቆልና አንዱን በጡጫ ሌላውን በርግጫ ማለት ተሳነው:: ሶምሶምም ለምርኮ ተዳረገ ፍልስጥኤማውያንም ይዘው ዓይኖቹን አወጡት፤ ወደ ጋዛም አምጥተው በናስ ሰንሰለት አሰሩት፤ በግዞትም ሆኖ እህል ይፈጭ ነበር። መ.መሳፍ 16፥21
ከውስጥ እና ከውጭ ጠላቶቻቸው ጥርስ ውስጥ የገቡት ቴዎድሮስ ለነጭ ቀኝ ገዢና ለጥቁር ከፋፋይ አሳልፌ አልሰጥም ብለው ከታማኝ ወታደሮቻቸው ጋር ያሰሩትን ሴቫስቶፎል መድፍ ይዘው ወደ መቅደላ ገሰገሱ በዚያም የጠላት ጦር ገፍቶ በመምጣቱ ከአራቱም መዓዘን በአንድነት የሰበሰቧቸውን ሽፍቶች እንደ ቀድሞ በአራቱም መዓዘን ተበትነው ለጠላት የማይጨበጩ ይሆኑ ዘንድ አሰማርተው ለጠላት እጅ ሳይሰጡ በነገሱ 13 ዓመት በተወለዱ ደግሞ በ49ዓመታቸው 1860ዓ.ም በሚያዚያወር በገዛ እጃቸው እራሳቸውን ሰውተው የጀግና ሞት ሞቱ::

አልደፈር ብሎ እራሱን ገደለ
ጀግና ሰው ሰውቶ ካሳ መች ከፈለ
በመቅደላ በኩል ጮኸት በረከተ
የሴቱን አናውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ
........................
አያችሁት በያ የጀግናሁን ሞት
በሰው እጅ መሞትን ነውር አድርጎት
ገደልን እንዳይሉ ሞተው አገኟቸው
ማረክንም እንዳይሉ ሰው የለ በጃቸው
ምን አሉ እንግሊዞች ሲገቡ አገራቸው
ለወሬ አይመቹም ተንኮለኛ ናቸው
.

በትውልድ ስማቸው ካሳ ኃይሉ በፈረስ ስማቸው አባ ታጠቅ በውትድርና ስማቸው ደግሞ መይሳው ካሳ እየተባሉ የሚጠሩት ኢትዮጵያው ሶምሶም ዳግማዊው አፄ ቴዎድሮስም እንደ ደሊላ ለወደዷት ሀገራቸው ዋጋ ከፍለዋል በፍቅሯ ጭኖች ተይዘው መቅደላ አምባ ላይ ተኝተዋል ለማዕተባቸው አድረዋል:: በግብር ፍልስጤማዊያን በሚባሉ እንግሊዛዊያን የእራስ ጸጉራቸው ቁንድላ ከእራሳቸው ላይ እንደ በግ ከነቆዳቸው ተገፏል አስክሬናቸውም በግፍ ተደብድቧል :: ደሊላ በሶምሶም ተጠቅማለች ሶምሶም ግን ከደሊላ ያተረፈው ሞት ብቻ ነው



#የግርጌ_ማስታወሻ :- እንግሊዞች ገፈው ወስደውት የነበረው የአፄ ቴዎድሮስ ቁንዱላ (የተጎነጎነ የእራስ ፀጉር፣ ሹሩባ ) በአንድ ድርድር በቅርቡ ወደ ሀገር ተመልሷል::

