አትሮኖስ
286K subscribers
122 photos
3 videos
41 files
578 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#የድብልቅልቅ_ሰፈር_ሰዎች


#ክፍል_ሁለት(የመጨረሻ ክፍል)


#በእየሩስአሌም_ነጋ


ቁጥራቸው ወደ ሃያ የሚጠጋ ውሾች እየተነካከሱ መንደሯን ድብልቅልቋን አወጧት፡፡ ድንገት ግር ብለው ወደኔ ሲመጡ ከውሾቹ ስሸሽ ተደነቃቅፌ ከመውደቅ ለመዳን ባደረግኩት መፍጨርጨር አንድ በር ላይ እጆቼ አረፉ፡፡

በሩ ያለምንም ማንገራገር ተበርግዶ እኔን ይዞኝ እንደዘሉ የተነባበሩ ሰዎች ከተኙበት አልጋ ላይ ተዘረጋሁ፡፡ወደያው በድንጋጤ ለመነሳት ባደረኩት ጥረት የሰውየውን ወገብ በኃይል ስጫን ሴትየዋ ሁለት ጊዜ አቃስተች፡፡ ፊቱ ላይ ስጋ ያልተፈጠረበት
የሚመስል መጣጣ ጠይም ስውዬ በፍጥነት ከወገቡ ቀና አለ የሴትየዋን ደረት እየተጫነ፣

“እያለሁ? እስክወጣ እንኳ አላስችል አለህ?” የግንባሩ ላብ ተንጠባጠበ፡፡

“ደግሞ ያፈጣል እንዴ? ማን ጠራህና ነው የሰው በር በርግደህ የገባኸው?” በማለዳ ወፍራም ድምጿ አጉረመረመች።
በገባው ጥቂት ብርሃን ፍንጣቂ ጥርሷ ብቻ ሲብለጨለጭ ታየኝ፡፡
“አንቺ የቀጠርሺውን ምን ያድርግ? አስተዳዳሪ እስኪወጣ እንኳ አላስችል ብሎት...” ሌላ ነገር እንዲያስደምጡኝ እድል አልሰጠኋቸውም፤ ተመልሼ በመጣሁበት በር ወጣሁ።

ራመድ እንዳልኩ መለስ ብዬ የገባሁበትን ቤት ተመለከትኩ። በሩን ባለመዝጋቴ ምስጢራቸው ባደባባይ ተጋልጧል። በፍጥነት ተመልሼ ልዘጋ ስል ሴትየዋ ልትነሳ ትድበሰበሳለች፡፡ በድንጋጤ
እየተርበተበትኩ አልፌ ሄድኩ፡፡

ዐይኔን ወደጎን ሳዞር ሁለት ሰዎች በላስቲክ በተሰራ ዳስ ውስጥ ሻይ ይዘው ሲጠጡ አየሁ። ወደ ስደት ለመሄድ ካስብኩ ጀምሮ የምግብ ፍላጎቴ ሁሉ ተዘግቶ መብላት፣ የምጠላው አስተማሪ
የሚሰጠኝ ከባድ የቤት ስራ መስሎ ይታየኝ ከጀመረ ሰንብቷል።
ሕይወትን ለማራዘም ምግብ ግድ ስለሆነ ይህንን አስጨናቂ የቤት ስራ እሰራ ዘንድ ጎራ አልኩኝ፡፡

ሙሉ በሙሉ ተቀይሬ ሌላ ሰው እንደሆንኩ ተረዳሁ፡፡ምክንያቱም
በፊት የማሳያቸውን ቆሻሻ ነገሮች ዛሬ ማጤን ጀምሬያለሁ፡፡ በቤቱ ውስጥ የማያቸው ሁሉ ቆሻሻ መስለው ታዩኝ፡፡
በተስፋ መቁረጥ የተነሳ አለም በቃኝ ብዬ ክፉና ደጉን ማየት ተስኖኝ ነበር፡፡ የቀረበልኝን የሻይ ብርጭቆ ገና ወዳፌ ከማድረሴ ክርፋት ክርፋት ሸተተኝ፡፡ እንደማሽተት አድርጌ መልሼ አስቀመጥኩት፡፡

አስተናጋጇ ሌሊት የለበሰችውን ወፈር ያለ አብለጭላጭ ፒጃማ አልቀየረችም፡፡ የተበላባቸውን እቃዎች አነሳስታና ጀርባዋን ለኔ ስጥታ ጠረጴዛውን ትወለውላለች፡፡

ፒጃማዋ ላይ የፈሰሱ ቆሻሻዎች የፈጠሯቸውን ውስብስብ ካርታዎች አየሁ፡፡ የፈሰሰባት ነገር እጣ ፈንታችንን በጭላጭ ስኒ የሚተነብዩትን ጎረቤቴን አስታወሰኝ፡፡ “የኔም እጣ ፈንታ ከመቀመጫዋ ላይ ይነበብ ይሆን? ወይስ የምሄድበት መንገድ ካርታ ተስሎበት ይሆን?” አልኩና ብቻዬን ፈገግ አልኩ፡ ስትንቀሳቀስ መቀመጫዋ ዳንኪራ ይረግጣል።

ዐይኔን መግታት እንዳለብኝ ተሰምቶኛል። ዐይኔን ብቻ ሳይሆን ዐይነ ህሊናዬን ጭምር ማቀብ እንዳለብኝ ወስኛለሁ፡፡
የሩጫ ጊዜ፣ የዝላይ ጊዜ፣ የመቆሽሽ ጊዜ ማክተም አለበት፡፡

የበረደውን ሻይ አንስቼ ወደ አፌ ላንዶለዱለው ስል... ከኋላ ኪሴ ያስቀመጥኩት ሞባይል ንዝረት በመላ አካላቴ ፈሰሰ፡፡ አውጥቼ አየሁት፡፡ ለጉዞ መሰናዶ የሚሆነንን ነገር እንድንነጋገር
የቀጠርኳቸው ጓደኞቼ ነበሩ፡፡ “ዶሮ ማታ” እንደሚባል ልጅ እንደ ኮሶ እያንገሸገሸኝ የቀረበልኝን ሻይ ጠጥቼና ሂሳቤን ከፍዬ በፍጥነት ተነሳሁ።

ጥቂት ከተራመድኩ በኋላ አንድ ጋዜጠኛ የተለያዩ ሰዎችን እያፈራረቀ ሲጠይቅ አየሁ። ሰዎቹ የድብልቅልቅ ሰፈር ሰዎች
ናቸው፡፡
አንዱን ሰውዬ ጠጋ ብዬ ጠየኩት፡፡ የድብልቅልቅ ሰፈር ፈርሳ በአዲስ መልክ ልትገነባ እንደሆነና ሰዎቹ የተሰማቸውን ሀሳብ እየተናገሩ እንደሆነ አስረዳኝ፡፡ አብረን ልንለወጥ ቀጠሮ የነበረን
አንመስልም? አልኩና ማየቴንና ማዳመጤን ቀጠልኩ፡፡

ድብልቅልቅ ሰፈር ከፊል አካሏ እንደ ባቢሎን ፈራርሷል። ድህነትና ማይምነትም አብረው ሲፈራርሱ ታየኝና ፈገግ አልኩ፡፡ የድብልቅልቁ አሸባሪ እብዱ መሐሪ የጋዜጠኛውን መቅረጸ ድምጽ
ቀምቶ ዐይኑን እያጉረጠረጠ ጋዜጠኛውን ካስፈራራ በኋላ፣

ስማ እኔና አንተ ሳንለወጥ ሀገር ይለወጣል ብለህ አታስብ፡፡እስቲ እኔን እየኝ ፈርሼ በስብሼ እንደገና የምነሳ አይመስልህም?”ጋዜጠኛው ደንግጦ በፍርሃት ያየዋል።
“ይመስለሀል አይመስልህም? እኔ ደግሞ እራሴን ልክ እንደ ድብልቅልቅ ሰፈር ሳላፈራረስ ብቀር...ግን ቆሻሻ የፈጠሩ
ሰዎች ሳይፈራርሱ እንዴት ድብልቅልቅ ሰፈር ትነጻለች?
ድብልቅልቅን የፈጠሯት እኮ እነሱ እንጂ እርሷ ራሷ አይደለችም፡፡”

አንገቱን ወደ ሰማይ አቅንቶ ሳቀ፤ ወዲያው ደግሞ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ሳቁን ገታና ቀጠለ፡፡ ጋዜጠኛው መቅረጸ
ድምጹን ለመቀበል ሲሞክር ዐይኑን ሲያጉረጠርጥበት እንደ መፍራት ብሎ እጁን መለሰ።

ካንተ ይልቅ እኔ እውነት እናገራለሁ። ስለዚህ ድምጽ መቅረጫው ምን ያደርግልኸል?…እ?” ጋዜጠኛው ግራ በመጋባት ወደኃላው እንደ ማፈግፈግ ብሎ ተመልሶ ቆመ።

“ስማ ለመሆኑ ከራስህ ጋር ተጣልተህ እስከመቼ ነው?እስከመቼ? እንደኔ እውነት ለመዘገብ ማበድ አለብህ?...አለብህ
የለብህም? ንገረኝ! ምንድነህ አንተ አህያ ነህ? የጫኑህን የምትጫን፣በል ያሉህን የምትል። ጠይቅ ያሉህን የምትጠይቅ አንተ ለምን አትተወውም? ለምን አታብድም? እ..የዚያች ልጅ! አሁን በናንተ
ቤት አዲስ መንደር ልትሰሩ ነው አይደል? ዳግመኛዋ ድብልቅልቅ ሰፈር አትሏትም? ትሏታላችሁ አትሏትም?” ወዲያውኑ ጥቀርሻ በመሰለው የላስቲክ ቤቱ አጠገብ አንድ ሰው ቆሞ አየ።

“ቤቴን! ቤቴን!” ካለ በኋላ በድጋሚ ወደ ጋዜጠኛው ዞሮ
“ሆዳም! ለሆድህ ያደርክ! ህሊናህን የሸጥክ! እኔ እኮ እንዳንተ
ዋሽቶ መብላት አላቃተኝም! ግን ወገኔን አልበላም። ደሞ ሀቀኛ
ጋዜጠኞችን አታሰድብ እ...? አየህ? ቤቴን ሲያፈርሱት! አየህ?
አሁን ለኔ ኮንደሚኒየም ቤት ሊሰጡኝ? ነው? ይመስልሀል አይመስልህም? የዚያች ልጅ!” እንደገና ፊቱን ወደ ቤቱ መለሰ፡፡
“ቤቴን! ቤቴን! ከሙስና በጸዳ በንጹህ ገንዘቤ፣ በላቤ የሰራሁትን ቤቴን! አንድ ሰው እንዳያፈርስብኝ ቤቴን!” ድምጹን ከፍ
አድርጎ ጮኹ፡፡ አንድ እርምጃ ወደ ፊት ቀረብ ብሎና ወደ ጋዜጠኛው ተጠግቶ፣ “ውሸት የጠጣች የድምጽ መቅረጫ ምን
ታድርግልኛለች? አየሃት እንዴት እንደከሳች... አየሃት እንዴት
እንደተጎሳቆለች?... አየህ! ውሸት በሽታ ነው፡፡ ሀገርህንም እንዲህ
ነው የምታከሳት! ገባህ? የዚያች ልጅ! ምን ይገባሀል አንደኛህን
ደንቁረህ! ብኩርናህን በጭብጥ ሽንብራ የሸጥክ!" መቅረጸ ድምጹን ጋዜጠኛው አፍንጫ ላይ ወርውሮ ሮጠ፡፡

ህንጻ ወደ ሆነው ወደ ራሴ ሰውነት አስተዋልኩ።በእርግጥም ድብልቅልቅ ሰፈርን የፈጠሩ ሰዎች እንደገና መፈጠር
አለባቸው።ለእውቀት ለእውነታ ለትጋት።ለውጡ ከራስ ይጀምራል፡፡

ያ የቆሸሸውና ሊፈራርስ የነበረው እኔነቴ ሊሰሩ እንደታሰቡት ህንጻዎች ሲደምቅ ታየኝ፡፡ እነዚያን የከብት መንጋ ይመስል
በየመንገዱ የሚርመሰመሱ ውሾች፣ ምርጊታቸው የፈራረስ ቤቶች፣ በሰው ላይ የሚደፉ ፍሳሾች፣ የሚጨፈላለቁ ነገሮች፣ የሚኮረኩመ ጣራያዎች፣
የሚገጩና የሚያጋጩ ሸክሞች፣
ቆሻሻዎችና ኮንደሞች... ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ በዐይነ ህሊናዬ
ተሰናበትኳቸው፡፡

