አትሮኖስ
281K subscribers
110 photos
3 videos
41 files
480 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#ለእኔ_ያላት_እንጀራ
:
#በሕይወት_እምሻው
:
:
#ክፍል_አንድ
:
:
ሰው አይወጣልኝም።

በሠላሣ ሰባት አመቴ ህይወቴ ከጥቂት ሰዎች የተሰራ ነው።ሁለት በሠላሳዎቹ ዕድምዬ ያገኘኋቸው የልብ የማይባሉ ጓደኞች፣ እናቴ፣ አባቴ፣ አንድ ግማሽ እህት (አባቴ ከእናቴ በፊት የወለዳት) እና ጊዚያዊ ወንዶች።

እግዜር ከሰጠኝ ሰዎች ውጪ የእኔ ብዬ ያቆምኩትና የጸና የረጅም ጊዜ ግኑኝነት የለኝም። አብሬው አንድ በዐል ሁለት ጊዜ ያከበርኩት የወንድ ጓደኛ ኖሮኝ አያውቅም።

ሚስጥረኛ የለኝም።

የፍቅር ግኑኝነቶቼ አጭርና በጉድፍ የተሞሉ ናቸው። ይህ ሁሉ በልጅነቴ ያመንኩት ሰው ከድቶኝ፣ ወንድ አላምን ብዬ ምናምን አይደለም። እስከማምነው አብሮኝ የሚቆይ ወንድ አላገኘሁም እንተዋወቃለን። የተገግባባን እንመስላለን። ቡና፣ ማክያቶ እንባባላለነን። ክትፎ፣ በየአይነቱ እንገባበዛለን። ወይን፣ ቢራ አብረን እንጠጣለን። ቤርጎ ወይም ቤቱ ሄደን እንተኛለን። ከዚያ ሁሉ ነገር ይከስማል። ይጸድቃል የተባለው ይጠወልጋል። እንደ እሳት የተንቀለቀለው፣ በቀናት ወደ አመድነት ይለወጣል።

እንደሰው ባል የሚሆን ወንድ አግኝቼ መሰብሰብ፣ ልጅ ወልዶ መሳም ጠልቼ አይደለም። በጉልምስና እድሜዬ ፣ በሃያዎቹ መባቻ ላይ ሆና፣ ጊዜ ተርፏት እንደምትሽኮረመም እና ከአንዱ አንዱን የምታማርጥ ልጃገረድ፤ በየካፌው የማይረባ ማክያቶ የማንቃርረው ፣ በየቤርጎው ያልታጠበና ሌላ ሰው-ሌላ ሰው የሚሸት አንሶላ ላይ የምጋደመው፣ ሰው ፍለጋ ፤ ባል ባገኝ ብዬ ነው። ግን ሰው አልወጣልኝም።

ለዚህ ነው መስፍን የተለየብኝ።

መስፍኔ!

ቢሯችን ጨረታ ሊያስገባ መጥቶ ነው የተዋወቅነው። እንደታየሁ የወንድ ልብ ትርክክ የሚያደርግ ውበት፣ የሚያስደነብር ቁንጅና፣ እስቲ ስልክሽን አስብሎ የሚያስለምን ቁመና የለኝም። ግን መስፍን እንደሱ ሰራው።

ጨረታውን እንኳን ሳያስገባ ስምሽ ማነው ብሎ ጠየቀኝ።
''ማህደር....'' አልኩኝ። ትኩር ብለው የሚያዩኝን ዐይኖቹን ሽሽት፣ ጠረጴዛዬ ላይ ተመሳቅለው የተቀመጡትን ወረቀቶች እያየሁ። ከዛ ደግሞ ቀና ብዬ እያየሁት።

''ፐ....የሚያምር ስም ....l ማህ....ደር!'' አለ፣ አለ፣ ስሜን ሁለት ቦታ ከፍሎ። ስሜን እንዲህ ከወደደው፣ ስልክ ቁጥሬንማ በጣም ይወደዋል፣ ብዬ ለራሴ ቀልድ ነግሬ ራሴው ፈገግ ስል፣

''ምነው? ፊቴ ላይ የሚያስቅ ነገር አለ?'' አለኝ።

''አረ የለም.....''

''ወደሽኝ ነው?''

