አትሮኖስ
286K subscribers
122 photos
3 videos
41 files
576 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
ፍርሥራሽ ብቻ አገኘን፡፡
እናትና አባቴ ቤታቸውን መልሰው ሰሩት፡፡ የተከሰተውንም ነገር ቢያንስ ከኛ ከልጆች ጋር ፈጽመው ተወያይተውበት አያውቁም፡፡ ምንም እንኳን ወላጆቼ በ1959 በተመሳሳይ ጸረ-ቱትሲ ረብሻዎች ዒላማ የነበሩ ቢሆንም ሁቱዎችን የሚያጥላላ አንዳች ቃል ሲናገሩ ሰምቻቸው አላውቅም፡፡ በፍጹም የመሠረተ-ቢስ ጥላቻ ተጠቂዎች አልነበሩም፡፡ ይልቁንም ከዘውግም ሆነ ዘር ይልቅ ርኩስ መንፈስ ሰዎችን ክፉ ነገር እንዲያደርጉ አነሳስቷቸዋል ብለው ያምናሉ፡፡ እናቴና አባቴ ይኖሩበት የነበረውን ማኅበራዊና አስተዳደራዊ እውነታ ቸል ብለው ይልቁንም ሁሉም እኩል ነው እያሉ ያስገነዝባሉ፡፡ ልጆቻቸውን ቱትሲ ሆነው ስለተወለዱ የሌለ የበታችነት ስሜት እየተሰማቸው እንዲያድጉ አልፈለጉም፡፡

ስለዚህ መምህሬ ቡሆሮ ዘውጌን ባለማወቄ ሲያበሻቅጠኝ ለምን ግራ እንደገባኝ መገንዘብ አይከብድም፡፡
ዳማሲን የዚያን ቀን እጁን በትከሻዬ ጣል አድርጎ አቅፎኝ ወደ ቤት ወሰደኝ፡፡ ሁለታችንም አንድ አጉል ነገር እንደገጠመን ገብቶናል፤ ምንነቱን ግን አላወቅነውም፡፡ በዚያን ምሽት ራት ላይ ለአባቴ የተከሰተውን ነገር ነገርኩት፡፡ ጸጥ ብሎ ቆየና ከመማሪያ ክፍል ውጪ ከተባልኩ በኋላ ለምን ያህል ጊዜ በጥሻ ውስጥ ተቀምጬ ሳለቅስ እንደቆየሁ ጠየቀኝ፡፡
‹‹ሙሉ ቀን ሊሆን ምንም አልቀረው አባባ፡፡››
አባቴ ሹካውን አስቀምጦ መብላቱን አቆመ - ይህም እንደተናደደ የሚያሳይ እርግጠኛ ምልክት ነው፡፡ ‹‹ቡሆሮን ነገ አናግረዋለሁ›› አለኝ፡፡
‹‹ግን አባባ፣ ምን ዘውግ ነኝ?››
‹‹አይ! አሁን ስለዚያ አትጨነቂ፡፡ እሱን ነገ አስተማሪሽን ካነጋገርኩት በኋላ ልንወያይበት እንችላለን፡፡››
ምን ዘውግ እንደሆንኩ በዚያኑ ሰዓት ለምን እንደማይነግረኝ ለመጠየቅ ፈለግሁ፤ ሆኖም ግን በቤታችን አዋቂዎችን እንጠይቅ ዘንድ አይፈለግም፡፡ አባቴ እውነታውንም ለመደበቅ ፈልጎ ከሆነ ጥሩ ምክንያት እንደነበረው ገመትኩ፡፡ ቢሆንም ግን ተጨነቅሁ - ሁሉም የቤተሰቤ አባላት ስለ ዘውግ ሲያወሩ ለምን በጣም እንደተበሳጩ ሊገባኝ አልቻለም!
አባቴ በሚቀጥለው ቀን መምህሬን ቢያናግረውም ስለምን እንደተወያዩና ዘውጌም ምን እንደነበር ባለፈው ቀን እነግርሻለሁ ባለው መሠረት አልነገረኝም፡፡ እስከቀጣዩ ሳምንት፣ ማለትም ቡሆሮ በድጋሚ ስም ጥሪ እስኪያካሂድ ድረስ፣ የዚያን ጉዳይ መልስ አላገኘሁም፡፡ መቼም አባቴ ሳያሸማቅቀው አልቀረም፤ ከስም ጥሪ በፊት ወደሚቀመጥበት ወንበር ጠርቶ እጅግ በለሰለሰ ድምፅ አናገረኝ፡፡
‹‹ኢማኪዩሌ፣ ‹ቱትሲ› ስል ተነሺ፡፡››
ወደ መቀመጫዬ ተመልሼ ስሄድ በልቤ በቃ ቱትሲ ነኝ ማለት ነው ብዬ ፈገግ አልኩ - እሰይ! ብዬ በማሰብ፡፡ ቱትሲ ምን እንደሆነ ምንም የማውቀው ነገር አልነበረኝም፡፡ ከፋም ለማም አንዱን ጎራ በመቀላቀሌ ኮራሁ፡፡ በክፍሉ የተወሰን ቱትሲዎች ብቻ ስላለን የተለየን እንደሆን አሰብኩ - በዚያም ላይ ‹ቱትሲ› ስሙ ያምርና ሲሉትም ደስ ያሰኝ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ግን በቱትሲና ሁቱ ዘውጎች መካከል ይህ ነው የሚባል ልዩነት ማየት አልቻልኩም፡፡ ትዋዎች አካላቸው አነስተኛ በመሆኑ ለመለየት አያዳግቱም፡፡ አንድም ትዋ ግን ትምህርት ቤት ስለማይመጣ በሕይወቴ ያየኋቸው በጣም የተወሰኑ ናቸው፡፡ በሁቱዎችና ቱትሲዎች መካከል ያሉት ልዩነቶች ለመለየት የሚከብዱ ናቸው፡፡ ቱትሲዎች ረዘም፣ መልካቸው ፈካ ያለና ሰልከክ፣ ጠበብ ያለ አፍንጫ ያላቸው ናቸው ተብሎ ይታመናል፡፡ ሁቱዎች ደግሞ አጠር፣ ጠቆር ያሉና አፍንጫቸው ሰፋ ያለ ተደርገው ይታሰባሉ፡፡ ሆኖም ግን ያ ፈጽሞ እውነት አልነበረም፤ ምክንያቱም ሁቱዎችና ቱትሲዎች እርስ በእርሳቸው ለምዕተ-ዓመታት ሲጋቡ ስለኖሩ የዘረመል መለያዎቻችን ተቀላቅለዋል፡፡ ሁቱዎችና ቱትሲዎች ኪንያሩዋንዳ የሚባል ቋንቋ ይናገራሉ፡፡ ተመሳሳይ ታሪክም ይጋራሉ፡፡ ከሞላ ጎደል አንድ ባህል ነበረን - አንድ ዓይነት መዝሙሮችን የምንዘምር፣ አንድ ዓይነት መሬት ላይ የምንኖር፣ አንድ ዓይነት የእምነት ሥፍራዎችን የምንሳለምና አንድ አምላክ የምናመልክ ነበርን፡፡ ኑሯችንም በተመሳሳይ መንደሮች፣ መንገዶችና አብዛኛውን ጊዜም በአንድ ዓይነት ቤቶች ጭምር ነበር፡፡
በልጅ ዓይኔ (ወይም ቢያንስ በኔ ዓይን) ሳየው ሁላችንም አብረን መኖር የምንችል እንመስል ነበር፡፡ ሁቱዋ ጓደኛዬ ዣኔትና እኔ በእያንዳንዳችን ቤቶች ራት የበላንባቸውን ጊዜያት ቆጥሬ አልጨርሳቸውም፡፡ በልጅነቴ በሩዋንዳ የተለያዩ ዘውጎች መኖራቸውን ትዝ የሚያስብለኝ ነገር ቢኖር በመማሪያ ክፍል በሳምንት አንድ ጊዜ ለዘውግ ጥሪው መነሳቴ ብቻ ነው፡፡ የሚያበሳጭ ነገር! ሆኖም ግን ያኔ የመድሎውን ትርጉም ገና ስላላወቅሁ ብዙ አላስጨነቀኝም፡፡
ያም የሆነው ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መግባት እስከፈለግሁበት ጊዜ ነው፡፡
አሥራ አምስት ዓመት ዕድሜዬ በነበረ ጊዜ ስምንተኛ ክፍልን ስድሳ ተማሪዎች በነበሩበት ክፍሌ ሁለተኛ በመውጣት ጨረስኩ፡፡ 94 በመቶ አማካይ ውጤት አግኝቼ፣ አንደኛ ከወጣው ቱትሲ ተማሪ በሁለት ነጥብ ብቻ ዝቅ ብዬና ከሌሎችም ተማሪዎች በጣም በልጬ ነበር፡፡ በክፍለ ሀገሩ ከነበሩት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአንዱ ቦታና ነጻ የትምህርት ዕድልም ለማግኘት ከበቂ በላይ የሆነ ነጥብ ነው፡፡ በትምህርት ዓመቱ መጨረሻም ስለ አዲሱ የትምህርት ቤት የደንብ ልብሴ በማለምና ከቤተሰብ ርቆ ሁሉም ትምህርቶች በፈረንሳይኛ በሚሰጥበት ጥሩ ትምህርት ቤት መማር ምን እንደሚመስል በማሰብ እየጓጓሁ ወደ ቤቴ ሄድኩ፡፡ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴም በኋላ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት አቀድኩ፤ ከዚያ በኋላ ማን ያውቃል? አየር አብራሪ፣ የዩኒቨርሲቲ መምህርት፣ ወይንም የሥነ ልቦና ባለሙያ ልሆን እችላለሁ (በነገራችን ላይ በልጅነቴ መነኩሲት ለመሆን የነበረኝን ሐሳብ እርግፍ አድርጌ ትቼዋለሁ)፡፡ ወላጆቼ ጠንክሮ በመሥራትና በቁርጠኝነት ከማታባ ዓይነቷ ትንሽ መንደርም አንዲት ትንሽ ሴት ልጅ ትልቅ ሰው መሆን እንደምትችል አስተምረውኛል፡፡
ይህን በመመኘቴ ግብዝ ልጅ እንደሚያስብለኝ እንዴት ላውቅ እችላለሁ? እነዚያ ሳምንታዊ ዘውጋዊ የስም ጥሪዎች መጥፎ ዓላማ እንዳላቸው መች ጠርጥሬ! ያም መጥፎ ዓላማቸው ቱትሲ ሕፃናትን ‹‹ዘውጋዊ ምጣኔ›› የተባለ የግዙፍ መድሎ ዕቅድ አካል ማድረግ ኖሯል፡፡
በ1973ቱ መፈንቅለ-መንግሥት ሥልጣን የጨበጡት ሁቱው ርዕሰ-ብሔር ዡቬናል ሃብያሪማና የሚያስተባብሩት ይህ ዕቅድ መንግሥቱ የሀገሪቱን የዘውግ ስብጥር ለማንጸባረቅ የትምህርት ዕድል አሰጣጡንና ጥሩ የመንግሥት ሥራ ምደባን ‹‹ማመጣጠን›› አለበት ተብሎ የታወጀበት ነው፡፡ የሩዋንዳ ሕዝብ 85 በመቶ ገደማ ሁቱ፣ 14 በመቶ ቱትሲና አንድ በመቶ ትዋ ስለነበር አብዛኞቹ ሥራዎችና የትምህርት ዕድሎችም ለሁቱዎች ተሰጡ፡፡ በዕቅዱ ትግበራ በትክክል የተደረገው ቱትሲዎችን ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት፣ ከዩኒቨርሲቲና ጥሩ ደምወዝና ጥቅማጥቅም ከሚገኝባቸው ሥራዎች ማራቅ ሲሆን ይህም ሁለተኛ ዜጎች ሆነው መቅረታቸውን አረጋግጧል፡፡ የዘውግ ምጣኔው እውነተኛ ትርጉም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ከመጀመሬ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ተገለጠልኝ፡፡ ቤተሰቤ ለራት በተሰበሰበበት ሰዓት አንድ ጎረቤታችን መጥቶ ስሜ በመንደራችን አዳራሽ ጋር በተለጠፈው የትምህርት ዕድል ያገኙ ልጆች ስም ዝርዝር ውስጥ አለመካተቱን
👍1
ረዳን፡፡ ከፍተኛ ውጤት ባስመዘግብም ቱትሲ በመሆኔ ተዘልያለሁ - ሁሉም የነበሩት ቦታዎች ከኔ በጣም ያነሰ ውጤት ላገኙት ሁቱዎች ተሰጥተዋል፡፡ አንደኛ ወጥቶ የነበረው ቱትሲው ልጅም በዘውጉ ምክንያትነት ብቻ እድሉ ተጨናግፏል፡፡
አባቴ ወንበሩን ከጠረጴዛው ራቅ አድርጎ ወሰደና ዓይኖቹን በኃይል ጨፍኖ ለረጅም ጊዜ ተቀመጠ - በሐሳብ ባሕር ውስጥ የሰጠመ መሰለኝ - አድርጎ የማያውቀውን ነገር፡፡ ወላጆቼ ከመንግሥት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሥር እጥፍ ክፍያው በሚወደደው የግል ትምህርት ቤት እኔን ለማስተማር አቅሙ እንደማይኖራቸው አውቃለሁ፡፡ ሁለቱም ታላላቅ ወንድሞቼ ሌላ ቦታ በትምህርት ላይ ስለነበሩ ገንዘብ ይቸግረናል፡፡ በዚያም ላይ በሩዋንዳ የነበሩ የግል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መንግሥት ወጪያቸውን ከሚሸፍንላቸው የመንግሥት ትምህርት ቤቶች አንጻር በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ነበሩ፡፡ መምህራኑም ቢሆኑ ጥሩ የትምህርት ዝግጅት ያልነበራቸው፣ ሥርዓተ-ትምህርቱ እዚህ ግባ የማይባል፣ ብሎም ሕንጻዎቹ አስቀያሚና ለመማር የማይጋብዙ ነበሩ፡፡
‹‹አትጨነቂ ኢማኪዩሌ፡፡ የምትማሪበትን ሌላ መንገድ እንፈልጋለን›› በማለት አባቴ መጨረሻ ላይ ውሳኔውን አሳውቆኝ ስለ ገበታው ይቅርታ በመጠየቅ ምግቡን እንኳን ሳይጨርስ ወደ ማንበቢያ ክፍሉ ሄደ፡፡
‹‹ተስፋ አትቁረጪ›› ብላ እናቴም አቀፈችኝ፡፡ ‹‹ሁላችንም በዚህ ጉዳይ ላይ እንጸልይበታለን፡፡ አሁን ራትሽን ብዪ፡፡››
ከእራት በኋላ የአባቴን የግል ክፍል ዘግቼ ተቀምጬ እያለቀስኩ በትምህርት ቤት ልቤ እስኪጠፋ ያጠናሁትና የለፋሁት የከፍተኛ ትምህርት ሕልሜ እንዲህ ሊከስም ኖሯል? ስል አስብኩ፡፡ የወደፊት ዕጣ-ፈንታዬ ምን እንደሚሆን ሳስበው አንቀጠቀጠኝ፡፡ በማኅበረሰቤ ምንም ያልተማሩ ሴቶች እንዴት እንደሚያዙ አይቻለሁ፡፡ ምንም ዓይነት መብት፣ ተስፋ ወይም ክብር አልነበራቸውም፡፡ ቢያንስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን ካልተማርኩ አንድ ወንድ ወደ ቤታችን መጥቶ በሚስትነት እስኪወስደኝ ከመጠበቅ በስተቀር ምንም አማራጭ አይኖረኝም፡፡ ገና በአሥራአምስት ዓመቴ የወደፊት ሕይወቴ ተስፋ የማይታይበት መሰለኝ፡፡ በማግስቱ ጠዋት አባቴ በቁርስ ገበታችን ላይ አልተገኘም፡፡
‹‹ትንሽ ተአምር ለመሥራት እየሞከረ ነው›› በማለት እናቴ አስረዳችኝ፡፡
‹‹አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶችን ያስገቡሽ እንደሆነ ለመጠየቅ ሄዷል፡፡››
‹‹እማማ፣ ግን እኮ በጣም ውድ ነው፤ አንችልም እኮ - ››
‹‹እሽሽ›› አለችና አቋረጠችኝ፡፡ ‹‹ተስፋ እንዳትቆርጭ ነግሬሻለሁ እኮ፣ አይደል?›› በኋላ ነገሩ ሲገባኝ አባቴ ማልዶ ከቤት የወጣው እኔን ወደ ግል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለማስገባት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማግኘት ሁለቱን ላሞቻችንን ለመሸጥ ኖሯል፡፡ በሩዋንዳ ባህል ላሞች የማኅበራዊ ደረጃ መገለጫዎችና በጣም ዋጋ የሚሰጣቸው ንብረቶች ስለነበሩ አንድ ላም እንኳን መሸጥ አባካኝነት ሲሆን ሁለት መሸጥ ደግሞ በገንዘብ ረገድ ውድቀትን ያስከትላል፡፡ አባቴ ግን ከትምህርት ገበታዬ መለየት እንደሌለብኝ ቆርጧል፡፡ ከላሞቹ ሽያጭ ያገኘውን ገንዘብ ይዞ፣ በስተደቡብ ሦስት ሰዓት በተሸከርካሪው አዲስ ወደተከፈተው የግል ትምህርት ቤት ሄዶ የመጀመሪያ ዓመት የትምህርት ክፍያዬን በጥሬ ገንዘብ ከፈለልኝ፡፡ በሰው ፊት ስሜቱን በግልጽ ማሳየት ለአባቴ የሚያዳግተው ቢሆንም ለእኔ የነበረውን ፍቅር መደበቅ ግን አይሆንለትም፡፡
ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ ተጠናቅቄ ለመሄድ ተዘጋጀሁ፡፡ ዣኔት አቅፋ ተሰናበተችኝ፤ ተላቅሰን ብዙ ደብዳቤ ለመጻጻፍ ቃል ተገባባን፡፡ እናቴ እንባዋን እየተቆጣጠረች ደጋግማ ሳመችኝ፡፡ በቤታችን ካለነው ልጆች ትንሹ፣ ቪያኒ፣ ወደግል ክፍሉ ሄዶ መሰናበት አለመፈለጉን አሳየ፡፡ እኔና አባቴ በተሽከርካሪያችን ስንሄድ ብዙ ጎረቤቶቻችን ሊሰናበቱን ወጡ፡፡ ማታባን ለቅቄ ስሄድ የመለየት ሥቃይ ቢሰማኝም አዲሱን ሕይወቴን ለመጀመር ግን ጓጓሁ፡፡

