ግጥም ሲጥም - Gitem Sitem
1.85K subscribers
842 photos
55 videos
20 files
394 links
የዘመናችንን ቀለም ያሳያሉ ያልናቸውን የዚህ ትውልድ የስነ ግጥም ውጤቶችን እንጋራ - እናጋራ።
ለማካፈል የፈለጋችሁትን በGitem_Sitem ፣ gitemsitem@gmail.com የጸሃፊ ስም እና ርዕስ አክላችሁ ላኩልን።

We are all about sharing this generation's poetry. Please email us your pieces gitemsitem@gmail.com
Download Telegram
አንሶሻል ዘለዓለሜ
አካል ሥጋ ጠቦሻል
ረቂቅ ነፍስ በግዘፍሽ
ከአንቺ በልጦ ምን ይዘሻል?

(ጥልመት ድ'ቅድቅ
ብርሃን ድ'ብቅ
እ'ርስት
ዝን'ግት
.
ሕዋ ዐይንሽ ላይ
ንጋቴን ልታጋፍሪበት
ያንቺን ጀንበር መሸበት....

ዝም
ዝም
ዝም
ጭልም!)

አንቺን አልፌ ሁሉን
ሁሉን ሳልፈው ተመለስሁኝ
መኖሪያሽ ነኝ የምለው
ለካስ ነዋሪሽ ነበርሁኝ

(አድማስ እኔ
ብርሃኔ እ'ጥፍ
ጥልመት አንቺ ጥ'ልፍ
ብ'ርር
ክ'ንፍ!

አልነገሩኝ አልተረዳሁ
ስበት ብርሃንን እንዲያሸንፍ!

ሳብሺኝ! ል'ጥፍ!

ቦግ...እልም
ዳግም ዝም!)

ዘለዓለሜ አንሶሽ
መሆኔ ጠቦሽ
ከእኔ ገዝፈሽ
እኔን ያዝሺኝ።
ጥልመትሽ ሁሉን ቢሞላ
አድማስ ሙሉ አበራሺኝ።

..ተንጸባረቅሁ
..ነገሥሁብሽ!

(የማይሆንን አደረግነው
በቅጽበት ሁሌን ኖርነው

...ከዕለታት ጠይም
መልከ መልካሙ ላይ
ሁሉን የሚያህልን
አንድ ነጥብ ሰማይ
አቅፈነው አደርን
ነቅተን ሕልሞች ሆንን

አንቺን አልፌ ዓለሙን
ዓለሙን ሳልፍ ተመለስሁ
አንቺን ሳልፍ - አንቺ ሁሉን
ቀኔ ሲያልፈኝ
አንቺ ሁሌ - አንቺ አሁን
ሆንሁሽና ሆንሁት ሁሉን!

ከዕለታት አንቺ ዕለት
ሰማዩን አቀፍሁት
ተሸከምሁ ሁለንታ
ደቃቃ አሁን ላይ
ዘለዓለም ተረታ...)

አንሶሻል ዘለዓለሜ
(በማን ዐይን ተመዝኖ)
ጠቦሻል ሥጋ አካሌ
(በማን አንጻር ተነጻጽሮ)

የመውደዴን ልኬት
ከመዘንሽው በእነሱ አቅም
ከአሁን ሌላ አልወድሽም

(በእነሱ ዘለዓለም
አሁን የለም!)

ማርቆስ ዘመንበረ ልዑል

#ማርቆስ_ዘመንበረ_ልዑል #MarkOs #ግጥምሲጥም #gitemsitem #ግጥማዊቅዳሜ #poeticsaturdays