ስንክሳር
7.32K subscribers
825 photos
4 videos
37 files
237 links
በስንክሳር channal ስንክሳሩ ተገልጦ ቅዱሳን ይዘከራሉ፣ ወቅቱን የጠበቁ መረጃዎችን ያገኛሉ፡፡ ይከታተሉን!
Download Telegram
*እንኩዋን ለጻድቅ #አባ_ኅልያን ዓመታዊ የዕረፍት በዓል
በሰላም አደረሳችሁ *
+አባ ኅልያን ገዳማዊ +
ልቡናን የሚመረምር ጌታ ሊመራው ወዷልና 3
#ቅዱሳን ስውራንን ሰደደለት::
+ሦስቱም የብርሃን አክሊል ደፍተው: የብርሃን ካባ ላንቃ
ለብሰው: የብርሃን ዘንግ ይዘው ተገለጡለት:: እየመሩም
ወስደው በግራና በቀኝ ውሃ ከሚፈስባት: ደኗ ለዐይን ደስ
ከምታሰኝ ዱር አደረሱት:: አካባቢው እንኩዋን ሰው
እንስሳትም አልነበሩበትም:: 3ቱ ቅዱሳን ከቦታዋ እንደ ገቡ
በላዩዋ ላይ ዕንቁ ያለባት የብርሃን ዘንግ ሰጥተውት "ወደ
ፈጣሪ እንስገድ" አሉት::
+ሰግዶ ቀና ሲል ግን 3ቱም በአካባቢው አልነበሩም::
ተሠውረዋልና:: #አባ_ኅልያን ከቅዱሳኑ በመለየቱ ፈጽሞ
አለቀሰ::
+ተጋድሎውን ግን በጾምና በጸሎት: በስግደትም አጠነከረ::
ቅዱሱ የሚመገበው: የሚለብሰውም ቅጠል ነበር:: በእርሱ
ዘንድ ሌሊት የሚባል አልነበረም:: ምክንያቱም ያቺ ዘንግ
ሲመሽ ግሩም የሆነ ብርሃን ታወጣ ነበርና ነው::
+መንገድ መሔድ በፈለገ ጊዜም ትመራው: ጐዳናውንም
ታሳጥርለት ነበር:: እንዲህ ባለ ግብር ለበርካታ ዓመታት
ከሰው ተለይቶ ኖረ:: አጋንንት በተለያየ መንገድ ፈተኑት:: ግን
አልቻሉትም:: አቅም ሲያጥራቸው ወደ ከተማ ሔደው: በሰው
አርአያ ሽፍቶችን አናግረው ሊያስገድሉት ሞከሩ:: ነገር ግን
ከፊት ለፊት እያዩት ሽፍቶቹ ሲራመዱ ቢውሉም ሊደርሱበት
አልቻሉም::
#እግዚአብሔር በኪነ ጥበቡ መንገዱን ያረዝምባቸው
ነበር:: በሁዋላ ግን ሽፍቶቹ በድካምና በውሃ ጥም ሊያልቁ
ሆነ:: ጻድቁ ምንም እርሱን ለመግደል ቢመጡም አዘነላቸው::
ባሕሩን ያለ ታንኩዋ እየረገጠ ደረሰላቸው:: ከዱር ፍሬ
አብልቶ: ንጹሕ ውሃም አጠጥቶ ሸኛቸው::
እድሜው እየገፋ ሲሔድ አንድ ቀን እነዛ በፊት የተሠወሩ 3
ቅዱሳን እንደ ገና ተገለጡለት:: በደስታ ሲጨዋወቱ አድረው
ሲነጋ አባ ኅልያን ወደ ምሥራቅ ሰግዶ ዐረፈ:: 3ቱ ቅዱሳንም
ሥጋውን ገንዘው በበዓቱ ቀበሩት:: ዜና ሕይወቱንም ጽፈው
አስቀመጡትና እንደ ገና ተሠወሩ::
በረከቱ ይደርብን
እንኩዋን ለጌታችን ቅዱስ #ዕፀ_መስቀል የተአምር በዓል በሰላም አደረሳችሁ
#ቅዱስ_ዕፀ_መስቀል +"+
የዕፀዋት ሁሉ ንጉሣቸው የሚሆን ቅዱስ ዕፀ መስቀል
ለእኛም #ኃይላችን: #ቤዛችን: #መዳኛችን: #የድል_
ምልክታችን ነው:: መስቀል #በደመ_ክርስቶስ ተቀድሷልና
አንክሮ: ስግደት ክብርና ምስጋና በፀጋ ይገባዋል::
#ቅዱስ_መስቀለ_ክርስቶስ ላለፉት 2,000 ዓመታት ብዙ
ተአምራትን ሠርቷል:: ከእነዚህ መካከልም አንዱን በዚህ
ዕለት እናዘክራለን:: ታሪኩ: ምሥጢሩስ እንደ ምን ነው
ቢሉ:- በ400 ዓ/ም አካባቢ በግብፅ #አባ_ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ
ሳለ: #ቅዱስ_ቄርሎስም በሊቀ ዲቁና ሲያገለግል ሳለ
በእስክንድርያ ከተማ 2 ደሃ ክርስቲያኖች ይኖሩ ነበር:: የቀን
ሠራተኞች በመሆናቸው ከዕለት ምግብ አይተርፋቸውም
ነበር::
ከ2ቱ አንዱ ፍጹም አማኝ ሲሆን ሌላኛው ግን ተጠራጣሪ
ነበር:: ስለ ምን ነው ቢሉ:- በከተማዋ ብዙ ሃብታም አይሁድ
ነበሩና እነሱን እየተመለከተ ነው:: ለእርሱ #ክርስትና ማለት
ገንዘብ መስሎታልና ዘወትር "ለምን ክርስቶስን እያመለክን ድሃ
እንሆናለን?" እያለ ያማርር ነበር::
"ያዛቆነ ሰይጣን . . . " እንደሚባለው አንድ ቀን ባልጀራውን "ለምን ክርስቶስን አንክደውም? (ሎቱ ስብሐት!) እርሱን ከማምለክ የተረፈን ድህነት ብቻ ነው" አለው:: ባልንጀራው ሊመክረው ሞከረ:-
"እግዚአብሔር አምላከ-ነዳያን ነው:: ቅዱሳን #ነቢያት :
#ሐዋርያት : #ጻድቃን: #ሰማዕታትም በሥጋዊ ሃብት ነዳያን
ነበሩ" ብሎ ቢለውም ሰይጣን ሠልጥኖበታልና
አልሰማውም:: ያ ስሑት ደሃ ወዲያው ወጥቶ ወደ ማሕበረ አይሁድ ሔደ::
እነርሱ በቁጥር ብዙ ሁነው በአንድነት ይኖሩ ነበር::
"ሥራ ቅጠሩኝ" አላቸው:: "በእምነት አትመስለንምና
አይሆንም" አሉት:: ያን ጊዜ ለአለቃቸው ( #ፈለስኪኖስ)
"አንተ ሥራ ቅጠረኝ እንጂ እኔ ክርስቶስን እክዳለሁ" (ሎቱ
ስብሐት!) አለው::
ወዲያው የከተማው ሕዝብ ተጠርቶ: በጉባኤ መካከል
ሊያስክዱት ተዘጋጁ:: በፍጥነትም #መስቀል: ጦር: ሐሞት
አዘጋጁ:: ስዕለ ስቅለቱንም አመጡ:: ያን ደሃ ከሃዲም
"በል-ክርስቶስ ሆይ! ካድኩህ ብለህ ምራቅህን ትፋበት:
ሐሞቱን አፍስበት: በጦርም ውጋው" (ሎቱ ስብሐት!)
አሉት::
ያ ልቡ የደነቆረ መስቀለ ክርስቶስ ላይ ተፋ:: ሐሞትም
አፈሰሰበት:: በመጨረሻ በጦር ሲወጋው ግን ድንቅ ተአምር
ተገለጠ:: በጦር ከተወጋው ከመስቀሉ ጐን ብዙ ደም
ፈሰሰ:: ለረዥም ሰዓትም አላቁዋረጠም:: በዚህች ሰዓት
በአካባቢው የነበሩ ሁሉም አይሁድ በግንባራቸው ተደፍተው
ለክርስቶስና ቅዱስ መስቀሉ ሰገዱ::
ሁሉም በአንድነት "#ክርስቶስ_የአብርሃም_አምላክ_ነው
:: #መድኃኒትም_ነው " ሲሉ እየጮሁ ተናገሩ:: ባለማወቅ
ስላደረጉት እነርሱ ምሕረትን ሲያገኙ ያ አዕምሮ የጐደለውን
ደሃ ግን ዘወር ብለው ሲያዩት ወደ ድንጋይነት ተቀይሮ ነበር::
ነፍሱንም: ሥጋውንም በፈቃዱ አጠፋ::
የአይሁድ አለቃም ዐይነ ሥውር ዘመድ ነበረውና ወዲያው
አምጥቶ ከደሙ ቢቀባው ዐይኑ በራ:: ታላቅ ደስታም በዚያ
ሥፍራ ተደረገ:: ነገሩን የሰሙት #ቅዱሳን #ቴዎፍሎስ እና
#ቄርሎስ ሲመጡ ደሙ ከመፍሰስ አላቆመም ነበር::
በተአምሩ ደስ ተሰኝተው: ከደመ ክርስቶስ ለበረከት ተቀቡ::
የፈሰሰውን #ቅዱስ_ደም ከነ አፈሩ አንስተው: መስቀሉን
በትከሻ ተሸክመው: በፍፁም እልልታና ዝማሬ ወስደው በቤተ
መቅደስ አኑረውታል:: የከተማዋ ሁሉም አይሁድም
በክርስቶስ አምነው ተጠምቀዋል::
#ቅዱሳን_ስምዖንና_ዮሐንስ
