ዐውደ ምሕረት
3.66K subscribers
932 photos
24 videos
271 files
195 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
#ሰኞ
#መርገመ_በለስ እና #አንጾሖተ_ቤተ መቅደስ

‹‹ያቺ በለስ ጌታ ወደርሷ ከመምጣቱ በፊት ለምልማ ቅጠል አውጥታ ነበር››
#ቅ/ዮሐንስ_አፈወርቅ

#በማለዳ(ሲነጋ) ወደ ከተማ(ሀገር) መጣ ሲል:- ጌታችን አዳም ወደ ወደቀበት ስፍራ ወደዚያ ሀገር መጣ፤ያን ጊዜም ተራበ መራቡም እንጀራና ሕብስትን ሳይሆን ስለ ሰው ድኅነት ተራበ ራሱ በወንጌልም ሲናገር ‹‹የእኔስ መብል የላከኝን የአባቴን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ነው እናንተም በላከኝ በአባቴ ታምኑ ዘንድ ነው ››ዮሐ4፤34 ፤ክርስቶስ ወደ ዓለም ሲመጣ እንደ ማለዳ ጸሐይ ነው (የቀትርም የአመሻሽም ያይደለ) የማለዳ ጸሐይ ጨለማውን ገፎ ነው የሚመጣው ክርስቶስም ጨለማ የተባለ ክፉ ከይሲ ዲያብሎስን በጽንሰቱ ድል እየነሳው ተገለጠ፤የማለዳ ጸሐይ እንደ ቀትር ፀሐይ አይፋጅም አይለበልብም ክርስቶስም ለዓለሙ ተመጥኖ የሕይወት ብርሃን ሆኖ ከመዓቱ ምሕረቱ የቀረበ ሆኖ የተገለጠ ነው፡፡ጌታችን በወንጌሉም “የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ የሚከተሉኝ የሕይወት ብርሃንን ያገኛል እንጂ በጨለማ ውስጥ አይመላለስም “ዮሐ8፤12 ሲል በቃሉትምህርት በተአምራቱ በደሙ ፈሳሽነት በብዙ ወገን ድኅነተ-ብርሃኑን ሊሰጠን በመምጣቱ ነው፡፡ ፀሐይ ለሁለቱም እኩል ታበራለች ስለርሷ ብርሃንነት ራሷም ትመሰክራለች ሆኖም ግን ጸሐይን ማየት የተሳነው ሕልውናዋን አይረዳም እንዲሁ ክርስቶስም ጸሐይ ሆኖ ለእስራኤል ቢመጣ ፀሐይነቱን ተረድተው ለሞቁት ለሰውነታቸው ኃይልን ለልብ ዓይናቸው ማየትን የሰጠ ነው፡፡
#የበለስ_ፍሬ ፡- የተባሉ ጉባኤ አይሁድ (ቤተ አይሁድ) ናቸው፤ጌታችንም የሃይማኖት ፍሬ ፈልጎባቸው ቢመጣ ከመጽሐፍተ ኦሪት ከነቢያት በቀር አላገኘም ፤የተጻፈውን በተግባር ፍሬ አልተመለከተባቸውም፡፡ ያንጊዜም ረገማት ቤተ አይሁድም ክርስቶስን ባለማመናቸው በኋላም እንደ ወንበዴ በመስቀላቸው ርግማንን አትርፈዋል፡፡ነገር ግን አይሁዳውያን ቢረገሙም እነርሱን ያልመሰሉትን ቀትቷቸዋል ማለት አይደለም፡፡ምክንያቱም ከቤተ አይሁድ እስጢፋኖስን የመሰለ ሰማዕት ተገኝቷል፤እነ ቅዱስ ጳውሎስን የመሰለ ሐዋርያም ተገኝቷል ‹‹ በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ ከእስራኤል ትውልድ ከብንያም ወገን ከዕብራውያን ዕብራዊ ኝ ስለ ሕግ ብትጠይቁ ፈሪሳዊ ነበርሁ›› #ፊል3፤5

