ስንክሳር
7.32K subscribers
825 photos
4 videos
37 files
237 links
በስንክሳር channal ስንክሳሩ ተገልጦ ቅዱሳን ይዘከራሉ፣ ወቅቱን የጠበቁ መረጃዎችን ያገኛሉ፡፡ ይከታተሉን!
Download Telegram
#ቅድስት_ኄራኒ_ሐዋርያዊት_ሰማዕት
ይህቺ ቅድስት ወጣት መልክ ከደም ግባት: ምግባር
ከሃይማኖት: ስም ከመልካምነት የተባበረላት ሰማዕት
ናት:: #ኄራኒ ማለት "ሰላማዊት: የተወደደች" ማለት
ነው:: አንድም በጥሬው "ሰላምና ፍቅር" ማለት ነው::
ቅድስት ኄራኒ በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን በታናሽ
እስያ የንጉሥ #ሉክያኖስ ልጅ ናት:: ከተወለደች ጀምሮ
ስለ ክርስትና ሰምታ አታውቅም:: ምክንያቱም አባቷ
ጣዖት አምላኪ ከመሆኑ ባለፈ ክርስቲያኖችን ይቀጣ ስለ
ነበር ነው::
ልጁን ማንም እንዳያገኛት ሲል ንጉሡ ለቅድስት ኄራኒ
ቤተ መንግስት ሠራላት:: ማንም እንዳይገባ በዙሪያው
12 አጥር አጠረበት:: ጣዖቶቹን እንድታጥን
አገልጋዮችንም ሾመላት::
ምናልባት አጥር ሰውን ሊከለክለው ይችላል::
#እግዚአብሔር ግን እግዚአብሔር ነውና ምንም
አይከለክለውም:: ጌታ ደግሞ ይህቺን ወጣት ለወንጌል
አገልግሎት ይፈልጋታል:: አንድ ቀን አባቷ: ልጁ ምሑር
እንድትሆንለት አለ የተባለ ሽማግሌ ፈላስፋ ቀጠረላት::
ጥበበ እግዚአብሔር ማለት ይሔ ነው:: አባቷ ይሕ
ሽማግሌ ማንን እንደሚያመልክ አልተረዳም:: አረጋዊው
እጅግ የተዋጣለት ክርስቲያን ነው:: ግን ማንም
አያውቅበትም:: አረጋዊው ቅድስት ኄራኒን ዝም ብሎ
ሊሰብካት አልወደደም::
መጀመሪያ በስነ ምግባር አነጻት:: ቀጥሎ ግን "ጌታ ሆይ! ጐዳናህን ምራት" እያለ ይጸልይላት ገባ:: ጌታችን ልመናውን ሰምቶታልና ቅድስቷ አንድ ቀን ግሩም ራዕይን
አየች::
እርሷ ለማዕድ ተቀምጣ ሳለ: የምሥራቅና የምዕራብ
መስኮቶቿም ተከፍተው ሳሉ: በምሥራቁ መስኮት ነጭ
ርግብ በአፏ የወይራ ዝንጣፊ (ቆጽለ ዘይት) ይዛ ገባችና
ማዕዷ ላይ አኑራው ሔደች:: እርሷን ተከትሎ ደግሞ
ንስር በአፉ አክሊል ይዞ ገብቶ ማዕዷ ላይ ጥሎት ሔደ::
በ3ኛው ግን ቁራ: እባብ በአፉ ይዞ በምዕራቡ መስኮት
ገብቶ ማዕዷ ላይ ጥሎት ወጣ:: ቅድስት ኄራኒ ያየችው
ራዕይ ቢጨንቃት ሽማግሌ መምሕሯን "ተርጉምልኝ"
አለችው::
እርሱም "ልጄ ሆይ! ለዘመናት ስጠብቀው የነበረ ምኞቴን ነው ጌታ ያሳየሽ:: የሕልምሽ ትርጉም እንዲህ ነው:- ነጭ ርግብ የመንፈስ ቀዱስ (የሃይማኖት) ምሳሌ
ናት:: የወይራ ዝንጣፊው ደግሞ #ማሕተመ_ጥምቀት
( #ሜሮን ) ነው:: ቁራ የክፉ ነገሥታት ምሳሌ ሲሆን
እባብ የመከራ ምሳሌ ነው::
ንስር ድል የመንሳት ምልክት ሲሆን አክሊል ደግሞ
