ስንክሳር
7.32K subscribers
825 photos
4 videos
37 files
237 links
በስንክሳር channal ስንክሳሩ ተገልጦ ቅዱሳን ይዘከራሉ፣ ወቅቱን የጠበቁ መረጃዎችን ያገኛሉ፡፡ ይከታተሉን!
Download Telegram
+ሥሉስ_ቅዱስ +
በአንድነቱ ምንታዌ (ሁለትነት): በሦስትነቱ ርባዔ
(አራትነት) የሌለበት የዘለዓለም አምላክ: የፍጥረታት ሁሉ
ፈጣሪ #እግዚአብሔር ነው:: #አብ: #ወልድ :#መንፈስ_ቅዱስ በስም: በአካል: በግብር ሦስትነት:
በባሕርይ: በሕልውናና በፈቃድ አንድነት የጸኑ ናቸው:: በዚህ
ጊዜ ተገኙ: በዚህ ጊዜ ያልፋሉ አይባሉም:: መጀመሪያም
መጨረሻም እነርሱ ናቸውና::
+ርሕሩሐን ናቸውና በእናት ሥርዓት "#ቅድስት_ሥላሴ "
እንላቸዋለን:: የሚጠላቸው (የማያምንባቸውን) አይጠሉም::
የሚወዳቸውን ግን እጽፍ ድርብ ይወዱታል:: በቤቱም
መጥተው ያድራሉ::
+ከፍጥረታት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የአብርሃምን ያህል
በሥላሴ ዘንድ የተወደደ ፍጡር የለም:: አባታችን
#ቅዱስ_አብርሃም የደግነት ሁሉ አባት ነውና በኬብሮን
በመምሬ ዛፍ ሥር ሥላሴን ተቀብሎ አስተናግዷል:: ሥላሴ
አኀዜ ዓለም (ዓለምን በእጁ የያዘ) ነው:: ነገር ግን በፍቅር
ለሚሻው በፍቅር ይመጣል::
+አባታችን አብርሃም በ99 ዓመቱ: እናታችን ሣራ በ89 ዓመቷ
ሥላሴን በድንኩዋናቸው አስተናገዱ:: አብርሃም እግራቸውን
አጠበ:: (ወይ መታደል!) በጀርባውም አዘላቸው:: (ድንቅ
አባት!) ምሳቸውንም አቀረበላቸው:: እንደሚበሉ ሆኑለት::
በዚያው ዕለትም የይስሐቅን መወለድ አበሠሩት::
#ቅድስት_ሣራ ሳቀች:: እንደ ዘንድሮ ወገኖቻችን የማሾፍ
አይደለም:: ደስታና ጉጉት የፈጠረው እንጂ:: ሥላሴ "ምንት
አስሐቃ ለሣራ በባሕቲታ" ብለው ነበርና በዚህም ምክንያት
ነው " #ይስሐቅ " የተባለው::
+ሥላሴን ያስተናገደች ድንኩዋን (ሐይመት) የድንግል
እመቤታችን ማርያም ምሳሌ ናት:: በድንግል ላይ #አብ
ለአጽንኦ: #መንፈስ_ቅዱስ ለአንጽሖ: #ወልድ በተለየ አካሉ
ለሥጋዌ በእርሷ ላይ አርፈዋል / አድረዋልና::
እንኩዋን ለቅድስት #እናታችን_ማርያም_መግደላ
ዊት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ❖
#ቅድስት_ማርያም_መግደላዊት
ይህችን ቅድስት "ማርያም" ያሏት ወላጆቿ ሲሆኑ
"መግደላዊት" እያሉ የጠሯት ደግሞ ሐዋርያት
(ወንጌላውያን) ናቸው:: ለምን እንዲህ ብለው ጠሯት ቢሉ:-
በዘመኑ "ማርያም" የሚባሉ ብዙ ሴቶች ነበሩና ከእነሱ
ለመለየት ነው:: አንድም ሃገሯ ከእሥራኤል አውራጃዎች
በአንዱ (በመግደሎን) ተወልዳ ያደገች ናትና::
ማርያም መግደላዊት ይህ ቀረሽ የማይሏት ቆንጆ ነበረችና
ሰዎች ያደንቁዋት: ወንዶች ይከተሏት ነበር:: በዚህም 7
አጋንንት ተጠግተው 7 ዓይነት ኃጢአትን ያሠሯት ነበር::
በተለይ ደግሞ በዝሙት: በትውዝፍት (ምንዝር ጌጥ) እና
ትዕቢት በእጅጉ የታወቀች ነበረች::
በእንዲህ ያለ ግብር ጸንታ ለዘመናት ኖረች:: በዚያ ወራት
የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሥጋችንን ተዋሕዶ ያስተምር ነበርና ስለ እርሱ ሰማች:: "ጌታ ኃጥአንን አይጸየፍም (ይቀበላል): አጋንንትንም ያስወጣል" ብለውም
ነገሯት:: ጥሪው የእግዚአብሔር ነውና ማርያም መግደላዊት
አልዘገየችም::
ወደ እርሱ ሔዳ ጌታ ባያት ጊዜ ኩላሊትን የሚመረምር
አምላክ ነውና አቀረባት:: በቸርነቱም ከራስ ጸጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ የሞሉትን 7 የአጋንንት ነገድ አስወጣላት:: በዚያች ሰዓት ዕለቱኑ እንደተወለደ ሕጻን ከነበረባት ችግር ሁሉ ንጹሕ
ሆነች:: ጌታም ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት አንዷ ትሆን ዘንድ
መርጦ ተከታዩ አደረጋት::
ቅድስት ማርያም ከዚህች ቀን ጀምሮ ፍጹም ተቀየረች::
እርምጃዋ ሁሉ የተባረከና የንጽሕና ሆነ:: ጌታን እስከ ዕለተ
ሕማሙ ድረስ በመዓልትም: በሌሊትም በቅን አገለገለችው::
ጌታችን ስለ እኛ መከራን በተቀበለባት በዚያች ዕለተ ዐርብም ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ከጐኑ ነበረች::
ከግርፋቱ እስከ ስቅላቱ እያለቀሰች ተከትላዋለች:: በእግረ
