ዐውደ ምሕረት
3.69K subscribers
929 photos
24 videos
271 files
192 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
#ሰኞ
#መርገመ_በለስ እና #አንጾሖተ_ቤተ መቅደስ

‹‹ያቺ በለስ ጌታ ወደርሷ ከመምጣቱ በፊት ለምልማ ቅጠል አውጥታ ነበር››
#ቅ/ዮሐንስ_አፈወርቅ

#በማለዳ(ሲነጋ) ወደ ከተማ(ሀገር) መጣ ሲል:- ጌታችን አዳም ወደ ወደቀበት ስፍራ ወደዚያ ሀገር መጣ፤ያን ጊዜም ተራበ መራቡም እንጀራና ሕብስትን ሳይሆን ስለ ሰው ድኅነት ተራበ ራሱ በወንጌልም ሲናገር ‹‹የእኔስ መብል የላከኝን የአባቴን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ነው እናንተም በላከኝ በአባቴ ታምኑ ዘንድ ነው ››ዮሐ4፤34 ፤ክርስቶስ ወደ ዓለም ሲመጣ እንደ ማለዳ ጸሐይ ነው (የቀትርም የአመሻሽም ያይደለ) የማለዳ ጸሐይ ጨለማውን ገፎ ነው የሚመጣው ክርስቶስም ጨለማ የተባለ ክፉ ከይሲ ዲያብሎስን በጽንሰቱ ድል እየነሳው ተገለጠ፤የማለዳ ጸሐይ እንደ ቀትር ፀሐይ አይፋጅም አይለበልብም ክርስቶስም ለዓለሙ ተመጥኖ የሕይወት ብርሃን ሆኖ ከመዓቱ ምሕረቱ የቀረበ ሆኖ የተገለጠ ነው፡፡ጌታችን በወንጌሉም “የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ የሚከተሉኝ የሕይወት ብርሃንን ያገኛል እንጂ በጨለማ ውስጥ አይመላለስም “ዮሐ8፤12 ሲል በቃሉትምህርት በተአምራቱ በደሙ ፈሳሽነት በብዙ ወገን ድኅነተ-ብርሃኑን ሊሰጠን በመምጣቱ ነው፡፡ ፀሐይ ለሁለቱም እኩል ታበራለች ስለርሷ ብርሃንነት ራሷም ትመሰክራለች ሆኖም ግን ጸሐይን ማየት የተሳነው ሕልውናዋን አይረዳም እንዲሁ ክርስቶስም ጸሐይ ሆኖ ለእስራኤል ቢመጣ ፀሐይነቱን ተረድተው ለሞቁት ለሰውነታቸው ኃይልን ለልብ ዓይናቸው ማየትን የሰጠ ነው፡፡
#የበለስ_ፍሬ ፡- የተባሉ ጉባኤ አይሁድ (ቤተ አይሁድ) ናቸው፤ጌታችንም የሃይማኖት ፍሬ ፈልጎባቸው ቢመጣ ከመጽሐፍተ ኦሪት ከነቢያት በቀር አላገኘም ፤የተጻፈውን በተግባር ፍሬ አልተመለከተባቸውም፡፡ ያንጊዜም ረገማት ቤተ አይሁድም ክርስቶስን ባለማመናቸው በኋላም እንደ ወንበዴ በመስቀላቸው ርግማንን አትርፈዋል፡፡ነገር ግን አይሁዳውያን ቢረገሙም እነርሱን ያልመሰሉትን ቀትቷቸዋል ማለት አይደለም፡፡ምክንያቱም ከቤተ አይሁድ እስጢፋኖስን የመሰለ ሰማዕት ተገኝቷል፤እነ ቅዱስ ጳውሎስን የመሰለ ሐዋርያም ተገኝቷል ‹‹ በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ ከእስራኤል ትውልድ ከብንያም ወገን ከዕብራውያን ዕብራዊ ኝ ስለ ሕግ ብትጠይቁ ፈሪሳዊ ነበርሁ›› #ፊል3፤5

