ዐውደ ምሕረት
3.68K subscribers
930 photos
24 videos
271 files
193 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
#ቀዳም_ሥዑር (የተሻረች ቀዳሚ ሰንበት)

የሰሞነ ሕማማት ቅዳሜ በዝምታ ድባብ የተዋጠች ሐዋርያት አዝነውና ተጨንቀው እንዳይወጡ የጌታ ወዳጅ ብለው አይሁድ እንዳይወግሯቸው ፈርተው በራቸውን ዘግተው ግራ ተጋብተው የዋሉበት ዕለት ከመሆኑም በሻገር ሊቃውንት በተለያየ ስያሜ ይጠሯታል፣

#ቀዳም_ሥዑር

ይህ የተባለበት በሰንበት ከእህል ከውሃ መጾም አይፈቀድም ፡፡ ነገር ግን በዚህ ዕለት ጌታ በመቃብር ውስጥ በመሆኑ ሐዋርያት ትንሣኤውን ሳናይ አንበላም አንጠጣም ብለው በማክፈል ስለጾሙትና ሰንበተ አይሁድነቱ በመሻሩ ነው፡፡ ይህም ይታወቅ ዘንድ ከሰዓት በፊት ቄጤማ እስኪዞር ሥራ ይሠራል፡፡

#ለምለም_ቅዳሜም ይባላል።

ምክንያቱም በዚህ ዕለት ለምለም ቄጤማ ስለሚታደልበት ነው፡፡ ቄጤማ የሚታደልበት ምክንያት ምሳሌያዊና ምሥጢራዊ ትርጉም ስላለው ነው ምሳሌያዊ ትርጉም በኖኅ ዘመን የዘነበው ማየ አይኀ መድረቁን ለማረጋገጥ፣ ኖኅ ርግብን በመስኮት አውጥቶ ላከ በመጀመሪያው ዝም ብላ ተመልሳለች በሁለተኛው ስትላክ ‹‹ነትገ ማየ አይኀ ሐፀ ማየ ኃጢዓት›› እያለች ቄጤማ በአፏ ይዛ ስትመለስ ኖኅ እጁን ዘርግቶ ተቀብሏታል፡፡ የርግቢቱ ድርጊት የጥፋት ውሃ ደረቀ፣ የኃጢዓት ውሃ ደረቀ የሚል የምስራች አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡ (ዘፍ 8፡6-11)
ምሥጢራዊ ትርጉሙ ደግሞ ርግብ የተባለችው አማናዊት ርግብ እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት፣ ለምለም ቄጠማ በአፏ ይዛ እንደመታየት፣ አምላክ ወልደ አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና መውለዷን የሚያመለክት ነው፡፡ ከእርሷ የተወለደው ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ በሞቱ ሞትን እንዳጠፋልን "ማየ አይኀ" የተባለ ሞተ ነፍስን እንዳስቀረልን ለማመልከት የምስራች ሲሉ ካህናት ቄጤማ ያድላሉ፣ ምዕመናንም እስከ ትንሳኤ ሌሊት በራሳቸው ላይ ያሥሩታል፡፡

#ቅዱስ_ቅዳሜ ይባላል።

ቅዱስ ቅዳሜ መባሉ ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ከፈጠረ በኋላ በዚህ ቀን ከሥራው ሁሉ ያረፈበት ሲሆን፣ በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ሥራውን ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው መቃብር ሲያርፍ በነፍሱ ሲዖልን በርብሮ ባዶዋን አስቀርቷታል፡፡ በዚያ ለነበሩት ነፍሳትም የዘላለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ከሌሎች ዕለታት የተለየ ዕለት ለማለት ቅዱስ ቅዳሜ ተብሏል፡፡
በዚህ ዕለት በቤተክርስቲያን የሚፈጸሙ ሥርዓቶች መኀልየ መኅልየ ይነበባል ምክንያቱም ተስፋ ትንሳኤ አለባትና እስካሁን በሌሎች ዕለታት ሳይደርስ የሰነበተው እግዚአ ሕያዋን (የሕያዋን ጌታ) ፣ ፍትሐተ ዘወልድ፣ ጸሎተ ዕጣን "ዘእንበለ ስኢም" ይደረሳል፣ ያለመሳሳም ወይም ያለ ሰላምታ ማለት ነው፡፡
ገብረ ሰላመ በመስቀሉ (በመስቀሉ ሰላምን አደረገ የሚለው መዝሙር ይዘመራል ምክንያቱም በሲኦል ያሉትን ነፍሳት በርብሮ በገነት ዕረፍተ ነፍስን (ሰላምን) ለሰው ልጅ የሰጠው በመስቀል ላይ ከተሰቀለ በኋላ ስለሆነ ነው፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ከላይ እንዳየነው ጌታ በዕፀ መስቀል ከመሰቀሉ በፊት መስቀል የሰላም ምልክት አልነበረም፡፡ እርሱ ከተሰቀለበት በኋላ ግን የሰላም ምልክት ሆኗልና ከፊተኛው ለመለየት ነው፡፡
ከዚህ ሁሉ በኋላ በረከተ ቄጤማ ይዞራል

#አክፍሎት ፡- ዓርብና ቅዳሜ ይሆናል፣ ያልቻለ አንድ ቅዳሜን ያከፍላል የዚህ አክፍሎት ጦም የተጀመረው በሐዋርያት ነው፡፡ ጌታ በመዋዕለ ትምህርቱ ሳለ ፈሪሳውያን እኛና የዮሐንስ ደቀመዛሙርት እንጦማለን አንተ ደቀመዛሙርት የማይጦሙት ለምንድን ነው? ብለው ጠይቀውት ነበር እርሱም ሙሽራ ከነሱ ጋር ስለ ሚዜዎች ሊጦሙ አይገባም ነገር ግን ሙሽራው ከነሱ የሚወስድበት ጊዜ ይመጣልና ያን ጊዜ ይጦማሉ ብሎ መለሰላቸው በዚህ መሠረት ሐዋርያት ሙሽራው ክርስቶስ ከነሱ ከተለየበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ትንሣኤው ድረስ ከሰው ርቀው፣ ከእህል ከውሃ ተለይተው፣ በዝግ ቤት ተወስነው ጹመዋል ካህናትና ምዕመናን የሐዋርያትን ፈለግ በመከተል ሐሙስ ማታ ከበሉ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ይቆያሉ ሁለቱን ቀን ያልቻሉ ግን ቅዳሜን ብቻ ያከፍላሉ፡፡
በሌላ መልኩ አክፍሎት ማለት ማካፈል ማለት ነው በዚህ ዕለት ካህናት ምዕመናን ካመጡላቸው የትንሣኤ መዋያ በረከት ለድሆች ያካፍላሉና፡፡

🎤🎤🎤🎤🎤🎤🎤🎤
📢 @AwediMeherit📢
📢 @AwediMeherit📢
📢📢📢📢📢📢📢📢