በቤተ ክርስቲያን ታሪክ አስደናቂ ታሪክ ካላቸው #ጻድቃን
እነዚህ 2ቱ ቅድሚያውን ይይዛሉ:: እርሱስ እንደ ምን ነው
ቢሉ:-
ቅዱሳኑ በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን ሶርያ አካባቢ ተወልደው
ያደጉ ክርስቲያኖች ናቸው::
ዘመዳሞች ከመሆናቸው ባሻገር አብረው ስላደጉ እጅጉን
ይፋቀሩ ነበር:: የዋሃንም ነበሩ:: ወጣት በሆኑ ጊዜ ትልቁ
#ዮሐንስ ሚስት አገባ:: ታዲያ አንድ ቀን ከጌታችን መቃብር
#ኢየሩሳሌም ደርሰው ሲመለሱ #ገዳመ_ዮርዳኖስ አካባቢ
ደረሱ:: እርስ በርሳቸውም "ይህ ገዳምኮ የመላእክት ማደሪያ
ነው" ተባባሉ::
በዚያውም መንነው ለመቅረት አሰቡ:: ፈረስና ንብረታቸውን
ለዘመዶቻቸው ልከው ጸሎት አደረሱ:: ፈቃደ እግዚአብሔርን
ሊረዱም ዕጣ ተጣጣሉ:: ዕጣውም "ወደ ገዳም ሒዱ"
የሚል ስለሆነ ተቃቅፈው ደስ አላቸው::
ወደ ገዳሙ ሲደርሱም አበ ምኔቱ #አባ_ኒቅዮስ ፈጣሪ
አዞት የገዳሙን በር ከፍቶ ጠበቃቸው:: ተቀብሎ
ሲያስገባቸውም አንድ ደግ መነኮስ ሲያልፍ: ቆቡ ቦግ ቦግ
እያለ እንደ ፋና ሲያበራ እና #መላእክት ከበውት አዩ::
ወዲያውም አበ ምኔቱን "እባክህ አመንኩሰን" አሉት::
እርሱም የአምላክ ፈቃድ ነውና በማግስቱ አመነኮሳቸው::
ፍቅረ ክርስቶስ ገዝቷቸዋልና በጥቂት ዓመታት ተጋድሎ
ከብቃት (ከጸጋ) ደረሱ:: 2ቱም ቆመው በፍቅር ሲጸልዩ
የብርሃን አክሊል በራሳቸው ላይ ይወርድ ነበር:: አካላቸውም
በሌሊት ያበራ ነበር::
እንዲህ ባለ ቅድስና ለዓመታት ቆይተው ከገዳሙ ወደ ጽኑ
በርሃ ሊሔዱ ስለ ፈለጉ የገዳሙ በር በራሱ ተከፈተ:: አበ
ምኔቱ አባ ኒቆን (ኒቅዮስ) እያነባ በጸሎት ሸኛቸው::
በበርሃም በጠባቡ መንገድ: በቅድስና ተጠምደው ለ29
ዓመታት ተጋደሉ:: በዚህ ሰዓት ግን 2ቱን የሚለያይ ምክንያት
ተፈጠረ::
#እግዚአብሔር ቅዱስ ስምዖን ወደ ከተማ እንዲገባ: ቅዱስ
ዮሐንስ ግን በዚያው እንዲቆይ አዘዘ:: 2ቱ ለረዥም ሰዓት
ተቃቅፈው ተላቅሰው ተለያዩ:: ከ50 ዓመታት በላይ
ተለያይተው አያውቁም ነበርና::
#ቅዱስ_ስምዖን ወደ ከተማ ሲገባ ክብሩን ይደብቅ ዘንድ
እንደ እብድ ሆነ:: በዚህ ምክንያትም የወቅቱ ከተሜዎች
ይንቁት: በጥፊም ይመቱት ነበር:: (እባካችሁ ብዙ
በየመንገዱ የወደቁ አባቶች አሉና እንጠንቀቅ!) ቅዱሱ ግን
ስለ እነርሱ ይጸልይ ነበር::
በከተማዋ የነበሩ እብዶችን ሁሉንም በተአምራት
ፈወሳቸው:: አንድ ቀን ግን ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች
ደብድበውት ደከመ:: የእግዚእብሔር መልአክ ወርዶ "ና
ልውሰድህ" ብሎ ዮሐንስን ከበርሃ: ስምዖንን ከከተማ
በዚህች ቀን ወሰዳቸው:: እነሆ ብርሃናቸው ዛሬም ድረስ
ለሚያምንበት ሁሉ ያበራል::
#ታላቁ_ቅዱስ_መቃርስ
ታላቁ ቅዱስ መቃርስ ( #መቃሬ ) "ጽድቅ እንደ መቃርስ"
የተባለለት: የመነኮሳት ሁሉ አለቃ: ከ80 ዓመታት በላይ በበርሃ
የኖረ: በግብፅ ትልቁን ገዳም (አስቄጥስን) የመሠረተ:
ከ50,000 በላይ መነኮሳትን ይመራና ይመግብ የነበረ ፍፁም
ጻድቅ ነው::
በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን አርዮሳውያን ደጉን ታላቅ አባት
በሰንሰለት አስረው ከግብፅ ወደ እስያ በርሃ ከጉዋደኛው
#ቅዱስ_መቃርዮስ እስክንድርያዊ ጋር አሰድደውታል:: በዚያ
ለ2 ዓመታት ስቃይን ከተቀበሉ በሁዋላ በአረማውያን ፊት ድንቅ
ተአምር አድርገው አረማውያንን ከነንጉሳቸው አጥምቀዋል::
በተሰደዱባት ሃገርም #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ (ስም
አጠራሩ ይክበርና) #እመቤታችንን : #ቅዱሳን_ሐዋርያትን :
#አዕላፍ_መላእክትን : በተለይ ደግሞ ቅዱሳኑን #ዳዊትን:
#ዮሐንስ መጥምቁንና ወንጌላዊውን: #ማርቆስን:_
ዼጥሮስን:_ዻውሎስን አስከትሎ ወርዶ ተገልጦላቸዋል::
በቅዱስ አንደበቱም የምሕረት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል::
ታላቁ ቅዱስ መቃርስና መቃርዮስ ከ2 ዓመታት ስደትና መከራ
በሁዋላ ስደት በወጡባት በዚችው ዕለት መልዐኩ ኪሩብ በክንፉ
ተሽክሞ ወደ ግብፅ መልሷቸዋል:: በወቅቱም ጻድቁን ለመቀበል
ከ50,000 በላይ የሚሆኑ ልጆቻቸው መነኮሳት በዝማሬ
ወጥተዋል::
ይህች ዕለት ለአባታችን መቃሬ በዓለ ፍልሠቱ ናት::
#ቅድስት_ኄራኒ_ሐዋርያዊት_ሰማዕት
ይህቺ ቅድስት ወጣት መልክ ከደም ግባት: ምግባር
ከሃይማኖት: ስም ከመልካምነት የተባበረላት ሰማዕት
ናት:: #ኄራኒ ማለት "ሰላማዊት: የተወደደች" ማለት
ነው:: አንድም በጥሬው "ሰላምና ፍቅር" ማለት ነው::
ቅድስት ኄራኒ በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን በታናሽ
እስያ የንጉሥ #ሉክያኖስ ልጅ ናት:: ከተወለደች ጀምሮ
ስለ ክርስትና ሰምታ አታውቅም:: ምክንያቱም አባቷ
ጣዖት አምላኪ ከመሆኑ ባለፈ ክርስቲያኖችን ይቀጣ ስለ
ነበር ነው::
ልጁን ማንም እንዳያገኛት ሲል ንጉሡ ለቅድስት ኄራኒ
ቤተ መንግስት ሠራላት:: ማንም እንዳይገባ በዙሪያው
12 አጥር አጠረበት:: ጣዖቶቹን እንድታጥን
አገልጋዮችንም ሾመላት::
ምናልባት አጥር ሰውን ሊከለክለው ይችላል::
#እግዚአብሔር ግን እግዚአብሔር ነውና ምንም
አይከለክለውም:: ጌታ ደግሞ ይህቺን ወጣት ለወንጌል
አገልግሎት ይፈልጋታል:: አንድ ቀን አባቷ: ልጁ ምሑር
እንድትሆንለት አለ የተባለ ሽማግሌ ፈላስፋ ቀጠረላት::
ጥበበ እግዚአብሔር ማለት ይሔ ነው:: አባቷ ይሕ
ሽማግሌ ማንን እንደሚያመልክ አልተረዳም:: አረጋዊው
እጅግ የተዋጣለት ክርስቲያን ነው:: ግን ማንም
አያውቅበትም:: አረጋዊው ቅድስት ኄራኒን ዝም ብሎ
ሊሰብካት አልወደደም::
መጀመሪያ በስነ ምግባር አነጻት:: ቀጥሎ ግን "ጌታ ሆይ! ጐዳናህን ምራት" እያለ ይጸልይላት ገባ:: ጌታችን ልመናውን ሰምቶታልና ቅድስቷ አንድ ቀን ግሩም ራዕይን
አየች::
እርሷ ለማዕድ ተቀምጣ ሳለ: የምሥራቅና የምዕራብ
