አትሮኖስ
286K subscribers
120 photos
3 videos
41 files
568 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#የታካሚው_ማስታወሻ(ህመም አልባው በሽታ)


#ክፍል_አንድ


#ድርሰት_በመለሰ_ታዬ(MD)

1.ቅድመ ታሪክ

ከአንድ ዓመት ስራ መፍታት በኋላ፣ እንደገና ስራ ልጀምር ነው። በማኔጅመንት ሁለተኛ ድግሪና ከአስር ዓመት በላይ የስራ ልምድ አለኝ። ያለ ስራ በቆየሁበት ግዜ፣ ያጠራቀምኩትን ገንዘብ ጨርሼ
ንብረቶቼን ሸጥኩ፡፡ አሁን መኪናዬን ለመሸጥ በማሰብ ላይ ሳለሁ ስራ
አገኘሁ፡፡ ከባድ ግዜ ነበር፡፡ ንብረት ከማጣት በተጨማሪ፣ የስነ ልቦና ጉዳቱ ይሄ ነው ሚባል አይደለም፡፡ በራሴ ያለኝ መተማመን በከፍተኛ ደረጃ አሽቆልቁሏል፡፡ ከዚህ በፊትም፣ በተመሳሳይ ስራ ለቅቄ እስክፀፀት
ተቸግሬ አውቃለሁ፡፡ ሁለተኛ ብዬ ለራሴ ቃል ገብቼ ነበር፡፡ ቃሌን መጠበቅ አቅቶኝ፣ ይኸው ለአመት ተንከራተትኩ፡፡

የመጨረሻው ድርጅቴ በጣም ጥሩ ክፍያን ይከፍለኝ ነበር፡፡በተጨማሪም፣ ለሙያዬ እድገት የሚረዱኝ የተለያዩ የስልጠና እድሎችን በሃገር ውስጥና በውጪ ሃገራት ያመቻችልኝ ነበር፡፡ በጣም ደስተኛ ሆኜ ነበር፡፡ ብዙ እንደምቆይበት ተሰምቶኝ ነበር፡፡ ከተወሰነ ግዜ በኋላ ግን፣ሰራተኛው የተከፋፈለና በየቀኑ የሚካሰስ እንደሆነ እየተሰማኝ መጣ፡፡እኔ ደግሞ እንደ አስተዳደር ስራዬ መዳኘት ነው፤ አንዱን በዳይ፣አንዱን ተበዳይ አድርጎ መፍረድ፡፡ እኔ ደግሞ፣ ከመፍረድና ከመቅጣት ይልቅ፣ ችግሩን በማስታረቅ መፍታት የተሻለ መስሎ ተሰማኝ፡፡ እንደዛ ሞከርኩ። አይሳካም፡፡ ጭራሽ ወደኋላ አምስት፣ አስር ዓመት
ተመልሰው፣ “እርሱ/እርሷ፣ ባለፈውም እንዲህ በድሎኝ/ላኝ፣” እያሉ ሌላ
የክስ ቱባ ይተረትራሉ።

ጓደኛ ሆኜ ቀርቤያቸው፣ መሰረታዊ የፀባቸውን መንስኤ ለማወቅ
ሞከርኩ፡፡ ከአሉባልታ የዘለለ፣ ይሄ ነው የሚባል የከፋ ነገር የላቸዉም፡፡ክሶቻቸው ከጥርጣሬና፣ ሳይቀድመኝ ልቅደመው ከማለት የሚመነጩ ናቸው። እኩል ቀርቤ፣ እንደ ድልድይ ላቀራርባቸው ሞከርኩ፡፡ የሚሆን አይደለም፡፡ ያለበቂ ምክንያት፣ ላይታረቁ ተጣልተዋል፡፡ ለተጣላ ሰው ደግሞ፣ መካሰሻ ምክንያት አሽዋ ነው፡፡ መዳኘት ስራዬ ቢሆንም፣
ሰለቸኝ፡፡ ሁሉም ተበደልኩ ባይ ነው፡፡ ቀስ በቀስ ደስታዬ ተነነ፣ ሳቄና ጨዋታዬም ጠፋ፡፡ ብስጩና ነጭናጫ ሆንኩ፡፡ ወደ ስራዬ መሄድ ይሰለቸኝና ይጨንቀኝ ጀመረ። ስራተኛውና ድርጅቱ አንገሸገሹኝ፡፡ ካሁን በኋላ ስራ በፍፁም አለቅም ብዬ የገባሁትን ቃል መጠበቅ አቃተኝ፡፡ ሌላ ስራ እንኳን ሳላገኝ እንደዘበት መልቀቂያ አስገብቼ ጠፋሁ፡፡ ለአመት ተንከራተትቼ አዲስ ስራ አገኘሁ፡፡ አሁንም፣ እንደገና አይለምደኝም ብዬ
ስራ ልጀምር ነው፡፡

