አትሮኖስ
286K subscribers
121 photos
3 videos
41 files
576 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
ሰሜን ኢትዮጵያ፤ ወንድ ልጇን ያስገበራት ኢትዮጵያዊት እናት የለችምና የወላድ እርግማንን የደረሰበት ይመስል ቦምብና መትረዬስ እየለበለበው የደጋ በረሃ ሲሆን የተቃረበ ምድር! ያ ሰሜን ኢትዮጵያ፤ ደም እንደ ውሃ እየወረደበት፣ አጥንት
እየተከሰከሰበት፣ የሰው ልጅ አስክሬን በአውር እየተጎተተበት፣ የዋይታና ኡኡታ ጩኸት እያደነቆረው እራሱም ሲያለቅስ የሚኖር ያልታደለ ቦታ! ገና የወደፊት ዕጣ ፋንታው እንኳ በውል ያልታወቀ የሀገር ክፋይ!

ታዲያ በሔዋን አቅም እንዴት ይደፈር? ከቶ በየት አድርጋ፣ እንዴት ብላ የአስቻለውን ዱካ ለማነፍነፍ ትሂድ? ዙሪያው በእሳት የታጠረ ሲኦል፡ ገና ስታስበው ወላፈኑ ይገርፋታል፡፡ ገና ትዝ ሲሳት ነበልባሉ ያቃጥላታል። አስቻለውን በዚህ የመከራ ቦታ ላይ በሀሳብ ስታየው ትጨነቃለች፡፡ ትጠባለች። እንባዋ ብቻሲረግፍ ይኖራል።

ከቀኑ አሥር ሠዓት አለፍ እያለ ነው፡፡ ቡናው ሊያከትም ትንሽ
ሲቀረው ሔዋንም ስትጽፍ የቆየችውን ወረቀት እጥፍ አድርጋ በማስደገፊያዋ ደብተር ውስጥ
ከተተች፡፡ እናቷም ልብ ብለው ተመለከቷትና ብድግ ብለው ወደ ቤት አመሩ፡፡የሔዋን ታናሽ ወንድም የሆነው አስራት ተስፋዬ መደብ ላይ ቁጭ ብሎ ሲያጠና
አገኙትና «አስራቴ!» ሲሉም በሹክሹክታ ዓይነት ጠሩት፡፡
«አቤት!» አላቸው አስራት ቀና ብሎ እየተመለከታቸው። ወደ አሥራ ስድስት ዓመት የሚጠጋው ጠየም ያለ ለግላጋ ወጣት ነው::
«እስቲ ሆዴን አሞኛል' ብለህ መደቡ ላይ ተኛ፡» አሉት
«ለምን?» አላቸው አስራት ደንገጥ እያለ፡፡

«እየው» አሉት ወደ ጆሮው ጠጋ በማለት «እሙዬን ራሴን አሞኛልና
መድሃኒት ግዢልኝ ብዬ ወደ ከተማ ልልካት ነው። እሷ ከሄደች በኋላ የምነግርህ ነገር አለኝ። በል ቶሎ ተኛ፡፡» አሉት እያዋከቡት።....

💫ይቀጥላል💫
👍10
#ሕይወት_ያለው_መንገድ

እዚያ ቦታ ቀኑ መሽቶ እዚህ ቦታ ቀኑ ሳይመሽ
የልብሽን እያወራሽኝ የነፍሴን ደግሞ እያሳየሁሽ
“እስካሁን ድረስ እስካሁን
የት ነበርክ?” ብለሽ እየጠየቅሽ
እስካሁን ድረስ እስካሁን
“አንቺስ የት ነበርሽ?” እያልኩሽ
በእጆችሽ ልታቅፊኝ ስትይ
ከእነ እጆችሽ እያቀፍኩሽ
“ፍቅር እንዲህ ነው?” እያልሽኝ
“ፍቅር አንች ነሽ” እያልኩሽ
“ተበድያለሁ” ስትይኝ
በበደሉሽ እየተቆጣሁ
ከቀረበው መጠጥ በላይ
ውብ ሳቅሽን እየጠጣሁ
የነበርኩበትን ትቼ
ወዳለሽበት እየመጣሁ
ከተደበቅሽበት ሳገኝሽ
አንችም ወጣሽ እኔም ወጣሁ
የበረደው ልብሽን
ለፍቅር ፀሐይ አሰጣሁ
ዘለላ የዕድሜዬን ክር
ስሩን ፈልጌ በጣሁ
እኔንም አንቺንም ሆኜ
ብቸኝነትን ቀጣሁ
ፍቅር በላሽ ፍቅር ጠጣሁ።

🔘ሰለሞን ሳህለ🔘
6👍1
21 እንኳን አደረሳችሁ🙏
👍1
#ምንትዋብ


#ክፍል_አስራ_ዘጠኝ


#ድርሰት_በሕይወት_ተፈራ

....ምንትዋብ፣ ኢያሱ ራቱን እስኪበላና እስኪተኛ ጠብቃ እሷም በድንጋጤና በለቅሶ የደነዘዘ ሰውነቷን ለማሳረፍ ከጎኑ ጋደም አለች። አካሏ ዝሎ፣ መንፈሷ ረግቦ፣ እንቅልፍ በዐይኗ አልዞር አለ። አእምሮዋ በውስጡ ያለተራ ብቅ ጭልጥ የሚለውን የሐሳብ ውዥንብር መቆጣጠር ተሳነው። መላ የጠፋው አእምሮዋ ቢሰክንልኝ ብላ ከመኝታ ክፍሏ ወደ ሰገነቱ ከሚያወጡት ከሶስቱ በሮች በመካከለኛው በኩል አድርጋ ሰገነቱ ላይ ቆመች። ባሏም ብዙ ጊዜ በዛ በር እየወጡ፣ አንዳንዴም አብረው እየሆኑ ከተማውንና ግቢውን ይቃኙ ነበርና እንባ ተናነቃት።

ለሰባት ዓመታት ያህል ከእሳቸው ጋር ያሳለፈችውን ሕይወት
በሐሳቧ መለስ ብላ አየች። ንጉሠ ነገሥቱ እንደ ተራ ሰው እናት አባቷ
ቤት መደብ ላይ ተኝተው ያስታመመቻቸውን አስታወሰች። ምንትዋብ ብለው ስም ያወጡላት፣ “የኔ ዓለም” እያሉ ያቆላመጧት ሁሉ በየተራ ፊቷ ድቅን አሉባት። ምነው እንዲህ ዕድሜያቸውን አሳጠረባቸው?
አለችና ምርር ብላ አለቀሰች።

ከቤተመንግሥት ግቢ አሻግራ ጥቅጥቅ ባለው ጭለማ ውስጥ ጐንደርን ለማየት ሞከረች። ማታ ማታ ጐንደርን ያለ ከልካይ ከሚፈትሹት ጅቦች ሌላ የሚንቀሳቀስ ነገር የለም። አልፎ አልፎ ጅቦቹን ከሚያስፈራሩት
ውሾች ጩኸት በስተቀር ድምፅም አይሰማም።
ምንትዋብ ከጐንደር ወደ ራሷ ተመለሰች። ሕይወት ያልታሰበ
ፀጋ አምጥታላት መልሳ መንጠቋ ገረማት። የሕይወት መንገዶች
አለመጣጣማቸው ደነቃት። ሞት ሌላው የሕይወት ገፅታ መሆኑን
አሰበች። ሕይወት ምስጢሯን ያካፈለቻት መስሎ ተሰማት። ነገ እዛ ራሷ ረጋፊ መሆኗ በአእምሮዋ ተመላለሰና ዘገነናት። ለጊዜውም ቢሆን የመኖር ትርጉሙ ተናጋባት። የሙት ሚስት መሆኗ ወለል ብሎ
ታያት። ሞት ተስፋዋን ሁሉ ሸራረፈባት።

በዚያች ቅጽበት ሕይወቷ ዳግመኛ እንደተለወጠ ተረዳች።

መኝታ ክፍላቸው ስትገባ እንደገና እንባ አሸነፋት። ቤቱ የሚበላት፣
አልጋው ብቻዋን በመምጣቷ የሚታዘባት መሰላት። ለባሏ እንደሚገባቸው ያላዘነች፣ ያላነባች መስሎ ተሰማት። ቆም ብላ ክፍሉን ቃኘች። በርካታ
ትዝታዎች በአእምሮዋ ውስጥ ተመላለሱ። ወደ ኢያሱ ስትመለከት ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ላይ ነው። ሆዷ ባባ። አባቱን ሲሰናበታቸው ምን ተሰምቶት እንደሆነ መገመት አቃታት። እመንናለሁ ብላ የእሱን ሕይወት አደጋ ልትጥል እንደነበር አስታወሰችና ስቅስቅ ብላ አለቀሰች። ተጠግታው ራሱን እያሻሸች፣ በዚች ምድር ላይ ካሉ ክፉ ነገሮች ሁሉ፣ከሞት ጭምር፣ ልትደብቀው እቅፏ ውስጥ ሽጉጥ አድርጋው ጋደም
አለች።

አእምሮዋ እረፍት አጥቶ እንቅልፍ በዐይኗ ሳይዞር ወፍ ተንጫጫ።
ተነስታ ወደ ሰገነቱ ወጣች። ሰማይና ምድር ገና አልተላቀቁም።
ጐንደርም ገና እንቅልፍ ላይ ናት። በቦዘዙ ዐይኖቿ ዙርያውን አየች።
የጠዋቱ ቅዝቃዜ ፊቷን ሲዳስሳት፣ ነቃ አለች።

አሻግራ ጐንደርን ወደከበቧት ተራሮች ተመለከተች። ፍም እሳት
የከበባት የምትመስለውን ፀሐይ ብቅ ስትል ስታይ የጥድፊያ ስሜት
ተሰማት። በመመርያ ኸዋና ዋናዎቹ ግቢ አዛዥና ኸሊጋባው፣
እንዲሁም ኸመሣፍንቱና ኸመኳንንቱ ጋር መክራለሁ። ጃንሆይ አገር አለ ምክር፣ ቤት አለ ማገር ይሉ ማልነበር? ኸዛ በኋላ፣ ኢያሱ በምሥጢር ይነግሣል። የልጄቼን አልጋማ ለማንም አሳልፌ አልሰጥም

ለካንስ እሷም መንገሷ ነው! ደነገጠች።

ይህ ሳይታሰብ እላይዋ ላይ የወደቀው ኃላፊነት ከየት እንደመጣ ማወቅ አቃታት። ሃገር ልታስተዳድር መሆኑ ሲገባት ታላቅ የኃላፊነት ስሜት ተጫጫናት፡፡ እሳቸው ያሰቡትን ሁሉ ሳያሳኩ አለፉ፤ እኔስ ብሆን መቸ እንደምሞት በምን አውቃለሁ? ሞት እንደሁ ለማንም አይመለስ፡ ብቻ እንዳው አንዴ የሳቸውን ቀብርና የልጄን ንግሥ
ያለምንም ሳንካ ላሳካ እያለች አእምሮዋ ውስጥ የሚወራጨውን ሐሳብ ሁሉ በየፈርጁ ማስቀመጥ ሞከረች።

ድንገት ክፉኛ የመንገሥ ፍላጎት አደረባት። ባሏ፣ “እሷ አገር
ማስተዳደር ትችላለች” ያሉት በከንቱ እንዳልሆነ፣
ስለቤተመንግሥትም ጉዳይ ቢሆን ላለፉት ሰባት ዓመታት በቂ
እውቀት እንዳካበተች፣ በደጉ ጊዜ ቤተመንግሥት ውስጥ ቦታቸውን
ያመቻቸችላቸው የኒቆላዎስ፣ የወልደልዑል፣ የአርከሌድስና
የሌሎቹም መኖር ታላቅ ድጋፍ እንደሚሆናት ተረዳች። ኒቆላዎስ
እያረጀ በመምጣቱ፣ ወንድሟ ወልደልዑል ጉልህ ችሎታ በማሳየቱና ቤተመንግሥት ውስጥ የማይናቅ አስተዋጽኦም በማድረጉ ቀኝ እጇ ሊሆን እንደሚችል አመነች። ዐዲስ ማንነት ውስጧ ሲጠነሰስ ተሰማት።

ከፍተኛውን የሥልጣን ዕርከን ስትወጣ ታያት።

ልቧ መታ፤ መላ ሰውነቷ ተቅበጠበጠ። ዳግም የጥድፊያ ስሜት ተሰማት። ይህንን ዕድል ለማንም አሳልፋ ልትሰጥ እንደማትችልና የኢያሱን ሆነ የራሷን ንግሥ ለማስከበር በችሎታዋና ሥልጣንዋ ስር ያለውን ሁሉ ማድረግ እንዳለባት ለራሷ አስገነዘበች። አሁን ፊቷ ተደቅኖ
የሚታያት ምኞት ወይንም ተስፋ ሳይሆን በቅርብ ያለ፣ሊጨበጥ የሚችል በመሆኑና ከለቀቀችው፣ ካመነታች እዳው ለእሷ ብቻ ሳይሆን ለልጇ ጭምር በመሆኑ በአስቸኳይ እርምጃ መውሰድ
እንዳለባት ተረዳች።

እኔም ኢያሱም ኸነገሥን በኋላ፣ ኣመጥ እንዳይኖር ጥርጣሬ
አስወግጀ ሰዉ እኔ ላይ አመኔታ እንዲኖረው ማረግ አለብኝ። መቸም መልካም ሥራ ኸሠራሁና ጥሩ አርጌ ኻስተዳደርሁ ሰዉ ይደግፈኛል::እምነትም ይጥልብኛል አለች፣ ሞላ ባለ ልብ። ከሁን ታሪክ የምትሠራበት፣ ስሟን ካለፉት ነገሥታት ተርታ የምታሰልፍበት ወቅት
እንደተቃረበ አስተዋለች። ሃገሯ ታላቅ ጥንካሬ፣ ዘዴ፣ ቆራጥነትና
ቀናነት እንደምትጠብቅባት ተረዳች።

ከሐሳቧ ስትነቃ ምድር ለቋል፤ ጐንደር ብርሃን ለብሳለች፤ ነፍስ
ዘርታለች። ። ጐንደርን ለመጀመሪያ ጊዜ በተለየ ዐይን አየቻት። ጐንደር
ጐንደር! አለች፣ በለሆሳስ፡ ፊቷን እያዟዟረች ከተማዋን የከበቡትን
ሰንሰለታማ ተራራዎች ትክ ብላ አየቻቸው። በተፈጥሮዋ የጠላት
መከላከያ አላት አለች። እንደገና ከተማዋን ከላይ ወደታች ቃኘች።
ጐንደር... ያቺ የነገሥታቱ፣ የመሣፍንቱና የመኳንንቱ የትንቅንቅ ቦታ ሳትሆን የተለየች ጐንደር ሆና፣ እንባዋን ጠራርጋ ወጣ ገባ ስትል ታየቻት። የዕድል ማሳ ሆና እሷ ማሳው ላይ ስትዘራ ጐንደር ስታብብ፣ስታፈራ፣ ይበልጥ ገናና ስትሆን ታያት።

በራሷ አምሳል የቀረጸቻት ጐንደር ፊቷ ወለል አለች።

ጐንደርን በጃን ተከል በኩል ለማየት ወደ ላይኛው ሰገነት በደረጃ ወጣች። የሁሉ መኖሪያ፣ ሁሉን እንደ ሃይማኖቱ፣ እንደ ሙያውና እንደ ልማዱ የምታስተናግደውንና፣ መንፈሰ ለጋሷን ጐንደርን እንደ
ዐዲስ ወደደቻት፤ ከክፉ ልትታደጋት ፈቀደች። ምን ዓይነት ቦታ እንደሆነችና ሕዝቧም ምን ዓይነት እንደሆነ ይበልጥ ማወቅ ፈለገች።