''ሆሆ....''

''ምነው የምወደድ አደለሁም?''

ሣቅኹ። የሚወደድ አይነት ነበር። ፍቅር ጀመርን።

ሁለት ወር በየቀኑ የሚባል መጠን እንገናኝ ነበር። ያልተገናኘንባቸውን ጥቂት ቀናትና ሰዓታት፣ በለሊት የስልክ ወሬዎች እንሞላቸው ነበር።

የምወደውን ስለሚወድ፣ የሚወደውን ስለምወድ፣ ሁሉ ነገር ቀላል ነበር።

ቲያትር ብንገባ ብዬ ያሰብኩ ቀን ቀድሞ፣''ዛሬ ትያትር እንይ'' ይለኛል።

የከቤ ኬክ ቤት ኬክ ውል ሲለኝ፣ ፊቴ ላይ የተፃፈ ይመስል፣ ''ዛሬ ኬክ አላመረሽም?'' እስቲ ከቤ ኬክ ወክ እናድርግ'' ይለኛል።

የሚወደድ አይነት ነበር። ትሁትና ደግ፣ ቁጥብና እርጋታ ያለው ሰው ነበር።

ብቻችንን ስንሆን ደግሞ ቁጥብነቱ ወደ ስግብግብነት ፣ እርጋታው ወደ የሚያስገርም ጥድፍያ...ደስ በሚል ሁኔታ ይለወጥ ነበር። በአደባባይ በትህትና እጆቼን ይዞ እንደማይጎዝ፣ ቤት ውስጥ ለፍቅር እያዘጋጀ ሲያቅፈኝ በመሀከላችን አየር እንኳን አያልፍም ነበር።

ከንፈሮቼን ተርቦ እህል እንዳገኘ ሰው ሲጎርሳቸው... እያንዳንዳቸው ዐሥር ጣት ያላቸው አምስት እጆች እንዳሉት ሀሉ፣ ልገምት በማልችለው ፍጥነት መላ ሰውነቴን አንድ በአንድ፣ ግን ደግሞ ባንድ ግዜ ሁሉም ቦታ ሲነካካኝ፣ ሲዳብሰኝ....ጀርባዬ ጋር ነው ስል ጭኖቼ ጋር፣ ጭኖቼ ጋር ስል ጡቶቼ ጋር .....ጡቶቼ ላይ ናቸው ስላቸው ጭኖቼ መሀል የሚገቡት እነዛ ጣቶቹ... እነዛ ለሦስት ሰው የሚበቁ ወፋፍራም ከንፈሮቹን አስተባብሮ ጆሮዬን እየሳመ ስሜን አጣፍጦ ሲያንሾካሹክ (ማ...ዲ...ዬ....ዬ) ፍቅር ሳንሰራ ጧ ብዬ የምፈነዳ ይመስለኝ ነበር።

ወ....ደ....ድ....ኩ.....ት።

እኔም በተራዬ ሰው ወጣልኝ። ስንቴ የተማለድኩት ፈጣሪዬ መስፍኔን ባል አድርጎ ሠርቶ ላከልኝ።

ግን ፈራሁ። ስለ መጋባት፣ ስለ ትዳር ወሬ ላወራው ፈራሁ። ግጣሜ መሆኑን ባውቅም፣ በሁለት ወር ውስጥ ብንጋባስ የሚል ሐሳብ ከአፌ አውጥቼ ማስደንበሩን ፈራሁ።

ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ውስጥ ነበር ራሴን ያገኘሁት። ለጋብቻ የረፈደ እድሜዬን ሳስብ ስለ ጋብቻ አለማውራት አልችልም። ረፍዶብኛል። የሁለት ወር ግኑኝነታችንን ዕድሜ ሳስብ ግን ስለ ጋብቻ ማውራት አልችልም። መዋከብ ይሆናል። ብሽቅ ሁኔታ አይደለም?

ሁለቱን ጓደኞቼን አማከርኩ። ቤቲ በዘወትር ችኮላዋ፤

''ስንት አመቱ ነው?'' አለችኝ። ያልጠበቁት ጥያቄ ነበር።

''ስንት ዓመቱ ነው እሱ?'' ደገመችው።

''እ....እኔንጃ....''