#መስቀሉ ያለቅሱ ከነበሩ ቅዱሳት አንስትም አንዷ እርሷ
ነበረች:: (ዮሐ. 19:25) ቅዱሳኑ #ዮሴፍና #ኒቆዲሞስ ጌታን
ሲቀብሩትም ከእሕቶቿ ጋር አብራ ተከትላ አይታለች::
እሑድ በሌሊት: ገናም ሳይነጋ መቃብሩን ታይ ዘንድ: ሽቱም
ልትቀባ ወደ ጐልጐታ ገሠገሠች:: ፍጹም የአምላክ ፍቅር
አድሮባታልና ግርማ ሌሊቱንና የአይሁድ ጭፍሮችን
አልፈራችም:: ጌታችንም #ከእመቤታችን ቀጥሎ ከፍጥረት
ወገን ትንሳኤውን ያየች የመጀመሪያዋ ሰው ትሆን ዘንድ
አደላት::
በመቃብሩ ራስጌና ግርጌም 2 መላእክትን
( #ሚካኤልና_ገብርኤልን ) ተመለከተች:: ዘወር ስትል ደግሞ
የክብርን ባለቤት አየችው:: አላወቀችውምና "ማርያም"
አላት:: "ረቡኒ-ቸር መምሕር ሆይ" ብላ ሰገደችለት::
ጌታም "ሑሪ ኀበ አኀውየ ወበሊዮሙ . . . ሒደሽ ለደቀ
መዛሙርቴ በያቸው . . . " ብሎ የትንሳኤው ሰባኪ አደረጋት::
"ወሖረት ወነገረቶሙ ለአርዳኢሁ . . . " እንዲል ትንሳኤውን
ለደጋጉ #ሐዋርያት ሰበከችላቸው::
#ቅድስት_ማርያም መግደላዊት ከክርስቶስ ትንሳኤ በሁዋላ
ለ40 ቀን #መጽሐፈ_ኪዳንን : #ትምሕርተ_ኅቡዓትን
ተምራለች:: በዕርገቱ ተባርካ: በበዓለ ሃምሳ ከቅዱስ መንፈሱ
ጸጋ ተካፍላለች:: በአዲሲቷ #ቤተ_ክርስቲያን ውስጥም ልዩ
አገልግሎት ነበራት::
ቅዱሱ #እስጢፋኖስ 8 ሺውን ማሕበር ሲመራ ሴቶችን
ታስተዳድርለት ነበር:: ከሁሉ በላይ ግን ቅድስቲቱ የቅዱሳን
ሐዋርያት መጋቢ ነበረች:: በዘመኑ #መንፈስ_ቅዱስ
የሚባርከውን #አጋፔ (የፍቅር ማዕድ) የምታዘጋጀው እርሷ
ነበረች::
እንዲያውም አንዴ የሚበላ ጠፍቶ ለሐዋርያት ማዕድ ፍለጋ
በሔደችበት እግሯ ቆስሎና ደምቶ መመለሷ ይነገራል::
እንዲህ አድርጋ ያዘጋጀችውን ማዕድ #ቅዱስ_መልአክ ወርዶ
ወደ ሰማይ ወስዶታል:: ለቅዱሳን ሐዋርያትም እያመጣ
ይመግባቸው ነበር::
እናታችን #ማርያም_መግደላዊት በስብከተ ወንጌልም
የተመሰከረላት ነበረች:: የመጀመሪያዋ የሐዲስ ኪዳን
#ዲያቆናዊት ሴት ስትሆን ክርስትናንም ተዟዙራ ሰብካለች::
ስለ ቅዱስ ስሙም ሽሙጥን: ስድብን: መንገላታትን እና
ግርፋትን ታግሳለች::
በተለይ አይሁድ ብዙ አሰቃይተዋታል:: ቅድስቷ እናታችን
መልካሙን ገድል ተጋድላ በበጐ እድሜ በዚህች ቀን
ሔዳለች:: በዓለም የሚገኙ ክርስቲያኖች ሁሉ (ከአንዳንዶቹ
በቀር) ያከብሯታል::
#ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ
¤የቅዱሳኑ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ልጅ
¤በማሕጸን ሳለ #መንፈስ_ቅዱስ የሞላበት
¤በበርኀ ያደገና በገዳማዊ ቅድስና ያጌጠ
¤እሥራኤልን ለንስሃ ያጠመቀ
¤የጌታችንን መንገድ የጠረገ
¤ጌታውን ያጠመቀና
¤ስለ እውነት አንገቱን የተቆረጠ ታላቅ ሰው ነው::
+ስለዚሕም ቤተ ክርስቲያን # ነቢይ: #ሐዋርያ: #ሰማዕት :
#ጻድቅ : #ገዳማዊ : #መጥምቀ_መለኮት : #ጸያሔ_ፍኖት
#ቃለ_ዐዋዲ ብላ ታከብረዋለች::
ቅዱሱ በዚህች ዕለት ወደ እሥር ቤት ገብቷል:: ይሕስ
እንደ ምን ነው ቢሉ:-
¤ንጉሡ ሔሮድስ የወንድሙን የፊልዾስን ሚስት ሔሮድያዳን
በማግባቱና በመሰል ክፋቶቹ ቅዱስ ዮሐንስ ይገስጸው ነበር::
ቅዱስ ዮሐንስ "መምሕር ወመገስጽ: ዘኢያደሉ ለገጽ - ፊት
አይቶ የማያዳላ" ነውና ገሰጸው::
ሔሮድስ ቅዱሱን ይፈራው: ያከብረውም ነበር:: በሁዋላ
ግን ፈቃደ ሥጋው ስላየለበት: በተለይ ደግሞ ከ7 ቀናት
በሁዋላ ልደቱን ሲያከብር እንዳይረብሸው በመስጋት በዚህች
ቀን በወታደሮቹ አስይዞ እሥር ቤት ውስጥ ጥሎታል:: ለ7
ቀናት በጨለማ ውስጥ አሥሮ መስከረም 2 ቀን አንገቱን
እንዴት እንዳስቆረጠው ዕለቱን ጠብቀን እንመለከታለንና የዚያ
ሰው ይበለን::
አባ ባይሞን /ዼሜን/
ይህ ቅዱስ አባት የ4ኛው መቶ ክ/ዘ የቤተ ክርስቲያን ፍሬ
ሲሆን ተሰምተው በማይጠገቡ መንፈሳዊ ቃላቱ (ምክሮቹ)ና
በቅድስና ሕይወቱ ይታወቃል:: ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው
ቢሉ:-
በተጠቀሰው ዘመን በምድረ ግብጽ የምትኖር አንዲት ደግ
ሴት ነበረች:: አምላክ በፈቀደው ጋብቻ ውስጥ ገብታ 7
ወንዶች ልጆችን አፈራች:: እነዚህ 7ቱ የቁጥር ጭማሪ:
የጾታም ቅያሪ የላቸውም:: 7ቱም ወንድማማቾች ገና ሕጻን
እያሉ አባት በመሞቱ እናት ፈተና ውስጥ ገባች::
ነገር ግን ብርቱ ሴት ነበረችና በወዟ ደክማ አሳደገቻቸው::