ልክ በዛን ሰዐት የእሷም የጐንደርም ዕጣ የተለየ አቅጣጫ ያዘ።

እንዴ! አገሬ? አገሬስ? ጐንደር አላገር ትኖራለች እንዴ? አለች
ደረቷን እየመታች። አገሬ ውስጥ ሰላም አምጥቸ እኼ ነው ምኞቴ
አለች፣ ባሏ የነበረባቸውን ዓመጽ አስባ። ሃገሯን ልትታደጋት፣
ልታረጋጋት፣ ሰላም ልታሰፍንባት ወሰነች።

የደብረብርሃን ሥላሤ ደወል ሲደወል ከሐሳቧ ነቃች፣ ተረበሸች።

ደወሉ ለአባታቸው ለአፄ አድያም ሰገድ ኢያሱ ከሆላንድ ንጉሥ
የተላከ ነበርና ንጉሠ ነገሥቱ ደወሉን ሲሰሙ ከእንቅልፋቸው ብንን ብለው ሲያማትቡ፣ ተነሥተው ዳዊታቸውንና ውዳሴ ማርያማቸውን ሲደግሙ ፊቷ ላይ ድቅን አለ። አየ ያ ሁሉ ቀረ አለችና እንባዋን ጠራረገች።
👍132
ዐይኗን የጋረደውን እንባ በእጇ ስታብስ ሰዎች የረቡዕ ተግባራቸውን ለማከናወን ይርመሰመሳሉ። መንገደኞች ወደየሚሄዱበት በበቅሎ
ይሰግራሉ፣ በፈረስ ይጋልባሉ። ከየአድባራቱ የቅዳሴ ድምፅ ይሰማል። ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ፣ ተማሪው፣ ወንዶችና ሴቶች ወደየደብራቸው ለቅዳሴ ይጣደፋሉ። አንዳንዶቹ በቀጭን አሸዋ በር አድርገው በቀኝ
በኩል ወደእምትታያት ግምጃ ቤት ማርያም ይገሰግሳሉ። ቆም ብለው
ሰላምታ ይሰጣጣሉ፤ ሰዎቻቸውና ከብቶቻቸው ደሕና እንዳደሩ
ይጠያየቃሉ።

ወደ ጎን ስታይ ልጃገረዶች ጀርባቸው ላይ ገንቦ አስረው እየተጨዋወቱ ወደ ቀሀ ወንዝ ይወርዳሉ፤ ገበሬዎች ወደ እርሻቸው ከብቶቻቸውንና
ሞፈር ቀንበራቸውን ይዘው እየተጫወቱ ያዘግማሉ። በቀልጣፋ እንቅስቃሴያቸው የሚታወቁት፣ ለንጉሠ ነገሥቱ ታማኝ የሆኑትና የከተማዋን ጸጥታ የሚያስከብሩት ወታደሮች ይዘዋወራሉ።

ወደ ግቢው ስትመለከት ሰው ውልብ ሲል ያየች መሰላትና ቁልቁል ተመለከተች። ማንም የለ። ለመጀመሪያ ጊዜ ጐንደር ስትመጣ የቆመችበትን ቦታ አየችው። የዛን ዕለት ከታች ወደ ላይ ሰገነቱን ስታይ ለከፍታው የማትመጥን ሆና የተሰማትን ስሜት አስታወሰች። እዛው
ሽቅብ ያየችው ሰገነት ላይ ቆማ ሁሉን ቁልቁል ማየቷ አስደነቃት። ዛሬ ምንም የማታውቀው የአስራ ስድስት ዓመቷ ኮረዳ ሳትሆን፣ ሀያዎቹን ልታጋምስ የተቃረበችው እጩ ንግሥት ናት።

ሰባት ዓመት ከሆነው በላይ ረጅም መሰላት።ፊቷን መለስ ስታደርግ ከየቤቱ ጣርያ የሚወጣውን ጭስ አይታዐአረቄ ቤቶቹ መሆናቸውን አወቀች። መቸም የጐንደርን ባላባትና ወታደር ይዘውታል። ማታ ማታ ቤታቸው አሸሼ ገዳሜ ነው አሉ ብላ ፈገግ አለች።

ፊቷን ስትመልስ ሴቶች ገሚሱን ዕቃ ጀርባቸው ላይ አዝለው
ቀሪውን ጭንቅላታቸው ላይ ቆልለው ወደ ገበያ ይጣደፋሉ። እነዝኸ አጣሪዎች ናቸው። እነዝኸ ቸርቻሪዎች እንዴት ያሉ ብርቱዎች ናቸው።ኸስናር... ኸሌላም ኸሌላም ሲራራ ነጋዴ ሚያመጣውን ሸቀጥ እገባያው
ያጣራሉ። አንድም ጐንደርን ነፍስ ሚዘሩባትና ሚያንቀሳቅሷት እነሱኮ ናቸው። ይገርማል! ሰዉ ሚፈልገውን ያቃሉና ያቀርባሉ አለች።

እኔም እኮ ኸንግዲህ ሚጠበቅብኝ እኼ ነው…. ሰዉ ሚፈልገውን ማቅረብ መስጠት። በመዠመሪያ ሰዉ ሰላምንና መረጋጋትን ይፈልጋል። ስለዝኽ እሱን መስጠት አለብኝ፡፡ ቁስቋም ትርዳኝ እስቲ፡ ጠንክሬ ሠራለሁ ብላ በረጅሙ ተነፈሰች። ለመሆኑ እችን ጐንደርን እንዴት አርጌ ኑሯል ጥዬ ለመኸድ፣ ጭራሹንም ልመንን አስቤ የነበረው? አገሬንስ ለማን ጥየ ነበር ገዳም ልገባ ያሰብሁት? አልኸድም፣ አገሬን እታደጋታለሁ አለች።

ምን ያህል እዚያ እንደቆመች አላወቀችም። ፀሐይዋን ስታያት ሞቅ ብላለች። እስቲ ለዝኸ ከባድ ቀን ልዘገጃጅ ብላ ወደታች ወረደች።....

ይቀጥላል
👍9🔥1
#ኢ_ስብራት

ለተሰበረ እግር ድጋፍ ቢፈጠርም
ምርኩዝን ተማምኖ እግር አይሰበርም

🔘ልዑል ሀይሌ🔘
👍53
#የቀን_አጠፋፍ

ቀና በል ቀን አለ

ሲሉኝ ቀና ብዬ ቀኔን መች አገኘሁ

ቀን እስኪያልፍ አቀርቅር

ሲሉኝ ሳቀረቅር ቀን አልፎኝ ተገኘሁ

🔘ልዑል ሀይሌ🔘
7👍4
#ፍቅር_ከራስ_ያልፋል

በሕይወት ጎዳና ዕጣ ሲደለደል
ላንዱ ሜዳ ሆኖ ለሌላኛው ገደል
ግማሽ ግራ ገብቶት የቀረው ሲበደል
እኔ ዝምተኛው ካንቺ ሆንኩኝ አይደል?
ምርቃቱ ደርሶ ፍቅር ያጠመቀኝ
በየትኛው ዘመን ማነው የመረቀኝ?
በሚሆነው ሁሉ
ግራ ለተጋባው ለዚህ #ላገሬም_ሰው
ከማይሆነው መንገድ ይዞ እንዲመልሰው
መርቆ ሰምሮለት ፍቅር እንዲዳብሰው
ባወኩት ባወኩት ባወኩት ያንን ሰው።

🔘ሰለሞን ሀይሌ🔘
👍13
#ምንትዋብ


#ክፍል_ሀያ


#ድርሰት_በሕይወት_ተፈራ

.....ጐንደርን እንዴት አርጌ ኑሯል ጥዬ ለመኸድ፣ ጭራሹንም ልመንን አስቤ የነበረው? አገሬንስ ለማን ጥየ ነበር ገዳም ልገባ ያሰብሁት? አልኸድም፣ አገሬን እታደጋታለሁ አለች።

ምን ያህል እዚያ እንደቆመች አላወቀችም። ፀሐይዋን ስታያት ሞቅ ብላለች። እስቲ ለዝኸ ከባድ ቀን ልዘገጃጅ ብላ ወደታች ወረደች።

ተዘጋጅታ ስትጨርስ፣ ቤተሰቧን አስከትላ ወደ አሸዋ ግንብ ሄደች።
የተጠሩት መሣፍንት፣ መኳንንት፣ አቡኑ፣ ዕጨጌውና ዐቃቤ ሰዐቱ
ሲገቡ የተጠሩበትን ምክንያት መገመት አልቻሉም። እሷ ምንም
እንዳልተፈጠረ ተረጋግታ ተቀምጣለች። እነሱ ንጉሠ ነገሥቱ ከአሁን አሁን ይመጣሉ በማለት በር በሩን ይመለከታሉ። በመጨረሻም ግራዝማች ኒቆላዎስ ከተቀመጠበት ተነሥቶ በመሃከላቸው ሲቆም ፀጥታ ሰፈነ። የሁሉ ዐይን ወደ እሱ ሆነ። ቀደም ብሎ ምንትዋብ
የነገረችውን መልዕክት አስተላለፈ።

ክቡራን ሆይ! ለእናንተ ሚደርስ መልክት ኸጃንሆይ ይዠ እናንተ
ዘንድ ቀርቤአለሁ። ልዤን ኢያሱን አንግሡልኝ፤ ይቀመጥ በወንበሬ፣
ይናገር በከንፈሬ፣ ይፍረድ - ይዳኝ ላገሬ። እኔ መንኩሻለሁ፤ ገዳም
ኸጃለሁ። አልመለስም። ሁሉንም ነገር እንደሚገባ አርጉ” ብለዋል
አላቸው።

ያልታሰበ ዜና በመሆኑ ሁሉም ተደናገጡ። ንጉሠ ነገሥቱ የሞቱ
የመሰላቸውም አልጠፉ። ያንን የሚያመላክት ነገር ግን ባለማየታቸው ግራ ተጋቡ። በእውነትም መንኩሰው ይሆናል ብለው ያመኑት የንጉሠ ነገሥቱን ጥልቅ ሃይማኖተኝነት ስለሚያውቁ ለማመን ብዙም አልተቸገሩ። አባታቸው ታላቁ ኢያሱ እንደዚሁ በመጨረሻ ዘመነ ንግሥናቸው፣ “እስተ መቸ ድረስ በሥጋዊ ባሕር ጠልቄ፣ ተጨንቄ ኖራለሁ” ብለው ጣና ገዳም ገብተው ስለነበር፣ ልጅየውም የአባታቸውን
ፈለግ መከተላቸው እምብዛም የሚያጠራጥር አልሆነባቸውም።

ባንድ ቃል፣ “ይበጅ! ይበጅ! ግድ የለም፤ እኼ ፈቃደ እዝጊሃር ነው”
ብለው ተበተኑ።

ምንትዋብ ብላቴን ጌታ ዳዊትና ሻለቃ ወረኛን ከሙስሊም
ነፍጠኞችና ከፎገራ የዘዌና የቱለማ መሪዎች ጋር በመሆን በፍጥነት ሄደው ወህኒ አምባን በጥብቅ እንዲጠብቁ ትዕዛዝ ሰጠች፤ መሣሪያም
እንዲሰጣቸው አዘዘች።

ለኒቆላዎስ፣ “ከካህናቱም ኢያሱን ቀብተው እንዲያነግሡ ሊቁን
ጽራግ ማሰሬ ማሞን፣ ቄስ እልፍዮስንና ሁለቱን ጸሐፍተ ትዕዛዝ...” እያለች የንግሥ ሥርዐት የሚፈጽሙትንና ሌሎች መገኘት አለባቸው ብላ ያሰበቻቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር ሰጠችው። ግራዝማች ኒቆላዎስ መልዕክቱን እጅ ነስቶ ተቀበለ።
ሐሙስ ሌሊት ግራዝማች ኒቆላዎስ፣ አፈ ንጉሥ ኢዮብና አዛዥ ባለሟሎች ዐይን ለመሸሸግ ሻሸና በተባለው የስርቆሽ መንገድ የንግሥ አርከሌድስ ምንትዋብን፣ ኢያሱን፣ ዮልያናንና እንኰዬን ከቤተመንግሥት ሥርዐት ወደሚፈፀምበት ወደ መናገሻ ግንብ ወሰዷቸው። መናገሻ ውስጥ በአፄ በካፋ ጽራግ ማሰሬነት ማዕረግ የተሾሙትንና ቤተመንግሥት ተቀማጭ የሆኑትን ንጉሥ አንጋሹ መነኩሴ ማሞ፣ ቡራኬ ሰጪው
ቄስ እልፍዮስ፣ የመናገሻ ግንብ አጋፋሪዎች አቡሊዲስ፣ ገላውዲዎስ፣ አደሩና ሌሎችም ባሉበት ምንትዋብ ዙፋን ላይ ስትቀመጥ ኢያሱ እግሯ ሥር ተቀመጠ። ኢያሱ ነገሩ እምብዛም ባይገባውም አባቱ እንደሞቱና ሊነግሥ መሆኑ ስለተነገረው የንግሥናው ደስታ ሳይሆን
የአባቱ ሞት ሐዘን ፊቱ ላይ ይታያል።

የንግሥ ሥርዐቱን ለመጀመር በጅሮንድ አብርሃም ዘውዱን ለጽራግ ማሰሬ ማሞ አቀረቡ። ጽራግ ማሰሬ ማሞም ዘውዱን አፄ በካፋ ዙፋን ላይ አስቀመጡ። ንጉሥ ሲነግሥ የሚጸለየውን ጸሎት ጸለዩ።ከመዝሙረ ዳዊት፣ ከብሉያትና ከሐዲስ ኪዳንም የተመረጡ ምንባቦችን አነበቡ። አቡነ ዘበሰማያትም ደገሙ። ኢያሱን ወደ እሳቸው አምጥተው
እጃቸውን አናቱ ላይ አስቀምጠው በአንብሮተ እድ ባረኩት፣ ጸለዩለት፡-

“አቤቱ ፍርድህን ለንጉሡ ስጠው
እውነትኸንም ለንጉሡ ልጅ
ሕዝብኸን በእውነት ይፈርድላቸው ዘንድ
ድኾችኸንም በፍትሕ ይገዛ ዘንድ
አድባር አውጋሩ የሕዝብኸን ሰላም ይቀበሉ።
ከዚያም መከሩት፣
ኰንን በጽድቅ ነዳያነ ሕዝበከ
ወአድኅኖሙ ለደቂቀ ምስኪናኒከ
ወአሕስሮ ለዕቡይ
ተስፋም ሰጡት፡-
በዘመኑ እውነት ይሠርጻል
ከባሕር እስከ ባሕርም ይገዛል
ከወንዞችም እስከ ዓለም ጥጋጥግ
ኢትዮጵያ ይገዙለታል
ጠላቶቹ ግን አፈር ይበላሉ።”

ከዚህና ከበርካታ ሌሎች ጸሎቶች በኋላ፣ በዕንቁ ያጌጠውን የአባቱን
ዘውድ ራሱ ላይ ደፉለት፣ በአባቱ ዙፋንም ላይ አስቀመጡት። ከዚያም የጫነው ዘውድ ለጌጥ የተሠራ ሳይሆን የሕዝቡን ችግርና መከራ የሚሸከምላቸው መሆኑን የሚዘክር፣ ንጉሣቸውና አገልጋያቸው መሆኑን
የሚያሳስብ እንደሆነ ተናግረው መረቁት፡ አስመረቁት፡-

“ሺሕ ዓመት ንገሥ

ወንድ ልጅ ለፈረስ፣ ሴት ልጅ ለበርኖስ አድርስ።”
አሉት፤ በዚያው የተሰበሰው ሕዝብም ይህንን ሦስት ጊዜ መላልሰው በአንድ ድምጽ አስተጋቡ።

