ግጥም ሲጥም - Gitem Sitem
1.85K subscribers
842 photos
55 videos
20 files
394 links
የዘመናችንን ቀለም ያሳያሉ ያልናቸውን የዚህ ትውልድ የስነ ግጥም ውጤቶችን እንጋራ - እናጋራ።
ለማካፈል የፈለጋችሁትን በGitem_Sitem ፣ gitemsitem@gmail.com የጸሃፊ ስም እና ርዕስ አክላችሁ ላኩልን።

We are all about sharing this generation's poetry. Please email us your pieces gitemsitem@gmail.com
Download Telegram
አንሶሻል ዘለዓለሜ
አካል ሥጋ ጠቦሻል
ረቂቅ ነፍስ በግዘፍሽ
ከአንቺ በልጦ ምን ይዘሻል?

(ጥልመት ድ'ቅድቅ
ብርሃን ድ'ብቅ
እ'ርስት
ዝን'ግት
.
ሕዋ ዐይንሽ ላይ
ንጋቴን ልታጋፍሪበት
ያንቺን ጀንበር መሸበት....

ዝም
ዝም
ዝም
ጭልም!)

አንቺን አልፌ ሁሉን
ሁሉን ሳልፈው ተመለስሁኝ
መኖሪያሽ ነኝ የምለው
ለካስ ነዋሪሽ ነበርሁኝ

(አድማስ እኔ
ብርሃኔ እ'ጥፍ
ጥልመት አንቺ ጥ'ልፍ
ብ'ርር
ክ'ንፍ!

አልነገሩኝ አልተረዳሁ
ስበት ብርሃንን እንዲያሸንፍ!

ሳብሺኝ! ል'ጥፍ!

ቦግ...እልም
ዳግም ዝም!)

ዘለዓለሜ አንሶሽ
መሆኔ ጠቦሽ
ከእኔ ገዝፈሽ
እኔን ያዝሺኝ።
ጥልመትሽ ሁሉን ቢሞላ
አድማስ ሙሉ አበራሺኝ።

..ተንጸባረቅሁ
..ነገሥሁብሽ!

(የማይሆንን አደረግነው
በቅጽበት ሁሌን ኖርነው

...ከዕለታት ጠይም
መልከ መልካሙ ላይ
ሁሉን የሚያህልን
አንድ ነጥብ ሰማይ
አቅፈነው አደርን
ነቅተን ሕልሞች ሆንን

አንቺን አልፌ ዓለሙን
ዓለሙን ሳልፍ ተመለስሁ
አንቺን ሳልፍ - አንቺ ሁሉን
ቀኔ ሲያልፈኝ
አንቺ ሁሌ - አንቺ አሁን
ሆንሁሽና ሆንሁት ሁሉን!

ከዕለታት አንቺ ዕለት
ሰማዩን አቀፍሁት
ተሸከምሁ ሁለንታ
ደቃቃ አሁን ላይ
ዘለዓለም ተረታ...)

አንሶሻል ዘለዓለሜ
(በማን ዐይን ተመዝኖ)
ጠቦሻል ሥጋ አካሌ
(በማን አንጻር ተነጻጽሮ)

የመውደዴን ልኬት
ከመዘንሽው በእነሱ አቅም
ከአሁን ሌላ አልወድሽም

(በእነሱ ዘለዓለም
አሁን የለም!)