የመንግስተ ሰማያት ምሳሌ ነው:: ልጄ! ክርስቲያን ሆነሽ
የሚደርስብሽን ሁሉ ጌታ አሳይቶሻል" ብሎ ተርጉሞላት
ተሰናበታት::
እርሷም ወደ ምሥራቅ ዙራ ጸለየች:- "የማላውቅህ
አምላክ ሆይ! ወደ እውነትህ ምራኝ" ስትል ለመነች::
በዚያች ሰዓት የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ አጽናናት::
የሚያጠምቃትም እንደሚልክላት ነገራት::
በዚያን ጊዜ አባቷ ገብቶ "ልጄ! ከመሣፍንቱ ላንዱ ልድርሽ ስለሆነ ምን ትያለሽ?" አላት:: "3 ቀን ስጠኝ" አለችውና ሰጣት:: ወደ ጣዖቶቹ ዕለቱኑ ወርዳ "ላግባ
ወይስ ይቅርብኝ?" አለቻቸው:: ከቀድሞም በወርቅ
የተለበጡ ድንጋዮች ናቸውና ዝም አሉ:: በሙሉ ቀጥቅጣ
ሰባብራቸው ተመለሰች::
በዘመኑ #ቅዱሳን_ሐዋርያት (በተለይ እነ
#ቅዱስ_ዻውሎስ ) በሕይወተ ሥጋ ነበሩና ከቅዱስ
ዻውሎስ ደቀ መዛሙርት አንዱ ቤቷ እንደ ተዘጋ ገባ::
ክርስትናን ከጥንቱ እስከ ተፍጻሜቱ አስተምሮ አጠመቃት::
በ3ኛው ቀን አባቷ "ምን መከርሽ?" ቢላት "የእኔ ምክር
#መርዓተ_ክርስቶስ (ሰማያዊ ሙሽራ) መሆን ነው"
አለችው:: አባቷ ደነገጠ:: እጅግ ስለ ተናደደ ወደ
አደባባይ አውጥቶ: አስሮ መሬት ላይ ጣላትና በመቶ
የሚቆጠሩ ፈረሶች እንዲረግጧት አደረገ::
በወቅቱ ሰው የሚጠብቀው የአካሏን ቁርጥራጭ ነበር::
ነገር ግን ጌታ ከእርሷ ጋር ነበርና ልብሷ እንኩዋ ጭቃ
አልነካም:: አባቷ ንጉሥ ሉክያኖስና ሠራዊቱ ያዩትን
ማመን አልቻሉም:: ሁሉም ድምጻቸውን ከፍ አድርገው
"ከክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም" አሉ:: ቅድስት
ኄራኒ ምንም ሳትናገር ይህንን ሁሉ ሰው ማረከች::
ወዲያውም ንጉሡ መልእክተኛ ልኮ: የቅዱስ ዻውሎስ
ደቀ መዝሙርን አስጠርቶ: ከነ ቤተሰቦቹ ተጠመቀ::
የዚህን ዓለም ክብር ንቆም ንግሥናውን ተወ:: የጸሎት
ሰውም ሆነ:: የቅድስት ኄራኒ ተጋድሎ ግን ቀጠለ::
በአካባቢው የነበረ ንጉሥ መጥቶ የአባቷን መንግስት
ቀማ:: እርሷንም እጅግ አሰቃያት:: እርሱ አልፎ
አርማንዮስ የሚባል ንጉሥ እንዲሁ አሰቃያት:: እርሱም
አለፈ:: ከእርሱ ቀጥሎ የመጣው ንጉሥ ብዙ
መከራዎችን በእርሷ ላይ አደረሰ:: በጦርም ጐኗን ወግቶ
ገደላት::
ከጥቂት ሰዓታት በሁዋላ ግን ልክ ከእንቅልፉ
እንደሚነቃ ሰው ተነስታ ጠራችው:: በጣም ደንግጦ
"አምላክሽ አምላኬ ነው" ሲል አመነ:: ከ30,000 በላይ
ሠራዊቱን ይዞም ተጠመቀ::
ቅድስት ኄራኒ በቀረ ሕይወቷ በስብከተ ወንጌል እስያን
አድርሳለች:: ጌታ አብርቶላት: እርሷም አብርታ: እልፍ
ፍሬን አፍርታ: በዚህች ቀን ዐርፋለች:: የሐዋርያትንም:
የሰማዕታትንም አክሊል ተቀዳጅታለች::