“ዳዊት ቤት ቀርነ መድኃኒት የሆነ ንጉሥ ስላነሳልን እግዚአብሔር
ይመስገን፤” አሉ፣ ጽራግ ማሰሬ ማሞ።

ኢያሱ ዳግማዊ ኢያሱ ንጉሠ ነገሥት ተብሎ ነገሠ።

ጽራግ ማሰሬ ማሞ ዙፋኑ ስር ተንበርክከው ሰገዱለት። በዓሉ ላይ ተገኝቶ የነበረው ሁሉ ተነስቶ ለሰባት ዓመቱ ልጅ ለኢያሱ ሰገደ።

በተራው ንጉሥ ባራኪው እልፍዮስ ወደ ኢያሱ ተጠግተው የብዙ
ታላላቅ ነገሥታት ነብያትና ታላላቅ ነገስታት በረከት እንዲያድርበት መረቁት።
“የቅዱስ ዳዊት በረከት ይደርብህ። የጠቢቡ ሰለሞን ፍትሕና ጥበብ አይለይህ። የኢዮሲያስ፣ የሕዝቅያስና የቆስጠንጢኖስ በረከት ይደርብህ”እያሉ ባረኩት። በመጨረሻም ለኢያሱ ዳግመኛ ሰግደው ወደነበሩበት ተመለሱ። ዘውዱ ለትንሹ ኢያሱ ከባድ በመሆኑ ጽራግ ማሰሬ ማሞ
ከራሱ ላይ አንስተውለት በክብር ጠረጴዛው ላይ አኖሩት::

ምንትዋብ ከተቀመጠችበት ተነስታ እጆቿን ዘርግታ፣ “እኔን
ታናሺቱን ለዝኸ ክብር ላበቃኝ እዝጊሃር ምስጋና ይግባው። ፈጣሪዬ ሆይ ለኔ ለባርያህ በንጉሡ በአባቱ በአጤ በካፋ ዙፋን ላይ መቀመጥ ዘር
ስለሰጠኸኝ ክብር ምስጋና ይግባህ” ብላ ምስጋና አቀረበች። በኋላም ኢያሱን ላነገሠው ለጽራግ ማሰሬ ማሞ፣ ለአንጋሽ እንደሚደረገው አስር ሰቅለ ወርቅ እንዲሰጥ ትዕዛዝ አስተላለፈች።

ትውፊቱን ጥሳ፣ የልጇ ንግሥ ላይ ባሏን ያነገሡት አቡነ ክርስቶዶሌ
ተገኝተው ዘውድ እንዲጭኑለት እንኳን ሳታደርግ፣ መፈጸም ያለባቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች ብቻ ፈጽማ የኢያሱ የንግሥ ሥርዐት በምሥጢር ያለአንዳች ኮሽታ ተጠናቀቀ።

ወዲያው ባሻ ኤልያስን አስጠርታ፣ ሲነጋ የንጉሠ ነገሥቱ ሕልፈትና
የኢያሱ መንገሥ እንዲታወጅና ለንጉሥ ቀብር የሚደረገውን ሥርዐት ሁሉ እንዲያደርግ አዘዘችው። እጅ ነስቶ ሄደ።
ጠዋት ላይ፣ በታዘዙት መሠረት እነባሻ ኤልያስ ድብ አንበሳ ይዘው
ወደ ጃን ተከል ወረዱ። ሊጋባው፣ ከአዛዡ በተቀበለው ትዕዛዝ መሠረት ነጋሪት እየጎሰመ፣ “አዋጅ! አዋጅ! አዋጅ! የሞትንም እኛ፣ ያለንም እኛ ንጉሥ በካፋ ዐርፈዋል። ልጃቸው ኢያሱ ነግሠዋል፣ የሰማ ላልሰማ
ያሰማ። ጠላቶቻችን ይፈሩ፤ ወዳጆቻችን ትፍሥሕት ያድርጉ፣ ባለህበት እርጋ፤ ነጋዴም ነግድ፤ ገበሬም እረስ!” እያለ አዋጅ ነገረ።

ጐንደሬዎች ግልብጥ ብለው ወጡ። “ይበጅ! ይበጅ! ያድርግ!”
አሉ። በኢያሱ መንገሥ ተደሰቱ፤ እምብዛም ባይወዷቸውም ለበካፋም አለቀሱ።
👍131
አባ ዐደራ የንጉሠ ነገሥቱን አስከሬን የክብር ልብሳቸውን አልብሰው፣ ሽቱ ቀብተው ገነዟቸው። በምንትዋብ ጥያቄ አቡነ ክርስቶዶሉ፣ ዕጨጌ
ተክለሃይማኖት፣ ዐቃቤ ሰዐት ወልደ ሃይማኖትና ሌሎችም ካህናት ወጉ በሚፈቅደው መሠረት የወርቅ አክሊላትና መስቀላት ይዘው፣ የአፄ በካፋ አስከሬን በስርቆሽ በር ወደ አደባባይ ተክለሃይማኖት ተወስዶ
ጸሎተ ፍታት ከተደረገላቸው በኋላ፣ ተቀበሩ። ከቀብር በኋላ፣ ለቀስተኞቹ መኻል ግንብ ሄደው ምንትዋብንና ኢያሱን እጅ እየነሱ ተሰናበቱ።

ከቀብር ሥርዐቱ በኋላ፣ ባህሉ እንደሚጠይቀው ምንትዋብ የቅጥር ለቅሶ ውሎ አሳወጀች። በጥቂት ቀናት ውስጥ የንጉሠ ነገሥቱን ምስል አሠርታ፣ ሰጋር በቅሎዋን ጨበሪትን
በንጉሣዊ አልባሳት አስጊጣ
የንጉሠ ነገሥቱ አልባሳትና ሌሎችም ንብረቶች ተጭነውባት ለሕዝብ እይታ ወጣች።

ሰንደቅ ተይዞ፣ መለከት እየተነፋ፣ ነጋሪት እየተጎሰመ ባለነፍጡ፣
ባለሠይፉ፣ ካህናቱ፣ ዲያቆናቱ፣ መነኮሳቱ፣ መሣፍንቱ፣ መኳንንቱ፣
የጦር አበጋዞቹ፣ ሊቃውንቱና ወይዛዝርቱ የክብር ልብሳቸውን ለብሰው እንደየማዕረጋቸው ተሰልፈው ወጡ።

ተራው ጐንደሬ፣ አልቃሹ፣ ሀሚናውና ከጐንደር ዙርያ የመጣውም ከኋላ እየተከተለ ለቅሶውን አደመቀ። ኢያሱ ፋሲለደስ ግንብ ላይ ቆሞ
ትዕይንቱን ሲመለከት ሕዝቡ እሱን እያየ በዛ ለጋ ዕድሜው አባቱን
ላጣው ልጅ ዋይታ አበዛለት።

ምንትዋብ፣ ወንድሟ ወልደልዑል፣ የአጎቷ ልጆች፣ ዮልያና፣ እንኰዬ፣
ግራዝማች ኒቆላዎስና ሌሎችም የቅርብ ዘመዶች ከጥቁር ማቅ የተሠራ ሠቅ ለብሰው ሲላቀሱ፣ ዋይ ዋይ ሲሉና ሙሾ ሲያወርዱ ዋሉ።

ዋይታ የተመለከተው ለቀስተኛ፣
ስለጉዳቷ አብዝቶ አነባ። በውበቷና በድምፅዋ ማማር ተደንቀው
በለቅሶና በጩኸት ዐጀቧት። በግጥሞቿ ብስለትና በቅኔ አዋቂነቷም የምንትዋብን እንጉርጉሮና አደነቋት።

ምነው ምን በደልነ ዝናብ እኮ ቀረ፣

ሁሉን ሚያስደስት ባካፋ ነበረ።

ዝናቡ ቀረ እንጂ ዝናቡ ባካፋ፣

ለሕዝቡ ለእንስሳው ይሆን ነበር ተስፋ፣

እያለች አልቅሳ ሕዝቡን በእንባ አራጨችው።

እንባ ከረጩት መሃል አንዱ ጥላዬ ነበር። የአለቃ ሔኖክን ማረፍ
ሲሰማ፣ ወርቄጋ ለቅሶ ሊደርስ ከደብረ ወርቅ በመጣ በሁለተኛው ቀን በካፋ መሞታቸውን ሲሰማ ከወርቄ፣ ከወላጆቿና ከአብርሃ ጋር አደባባይ ወጣ፡፡

የሕዝቡን ግፊያ አሸንፎ ከፊት ሲቆም፣ ምንትዋብን አያት።
ለወትሮዋ ፊቷን የምትከልልበት ዐይነርግብ ባለመኖሩ ፊቷ ወለል
ብሎ ይታያል። ያቺ ከሰባት ዓመታት በፊት የሚያውቃት ለጋ ወጣት ሳትሆን፣ በውበትና በሰውነት አቋም የበለጠ የደረጀች ሴት ሆና አገኛት።በለቅሶ ጎንበስ ቀና ስትል፣ ግጥም ስትደረድር፣ እንባዋ እንደ ጎርፍ ሲወርድ፣ አይቶ እንባውን መቆጣጠር አቃተው፤ አንጀቱ ተላወሰ፤ ሐዘኗ አጥንቱ ድረስ ዘልቆ ገባ። አየ ወለቴ ጠጋ ብየ ባጥናናሁሽ፡፡ እኔ አልረሳሁሽም። የሩቅ ቅርብ ሁኜ ስላንቺ አስባለሁ። ምንግዝየም ኸልቤ አትጠፊም አለ።......

ይቀጥላል
👍121
አትሮኖስ pinned «#ምንትዋብ ፡ ፡ #ክፍል_ሀያ ፡ ፡ #ድርሰት_በሕይወት_ተፈራ .....ጐንደርን እንዴት አርጌ ኑሯል ጥዬ ለመኸድ፣ ጭራሹንም ልመንን አስቤ የነበረው? አገሬንስ ለማን ጥየ ነበር ገዳም ልገባ ያሰብሁት? አልኸድም፣ አገሬን እታደጋታለሁ አለች። ምን ያህል እዚያ እንደቆመች አላወቀችም። ፀሐይዋን ስታያት ሞቅ ብላለች። እስቲ ለዝኸ ከባድ ቀን ልዘገጃጅ ብላ ወደታች ወረደች። ተዘጋጅታ ስትጨርስ፣ ቤተሰቧን…»
#ያልታበሱ_እንባዎች


#ክፍል_ሰላሳ_ስድስት


#ድርሰት_በአሰፋ_በቀለ_ገየሱስ

...«እየው» አሉት ወደ ጆሮው ጠጋ በማለት «እሙዬን ራሴን አሞኛልና
መድሃኒት ግዢልኝ ብዬ ወደ ከተማ ልልካት ነው። እሷ ከሄደች በኋላ የምነግርህ ነገር አለኝ። በል ቶሎ ተኛ፡፡» አሉት እያዋከቡት።

“ምንድነው እሱ?» አላቸው አስራት ዓይኑን ዓይናቸው ላይ ትክል አደርጎ።
«ብኋላ እነግርህ የለ! አሁን ተኛ፣» አሉትና ወደ ጓዳ ገባ ብለው ጋቢ
አምጥተወ ሰጡት፡፡ በል ቶሎ በል!ካሉ በኋላ አሁንም ወደ ጆሮው ጠጋ ብለው «እሙዬ ምን ሆንክ ታለችህ ድንገት ቁርጠት ተነሳብኝ ብለህ ቅልስልስ እያልክ ንገራት።
አሉት ጣደፍ ጣደፍ እያሉ።
አስራት ግራ እየገባው ጋቢውን ለብሶ ቁጭ ብሎበት በነበረ መደብ ላይ ጥቅልል ብሎ ተኛ፡፡ በጆሮው ግን የእናቱን እንቅስቃሴ በጥንቃቄ ያዳምጣል፡፡
የሔዋን እናት የአስራትን አተኛኘት ካረጋገጡ በኋሳ ወደ ጓሮ ዞሩ። ልክ እንደ ታመሙ" ሁሉ ሰውነታቸውን ድክምም፤ ዓይናቸውን ቅዝዝ፣ ፊታቸውንም
ጭምድድ አድርገው ከሔዋን አጠገብ ደረሱና በቀስታ እየተቀመጡ «እንዴት ይሻለኛል
እሙዬ ስላልተቀሳቀስኩበት ነው መሰለኝ ይኸ ራሴ ተነሳና ይፈልጠኝ ጀመር ያንን ኪኒንና የምትሉትን ነገር ግዛልኝ ልለው ወደ ቤት ብገባ አስራቴ ደሞ ሆዴን አመመኝ ብሎ ተኝቶ አገኘሁት።
አሉና ኧረ እዲያ» በማለት ብስጭትና ምሬታቸውን ለመግለፅ ሞከሩ።

«አመመሽ እማ?» አለቻቸው ሔዋን ሁኔታቸውን ሰለል እያደረገች፡፡ብታይ ጦሩን ይዞ ሽቀሽቀኝ፡፡ አሏት ራሳቸውን በሁለት እጃቸው ይዘው
ወደ መሬት በማጎንበስ።
«ምን ዓይነት ኪኒን ይሆን?»
«ይኽ እምብሮ ነው ምንትስ የምትሉት!
«አስፕሪን ይሆናል::»
«ይሆናላ! እኔ አላቀው፡፡ እንዳንዴ ሲያመኝ ይኸው አስራቴ ነበር
የሚገዛልኝ። እንግዲህ አባታችሁ እስከሚመጣ ልጠብቅና የሚያውቀው ተሆነ ይገዛልኛላ::"» አሏት በግማሽ ልባቸው ወደ ሔዋን ወረቀቶች ዓየት እያረጉ፡፡
«እኔ እገዛልሻለሁ እማ!» አለቻቸው ሔዋን።
«አዬ...ልጄ! መንገዱ ይርቅሻል። የኛ ሰፈር ደሞ ገጠር አይሉት ከተማ አጉል ነው።ከሱቅ እስቲደርሱ ድረስ ያለው መንገድ መች ቀላል ነውና።ክ
«ግድየለም እማ! መግዣውን ስጪኝ፡፡» አለቻቸው።
«ተበረታሽ ደግ የኔ ልጅ!» ብለው ከተቀመጡበት ተነሱና ነይ ቤት
እሰጥሻለሁ፡፡» እያሉ ወደ ቤት አመሩ፡፡ አስራት ጥቅልል ብሎ እንደተኛ ነው፡፡
የእናቱንና የሔዋንን ወደ ቤት መግባት እውቆ የሚደረገውን ለመከታተል ጆሮውን አቁሞ ሳለ ሔዋን ተናገረችው።
«አመመህ እንዴ አስራት!»
«አረ ቁርጠት ሊገለኝ ነው፡፡» አላት ገልበጥበጥ እያለ።
የሔዋን እናት ፈጥነው ወደ ጓዳ ገብተዋል። «ቆይ ተኔ መድሃኒት
እንሰጥሀለን፡፡ እስከዚያው ቻለው፡፡» እያሉ ይዘው የመጡትን ገንዘብ ለሔዋን ሰጧት፡፡ ተቀብላቸው ከቤት ስትወጣ እስከ ውጭ ድረስ ሸኟት፡፡
ጥቂት ርምጃዎች እስክትራመድ ድረስ በዓይናቸው ሲከታተሏት ከቆዩ በኋላ ፊታቸውን ወደ ግቢው በር ምልስ አድርገው እስከ ቁርጭምጭሚታቸው ይደርስ
የነበረ የአበሻ ቀሚሳቸውን እስከ ጉልበታቸው ድረስ ሰቀሰቁና ወደ ቤት ሳይገቡ ወደ ጓሮ
በሚወሰደው መተላለፊያ መንገድ ሮጡ። ከቦታው ሲደርሱ የሔዋንን የወረቀት አቀማመጥ ልብ ብለው ተመለከቱ፣ወረቀቷን ሲመልሱ
አቀማመጡ እንዳይጠፋባቸው ተጠነቀቁ። ከዚያም የጻፈችባትን ወረቀት ከማስደገፊያዋ ደብተር
ውስጥ ቀስ ብለው መዝዘው አወጧትና አሁንም በሩጫ ወደ ቤት ገሰገሱ።
“እስቲ ተነስ እስራቴ! አሉት ቶሎ ቶሎ እየተነፈሱ።
አስራት ከተሸፈነበት ገለጥ ብሎ ከፊትለፊቱ የቆሙ እናቱንና በእጃቸው የያዝዋትን ወረቀት እየተመለከተ «ምንድነው?» ሲል ጠየቃቸው፡፡
«ቶሎ ተነስ! እሙዬ የጣፈችው ወረቀት ነው፡፡ ሳትመጣብን አንብበውና ከአስተቀመጠችበት ቦታ ልመልስ አሉት በተቻኮለ አነጋገር፡፡
አስራት ከተኛበት ቀና ብሎ ወሪቃቱን ተቀበለና አየት ሲያዩርግ ግጥም ደረድርበታለች፡፡ ከግጥሙ ዳርና ዳር ደግሞ የተለያዩ ቃላት ተሞነጫጭረውበታል።
አስቹ ሆዴ፣ የኔ ምስኪን.. ወዘተ የሚሉ፡፡ ወደ ዋናው ግጥም ከመግባቱ በፊት እነዚህን ቃላት አየት አየት ሲያደርግ ለካ ለሔዋን እናት ዘግይቶባቸው ኖሯል፡፡