#የበለስ_ፍሬ :- ጌታችን የረገማት በለስ አዳምና ሔዋንን የጣለች ዕጸ በለስ ናት፤ጌታም ለዘላለም ፍሬ አይገኝብሽ ማለት በሰው ላይ አትሰልጥኚ ብሎ ፍዳ መርገምን እንዳጠፋት አስረዳን፡፡ በርግጥ ፍዳ መርገሙን የፈጸመው በጽንሰት ጀምሮ በስቅለት ነው፡፡ በለስ ፍሬ የተባለ በሰው ላይ ሰልጥኖ የነበረ ምልዓተ ኃጢአት ነው መጽሐፍት ኃጢአትን በለስ ይሏታል፤ምክንያቱም የበለስ ቅጠል ሰፊ ደስ የምታሰኝ ናት እንዲሁም የኃጢአት መንገድ ወደ ጥፋት የምትወስድ ሰፊ በር ናት፤የበለስ ፍሬ በመብላትና በማላመጥ ጊዜ ጣፋጭ ናት እንዲሁ ኃጢአት ሲሠርዋት ደስ ታሰኛለች ከሠርዋት በኋላ ግን መከራ ታመጣለች በሚሠርዋት ጊዜ ጣፋጭ ከሠርዋት በኋላ ግን መራራ ናት፡፡ አዳምና ሔዋንም ለጊዜው በለሷ ጣፋጭና ውብ ሆና ታየቻቸው በውሃላ ግን መራራ ሞት አመጣችባቸው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ከአመንዝራ ሴት ከንፈር ማር ይንጠባጠባልና አፍዋም ከቅ የለሰለሰ ነውና ፍጻሜዋ ግን እንደ እሬት የመረረ ነው ሁለት አፍ እንዳው ሰይም የተሳለ ነው እግሮችዋ ወደ ሞት ይወርዳሉ አረማመድዋም ወደ ሲዖል ነው›› #ምሳ5፤3-5 ማርን በቀመስናት ጊጊ ለአፍና ለጉሮሮ ጣፋጭ ናት ከዚያ በውሃላ ግን የሚጎዳ መራራ ሆኖ እናገኘዋለን፤አመንዝራም ሴት አንደበተ ለስላሳ ናት ከማር ከስኳር የሚጣፍጥ ነገርን ትናገርሃለች ወዲያውኑ መራራ ሞትም ከእርሷ ያገኝሃል ሲል ነው፡፡ አርዌ ምድር እባብም(ሰይጣን ተዋሕዷት) ሔዋንን ስትናገራት አንደበቷ የጣፈጠ ነበር፤በሽንገላዋ ግን መራራ ነበረች፡፡

#የበለስ ፍሬ:- የተባለ አዳም የበለስ ፍሬ ከበላ በውሃላ ፈርቶ የተሸሸገባት የበለስ ቅጠል ናት፡፡ ‹‹የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ እነርሱም ዕራቁታቸውን እንደሆኑ አወቁ የበለስንም ቅጠሎች ሰፍተው ለእነርሱ ለራሳቸው ግልድ አደረጉ›› ዘፍ3፤7 አዳምና ሔዋን ፈርተው የተሸሸጉበት በለስ አስቀድሞ ዕጸ በለስን የቀጠፉባስ ዛፍ ቅጠል ነው፡፡