ሥጋዊ ማሳደጉስ ብዙም አይደንቅም:: ምክንያቱም ሁሉም
እናቶች ይህንን ያደርጉታል ተብሎ ይታመናልና:: የዚህች
እናት የሚገርመው ግን ሁሉንም ንጹሐን: የተባረኩ:
የክርስቶስ ወዳጆች: የቤተ ክርስቲያንም አለኝታዎች እንዲሆኑ
አድርጋ ማሳደጉዋ ነው::
እነዚህ 7 ወንድማማቾች:-
1.አብርሃም
2.ያዕቆብ
3.ዮሴፍ
4.ኢዮብ
5.ዮሐንስ
6.ላስልዮስ እና
7.ባይሞን ( #ዼሜን ) ይባላሉ:: ለእነዚህም ዮሐንስ በኩር
ሲሆን ባይሞን መቁረጫ ነው::
+7ቱም ወጣት በሆኑ ጊዜ ወገባቸውን ታጥቀው እናታቸውን
ያገለግሉ: ለፈጣሪያቸው ይገዙ ያዙ:: ያየ ሁሉ "ከዐይን
ያውጣችሁ" የሚላቸው: ቡሩካንም ሆኑ:: አንድ ቀን ግን
#መንፈስ_ቅዱስ በ7ቱ ልብ ውስጥ አንድ ቅን ሃሳብን
አመጣ:: ሁሉም እንደ አንድ ልብ መካሪ: እንደ አንድ ቃል
ተናጋሪ ስለ ምናኔ አወሱ::
ይህንን ዓለም ከነ ኮተቱ ይተውት ዘንድ መርጠዋልና ወደ
በርሃ ለመሔድ ተስማሙ:: እናታቸው ምን መንፈሳዊ ብትሆን
የትኛዋም እናት ሁሉን ልጆቿን በአንዴ ማጣትን
አትፈልግምና አላማከሯትም:: ይልቁኑ እነርሱ ከሔዱ በሁዋላ
እንዳትቸገር የምትታገዝበትን መንገድ አዘጋጅተውላት
ተሰወሩ::
7 ልጆቿን በአንዴ ያጣችው እናት ብቻ አይደለችም: ሁሉም
አዘነ:: ተፈለጉ: ግን አየሁዋቸው የሚል ሰው አልተገኘም::
7ቱም # ቅዱሳን ከቤታቸው እንደ ወጡ ወደ ገዳም ሔደው
አንዲት በዓት ተቀበሉ:: 7ቱም የሚጸልዩ በጋራ: የሚሠሩ:
የሚመገቡ: የሚውሉ: የሚተኙም በጋራ ነው::
በአገልግሎታቸውም ሆነ በፍቅራቸው አበውን ደስ አሰኙ::
"እምኩሉ የዓቢ ተፋቅሮ - እርስ በርስ መዋደድ ከሁሉ
ይበልጣል" እንዲሉ አበው:: ከዘመናት ተጋድሎ በሁዋላ ግን
ዝናቸው ከገዳሙ አልፎ በከተሞች ተሰማ:: ይህንን
የሰማችው እናታቸው የእርሷ ልጆች መሆናቸውን በማወቁዋ
ፈጥና ወደ ገዳሙ ገሰገሰች::
"ልያችሁ ልጆቼ?" ስትልም ላከችባቸው:: እነሱ ግን
"እናታችን በመንግስተ ሰማያት እንድታይን በዚህ ይቅርብሽ"
አሏት:: ምክንያቱም 7ቱም የሴትን ፊት ላያዩ ቃል ገብተው
ነበርና:: ይህ ለአንድ እናት ከባድ ቢሆንም እርሷ ግን
ተረዳቻቸው:: ፈጥናም ወደ ቤቷ ተመለሰች::
ከኮከብ ኮከብ ይበልጣልና (1ቆረ. 15:41) ከ7ቱ ቅዱሳን
ደግሞ ትንሹ #አባ_ባይሞን የተለየ አባት ሆነ:: ከንጽሕናው:
ቅድስናና ትጋቱ ባሻገር ከአንደበቱ የሚወጡ ቃላት ሕይወትነት
ያላቸው ሆኑ:: በዘመኑም ከሕጻን እስከ አዋቂ ድረስ ብዙዎች
ከመንፈሳዊ ቃላቱ ተጠቅመዋል::
+እነዚህ ምክሮቹ ዛሬ ድረስ ለምዕመናንም ሆነ ለመነኮሳት
ጣፋጮች ናቸው:: እልፍ አእላፍ ከሆኑ ምክሮቹ እስኪ አንድ
አምስቱን እንጥቀስ:-
1."ባልንጀራህ በወደቀ ጊዜ በፍጹም ተስፋ አትቁረጥበት::
ይልቅስ አንቃው: አበረታታው: ሸክሙንም አቅልለት እንጂ"
2."ለጥሩ ባልጀራህ የምታደርገውን ደግነት ለክፉው በእጥፍ
አድርግለት::
መድኃኒትን የሚሻ የታመመ ነውና:: አልያ ግን ለበጐው
ያደረከው ከንቱ ነው"
3."ባልጀራህ በበደለ ጊዜ አትናቀው:: ያንተ ተራ በደረሰ ጊዜ
ጌታህ ይንቅሃልና"
4."የማንንም ኃጢአት አትግለጥ (አታውራ):: ካላረፍክ ጌታ
ያንተኑ ይገልጥብሃልና"
5."አንደበትህ የተናገረውን ሁሉ ለመሥራት ታገል:: አልያ
ውሸታም ትሆናለህ"
7ቱ ቅዱሳን ወንድማማቾች ለብዙ ዓመታት በፍቅርና
በተጋድሎ ኑረው በዚህች ቀን ዐርፈዋል::
#ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ
ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነ ዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር
ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል:: #ቅዱስ_ሉቃስ
ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ
ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል:: "#ዘካርያስ ካህኑና
#ቅድስት_ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ
ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: (ሉቃ. 1:6)
የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ
መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል!
እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው
ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ
ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90
የዘካርያስ 100 ደግሞ ደርሶ ነበር::
ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ
እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ: ትንቢት ለብቻው
የተነገረለት (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) ታላቅ ነቢይን
ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን
ላከላቸው::
ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ
ድዳ ሆነ:: ቅድስቲቷ ግን መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው
ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች:: በ6ኛው ወር የፍጥረት
ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል
#እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች::
ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው::
የአምላክ እናቱ ስትደርስና "#ሰላም " ስትላቸው መንፈስ
ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና: ዮሐንስ
ደግሞ ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ):: ከዚህ
በሁዋላ ሰኔ 30 ተወልዶ: አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው
አንደበቱ
ተፈትቶለታል::
ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ 2 ዓመት ከ6 ወር በሆነው
ጊዜ #ሰብአ_ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር
የሚገኙ ሕጻናትን ሔሮድስ ቁዝ አስፈጀ:: ትንሽ ቆይቶም
አይሁድ ለሔሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕጻን ነገሩት:: "ሲጸነስ
የአባቱን አንደበት የዘጋ: ሲወለድ ደግሞ የከፈተ
'ዮሐንስ' የሚባል ሕጻን አለና እሱንም ግደል" አሉ::
እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን
ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል::
አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕጻኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ
ለ3 (5) ዓመታት ቆይታለች:: ቅዱስ ዮሐንስ 5 (7)
ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች::
ከሰማይ ዘካርያስና # ስምዖን ወርደው ቀበሯት::
ሕጻኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ #ድንግል_ማርያም ስንት አገር
አልፋ ሰማችው:: እርሷም ስደት ላይ ነበረችና:: ከጌታ
ጋር በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው:: ጌታንም
"እንውሰደው ይሆን?" አለችው:: ጌታችን ግን
"ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ" አላት::
ባርካው: አጽናንታውም ተለያዩ::
ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በሁዋላ በዚያ ቆላ የግመል
ጠጉር ለብሶ: ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ:: ለ25
(23) ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና
ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም:: ይሕችን
ዐመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም::
ከዚህ በሁዋላ 30 ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር
ከሰማይ ተናገረው:: "ሒድ! የልጀን ጐዳና ጥረግ"
አለው:: ነቢያት ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና:: (ኢሳ.
40:3, ሚል. 3:1) አባቱ ዘካርያስም "ወአንተኒ ሕጻን
ነቢየ ልዑል ትሰመይ: እስመ ተሐውር ቅድመ
እግዚአብሔር ከመ ትጺሕ ፍኖቶ" (ሉቃ. 1:76) ብሎ
መንገድ ጠራጊነቱን ተናግሮ ነበርና::
ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ #መንፈስ_ቅዱስ
እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ:: ያዩት ሁሉ ፈሩት:
አከበሩት:: ቁመቱ ቀጥ ያለ: ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር
የወረደ: ጸጉሩ የቁራ ያህል የጠቆረ: መልኩ የተሟላ:
ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ነውና::
ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሃ ሰበከ:: ለንስሃም በርካቶችን
አጠመቃቸው:: በዚህ አገልግሎት ለ6 ወራት ቆይቶ
ጌታችን ወደ እርሱ ዘንድ መጣ:: ዮሐንስ ሰማይን
ከነግሱ: ምድርን ከነ ልብሱ የያዘ ፈጣሪ 'አጥምቀኝ'
ብሎ ሲመጣ ደነገጠ:: የሚገባበትም ጠፋው::
"እንቢ ጌታየ! አንተ አጥምቀኝ" አለው:: ጌታ ግን
"ፈቅጄልሃለሁ" አለው:: አጠመቀው:: በዚህ ምክንያት
ይሔው እስከ ዛሬም "#መጥምቀ_መለኮት " ሲባል
ይኖራል:: ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻ ሔሮድስን ገሰጸው::
ንጉሡም ተቀይሞ ለ7 ቀናት አሠረው::
በዚህች ቀንም ልደቱን ባከበረ ጊዜ ወለተ ሔሮድያዳ
በዘፈን አጥምዳ አስማለችው:: እርሱም የታላቁን ነቢይ
ራስ አስቆርጦ በወጪት አድርጐ ሰጣት:: አበው
"እምሔሶ ለሔሮድስ ይብላዕ መሐላሁ - ሔሮድስ
መሐላውን በበላ በተሻለው ነበር" ይላሉ:: የቅዱስ
ዮሐንስ ራሱ በርራ ስትሔድ አካሉን ግን ደቀ መዛሙርቱ
ቀብረውታል:: (ማቴ. 3:1, ማር. 6:14, ሉቃ. 3:1, ዮሐ.