“አንብበው እንጂ! አቃተህ እንዴ?» ሲሉ ጮሁበት፡፡ አስራት ግጥሞቹን ማንበብ ጀመረ።
እናቱም፣ ጀሮአቸውን አቁመው ያዳምጡ ጀመር።

«የኔ ሆድ አስቻለው አንተ የኔ ከርታታ!
ላመንከው ለመሞት የማታመነታ።
እመጣለሁ ብለህ ሄደህ እንደዋዛ፣
አንተም በዘያው ቀረህ የኔም አሳር በዛ፡፡
በእርግጥ ባትኖር እንጂ ፍጹም በሕይወት፣
አይጨክንም ነበር አስቹ የአንተ አንጀት።

የበላክን አውሬ ምነው ባገኘሁት፣
በውስጡ ባገኝክ እኔም በበላሁት።
ደምህን ከደሜ አጥንቴን ከአጥንትህ፤
አገናኝህ ነበር ነፍስ እንዲዘራብህ፡፡

የሳምከው ከንፈሬ ደርቋል እንደ ኩበት፤
እህል ውሃ ጠልቶ አንተ የሌለህበት፡፡

እንደው ሂጂ ሂጂ ብረሪ ይለኛል፣
እልም ያለው ገደል ባህሩ ይታየኛል።
ዛሬ ነገ አልኩ እንጂ ልቤ እየዋለለ፣
ስሜቴስ ይጮሀል በርቺ በርቺ እያለ።
ይጎነትለኛል የናፍቆት ሰቀቀን፣
አንተን ካላገኘሁ አይቀርም አንድ ቀን።»
«ኧ! ኧ! እስቲ እስቲ ድገመው!» አሉ የሔዋን እናት አሁንም ጆሮአቸውን ወደ አስራት ጣል አድርገው:: ዓይናቸው ፍጥጥ ማለት ጀምሯል፡፡
አስራት ቀስ ረጋ ብሎ ደግሞ አነበበላቸው: አንብቦ ከጨረሰም በኋላ እናቱ የሚሆኑትን ለማየት ቀና ብሎ በስጋት ዓይን ያያቸው ጀመር።
የሔዋን እናት ድንገት ጥርሳቸውን ግጥጥ፣ ፊታቸውን ክፍት አደረጉና
እንባቸውን እያዘሩ "እክክክክ..እክክክክ...እክክክክ" አሉ አንዳች የሀዘንና የስጋት
ስሜት ውስጣቸው ገብቶ በረብራቸውና፡፡ቀጠሉ አሁንም እጆቻቸውን በነጠላ ላይ ሸፍነው በወገባቸው ላይ በማሳረፍ ቀሚሳቸው በአየር ተንሳፎ
እስኪገለብ ድረስ በቆሙበት ላይ ወደ ግራ ቀኝ እየተወዛዙ «አንቲ» አሉ የጥሪ ያህል በረዘመ ድምፅ።
ሟቿን የአስቻለውን እናት መጥራታቸው ነው።«የጠጡት ጥዋ የለም? የካደሟት አድባር የለችም? የሳሙት ቤተክሲያን የለም፣? አረ አንድ በሉኝ! ኧረ በውቃቢዎ! ድረሱልኝ! ኧረ ልጆዎ ልጄን በላብኝ! ኧረ ልጄን አስመነነብኝ! ኧረ ምን አባቴን ልሁነው! እያሉ ዓይንና አፍንጫቸውን በነጠላቸው
እየጠራረጉ ልክ ሞታ ቀብረዋት ሀዘናቸው ገና እንዳልወጣላቸው አይነት ወያኔ ልጄን ወይኔ ልጄን እመዬ ምን ላርግሽ? እንደው ምን ልሁንልሽ? ልጄ! ልጄ! ልጄ! አሉ በተከታታይ።
“ምነው እማዬ! ምን ሆንሽ?» አላቸው አስራት ደንግጦ ።
በቃ እኮ እንግዲህ እኔም ልጄ በህይወት አለች ብዬ ተስፋ አላደርግም አንተም እህት አለችኝ ብለህ አታስብ! ልጂ ማምለጧ ነው። እሙዩ ተእንግዲህ ሰው አልሆነችም በቃ በቃ! በቃ በቃ! እህህህ።
«አረ ምንም አትሆን እማ»
«ኧረ ወዲያ አስራቴ በቃ ቁርጡን ነገረችን እኮ! በቃ ተናዘዘች እኮ!
«እሙዬ ገደል መግባቷ ነው እኮ! እ፤ህህህህህህ…"
«እንጠብቃታለና»
«አየየ... ጥበቃ! አየየ... ጥበቃ ዋልኝ! የሷ ነገር ተእንግዲህ ከበቃ
እኔም አብሬ ወደ ገደል ነው! እኔም ከእሷ ጋር ወደ ባህር ነው እህህህህህ» አስራት
👍8
እጆቹን ከእናቱ ትከሻ ላይ አውርዶ ወደ መሬት በማጎንበስ እንባውን ጠረግ ሲያደርግ እናቱም በቤቱ መሀል ወለል ላይ ቆመው እየየ ሲሉ ድንገት ከወደ ውጭ በኩል ድምጽ ስሙ:: የሔዋን እናት ያቺን ወረቀት ከቦታዋ ሳይመልሱላት
ሔዋን የመጣች መስሏቸው በመደንገጥ ፈጥነው በበር በኩል አንገታቸውን መዘዝ አድርገው ሲያዩ ባለቤታቸው አቶ ተስፋዬ ሆነው አገኟቸው፡፡ ከብቶቻቸውን መስክ ይዘው ውለው ወደ ግቢ እያስገቧቸው ነው።
«አንተ ተስፋዬ» ሲሉ የሔዋን እናት ከቤቱ በር ላይ ሆነው ግቢ ውስጥ
ገና እየገቡ ያሉትን ባለቤታቸውን ተጣሩ።
«ወይ» አሏቸው አቶ ተስፋዬ ድንገጥ ብለው፡፡
«ቶሎ ግባና ለልጅህ መላ ትፈልግ እንደሆነ ፈልግ! አለበለዚያ ተእንግዲህ እንኳን በቀን እኔንም አታገኘኝ»
«የት ልትሄዱ አሰባችሁ?» አሉ አቶ ተስፋዬ ግራ ገባ እያላቸው፡፡
«በቃ የትም! ሲያሻን ወደ ገደል፣ አለያም ወደ ባህር፡ ቀልድ መስሎህ እንዳትቀልድ!» አሉና የሔዋን እናት ፊታቸውን ወደ ቤት ምልስ አደረጉ፡፡
የሔዋን አባት በሁኔታው ተደናግጠው ፈጠን ብለው ወደ ቤት በመግባት ዙሪያውን በዓይናቸው ሲሰልሉ ሔዋንን አጧት። ሔዋኔ የታለች?» ሲሉ ጠየቁ::
የሔዋን እናት ሔዋን የትና እንዴት እንደሄደች ከገለጹላቸው በኋላ በችኮላ አነጋገር “ቁጭ በልና ጉድህን ልንገርህ!» አሏቸው::

የሔዋን አባት መደብ ላይ ቁጭ አሉና አፋቸውን ከፍተው ባሰቤታቸው የሚነግሯቸውን ለመስማት በጉጉት ይጠብቁ ጀመር፡፡ የሔዋን እናት ግጥሙ ለአቶ ተስፋዬና እንዲነበብላቸው አደረጉ። ተነበበላቸው።
«እንዴት እንዴት» አሉና የሔዋን አባት" ንባቡ እንዲደገምላቸው ጠየቁ፡፡
ተደገመላቸው።
«ምን ይሻላል ትላለህ ታዲያ» አሏቸው የሔዋን እናት::
የሔዋን አባት ፍዝዝ አሉ። አሳቡ አሰቡና «እንደው በአንቺ በኩል ምን ይታይ ይሆን ስንዴ! መላ የጠፋው ነገር ሆነ እኮ! አሏቸው ጉንጫቸውን በመዳፋቸው ደግፈው ዘመም ብለው በመቀመጥ።
መላ አጣሁ! ግራ ገባኝ የት ልገባው? ኧረ የት ልድረሰው አሉና
የሔዋን እናት አሁንም ምርር በለው እያለቀሱ፡፡ የሔዋን አባት እንደ ባለቤታቸው ባያለቅሱም ነገር ግን ጭንቅ አላቸው። የልጃቸው ነገር አሳሰባቸው። ችግሩን ያውቁታል ያው የአስቻለው ጉዳይ ነው:: መነሻው ደግሞ የሆነውን ነገር ባለማወቋ
ነው ይህን ሁሉ ሲያስቡ ቆዩና
ቀደም ሲል አልፎ አልፎ ይታያቸው የነበረውን መላ በእናቷ ፊተ መተንፈሰሰ ፈለጉና፦
«ሰንዴ» ሲሉ ጠሯቸው ባለቤታቸውን፡ የሕዋን እናት ምድጃ አጠገብ ኩርምት ብለው ተቀምጠዋል።
«ወይ»
«ታልሆነ እንግዲህ መቸስ ቁርጥ እወቅ አትደንግጥ ይባል የለ! በአንድ ፊት ሞቷል ብለን እንንገራትና…" ብለው ሳይጨርሱ የሔዋን እናት ከተቀመጠበት ድንገት ብድግ እያሉ፡-
«ሆ'ሆይ! እንዴት እንዴት በል! አበድክ እንዴ አንተ ሰው!» በማለት በአቶ ተስፋይ ላይ አፈጠጡ፡፡ «ዛሬውኑ ብርር ብላ እንድትጠፋልህ ፈልግሃላ!?
«ግራ ገብቶኝ ነው እኮ ስንዴ! አሉ አቶ ተስፋዬ፡፡ እንደማፈርም አሉና
ጎንበስ ብለውኑ ነጩ በዛ ያለ ገብስማ ጺማቸውን ጎተት ጎትተ ያደርጉ ጀመር፡፡
«አንተን ግራ ስለገባህ እሙዬ አብዳ ትረፍ!?»
«እኔ እኮ ቁርጡን አውቃ ማረፏ " ብለው ሳይጨርሱ የሔዋን እናት
አሁንም አቋረጧቸው።
«ኧረ በወላይቱ ይዤሃለሁ!»
«አንቺንም እኔንም ባይልልን ነው እንጂ እሷስ ቢሆን ይኸን ያህል አየሆነች በሰው አፍ ልጃቸው ወንድ ወንድ ባንባል» ብለው አቶ ተስፋዬ ሳይጨርሱ የሔዋን እናት አሁንም ጮህባቸው።
«ኧረ በሚካኤል፤ በምትጠጣው ጥዋ! ምናለ ልጅህን እንደ ባዳ ባታማት» አሏቸው::
“ማማቴ እኮ አይደለም ስንዴ ሰው አያውቅልንም ብየ ነው እንጂ
እውነተኛውንማ ነገር አንቺ ነግረሽኝ የለም!» አሉና በዘንጋቸው መሬቱን መታ መታ ያደረጉት ጀመር አቶ ተስፋዬ ቀይ ናቸው፡፡ ፊታቸው አነስ ብሎ ከበብ ያለ።
የታችኛው ሂማቸው ረዘም ያለና ገብስማ ነው። አረንጓዴ ኮትና ሱሪ ለብስዋል::ነጭ ጋቢ ደርበው ራሳቸው ላይ ነጭ ሻሽ ጠምጥመዋል፡፡ ጥቁር ኮንጎ ጫማ ያለ ካልሲ አድርገዋል:: ጠንከር ያሉ የስልሳ ዓመት አዛውንት ይመስሳሉ፡፡

«ይለቅስ የኔን ሀሳብ ስማኝ፡»
«እስቲ ምን? ከሆነማ ያንቺ ይበልጥ የለ፡፡ »አሉ የሔዋን አባት ጓጓ እያሉ።
«ለሸዋዩ ደብዳቤ እንፃፍ::»
«ምን ብለን»
«እሙዬን መጥታ ትውሰዳት፡፡»
«አዬ….ያቺ ከይሲ ልቧ ይራራል ብለሽ ነው? ወስዳስ ሰላም ትሰጣታለች ብለሽ ገመትሽ?።
አሏቸው የሔዋን አባት ቅር እያላቸው።
«ምን አስቤ መሰለህ አቶ ተሰፋዬ»
«ምን አስበሽ ይሆን»
«ሽዋዬ ለእሙዬ ትሆናታለች ብዩ አያደለም። ግን እሷን ሰበብ አድርገን እነዚያ ወርቆች ናቸው ብዬ ከነገርኩህ ልጆች ጋር ትቀላቀል ተብዬዎች ነው። ተኛ እነሱ ይሻሏታል።እነሱን ስታገኝ ትጥናናለች፡፡ ሀሳብና ጭንቀቷ
ቀለል ይልላት አንደሆን ብዬ ነው።
«ከእህቷ የበለጠ ባዳ ይታመናል ብለሽ ነው?» አሉ የሔዋን አባት ፂማቸውን ጎተት በማድረግ ውጭ ውጭ በማየት:
«እማዬ ያለችው ነገር ጥሩ ነው አባባ፡ ባይሆን እት አበባ እዚህ ድረስ እንድትመጣና አስታርቃችኋቸው ይዛት ተሂድ።» አለ አስራት ከእስካሁኑ የአባትና የእናቱ ምክክር ይኸኛው የተሻለ መሆኑን በማመን።
«ከሆነስ ሆነና ደብዳቤውስ ቢጣፍ ማን ያደርሰዋል? እሷ እንደሆነች ሰው ገድላ የሄደች ይመስል እኛንም ተወችን
ቀየውንም ጠላችው።ባይሆን ስልክ ቢመታላት ይሻል እንደሆነ እንጂ!» አሉ የሔዋን አባት አሁንም ውጭ ውጭ እያዩ።
«እንኳን ስልክ ወረቀቱም የልብ አያደርስ፡፡ ይልቅስ መሳፈሪያ ፈልጉልኝና እኔ ሄጄ ሁሉን ነገር ሳስረዳትና ይዤት ልምጣ?» አለ አስራት አባትና እናቱን ተራ በተራ እየተመለከተ።
«እንዴት ታገኛታለህ አስራቴ!›› እሉ የሔዋን እናት በዚያውም ሀሳቡን
የደገፉት መሆኑን ለባለቤታቸው ለመግለፅ።
«ኤዲያ!» አለና አስራት እጁንም እያወናጨፈ «እንኳን እኔ እንቺስ
አግኝተሻት የለ?» አላቸው
«በያ ላይ ደግሞ ትምህርትህም ይቋረጣል ብዬ ነዋ!»
«ቅዳሜና እሁድን አስደግፌ ብሄድና ለአንድና ለሁለት ቀን ከትምህርት ከቀረ ምን ያህል ይጎዳኛል?»
«የእስራቴ አሳብ ጥሩ ነው አቶ ተስፋዬ ባይሆን ተጨማሪ እንዲሆን የኔና የአንተም ቃል ይጣፍና ይዞላት ይሂድ፡፡» አሉ የሔዋን እናት
«ይሁን ታላችሁ ይሁን በያ ላይ ፈጣሪ አምላክ ብላቱን ያምጣልን። መቸስ ያን ይደረጋል?፡፡» ብለው አቶ ተስፋዬ ከብቶቻቸውን ወደ በረት ሊያስገቡ ወደ ውጭ ወጣ አሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የሔዋን እናት አንድ ነገር ትዝ አላቸውና በድንጋጤ ብድግ አሉ:: «አንተ እስራቴ!» ሲሉ ጠሩት እየተጣደፉ፡፡
«አቤት»
«የእሙዬን ወረቀት አምጣ አደራህን የተነካባት መስሏት ልጄ
እንዳይከፈት ልክ እሷ አድርጋው እንደነበረ አድርገህ እጠፈው» አሉት

አስራት ወረቀቷን ቀድሞ በታጠፈችበት ሁኔታ አራት ቦታ አጣጥፎ ሰጣቸውና ወደ ጓሮ ይዘው በመሄድ እንደነበረ አድርገው አስቀመጡት.....