መስኮቶቿም ተከፍተው ሳሉ: በምሥራቁ መስኮት ነጭ
ርግብ በአፏ የወይራ ዝንጣፊ (ቆጽለ ዘይት) ይዛ ገባችና
ማዕዷ ላይ አኑራው ሔደች:: እርሷን ተከትሎ ደግሞ
ንስር በአፉ አክሊል ይዞ ገብቶ ማዕዷ ላይ ጥሎት ሔደ::
በ3ኛው ግን ቁራ: እባብ በአፉ ይዞ በምዕራቡ መስኮት
ገብቶ ማዕዷ ላይ ጥሎት ወጣ:: ቅድስት ኄራኒ ያየችው
ራዕይ ቢጨንቃት ሽማግሌ መምሕሯን "ተርጉምልኝ"
አለችው::
እርሱም "ልጄ ሆይ! ለዘመናት ስጠብቀው የነበረ ምኞቴን ነው ጌታ ያሳየሽ:: የሕልምሽ ትርጉም እንዲህ ነው:- ነጭ ርግብ የመንፈስ ቀዱስ (የሃይማኖት) ምሳሌ
ናት:: የወይራ ዝንጣፊው ደግሞ #ማሕተመ_ጥምቀት
( #ሜሮን ) ነው:: ቁራ የክፉ ነገሥታት ምሳሌ ሲሆን
እባብ የመከራ ምሳሌ ነው::
ንስር ድል የመንሳት ምልክት ሲሆን አክሊል ደግሞ
የመንግስተ ሰማያት ምሳሌ ነው:: ልጄ! ክርስቲያን ሆነሽ
የሚደርስብሽን ሁሉ ጌታ አሳይቶሻል" ብሎ ተርጉሞላት
ተሰናበታት::
እርሷም ወደ ምሥራቅ ዙራ ጸለየች:- "የማላውቅህ
አምላክ ሆይ! ወደ እውነትህ ምራኝ" ስትል ለመነች::
በዚያች ሰዓት የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ አጽናናት::
የሚያጠምቃትም እንደሚልክላት ነገራት::
በዚያን ጊዜ አባቷ ገብቶ "ልጄ! ከመሣፍንቱ ላንዱ ልድርሽ ስለሆነ ምን ትያለሽ?" አላት:: "3 ቀን ስጠኝ" አለችውና ሰጣት:: ወደ ጣዖቶቹ ዕለቱኑ ወርዳ "ላግባ
ወይስ ይቅርብኝ?" አለቻቸው:: ከቀድሞም በወርቅ
የተለበጡ ድንጋዮች ናቸውና ዝም አሉ:: በሙሉ ቀጥቅጣ
ሰባብራቸው ተመለሰች::
በዘመኑ #ቅዱሳን_ሐዋርያት (በተለይ እነ
#ቅዱስ_ዻውሎስ ) በሕይወተ ሥጋ ነበሩና ከቅዱስ
ዻውሎስ ደቀ መዛሙርት አንዱ ቤቷ እንደ ተዘጋ ገባ::
ክርስትናን ከጥንቱ እስከ ተፍጻሜቱ አስተምሮ አጠመቃት::
በ3ኛው ቀን አባቷ "ምን መከርሽ?" ቢላት "የእኔ ምክር
#መርዓተ_ክርስቶስ (ሰማያዊ ሙሽራ) መሆን ነው"
አለችው:: አባቷ ደነገጠ:: እጅግ ስለ ተናደደ ወደ
አደባባይ አውጥቶ: አስሮ መሬት ላይ ጣላትና በመቶ
የሚቆጠሩ ፈረሶች እንዲረግጧት አደረገ::
በወቅቱ ሰው የሚጠብቀው የአካሏን ቁርጥራጭ ነበር::
ነገር ግን ጌታ ከእርሷ ጋር ነበርና ልብሷ እንኩዋ ጭቃ
አልነካም:: አባቷ ንጉሥ ሉክያኖስና ሠራዊቱ ያዩትን
ማመን አልቻሉም:: ሁሉም ድምጻቸውን ከፍ አድርገው
"ከክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም" አሉ:: ቅድስት
ኄራኒ ምንም ሳትናገር ይህንን ሁሉ ሰው ማረከች::
ወዲያውም ንጉሡ መልእክተኛ ልኮ: የቅዱስ ዻውሎስ
ደቀ መዝሙርን አስጠርቶ: ከነ ቤተሰቦቹ ተጠመቀ::
የዚህን ዓለም ክብር ንቆም ንግሥናውን ተወ:: የጸሎት
ሰውም ሆነ:: የቅድስት ኄራኒ ተጋድሎ ግን ቀጠለ::
በአካባቢው የነበረ ንጉሥ መጥቶ የአባቷን መንግስት
ቀማ:: እርሷንም እጅግ አሰቃያት:: እርሱ አልፎ
አርማንዮስ የሚባል ንጉሥ እንዲሁ አሰቃያት:: እርሱም
አለፈ:: ከእርሱ ቀጥሎ የመጣው ንጉሥ ብዙ
መከራዎችን በእርሷ ላይ አደረሰ:: በጦርም ጐኗን ወግቶ
ገደላት::
ከጥቂት ሰዓታት በሁዋላ ግን ልክ ከእንቅልፉ
እንደሚነቃ ሰው ተነስታ ጠራችው:: በጣም ደንግጦ
"አምላክሽ አምላኬ ነው" ሲል አመነ:: ከ30,000 በላይ
ሠራዊቱን ይዞም ተጠመቀ::
ቅድስት ኄራኒ በቀረ ሕይወቷ በስብከተ ወንጌል እስያን
አድርሳለች:: ጌታ አብርቶላት: እርሷም አብርታ: እልፍ
ፍሬን አፍርታ: በዚህች ቀን ዐርፋለች:: የሐዋርያትንም:
የሰማዕታትንም አክሊል ተቀዳጅታለች::
#ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ
ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነ ዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር
ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል:: #ቅዱስ_ሉቃስ
ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ
ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል:: "#ዘካርያስ ካህኑና
#ቅድስት_ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ
ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: (ሉቃ. 1:6)
የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ
መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል!
እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው
ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ
ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90
የዘካርያስ 100 ደግሞ ደርሶ ነበር::
ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ
እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ: ትንቢት ለብቻው
የተነገረለት (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) ታላቅ ነቢይን
ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን
ላከላቸው::
ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ
ድዳ ሆነ:: ቅድስቲቷ ግን መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው
ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች:: በ6ኛው ወር የፍጥረት
ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል
#እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች::
ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው::
የአምላክ እናቱ ስትደርስና "#ሰላም " ስትላቸው መንፈስ
ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና: ዮሐንስ
ደግሞ ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ):: ከዚህ
በሁዋላ ሰኔ 30 ተወልዶ: አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው
አንደበቱ
ተፈትቶለታል::
ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ 2 ዓመት ከ6 ወር በሆነው
ጊዜ #ሰብአ_ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር
የሚገኙ ሕጻናትን ሔሮድስ ቁዝ አስፈጀ:: ትንሽ ቆይቶም
አይሁድ ለሔሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕጻን ነገሩት:: "ሲጸነስ
የአባቱን አንደበት የዘጋ: ሲወለድ ደግሞ የከፈተ
'ዮሐንስ' የሚባል ሕጻን አለና እሱንም ግደል" አሉ::
እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን
ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል::
አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕጻኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ
ለ3 (5) ዓመታት ቆይታለች:: ቅዱስ ዮሐንስ 5 (7)
ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች::
ከሰማይ ዘካርያስና # ስምዖን ወርደው ቀበሯት::
ሕጻኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ #ድንግል_ማርያም ስንት አገር
አልፋ ሰማችው:: እርሷም ስደት ላይ ነበረችና:: ከጌታ
ጋር በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው:: ጌታንም
"እንውሰደው ይሆን?" አለችው:: ጌታችን ግን
"ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ" አላት::
ባርካው: አጽናንታውም ተለያዩ::
ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በሁዋላ በዚያ ቆላ የግመል
ጠጉር ለብሶ: ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ:: ለ25
(23) ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና
ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም:: ይሕችን
ዐመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም::
ከዚህ በሁዋላ 30 ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር
ከሰማይ ተናገረው:: "ሒድ! የልጀን ጐዳና ጥረግ"
አለው:: ነቢያት ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና:: (ኢሳ.
40:3, ሚል. 3:1) አባቱ ዘካርያስም "ወአንተኒ ሕጻን
ነቢየ ልዑል ትሰመይ: እስመ ተሐውር ቅድመ
እግዚአብሔር ከመ ትጺሕ ፍኖቶ" (ሉቃ. 1:76) ብሎ
መንገድ ጠራጊነቱን ተናግሮ ነበርና::
ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ #መንፈስ_ቅዱስ
እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ:: ያዩት ሁሉ ፈሩት:
አከበሩት:: ቁመቱ ቀጥ ያለ: ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር
የወረደ: ጸጉሩ የቁራ ያህል የጠቆረ: መልኩ የተሟላ:
ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ነውና::
ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሃ ሰበከ:: ለንስሃም በርካቶችን
አጠመቃቸው:: በዚህ አገልግሎት ለ6 ወራት ቆይቶ
ጌታችን ወደ እርሱ ዘንድ መጣ:: ዮሐንስ ሰማይን
ከነግሱ: ምድርን ከነ ልብሱ የያዘ ፈጣሪ 'አጥምቀኝ'
ብሎ ሲመጣ ደነገጠ:: የሚገባበትም ጠፋው::
"እንቢ ጌታየ! አንተ አጥምቀኝ" አለው:: ጌታ ግን
"ፈቅጄልሃለሁ" አለው:: አጠመቀው:: በዚህ ምክንያት
ይሔው እስከ ዛሬም "#መጥምቀ_መለኮት " ሲባል
ይኖራል:: ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻ ሔሮድስን ገሰጸው::
ንጉሡም ተቀይሞ ለ7 ቀናት አሠረው::
በዚህች ቀንም ልደቱን ባከበረ ጊዜ ወለተ ሔሮድያዳ
በዘፈን አጥምዳ አስማለችው:: እርሱም የታላቁን ነቢይ
ራስ አስቆርጦ በወጪት አድርጐ ሰጣት:: አበው
"እምሔሶ ለሔሮድስ ይብላዕ መሐላሁ - ሔሮድስ
መሐላውን በበላ በተሻለው ነበር" ይላሉ:: የቅዱስ
ዮሐንስ ራሱ በርራ ስትሔድ አካሉን ግን ደቀ መዛሙርቱ
ቀብረውታል:: (ማቴ. 3:1, ማር. 6:14, ሉቃ. 3:1, ዮሐ.
1:6)
ርጉም ሔሮድስ አንገቱን ካስቆረጠው በሁዋላ
የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራሱ የጸጋ ክንፍ ተሰጥቷት
ጌታችን ወዳለበት #ደብረ_ዘይት ሔዳ በፊቱ ሰገደች::
#ቅዱሳን_ሐዋርያት በአዩት ነገር ተገርመው ራሱን እጅ
ነሷት::
ከዚሕ በሁዋላ ጌታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ ለቅዱስ
ዮሐንስ ራስ የማስተማር ስልጣን ሰጥቶ አሰናበታት::
በመላው ዓለም ለ15 ዓመታት ስትሰብክ ኑራ በዚህች
ቀን ዓረቢያ ውስጥ ዓርፋለች::
📗📒 እንኳን ለቅዱሳን ነገሥታት "አብርሃ ወአጽብሃ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ📒📕