''እንዴ! አታውቂም እንዴ ? ዕድሜውን ሳታውቂ ነው እስካሁን ላይ እታች የምትይው ?''

መስፍኔን ዕድሜውን በቀጥታ አልጠየኩትም። መጠየቅ ትልቅ ነገር ሆኖ ሳይሆን ያንን ጥያቄ የሚያስነሳ የወሬ ክር ስላልጀመርን ነው። አለ አይደል...ስለ ዶክተር አብይ ምናምን እያወራን ''ለመሆኑ አንተ እድሜክ ስንት ነው?'' አይባል ነገር ....

''አልጠየኩትም ግን መገመት እችላለሁ...'' አልኩ።

''እ....ስንት ነው?'' ቤቲ አሁንም በጥድፍያ ጠየቀችኝ።

''ኦኬ....ዩኒቨርስቲ ....ግራጅዌት ያረገው በ 92 ነው.....''

''በእኛ?''

''እንዴ ኦፍ ኮርስ በእኛ! ይሄን ያህል ሽማግሌ አረግሽው እንዴ!''

አልኩ እየሳኩ።

''የዛሬ ወንድ ምኑ ይታመናል! ለራሳቸው ሰርግ ሽማግሌ ሆነው መሄድ ሁሉ ጀምረዋል እኮ...'' ሁላችንም ሳቅን።

አፍታም ሳትቆይ ቤቲ ስልኳን ከቦርሳዋ በፍጥነት አወጣች መስፍኔ በሌለበት እድሜው ሊሰላለት ነው። ጎንበስ ብላ ጠቅ ጠቅ አድርጋ ቀና ብላ ዐየችኝና፣

''የአዲስ አበባ ልጅ ነው?'' አለችኝ። ግር ብሎኝ...

''እሱ ደግሞ እድሜው ውስጥ ምናገባው?'' አልኳት።

''እንዴ.... የገጠር ልጅ ከሆነ ትምህርት ቶሎ ስለማይጀምር፣ አንድ አምስት ልጨምርበት ነዋ!'' ብላ ስትስቅ ፣ እስካሁን ዝም ብላ የነበረችው ሄዋንም አጀበቻት።

''ወይ ጉድ...ያንቺ ጉድ ብዙ ነው....የአራት ኪሎ ልጅ ነው....''

አልኩ።

''ፈይን እንግዲህ ሁለት ሺ አስራ አንድ ገባን አይደል...በሃያ ሁለት ዓመቱ ጨረሰ ብንል እንኳን፤ አርባ አንድ ወይ አርባ ሁለቱን ጠጥቷል ማለት ነው!'' አለችና፣ ትልቅ ሚስጢር ቆፍሮ እንዳገኘ ሰው ኮራ ብላ ሦስት ጊዜ አጨበጨበች።

ከግምቴ ብዙም የራቀ ስላልነበር አልተገረምኩም

''እሺ...እድሜው ይሁንና ምንድን ነው የምትመክሩኝ?'' አልኩ ቤቲንም ሄዋንንም እያየሁ። ሄዋን ንግግሯን ለመጀመር አፏን ስትከፍት ቤቲ ቀደመቻትና፤

''እኔ ጠይቂውና ያበጠው ይፈንዳ ነው የምለው...እሱም ትልቅ ሰው ነው ደግሞ...ከማይሆን ሰው ጋር ጊዜሽን ዌስት የምታደርጊበት ዕድሜ ላይ አይደለሽም....በዛ ላይ አሪፍ ነው ምናምን ብለሻል...እና.... ጠይቂው ባይ ነኝ።'' አለችኝ ምክሯ አልገረመኝም። የቤቲ የኑሮ ዘይቤ ችኮላና ያበጠው ይፈንዳ ነው። ፍጥነት ነው። ዛሬን መኖር ነው።

ሄዋንን አየኋት።

💫ይቀጥላል💫

ለአስተያየቶ @atronosebot ን ይጠቀሙ መልካም ምሽት። 🙏
👍71🥰1
#ለእኔ_ያላት_እንጀራ
:
#በሕይወት_እምሻው
:
:
#ክፍል_ሁለት
:
:
....ሄዋንን አየኋት