💫ይቀጥላል💫
👍7🥰1
"ጨለማ ከብርሃን ፣ምንስ ኀብረት አለው?"
ብሎ ቃሉ ቢልም፣
የኔና አንቺን ፍቅር ፣ደርሶ አይወክልም፤
ችሎ አይመጥንም፤
ጨለማ ማን?ካልሽን፣
ማን ብርሃን?ካልሽን፣
እንጃ እኔ፤
ብቻ ግን ፣ ባንጠቅስም ምዕራፍ፣
እንዴት ይጠፋናል?
በጨለማ ገብተን
በቀን የወጣነው ፣ የኔና አንቺ በራፍ።

🔘ኤልያስ ሽታኹን🔘
4👍1
ዕድሜ ለፍቅራችን! ኹለት ጌታ አመንን።
ስብሐት ለአብ፣ለወልድ፣ለመንፈስ ቅዱስ፤
ስብሐት ለአላህ ፣ ዓለምን ላቆመ ንጉሥ፣
አንቺን ስላደለኝ፣
መስጊድ እና መቅደስ፣ኹለት ስለት አለኝ።
በሰው መቁጠሪያ ልክ የማትቆጠሪ፤
(እንደ ሊቃውንትሽ)
በሰው መላኪያ ልክ ፣ከቶ ማትለኪ፤
.
.
.
(ነይ አኑሪኝ እስኪ)

🔘ኤልያስ ሽታኹን🔘
👍10
#ምንትዋብ


#ክፍል_ሀያ_አንድ


#ድርሰት_በሕይወት_ተፈራ

... አየ ወለቴ ጠጋ ብየ ባጥናናሁሽ፡፡ እኔ አልረሳሁሽም። የሩቅ ቅርብ ሁኜ ስላንቺ አስባለሁ። ምንግዝየም ኸልቤ አትጠፊም አለ።..

ከለቅሶው በኋላ፣ ሕዝቡ ወደ መኻል ግንብ ለስንብት ሲሄድ አብሮ ሄደ። በግርግሩ መሃል ከነአብርሃ ጋር በመጠፋፋቱ፣ ከተሰናዳው የእዝን ግብር ከሕዝቡ ጋር መካፈል ሆዱ እንቢ ብሎት፣ በሰዎች ተከልሎ ምንትዋብና ኢያሱን እጅ ነስቶ አልፎ ወርቄ ቤት ሄዶ ውጭ ተቀምጦ ጠበቃቸው።

እነወርቄ እንደተመለሱ፣ አብርሃ ለብቻው ከተፍ አለ። “የት ኸዳችሁ
ነው የተጠፋፋን? ወዲህ ብል ወዲያ ብል አጣኋችሁ” አላቸው።

ሁሉም የነበሩበትን ቦታ ከተነጋገሩ በኋላ፣ ውስጥ ገብተው ወርቄ
ምሳ አቀረበች። በልተው ሲጨርሱ፣ ጠላ እየተጎነጩ ስለ ቀኑ ውሎ ማውጋት ጀመሩ።

“መቼም ሰዉ ሁሉ ሚያወራው ስለ እቴጌ ጥንካሬ ነው” አለ፣
አብርሃ። “ቀብሩን ሆነ የቅጥር ልቅሶውን እንዴት አርገው እንዳዘጋጁት ይገርማል ። ባላባቱ፣ ካህናቱና ሊቃውንቱ፣ “በርግጥም በካፋ አልሞቱም ሲሉ ነበር አሉ” አላቸው።

ጥላዬ ዝም አለ። ምንትዋብ በልጅነቷ ባሏን በማጣቷ ጉዳቷ
ተሰምቶታል። አጠገቧ ሆኖ ሊያጽናናት ባይችልም፣ ደብረ ወርቅ መመለስ ከብዶታል። በሩቅም ቢሆን ሐዘኗን መካፈል መርጧል።ምንም ቢሆን ወለቴ እኮ አብሮ አደጌ ናት። ኑሯችን እየቅል ቢሆንም በዕዘኗ ሆነ በደስታዋ የሩቅ ቅርብ ሁኜ መካፈል አለብኝ አለ፣ ለራሱ።

በሌላ በኩል አለቃ ሔኖክን ደግሞ ሳያያቸው ማረፋቸው አሳዘነው።
ደብረ ወርቅ በነበረበት ወቅት ስለእሳቸው ሲያስብ፣ የተማረውን ሁሉ ሊያወራቸው ሲመኝ ቆይቶ፣ እንደ አባት የሚያያቸውን መምህሩን ሞት ስለነጠቀው ከፋው። በሌላ በኩል ወርቄ ወላጆቿ መጥተውላት አጠገቧ
በመሆናቸው ደስ አለው። አርባቸውን ሳላወጣ አልኸድም አለ፣ ለራሱ።

ወርቄ፣ ሐሳብ ውስጥ እንደገባ አስተዋለች። ደብረ ወርቅ እስኪመለስ ድረስ የቀድሞ ቤቱ መክረም እንደሚችል ነገረችው።
አብርሃ፣ ጥላዬን ከስድስት ዓመት በኋላ፣ በማግኘቱ ደስታው መጠን
አጥቶ ነበርና፣ “ኸኔ ዘንድ ይቆያል” አላት።

እኔማ ያው ቤቱ አለ ብየ እንጂ” አለች ወርቄ፣ ጥላዬን እያየች።
“ኸብረሃም ዘንድ እየተጫወትን እንከርማለን። ኸናንተም አልለይም።አልሰማሁ ሁኘ አለቃን ሳልቀብራቸው ቀርቸ እኼው ዛሬ እንጉሥ ለቅሶ ለመድረስ በቃሁ። እንዳው አለቃን ከዛሬ ነገ አያቸዋለሁ ስል አመለጡኝ” አላት።

ወርቄ በዐይኗ ውሃ ሞላ።

“ተይ ልዤ ጠሐይ ላይ ውለሽ መጥተሽ። መቀበል ነው እንጂ ሌላ ምን ማረግ ይቻላል?” አሏት እናቷ።

አብርሃ፣ ትኩር ብሎ አያትና፣ “የአለቃ ሞት ሁላችንንም ነው የጎዳ።መጥናናት ነው እንጂ ሌላ ምን እናረጋለን። ሞት እንደሁ ያለ ነው” አላት።

“የአለቃን ነፍስ በገነት ያኑርልን። የጃንሆይንም ነፍስ እዝጊሃር
ይማር” አሉ፣ የወርቄ አባት።

“አሜን” አሉ፣ ሁለም።

“እቴጌም ቢሆኑ አሳዘኑኝ በልዥነታቸው ባላቸውን አጥተው። ዕጣ ፈንታቸው እንደኔ የሙት ሚስት መሆኑ ያሳዝናል” አለች ወርቄ ለምንትዋብም ለራሷም በማዘን።

ሁሉም አንገታቸውን ደፍተው ዝም አሉ።

አብርሃ፣ እኔማ ትምርቱስ እንዴት ሁኖለት ይሆን እያልሁ ሳስብ”
አለው ጥላዬን፣ ቤቱን የከበበውን የትካዜ ድባብ ለመቀየር።

“ትምርቱማ... ያው ኸዝኽ አንድ ዓመት አርጌ ማልነበር ወደ ደብረ
ወርቅ ማርያም የኸድሁት? ኸዛ ያገኘዃቸው መምህር... ሊቀጠበብት አዳሙ እንዴት ያሉ ሰው መሰሉህ። አለቃ ሔኖክ እሳቸው ዘንድ ስለላኩኝ እንዳመሰገንዃቸው አለሁ። ያው... ኸዝኸ እንደኸድሁ ሥጋ
ለባሾችን ሠራሁ።”

“ሰዎችን ማለቱ ነው” ሲል አብራራ አብርሃ፣ የወርቄ ወላጆች ግር
ሲላቸው አይቶ።

“ቤተስኪያን አካባቢ ያሉ ቀሳውስት፣ መነኮሳት... መምህር
የመሳሰሉትን ማለቴ ነው” አለ፣ ጥላዬ። “ታስታውሳለህ አለቃ ሔኖክ...ነፍሳቸውን ይማርና... ስዠምር ጥቁር ቀለም ብቻ ነው ምትጠቀመው ሲለኝ? ኋላ ሌሎች ዓይነት ቀለሞችም ተጠቅሜያለሁ።”

“ራስህ እያዘጋጀህ?"

ኋላ! ራስህ ነህ እንጂ ሌላ ማን ያዘጋጅልሀል? እና ... የቤተክህነት
ሰዎችን ስትሥል፣ የልብሳቸውን ሆነ የካባቸውን ቀለም አሳምረህ
ትሠራለህ። ጥምጥማቸውንም እንዲሁ ትክክል አርገህ ትሥላለህ። ንድፉ እንዳይንጋደድብህም ትጠነቃቃለህ። የልብሳቸውንና የካባቸውንም ዕጥፋት ሳይቀር ነው በጥንቃቄ ምትሠራው።”

“ስንታቸውን ሣልህ በል?”

“ምን አለፋህ ብዙዎቹን ሥያለሁ። የዠመርሁት በአንድ መነኩሴ
ነበር። መነኩሴው ሲያዩት ደስ አላቸው። ማስታወሻ ብየ ሰጠኋቸው።ሁለተኛ ሊቀጠበብት አዳሙን ነበር የሣልሁት። እሳቸውም እንደዝሁ ደስ አላቸው። እንዲህ እያልሁ ወደሚቀጥለው ተሻገርሁ።”

“ምን ሠራህ?”

“ጻድቃንን ሣልሁ። አቡነ ተክለሃይማኖትን፣ ቅዱስ ያሬድን፣ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስን፣ አቡነ ኪሮስን፣ እናታችንን ክርስቶስ ሣምራን የመሰሉትን ሣልሁ።”

“የሁሉን መልክ አውቃችሁ ነው ምትሥሉ?” ሲሉ ጣልቃ ገቡ፣
የወርቄ አባት።

“የለ... የለ... እነሱን ስንሥል መልካቸውን ስለማናውቅ... የተሰወሩ ስላለባቸውም ... ታሪካቸውን፣ ታምራቸውንና ገድላቸውን ጠንቅቀን
አውቀን ነው ምንሥል። እነሱን ለመሣል ኸመነሣታችን በፊት
ታሪካቸውንና ገድላቸውን ለማወቅ ንባብ አድርገን ነው ምንሥላቸው።
ሥጋ ወደሙን ተቀብለን ስንሠራ ደሞ ትክክለኛ መልካቸው
ይገለጥልናል” አላቸው፣ ጥላዬ።

“እህ” አሉ የወርቄ አባት፣ እንደገባቸው ለማሳወቅ ራሳቸውን
እየነቀነቁ።
“እንደ ቅኔ ነው በለኛ! እኛም እኮ ክብረ ነገሥት፣ ገድላት፣ ድርሳናት
ወንጌል... መጽሐፍ ቅዱስ... ኻላወቅን ቅኔ አንቆጥርም” አለው
አብርሃ።
“አውቀው የለ። ደሞ ሰማዕታትን ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ እንደ መርቆርዮርስና ገላውዲዮስ የመሳሰሉትን ሣልሁ። ሰማዕታት ቤተክሲያን ውስጥ ሲሣሉ በግራ በኩል ነው ሚሣሉ። ሁሉም ሚሣሉበት ቦታ ቦታ አላቸው። ሚሣሉበት ቀለምም እንደዝሁ ይለያያል። ሰማዕታት ለጌታችን ለክርስቶስ ፍቅር ሲሉ፣ ስለአዳኝነቱ ሲመሰክሩ አንገታቸው
በሠይፍ ተቀልቶ፣ ወይ ከእሳት እቶን ተጥለው ማዶል የሞቱት? እናም ያነን ያፈሰሱትን ደም ለመዘከር በቀይ ቀለም ይሣላሉ። መላዕክት የመንፈስ ቅዱስ ሕይወት በነሱ ላይ ስላደረ... ብርሃንና ተስፋ ሰጪዐስለሆኑ፣ እነሱን ለመሣል ምትጠቀመው ቀለም ደማቅ መሆን አለበት።
ደማቅ ቀለም የተስፋ ምልክት ነው። ጻድቃን.. ይኸን ዓለም ንቀው በጽድቅ ኖረው ያለፉ አባቶቻችን ደሞ ፈዘዝ ባለ ቀለም ይሣላሉ።ድንግል ማርያም ደሞ ልብሷ ከላይ በሰማያዊ፣ ከውስጥ በቀይና ምትከናነበው ደሞ በአረንጓዴ ቀለሞች ይሣላል። ምትሥለው ሥዕል
እንደ ተሣዩ ማንነትና ታሪክ ምትመርጠው ቀለም ይለያያል። ሰማያዊ መንፈሳዊ ንፅህናን ያሳያል፤ ነጭ እንደምታውቀው ብርሃን ነው፤ ብጫ
ደሞ የዠግንነት ምልክት ነው።”

“ዘይገርም!” አለ፣ አብርሃ።

“ምን አለፋህ መላዕክትን... ሰባቱን ሊቃነ መላዕክት... እነቅዱስ ገብርኤልንም ሣልሁ” ሲል ቀጠለ ጥላዬ። “መላዕክት እንደምታውቀው መከሠቻ አላቸው። ሚከሠቱበት መንገድም ይለያያል...”
“መከሠቻ?” አሉ፣ ሁሉን በጥሞና ሲያዳምጡ የቆዩት የወርቄ እናት።
“ኣዎ መገለጫ ማለቴ ነው።”
“እንዴት እንዴት ሁነው ነው ሚገለጡ?”
👍11
“ብዙ ነው መገለጫቸው። ርግብ ሁነው ሊገለጡ ይችላሉ። እ... አረጋዊ መስለው ሊመጡ ይችላሉ። ብቻ ይኸን ሁሉ ለመሣል ታሪካቸውን በደንብ ማወቅ... ብዙ ንባብና ዕውቀት ይጠይቃል። መላዕክት ያው
ፊታቸው ክብ ነው ሚሆን። ክንፍም አላቸው። መዠመሪያም ሆነ መጨረሻ እንደሌላቸው ለማሳየት ነው። መላዕክት ሆኑ ቅዱሳን በግማሽም አይሣሉም።”
“በግማሽ?” አሉ፣ የወርቄ አባት።
“ፊታቸውን ሙሉ ለሙሉ እንጂ በጎን መሣል አይችሉም።
መላዕክትና ቅዱሳን ምንግዝየም ቢሆን ሲሣሉ ፊት ለፊት፣ አንድ
ዦራቸውና ሁለቱም ዐይኖቻቸው እየታዩ ነው። አጋንንት፣ ከሀዲያንና
ክፉ አድራጊዎች ብቻ ናቸው በጎን ሚሣሉ። መላዕክት ረቂቅ ስለሆኑ
መሽጋገሪያም ናቸው።”