📗📗📗📒📒📒📕📕📕
#ቅዱሳን_አብርሃ_ወአጽብሃ

=>እነዚህ ነገሥታት ሞገሶቻችን: ብርሃኖቻችን ናቸውና ደስ እያለን እንወዳቸዋለን: እናከብራቸዋለን:: ሥላሴ ቢመርጧቸው ዛሬ ላለንበት ሕይወት መሠረቱን ጥለው አልፈዋልና::
+2ቱ ቅዱሳን ነግሥታት መንትያዎች ሲሆኑ ወላጆቻቸው ንጉሥ ታዜር / አይዛና / ሠይፈ አርዕድ እና ንግሥት አሕየዋ / ሶፍያ ይባላል:: ንጉሡና ባለቤቱ ልጅ ቢያጡ ወደ እግዚአብሔር ለመኑ:: ፈጣሪም በቅዱስ ሚካኤል አብሳሪነት 2 ዕንቁዎችን አስረከባቸው::
+ንግስት አሕየዋ (ሶፍያም) መጋቢት 29 ቀን በ311 ዓ/ም ጸንሳ: ታሕሳስ 29 ቀን በ312 ዓ/ም 2ቱን ቅዱሳን ወልዳቸዋለች:: "አምላክ ሽሙጥን አራቀልኝ" ስትልም "አዝጉዋጉ" ብላቸዋለች:: እነዚህ 2 ፍሬዎች በልጅነታቸው ከወቅቱ ሊቀ ካህናት እንበረም ኦሪቱን ጠንቅቀው ተምረዋል።
+ከእግዚአብሔር የተሰጡ ናቸውና በ12 ዓመታቸው ወደ ቤተ መቅደስ ገብተዋል:: ትንሽ ቆይቶ ግን አባታቸው ታዜር በማረፉ ሕዝቡ 2ቱን ቅዱሳን "ንገሡልን" አሏቸው:: እነርሱም "እኛ የፈጣሪ አገልጋዮች ነንና አንችልም" በማለታቸው ለተወሰነ ጊዜ እናታቸው አስተዳደረች::
+ቆይቶ ግን ቅዱስ ሚካኤል ለሊቀ ካህናቱ እንበረም "የፈጣሪ ፈቃዱ ስለ ሆነ አትዘኑ:: 2ታችሁም በአንድ ዙፋን ላይ ንገሡ: ታላቅ ጸጋ ለሃገሪቱ ይሆናል በላቸው" አለው።
+ሊቀ ካህናቱም የታዘዘውን ተናግሮ: በ19 ዓመታቸው: 2ቱንም በአንድ ዙፋን ላይ "ነገሥተ ኢትዮዽያ" ሲል አስቀምጦ ቀባቸው:: ስማቸውን "ኢዛና" እና "ሳይዛና" አላቸው:: ቅዱሳኑ እንደ ነገሡ ቀዳሚ ሥራቸው የቀናችውን ሃይማኖት መፈለግ ሆነ::
+በወቅቱ ፍሬምናጦስ (የሁዋላው አቡነ ሰላማ) በቤተ መንግስቱ ውስጥ የቅርብ አማካሪ ነበርና ጠርተው ተጨዋወቱት:: "አንተ ወንድማችን! ክርስቶስ ይወርዳል: ይወለዳል ተብሎ የተቆጠረው ሱባኤ እኮ አልፏል:: ምነው ቀረሳ? በርግጥ ምሥጢሩ ንገረን" አሉት::
+እርሱም አትቶ: አመሥጥሮ: ከ300 ዓመታት በፊት አምላክ ሰው መሆኑንና ዓለምን ማዳኑን አስተማራቸው:: "አጥምቀን?" ቢሉት "አልችልም" አላቸው:: እነርሱም ከብዙ ስጦታ ጋር ወደ ግብጽ ላኩት::
+ቅዱስ አትናቴዎስም ፍሬምናጦስን "አቡነ ሰላማ" ብሎ ከብዙ መጻሕፍት ጋር ላከው:: በመጀመሪያ ኢዛናና ሳይዛና ተጠመቁ:: ስማቸውም "አብርሃ ወአጽብሃ" ተባለ:: ቀጥሎም ሠራዊቱና ሕዝቡ ተጠመቀ::
+ሃገራችንም በእነዚህ ቅዱሳን አማካኝነት ከጨለማ ወደ ብርሃን መጣች:: የክርስትና ደሴት ሆነች:: ሃገረ እግዚአብሔርነቷንም አጸናች:: ቅዱሳኑ ከዚህ በሁዋላ በሞገስ ክርስትናን ያስፋፉ ዘንድ ደከሙ:: ከ154 በላይ አብያተ ክርስቲያናትን ሲያንጹ አብዛኞቹ ፍልፍል ነበሩ::
+በተለይ ግን በአክሱም ከተማ ላይ ያነጿትና 12 ቤተ መቅደሶች የነበሯት የጽዮን ቤተ ክርስቲያን ልናያት ትናፍቀናለች:: ጌጧ: ብርሃኗ ውል ውል ይልብናል:: ይህቺው ቤተ ክርስቲያን በ10 ኛው ክ/ዘመን ዮዲት ጉዲት በእሳት አውድማታለችና:: መሠረቱ ግን ዛሬም አለ::
+ቅዱሳን አብርሃ ወአጽብሃ ግን ክርስትናን ለማስፋፋትና መንግስትን ለማጽናት ሲሉ ከአክሱም በተጨማሪ በሽዋም ዙፋንን ዘረጉ:: ለብዙ ዓመታትም አምላክ በፈቀደው መንገድ እስከ የመን ድረስ ገዙ:: ክርስትናንም አስፋፉ::
+ቅዱስ አብርሃ በተወለደ በ52 ዓመቱ: በ364 ዓ/ም ጥቅምት 4 ቀን ሲያርፍ ወንድሙ ለ15 ዓመታት ብቻውን አስተዳድሯል:: በ379 ዓ/ም ደግሞ በዚሁ በጥቅምት 4 ቀን ቅዱስ አጽብሃም በተወለደ በ67 ዓመቱ በክብር ዐርፏል::
+ከሁለቱም መቃብር ላይ ለ30 ቀናት የብርሃን ምሰሶ ተተክሎ ታይቷል:: ጌታችንም በማይታበል ቃሉ "ስማችሁን የጠራውን: መታሰቢያችሁን ያደረገውንም እምርላቹሃለሁ" ሲል ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል::
አምላከ አብርሃ ወአጽብሃ "ድሃ ተበደለ: ፍርድ ተጉዋደለ" የሚል ዳኛ: ሃይማኖቱ የቀና መሪንም ያምጣልን:: የቅዱሳኑን ክብር በእኛ ላይ ያድርግልን። አሜን
@senkesar
@senkesar
#ቅዱሳን_ሐዋርያት (12 ናቸው)
-----------------------------
ሊቀ ሐዋርያት ጴጥሮስ (ስምዖን)
ቅዱስ እንድርያስ (የጴጥሮስ ወንድም)
ቅዱስ ያዕቆብ ወልደ ዘብዴዎስ
ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ዘብዴዎስ
ቅዱስ ፊሊጶስ
ቅዱስ በርተሎሜዎስ
ቅዱስ ቶማስ ዘህንደኬ (ዲዲሞስ)
ቅዱስ ማቴዎስ (ቀራጭ)
ቅዱስ ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ
ቅዱስ ታዴዎስ (ልብድዮስ)
ቅዱስ ናትናኤል (ስምዖን ቀነናዊ)
ቅዱስ ማትያስ
#ቅዱሳን_ሐዋርያት (12 ናቸው)
-----------------------------
#ቅዱሳን_አርድእት (72 ናቸው)
-------------------------------
ወንጌላዊው ማርቆስ
ሊቀ ዲያቆናት እስጢፋኖስ
ሐዋርያው ጳውሎስ
ቅዱስ ጢሞቴዎስ (የጳውሎስ የመንፈስ ልጅ)
ቅዱስ ሲላስ
ቅዱስ በርናባስ
ቅዱስ ቲቶ (የጳውሎስ የመንፈስ ልጅ)
ቅዱስ ፊሊሞና (የጳውሎስ የመንፈስ ልጅ)
ቅዱስ ቀሌምንጦስ
ቅዱስ ዘኬዎስ
ቅዱስ ቆርኔሌዎስ
ቅዱስ ቴዎፍሎስ
ቅዱስ ኤውዴዎስ
ቅዱስ አግናቴዎስ
ቅዱስ አናንያኖስ (ይሁዳ)
ቅዱስ ማልኮስ (አድሊጦስ)
ቅዱስ ኤሌናስ (ኢተኮስ)
ቅዱስ አርሳጢስ (አርጣቦሉ)
ቅዱስ አስተራቲዮስ (ሐናንያ)
ቅዱስ አርስጦበሌስ
ቅዱስ ጋይዮስ
ቅዱስ አድማጥስ
ቅዱስ ሉኪዮስ
ቅዱስ ድዮናስዮስ
ቅዱስ መርአንዮስ
ቅዱስ አርክቦንዮስ
ቅዱስ አናሲሞስ
ቅዱስ ከርላዲስ
ቅዱስ አኪላስ
ቅዱስ ንኪትስ (ኢያሶን)
ቅዱስ ቀርጶስ (ጢባርዮስ)
ቅዱስ ክርስቶፎሮስ
ቅዱስ ፊሊጶስ ካልዕ
ቅዱስ ጰርኮሮስ
ቅዱስ ኒቃሮና
ቅዱስ ጢሞና
ቅዱስ ጰርሚና
ቅዱስ ኒቆላዎስ
ወንጌላዊው ሉቃስ
ቅዱስ ዮሴፍ
ቅዱስ ኒቆዲሞስ
ቅዱስ ያዕቆብ እሁሁ ለእግዚእነ
ቅዱስ አብሮኮሮስ
ቅዱስ ሮፎስ
ቅዱስ እስክንድሮስ
ቅዱስ ስልዋኖስ
ቅዱስ ሳንቲኖስ
ቅዱስ ኢዮስጦስ
ቅዱስ አክዩቁ (አጋቦስ)
ቅዱስ አፍሮዲጡ
ቅዱስ አንሞስ
ቅዱስ ገማልኤል
ቅዱስ አንዲራኒቆስ
ቅዱስ አናንያ
ቅዱስ ድርሶቅላ
ቅዱስ አቄላ
ቅዱስ አጴንጤስ
ቅዱስ አንደራኒቆስ
ቅዱስ ዮልያል
ቅዱስ ጰልያጦስ
ቅዱስ መርማርያን
ቅዱስ ኬፋ
ቅዱስ ኡርባኖስ
ቅዱስ ስጠክን
ቅዱስ አጤሌን
ቅዱስ አክሌምንጦስ
ቅዱስ ሄሮድያኖስ
ቅዱስ ጥርፌናስ
ቅዱስ ጠርፌስ
ቅዱስ አስከሪጦስ
ቅዱስ ሉቅዮስ
ቅዱስ ሱሲ
@senkesar
💚💛 አቡነ ተጠምቀ መድኅን 💛❤️