#እንደገና
“..ቋ..ቋ...ቋ...” ከአለቃዬ ቢሮ እንደወጣሁ፣ ኮሪደሩ ላይ፣ የሂል
ጫማ ድምፅ ተቀበለኝ፡፡ ድምፁን ወደሰማሁበት ቀና ብዬ ተመለከትኩ።
ፈዘዝ ያለ ቢጫ ቦዲ፣ በጥቁር ጨርቅ ሱሪ፣ የሚያምር የሰውነት ቅርፅ፣በረጅም ሂል ጫማ የተጫማች ልጅ ወደኔ አቅጣጫ እየመጣች ነው።ከአለቃዬ ቢሮ፣ የኔ ቢሮ ሩቅ ሚባል አይደለም፡፡ የጎረምሳ ነገር ልጅቷን በቅርበት ሳላያት ወደቢሮዬ መግባት አልፈለኩም፡፡ እንድትደርስብኝ እንደ ኤሊ ተጎተትኩ፡፡ አልተሳካም! ቢሮዬ በር ደረስኩ፡፡ ይሄኔ የሚመጣው
ሰው ማልፈልገው ሆኖ እንዳላየ ለመግባት ብጣደፍኮ ኖሮ.....። መጠበቅ
አለብኝ፡፡ ከአለቃዬ የተቀበልኩትን ወረቀት፣ የቢሮዬ በር ላይ ቆሜ
ማንበብ ጀመርኩ፡፡
ሄይ! አዲሱ ስታፋችን?” እጇን ዘረጋችልኝ..

“አዎ! ያቤዝ እባላለሁ፡፡” እጇን ጨብጬ ከላይ እስከታች በዐይኔ እየዳበስኳት፡፡

“ማሂ ቆንጆ እባላለሁ፡፡”

“እመሰክራለሁ! በጣም ቆንጆ ነሽ!፡፡”

ኪ.ኪ...ኪ...፣ አመሰግናለሁ፡፡ እንኳን ደህና መጣህ፡፡
በስርዓት አቀባበል እናደርጋለን፡፡” ብላ፣ የቆምኩበት ትታኝ፣ ወደ አለቃዬ
ቢሮ መሄድ ጀመረች፡፡

“አመሰግናለሁ!” እያልኩ፣ የጀርባ ውበቷን ለማረጋገጥ ካንገቴ ዞሬ በዐይኔ ተከተልኳት፡፡ ትንሽ እንደተራመደች እያየኋት እንደሆነ ለማረጋገጥ ይመስል፣ ድንገት ዞር ስትል ዐይን ለዐይን ተጋጨን፡፡ ወደ ቢሮዬ ተስፈንጥሬ ገባሁ፡፡ ሃሳቤ ግን ተከትሏት ሄዷል፡፡ ውበቷ ሙጫ ነው፣ ተጣብቆ የሚቀር፡፡ ማራኪ ነች፡፡ በዛ ላይ በደንብ ተኳኩላለች።ቢሆንም፣ ሲፈጥራትም ልቅም ያለች ቆንጆ ነች፡፡ ሃም...፣ ጥሩ ጥቅማ ጥቅም ያለው አሪፍ መስሪያ ቤት ነው የገባሁት፡፡ ይሄንን ቢነግሩኝ ኖሮ፣መች ደሞዙን እንደዛ እጨቃጨቃቸው ነበር፡፡ ምን ክፍል ይሆን
ምትሰራው...?”