አዲሱ ትምህርት ቤቴ ያን ያህል የሚወደድ አልነበረም፡፡ ጠባቡ መኝታ ክፍላችን ወለሉ ሊሾ ቢሆንም ከአሸዋ፣ ስሚንቶና ድንጋይ ከሰል ድቃቂ የተሠራው ጣውላ መሰል የግድግዳው ልባጥ ቀለም ቀቡኝ ቀቡኝ ይል ነበር፡፡ በጣም ተቀራርበው በተደረደሩና የክፍሉን ወለል ሙሉ በሙሉ በሸፈኑ ፍራሾች ላይ ከሌሎች አሥር ሴት ልጆች ጋር እተኛለሁ፡፡ የቧንቧ ውሃ ስለሌለ በየማለዳው ባልዲ እየያዝን ወደ አቅራቢያችን ምንጭ ሄደን ለማጠቢያና ምግብ ማሰናጃ የሚሆነን ውሃ እንቀዳለን፡፡ በቤቴ የነበረኝ አልጋ፣ የእናቴ ሩዝና ፎሶሊያ ናፈቁኝ፡፡
ይሁን እንጂ በማይስማማኝ ሁኔታ ለዚያች አጭር ጊዜ እንኳን መኖር ከባድ ቢሆንብኝም ትምህርቴን አቋርጬ ቤተሰቦቼ ወደ ቤቴ መልሰው እንዲወስዱኝ ለመጠየቅ ግን አልፈለኩም፡፡ በእርግጥም ለትምህርት ዓመቱ የሚሆኑንን የትምህርት ዓይነቶች የምንመርጥበት ጊዜ ሲደርስ በጣም አስቸጋሪዎቹን ትምህርቶች፣ ሒሳብንና ፊዚክስን፣ መረጥኩ፡፡ አባትና እናቴን ማስደሰት ብቻ ሳይሆን በወንድሞቼም ላይ ነጥብ ማስቆጠር ፈልጌያለሁ፡፡ እንደማናቸውም ሩዋንዳውያን ወንዶች ሁሉ፣ ሴቶች ኩሽና እንጂ መማሪያ ክፍል መገኘት እንደማይገባቸው በመናገር ይሳለቁብኝ ነበር፡፡ ይሁና! አሳያቸዋለሁ!
ከሁለት ዓመታት በኋላ በትምህርት ቤቱ ካሉት ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገቡ ተማሪዎች ውስጥ አንዷ ሆንኩ፡፡ መንግሥት ከፍተኛ ነጥብ ላላቸውና በመንግሥት ትምህርት ቤቶች መግባት ለሚፈልጉ ተማሪዎች ልዩ ፈተና እንደሚፈትን ሲያስታውቅም ለመፈተን ወሰንኩ፡፡ በሀገሪቱ ከፍተኛውን ውጤት ባመጣም እንኳን ዋጋ እንደሌለውና ቱትሲ በመሆኔ አሁንም እንደምዘለል ተሰማኝ፡፡ ቢሆንም ግን በትጋት አጠናሁ:: ፈተናውንም እጅግ በሚያረካኝ መልኩ እንደሠራሁት እርግጠኛ ሆንኩ፡፡ ይሁን እንጂ ምንም ወሬ ሳይሰማ ሳምንታት አለፉ፤ ስለሆነም ጉዳዩን ከአእምሮዬ አወጣሁት፡፡
ከወራት በኋላ ለክረምት ረፍት እቤቴ ሳለሁ ዳማሲን ቁና ቁና እየተነፈሰ እቤት ይመጣና ‹‹ኢማኪዩሌ! ኢማኪዩሌ ኢሊባጊዛ! የሥም ዝርዝሩን አየሁት፤ ፈተናውን አልፈሻል! በሊሴ ደ ኖትረ ደ አፍሪክ ተቀብለውሻል፡፡ በሩዋንዳ ካሉት ምርጥ ትምህርት ቤቶች አንዱ ሲሆን፤ ወደ ትምህርት ቤቱ የሚወስደው መንገድም የሚያልፈው በኔ ትምህርት ቤት አጠገብ ነው!››
በወቅቱ የቤተሰባችን አባላት በሙሉ በዋናው ቤት ስለነበሩ ሁሉም በደስታ አበዱ፡፡ ከመቀመጫዬ ዘልዬ ‹‹ተመስገን እግዚአብሔር፤ ተመስገን ጌታዬ!›› በማለት ጮኬ እያማተብኩ ቤት ውስጥ በአሸናፊነት ጨፈርኩ፡፡ የእናቴ ዓይኖች እንባ አቀረሩ፤ አባቴ በበኩሉ ‹‹ይህ በሕይወቴ ሁሉ ወደር የማይገኝለት ደስታዬ ነው! ላለፉት ሁለት ዓመታት በየቀኑ እየተንበረከክሁ እዚያ ትምህርት ቤት ትገቢልኝ ዘንድ ጸልያለሁ፡፡ ይኸዋ! አምላክ ለልመናዬ መልስ ሰጠኛ!››
‹‹ምንም እንኳን ሴት ብትሆኚ እኮ ጎበዝ ሳትሆኚ አትቀሪም›› እያለ ኤይማብል ቢስቅም በደስታዬ እንደተደሰተልኝ ይታየኛል፡፡
ዳማሲን ቆንጆ ፈገግታውን እያሳየና በኩራት ተሞልቶ ስለነበር የሚፈነዳ መሰለኝ፡፡
ያን ምሽት የቤተሰብ ድግስ ደግሰን በደስታ አሳለፍን፡፡ ለረጅም ጊዜ ካሳለፍናቸው ደስታ የተሞላባቸው ጊዜያት መካከል አንዱ መሆኑ ነው፡፡ ሊሴ የብዙዎቹ የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ሴት ልጆች የሚማሩበት ግሩም የልጃገረዶች ትምህርት ቤት ነበር፡፡ ማንኛዋም ሩዋንዳዊት ብታገኘው
👍3
የምትመኘውን እጅግ ምርጥ የሆነውን ትምህርት ማግኘት ከመቻሌም በላይ ወላጆቼ በግል ትምህርት ቤት ክፍያዎች አይጨናነቁብኝም፡፡ ብቸኛው ችግር ትምህርት ቤቱ ራቅ ብሎ በሚገኘው በጊሰኚ ክፍለ ሀገር መገኘቱ ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ እጅግ በሚያስቸግረው መንገድ ከማታባ የአራት ሰዓት የተሸከርካሪ ጉዞ ስለሚጠይቅ ወላጆቼ ቶሎ ቶሎ ሊጠይቁኝ አይችሉም፡፡ በተጨማሪም ከነዋሪዎቹ የሚበዙት ሁቱዎች በሆኑበትና ለቱትሲዎች ግልጽ ጥላቻ ባለበት አካባቢ የሚገኝ ነው፡፡
‹‹አይዞሽ የልጃገረዶች ትምህርት ቤት ነው›› አለኝ ዳማሲን፡፡ ‹‹ያንቺን ደህንነት ለመጠበቅ ብዙ ዘበኞችና ትልቅ አጥር አለው፡፡ የእኔም ትምህርት ቤት በጣም ቅርብ ስለሆነ ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ እጎበኝሻለሁ፡፡››

ሊሴን ወዲያውኑ ወደድኩት፡፡ ሕንጻዎቹ ሰፋፊ፣ ቆንጆና ንጽሕናቸው ደግሞ እንደ ጸሐይ የሚያበራ ናቸው፡፡ መማሪያ ክፍሎቹ ብሩህ ቀለም ከመቀባታቸውም በላይ በግቢው ዳር እስከዳር ውብ አበቦች ተተክለዋል፡፡ ግቢው ዙሪጰያውን ከፍ ያለ የደህንነት አጥር ስላለው ሰላም ተሰማኝ፡፡ በተለይ መነኩሲቶቹ ከምግብ በፊትና በኋላ እንደምንጸልይ ሲነግሩን እኔ ደስተኛ እንደነበርኩት ሁሉ አባቴም ደስተኛ እንደሚሆን እርግጠኝነት ተሰማኝ፡፡
ሳራ የምትባል ሁቱ ልጅ ካፈራኋቸው የመጀመሪያ ጓደኞቼ ውስጥ አንዷ ነበረች፡፡ እንደ እህት እጅግ የተቀራረብን ሲሆን በሩዋንዳ ዋና ከተማ፣ ኪጋሊ፣ ባለው የቤተሰቧ ቤትም ጋብዛኛለች፡፡ ልከኛ ሕይወት ለለመድኩት ለገጠር ልጇ ለእኔ ወደ ትልቁ ከተማ ያደረግሁት ጉዞ ዓይን መግለጫ ሆነኝ - በተለይ ጠያራዎቹን ለመጀመሪያ ጊዜ ቀርቤ ሳይ፡፡ ሳራና እኔ ወደ አየር ማረፊያው በምሽት ሄደን መንደርደሪያው በረጃጅም መብራቶች ሲደምቅ፣ የማረፊያው ሜዳ በቀይ፣ ነጭና አረንጓዴ የብርሃን ጎርፍ ሲጥለቀለቅ ሳይ፣ ትላልቆቹ ጠያራዎች ከሰማይ ሲወርዱና ጩኸታቸውንም ስሰማ አፌ በአግራሞት ተከፈተ፡፡
‹‹ውይ እስቲ እዪአቸው!›› ስላት ሳራ በሣቅ ሞተች፡፡ ‹‹አሁን እንግዲህ በቃ ሁሉንም ነገር አይቼዋለሁ›› ብዬ ተኩራራሁ፡፡
በመጀመሪያ ቀን ያገኘኋት ሌላኛዋ ጓደኛዬ ዓይናማዋ ክሌሜንታይን ነች፡፡ ከአዳዲስ ተማሪዎች መካከል እንዳየችኝ ወደኔ መጣች፡፡ እኔ ከአብዛኛው ተማሪ በቁመት የምበልጥ ብሆንም እርሷ ግን ይብሱኑ ቢያንስ 1፡80 ያህል ትረዝማለች፡፡ ቱትሲዎች እርስ በርሳችን በቁመታችን እንተዋወቃለን፡፡
‹‹እንዳንቺ ዓይነት ቆንጆ ቱትሲ ልጃገረድ እዚህ ድረስ መጥተሸ ከነዚህ ሁሉ በጠላትነት ከሚያዩሽና ፊታቸውን ከሚያጠቁሩብሽ ሰዎች በአጥር ብቻ ተለያይተሽ እንዴት ነው በማለት ክሌሜንታይን ፈገግ አለች፡፡ ‹‹አብረን መሆንና እርስ በርሳችን መፈላለግ አለብን›› ብለን ወዲያውኑ ጓደኛሞች ሆንን፡፡ ክሌሜንታይን ፊታቸውን ያጠቁሩብሻል ያለችው ልክ ነው፡፡ ከትምህርት ቤቱ አጥር ግቢ ውጪ መሄድ ከባድ ነው - በሄድኩም ጊዜ አገሬው እኔን አትኩሮ ማየቱን እታዘብና በሚያስፈራ ሁኔታ ‹‹ቱትሲ›› እያለ ማንሾካሾኩን እሰማለሁ፡፡ ትምህርት ቤቱን የሚያስተዳድሩት ቄሶችና መነኩሲቶች፣ ተማሪዎችና ያገሬው ሰዎች በቤተክርስቲያን ባንድ ላይ ቅዳሴ እንዳያስቀድሱ ተጠንቅቀው ይጠባበቃሉ፡፡ ያለ ትምህርት ቤታችን ሠራተኞች አጀብ የትምህርት ቤቱን ቅጥር-ግቢ ለቅቀን እንዳንሄድ የሚከለክል ጥብቅ ትዕዛዝም ተሰጥቶናል፡፡ ውጪው ቢያስፈራም በትምህርት ቤቱ ውስጥ ግን ምንም ዓይነት የዘውግ መድሎ አልተሰማኝም፡፡ መምህራን የዘውግ ስም ጥሪ በፍጹም የማይጠሩ ሲሆን አብዛኞቹ ልጆች ሁቱዎች ቢሆኑም ቅርርባችን እንደ ቤተሰብ ነው፡፡


ጊዜዬን በትምህርት ቤት ብቻ እያሳለፍኩ፣ በጣም እያጠናሁና ራሴን ከናፍቆት ስሜት እያራቅሁ ከረምኩ፡፡ ወላጆቼና ሕፃኑ ወንድሜ ግን ይናፍቁኝ ጀመር፡፡ የቪያኒ ጭቅጭቅ ሳይቀር ውል ውል አለኝ፡፡ ሕፃኑን ወንድሜ ልብ የሚነካና የሚያስጨንቅ ደብዳቤ ከቤት ከሄድኩ ከጥቂት ወራት በኋላ ልኮልኛል፡፡ እጅጉን እንደናፈቀኝ፣ እኔ ከተለየሁት ወዲህ መተኛት እንዳልቻለና አንዳንድ ሌሊት ደግሞ መናፍስት ከክፍል ክፍል ሲዘዋወሩ እንደሚያይ ጽፎልኛል፡፡ ባያቸው ጊዜም በመሸበር በቤታችን ውስጥ በድንጋጤ ይሯሯጣል፡፡ ደብዳቤው ልቤን ነካው - አዎ ቪያኒና እኔ ብዙ ጊዜ በሆነ ባልሆነው እንነታረካለን፤ አሁን ግን እኔ ለእርሱ ምን ማለት እንደሆንኩ ገባኝ፡፡ ጥዬው በመጥፋቴ ጥፋተኝነት ሲሰማኝ ለእርሱ የተሻለች እህት ለመሆን ለራሴ ቃል ገባሁ፡፡ ዳማሲን ለቃሉ ታምኖ በወር አንድ ጊዜ ይጠይቀኝ ጀመር፡፡ አብረን በሳሩ ላይ ተቀምጠን ለሰዓታት እናወራለን፡፡ በተለይ ጥናትን በተመለከተ ሁልጊዜ ጥሩ ምክር ይለግሰኛል፡፡
‹‹ጸልዪ ኢማኪዩሌ፡፡ የቤት ሥራሽን ከመሥራትሽ በፊትና ለፈተናዎች በምትዘጋጅበት ጊዜ ሁሉ ጸልዪ፡፡ ከዚያም በቻልሽው መጠን አጥኚ›› ይለኛል፡፡ በምክሩ መሠረትም በተለይ ከሒሳብ ፈተናዎቼ በፊት በጣም በማጥናት በትምህርት ቤቱ ካሉ ተማሪዎች ሁሉ ከፍተኛ ውጤት እያገኘሁ ሄድኩ፡፡ ዳማሲን ሊጠይቀኝ ሲመጣ ሴቶች ጓደኞቼ እንደዚያ አፍ ለአፍ ገጥሜ የማዋራውን ቆንጆ ልጅ ማንነት ሲጠይቁኝ ‹‹ታላቅ ወንድሜ ዳማሲን ነዋ!›› በማለት በኩራት እመልሳለሁ፡፡
‹‹አይ፣ አይሆንም፡፡ ማንም ሰው ከወንድሙ ጋር እንደዚያ አይቀራረብም፡፡ ከእርሱ ጋር መሆንን በእርግጥ የወደድሽው ነው የምትመስይው፡፡›› በሕይወቴ ውድ ዳማሲንን በማግኘቴ በጣም እድለኛ ነበርኩ፡፡

💫ይቀጥላል💫

Like 👍👍 ማድረግ እንዳይረሳ

ማንኛዉንም አስተያየት በ @atronosebot አድርሱን ምን ይጨመር? ምን ይቀነስ? ድርሰቱን እንዴት አገኛችሁት? መልሳችሁን አድርሱን።
አትሮኖስ pinned «#ሁቱትሲ ፡ ፡ #የወጣቷ_ልብ_አንጠልጣይ_ትውስታዎች ፡ #ትርጉም_በመዝምር_ግርማ ፡ ፡ #ምዕራፍ_ሁለት #ከመቀመጫችን_ሲያስነሡን ‹‹ቱትሲዎች ከመቀመጫችሁ ተነሡ!›› አንድ ቀን አራተኛ ክፍል ሆኜ እማርበት በነበረው መማሪያ ክፍል ውስጥ ስድስት ልጆች ከመቀመጫቸው ተስፈንጥረው ሲቆሙ ግማሽ ደርዘን ወንበሮች ወደ ኋላ ተንጓጉ፡፡ ከዚያ በፊት ሁልጊዜ እናቴ በምታስተምርበት አነስተኛ ትምህርት…»
#ሁቱትሲ


