ዐውደ ምሕረት
3.68K subscribers
930 photos
24 videos
271 files
193 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
ፍልሰታ ለማርያም ድንግል
🌈🌈🌈🌈🌈🌈🌈🌈

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥር ፳፩ ቀን በ፵፱ ዓ.ም በ፷፬
ዓመቷ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድና ድካም ባረፈች ጊዜ ቅዱሳን
ሐዋርያት ሊቀብሯት ወደ ጌቴሴማኒ ይዘዋት ሔዱ፡፡ በዚህ ጊዜ
አይሁድ ‹‹እንደ ልጇ ‹ተነሣች፤ ዐረገች› እያሉ እንዳያውኩን በእሳት
እናቃጥላት›› ብለው ሥጋዋን ሊያጠፉ በዓመፃ ተነሡ፡፡ ታውፋንያ
የሚባል አይሁዳዊም አጎበሩን ይዞ ሊያወርዳት ሲል የእግዚአብሔር
መልአክ ሁለት እጆቹን ቀጣው፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ
ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስን ጨምሮ እመቤታችንን በደመና ነጥቆ ወደ
ገነት ወስዶ ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጣት፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም
እመቤታችን ያለችበት ቦታ እንዲገለጥላቸው ባረፈች በስምንተኛው
ወር ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ገብተው እግዚአብሔርን በጸሎት
መጠየቅ ጀመሩ፡፡
ከዚህ ላይ ‹‹ስምንት ወር ሙሉ ምን ይዘው ቆይተው ነሐሴ ላይ ሱባዔ
ገቡ?›› የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡ በመሠረቱ ቅዱሳን ሐዋርያት
ከስብከተ ወንጌል፣ ከጾም፣ ከጸሎት፣ ከገቢረ ተአምራት ተለይተው
እንደማያውቁ መንፈሳዊ ሕይወታቸው ምስክር ነው፡፡ በመኾኑም
እመቤታችን ካረፈችበት ቀን ከጥር ወር ጀምሮ እስከ ነሐሴ ድረስ
ጥያቄያቸውንና ጸሎታቸውን ባያቋርጡም ከሰው ተለይተው ሱባዔ
ገብተው ጾም ጸሎት የጀመሩት ግን ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ነው፡፡
ቀድሞስ የክብር ባለቤት የጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ኾነው እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም
ተሰውራባቸው እንዴት ዝም ብለው ይቀመጣሉ? ቅዱሳን ሐዋርያት
ሁለት ሱባዔ (ዐሥራ አራት ቀናት) ካደረሱ በኋላም የነገሩትን
የማይረሳ፣ የለመኑትን የማይነሳ እግዚአብሔር አምላካችን ጸሎታቸውን
ሰምቶ ነሐሴ ፲፭ ቀን የእመቤታችንን ሥጋ ሰጥቷቸው በክብር ገንዘው
በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል፡፡ በሦስተኛው ቀንም እንደ ልጇ እንደ ጌታችን
አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይታ
ተነሥታለች፡፡ ትንሣኤዋን ‹‹ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ እንደ ልጇ ትንሣኤ››
ያሰኘውም ይህ ምሥጢር ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ሲሰብክ ቆይቶ ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ
ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ወደ
ሰማይ ስታርግ ጠፈር ላይ አገኛት፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ቀድሞ የልጅሽን
ትንሣኤ፤ ዛሬ ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁን?›› ብሎ ትንሣኤዋን
ባለማየቱ ኀዘን ስለ ተሰማው ከደመናው ይወድቅ ዘንድ ወደደ፡፡
‹‹ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ›› እንዲል፡፡ እመቤታችንም ‹‹አይዞህ!
አትዘን፤ ባልንጀሮችህ ሐዋርያት ያላዩትን ትንሣኤዬን አንተ አይተሃልና
ደስ ይበልህ!›› ብላ ከሙታን ተለይታ መነሣቷንና ማረጓን ለሐዋርያት
እንዲነግራቸው አዝዛ የያዘቸውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው፡፡ ከዚያም
እርሷ ወደ ሰማይ ዐረገች፤ እርሱም ወደ ኢየሩሳሌም ወረደ፡፡ ቅዱስ
ቶማስ ትእዛዟን ተቀብሎ በክብር ከተሰናበታት በኋላ ወደ ሐዋርያት
ሔዶ እንዳልሰማ እንዳላየ መስሎ ‹‹የእመቤታችን ነገር እንደምን
ኾነ?›› ሲል ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም ‹‹አግኝተን ቀበርናት›› ሲሉት ‹‹ሞት
በጥር በነሐሴ መቃብር እንዴት ይኾናል?›› አላቸው፡፡
በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ከዚህ በፊት የክርስቶስን ትንሣኤ
መጠራጠሩን ጠቅሶ እየገሠፀ መከራከሩንና መጠራጠሩን ትቶ ስለ
እመቤታችን መቀበር እነርሱ የሚነግሩትን ዅሉ አምኖ መቀበል
እንደሚገባው ለቅዱስ ቶማስ አስረዳው፡፡ ቅዱስ ቶማስም የያዘውን
ያውቃልና ጸጥ ብሎ ሲሰማው ቆየ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ተቈጥቶ
የእመቤታችንን ክቡር ሥጋ ለቅዱስ ቶማስ ለማሳየት ሔዶ መቃብሯን
ቢከፍት የእመቤታችንን ሥጋ ሊያገኘው አልቻለም፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ
ጴጥሮስ ደንግጦ ቆመ፡፡ ቅዱስ ቶማስም ‹‹ወንድሞቼ! አታምኑኝም
ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ስታርግ
አግኝቻታለሁ›› ብሎ እመቤታን የሰጠችውን ሰበን ለሐዋርያት
ሰጥቷቸዋል፡፡ እነርሱም በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም
ትንሣኤና ዕርገት እየተደሰቱ ሰበኑን ለበረከት ተካፍለውታል፡፡
ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩን በቅዳሴ ጊዜ ሠራዒ
ዲያቆኑ በሚይዘው መስቀል ላይ የሚታሠረው መቀነት መሰል ልብስ፤
እንደዚሁም አባቶች ካህናት በመስቀላቸው ላይ የሚያደርጉት ቀጭን
ልብስና በራሳቸው ላይ የሚጠመጥሙት ነጭ ሻሽ የእመቤታችን ሰበን
ምሳሌ ነው፡፡
በዓመቱ ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹ቶማስ የእመቤታችን ትንሣኤዋንና
ዕርገቷን አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን?›› ብለው ከየሀገረ
ስብከታቸው ተሰባስበው ሥጋዋን ይሰጣቸው (ያሳያቸው) ዘንድ
ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ይዘው ጌታችንን ጠየቁት፡፡ እርሱም
ልመናቸውን ተቀብሎ ነሐሴ ፲፮ ቀን እመቤታችንን መንበር፤ ጴጥሮስን
ተራዳኢ ካህን፤ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ
እመቤታችንንም ሐዋርያትንም አቍርቧቸዋል፡፡ እነርሱም
እመቤታችንን በዓይናቸው ከማየት ባሻገር አብረው ሥጋውን ደሙን
ተቀብለዋል (ነገረ ማርያም፤ ትርጓሜ ውዳሴ ማርያምና ቅዳሴ
ማርያም)፡፡
ይህንን ትምህርት መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ቀን ያለው ሁለት ሱባዔ
ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ኾኖ በምእመናን ዘንድ መጾም እንደሚገባው
ሥርዓት ሠርተውልናል (ፍት.ነገ.አን.፲፭)፡፡ ይህ ጾምም ‹‹ጾመ
ማርያም (የማርያም ጾም)›› ወይም ‹‹ጾመ ፍልሰታ ለማርያም
(የማርያም የፍልሰቷ ጾም)›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ‹ፍልሰት› የሚለው
ቃል ‹‹ፈለሰ ሔደ፤ ተሰደደ›› ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን
ትርጕሙም ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር መሔድን ያመለክታል፡፡
‹ፍልሰታ ለማርያም› ሲልም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም
ካረፈች በኋላ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መወሰዷን (ማረጓን) የሚያስረዳ
መልእክት አለው፡፡
በጾመ ፍልሰታ ወቅት በቤተ ክርስቲያናችን በየቀኑ በማኅሌቱ፣
በሰዓታቱና በቅዳሴው በሚደርሰው ቃለ እግዚአብሔር ነገረ ማርያም
ማለትም የእመቤታችን ከመፀነሷ ጀምሮ እስከ ዕርገቷ ድረስ ያለው
ታሪኳ፣ ለአምላክ ማደሪያነት መመረጧ፣ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ክብሯ፣
ርኅርራኄዋ፣ ደግነቷ፣ አማላጅነቷ፣ ሰውን ወዳድነቷ በስፋት ይነገራል፡፡
እመቤታችንን ከሚያወድሱ ድርሳናት መካከልም በተለይ ምሥጢረ
ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌንና ነገረ ድኅነትን ከነገረ ማርያም ጋር
በማዛመድ የሚያትተው ቅዳሴ ማርያም፤ እንደዚሁም ነገረ ድኅነትን
ከምሥጢረ ሥጋዌ (ከነገረ ክርስቶስ) እና ከነገረ ማርያም ጋር
በማመሣጠር የሚያትተው ውዳሴ ማርያምም በስፋት ይጸለያል፤
ይቀደሳል፤ ይተረጐማል፡፡ በሰንበታት የሚዘመሩ መዝሙራት፤ በየዕለቱ
በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር ለተዋሕዶ መመረጧን፣
ዘለዓለማዊ ድንግልናዋን፣ ክብሯን፣ ቅድስናዋን፣ ንጽሕናዋን የሚያወሱ
ናቸው፡፡
በጾመ ፍልሰታ ባሕታውያን ብቻ ሳይኾኑ ዓለማውያንም
በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በእመቤታችን አማላጅነት የሰይጣንን ፈተና
ድል ለማድረግ እንዲቻላቸው ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በየገዳማቱና
በየአብያተ ክርስቲያናቱ በዓት አዘጋጅተው፣ ሱባዔ ገብተው፣ ፈቃደ
ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው ይጾማሉ፤ ይጸልያሉ፡፡
እንደዚሁም ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡ ይህ ጾም
ለእመቤታችን ያለንን ፍቅርም የምንገልጽበት ወቅት ነው፡፡ በተለይ
ኦርቶዶክሳውያን ሕፃናት በአብዛኛው ትምህርተ ወንጌል የሚማሩት፤
ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን የሚቀበሉት በዚህ በጾመ ፍልሰታ ነው፡፡
ጌታችን በስሙ ሁለትም ሦስትም ኾነን ለጸሎትና ለመልካም ሥ