''እኔ.....እኔ.....'' ብላ ጀመረች። ልትሽከረከር ነው እንግዲህ! ሄዋን አንዲት ነጥብ ለማንሳት ቃላትን ስለምትፈጅና የምትፈልገውን ነገር ለመናገር ጊዜ እንደምትወስድ ስለምናውቅ፣ እኔም ቤቲም ወንበራችን ላይ ለጠጠ ብለን ተቀመጥን።

''እኔ.... እኔ ግን ትንሽ ብታይው ጥሩ ነው ባይ ነኝ። እኔ እንደሚመስለኝ...ማለቴ ሲመስለኝ....እስካሁን ያላገባበት ምክንያት ይኖራል....ትዳር ይፈራ ይሆናል....ወይ ደግሞ መጥፎ ነገር ደርሶበት ቢሆንስ...ለማለት የፈለኩት ምንድን ነው... ቶሎ ጠይቀሽ እንዳታስደነብሪው....ቢሸሽስ? ትንሽ ብትታገሺ ከራሱ ሊመጣ ይችላል....እኔ እንደሚገባኝ...ወንዶች....ማለቴ ብዙ ወንዶች ትዳር ትዳር ሲባሉ አይወዱም...እኔ የምለው... እንደውም እንደውም እንዲያገባሽ ከፈለክሽ ትዳር የሚባል ሐሳብ ውስጥሽ እንደሌለ ማሳመን አለብሽ....

ሰናይ ሁሌ ነው ለእኔ የሚነግረኝ.... ሰናይ ምን ይላል መሰለሽ....ወንድ የሚወደው እንደዛ አይነት ሴት ነው....ዛሬን የምትኖር....አለ አይደል....ነገ ነገ የማታበዛ...አሁን እኔን አታይም? ማለቴ ሰናይን አታይም? አንድ ቀን ስለትዳር ሳላነሳበት ሁለት ዓመት ኖረን ነው እራሱ የጠየቀኝ...ለጓደኞቹ ምን ብሎ እንደነገራቸው ታውቂያለሽ? ''እንጋባ እንጋባ ብላ የማትነዛነዝ የመጀመርያ ገርልፍሬንዴ እሷ ነበረች'' እያለ ነው የሚነግራቸው...ለእኔም ምኔን ወደድከው ስለው ፣ እሱ ነው የሳበኝ ምናምን ሲለኝ ነበር...እነሱ...ማለቴ ጓደኞቹ...ራሳቸው ታድለህ ምናምን ሲሉት ነበር...

እና....ፈታ በይ....ኢንጆይ....በዛ ላይ ሴክሱ አሪፍ ነው አይደል?''

ሣቅኩ።

''ምናባሽ....አሪፍ ነው አይደል?'' አለች ሄዋን።

''አዎ....በጣም....'' አልኩና ተሽኮረመምኩ።

''ከመጋባታችሁ በፊት ኢንጆይ ኢት እናቴ! ከዚያ እንደኛ ድር ያደራበታል'' አለች ሄዋን፣ እየሳቀች።

አብረናት ስቀን ስንጨርስ ሁለቱንም አፈራርቄ አየኋቸው። ያበጠው ይፈንዳ ባይዋ ቤቲ በሰላሳ ስድስት አመቷ አሁንም ላጤ ናት። ረጋ በይ ባይዋ ሄዋን ደግሞ፣ በሠላሳ ሁለት ዓመቷ አግብታ ሁለት ወልዳለች።

ዓላማዬ ሄዋንን እንጂ ፣ ቤቲን መሆን ስላልሆነ፣ ልቤ ወደ ሄዋን ምክር አደላ። ሐሳቤ ፊቴ ላይ አስታወቀብኝ መሰል፣ ቤቲ በራስሽ ጉዳይ ትከሻዋን ሰበቀች ።

ሺህ ጊዜ ትስበቅ።

''ለእኔ ያላት እንጀራ ትሻገታለች እንጂ ማንም አይበላትም!'' ይላል ሃበሻ። ለኔ ያለው ባል ቆሞ ይቀራል እንጂ ማንም አያገባውም።

እስቲጠይቀኝ አልጠይቀውም።

አንዱን ቅዳሜ መስፍኔ ቤት አድሬ ካልጋ ላለመውጣት አገላብጣለሁ። ጥልኝ ሲወጣ ተገርሜ፣

''በናትህ ዛሬ እንደ ሮማን እና ፀጋዬ አልጋ ውስጥ እንበስብስ''