ዓውደ ምህረት የእናንተ
👇👇👇👇👇👇
@AwediMeherit
@AwediMeherit

ነሐሴ ፳ ፰ - ፳ ፻ ፲፪ ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
ተርቢኖስ ሰብስቤ ኃ/ማርያም
#ዛቲ_ዕለት_ቅድስት_ይዕቲ
(ይህቺ ቀን የተቀደሰች ናት)
*****************************
#ቅድስት_ማለት የተለየች የጸናች ክብርት ማለት ነው:: ቤተ ክርስቲያንም በዚህ በዐብይ ጾም ሁለተኛውን ሳምንት ቅድስ ብላ በመሰየም የሰንበትን ቅድስና ታስባለች ::
ሰንበትን ቅድስት ያሰኛት ምንድነው?
_________________________
ፈጣሪ ዓለማት ልዑል እግዚአብሔር በሰድስቱ ዕለታት ፍጥረታትን ከፈጠረ በኃላ በሰባተኛው ዕለት ከሰራው ሥራ ሁሉ አረፈ "ለሙሴም የሰንበትን ቀን ትቀድሳት ዘንድ አሰብ "የምትለውን ትዕዛዝ ሰጠ ስለዚህ ሰንበትን ቅድስት ያሰኛት ከስራ ሁሉ የሚታረፍባት ሕመምተኛ የሚጠየቅባት ወደ ቤተ እግዚአብሔር የሚገሰገስባት ቀን በመሆኗ ነው ::
በግብራቸው የተነሳ ዕረፍት እየተባሉ የሚጠሩ
***********************************
1) (ሰንበት ክርስቲያን )ዕለት እሁድ :- ዕረፍት ተብላ ትጠራለች: ዕለተ እሁድ በሌላ ስሟ ሰንበተ ክርስቲያንም ተብላ ትጠራለች :: አንዳንድ ጊዜ ሰንበት እሁድ ከሆነች ቅዳሜ ታድያ ምንድነች??? ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል :: አስቀድሞ ዕለተ ቅዳሜ የአይሁድ ሰንበት ነበረች ጌታችንም እንደተናገረው ሕግ ና ነቢያትን ልፈጽም እንጂ ልሽራቸው አልመጣውም እንዳለ የአይሁድ ሰንበት ቅዳሜም አልተሻረችም ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ቀዳዊት ሰንበት የቀደመች ሰንበት ብላ ታስባታለችች :: ማቴ5÷17 አንድም ደግሞ የኦሪት ሥርዓቶች ሁሉ ለአዲስ ኪዳን ሥርዓቶች ምሳሌ ጥላ መርገፍ ናቸውና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ቅዳሜን እንደ ምሳሌ አድርጋ እሁድን አማናዊት ሰንበት አድርጋ ታስባቸዋለች ::
ዕለተ እሁድ( ሰንበተ ክርስቲያን)
*ጥንተ ዕለት ናት :- ፍጥረታት መፈጠር የጀመሩባት ዕለት ናትና "ይህቺ ዕለት ከ7ቱ ዕለታት ቀድማ የተገኘች ናት እንጂ በኃላ የተገኘች አይደለችም " እንዳለ ቅዱስ አትናቲዮስ በኩረ በዓላት ናት :-
* #የበዓላት ሁሉ መጀመሪያ ናትና ዓለም የተገኘባት
* #ወልድ ሰው የሆነባት
* # ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተነሳባት
* #ዳግመኛ ለፍርድ የሚመጣበት ዕለት ጭምር ናት::
2) #እመቤታችን ዕረፍት ተብላ ትጠራለች
____________________________