ጻድቁ የተወለዱት በአፄ ሱስንዮስ ዘመን በ1610 ዓ/ም ሲሆን ወላጆቻቸው #ወልደ_ክርስቶስና #ወለተ_ማርያም ይባላሉ:: ታሕሳስ 2 ቀን እንደ መወለዳቸው ክርስትና የተነሱት ጥር 11 ቀን ነበርና ካህኑ "ተጠምቀ መድኅን" አላቸው:: በምድረ #ጐጃም ከበቀሉ ታላላቅ #ቅዱሳን አንዱ የሆኑት አባ ተጠምቀ መድኅን ገና ከሕጻንነታቸው ጀምሮ #ጸጋ_እግዚአብሔር የጠራቸው ነበሩ::

ሕጻን እያሉ #ቃለ_እግዚአብሔር መማር ቢፈልጉም አባታቸው በግድ እረኛ አደረጋቸው:: እርሳቸው ግን በሕጻን ልባቸውም ቢሆን ቤተሰብን ማሳዘን አልፈለጉም::

ይልቁኑ ወደ በርሃ ይወርዱና አንበሳውን: ነብሩን: ተኩላውን ሰብስበው:- "በሉ እኔ ልማር ልሔድ ስለ ሆነ እስከ ማታ ድረስ ጠብቁልኝ" ብለው ለአራዊቱ አደራ ይሰጣሉ:: አራዊቱ ከበጉ: ከፍየሉ: ከላሙ ጋር ሲቦርቁ ይውላሉ:: ተጠምቀ መድኅን ደግሞ ዳዊቱን: ወንጌሉን ሲማሩና ሲጸልዩ ውለው ማታ ይገባሉ::

ተጠምቀ መድኅን በሕጻንነታቸው ቁርስና ምሳቸውን ለነዳያን በመስጠት በቀን አንድ ማዕድ ብቻ ይቀምሱ ነበር:: 23 ዓመት ሲሞላቸው ወደ #መርጡለ_ማርያም ሔደው መንኩሰዋል:: ከዚሕ ጊዜ በሁዋላ ለ37 ዓመታት:-

1.በፍጹም ተጋድሎ ኑረዋል
2.ራሳቸውን ዝቅ አድርገው አገልግለዋል
3.ከጐጃም እስከ ሱዳን ድረስ ወንጌልን ሰብከው በርካቶችን አሳምነው አጥምቀዋል (ካህን ናቸውና)
4."7" ገዳማትንና "12" አብያተ ክርስቲያናትን አንጸዋል::

ጻድቁ በተሰጣቸው መክሊት አትርፈው በ60 ዓመታቸው በ1670 ዓ/ም (በአፄ #ዮሐንስ_ጻድቁ ዘመን) ዐርፈዋል::
እግዚአብሔር የምሕረት ቃል ኪዳን የገባላቸው ሲሆን አጽማቸው ዛሬ #በጋሾላ_ቅዱስ_ጊዮርጊስ የእናቶች ገዳም ውስጥ ይገኛል::
from: d/n yordanos abebe

@senkesar @senkesar

-----------+++++++++++-----------
እንድትከታተሉት የምንጋብዞ ቻናል
1⃣ዓውደ ምህረት
@AwediMeherit

2⃣ ተዋህዶ የወጣቶች ቻናል @Tewahedoyouth

3⃣ሐዊረ ሰላም
@hawireselam
Forwarded from ዐውደ ምሕረት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

"የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል #ያድናቸውማል።" መዝ 33:7

👉 ይህን ኃይለ ቃል የተናገረው ልበ አምላክ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ነው። በግልጽ እንደነገረን የእግዚአብሔር የሆኑት ቅዱሳን መልአክት የሚያድኑ አዳኞች ናቸው። እነርሱን ከሚፈሯቸውና ከሚያምኗቸው ሰዎች አይለዩም። ከሚደርስባቸው መከራ እና ችግር ፈተና ሁሉ ያድኗቸዋል ይታደጓቸዋል። ቅዱሳን መልአክት የሰው ልጆችን የሚያድኑ አዳኞች መሆናቸውን ቅዱስ ያዕቆብ ዮሴፍንና ልጆቹን በባረከ ጊዜም እንዲህ ሲል መስክሯል። "ከታናሽነቴ ጀምሮ እኔን የመገበኝ እግዚአብሔር ከክፉ ነገር ሁሉ #ያዳነኝ_መልአክ እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ።" ዘፍ 48:15

👉 እሱም ብቻ አይደለም የሰው ልጅ አምላክ በፈጸመለት የማዳን ተግባር ውስጥ የቅዱሳን መላእክት ሱታፌ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገልገል የሚላኩ የሚያግዙ መናፍስት አይደሉምን?" ብሎ የሰው ልጅ እንዲድን የቅዱሳን መላእክት አገልግሎት እና እገዛ የግድ እንደሚያስፈልገው ተናግሯል። ዕብ 1:14 እንዲሁም የሰው ልጅ የመዳኑ ነገር ለቅዱሳን መልአክት ታላቅ ደስታ መሆኑን ጌታ በወንጌል እንዲህ በማለት ተናግሯል። "እላችኋለሁ እንዲሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል።" ሉቃ 15: 7

