አትሮኖስ
282K subscribers
110 photos
3 videos
41 files
496 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#ትንግርት


#ክፍል_ሰላሳ_ሶስት


#በዘሪሁን_ገመቹ_ዋቤ

ሁሴን ኢትዬጵያን ለቆ ከሄደ ሁለት ወራት አለፈው፡፡ትንግርት ሙሉ ለሙሉ የስራ አስኪያጅነቱን ቦታ ለመለማመድ ደፋ ቀና እያለች ስለነበር ብቸኝነቱ ብዙም አልከበዳትም፡፡ በዛ ላይ እንደ ጓደኛም እንደ እህትም የምትንከባከባት ፎዚያ ከጎኗ አለችላት፡፡ስራውም ቢሆን አልከበዳትም..፡፡

ሁሴን ትንታግ የሆኑ ጋዜጠኞችን ነው አደራጅቶላት የሄደው ፡፡እነሱን መምራት፤መምራት እንኳን አይባልም ማስተባበር ብዙም አልከበዳትም፡፡

ትንግርት ዛሬ በጥዋት ተነስታ ወደ ቢሮዋ ገብታለች፡፡ የወጪ ሰነዶች፤የተገዙ ዕቃዎች ዝርዝሮች የመሳሰሉትን የቀረቡላትን ሪፖርቶች በጠቅላላ በዝርዝር አየችና የሚፈረመውን ፈርማ የሚሰረዘውን ሰርዛ ጨረሰችና.. በሚቀጥለው ቀን እሁድ ለሚታተመው ጋዜጣ የተዘጋጁ ፅሁፎችን በየደርዛቸው ማንበብ
ጀመረች፡፡ቅር ያለት ቦታ ቆም ትልና መልሳ ታነበዋለች፤ካልተዋጠላት በማስታወሻዋ አስፍራ ወደ ሚቀጥለው ትሸጋገራለች፤ እንዲህ እንዲህ እያለች ጨርሳ ቀና ስትል ሁሉም ሰራተኞች ገብተው የአለት ስራቸውን ተያይዘውት ነበር፤ዋና አዘጋጁን ኤልያስን ጠራችው፡፡ ወደእሷ ተጠጋና ከፊት ለፊቷ ተቀመጠ፡፡

‹‹ምነው ጥቁርቁር አልሽ ?ሁሴን ናፈቀሽ እንዴ?››

‹‹ገና ሶስት ወር ሳይሞላው እስክጠቁር ድረስ ሚናፍቀኝ ይመስልሀል?››

‹‹ለምን አይመስለኝም፤ የሚያፈቅሩት ሰው ለአንድ ቀንም ቢሆን ከፊት ዞር ሲል ማንገብገቡ የት ይቀራል?››

‹‹ባክህ እሱ ለእንደናንተ ዓይነቱ ነው፡፡ አሁን የሀዋሳውን ልጅ እንዴት እንደምናገኘው ነው ግራ የገባኝ?ባለፈው አይደል ላይ ልጆቹ ሲወዳደሩ ያየሁት እና ትናንትና ድጋሚ በደቡብ ቴሌቨዥን አየሁት ያልኩህን ፤ሁኔታው በጣም ነው ያስደመመኝ፡፡እንዲህም የሚያስብ ሰው አለ እንዴ.?ብዬ እራሴን ደጋግሜ እንድጠይቅ ነው ያደረገኝ፡፡ፈጽሞ ከአዕምሮዬ ላወጣው አልቻልኩም፡፡

‹‹እሱስ እኔም በጣም ነው ያስደመመኝ… የልጆቹ ብቃትማ አፍ ያስከፍታል፡፡››

‹‹አንድ ነገር አስቤያለሁ፡፡››

‹‹ምን አሰብሽ?››

‹‹ታሪኩን በጋዜጣችን መዘገብ፡፡››

‹‹ቴሌቭዥኑን እንደምንጭነት ተጠቅመን?››

‹‹አይደለም... ቦታው ላይ በመሄድ ልጁንም ከነልጆቹ በማግኘትና በጥልቀት በማጥናት፤ቃለ መጠየቅ በማድረግ ፤ዶክመንተሪ በመስራት፡፡››