ነገር ግን በዚህ ቅጠል ይሸፈን ዘንድ የቁርበት ልብስ አለበሳቸው ፡፡ ጌታችን ያደረቃት በለስ ይህቺ አዳምና ሔዋን ተሸሽገውባት የነበረችውን ምክንያተ ፍዳ ወመርገም የሆነችውን ነው፡፡ ሊቁ አፈወርቅ ዕደ ወርቅ ዮሐንስ ‹‹አዳም በገነት ዕርቃኑን ሆኖ ሳለ በየትኛው ቅጠል ነበር መሸፈኛ ሰፍቶ ዕርቃኑን የሸፈነ ይህች ቅጠል እንዴት እንደደረቀች አየህን አዳም የለበሳት ዕርቃኑን የሸፈነባት አይደለችምን ጌታ ኢየሱስ ወደ ለመለመችው ዛፍ መጥቶ አዳም ዕርቃን የሸፈነባትን ቅጠል በቃ አደረቃት አዳምን ድኃ ሁኖ ስለዘገኘው ንጹሕ የሆነ የብርሃንንም
ልብስ ሰጠው ይኸውም ብርሃን ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ የተሰራ ነው ፤የበለስን ቅጠል አድርቆ የነፍስን ድኅነት ሰጠው ተድላ ደስታ ባለባት ገነት ፍጹም የሆነ የተድላ ደስታ ልብስ ተጎናጽፎ እንደ መላእክት ሕያው ሁኖ ሲኖር ከይሲ ያሳተችው አዳምን እንዴት እንደዳነ አስባለሁ›› #ግብረ_ሕማማት ገጽ 163/164 ቁ.ጀ50-54
#ፍሬ_ግን_አላገኘባትም
________________
ወንጌሉ እንዳስቀመጠው ጊዜው የፍሬ ወር አልነበረም;ለምስጢሩ ግን ወዲያውኑም ደረቀች ሲል ደግሞ ለዘመናት የሰለጠነ ፍዳ መርገም ሞት ዲያብሎስ ጠፋ ተሸረ ሲል ነው፡፡ #ኛ_ቆሮ 15÷55 ‹‹ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ፤ሲዖል ሆይ ድል መንሳትህ የት አለ››የሚለው ተፈጸመ፤ምክንያቱም አስቀድሞ በትንቢት ተነግሮ ነበርና ‹‹ከሲዖል እጅ እታደጋቸዋለሁ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ ሞት ሆይ ቸነፈርህ ወዴት አለ ሲዖል ሆይ ማጥፋትህ ወዴት አለ ርኅራኄ ከዓይኔ ተሰወረች›› #ት.ሆሴዕ 13፤14 ክርስቶስ በሰው ላይ የሰለጠኑ ክፉ በለሶችን አድርቆ አጥፍቶልናል ይህንንም ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹‹መጥቶም ፍትወታት እያትን ኃጣውዕ ርኩሳንን አጠፋ ሁከቱን ጸጥ አደረገ ዕጸ በለስንም አድርቆ
ብሩህ በሆነ ሕይወት በሃይማኖት የበቀለውን ዕጸ መስቀል ተከለልን ›› #ግብረ_ሕማማት ገጽ 167 ቁ.104 በበለስ የመጣውንም ርግማን በዕጸ መስቀሉ ድል ነሳው ፤በለሷን ሲረግም በአንጻሩ በለስ ዕጸ መስቀልን ተከለልን፡፡
#ይህ_የከበረ የተዘረጋ መስቀል ሥሩ በምድር ጫፉ በሰማይ ያለ ቅጠሉ የማይረግፍ አበባው ለጥፋት ፍሬው ለሞት ያልሆነ ነው፡፡ባለ በገናው ነቢዩ ዳዊትም ‹‹ወይከውን ከመዕጽ እንተ ትክልት ኅበ ሙሐዘ ማይ እንተ ትሁብ ፍሬሃ በበጊዜሃ ወቁጽላኒ ኢይትነገፍ -በውኃ ዳር የተተከለ በየጊዜው ፍሬውን የሚሰጥ ቅጠሉም የማይረግፍ ›› #መዝ1÷3 ክርስቶስ በዕጸ መስቀሉ ክፉ በለስ የተባሉ ዲያብሎስና ሠራዊቱን የቀጣበት ፤ዛሬም ለሚያምኑበት ወደ ሰማይ የሚያወጣ መሰላል ነው፡፡ይቺ ዕለትም መርገመ በለስ ተብላለች

#ከዚህ ቀጥሎ ወደ ቤተ መቅደስ ሔደ፤ ቤተ መቅደስ ቤተ ጸሎት፣ ቤተ መሥዋዕት መሆኑ ቀርቶ ቤተ ምሥያጥ /የንግድ ቤት/ ሆኖ ቢያገኘው፤ «ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች… እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት» ማቴ. 21፤13 ብሎ የሚሸጡበትን ሁሉ ገለበጠባቸዉ፣ ገርፎም አስወጣቸዉ፣ ይህም የሚያሳየዉ ማደሪያው ቤቱ የነበርን እኛ የአዳም ልጆች ኃጢአት ሰፍኖብን ስንኖር ቢያገኘን ኃጢአታ ችንን ሁሉ እንዳራቀልን
............ #ይቆየን ..........
ግብሐት :- ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሰ/ት ቤት ሰሌዳ መጽሔት
#ዐውደ_ምሕረት_የእናንተ
አ.አ ኢትዮጵያ
ሚያዝያ ፲ ፰ / ፳ ፲ ፻ ፲ ፫ ዓ.ም
#ማግስተ_ሰኞ /ማክሰኞ/ #የጥያቄ_ቀን