#የበለስ_ፍሬ :- ጌታችን የረገማት በለስ አዳምና ሔዋንን የጣለች ዕጸ በለስ ናት፤ጌታም ለዘላለም ፍሬ አይገኝብሽ ማለት በሰው ላይ አትሰልጥኚ ብሎ ፍዳ መርገምን እንዳጠፋት አስረዳን፡፡ በርግጥ ፍዳ መርገሙን የፈጸመው በጽንሰት ጀምሮ በስቅለት ነው፡፡ በለስ ፍሬ የተባለ በሰው ላይ ሰልጥኖ የነበረ ምልዓተ ኃጢአት ነው መጽሐፍት ኃጢአትን በለስ ይሏታል፤ምክንያቱም የበለስ ቅጠል ሰፊ ደስ የምታሰኝ ናት እንዲሁም የኃጢአት መንገድ ወደ ጥፋት የምትወስድ ሰፊ በር ናት፤የበለስ ፍሬ በመብላትና በማላመጥ ጊዜ ጣፋጭ ናት እንዲሁ ኃጢአት ሲሠርዋት ደስ ታሰኛለች ከሠርዋት በኋላ ግን መከራ ታመጣለች በሚሠርዋት ጊዜ ጣፋጭ ከሠርዋት በኋላ ግን መራራ ናት፡፡ አዳምና ሔዋንም ለጊዜው በለሷ ጣፋጭና ውብ ሆና ታየቻቸው በውሃላ ግን መራራ ሞት አመጣችባቸው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ከአመንዝራ ሴት ከንፈር ማር ይንጠባጠባልና አፍዋም ከቅ የለሰለሰ ነውና ፍጻሜዋ ግን እንደ እሬት የመረረ ነው ሁለት አፍ እንዳው ሰይም የተሳለ ነው እግሮችዋ ወደ ሞት ይወርዳሉ አረማመድዋም ወደ ሲዖል ነው›› #ምሳ5፤3-5 ማርን በቀመስናት ጊጊ ለአፍና ለጉሮሮ ጣፋጭ ናት ከዚያ በውሃላ ግን የሚጎዳ መራራ ሆኖ እናገኘዋለን፤አመንዝራም ሴት አንደበተ ለስላሳ ናት ከማር ከስኳር የሚጣፍጥ ነገርን ትናገርሃለች ወዲያውኑ መራራ ሞትም ከእርሷ ያገኝሃል ሲል ነው፡፡ አርዌ ምድር እባብም(ሰይጣን ተዋሕዷት) ሔዋንን ስትናገራት አንደበቷ የጣፈጠ ነበር፤በሽንገላዋ ግን መራራ ነበረች፡፡

#የበለስ ፍሬ:- የተባለ አዳም የበለስ ፍሬ ከበላ በውሃላ ፈርቶ የተሸሸገባት የበለስ ቅጠል ናት፡፡ ‹‹የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ እነርሱም ዕራቁታቸውን እንደሆኑ አወቁ የበለስንም ቅጠሎች ሰፍተው ለእነርሱ ለራሳቸው ግልድ አደረጉ›› ዘፍ3፤7 አዳምና ሔዋን ፈርተው የተሸሸጉበት በለስ አስቀድሞ ዕጸ በለስን የቀጠፉባስ ዛፍ ቅጠል ነው፡፡