“መሸጋገሪያ ማለቱ መላዕክት በሰውና በአምላክ መኻል በመሆናቸው ነው” አለ አብርሃ፣ ለእነወርቄ ለማስረዳት። ቀጠለና፣ “ሚገርመኝ ለሥዕል ያለህ ፍቅር ነው” አለው፣ ጥላዬን።

“እንዴት በል? አንተስ ብትሆን ለቅኔ ጥልቅ ፍቅር ስላለህ ማዶል
እንዴ እዝል ድረስ የዘለቅኸው? ቅኔ ቆጥሬ አውቃለሁ... አንተም ቅኔ ስትቆጥር ሆነ ቅኔ ስትዘርፍ ታውቀዋለህ። ሥዕል ስትሥል ምድሪቱ መነሻህ እንጂ መድረሻህ አትሆንም። ኸመመሰጥህ የተነሳ ሌላ ዓለም ውስጥ የገባህ ነው ሚመስልህ። ቁንጫ ሲበላህ የበላህን ቦታ ልታክ እጅህን ኻነሳህ፣ ሆድህ ርቦት ሲጮህ ኸሰማኸው ሥራህ ላይ አላተኮርህም ማለት ነው። ቅዱስ ያሬድ ኸመመሰጡ የተነሳ ማዶል እንዴ የንጉሡ የዘንግ ሠላጢን እግሩ ላይ ቢቸነከርበት ልብ ሳይል ሕመሙንም ሆነ የደሙን መፍሰስ ሳያውቅ ዝማሬውን የቀጠለ? ስለዝኽ አብርሃ ሥዕል ሆነ ቅኔ ቆጠራና ዘረፋ ኸኛ ላይ በሚያሳድሩት ፍቅርና ተመስጦ ልዩነት የላቸውም። አንተ ቅኔ እየቆጠርህ ታሪክን ባፍህ እንደምትነግረው፣ የሰውን ባሕሪና የተፈጥሮን ድንቅነት እንደምትገልጠውና የዝኸን
ዓለም ምሥጢር እንደምታብራራው እኔም ይኸን ሁሉ ብራና ላይ አኖረዋለሁ። ስለዝኸ ልዩነት የላቸውም። ሁለታችንም የታደልነው ጸጋ
ይኸ ነው።”

“እኛም የደከምንለት። በል እስቲ ደሞ የትምርትህን ጉዳይ
ጨርስልኝ። መላዕክትን ከሠራህ በኋላ ምን ሠራህ?”

“ገና አድኅኖትን... ሥነ-ስቅለትን..
የደረሰበትን መከራ ሁሉ... ለዓለም ቤዛ ሁኖ እንደመጣ እሥላለሁ።
ድንግል ማርያምንም ኸነልጇ መሣል አለብኝ። ሌላ እስታሁን
በየደብሩ እየተዘዋወርሁ የሌሎች ሠዓሊዎችን ሥራዎችም አየሁ።
የአሣሣል ዘዴያቸውን፣ አቀራረባቸውን፣ ቀለም አጠቃቀማቸውን ማለቴ
ነው። አንዱን ቀለም ኸምን ጋር ስትደባልቀው ምን ዓይነት ቀለም
እንደሚሰጥህ ጭምር ትማራለህ። ወደር የሌላቸው ሠዓሊዎች አሉና የእነሱን ሥራ ማየት ይጠቅምሀል ።”

“ያው እንደ ቅኔ ነዋ! እኛስ ኸደብር ደብር መምህር ፍለጋና የቅኔ
ዓይነትና ስልት ልንማር ማዶል ምንዞረው?”

“ብዙ ትማራለህ ኸመምህሮችም ኸተማሮችም። በመምህሮች
ሚደረገው ቁጥጥር ደሞ እንዲህ እንዳይመስልህ፣ ጥብቅ ነው።”
“ስድስት ዓመት ቆየህ ኸዛ፤ ጐንደር ማትመለስ? ኸንግዲህ ምን ቀረህ?”

“ሥነ-ስቅለትን ልዠምር ስል ልቅሶውን ስሰማ ወዲህ ተነሳሁ። ብዙ ለፈለፍኩ። ለመሆኑ አንተስ እንዴት ከረምህ?”

“እኔማ... አስታውሳለሁ እጐንደር እንደመጣህ መወድስ ዠምሬ
ነበር። መወድስን እንደጨረስሁ ያው ቅኔ ሞላሁ። ኸዚያ በኋላ እጣነ ሞገር ተቀኝቸ ተመረቅሁ። ወዲያው ዋድላ ኸድሁ። ዐራት ዓመት አረግሁ ኸዛ። የዋድላ ቅኔ ቀላል እንዳይመስልህ። ጥልቅ ነው። ብርዱ ሚቻል አዶለም። ዕድሜ ለደበሎ አከረመኝ። ዋድላ ብኸድ ቅኔ ብቻ ሳይሆን ምሽትም አገኘሁ። ባለቤቴ ዛሬ ሳትመጣ የቀረችው አራስ ሁና ነው።”

“ምነው እስታሁን ሳነግረኝ? ምን ወለድህ?

“ሴት።”

ጥላዬ፣ “እንኳን ደስ ያለህ!” አለና ተነስቶ አቀፈው።

“እንዳው ተመልሰን ስንኳ ሳንጠይቃት” አሉ የወርቄ ኣባት፣ አብርሃን እያዩ።

“እንዴ ወርቄ ተመላለሰች ማዶል? ምን ቀረባት? በዝኸ ላይ ዐዘኑም
አለ” አላቸው አብርሃ፣ እሱና ጥላዬ ተመልሰው ቦታቸው ከተቀመጡ
በኋላ። ፊቱን ወደ ጥላዬ መልሶ፣ “ጐንደር ኸመጣሁ ዓመት ሆነኝ።
እኼው መጋቤ ተብየ እደብረብርሃን ሥላሤ ወንበር ዘርግቸ ቅኔ እነግራለሁ። አፌ ላይ እየመጣ ሳልጠይቅህ ... ለመሆኑ ሥጋዎችህ እንዴት ናቸው? ወሬያቸውን ትሰማለህ?” ሲል ጠየቀው።

“የዛሬ ሦስት ዓመት ቋራ ኽጀ ነበር እኮ። አባቴ ሙተው ነው
የደረስሁት። እኔ ወዲህ እንደመጣሁ ነው አሉ ያለፉት። በኔ መጥፋት ተጎድተው ነበረ፡፡ 'ልጄን አማርሬ እንዲጠፋ አረግሁት እያሉ ይቆጩ ነበር አሉ። እናቴ ደሕና ነች። እቶቿ መጥተውላት ከነሱጋ ነች።የእቴጌ ምንትዋብም አባት መሞታቸውን እዛው ሰማሁ።”

“ታውቃቸው ኑሯል እንዴ?”

ጥላዬ ደነገጠ። “የለ... እዛ ሁኜ የወሬ ወሬ ሰምቸ ነው።”

“ወደዝኸ መቸ ትመለሳለህ? ጐንደርን ጠላህ መሰል። ኸዝኸ መማር አይሆንልህም እንዴ?”

ደብረ ወርቅ ከመሄዱ በፊት የነበረውን ቅሬታ አስታወሰ። ደብረ
ወርቅ ግን ስለሥዕል ብዙ የተማረበት ቦታ በመሆኑ፡ ከሄደ በኋላ ምንም ቀን ተከፍቶ ባለማወቁ ለደብረ ወርቅ ፍቅር አዳብሯል። የጐንደር ነገር እንደማይሆንለት ግን አውቋል።

“የለ ኸዛው ልጨርስ ብየ ነው” አለው። “ ጐንደርን ጠላህ መሰል
ምትለኝ ጐንደርን በምን አንዠቴ ነው ምጠላ? ጐንደር ዕጣ ፈንታየ፡
እትብቴ አይቀበርባት እንጂ አገሬ ናት። ያጎለመሰችኝ፣ ዕድሌ የተሰበረ ሲመስለኝ ያቃናችልኝ፣ ቀልቤ ያረፈበትን ሥዕል እንድሠራ፣ እንድማር ዕድል የሰጠችኝ፣ ያጣሁትን ተስፋ ያገኘችልኝ፣ ኸሰው ተራ ያቆመችኝ
ናት። ልቤ፣ መንፈሴ... ኧረ እንዳው ሁለመናየ... እጐንደር ነው ያለ።”

“ቋራስ?” ተወልደህ ያደግህበት፣ እትብትህ የተቀበረበት ማዶል?”

ጥላዬ ለራሱ፣ ቋራ ተወልጀ ያደግሁበት ብቻ ሳይሆን ልቤን ኸሌላ ያቆራኘ ነው አለና ለአብርሃ፣ “ውነት ብለሀል። ግና ኸዛ ቀርቸ ቢሆን ኑሮ ምን አገኝ ኑሯል? ጐንደር ብመጣ ስመኝ የኖርሁትን ሰጠችኝ:
አንድ ምልህ ነገር ምንም ብትመኝ ምንም ምኞትህን ሚያሳካልህ
ስፍራ ኻልሆንህ ይሳካልሀል ማለት ዘበት ነው። ላም ባልዋለበት
ኩበት ለቀማ እንደሚሉት ይሆንብሀል። ሁሉ ሚሆነው በቦታና በግዝየ ነው። እናቴ ብልህ ናት። እኼን አውቃ “ዕድሜ ኻላነሰው፣ ጊዜ አለው ሰው” ብላኝ ታውቃለች። ሰው ኻልሞተ በግዝየው ሚሆነለት ሁሉ
ይሆናል ማለቷ ማዶል? ጐንደር ጠፍቸ የመጣሁት ግዝየው በመሆኑ ነው። ሥዕልም ቢሆን መማር ያቻልሁት ግዝየው በመሆኑና በቦታው በመገኘቴ ነው” አለና ለራሱ፣ ጐንደር ጐንደር ባለ ግዝየ አረገችኝ አለ፣
አጎንብሶ መሬቱን በእግሩ እየመታ፡ ቀና ብሎ አብርሃን ተመለከተና፣
“ለማነኛውም ትምርቴን ሳጠናቅቅ መለሳለሁ።”

“እውነት ብለኻል፤ ከቦታም ደግሞ ትምህርት ቤት የተተከለበት ቦታ
ለእኛ ብጤው ክፍላችን ነው። "ድጓው ጤፍ እንጀራ አቋቋሙ ማር

ጐንደር ጐንደር ነይ ነይ ጐንደር
ጐንደር አለቃ መምህር

ብለንም እናወድሳታለን የትምህርት አገራችንን” አለ አብርሃ ከጥቂት ዝምታ በኋላ፣ ግጥሙን በሚያምር ዜማ አዚሞ አድማጮቹን የሞቀ ፈገግታ እያላበሰ።

“እጠይቃችኋለሁ እያልሁ... አጤ ኢያሱ ነገሡ። ገና ልዥ ናቸው።
እንዴት አርገው ነው አገር ሚመሩ?” አለች፣ ወርቄ።

እተጌ ምንትዋብ ሞግዚት ሁነው ይነግሣሏ” አለ፣ ጥላዬ።

“ሞግዚት ሁነው ይነግሣሉ?” አለች፣ ወርቄ።

ጥላዬ በአዎንታ ራሱን ነቀነቀና ለራሱ፣ የወለቴንም ንግሥ ሳላይ
ደብረ ወርቅ አልመለስም አለ።....

ይቀጥላል
👍9
#ያልታበሱ_እንባዎች


#ክፍል_ሰላሳ_ሰባት


#ድርሰት_በአሰፋ_በቀለ_ገየሱስ

....ሸዋዬ በህዳር ወር የመጨረሻ ሳምንት ላይ ቆማ የመጀመርያው መንፈቅ ትምህርት አልቆ ለአጭር ጊዜ እረፍት ትምህርት ቤት የሚዘጋበትን የጥር ወር መጨረሻ በናፍቆት ትጠባበቃለች። ከብረ መንግስት የምትደርስበት ቀን ሳይቀር ተወስኗል።እቅዷ ከሔዋን
ወይም ከወላጆቿ ተቃውሞ ቢገጥመው ማሳመኛ ይሆናል የምታስበውን እያዘጋጀች ነው። ዘዴና ብልሀት በልቧ ይውጠነጠናል።

ለሆዳም በሬ ጭድ ያዝለታል እንዲሉ ወንድሟ አስራት ተስፋዬ ባላሰበችው ቀንና ሰአት ከቤቷ ከች ብሎ ያደረሳት ብሥራት ግን ሰጋትና ፍርሃቷን ሁሉ ከልቧ ውስጥ እንደ እድፍ አጠበው። ሔዋን የልብ ህመምተኛ ሆናለች በሰው ላይ ክፉ ደግ አለና መተሽ እያት ከማለት ውጭ ስለ ሔዋን ሁኔታ ምንም አይነት ፍንጭ ለሸዋዬ እንዳይሰጥ በተለይ በእናቱ አደራ የተባለው አስራት የልጅ ነገር ሆኖበት አንዳንድ ነገሮችን ማፈንዳቱ አልቀረም ሔዋን ዛፍ ስር ተቀምጣ መዋል ማዘውተሯን በሀሳብ እየተዋጠች ቤተሰቧን ማሳሰቧንና በተለይ በህመሟ ምክንያት አገር ብትቀይር የተሻለ መሆኑ መታመኑን ሁሉ አልደበቃትም።

የሔዋን አገር መቀየር አስፈላጊነት የታመነበት ስለመሆኑ መስማቷ ሸዋዬን ከምንም ነገር በላይ አስፈነጠዛት። ሔዋን አገር መቀየር ካለባት ቀላሉ ከክብረ መንግስት ወደ ዲላ ነው ይህ ደግሞ በቤተሰቦቿ ዘንድ ተፈጥሮ ይሆናል ብላ ከምታስበው ቅሬታ ነፃ የምትሆንበት አጋጣሚን ይፈጥራልና ወቅትና ጊዜ ያለ ሽማግሌ ሲያስታርቃት በመቅረቡ አምላኳን አመሰገነች፡፡ ወደ ክብረ መንግስት ልትሄድ በልቧ ይዛው የነበረውን የጊዜ ቀጠሮ አሳጠረችው፡፡ ወንድሟ አስራት
ከቤቷ በደረሰ በአራተኛው ቀን እንዲሆን አደረገችው:: በመሀል ያሉት ሁለት ቀኖችም የዝግጅት ጊዜ ሆነ::
ብሥራቱን ያካፈለቻችው በድሉና ማንደፍሮ በእነዚህ ሁለት ቀናት
አልተለዮትም፡፡ ወደ ክበር መንግስት አካሄዷን ሊያሳምሩ ሽርጉድ አሉ። አብረዋት
እየዋሉ አብረዋት አመሹ። በየገበያው ቦታ አብረዋት ዞሩ። አዘጋጇት፤ አዘገጃጇት ጠዋት ወደ ክበረ መንግስት ልትሄድ ሻንጣዋ የያዘውን ይዞ ማታውኑ ተቆለፈ
የማግስቷ ጀምበር ክብረ መንግስት የምታደርስ የልቧ መብራት ሆነች::