ከ5500 ዘመን የድካም የመከራ ጊዜ ሁሉ በእርሷ እረፍትን አግኝተናልና :: እንዴት ቢሉ መላእኩ ቅዱስ ገብርኤል መጥቶ ባበሰራት ጊዜ ለዓለም መዳን ምክንያት ትሆኚ ዘንድ መርጦሻል ብሎ ፍቃዷን በጠየቀ ጊዜ "ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ "እነሆኝ የጌታ ባርያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ" በማለት ለድኅነተ ዓለም ምክንያት እረፍት ሆናለች:: #ሉቃ 1÷26
3) #ቅዱሳን :- እረፍት ተብለው ይጠራሉ::ቅዱሳን በሳኦል መንፈስ ለተያዘችው ደካማዋ ዓለም እረፍት ናቸው " እንዲህም ሆነ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ መንፈስ በሳኦል ላይ በሆነ ጊዜ ዳዊት በገና ይዞ በእጁ ይመታ ነበር፤ ሳኦልንም ደስ ያሰኘው ያሳርፈውም ነበር፥ ክፉ መንፈስም ከእርሱ ይርቅ ነበር። (መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 16÷23) አንድም ጻድቃን በጸሎታቸው ሕዝብ የሚያሳርፉሁ ናቸው ጻድቃንም በበዙ ጊዜ ሕዝብ ደስ ይለዋልና በመወለዳቸውም ብዙዎች ደስ ተሰኝተዋልና ምሳ 29÷2 ሉቃ 1÷14 ያዕ 5÷16
4) #ቅድስት_ቤተ ክርስቲያን እረፍት ትባላለች :-
__________________________________
ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት እግዚአብሔር እረኛዬ ነው የሚያሳጣኝም የለም በለመለመ መስክ ያሰማራኛል በእረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል " ብሎ ቤተ እግዚአብሔርን እንደ እረፍት ሥፍራ በውስጧ የሚፈሰውን ቃለ እግዚአብሔርን ደግሞ እንደ መብል እንደ መጠጥ አድርጎ ተናግሯል:: መዝ 22(23)÷1 አንድም የእረፍት ቦታ የሆነችው የመንግስተ ሰማያት የሰማያዊት ኢየሩሳሌም ምሳሌ ናትና ዕረፍት ተብላ ትጠራለች ::
5) #መንግሥተ ሰማያት ራሷ እረፍት ትባላለች
_______________________________
እስራኤል ዘሥጋ ድካም ከበዛባት ከምድረ ግብጽ ወተው እረፍት የሆነችውን ምድረ ከንዓንን ወረሰዋል እኛም እስራኤል ዘነፍሶች ከዚህች ድካም ከበዛባት ዓለም እረፍት የምናገኘው በመንግስተ ሰማያት ነውና መንግስተ ሰማያት እረፍት ትባላለች :: " ነገር ግን። ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንድተጻፈ፥ እንዲህ እንናገራለን።" (1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2:9)
6) #ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ዕረፍት ይባላል :-
___________________________________
" እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።" ብሏልና ዕረፍታችን ነው (የማቴዎስ ወንጌል 11:28) አንድም የእግዚአብሔር መንግስት(የዕረፍት ሥፍራ) ከወድየት አለች ብለው በጠየቁት ጊዜ " ደግሞም። እንኋት በዚህ ወይም። እንኋት በዚያ አይሉአትም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና አላቸው።" (የሉቃስ ወንጌል 17:21) ይህን ያለው በመካከላቸው የነበረው እርሱ መንግስተ ሰማያት የእረፍት ሥፍራ ወይም እረፍታችን በመሆኑ ነው ::
ስለዚህ እኛ ክርስቲያኖች የሰንበትን ቅድስና ስናስብ እግዚአብሔርን እመቤታችንን ቅዱሳንን መንግስተ ሰማያትን ሁሉ ታሳቢ ማድረግ ይገባናል ማለት ነው::
#የግርጌ_ማስታወሻ
++++++++++++++
እረፍትን ለማግኘት አስቀድሞ ሥራ ሊኖር ይገባል ሥራ በሌለበት እረፍት የለም:: እንድ ሰው አረፈ ለማለት አስቀድሞ ሥራ ሰራ ሊባል ይገባዋል:: እግዚአብሔርም ከሰራው ሥራ ሁለ አረፈ ተብሎ ተጻፈ እንጂ አረፈ ተብሎ ብቻ አልተጻፈልንም በመሆኑም እኛ ክርስቲያኖች እረፍተ መንግስተ ሰማያትን እረፍት እግዚአብሔርን እረፍት እመቤታችንን እረፍት ቅዱሳንን ለማግኘት በጎ ሥራን ሁሉ ልንሰራ ያስፈልጋል :: አንድ ሊቅ በሰንበት አንድ ሥራ ሲሰሩ የኔ ቢጤ ጨዋ መቶ ምነው አባ እግዚአብሔር እንኳን ባረፈበት ቀን በሰንበት ለምን ሥራ ይሰራሉ አላቸው ሊቁም ፈገግ ብለው አዮትና ልጄ እርሱ ኮ ያረፈው ሥራውን ሁሉ ጨርሶ ነው እኔ ምን ሰርቼ ነው የማርፈው አሉት ይባላል :: በሰንበት ለሰንበት የሚገባ ሥራ ልንሰራበት ይገባል እንጂ ሥራ ፈተን መቀመጥ አይገባንም ሥራ የፈታ አህምሮ የሰይጣን ቢሮ ነውና ያለ ሥራ የተቀመጠ ሰው ሊስት ሊሳሳት ይችላል::
በሰንበት ዝም ብሎ ከመቀመጥ ወደ ቤተ እግዚአብሔር መሄድ የታመመ ካለ መጠየቅ መጸለይ ሌላም ሌላም የትሩፋት ሥራ ልንሰራ ይገባል :: ይህን ካደረግን ቅድስት ከሆነችው ከሰንበት ረድኤትና በረከትን እናገኛለን::
.........ይቆየን...........
አ.አ ኢትዮጵያ
ተክለ ኤል ኃ /ማርያም
የካቲት 12/2010 ዓም