ብንሰባሰብ እርሱ በመካከላችን እንደሚገኝ የገባልንን ቃል ኪዳን
መሠረት በማድረግ (ማቴ. ፲፰፥፳)፣ ዅላችንም በጾመ ፍልሰታ
ሳምንታት በጌታችን፣ በእመቤታችንና በቅዱሳን ሐዋርያት ስም በቤተ
ክርስቲያን ተሰባስበን ቅዱሳት መጻሕፍትን ከመማር ባሻገር ብንጾም፣
ብንጸልይ፣ ብናስቀድስ፤ እንደዚሁም ሥጋውን ደሙን ብንቀበል
በበረከት ላይ በረከትን፤ በጸጋ ላይ ጸጋን እናገኛለን፡፡ በኋላም
ሰማያዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንችላለን፡፡
ስለኾነም የእመቤታችንን ዕረፍትና ትንሣኤ በማሰብ ከልጇ ከወዳጇ
የሚገኘውን ጸጋና በረከት ተስፋ በማድረግ የአባቶቻችንንና
የእናቶቻችንን ፈለግ ተከትለን በየዓመቱ ጾመ ፍልሰታን እንጾማለን፤
የምንችል ደግሞ ንስሐ ገብተን አስቀድሰን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር
ደሙን እንቀበላለን፡፡ ነገር ግን በሕግ የተከለከለ እስኪመስል ድረስ
በዚህ ወቅትም ኾነ በሌላ ጊዜ ሥጋውን ደሙን የሚቀበሉ ወጣቶች
ጥቂቶች ናቸው፡፡ ስለዚህም አረጋውያንና ሕፃናት ብቻ ሳይኾኑ
ወጣቶችም ጭምር የመቍረብና የመዳን ክርስቲያናዊ መብት
እንዳለን በመረዳት ራሳችንን ገዝተን፣ ንስሐ ገብተን፣ ቅዱስ ሥጋውንና
ክቡር ደሙን በመቀበል መንግሥቱን ለመውረስ መዘጋጀት
ይኖርብናል፡፡ አምላካችን በማይታበል ቃሉ ‹‹ሥጋዬን የሚበላ፤
ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው›› በማለት ተናግሯልና
(ዮሐ. ፮፥፶፬)፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት
ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት ጸጋና በረከት
አይለየን፡፡

ምንጭ :-ዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
ሐምሌ ፴ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም( ማህበረ ቅዱሳን)
ዓውደ ምህረት የእናንተ
👇👇👇👇👇👇👇
@AwediMeherit
@AwediMeherit

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
#ሱባዔ

ሱባዔ በሰዋሰው ትርጉሙ ቆየ ሰነበተ ዘገየ ሰባት ማለት ሲሆን ምሥጢራዊ ትርጓሜውም ደግሞ አንድ ሰው ከዚህ ቀን እከዚህ ቀን ድረስ ፈጣሪዬን በጸሎት እገናኛለሁብሎ የሚያቅደው ዕቅድ ነው። ሰባት ቁጥር በእስራኤላዊያን ዘንድ በሥራም በቃልም የሚገለጥ ፍጹም ቁጥር ነው ፈጣሪ ዓለማት እግዚአብሔር በሰባተኛው ቀን ሥነ ፍጥረትን ከመፍጠር አረፈ እንዲል በጸሎት የሚተጉ ምዕመናንም በቀን ሰባት ጊዜ ማመስገናቸው የሰባት ቁጥርን ፍጹምነት ያመለክታል ። ሱባዔ የተጀመረው ከመጀመሪያው ሰው አዳም ውድቀት በኋላ ነው ቅዱሳን መላእክት አዳምን ጸሎት እንዴት እንደሚጸለይ እንዳስተማሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ይናገራሉ። ለአዳምም የጸሎት ጊዜያትን አስተምረውት አስተምረውት ነበርና ጥፈቱን አምኖ ሱባዔ በመግባቱና በመጸለዩ እግዚአብሔርም በማይታበል ቃሉ ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ቃል ኪዳን ገባለት ።