በረጅሙ እግረ መንገዴ ውስጥ ከራሴ ጋር ያደረኩት ሙግት ቀላል አልነበርም፡፡ ወስኛለሁ ብዬ ከቤት መውጣቴና ለጓደኞቼ ልናገር ማሰቤ ልክ እንዳልነበረ ታወቀኝ፡፡ በተለይ የድብልቅልቅ
ሰፈር ፈርሶ እንደገና መሰራት የመሄዴን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ እንድለውጥ አድርጎኛል።በሃሳቤ
1
እንደገና የፈጠርኩትን ማንነቴን ፈርሶ በሚስራው መንደሬ ሳኖረው ከቶ የምን ስደት አስባለኝ፡፡ ለሊት ስገነባው
ያደርኩትን ሀሳብ አሁን አፈራረስኩት። ደግሞ ነገ ተራውን ጠብቆ ወደ ሚፈርስው የኖርኩበት መንደር ውስጥ የናቴ መንፈስ አለ። ያን መንፈሷን ያንን ፈገግታዋን ግን ላጣ አልፈልግም፡፡ በፍጹም ትቻት አልሄድም፡፡ እዚሁ ሀገሬ ላይ፣ ሰው ስሆን አሳያታለሁ። በፍጥነትና
በቆራጥ ውሳኔ... ወደ መጣሁበት ቤቴ፣ ወደመሃል ደብልቅልቅ ተመለስኩ፡፡

💫ይሄም አለቀ💫

እስቲ ሌላ ደሞ እንቀጥላለን ብቻ አስታያየታችሁን ወዲ በሉ @atronosebot ይጠቀሙ
👍2
አትሮኖስ pinned «#የድብልቅልቅ_ሰፈር_ሰዎች ፡ ፡ #ክፍል_ሁለት(የመጨረሻ ክፍል) ፡ ፡ #በእየሩስአሌም_ነጋ ቁጥራቸው ወደ ሃያ የሚጠጋ ውሾች እየተነካከሱ መንደሯን ድብልቅልቋን አወጧት፡፡ ድንገት ግር ብለው ወደኔ ሲመጡ ከውሾቹ ስሸሽ ተደነቃቅፌ ከመውደቅ ለመዳን ባደረግኩት መፍጨርጨር አንድ በር ላይ እጆቼ አረፉ፡፡ በሩ ያለምንም ማንገራገር ተበርግዶ እኔን ይዞኝ እንደዘሉ የተነባበሩ ሰዎች ከተኙበት አልጋ ላይ ተዘረጋሁ፡፡ወደያው…»
#ከዕለታት_ግማሽ_ቀን


#ክፍል_አንድ


#በአሌክስ_አብርሃም

የዛሬ አሥራ ሦስት ዓመት እግዚእብሔርን ለመሆን ተመኝቼ ነበር፤ አልተሳካልኝም፡፡ .
እግዚእብሐርን መሆን ስላልተሳካልኝ “በቃ ለምን ሰይጣን አልሆንም?” የሚል ሐሳብ
ውል ብሎብኝ፡ ሰይጣን ለመሆን ሞከርኩ እሱም ቢሆን እንዲህ እንደሚወራው ቀላል አልነበረም(ክፋት በሰይጣን እጅ ያምር፤ሲይዙት ያደናግር) እንግዲህ ሁለቱንም ካልሆንኩ ራሴን ልሁነውና የመጣውን ልጋፈጠው” ብዬ እግዜርነትንና ሰይጣንነት ልለካ አውልቄ ያስቀመጥኩትን እኔነት ፍለጋ ዙሪያዬን ባስስ ራሴም የለሁም፡፡ ይሄ ደግሞ ማነው?” እስክል ራሴን ፈጽሞ የማላውቀው አዲስ ፍጡር ሆኖ አገኘሁት፡፡ይኼው እስራ ሦስት ዓመት ጊዜ ፈጣን ነው፡፡ እንደ ደራሽ ጎርፍ ጠራርጎ የማይወሰድብን እያግበሰበሰም አምጥቶ የማይጭንብን ጉድ የለም፡፡

የአሥራ ሁለተኛ ክፍል የማትሪክ ውጤት የተነገረበት ሰሞን ነበር፤ ከብዙዎች ተመርጠን ወደ ዩኒቨርስቲ መግቢያ ከፍተኛ ውጤት ስላመጣን “በምድር ላይ መከፈት የማንችለው በር የለም! የሚል የወጣትነት የዋህ ትዕቢት፣ ወጣት ልባችንን የሞላበት ጊዜ፣ የሰፈሩ
ወጣት ሴቶች እናተ ልጆች ያሻችሁን ጠይቁን” በሚል ዘወርዋራ ፈገግታ፡ የዕድሜ እኩያ እንዳልገንን ሁሉ ለትልቅ ሰው ከሚሰጥ አክብሮት ጋር ይሽኮረመሙልን የነረበት ጊዜ( ለእናተ ያልሆነ ሴትነት ዓይነት) ትምህርት ላይ ደከም ያሉ የሰፈራችን ልጆች
በወላጆቻቸው እንደነሱ አትሆኑም?” እየተባሉ ስማችን ከኩርኩም ዝናብ በፊት
እንደመብረቅ ጆሯቸው ላይ ይንባረቅባቸው የነበረበት ጊዜ “ምነው እነዚህን ልጆት ከዚህ ሰፈር በነቀለልን”ብለው በሆዳቸው ሳይረግሙን አልቀሩም (መማር ባይሆንላቸው
መራገም አያቅታቸው) አላፊ አግዳሚው በኩራት ፈገገ ይልልን በነበረበት ጊዜ ይኼም ፈገግታ ትምህርት ሚንስቴር እውቅና ሰጥቶቷቸው ከፈተነን “ኬሚስትሪና ማተማቲክስ ምናምን 'ሰብጀክቶች በላይ፡ የሰፈሩ ሰው በአደራ ሰጥቶን በከፍተኛ ውጤት ላለፍነው
“በጎ አርአያነት ነፍሳችን ካርድ ላይ የሚያስቀምጠው “A” በነበረ ጊዜ
ያ ጊዜ ሕይወት ያለ የሌለ እንደ በረዶ የነጣ ጥርሷን ፈገግ ብላ ታሳየን የነበረችበት የክረምት ወር ነበር፡፡ ለእኔና ለጓደኛዩ መሐሪ! “ምን ጓደኛ ናቸው እነዚህ፣ ወንድማማች እንጂ እማምላክንም ይሉ ነበር የሚያውቁን ሁሉ፡፡ አልተጋነነም፡፡ አንድ ሰፈር ነው
ተወልደን ያደግነው፡፡ በቤታችንና በቤታቸው መሃል ያሉት አንድ አምስት ቤቶችና፣የሰፈሩ ልጆች ኳስ የምንጫወትበት አቧራማ ሜዳ ብቻ ነበሩ የመሃሪ እናት ዝንጥ ያለች የቢሮ ሠራተኛ ነበረች፡ ማሚ የምንላት መልከመልካም እናት፤ አገር ምድሩ እትዬ ሮሚ” የሚላት፡ ዘርፋፋ ባለ ከሸከሽ ቀሚስ በመቀነት ሸብ አድርገው ነጠላ በሚያጣፉ እናቶች መሃል ጉልበቷ ድረስ ያጠረ ቀሚስ የምትለብስ፣ ቀጥ ያለ አቋም ያላትና ጸጉሯን ባጭሩ የምትቆረጥ በእውቅ የተቀረጹ ዓምዶች በመሳሰሉ ውብ ጠይም እግሮቿ በተራመደች ቁጥር፣ እንደ ሙዚቃ በተመጠነ ርቀት ቋ ቋ ቋ የሚል ድምፅ በሚያወጣ ባለረዥም ተረከዝ ጫማ የምትውረገረግ ዘመናዊ እናት፡፡ ባሏ የጸሐፊነት ሥራዋን እንድታቆም አድርጓት በኋላ ተወችው እንጂ፡ በፊት በፊት መሐሪን ጧት እቤታችን አምጥታ ለእናቴ ትተወውና ወደ ሥራዋ ትሄዳለች፤ ስትመለስ ትወስደዋለች።አብረን ነው ያደግነው፡፡ ነገሩ ዋጋ ተቆርጦለት የልጅ ጠባቂነት አይሁን እንጂ፡ ለቤተሰቦቼ
በሰበብ አስባቡ ገንዘብም ቁሳቁስም መደገፏ አይቀርም ነበር፡፡ ከዚያ
ዕድሜያችን ጀምሮ እኔም ሆንኩ መሐሪ ሌሎች የመንደሩ ልጆች ጋር ቅርበታችን
እምብዛም ነበር፡፡

ማሚ ሁለታችንንም ግራና ቀኝ ይዛን ቄስ ትምህርት ቤት ስትወስደን ትዝ ይለኛል፡፡
በሕፃንነት ዕድሜያችን (አምስት ዓመት ቢሆነን ነው) ያኔ መንገድ ላይ ሰላም ያሏትን ሰዎች ስም ዝርዝር ብባል፣ አንድ ባንድ አስታውሳቸዋለሁ፤ በተለይ ወንዶቹ
የሚያሽቆጠቁጣቸው ነገር ነበር!

ታዲያ መምሬ ምስሉ ለተባሉ ፊደል አስቆጣሪ ስታስረክበን፣ በሹክሹክታ እንዲህ ስትላቸው ሰማኋት"የኔታ አንድ ላይ ከተቀመጡ መላም የለው፧ አነጣጥለው ያስተምሯቸው መሐሪ ግን እንዲህ ስትል አልሰማኋትም አለኝ፡ አቋቋማችን እኮ ከእኔ ይልቅ እሱ ይቀርብ ነበር፡፡ ስንት ዓመት አልፎ፣ ካደግን በኋላ፣ ማሚን ስንጠይቃት “ውይ! በምን አስታወስከው ልጄ?” ብላ በሳቅ ፍርስ አለችና ብያቸዋለሁ እውነትህን ነው ብላ አመነች። መሐሪ እየሳቀ የሆነ ሼባ ነገር ነው ነገር አይረሳም አለ ሁልጊዜም
ዝንጉቱን የሚያስተባብለው፤ እኔን ነገር ከነከስኩ የማለቅ ሽማግሌ በማድርግ ነበር፡፡
ጎን ለጎን ተቀምጠን ሰዎቸ ለሁለታችንም ያወሩልንን አለፍ ስንል “ምናሉ? ብሎ
የሚጠይቅበኝ ጊዜ ብዙ ነው ለዙሪያው ቸልተኛ ነበር!

መምሬ ምስሉ የማሚን አደራ ለመጠበቅ በቁጣም በአለንጋም ሊነጣጥሉን ብለው
ብለውን አልሆን ስላላቸው እኒህ ልጆች፣ እንደ ዳዊትና የዮናታንን ጓደኝነት ነብሳቸው አብሮ የተሰፋ ነው!” ከሚል ምሳሌ ጋር እንደ ፍጥርጥራችሁ ብለው ተውን፡፡ ለረዥም ጊዜ ዳዊትና ዮናታን ረባሽ የቄስ ትምህርት ቤት ሕፃናት ይመስሉኝ ነበር፣ ሮሐ ናት በኋላ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ ጓደኛሞች መሆናቸውን የነገረችን (ሰንበት ትምህርት
ቤት ተማርኩ ብላ) ይኼንንም የነገረችን ቀን አብረን ሰምተን ዞር ስትል መሐሪ
ምናለች” ብሎኛል፣ አድጎም አልለቀቀው! ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አስራ ሁለተኛ ክፍል
እስክንደርስ እኔና መሐሪ ተነጣጥለን አናውቅም።አንድ ክፍል፣ አንድ ወንበር፣ አልፎ አልፎ ጎን ለጎን ያሉ ክፍሎች፡ ግን አንድ ትምህርት ቤት ነበር ያሳለፍነው።

ዐሥረኛ ክፍል ስንደርስና መሐሪ ሮሐ ከምትባል ልጅ ፍቅር ሲጀማምረው ነበር፣ ሦስተኛ ሰው አብሮን የታየው፤ያኔ ታዲያ ሮሐን ወደድኩ ሲል (ባይወዳት ነበር የሚገርመኝ ሁለታችንም ብርክ ያዘን፤ ነገሩ ጋሼ ጋር ከደረሰ ሁለታችንንም ከገጸ-ምድር ያጠፋናል የሚል ፍርሃት ነበር ያራደን፡፡ ጋሼ የምንለው የመሐሪን አባት ነው፡፡ ጋሽ ዝናቡ ዶፍ ቢሉት ይሻል ነበርኮ” እንባባላለን እኔና መሐሪ ስናማው። ጋሽ ዝናቡ ሲቆጣ፣ ቁጣው ልክ እንደ ርዕደ መሬት ከሰው አልፎ የቤቱን እቃዎችና የግቢውን ዛፎች የሚያንዘፈዝፍ ይመስል ነበር፡፡ ፊቱ የማይፈታ፣ ረዥም ቦክሰኛ የሚመስል ሰው ነበር፡፡ ዳኛ ስለሆነ ነው መስል ቤታቸው ፍርድ ቤት ነበር የሚመስለኝ፡፡ መሐሪም፣ ማሚም ተሽቆጥቁጠው ነው
የሚኖሩት፡፡ ደግነቱ ቁጣው በየአራት ዓመት አንዴ የሚከለት የተፈጥሮ አደጋ ዓይነት ነበር፡፡ ያንን መሬት አንቀጥቅጥ ቁጣውን ያስነሳሉ ተብለው በቤተሰቡ የታወቁ እና ቤተሰቡ እንደተላጠ የኤሌክትሪክ ሽቦ ላለመንካት የሚጠነቀቃቸው፣እንደ ዐሠርቱ
ትዕዛዛት ከቤተሰቡ አልፎ በእኔም ልብ በፍርሃት ፊደላት የተቀረጹ ምክንያቶች ቢበዙ ከሦስት አይበልጡም ነበር