‹‹እሱ ትክክል ነሽ.. ከፈለግሽ አድራሻውን ላገኝልሽ እችላለሁ፡፡››

‹‹በእውነት ..እንዴት?››

‹‹ኢንተርቪውን የሰራው ጋዜጠኛ የማውቀው ልጅ ነው፡፡ደውዬለት አድራሻውን እንዲሰጠኝ ቀጠሮም እንዲያሲዝልን ማድረግ እችላለሁ፡፡››

‹‹አይ ጭንቅላት ነበረ እኮ!!! ይህቺ ሀገር አልተጠቀመችብህም እንጂ፡፡››በማለት ከአንጀቷ አሞገሰችው፡፡

‹‹ያው ባልሽ እና አንቺ እየተፈራረቃችሁ ጥፍጥፍ አድርጋችሁ እየተጠቀማችሁብኝ አይደል..?››

‹‹በላ አሁንኑኑ ደውልለት፡፡››

<<አሁን??>>

<<አዎ አሁን>>

በገረሜታ ሞባይሉን ከኪሱ አወጣና ደወለለት፤ሁኔታውን በዝርዝር አስረዳው፤ከአደራ ጋር ውለታውን ጠየቀና በመሰናበት ስልኩን ዘጋ፡፡

‹‹ከተሳካ አሪፍ ምሳ ግብዣ አለህ›፡፡›አለችው፡፡

‹‹ለእኔ ሳይሆን ሀዋሳ ስትሄጂ ጓደኛዬን በመጋበዝ ለውለታው ታመሰግኚልኛለሽ፡፡››

‹‹ቃሌን ሰጥቼሀለሁ›› አለችው፡፡

ከሁለት ቀን በኃላ መልሱ መጣ‹‹ተሳክቷል››አላት ኤልያስ ተንደርድሮ ከውጭ ወደ ቢሮ እየገባ ነው የሚናገረው፡፡

‹‹አትለኝም..!!››በደስታ ከመቀመጫዋ ተነሳች፡፡

‹‹አዎ አልኩሽ ሁሉ ነገር ዝግጁ ሆኗል፡፡››

‹‹በጣም ደስ ብሎኛል፡፡››

‹‹እኔም..እና መቼ ልትሄጂ ነው?››

‹‹አይ አብረን ነው የምንሄደው፡፡አንተ ለጋዜጣው የሚሆን ዘገባ ትሰራለህ….እኔ ደግሞ ይሄንን ሰውዬ ገፀ ባህሪ አድርጌ አንድ ምርጥ መፅሀፍ መፃፍ እፈልጋለሁ፡፡ ተዘጋጅ ነገ በጥዋት እንሄዳለን፡፡››

<<ነገ ነገውኑ>>

‹‹አዎ... የሚሰራ ስራ እጅህ ላይ ካለ ለሌሎቹ አስተላልፍ..ለሶሰት ቀን ሀዋሳ ነን፡፡››

‹‹ተቀብያለሁ ኮማንደር ››አላት ቅፅበታዊ ውሳኔዋ አስገርሞት፡፡

በማግስቱ ትንግርት መኪናዋን እያሽከረከረች ከኤልያስ ጋር ከረፋዱ 5 ሰዓት አካባቢ ሀዋሳ ከተማ ደረሱ፤እንደደረሱ የኤልያስን ጓደኛ ጋዜጠኛውን አገኙት፡፡

‹‹እሺ ለመቼ ልቅጠርላችሁ?›› አላት ትንግርትን፡፡

‹‹ከተቻለ አሁኑኑ ባገኘው ደስ ይለኛል፡፡››

‹‹ከተመቸው ልደውልለት >>አለና ሞባይሉን አወጥቶ ታዲዬስ ጋር ደወለለት...

ስልኩ ሲደወል ታዲዬስ እና ዶ/ር ሶፊያ ሰሜን ሆቴል ምሳ እየበሉ ነበር..ዶ/ር ሀዋሳ ለስራ ከመጣች አንድ ሳምንት ያለፋት ቢሆናትም ታዲዬስና ልጆቹ ዙሪያ ስትሽከረከር በራሷ ፍቃድ እስከዛሬ ቆይታለች ..ዛሬ ግን የግድ መሄድ አለባት፡፡ታዲዬስን ለመጨረሻ ጊዜ ልትሰናበተው ነው በስንት ጭቅጭቅ ለዚህ የምሳ ግብዣ በማሳመን አሁን አብራው ያለችው፡፡