👉 ቅዱሳን መልአክት በተጨነቅን እና በተቸገርን ጊዜ በጸሎት ስንጠራቸው መጥተው ያበረቱናል ያረጋጉናል። ጌታችን በመዋለ ሥጋዌው ለእኛ አርአያ አብነት ይሆነን ዘንድ በምሴተ ሐሙስ መከራን ከመቀበሉ በፊት ሲጸልይ "ከሰማይም መጥቶ የሚያበረታው መልአክ ታየው።" ይላል። ሉቃ 22:43 የመልአክት ፈጣሪያቸው እርሱ ሆኖ ሳለ የሚያበረታው መልአክ ታየው መባሉ ስለምንድን ነው ቢሉ እናንተም በጨነቃችሁ በጠበባችሁ መከራ ውስጥ በገባችሁ ጊዜ ብትጸልዩ ቅዱሳን መልአክት እናንተን ለማበርታት ይላካሉ ሲለን ነው።

👉 ቅዱሳን መልአክት ስለ ሰው ልጆች ዘውትር በአምላክ ፊት ያማልዳሉ። እግዚአብሔርም ምልጃቸውን ቸል አይልም። ዘካ 1:12–13 "የእግዚአብሔርም መልአክ መልሶ። አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ እነዚህ ሰባ ዓመት የተቈጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው? አለ። እግዚአብሔርም መልሶ ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረው መልአክ በመልካምና በሚያጽናና ቃል ተናገረው።" እንዲል። መልአኩ እግዚአብሔርን አሳዝነው 70 ዓመት ለተቆጡት እስራኤል ዘሥጋ ከለመነ፤ በቅዱሳን መልአክት ለታመንን እስራኤል ዘነፍስ ለሆንን ለኛ እንዴት አይማልዱልንም? እነርሱም ዘውትር በእግዚአብሔር ፊት ይቆማሉ፣ የእግዚአብሔርንም ፊት ያያሉ። ማቴ 18:10 ኢዮ 1:7 ሉቃ 1:9 "የእግዚአብሔር ዐይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና።" እንዲል የቅዱሳን መልአክትንም ምልጃቸውን ይቀበላል። መዝ 33(34):15

በተጨማሪም #ቅዱሳን_መልአክት

👉 አጽናኞቻችን ናቸው። ዳን 10:20
👉 ይረዱናል። ዳን 10:13
👉 ይጠብቁናል። መዝ 90:1
👉 እንሰግድላቸው ዘንድ ይገባል። ኢያ 5:14 ዘፍ 19:1 ራዕ 19:10 ራዕ 22:8

ሰኔ 12 በዚህች ቀን መልአኩ #ቅዱስ_ሚካኤል የተሾመበት፣ ቅድስት አፎምያን ከሰይጣን ያዳነበት፣ የባሕራንን የሞት ደብዳቤ ወደ ህይወት የቀየረበት ዕለት ነው።

ከመልአኩ ከቅዱስ ሚካኤል ረድኤት በረከት ያሳትፈን።

ይቆየን።

አዘጋጅ #አቤኔዘር

👉 @AwediMeherit
👉 @AwediMeherit
👉 @AwediMeherit

..............+++++++++++............
እንድትከታተሉት የምንጋብዝዎ መንፈሳዊ ቻናል

ስንክሳር… @senkesar
💚💛ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ 💛❤️
ቅዱስ ቄርሎስን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን " #ዓምደ_ሃይማኖት- የሃይማኖት ምሰሶ" ይሉታል:: ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

ሊቁ የተወለደው በእስክንድርያ (ግብጽ) በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: እናቱ የወቅቱ ፓትርያርክ #ቅዱስ_ቴዎፍሎስ እህቱ ነበረችና አጎቱ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ወስዶ አሳድጐታል:: ገና በልጅነቱ ወደ #አባ_ሰራብዮን ገዳም ገብቶ ቅዱሳት መጻሕፍትንና ገዳማዊ ሕይወትን ተምሯል:: በጾም: በጸሎትና በትሕትና የታሸ ነውና ሲማር አንድ ጊዜ ካነበበው በሕሊናው ተስሎ ይቀር ነበር::
ቅዱስ ቴዎፍሎስ "ምዕመናንን አስተምርልኝ" ብሎ ወደ ከተማ አመጣው:: #መንፈስ_ቅዱስ አድሮበታልና ሲያስተምር ወይ ደግሞ መጻሕፍትን ሲያነብ ከምዕመናን ወገን ስንኩዋን የሚያወራና የሚንቀሳቀስ ቀርቶ የሚቀመጥም አልነበረም:: ጣዕመ ስብከቱም ብዙዎችን ለወጠ::
ከዚያም በ412 ዓ/ም አጎቱ የነበረው ፓትርያርክ አባ ቴዎፍሎስ ሲያርፍ ዻዻሳትና ሊቃውንት በአንድነት ቅዱስ ቄርሎስን መረጡ:: የእስክንድርያም 24ኛ ሊቀ ዻዻሳት ሆኖ ተሾመ:: በዘመኑ #ቤተ_ክርስቲያን አበራች:: በቅድስናው: በሊቅነቱ: በስብከቱ: በድርሰቶቹና በትጋቱ በፍጹም አገለገላት::

በወቅቱ ስመ ክፉ መናፍቅ ንስጥሮስ ተነስቶ የእስያ አብያተ ክርስቲያናትን አወካቸው:: ትምሕርቱ ክርስቶስን "2 አካል: ባሕርይ ነው" (ሎቱ ስብሐት!) የሚል ነበር:: በእውነት እንየው ከተባለ ግን ጠቡና ጥላቻው ከድንግል ማርያም ጋር ነበር:: ምክንያቱም ጌታችንን ወደ 2 የከፈለው #እመቤታችንንየአምላክ እናት አይደለሽም ለማለት ነው:: (ላቲ ስብሐት!)
ነገሩን #ቅዱስ_ቄርሎስ በሰማ ጊዜ ወዳለበት ሒዶ ቢመክረውም ንስጥሮስ ሊሰማ አልፈለገም:: በዚህ ምክንያት በትንሹ ቴዎዶስዮስ (የቁስጥንጥንያ ንጉሥ) ትዕዛዝ በኤፌሶን ታላቅ ጉባኤ እንዲሰበሰብ ሆነ:: ይህ ጉባዔ በቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻው የተቀደሰ ጉባዔ ነው:: በ431 ዓ/ም #በኤፌሶን ከተማ የመናፍቃኑን ጥርቅም ሳንቆጥር ሃይማኖታቸው የቀና 200 #ቅዱሳን_ሊቃውንት ተገኙ::

የሚገባው ጸሎትና ሱባዔ ከተፈጸመ በሁዋላ ጉባዔው ተጀመረ:: አፈ ጉባዔው ሊቀ ማሕበር ማር (ቅዱስ) ቄርሎስ ነበርና በጉባዔ ፊት ንስጥሮስን ተከራክሮ ረታው:: ምላሽም አሳጣው:: ከቅዱሳት መጻሕፍት #ክርስቶስ አንድ ባሕርይ መሆኑን: #ድንግል_ማርያምም #ወላዲተ_አምላክ መሆኗን እየጠቀሰ: በምሳሌም እያሳየ አስረዳ::
የሰይጣን ማደሪያ ንስጥሮስ ግን እንቢ: አላምንም በማለቱ ተወግዞ ተለየ:: ቅዱሳን ሊቃውንቱም በቅዱስ ቄርሎስ አርቃቂነት 12 አንቀጾችን አዘጋጅተው ወደ ዓለም ሁሉ ላኩ:: እሊህ አንቀጾች ዛሬም በሊቃውንቱ እጅ አሉ:: ይነበባሉ: ይተረጎማሉ::