የመጀመሪያው ምክንያት ዝርዝሩ አይገባኝም እንዲሁ እቤታቸው ጎራ ባልኩበት ጊዜ ሁሉ ከለቃቀምኩት ደመ ነፍሳዊ መረጃ ገባኝ ያልኩት ወደ እውነት የሚጠጋ ጥርጣሬ ነው በማሚ(በሚስቱ) እንደሚበሳጭ ይገባኝ ነበር …ነገረ ሥራዋ ያበሳጨዋል! ምንጊዜም እቤት ሲገባ አጋጣሚ ቤት ውስጥ ከሌለች በቁጣ ይጠይቃል “የት ሄደች?” መሐሪ በፍርሃት እየተንተባተበ ማሚ የሄደችበትን ያስረዳል፡፡ ብዙ ጊዜ ወይ የታመመ
ልትጠይቅ፣ አልያም ለቅሶ ልትደርስ ነው የሚሆነው መልሱ! ጋሽ ዝናቡ ታዲያ “የሷ ለቅሶ አያልቅም!” ይላል! ድምፁ ውስጥ መነጫነጭ አለ! ጋሽ ዝናቡ እንዲህ ይጠይቅ እንጂ፣ ማሚን እቤት ቢያገኛት ደግሞ፣ ሰላም እንኳን ሳይላት አልፎ ነበር የሚገባው…ብዙ ጊዜ እንደባልና ሚስት ፈታ ብለው አይነጋገሩም
1👍1
ሁለተኛው የጋሽ ዝናቡ ቁጣ መነሻ፣ የመሐሪ ትምህርት ነበር፡፡ መሐሪ በምንም ምክንያት ከትምህርቱ የሚያዘናጋ ነገር ፈጸመ፣ አልያም ዝቅተኛ ውጤት አመጣ ማለት በቃ ቤቱ በአንድ እግሩ ቆመ! እንዲህ በቀላሉ “ቁጣ!” ተብሎ የሚታለፍ ዓይነት አልነበረም! ከዚህ ቁጣ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቅሁት እኔና መሐሪ የአምስተኛ ክፍል ተማሪዎች እያለን ነበር፡፡ እስከ እዚያ ጊዜ ድረስ እንኳን ከክፍል ከአጠቃላይ ትምህርት ቤቱ አንደኛ
እየወጣን የምናልፍ ልጆች በዚያ ዓመት መሐሪ ከክፍሉ ተማሪዎች አራተኛ፡እኔ አምስተኛ ደረጃ ወጥተን ወደ ስድስተኛ ክፍል ተዘዋወርን፡፡ መዘዋወር አይበለው፡፡
ለውጤታችን ማሽቆልቆል ምክንያቶቹ ሙዚቃ፣ሥነ-ሥዕልና እና እጅ-ሥራ የሚባሉ ትምህርቶች ነበሩ፡፡ ለማሳበብ ሳይሆን፣ የእውነትም እነዚህ ትምህርቶች ነበሩ የነጀሱን፡፡ ደግሞ ሦስቱንም የትምህርት ዓይነቶች አንወዳቸውም! በተለይ የእጅ-ሥራ የሚባለው
የትምህርት ክፍለ ጊዜ ደመኛችን ነበር፡፡

አስተማሪዋ ወደ ክፍላችን ስትገባ አንዳች ከአንታርክቲካ ድረስ ትከሻዋ ላይ ተፈናጦ
የመጣ የሚመስል ቀዝቃዛ አየር ተከትሏት ይገባና ክፍሉን ይሞላዋል፡፡ ደግሞ ለከፋቱ ከዚያ አስቂኝና ክፍሉን ሳቅ በሳቅ ከሚያደርገው የሒሳብ አስተማሪያችን ቀጥሎ ባለው ክፍለ ጊዜ ነበር የምትገባው፡፡ ስላቅ፣ በጨዋታ፤ በጥያቄና መልስ፣ በጭብጨባ፣ ልክ እንደብረት ግለን፣ ቁጥሮችን እንደጥይት ስንተፋ…. ያች አስተማሪ ቀሰስ እያለች ስትገባ
በጋለ ብረት ላይ እንደተደፋ ቀዝቃዛ ውሀ ቸሰሰሰሰሰሰሰስ ያልን ይመስለኛል፡፡ የሌላውን ተማሪ እንጃ፣ እኔ ግን ብርድ ብርድ ነበር የሚለኝ፡፡ ነገረ ሥራዋ ሁሉ የሚሸክክ ሴትዮ፡፡በፊቷ ላይ ሳቅም ቁጣም የለም፣ ድምፁዋ ዝቅም ከፍም አይል፡፡ እራሷ ከጅብሰም ምናምን ተፈልፍላ የተሠራች እጅ ሥራ ነገር ነበር የምትመስለኝ፡፡

ይቀጥላል

ለአስተያየቶ @atronosebot ን ይጠቀሙ
አትቋጥሩ #Share እያደረጋቹ ቤተሰብ
👍1
አትሮኖስ pinned «#ከዕለታት_ግማሽ_ቀን ፡ ፡ #ክፍል_አንድ ፡ ፡ #በአሌክስ_አብርሃም የዛሬ አሥራ ሦስት ዓመት እግዚእብሔርን ለመሆን ተመኝቼ ነበር፤ አልተሳካልኝም፡፡ . እግዚእብሐርን መሆን ስላልተሳካልኝ “በቃ ለምን ሰይጣን አልሆንም?” የሚል ሐሳብ ውል ብሎብኝ፡ ሰይጣን ለመሆን ሞከርኩ እሱም ቢሆን እንዲህ እንደሚወራው ቀላል አልነበረም(ክፋት በሰይጣን እጅ ያምር፤ሲይዙት ያደናግር) እንግዲህ ሁለቱንም ካልሆንኩ ራሴን…»
#ከዕለታት_ግማሽ_ቀን


#ክፍል_ሁለት


#በአሌክስ_አብርሃም


የሌላውን ተማሪ እንጃ፣ እኔ ግን ብርድ ብርድ ነበር የሚለኝ።ነገረ ስራዋ ሁሉ የሚሸክክ ሴትዮ።በፊቷ ላይ ሳቅም ቁጣም የለም፣ ድምፁዋ ዝቅም ከፍም አይል። እራሷ አጅብሰም ምናምን ተፈልፍላ የተሰራች እጅ ሥራ ነገር ነበር የምትመስለኝ።ገና በመጀመሪያው ቀን የእጅ ሥራ የሚባለውን ትምህርት ስንጀምር፣ ሰላም ! ከሰፈነበት ክፍላችን አሰልፋ የእግር ኳስ ሜዳውን ተሻግሮ ወደ ሚገኘው “የእጅ ሥራ ክፍሉ ወደሚባል ሕንፃ ወሰደችን፡፡ ከትልልቅ ጥርብ ድንጋዮች የተሠራና ግራጫ የሸክላ ጣሪያ
የተደፋበት ግብ ቤት ነው፡፡ በድንጋዮቹ መጋጠሚያ ላይ እረንጓዴ ሻጋታ እንደ
አረንጓዴ ሽበት የጋገረበት ጣሪያው ላይ ብዙ ሣር ያበቀለበት፣ ለሞላ የወፍ ዘር
ድብርታም ዋነሶች ብቻ የሚሰፍሩበት ዕድሜ ጠገብ ግንብ ቤት ነው፡፡ ዱሮ ጣሊያን ሰዎችን እያሰረ የሚያሰቃይበት
እስር ቤት ነበር ይባላል! በመስኮቱ ትክክል በዕድሜ ብዛት የዛገ የ በ ቅርጽ ያለው የብረት ጎል አለ፡፡እስረኞችን ከዚህ ክፍል እያወጡ እዚህ ብረት ላይ በስቅላት ይቀጧቸው ነበር፡፡ ሆነ ብለው ነው በመስኮቱ ትክክል የሰሩት፡፡
እስረኞቹ ሰው ሲሰቀል በመስኮት በኩል አሻግረው እንዲመለከቱና ሞትን ፈርተው
ጣልያንን እንዲተባበሩ፡፡ ነገሩ ነበር ብቻ ሳይሆን፣ ምስክር ያለው ታሪክም ነው።

አፈሩ ይቅለላቸውና፣ ከዓመት እስከ ዓመት የጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ጥበቃ ሆነው ይሠሩ የነበሩ፣ በየዓመቱ የአርበኞች ቀን ሲከበር ደረቱ ላይ ግራና ቀኝ ብዙ ሜዳሊያ የተደረደረበት የአርበኛ ካኪ ልብሳቸውን ለብሰውና፤ ወርቃማ የዘንባባ ጥልፍ ያለበት ባርኔጣቸውን ደፍተው፣ አሮጌ ጦር እየሰበቁ (በኋለኛው ዘመን እርጅናው ተጭኗቸው ተውት እንጂ ትልቅ ጋሻም ነበራቸው) በቴሌቪዥን የሚቀርቡት ሰውዬ ታሪክ ሲናገሩ
በጆሮዬ ሰምቻቸዋለሁ “ጥሊያን አርበኞቹ በዱር በገደል ሲያስቸግሯት፣ የአርበኞች
ቤተሰቦች ማሰቃየት ጀመረች እዚህ ታች አሁን “አጤ ብልጣሶር ተማሪ ቤት” የተባለው ውስጥ፣ የግንብ እስር ቤት ሠርታ ሰውን ሁሉ እየሰበሰበች ማጎር፣ ጠቁሙ እያለች መግረፍ፣ መስቀል ጀመረች እስከ አሁን ያ እስር ቤት ተማሪ ቤቱ ውስጥ አለ” ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ “ዓፄ ብልጣሶር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” ማለት እንግዲህ፣ የኛ ትምህርት ቤት ነው።

ያች አስተማሪ ታዲያ አሰልፋ የወሰደችን ወደዚያ ከፍል ነበር፡፡ ውስጡ በጠራራ ፀሐይ እንኳን የሚያንዘፈዝፍ ብርድ ያለበት ሰፊ አዳራሽ፣ የንብረት ማስቀመጫ ሆኖ በመከረሙና ተጸድቶ ባለማወቁ፣ እምክ እምክ የሚሸትና በአቧራ የተሸፈነ ነበር።ግማሽ የሚሆነው የአዳራሹ ክፍል ተማሪዎች ከወረቀት፣ ከካርቶን፣ ከጣውላና ከብዙ ዓይነት ቁሳቁስ በሠሯቸው የእንስሳትና ሰው ቅርጻ ቅርጾች፣ በተሰባበሩ ወንበሮች፡
በተከመሩ እሮጌ መጻሕፍትና ገና ባልተከፈቱ ብዙ ካርቶን ጠመኔዎች የተሞላ ነበር

እንግዲህ በመጀመሪያ ከፍለ ጊዜ ስሟን እንኳን በወጉ ሳታስተዋውቀን በዚያ ቅዝዝ ባለ ድምፅ ይሄን አዳራሽ አፅዱ!” አለችን፡፡ ከዚያን ቀን ጀምሮ ያ ክፍል እኔም መሐሪም ማየት ራሱ ያንገሸግሸን ነበር፡፡ ከስንት ዓመት በኋላ ትምህርት ቤቱ ሙሉ ለሙሉ ፈርሶ ሲታደስ፣ ያ…የድንጋይ ከፍል ቅርስ ነው!” ተብሎ እንዳለ ነበር የተተወው፡፡ በኋላ እኔና መሀሪ አስራ ሁለተኛ ክፍል እንደጨረስን ሮሐን በመሀላችን አድርገን በሩ ላይ ፎቶ ተነስተናል፡፡ እሷ እንዳካበዳትሁት አይደለም ያምራል” አለች! ተያይተን በሳቅ ፈረስን!