1:6)
ርጉም ሔሮድስ አንገቱን ካስቆረጠው በሁዋላ
የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራሱ የጸጋ ክንፍ ተሰጥቷት
ጌታችን ወዳለበት #ደብረ_ዘይት ሔዳ በፊቱ ሰገደች::
#ቅዱሳን_ሐዋርያት በአዩት ነገር ተገርመው ራሱን እጅ
ነሷት::
ከዚሕ በሁዋላ ጌታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ ለቅዱስ
ዮሐንስ ራስ የማስተማር ስልጣን ሰጥቶ አሰናበታት::
በመላው ዓለም ለ15 ዓመታት ስትሰብክ ኑራ በዚህች
ቀን ዓረቢያ ውስጥ ዓርፋለች::
ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት ወቀዳሜ ሰማዕት
በሕገ ወንጌል (ክርስትና) የመጀመሪያው ሊቀ
ዲያቆናትና ቀዳሚው ሰማዕት ይህ ቅዱስ ነው:: ቅዱሱ
በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን አስገራሚ ማንነት
ከነበራቸው እሥራኤላውያን አንዱ ነበር:: ይህስ እንደ
ምን ነው ቢሉ:-
የቅዱስ እስጢፋኖስ ወላጆቹ ስምዖንና ማርያም
ይባላሉ:: (ሌሎች ናቸው የሚሉም አሉ) ገና ከልጅነቱ
ቁም ነገር ወዳድ የነበረው ቅዱስ በሥርዓተ ኦሪት አድጐ
እድሜው ሲደርስ ወደ ት/ቤት ገባ:: የወቅቱ ታላቅ
መምሕር ገማልያል ይባል ነበር:: ይህ ሰው በሐዋርያት
ሥራ ምዕራፍ 5:33 ላይ ተጠቅሷል::
በትውፊት ትምሕርት ደግሞ ይህ ደግ (ትልቅ) ሰው
በርካታ ቅዱሳንን (እስጢፋኖስን: ዻውሎስን: ናትናኤልን:
ኒቆዲሞስን . . .) አስተምሯል:: በጌታችን መዋዕለ
ስብከት ጊዜም ከፈጣሪያችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ
እየቀረበ ይጨዋወት ነበር:: በፍጻሜውም አምኗል::
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱስ እስጢፋኖስ
ከዚህ ምሑር ዘንድ ተምሮ: ኦሪቱን ነቢያቱን ጠንቅቆ
ወጣ:: ወቅቱ አስቸጋሪና ለኃጢአት ሕይወት የተመቸ
ቢሆንም ቅዱሱ ግን የመሲህን መምጣት በጸሎትና
በተስፋ ይጠባበቅ ነበር::
በወቅቱ ደግሞ #መጥምቁ_ቅዱስ_ዮሐንስ የንስሃ
ጥምቀትን እየሰበከ መምጣቱን የተመለከተ ቅዱስ
እስጢፋኖስ ነገሩን መረመረ:: ከእግዚአብሔር ሆኖ
ቢያገኘው የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ሆነ:: ለ6
ወራትም በትጋት ቅዱስ ዮሐንስን አገለገለ::
ለ6 ወራት ከቅዱስ #ዮሐንስ ዘንድ ከተማረ በሁዋላ
ለስም አጠራሩ ስግደት ይድረሰውና ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ተጠመቀ::
በወቅቱ የተደረገውን ታላቅ ተአምር ልብ ያለው ቅዱስ
እስጢፋኖስ መምሕሩን ቅዱስ ዮሐንስን እንዲያስረዳው
ጠየቀው::
"ከእኔ ይልቅ ከፈጣሪው አንደበት ይስማው" በሚል
ላከው:: ቅዱሱም ከጌታ ዘንድ ሔዶ: እጅ ነስቶ ተማረ::
(ሉቃ. 7:18) በዚያውም የጌታ ደቀ መዝሙር ሆኖ ቀረ::
ጌታም ከ72ቱ #አርድእት አንዱ አድርጐት ለአገልግሎት
ላከው:: አጋንንትም ተገዙለት:: (ሉቃ. 10:17)
ቅዱስ እስጢፋኖስ ጌታችን #መድኃኔ_ዓለም ከዋለበት
እየዋለ: ካደረበት እያደረ ወንጌልን ተማረ:: ምሥጢር
አስተረጐመ:: ጌታ በፈቃዱ ስለ እኛ ሙቶ ከተነሳ በሁዋላ
ሲያርግ ደቀ መዛሙርቱን በአንብሮ እድ ባርኩዋል::
በዚህ ጊዜም ቅዱሱ እንደ ወንድሞቹ #ሐዋርያት
ቅስናን (ዽዽስናን) ተሹሟል:: በበዓለ ሃምሳም
#መንፈስ_ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከ72ቱ አርድእት የእርሱን
ያህል ልሳን የበዛለት: ምሥጢርም የተገለጠለት የለም::
በፍጹም ድፍረትም ወንጌልን ይሰብክ ገባ::
በመጀመሪያይቱ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ከማዕድ ሥርዓት
ጋር በተያያዘ ፈተና ሲመጣ በመንፈስ ቅዱስ ምርጫ 7
#ዲያቆናት ሲመረጡ አንዱ እርሱ ነበር:: አልፎም የ6ቱ
ዲያቆናት አለቃ እና የ8ሺው ማሕበር መሪ (አስተዳዳሪ)
ሆኗል::
8ሺ ሰውን ከአጋንንት ፈተና መጠበቅ ምን ያህል ከባድ
እንደ ሆነ ለማወቅ አባቶቻችንን መጠየቅ ነው:: አንድን
ሰው ተቆጣጥሮ ለድኅነት ማብቃት እንኩዋ እጅግ ፈተና
ነው:: መጽሐፍ እንደሚል ግን 'መንፈስ ቅዱስ የሞላበት:
ማሕደረ እግዚአብሔር' ነውና ለእርሱ ተቻለው:: (ሐዋ.