#ምዕራፍ_ሦስት


#የወጣቷ_ልብ_አንጠልጣይ_ትውስታዎች

#ትርጉም_በመዝምር_ግርማ

#ቅድመ_ከፍተኛ_ትምህርት

በሦስተኛውና በመጨረሻው ዓመት ጦርነት ከመፈንዳቱ በቀር ሕይወት በሊሴ ጥሩ ነበር፡፡
የ1990 የጥቅምት ወር የመጀመሪያዋ ቀን ከሰዓት ቆንጆና ብሩህ ነበረች፡፡ የክፍል ጓደኞቼና እኔ የግብረገብ ትምህርት ክፍለጊዜያችን እስኪጀምር እየጠበቅን መምህሩ ለምን እንደዘገየ እናስባለን፡፡ አቶ ጋሂጊ ለመግባባት የማያስቸግር፣ የተረጋጋና ምናልባትም ካገኘኋቸው ሰዎች ሁሉ ልስልስ ጸባይ ያለው ነው፡፡ ስለሆነም በመጨረሻ እጆቹን አያይዞ ሲመጣና በክፍሉ ፊትለፊት ወደፊትና ወደኋላ ሄድ መለስ ሲል አንዳች ነገር እንደተከሰተ ገምተናል፡፡ አንደኛዋ ተማሪ ችግሩ ምን እንደሆነ ብትጠይቀውም ወደ እኛ ሳያይ መለስ ቀለስ ማለቱን ቀጠለ፡፡
መምህራችን አንዳች መጥፎ ዜና እንደደበቀንና ምን አልባትም የተንቀሳቃሽ ምስል ትዕይንት ምሽትን መነኩሲቶቹ ሰርዘውት እንደሆነ ሊነግረን ይሆናል ብዬ አሰብኩ፡፡ ጉዳዩ ግን ከዚያ የባሰ ነበር፡፡ በትምህርት ቤት ውስጥ የዜና ዘገባዎችን ማዳመጥ ስለማይፈቀድልን በመኖሪያ ቤቴ እንደነበረው ሁሉ ከዓለም ወሬ ተነጥያለሁ፡፡
‹‹በሀገሪቱ ላይ ጥቃት እንደተፈጸመ ሰማሁ›› ሲል አቶ ጋሂጊ በሃዘኔታ ነገረን፡፡ ‹‹በጣም አደገኛና በሁላችንም ላይ ለረጅም ጊዜ ተጽዕኖ የሚኖረው ይሆናል ብዬ እፈራለሁ፡፡››
ክፍሉ በጸጥታ ተዋጠ - ከዚያ ሁሉም ባንዴ ማውራት ጀመረ፣ ጥያቄ መጠያየቅ፣ ሩዋንዳን ማን ለምን እንደሚያጠቃት ለማወቅ መጠባበቅ፡፡
‹‹በዩጋንዳ የሚኖር የአማጽያን ቡድን የአገሪቱን ድንበር አቋርጧል›› ሲል መለሰልን፡፡ ‹‹በዋነኝነት ከሩዋንዳ የሄዱ ጥገኞች ልጆች ሲሆኑ ተሰባስበው ወደ ሀገሪቱ ለመግባት እየተዋጉ ነው፡፡ ከዚህ ስፍራ በስተሰሜን በኩል በአሁኑ ሰዓት በአማጽያንና በሩዋንዳ መንግሥት ወታደሮች መካከል ከባድ ውጊያ በመካሄድ ላይ ነው፡፡›› አቶ ጋሂጊ ፍርሃትና ንዴትን የሚያንጸባርቅ የጥያቄዎች ዝናብ ወረደበት፡፡ ‹‹ቱትሲዎቹ ሽፍቶች ግን ምንድን ነው የሚፈልጉት? ለምን ጦርነት ይከፍቱብናል? ትምህርት ቤቱ ጋር ከደረሱስ ምን ያደርጉን ይሆን?››
የሃፍረት ሙቀት በማጅራቴ ተሰማኝ፤ በማስደገፊያዬም ስር ለመደበቅ ፈለግሁ፡፡ በክፍሉ ውስጥ ካለነው 50 ተማሪዎች 47ቱ ሁቱዎች ናቸው፡፡ በጣም ስለፈራሁና ስለራሴ ስለተጨነቅሁ ሌሎቹን ሁለት ቱትሲ ልጃገረዶች ማየት እንኳን ተሳነኝ፡፡ በቱትሲነቴ ሳፍርና በሊሴም ተለይቼ ስታይ የመጀመሪያዬ ነው፡፡
‹‹አማጽያኑ ራሳቸውን የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር (ሩአግ) ብለው አደራጅተዋል፡፡ ቡድኑ ሩዋንዳን ከዓመታት በፊት ለቀው የሄዱና እንዳይመለሱ የተከለከሉ የቱትሲዎች ድርጅት ነው፡፡ እነዚህ የውጪ ዜጎች ወደ ሩዋንዳ በመግባት መንግሥታዊውን ለመያዝ ጦርነት አውጀውብናል›› አለ፡፡
ስለ ሩአግ ምንነት ግንዛቤው ነበረኝ፡፡ አባላቱ መንግሥትን ለመጣል ሲሉ ብቻ እንደማይዋጉም አውቃለሁ፡፡ እኩልነት በሰፈነባትና በነጻ ሀገር መኖርን ይፈልጋሉ፡፡ አብዛኞቹ የሩአግ ወታደሮች ስደተኞች ቱትሲዎች ወይንም ልጆቻቸው ናቸው፡፡
በ1959ና በ1973ቱ ችግሮች እንዲሁም ሁቱ ጽንፈኞች የግድያ ዘመቻዎችን ባካሄዱባቸው ሌሎች በርካታ ጊዜያት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ቱትሲዎች የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ሕይወት ለማዳን ከሩዋንዳ ሸሽተዋል፡፡ አቶ ጋሂጊ አማጽያኑን ‹‹የውጪ ዜጎች›› ያላቸው አብዛኞቹ እንደ ዩጋንዳና ዛየር ባሉ ጎረቤት ሀገራት ስላደጉ ነው - ያ የሆነው ግን ርዕሰ-ብሔር ሃብያሪማና ስደተኞች ፈጽሞ ወደ ሀገራቸው አንዳይመለሱ የሚከለክል ሕግ ስላወጡ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ግዙፍ የቱትሲ ስደተኞች ስብስብ እንዲፈጠር ያደረጉ ሲሆን አንድ ሙሉ የሩዋንዳ ቱትሲዎች ትውልድንም አንዴ እንኳን የእናት አገሩን አፈር ሳይረግጥ እንዲያድግ አስገድደዋል፡፡ አቶ ጋሂጊ ያንን ፈጽሞ ባይገልጽም ቱትሲዎች ራሳቸውን ከጽንፈኛ ሁቱዎች ለመከላከል በሞከሩ ቁጥር ግን ምን እንደሚከሰት ያውቃል፡፡ ለእኛ መጨነቁን ‹‹ይህ ለቱትሲዎች በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል - ይህን ዓይነት ነገር ወደ ብዙ ግድያዎች ሊያመራ ስለሚችል መንግሥትና አማጽያኑ ችግራቸውን እንዲፈቱና ደም መፋሰስ እንዲቆም እንጸልይ፡፡››
የዕለቱ ትምህርታችን በዚሁ አበቃ፡፡ ሴቶቹ ልጆች ግን የሚያወሩት ስለጥቃቱና ቱትሲ ወታደሮቹ ወደ ትምህርት ቤታችን ቢደርሱ ምን ማድረግ እንደሚኖርባቸው ብቻ ሆነ፡፡ ከሁለት ቱትሲ የክፍል ጓደኞቼ ጋር ጸጥ ብዬ ላለመታየት እየሞከርኩ ተቀመጥሁ፡፡ ቱትሲዎች እንዴት ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንደተያዙ ሳስብ ሃፍረቴ ወደ ንዴት ተለወጠ፡፡ የመንግሥት ወታደሮችን አሸንፎ ለመድሎው ፍጻሜ ያበጅለት ዘንድ ተስፋ በማድረግ በልቤ ለሩአግ አጋርነቴን አሳየሁ፡፡ በመጨረሻ ግን ንዴቴ ወደ ፍራቻ የተቀየረው ስለመንደሬና ስለቤተሰቤ በተጨነቅሁ ጊዜ ነው፡፡ አምላኬ ቤተሰቤን ሰላም ያደርግልኝ ዘንድ ዓይኖቼን ጨፍኜ ተማጸንኩት - በወቅቱ ያለ-ነሱ እንዴት በሕይወት እንደምቆይ ስለማላውቅ፡፡
ብዙዎቹ ተማሪዎች ጦርነቱ አስከፊ በነበረበት በሰሜኑ ክፍል ዘመዶች ስለነበሯቸው የትምህርት ቤቱ ርዕሰ - መምህር የሬድዮ ዘገባ እንድናዳምጥና ስለ ክስተቱ እንድንረዳ ፈቀደልን፡፡ ብሄራዊው ሬድዮ የሚያስተላልፈው ዘገባ ከሞላ ጎደል የጥላቻ ውትወታ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ዘጋቢዎቹ አማጽያኑ እንደ አውሬ በጫካ እንደሚኖሩ፣ የሰው ስጋ እንደሚበሉና ከዝንጀሮዎች ጋር ወሲብ እንደሚፈጽሙ አተቱ፡፡ የለየላቸው ሰይጣኖች ስለሆኑ ቀንድ አብቅለዋል ተባለ፡፡ ‹‹አማጽያን በረሮዎቹ›› በማናቸውም ስፍራና ጊዜ ሊተናኮሉ ስለሚችሉና መሰሪ ስለሆኑ ሩዋንዳውያን ራሳቸውን እንዲጠብቁ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው፡፡ እነዚህ ዘገባዎች ቀድሞውንም የተዛባ አመለካከት የነበራቸውን ልጃገረዶች አቀጣጠሏቸው፡፡ አንዷማ በጣም ፈርታ ስለነበር ልታስገድለኝ ነበር፡፡
ዳኒዳ ከመኝታ ቤት እህቶቼ አንዷ ስትሆን ስለአማጽያን ወታደሮቹ የተነገሩትን ሁሉንም አስፈሪ ገለጻዎች አምናቸዋለች፡፡ አንድ ምሽት ከመኝታ ቤቱ ውጪ ወደሚገኘው መታጠቢያ ክፍላችን ለመጠቀም ስሄድ ከእንቅልፏ ሳልቀሰቅሳት አልቀርም፡፡ ምሽቱ በጣም ይቀዘቅዝ ስለነበር እንዲሞቀኝ ትልቅ ፎጣዬን በራሴ አስሬ የሚረዝምብኝ የነበረ የሌሊት ልብስ ለብሻለሁ፡፡ ትንሽ ሳላስፈራ አልቀርም፣ ተመልሼ ለመግባት በሩን ለመክፈት ስሞክር ዳኒዳ ፊቴ ላይ በኃይል ዘጋችብኝ፡፡ ኡኡታዋን ስታቀልጠው ግቢው ተሸበረ፡፡
‹‹አድኑኝ! እርዱኝ! ወይኔ አምላኬ! ኧረ እርዱኝ፡፡ የሩአግ ወታደር ነው - ሊገድለን፣ ሊበላን መጣ፡፡ አቤት ቀንዶቹ!››
የዳኒዳን ጆሮ ሰንጥቆ የሚገባ ድምፅ ስላወቅሁት በእርጋታ ‹‹ዳኒዳ፣ እኔ እኮ ነኝ፣ ኢማኪዩሌ ነኝ፡፡ ወታደር አይደለሁም፡፡ ቀንድም የለኝ፤ ፎጣዬን ነው እኮ ራሴ ላይ ያሰርኩት!›› አልኳት፡፡
ሞቅ አድርገው የሚረግጡ እግሮች ከኮረኮንቹ ጎዳና በኩል ሰምቼ ዘወር ስል የትምህርት ቤታችን ትልቁ ዘበኛ በደረቴ ትይዩ ያነጣጠረ ጦር ይዞ በጨለማው ወደኔ ይገሰግሳል፡፡ ብርክ ይዞኝ ጉልበቴ ተሽመድምዶ መሬት ላይ ቁጭ አልኩ፡፡ ዘበኛው ከእኔ መጠነኛ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ! ኢማኪዩሌ፣ ገድዬሽ ነበር እኮ! ማናባቷ ነች እንደዚያ የምትጮኸው?›› አለ፡፡
በወቅቱ
በመኝታ ቤታችን የነበሩት ሁሉም ልጆች እየጮኹ ስለነበር እኔም በሁካታው መካከል ዘበኛው እንዲሰማኝ መጮህ ነበረብኝ፡፡ ቢያንስ ለግማሽ ሰዓት በርካታ ጥበቃዎች ልጆቹን በሩን መክፈት ችግር እንደሌለው ለማሳመን ቢሞክሩም አሻፈረኝ አሏቸው፡፡ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ-መምህር ማናቸውንም በር የሚከፍት ቁልፍ ይዘው እንዲመጡ ተጠርተው በሩን ከፍተውልን ወደ ውስጥ ከገባን በኋላ ፍርሃታችን እኛን እንዲቆጣጠረን መፍቀድ ስላለው አደጋ ሲያስተምሩን ብዙ ቆዩ፡፡ የነበረው ሁኔታ አሳሳቢ ቢሆንም በትምህርት ቤቱ ውስጥ የነገሰው ውጥረት ሁሉ ግን አያስበረግገንም፡፡ አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ ለእግር ጉዞ ወጥተን ሳለ በአገሬው ሁቱ ቡድን አቅራቢያ እናልፋለን፡፡ ከሰዎቹ አንደኛው ትልቅ ቢላዋ ይዞ ወደኔ ይሰብቃል፡፡ ‹‹ይችኛዋ እንዴት እንደተንቀፈረረች እዩ›› በማለት እያጉረመረመ ያስፈራራኛል፡፡
‹‹አስቀድመን እንገድልሻለን፡፡ አማጽያን ወንድሞችሽ እያደረጉ ላሉት እንድትከፍይ እናደርግሻለን!››
ሆዴ ከመሸበሩ የተነሣ ሊያስመልሰኝ ቃጣው፡፡ ሰው በአመፅ ሲያስፈራራኝ የመጀመሪያዬ ስለነበር ጉዳዩን እንዴት ማስተናገድ እንደነበረብኝ አላወቅሁም፡፡ ወደ መኝታ ቤቴ ሮጬ ተመልሼ በትምህርት ቤታችን ሽርሽር በፍጹም ድጋሚ አልሳተፍም ብዬ ማልኩ፡፡ ቁመናዬንም ረገምኩት፤ ረጅም መሆን በሀገሬ ለምን እንዲህ ወንጀል ሆነ ብዬም ተማረርኩ፡፡ ምን እንዳደርግ ነበር የሚፈለገው? ማደጌን ላቆመው አልችልም፡፡ ቱትሲነቴንም አልፍቀው!
በቀጣዩ ቀን በትምህርት መካከል ክሌሜንታይን ወደኔ ክፍል መጥታ በጆሮዬ ‹‹ነይ ተከተዪኝ ኢማኪዩሌ! እንደዚያ ቢላዋ እንደያዘው ሰውዬ ዓይነት ሰዎች ሲመጡብን ምን ማድረግ እንዳለብን ላሳይሽ፡፡››
ብዙም ሰው ወደማይገባበት ሕንጻ ወስዳኝ ውስጡ ባለ አንድ ክፍል ውስጥ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ያለው ሣጥን ከፈተች፡፡ ‹‹ከ1500 ቮልት በላይ ኤሌክትሪክ እዚህ አለ›› ስትል ታስረዳኝ ያዘች፡፡ ‹‹ሁቱ ጽንፈኞች ትምህርት ቤቱን ከወረሩና የምናመልጥበት መንገድ ካጣን እዚህ መጥተን ይህን መክፈቻ ቁልቁል ሳብ አድርገን እጆቻችንን ወደ ውስጥ ማስገባት እንችላለን፡፡ ወዲያውኑም እንሞታለን - በሰው ከመገረፍ፣ ከመደፈርና ከመገደል በኤሌክትሪክ ተቃጥሎ መሞት በስንት ጣሙ፡፡ አረመኔዎች እኔን ከመግደላቸው በፊት በሰውነቴ ላይ እንዲጫወቱበት አልፈቅድላቸውም፡፡ እጅግም አይግረምሽ - በክፉ ቀናት ቱትሲ ሴቶች የማምለጫ ዕቅድ ስላልነበራቸው የተደፈሩባቸውንና የተሰቃዩባቸውን በርካታ ታሪኮች ሰምቻለሁ፡፡››
በመስማማት ራሴን ነቀነቅሁ፡፡ ሕይወታችንን ስለመቅጨት በ19 ዓመታችን ማውራት እንግዳ ነገር ቢሆንም ከሌላኛው አማራጭ የተሻለ ይመስላል፡፡ የትምህርት ቤቱ ባለስልጣናት ይህን ዕቅድ ሰምተው ሳጥኑን እንዳይዘጉት ክሌሜንታይንና እኔ ለማንም ላንናገር በመስማማት ተማማልን፡፡

አዲስ ዜና ለመስማት ስንል ሬድዮ ማዳመጣችንን ቀጠልን፡፡ የመንግሥቱ ጣቢያ ግን የተሳሳተ መረጃ በማሠራጨት አቻ የማይገኝለት ስለነበር ሩአግ ኪጋሊ ድረስ ተዋግቶ የርዕሰ-ብሔሩን ቤተ-መንግሥት እንዳጠቃ ወሽክቶልናል፡፡ ርዕሰ-ብሔሩ በብሔራዊው ሬድዮ ወጥቶ ጦሩ ሁሉንም ‹‹በረሮ›› ወራሪዎች ገድሎ እስኪጨርስ ሕዝቡ በየቤቱ እንዲቆይ አስጠነቀቀ፡፡ በኋላ ላይ ከብሪታንያው የዜና ምንጭ ከቢቢሲ እንደሰማነው ከዋና ከተማው በኪሎሜትሮች ርቀት ምንም የሩአግ ወታደር አልታየም - ርዕሰ-ብሔር ሃብያሪማና ጥቃቱን ራሳቸው ፈጥረው በሬድዮ የዋሹት ከሀገሪቱ ውጪ የሚኖሩ ዘመዶች ስለነበራቸው ብቻ በሺህዎች የሚቆጠሩ ቱትሲዎችን ለማሠራቸው የትክክለኝነት ማስረጃ መፍጠራቸው ነው፡፡ ርዕሰ-ብሔሩ ማንኛውንም በዩጋንዳ የአክስት ወይንም የአጎት ልጅ የነበረው ቱትሲ ከአማጽያኑ ጋር መተባበሩ አይቀሬ ነው ብለው አምነው ቅዠት ውስጥ የገቡ ይመስላል፡፡
ቢቢሲ በዘገባው እጅግ ብዙ ንጹሃን ቱትሲዎች በመታሠራቸውና በሩዋንዳ በቱትሲ እስረኛ ያልታጨቀ እስር ቤት በመጥፋቱ ለወንጀለኞች ማሰሪያ የተረፈ ቦታ አልነበረም ብሏል፡፡ እንደሚባለው ከሆነ በወቅቱ ብዙዎቹ ቱትሲዎች በረሃብ እየተሰቃዩ፣ ድብደባ እየተፈጸመባቸውና የተወሰኑትም እየተገደሉ ነበር፡፡ ለገና በዓል ወደ ቤቴ እንደሄድኩ አባቴ በወቅቱ ታስረው ከነበሩት አንዱ መሆኑን አወቅሁ፡፡ በማታባ ከሕዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪ እንደወረድኩ ከረጅም ጊዜ ጎረቤቶቻችን አንዷና ቀንደኛ ወሬኛ ከነበሩት ከእመት ሲራኬ ጋር በድንገት ተገናኘን፡፡ ‹‹እስቲ ነይ ሳሚኝ ልጄ›› ሲሉ አለቀሱ፡፡ እንኳንም አንቺን አሳየኝ! አንጀትሽ እንዴት ነው የተጣበቀው አንቺ! - እነዚያ መነኩሲቶች አያበሉሽም እንዴ?››
‹‹ኧረ በደንብ ያበሉናል፡፡ ግን ከቤተሰቤ ጋር ራት ለመብላት ጓጉቻለሁ፡፡››
‹‹እንዲያው ያ አባትሽ በተለይ ያን ሁሉ ችግር አሳልፎ አሁን ዓይንሽን ሲያይ ደስ እንደሚለው ይታየኛል፡፡››
‹‹ምን ማለትዎ ነው?››
‹‹አልሰማሽም ልጄ?››
ልቤ ተቻኮለ፡፡ ጦርነቱ ከጀመረ ወዲህ ወላጆቼን አላየኋቸውም፤ ለሳምንታት ያህልም ከቤት ምንም ዓይነት ወሬ አልመጣልኝም፡፡
‹‹በእውነቱ ታውቂያለሽ ብዬ ነበር ያሰብኩት›› አሉ እመት ሲራኬ ‹‹አባትሽ እኮ ታስሮ ከረመ፡፡››
በድንጋጤ አጠገቤ በተጋደመ ግንድ ላይ ቁጭ አልኩ፡፡ አባቴ ቱትሲ ከመሆኑ በቀር ሊያሳስረው የሚችል ምንም ነገር ሊያደርግ ይችላል ብዬ ማሰብ አልቻልኩም፡፡ ስለ እናቴም ጤና ተጨነቅሁ፡፡ የአባቴ መታሰር የሚያስከትልባት ጭንቀት አስሟን አስነስቶባት እንዳይሆን! የሰላሳ ደቂቃውን የእግር መንገድ መቼም ሄጄ በማላውቅበት
ፍጥነት ፉት ብዬው እናቴን በሩ ጋ ስትጠብቀኝ አገኘኋት፡፡
እቅፍ አደረገችኝና ‹‹እንዴት ነሽ ሆዴ?›› ስትል ጠየቀችኝ፡፡ ስለ አባቴ መታሰር ምንም አላነሳችም - ሁልጊዜ ከመጥፎ ስሜት ትጠብቀናለች፤ መቼም የማትቀየር መሆኗንም ታዘብኩ፡፡
‹‹መቼም ርቦሻል፣ ኢማኪዩሌ፡፡ ምግብ እስካሰናዳልሽ ገላሽን ታጠቢያ፡፡ ዳማሲንና ቪያኒ የሆነ ቦታ አብረው ሄደዋል፤ ኤይማብልም ከዩኒቨርሲቲ ገና አልመጣም፡፡ አባትሽ ሥራ ቦታ ነው፤ ዓይንሽን ለማየት እንዴት እንደጓጓ አትጠዪቂኝ፡፡››
‹‹ሁላችሁም ደኅና ናችሁ? አንዳችሁም ላይ ምንም ነገር አልተከሰተም?››
‹‹አይዞሽ! ሁላችንም ሰላም ነን፡፡››
‹‹በፈጠረሽ እማማ! አባባ ታስሮ መክረሙን አውቃለሁ፤ ስለዚህ ማለባበሱን ተዪና የተከሰተውን ሁሉ ንገሪኝ፡፡››
እናቴ መጥፎውን ዜና ለኔ መንገሩ ስለቀረላት ቅልል አላትና ወዲያውኑ ቁጭ ብላ ሁሉንም ነገር አጫወተችኝ፡፡
ጦርነቱ ከጀመረ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አራት የመንግሥት ወታደሮች ወደ አባቴ የሥራ ቦታ ሄደው እጆቹን ወደኋላ አስረው ከግማሽ ደርዘን የሥራ ባደረቦቹ ጋር ኪቡዬ ከተማ እስር ቤት ወስደው ወረወሩት፡፡ ዘበኞቹንም ለብዙ ቀናት ምግብም ሆነ መጠጥ እንዳይሰጧቸው ከለከሏቸው፡፡ በኋላ ላይ አባቴ ሁቱውን ዘበኛ በጉቦ ደልሎ በቅርቡ ለምትኖረው አክስታችን ሲሲሌ መልዕክት እንዲወስድለት ያደርጋል፡፡ ሲሲሌም ወደ እስር ቤቱ ምግብ አምጥታ ዘበኛው ምግቡን ለአባቴና ጓደኞቹ አስገባላቸው፡፡
ከሁለት ሳምንታት በኋላ አባቴ እንዲታሰር የታዘዘው በዱሮ ጓደኛው በካባዪ እንደሆነ ይደርስበታል፡፡ ካባዪ የወረዳው አስተዳዳሪና አድራጊ ፈጣሪ ተደርጎ የተሾመ ሁቱ ነው፡፡ ካባዪና
👍1
የኔ አባት አብረው የተማሩ ጥሩ የልጅነት ጓደኛሞች ነበሩ፡፡ ርዕሰብሔር ሃብያሪማና ለዓለምአቀፍ ጫና ተንበርክከው በስህተት የታሰሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ቱትሲዎችን ለመፍታት ከተስማሙ በኋላ ነበር ካባዪ ወደ እስር ቤት ሄዶ ዘበኞቹ አባቴንና ጓደኞቹን እንዲፈቷቸው ያዘዘው፡፡ ካባዪ ዘበኞቹ ለአባቴ ምንም ዓይነት ምግብ እንዳይሰጡት አዟቸው ስለነበር በሕይወት ሲያገኘው ክው አለ፡፡ የተበሳጨ መስሎና የሚገርም ስህተት መፈጸሙን ገልጾ አባቴን በእጅጉ ይቅርታ ጠየቀው፡፡
በዚያ ምሽትም ከእራት በኋላ ከበን ተቀምጠን ሳለ የተከሰተውን ነገር ከአባቴ ጋር ለመወያየት ስሞክር አባቴ ‹‹የተደበላለቀ ነገር ነው፡፡ ካባዪ የታዘዘውን ነበር የሚፈጽመው፤ የግል ጉዳይ እንኳን አይደለም፡፡ እነዚህ ነገሮች ከፖለቲካ ጋር የሚያያዙ ስለሆኑ እናንተ ልጆች ባትነካኩ ይሻላል፡፡ ሁሉንም ነገር እንርሳው›› አለ፡፡
ወንድሞቼ አባታችን ያን ያህል ይቅር ባይ መሆኑን ሊያምኑ አልቻሉም፡፡ ካባዪን በሕይወታቸው ሙሉ ያውቁት ስለነበር በአባታችን ላይ እንደዚያ በመነሳቱ ተናደዋል፡፡
‹‹ካባዪ እኮ ጓደኛህ ነበር አባባ፡፡ ጠላትህ ሆኖማ ቢሆን ምን ሊከሰት እንደሚችል አስበው እስኪ፡፡ ለምንድነው ለሱ የምትሟገትለት? እነዚህ የምትቆምላቸው ሰዎች እኮ ሊያጠፉህ ይፈልጋሉ! ጦርነቱ እስኪያልቅ ድረስ አገሪቱን ለቀን መሄድ አለብን፡፡ ሌላው ቢቀር እማማንና ኢማኪዩሌን ከዚህ ማራቅ ይኖርብናል - የእነርሱ ነገር አሳስቦኛል›› አለ ኤይሚየብል፡፡
‹‹አይ እንግዲህ፣ ምነው አጋነንከው በል - ምንም ሥጋት የለብንም፡፡ ሁኔታው ከበፊቱ እየተሻሻለ ነው፤ ይህ ከፖለቲካ ጋር ብቻ የሚያያዝ ጉዳይ ነው፡፡ እናንተ ልጆቹ አትጨነቁለት፡፡ ምንም አንሆንም፤ ምን አለ በሉኝ›› ሲል አባታችን አረጋገጠልን፡፡
እናቴ ወንድሞቼን ሌሎች በርካታ ቱትሲ ወንዶች ያደርጉት እንደነበረው ሾልከው የሩአግ ተዋጊዎችን እንዳይቀላቀሉ ለመነቻቸው - ‹‹አንዳችሁ እንኳን ከአማጽያኑ ጎን ለመዋጋት ብትሄዱ ውሳኔያችሁ እንደሚገድለኝ እንድታውቁት እፈልጋለሁ! አንገብግቦ ይገድለኛል! እናታችሁን መግደል ግድ ካላላችሁ አሁኑኑ ሂዱ፡፡ ከወደዳችሁኝ ግን ጠፍታችሁ ለሥቃይ እንደማትተውኝ አሁን ቃል ትገቡልኛላችሁ፡፡ በሉ ማሉልኝ!›› እናቴ ራሷን በዚህ ሁኔታ ውስጥ በመክተቷ ወንድሞቼ አማጽያኑን እንደማይቀላቀሉ ደጋግመው ቃል ገቡላት፡፡
እኔም ወደ ሊሴ ሄጄ ቀሪ የተወሰነ ወራት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ጨርሼ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናዬን ተፈተንኩ፡፡ በድጋሚም አመርቂ ውጤት አመጣሁ፤ ያለችኝ የመግባት ተስፋ ግን የመነመነች ነበረች፡፡ የዘውግ ተዋፅዖ የሚባው አሰራር ሩአግ መጨረሻ ይኖራቸው ዘንድ ከሚዋጋላቸው ነገሮች አንዱ ነው፣ በወቅቱ ግን ይህ ተዋፅዖ ተብዬው ለትምህርት ሕይወቴ መጨረሻ ያበጅለት መሰለኝ፡፡ በሊሴ ለነበሩኝ መልካም ጓደኞቼ ስንብት አድርጌ ዕጣ-ፈንታ ወዴት እንደምታመራኝ ወደምጠባበቅበት ወደ ቤቴ ለክረምት እረፍት አመራሁ፡፡ ጦርነቱ እየተፋፋመ መጣ፤ አማጽያኑም ብዙ ጦርነቶችን እያሸነፉና መንግሥትንም በስደት የሚኖሩ ሩዋንዳውያንን ወደ ሀገራቸው ይመለሱ ዘንድ እንዲፈቅድና ሥልጣንንም ለአማጽያኑ እንዲያጋራ ግፊት እያሳደሩበት መጡ፡፡