#እኔም_ይህን_በምን_ሥልጣን_እደማደርግ አልነግራችሁም "
_________________________________
በማቴዎስ ወንጌል ፳፩፥፳፰፤ ፳፭፥፵፮፤ ማርቆስ ወንጌል ፲፪፥፲፪፤ ፲፫፥፴፯፤ በሉቃስ ወንጌል
፳፥፱፤ ፳፩፥፴፰ የሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ማክሰኞ ዕለት የሚነገሩ ትምህርቶችን
ይዘዋል፡፡ በዚህ ዕለት ጌታችን በቤተ መቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረ ዕለቱ
‹የትምህርት ቀን› ይባላል፡፡ ክርስቲያን የኾነ ዅሉ ከሥጋዊ ነገር ርቆ በዚህ ሰሞን
የሃይማኖት ትምህርት ሲማር፣ ሲጠይቅ መሰንበቱ መጽሐፋዊ ሥርዓት ነው፡፡
በዚህ ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሥልጣኑ ተጠይቋል፡፡ ጠያቂዎቹ
የካህናት አለቆችና የሕዝብ አለቆች ሲኾኑ፣ ጥያቄውም፡- ‹‹በማን ሥልጣንእነዚህን
ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን የሰጠህማነው?›› የሚል ነበር፡፡ ይህ ጥያቄ ጌታችን ሰኞ
ዕለት ሁለት ነገሮችን ማከናወኑን ተከትሎ የተነሣ ጥያቄ ነው፡፡ ይኸውም ጌታችን
ሲያደርጋቸው የነበሩ ተአምራትና ድንቅ ድንቅ ሥራዎች የካህናት አለቆችን ስላስቀኗቸው
ጌታችንን ከሮማ መንግሥት ባለ ሥልጣናት ጋር ለማጋጨት የቀየሱት ስልት ነው፡፡ ጌታችን
በቤተ መቅደስ የነበሩትን ነጋዴዎችን አባሯል፤ መደባቸውን ገለባብጧል፡፡ ነጋዴን ማባረርና
መደብን ማስለቀቅ መንግሥታዊ ሥራ ነው፡፡ ጌታችን ‹‹በራሴ ሥልጣን››ቢላቸው ፀረ
መንግሥት አቋም አለው በማለት ከሮማ መንግሥት ዘንድ ለማሳጣት ነበር ዕቅዳቸው፡፡
ጌታችን ግን የፈሪሳውያንን ጠማማ አሳብ ስለሚያውቅ ‹‹የዮሐንስ ጥምቀት ከየት ነው?
ከሰማይ ነው ወይስከምድር?›› ሲል ጠይቋቸዋል፡፡ ጌታችን ፈሪሳውያን ላቀረቡለት ጥያቄ
ቀጥተኛ ምላሽ አልሰጠም፡፡ ምክንያቱም ጥያቄው ለከሳሾቹ ዓላማ መሳካት አመቺ ኹኔታን
ስለሚፈጥር ጥያቄውን በጥያቄ መልሶላቸዋል፡፡ እነርሱም ‹‹ከሰማይ ነው›› ቢሉት
‹‹ለምንአላመናችሁበትም?›› እንዳይላቸው፤ ‹‹ከሰው ነው››ቢሉት ደግሞ ሕዝቡ ዮሐንስን
እንደ አባት ይፈሩት፣ እንደ መምህር ያከብሩት ነበርና ሕዝቡ እንዳይጣሏቸው ስለፈሩ ‹‹ከወዴት እንደ ኾነ አናውቅም›› ብለው መለሱለት፡፡ እርሱም ‹‹እኔም በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ አልነግራችሁም›› አላቸው፡፡ ይህን ጥያቄ መጠየቃቸውም እርሱ የሚያደርጋቸውን ተግባራት ዅሉ በራሱ ሥልጣን እንዲያደርግ አጥተውት አልነበረም፤ ልቡናቸው በክፋትና በጥርጥር ስለተሞላ ነበር እንጂ፡፡
ዛሬም ቢኾን መልካም ሥራን በሠራን ጊዜ ከልዩ ልዩ ወገኖች የሚመጡ ፈተናዎች
ለመልካም ሥራችን እንቅፋት ሊኾኑ እንደሚችሉ መገንዘብ አለብን፡፡ ብዙ ወገኖች ‹‹ለቅን አሳባችን ለምን ሰዎች ክፉ ነገርይመልሱልናል?›› በማለት ሲጠይቁ ይሰማል፡፡ ለቅን አሳባችን ከዓለም ዘንድ ተቃራኒ ነገር እንደሚጠብቀን ለመረዳት ‹‹ዓለም የሚወደው የገዛ ወገኑን ነው›› የሚለውን የጌታችንን ትምህርት ልብ ይሏል፡፡ በዘመናችን አሳልፈው ሊሰጡን የሚፈልጉ ሰዎች ፈታኝ ጥያቄ እንደሚያቀርቡልንም ከወዲሁ ልንገነዘብ ይገባል፡፡
# ይቆየን !!!
# ዐውደ +ምሕረት_የእናንተ
#ረቡዕ #የምክር_ቀን
" #ምስጉን_ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ"
_______________________
#መዝ 1÷1