አልኩት።

የበአሉ ግርማ በተለይ የኦሮማይ ፍቅሩ ሌላ ነው። ከአስራ አምስት ጊዜ በላይ እንዳነበበው፣ ከአስራ አምስት ጊዜ በላይ ነግሮኛል። አልጋ ውስጥ አብሮኝ ማርፍድ ከፈለገ ሁሌም የሚለኝ ነገር ነው።
እንደ ሮማን እና ፀጋዬ አልጋ ውስጥ እንበስብስ።

''አይ....ባንክ መሄድ አለብኝ....'' አለ፣ ትላንት አውልቆ የጣለውን ካኪ ሱሪና ሸሚዝ ቶሎ ቶሎ እየለበሰ።

''ባንክ? ብር ለማውጣት ከሆነ ኤቲኤም አለህ... አይደል፣ አልኩልኝ፣ ሀሌላ ጎኔ ተገላብጬ። በዐይኖቼ ስቤ አልጋ ውስጥልጨምረው እየተስለመለምኩ።

''አይደለም..... አርባ ስልሳ ማስገባት አለብኝ.... ቀኑ አልፎብኛል....ትላንት ወይንዬ የሷን ስታሰገባ የኔንም አስገቢልኝ ብዬ እሰጣታለሁ ብዬ እረሳው። ጫማውን ማድረግ እየጀመረ መለሰ። አርባ ስልሳ ይቆጥባል! ልቤ በስስ ካኔተራዬ ላይ ትር ትር ስትል እስኪሰማኝ ደስ አለኝ። አርባ ስልሳ የሚቆጥብ ወንድ ስለ ወደፊት የማያስብ ነው።ስለወደፊት የማያስብ ወንድ ደግሞ ስለትዳር የማያስብ ነው። ስለትዳር ካሰበ ደግሞ....

የልቤን ፈንጠዝያ በቃላት አሽጌ ከአፌ ላወጣው ስል፤ ሄዋን ትዝ አለችኝ።

''እንዲያገባሽ ከፈለክሽ ትዳር የሚባል ሃሳብ እንደሌለሽ ማሳየት አለብሽ....ወንድ ልጅ የማወደው እንደዚያ አይነቷን ነው....ሰናይን አታዬውም...በሁለት አመቱ እራሱ አገባኝ.....''

''አርባ ስልሳ ትቆጥባለህ እንዴ....? ውይ ምስኪን.'' አልጋው ጫፍ ላይ ተቀምጦ ሁለተኛ ጫማውን እያሰረ ነበር። አንገቱን ዞር አድርጎ አየኝና፣

''ምስኪን?'' አለኝ።

''አዎ...ሕልም እኮ ነው እሱ...ዝም ብለህ ነው...እኔን አታይም? ቤተሰቦቼ ጋር በዚህ እድሜዬ የምኖረው ለምን ይመስልካል? ተስፋ የለውም። መቶ ፐርሰንት ለከፈልኩት አከፋፍለው ጨረሱት አይደል...?'' አልኩ ቃላቶቼ እያነቁኝ።

''እና ዘላለም የሰው ኩሽና ውስጥ ኑር ነው የምትይኝ? መሞከር አይሻልም?'' አለኝ ተነስቶ እየቆመ።

''መሞከር ....እኔ የማላውቀውን ወደፊት ለማሳካት መሞከር ምናምን አይገባኝም...ይልቅ ዛሬን ነው መኖር...''

ዝም አለ።

''ስማ መስፍኔ...'' አልኩት ጃኬቱን ለብሶ ለመውጣት ሲሰናዳ ፣

''ወይ....''

''እነ ቤቲ እኮ አስመራና ምፅዋ ሄደው መጡ....ብንሄድ አሪፍ አደለም?''

''አስመራና ምፅዋ?''

''አዎ...ትኬት ውድ ግን የሚያውቁት ሰው ስላለ የሆቴል ወጪ ብዙ አይኖርብንም....ለምን ሄደን ሽር ብትን አንልም....
የድሮ ባህራችን ላይ?''