ሱባዔ ለምንምክንያት እንገባልን ቢሉ የመጀመሪያው የሚሆነው የሰው ልጅ በባህሪው ኃጢአት የሚስማማው ነው በሥጋ ሰውነቱ ፈጣሪን ይበድላል በፈጸመው በደል / ኃጢአት/ ሕሊናው ይወቅሰዋል በዚህም ያዝናል ይጸጸታል በሰራው ኃጢአትም ልቡ ይደነግጣል በዚህ ጊዜ የፈጣሪን ይቅርታ ለማግኘት ሲል ሲል ሱባዔ ይገባል ።እግዚአብሔርን ለመማፀን የሚገባ ሱባዔ አለ ። ማንኛውም ሰው ሱባዔ በገባ ቁጥር ወደ ፈጣሪው የሚያቀርበው ተማጽኖ ሊኖረው ይገባል ምንም የምንለምነውና የምንጠይቀው ነገር ሳይኖር ሰባዔውን ብንገባ የምናገኘው ምንም አይነት መልስ አይኖርም
ስለዚህ ተማፅኖ ሊኖረን ይገባል ። ያለ ምንም ቅድመ ሆኔታና ዝግጅት ሱባዔ የሚገቡ ሰዎች ከሱባዔው በኋላ ምን እንደተመለሰላቸው የሚያውቁት ነገር ስለማይኖራቸው ሱባዔ በመግባታቸው የሚገኙት ነገር አይኖርም ይህን ተገንዝበው ከመግባታቸው በፊት የሚገቡበትን ምክንያት ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው ። ቅዱሳን አባቶችና ቅዱሳት እናቶቻችን ደማቸውን ካፈሰሱበት አጥንታቸውን ከከሰከሱበት ድንቅ ድንቅ ገቢረ ተአምራት የሰሩበት ቦታ ገዳማቸውና አድባራት ላይ የሚገባ ሱባዔ ከቅዱሳኑ ረድኤት ተካፋይ ይደርጋል ። ሱባዔ የተደበቀን ምሥጢር የሚገለጥበት ቁልፍ የቤተክርስቲያን ሥርዓት ነው ቅዱሳን አባቶቻችን ያዩት እራይ ምሥጢሩና ትርጉሙ አልገለጥ ሲላቸው ሱባዔ ይገቡ ነበር እግዚአብሔርም በንጽሕና ሆነ ነው የገቡትን ሱባዔ ተመልክቶ ምሥጢሩንና ትርጉሙን ይገልጥላቸዋል ። ነቢዬ ዕዝራ የመጽሐፍታት ምሥጢር እንዲገልጥለት ሱባዔ ገባ እግዚአብሔር አምላክም ሁሉን ገለጸለት የጠፉትን የብሉይ ኪዳን መጽሐፍታት ደግሞ ለመጻፍ ችሏል ይህ ምሥጢር የተገለጠለት በሱባዔ ነው ።

ከብሉይ ጀምሮ ያሉ የሱባዔ አባቶቻችን የገቡት ሱባዔ ሱባዔ አዳም ፣ ሱባዔ ሔኖክ ሱባዔ ነብያት
፣ሱባዔ ዳንኤል ሱባዔ ዳዊት በተጨማሪም የግል ሱባዔ የማኀበር ሱባዔ የአዋጅ ሱባዔ በመባል ይታወቃሉ በሐዲስ ኪዳን ከአራት ቀን በኋላ የምገባ ሐዋርያት የገቡት ሱባዔ ነው የፍልሰታ ሱባዔ በዚህ ሱባዔ ተሰውሮ የነበረውን የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ሥጋ የተገኘበት ትንሣኤዋ እንዲገለጥላቸው የተገባ ሱባዔ ነው ። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን 14 ቀን ያክል በጻም በጸሎት ተማጽነው ትንሣኤዋን ገለጠችላቸው ። እንግዲህ ሱባዔ ከብዙ በጥቂቱ ይህንን ይመስላል ወቅቱ የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የፍልሰታ ስባዔ እንደ መሆኑ መጠን እኛም የሐዋርያቱን ፈለግ በመከተል በንጹሕ ልቦና በትሁት መንፈስ ሆነን የእናታችን ትንሣኤ ይገለጥልን ዘንድ በሱባዔው እንትጋ ። ለሐዋርያቱ በሙሉ የልባቸውን መሻት የፈጸመች የጌታችን እናት ድንግል ማርያም የእኛንም የልባችንን ትፈጽምልናለች። ወቅቱን የጾም፣የጸሎት፣የስግደት፣ የምጽዋት፣ ስለ ሀገራችን ኢትዮጲያ የምናለቅስበት ነው ። ስለዚህ ሁላችን በሱባዔው እንበርታ

“በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቍረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር።”
— ሐዋርያት 2፥42
#ዓውደ ምህረት የእናንተ
👇👇👇👇👇👇👇
@AwediMeherit
@AwediMeherit

.....ይቆየን.......
ምንጭ :-እናት ማህበሬ ምክሐ ደናግል ሰሌዴ መጽሔት ሐምሌ ና ነሀሴ2010ዓ.ም የተለጠፈ
#ሱባዔ ነቢያት

እግዚአብሔር ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ ቀደምት ነቢያት በተነሡበት ዘመን ቅደም ተከተል ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆንና ዳግም መምጣት ትንቢት ተናግረዋል፡፡ ሱባዔም ቆጥረዋል፡፡ ኢሳ.7.14፡፡ መዝ.49.3፡፡ ዘካ.13.6፤ ዘካ.14.1፡፡ የአንዱ ነቢይ ትንቢታዊ ንግግርና ሱባኤ በአነጋገርና በአቆጣጠር ከሌላኛው ነቢይ ጋር ይለያያል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ትንቢቱን ሲያናግር ምሳሌውን ሲያስመስል ጐዳናው ለየቅል በመሆኑ ነው፡፡ «ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ፡፡» እንዲል፡፡ ዕብ.1.1፡፡ የአቆጣጠር ስልታ ቸውና የሱባዔ መንገዳቸው ቢለያይም ዓላማና ግባቸው ግን አንድ ነው፡፡

#ሱባዔ አዳም

አዳም ትንቢት በመናገርና ሱባዔ በመቁጠር የመጀመሪያውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ምክንያቱም በገነት ሰባት ዓመት ከአንድ ወር ከዐሥራ ሰባት ቀን በተድላና በደስታ ከኖረ በኋላ ሕግ በማፍረሱና የፈጣሪውን ቃል በመጣሱ ያለምንም ትካዜና ጉስቁልና ከሚኖርበት ዔደን ገነት ተባርሯል፡፡ ዘፍ.3.24፡፡ እርሱም ፈጣሪው እንዲታረቀው፣ በዐይነ ምሕረት እንዲጐበኘው፣ ቅዝቃዜው ሰውነት ከሚቆራርጥ ባሕር ውስጥ በመቆም ለሠላሳ አምስት ቀን /አምስት ሱባዔ/ ሱባዔ ገብቷል፡፡ በባሕርዩ የሰውን ልጅ እንግልት የማይወድ ቸሩ ፈጣሪ የአዳምን ፈጽሞ መጸጸት ተመልክቶ «በኀሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ ወእድኅክ ውስተ መርህብከ ወእቤዝወከ በመስቀልየ ወበሞትየኸ በአምስት ቀን ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ» ብሎ ተስፋውን ሰጠው፡፡ አዳም የተሰጠውን ተስፋ ይዞ በዓለመ ሥጋ ለዘጠኝ መቶ ሠላሳ አመት ከኖረ በኋላ መከራና ችግር ከበዛበት ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡
በወንጀል ተከሶ በወኅኒ የተፈረደበት ሰው ከእስር የሚፈታበትን ዕለት በማውጣት በማውረድ ወራቱንና ዓመታቱን እንደሚቆጥር፣ አዳምም በሞት ቢለይም በሲኦል የነፍስ ቅጣት ካለበት ሥፍራ ይኖር ስለነበር የተሰጠውን ተስፋ በማሰብ ሱባዔውን እየቆጠረ የተናገረውን የማያስቀር የማያደርገውን የማይናገር ጌታየ «እነሆ አድንኀለሁ» ብሎ የገባልኝ ዘመን ተፈጸመ፤ ሰዓቱ አሁን ነው፤ እያለ ሲያወጣ ሲያወርድ ቸር አምላክ ሰው ኾኖ ሥጋ ለብሶ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ፡- «ተንሥኡ ለጸሎት ለጸሎት ተነሡ፤ ሰላም ለኩልክሙ፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን» በማለት አዳምን ከነልጅ ልጆቹ ነጻ አውጥቶታል፡፡ አዳምን በመከተል ልጆቹም አበው ቅዱሳን ነቢያት ሱባዔ በመግባት የተስፋን ዘመን በመቁጠር በመልካም ግብር ተከትለውታል፡፡ በዚህም መሠረት በርካታ ነቢያት በተለያየ ስልት ሱባዔ ቆጥረዋል፤ እኛም ሱባዔ ከቆጠሩ ነቢያት የተወሰኑትን በዚህ ጽሑፍ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡

#ሱባዔ ሔኖክ

ጻድቁ ሔኖክ፣ የያሬድ ልጅ ሲሆን፣ በትውልድ ከአዳም ሰባተኛ ነው፡፡ እርሱም በሕይወቱ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ቤት ንብረቱን በመተው በሱባዔና በትሕርምት እግዚአብሔርን አገልግሏል፡፡ ፍጹም አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ ሰው በመሆኑ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን መልካም ግብር ተመስክ ሮለታል፡፡ «ሔኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ፡፡» ዘፍ.5.22፡፡ ይህም በመሆኑ እግዚአብሔር የሱባዔውን ዋጋ ቅዱስ መንፈሱን በረድኤት ስለ አሳደረበት ትንቢት ተናግሯል፤ ሱባዔ ቆጥሯል፡፡ በሰማይ ተሰውሮ ሳለ ስለ ቅዱሳን መላእክት፣ ስለ መሲሕ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ስለ ፀሐይና ጨረቃ አመላለስ /ዑደት/ የሚተርክ በስሙ የተሰየመውን መጽሐፍ ጽፏል፡፡ ዘፍ.5 21-24፡፡ ይሁዳ ቁ.14፡፡ ሔኖክ 1.9፡፡
ሱባዔ ሔኖክ የሚባለው ነቢዩ ሔኖክ በመስፈርት የቆጠረው ሱባዔ ነው፡፡ መስፈርቱ /ማባዣ ቁጥር/ 35 ሲሆን 35'19 ሲበዛ በውጤቱ 685 ዓመት ይሆናል፡፡ 685'12 ስናባዛው 7980 ይሆናል፡፡ ይኸውም ሐሳብ የሚያስረዳው ስለክርስቶስ ምጽአት ነው፡፡
ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አሁን የደረስንበት ዘመን 7497 ይሆናል፡፡ ይህን ለማረጋገጥ በ5500 ዓመት ላይ 1997 ዓመትን መደመር ነው፡፡ በዚህን ጊዜ ከላይ ያስቀመጥነውን 7497 ዓመት ይሰጠናል፡፡ በነቢዩ ሔኖክ አቆጣጠር መሠረት ምጽአተ ክርስቶስ በ7980 ይሆናል፡፡ ከላይ ሔኖክ የቀመረውን ቁጥር ይዘን ከ7980 ዓመት ላይ አሁን ያለንበትን ዘመን /1997/ ስንቀንስ 483 ዓመት እናገኛለን፡፡ ስለዚህ በሔኖክ ሱባዔ መሠረት ምጽአተ ክርስቶስ ሊሆን 483 ዓመት ይቀራል፡፡

#ሱባዔ ዳዊት

ነቢዩ ዳዊት ከእስራኤል ነገሥታት ሁሉ ታላቅና ተወዳጅ ንጉሥ ነበር፡፡ ዘመነ መንግሥቱ 1011-971 ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደ ነበር ይታመናል፡፡ ነቢዩ ዳዊት ልበ አምላክ እንደ መሆኑ ትንቢት ተናግሯል፡፡ ሱባዔ ቆጥሯል፡፡ ይኽውም ቀመረ ዳዊት በመባል ይታወቃል፡፡ «እስመ ዐሠርቱ ምእት ዓመት በቅድሜከ፤ ከመ ዕለት እንተ ትማልም ኃለፈት፤ ሺ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትላንት ቀን»፡፡ /መዝ.89.4/ የሚለውን መምህራን ሲቆጥሩት 1140 ዓመት ይሆናል፡፡ ይኸውም በጌታ ዘንድ 1140 ዓመት እንደ አንድ ቀን እንደሆነ ነቢዩ ዳዊት ተናግሯል፡፡ ይህም ለዳዊት ሱባዔ መቁጠሪያ /መሥፈሪያ/ ሆኖ አገልግሏል፤ 1140’7= 7980 ዓመት ይሆናል፡፡ ይህም ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በ7980 ዓመት ክርስቶስ ዳግም እንደ ሚመጣ የሚያመለክት ነው፡፡

#ሱባዔ ዳንኤል

ነቢዩ ዳንኤል ምድቡ ከዐበይት ነቢያት ነው፡፡ እስራኤል ወደ ባቢሎን ሲማረኩ ተማርኮ ወደ ባቢሎን ወርዷል፡፡ እርሱም ስለ ክርስቶስ መምጣት ትንቢት ተናግሯል፤ ሱባዔም ቆጥሯል፡፡ «ሰብአ ሰንበታተ አድሞሙ ለሕዝብከ፤ ሰባ ሰንበት ወገኖችህን ቅጠራቸው፡፡» ይኸውም ክርስቶስ ከ490 ዓመት በኋላ ሰው መሆኑን የሚያመለክት ትንቢት ነው፡፡ እንዲሁም «እስከ ክርስቶስ ንጉሥ ትትሐነፅ መቅደስ ወእምዝ ትትመዘበር፤ እስከ ንጉሥ ክርስቶስ ድረስ መቅደስ ትታነፃለች በኋላም ትፈርሳለች» ሲል ተናግሯል፡፡
የአቆጣጠር ስልቱም በዓመት ሲሆን ይኸውም ሰባቱን ዓመት አንድ እያሉ መቁጠር ነው፡፡ ይኽውም ሱባዔ ሰንበት ይባላል፡፡ ዳንኤል ሱባዔ ከቆጠረበትና ትንቢት ከተናገረበት ጀምሮ ክርስቶስ እስከ ሚወለድ 490 ይሆናል፡፡ መስፈርቱ /ማባዣው/ ሰባት ስለሆነ 7’70 ስናባዛው 490 እናገኛለን፡፡ ይኸውም ነቢዩ ሱባዔ ከቆጠረና ትንቢት ከተናገረ ከ490 ዓመት በኋላ የክርስቶስን መወለድ ያመለክታል፡፡
በአጠቃላይ ከላይ የተመለከትናቸው ቅዱሳን ነቢያት አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር በማድረግ ሱባዔ ገብተው በትሕርምት በመኖራቸው ድንቅ የሆነውን የክርስቶስን ልደትና ዳግም ምጽአት ለመተንበይ ችለዋል፡፡ ሱባዔ መግባት የራቀን ለማቅረብ የረቀቀን ለማጉላት ብቃትን ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስገኝ መንፈሳዊ ጥበብ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

**** ይቀጥላል*****
#የሱባዔ ዓይነቶች

#የግል ሱባዔ/ዝግ ሱባዔ/

የግል ሱባዔ አንድ ሰው ብቻውን ሆኖ በቤትና በአመቺ ቦታ የሚይዘው ማንም ሰው ሳያየው በግሉ የጸሎት በኣቱን ዘግቶ በሰቂለ ኅሊና ሆኖ ፈጣሪው ብቻ እንዲያየው እንዲሰማው በኅቡዕ የሚፈጽመው ሱባዔ ነው፡፡ ማቴ.6፡5-13፡፡ በዚህ ዓይነት መልክ አንድ ሰው ሱባዔ ሲገባ ዘጋ ይባላል፡፡ ዝግ ሱባዔ የያዘ ሰው የሚያስፈልገውን ነገር ይዞ ወደ በኣቱ ከተከተተ በኋላ ሱባዔው እስኪፈጸም ድረስ ከሰው አይገናኝም፡፡ መዝ. 101-6-7፡፡

#የማኅበር ሱባዔ
የማኅበር ሱባዔ የሚባለው ካህናት፣ ምእመናን ወንዶችና ሴቶች፣ ሽማግሌዎችና ወጣቶች በአንድ ሆነው በቤተ ክርስቲያንና አመቺ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ ተሰብስበው የሚገቡት ሱባዔ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበሩ ምእመናን ወደ እግዚአብሔር በመሄድ ይጸልዩ ነበር፡፡ 1ኛ ሳሙ.1፡9፤ መዝ.121፡1፤ ሉቃ.18፡10-14፡፡
በሐዲስ ኪዳንም የሐዋርያት ተከታዮች የኾኑ መነኮሳት፣ ካህናትና ምእመናን በገዳማት፣ በአድባራት፣ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች፣ የጽዋ ማኅበርተኞች ስለ ማኅበራቸው ጥንካሬና ከማኅበርተኞቹ መካከል አንዱ ችግር ሲገጥመው የማኅበር ሱባኤ ይያዛል፡፡.