ልክ በዚያ ዕለት ምሽት ላይ ክብረ መንግስት ሌላ ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው። የሄዋን አባትና እናት ሔዋን ወደ ዲላ መሄድ ያለ መሄድ ፍላጎቷን ለመጠየቅ ሊያነጋግሯት በተመካከሩበት መሠረት ውይይቱ ተጀመረ፡፡
«እሙዬ !» ሲሉ ጠሯት ለስለስ ባለ አነጋገር።
«አቤት እማ» አለቻቸው ሔዋን ከአጠገባቸው መደብ ላይ ገደም ብላ ሳለች። አባቷ ደግሞ ከባላቤታቸው ፊት ለፊት ምድጃኑ እጠገብ ተቀምጠው እሳት ይሞቃሉ።
«እንደው ይቺ ልብሽ ያስቸገረችሽ ይኸን አገር ጠልታብሽ ይሆን? እማስበው ባጣ ይህን ነገር በእሊናዬ አውጠነጥነው ጀመር ልጄ? አሏት ጉልበታቸውን በሁለት
እጆቻቸው ደገፍ በማድረግ ዓይን ዓይኗን እየተመለከቱ፡፡
«አዩ! እማ ቢቸግርሽ!»
«ቸገረኝ ልጄ! በጣም ችግረኝ፡፡»
«የት ልሂድ ታዲያ እማ»
«እውነትሽ ነው:: መሄጃማ ይቸግራል የኔ ልጅ፡፡» ካሉ በኋላ የሔዋን እናት ወደ አቶ ተስፋዩ ዞር በማለት «እንደው ወደ ዲላ ትሂድ ይሆን አቶ ተስፋዬ» ሲሉ ጠየቋቸው።
«ተሆነማ ወደዚያው ነው ኋላማ መይት ትሄደዋለች? ከዚያ ሌላ አገር አታውቅ አሉ አቶ ተስፋዬ አንገታቸውን ወደ እሳቱ ደፋ አድርገው፡፡
«ከማን ጋር ልኖር?»ስትል ሔዋን ጠየቀቻቸው፡፡
«በኔ ልብማ ከነዚያ ከነታፈሡ ጋር ትንሽ ተጨዋውተሽ ትመለሽ እንደሆን ብዬ ነዋ!»አሉ እናቷ ለስለስ ባለ አነጋገር።
«እህቷስ አለች አይደል! »አሉ አቶ ተስፋዬ ወደ እሳቱ እንዳቀረቀሩ።
«እንደገና ከእታ አበባ ጋር?» አለች ሔዋን ደንገጥ ብላ።
«እሷን ለሰበብ ተዚያ በኋላ ደግሞ ከእነዚያ ልጆች ጋር አንዳንድ ጊዜ
መጫወቱ ትንሽ ያፍታታሽና ልብሽም እየተወችሽ ትሄድ እንደሆነ ብዬ እኮ ነው፡፡»
አሉ እናቷ የሔዋንን ቁጣ ለመመለስ ረጋ ብለው።
«ተይ እማ! እንዲህማ አይሆንም::»
«ቀለብሽን ተሆነ እኔ እችላለሁ ሔዋኔ ከቶ የአንቺ ጤና ይመለስ እንጂ፣ደሞ ላንቺ ያልሆነ አዱኒያ ምን ሊያደርግልኝ! ላም ተሆነች ላም! በሬ ተሆነም በሬ ይሸጣል :: አይዞሽ!» አሉ የሔዋን አባት በቆራጥነት።
«እናንተ የማታወቁት ልላም ችግር አለ:: አለች ሔዋን፡፡
«ብትነግሪን አይፈታም?» አሏት እናቷ፡፡ ግን ትዝ ያላቸው ነገር አለ፤ ያኔ ታፈሡ በማትፈልገው ሰው ልታስደፍራት ያለቻቸው ነገር። ፈታ ብላ ብታወባና ሁኔታውን በግልጽ ቢረዱት ፈለጉ፡፡
«እኔና እት-አባበ አብረን መኖር አንችልም፡፡» አለች ሔዋን ነገሩን ደፈንፈን አድርጋ።
«ኧረ ተይ ሔዋኔ፣ በእትማማቾች መካከል ቂም ተያይዞ አይኖርም!» አሉ አባቷ አሻግረው መልከት እያሏት፡፡
«ከበድኳችሁ እንዴ አባዬ?»
«ለአንቺ ብለን ነው እንጂ እሙዬ ደሞ አንቺ ምን ትከብጅናለሽ የኔ ልጅ?»
አሏት እናቷ በማሳዘን ዓይነት አነጋገር፡፡
«እንግዲያው እዚሁ ብሆን ይሻለኛል፡፡» አለችና ሔዋን በረጅሙ ተነፈስች።

የሔዎን እናትና አባት ግራ ተጋቡ። ልጃቸው ወደ ዲላ ለመሄድ ፈቃደኛ አለመሆኗ ገባቸው። ከዚያ በኋላ ምንም ሳይነጋገሩ ጊዜው መሸ፡፡ እንደ ተዳፈጡ ተኙ፡፡ ሌሊቱ በሀሳብ ነግቶ ቀኑም በትካዜ አለቀ።

የደስታ ፈረስ ጋልባ ሶምሶማ ስትጋልብ የዋለችው ሸዋዬ ከቤተሰቦቿ ቤት የደረሰችው ከአመሻሹ አስራ አንድ ሰዓት አካባቢ ነው፡፡ በዚያ ሠዓት አባቷ
ከብቶቻቸውን ይዘው ከመስክ እየተመለሱ ነው። እናቷ ደግሞ ምናልባት ሔዋን ሸዋዬ ስትመጣ ሀሳቧን የቀየረች እንደሆነ ብለው ለወደፊቱ ግንኙነት እንዲያመች
የዘመድ ስልክ ቁጥር ሊያመጡ ወደ ከተማ ሄደው እየተመለሱ ገና በመንገድ ላይ ናቸው:: ሽዋዬና አባቷ በር ላይ ተገናኝተው በመሳሳም ናፍቆታቸውን አውጥተው እየተነጋገሩ ወደ ቤት ሲገቡ ሔዋን በጎሮ በር በኩል ወደ ቤት ስትገባ ዓይን ለዓይን ግጥምጥም አሉ።

"እማሃይዬ! አለች ሔዋን ሸዋዬን ስታይ ደንግጣ። የትናንት ማታው ወሬ መሰረቱ ምን እንደነበር ልቧ ጠረጠረ።
«እህትሽ መጣች ሔዋኔ!» አሉ አባቷ ቀድመው::
«ጠፋሁባት ይሆን?» በማለት ሽዋዬም ሳቅ እያለች ወደ ቤት ገባችና በሔዋን ላይ ጥምጥም ብላ ሳመቻት::
«አንቺ! አለቻት አጠገቧ ቆማ ከእግር እስከ ራሷ እየተመለከተቻት፡፡
«አቤት» አለች ሔዋን ወደ መሬት እንዳቀረቀረች::
«በቃ አንዲህ ሆነሽ ቀረሽ?»
ሔዋን ሽዋዩ ምን እያለች እንደሆነ አልገባትም፡፡ ጠቁራባት ይሁን
ከስታባት ብቻ ያየችባትን አካላዊ ለውጥ ገና ትነግራት እንደሆነ እንጂ ለጊዜው አለየላትም።
ሸዋዬ እንደ መናደድ ዓይነት እጆቿን ጨብ ጨብ ጨብ እያረገች ዋይ-ዋይ-ዋይ-ዋይ…አለች ደጋግማ:: በአባታቸው ግብዣ
ሁሉም በመደብ ላይ ተቀመጡ።

«ሔዋኔ ክብረ መንግስት እንዳላደገችበት ሁሉ ዛሬ ዛሬ አልስማማት ብሏል የሸዋ!» አሉ የሔዋን አባት የሸዋዬ ቁጭት መነሻው የሔዋን መጎሳቆል መስሏቸው።
«ለመሆኑ ያምሻል?» ስትል ሸዋዬ ሔዋንን ጠየቀቻት፡፡
«እል አልፎ ልቢን ያመኛል::
👍51
«ተመርምረሻል?»
«አዎ! መድሃኒትም እየወሰድኩ ነው፡፡»
«ኤዲያ!» አለች ሸዋዬ በመመናጨቅ ዓይነት፡ «ወጉ እንዳይቀር ነው እንጂ ቀድሞ ነበረ ክብረ መንግስት ምን ህክምና አለና!» አለች ውጭ ውጭ እያየች፡፡
«እንደው ደህና ሀኪም የት ይገኝ ይሆን የሸዋ?» አሉ የሔዋን አባት
በዓይንና በቀልባቸው ኤዋንን ስለል እያደረጉ፡፡
«ዘገያችሁ! በጣም ዘገያችሁ!» አለችና ሽዋዬ ከተቀመጠችበት ብድግ እያለች
«ሰው የገዛ ልጁን እፍኖ ይገድላል እንዴ?» ብላ በጓሮ በር በኩል ወጣች፡፡
የናፈቃትን የወላጆቿን ጓሮ ለመጎብኘት ነበር፡፡ ውስጥ ውስጡን ስትዘዋወር አስራት
የነገራትን የሔዋንን የዛፍ ስር መዋያ መደብ አይታ በጣምም ተገረመች።
የሔዋን እናትና ከቤታቸው ሲገቡ
ዓይናቸው በመጀመርያ ያረፈው
በሚያብረቀርቀው የሸዋዬ ተሽከርካሪ ሻንጣ ላይ ነው። ዋናው መልኩ ጥቁር ሆኖ
የፍሬሙ፡ ብረት ከሩቅ ያበራል፡፡ «ማ መጣ?» አሉ ገና በር ላይ ብቅ ብለው ፊት ለፊት መደብ ላይ ያን የልብስ ሻንጣ ሲያዩት፡፡
«የሽዋ መጣች እኮ ስንዴ!» አሏቸው የሔዋን አባት እሳቸውም ያንኑ ሻንጣ እንደገና እየተመለከቱ፡፡ የሔዋን እናት ወደ ቤት ገባ ብለው በግራ በኩል አየት
ሲያደርጉ አስራት ቁጭ ብሎ ፈገግ እያለ ያያቸዋል።
«ይዘሃት መጣህ እንዴ እስራቴ?» አሉና ለአራት ቀናትም ቢሆን
ተለይተውታልና ሊስሙት ጠጋ አሉ የገና እና የጥምቀት ልብስ አስገዛታለሁ ብለህ ሄደህ ራሷን ይዘህ ምጥት!» እያሉ ይስሙት ጀመር። ይህ ዘዴ የአስራት ወደ
ዲላ መሄጃ ሰበቡ ተደርጎ ለሔዋን ሲነገር የሰነበተ ነበር። «የታለች ታዲያ?» ሲሉ እንደገና ጠይቀው ገና መልስ ሳይስጣቸው ራሷ ሸዋዬ በጓዳ በር በኩል ብቅ አለች፡፡ የማይቀረው የእናትና ልጅ የናፍቆት ስሞሽና ጥይይቅ ተፈፀመ።
የዋናው ጉዳይ ውይይት የተጀመረው ማታ እራት ተበልቶ አብቅቶ ቡና እየተፈላና ሽዋዬ በሻንጣዋ ወስጥ ያጨቀቻቸውን የስጦታ ልብሶች ለየተመደበላቸው
ሰዎች ማደል ስትጀምር ነው፡፡ በመጀመሪያ ለአባትና ለእናቷ የገዛቻቸውን ነጠላና ኩታ እንዲሁም በልክ ተሰፍቶ የሚለበስ ብትን ጨርቅ አደለቻቸው፡፡ ለሔዋን ደግሞ
የተዘጋጀ ጉርድ ቀሚስና ማላበሻዎች እንዲሁም አረንጓዴ ዓይነት ስካርፍ ሰጠቻት፡፡
ማሰሪያውን ጨምሮ በወርቅማ ቀለም ቅብ የሚያብረቀርቅ የእጅ ሰዓት ከእጅ ቦርሳ ውስጥ አወጣችና በሔዋን ግራ እጅ ላይ ማሰር ጀመረች፡፡
በሁኔታው የተደነቁ እናቷ “ታዲያ እኮ ለእሙዩ ያረግሽው ብቻ በቂ ነበር የሸዋ! ለኛ ምን አሳሰበሽ?» አሉ ፈገግ ብለው ልጆቻቸውን ተራ በተራ እያዩ።
“ከሆነማ ቅድሚያ ለእናንተ ነው፡፡ ሔዩ ልጅ ስለሆነች ገና ብዙ
ይደረግላታል፡፡ እናንተ ግን አሮጊትና ሽማግሌ ስለሆናችሁ…» ብላ ነገሯን ሳትጨርስ ኪ ኪ ኪ ኪ ብላ ሳቀች።
እናንተ ሲያምርባችሁ እኮ እኛ እንዋባለን፡፡» አሉ አቶ ተስፋዩ በተራቸው።
«ኧረ እኔ በጣም ያሳሰበኝ የሔዩ የልብ ህመም ነው::» አለችና ሸዋዬ በተለይ ወደ እናቷ በማተኮር ለመሆኑ ታስባለች? ትጨነቃለች?» ስትል ጠየቀቻቸው።
«ኧረ እሷ እቴ ደሞ እኔ እናቷ እያለሁ የምን ሀሳብ የምንስ ጭንቀት?»
«ታዲያ እንዴት ጀመራት?»
«እንደው ተሜዳ::>
«ታዲያ ዲላ ሆስፒታል መኖሩን አታውቁም ወይስ…» ብላ ሸዋዬ ሁሉንም አየት አየት ስታደርጋቸው የሔዋን አባት ቀጠሉ፡፡
«ተተመካከሩበት አሁንም ይደርሳል፡፡»
ሔዋን ግን ወደ መሬት አቀርቅራ ዝም አለች::
«ታውቂ ኖሯል እመዬ?» ሲሉ እናቷ ጠየቋት፡ እሳቸውም የሚያውቁ
ቢሆንም ስሜቷን መሰለያ መንገድ መፈለጋቸው ነበር
«አዎ፡፡» አለች ሔዋን አሁንም እንዳቀረቀረች፡፡
«ታዲያ ዝም ብለሽ መሞት ፈለግሽ?» ስትል ሸዋዬ ቆጣ ብላ ጠየቀቻት፡
«እኔ ሀኪም እያድነኝም፡፡» አለች ሔዋን እንዳቀረቀረች፡፡
«እናስ? ጠንቋይታ» አለች ሸዋዬ በፌዝ አነጋገር።
«እስቲ እሙዬ ከእህትሽ ጋር ረጋ ብላችሁ ተመካከሩ» አሉ የሔዋን እናት ጭንቅ ጥብብ እያላቸው:: ሔዋን አቀርቅራ ዝም ስትል ልባቸው ፈራ።
«ሔዋኔ» ሲሉ ጠሯት አባቷ።
«አቤት»
«የሸዋ የምትለውን ተቀብለሽ መሞከሩ ይሻላል። ታልሆነ ታልሆነ የአባትና የእናታሽን መደብ የሚከለክልሽ የለም የኔ ልጅ! ይኸን ነገር ችላ አትበይው፡፡»
«ምናልባት እንደዚ ቀደሙ የት ወጣሽ? የት ገባሽ? የምልሽ መስሎሽ እየሰጋሽ ይሆን?» አለችና ሽዋዬ አሁንም ቀጥላ ያኔ እኮ ተማሪ ስለሆንሽ እንዳትዘናጊ ነው። ጭራሽ ዝም ካልኩሽ መረን እንዳትሄጂ ያታላቅነቴን ከአንገት
በላይ ቆጣ ማለት እንዳለብኝ በማመን ነበር።" አለችና ሽዋዩ ወደ እናቷ አየት እያረገች እንደዚያ “ማድረግ አልነበረብንም እማዬ?» ስትል ጠየቀቻቸው፡፡
«እንዲታ ልጄ! እንዴታ!» በማለት የሽዋዬን አነጋገር ያደነቁ ከመስሉ በኋላ «ምናልባት የልጅ ነገር ሆኖባት ሳታውቀው ቅሬታ ተሰምቷት ይመስለኛል።»አሉ
ሸረፍ አድርገው ሔዋንን እየተመለከቷት።
«ዛሬ ግን በፈለገችው ሠዓት ወደ ፈስገችው ቦታ ብትሂድ በሰላም መመለሷን ከመመኘት በቀር ማን ይጠይቃታል።» አለች ሸዋዬ ፈገግ ባለ ሁኔታ
«ተእንግዲህ ወዲያ እሷስ ሴትዮ እየሆነች እይደል!» አሉና የሔዋን እናት ብትሄድም እኮ ወደነዚያ ታፈሡና በልሁ ወደሚባሉ ልጆች ነው፣ ሌላ የት ትሄዳናለች አሉ የሔዋንንም የሽዋዩንም አስተያየት ለመሰለል ፈልገው።
«እንኳን እነሱ ጋ የትም ትሂድ አልኩሽ እማዬ! ቀና ብዬ ላላያት ለእሷም ለእናንተም ቃል እገባለሁ!» አለች ሽዋዬ በተለይ እናቷን እያየች።
ሔዋን ድንገት ቀና አለችና በተለይ ሸዋዬን ትኩር ብላ ትመለከታት
ጀመር:: የሽዋዩን ንግግር ደግማ ደጋግማ ከጆርዋ ላይ ትፈልገው ጀመር፡፡ ግን ደግሞ ማመኑም የቸገራት ትመስላለች ።
«ትጠራጠሪያለሽ ሔዋን» አለቻት ሽዋዬ ሔዋንን አየት እያረገች፡፡
ሔዋን መልስ ሳትሰጥ ወደ መሬት አቀረቀረች፡፡
«እሙዬ ፣ እህትሽን አነጋግሪያታ!» አሉ እናቷ።
«በርታ በርታ በይ ሔዋኔ!» አሉ አባቷ በበኩላቸው።
«የመጣሁት መታመምሽን ሰምቼ በችኮላ ነው፡፡ ፈቃድ እንኳ ስላላገኘሁ ነገውኑ እመለሳለሁና ቁርጡን ንገሪኝ፡፡» አለች ሽዋዬ በሔዋን ላይ አተኩራ::
በዚህ ጊዜ የሔዋን እናት ድንገት ብድግ አሉና ወደ ሽዋዬ ጠጋ አሉ፡፡ ጡታቸውን አወጡና «በይ የሽዋ፣ እሙዬ ዲላ ሄዳ ከእነዚያ ልጆች ጋር መገናኘት ብትፈልግ ላትከለክያት በጠባሽው ጡት ቃል ግቢልኝ::» አሏት።
ሸዋዬ የእናቷን ጡት በእጁ ነካ አድርጋ መልሳ እጇን እየሳመች «ይኸው» አለች። «እልልልል….!» አሉ እናቷ፡፡......