ከእነዚህም አንዱ ድንግል ማርያም " #ታኦዶኮስ(የእግዚአብሔር እናቱ) ናት" የሚል ነው:: እመቤታችንን:-
¤የአምላክ እናት:
¤ዘላለማዊት ድንግል:
¤ፍጽምት:
¤ንጽሕትና አማላጅ ብሎ ማመን ለሰማያዊ ርስት የሚያበቃ በጐ ሃይማኖት ነውና::
ጉባዔው ከተጠናቀቀ በሁዋላ ቅዱስ ቄርሎስ ንስጥሮስን ጠርቶ "በድንግል ማርያም እመን:: እርሷ ከልጇ ታስታርቅሃለች" ቢለው በድጋሚ "እንቢ" አለው:: ያን ጊዜ ሊቁ "ለአምላክ እናት ያልታዘዘ ምላስህ ላንተም አይታዘዝህ" ብሎ ረገመው:: ወዲያው ምላሱ ተጐልጉሎ ወጥቶ ደረቱ ላይ ወደቀ::
እንደ ውሻ እየተዝረከረከ ሒዶ ከወዳጆቹ ጋር ቁሞ ሳለ መሬት ተከፍታ ውጣዋለች::
ቅዱስ ቄርሎስ ግን ለ32 ዘመናት በመንበሩ ላይ አገልግሎ: ፍሬ ትሩፋት አፍርቶ: ብዙ ድርሰቶችንም ደርሶ በ444 ዓ/ም በዚህች ቀን ዐርፏል:: ከድርሰቶቹም ቅዳሴው: ድርሳነ ቄርሎስና ተረፈ ቄርሎስ ይጠቀሳሉ::

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአባቶቻችን ጸሎት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቅልን:: ከሊቁም በረከቱን ይክፈለን::
From:- d/n yordanos abebe

@senkesar @senkesar
💚💛አባ ኅልያን ገዳማዊ 💛❤️
ጻድቁ ተወልዶ ያደገው ዐይነ ፀሐይ በምትባል የቀድሞ የግብፅ ክፍለ ሃገር ሲሆን ወላጆቹ ዲስጣና ካልሞና ይባላሉ:: እነርሱ መልካም ክርስቲያኖች ነበሩና ገና በልጅነት ይህንኑ አጥብቀው አስተምረውታል:: ቅዱሱ #ኅልያን ጾምን: ጸሎትን ብቻ ያይደለ በሥጋዊ ሙያውም የተመሰገነ አንጥረኛ ነበር::

በወዙ በላቡ ሠርቶ ያገኘው ሃብት ነበረው:: በተለይ ወርቅና ብር እየሠራ ይተዳደር: ከገቢውም ነዳያንን ያስብ ነበር:: እንዲህ ባለ ግብር ሳለ አንድ ቀን ፈተና መጣበት:: አንዲት ዐረባዊት ሴት መጥታ የጀሮ ጌጥ (ጉትቻ) እንዲሠራላት ትጠይቀውና እርሱም ከወርቅ ይሠራላታል:: የጀሮ ጌጡን ከሰጣት በሁዋላ ግን "ዋጋውን አልሠጥህም" ትለዋለች::

እርሱም "ምነው እህቴ! የደከምኩበትን ለምን አትከፍይኝም?" ሲላት ገላዋን አጋልጣ "ሴትነቴን ልስጥህ" ብላ ለዝሙት ጠየቀችው:: ድንግሉ ኅልያን ከአነጋገሯና ከድርጊቷ የተነሳ በጣም ደነገጠ:: ከፊቷ ላይ አማትቦ: ገስጿት ወደ ቤቱ ሔደ:: ሙሉ ሌሊት ሲያዝን አደረ:: ሊነጋጋ ሲል በልቡ ወሰነ:: ይሕችን ዓለም ሊተዋትም ቆረጠ::

በወጣት ጉልበቱ ደክሞ ያፈራው ሃብቱ: ንብረቱ: ቤቱ: መሬቱ: ወርቁ: ብሩ አላሳሳውም:: ነዳያንን ሁሉ ወደ ቤቱ ጠርቶ ሙሉ ንብረቱን አካፈላቸው:: የተረፈችው የለበሳት ልብስ ብቻ ነበረችና ፈጽሞ ደስ እያለው ከተማውን ጥሎ ወደ በርሃ ተሰደደ:: ልቡናን የሚመረምር ጌታ ሊመራው ወዷልና 3 #ቅዱሳን ስውራንን ሰደደለት::

ሦስቱም የብርሃን አክሊል ደፍተው: የብርሃን ካባ ላንቃ ለብሰው: የብርሃን ዘንግ ይዘው ተገለጡለት:: እየመሩም ወስደው በግራና በቀኝ ውሃ ከሚፈስባት: ደኗ ለዐይን ደስ ከምታሰኝ ዱር አደረሱት:: አካባቢው እንኩዋን ሰው እንስሳትም አልነበሩበትም:: 3ቱ ቅዱሳን ከቦታዋ እንደ ገቡ በላዩዋ ላይ ዕንቁ ያለባት የብርሃን ዘንግ ሰጥተውት "ወደ ፈጣሪ እንስገድ" አሉት::

ሰግዶ ቀና ሲል ግን 3ቱም በአካባቢው አልነበሩም:: ተሠውረዋልና:: #አባ_ኅልያን ከቅዱሳኑ በመለየቱ ፈጽሞ አለቀሰ::

ተጋድሎውን ግን በጾምና በጸሎት: በስግደትም አጠነከረ:: ቅዱሱ የሚመገበው: የሚለብሰውም ቅጠል ነበር:: በእርሱ ዘንድ ሌሊት የሚባል አልነበረም:: ምክንያቱም ያቺ ዘንግ ሲመሽ ግሩም የሆነ ብርሃን ታወጣ ነበርና ነው::

መንገድ መሔድ በፈለገ ጊዜም ትመራው: ጐዳናውንም ታሳጥርለት ነበር:: እንዲህ ባለ ግብር ለበርካታ ዓመታት ከሰው ተለይቶ ኖረ:: አጋንንት በተለያየ መንገድ ፈተኑት:: ግን አልቻሉትም:: አቅም ሲያጥራቸው ወደ ከተማ ሔደው: በሰው አርአያ ሽፍቶችን አናግረው ሊያስገድሉት ሞከሩ:: ነገር ግን ከፊት ለፊት እያዩት ሽፍቶቹ ሲራመዱ ቢውሉም ሊደርሱበት አልቻሉም::

#እግዚአብሔር በኪነ ጥበቡ መንገዱን ያረዝምባቸው ነበር:: በሁዋላ ግን ሽፍቶቹ በድካምና በውሃ ጥም ሊያልቁ ሆነ:: ጻድቁ ምንም እርሱን ለመግደል ቢመጡም አዘነላቸው:: ባሕሩን ያለ ታንኩዋ እየረገጠ ደረሰላቸው:: ከዱር ፍሬ አብልቶ: ንጹሕ ውሃም አጠጥቶ ሸኛቸው::

እድሜው እየገፋ ሲሔድ አንድ ቀን እነዛ በፊት የተሠወሩ 3 ቅዱሳን እንደ ገና ተገለጡለት:: በደስታ ሲጨዋወቱ አድረው ሲነጋ አባ ኅልያን ወደ ምሥራቅ ሰግዶ ዐረፈ:: 3ቱ ቅዱሳንም ሥጋውን ገንዘው በበዓቱ ቀበሩት:: ዜና ሕይወቱንም ጽፈው አስቀመጡትና እንደ ገና ተሠወሩ::
🌿🌿🌿🌿🌿🌿🌿🌿🌿🌿🌿🌿
የቅዱሳን አምላክ ለእኛም የአባቶችን ረድኤት ይላክልን:: ከጻድቁም በረከትን ይክፈለን::
from:- dn yordanos abebe
@senkesar @senkesar