‹‹ማን ነው የደወለልህ?››

‹‹ከአዲስአበባ የመጡ እንግዶች ናቸው፤ቢቀላቀሉን ቅር አይልሽም ብዬ ነው እዚህ የቀጠርኳቸው› .አላት፡፡

<<ችግር የለውም..እነሱ እስኪመጡ ካወራን ይበቃናል፤ከዛ ወደማልቀርበት ሀገሬ ጉዞ እጀምራለሁ፡፡››

‹‹ጥሩ ዕቅድ ነው፡፡››አላት፡፡

‹‹በናትህ ግን፤ ቢያንስ በቀን አንዴ መደዋወል አለብን፡፡››

‹‹በቀን አንዴ!!!››

‹‹ምነው ችግር አለው?››

‹‹እንዴ በየቀኑ ተደዋውለን የምናወራው ርዕስ ከየት እናመጣለን?››

<< ደግሞ መደወል እንጂ የሚወራ ርዕስ ይጠፋል?››

‹‹አዎ..እኔ በየቀኑ እየደወልኩ ፍሬ ቢስና ተደጋጋሚ ሀሳብ እያላዘንኩ ያንቺንም የእኔንም ወርቅ ጊዜ አላባክንም..በዛ ላይ ስልኩም በሳንቲም ነው የሚሰራው፡፡››

‹‹እኔ እኮ ነኝ የምደውልልህ?››

‹‹አንቺ ደወልሽ እኔ ምን ለውጥ አለው? ለማንኛውም በሳምንት አንድ ቀን ከተደዋወልን
ወዳጅነታችንን ለማቆየት በቂ ይመሳለኛል፡፡››

‹‹እንዴ!!! በሳምንት አንድ ቀን... ጨካኝ ነህ፡፡››

‹‹ጭካኔን እዚህ ላይ ምን አመጣው?››

‹‹ትቀልዳለህ?ስሜት የለህም እንዴ? ናፍቆት የሚባል ነገር በልብህ አይበቅልም ማለት ነው?>>

‹‹ኧረ ንግግርሽን አጠጠርሽው፡፡እኔ ቀላል ነገር ነው የተናገርኩት፡፡ስልክን አግባብ ለሆነ ነገር በስርዓት መጠቀም አለብን ብዬ የማምን ሰው ነኝ፡፡ምክንያት እየፈጠርን በየሰከንዱ እዚህም እዛም እየደወልን ገንዘባችንንም ጊዜያችንንም ከማባከናችንም በላይ የምንደውልለትንም ሰውዬ ጊዜውን እናባክንበታለን፡፡ደግሞ ሰውዬው የማውራት ፍላጎት አለው ወይ?

ሚመች ቦታ ላይ ላይሆን ቢችልስ?ስራ ላይ ይሆን እንዴ?ትዝ አይለንም፡፡መጫኛ የሚያህል ውል የሌለው ፍሬከርስኪ ወሬያችንን እንተረትራለን..እንዲህ አይነት ነገር አይመቸኝም፡፡ለማንኛውም በሶስት ቀን አንዴ እንደዋወላለን፤ከዛ በላይ የተለየ ነገር ካለሽ በመልዕክት ልትልኪልኝ ትችያለሽ ..በቃ፡፡››

‹‹በየቀኑ ብደውልልህስ?››

‹‹አላነሳልሽም፡፡››

<<እንዴ.!!!>>

በዚህ ጊዜ የታዲዬስ ሞባይል ዳግመኛ ጮኸች፡፡አነሳ፡፡ እንግዶቹ ናቸው እጁን ወደላይ አንጠልጥሎ ያለበትን ቦታ ጠቆማቸው፡፡ ትንግርት፤ኤልያስ እና ጋዜጠኛው ወደእነሱ ተጓዙ፡፡ ዶክተር ሶፊያ ጀርባውን ሰጥታቸው ነው የተቀመጠችው፡፡ደረሱ

‹‹ታዲዬስ›.አለችው ትንግርት ፊት ለፊት የምታየው ፈርጣማ ወጣት በቲቪ ካየችው ምስል ጋር አልገናኝ እያላት ...በዚህ ጊዜ ዶ/ር ሶፊያ ልብን የሚሰነጥቅ አስደንጋጭ ድምፅ ነበር በጆሮዋ የገባው፡፡ በደመነፍስ አንገቷን ጠምዝዛ ዞር አለችና ‹‹ትን..ግር.ቴ.......››አለች፡፡
👍9812😁4👏1
#ትንግርት