እናቴ እየተከሰተ በነበረው ነገር በጣም ተጨንቃ አዋቂዎችን ሳይቀር መጠየቅ ጀምራ ነበር፡፡ አንዷ ጠንቋይ ወደ ቤታችን እየመጡ ኩሽና ውስጥ ከእናቴ ጋር ሲቀመጡ አስታውሳለሁ፡፡ እናቴም ጦርነቱ ያበቃ እንደሆነና ሰላምንም መልሰን እናገኛት እንደሆነ ትጠይቃቸዋለች፡፡
‹‹በሁላችንም ዙሪያ መብረቅ ይታየኛል፣ ግን እነዚህ ሕፃናት ማዕበሎች ናቸው›› አሏት አዋቂዋ፡፡ ‹‹እናትየዋ ማዕበል እየመጣች ነው፡፡ ስትደርስ መሬቱን ታጋየዋች፣ ድርቅርቋ ያደነቁረናል፤ ከባዱ ዶፏም ሁላችንንም ያሰጥመናል፡፡ ለሦስት ወራት የሚቆየው ማዕበል ብዙዎቹን ይፈጃል፡፡ የሚያመልጡት ሰዎች የሚሸሽጋቸው አያገኙም - ሁሉም የሚያውቁት ፊት ይጠፋባቸዋል፡፡ ‹ይብላኝ ለእነርሱ›››

💫ይቀጥላል💫

Like 👍 በጣም ቀንሷል ፅሁፉ አልተመቻችሁም? ፁሁፉ ትንሽ ረዘም ስለሚል በትግስት አንብቡት በዘር መቧደን ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ የምንማርበት ፅሁፍ ነው በተለይ ለኛ በጣም ይጠቅመናል ስለዚህ እያነበባችሁ Like👍 እያደረጋቹ

ማንኛዉንም አስተያየት በ @atronosebot አድርሱን

አትሮኖስ pinned «#ሁቱትሲ ፡ ፡ #ምዕራፍ_ሦስት ፡ ፡ #የወጣቷ_ልብ_አንጠልጣይ_ትውስታዎች ፡ #ትርጉም_በመዝምር_ግርማ ፡ #ቅድመ_ከፍተኛ_ትምህርት በሦስተኛውና በመጨረሻው ዓመት ጦርነት ከመፈንዳቱ በቀር ሕይወት በሊሴ ጥሩ ነበር፡፡ የ1990 የጥቅምት ወር የመጀመሪያዋ ቀን ከሰዓት ቆንጆና ብሩህ ነበረች፡፡ የክፍል ጓደኞቼና እኔ የግብረገብ ትምህርት ክፍለጊዜያችን እስኪጀምር እየጠበቅን መምህሩ ለምን…»
#ሁቱትሲ


#ምዕራፍ_አራት


#የወጣቷ_ልብ_አንጠልጣይ_ትውስታዎች

#ትርጉም_በመዝምር_ግርማ


#ወደ_ዩኒቨርሲቲ

በ1991 ክረምት መጨረሻ የማይቻለው ተከሰተ - በቡታሬ በሚገኘው ብሄራዊው ዩኒቨርሲቲ መማር የሚያስችለኝ የትምህርት ዕድል ተሰጠኝ፡፡ በሕይወቴ ሙሉ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባትን በጽኑ ስመኝ ነበር፡፡ በመሆኑም በፊቴ እነዚያ ሁሉ መሰናክሎች ቢጋረጡብኝም በድንገት ሕልሜ እውን ሆነ፡፡
ወላጆቼ ዜናውን ሲሰሙ በጣም ተደስተው ተቁነጠነጡ፡፡ በትክክለኛው የሩዋንዳ ደንብ - ያው በድግስ መሆኑ ነው - እናከብረው ዘንድም ምግብና መጠጥ ለማዘጋጀት ተፍ ተፍ ይሉ ጀመር፡፡
‹‹ዩኒቨርሲቲ በመግባት ከቤታችን የመጀመሪያዋ ሴት ልጅ ነሽ፣ ስለሆነም አሁኑኑ ይህን ለሁሉም ሰው ማሳወቅ አለብን!›› ሲል አባቴ በኩራት ተናገረ፡፡ በማግስቱ ረጅም መንገድ ተጉዤ ለአያቴ፣ ለአክስቶቼ፣ ለአጎቶቼና ለሁሉም በአቅራቢያችን መንደሮች ለሚኖሩት ልጆቻቸው ወሬውን እንዳበስር አመቻቸልኝ፡፡
ሌሊቱን ሙሉ ስንስቅ፣ ስንበላና ወደፊት ስለሚኖሩት በጎ ነገሮች ሁሉ ስናወጋ አሳለፍን፡፡ ወላጆቼ በዚያ ምሽት ሸክም ከትከሻዎቸው እንደወረደላቸው ሁሉ ወደ ወጣትነት የተመለሱ መሰሉኝ፡፡
እናቴ በደስታ ፈክታ አመሸች፡፡ ‹‹ሁሉም ነገር ላንቺ ብሩህ የሆነልሽ ይመስላል፣ ኢማኪዩሌ›› አለችኝ፡፡ ‹‹ከአሁን በኋላ ሙሉ በሙሉ የራስሽን መንገድ ማበጀት ትችያለሽ፤ ቀና በይ፤ ማንም ሌላ ሰው በገበታሽ ላይ በፍጹም ምግብ እንዲያስቀምጥልሽ አትጠባበቂ፡፡››
አባቴም ከኔ ጋር መጠጫ አጋጭቶ ብዙ አባታዊ ምክር ለገሰኝ፡፡ ‹‹ብዙውን ጊዜ በዩኒቨርሲቲ የሚማሩት ወንዶች ሲሆኑ እነርሱም አንቺን እንደነርሱ ጎበዝ ነች ብለው አያስቡም፡፡ ግን እንደነሱ መትጋት እንደምትችዪ አውቃለሁ፤ አንዲያውም ከማንኛውም ወንድ በተሻለ፡፡ አንቺ ቱትሲ ስለሆንሽ ዩኒቨርሲቲ መግባት ፈተና ሆኖብሽ ቆይቷል፤ ይኸው አስቸጋሪው ወቅት አለፈ፡፡ እንግዲህ የራስሽ ድርሻ ነው - በደንብ አጥኚ፣ ጸልዪ፤ ስታድጊ በስስት እናይሽ እንደነበርሽው ምስጉን፣ ደግና ቆንጆ ልጅ መሆንሽን ቀጥዪበት፡፡››
በጣፋጭና ፍቅር የተሞላባቸው ቃላቱ ልቤ ሐሴት አደረገች፡፡ ‹‹ሃሳብ አይግባህ አባባ›› አልኩት፡፡ ‹‹አንተንም ሆነ እማማን አላሳፍራችሁም፡፡ አኮራችኋለሁ፡፡››

ስለ ሰው ልቦናና አእምሮ አሠራር ለመማር ሥነ ልቦናንና ፍልስፍናን ለማጥናት ብፈልግም የትምህርት ዕድሉ በተወሰኑ የትምህርት ዓይነቶች ባሉ ክፍት ቦታዎች የተወሰነ ስለነበር ራሴ የምፈልገውን የጥናት መስክ እንድመርጥ አልተፈቀደልኝም፡፡ በተግባራዊ ሳይንስ መርሃ-ግብር መመደቤ ተስማምቶኛል፡፡ በሊሴ ለወንድሞቼ ችሎታዬን ለማሳየት ስል ራሴን በሒሳብና ፊዚክስ አብቅቼ ስለነበር አሁን ያ ሥንቅ ይሆነኛል፡፡ ሻንጣዎቼን አዘገጃጅቼ ወዲያውኑ ከመንደሬ ደቡብ ምሥራቅ አራት ሰዓት ወደሚያስነዳውና ፍጹም አዲስ ሕይወት ወደሚጠብቀኝ ወደ ቡታሬ አቀናሁ፡፡

ትምህርት ቤቱ ቅጥር-ግቢ ስደርስ ክሌሜንታይንን ጨምሮ ከሊሴ ስድስቱ የሴት ጓደኞቼ፣ የትምህርት ዕድሉን ማግኘታቸውን ተረዳሁ፡፡ ጓደኛዬ ሳራ እዚያው አንድ ዓመት ቀድማ ገብታ ስትማር የቆየች ሲሆን አንድ መኝታ ክፍል ውስጥ አብረን እንድንኖር ስትጠብቀኝ ኖሯል፡፡ በተጨናነቁ ክፍሎች ውስጥ ከተኛሁባቸው ከእነዚያ ዓመታት በኋላ ከአንዲት ሴት ልጅ ጋር ብቻ አንድ ክፍል መጋራት እጅግ ይመቻል፡፡ ክሌሜንታይን ብዙ ጊዜ የኛን ክፍል ትጎበኝ የነበረ ሲሆን በጦርነቱ መጀመሪያ ሰሞን ራሳችንን በኤሌክትሪክ የማቃጠሉን ዕቅዳችንን ባለመፈጸማችን እንዴት ዕድለኞች እንደነበርን በጨዋታ መካከል እናነሳለን፡፡ ያ ቢሆን ኖሮ የዩኒቨርሲቲን አስደሳች ነገሮች ሁሉ መች እናይ ነበር?
ትምህርቱን ወደድኩት፤ በጣም ጠንክሬም አጠና ጀመር፡፡ የዩኒቨርሲቲን አስደሳችነትና ነጻነት እንዴት እንደወደድኩት! የትምህርት ዕድሉ ለእኔ ትልቅ ነገር የነበረውን ወደ 30 የአሜሪካን ዶላር የሚሆን ወርሃዊ የኪስ ገንዘብንም ይጨምራል፡፡ በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ትልቅ ሰው ነጻነት ተሰማኝ፡፡ የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ መልበስ ቀረልኝ፤ ከተማም ሄድ ብዬ ከጓደኞቼ ጋር ቆንጆ ቆንጆ ልብሶችን መግዛት ቻልኩ፡፡ አቤት ሲያስደስት!
ቡና ተፈልቶ በሚሸጥባቸው ስፍራዎች፣ በሰንበት ተንቀሳቃሽ ምስል በሚታይባቸው ቦታዎችና በየአሥራ አምስት ቀኑ ቅዳሜ ምሽት በሚካሄዱት የትምህርት ቤት አቀፍ የዳንኪራ ጊዜያት እስከመገኘት ደርሼ በማኅበራዊ ሕይወት በጣም ንቁ ተሳታፊ ሆንኩ፡፡ የትዕይንት ማሳያ ቡድንንም ተቀላቅዬ ብዙውን ጊዜ የቡታሬ ከንቲባ በሚገኙባቸው በሁሉም ትዕይንቶች እዘፍንና እጨፍር ነበር፡፡ ሃይማኖታዊ ገጸባህርያትን ወክሎ መተወን ምርጫዬ በመሆኑ እንዲያውም አንድ ጊዜ የምወዳትን ቅድስት ድንግል ማርያምን ወክዬ ተጫውቻለሁ፡፡ ሁልጊዜ ለጸሎት የሚሆን ጊዜ እተዋለሁ፡፡ ያንን ጽናት ማግኘቴና ጸሎት ማድረጌ እጅጉን አረጋግቶኝና አትኩሮቴን እንድሰበስብ ረድቶኝ ነበር፡፡ ቤተ-ክርስቲያን በሳምንት ብዙ ጊዜ እሄዳለሁ፤ ከሴት ጓደኞቼም ጋር የጸሎት ቡድን አቋቁሜያለሁ፡፡
ለናፍቆት ጊዜ ባይኖረኝም ከአባቴ የሚላኩልኝ ብቸኝነት የሚንጸባረቅባቸው ደብዳቤዎች ቤተሰቤን ቶሎ ቶሎ መጎብኘት እንዳለብኝ አስገነዘቡኝ፡፡ በወቅቱ ቪያኒ በአዳሪ ትምህርት ቤት ስለነበር ወላጆቼ ብቸኝነትን መላመድ አቅቷቸዋል፡፡ ‹‹ከልጆቼ አንዳቸውም እዚህ ሳይኖሩ ሕይወቴ እንደ ዱሮው ሊሆን አይችልም›› ሲል አባቴ ጻፈልኝ፡፡ ‹‹ቤቱ በጣም ጭር ብሏል፡፡ አንዳንዴ እኔና እናትሽ እርስ በርሳችን እንተያይና እንገረማለን፣ ‹ያ ሁሉ ሣቅ የት ሄደ?› እንላለን፡፡ የራስሽ ልጆች ሲኖሩሽ፣ ኢማኪዩሌ፣ ሳትጠግቢያቸው ስለሚሄዱብሽ አብረውሽ እያሉ እያንዳንዷን ደቂቃ በደስታ ማሳለፍሽን እርግጠኛ ሁኚ፣ …››
በማታባ ያሉትን የተወሰኑትን ጓደኞቼን የሚያውቅ ዮሃንስ የሚባል ተማሪ ጓደኛም አገኘሁ፡፡ ከእኔ ሦስት ዓመት ይበልጥ የነበረና ‹‹ድንገት›› ከኔ ጋር በትምህርት ቤቱ የተለያዩ ስፍራዎች ግጥምጥም የማለት የተለየ ጸባይ የነበረው ልጅ ነው፡፡ መጽሐፍቴን ይይዝልኝ፣ የትምህርት ቤታችንን ግቢ ያሳየኝና ከጓደኞቹ ጋር ያስተዋውቀኝ ጀመር፡፡ አማላይ፣ ታጋሽና ለሰው አሳቢ ልጅ ነበር፡፡ በጫካው ውስጥ ለረጅም የእግር ጉዞ አብረን እየሄድን ለእኛ አስፈላጊ ስለሆነው ጉዳይ እናወራለን - ስለ እግዚአብሔር፣ ስለ ቤተሰብና ስለ ጥሩ ትምህርት፡፡ በኋላም ላይ ፍቅር ለመጀመር በቃን፤ በመጭዎቹም ዓመታት ውስጥ አንዳችን ለሌላችን በጣም እንተሳሰብ ጀመር፡፡ ዮሃንስ ሁቱ ቢሆንም ግን ይህ ጭራሽ ጉዳያችን አልነበረም፡፡ ለአባቴ ይልቁን ዮሃንስ ወንጌላዊ ክርስቲያንና የሰባኪ ልጅ መሆኑ ያሳስበዋል፡፡
‹‹ካቶሊክ መሆንሽን አትርሺ›› እያለ አባቴ ያስታውሰኛል፡፡ ‹‹ዮሃንስ ጥሩ ልጅ ይመስላል፤ እንድታፈቅሪውም መርቄሻለሁ - ግን ወደ እርሱ ኃይማኖት ሊቀይርሽ እስካልሞከረ ድረስ ነው፡፡›› አባቴ በጣም ታጋሽ ሰው ሲሆን ሃይማኖተኛም ነው በዩኒቨርሲቲ የቆየሁባቸው ሁለቱ የመጀመሪያ ዓመታት በረሩ፤ ሁሉም ነገር መልካም ሆነልኝ - ውጤቴ ጥሩ፣ ቤተሰቤ ጤነኛ፣ ሕይወቴም አስደሳች ሕይወት ስለሚመች አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ጦርነት መኖሩን ለመርሳት አይከብደንም፡፡ አልፎ አልፎ የሚካሄዱ የሰላም ድርድሮችና የተኩስ አቁም ስምምነቶች ቢኖሩም በቱትሲ አማጽያንና በመንግሥት
👍1
ወታደሮች መካከል የሚደረገው ከባድ ውጊያ ቀጥሏል፡፡ አንዳቸው ሌሎቻቸውን አጥብቀው የሚቃወሙ ጽንፈኛ የፖለቲካ ድርጅቶች በብዙ ከተሞች አቆጠቆጡ፡፡ ሥራአጥ ወጣቶች ምንም ሌላ የተሻለ የሚሰሩት ነገር ስላልነበራቸው ወደ ተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች የወጣት ክንፎች ጎረፉ፡፡ ብዙዎቹም የፖለቲካ ተቋማቱን ለአልኮል መጠጥ ወይንም አደንዛዥ እጽ ሲሉ የሚቀላቀሉ የመንገድ ላይ የወሮበላ ቡድኖች አባላት ነበሩ፡፡ የርዕሰ-ብሔር ሃብያሪማና የፖለቲካ ፓርቲ ራሱ ኢንተርሃምዌ፣ ማለትም ‹‹አብረው የሚያጠቁት››፣ የተባለ የወጣት ክንፍ አቋቋመ፡፡ ኢንተርሃምዌም በሺዎች የሚቆጠሩ ቤት-አልባ ልጆችን ሳበ፤ የአባላት ስርጭቱም በሀገሪቱ ዳር እስከ ዳር እንደ ወረርሽኝ ተስፋፋ፡፡ ስብስቡ የሁቱ ጽንፈኛ ታጣቂ ቡድን ለመሆን በቃ፡፡ ብዙዎቹ አባላቱም ሰው አገዳደልና ጥይት አተኳኮስ የሠለጠኑት በመንግሥት ወታደሮች ነው፡፡ በቡድን ይሄዱና የተለየ የደንብ ልብስ ይለብሱ ጀመር - ደማቅ ቀይ፣ ቢጫና አረንጓዴ የድርጅታቸውን ባንዲራ መሳይ ያለበት ሰፊ ጥብቆ ይለብሳሉ፡፡ የቱንም ያህል ቢደራጁ በግሌ ሁልጊዜ እንደ ህገወጥ የመንገድ ላይ ወሮበሎች እቆጥራቸዋለሁ፡፡ ኢንተርሃምዌዎችን መጀመሪያ ያየሁት በሚከተለው አኳኋን ነው፡- በ1993 የትንሣኤ እረፍቴ ኪጋሊ ላይ ከዮሃንስ ጋር ሳራንና ቤተሰቧን ለመጎብኘት ሄጄ ሳለ የተሳፈርንበት መጓጓዣ በመንገድ መጨናነቅ ምክንያት ይቆማል፡፡ ቆመን በመጠበቅ ላይ ሳለን በመካከለኛ ዕድሜ ላይ ያለች ቱትሲ ሴትዮ ከገበያ ወደ ቤቷ ስትመለስ የወጣቶች ቡድን ከቧት በመስኮት አየሁ፡፡ ልጆቹ እንደዋዛ ቦርሳዋን ነጥቀው፣ ጌጣጌጧን ቀምተውና የገዛችውን ሁሉ ወስደው ደበደቧት፡፡ ጫማዋን በኃይል አወለቁ፤ ቀሚሷንም ገፈፏት፡፡ ይህ እንግዲህ የተከሰተው በከተማው መካከል ሰው ይበዛበት በነበረ መንገድ ላይ ቀን በቀን ነው፡፡ ወጪ ወራጁ እንዳላየ ያልፋል እንጂ አንድ እንኳን ሃይ ለማለት ድፍረቱ ያለው አልነበረም፡፡
ዘልዬ ተነሥቼ በመስኮት እንዲያቆሙ መጮህ ስጀምር ዮሃንስ ሳብ አድርጎ አስቀመጠኝ፡፡ ‹‹ምንም አትበይ!›› አለኝ፡፡ ‹‹በዚህ ከተማ ምን እየተከሰተ አንዳለ አታውቂም ኢማኪዩሌ፡፡ ከነዚህ ልጆች ጋር መነካካት የለብሽም - ይገድሉሻል፡፡››
‹‹አንድ ነገር እናድርግ እንጂ ዮሃንስ፡፡ ሌላው ቢቀር ጸጥታ አስከባሪ እንፈልግ፡፡››
‹‹ጸጥታ አስከባሪ ምንም አያመጣም፡፡ እነዚህ ኢንተርሃምዌዎች የመንግሥት አካላት ናቸው፤ አታናግሪያቸው፤ በተለይ አንቺ ቱትሲ ስለሆንሽ እንዲያውም ባታዪአቸው ይሻልሻል፡፡››
ቀፈፈኝ፤ ረዳት-አልባነትም ተሰማኝ፡፡ ልጆቹ ጥለዋት ሲሄዱ ያቺ ምስኪን ከመሬት ለመነሳት ስትውተረተር ተከታተልኳት፡፡ የውስጥ ልብሷንና ሻሽ ብቻ ለብሳ ባዶ እግሯን እያነከሰች ሄደች፡፡
ሴትዮዋ በመንገዱ ስትዘልቅ እያየሁ እንደነዚህ ዓይነት ሰይጣናት መንገዶቻችንን
እንዲቆጣጠሩ ከፈቀድን በከፋ ችግር ውስጥ ነን ስል አሰብኩ፡፡
ከተወሰኑ ወራት በኋላ ከዚህ የባሰ የሚረብሽ ክስተት ገጠመኝ፡፡ ዳማሲንና እኔ ከማታባ ወደ ኪጋሊ ለሠርግ እንሄዳለን፡፡ ረጅም፣ ወበቃማና አቧራማውን ጉዞ
እያገባደድን ሳለን የመንገደኞች ማጓጓዣ ተሸከርካሪያችን ድንገት ቆመ፡፡ ቢያንስ 300 የሚሆኑ ኢንተርሃምዌዎች መንገዳችንን ዘግተው ቆመዋል፤ የሁሉም አለባበስ ለዓይን ይቀፋል፤ አስተያየታቸውም እጅግ ያስፈራል፡፡ ብዙዎቹ አላፊ አግዳሚው ላይ እየጮሁና እየተሳሰደቡ በቡድን ሲጨፍሩ የጠጡ ወይንም አደንዛዥ እጽ የወሰዱ ይመስላሉ፡፡ ነጂው ወደፊት ለመሄድ በጣም ስለፈራ ተሸከርካሪውን ወደኋላ ሊመልሰው እንደሆነ ነገረን፡፡ አብረነው የሁለት ሰዓቱን ለውጥ መንገድ እንድንሄድ፣ አሊያም ወጥተን በእግራችን እንድናዘግም አማራጭ ሰጠን፡፡
‹‹ተሽከርካሪው ውስጥ እንቆይ›› አለ ዳማሲን፡፡ ‹‹እነዚህ ሰዎች አብደዋል፡፡›› እኔ ግን በተለይ በነዚህ ወረበሎች ተግባር ለመፍራት ባለመፍቀዴና በሌሎችም ምክንያቶች ተሸከርካሪው ላይ መቆየቱን አልመረጥኩትም፡፡
‹‹እንውረድ እንጂ ሠርጉ ያመልጠናል እኮ›› አልኩት፡፡ ‹‹በእግራችን ብናዘግም ቤተ-ክርስቲያኑ ጋ አሁን እንደርሳለን፡፡››
ከተጓዦቹ ግማሽ ከሚሆኑት ጋር ወረድን፡፡ እንደወጣንም አልፏቸው የሚሄደውን ሰው መታወቂያ ከሚያዩት ኢንተርሃምዌዎች ብዙዎቹ ገጀራ እንደያዙ አየን፡፡ ንዴት ተሰማኝና ‹‹ማነው መብቱን የሰጣቸው?›› ስል ጠየቅሁ፡፡ ዳማሲን ተጨንቆ ‹‹ብንመለስ ጥሩ ይመስለኛል፣ ኢማኪዩሌ፡፡ ስለነዚህ ሰዎች መጥፎ ነገሮች ሰምቻለሁ፡፡ ተይ በእግራችን ወደ ቤታችን እንመለስ›› አለኝ፡፡
‹‹በእግራችን? በተሽከርካሪ አራት ሰዓት የፈጀብን በእግራችንማ በሦስት ቀንም አያልቅልን፡፡ ደግሞ እውነት እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን እንደ ጸጥታ አስከባሪ አደራጅተው እኛ ቱትሲዎች ስለሆንን ብቻ ጉልበታቸውን ሊያሳዩን አይገባም፡፡›› የዳማሲን ፊት ላይ ከሚነበበው ፍርሃት ይልቅ የኢንተርሃምዌዎቹ ነገር ቀላል ሆኖ አገኘሁት፡፡ ሁልጊዜ ሳቂታ ገጽታ የነበረውና ምናልባትም ከማውቃቸው ሰዎች ሁሉ ጠንካራው ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ግን በእርግጥ እንደፈራ አየሁ፡፡ ለወትሮው ምን እንደሚሻል እጠይቀው የነበረ ቢሆንም አንዳች ነገር ወደፊት እንድሄድ ገፋፋኝ፡፡
‹‹ና አልፈናቸው እንሂድ›› አልኩት፡፡ ‹‹ምንም አንሆንም፡፡››
‹‹ያንን እንዴት አወቅሽ? እንደማይገድሉን ያሳሰበሽ ምንድነው? መንግሥት የፈለጉትን እንዲፈጽሙ ይፈቅድላቸዋል፡፡ ጸጥታ አስከባሪ አይነካቸውም፡፡››
‹‹ችግር በሚገጥመን ቁጥር የምትለውን እናድርግ ዳማሲን፡፡ እንጸልይ፤ እግዚአብሔር እንደሚጠብቀንም እንተማመን፡፡››
ከቁጡ ጽንፈኞቹ ቡድን አሥር እርምጃ ርቀት ላይ በመንገዱ ዳር ቆመን ጸለይን፡፡ እግዚአብሔር ለአጭሯ መልዕክት ይቅር እንዲለኝ ጠይቄው በደኅና ወደ ቤተክርስቲያኑ እንደርስ ዘንድ ግን የእርሱን ድጋፍ እንደምንፈልግ ነገርኩት፡፡ ወደኬላው
ሄድኩ፤ የተወሰኑ ወጣት ወንዶች አይተውኝ በገጀራዎቻቸው ጭኖቻቸውን መታ መታ ያደርጋሉ፡፡