ይህ ዕለት የምክር ቀን ይባላል፣ ምክንያቱም የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጻሕፋት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚገባቸው ምክር የጀመሩበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡ ወቅቱ አይሁድ የፋሲካ በዓላቸውን የሚያከብሩበት በመሆኑና ብዙ ሕዝብም በጌታችን ትምህርት የተማረከ ተአምራቱንም የሚያደንቁ ስለነበር ምናልባት ሁከት ይፈጠራል ብለው ሕዝብን እየፈሩ ሊይዙት ያመነቱ ነበር። ተሳክቶላቸው እንያዘው ቢሉ እንኳን ኢየሱስ ክርስቶስን ከደቀ መዛሙርቱ ለይተው አያውቁትም ስለዚህ እርሱን በቅርብ የሚያውቅ ሰው ያስፈልጋቸዋልና በክፉ ምክራቸው እጅግ ተጨነቁ። ትንሽ ቆይቶ ግን ከደቀመዛሙርቱ መካከል አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ በክፉ ምክራቸው በመሳተፍ ጌታን በመሳም አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ቃል ገባላቸው ። ለምልክት ይሁናቸውም ዘንድም እኔ ሄጄ የምስመው ሰው እርሱ ክርስቶስ ነውና ያዙት ብሎ ተማከረ ጭንቀታቸው ተወገደ ለወረታውም ሰላሣ ብር መዘኑለት (ማቴ 26፡1-5 ፣ ማቴ26፡14-15 ፣ ማር 14፡1-2፣ ሉቃ 22፡1-6) 
#ዕለተ_ረቡዕ_መልካም_መዓዛ_ያለው_ቀንም_ይባላል፣ ምክንያቱም ጌታችን በዚህ ዕለት በቤተ ስምዖን ዘለምጽ ተቀምጦ ሳለ መላ ሕይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት (ባለ ሽቶዋ ማርያም) ከእንግዲህ ወዲህ በኅጢዓት ተበላሽቶ ይኖር የነበረውን ሕይወቴን እንደዚህ መልካም ሽቱ የሚያጣፍጥ፣ ኀጢዓትን ይቅር የሚል አምላክ መጣ ስትል ዋጋው እጅግ በጣም ውድ የሆነ ከሦስት መቶ ዲናር በላይ የሚያወጣ፣ በአልባሲጥሮስ ብልቃጥ የሞላ ሽቱ ይዛ በመሄድ በጠጉሩ (በራሱ) ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባቸው ነው፡፡ የእንባ ቀን ይባላል ይህም ስያሜ የተሰጠበት ምክንያት ይህችው ማርያም እንተእፍረት በጌታችን እግር ላይ ተደፍታ መላ ኃጢዓቷን ይቅር እንዲልላት በእንባዋ እግሩን አጥባዋለችና፣ በጠጉሯም በእንባዋ ያጠበችውን እግሩን አብሳዋለችና፡፡ በጠጉሯም ማበሶ አክሊሌ ነክ ስትል ነው ። የማርያም እንተእፍረትን ኃጢዓት ይቅር ብሎ መባዋን የተቀበለ አምላክ ዛሬ በመካከላችን አለና በማንኛውም ጊዜና ሰዓት የራሳችንን ኃጢዓት በማሰብ በማልቀስና የተወደደ መስዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር በማቅረብ በመልካም ሥራዋ ልንመስላት ይገባል፡፡ (ማቴ 26፡6-13 ፣ ሉቃ 7፡36 ፣ ማር 14፡3-9 ፣ ዮሐ 12፡1-8)