💫ይቀጥላል💫
👍15
#ምንትዋብ


#ክፍል_ሀያ_ሁለት


#ድርሰት_በሕይወት_ተፈራ

“ይደልዎ ይደልዎ”

ምንትዋብ፣ ኢያሱ በነገሠ በሁለተኛው ወር ረጅም ነጭ ሐር ቀሚስ ለብሳ፣ በወርቅና በዕንቁ የተንቆጠቆጠ ካባ በላዩ ላይ ደርባ፣ በወርቅ አጊጣ፣ ፊቷን በነጭ ዐይነ ርግብ ከልላ፣ የወርቅ በትረ መንግሥት ጨብጣና ከወርቅ የተሠራ ነጠላ ጫማ ተጫምታ ተሸልማ በወጣችው
በቅሎዋ ላይ ተሰይማ፣ የንግሥ ሥርዐት ወደሚፈጸምበት ወደ መናገሻ ግንብ አመራች።

መናገሻ ግንብ ውስጥ መሣፍንት፣ መኳንንት፣ አዛዦች፣ ካህናት፣ ሊቃውንትና ወይዛዝርት
እንደየማዕረጋቸው ቦታቸውን ይዘው የንጉሥ መሞት የሚያመጣውን ቀውስ ጠንቅቃ
የምታውቀው ምንትዋብ፣ አክሱም ጽዮን የሚደረገውን ሁለተኛውን
የኢያሱን የንግሥ ሥርዐት አስቀርታ በነገሠ በወሩ ብርሃን ሰገድ የሚል ስመ መንግሥት ከተሰጠው ከዳግማዊ ኢያሱና ከቤተሰቦቿ ጋር ስትገባ ሁሉ ተነሥቶ እጅ ነሳ።

በወርቅ ያጌጠውን የአባቱን ዘውድ የጫነውና የእሳቸውን የወርቅ
በትረ መንግሥት የጨበጠው ብርሃን ሰገድ ኢያሱ ከተቀመጠበት ተነስቶ፣ “እናቴን አንግሡልኝ፣ መንግሥቴ ያለሷ አይጠናም” ሲል ተሰብሳቢዎቹ፣ “ይደልዎ ይደልዎ! ይገባታል! ይገባታል! ጎበዝ ክርስቲያን፣ አዋቂ ናት። ሽህ ዓመት ንገሥ። የቆስጦንጢኖስን ምሽት
እሌኒን ትመስላታለች” አሉ።
አንጋሹ ጽራግ ማሰሬ ማሞ ከዕንቁ፣ ከወርቅና ከብር የተሠራውንና በሻሽ ተሸፍኖ ጠረጴዛ ላይ የተቀመጠውን የአፄ ሚናስ የነበረውን ዘውድ አንስተው ምንትዋብ ራስ ላይ ጭነውላት ሲያበቁ ዝቅ ብለው ሰገዱላት፣ ከኢያሱ ቀኝም አስቀመጧት።

ባራኪው እልፍዮስ፣ “እዝጊሃር ክፉዎችን እንዲያሸንፉ ኃይል ይስጥዎ። ክብርዎን ያብዛልዎ። ፈሪሐ እዝጊሃርን በልብዎ ያሳድርልዎ። አቤቱ አምላካችን ሆይ! በአገልጋይህ በእቴጌ ምንትዋብ ላይ እኼን የደስታና
የክብር ዘውድ አኑር፤ እኼውም የቸርነት፣ የርህራሄ፣ የዕውቀትና የጥበብ ዘውድ ይሁንላቸው” ብሎ ሲባርካት፣ ከኋላዋ ቆመው የነበሩት ሴት የመሣፍንት ዘሮችና ወይዛዝርት ዕልልታውን አቀለጡት።

ምንትዋብ ለአምላኳ በልቧ ምስጋና አቀረበች።

ካህናት ዘመሩ፣ ወረቡ፣ ሊቃውንቱ ቅኔ አወረዱ። እንደ ንግሥተ
ሳባ፣ እቴጌ እሌኒ፣ እቴጌ ሰብለወንጌልና እቴጌ መስቀል ክብራን የመሳሰሉ የታላላቅ ሴቶች ስም እየጠቀሱ አሞካሿት። “አንቺ እሌኒ ማለት ነሽ። ልዥሸን ብርሃን ሰገድ ኢያሱን ኸጎኑ ሁነሽ እንደምትረጂው አንጠራጠርም” ሲሉ እሷ ላይ ያላቸውን ሙሉ እምነት ገለፁላት።
ምንትዋብ፣ አባቷ ዕጣ ፈንታ፣ እናቷ ዕድል አያቷ ግን የተገባት ያሉትን ስትጎናፀፍ ተስተዋለ።

ሕይወት ሲሻት ለጋሥ መሆኗን አስመሰከረች።

ባለ ክራሩና ባለ መሰንቆው የውዳሴና የሙገሳ ግጥም ሲያንቆረቁር፣ፎካሪው በቀረርቶ፣ ሽላዩ በሽለላ የበኩሉን ምስጋና አበረከተ። አንዱ ሀሚና ተነሰቶ በመሰንቆ፣

በወለተጴጥሮስ ተወልዳ በንግርት፣

በእዝጊሄር ፈቃድ በነብያት ትንቢት፤

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ያገራችን ውበት፤

የምታስተባብር ጥድቅ ተሃይማኖት፣

ዳር ድንበር ጠባቂ ያባቶቿን ርስት፣

ኸዝኸ በላይ ጠጋ ኻአምላክ መሰጠት፣

ምንድን ሊሰጧት ነው ምንትዋብ ሚሏት?

እያለ ሲያሞግሳት፣ የተሰበሰበው ሰው ደግሞ እሱን አመሰገነው።
ነጋሪት እየተጎሰመ፣ መለከት እየተነፋ ከመናገሻ ግንብ በደጅ
አጋፋሪው አቀናባሪነት የፊቱን ወጀብ ሰንደቅ የያዙ፣ የእልፍኝ አሽከሮች፣ባለሟሎችና ሠይፈ ጃግሬዎች ፈንጠር ብለው እየመሩ፣ የመሃል ዐጀቡ
በእልፍኝ አስከልካዩ እየተጠበቀ፣ ኢያሱና ምንትዋብ ጎን ለጎን ሆነው
ድባብ ተይዞላቸው፣ መሣፍንት፣ መኳንንት፣ ሊቃውንት፣ ወይዛዝርት፣ግራዝማቾች፣ ቀኛዝማቾችና የጦር አበጋዞች እንደየደረጃቸው ከኋላ
እያጀቧቸው፣ ሰልፍ አስከባሪዎቹና የንጉሠ ነገሥቱ ጠባቂ የሆኑት ጋሻዐጃግሬዎቹ ተከትለው የሰልፉን ግራና ቀኝ አንጋቾች እየጠበቁ ራስ ቢትወደዱ በመጨረሻ ተሰልፈው ነገሥታቱ በዘፈንና በጭፈራ ከግቢ
ሲወጡ ካህናት፣

መንክር ግርማ መንክር ግርማ

ወልደልዑል ጸለላ መንክር ግርማ

የምትደንቅ ግርማ ሞገስን

የምትደንቅ ግርማ ሞገስ

የወልደልዑል ልጅ፣ እጅግ የላቀው አባት ልጅ፤

እያሉ፣ ምንትዋብ በወንድሟ በወልደልዑል መከታነት መንገሧን
በቅኔ ጠቅ እያደረጉ በፀናፅልና በከበሮ ዐጀቧት።
ዘውዷን እንደጫነች በቅሎዋ ላይ ተሰይማና ታጅባ፣ ወደ ሕዝቡ
አመራች። ከጐንደርና ከአካባቢዋ የመጣው ነፍጠኛ፣ ገበሬ፣ እረኛ፣
ነጋዴ፣ ወታደር፣ አንጥረኛ፣ ሸማኔ፣ ቆዳ አልፊ፣ ጥልፍ ጠላፊ፣ ሹሩባ ሠሪ መድኃኒት አዋቂ፣ ወጌሻ፣ የቤት እመቤት፣ አረቄና ጠላ ሻጭ፣ ዲያቆን ተማሪ ፣ የቁም ጸሐፊ፣ ሠዓሊ፣ ብራና ሠሪ፣ ባለክራሩና ባለመሰንቆው
ሴቱ ሹሩባውን አንዠርጎ፣ ነጠላውን አጣፍቶ፣ ወገቡን በድግ ደግፎ ማተቡ ላይ የእንጨት መስቀሉን፣ ድሪውን፣ ጨሌውን፣ ዶቃውን ቁርጭምጭሚቱ ዙርያ አልቦውን፣ የእጁ አንጓ ላይ አንባሩን ደርድሮ ገሚሱ የቀርከሀ ጃንጥላውን አጥልቶ፣ ወንዱ ፀጉሩን አጎፍሮ፣ ለምዱን ደርቦ፣ ዱላውን ትከሻው ላይ ጣል አድርጎ፣ ልጆች ጥብቋቸውን
አጥልቀው፣ ክታባቸውን አንጠልጥለው ምንትዋብ ከኢያሱ ጋር ጃን ተከል ብቅ ስትል አካባቢው ድብልቅልቁ ወጣ።

ሴቶች በዕልልታና በእስክስታ፣ ወንዶች በሆታና በጭፈራ አካባቢውን አናጉት፤ ካህናት በሽብሸባ አደመቁት። እነምንትዋብ ካለፉ በኋላ፣
ሕዝቡ መስመሩን ተከትሎ እየሮጠ ዕልል! ሆ! እያለ ዐጀባቸው።

ጐንደሬዎች እንደዛ ውበት የነገሠበት ሰው አይተው አያውቁምና በምንትዋብ ውበት ተደመሙ። “አቤት መልኳ እንደ ጠሐይ ሚያበራ አቤት ወርቅ አካል!” እያሉ ተደነቁ። በደስታ ተሳክረው ለአፄ ፋሲለደስ፣

አሁን ወጣ ጀንበር

ተደብቆ ነበር

ተብሎ እንደተዘፈነው ሁሉ ለእርሷም፣

አሁን ወጣች ጀንበር

ተሸሽጋ ነበር

እያሉ አዜሙ፤ ጨፈሩ።

አሁን ወጣች ጨረቃ፣
የምትለን ፍርድ ይብቃ።

ደስ ይበልህ ዘመድ፣
ከነገሠች በዘውድ።

ደስ ይበልሽ ወይዘሮ፣
ጭና መጣች ወገሮ።

ደስ ይበልህ ባለእጌ፤
ነገሠች እቴጌ።

ደስ ይበልህ ጐንደር፤
ቀድሞ ከፍቶህ ነበር፣

ሲሉ ጐንደሬዎች ለውዷ ከተማቸው መልካሙን ተመኙላት።

ምንትዋብ የተስፋ ጨረር ፈነጠቀችላቸው።

ዐዲስ ንጉሥ በመጣ ቁጥር የተስፋ ስንቅ ሰንቆ የሚወጣው
መልካሙን ተመኘ ለጦርነት ሳይዳረግ፣ በወታደር ሳይዘረፍ፣ ሚስቱና ልጁ ሳይደፈሩ እኖራለሁ በሚል ተስፋ፣ ከትናንቱ ዛሬ ይሻለኝ ይሆን በሚል ምኞት።

ጐንደሬዎች ምንትዋብን ወደዷት፤ ቀልቧ ገዛቸው፤ መልኳ
አባበላቸው፤ ግርማ ሞገሷ ማረካቸው፣ ኩራታቸው በእሷ ሆነ። በዓለ ንግሥናዋን አደመቁላት፤ ዐደራቸውን ሰጧት፤ ተስፋቸውን ልባቸው ጫፍ ላይ አንጠልጥለው ፎከሩላት፤ ሽለሉላት፤ ዘፈኑላት፤ ጨፈሩላት፤
ዕልል! ሆ! አሉላት።

ጥላዬ፣ ከእነአብርሃ ጋር ከካህናቱ ኋላ ሆኖ አብሮ እየዘመረ ሲሄድ
ድንገት ምንትዋብን ከኢያሱ ጋር አያት። የለበሰችው ነጭ ሐር ቀሚስ፣ፊቷን የጋረደው ነጭ ዐይነርግብ ከፀሐይዋ ብርሃን ጋር ተደምሮ ዐይኑ ላይ አንፀባረቀበት። ያየውን ሁሉ ማመን አቃተው። የባሏ ለቅሶ ላይ አዝኖላት እንባውን እንደረጨላት ሁሉ አሁን የያዘውን የደስታ ሲቃ መቆጣጠር አቃተው። እንባው ፊቱን አራሰው። እነአብርሃ እንባውን እንዳያዩበት በሰዉ መሃል ተሸለክልኮ ወጥቶ “ኸንግዲህ ደብረ ወርቅ ብመለስም አይቆጨኝ” ብሎ ወደ ቤት ሄደ።
👍16