ስንክሳር
7.32K subscribers
825 photos
4 videos
37 files
237 links
በስንክሳር channal ስንክሳሩ ተገልጦ ቅዱሳን ይዘከራሉ፣ ወቅቱን የጠበቁ መረጃዎችን ያገኛሉ፡፡ ይከታተሉን!
Download Telegram
#ቅዱስ_ዑቲኮስ_ሐዋርያ
ቅዱሱ ሐዋርያ ጭራሽ ከነ ስማቸው እንኩዋ እየተዘነጉ
ከሔዱ #ሐዋርያት አንዱ ሲሆን ቁጥሩም ከ72ቱ #አርድእት
ነው:: በወጣትነት ዘመኑ የጌታችን ደቀ መዝሙር መሆንን
መርጦ ለ3 ዓመታት ከ3 ወራት ምሥጢረ ወንጌልን ጠንቅቆ
ተምሯል::
መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜም እንደ መጠኑ ተቀብሎ
ለአገልግሎት ወጥቷል:: በመጀመሪያ የወንጌላዊው ዮሐንስ
ተከታይ ሁኖ ብዙ ምሥጢራትን ተካፍሏል:: ቀጥሎም ቅዱስ
ዻውሎስን ተከትሎ ብዙ አሕጉራትን በስብከተ ወንጌል
አዳርሷል::
በመጨረሻም በእስያ አካባቢ ለብቻው ተጉዞ: ብዙ ነፍሳትን
ማርኮ: ጣዖታትን አጥፍቷል:: ስለዚህ ፈንታም በእሳት:
በስለትና በግርፋት ብዙ መከራዎችን አሳልፏል:: በዚህች
ቀንም በበጐው እርግና (ሽምግልና) ዐርፏል::
ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት ወቀዳሜ ሰማዕት
በሕገ ወንጌል (ክርስትና) የመጀመሪያው ሊቀ
ዲያቆናትና ቀዳሚው ሰማዕት ይህ ቅዱስ ነው:: ቅዱሱ
በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን አስገራሚ ማንነት
ከነበራቸው እሥራኤላውያን አንዱ ነበር:: ይህስ እንደ
ምን ነው ቢሉ:-
የቅዱስ እስጢፋኖስ ወላጆቹ ስምዖንና ማርያም
ይባላሉ:: (ሌሎች ናቸው የሚሉም አሉ) ገና ከልጅነቱ
ቁም ነገር ወዳድ የነበረው ቅዱስ በሥርዓተ ኦሪት አድጐ
እድሜው ሲደርስ ወደ ት/ቤት ገባ:: የወቅቱ ታላቅ
መምሕር ገማልያል ይባል ነበር:: ይህ ሰው በሐዋርያት
ሥራ ምዕራፍ 5:33 ላይ ተጠቅሷል::
በትውፊት ትምሕርት ደግሞ ይህ ደግ (ትልቅ) ሰው
በርካታ ቅዱሳንን (እስጢፋኖስን: ዻውሎስን: ናትናኤልን:
ኒቆዲሞስን . . .) አስተምሯል:: በጌታችን መዋዕለ
ስብከት ጊዜም ከፈጣሪያችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ
እየቀረበ ይጨዋወት ነበር:: በፍጻሜውም አምኗል::
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱስ እስጢፋኖስ
ከዚህ ምሑር ዘንድ ተምሮ: ኦሪቱን ነቢያቱን ጠንቅቆ
ወጣ:: ወቅቱ አስቸጋሪና ለኃጢአት ሕይወት የተመቸ
ቢሆንም ቅዱሱ ግን የመሲህን መምጣት በጸሎትና
በተስፋ ይጠባበቅ ነበር::
በወቅቱ ደግሞ #መጥምቁ_ቅዱስ_ዮሐንስ የንስሃ
ጥምቀትን እየሰበከ መምጣቱን የተመለከተ ቅዱስ
እስጢፋኖስ ነገሩን መረመረ:: ከእግዚአብሔር ሆኖ
ቢያገኘው የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ሆነ:: ለ6
ወራትም በትጋት ቅዱስ ዮሐንስን አገለገለ::
ለ6 ወራት ከቅዱስ #ዮሐንስ ዘንድ ከተማረ በሁዋላ
ለስም አጠራሩ ስግደት ይድረሰውና ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ተጠመቀ::
በወቅቱ የተደረገውን ታላቅ ተአምር ልብ ያለው ቅዱስ
እስጢፋኖስ መምሕሩን ቅዱስ ዮሐንስን እንዲያስረዳው
ጠየቀው::
"ከእኔ ይልቅ ከፈጣሪው አንደበት ይስማው" በሚል
ላከው:: ቅዱሱም ከጌታ ዘንድ ሔዶ: እጅ ነስቶ ተማረ::
(ሉቃ. 7:18) በዚያውም የጌታ ደቀ መዝሙር ሆኖ ቀረ::
ጌታም ከ72ቱ #አርድእት አንዱ አድርጐት ለአገልግሎት
ላከው:: አጋንንትም ተገዙለት:: (ሉቃ. 10:17)
ቅዱስ እስጢፋኖስ ጌታችን #መድኃኔ_ዓለም ከዋለበት
እየዋለ: ካደረበት እያደረ ወንጌልን ተማረ:: ምሥጢር
አስተረጐመ:: ጌታ በፈቃዱ ስለ እኛ ሙቶ ከተነሳ በሁዋላ
ሲያርግ ደቀ መዛሙርቱን በአንብሮ እድ ባርኩዋል::
በዚህ ጊዜም ቅዱሱ እንደ ወንድሞቹ #ሐዋርያት
ቅስናን (ዽዽስናን) ተሹሟል:: በበዓለ ሃምሳም
#መንፈስ_ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከ72ቱ አርድእት የእርሱን
ያህል ልሳን የበዛለት: ምሥጢርም የተገለጠለት የለም::
በፍጹም ድፍረትም ወንጌልን ይሰብክ ገባ::
በመጀመሪያይቱ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ከማዕድ ሥርዓት
ጋር በተያያዘ ፈተና ሲመጣ በመንፈስ ቅዱስ ምርጫ 7
#ዲያቆናት ሲመረጡ አንዱ እርሱ ነበር:: አልፎም የ6ቱ
ዲያቆናት አለቃ እና የ8ሺው ማሕበር መሪ (አስተዳዳሪ)
ሆኗል::
8ሺ ሰውን ከአጋንንት ፈተና መጠበቅ ምን ያህል ከባድ
እንደ ሆነ ለማወቅ አባቶቻችንን መጠየቅ ነው:: አንድን
ሰው ተቆጣጥሮ ለድኅነት ማብቃት እንኩዋ እጅግ ፈተና
ነው:: መጽሐፍ እንደሚል ግን 'መንፈስ ቅዱስ የሞላበት:
ማሕደረ እግዚአብሔር' ነውና ለእርሱ ተቻለው:: (ሐዋ.