#የዐዋጅ ሱባዔ

የዐዋጅ ሱባዔ በአገር ላይ ድንገተኛ አደጋ፣ አባር ቸነፈርና ጦርነት ሲነደ እንዲሁም ለማኅበረ ምእመናን አስጊ የሆነ መቅሰፍት ሲከሰት፣ እግዚአብሔር መሽቱን በምሕረት ቁጣውን በትዕግሥት እንዲመልስ የሚያዝ የሱባዔ ዓይነት ነው፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ሱባዔ የነነዌ ሰዎችና በፋርስ በስደት ይኖር የነበረ እስራኤላውያን ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የነነዌ ሰዎች የዮናስን ስብከት ሰምተው ከሊቅ እስከ ደቂቅ ለሦስት ቀን ከመብል ከመጠጥ ተከልክለው በመጾም በመጸለይ እግዚአብሔር መዓቱን በምሕረት ቁጣውን በትዕግሥት እንዲመልስ አድርገዋል፡፡ ሌላው በፋርስ በስደት ይኖር የነበረ አይሁድ በአስቴር ትእዛዝ የያዙት ሱባዔ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚያን ዘመን አርጤክስስ አይሁድ በያሉበት እንዲገደሉ በማዘዙ ከዚህ የጅምላ ጭፍጨፋ ለመዳን አይሁድ በዐዋጅ ሱባዔ ገብተዋል፡፡ አስቴር ገብታ ንጉሡን ስታናግረው ሌላው ሕዝብ በውጭ ዐዋጅ ዐውጀው ሱባዔ ገብተው ፈጣሪያቸውን ተማፅነዋል፡፡ አስቴር 4፡16 - 28፡፡
በአገራችንም ይህን የመሰለ የዐዋጅ ሱባዔ በዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ተደርጓል፡፡ ፋሽስት ጣልያን አገራችንን በመውረር ኢትዮጵያን ቅኝ ተገዥ ለማድረግ ድንበሯን አልፎ በመጣበት ወቅት ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ፡- «ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ጉልበት የሌለህ በጸሎትህ ርዳኝ» በማለት የዐዋጅ ሱባዔ መያዛቸው ይነገራል፡፡ በዚህም መሠረት በየገዳማቱ ምሕላ ተይዟል፤ ንጉሡም ታቦተ ጊዮርጊስን ይዘው ዓለምን እጅግ ያስደነቀ ጥቁሮችን ለነጻነታቸው እንዲነሣሱ የሚያስችል ፋና ወጊ የሆነ ድል አግኝተው አገራችንን ለቅኝ ግዛት ያሰበውን ፋሽስት ጣልያንን ማሸነፋቸው በከፍተኛ ስሜት የምናስታውሰው ነው፡፡

#ቅድመ ሱባዔ(ከሱባዔ በፊት) ዝግጅት

ሱባዔ መግባት የሚፈልግ ምእመን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ያለምንም ዝግጅት ሱባዔ መግባት ለፈተና ያጋልጣል፡፡ ስለዚህ ቅድመ ሱባዔ /ሱባዔ ከመግባት አስቀድሞ/፣ ጊዜ ሱባዔ/ በሱባዔ ጊዜና ድኅረ ሱባዔ /ከሱባዔ በኋላ/ ዝግጅት አስፈላጊ ነው፡፡
ቅድመ ሱባዔ /ሱባዔ ከመግባት አስቀድሞ/በመጀመሪያ ሱባዔ የምንገባበትን ምክንያት ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሰው ሱባዔ የሚገባበትን ዓላማ ለይቶ ካስቀመጠ ከሱባዔ በኋላ የሚጠበቀውን ነገር ማግኘት አለማግኘቱን ይረዳል፡፡ ይህ ሳይሆን ሱባኤ ቢገባ ከሱባኤው በኋላ የጠየቀው ነገር ስለሌለ ትርጉም ያጣል፡፡ ስለዚህ ሱባዔ ከመግባታችን በፊት ለምን ሱባኤ ለመግባት እንዳሰብን ለይተን ማወቅ ይኖርብናል፡፡
ሱባዔ ለመግባት የወሰንበትን ምክንያት ከለየን በኋላ ምክንያታችንን ይዘን የንስሐ አባታችንን ማማከር ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም በምክረ ካህን መጓዝ መጀመር ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በአባትነታቸውና በሕይወት ልምዳቸው ምን ማድረግ እንደሚገባን ምክር ለማግኘት እገዛ ያደርግልናል፡፡ ቅድመ ሱባኤ ከንስሐ አባት ጋር መመካከር ተገቢ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው በሱባዔ ወቅት የተለያዩ ፈተናዎች ቢያጋጥሙት የተሰጠውን ምክር በመጠቀም ፈተናውን ለመቋቋም ይችላል፡፡ እንዲሁም የንስሐ አባቱ በሱባዔ ወቅት በጸሎት እንዲያስቡት መማከር የራሱ የሆነ ድርሻ አለው፡፡
ሱባዔ ለመግባት ስናስብ ለምን ያህል ቀናት መቆየት እንዳለብን መወሰን ያስፈልጋል፡፡ ሱባዔ ከዚህ እስከዚህ እቆያለሁ ብለን ዕቅድ የምንይዝበት ነው፡፡ እንደ አቅማችንና እንደ ችሎታችን ከዚህ ቀን እስከዚህ ብለን በመወሰን ሱባዔ መግባት ተገቢ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ፡- ምንም ዓይነት ልምድ ሳይኖረው አንድ ሰው «በዋሻ እዘጋለሁ» ቢል ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል፡፡ ምክንያቱም በሱባዔ ወቅት ፈተና ስለሚበዛ የሚመጣበትን ፈተና መቋቋም ባለመቻል ሱባዔው ሊቋረጥ ይችላል፡፡ ስለዚህ ቅድመ ሱባዔ ዐቅምንና ችሎታን አገናዝቦ መወሰን ተገቢ ነው፡፡
ሌላው ቅድመ ሱባዔ ለሱባዔ ተስማሚ የሆነ ወቅትና ቦታ መምረጥ ተገቢ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን በአብዛኛው ሱባዔ የሚገባው አጽዋማትን ተከትሎ ነው፡፡ ስለዚህ ሱባዔ የምንገባበት ወቅት የጾም ወቅት መሆን አለመሆኑን መለየት ያስፈልጋል፡፡ በአጽዋማት ወቅት የሚያዝ ሱባዔ ለተሐራሚ ጠቀሜታው እጅግ የጐላ ነው፡፡ ምክንያቱም በአጽዋማት ወቅት ብዙ አባቶች ሱባዔ ስለሚይዙ ከአባቶች ጸሎት ጋር ልመናችንና ጸሎታችን ሊያርግ ይችላል፡፡ ስለዚህ ወቅትን ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
እዚህ ላይ «ከወርኃ አጽዋማት ውጭ ሱባዔ አይያዝም» የሚል አቋም ለመያዝ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ፈተና ከአጋጠመው በማንኛውም ጊዜ ሱባዔ ሊገባ እንደሚችል እዚህ ላይ ለመጠቆም እንወዳለን፡፡ ከዚህም ባሻገር ሱባዔ የምንይዝበትን ቦታ መምረጥ አለብን፡፡ ለሱባዔ የምንመርጣቸው ቦታዎች ለፈተና የሚያጋልጡ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ይኸውም ሱባዔ ከተገባ በኋላ ኅሊናችን እንዳይበተን እገዛ ያደርግ ልናል፡፡ ጫጫታና ግርግር የሚበዛበት ቦታ በሰቂለ ኅሊና ለመጸለይ አያመችም፡፡ ስለዚህ ሱባዔ የምንይዝባቸው ቦታዎች ከከተማ ራቅ ያሉ ገዳማትና አድባራት ተመራጭ ናቸው፡፡