#ክፍል_ሰላሳ_አራት


#በዘሪሁን_ገመቹ_ዋቤ


ትንግርት ፖሊስ ጣቢያ ተወስዳ ከታሰረች ከአንድ ሰዓት በኃላ የዕለቱ ተረኛ መርማሪው ፖሊስ ዘንድ እንድትቀርብ ተደረገ፡፡

‹‹ሙሉ ስምሽን ብትነግሪኝ?››መርማሪው ብዕሩን መዝገቡ ላይ ቀስሮ ጠየቃት፤ነገረችው፡፡

‹‹በምን ምክንያት በቁጥጥር ስር እንደዋልሽ ታውቂያለሽ?››

‹‹አዎ አውቃለሁ፡፡››

‹‹እስቲ የተፈጠረውን በዝርዝር አስረጂኝ?››

ዝም አለች፡፡ትንግርት ዶ/ር ሶፊያ ጋር ባላሰበችው ቦታ ባልታሰበ አጋጣሚ ስትገናኝ እራሷን የመሳት ያህል ስሜቷ ጡዞ አቅሏን ስታ ነበር፡፡ በወቅቱ ምን እንደተከሰተ ምን እንዳደረገች በትክክል አታስታውስም፡፡.

‹‹ምንም የማስታውሰው ነገር የለም?››

‹‹የሰራሽውን ወንጀልማ ማስታወስ አለብሽ ፡፡››

‹‹ምንም ወንጀል አልሰራሁም አላልኩም፤እያንዳንዱን ድርጊት አስታውሼ ግን ልዘረዝርልህ አልችልም፡፡››

‹‹ግድ የለም የምታስታውሺውን ያህል ንገሪኝ፡፡ ዶ/ር ሶፊያ በምትባል ግለሰብ ላይ ከባድ ድብደባ አድርሰሺባታል ፡፡ግለሰቧ አሁን በህያወት እና በሞት መካከል ትገኛላች፡፡››

‹‹እኔም እሷ ከዓመታት በፊት ባደረሰችብኝ ጥቃት ለሦስት ጨለማ ዓመታት በህይወት እና በሞት መሀከል ተንጠልጥዬ ስቃትት ነበር፡፡ ስለዚህ ብትሞት እንኳን በእኔ ላይ የፈፀመችብኝን በደል በማካካስ ስርየት
አያስገኝላትም፡፡>>

‹‹እስቲ በደለችኝ የምትያቸውን ነገሮች ንገሪኝ?››

‹‹አልችልም::››

‹‹የምርመራ ስራዬን አስቸጋሪ እያደረግሺብኝ ነው፡፡››

‹‹ይገባኛል ...ግን አሁን ምንም ልነግርህ አልችልም ፤ጊዜ እፈልጋለሁ፡፡››

መርማሪው ፖሊስ ለተወሰነ ደቂቃዎች በዝምታ አሰላሰለና ‹‹እንግዲህ የተጠቂዋ ሁኔታ እስኪለይለት ማረፊያ ቤት ትቆያለሽ ፡፡ ዛሬ ቅዳሜ ነው ሰኞ ፍርድ ቤት እንድትቀርቢ እናደርጋለን፡፡ፍርድ ቤቱ ምን አልባት ዋስ ሊፈቅድልሽ ይችላል፡፡››በማለት ወደ ማረፊያ ቤቱ እንድትመለስ አደረገ፡፡

ኤልያስ የዶክተር ሶፊያን የህክምና ሁኔታ ሲከታተል ከቆየ በኃላ ትንግርትን ሊያያት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄደ፡፡ፖሊሶቹን አስፈቅዶ ወደ እሷ ተጠጋ፤ከአጥሩ ወደዚያና ወደዚህ ሆነው መስኰት በመሰለች ክፍተት መነጋገር ጀመሩ፡፡