...........ይቆየን…..........
#ዐውደ_ምሕረት_የእናንተ
📢ዓውደ ምህረት 🎤


#ዕለተ_ሐሙስ

#ሕፅበተ_ሐሙስ_ይባላል
__________________

በዚህ ዕለት መምህራቸው ሆኖ ሳለ ክርስቶስ በአጭር ታጥቆ አደግድጓ ወገቡን አስሮ የደቀመዛሙርቱን እግር ያጥብ ዘንድ በትህትና ዝቅ አለ:: ቅዱስ ጴጥሮስም እንዴት የእኛን እግር ታጥባለህ አንተኮ ጌታዬ ነኘ ብሎ ላላመታጠብ በትህትና እግሮቹን ሰበሰበ ጌታችንም በጥምቀት አክብሮ ልጅነትን ሊሰጣቸው ወዶ ነበርና ዛሬ ያልታጠበ ከእኔ ጋር ጽዋ ተርታ ዕድል ፍንታ የለውም አለው። ይህን ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ደንግጦ እንደዛማ ከሆነ እንሬን ብቻ ሳይሆን ሰውነቴንም ጭምር እጠበኝ ብሎ ተናገረ ጌታችን ግን እግሩን የታጠበ ሰውነቱ ንፁዕ ነው ነገር ግን ሁላችሁ ንፁዕ አይደላቹሁም አላቸው አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳ በመካከላቸው ነበርና ዮሐ13÷10 ይህን ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ታጠበ::
ይህም የሚያሳየው ከትህትናው ባሸገር የዓለምን ኃጢዓት ለማጠብ የመጣ መሆኑን ነው ‹‹ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘያአትት ኃጢዓተ ዓለም›› የዓለምን አጢኃት የሚስወግድ የእግዚአብሔር በግ ዮሐ 1÷29 እንዲል፡፡ ይህንን ለማስታወስ ዛሬም ካህናት በተለይም ሊቃነ ጳጳሳትና የደብር አስተዳዳሪዎች በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝብህን ኃጢዓት እጠብ ሲሉ በዕለቱ በአጸደ ቤተክርስቲያን የተገኙትን ምዕመናንን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ሲያጥቡያረፍዳሉ፡፡


#የምሥጢር_ቀንም_ይባላል
____________________

ለደቀ መዛሙርቱ ይህ ስለ እናንተ የሚፈሰው ደሜ ነው ይህ ደግሞ ስለ እናንተ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው ብሎ ዕብስቱን ባርኮ ወይኑንም ቀድሶ ለሐዋርያት የሰጠበት ቀን ነው ሐዋርያትም ከእጁ ተቀብለው በልተዋል ጠጥተዋል በዚህም ምስጢረ ቁርባንን ፈጽሞላችዋልና ዕለቲቱ የምስጢር ቀን ተብሎ ይጠራል ። #ማቴ 26÷ 26-28

#ጸሎተ_ሐሙስ_ይባላል
__________________

በፍጥረታት የሚለመንና የሚመሰገን አምላክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለምንና አላዋቂ የሆነውን ሥጋ የተዋሐደ አምላክ፣ ፍጹም ሰው መሆኑን ለመግለጥ አንድም የስጋ ሞት እጅግ አስፈሪ መሆኑን ለማጠየቅና በመከራቹ ጊዜ ወደ ሰማይ አባታችሁ ጸሎትን ጸልዮ ሲል ለአርያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት ድረስ በጌቴ ሰማኔ በአታክልቱ ሥፍራ ሲጸልይ አድሮል በዚህም ዓብይ ምክንያት ይህ ዕለት ጸሎተ ሐሙስ ተብሏል፡፡ (#ማቴ 26፡36-46 ፣ ዮሐ 17)


. ......ይቆየን.........

👇👇👇👇👇👇
@YEAWEDIMERITE
@YEAWEDIMERITE

🎤🎤🎤🎤🎤🎤🎤🎤
📢 @AwediMeherit📢
📢 @AwediMeherit📢
📢📢📢📢📢📢📢📢
"ሰው ሆይ ከሰው ተጠበቅ"
#ማቴ 10÷17

#ዕለቱ_የዕሣዕና ዕለት ነው ! አህያ የያዙ የቤተክርስቲያን ወጣቶች ወደ አንድ ካህን አባት ቀረቡና አባታችን እርሶ እንደ ጌታ አምሳል በአህያዋ ላይ ይቀመጡና በዓለ ሆሣዕናን በምሳሌ ከሕዝቡ ጋር በድምቀት እናክብረው አሏቸው። አባም ዛሬስ እሺ ብዬ ብቀመጥላችሁ ችግር አልነበረውም ግን በሳምንቱ ማንን ስቀለው ስቀለው ልትሉ ነው አሏቸውና በአህያዋ መቀመጥን እንቢ አሏቸው ይባላል። #የዛሬን_ሳይሆን_የነገን አስብ !
#ሁለት ዓሣና አምስት የገብስ እንጀራ አበርክቶ ቢያበላቸው ካላነገስንክ አሉት በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ ሲመጣም "ሆሣዕና በአርያም ለዳዊት ልጅ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው" እያሉ ልብሳቸውን ጭምር በማንጠፍ አመሰገኑት። #ማቴ 21 ÷ 9 በሳምንቱ ጲላጦስ አስሮ ምን ላድርገው ቢላቸው ሕዝቡ ሁሉ " ስቀለው ስቀለው ስለቀው " እያሉ ጮሁ #ሉቃ 23÷21 የሐሰት ከሳሾች ጸሐፍት ፈሪሳዊያንን በጭፍን ተከትለው ሌባ ሌባ ሲባል ሰሙና ሌባ ሌባ ማለት አማራቸው ሳይመረምሩ ምን አጠፋ ሳይሉ ስቀለው ስቀለው እያሉ ጮኹ የኛ የሰው ልጆች መዋደዳችን የቀናት ነው መፋቀራችም ከአንድ ሳምንት አያልፍም ። እናም ሰው ሆይ ከሰው ተጠበቅ! “ነገር ግን ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ በምኩራቦቻቸውም ይገርፉአችኋልና ከሰዎች ተጠበቁ፤” #ማቴ 10፥17 ዛሬ ያጨበጨበልን ነገ ያጨበጭብብናል ፣ ዛሬ የሳቀልን ነገ ይስቅብናል እርሱ ግን ሁሉን ያውቅ ነበረና አስቀደሞ ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠበቁ ብሎ መክሮ ነበር #ማቴ 16÷6