''ከየት መጣልሽ ይሄ ሀሳብ?''

''አንተ ነህ ኦሮማይ አስመራ....ኤርትራ ምናምን የምትለው በፅሁፍ የምታውቀዎን ሀገር ብታይ ደስ አይልህም?''

ዝም ብሎ ሲያየኝ ቆየና ፣

''አሁን መሄድ አለብኝ ማዲዬ። ከፈሐግሽ እዚሁ ቆዬኝ....ከፈለግሽ ደግሞ ቆልፈሽ ሂጂ...'' ብሎ ከንፈሬን ለዐመል ስሞኝ ወጣ።

እንደ ወጣ ለሄዋን ደውዬ ግዴለሽ የመምሰል ገድሌን እንደጀመርኩ ነገርኳት፣ ''አንበሳ'' ብላ አንቆለጳጰሰችኝ። ''በዚሁ ከቀጠልሽ በዓመት ውስጥ ቬሎ ትለብሻለሽ'' ብላ አበረታታችኝ። ትንሽ አብዝቼው ይሆን በሚል ጥርጣሬ ገብቶት የነበረው ልቤ ረጋ።
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
ከሳምንት በኋላ ልደቱ ስለነበር፣ አዲስአባ ውስጥ ምርጡን ክላርክ ጫማ ያስመጣል የተባልኩት ቤት ሄጄ የደሞዜን አርባ አምስት ፐርሰት ሆጭ አድርጌ ጫማ ገዛሁለትና፣ የሚወዳቸውን ምግቦች ከሁለት ምግብ ቤቶች ገዝቼ፣ ቤት ሄጄ ድግሱንም ራሴንም አዘጋጅቼ እጠብቀዋለሁ። ለአንድ ሰአት እሩብ ጉዳይ ላይ መጣ። እንኳኖ ተወለድክልኝ ምናምን ብዬ አቅፌ ስሜው ራት እየበላን ነበር። ''ምንድን ነው ይሄ ሁሉ?''...

💫ይቀጥላል💫

ለአስተያየቶ @atronosebot ን ይጠቀሙ መልካም ምሽት። 🙏
👍1
#ለእኔ_ያላት_እንጀራ
:
#በሕይወት_እምሻው
:
:
#ክፍል_ሦስት (የመጨረሻ ክፍል)
:
:
...''ምንድን ነው ይሄ ሁሉ ?'' አለ፣ አንዴ እኔን አንዴ ትንሾ ጠረጴዛ ላይ ተፋፍገው የተቀመጡትን የምግብ የምግብ አይነቶች ፣ ከዚያ ደግሞ በትልቅ ብልጭልጭ ወረቀት የጠቀለልኩትን ስጦታዬን እያየ።

ሻማም አልቀረኝ።

''ልደትህ አይደል.... በደንብ ይከበርልህ ብዬ ነዋ ...'' አልኩት ፣ ከጥብሱ ጎርሼ ቀይ ወይኔን እየተጎነጨሁ...

''እሱማ ገባኝ ግን በጣም በዛ ሜዲዬ...ብዙ ወጪ ሳታወጪ አትቀሪም ለዚህ ሁሉ....''

''ታድያ ምናባቱ! እኔ ለዛሬ ነው የምኖረው ጌታዬ!'' አልኩ! ግራ እጁን ጎትቼ ጭምቅ አድርጌ እየያዝኩ። ሰውነቴ የኔ ነው አፌ ግን የሄዋን ከሆነ ቆየ። ዝም አለ።

''ደስ አላለክም መስፍኔ?'' እጁን እንደያዝኩ ጠየቅኩ።

''ደስ ብሎኛል....'' ቅዝዝ ብሎ መለሰ ራት ስንጨርስ ስጦታውን ሰጠሁት። ዋጋውን ጠየቀኝ።

''እንዴት የስጦታ ዋጋ ይጠየቃል ?'' ምናምን ብዬ አኮረፍኩት።

''ውድ ይመስላል....'' አለኝ።

''እና?''

''አይ ምንም....''

ልደቱን ካከበርን በኋላ ባሉት ሳምንታት፣ መስፍኔ ቀስ በቀስ እየተሸራረፈ ሌላ ሰው መሆን ጀመረ።

ስደውል አያነሳም። ሲያነሳ ሰበብ ይደረድራል። አንዴ ''ስራ በዝቶ ነው፣ስብሰባ ነበርርን፣ ስልኬ ጠፍቶ ነበር፣ ካርድ አልነበረኝም....''