የዚች አስተማሪ ሌላው አስገራሚ ሥራ፣ አንድ ቀን ከቀንም ቀን ቅዳሜ ቀን ጧት
ትምህርታዊ ጉብኝት እናደርጋለን፡፡” ብላ ጠራችን፡፡ ቅዳሜን በሚያህል ቀን ትምህርት ቤት መጠራታችን ሳያንስ፤ልታስጎበኘን የወሰደችብን ቦታ ይኼው ሩብ ክፍለ ዘመን ሊሆነው ተቃርቦ እንኳን ትዝ ሊለኝ ይዘገንነኛል፡፡ ያው እንግዲህ እሷ እንደምትለውና ድሮ እጅ ሥራ ደብተሬ የመጀመሪያ ገጽ ላይ ጽፌው እንደተኘው የእጅ ሥራ ትምህርት መሠረታዊ ዓላማው የተማሪዎችን የፈጠራ ክህሎት እና የአምራችነት ፍላጎት
ከፍ በማድረግ አምራች ዜጋ ማፍራት ነው" ይህን ከህሎት ያዳበሩና ለእኛ አርአያ ሊሆኑን የሚችሉ የእጅ-ሥራ ጥበብ ባለሙያዎች ወደሚገኙበት ቦታ ነበር ለጉብኝት የወሰደችን፡፡ የከተማው ማረሚያ ቤት! ከጣሊያን እስር ቤት ወደ ሐበሻ እስር ቤት፡፡

የማረሚያ ቤቱ የግንብ አጥር የተሠራበት ድንጋይ የትምህርት ቤታችን የእጅ-ሥራ ክፍል ከተሠራበት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ድንጋዩ ብቻ ሳይሆን፣ አሰካኩም አንድ ዓይነት ነበር፤ ወይ ይኼንንም ጣሊያን ሠርቶታል አልያም ከጣሊያን እግር ሥር ቁጭ ብለው የተማሩ የአበሻ መሐንዲሶች አንጸውታል፤ መቼስ ደግደጉን መማር ባንዳነት አያስብል፡፡ የማማው ከፍታ ደመናውን ሰንጥቆ የገባ ነበር የሚመስለው፡፡ ከብዙ ፍተሻ ሰኋላ ከባዱ
ተንሸራታች የብረት በር በሁለት መሣሪያ በታጠቁ ወታደሮች እየተገፋና ሲጢጢጢ እያለ ሲከፈት፣ የሚያለቅስ ይመስል ነበር… በሰሩ መንሸራተቻ የብረት ሃዲድ ላይ የተደፈደፈው የጆሮ ኩክ የመሰለ ግራሶ እንደእንባ ግራ ቀኝ ቀልጦ ይፈስሳል፡፡

ወደ ግቢው በሰልፍ ስንገባ፣ በሕይወቴ ይኖራል ብዬ የማላስበው ዓለም፣ ፊት ለፊቴ ተጋረጠ… መጨረሻቸው የማይታይ፣ በጣም ብዙ እሮጌ የቆርቆሮ ቤቶች ከስንትና ከስንትና ዓመታት በፊት ፋሽናቸው ነፍሶበት ወደ ቅርስነት የሚያዘግሙ፣ የተረሱ የድሮ ፎቶዎች
ላይ ብቻ የማውቃቸውን ልብሶች የለበሱ ታራሚዎች ግቢውን ሞልተውታል።

እንዳንዶቹ አቧራው እንደ ደመና የሚነሳ ሜዳ ላይ እየተጯጯሁ መረብ ኳስ ይጫወታሉ።ግቢው ራሱ ይኼ ነው የማይባል የተለየ ሽታ ነበረው።ለምንም ነገር ግድ የሌላቸው የሚመስሉ ታራሚዎች፣ በቸልታ ያዩናል …ደግሞ ለከፋቱ ገና በሩ ላይ እንደደረስን የአእምሮ ሕመምተኛ የሆነ ታራሚ ፊት ለፊታችን ገጠመን፡፡ ልብሱ እላዩ ላይ አልቋል፣ በባዶ እግሩ ነበር … ልጋጉ ይዝረበረባል፣ እግርና እጁ የታሰረበትን ከባድ ሰንሰለት እያቅጨለጨለ ሳያቋርጥ ቻው ቻው ቻው መውጣት የለም ቻው በቃ ገባችሁ፣ መውጣት የለም …” ይለናል ያ ድምፅ እስከ ዛሬ ጆሮዬ ላይ አለ።

እንደተሰለፍን በእስረኞች መሃል አልፈን፣ የእደ ጥበብ ክፍል ወደሚባለው ትልቅ የቆርቆሮ አዳራሽ ተወሰድን፡፡ ወደ ውስጥ ስንገባ ብዙ የሽመና ሥራ የሚሰሩ
ታራሚዎች እግራቸውን ጉድጓድ ውስጥ ቀብረው ነጠላ ጋቢ ይሰራሉ…አንዳንዶቹ
ረዣዥም የክር ድር እዚያና እዚህ ግድግዳ ላይ በተሰኩ ሚስማሮች ላይ ያደራሉ።ግርግሩ ለጉድ ነው፣ ጫጫታው ይጨንቃል፡፡ አስተማሪያችን ሰብሰብ አደረገችንና “ወደሚሰሩት ሰዎች እየሄዳችሁ፣ ምን እንደሚሰሩ? እንዴት እንደሚሰሩ? የመሥሪያ መሣሪያዎቻቸው ስም ምን እንደሚባል እየጠየቃችሁ ማስታወሻ ያዙ:” አለችን፡፡ግራ
እንደገባን እኔና መሐሪ ወደ አንዱ ጸጉሩን ወደተላጨ ሸማኔ ጠጋ ብለን ከግራ ወደቀኝ ከቀኝ ወደግራ የሚወረውራትን፣ ውስጧ የሚተረተር ነጭ ክር ያለባትን መወርወሪያ ስንመለከት፣ ሸማኔው ድንገት በዜማ፤

ተማሪ ውሻ ቀባሪ ውሻ ሲቀብር… አነቀው ነብር…” አለና ልክ እንደ ነብር ጥፍር
ጣቱን ለቀልድ እንጨፍርሮ ሲቃጣን፤ ደንግጠን ወደኋላ ስናፈገፍግ ሌሎቹ በሳቅ አውካኩ።

ወይ የዘንድሮ ተማሪ ቤት ….እንደያው እሁን ምን ሊያስተምሩ እዚህ ሲኦል
አመጧችሁ?” አለን፣ ለራሱ በሚመስል አነጋገር፡፡ ትኩስ የተላጨው ሞላላ አናቱ ላይ አልፎ አልፎ ቋቁቻና ጠባሳ ነገር አለው፡፡

“ለምንድነው የታሰርከው” አልኩት ድንገት፡፡ ያልጠበቀው ጥያቄ ስለሆነ የገረመው ይመስል፣ አንዴ እኛን፣ አንዴ ጓደኞቹን ተመለከተና፣
👍3
ከት ከት ብሎ ስቆ

አረግ! ጋዜጠኛ ነውና የላኩብን ጃል?” ብሎ ሳቀ፡፡

“ምናሉ?” አለ አንድኛው

ለምን ታሰርክ ይለኛል?”

ከጎኑ ያለ ሌላ ታራሚ ጮክ ብሎ " ሚስቱን ገሎ ነው” አለ፡፡ አሁንም አውካኩ…

ለምን?” አለው፣ መሐሪ ደንግጦ! ፊቱ ጭው ብሎ ነበር

ለሌላ ሰጥታበት!” ያው የመጀመሪያው ሰውዬ ነበር፤ ሳቃቸው መቆም አልቻለም፡፡
እየተቀባበሉ እውካኩ፡፡ “በተኛችበት ጨፍጭፎ …ሃሃሃሃሃ…” ሳቃቸው፡፡ ያስፈራ ነበር፡፡

ሰውዬው ግን ድንግት ኮስተር ብሎ፣ “ልጅ ናችሁ …ሸማ ሸማውን አይታችሁ ሂዱ!”
አለና፣ ወደ ሽመናው ተመለሰ፡፡ መወርወሪያዋን ሲወረውር ተስፈንጥራ ወደቀችበት፡፡የተቆጣ ይመስል ነበር፡፡ ቀስ ብለን ወደሌሎቹ አለፍን፡፡ በእደ ጥበብ አዳራሹ ውስጥ ሽመና፣ ጣውላ ሥራ፣ ሰሌን፣ የተለያዩ ጥልፎች የሚሠሩ ታራሚዎችን ስናይ ቆይተን ስንወጣ፣ የሚጨስ ትኩስ ክክ ወጥ የተሞላ ትልቅና የተትረከረከ የብረት ባልዲ፣ በማንጠልጠያው በኩል ረዥም እንጨት አስገብተው፣ ግራና ቀኝ ለሁለት የተሸከሙ ሰዎች ባጠገባችን አለፉ:: አካባሲው ወጥ ወጥ ሸተተ፡፡ ወዲያው፣ ቀጭን ለጆሮ የሚቀፍ የብረት ደውል ተደውሎ “ምሳ! ምሳ” እያሉ ታራሚዎቹ ሲተረማመሱ፣ እኛም እንዳመጣጣችን በሰልፍ ወጣን፡፡ ትልቁ የብረት በር እያለቀሰ ሲዘጋ፣ ሁሉም ነገር ከኋላችን ዝም አለ!! እጅ ስራም፣ የእጅ ሥራ ትምህርትም፣ እስር ቤትም አስጠልቶን
ቀረ፡፡ እጅ ሥራ የተማረ ሰው ሲያድግ የሚታሰር ይመስለኝ ነበር፡፡

ከጉብኝቱ በኋላ በነበረን የእጅ ሥራ ክፍለ ጊዜ “ስለጉብኝቱ ጥያቄ ካላችሁ ጠይቁ!”
በተባልነው መሠረት፣ መሐሪ ቀድሞ እጁን አወጣና “ቲቸር እስረኞቹ ግን ለምን በሌሊት አያመልጡም?” ብሎ ጠየቀ፡፡ “ቲቸር” ምንም ምንም ሳትናገር ቁማ መሐሪን ስታየው ቆየች፤ እናም ረጋ ባለ ድምፅ እንዲህ አለች፣

ሌላ ጥያቄ ያለው?”

ይቀጥላል

ለአስተያየቶ @atronosebot ን ይጠቀሙ
ለወዳጆ #Share እያደረጉ
አትሮኖስ pinned «#ከዕለታት_ግማሽ_ቀን ፡ ፡ #ክፍል_ሁለት ፡ ፡ #በአሌክስ_አብርሃም የሌላውን ተማሪ እንጃ፣ እኔ ግን ብርድ ብርድ ነበር የሚለኝ።ነገረ ስራዋ ሁሉ የሚሸክክ ሴትዮ።በፊቷ ላይ ሳቅም ቁጣም የለም፣ ድምፁዋ ዝቅም ከፍም አይል። እራሷ አጅብሰም ምናምን ተፈልፍላ የተሰራች እጅ ሥራ ነገር ነበር የምትመስለኝ።ገና በመጀመሪያው ቀን የእጅ ሥራ የሚባለውን ትምህርት ስንጀምር፣ ሰላም ! ከሰፈነበት ክፍላችን አሰልፋ…»
#ተአምረኛው_አባ

ለምድረ በዳይቱ አገራቸው
ሽፍታ ላስቸገረው ሕዝባቸው
ሊጸልዩ ሊሰግዱ
ሊማልሉ ሊማልዱ
አባ ተኝተው መሬት
በ'ንባ በሳግ በምሬት

“ጌታ ሆይ
አገሬን ባክህ አጽናናት
ከቀማኞች አድናት”
በማለት አርባ ዓመት ሙሉ
ኪራላይሶ ስማኝ ሲሉ
እሱም ተልቡ በማድመጡ
ቀማኞች ከሕዝቡ ወጠ
እናም ከጊዜ በኋላ
የመናኙ ያባ ገላ
ተለውጦ እንደ ዘበት
ግዙፍ ጫካ በቀለበት
አባም ይህን ታምር ቢያዩ
እንዲህ በለው ጸለዩ

“ጌታ ሆይ
እነሆ የጌ ብፅዕና
ይኸውልህ ዛሬ ገና
ቀማኞችን ከሕዝብህ
አውጥቶ አስኮበለለ
ከመሬታችን ተሽሎ
ገላዬም ደን አበቀለ
ከቀባሀቸው ጣድቃን መሀል
እኔን 'ሚያክል ማን አለ?”
በታብዮ ይህን ብለው
ምልጃቸውን ሲዘጉ
ከሕዝብ የሸሹ ሽፍቶች
መጥተው እየተንጋጉ
ጀርባቸው ላይ ባለው ደን ውስጥ
ጥልቅ ብለው ተሸሽጉ!፡፡

🔘በዕውቀቱ ስዩም🔘
👍1
#የእህል_ውሃ_ነገር

ለሕይወትሽ መቆያ ሆኜ እንደባቄላ
በነገርሽ ምጣድ በቋያሽ ስቆላ
እንደወይን ዘለላ ገፄ እንኳ ቢቀላ
ተጥጄ ብበስልም ፍሜም ሳልበላ
በ'ሳት ተንገብግቤ
በውሃ ተንገርግቤ
ለነፍስሽ ተሹቄ ራሴን አስርቤ
እኔ ጠፍቶ ሳቄ አንቺን ግን መግቤ
መኸርን ከርመሻል
ፀደይን አልፈሻል
በጋውን ዘልቀሻል
ወቅቱም ተፈራርቆ
ለክረምት በቅተሻል፡፡
ጊዜ ጊዜን ፈጅቶ
የእሳትሽ ወላፈን እቶኑ በርክቶ
ነበልባሉ ከፍቶ ቆዳዬ ሥር ዘልቆ
የኔ ገላ ነዶ የኔ ገላ ሾቆ
ባንቺው ውበት አጥቶ ባንቺው ጣዕሙ አልቆ
ያረረው ተተፍቶ ተጠርጥሮ ወድቆ
በለኮስሽው እሳት ባኖርሽው ማገዶ
እኔንም፤ ቤትሽንም ፤
አደረግሽን ኦና አደረግሽን ባዶ፡፡
አንቺ ትኩሳቴ!...
ባዶ ቤት በክረምት እኔ የሌለሁበት ፤
ከተስማማሽ ሕይወት ይድላሽ ተንቧቺበት፡፡
ይመችሽ ኑሪበት፡፡
እኔማ ምን አለኝ ?
ባዶ ነኝ፤ ወና ነኝ፡፡
ብሆንም ውዴ ሆይ.
ክረምቱን እንዳንቺ
እምጠለልበት
እማሳልፍበት
ባይኖረኝ ባዶ ቤት
ከልብ በመነጨ በእውነተኛ ስሜት
እኔስ እልሻለሁ ፍቅሬ ብቻ በርቺ
ውዴ የኔ እመቤት በይ ደህና ሰንብቺ፡፡

🔘በፋሲል🔘
#ከዕለታት_ግማሽ_ቀን


#ክፍል_ሶስት


#በአሌክስ_አብርሃም

ከጉብኝቱ በኋላ በነበረን የእጅ ሥራ ክፍለ ጊዜ “ስለጉብኝቱ ጥያቄ ካላችሁ ጠይቁ!”
በተባልነው መሠረት፣ መሐሪ ቀድሞ እጁን አወጣና “ቲቸር እስረኞቹ ግን ለምን በሌሊት አያመልጡም?” ብሎ ጠየቀ፡፡ “ቲቸር” ምንም ምንም ሳትናገር ቁማ መሐሪን ስታየው ቆየች፤ እናም ረጋ ባለ ድምፅ እንዲህ አለች፣

ሌላ ጥያቄ ያለው?