ማርቆስ ዘመንበረ ልዑል

#ማርቆስ_ዘመንበረ_ልዑል #MarkOs #ግጥምሲጥም #gitemsitem #ግጥማዊቅዳሜ #poeticsaturdays
አለ? ምልክት?
ላለመኖር ማስረገጫ
መኖርን በአንጻር ማስጌጫ?
ይገኛል ትርጉም?
ነፋስ ከሚወዘውዘው
ዐይኔ ከሚያየው ጀርባ
የለም እያልኩሽ ስላለው?
በማለም ሽንቁር ሾልኬ
ግልገል ሞቴን ተመርኩዤ
ከሐሳብ ቁልል መሐል
አለመኖርን መዝዤ
ስመላለስበት ባነጋ
(ሳውቅ)
ማመኔን ሳይደገፍ
መካድ ብቻውን እንዳይረጋ..
ጎሕ ቀደደ
እውኔ ብርሃን ሲያርፍበት
ሕልሜ ጥላ አረቀቀ
የካድሁትን ሆኜ ተነሳሁ
ያመንሁት ከእጄ ወደቀ
(እንዲህ እናምናለን
ስለማሰብ ሐሳብ ሆነን
ስለመፍጠር ተፈጥረን
ሕልሞቻችን እንዲያልሙ
መገፋት ደግፏቸው
ተቃርኖዎች እንደቆሙ...
እንዲህ እናምናለን
ስናምን እንክዳለን..
በማየት በማወቅ ብርታት ስልሽ
ከዚህ መለስ ህይወት የለም
የቱ ህይወት? ከየት ወዲያ?
ብለሽ ብትጠይቂ
መጥራት ህይወት አልፈጠረም?
በተቃርኖ እርቅ ጠራን
እንዲህ ክደን ማመን ዘራን!)
ግልገል ሞቴን ተንተርሼ
ነፍስ ስለመዝራት አስባለሁ
(ነጋ! ነቃሁ ብዬሽ ነበረ?)
ይሄን እየነገርኩሽ መምሸቱን ረስቻለሁ
(ስለማወቅ ስንታመም
መርሳት ደስታ አልሆነም?)
(ቃል ብርሃን ሆኖ ሕዋው ልብ ላይ ፈስሶኣል። እታች፥ ምድር እንደሕያው ዐይኖቼን በብልጭታው ተክዬ
እንዲህ ነን አይደለ?
ወደ'የሉም' ስንጠራ
ሰማይ ዜማ ልንሰራ
ግጥም ሆነን ልናበራ?
ባይ'ረዱን
የማይታይ ይቅር
የምንታይን ካዱን)
ጎሕ ቀደደ ዳግመኛ
በሄድሁበት ዞሬ መጣሁ
መኖሬ ላይ ሕይወት አጣሁ
አየሽ?
መንገድ መድረስን ሲረታው?
(ሕልሜና ዕውኔ መሐል የነበረች ስስ መጋረጃ ተገፈፈች። ነፋሱ የገፋት ቅጠል ተንሳፋ ፊቴ ላይ አረፈች... ሕይወት መገለጥ ሆነ!
ምን ነበረ የለም ያልኩሽ...?
እንዲህ እናምናለን
በማመን እንክዳለን!
በማየት በማወቅ ብርታት ስልሽ
ከዚህ መለስ ህይወት የለም
የቱ ህይወት? ከየት ወዲያ?
ብለሽ ብትጠይቂ
መጥራት ህይወት አልፈጠረም?
በተቃርኖ እርቅ ጠራን
እንዲህ ክደን ነፍስ ዘራን!)
በጀርባዬ ተንበልብዬ
ዐይኖቼን ሕዋው ልብ ላይ ተክዬ
እንደሌለሁ
እንደሌለሽ ይሄንን እውነት ስረሳ
(ብልጭ ያልነው እኛ አይደለን?)
ግጥሞች ሆነን ስንነሳ?
(እንረሳለን
እንጂ..
ካየነው ጀርባ አለን!)

ለ Migbar Siraj

#ማርቆስ_ዘመንበረ_ልዑል #ምግባርሲራጅ #ግጥምሲጥም #ግጥማዊቅዳሜ #ጥዑምግጥም
ግጥማዊ ቅዳሜን የሚያውቁ ሁሉ ማርቆስንና ጥዑም ግጥሞቹን ያውቃሉ። የተማረው ሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ቢሆንም የሳይንስም የኪነ ጥበብም ሰው መሆንን ከታደሉ ጥቂት ጸኃፍት አንዱ ነው - ባለ ብዙ ተሰጥዖም ነው። 'እናንንብብ፣ እንወያይ፣ ነጻ እንውጣ' በሚል በንባብ ዙሪያ የማሕበራዊ ሚድያውንና መተግበሪያን በመጠቀም ለጸኃፊዎችን አንባቢዎችም ዘመኑን የዋጀ ስራ ለመከወን የተነሳው የ'ንበብ' ባልደረባ ነው።

ግጥሞቹን በዚህ እዩበት 👉🏾 https://tttttt.me/thegreyspot

#𝖊𝖓𝖙𝖗𝖔𝖕𝖞
#ማርቆስ_ዘመንበረ_ልዑል #ዲበኩሉ_ጌታ #የምድር_ዘላለም #ግጥምሲጥም3 #ግጥማዊቅዳሜ #artinaddis #poetry #poetrylovers