ዓይነት።

ቴክስትም ስልክ አይመልስም። ለአስር ቴክስት አንድ ሲመልስም ሰበብ ይደረድራል፣ ወይ ስሜት የሌለው ነገር ይፅፋል። ለምሳሌ ''ትንሹ መስፍኔ ናፈቀኝ ዛሬ አብረን አናድርም?'' ዓይነት ነገር ፅፌለት፣ ''ኢን ኤ ሚቲንግ'' ምናምን የሚል ከስልኩ ጋር የመጣ መጠባበቅያ መልእክት ይልክልኛል። ካልመለሰልኝ ደግሞ አግኝቼው ''ምነው?'' ስለው፣ ''ካርድ የለውም ነበር። ስብሰባ አለቃዬ ፊት ተቀምጬ ስለነበር ነው'' ይለኛል።

እንደበፊቱ ቀን በቀን ቀርቶ ፣ በሳምንት አንዴ ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘን ባለቀ ሰአት ይሰርዝብኛል ሲሰርዝ ሰበብ ይደረድራል ። እንደ ድንገት ፊልድ ሂድ ተባልኩ፣ እማዬን ትንሽ አመማት ፣ ሃይለኛ ጉንፋን ይዞኛል፣ የወይንዬ እናት አረፉ...''ዓይነት።

''ምን አጠፋሁ ?'' ስለው፣

''ውይ አረ ምንም'' ብሎ ፣ ይምላል፣ ይገዘታል። ከሰበቦቹ ተርፈው በማገኘው ቀን ግን ከወትሮው ተለይቶ ዝም ይለኛል። ፊቴ ይደበታል። አጠገቡ በመቀመጤ አየሩን የተሻማሁ እስኪመስለኝ ድረስ ዐስሬ ቁና ቁና ይተነፍሳል።

ጨነቀኝ።

ጠማማ እድሌ አድብቶና ዘግይቶ፣ቀስ ብሎ የቀደመኝ መሰለኝ። ብሮጥ የማላመልጠው የአርባ ቀን እድል አለኝ ልበል? ጸደቀ ያልኩት የሚደርቅብኝ፣ ሞቀ ያልኩት የሚበርድብኝ፣ የሣሣሁለት የሚሸሸኝ ለምንድን ነው ?

ሳምንታት በእንዲህ ሁኔታ ሲያልፉ የማደርገው ጠፋኝና ተውኩት። ሄዋን፣ ''ወንድ እንዲህ ነው። መወትወትሽን ብታቆሚ ራሱ ይፈልግሻል'' ስትለኝ ተውኩት።

ግን እኔ መደወል ሳቆም በስልክም መነጋገር አቆምን። እኔ እንገናኝ ብዬ መጠየቅ ስተው መገናኘት ተውን። ጥፋቴ ሳይገባኝ እንደዛ የወደድኩት ሰው እንደ ጠዋት ጤዛ ባንዴ ታይቶ ባንዴ ጠፋ።

ጠፋ፣ ጠፋ፣
፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥
ከሰባት ወራት በኋላ......

ከመስፍኔ ህመም እንደምንም ማገገም በጀመርኩበት ሰሞን፣ ከቤቲና ሄዋን ጋር ቁጭ ብለን ቡና እየጠጣን ነበር። ከማይረባ ብዙ ወሬ በኋላ ቢቲ በተለመደ ችኮላዋ ፣

''ሰምተን መደበቅ ሙድ የለውም...በቃ ዕወቂው '' አለች እያየችኝ ሄዋን ክው አለችና ፣ ''በናትሽ ቤቲ ..! ራሷ ሌላ ጊዜ ትስማው በናትሽ'' አለች።

''ምንድን?'' አልኩኝ ቆጣ ብዬ...

ተያዩ።

''ምንድን ነው ለምን አትነግሩኝም?'' አልኩ እንደገና ተቆትቼ። ቤቲ ያለወትሮዋ ትንሽ አቅማማችና ፣

''ማዲዬ...፣ መስፍን አግብቶል። ማወቅ አለብሽ ብዬ ነው...''

