አትሮኖስ
279K subscribers
110 photos
3 videos
41 files
458 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#ትንግርት


#ክፍል_ዘጠኝ


#በዘሪሁን_ገመቹ_ዋቤ


...‹‹ስሚ አሁኑኑ ጨርቅሽን ይዘሽ ከቤቴ እንድትወጪልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ልጆቼን ላሳድግበት፡፡ ከፈለግሽ ሽርሙጥና ቤት ግቢና እንደፈለግሽ ሁኚ፤አልፈልግሽም፡፡>> በማለት ጨርቄንና ደብተሮቼን ሠብስባ አስታቅፋኝ እየገፈተረችኝ ከቤቷ አውጥታ አባረረችኝ፡፡

በእንደዚህ ሁኔታ ነበርሰ ታሪኳን ያስረዳችው፡፡ ከዛም እንደ እህቱ አድርጎ ተቀበላት፡፡."

ትምህርቷንም እንድትቀጥል አደረጋት፡፡ በወቅቱ እሱ ጋር ስትመጣ የአስረኛ ክፍል ተማሪ ነበረች፡፡ አሁን በዲፕሎማ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የሦስተኛ አመት ተማሪ ነች፡፡

....ሁሴን የሀሳብ ውቅያኖስ ተንፈራግጦ ሲወጣ እቤቱ ሞቆና ተጫጭሷ ነበር፡፡ ፎዚያ ቅድም የለበሠችውን ልብስ አውልቃ ድርያ ለብሳለች፡፡ ብዙውን ጊዜ የምትሸፍነውን ፀጉሯን በነፃነት ለቃዋለች፡፡ አጭር ቢሆንም ሉጫ ስለሆነ ለውበቷ ልዩ ድምቀት ለግሷታል፡፡

‹‹እሺ ፎዚያ ትምህርት እንዴት ነው?›› አላት፡፡

‹‹አሪፍ ነው፡፡አሁንማ ልጨርስ አራት ወር ብቻ ቀረኝ እኮ!››

‹‹በጊዜ ስራ ፈልጉ ማለትሽ ነው?››

‹‹ለስራው እንኳን ብዙም ጉጉት የለኝም፡፡ ዋናው ተምሬ እዚህ ደረጃ መድረሴ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ዕቅዴ አንተን በተሻለ መንገድ መንከባከብ ነው፡፡››

‹‹እንዴት ባክሽ? እኔን ለመንከባከብ እኮ ሦስት ዓመት ሙሉ ኮሌጅ ገብቶ መማር አያስፈልግሽም ነበር

‹‹...እንዲህ ብለህ አታሳምነኝም...አንተ ለእኔ ምርጥ ወንድሜ ብቻ ሳትሆን አባቴም ጭምር ነህ ፡፡ብዙ ነገር አድርገህልኛል፡፡አላህ አንተን ባይጥልልኝ ኖሮ ዛሬ ዕጣ ክፍሌ የሰው ቤት ግርድና ካልሆነም ሽርሙጥና ነበር፡፡ስለዚህ የእኔ አንተን ለመንከባከብ መወሰን ያንስብሀል እንጂ አይበዛብህም፡፡››

‹‹...ፎዚ ለእኔም እኮ ምርጥ እህት ሆነሽኛል፡፡ ይሁን እንጂ እህትም አንድ ቀን የታለቅ ወንድሟን ቤት ጥላ የራሷን ቤት ትገነባለች፡፡ የወንድም ኃላፊነት ደግሞ እህቱ እዚህ ደረጃ እንድትደርስለት ማበረታታትና መደገፍ ነው፡፡ እርግጥ ነገሮች ቀላል አይደሉም፡፡ እኔም እኮ አንድ ቀን ስራ ይዘሽ ፣የፍቅር ጓደኛ አበጅተሸና ትዳር መስርተሸ ጥለሺኝ እንደምትሄጂ ሳስብ በጣም ይጨንቀኛል፤ ቢሆንም ግን የግድ መቀበል እንዳለብኝ አምናለሁ፡፡