6:5)
አንዳንዶቻችን ቅዱስ እስጢፋኖስ 'ሊቀ ዲያቆናት'
ሲባል እንደ ዘመኑ ይመስለን ይሆናል:: እርሱ
በመጀመሪያ ሐዋርያና ካህን ነው:: ዲቁናው ለእርሱ 'በራት
ላይ ዳረጐት' ነው እንጂ እንዲሁ
ዲያቆን ብቻ አይደለም::
ቅዱስ እስጢፋኖስ ከጌታ ዕርገት በሁዋላ ለ 1 ዓመት
ያህል 8ሺውን ማሕበር እየመራ: ወንጌልን እየሰበከ
ቢጋደል #ኦሪት 'እጠፋ እጠፋ': #ወንጌል ደግሞ 'እሰፋ
እሰፋ' አለች:: በዚህ ጊዜ 'ክርስትናን ለማጥፋት
መፍትሔው ቅዱስ እስጢፋኖስን መግደል ነው' ብለው
አይሁድ በማመናቸው ሊገልድሉት አስበውም አልቀሩ
ገደሉት::
እርሱ ግን ፊቱ እንደ #እግዚአብሔር መልአክ እያበራ
ፈጣሪውን በብዙ ነገር መሰለው:: በመጨረሻውም ስለ
እነሱ ምሕረትን እየለመነ በድንጋይ ወገሩት:: ደቀ
መዛሙርቱም ታላቅ ለቅሶን እያለቀሱ ቀበሩት::
ፍልሠት
ቅዱስ እስጢፋኖስ ካረፈ ከ300 ዓመታት በሁዋላ
በኢየሩሳሌም የሚኖር አንድ ደግ ሰው ነበር:: ስሙም
#ሉክያኖስ ይባል ነበር:: በተደጋጋሚ በራዕይ ቅዱሱ
እየተገለጠ "ሥጋየን አውጣ" ይለው ነበርና ሒዶ
ለዻዻሱ ነገረው:: ዻዻሱም ደስ ብሎት ካህናትና
ምዕመናንን ሰብስቦ ወደ አጸደ # ገማልያል (የመምሕሩ
ርስት ነው) ሔደ::
ቦታውንም በቆፈሩ ጊዜ ታላቅ መነዋወጥ ሆነ::
መላእክት ሲያጥኑ በጐ መዓዛ ሸተተ:: ዝማሬ
መላእክትም ተሰማ:: ሕዝቡና ዻዻሱም በቅዱስ
እስጢፋኖስ ፊት ሰግደው: በታላቅ ዝማሬና በሐሴት
ዐጽሙን ከዚያ አውጥተው: በጽርሐ #ጽዮን
(በተቀደሰችው ቤት) አኖሩት::
#እለ_እስክንድሮስ የተባለ ደግ ሰውም ቤተ ክርስቲያን
አንጾለት ወደዚያ አገቡት:: ከ5 ዓመታት በሁዋላም እለ
እስክንድሮስ ሲያርፍ በሳጥን አድርገው በቅዱሱ ጐን ስለ
ፍቅሩ አኖሩት:: ሚስቱ ወደ ሃገሯ #ቁስጥንጥንያ
ስትመለስ የባሏን ሥጋ መስሏት የቅዱስ እስጢፋኖስን
ቅዱስ ሥጋ በመርከብ ጭና ወሰደችው::
መንገድ ላይ ከሳጥኑ ውስጥ ዝማሬ ሰምታ ብታየው
ያመጣችው የቅዱሱን ሥጋ ነው:: እጅግ ደስ አላት:
አምላክ ለዚህ አድሏታልና:: እርሷም ወስዳ ለታላቁ
ንጉሥ #ቅዱስ_ቆስጠንጢኖስ አስረከበች:: በከተማውም
ታላቅ ሐሴት ተደረገ::
ሥጋውን ሊያኖሩት በበቅሎ ጭነው ሲወስዱትም
በቅሎዋ በሰው ልሳን ተናግራ ማረፊያውን አሳወቀች::
በዚያም ላይ ትልቅ ቤተ ክርስቲያን ታንጾለታል:: ቅዱስ
እስጢፋኖስ ሲመቱ ጥቅምት 17: ዕረፍቱ ጥር 1:
ፍልሠቱ ደግሞ መስከረም 15 ቀን ነው::
#ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ
ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል:: #ቅዱስ_ሉቃስ የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል:: "ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: (ሉቃ. 1:6)
የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል! እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር::
እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90 የዘካርያስ 100 ደግሞ ደርሶ ነበር:: ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ: ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ #መልአከ_ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው::
ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ:: ቅድስቲቷ ግን መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች:: በ6ኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ
#የአርያም_ንግሥት ድንግል እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ #ኤልሳቤጥ መጣች:: ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው::
የአምላክ እናቱ ስትደርስና "ሰላም" ስትላቸው
#መንፈስ_ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና: ዮሐንስ ደግሞ ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ):: ከዚህ በሁዋላ ሰኔ 30 ተወልዶ: አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል::
የእመቤታችን ልመናዋ: ክብሯ: የልጇ የወዳጇም ቸርነት በእውነት ከሁላችን ጋር ይሁን:: የመጥምቁንም በረከት ያብዛልን::
💚💛 #ቅድስት_አትናስያ 💛❤️
የዚህች ቅድስት ሕይወት በብዛት የእግዚአብሔርን ቸርነትና የንስሃን ፍጹምነት የሚያሳይ ነው:: ጥንተ ነገሩስ.እንደ ምን ነው ቢሉ:-
ቅድስት አትናስያ ግብፃዊት ስትሆን የነበረችውም #መኑፍ
በሚባል አውራጃ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ይህ ዘመን
"ዘመነ ከዋክብት" ይባል ነበር:: ከቁጥር የበዙ ቅዱሳንም በዘመኑ ነበሩ:: ቅድስት አትናስያም ከክርስቲያን ወላጆች ተወልዳ:
እንደሚገባ አድጋ: ገና በወጣትነቷ ሁለቱም ወላጆቿ ሞቱባት:: ነገር ግን ብዙ ሃብት ትተውላታልና ምን
እንደምታደርገው ሃሳብ ሆናት:: #መንፈስ_ቅዱስ ግን
መልካሙን ሕሊና አደላትና አብርሃማዊ ሥራን ለመሥራት
ቆረጠች:: መጀመሪያ አገልጋዮችን አዘጋጀች:: እንደየ ወገኑ
ለእንግዶችና ለነዳያን ቤትን ሠራች:: በጐውን እድል