‹‹አይ በፍጹም፣ አይሆንም ኢማኪዩሌ… ስለዚህ ነገር እርግጠኛ ነሽ?››
‹‹አዎን፣ አዎን በቃ ምንም እንዳልተከሰተ ሁን - እንዲያውም ምናልባት መቁጠሪያህን ከኪስህ ብታወጣ ሳይሻልህ አይቀርም፡፡››
ወደ ኢተርሃምዌዎቹ ስንሄድ መቁጠሪያዬን በእጄ አጥብቄ ይዣለሁ፡፡ ደርዘን የሚሆኑት ከበቡን፣ ላይ ታች አዩኝና መታወቂያ ደብተራችንን እንድናሳይ ጠየቁን፡፡ በመጀመሪያ ዓይናቸው ላይ ትክ ብዬ አየኋቸው፡፡ ከዚያም ፈገግ አልኩ፡፡ በመጨረሻም ሰነዶቹን ሰጠኋቸው፡፡ በጣም ደፋር በመሆን እንዳስቸገርኳቸው ታየኝ - አንዲት ቱትሲ ሴት እነርሱንም ሆነ ገጀራዎቻቸውን ለምን እንደማትፈራ ሊገባቸው አልቻለም፡፡ መታወቂያዎቻችንን መልሰው ሰጥተውን አሳለፉን፣ ሆኖም ግን በዳማሲን ዓይኖች ውስጥ ያየሁትን ፍራቻ በፍጹም አልረሳውም፡፡ ሲፈራ ሳየው የመጀመሪያ ጊዜዬ ሲሆን በሩዋንዳ ላይ አንዳች ክፉ ነገር እንደመጣባት የሚያሳየውን ስሜቴን ላናውጠው አልተቻለኝም፡፡
መንገድ ከተዘጋብን ከዚህ ገጠመኝ ከአንድ ወር በኋላ ርዕሰ-ብሔር ሃብያሪማና ወደ ታንዛኒያ ሄደው ከቱትሲ አማጽያን ጋር የሰላም ስምምነት ተፈራረሙ፡፡ ስምምነቱ የእርስ በርስ ጦርነቱን አቁሞ ቱትሲዎችን ሀገራቸውን በማስተዳደር ላይ ሚና እንዲኖራቸው
ያደርጋል፡፡ ግሩም ሐሳብ ይመስላል - ሩዋንዳ ሰላም ይሰፍንባትና ቱትሲዎችና ሁቱዎችም በመግባባት እኩል ዜጎች ሆነው ይኖሩባታል ስል አሰብኩ፡፡ ይህ የሰላም ተስፋቸ ግን ብዙ ተቃውሞዎችን አነሳሳ፤ መጠነ-ሰፊ ሁከትንም ቀሰቀሰ፡፡ ከነዚያ ያየለ ሁከት እንደሚመጣም ማስፈራሪያዎች ተሰነዘሩ፡፡ ስምምነቱ በተፈረመባት ደቂቃ ከሩዋንዳ እጅግ አደገኛ ወታደራዊ መኰንኖች አንዱና የኢንተርሃምዌ ዋና አዛዥ የነበረው አስፈሪው ኮሎኔል ቲዎኔስቴ ቦጎሶራ ከስምምነቱ አሻፈረኝ ብሎ ይወጣል፡፡ ቦጎሶራ ‹‹እባብ ቱትሲ›› ብሎ ከሚጠራው ከሩአግ መሪ ከፖል ካጋሜ ጋር ርዕሰ-ብሔር ሃብያሪማና እጅ ለእጅ ሲጨባበጡ በማስተዋሉ ተጠይፏል፡፡ ከዚያም ከቱትሲዎች ጋር በምንም ዓይነት ስምምነት እንደማያደርግ ምሎ ወደ ሩዋንዳ በመመለስ ‹‹ለፍጅት ለመዘጋጀት›› ቃል ገባ፡፡ በትክክል ያደረገውም ያንን ነው፡፡

💫ይቀጥላል💫

Like 👍👍 ማድረግ እንዳይረሳ

ማንኛዉንም አስተያየት በ @atronosebot አድርሱን
👍1
አትሮኖስ pinned «#ሁቱትሲ ፡ ፡ #ምዕራፍ_አራት ፡ ፡ #የወጣቷ_ልብ_አንጠልጣይ_ትውስታዎች ፡ #ትርጉም_በመዝምር_ግርማ ፡ ፡ #ወደ_ዩኒቨርሲቲ ፡ በ1991 ክረምት መጨረሻ የማይቻለው ተከሰተ - በቡታሬ በሚገኘው ብሄራዊው ዩኒቨርሲቲ መማር የሚያስችለኝ የትምህርት ዕድል ተሰጠኝ፡፡ በሕይወቴ ሙሉ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባትን በጽኑ ስመኝ ነበር፡፡ በመሆኑም በፊቴ እነዚያ ሁሉ መሰናክሎች ቢጋረጡብኝም በድንገት ሕልሜ እውን ሆነ፡፡…»
#እ !”


#በኤፍሬም_ስዩም


በነገረ ስራቸው ቦዘኔ ከሚመስሉ፡ በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ግን
በትጋታቸው አገርን እናስተዳድራለን ታላላቅ ድርጅቶችንም
እንስራለን ከሚሉ ልቀው የሚገኙት ታክሲ ረዳቶች ናቸው፡፡
የታክሲው ከርስ ካልሞላ እነሱ እና ቤተሰቦቻቸው ፅኑ በሆነው
የርሃብ መዳፍ ላይ ይወድቃሉና።

ስራቸው ላይ ፌዝ ከሌለባቸው ረዳቶች መካከል አንደኛው
ወደተሰማራበት ታክሲ ውስጥ ገባሁ፡፡

ወያላው እየጠራ ነው

ፊቱ መጣጣ ሰውነቱ የገረጣ ነው

ልብሱ ኣዳፋ... እርምጃው ሽፋፋ ነው፡፡

ሲለው ሚኒባሱ ላይ ይንጠለጠላል። ሲለው ተስፈንጥሮ ይወርዳል፡፡ በየመሃሉ ደግሞ የታክሲውን ጣሪያ ይደበድባል፡፡
ከመግባቴ በፊት እንደሰማሁት፡፡ አሁን ደግሞ ውስጥ ተቀምጬ እያዳመጥኩት ነው፡፡

መሳለሚያ

መሳለሚያ!!

አውቶቡስ ተራ

አውቶቡስ ተራ መሳለሚያ

ጎጃም በረንዳ

ሃብተ-ጊዮርጊስ

ሃብተ-ጊዮርጊስ ጎጃም በረንዳ

አትክልት ተራ

አትክልት ተራ ፒያሳ... ፒያሳ

እራት ኪሎ

አራት ኪሎ ፒያሳ መገናኛ

ፒያሳ መገናኛ ..

ተሳፋሪዎች በታክሲው ጉረኖ ውስጥ በረከቱ፡ እረዳቱ በሩን ዘግቶ
ለሹፌሩ 'እኒድ' የሚል ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ ሹፌሩ ትዛዙን ሰማ፤
ታክሲው መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ የተሳፋሪዎች አንደበት
ረቂቅ በሆነ ዝምታ ውስጥ ነበረ፡፡

ጥቂት መጓዝ እንደ-ጀመረ የታክሲውን ተሳፋሪ ፀጥታ
የሚበጠብጥ የስልክ ጥሪ ከሆነ ስፍራ ላይ ተሰማ “ሄሎ” አለ
ባለ-ስልኩ፡፡ ደዋይ ምን እንደሚል አላውቅም :: “ሄሎ” ባይ ግን
ለደዋዩ ፋታ አልሰጠውም፡፡ ፀጥ ባለ ታክሲ ውስጥ ጮክ ብሎ
የተጀመረ ወሬ ስለነበረ እየሰማሁ ነው፡፡ ተደዋይ ያወራል፡፡
"እሺ ብሩን ተቀበልሽው። በቼክ እንዳትቀበይ! ደግሞ ሁሉንም ተቀበይ፡፡ ጠቅላላ ስንት ነው? ከበቀደሙ ጋር መቶ ስልሳ ዘጠኝ ሺ አራት መቶ ሃያ ኣምስት፡፡ እኔ አሁን ወደ ጉምሩክ እየሄድኩ
ነው። ሌላውን ስመለስ እናወራለን፡፡ ይኸውልሽ ያሲን የሆነ እቃ
ይሰጥሻል ተቀበይው፡፡ስልኩ ተዘጋ፡፡

በልቤ እውነት የሚመስል ወሬ አልመስለኝ አለ፡፡ በጣም ጮክ
ብሎ እንዲህ አይነት ወሬ የሚያወራ ሰው አላምንም፡፡ ጮኸታው
አንዳች መልዕክት ያለው ይመስለኛል፡፡ በራስ መተማመን
ማጣት፡፡ ከመሆን ይልቅ ራስን በወሬ ለመግለፅ መጣር፡፡ ወይም
አንዳች ሴትን ለማማለል በቁስ የተደገፈ ማንነትን መግለፅ፡፡ደረስኩና ወረድኩ፡፡

ሁለት ማኪያቶ

ሶስት ሻይ ፣ አንድ ቡና፣ሶስት እስፕሪስ

አንዳንዴ በማያገባኝ ነገር እገባለሁ፡፡ የቅድሙን ሰውዬ እዚህ
ድረስ ይዤው መጥቻለሁ፡፡ የአንድን ነገር ጥጉን ካላየሁ መሃል
ላይ ባለው ሁኔታ መቆም አልችልም፡ ጥጉን እስካይ የሃሳብ
ዥዋዥዌን እቀጥላለሁ፡፡ ያንን እያሰብኩኝ ፊቴ ከተቀመጡት
ሁለት ጥንዶች ሌላ የሚያሳስበኝ መስማት ጀመርኩ፡፡ ቅድም
ታክሲ ውስጥ የነበረው ሰው አይነት ሞክሼ

“ይገርምሻል “አለ ወንዱ..... “ሲስተሬ መኪናዬን ይዛብኝ ሄዳ
በጣም ተበሳጭቻለሁ፡፡ ደግሞኮ እርሷ ምን የመሰለች ቪትዝ
አለቻት፡፡ ከኔ መኪና ምን እንዳላት አላውቅም.... ደግሞ'ኮ
ብስጭት ያረገኝ ስልክ አለማንሳቷ ነው፣ ግን አይገርምሽም?
አላት....

“እ” አለችው “እ!”

አንድ ቡና ቀጠን ያለ፡፡

እና ማኪያቶ ....

ሌላ ደግሞ አንድ ሻይ ያለ ቅመም......

ልጁ ማንነቱን የሚገልፅ የመሰለውን የትምክህት ወሬውን
እንደቀጠለ ነው።መገለጫው ውስጥ ግን እርሱ የለም፤ ያሉት እቃዎች ናቸው::'ባለፈው የዛሬ ወር ይገርምሻል ምን የመሰለ Gucci (ጉቺ) መነፅር ከዱባይ ይዤ መጥቼ 'ቴዲ ካልወሰድኩት
ብሎ አልወሰደው መሰለሽ ሰው ግን አይገርምሽም?”

እ! በጣም እንጂ:: አለች:: ወሬው ወደላይ ሊላት የተናነቃት
ይመስላል። እርሱ ደግሞ ግንባር እና ሁኔታን አይቶ መረዳት
የሚችል አይነት አይደለም...ይቀጥላል አሰልቺውን፡፡

“አንዴ ይገርምሻል፡ እኔ እና ማክ ማክን አወቅሽው አደል? ይሄ
ከነ ማህደር ጋር ፊልም የሚሰራው፡፡ብታይ የሚገርም ፎጋሪ እኮ
ነው፡፡ እና በቃ አብረን እየቃምን በሳቅ ሊያፈነዳኝ ቆይ
አሰተዋውቅሻለሁ።የሰራቸውን ፊልሞች አይተሻል? ገራሚ አይደሉም?”

«እ» ገራሚ ናቸው።(ዝነኛ ሰው ማወቁን ፤የዝነኛ ሰው ጓደኛ መሆኑን ሊያስረዳት በጎረቤቱ አጥር ሲመካ፡፡የግል እምነቱን ጓዳ አፍሮበታል፡፡ የእሷ ፍላጎት ግን እርሱ ነበር፡፡ይሄኔ ሲተዋወቃት
የምትፈልገው አይነት ሰው መስሏት ነበር፡፡ነገር ግን እንደ
አብዛኞቹ አይነት ወንድ ነው፡፡የሰለቿት አይነት፡፡) ቀጥሏል፡፡
እርሱ ወሬ የታከታት ሴት ምን አይነት እንደሆነች ለመረዳት
የእውቀት እድል ከእርሱ ጋር አይደለችም፡፡

«የዛሬ ሳምንት ይገርምሻል...የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ አልነበር?::
አዎ ነፍ ነበርን እና በቃ ተይኝ ወላ «ክላውድ ናይን» ወላ ሮዲዮ» ከዛ የት ነበርን? እንትን እዎ "ስቶክ ሆልም» በቃ
ሊነጋ አካባቢ ሙትት ብለን «ኢሉዥን»:: ቆይ እነዚህን ቤቶችማ ማየት አለብሽ መዝናናት ካልቀረ እዚያ ነው፡፡ አይደል እንዴ?።

“እ!» አለችው ከ«እ» ሌላ ምን ትበለው?