አለች።

እሳት የተፋችብኝ ይመስል ፊቴ ተቃጠለ። በቀለም ተነፍታ በነበልባል የምትቃጠል ዶሮ የሆንኩ መሰለኝ። አጥንቶቼ ሁሉ የቀለጡና ከስጋ ብቻ የተሰራሁ መሰለኝ። ምራቄ ከአፌ ያለቀ መሰለኝ። እንደምንም ሶፋውን ደገፍ ብዬ ሁለቱንም አየኋቸው።

''ሶሪ ማዲዬ በቃ...ተይው...'' አለች ሄዋን ፣ ፀጉሬን እየደባበሰች። ''ራይድ ጥሩልኝ ቤቴ መሄድ እፈልጋለው....'' ስል ብቻ ትዝ ይለኛል።

ቤቴ ገብቼ አንዴ እያለቀስኩ፣ አንድ በንዴት ጦፌ መኝታ ቤቴ ውስጥ እየተንጎራደድኩየሆነውን ሁሉ አንድ በአንድ ሳብሰለስል ብውልም ፣ ባወጣም ባወርድም፣ የሆነው ለምን እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም። የእኔና የመስፍኔ መጨረሻ ይሄ መሆኑ በምንም ስሌት ባስበው ሊገባኝ አልቻለም ።

ሞባይሌን አንስቼ ሰዐቴን ዐየሁ። ሁለት ሰዐት ከሀምሳ አምስት ደቂቃ። በጣም አልመሸም።

ደወልኩት። ለመስፍኔ ደወልኩለት ። ያነሳ ይሆን ሁለቴ እንኳን ሳይጠራ አነሳው። ይባስ ብሎ፤ ልክ ስልኬን ይጠብቅ እንደነበር ሰው ፣ ሳይገረም ሰላም አለኝ።

''ሃይ....መሀደር እንዴት ነሽ?''

ማህደር? ማህደር ነው ያለኝ?

''ደህና ነኝ...እንኳን ደስ ያለክ ልልክ ነው...''

''አመሰግናለው....አንቺ ደህና ነሽ?''

''ደህና ነኝ...ማውራት ትችል ይሆን ? አንድ ነገር ልጠይቅክ ነበር?''

''እንችላለን...''

ስሜቴን ተቆጣጠርኩ። ጉሮሮዬን ጠረኩ። ቃላቶቼን መረጥኩ።

''በዚህ ፍጥነት እንዴት አገባህ...? ማለቴ...ማ..ለቴ ለምን እኔን ለማግባት...''

ሳልጨርስ አቋረጠኝ።

''ትዳር የምትፈልጊ አልመሰለኝም...ማህደር ፣ እኔ ሀያ ምናምን ዓመት ሙሉ ገርል ፍሬንድ ነበረኝ። በዚህ እድሜዬ ሚስት ነበር የምፈልገው....ሳይሽ ስለወደፊት አታስቢም ...እና...ጊዜ ማጥፋት አልፈለኩም ....እ?''

ዝም አልኩ።

''ማህደር?''

''አ..ለ..ሁ....'' አልኩ። ግን አልነበርኩም።

''እህ...ማንን ነው ያገባከው?'' አልኩ፣ የሚያውቃቸውን ሴቶች በሙሉ በአእምሮዬ ሳመላልስ መዋሌ በማያስታውቅ ሁኔታ።

''እ..ወይንሸትን...ወይንዬን ነው ....''

ባለ አርባ ስልሳዋ ወይንሸት !

ምን ብዬ እንደጨረስኩ ሳላውቅ ስልኩን ዘጋሁ ። ፊቴ እንደገና ሲነድ፣ዐጥንቴ በንዴት ሲቀልጥ ይሰማኛል። አልጋዬ ላይ ተዘረጋሁ።

ለኔ ያላትን እንጀራ እኔ ብገፋትም አልሻገተችም። ወይንሸት በልታታለች።

ሔዋን.... አንቺ ደሞ አፈር ብዬ። አፈር ያስበላሽ።

🔘አለቀ🔘

ለአስተያየቶ @atronosebot ን ይጠቀሙ መልካም ምሽት። 🙏
👍4😁21