6:5)
አንዳንዶቻችን ቅዱስ እስጢፋኖስ 'ሊቀ ዲያቆናት'
ሲባል እንደ ዘመኑ ይመስለን ይሆናል:: እርሱ
በመጀመሪያ ሐዋርያና ካህን ነው:: ዲቁናው ለእርሱ 'በራት
ላይ ዳረጐት' ነው እንጂ እንዲሁ
ዲያቆን ብቻ አይደለም::
ቅዱስ እስጢፋኖስ ከጌታ ዕርገት በሁዋላ ለ 1 ዓመት
ያህል 8ሺውን ማሕበር እየመራ: ወንጌልን እየሰበከ
ቢጋደል #ኦሪት 'እጠፋ እጠፋ': #ወንጌል ደግሞ 'እሰፋ
እሰፋ' አለች:: በዚህ ጊዜ 'ክርስትናን ለማጥፋት
መፍትሔው ቅዱስ እስጢፋኖስን መግደል ነው' ብለው
አይሁድ በማመናቸው ሊገልድሉት አስበውም አልቀሩ
ገደሉት::
እርሱ ግን ፊቱ እንደ #እግዚአብሔር መልአክ እያበራ
ፈጣሪውን በብዙ ነገር መሰለው:: በመጨረሻውም ስለ
እነሱ ምሕረትን እየለመነ በድንጋይ ወገሩት:: ደቀ
መዛሙርቱም ታላቅ ለቅሶን እያለቀሱ ቀበሩት::
ፍልሠት
ቅዱስ እስጢፋኖስ ካረፈ ከ300 ዓመታት በሁዋላ
በኢየሩሳሌም የሚኖር አንድ ደግ ሰው ነበር:: ስሙም
#ሉክያኖስ ይባል ነበር:: በተደጋጋሚ በራዕይ ቅዱሱ
እየተገለጠ "ሥጋየን አውጣ" ይለው ነበርና ሒዶ
ለዻዻሱ ነገረው:: ዻዻሱም ደስ ብሎት ካህናትና
ምዕመናንን ሰብስቦ ወደ አጸደ # ገማልያል (የመምሕሩ
ርስት ነው) ሔደ::
ቦታውንም በቆፈሩ ጊዜ ታላቅ መነዋወጥ ሆነ::
መላእክት ሲያጥኑ በጐ መዓዛ ሸተተ:: ዝማሬ
መላእክትም ተሰማ:: ሕዝቡና ዻዻሱም በቅዱስ
እስጢፋኖስ ፊት ሰግደው: በታላቅ ዝማሬና በሐሴት
ዐጽሙን ከዚያ አውጥተው: በጽርሐ #ጽዮን
(በተቀደሰችው ቤት) አኖሩት::
#እለ_እስክንድሮስ የተባለ ደግ ሰውም ቤተ ክርስቲያን
አንጾለት ወደዚያ አገቡት:: ከ5 ዓመታት በሁዋላም እለ
እስክንድሮስ ሲያርፍ በሳጥን አድርገው በቅዱሱ ጐን ስለ
ፍቅሩ አኖሩት:: ሚስቱ ወደ ሃገሯ #ቁስጥንጥንያ
ስትመለስ የባሏን ሥጋ መስሏት የቅዱስ እስጢፋኖስን
ቅዱስ ሥጋ በመርከብ ጭና ወሰደችው::
መንገድ ላይ ከሳጥኑ ውስጥ ዝማሬ ሰምታ ብታየው
ያመጣችው የቅዱሱን ሥጋ ነው:: እጅግ ደስ አላት:
አምላክ ለዚህ አድሏታልና:: እርሷም ወስዳ ለታላቁ
ንጉሥ #ቅዱስ_ቆስጠንጢኖስ አስረከበች:: በከተማውም
ታላቅ ሐሴት ተደረገ::
ሥጋውን ሊያኖሩት በበቅሎ ጭነው ሲወስዱትም
በቅሎዋ በሰው ልሳን ተናግራ ማረፊያውን አሳወቀች::
በዚያም ላይ ትልቅ ቤተ ክርስቲያን ታንጾለታል:: ቅዱስ
እስጢፋኖስ ሲመቱ ጥቅምት 17: ዕረፍቱ ጥር 1:
ፍልሠቱ ደግሞ መስከረም 15 ቀን ነው::