"እ"

"እ" የሚለው ቃል ከመሰልቸት የሚመጣ ይመስለኛል፡፡ሆድ በውሽት ሲሞላ፡፡ሆድ በነገር ሲወጠር«እ» ይላሉ ሰዎች፡፡

አንድ ቡና

ሁለት ሻይ ፤

አንድ ውሃ፡፡ ትንሹን፡፡

በውስጤ የታክሲው እና እዚያ ቤት የገጠመኝ የሃሳብ ዥዋዥዌ
ቀጥሏል፡፡ለምንድን ነው እንዲህ አይነት ቁስ ላይ የተመሰረቱ
መደለያዎች በወንዶች የሚመሩት? እቃ ላይ ገንዘብ ላይ ያተኮሩ
ነገሮች በእውነትም በሀሰትም በሆነውም ባልሆነውም በቦታውም
ያለቦታውም የሚደሰኩሩት ለምንድነው?ስለምንስ ወንዶች
ከሴቶች ጋር ሲሆኑ ይሄ ነገር በዛ?...

ዥዋዥዌው ወደዛ አስፈነጠረኝ፡፡እንግዲህ ወንዶች ከግል
ማንነታቸው በላይ ራሳቸውን በገንዘብ እና በቁስ የሚገልጹ ከሆነ
ለሴቲቱ «እኔ አንስብሻለሁ»:: ከኔ በላይ እነዚህ አሉልሽ እያሉ
አይደለም ወይ?በዚህ የወንዶች የተሳሳተ አመለካከት ምክንያት
ሴቶች ቁስ ወዳድ ቢሆኑ ጥፋቱ የማን ነው?

ብዙ ወንዶች ሴቶች ቁስና ገንዘብ ወዳድ እንደሆኑ ሲያወሩ
ይሰማል፤ ነገር ግን ይሄ ቁስና ገንዘብን መውደድና ማምለክ
የሚፈጠረው በወንዶች ነው፡፡ሰባኪዎቹ ወንዶች ናቸው.በየታክሲውና በየካፌው፡፡

ሁለት ማኪያቶ። ነጣ ያለ

አንድ ሻይ

አንድ ቡና፡፡እንደ-ወረደ፡፡

ራስን በቁስ መከለል በራስ ማፈር ነው፡፡ከአማናዊው ስብዕና ይልቅ ስብዕናው የተጋረደበትን መጋረጃ ማሳየት፤ በግል ማንነት ከመሳቀቅ ወይም የግል ማንነትን ለመግለፅ ካለመቻል የሚመጣ
ህመም ነው፡፡

እኔ አንስብሻለሁ፡፡ከኔ ይልቅ እህቴ የወሰደችብኝ «ቪትዝ»
ጉሙሩክ ተይዞ ያለው ዕቃ፣ ጅቡቲ ላይ እየወረደ ያለው
ኮንቴይነር፣ እያሉ ማግሳት ሴትን የግል ለማድረግ የምትሞክር
የሰነፍ ዘዴ ናት፡

በሴቶቹ ዘንድ እውቅና የላትም፡፡

ብትታወቅም በልብ አትደገፍም፡፡እውቅናዋ አሰልቺ ከመሆኑ
የተነሳም ለእንዲህ አይነቱ ወሬ የሴቶቹ ምላሽ «እ» የምትል
ናት፡፡

እዚህ?

አንድ ቡና

አንድ ሻይ

💫አለቀ💫

ለአስተያየቶ @atronosebot ን ይጠቀሙ መልካም ምሽት። 🙏
#ሁቱትሲ


#ክፍል_አምስት


#የወጣቷ_ልብ_አንጠልጣይ_ትውስታዎች

#ትርጉም_በመዝምር_ግርማ


#ወደ_ሀገር_ቤት

ሁልጊዜ ጠዋት ከእንቅልፌ ስነቃ የጥላቻ ድምፅ እሰማለሁ፡፡ የአር.ቲ. ኤል. ኤም. ሬድዮ የጥላቻ ድምጾች በመኝታ ቤቴ መስኮት ገብተው ህልሞቼ ውስጥ እስኪደነቀሩ ሌሊቱን በሰላም ተኝቼ አሳልፋለሁ፡፡ ልብ ይበሉ፣ በሦስተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ አር. ቲ. ኤል. ኤም. በጽንፈኛ ሁቱዎች ዘንድ አዲሱና በጣም ታዋቂው ሬድዮ ጣቢያ ለመሆን ችሏል፡፡ ጸረ-ቱትሲ መርዝን የሚረጭ የተለየ የጥላቻ መሣሪያ ወጥቶታል፡፡
ሁሌ ‹‹ስለ ሁቱ የበላይነት›› የሚጮህ አካል-አልባ ክፉ ድምፅ ሆነ፡፡ የሁቱ የበላይነትም ሁቱዎችን በቱትሲ ወዳጆቻቸውና ጎረቤቶቻቸው ላይ እንዲነሱ የሚያደርግ ተናዳፊ ተርብ ለመሆን ቻለ፡፡ ‹‹እነዚያ በረሮ ቱትሲዎች ሊገድሉን ወጥተዋል፡፡ አትመኗቸው… እኛ ሁቱዎች ቀድመናቸው ልንነሳ ይገባናል! መንግሥታችንን ገልብጠው ሊያሳድዱን እየዶለቱብን ነው፡፡ በርዕሰ-ብሔራችን ላይ አንዳች ነገር ቢከሰት ሁሉንም ቱትሲዎች ወዲያውኑ ማውደም ግድ ይለናል! እያንዳንዱ ሁቱ ሩዋንዳን ከነዚህ ቱትሲ በረሮዎች ለማጽዳት እጅ ለእጅ መያያዝ
አለበት! የሁቱ የበላይነት! የሁቱ የበላይነት!››
ይህን በመሰለ አጉለኛ ሁኔታ ከእንቅልፌ እነቃለሁ፡፡ በእርግጥ ዘገባዎቹ እጅጉን በሚያስጠላ ሁኔታ እንጭጭ በመሆናቸው አልፎ አልፎ ያሥቃሉ፡፡ እነዚያን የልጅ ስድቦችና ልቅ ማስፈራሪያዎች ማንም ሰው ከምር ይቀበላቸዋል ብሎ ማመን አሰቸጋሪ ሲሆን መንግሥቱም የሕዝብ ንብረት የሆነውን የአየር ሰዓት ቱትሲዎችን ለማስፈራሪያ መፍቀዱን ማወቁ ይረብሻል፡፡ በወቅቱ ግን በሀገሪቱ በርካታ ስፍራዎች ቱትሲዎች በጽንፈኞች እየተገደሉ መሆኑን በሚገልጹ ወሬዎች ይበልጡን ተረበሽኩ፡፡ በዩኒቨርሲቲው ግቢ እንዳሉት ጓደኞቼ ሁሉ በመገናኛ ብዙሃን ስለሚተላለፉት ዘገባዎች ብዙ ላለማሰብና ላለማውራት ሞከርኩ፡፡ ቤተሰቤ ሁሌ አስደሳችና ልዩ ጊዜ የሚያሳልፍበት የትንሣኤ በዓል እየደረሰ ነው፡፡ ይህን የበዓል ወቅት ጎረቤቶቻችንን በመጋበዝና ወዳጅ-ዘመዶቻችንን በመጠየቅ እቤታችን እናሳልፋለን፡፡ የቤተሰቡ አባላት በሙሉ የምንገናኝበትን የትንሣኤን በዓል እቤቴ ማሳለፍ አምልጦኝ የማያውቅ ቢሆንም እየቀረቡ መጥተው ለነበሩት ፈተናዎቼ ለመዘጋጀት ያግዘኝ ዘንድ በትምህርት ቤቱ ለመቆየት ፈለግሁ፡፡ በፈተናው ጥሩ ውጤት ለማምጣት ቆርጫለሁ፡፡ ወላጆቼ ስልክ ስላልነበራቸው ለአባቴ ለምን እቤት እንደማልሄድ የሚያብራራ ደብዳቤ ጻፍኩለት፡፡ ወላጆቼ ሁልጊዜ ልጆቻቸው የተሻለ ውጤት ያመጡ ዘንድ

ከሚጠበቀው በላይ እንዲያጠኑ ስለሚፈልጉ ቅር እንደማይሰኙብኝ በጣም እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ይህ ለካ ትልቅ ስህተት ኖሯል!
አባቴ እቤት እንድሄድ የሚለምን ደብዳቤ ጻፈልኝ፡፡ እንዲያውም የጠየቀኝ የትምህርት ቤት እረፍቴ እስኪደርስ ሳልጠብቅ ወዲያውኑ እንድሄድ ነው፡፡ ከእርሱ ጋር እንድሆን እንደሚፈልግና እቤት ያላንዳች ረብሻ ማጥናት እንደሚቻለኝ ቃል ገባልኝ፡፡ ልባዊ ተማጽኖው በዓይኖቼ እንባ ሞላባቸው፡፡ ውድ ልጄ፣
ትምህርት አንቺን ከኛ እንደነጠቀን ይሰማኛል፡፡ እናትሽና እኔ እረፍትሽ እስኪጀምር በጉጉት እየጠበቅን ነው፡፡ ምክንያቱም ከጀመረ አንቺ እቤት መጥተሽ እንደገና እንደ ቤተሰብ ስለምንኖር ነው፡፡ መምጣትሽን እንፈልገዋለን፤ ወላጆችሽ ነን፤ እንወድሻለን፤ በእጅጉ እንናፍቅሽማለን - ይህን ሃቅ በፍጹም አትርሺው! ለሁለት ቀናት ቢሆንም እንኳን ልታዪን ልትመጪ ግድ ይልሻል፤ ጊዜውን ለሌላ ለምንም ጉዳይ መስዋዕት እንዳታደርጊው፡፡ ነዪልን፤ አብሮነትሽን እንፈልገዋለን …
ደብዳቤውን አንብቤ ሳልጨርሰው ወደ ቤት ለመሄድ ወሰንኩ፡፡ ከወላጆቼ ጋር ስድስት ቀናትን አሳልፌ ለፈተናዎቼ በሳምንቱ መጨረሻ ትምህርት ቤት ለመመለስ አቀድኩ፡፡ የጉዞ ዝግጅቴን ሳደርግ የሳራ ታናሽ ወንድም የሆነው ኦገስቲን ከእኔ ጋር ለበዓሉ ወደ ወላጆቼ ቤት ሄዶ መዋል ይችል እንደሆን ጠየቀኝ፡፡ ኦገስቲን የወንድሜ የቪያኒ የልብ ጓደኛ ሲሆን የመንፈቀ-ዓመቱን ትምህርቱን ኪጋሊ ላይ ካገባደደ በኋላ በትምህርት ቤት መኝታ ቤታችን ውስጥ ቆይቷል፡፡ መለሎው፣ መልከ-ቀናውና አስደሳቹ የ18 ዓመቱ ኦገስቲን ከቪያኒ በቀር ማንም ሰው ፊት አያወራም፡፡ እንግዳችን ቢሆንልን እንደምንደሰት ነገርኩት፡፡

ኦገስቲንና እኔ ማታባ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ደረስን፤ የቤተሰቤም አባላት በመምጣቴ በእጅጉ ተደሰቱ፡፡ በሳይንስ የድህረ-ምረቃ ትምህርቱን ለመከታተል ዓለም አቀፍ የትምህርት ዕድል ካገኘው ከኤይማብል በስተቀር ቤተሰቡ ተሟልቷል፡፡ ኤይማብል አገሪቱን ለቆ ከ5 000 ኪሎሜትሮች በላይ ወደምትርቀው ሴኔጋል ሄዷል፡፡ ዳማሲን በበኩሉ በታሪክ በሁለተኛ ዲግሪ ከተመረቀ ጀምሮ ከሚያስተምርበት ከኪጋሊ ተሳፍሮ መጥቷል፡፡ ቪያኒም ከአዳሪ ትምህርት ቤት ተመልሷል፡፡
የመጀመሪያዋን ቀን ከዳማሲን የመንደር ወሬ ስሰማ፣ ጓደኞቼን ስጠይቅ፣ ከቪያኒ ጋር ስንጫወትና ስንከራከር አሳለፍኩ፡፡ በመጭው ቀን፣ በትንሳኤ እለት፣ አብረን ጥሩ ምግብ በላን፡፡ አምላክን ስለሰጠን ነገር ሁሉ አመስግነን በቤተሰባችንና በመንደራችን ስላለው ስለ ሁሉም ሰው ደህንነት ጸለይን - በተጨማሪም ስለብቸኛው ቀሪ አባላችን ስለ ኤይማብል ልዩ ጸሎት አደረስን፡፡ በላያችን ያንዣብብ ከነበረው የፖለቲካ ውጥረት በስተቀር አዝናኝ ጊዜ በማሳለፍ ላይ ነን፡፡ ከወላጆቼ ጋር በመሆኔ ደህንነትና ችግር-አልባነት ተሰማኝ - ይህም የሆነው ምንም ነገር ቢከሰት ታጽናናን ዘንድ እናቴ ስለምትኖርና አባቴም እኛን የመከላከሉን ሥራ ስለሚሠራ ነው፡፡ ቢያንስ ያንን ነው ያሰብኩት ፡፡
ይህ ምሽት የኛ ዓለም እስከዘላለሙ ልትቀየር ትንሽ የቀራት መሆኑን ለመገመት የሚያዳግትበት እንደወትሮው ያለ ምሽት መሆኑ ነው፡፡ ስለ ትምህርት፣ ሥራና በመንደሩ እየተከሰተ ስላለው ነገር እቤት ቁጭ ብለን እናወራለን፡፡ እናታችን ስለ ሠብሉ ስትነግረን አባታችን ደግሞ የቡና ኅብረት-ሥራው የትምህርት ወጪያቸውን ስለሚሸፍንላቸው ሕፃናት ያወራልናል፡፡ ኦገስቲንና ቪያኒ ይቃለዳሉ፡፡ እኔ በበኩሌ እየተዝናናሁና ሁሉንም ነገር እየታዘብኩ እቤት በመሆኔ ደስተኝነት ተሰምቶኛል፡፡ ያልተደሰተው ዳማሲን ብቻ ነው፡፡ ሁልጊዜ በዓል ላይ ሕይወት የሚዘራው እሱ የነበረ ቢሆንም ምሽቱን ሙሉ ሲብሰለሰልና በሥጋት ሲናጥ ቆይቷል፡፡
‹‹ዳማሲን ምን ሆነሃል?›› ስል ጠየኩት፡፡
ወንድሜ ቀና ሲል ዓይኖቻችን ተገጣጠሙ፡፡ ከዚያም በኋላ ዝም ብሎ መቆየት አልተቻለውም፡፡ በተጣደፈ ቃላትና ስሜት ሸክሙን እኔ ላይ አቃለለ - ‹‹ኢማኪዩሌ አይቻቸዋለሁ፤ ገዳዮቹን አይቻቸዋለሁ፡፡ ወደ ቦን ቤት ስንሄድ በርቀት አይተናቸዋል፡፡ የኢንተርሃምዌን ባለ ደማቅ ቀለማት ልብሶች ለብሰዋል፤ የእጅ ቦምቦችንም ይዘዋል፤
ቦምቦች ነበሯቸው ኢማኪዩሌ!›› ሲል ድምጹ አሰቀቀኝ፡፡
ሁሉም ሰው ንግግሩን ስለሰማው ቤቱ እርጭ አለ፡፡ ወላጆቼ እርስ በርሳቸው ተያዩና ዳማሲንን አዩት፡፡
አባቴ ልጁን ለማረጋጋት ሲል ‹‹ምናልባት ሐሳብህ አሸንፎህ እየወጣ እንዳይሆን›› አለው፡፡ ‹‹ብዙ መጥፎ ወሬ ይሰማል፡፡ ሰዎችም አደጋን በሌለበት እያዩት ነው፡፡››
‹‹አይ፣ ዝም ብዬ እኮ እየቃዠሁ አይደለም›› አለ ዳማሲን በድንገት ቆሞ የጉዳዩን አጣዳፊነት በሚያንጸባርቅ መልኩ በመናገር፡
👍2😁1
‹‹ያየሁት ያንን ብቻም አይደለም፡፡ በአካባቢው ያሉት የሁሉም የቱትሲ ቤተሰቦች ስም ዝርዝር አላቸው፤ የኛም ስም በዚያ ስም ዝርዝር ላይ ሰፍሯል! በዝርዝሩም ላይ ያሉትን ዛሬ ማታ መግደል ለመጀመር አቅደዋል!››
ዳማሲን በቤቱ ውስጥ እየተንቆራጠጠ አባቴን ይለምን ገባ፡፡ ‹‹አባባ፣ እባክህ እንሂድ፤ተለመነኝ፡፡ ነገሩን ማድረግ በሚቻልበት በዚህ ሰዓት ከዚህ ስፍራ መጥፋት አለብን፡፡ ቁልቁለቷን ወርደን፣ ጀልባ ፈልገን፣ የኪቩ ሐይቅን አቋርጠን እኩለ-ሌሊት ላይ ዛየር በደኅና መግባት እንችላለን፡፡ ይሁን እንጂ ጊዜያችንን ሳናባክን አሁኑኑ መሄድ ግድ ይለናል፡፡››
ዳማሲን ያለወትሮው በድንገት እንደዚያ መጮሁ ሁላችንንም አስጨነቀን፡፡ ወንድሜን ስለማውቀው ምሽቱን በሙሉ ሲያወጣና ሲያወርድ ብሎም ሲጨነቅ አምሽቶ መሆን አለበት እላለሁ፡፡ የማምለጫው ዕቅድ እስኪመጣለት ድረስ ግን ምንም ሊለን አልፈለገም፡፡
‹‹ቆይ ዳማሲን ለደቂቃ ረጋ በል›› አለ አባቴ፡፡ ‹‹እናትህንና እህትህን እያበሳጨሃቸው እኮ ነው፡፡ ዛሬ በትክክል አየሁት፣ ሰማሁት ብለህ የምታስበውን ነገር ምንነት እንተንትነው፡፡ በደነገጥክና በፍርሃት በራድክ ጊዜ ውሳኔዎች ላይ ከደረስክ ስህተት ትፈጽማለህ፡፡ ሁሉንም ነገር በጥንቃቄ እንየው፡፡ እሺ፣ የተባለውን የሥም ዝርዝር በትክክል አይተኸዋል?››
ዳማሲን በአባቴ ጥርጣሬ ቢበሳጭም ዝርዝሩን በዓይኑ እንዳላየ ግን አመነ - ከጓደኞቹ ግን ስለዚህ ነገር ሰምቷል፡፡ ያያቸው ሰዎች ኢንተርሃምዌ ስለመሆቸውም እርግጠኛ ነው፡፡
‹‹አየህ፣ እንዳልኩት ነው›› አለ አባቴ፡፡ ‹‹ሁሉም ሰው ተደናግጧል፡፡ አንተም ብትሆን የራስህ ስሜት ሁኔታዎቹን ከሆኑት በላይ እያጋነናቸው ነው፡፡ ይህን ሁኔታ እኔ ካሁን በፊት አይቼዋለሁ፡፡ ስለ ገዳይ ቡድኖች የሚወሩ አሉባልታዎችንና ስለ ሟቾች ዝርዝር የሚነዛ ወሬ ትሰማለህ፣ ግን ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ሁሉም ነገር በእጅጉ ተጋኖ እንደነበር ትረዳዋለህ፡፡ በበኩሌ በአሉባልታ ምክንያት ቤተሰቤን አንጋግቼ አልሸሽም፡፡ ፈሪዎች ለነሱ ግልጽ የሚመስላቸው ምናባዊ እይታ ስላላቸው ብቻ ቤታችንንና የለፋንበትን ሁሉ ትተን አንሰደድም፡፡››
‹‹ግን አባባ›› ጣልቃ ገባሁ፤ ‹‹ዳማሲን ፈሪ የሚባል ዓይነት አይደለም፡፡ ጎበዝና እንዲህ በቀላሉ የማይታለል ነው፡፡ ምናልባት ብንሰማው ሳይሻለን ይቀራል?›› ተጨነቅሁ፡፡ በእርግጥ ኢንተርሃምዌዎች የሚገደሉ ሰዎችን ሥም ዝርዝር ይዘው በዚያ ምሽት ሰው መግደላቸው እውነት ከሆነ ወደ እኛም በማናቸውም ደቂቃ ይመጡብናል፡፡
‹‹በእርግጥ ዳማሲን እንደሚለው ማድረግ ይኖርብናል›› በማለት አባቴን ገፋፋሁት፡፡ ‹‹በሬድዮ ስንሰማ የቆየናቸውን ነገሮች ሁሉ እስኪ አስቧቸው፡፡ የምር አልመሰሉኝም ነበር፤ ግን ተሳስቻለሁ፡፡ ሁሉም ቱትሲዎች መገደል አለባቸው ይላሉ፡፡ ምናልባት ዳማሲን ልክ ሳይሆን አይቀርም - እኔም አሁን መሄድ አለብን ባይ ነኝ!››
‹‹አይሆንም ኢማኪዩሌ፣ አንሄድም፡፡ መንግሥት ነገሮችን እያሻሻለ ነው፤ ሰላምም በቅርቡ ይሰፍናል፡፡ በሬድዮ እየቀሰቀሱ ያሉት ሰዎች አብደዋል፡፡ ሰዉም ከመጤፍ አይቆጥራቸው! አትጨነቂ፡፡ ተረጋግተን በዓላችንን እናሳልፍ፡፡ የግድያ ዝርዝር ብሎ ነገር የለም፤ ሊገድለን የሚመጣም አለ ብለሽ አትስጊ፡፡ ዕድሜ ብዙ አሳይቶኛል›› አለ አባቴ ደከም ባለ ፈገግታ፡፡ ‹‹እስኪ በፈጠራችሁ ተቀምጠን አብረን ራታችንን እንብላ፡፡››
የአባቴ ማረጋገጫ ሁሉ ነገር ጥሩ እንደሚሆን ለጊዜው አሳመነኝ፡፡ በኋላም ሁላችንም በመመገቢያ ክፍላችን ለእራት ተሰባሰብን፡፡ ምንም እንኳን ዳማሲን በአባታችን መከራከሪያዎች ፈጽሞ እንዳላመነ ለማየት የቻልኩ ቢሆንም በዚያ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ወንድሜ በራስ በመተማመን ስሜት ተቀምጦና እንደ ወትሮው ለመሆን እየጣረ ቀልድ የተሞላባቸውን ዘፈኖች መዝፈን፣ በሰፈራችን ባሉት ሰዎች ላይ መቀለድና ቪያኒን ስለ ሴት ጓደኞቹ በነገር ጠቅ ማድረጉን ተያያዘው፡፡ ግን ብዙ ባሳቀን ቁጥር እያስመሰለ እንደሆነ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ በአስደሳች ፈገግታው ሸፋፈነው እንጂ ወንድሜ በእጅጉ ተሸብሯል፡፡
የዚያን ምሽቱ እራት የቤተሰባችን የመጨረሻው መሆኑን ባውቅ ኖሮ ደስ ባለኝ፡፡ ከመቀመጫዬ ተነሥቼ አምላክን ስለ ሁሉም የቤተሰቤ አባላት አመሰግነው ነበር፡፡ በዚያ ገበታ ዙሪያ የተሰበሰቡትን ሁሉንም ስለወደዱኝ ምን ያህል እንደምወዳቸውና እንደማመሰግናቸው በነገርኳቸው፡፡ ግን የት አውቄ፡፡