የፈላውን ቡና በመቅዳት ስኳር ጨምራ በማማሰል አቀበለችውና ለራሷም ቀድታ ንግግሯን ቀጠለች፡፡

‹‹እንግዲህ ውሳኔዬ የማይቀየር ነው፡፡ ምን አልባት አግብተህ ባለቤትህ ቤቱን ከተረከበችኝና ከልብ እንደምትንከባከብህ እርግጠኛ ከሆንኩ.. ያኔ ያልከውን አደርግ ይሆናል፡፡›

‹‹ዝም ብለን በባዶ ሜዳ እኮ ነው የምንጨቃጨቀው፡፡>>

‹‹እንዴት ማለት?›› ሁሴን ሊላት የፈለገው ምን እንደሆነ ስላልገባት ጠየቀችው፡፡

‹‹እኔ አሁን በቅርብ የማገባ ይመስልሻል? >>

‹‹ለምንድነው የማታገባው?››

‹‹ማን ነች ፍቃደኛ ሆና እኔን ልታገባኝ የምትችለው?››

‹‹በጣም ዕድለኛዋ ሴት ነቻ፡፡›› ፎዚያ ከምሯ ነው እውነተኛ ስሜቷን የምታወራው፡፡

‹‹አይምሰልሽ .. በዙሪያዬ ያሉ ሴቶች ሁሉ በፍቅር እንጂ ትዳርን ለሚያህል ቁም ነገር ብቁ እንዳልሆንኩ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡››

‹‹ይሄ አንተን በተመለከተ ትክክለኛ ምልከታ ነው ብዬ አላስብም፡፡›› አለች ቅሬታን በዛለ ድምፅ፡፡

‹‹እንዴት ... ? ሌላው ይቅር በአንቺ አመለካከት እኔ ለትዳር የምሆን ግለሠብ እመስልሻለሁ?›› ሲል ጠየቃት ፡፡

‹‹እውነቱን ልንገርህ?›› በታፈነ ድምፅ ጠየቀችው፡፡

‹‹አዋ!.. ንገሪኝ ... ትክክለኛ ስሜትሽን ንገሪኝ፡፡››
‹‹እንግዲያው እኔ ሙሉ በሙሉ ያንተ አይነት ወንድ እስከማገኝ ትዳር ሚሉት ነገር አልሞክርም፡፡››
ደነገጠ፡፡ እንደምትወደው ያውቃል፡፡ ይሄን ያህል ተፅዕኖ ውስጥ እንደከተታት ግን ልብ ብሎ አስተውሎት አያውቅም፤ ውይይታቸው ከወትሮው በመጠኑም ቢሆን ጠንከር እያለ ስለመጣበት ርዕስ ለመቀየር ተገደደ፡፡

‹‹ኦ! ይሄ ቡናሽ ልዩ ነው፤ ከደባሪው እራስ ምታቴ ገላገለኝ›› አላት፡፡

‹‹ስለተሻለህ ደስ ብሎኛል፤በነገራችን ላይ ቀን ትንግርት መጥታ ነበር፡፡››

‹‹እንዴት ሳትደውልልኝ መጣች ..…?››

‹‹እኔ እንጃ፡፡ ሁኔታዋ ግን ከወትሮው የተለየ ሆነብኝ፡፡ ሁሉ ነገሯ ወደ ኖርማል ተመልሷል... አገባች እንዴ?›› የገረማትን ነገር ጠየቀችው፡፡