ይኼ ሁሉ ነገር ሳያንሰን፣ አስተማሪያችን ሥሩ እያለች የምታዘው ነገር ሁሉ ያበሳጨን ነበር። እኔና መሐሪ አንድም ቀን የምታዘውን ሠርተን እናውቅም… ከሙቅና ከወረቀት ሰሃን ሥሩ አለችን ድፍን የከፍሉ ልጅ የወረቀት ሰሀኑን፣ ሰባት ቀን ያደረ ደረቅ ቂጣ አስመስሎ ሲመጣ(ደግሞ ሽታው ሲያስጠላ) ሁለታችን ብቻ ባዶ እጃችንን ቁልጭ ቁልጭ እያልን ተገኘን፡፡ ከሃያ ዜሮ ሰጠችን!! ከሃያ ዜሮም፣ ከሃያው ሃያም ስትሰጥ ፊቷ ላይ ምንም የተለየ ስሜት አይነበብም ነበር፡፡ የመሐሪን እናት ማሚ ስለሙቁ ስንነግራት ፈገግ ብላ “መሥራት ነበረባችሁ!” አለችን፡፡ ተባብረን ልናሳምናት ሞከርን፡፡

እንዴ ማሚ! ስንት ሕዝብ በሚራብበት አገር፣ በእርዳታ የሚገኝ ስንዴ ለእጅ ሥራ እያልን...

ትክ ብላ አየችንና “ወሬኞች!” ብላ ወደ ሥራዋ ሄደች፡፡ ፊቷ ላይ ግን ፈገግታ ነበር፡፡ማሚ ሁልጊዜ እኛ ጋር ስታወራ፣ ፊቷ ላይ ወይ ለይቶለት የማይፈነዳ፣ አልያም ለይቶለት የማይከስም፣ ልክ እንደጥዋት ጤዛ የተንጠለጠለ ውብ ፈገግታ ነበር፡፡ ፈገግታው ሁልጊዜ
ዓይኗ ላይ ነበር፣ ከእንድ ቀን በስተቀር፡፡

ከማረሚያ ቤት ጉብኝታችን የተመለስን ቀን፣ ማሚ ጋር ስላየነው ነገር ስናወራ መሐሪ ካለወትሮው ዝም ብሎ፤ እኔ ነበርኩ የባጥ የቆጡን የማወራው፡፡ ማሚ በጣቷ ጉንጩን ነካ እያደረገች “ምነው ለምቦጭህን ጣልክ?” ስትለው ነበር ዝም ማለቱ ትዝ ያለኝ!እንዳቀረቀረ ሹክሹክታ በሚመስል ድምፅ “ሚስቱን የገደለ ሰውዬ አዬን እዚያ ታስሯል!” አላት፡፡ ማሚ ኮስተር ብላ…

እ? አለች

እኔ ነበርኩ ወሬውን የጨረስኩት፡፡ ስለ ሰውዬው ነገርኳት፡፡ በተለይ ስለ ራሱ ሞላላነትና ስለ መላጣው …ስለ ሚስቱም ጉዳይ!

ማሚ መሐሪን ድንገት ወደ ራሷ ሳብ አድርጋ አቀፈችው፡፡ አጥብቃ አቀፈችው፤ እሱም ታፋዋን አቅፎ ቀሚሷ ውስጥ ተሸጎጠ እና እንዲህ አለች “ሕፃን ስለሆናችሁ እየቀለዱባችሁ ነው” ግን እንደዛም እያለች ማሚ ዓይኖቿ በእንባ ተሞልተው ከንፈሯ ይንቀጠቀጥ ነበር…መሐሪን ትንሽ ገፋ አደረገችውና፣ አፏን በመዳፏ አፍና ወደ ውስጥ እየተጣደፈች ገባች! ወደ መኝታ ቤቷ !
ሌላኛው ጠላታችን የሙዚቃ ትምህርት ነበር! ሙዚቃ አስተማሪያችን ከዓመት በፊት የትምህርት ቤታችን ሜዳ የሚጠበው ስፖርት አስተማሪ ነበር፡፡ የመኪና አደጋ ደርሶበት ግራ እግሩ በከባድ ጀሶ ተጠቅልሎ፣ በአንድ የብረት ምርኩዝ እየታገዘ መሄድ ከጀመረ
በኋላ ነው የሙዚቃ አስተማሪ የሆነው ድፍን መንፈቅ ዓመቱን ውጭ ሜዳ ላይ
እያስወጣ “ ተጫወቱ!” ይለንና አንዲት ዛፍ ሥር ተቀምጦ፣ ጥርሱን በቀጭን የወይራ እንጨት እየፋቀ ያየናል፡፡ የፈተና ቀን ሲደርስ ግን፣ “በየተራ ተማሪ ፊት እየወጣችሁ ዝፈኑ፣ ሀምሳ ማርክ አለው!” አለን፡፡ “እዚች አገር እንኳን እኛ፣ ዘፋኙ ራሱ ሃምሳ ማርክ አያገኝም!" እያልን አላገጥን እኔና መሐሪ። ብንደረግ ብንሠራ አንዘፍንም አልን፡፡ “ዝፈኑ ስትባሉ ማልቀስ ከፈለጋችሁ ጥሩ!” ብሎ ከሀምሳው ዜሮ አከናነበን፡፡

በኋላ ጎበዝ ተማሪዎች ናቸው እባክህ በሌላም መንገድ ቢሆን ፈትናቸው” ተብሎ በስም ጠሪያችን አማላጅነት ተለምኖና አዝኖልን (እኔ ግን ስጠረጥር ጎበዝ ነን በሚል ትዕቢት ተወጥረው የሙዚቃ ክፍለ ጊዜን እንደናቁ አስተነፍሳቸዋለሁ በሚል ቂም በቀል)
እያንዳንዱ ጥያቄ ዐሥር ነጥብ ያለው የቃል ፈተና ፈተነን፡፡

በገና ስንት ክር አለው …?

ባስብ ባስብ አልመጣልህ አለኝ፡፡ መቼም መንፈሳዊ ነገር ላይ ሰባት ቁጥር አይጠፋም ብዬ ሰባት አልኩ፡፡ፊቱ ላይ የነበረው ቁጣ በሆዱ ለሰባት ይቆራርጥህ!” የሚል አስመስሎት ነበር፡፡ ከፈተናው በኋላ እልህ ይዞን፣ ሰፈራችን ወደ አለው መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን መዝሙር ቤት ሄድን፡፡ መዝሙር ቤቷ በር ላይ ተቀምጦ ያገኘነውን ዘበኛ “በገና ስንት ክር አለው? “ስንለው፣ እኔ አላቅም! መሪ ጌታ ሲመጡ ጠይቁ ብሎ
በቆምንበት ረሳን ፡፡ በገናውኮ ከኋላው ነበር፡፡ እሺ! እንቁጠረው ስንል፣ መሪ ጌታ
ካልፈቀዱ አይቻልም ብሎ ጠመመ! በዚያው ረሳነው!

2ኛ እምቢልታ ከምን ያሠራል?

እምቢልታ ራሱ ምን እንደሆነ አላውቅም…እምቢልታ ማለት ብሎ በሚነጫነጭ ድምፅ በሰፊው እብራራልኝ፣ ያውም ያልጠየቀውን ነጋሪት ሁሉ ጨምሮ! “የሆነ ሆኖ አልመለስከውም” ከሚል መደምደሚያ ጋር፡፡ ስለ እምቢልታና ነጋሪት የዚያን ቀን
አውቅሁ!

3ኛ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅኝቶች ምን ምን ናቸው?

ትዝታ፣ ብዬ ጀመርኩ፡፡ ሌሎቹን ማወቅ አልቻልኩም፡፡ መምህሩ በስክርቢቶው ጫፍ ጢረጴዛውን ሲጠቀጥቅ ቆየና፣ ትክ ብሎ እየተመለከተኝ .. ሌላው ይቅር… ሰው እንዴት አምባሰል ይጠፋዋል? እንዴት ባቲ ይጠፋዋል? አላየንም ጎበዝ ተማሪ !" አለና ወደ ቀጣይ ጥያቄው አለፈ፡፡

4ኛ ሦስት የክር የሙዚቃ መሣሪያዎችን ጥቀስ (ይኼ ሰውዬ የሙዚቃ አስተማሪ ነው ወይስ የዳንቴል ሥራ?ክር ክር ብሎ ሊሞት ነው እንዴ! እያልኩ በውስጤ
ክራር ፣ በጎና ፣ ጊታር ተመስገን!” አለ፡፡ አነጋገሩ ያበሳጭ ነበር ፡፡ በጣም ያበሳጨኝና፣ ሰውየው ነገር መፈለጉ የገባኝ ከዚህ ሁሉ ጥያቄ በኋላ ወደመጀመሪያው ነገር ሲመለስ
ነበር፡፡

የምታውቀውን የአንድ ዘፈን አዝማች በዜማ አንጎራጉር አስተማሪ አይጥመድ! ከዛም ብሶቱን ተነፈሳት “ስማ! ጎበዝ ሁነህ ናሳ ብትቀጠር ፣ጨረቃ… ማርስ ብትረግጥ፣ ካለባህሪ ዋጋ የለውም፣ ዋናው ትሕትና ነው:: ይች አገር ገና
ከጥንት ከአክሱምና ከዛገዌ ዘመን
ጀምሮ፣ ስንት ሊቃውንት፣ ስንት ጠቢባን ነበሯት፣አሏትም፡፡አዋቂ ነጥፎባት
አያወቅም ትሕትና ነው ዋናው ትሕትና! እኔ ተፈሪ ሃያ ሦስት ዓመት ሳስተምር፣ ማንም
እከሌን ፈትን፣ እከሌን ፈተና ቀይርለት ብሎኝ አያውቅም…” ብሎ፣ ግማሽ ዛቻ… ግማሽ ፉከራ የቀላቀለ ረዥም ምከር ከመከረኝ በኋላ፣ መሐሪን ጠራው፡፡
መሐሪም የኔው ዕጣ ነበር ያጋጠመው፡፡ በሕይወት ዘመኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመቶው ሃያ ሦስት ያመጣሁበት ትምህርት ሆነ፡፡ የሚገርመው ነገር መሐሪ ከመቶው ሠላሳ አምስት ማምጣቱ ነበር እንዴት ሠላሳ አምስት ሰጠህ?” ብለው፡፡

“ዘፈንኩ!” አለኝ።

ከምርህ ነው? … "

ታዲያ! ጋሽ ዝናቡ እኔንም ማሚንም ከሚገለን ብዘፍን አይሻልም” ከዚያን ቀን ጀምሮ ለስንት ዓመት፣ እኔም ፍቅረኛው ሮሐም ምን እንደዘፈነ እንዲነግረን ብንጠይቀው፣ ብንለምነው ምስጢር ነው ብሎ ሳይነግረን ቀረ፡፡ ባሕሪው እንደዚህ ነው:: አንድ ነገር ምስጢር ነው ካለ፣ ለምን አይገድሉትም ትንፍሽ አይልም፡፡

በእነዚህ ይዞ ሟች ትምህርቶች ምክንያት፣ እኔና መሐሪ ተያይዘን ገደል ገባን! መብረቅ የወደቀብን ያህል ነበር የደነገጥነው! …ቀድሞ እንዴት እንዳልታየን አልገባኝም፡፡ እኔ እንኳን አራተኛ፣ አርባ አራተኛም ብወጣ “እሰይ ዋናው ጤና! የምትል እናትና አብርሃም ስትመለስ ታሳየኛለህ፤ እስቲ ሂድና ዕቁብ ከፍለህ ና!” በሚል አባት ተባርኪያለሁ፡፡ ለመሐሪ ነበር ሁለታችንም የደነገጥነው፤ እንዲያውም ያንን ካርድ ይዘን ስንመለስ፣ እንደፍጥርጥርህ ብዬው ወደ ቤቴ ልሄድ ነበር፡፡ መሐሪ ግን በቁጣ ቦግ ብሎ
እኔን አጋፍጠኸኝ ልትሄድ ነው እንዴ? አታስብም?” ሲለኝ፣ አሳዝኖኝ አብሬው መብረቅ ልመታ
👍1
እግርና እግሬ በፍርሃት እየተጋጨ ወደ እነ መሐሪ ግቢ ዘለቅን፡፡