ወደ መኝታ ከመሄዳችን በፊት ሁልጊዜ እናደርግ እንደነበረው አንድ ላይ የቤተሰብ ጸሎታችንን አደረስን፡፡ እናቴ ስማ ተሰናበተችን፤ አባቴም ምንም መጥፎ ነገር እንደማይከሰት ቃል ገብቶ ሰላማዊ እንቅልፍ ተመኘልን፡፡
የወላጆቻችን መኝታ ቤት በር መዘጋቱን አንደሰማን አራታችን - ዳማሲን፣ ቪያኒ፣ ኦገስቲንና እኔ - በዋናው ክፍል ተሰበሰብን፡፡ ዳማሲን በእለቱ ስለሰማቸው ወሬዎችና ስላያቸው ነገሮች ቢያንስ ለአንድ ሰዓት ያህል አወራልን፡፡ የዳማሲንን ስጋት ከምር ለመቀበል አባቴ ባሳየው ቸልተኝነት የተነሣም ተጨነቅን፡፡
‹‹በነገራችን ላይ አባታችሁን አለማክበር እንዳይመስላችሁ እንጂ›› ኦገስቲን አንሾካሾከ፡፡ ‹‹ደግሞ ከታላላቆቼ ጋር መሟገት እንደሌለብኝ አውቃለሁ፡፡ ቢሆንም ግን አባታችሁ የተሳሳቱ ይመስለኛል፡፡ በዳማሲን ሐሳብ እስማማለሁ - እዚህ መቆየት አደገኛ ይመስለኛል፡፡ የቤተሰባችሁ ስም በሚገደሉ ሰዎች ዝርዝሩ ላይ ካለ ይመጣሉ፣ ልናስቆማቸውም የምንችልበት ምንም መንገድ የለንም! አባታችሁም እንሂድ በሚለው ጉዳይ ላይ ሃሳባቸውን የሚቀይሩ ስለማይመስለኝ አሁኑኑ ወላጆቻችሁን ትተን ብንሄድ ሳይሻል አይቀርም›› ሲለን በጸጥታ ተዋጥን፡፡ ወደ ኪቩ ሐይቅ በአንድነት ሮጠን ወደ አንድ አነስተኛ በእጅ የምትንቀሳቀስ ጀልባ መዝለልን እንደፈለግን እርግጠኛ ነኝ፡፡ ግን ወንድሞቼና እኔ ወላጆቻችንን ደኅና ሁኑ ሳንል ልንሄድ አንችልም፡፡ በተጨማሪም አባታችን በቤተሰቡ ውስጥ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ስለለመድነው የእርሱን መርህ መከተል ልማዳችን ነው፡፡ ከዚህም በላይ ኦገስቲንና ቪያኒ በየተቀመጡባቸው ወንበሮች ላይ እንቅልፍ እያዳፋቸው ስለሆነ በጣም ዘግይተናል የሚል ምክንያት አመጣን፡፡ ስለዚህ ዳማሲንና እኔ አባታችንን እንደገና ለማናገር እስከ ጠዋት መጠበቅ እንዳለብን ወስነን ሁላችንም ወደየመኝታችን አመራን፡፡
መኝታ ቤቴን እንደ ጸሎት ቤቴ እቆጥራታለሁ፡፡ በስተቀኜ ባለው የምሽት ጠረጴዛዬ መጽሐፍ ቅዱሴንና የኢየሱስንና የድንግል ማርያምን ሐውልቶች አስቀምጬ ከአምላኬና ከራሴ መንፈሳዊ ኃይል ጋር እገናኛለሁ፡፡ አልጋዬ አጠገብ ተንበርክኬ ሐውልቶቹን እያየሁ እግዚአብሔር ቤተሰቤን ከአደጋ ይጠብቅልኝ ዘንድ ጸለይኩ፡፡ አጠገቤ የተቀመጠ ለዳማሲን የገዛሁት የልደት ካርድም አለ፡፡ ሃያ ሰባተኛው የልደት በዓሉ ተቃርቧል፡፡ ለቀናትም ምን ያህል እንደምወደውና እንደማደንቀው የሚገልጽ ግጥም ለመጻፍ ሞክሬያለሁ፡፡ ወላጆቻችን በግልጽ እንዴት እንደምንዋደድ እርስ በርስ እንድንገልጽ ባያስተምሩንም እኔ ያንን ልማድ ለመቀየር ፈልጌያለሁ፡፡ አዲሱ ተግባር በጣም ከምወደው፣ ከማከብረው እንዲሁም በዓለም ላይ ከማንም በላይ ከሚያበረታታኝ ከዳማሲን ሌላ ታዲያ በማን ይጀመራል?
ልጆች ሳለን ካጠፋሁና እንዳይሆን ካደረግሁ ዳማሲን ይቆጣኛል፡፡ ቃላቱ ይናደፉና ያበሳጩኝ የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ግን የመከረኝን
👍1
ሳስበው ትክክል እንደነበረ ይገባኛል፡፡ ልጅ ሆኖ እንኳን የማስተማር ተሰጥዖና ከዕድሜው በላይም ጥበብ ነበረው፡፡ በአሥራዎቹ ዕድሜዎች ሳለሁ የድምጹን ማራኪነትና ልግስናውን እያየሁ እግዚአብሔር እንደ እርሱ ያደርገኝ ዘንድ እጸልይ ነበር፡፡ አልባሳቱን ለደሆች በመቸር፣ በህመም፣ በድህነት ወይንም በአእምሮ ችግር የተገፉ ሰዎችንም በማረጋጋት ሰዓታትን ሲፈጅ እከታተለዋለሁ፡፡
ዳማሲን የመንደራችን ኮከብ ነው፡፡ በዚያን ምሽት እንደነገሩ ጋደም ብዬ ወንድሜ ለኔ ምን ማለት እንደሆነ አሰብኩ፡፡ ትንሽ ፈገግ አንደማለት ብዬ ቃላቱን ባነበበ ጊዜ ምን ያህል ሃፍረትና ደስታ እንደሚሰማው በማሰብ ብዕሬን አንስቼ በልደት ካርዱ ላይ በጻፍኩት ግጥም ላይ የተወሰኑ መስመሮችን አከልኩ፡፡ በፊቴ ላይ የነበረው ፈገግታ ሳይጠፋ መብራቴን አጥፍቼ ጋደም አልኩ፡፡
በሬ ብርግድ ብሎ ሲከፈት ዓይኖቼ ለደቂቃዎች ያህል የተከደኑ መሰለኝ እንጂ ተኝቼ ነቃሁ አልልም፡፡ ከእንቅልፌ ነቅቼ ተቀምጬ መንጋቱን ተገነዘብኩ፡፡ በግራጫው የመኝታ ቤቴ ብርሃን የዳማሲንን የተሸበረ ፊት እያየሁ በሆዴ ‹‹የባሰ አታምጣ›› አልኩ፡፡ ‹‹ምንድነው ዳማሲን? ገዳዮቹ መጡ እንዴ? ገዳዮቹ እዚህ ናቸው እንዴ?›› ስል አንሾካሾክሁ፡፡ ፍርሃት የሚንጸባረቅበትን የራሴን ድምፅ እንኳን መስማት አልተቻለኝም፡፡
ወንድሜ አንዲት ቃል አልተነፈሰም፡፡ በሩ ላይ እንደቆመ ትንፋሹን ለመዋጥ ሲሞክር እሰማዋለሁ፡፡ መጨረሻ ላይ ሲናገር ድምጹ ከጥልቅ ጉድጓድ ጥግ የሚወጣ ይመስላል፡፡ ‹‹ተነሺ ኢማኪዩሌ - በፈጠረሽ ተነሺ፡፡ ርዕሰ-ብሔሩ ሞተዋል!››
‹‹ምን? ርዕሰ-ብሔሩ ሞተዋል ስትል ምን ማለትህ ነው?›› ስል ጮህኩበት፡፡ የሰማሁትን ማመን አልቻልኩም፡፡ ርዕሰ-ብሔሩ በሩዋንዳ ሰላምንና እኩልነትን ለማምጣት ቃል ገብተዋል፡፡ እንዴት ይሞታሉ?››
‹‹ርዕሰ-ብሔር ሃብያሪማና ሞተዋል ማለቴ ነው! ትናንት ማታ ነው የተገደሉት፡፡ ጠያራቸው በሰማይ ሲበር ተመቶ ነው፡፡››
ከተወሰኑ ቀናት በፊት በሬድዮ የሰማሁት ታሰበኝ - ‹‹ርዕሰ-ብሔራችን አንድ ነገር ቢሆኑ ሁሉም ቱትሲዎች ያልቃሉ!›› የሚለው ዛቻ፡፡
በፍጥነት ከአልጋዬ ተነሥቼ በድንጋጤ የሚለበስ ነገር እፈልግ ጀመር፡፡ ጅንስ ሱሪዬን በለበስኩት ረጅም አረንጓዴ ሌሊት የምለብሰው ቀሚሴ ስር አጠለቅሁ፡፡ በወንድሜም ፊት ስለለበስኩ አፈርኩ፤ ይህ በሕይወቴ በፍጹም አድርጌው የማላውቀው ነገር ነው፡፡
‹‹ርዕሰ-ብሔሩ ተገድለዋል፤ የሆነ አካል ርዕሰ-ብሔሩን ገድሏቸዋል›› እያልኩ በተምታታበትና ባለማመን በተሞላ ሁኔታ ለራሴ ማጉተምተም ቀጠልኩ፡፡ ከመኝታ ቤቴ መስኮት ላይ ግርዶሾቹን ገላልጬ ወደ ውጪ አየሁ፡፡ የኔ ሐሳብ ይሁን አይሁን ባላውቅም መንደሩን ክብድ የሚል ቢጫ ጭጋግ ሸፍኖታል፡፡
‹‹ሰማዩ ራሱ እየተቀየረ ነው›› አልኩ አልጋው ላይ ተቀምጬ ራሴን በእጆቼ ይዤ፡፡ ‹‹ወይኔ ዳማሲን ሁላችንም ልንሞት ነው፡፡ በቃ አሁን ይመጡና በእርግጠኝነት ይገድሉናል፡፡››
ወንድሜ ተቀምጦ አቀፈኝ፡፡ ‹‹አዳምጭኝ ኢማኪዩሌ፣ አንሞትም›› ሲል በልበሙሉነት ተናገረ፡፡ ‹‹እኛን ከዚህ ነገር ጋር የሚያያይዘን አንዳች ነገር የለም፡፡ ርዕሰብሔሩ በታንዛኒያ ይካሄድ ከነበረ የሰላም ድርድር ከቡሩንዲው መሪ ጋር በመመለስ ላይ ነበሩ፡፡ ጠያራው ኪጋሊ ላይ ለማረፍ ሲሞክር ነው የተመታው… ኪጋሊ ላይ! አየሽ እዚህ ድረስ መጥቶ እኛን ማንም አይወነጅለንም፡፡››
በወቅቱ ዳማሲን ለእኔ ጀግና ለመሆን ቢሞክርም ቀሽም ተዋናይ ወጣው፡፡ እኔን ለማሳመን እየጣረ እንዳለው ሁሉ ራሱንም ለማሳመን ሙከራ እያደረገ መሆኑን አውቃለሁ፡፡
‹‹ምናልባት አሁን እርሳቸው ስለሞቱ ሁኔታዎች ሊሻሻሉልን ይችላሉ›› ሲል ቀጠለ፡፡ ‹‹ብዙዎች እነዚህን የሰላም ድርድሮችና የሃብያሪማናን የለዘብተኛ መንግሥት እቅድ አልደገፏቸውም፤ ስለዚህ ሞታቸው በእርግጥ ውጥረቶቹን ሊያረግብ ይችላል፡፡ እንደዚህ አትፍሪ፣ ኢማኪዩሌ፡፡ ነይ ውጪ እንውጣ፡፡ ሁሉም ሬድዮ እያዳመጠ እዚያ ነው ያለው፡፡››
እጄን ይዞ ወላጆቼ፣ ቪያኒና ኦገስቲን ሬድዮ ለማድመጥ ወደተቀመጡበት ወሰደኝ፡፡ ዜና አንባቢው የርዕሰ-ብሔሩ ጠያራ ከተመታ ከደቂቃዎች በኋላ በዋና ከተማዋ በሙሉ የመንገድ ኬላዎችና ወታደራዊ የፍተሻ ጣቢያዎች እንደተቋቋሙ አስታወቀ፡፡ በዚያን ምሽትም ኪጋሊ ላይ ሃያ የሚሆኑ ቱትሲ ቤተሰቦች መገደላቸውን አረዳን፡፡
ዘገበ የሚለውን ቃል ላለመጠቀም አንገራግራለሁ፡፡ ምክንያቱም የሬድዮው ሰውዬ የገዳዮቹ መሪ እንጂ ጋዜጠኛ ስለማይመስል ነው፡፡ የርዕሰ-ብሔሩ ልዩ ጥበቃ ጓድ አባላት ፍትህን በራሳቸው እጅ አስገብተው የመሪያቸውን ደም ለመበቀል ቱትሲዎችን መግደላቸውን ሲያስታውቅ የግድያዎቹን አግባብነት ሊያረጋግጥ በመሞከር ነው፡፡ የቤተሰብ አባላትን በሙሉ ወደ መንገድ እየጎተቱ አውጥቶ በግፍ መግደልን ሙሉ በሙሉ ምክንያታዊ አስመስሎ ተናግሯል፡፡
በማስከተልም ወታደሮቹ እስከዚያ ሰዓት ድረስ በኪጋሊ የገደሏቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር አነበበ፡፡ አምስተኛውም ስም የአጎቴ የትዋዛ ሆኖ አረፈው፡፡
‹‹ትዋዛን ገደሉት?›› እናቴ ዓይኖቿን በእጆቿ ቶሎ ሸፍና ራሷን ባለማመን እየነቀነቀች ጮኸች፡፡ ‹‹ትዋዛን ለምን ይገድሉታል? እሰው ጥግ አይደርስ፡፡›› በባለፈው ምሽት የማምለጥ እድላችን እንደተቃጠለብን ሲገባን የቤተሰቤ አባላት በሙሉ በአሰቃቂ ጸጥታ ተዋጥን፡፡ አባቴ እንደገና ፍራቻችንን ለማቅለል ጣረ፡፡ ‹‹በዋና ከተማዋ የሰዉ ስሜት በጣም እየተጋጋለ ነው፡፡ አብዛኞቹ ወታደሮች የሚኖሩት እዚያ ስለሆነ ግድያዎቹም የሚፈጸሙት እዚያ ነው›› አለ የነበረውን እውነታ በማገናዘብ፡፡ ‹‹በአንድ ወይም ሁለት ቀን ውስጥ ሁሉም ነገር ይረጋጋል፤ ምናለ በሉኝ፡፡››
‹‹ወደ ቤቴ ልሂድ መሰለኝ›› አለ ቤተሰቡ ኪጋሊ የሚኖሩት ኦገስቲን፡፡ የትም ቦታ መሄድ የባሰ አደገኛ መሆኑን ስለምናውቅ ትኩር ብለን አየነው፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በተከታታይ በራዲዮ በተነገሩ ማስታወቂያዎች ስጋታችን ተረጋገጠልን - ‹‹በየቤቶቻችሁ ቆዩ፡፡ መጓጓዝ ክልክል ነው፡፡ በመንገዶች ላይ መዘዋወር የሚችሉት


ወታደሮች ብቻ ናቸው፡፡ ከቤታችሁ ውጪ አትውጡ፡፡ የሕዝብ መጓጓዣ ስራ እንዲያቆም ተደርጓል፡፡ ቤቶቻችሁን ትታችሁ እንዳትሄዱ!››
‹‹ሲመጡ እንዲያገኙን ተቀምጠን እንድንጠብቃቸው ይፈልጋሉ፡፡ እንደበግ ዝም ብለን እንታረድላቸዋለን!›› አለ ዳማሲን ዓይኖቹ እየፈጠጡ፡፡ ‹‹ስሞቻችን በሟች ዝርዝራቸው ውስጥ ካሉ የት እንዳለን ያውቃሉ፤ እቤታችን መሆናችን ከእነርሱ የተሠወረ አይደለም፡፡››
የሚያዝያ 7፣ 1994 ማለዳ፣ ለእኛ ገና ባይታወቀንም የዘር ጭፍጨፋው ግን ተጀምሯል፡፡

💫ይቀጥላል💫

Like 👍👍 ማድረግ እንዳይረሳ

ማንኛዉንም አስተያየት በ @atronosebot አድርሱን
👍21
አትሮኖስ pinned «#ሁቱትሲ ፡ ፡ #ክፍል_አምስት ፡ ፡ #የወጣቷ_ልብ_አንጠልጣይ_ትውስታዎች ፡ #ትርጉም_በመዝምር_ግርማ ፡ ፡ #ወደ_ሀገር_ቤት ፡ ሁልጊዜ ጠዋት ከእንቅልፌ ስነቃ የጥላቻ ድምፅ እሰማለሁ፡፡ የአር.ቲ. ኤል. ኤም. ሬድዮ የጥላቻ ድምጾች በመኝታ ቤቴ መስኮት ገብተው ህልሞቼ ውስጥ እስኪደነቀሩ ሌሊቱን በሰላም ተኝቼ አሳልፋለሁ፡፡ ልብ ይበሉ፣ በሦስተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ አር. ቲ. ኤል. ኤም.…»
#የሚስቴውሽማ


#በአልቤርቶሞራቪያ


ነገሩ የሆነው እንደዚህ ነው። ጠዋት አንግቼ ነበር የተነሳሁት። ፊሎሜና ግን ተኝታ ነበር። እቃዎቼን የምሸክፍበትን ቦርሳ ይዤ ከቤቴ እየተጎተትኩ እንደሆንኩ ያህል ወጣሁና ወደ ሞንቴ ፐርዮሊ ግራሜሺ ጎዳና አመራሁ። እዛ የምንጠግነው ነበር። ጥገናውን ለማከናወን ምን ያህል ግዜ ይወስድብኝ ይሆን? ምን አልባትም ሁለት ሰአታት። ምክንያቱም ቧንቧውን ለመፍታትና መልሶ ለመግጠም ብዙ ጊዜ ይፈጃል። ሥራዬን ከጨረስኩ በኋላ በአውቶብስ ቤቴና ሱቄ ወደሚገኝበት ወደ ኮሮኔሪ ጎዳና እመለሳለሁ። ሀለለት ሰዓታት በሞንቴ ፐሪዮሊ፣ ግማሽ ሰዓት ቦታውን ለማግኘት፣ ግማሽ ሰዓት ለመመለስ በድምሩ ሦስት ሰዓታት። እነዚህ ሦስት ሰዓታት ምንድን ናቸው? በዛም አነሰም በሁኔታዎች መሠረት መሆን ያለበት ነው አልኩ ለራሴ። እኔ የቧንቧ ቁራጭ ለመጠገን ሦስት ሰዓት ወሰደብኝ በአንፃሩ ሌላ ሰው ቢሆን ግን...