#ጊዜ ሱባዔ /በሱባዔ ጊዜ/

በጸሎት ሰዓት ዓምድና ግድግዳ ሳይደገፉ መቋሚያ ሳይዙ በሁለት እግር ቀጥ ብሎ በመቆም መጸለይ ይኖርብናል፡፡ እንዲሁም ፊትን ወደ ምሥራቅ መልሶ መቆም ወዲያና ወዲህ ወደ ግራ ወደ ቀኝ አለመዟዟር በሰፊሐ እድ በሰቂለ ኅሊና ኾኖ መጸለይ ይገባል፡፡ መዝ.5፡3፤ መዝ.133፡2፤ ዮሐ.11፡41፡፡
በሱባዔ ወቅት በቅደም ተከተል መጸለይ አለብን፡፡ መጀመሪያ «በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አአትብ ገጽየ ወኩለንታየ በትእምርተ መስቀልኸ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አንዱ አምላክ መላ ሰውነቴን በትእምርተ መስቀል አማትባለሁ» እያለ ሰጊድን ከሚያነሣው ሲደርስ መስገድ መስቀልን ከሚያነሣ ላይ ስንደርስ ማማተብ ይገባል፡፡
በማስከተል አቡነ ዘበሰማያት፣ መዝሙረ ዳዊት፣ ውዳሴ ማርያምና ሌሎች በመዝገበ ጸሎት የተካተቱትን መጸለይ፤ ቀጥሎ አቡነ ዘበሰማያት፣ ጸሎተ እግዝእትነ ማርያምን፣ ጸሎተ ሃይማኖትን ከጸለይን በኋላ አቡነ ዘበሰማያት መድገም፤ ከዚያ 41 ጊዜ ኪርያላይሶን ይባላል፡፡ ሌላው በሱባዔ ጊዜ ከተሐራሚ የሚጠበቀው ነገር ኃጢአቱን እያሰበ ማዘን ማልቀስ ነው፡፡ ሲያለቅስም ለእያንዳንዱ በደል እንባ ማፍሰስ ያስፈልጋል፡፡
በመጨረሻም ሱባዔ የገባ ሰው ሱባዔውን ሳይጨርስ ወይም ሱባዔውን አቋርጦ ከማ
ንም ሰው ጋር ፈጽሞ መገናኘት የለበትም፡፡

#ድኅረ ሱባዔ /ከሱባዔ በኋላ/

ለቀረበ ተማኅፅኖ እግዚአብሔር የሚያደርግልንን ነገር መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ እግዚአብሔር ላቀረብንለት ምልጃና ጸሎት እንደ ልባችን መሻት እንደ እርሱ ቸርነት እርሱ በወደደ ጊዜ ያደርግልናል፡፡ ሱባዔ የገባ ሰው ሁሉ ራእይ ላያይ ይችላል፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር መልስ አሰጣጥ ለማንም ግልጽ አይደለም፡፡ ከሱባዔ በኋላ መጀመሪያ የምናገኘው የኅሊና ሰላምን ነው፡፡ ይህ ትልቅ የአምላክ ስጦታ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ሱባዔ ገብተን ያሰብነውን ካላገኘን ዳግመኛ ተዘጋጅተን እስከ መጨረሻው ሰዓት መማፀን መጽናት ይኖርብናል፡፡
ምንጭ:-Info:- Mk website
#ዓውደ ምህረት የኛ
👇👇👇👇👇👇
@AwediMeherit
@AwediMeherit
#ድንግል ሆይ በምንና በማን እንመስልሻለን? #ምሳሌ የለሽም!
#አባ_ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
#ሀሳብ ይጹም !
_______________
| #ሸንኮራም ቢሆን ቅልጥምን እያሰብክ ከበላህው ጾም አለው!
ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ማኅሌታይ በጾመ ድጓው ዐይን ይጹም ፣ጀሮ ይጹም፣አፍ ይጹም ፣እጅ ይጹም እያለ ይመክራል ። እኔ ደግሞ ዛሬ ሀሳብ ይጹም እላለሁ ብዙዎች በጾም ወቅት ሥጋ ሲከለከሉ ከሥጋ ይርቁና ሥጋን ከሚመስሉ ነገሮች ጋር ቁርኝነት ለመፍጠር ሲጥሩ ይታያሉ ሥጋን በቴስቲ ሶያ ወተትን በሱፍ ውኃ እንቁላልን በአቮካዶ ለውጦ መመገብን ይመርጣል በእውነቱ ግን የጾም ዐላማ የምግቡን ኮንቴንት (ይዘት መለወጥ ሳይሆን የሀሳብንም ኮንቴንት መቀዬር ማስቻል ነው #ሸንኮራም ቢሆን ቅልጥምን እያሰብክ ከበላህው ጾም አለው።
[ደብረ ታቦር]
ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
❖ ይኽ በዓል ከጌታችን 9ኙ ዐበይት በዓላት አንደኛው ሲኾን በዓሉ በየዓመቱ ነሐሴ 13 ላይ በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡ ታሪኩ በ3ቱ ወንጌላት ላይ የተጻፈ ሲኾን ጌታችን አምላችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሌሎቹን ሐዋርያትን ከእግረ ደብር (ከተራራው ሥር) ትቶ የምስጢር ደቀ መዛሙርት የሚባሉት፣ በእምነት በተስፋ በፍቅር የሚመሰሉት ሦስቱን (ጴጥሮን፣ ያዕቆብን፣ ዮሐንስን) ይዟቸው ወደ ታቦር ተራራ ወጣ።

💥 የሞተውን ሙሴን ከ1644 ዓመታት በኋላ አምጥቶ፤ የተሰወረውን ኤልያስንም ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ የሕያዋን አምላክና የሙታን አሥነሺያቸው ርሱ መኾኑን የገለጸበት ታላቅ ምስጢር የተከናወነበት ነው፡፡ (ማቴ 17፡1-9)።

❖ ጌታ 8ቱን ሐዋርያት ይዟቸው ያልወጣበት በይሁዳ ምክንያት ነው ምክያቱም ከምስጢረ መንግሥቱ ቢለየኝ ከሞቱ ገባኹበት ባለ ነበርና ነው፤ ነገር ግን በተራራው ላይ ለ3ቱ የተገለጸው ምስጢር ከተራራው ሥር ላሉት ከይሁዳ በስተቀር ተገልጾላቸዋል፤ ለእኛም እንደ ሐዋርያት ምስጢሩን ጥበቡን ይግለጽልን፡፡

❖ ብዙ ተራሮች ሳሉ የታቦር ተራራን የመረጠበት
1)አስቀድሞ የጌትነት ክብሩ በዚያ ተራራ ላይ እንደሚገልጽ ነቢዩ ዳዊት በመዝ 88፡12 ላይ፦ “ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚኣከ ይትፌሥሑ” (ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ይደሰታሉ) በማለት ጌታ በዚያ ተራራ ላይ ብርሃኑን ሲገልጽ የብርሃኑ ነጸብራቅ እስከ አርሞንኤም ተራራ ድረስ እንደሚታይ የተናገረውን ትንቢት ለመፈጸም ነው፡፡

❖ ሌላው ታቦር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ 12 ጊዜያት ሲጠቀስ በተለይ በመሳ 4 እና 5 ላይ እንደተጻፈው አስቀድሞ በብሉይ ኪዳን የእስራኤል ጠላት የነበረው ሲሳራን መስፍኑ ባርቅ በተራራው ላይ ድል ነሥቶበት ነቢይቱ ዲቦራም በተራራው ላይ በደስታ አመስግናበታለች ዘምራበታለች። በተመሳሳይ መልኩ የእስራኤል ዘነፍስ የክርስቲያኖችን ጠላት የኾነውን ዲያብሎስን የኹላችን ፈጣሪ ንጉሠ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ላይ አምላክነቱን ገልጦ ድል ስለነሣው ነቢያት ሐዋርያት ምእመናን የሚያመሰግኑት ስለኾነ ለምሳሌነቱ ተስማሚነት ያለውን የታቦርን ተራራን መርጦታል፡፡