ያ! በሰላሙ ቀን እንደ እብድ ስንቦርቅበት የሚጠበን ግቢ፣ ፈንጂ የተቀበረበት የጦር ሜዳ የሆነ ይመስል፣ በጥንቃቄ ፊትና ኋላ ሆነን እየተራመድን ወደ ዋናው ቤት ተጠጋን፡፡
ገና በረንዳው ላይ ስንደርስ ነበር ጋሽ ዝናቡ የሚወዛወዝ ወንበሩ ላይ ተደላድሎ “እሺ! ጎረምሶች” በሚል አስፈሪ ድምፁ የተቀበለን፡፡ እኔና መሐሪ ተያየን! እንዴት በዚህ ሰዓት ጋሸ ዝናቡ በረንዳ ላይ ተገኘ?…ገና ከቀኑ አምስት ሰዓት አካባቢ ነቀር፣ ጋሼ ብዙ ጊዜ ሥራ ከሌለው ከምሳ ሰዓት በኋላ ነበር በረንዳ ላይ ተቀምጦ የሚያሳልፈው ! የተቀመጠበት ወንበር ደጋን በመሳሰሉ ግማሽ ክብ እግሮቹ ወደ ፊትና ወደ ኋላ በተንቀሳቀሰ ቁጥር፣በተረት እንደሰማነው ጭራቅ ጥርስ ቀርጨጭ ቀርጨጭ ቀርጨጭ የሚል ድምፅ ያውጣል! …መሐሪ ካርዱ ከእጁ አምልጦት ወደቀ! ጋሽ ዝናቡ ወንበሩን
ማወዛወዙን አቆመና፣ እጁን ወደፊት ዘርግቶ “እስቲ አምጣው!?” አለ፡፡ ዓይኑን
በወደቀው ካርድ ላይ ተከሎ፤ መሐሪ መንቀሳቀስ ስላልቻለ፣ እኔ ያለ የሌለ ድፍረቴን አሰባስቤ ካርዱን አነሳሁና፣ ደረጃውን ወጥቼ ሰጠሁት፡፡ ካርዱን አሰጣጤ ለሆነ ተናካሽ እንስሳ ሥጋ እንደሚወረውር ሰው በጥንቃቄ ነበር!... ከእጄ እንዳይወስደው!

ይቀጥላል

ለአስተያየቶ @atronosebot ን ይጠቀሙ
ለወዳጆ #Share እያደረጉ
አትሮኖስ pinned «#ከዕለታት_ግማሽ_ቀን ፡ ፡ #ክፍል_ሶስት ፡ ፡ #በአሌክስ_አብርሃም ከጉብኝቱ በኋላ በነበረን የእጅ ሥራ ክፍለ ጊዜ “ስለጉብኝቱ ጥያቄ ካላችሁ ጠይቁ!” በተባልነው መሠረት፣ መሐሪ ቀድሞ እጁን አወጣና “ቲቸር እስረኞቹ ግን ለምን በሌሊት አያመልጡም?” ብሎ ጠየቀ፡፡ “ቲቸር” ምንም ምንም ሳትናገር ቁማ መሐሪን ስታየው ቆየች፤ እናም ረጋ ባለ ድምፅ እንዲህ አለች፣ ሌላ ጥያቄ ያለው? ይኼ ሁሉ ነገር…»
#የራስ _ምስል

ከተራራው ደረት፣ ምን አለ፣
የፈሰሰ ብሌን፣ የብርሀን ትል መሳይ
ህይወት አዳይ ፤
ውበት አዋይ፡፡
የከሰመ ይለመልማል፤
ያረገፈ ያቆጠቁጣል፤
ፍሬ ያጎነቁላል ፤
ትንፋሽ
ገነትን ይመስላል፡፡

ከተራራው ስር፣ ዥረት ይገማሽራል፤
እየደነፋ ይንዳል ፤
እየነቀለ ይገድላል፡፡
መርገምት!
ሲኦልን ይመስላል፡፡

ከዥረቱ ጫፍ ውቅያኖስ፣
ሁሉን ቻይ የእርጋታ የዝምታ በርኖስ፡፡
ምንጩም ዥረቱም አይመስል፡፡
የራስ ግምጃ፣ የራስ ምስል።

🔘?🔘
#ከዕለታት_ግማሽ_ቀን


#ክፍል_አራት


#በአሌክስ_አብርሃም

…መሐሪ ካርዱ ከእጁ አምልጦት ወደቀ! ጋሽ ዝናቡ ወንበሩን ማወዛወዙን አቆመና፣ እጁን ወደፊት ዘርግቶ “እስቲ አምጣው!?” አለ፡፡ ዓይኑን በወደቀው ካርድ ላይ ተከሎ፤ መሐሪ መንቀሳቀስ ስላልቻለ፣ እኔ ያለ የሌለ ድፍረቴን አሰባስቤ ካርዱን እነሳሁና፣ ደረጃውን ወጥቼ ሰጠሁት፡፡ ካርዱን አሰጣጤ ለሆነ ተናካሽ
እንስሳ ሥጋ እንደሚወረውር ሰው በጥንቃቄ ነበር!... ከእጄ እንዳይወስደው!

ከዘላለም የረዘመ ለሚመስል ጊዜ ካርዱን ሲመረምር ቆየቶ፣ በረዥሙ እህህ ብሎ
አቃሰተ እና እዚህ መርዶ ላይ የሚፈርም አባት አለኝ ብለህ አንከርፍፈህ መጣህ እ
" ብሎ በሚያስደነግጥ ፍጥነት ምንጥቅ ብሎ ሲነሳ፣ ሁለታችንም ወደኋላ ሸሸት አልን ጋሼ ተነሰቶ ሲሄድ ተቀምጦበት የበረው ወንበር፣ ከዚህ ጉድ ሩጦ ማምለጥ ፈልጎ አቅም ያነሰው ይመስል፣ ባለበት ሆኖ ወደ ኋላና ወደፊት ተራወጠ፡፡ ወንበሩ ላይ የነበረው በፈዛዛ ቀይ ጨርቅ ከረጢት የተቋጠረው የስፖንጅ ድልዳል ተንሸራቶ መሬት ላይ ወደቀ፡፡

መሐሪ በድንጋጤ የተሰነዘረበትን ቡጢ እንደሚከላከል ቦክሰኛ ፊቱን በቀጫጫ ክንዶቹ መህል ቀብሮ ነበር ወደ ኋላው የሸሸው::ያች አቋቋሙ እስካሁን እንደፎቶ ቁልጭ ብላ ትታየኛለች፡፡ ሸሽቶ ደግሞ ከእኔ ኋላ ነበር የተደበቀው፡፡ ጋሼ እቆምንበት ትቶን ወደ ውስጥ ሲገባ እንኳን፣ መሐሪ አላየውም!! ነገሩ ጸጥ ሲልበትና የጠበቀው ኩርኩም
ሲዘገይ፣ ቀስ ብሎ ከከንዶቹ መሀል ቀና አለ፡፡ የጋሼን አለመኖር ሲያይ፣ ድንገት “ማሚን ገደላት!” ብሎ ወደ ውስጥ ሮጠ!እኔ ባለሁበት አንዴ የግቢውን በር፣ አንዴ አባትና ልጅ ተከታትለው የገቡበትን የቤቱን ዋና በር እየተመለከትኩ እንደቆምኩ፣ ከውስጥ የሆነ ከባድ እቃ ሲወድቅና ሲሰባበር ሰማሁ፡፡ ምን እንደገፋኝ እንጃ በሩጫ ተከትያቸው
ገባሁ፡፡ ደመነፍሴ ጓደኛህን ታደግ ብሎ ገፍቶኝም እንደሆነ እንጃ:: ከዋናው ቤት ጋር ተያይዞ ወደተሠራው ኩሽና በሚወስደው በር ላይ ተቀምጦ የነበረው ተደራራቢ የአበባ ማሰቀመጫ፣ ወለሉ ላይ ወድቆ ብትንትኑ ወጥቷል፡፡ ጋሽ ዝናቡ ኩሽናው ውስጥ ገብቶ በዚያ ንጋሪትና እምቢልታ ቢጨመርበት የክተት ጥሪን በሚያስንቅ ድምፁ ማሚ ላይ ያንባርቅበታል …

“ለስሙ ሴት ነሽ! …እናት ነሽ! እዚህ ተጎልተሸ እየዋልሽ፣ አንድ ልጅ እንኳን እንድ ልጅ መቆጣጠር ያቃተሸ ዳሩ በልደትና ሰርግ ሰበብ ማን እየተኳኳለና እግሩን እያነሳ ይዙርልሽ? አራተኛ …አራተኛ … ምን ማለት ነው ይኼ? , እ? ….ዳሩ አራተኛ ይሁን አስራ አራተኛ አይገባሽ አንች .…አራተኛ .…” ማሚ ምን መዓት ወረደብኝ ብላ ነው መሰል
ድምፅዋ አይሰማም! ለነገሩ እንኳንስ እንዲህ ዓይነት ውርጅብኝ ፊት ቁማ መመላለስ ቀርቶ በሰላሙም ቀን ንግግሯ የተቆጠበ ነው !

መሐሪ፣ አባቱን ያረጋጋ መስሎት እንዲህ ሲል ሰማሁት “ጋሽ፣ አብርሽኮ አምስተኛ ነው የወጣው” ወደኋላዬ ልሮጥ ነበር፤ ምነካው… እንዴት በዚህ እሳት ውስጥ ስሜን ያንሳል? እያልኩ ሳስብ

“ኧረ? ይኼ ነው “ኤክስኪውዝህ?”… በማኀበር ነው የሞትነው በለኛ ?,ደሞ አብርሽ ይባልልኛል …ግም ለግም አብረህ አዝግም ምድረ ድኩማን! ጧ! “ ጥፊ መሆን አለበት!" እቆምኩበት ሁኜ ጉንጬ ሲግል ተሰማኝ፡፡ ስለዛች “ጧ” ከዚያ በኋላ ሁለታችንም አንስተን አናውቅም !

“አትምታው! …ልጄን አትምታው!! ..ጆሮውን ልታደነቆረው ነው እንዴ?” ከዚያም በፊትም ሆነ ከዚያም በኋላ ሰምቼው የማላውቀው የማሚ ቁጡ ድምፅ አንባረቀ!

“ይችን ይወዳል ዝናቡ! …ለኔ ነው ቢላ ያነሳሽው? …እኮ ለኔ? …ግደይውና ነይ አብረን እንኑር አለሽ? …ታዲያ መርዝ አይሻልሽም? እ!” እንደፈለክ በል! ብቻ ልጄን ትነካውና ውርድ ከራሴ …እስቲ አሁን ምናለ? አብሮት ከሚያጠናው ጓደኛው ጋር ትምህርት ከበዳቸው፣ እሱ ብቻ አይደለም …ይኼ ያስመታል?
ደግሞ ወደ ስድስት አልፈዋል …በቃ

“ፓ! አንችም ብሎ ማብራሪያ ሰጭ .
ወደ ስድስት አልፈዋል ትላለች እንዴ? በዚህ የሞተ ውጤት ከአምስት ወደ ስድስት ወድቀዋል ነው የሚባለው … ማለፍ ሁሉ ስኬት አይደለም ..ከገባሽ! እንዲያውም አብርሃም የሚባል ካንተ የባሰ እንቅልፋም! ሁለተኛ እዚች ቤት ድርሽ ይልና .