ወደ ኮሮነሪ ጎዳና እየተመለስኩ ሳለ በግንቡ አጠገብ በችኮላ እየተራመድኩ ነበር። ከመቅፅበት ስሜ ሲጠራ ስሰማ ዞር አልኩና ከእኛ ቤት ፊት ለፊት የምትኖረውን አሮጊቷን ቤት አከራይ ፌዴን አየኋት። ይህች ምስኪን ፍጥረት ፊዴ የዝሆን የሚመስሉ ወልጋዳ እግሮች ነበሯት። ቁና ቁና እየተነፈሰች ነበር።

"ምን ዓይነት ቀፋፊ ቀን ነው! በጎዳናው ወደ ላይ እየወጣህ ነው? እስቲ ይህንን ቅርጫት እርዳኝ እባክህ" አለችኝ።

ዕቃዎቼን የያዝኩበትን ሻንጣ ወደ ሌላኛው ትከሻዬ አዛወርኩትና ቅርጫቱን ተቀበልኳት። በሁለቱ ምሶሶ መሳይ እግሮቿ እንደ ቀንድ አውጣ

"እቤት" ብዬ መለስኩላት። "ከዛ ውጭ ሌላ የት ልትሆን ትችላለች?" "አዎ! እቤትማ በእርግጥ አይቻታለሁ" አለች ጭንቅላቷን ወደ ግራ እያጋደለች።

"ለምን በእርግጥ አልሽ?" ጠየቅኳት።

"አዎ በርግጥ! ምስኪን ልጅ" አለችኝ።

ድንቅ ይለኝ ገባ። ሁኔታውን አጥኚ "እና ለምን ምስኪን ልጅ አልሽኝ" አልኳት።

"ምክንያቱማ ስላዘንኩልህ ነው" አለች አስጠሊታዋ አሮጊት ፍጥረት፤ እኔን ሳትመለከት።

"ምን ማለትሽ ነው?"

"ማለቴ የአሁን ሴቶች በእኔ ጊዜ እንደነበሩ ሴቶች አይደሉም"

"ለምን?"

"ድሮ በእኛ ጊዜ አንድ ባል ሚስቱን ቤቱ ትቷት ሲወጣ ሲመለስም ልክ እንደ ተዋት ቤቷ ውስጥ ሆና ያገኛታል። በአሁኑ ዘመን ግን..."

"አሁን ምን?"

"አሁን እንደድሮው አይደለም...በአሁን ጊዜ. ..ደህና...ብቻ ቅርጫቴን ስጠኝ ልሂድበት፣ በጣም ነው የማመሰግንህ"

እነዚያ የጥዋት ደስታዎቼ አሁን በውስጤ ወደ መርዝነት ሲቀየሩ ተሰማኝ። ቅርጫቱን በእጄ እንደያዝኩ ፦

"የጀመርሽውን በደንብ ካላብራራሽልኝ አልሰጥሽም... ፌሎሜናን እንዴት ወደዚህ ጉዳይ ልታመጭያት ቻልሽ? ወተወትኳት።

"ምንም የማውቀው ጉዳይ የለኝም " አለች "ግን ማስጠንቀቅ ማለት ማስታጠቅ ነው"

"ንገሪኝ እንጂ" ጮሁኩባት "ፊሎሜና ምንድን ነው ያደረገችው?"

"አዳልጂሳን ጠይቃት" ብላ መለስችልኝና ቅርጫቱን ከእጄ መንጭቃ እንዴት እንደዚህ መራመድ እንደቻለች ሳይገባኝ በረዥም እርምጃ ተፈተለከች።

በዚህ ሰዓት ወደ ሱቅ መሄድ ምንም እርባና እንደሌለው አሰብኩና አዳልጂሳን ለመፈለግ ወሰንኩ። ደስ የሚለው እሷም የምትኖረው በኮሮናሪ ጎዳና ውስጥ ነው። ፊሎሜናን ከማግኘቴ በፊት እኔና አዳልጂሳ ለመጋባት አቅደን ነበር።ግን ሴተ ላጤ ሆና ቀረች። እናም ይህንን የፊሎሜናን ስም የማጥፋት ወሬ የፈጠረችው እሷ ናት ብዬ ጠረጠርኩ። አራት ደረጃዎች ወጥቼ በጡጫ በሩን ደበደብኩት። እሷም በሩን በፍጥነት ስለከፈተችው ፊቷን ሳልመታት ለትንሸ ነበር የተረፈችው። እጅጌዎቿ ተሰብስበው በእጆ መጥረግያ ይዛ ነበር። ጎልቶ በወጣ ድምፅ "ጂኖ! ምን ፈለግክ! አለችኝ።

አዳልጂሳ አጭር ማራኬ ሴት ነበረች።ሆኖም ትንሽ ተለቅ ያለ የእራስ ቅልና ትንሽ ሰፋ ያለ አገጭ ነበራት። በአገጯ መስፋት ምክንያት "አካፋዋ" ብለው ይጠሯታልት። በእርግጥ ፊተዋ እንደዛ ሊባል የሚችል ዓይየነት ነው ። እኔም በጣም በጣም ተበስጭቼ "አንቺ አካፋ! አንቺ ነሽ ፊሎሜና ልታደርገው የማትችለውን ነገር እኔ ስራ ስሄድ አደረገች ብለሽ ያስወራሽ?" አልኳት።

ሁለቱ የተቆጡ ዐይኖቿን በእኔ ላይ ተከለቻቸውና "አንተ የፈለከው ፊሎሜናን ነበር...እናም አሁን እሷን አግኝተሀል" አለችኝ።

ተንደርድሬ ሄጄ እጇን ያዝኩት። ግን ደስ እንዳላት ስገነዘብ ወዲያውኑ ለቀኳትና "እና አንቺ ነሽ?" አልኳት።

"እኔ አይደለሁም....እኔ የሰማሁትን ነው የደገምኩት"

"እና ከማን ነው የሰማሽው ታድያ?"

"ከጂያኒና"

ምንም ሳልናገር ወጣሁ። ሆኖም ጀርባዬን ያዘችኝና አንዳች ስሜት በሚቀሰቅስ እይታ እያየችኝ "አካፋ ብለህ አትጥራኝ" አለችኝ።

"ለምን? አካፋን የሚመስል ፊት የለሽምን?" ብያት፣ ራሴን ከእጇ አላቅቄ እየተጣደፍኩ ደረጃዎቹን መውረድ ጀመርኩ።

"ከጥንድ ቀንዶች ይልቅ አካፋ የሚመስል አገጭ ይሻላል" ብላ ከኋላ ጮኸች የቤቱን ግድግዳ እየተደገፈች።

አሁን መጥፎ ስሜት ይሰማኝ ጀመር። ፊሎሚና እያታለለችኝ መሆኑ አልመስልኝ አለኝ። ምክንያቱም ከተጋባን ከሦስት ዓመት በፊት ጀምሮ ያላትን ፍቅር እንዳለ ትለግሰኝ ነበር። ግን እንዴት የሚያስቀና ነገር ነው። እነዚህ የፍቅር መግለጫዎች አሁን በፌዴና አዳልጂሳ ጥቆማዎች እርዳታ የክህደት ማስረጃዎች ሆነው ይታዩኝ ጀመር። ደህና ደህና....ጂያኒና በዛው ጎዳና አጠገባችን በሚገኝ ቡና ቤት የምትሰራ ገንዘብ ተቀባይ ነች። ፈዛዛ ቢጫና ለስላሳ ፀጉርና የቻይናዎች የሚመስሉ ሰማያዊ ዐይኖች አሏት። ረጋ ያለች፣ አሳቢና ቁጥብ ነች።

ወደ ገንዘብ መቀበያው ሄድኩና "ንገሪኝ፣ እኔ ከቤት ስወጣ ፊሎሚና ቤት ውስጥ ሰዎች ታስገባለች ብለሽ ያወራሽው አንቺ ነሽ?" አልኳት።

አንዱን ደንበኛ እያስተናገደች ነበር። የገንዘብ ማስሊያ ማሽኑን ተጫነችና ትኬት ስባ አወጣች። ድምፆን ሳትጨምር "ሁለት ቡና" ብላ አስታወቀች። ቀጥላ "ምን አልከኝ ጂኖ?" ጠየቀችኝ።
ጥያቄዬን ደገምኩላት። ከፊቷ ለቆመው ደንበኛ መልስ ሰጠችና "ጂኖ፣ እንደዛ አይነት ወሬ ስለ ውድ ጓደኛዬ ፊሎሚና ራሴ ፈጥሬ አወራለሁ ብለህ በርግጥ ታስባለህ?" መልሳ ጠየቀችኝ።

"እና አዳልጂሳ አልማው መሆን አለባታ"

"አይደለም" ብላ አስተካከለችኝ። "አይደለም...እሷ አልማው አይደለም፣ እኔም አልፈጠርኩትም፣ እኔ የሰማሁትን ደገምኩት። ለራሴ ግን እኔ አላምንም ነው ያልኩት..በእርግጥ አዳልጂሳ አልነገረችህም"

"ደህና! እሺ ለአንቺስ ማን ነው የነገረሽ?"

"ቪንቸንሲና ናት ከላውንደሪው መጥታ የነገረችኝ "

ቻው ሳልላት እየተቻኮልኩ ወጣሁና በቀጥታ ወደ ላውንደሪው አቀናሁ። ከመንገዱ ሆኜ ከጠረጴዛ አጠገብ በሁለት እጇቿዋ የካውያውን እጀታ ስትጨብጥ ከሩቅ ለየኋት። ቪንቸንሲና ትንሽ ቀጭን እንደ ድመት ደፍጣጣና ደማቅ ብሩህ ፊት ያላት ሴተሸ ነች። ለእኔ የሚጨክን ልብ እንደሌላት አውቃለሁ። እናም በጣቶቼ ስጠቁማት ወድያውኑ ይዛው የነበረውን ካውያ ትታ ወደ ውጭ ወጣች

"ጂኖ፣ አንተን ሳይ እንዴት ደስ አለኝ መሰለህ" አለች ፍልቅልቅ ገፅታዋን እያሳየች

"አንቺ እርባና ቢስ! ፊሎሚና እኔ በሌለሁበት ሌሎች ወንዶችን እየጠራች ታስገባለች ብለሽ ታወሪያለሽ የተባለው እውነት ነው?" አልኳት።

እጇቿን ከአንዱ የሽርጥ ኪስ ወደሌላው እያስገባች "እንደዛ ብታደርግ ቅር ይልሃል እንዴ? አለች የተከፋ መስላ።

"መልሺልኝ ይህን መጥፎ

ተረት የፈጠርሽው አንቺ ነሽ?"

"ኧረ! እንዴት ቀናተኛ ነህ እባክህ!" አለች ትከሻዋን እያነቃነቀች
👍1
እያነቃነቀች። "ወይኔ አምላኬ አንድ ሴት ከጓጀኛዋ ጋር ብታወራ ምን ይላል...."

"እናም አንቺ ነሽ...."

"በእውነት በጣም ነው ያዘንኩት " አለች፣ ይህች ተንኮለኛ ሴት። ቀጥል "ስለሚስትህ ትጨነቃለች ብለህ እንዴት ታስባለህ? ምንም ነገር አልፈጠርኩም...ለእኔ የነገረችኝ አፔዝ ነች። እሷ ስሙንም ጭምር ታውቀዋለች።"

"እና ማን ነው የሚባለው? "

"እሷ ብትነግርህ ይሻልሀል"

በዚ ጊዜ ፊሎሜና እያታለለችኝ መሆኑን እርግጠኛ ሆንኩ። ስሙም ጭምር ይታወቃል። "በቦርሳዬ ውስጥ መሣርያ አለመያዜ ጥሩ ነው። ምናልባትም ራሴን መቆጣጠር አቅቶኝ ልገድላት እችል ነበር" የሚል ያልፈለኩት ሀሳብ በጭንቅላቴ ውስጥ ይሽከረከራል። ራሴን ሙሉ በሙሉ ማመን ግን አልቻልኩም። ሚስቴ ፊሊሞና ከሌላ ወንድ ጋር....አፔዝ ወደምትሰራበት የአባትዋ የትምባሆ መሸጫ ሱቅ ሄድኩ።

"ሁለት ናሲዮናሊ (የሲጋራ ስም)" አልኳት ብሩን ባንኮኒዉ ላይ እየወረወርኩ። አፔዝ የአስራ ሰባት ዓመት ወጣት ሴት ነች። በክብ ተቆርጦ በጭንቅላቷ ላይ የቆመ ፀጉር አላት። ያበጠ የሚመስል ደብዛዛ፣ ወጥ ቀለም የሌለውና ሐምራዊ ቅባት የተቀባ ፊት አላት። ዐይኖቿ ጥቋቁር ናቸው። ልክ እንደማንኛውም ሌላ ሰው በኮሮነሪ አውራ ጎዳና ነው የማውቃት። እናም ደግሞ ሁሉም ሰው እንደማያውቀው ነፍሷን ለገንዘብ ብላ የምትሸጥ ቅጥረኛ እንደነበረች አውቃለሁ። ሲጋራዎቹን እንዳቀበለችኝ ወደ እሷ ወደ እሷ ጎንበስ አልኩና "ስሙን ንገሪኝ" ብዬ ጠየኳት።

"የማንን ስም?" መለሰች ደንገጥ ብላ።

"የሚስቴን ውሽማ"

ልክ እንደነገጠች ትክ ብላ አየችኝ። ፊቴ ላይ አንዳች አስጠሊታ ሁኔታ አይታ መሆን አለበት።

"ስለዛ ነገር ምንም አላውቅም" ብላ ድርቅ አለች።

ፈገግ ለማለት ሞከርኩኝ። "እንዴ ንገሪኝ እንጂ! ሁሉም ሰው ያውቀዋል እኮ። እኔ ብቻ ነኝ ሳላውቀው የቀረሁት"

ጭንቅላቷን እያወዛወዘች ፍዝዝ ብላ አየችኝ። እኔም ቀጠልኩና፦

"ይሄውልሽ ከነገርሽኝ ይህንን እሰጥሻለሁ ብዬ ጠዋት የሰራሁበትን አንድ ሺ ሊሬ አወጣሁት። ገንዘቡን ስታየው በስሜት ፈነደቀች፣ ልክ እርሷን ለፍቅር እንደጠየኳት ዓይነት። ከንፈሮቿ ተነሸቀጠቀጡ። ወደ ሁሉም አቅጣጫ ተገላመጠችና እጇን ወደ ገንዘቡ እየላከች "ማሪዮ" አለች በለሆሳስ።

"እና እንዴት ልታውቂው ቻልሽ?"

"እናንተ በምትኖሩበት ቤት ያለችው ዘበኛዋ ናት የነገረችኝ"

እናም እውነት ነው ማለት ነው ። ከመኖርያ ቤቴ አጠገብ ነበርን። የትንባሆ መሸጫ ሱቁን ትቼ ወደ ቤት ገሰገስኩ። ጥቂት ቤቶች እንዳለፍኩ ነበር። በዚህ ሰአት "ማርዮ" የሚሊውን ስም እየደጋገምኩት ነበር። በሕይበቴ የማውቃቸው ማርዮዎችን መጥራት ጀመርኩ። ማርዮ ቁምሳጥል ሠሪው፣ ማሪዮ የአትክልት መደብሩ ባለቤት፣ ማሪዮ ወተት ሻጩ፣ ወታደር የነበረና አሁን ስራ አጥ የሆነው ማሪዮ፣ ማሪዮ የአሳማ አራጁ ልጅ? ሮማ ውስጥ አንድ ሚሊዎን የሚሆኑ ማሪዮዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ከእነሱ አንድ መቶ የሚሆኑ ደግሞ በኮሮኘሪ ይገኙ ይሆናል።

የምኖርበትን ቤት መግቢያ አልፌ ወደ ውስጥ ዘለኩና በቀጥታ ወደ ዘበኛዋ ጎጆ ተንደረደርኩ። እሷም እንደ ፋዴ አሮጊት ነች። እግሮቿን አራርቃ በሁለቱ ጭኗቿ መካከል ምስር ቆልላ እየለቀመች ነበር። ራሴን ወደ ጎጆው አስገብቼ "እኔ ስወጣ ፊሎሜና ማሪዮ ከሚባል ውሽማዋ ጋር ትባልጋለች ብለሽ ፈጥረሽ ያወራሽዉ አንቺ ነሽ?" ብዬ ጠየኳት።

በአንዴ ተበሳጨችና "ማንም ሰው አልፈጠረውም....ራሷ ሚስትህ ናት የነገረችኝ" አለችኝ።

"ፊሎሜና?"

"አዎ....ራሷ ነች እንደዚህ ያለችኝ ። ማሪዮ የሚባል ወጣት ወንድ ሲመጣ ጂኖ ቤት ካለ እንዳይገባ ፣ ጂኖ ቤት ከሌለ ግን እንዲገባ ንገሪው"ያ ለችኝ። "አሁንም እዚህ ነው ያለው?"

"አሁንም እዚህ ነው ያለው?"

"አዎ! በእርግጥ ከአንድ ሰዓት በፊት ይሆናል የመጣው"

እና ማሪዮ አሁን አይኖር ይሆናል። ግን አፖርታማው ውስጥ ከፊሎሜና ጋር ነበር። እንዲያውም ለአንድ ሰዓት ያህል። ወደ ደረጃዎቹ ተፈተለኩና ሦስት ደረጃዎች ወጥቼ በሩን አንኳኳሁ። ፊሎሜና ልትከፍተው መጣች። እኔም "እና እኔ ስወጣ ማሪዬ ሊያይሽ ይመጣል" አልኳት።

"ግን እንዴት በምድር ላይ..." ብላ ስትጀምር

"ስለ ሁሉም ነገር አውቄለሁ" ብዬ ጮሁኩባትና ወደ ውስጥ መዝለቅ ጀመርኩ። እሷ ግን መንገዱን እየዘጋች "እስቲ ተረጋጋ። ምን እንደዚህ ያስቆጣሀል፣ ትንሽ ቆይተህ ተመለስ" አለች።

በዚህ ጊዜ ራሴን መቆጣጠር አቃተኝ። ፊቷን በጥፊ መተኋትና "ኧ፣ እንደዚህ እስከ ማለትም ደርሰሻል ለካ። ምን ያስቆጣሀል?" ብዬ ጮኸኩባት። ገፍትሬያት ወደ ጓዳ ገባሁ። ስገባ ግን... አይ አሉባልታ ፈ! የሴቶች አሉባልታ! እዛ ውስጥ በርግጥ ማሪዮ ነበር። በጠረጴዛው ጋ ተቀምጦ ሻይ እየጠጣ። ግን...አዎ ግን ቁምሳጥን ሠሪው ማሪዮ አልነበረም፣ አትክልት ሻጩ ማሪዮም አልነበረም ፣ የአሣማ አራጁ ልጅም አልነበረም። እኔ ከገመትኳቸው ማሪዮች ውጭ ነበር። ቤቴ ውስጥ የቆየ የፊሎሚና ወንድም ማሪዮ ነበር። ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ ወደ ቤት እንዳይመጣ አስጠንቅቄያት ስለነበረ እሷ ግን ለብቸኛው ወንድሟ ካላት መውደድ የተነሳ እኔ በሌለሁበት እንዲመጣ ነበር የነገረችው። ማሪዮ እኔን ሲያይ ብድግ አለና፣

"እንግዲህ ልውጣ፣ በጣም ይቅ...." ሲል እኔ ትንፋሼን ልሰበስብ እየተጣጣርኩ

"አይ ቆይ ማሪዮ...አብረን እራት እንበ..ላለን" አልኩት።

💫አለቀ💫

ለአስተያየቶ @atronosebot ን ይጠቀሙ መልካም ምሽት። 🙏
👍1
አትሮኖስ pinned «#የሚስቴውሽማ ፡ ፡ #በአልቤርቶሞራቪያ ፡ ፡ ነገሩ የሆነው እንደዚህ ነው። ጠዋት አንግቼ ነበር የተነሳሁት። ፊሎሜና ግን ተኝታ ነበር። እቃዎቼን የምሸክፍበትን ቦርሳ ይዤ ከቤቴ እየተጎተትኩ እንደሆንኩ ያህል ወጣሁና ወደ ሞንቴ ፐርዮሊ ግራሜሺ ጎዳና አመራሁ። እዛ የምንጠግነው ነበር። ጥገናውን ለማከናወን ምን ያህል ግዜ ይወስድብኝ ይሆን? ምን አልባትም ሁለት ሰአታት። ምክንያቱም ቧንቧውን ለመፍታትና…»