❖ ለምን ሙሴንና ኤልያስን ከነቢያት መኻከል መረጠ? ቢሉ፦
ሀ) በማቴ 16፡13 ላይ ሐዋርያትን ስለማንነቱ እንደጠያቃቸው እንደመለሱለት ኹሉ በእውነት ጌታችን የሙሴና የኤልያስ በአጠቃላይ የነቢያት ፈጣሪ የእግዚአብሔር ልጅ መኾኑን ሲገልጽላቸው ነው።

ለ) በዘፀ 33፡17-23 ላይ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ካለው ጥልቅ ግንኙነት የተነሣ “እባክኽ ክብርኽን አሳየኝ” ብሎ ልመናን አቀረበ፤ እግዚአብሔርም "ወአነብረከ ውስተ ስቊረተ ኰኲሕ ወእከድን እዴየ በላዕሌከ እስከ አኃልፍ" (በሰንጣቃው ዐለት አኖርሃለኍ፤ እስካልፍ ድረስ እጄን በላይኽ እጋርዳለኍ፤ ካለፍኍ በኋላ እጄን አንሥቼልኽ ጀርባዬን ታያለኽ፤ ፊቴ ግን አይታይም) ብሎታል (ዘፀ ፴፫፥፲፯-፳፫)፡፡

❖ ይኸውም ጀርባ በስተኋላ እንደሚገኝ ኹሉ በኋላ ዘመን አካላዊ ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በታቦር ተራራ ላይ እንደሚገለጽለት ሲያመለክተው ነው።

❖ ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብም ስለ ታቦር በሚተነትነው መጽሐፉ ሙሴ በቃዴስ ባለው በመሪባ ውሃ ከእስራኤል ጋር በበደለው በደል ምክንያት ምድረ ርስት ኢየሩሳሌም እንዳይገባ አይቷት ብቻ በናባው ተራራ ላይ እንዲያርፍ ኾኗል (ዘፀ ፴፪፥፶፪፤ ዘፀ ፴፬፥፩-፰)፡፡

❖ ይኽ ለሙሴ አሳዛኝ ቢኾንም በኋላ ዘመን አካላዊ ቃል ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ሙሴ በፊት በሩቁ ያያት ግን ያልገባባት በምድረ ርስት በኢየሩሳሌም ያለች ታቦር ተራራ ላይ አምጥቶት በዘመነ ብሉይ በአካለ ሥጋ ያልገባባትን ርስት እንዲገባባት አድርጎታል፤ ይኸውም አዳምና ልጆቹ በአካለ ሥጋ ያጡትን ርስታቸው ገነትን በአካለ ነፍሳቸው ዳግመኛ ሊያገባቸው እንደመጣ የሚያመለክት መኾኑን በስፋት አስተምሯል፡፡

❖ ጌታችን በብሉይ ኪዳን ከነበሩት ከነቢያት ሙሴንና ኤልያስን በሐዲስ ኪዳን ከነበሩት ከሐዋርያት ሦስቱን በታቦር ተራራ ላይ ማውጣቱ፦

1) የታቦር ተራራ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ በመኾኗ ሲኾን በቤተ ክርስቲያናችን ብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳን እንደሚነገሩ ለማመልከት

2) በተራራ በተመሰለች በጉባኤ ቤት ብሉይና ሐዲስ እንደሚነገሩ ለመግለጽ፡፡

3) ሌላው የታቦር ተራራ የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ስትኾን ይኸውም ጌታ ነቢያትንና ሐዋርያትን በተራራዋ ላይ መሰብሰቡ መንግሥተ ሰማያትን ነቢያትም ሐዋርያትም እንደሚወርሷን ለማመልከት

4) ሙሴ ያገባ ሲኾን ኤልያስ ድንግል ነውና መንግሥተ ሰማያትን ደናግልም ያገቡም እንደሚወርሷት ለማጠየቅ ነው፡፡

5) እንደ ያዕቆብ ዘሥሩግ ትርጓሜ ሙሴ ኦሪት ዘፍጥረትን ሲጽፍ፦ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” (ዘፍ 1፡1) እንዳለ፤ ዮሐንስም “በመጀመሪያ ቃል ነበር” (ዮሐ 1፡1) ብሎ እንደ ሙሴ አምላክነቱን የሚመሰክር ነውና ሙሴ አስቀድሞ የጻፈልኝ፤ አኹንም ዮሐንስ አምላክነቴን የሚጽፍልኝ እኔ ነኝ ሲል ነው፡፡

6) ሙሴና ኤልያስ ይመሳሰላሉ፤ ይኸውም በሲና ተራራ 40 ቀንና ሌሊት እንደጾመ ኤልያስም በደብረ ኮሬብ 40 ቀንና ሌሊት የጾመ ነውና፨

7) ሙሴ ንጉሡ ፈርዖንን የገሠፀ እንደነበር ኤልያስም ንጉሡ አክዐብን የገሠፀ ነውና፨

8) ሙሴ ከንጉሡ ፈርዖን ፊት ሸሽቶ እንደሄደ ኤልያስም ከንግሥቲቱ ኤልዛቤል ፊት ሸሽቶ ሄዶ ነበር።

9) ዳግመኛም ሰማይኑን ዝናብ እንዳያዘንም በተሰጠው ሥልጣን ባሰረውና ከ3 ዓመት ከ6ወር ቆይታ በኋላ እንዲዘንብ በፈታው ኤልያስን እንዳመጣ ኹሉ የማሰር የመፍታት ሥልጣን ሥልጣነ ተሰጥቶት “እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል” (ማቴ 16፡18-19) ላለው ለጴጥሮስን ታላቅ ሰማያዊ ሥልጣን መስጠቱን ለማመልከት አምጥቷቸዋል፡፡

❖ በቤተ ክርስቲያንና በሀገራችን ያለው መንፈሳዊ አከባበር ደማቅ ነው፤ ይኽ በዓል በቤተ ክርስቲያን በማሕሌት በቅዳሴ በትምህርት የሚከበር በዓል ሲኾን በሀገርኛ የቡሄ በዓል ይባላል፤ ቡሔ ማለት ሊቁ ደስታ ተክለ ወልድ በመዝገበ ቃላት ላይ ሲገልጹት ቧ ብሎ በደብረ ታቦር የተገለጠው የጌታችንን የፊቱን ብርሃን ጸዳል የልብሱን እንደ በረዶ ነጭ መኾን ያስረዳል ስለዚኽ የብርሃን፣ ብርሃናዊ ማለት ነው፡፡

❖ በዚህ በዓል በታቦር የታየው የብርሃኑ ምሳሌ የሚሆን ችቦ ይበራል፤ ሌላው በዚኽ በዓል ሰሞን በገጠር ከተራራ ላይ እረኞች ሕጻናት ዥራፍ እየገመዱ ማስጮኻቸው ጌታ በተራራ ላይ ብርሃኑን በገለጸ ጊዜ አብ በደመና ኾኖ “እርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” ባለ ጊዜ ሐዋርያት በድምፁ ደንግጸው መውደቃቸውን ለማመለክት ነው፡፡

💥 ጌታችን ጌትነቱን ገልጦበታል። የአብ ድምፅ ተሰምቶበታልና ታቦር ተራራ ቅዱስ ነው። ቅዱስ ጴጥሮስም በመልእክቱ "ከገናናው ክብር፦ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና፤ ¹⁸ እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን።" በማለት ገልጦታል (2ኛ ጴጥ 1:17-18)
❖ ሌላው ሙሉሙሉ ዳቦ መጋገሩ በትውፊት እንደምንረዳው ጌታ ብርሃኑን ሲገልጽ ብርሃኑ እስከ አርሞንኤም ተራራ ድረስ ያበራ ስለነበር እረኞች ሌሊቱ ኹሉ ቀን መስሏቸው እዛው ስለዋሉ ቤተሰቦቻቸው “ኅብስት” ይዘውላቸው ሄደዋልና የዚያ ምሳሌ እንደኾነ ይነገራል፡፡