መርጣለችና ለብዙ ዓመታት ለነዳያን በማድላት: እንግዶችን
በመቀበል ተጠመደች:: በዚህ ሥራዋም እግዚአብሔርንም
ሰውንም ደስ አሰኘች::
ግብሯ እንዲህ ነው:: በሌሊት ጸሎት: በመዓልት ግን
እንግዶችን መቀበል: እግር ማጠብ: ማስትናገድ: ማስተኛት:
ስንቅ አሰንቆ መስደድ ነው:: በዚህ ግብሯ ከምንም በላይ የወቅቱን ጻድቃን አስደስታለች:: በዚያው ልክ ግን ዲያብሎስ ተቆጥቶ ይከተላት ጀመር::
በብዙ ጐዳና አልሳካልህ ቢለውም በክፉ ጐረቤቶቿ አማካኝነት ግን ተሳካለት:: የአካባቢዋ ሰወች ወደ እርሷ ተሰብስበው በብዙ ማታለል ከቅድስና ሕይወቷ ፈቀቅ
እንድትል አደረጉ:: እነርሱ መልካም ሥራዋን ያስተዋት በመልክ ቆንጆ ነበረችና
ይህንን ተጠቅመው ነው:: "ውበትና ሀብትሽን አታባክኚ"
ብለው ከጐዳና አስወጧት:: መጽሐፍ ክፉ ባልንጀርነትን
የሚቃወመው ለዛ ነው:: መልካም #ክርስቲያን ማለት
ባልንጀራውን የሚመርጥ ነው::
+የሚገርመው ያን ያህል እንግዳ ተቀብላበት ያላለቀ ገንዘብ
አሁን ግን ተመናመነ:: ክፉዎቹ ምክራቸውን ቀጠሉ:: አካሏን
እንድትሸጥ አሳምነው ሴተኛ አዳሪ አደረጉዋት:: ባንዴ ከዚያ
የቅድስና ከፍታ ወርዳ አካሏን ለዝሙት የምትሸጥ ሆነች::
+ነገሩን የሰሙ ገዳማውያን ሁሉ አዘኑ: አለቀሱላት:: ይልቁኑ
ለእነሱ የእናት ያህል ደግ ነበረችና ከዲያብሎስ ሴራ
ሊታደጉዋት ቆረጡ:: ከመካከላቸውም #ቅዱስ_ዮሐንስ_
ሐጺርን ለዚህ ተግባር መረጡ:: እርሱ በአጋንንት ላይ ስልጣን
ያለው ሰው ነውና::
እነርሱ ሱባ዗ ይዘውላት አባ ዮሐንስ ሐጺር ወደ መኑፍ
ከተማ ሔደ: ወደ ቤቷም ደረሰ:: ጠባቂዋን አስፈቅዶ ሲገባ
ለረከሰው ድርጊት የመጣ ሰው መስሏት ተዘጋጅታ ነበር:: አባ
ዮሐንስ ሐጺር ግን አጋንንትን ያርቅ ዘንድ እየዘመረ ገባ::
"እመኒ ሖርኩ ማዕከለ ጽላሎተ ሞት . . . በሞት ጥላ ሥር
እንኩዋ ብሔድ አንተ ከኔ ጋር ነሕና ክፉን አልፈራም" እያለ
ቀረባት:: (መዝ. 22)
ፈጠን ብሎ ከጐኗ ተቀምጦ ቅዱሱ ምርር ብሎ አለቀሰ::
አትናስያ ደንግጣ "ምነው?" አለችው:: "የአጋንንት ሠራዊት
በራስሽ ላይ ሆነው እየጨፈሩኮ ነው" አላት:: አስከትሎም
አጋንንቱን በጸሎቱ ቢያርቅላት በአንዴ ወደ ልቧ ተመለሰች::
ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ሰው የሠራችውን ሁሉ ማመን
አቃታት:: ተስፋም ቆረጠች:: ቅዱስ ዮሐንስ ግን
"ግዴለሽም: ንስሃ ግቢ:: ፈጣሪ ይምርሻል" ብሎ
አሳመናት:: "እሺ አባቴ" ብላ ከቀደመው ዘመን ሥርዓት
ያለውን አንዱን ቀሚስ ለብሳ: ጫማ ሳትጫማ: ሌላ ልብስ
ሳትደርብ: ምንም ነገር ሳትይዝ ከቤት ወጣች::
ቤቷን አልዘጋችም:: ዘወር ብላ ወደ ሁዋላም አልተመለከተችም:: ቅዱሱን ተከትላ ጉዞ ወደ በርሃ ሆነ:: ያበእንክብካቤ የኖረ አካል እሾህና እንቅፋት: ብርድና ፀሐይ
ጐበኘው:: ሲመሽ እጅግ ደክሟታልና "እረፊ" ብሏት ሊጸልይ
ፈቀቅ አለ:: መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜ #መላእክት ከሰማይ የብርሃን
ዓምድ ዘርግተው አንዲትን ነፍስ በዝማሬ ሲያሳርጉ አየ::
"የማን ነፍስ ትሆን" ብሎ ወደ #አትናስያ ሲሔድ መሬት ላይ
ዘንበል ብላ ዐርፋ አገኛት:: ቅዱሱም "ጌታ ሆይ! ምነው
ለንስሃ እንኩዋ ብታበቃት?" ብሎ አለቀሰ:: ፈጣሪ ከሰማይ ተናገረ:- "ገና ከቤቷ ተጸጽታ ስትወጣ ነው
ይቅር ያልኩዋትና ደስ ይበላችሁ" አለው:: ይህንን የአምላክ
ቃል ሁሉም ገዳማውያን ሰምተው እጅግ ደስ አላቸው:: "ጻድቅ 7 ጊዜ ይወድቃልና: 7 ጊዜ ይነሳል::"
@dn yordanos
💚💛ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ 💛❤️
ቅዱስ ቄርሎስን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን " #ዓምደ_ሃይማኖት- የሃይማኖት ምሰሶ" ይሉታል:: ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

ሊቁ የተወለደው በእስክንድርያ (ግብጽ) በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: እናቱ የወቅቱ ፓትርያርክ #ቅዱስ_ቴዎፍሎስ እህቱ ነበረችና አጎቱ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ወስዶ አሳድጐታል:: ገና በልጅነቱ ወደ #አባ_ሰራብዮን ገዳም ገብቶ ቅዱሳት መጻሕፍትንና ገዳማዊ ሕይወትን ተምሯል:: በጾም: በጸሎትና በትሕትና የታሸ ነውና ሲማር አንድ ጊዜ ካነበበው በሕሊናው ተስሎ ይቀር ነበር::
ቅዱስ ቴዎፍሎስ "ምዕመናንን አስተምርልኝ" ብሎ ወደ ከተማ አመጣው:: #መንፈስ_ቅዱስ አድሮበታልና ሲያስተምር ወይ ደግሞ መጻሕፍትን ሲያነብ ከምዕመናን ወገን ስንኩዋን የሚያወራና የሚንቀሳቀስ ቀርቶ የሚቀመጥም አልነበረም:: ጣዕመ ስብከቱም ብዙዎችን ለወጠ::
ከዚያም በ412 ዓ/ም አጎቱ የነበረው ፓትርያርክ አባ ቴዎፍሎስ ሲያርፍ ዻዻሳትና ሊቃውንት በአንድነት ቅዱስ ቄርሎስን መረጡ:: የእስክንድርያም 24ኛ ሊቀ ዻዻሳት ሆኖ ተሾመ:: በዘመኑ #ቤተ_ክርስቲያን አበራች:: በቅድስናው: በሊቅነቱ: በስብከቱ: በድርሰቶቹና በትጋቱ በፍጹም አገለገላት::

በወቅቱ ስመ ክፉ መናፍቅ ንስጥሮስ ተነስቶ የእስያ አብያተ ክርስቲያናትን አወካቸው:: ትምሕርቱ ክርስቶስን "2 አካል: ባሕርይ ነው" (ሎቱ ስብሐት!) የሚል ነበር:: በእውነት እንየው ከተባለ ግን ጠቡና ጥላቻው ከድንግል ማርያም ጋር ነበር:: ምክንያቱም ጌታችንን ወደ 2 የከፈለው #እመቤታችንንየአምላክ እናት አይደለሽም ለማለት ነው:: (ላቲ ስብሐት!)