‹‹አይመስለኝም.. ስራ ግን ቀይራለች›› መለሠላት፡፡

<<ለማንኛውም የሆነ ዕቃ አምጥታልሃለች፡፡ >>

‹‹ምን አይነት ዕቃ? >> ለማወቅ በተጣደፈ ስሜት ጠየቃት፡፡

‹‹እኔ እንጃ ሥዕል መሠለኝ፤ታሽጓል፡፡ መኝታ ቤት አስቀምጬልሀለሁ፡፡››

ተስፈንጥሮ ወደ መኝታ ክፍሉ ገባ፡፡ በግምት ሠማንያ በስልሳ የሚሆን በፍሬም የተወጠረ፤ በስጦታ ወረቀት የተጠቀለለ ሸራ አገኘ፡፡ በጥድፊያ ልባሱን አነሳው፡፡የሚያፈዝ ስዕል ነው፡፡ የጥንት ንግስቶች የሚለብሱትን አይነት አብረቅራቂ ወርቀዘቦ ልብስ የለበሠች እንስት ትታያለች፡፡ እግሮቿ መሬት አይረገጡም፡፡ በአየር ላይ የምትራመድ ትመስላለች፡፡ ፀጉሯን ንፋሱ እያንሳፈፈው በአየር ላይ ተበታትኖ ሲታይ ሰማይ ጠቀስ ማማ ላይ የተሰቀለ የታላቅ ሀገር የተከበረ ባንዲራ ይመስላል የእጆቿ ጣቶች ውበታቸው የገነት ደናግሎችን አይነት ነው፡፡ በቀኝ እጇ ዓይነ ሥውሮች የሚጠቀሙበትን አቅጣጫ መጠቆሚያ ነጭ ዘንግ ይዛለች፡፡ ፊቷ የተለየ ነው፡፡ እንደ ሠው ዓይን፣ አፍንጫ፤ ከንፈር ሳይሆን በቦታው የሙሉ ጨረቃ ቅርፅ ይታያል፡፡ በጨረቃዋ ዙሪያም በህብረ ቀለም የደመቀ የብርሃን አምድ ያንፀባርቃል፡፡የሥዕሉ ጥልቀትና ምጥቀት... ውስጡ የተዳፈነውን የፍቅር እቶን ቀሠቀሠበት፡፡ የናፍቆት እሳት መላ ሰውነቱን ሲለበልበው ተሠማው፡፡

ትንግርት መጽናኛ የሚሆነውን ውድ ስጦታ ስላበረከተችለት ከልብ አመሠገናት፡፡ ፊት አልባ ሥዕል የተሳለላት ድብቋ ደራሲ ግን በምን ተአምር በአካል ሊያገኛት እንደሚችል ከመቼውም ጊዜ በላይ ግራ ገባው፡፡ ስዕሉን እንደታቀፈ ወደ አልጋው ሄደና በጥንቃቄ ተኛ፡፡ የቀለሙ ሽታ ከደራሲዋ ሰውነት የሚመነጭ መግደላዊት ማሪያም የክርስቶስን እግር ያጠበችበትን የአልባስጥሮስ ሽቶ አይነት እንደሆነ ሁሉ በረጅሙ ስቦ ወደ ውስጡ ማገው.. የስሜቱ ጥጋ.. ጥግ ድረስ ገብቶ ለውስጡ ሀሴት እንዲሰጠው በመመኘት ፡፡ በስዕሏ ፋንታ ዋናዋንም አንድ ቀን በአካል አግኝቷት እዚሁ አልጋው ላይ እንዲህ አቅፎት በእጆቹ እየዳበሳት..በከንፈሮቹ እየመጠጣት. በትንፋሹ እያጋላት... በሙቀቱ እያቀለጣት... በፍቅሩ እያሰከራት አብሯት እንደሚተኛ ተስፋ በማድረግ…፡፡...

ይቀጥላል

ዩቲዩብ ቻናል በቅንነት  እየገባችሁ #ሰብስክራይብ #እያደረጋቹ ቤተሰቦች  በባለፈው #ፖስት 10 ሰው ብዬ 2 ሰው ብቻ ነው #ሰብስክራይብ ያደረገው 10 ሰው #ሰብስክራይብ አድርጉና ቀን በቀን እንልቀቅ

👇Sebscribe

YouTube link👇
https://www.youtube.com/@atronose
👍115👏1512👎2😁1