ተው እንጂ አልበዛም” አለች ማሚ

በዛ እንዴ? እንዴት ለልጅሽ ውድቀት ጠበቃ ትሆኛለሽ ?……እንዲያውም አሳይሻለሁ ብሎ ወደ ሳሎን በቁጣ ሲመለስ፣ እንደጨው ዓምድ ደርቄ በቆምኩበት ተገጣጠምን፡፡
በረንዳው ላይ ነው ያለው ብሎ አስቦኝ ሳለ፣ ሳሎን ውስጥ ስላገኘኝ ትንሽ እንደመደናገር አለውና በዚያው ድምፅ

ስማ አንተ ሁለተተኛ እዚህ ቤት አይህና ውርድ ከራሴ! … ሁለተኛ… ሂድ አሁን
ወጥቼ ወደ ቤቴ ተፈተለከሁ! የእውነት ምርር ያለ ድንጋጤና ሐፍረት ተሰምቶኝ ነበር !
እቤቴ እስክደርስ ኤልቆምኩም፡፡ እቤታችን በር ላይ ስደርስ የከሰል ምድጃ ላይ የተቀጣጠለ እሳት ይዛ ከቤት የምትወጣው እናቴ ጋር ልጋጭ ለትንሽ ተረፍኩ፡፡

ምን እያባረረህ ነው?' ብላ እንደ መሳቅም እንደ መደንገጥም አለች! ሁልጊዜ ሳኮርፍ
የምመናቀረው ነገር (እንደሷ አባባል) ያስቃታል! ለእናቴ የሆነውን ነገር አልነገርኳትም.. ጥያቄዋ ሲበዛብኝ ካርዴን ሰጥቻት “አምስተኛ ወጣሁ” አልኳት፡፡ ካርዱ እንዳይቆሸሽ፣
በሥራ የቆሸሽ እጁን ልብሷ ላይ ጠራረገችና ተቀብላኝ፣ አንዴ እንኳን ሳታየው እና እንኳን አምስተኛ ለምን መጨረሻ አትወጣም… እንዲህ እሳት ውስጥ እስክትማገድ ያመናቅራል እንዴ? ሳመኝ ና! ጎበዝ! ጎበዝ!" እያለች ካርዱን ጠረጴዛው ላይ አስቀምጣ እራሷ መጥታ አገላብጣ ሳመችኝ :: አባቴ ለምሳ እንደመጣ ፍልቅልቅ እያለች፣ ካርዴን
ልክ እንደምሳ አቀረበችለትና “አብርሽ አምስተኛ ወጣ!” አለችው፡፡

አምስት? . ብሎ በዛው ሌላ ወሬ ቀጠለበት እንደው ይኼን የጫማ ሶል በምን ብታጥቢው ነው እንዲህ የቆረፈደው?…ያልተላገ እንጨት ላይ ስራመድ የዋልኩ ነው የመሰለኝ ማታ በቅባት ካላሸሽልኝ፣ እግሬ ዋጋም የለው

“አንተ ደሞ! እስቲ ጎበዝ በለው :

እህ አልኩትኮ የኔ ልጅ ባይባልስ አገር ያወቀው አይደለም እንዴ …ማነው ስሙ
ይኼ የኛ ዕቁብ ሰብሳቢ ልጅ፣ ዘንድሮም ወደቀ መሰል፣ እዚያ ቦኖ ውሃው ግንብ ሥር ተቀምጦ ይነፋረቃል፡፡ ትምርቱስ ይከበደው መቼም ሰው እንዴት አሳምሮ ማልቀስ ያቅተዋል? " አባባ በቃ እንዲህ ነው።በራሱ ዓለም የሚኖር፡፡

የጋሽ ዝናቡ ነገር እንዲቹ ሲያብሰለስለኝ ዋለ! ወደማታ ላይ ከምሽቱ አንድ ሰዓት አካባቢ ታዲያ፣ የቤታችን በር ተንኳኳ፤ ጋሽ ዝናቡ ነበር: በጓሮ በር ወጥቼ ልሮጥ ሳስብ፣በተረጋጋ ድምፁ ከእናቴ ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ ስሰማ ተረጋጋሁ፡፡ እናቴ እንዲገባ ትለምነዋለች ረጋ ብሎ ወደ ቤት ገባ፡፡ ቡኒ የሱፍ ካፖርቱን እስከ አንገቱ ቆልፎ ለብሷል ጥቁር ቴክሳስ ባርኔጣውን በእጁ እያፍተለተለ …ቤታችን መሀል ላይ ቆመ! ረዥም ነው፡፡ አንገቴን ሳቀረቅር ተወልውሎ ከሚያብረቀርቅ ጥቁር ቆዳ ጫማው ጋር ተፋጠጥኩ፡፡

“ተቀመጥ! ጋሽ ዝናቡ፣ ምነው ከመሻ? በሰላም?” ሰላም ነው!ሰላም ነው አትጨነቂ! …ቀን ለምን ውጤታችሁ ዝቅ አለ ብዬ ልጆቹ ላይ አጓጉል ጮኸኩባቸው .…የኔን ነገር ታውቂው የለም … የኔውስ ለምዶታል አብርሃምን
አስደነገጥኩት መሰለኝ ይቅርታ ልጠይቅ ነው የመጣሁት …. አማልጅኝ እንግዲህ!” አለ።

እናቴ ወደኔ እያየች “ኧረ የታባቱ ደሞ ለሱ ይቅርታ! አንደኛ የሚወጡ ልጆች አምስተኛ ሲወጡ፣ ላይጮህባቸው ነበር ታዲያ ሲያርሱ ነው ሲያርሙ ዱላም ሲያንስ ነው ትንሽማ ቀበጥ ብለዋል …ተነስ አንተ!” አለችኝ በርግጌ ተነሳሁና
👍1
ወደጋሽ ዝናቡ ተራመድኩ አብርሽ ለእናተው ብዬ ነው…ዘላለም አብረናችሁ አንኖር! … ይች ዓለም ጨካኝ ናት፣
እንደኛ እሹሩሩ አትላችሁም…ከትምህርት ሌላ ምን እናወርሳችኋለን" አለኝ በትልቅ
መዳፉ ራሴን እያሻሸ፡፡ ያ ቀን የሰማሁት ድምፅ በምን ጸበል ቢለዝብ ነው እንዲህ
የለሰለሰው …ከምር አሳዘነኝ !

“ባይሆን ነገ እክሳለሁ!.… በሉ ልሂድ፣ እንደው ይዠው እንዳላድር ብዬ ነው? አለ፡፡ እናቴ እራት በልቶ እንዲሄድ ብትለምነውም እምቢ ብሎ ሄደ፡፡ በሩ ላይ ቁሜ ግዙፍ ሰውነቱ በጨለማው ውስጥ እየደበዘዘ ሂዶ፣ ከዓይኔ ሲሰወር ከበሩ ዞር ስል፣ እናቴ ከኋላዬ ቆማለች፡፡የሆነ ነገረ እንድነግራት እየጠበቀች ነበር፡፡ ምንም ነገር አልነገርኳትም፡፡ ጋሽ ዝናቡን ከልቤ ይቅር ብየው ነበር፡፡ ከጧቱ ቁጣው ይልቅ ይኼ ይቅርታው በትምህርቴ እንድበረታ ከራሴ ጋር ቃል አስገብቶኝ ነበር፡፡ በቀጣዩ ቀን እኔንና መሐሪን ወስዶ ለስላሳና ኬክ ጋብዘን፡፡ ስንወጣ ኬክ አስጠቅልሎ ለመሐሪ እያቀሰበው “ለእናትህ ውሰድላት አለው፡፡

ይቀጥላል

ለአስተያየቶ @atronosebot ን ይጠቀሙ
ለወዳጆ #Share እያደረጉ
👍2
#ከዕለታት_ግማሽ_ቀን


#ክፍል_አምስት


#በአሌክስ_አብርሃም

ለስላሳና ኬክ ጋብዘን፡፡ ስንወጣ ኬክ አስጠቅልሎ ለመሐሪ እያቀበለው “ለእናት ውሰድላት አለው፡፡

መሐሪ፣ ሮሐን አፈቀርኩ ሲል ቀድሞ በሐሳቤ የመጣው ታዲያ፣ ይኼው የጋሽ ዝናቡ ቁጣ ነበር፡፡ አራተኛ መውጣቱ ትልቅ ነገር ሆኖ፣ መላእክት እና ሰዎች ቢቧደኑ፣ መሀል ላይ የምትቆም ማሚንና ባለቤቷን ጋሽ ዝናቡን ቢለዋ ያማዘዘ፣ መሐሪ ከአንዲት ሴት ጋር ፍቅር ጀመረ የሚል ወሬ ጋሼ ጆሮ ሲደርስ፣ …ማሰቡ ራሱ አስፈርቶኝ ነበር! ቢሆንም ከመሐሪ ጎን ከመቆም ውጭ፣ ምናባቴ አማራጭ አለኝ ደግሞ ለከፋቱ ሮሐም ለመሐሪ
በፍቀር ክንፍ ብላ ተያይዘው ማበዳቸው እንዲያውም አንድ ቀን እኛ ቤት ነኝ ብሎ
ከሮሐ ጋር ማምሻቱ አስፈርቶኝ በቀጣዩ ቀን፣

ኧረ አንት ልጅ ሥርዓት ያዝ ጋሽ ቢሰማ ስለው ….በቁጣ ቱግ ብሎ…

“የራሱ ጉዳይ ነው! ከፈለገ ቤቱን ለቅቄለት እወጣለሁ!እለኝ፡፡ በውስጤ እሱንኳን ተወው! ያንን ቤት ለቆ ከወጣ የሚወጣው ነፍስህ ነው!” እያልኩ ዝም አልኩ፡፡ መሐሪ ባለችው ትርፍ ሰዓት ሁሉ ከሮሐ ጋር ተያይዘው የት እንደሚሄዱ እንጃ፣ መጥፋት ሆነ ሥራቸው፡፡ ሊያመሽ ከፈለገ ብቻ እየተጣደፈ “እናንተ ቤት ነኝ ይለኝና ነብሱን ስቶ ወደ ሮሐ ይበራል! ታዲያ ጋሽ ዝናቡን እየፈራሁም ቢሆን፣ ለጓደኛዬ ለመሐሪ ግን ልቤ በደስታ ይፈነጥዝ ነበር፡፡ ከሮሐ ጋር አብረው ሳያቸው፣ ልጁን እንደዳረ አባት ሐሤት አደርጋለሁ፡፡ ደግሞ ሲያምሩ፣ ከዓይናቸው የሚረጨው የፍቅር ብርሃን ድምቀቱ ሰው ፍቅር ለምን ያዘህ? አይባልም፡፡ሰው ላፈቀርካት ሴት ለምን ልብስህን ጣልክ? አይባልም እንዲያው ቀንበር ጠቦኝ እንጂ… እንደ ሮሐ ሥጋም በነፍስም ሲበዛ ውብ የሆነች ልጅ ያፈቀረ ጓደኛዬን፣ ባለፉበት ሁሉ ከፊታቸው ቀድሜ ያውም እንደ ንጉሥ ሰልፍ ነጋሪትና እንቢልታ አስይዤ “ይች ምናላት በደንብ እበዱ ወፎች ከበላያችሁ ያርግዱ ተማሪዎች በዙሪያችሁ ተኮልኩለው በፍቅራችሁ መልካም መዓዛ ይታወዱ …" እያልኩ ማወጅ ያምረኛል! ውብ ልጅ ነበረች ሮሐ ፈረንጅ የመሰለች” ይሏታል ፈረንጅ አትመስልም! ለኔ ቅላቷ በፈረንጅ ቀለም ላይ ትንሽ ጠይምነት ጠብ ተደርጎበት የተሰራ ለስላሳ ፍካት ነው፡፡
ልክ ወተት ላይ ቡና ጠብ እንደሚደረገው፡፡ ውብ ነበረች፣ ውብ፡፡ በዚያ የውብ ቆዳ መደብ ላይ፡ ምንኛ ዓይንን ተጠበበት የምለው፣ ዓይኗ ሲያርፍብኝ ነው፤አፍንጫን አንደም
አድርጎ አሳካው የምለው ከዓይኖቿ መሃል እስከ ላይኛው ከንፈሯ የተዘረጋ ቀጭን የገነት መንገድ አስመስሎ ቢያሰምረው ነው …የታችኛው ከንፈሯ ትንሽ ወደ ታች ወረድ ብሎ ቀበጥ አኩራፊ አስመስሏታል፡፡ የደላው ሰውነት አላት፡፡ ከረዥም ሉጫ ጸጉር ጋር ውብ ነበረች ሮሐን ለዐሥረኛ ክፍል ተማሪ ይኼ ሁሉ ውበት አልበዛም?እላለሁ እንዳንዴ ባየኋት ቁጥር፣ ስሙ ለተጠራ የዘራፊዎች መንደር፣ ያውም በጨለማ ወርቅ
ተሸከማ የምትሄድ ምስኪን ትመስለኛለች፡፡ ከመሬት ተነስቼ ሰዎች የሚጎዷት ይመስለኛል፡፡ መሐሪ ጋር በፍቅር አበዱ! እኔም ከዚያ ዝናቡ ከሚባል ሰውዬ ዶፍ ላስጥላቸው ራሴን ዣንጥላ እድርጌ ከበላያቸው ዘረጋሁ!!

አስባለሁ፤ሁልጊዜ አስባለሁ!… አእምሮዬ እንደ እስፖንጅ መጦ የያዘው ትላንታችንን፣ ፈሳሽ ትዝታ አድርጎ እየጨመቀ፣ ዙሪያዬን በጨቀየ ነበር ይከበዋል! ኤልረሳም፣ ያየሁ
የስማሁትን ነገር አልረሳም፡፡ ሰዎች ነገሬ ብለው የማይመለከቷቸውን ነገሮች እንኳን
ጨምድዶ ከያዘ የማይለቅ ተፈጥሮ ነው ያለኝ፡፡ ቆይቶ ይኼ ተፈጥሮዬ ከኋላዬ እየተከተለ የእኔኑ ጀርባ የሚገርፍ የእሳት ጅራፍ እየሆነ ሲያሰቃየኝ ብጠላውም፣ ልላቀቅ ያልቻልኩት መከራ እንደሆነ ይከተለኛል፡፡ እንደመርሳት ምን ፈውሽ አለ?!