#ከአንድ_ሳምንት_ፍቅርስ_ይሰውረን!

አ.አ ኢትዮጵያ
ተክለ ኤል ኃ/ማርያም
ሚያዝያ ፳ ፪/ ፳ ፻ ፲ ፫ .ዓ.ም
#ቀዳም_ሥዑር (የተሻረች ቀዳሚ ሰንበት)

የሰሞነ ሕማማት ቅዳሜ በዝምታ ድባብ የተዋጠች ሐዋርያት አዝነውና ተጨንቀው እንዳይወጡ የጌታ ወዳጅ ብለው አይሁድ እንዳይወግሯቸው ፈርተው በራቸውን ዘግተው ግራ ተጋብተው የዋሉበት ዕለት ከመሆኑም በሻገር ሊቃውንት በተለያየ ስያሜ ይጠሯታል፣

#ቀዳም_ሥዑር

ይህ የተባለበት በሰንበት ከእህል ከውሃ መጾም አይፈቀድም ፡፡ ነገር ግን በዚህ ዕለት ጌታ በመቃብር ውስጥ በመሆኑ ሐዋርያት ትንሣኤውን ሳናይ አንበላም አንጠጣም ብለው በማክፈል ስለጾሙትና ሰንበተ አይሁድነቱ በመሻሩ ነው፡፡ ይህም ይታወቅ ዘንድ ከሰዓት በፊት ቄጤማ እስኪዞር ሥራ ይሠራል፡፡

#ለምለም_ቅዳሜም ይባላል።

ምክንያቱም በዚህ ዕለት ለምለም ቄጤማ ስለሚታደልበት ነው፡፡ ቄጤማ የሚታደልበት ምክንያት ምሳሌያዊና ምሥጢራዊ ትርጉም ስላለው ነው ምሳሌያዊ ትርጉም በኖኅ ዘመን የዘነበው ማየ አይኀ መድረቁን ለማረጋገጥ፣ ኖኅ ርግብን በመስኮት አውጥቶ ላከ በመጀመሪያው ዝም ብላ ተመልሳለች በሁለተኛው ስትላክ ‹‹ነትገ ማየ አይኀ ሐፀ ማየ ኃጢዓት›› እያለች ቄጤማ በአፏ ይዛ ስትመለስ ኖኅ እጁን ዘርግቶ ተቀብሏታል፡፡ የርግቢቱ ድርጊት የጥፋት ውሃ ደረቀ፣ የኃጢዓት ውሃ ደረቀ የሚል የምስራች አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡ (ዘፍ 8፡6-11)
ምሥጢራዊ ትርጉሙ ደግሞ ርግብ የተባለችው አማናዊት ርግብ እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት፣ ለምለም ቄጠማ በአፏ ይዛ እንደመታየት፣ አምላክ ወልደ አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና መውለዷን የሚያመለክት ነው፡፡ ከእርሷ የተወለደው ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ በሞቱ ሞትን እንዳጠፋልን "ማየ አይኀ" የተባለ ሞተ ነፍስን እንዳስቀረልን ለማመልከት የምስራች ሲሉ ካህናት ቄጤማ ያድላሉ፣ ምዕመናንም እስከ ትንሳኤ ሌሊት በራሳቸው ላይ ያሥሩታል፡፡