💥[በደብረ ታቦር ላይ ብርሃኑን የገለጠው አምላካችን ክርስቶስ ምስጋና ይግባው]፡፡
[መልካም በዓል]
መጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
አርጋለች #ማርያም ተነስታለች!
በእርግጥ ኃይለ ቃሉ ለልጇ ለወዳጅዋ ለጌታችን ለመድኃኔታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የተነገረ ነው።

#ሆኖም ግን ለእርሷም ይሆናል ። የልጅ ሁሉ ነገር ለእናትም ጭምር ነውና።በቤተልሔም በከብቶች ግርግም በወለደችሁ ጊዜ ሰባ ሰገል እጅ መንሻ ስጦታን ወርቅ፣ዕጣን እና ከርቤን አምጥተውለት ነበር። ወርቅ ጽሩይ (የጠራ ፣የነጻ፣ ንጹሕ) እንደሆነ አንተም ጽሩይ ባሕሪ ነህ ሲሉ። ዕጣንም አመጡለት ሊቀ ካህናት ይባላልና፤ ከርቤንም አመጡ ከርቤ መራራ ነው መራራ ሙትን ትሞታለህ ሲሉ።

ሆኖም ይህ ስጦታ እናቱን አይመለከታትም ማለት አይደለም ልደቱን የሚያከብር አንድ ልጅ ምንም እንኳን ልደቱ የእርሱ ቢሆንም ስጦታው ግን እናቲቱንም ይመለከታል። ልጁማ የስጡታውን መንነትና ትርጉም ላይረዳ ይችላል። እናት ግን ጠንቅቃ ታውቀዋለች። " #ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ እያሰበች በልቧ ትጠብቀው ነበር " #ሉቃ 2÷19

#ስለዚህ የሰባ ሰገል ስጦታ እንኳን ወርቅ ዕጣን ከርቤ ልጇን ብቻ ሳይሆን እናቲቱ ድንግል ማርያምንም ይመለከታል። ወርቅ ንጽሑ የጠራ ነው። ንጽሐ ጠባይ አላደፈብሽም ሲሉ ወርቅ አመጡላት አንድም ወርቅ ከጭቃ ይገኛል ግን ጭቃ አይደለም እመቤታችን የኃጢያት ጭቃ ካቆሸሻቸው ከሰዎች ወገን ተገኝታለች ግን ጭቃ አይደለችም ። ዕጣንም አመጡ ዕጣን ምሁዝ (መልካም መሐዛ ያለሁ) ነው። እመቤታችንም ምሁዚት ማሕዛዋ ያማረ መልካም ዕጣን ነች ክርስቶስ ክርስቶስን ትሸታለችና። #ዕጣን_ይእቲ_ማርያም እንዲላት ሊቁ ።

ከርቤም አመጡላት ከርቤ የተለያዮትን አንድ አድርጎ ያጣብቃል ስለዚህ የፍቅር ምሳሌ ነው። ከርቤ እንዲያጣብቅ ፍቅር የሆነች ድንግል ማርያምም ወልድ ክርስቶስን ንጽሐ ሥጋዋን፣ ንጽሐ ነፍሷን ፣ ንጽሐ ልቡናዋን በማጽናት ወልድ ክርስቶስን ከመንበሩ ሥባ ሰው አምላክ፣ አምላክ ሰው ሆኖ ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባሕሪ አንድ ባሕሪ ከሁለት ፈቃድ አንድ ፍቃድ እንዲሆን ያደረገች የፍቅር ሰንሰለት የተዋሕዶ መዲና ናትና ከርቤ አመጡላት ። ንጉሥ ውበትሽን ወድዶአልና፥ እርሱ ጌታሽ ነውና። የጢሮስ ሴቶች ልጆች እጅ መንሻን ይዘው ይሰግዱለታል። የምድር ባለጠጎች አሕዛብ በፊትህ ይማለላሉ ። #መዝ 45÷11-12
#አንድም ከርቤ መራራ ነው። በልጅሽ ምክንያት መራራ ሐዘን ያገኝሻል ሲሉ መራራውን ከርቤን አመጡ። ይህ ብቻ አይደለም ተንበርክከውም ለልጇ የባሕር ለእርሷ ደግሞ የጸጋ ስግደትን አቅርበዋል። ስለዚህ ለልጅ የተደረገ ሁሉ ለእናት ደግሞ ተደረገ።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፤” ብሎ ክርስቲያኖች ኑሯቸውና ሞታቸው ክርስቶስ የመሰለ ክርስቶስን የተባበረ ከሆነ ትንሣኤያቸውም የክርስቶስን የመሰለ ወይም የተባበረ ትንሳኤ እንደሚኖራቸው ጽፏል ። #ሮሜ 6፥5

#ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ እርሷን የመሰላት የክርስቶስ እናቱ የድንግል ትንሣኤማ እንዴት አብልጦ ከልጇ ትንሳኤ ጋር የተባበረ የተመሳሰለ መሆኑን መገመት ቀላል ነው ። ስለዚህ ሕያዊትን ከሙታን መካከል ስለምን ትፈልጓታላችሁ ተነስታለች እንጂ በዚህ የለችም ብንል ትክክል ነን። ሞቷ እንደልጇ ሞት ትንሳኤዋም እንደልጇ ያለ ትንሣኤ ነውና።
ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሴን ላኖራትም ላነሳትም ሥልጣን አለኝ እንዳለና አባት ሆይ ነፍሴን በእጄ አደራ እሰጣለሁ ብሎ በፍቃዱ ነፍሱን እንደሰጠ እርሷም ከዚህ ዓለም ድካም ስታርፍ ፍቃዷን ተጠይቃለች እንጂ የሞት እንግድነት እርሷን አላስደነገጣትም ። #ዮሐ 10፥17 # ሉቃ 23፥46
#ሞት ማንንም አያስፈቅድም እርሷን ግን በእኔ ሞት ነፍሳት ከሲዖል የምታወጣልኝ ከሆነማ አንድ ጊዜ አይደለም ሰባት ጊዜ ልሙት እስክትል ድረስ ፍቃዷን ቆሞ ጠበቋል። የልጇ ሞት ነፍሳትን ከሲዖል ወደ ገነት ያጋዘ ነፃ ያወጣ እንደሆነ የእርሷም ሞት ነፍሳትን ወደ ገነት መልሷል፤ ልጇ በከርሰ መቃብር ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት ቆየቶ በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ እንደተነሳ እርሷም ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት በምድር ልብ ውስጥ ቆይ እንደልጇ ባለ ትንሣኤ በክብር በይባቤ በመላእክት ምስጋና ተነስታለች ።
#ልጇ ወደ አባቱ እንዳረገ እርሷም ወደ ልጇ ዐርጋለች።ልጇ በአባቱ ቀኝ በሥልጣን እንደተቀመጠ እርሷም በልጇ ቀኝ በክብር በሥልጣት ማር ይቅር በል እያለች በአማላጅነት ንግሥቱቱ ቆማለች።“የንጉሦች ሴት ልጆች ለክብርህ ናቸው፤ በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች ። ” #መዝ45፥9
ወዳጄ እመቤታችንን ትፈልጋታለህ ?ስለምን ታድያ ከሙታን መንደር ትፈልጋታለህ እንደተነገረላት ተነስታለች እንጂ በዚህ የለችም። “አቤቱ፥ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስህ ታቦት።” #መዝ132፥8


አ.አ ኢትዮጵያ
ተክለ ኤል ኃ/ማርያም
ነሐሴ ፲ ፮ / ፳ ፻ ፲ ፫ ዓ.ም
Audio