ድንገት ካለምንም ምክንያት (ከመሬት ተነስቶ እንደሚሉት) በተቀመጥኩበት የሚያናውዝ ትውስታ እንደደራሽ ጎርፍ እያላጋ ወደራቀ ጊዜ ይወስደኛል፡፡ ዛሬዬን አጣጥሜ መኖር አልቻልኩም፡፡ ትዝታው ከአእምሮዬ አልፎ ሰውነቴንም ስለሚያዝለኝ ልወደውም፡፡ ትዝታ ግን ታሪክ ነው? በታሪክና በትዝታ መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው? ትዝታ
ታሪክ ከሆነ፣ ለምንድነው ሰዎች ታሪክ አውርተው ሲጨርሱ ከድካም ይልቅ በወኔ የሚሞሉት? አስባለሁ ወደኋላ ተመልሸ አስባለሁ፣ ወደ ልጅነታችን …

እኔና መሐሪ የ3 ከፍል ተማሪዎች ሆነን አንድ ነገር ተፈጠረ፡፡ አልረሳም፡፡ ከትምህርት ቤት ሰፈራችን እስከምንደርስ ድረስ መንገድ ላይ የምናደርጋቸውን ነገሮች አንድ በአንድ አስታውሳለሁ፡፡ ቦርሳችንን በጀርባትን አዝለን መንገድ ለማቋረጥ ግራ ቀኝ እንመለከትና፣
የመኪናዎቹን ርቀት ገምቼ ለመሻገር መንገድ ስጀምር፣ መሐሪ ልብሴን አንቆ ወደኋላ ይጎትተኛል ይኼ ነገሩ ያበሳጨኛል፡፡ እሱ ደግሞ ድፍረቴ ያበሳጨዋል …እንነዛነዛለን

ገና የትና የት ያለ መኪና የምትፈራው፣ አንተ የገጠር ሰው ነህ እንዴ?”

“የትናየት እይደለም …እውር ነህ አታይም? ..አጠገባችን ደርሶ ነበር”

ነዳጅ ማደያው አጠገባችን ነው …እዛጋ ነበር መኪናው ትንሽ ብንጠብቅ ምን ትሆናለህ…ትሞታለህ?” መሐሪ መኪና ይፈራ ነበር።

እና ቆሜ ላድርልህ ነው? ከፈለክ አንተ ቆመህ እደር…ምናይነቱ ነው?!' በቆመበት ትቼውመንገዱንም በፈጣን ሩጫ ሳቋርጥ፣ ከባዱን የቦርሳውን ማንገቻ ግራና ቀኝ ደረቱ ላይ እንቁ፣
መገዱን ወዲያና ወዲህ እያየ በሩጫ ይከተለኛል፡፡ ቦርሳው ሁልጊዜ ከባድ ነው።የማያጭቀው፣ የማያዝለው ነገር የለም፡፡ ድንገት ዝናብ ቢጥል እያለች፣ ማሚ ጃኬት አጣጥፋ ታስገባለታለች… “ውሃ ደግሞ ጥሩ ነው ቶሎ ቶሎ ጠጣ” ትልና ክዳን ባለው ትልቅ የፕላስቲክ ኮዳ ሞልታ ታሸክመዋለች፡፡ አንድም ቀን ግን ጠጥቶት አያውቅም አንዳንዴ መንገድ ላይ እንረጭበታለን፡፡

ጋሽ ዝናቡ በተራው “አረፍ ስትል አትራገጥ…እንብብ!”ብሎ የሆነ መጽሐፍ ሸክሙ ላይ ይጨምርለታል፡፡ ያኔ ነው ከበደ ሚካኤል የሚባሉ ደራሲ መኖራቸውን ያወቅነው።አንዳንዴ የቦርሳው ክብደት ስለሚያደክመው “አግዘኝ!” ይለኛል፡፡ ሂድ ወደዚያ! ኩሊ
መሰልኩህ እንዴ” እያልኩ…ቦርሳችንን እንቀያየራለን፡፡ እየተነጫነጭኩም ቢሆን ሸከምን መሸከሜ አይቀርም፡፡ ታዲያ ሸክሙ ሲበዛብን (መቸስ ጋሽ ዝናቡን ማስቆም የማይታሰብ ነው) ማሚን አሳምነን ጃኬትና ውሃውን ለማስተው ተከራከርናት ፤ እየተቀባበልን
“እንዴ ማሚ አማርኛ መጽሐፍ አለ”
“እንግሊዝኛ መጽሐፍ ትተን መሄድ አንችልም …”
“ሒሳብ መጽሐፍ ይዘን ካልሄድን አስተማሪያችን ያብዳል …ምን እንደሚያክል ደግሞ
በዛ ላይ ደብተር! ተባብረን ስናጣድፋት፣ አንዴ እኔን… አንዴ መሐሪን እየተመለከተች ፊቷ ላይ ለይቶለት የማይፈነዳ ሳቅ እንዳረበበ እንደፈለጋችሁ አታድርቁኝ ኋላ ግን ብላ እጅ ሰጠች፡፡ከመሐሪ ቦርሳ ጃኬትና ውሃ ቀነስን፡፡ መንገድ ላይ ቀላሉን ቦርሳ ወደ
ላይ እያጓንን በመያዝ ድላችንን አጣጣምናት፡፡

መሐሪ ዕድለኛ ልጅ አልነበረም፡፡ በጭራሽ ዕድለኛ ልጅ አልነበረም፡፡ የዚያኑ ቀን፣
ከትምህርት ቤት ስንመለስ፣ ሰማዩን ቀዶ የተዘረገፈ የሚመስል ድንገተኛ ዶፍ ወረደ፡፡እቤት ስንደርስ ውሃ ውስጥ ነክረው ያወጧት ድመት መስለን ነበር፡፡ በተለይ መሐሪ ለአንድ ሳምንት የቆየ ትክትክ ሲያጣድፈው ከረመ ማሚ ከመጀመሪያው ይበልጥ የከበደ ባለወፍራም ገበር ጃኬት ገዝታ፣ መሐሪ ቦርሳ ውስጥ ጠቀጠቀችው፡፡ ዓመቱን
ሙሉ ያ ጃኬት ከቦርሳው ተለይቶ አያውቅም ነበር፡፡

መንገዱን ከተሻገርን በኋላ እየተነጫነጨ፣ “መገጨት ከፈለክ ራስህ ተገጭ አያገባኝም” ይላል፡፡ ከዋናው መንገድ ወደ ቤታችን ወደሚወስደው የኮረኮች መንገድ መገንጠያ ድረስ ተኮራርፈን በእግሮቻችን መንገድ
👍4
ላይ ያገኘናቸውን ጠጠሮች፣ የሲጋራ ካርቱኖች እየለጋን በዝምታ እንጓዛለን(ሁልጊዜ ስንኮራረፍ ለምን እግራችን እንደማያርፍ ይገርመኛል) …ወደ ቤታችን በሚወስደው መታጠፊያው ላይ ስንደርስ፣ የሁለታችንንም ፊት በፈገግታ የሚያደምቅ የዘወትር ደማቅ አቀባበል ይጠብቀናል …ሳሌም!!

ሁልጊዜ በምንመላለስበት መንገድ ላይ በግራ በኩል፣ ወደ ሁለት መቶ ሜትር
የሚረዝም የግንብ አጥር አለ፡፡ የአንድ የውጭ ድርጅት አጥር ነው፡፡ ግንቡ ወደላይ ወደ ሦስት ሜትር ስለሚረዝም፣ ከረዥሞቹ የጽድ ዛፎች ውጭ፣ ውስጡ ምን እንዳለ ማየት አይቻልም፡፡ እንዲሁ በልምድ “የፈረንጆቹ ቤት!” ይባላል፡፡ በተቃራኒ አቅጣጫ ባለው ትልቅ የብረት በር በኩል፣ የካቶሊክ መነኮሳትን ልብስ የሚለብሱ፣ ነጫጭ እራፊ ጨርቅ
ፀጉራቸው ላይ ሸብ የሚያደርጉ፣ ደረታቸውም ላይ ትልልቅ የብረት መስቀል
የሚያንጠለጥሉ፣ የፈረንጅ እና ሐበሻ ሴቶች ኤልፎ ኤልፎ ገባ ወጣ ይላሉ፡፡ አንዳንዴም በከባድ የፒያኖ ድምፅ የታጀበ የሕፃናት መዝሙር ከውስጥ ይሰማል፡፡ እኛ በምናልፈበት በኩል ታዲያ ግንቡ ላይ በደበዘዘ ቀይ ቀለም ሽንት መሽናት ነውር ነው፣ በሕግም ያስቀጣል” የሚል ጽሑፍ ቢኖርም፣ የግንቡ ጥግ ሽንት መሸኛ ነበር፡፡
የአጥሩ ሥር ድንጋይ የተነጠፈበት ሁለት ሰው ብቻ ጎን ለጎን የሚያሳልፍ የእግረኛ
መንገድ ነው፡፡ በዚያ ሲያልፉ የሚከረፋ የሽንት ሽታ ያፍናል፡፡ ልክ አጥሩ እንዳለቀ
ደመና ተነስቶ በቀስታ የሚንሳፈፍ ግራጫ ጉም የሚሠራ፤ ዝናብ ጠብ ካለ ደግሞ ጫማ። ጰጰተ የሚነጥቅ የዋልካ ጭቃ የሚነጠፍበት መንገድ፡፡ ታዲያ መታጠፊያዋ ጠርዝ ላይ ግንቡን
ተደግፋ የቆመች፣ ከላይ በፀሐይ የባዘት ሰማያዊ ላስቲክ ጣል የተደረገባት የእንጨት ጉሊት አለች መሀል ግንባሯ ላይ የ 'ቶ' ምልክት የተነቀሰች ቀይ ሴት በደማቅ ጎድጓዳ የፕላስቲክ ሰሀን የሞላ ለውዝ፣ በትንንሽ መስፈሪያዎች የምትቸረችርባት፣ በክረምት ደግሞ የተጠበሰ በቆሎ የምትሸጥባት ጉሊት፡፡ ፊቷ በማዲያት የተጠቃ ቀይ ሴት ናት፡፡
ሁልጊዜ ቅዳሜ ቅዳሜ ደግሞ ይችው ሴት እነ መሐሪ ቤት ልብስ ስለምታጥብና እንጀራ ስለምትጋግር እንደ ቤተሰብ ነበር የምንቀርባት። ጥድቄ ነበር ስሟ፡፡ ከተማ ስትገባ አስቀይራ እየሩስ አስባለችው! ይኼ ክፉ ዕድሌ ስሜ ላይ ተጣብቆ እየተከተለኝ እንደሆን ብዬ ፈርቼ እንጂ እኔስ ጥድቄ ሲሉኝ ነው የምወድ ትላለች

ሕጻን ልጅ አለቻት፣ ሳሌም የምትባል፡፡ ከአራስነቷ ጀምሮ እዚሁ መንገድ ላይ ያደገች፣ በፊት ይችን ሕጻን በእቅፏ ይዛ ነበር ለውዝ የምትሸጠው፡፡ ሕፃኗ እዚያው መንገድ ዳር መዳህ ጀመረች፡፡ (ምነው እዚህ ቆሻሻ ላይ? አንሽያት እንጅ! ቢያምብሽስ? ይላሉ መንገደኞቹ፡፡ እንደዚያ ይበሉ እንጂ አንዳንዶቹ መንገደኞች አለፍ ብለው ግንቡ ጥግ
ሽንታቸውን ይሸኑ ነበር) እዚያው መንገድ ዳር ድክ ድክ ማለት ስትጀምር (ኧረ! ይች
ልጅ ሩጣ መኪና እንዳትገባብሽ ያዠት እንጂ! እያለ አላፊ አግዳሚው) ያንን ሁሉ
አልፋ ሳሌም አደገች፡፡

መንገደኛ ሁሉ ቆም ብሎ ሳያጫውታትና ሳይስማት የማያልፍ፣ ቦግ ያለ ቅላት ያላት
ሕጻን ነበረች፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ ለከረሜላ መግዣ እያለ መንገደኛ ለሳሌም የሚሰጣት ሳንቲም፣ እናቲቱ ከምትሸጠው ሳይበልጥ አይቀርም፡፡ ኑሮ ሲያባዝነው የዋለው መንገደኛ እንዲጫወትባት መንገዱ ላይ የተቀመጠች ውብ አሻንጉሊት ነበር
የምትመስለው፡፡ መንግሥት ግብር ከፋዩን ኅብረተሰብ ዘንባባ ተከልኩ አልጸደቀም፣ አበባ ተከልኩ ደረቀ በመንገዱ ስታልፉ በዚች ውብ እንቦቀቅላ ነብሳችሁ ደስ ይበላት ብሎ ያስቀመጣት፡፡

ይቀጥላል

ለአስተያየቶ @atronosebot ን ይጠቀሙ
ለወዳጆ #Share እያደረጉ
👍1
አትሮኖስ pinned «#ከዕለታት_ግማሽ_ቀን ፡ ፡ #ክፍል_አምስት ፡ ፡ #በአሌክስ_አብርሃም ለስላሳና ኬክ ጋብዘን፡፡ ስንወጣ ኬክ አስጠቅልሎ ለመሐሪ እያቀበለው “ለእናት ውሰድላት አለው፡፡ መሐሪ፣ ሮሐን አፈቀርኩ ሲል ቀድሞ በሐሳቤ የመጣው ታዲያ፣ ይኼው የጋሽ ዝናቡ ቁጣ ነበር፡፡ አራተኛ መውጣቱ ትልቅ ነገር ሆኖ፣ መላእክት እና ሰዎች ቢቧደኑ፣ መሀል ላይ የምትቆም ማሚንና ባለቤቷን ጋሽ ዝናቡን ቢለዋ ያማዘዘ፣ መሐሪ ከአንዲት…»