ቢሮዬን ዝም ብዬ ተመለከትኩት፡፡ የሰለቸው የወንደ ላጤ ቤት መስሎ ተዝረክርኳል፡፡ እዚህ ቢሮ ውስጥ በቀን ስምንት ሰዓት መቆየት በራሱ ያደክማል፡፡ የጠረጴዛና ወንበሮቹ አቀማመጥ በዘፈቀደ ነው።ማስተካከል ጀመርኩ፡፡ ለስራ በሚመቸኝና ቢሮው የተሻለ እይታ
እስኪኖረው መላልሼ አዟዟርኳቸው፡፡ ማልፈልጋቸውን ወረቀቶች አስወገድኩ፤ ያስፈልጋሉ ምላቸውን፣ በየዘርፍ በየዘርፍ አድርጌ ፋይል ውስጥ አስቀመጥኳቸው፡፡ ስሰራ ሃሳቤ እንዲሰረቅ አልፈልግም፡፡ ቢሮ ውስጥ ያሉ ኮተቶችና ምስቅልቅሎች ሃሳብን ያናጥባሉ። በነፃነትና በትኩረት ስራዬን ለመስራት፣ በምችለው መጠን ቢሮዬን ስርዓት ያለውና ነፃ አደረኩት፡፡ ይህ በቀደሙት መስሪያ ቤቶቼም የምከውነው የመጀመሪያ ቀን ተግባሬ ነው፡፡ ጎንበስ ቀና ያልኩበት፣ እቃዎቹን
የጎተትኩበት ድካም ተሰማኝ፡፡ እርጅና ሊመጣ ነው፡፡ ትንፋሽ ለመውሰድ
ወንበር ላይ አረፍ አልኩ፡፡ ሰዓቴን ስመለከት የሻይ ሰዓት ደርሷል።
ሻይ በኋላ የቀረውን አስተካክለዋለሁ ብዬ እያሰብኩ፤

“ጤና ይስጥልኝ!...” ብለው አለቃዬ ወደ ቢሮዬ ገቡ። እጄን ጨብጠው ሰላምታ ተለዋወጥን፡፡ አለቃዬ መልከ መልካም፣ እድሜያቸው ጎልማሳነትን የዘለለ ይመስላሉ፡፡

“እንኳን ደህና መጡ!”

“ደግሞ ከመቼው ቢሮውን እንዲህ አሳመርከው...?፣ ይሄ ቢሮ እንዲህ ያምር ነበር እንዴ...?” በፈገግታ ጥርሳቸውን ፈልቀቅ አድርገው፡፡

“እንዲመቸኝ ትንሽ ነው የነካካሁት፡፡”

“ሌላ ቢሮ አስመስለህ አሳምረከዋል እንጂ፡፡ አይ ወጣት! መቼም ውበት ትወዳላችሁ! በል ና አሁን ቡና ልጋብዝህ፤ በዛውም ስታፎቻችንን ላስተዋውቅህ፤” ብለውኝ ከቢሮዬ ወጡ፡፡

“እሺ!” ብዬ ቢሮዬን ቆልፌ ተከተላኳቸው፡፡

ካፍቴሪያ ስንደርስ፣ ክብ ሰርተው እየተንጫጩ ሻይ ቡና የሚጠጡ ሰዎች ጋር ወስደው ቀላቀሉኝ፡፡ እየጮሁ ያወራሉ፤ እየጮሁ ይሳሳቃሉ፡፡ ይህ የግቢው አውራ ቡድን እንደሆነ ሁኔታቸው ይናገራል፡፡እየተሸቀዳደሙ ያወራሉ፤ ከፍ አድርገው ይስቃሉ፤ ያሽካካሉ፤ ሌላ ሰው
ይሰማናል፣ እንረብሻለን፣ ምን ይሉናል ሚሉት ነገሮች ሚያሳስቧቸው አይመስሉም፡፡

“ጎበዝ አዲሱ አድሚናችንን ትተዋወቁት ዘንድ ይዤው መጥቻለሁ፡፡ ያቤዝ ይባላል፡፡ እናንተ ደግሞ እራሳችሁን አስተዋውቁት፧”ብለው ወንበር ስበው ተቀመጡ፡፡ ጫጫታቸውን አቁመው፣ ፀጥ ብለው ካዳመጡ በኋላ፣ በአንድ ላይ፣ “እንኳን ደህና መጣህ! ዌል ካም!›› ብለው አልጎመጎሙ:: አራት ሴትና ሶስት ወንድ ናቸው፡፡ ሴቶቹ ወጣትና ቆነጃጅት ሲሆኑ፣ ወንዶቹ በእድሜ ከፍ ከፍ ያሉና፣ ሙሉ ሰውነት ያልደረሱ ጎልማሶች ናቸው።

ይቀጥላል

ለአስተያየቶ @atronosebot ን ይጠቀሙ ለወዳጆ #Share እያደረጉ
👍3👏2