#ቅዱስ_ቅዳሜ ይባላል።

ቅዱስ ቅዳሜ መባሉ ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ከፈጠረ በኋላ በዚህ ቀን ከሥራው ሁሉ ያረፈበት ሲሆን፣ በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ሥራውን ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው መቃብር ሲያርፍ በነፍሱ ሲዖልን በርብሮ ባዶዋን አስቀርቷታል፡፡ በዚያ ለነበሩት ነፍሳትም የዘላለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ከሌሎች ዕለታት የተለየ ዕለት ለማለት ቅዱስ ቅዳሜ ተብሏል፡፡
በዚህ ዕለት በቤተክርስቲያን የሚፈጸሙ ሥርዓቶች መኀልየ መኅልየ ይነበባል ምክንያቱም ተስፋ ትንሳኤ አለባትና እስካሁን በሌሎች ዕለታት ሳይደርስ የሰነበተው እግዚአ ሕያዋን (የሕያዋን ጌታ) ፣ ፍትሐተ ዘወልድ፣ ጸሎተ ዕጣን "ዘእንበለ ስኢም" ይደረሳል፣ ያለመሳሳም ወይም ያለ ሰላምታ ማለት ነው፡፡
ገብረ ሰላመ በመስቀሉ (በመስቀሉ ሰላምን አደረገ የሚለው መዝሙር ይዘመራል ምክንያቱም በሲኦል ያሉትን ነፍሳት በርብሮ በገነት ዕረፍተ ነፍስን (ሰላምን) ለሰው ልጅ የሰጠው በመስቀል ላይ ከተሰቀለ በኋላ ስለሆነ ነው፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ከላይ እንዳየነው ጌታ በዕፀ መስቀል ከመሰቀሉ በፊት መስቀል የሰላም ምልክት አልነበረም፡፡ እርሱ ከተሰቀለበት በኋላ ግን የሰላም ምልክት ሆኗልና ከፊተኛው ለመለየት ነው፡፡
ከዚህ ሁሉ በኋላ በረከተ ቄጤማ ይዞራል

#አክፍሎት ፡- ዓርብና ቅዳሜ ይሆናል፣ ያልቻለ አንድ ቅዳሜን ያከፍላል የዚህ አክፍሎት ጦም የተጀመረው በሐዋርያት ነው፡፡ ጌታ በመዋዕለ ትምህርቱ ሳለ ፈሪሳውያን እኛና የዮሐንስ ደቀመዛሙርት እንጦማለን አንተ ደቀመዛሙርት የማይጦሙት ለምንድን ነው? ብለው ጠይቀውት ነበር እርሱም ሙሽራ ከነሱ ጋር ስለ ሚዜዎች ሊጦሙ አይገባም ነገር ግን ሙሽራው ከነሱ የሚወስድበት ጊዜ ይመጣልና ያን ጊዜ ይጦማሉ ብሎ መለሰላቸው በዚህ መሠረት ሐዋርያት ሙሽራው ክርስቶስ ከነሱ ከተለየበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ትንሣኤው ድረስ ከሰው ርቀው፣ ከእህል ከውሃ ተለይተው፣ በዝግ ቤት ተወስነው ጹመዋል ካህናትና ምዕመናን የሐዋርያትን ፈለግ በመከተል ሐሙስ ማታ ከበሉ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ይቆያሉ ሁለቱን ቀን ያልቻሉ ግን ቅዳሜን ብቻ ያከፍላሉ፡፡
በሌላ መልኩ አክፍሎት ማለት ማካፈል ማለት ነው በዚህ ዕለት ካህናት ምዕመናን ካመጡላቸው የትንሣኤ መዋያ በረከት ለድሆች ያካፍላሉና፡፡

🎤🎤🎤🎤🎤🎤🎤🎤
📢 @AwediMeherit📢
📢 @AwediMeherit📢
📢📢📢📢📢📢📢📢
“አሁን ግን #ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን #ተነሥቶአል።”
#1ኛ_ቆሮንቶስ 15፥20
"ክርስቶስ ተንስአ እሙታን
በዓብይ ኃይል ወሥልጣን
አሰሮ ለሰይጣን አግአዞ ለአዳም ሰላም እምይእዜሰ ኮነ ፍስሃ ወሰላም፡፡"

" #መልካም_የትንሣኤ_በዓል "
ዐውደ ምሕረት የእናንተ
👉 @AwediMeherit
👉 @AwediMeherit
ዐውደ ምሕረት
Photo
“አሁን ግን #ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን #ተነሥቶአል።”
#1ኛ_ቆሮንቶስ 15፥20
"ክርስቶስ ተንስአ እሙታን
በዓብይ ኃይል ወሥልጣን
አሰሮ ለሰይጣን አግአዞ ለአዳም ሰላም እምይእዜሰ ኮነ ፍስሃ ወሰላም፡፡"

" #መልካም_የትንሣኤ_በዓል "
ዐውደ ምሕረት የእናንተ
👉 @AwediMeherit
👉 @AwediMeherit