ነገሩን #ቅዱስ_ቄርሎስ በሰማ ጊዜ ወዳለበት ሒዶ ቢመክረውም ንስጥሮስ ሊሰማ አልፈለገም:: በዚህ ምክንያት በትንሹ ቴዎዶስዮስ (የቁስጥንጥንያ ንጉሥ) ትዕዛዝ በኤፌሶን ታላቅ ጉባኤ እንዲሰበሰብ ሆነ:: ይህ ጉባዔ በቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻው የተቀደሰ ጉባዔ ነው:: በ431 ዓ/ም #በኤፌሶን ከተማ የመናፍቃኑን ጥርቅም ሳንቆጥር ሃይማኖታቸው የቀና 200 #ቅዱሳን_ሊቃውንት ተገኙ::

የሚገባው ጸሎትና ሱባዔ ከተፈጸመ በሁዋላ ጉባዔው ተጀመረ:: አፈ ጉባዔው ሊቀ ማሕበር ማር (ቅዱስ) ቄርሎስ ነበርና በጉባዔ ፊት ንስጥሮስን ተከራክሮ ረታው:: ምላሽም አሳጣው:: ከቅዱሳት መጻሕፍት #ክርስቶስ አንድ ባሕርይ መሆኑን: #ድንግል_ማርያምም #ወላዲተ_አምላክ መሆኗን እየጠቀሰ: በምሳሌም እያሳየ አስረዳ::
የሰይጣን ማደሪያ ንስጥሮስ ግን እንቢ: አላምንም በማለቱ ተወግዞ ተለየ:: ቅዱሳን ሊቃውንቱም በቅዱስ ቄርሎስ አርቃቂነት 12 አንቀጾችን አዘጋጅተው ወደ ዓለም ሁሉ ላኩ:: እሊህ አንቀጾች ዛሬም በሊቃውንቱ እጅ አሉ:: ይነበባሉ: ይተረጎማሉ::

ከእነዚህም አንዱ ድንግል ማርያም " #ታኦዶኮስ(የእግዚአብሔር እናቱ) ናት" የሚል ነው:: እመቤታችንን:-
¤የአምላክ እናት:
¤ዘላለማዊት ድንግል:
¤ፍጽምት:
¤ንጽሕትና አማላጅ ብሎ ማመን ለሰማያዊ ርስት የሚያበቃ በጐ ሃይማኖት ነውና::
ጉባዔው ከተጠናቀቀ በሁዋላ ቅዱስ ቄርሎስ ንስጥሮስን ጠርቶ "በድንግል ማርያም እመን:: እርሷ ከልጇ ታስታርቅሃለች" ቢለው በድጋሚ "እንቢ" አለው:: ያን ጊዜ ሊቁ "ለአምላክ እናት ያልታዘዘ ምላስህ ላንተም አይታዘዝህ" ብሎ ረገመው:: ወዲያው ምላሱ ተጐልጉሎ ወጥቶ ደረቱ ላይ ወደቀ::
እንደ ውሻ እየተዝረከረከ ሒዶ ከወዳጆቹ ጋር ቁሞ ሳለ መሬት ተከፍታ ውጣዋለች::
ቅዱስ ቄርሎስ ግን ለ32 ዘመናት በመንበሩ ላይ አገልግሎ: ፍሬ ትሩፋት አፍርቶ: ብዙ ድርሰቶችንም ደርሶ በ444 ዓ/ም በዚህች ቀን ዐርፏል:: ከድርሰቶቹም ቅዳሴው: ድርሳነ ቄርሎስና ተረፈ ቄርሎስ ይጠቀሳሉ::

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአባቶቻችን ጸሎት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቅልን:: ከሊቁም በረከቱን ይክፈለን::
From:- d/n yordanos abebe

@senkesar @senkesar
💚💛ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ 💛❤️
ለቤተ ክርስቲያን በንጹሕ ሕይወታቸው ካበሩላት ዐበይት ቅዱሳን አንዱ #ቅዱስ_ዱማድዮስ ነው:: እርሱ ወደ ክርስትና የመጣው ከባዕድ አምልኮ ሲሆን መሪው #መንፈስ_ቅዱስ ነው:: ጣዕመ ሕይወቱን ሲሰሙት ዕዝነ ልቡናን ደስ ያሰኛል::

ገና በወጣትነቱ እንደ #ሐዋርያት ሰብኮ አሕዛብን አሳምኗል:: እንደ #ጻድቃን አካሉ አልቆ አጥንቶቹ እስኪታዩ ተጋድሏል:: እርሱ #ድንግል: #ንጹሕ: #መነኮስ: #ባሕታዊና #ካህን ነው:: ግን ውዳሴ ከንቱን አምርሮ ይጠላል:: በዚህ ምክንያት ካደረበት አይውልም: ከዋለበትም አያድርም::
እርሱ በጸሎቱ የተዘጉ ማሕጸኖችን ከፍቷል:: ዕውራንን አብርቷል:: ለምጻሞችን አንጽቷል:: አንካሶችን አርትቷል:: በፈጣሪው ኃይል ፈሳሽ ወንዝን አቁሟል:: እንደ ገናም እንደ ነበረው መልሶታል::

የቅዱስ ዱማድዮስ መጨረሻው ደግሞ #ሰማዕትነት ነው:: በበዓቱ ውስጥ ሳለ ከደቀ መዝሙሩ ጋር ክፉዎች በድንጋይ ወግረው ገድለውታል:: ድንጋዩም የኮረብታ ያህል ነበር:: ልክ በዓመቱ በዚህች ዕለት ምዕመናን ሥጋውን አፍልሠዋል::
🌿🌿🌿🌿🌿🌿🌿🌿🌿🌿🌿🌿
ቸር አምላክ ከነቢያት: ሐዋርያት: ጻድቃንና ሰማዕታት ክብርን ያሳትፈን::
From:- dn yordanos abebe
@senkesar @senkesar