ነገር ግን በዚህ ቅጠል ይሸፈን ዘንድ የቁርበት ልብስ አለበሳቸው ፡፡ ጌታችን ያደረቃት በለስ ይህቺ አዳምና ሔዋን ተሸሽገውባት የነበረችውን ምክንያተ ፍዳ ወመርገም የሆነችውን ነው፡፡ ሊቁ አፈወርቅ ዕደ ወርቅ ዮሐንስ ‹‹አዳም በገነት ዕርቃኑን ሆኖ ሳለ በየትኛው ቅጠል ነበር መሸፈኛ ሰፍቶ ዕርቃኑን የሸፈነ ይህች ቅጠል እንዴት እንደደረቀች አየህን አዳም የለበሳት ዕርቃኑን የሸፈነባት አይደለችምን ጌታ ኢየሱስ ወደ ለመለመችው ዛፍ መጥቶ አዳም ዕርቃን የሸፈነባትን ቅጠል በቃ አደረቃት አዳምን ድኃ ሁኖ ስለዘገኘው ንጹሕ የሆነ የብርሃንንም
ልብስ ሰጠው ይኸውም ብርሃን ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ የተሰራ ነው ፤የበለስን ቅጠል አድርቆ የነፍስን ድኅነት ሰጠው ተድላ ደስታ ባለባት ገነት ፍጹም የሆነ የተድላ ደስታ ልብስ ተጎናጽፎ እንደ መላእክት ሕያው ሁኖ ሲኖር ከይሲ ያሳተችው አዳምን እንዴት እንደዳነ አስባለሁ›› #ግብረ_ሕማማት ገጽ 163/164 ቁ.ጀ50-54
#ፍሬ_ግን_አላገኘባትም
________________
ወንጌሉ እንዳስቀመጠው ጊዜው የፍሬ ወር አልነበረም;ለምስጢሩ ግን ወዲያውኑም ደረቀች ሲል ደግሞ ለዘመናት የሰለጠነ ፍዳ መርገም ሞት ዲያብሎስ ጠፋ ተሸረ ሲል ነው፡፡ #ኛ_ቆሮ 15÷55 ‹‹ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ፤ሲዖል ሆይ ድል መንሳትህ የት አለ››የሚለው ተፈጸመ፤ምክንያቱም አስቀድሞ በትንቢት ተነግሮ ነበርና ‹‹ከሲዖል እጅ እታደጋቸዋለሁ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ ሞት ሆይ ቸነፈርህ ወዴት አለ ሲዖል ሆይ ማጥፋትህ ወዴት አለ ርኅራኄ ከዓይኔ ተሰወረች›› #ት.ሆሴዕ 13፤14 ክርስቶስ በሰው ላይ የሰለጠኑ ክፉ በለሶችን አድርቆ አጥፍቶልናል ይህንንም ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹‹መጥቶም ፍትወታት እያትን ኃጣውዕ ርኩሳንን አጠፋ ሁከቱን ጸጥ አደረገ ዕጸ በለስንም አድርቆ
ብሩህ በሆነ ሕይወት በሃይማኖት የበቀለውን ዕጸ መስቀል ተከለልን ›› #ግብረ_ሕማማት ገጽ 167 ቁ.104 በበለስ የመጣውንም ርግማን በዕጸ መስቀሉ ድል ነሳው ፤በለሷን ሲረግም በአንጻሩ በለስ ዕጸ መስቀልን ተከለልን፡፡
#ይህ_የከበረ የተዘረጋ መስቀል ሥሩ በምድር ጫፉ በሰማይ ያለ ቅጠሉ የማይረግፍ አበባው ለጥፋት ፍሬው ለሞት ያልሆነ ነው፡፡ባለ በገናው ነቢዩ ዳዊትም ‹‹ወይከውን ከመዕጽ እንተ ትክልት ኅበ ሙሐዘ ማይ እንተ ትሁብ ፍሬሃ በበጊዜሃ ወቁጽላኒ ኢይትነገፍ -በውኃ ዳር የተተከለ በየጊዜው ፍሬውን የሚሰጥ ቅጠሉም የማይረግፍ ›› #መዝ1÷3 ክርስቶስ በዕጸ መስቀሉ ክፉ በለስ የተባሉ ዲያብሎስና ሠራዊቱን የቀጣበት ፤ዛሬም ለሚያምኑበት ወደ ሰማይ የሚያወጣ መሰላል ነው፡፡ይቺ ዕለትም መርገመ በለስ ተብላለች

#ከዚህ ቀጥሎ ወደ ቤተ መቅደስ ሔደ፤ ቤተ መቅደስ ቤተ ጸሎት፣ ቤተ መሥዋዕት መሆኑ ቀርቶ ቤተ ምሥያጥ /የንግድ ቤት/ ሆኖ ቢያገኘው፤ «ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች… እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት» ማቴ. 21፤13 ብሎ የሚሸጡበትን ሁሉ ገለበጠባቸዉ፣ ገርፎም አስወጣቸዉ፣ ይህም የሚያሳየዉ ማደሪያው ቤቱ የነበርን እኛ የአዳም ልጆች ኃጢአት ሰፍኖብን ስንኖር ቢያገኘን ኃጢአታ ችንን ሁሉ እንዳራቀልን
............ #ይቆየን ..........
ግብሐት :- ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሰ/ት ቤት ሰሌዳ መጽሔት