‹‹ሀይ ትንግርት ...እንዴት ነሽ?››

‹‹ሠላም ነኝ፡፡››

‹‹ፖሊሶቹ አናገሩሽ?››

‹‹አዎ ..…ማናገር አናግረውኛል፤አልተጋባባንም እንጂ፡፡››

‹‹አይዞሽ ..አንድ መቶ ሃለቃ ወዳጅ አለኝ፤ሁኔታውን ለእሱ አስረድቼዋለሁ፡፡ እንዲያናግራቸው አድርገን በዋስ ምትወጪበትን ሁኔታ እናመቻቻለን፡፡››

‹‹አይዞህ አትጨነቅ ምንም አልሆንም፡፡››

‹‹ቆይ ያልገባኝ... ምንድነው የተፈጠረው? ከልጅቷስ ጋር የት ነው ምትተዋወቁት?››

‹‹ኤልያስ ስለዚህ ጉዳይ አሁን ማውራት አልፈልግምም…አልችልምም፡፡››

‹‹ተይ እነጂ ትንግርት፤ችግር ውስጥ እኮ ገብተሻል፤ ሁኔታውን ካላወቅን እንዴት ልንረዳሽ እንችላለን?››

‹‹ምንም ዓይነት እርዳታ አልፈልግም፡፡ እሷ ሞታ እኔ እዚሁ እስር ቤት ለዘላለም ብበሰብስ እንኳን ደስተኛ ነኝ፡፡››አለችው እየተንዘረዘረች፡፡

‹‹ያን ያህል?››

‹‹ከዚያም በላይ፡፡አሁን ከዚህ በዋስ ብታስፈተኝ እንኳን ቀጥታ ወዳለችበት ሆስፒታል ሄጄ እስትንፋሷን እስከመጨረሻው ማቋረጥ ነው ምፈልገው፤አዎ እንደዛ ነው የማደርገው፡፡››

‹‹ኤልያስ ግራ ገባው ፡፡ትንግርትን በእንዲህ ዓይነት የቂመኝነትና የክፋት ባህሪ ውስጥ ወድቃ አጋጥሞት አያውቅም፡፡እሷን በአዛኝነቷ፤በትእግስተኝነቷ፤ ለሰው ባላት ሀሳቢነት : የሰውን ልጅ ቀርቶ እቤቷ የገባች አይጥ በወጥመድ ተይዛ ብታገኛት በሀዘኔታ ከወጥመዱ አላቃ ከነ ህይወቷ ወደ ጐሬዋ እንድትመለስ የምትፈቅድላት ሰው እንደሆነች ነው የሚያውቀው፡፡ታዲያ እንዴት እንዲህ ልትቀየር ቻለች? ፡፡የዚህን ዓይነት የገዘፈ አውሬነት እንዴት በውስጧ ተሸሽጐ ሊኖር ቻለ? ያቺ ልጅስ ምን ያህል ብትበድላት ነው ይሄን ያህል ልታስቆጣት የቻለችው?››

‹‹እሺ ፎዚያን ምን ልበላት ...በስልክ እያጨናነቀቺኝ ነው?..

‹‹እንዴ!!! ነገርካት እንዴ?››

‹‹አዎ ነግሬያታለሁ... ስታጨናንቀኝ ምን ላድርግ?››

‹‹ሰላም ነች በላት፡፡››

‹‹እሱማ ብያታለሁ..ግን ካልመጣሁ እያለቺኝ ነው፡፡››

‹‹በቃ ከመጣች ከእኔ መኝታ ቤት ካለው ኮመዲኖ ታችኛው መሳቢያ ውስጥ ሁለት ጥቁር ልባስ ያላቸው ዲያሪዎች አሉ..እነሱን ይዛልኝ ትምጣ፡፡››

‹‹እሺ ነግራታለሁ፡፡››አላት፡፡

ብዙ ማውራት ቢፈልጉም ተረኛ ፖሊስቹ ከዛ በላይ ሊፈቅዱላቸው ስላልቻሉ እሷ ወደ ማረፊያዋ እሱ ደግሞ አንዳንድ ነገሮችን ለመመካከር መቶ ሃለቃ ጓደኛው ወዳለበት ቦጋ አመራ፡፡

ይቀጥላል

ቤተሰቦች #subscribe እያደረጋቹ 5 ሰው #subscribe ካደረገ ቀጣዩ ክፍል ማታ 3 ሰአት ላይ ይለቀቃል

#Share and #subscribe my #YouTube 

👇Sebscribe

YouTube link👇
https://www.youtube.com/@atronose
👍8721👏4👎3🥰2