ዐውደ ምሕረት
3.67K subscribers
932 photos
24 videos
271 files
195 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
"፤አንደበትህን ከክፉ ከልክል፥ ከንፈሮችህም ሽንገላን እንዳይናገሩ። "
አንደበት እሳት ነው። አንደበትህን ካልተቆጣጠርህ አንድ የክብሪት እንጨት ትልቁን ግንድ እንደምታነደው ሁሉ ያንተ ምላስ ብዙኃንን ታስከፋለች ስሜት ትጎዳለች ቅዱሱ ያዕቆብ በመልዕክቱ ስለ አንደበት ሲናገር "(የያዕቆብ መልእክት ምዕራፍ 3 ) እንዲሁም አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል። እነሆ፥ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል ፤ አንደበትም እሳት ነው። አንደበት በብልቶቻችን መካከል ዓመፀኛ ዓለም ሆኖአል፤ ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና፥ የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል፥ በገሃነምም ይቃጠላል።" ብሎ ገልጦታል።
* ታዲያ አንደበታችንን ክፋውን ነገር ከመናገር እንዲቆጠብ ምን እናድርግ? ቀላል ነው! በማስተዋል ማውራት ይህም ማለት ሕሊናችንን( አዕምሮ ) ከአንደበታችንን (ምላስ) ጋር በማስተባበር በመጽሐፍ ቅዱስ እንደምናነበው አንድ ሰው ለጌታችን (የማርቆስ ወንጌል 9 ) "መምህር ሆይ፥ ዲዳ መንፈስ ያደረበትን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼአለሁ፤በያዘውም ስፍራ ሁሉ ይጥለዋል፤ አረፋም ይደፍቃል፥ ጥርሱንም ያፋጫል ይደርቃልም፤ እንዲያወጡለትም ለደቀ መዛሙርትህ ነገርኋቸው፥ አልቻሉምም አለው"። እርሱም መልሶ። የማታምን ትውልድ ሆይ፥ እስከመቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደ እኔ አምጡት አላቸው።ወደ እርሱም አመጡት። እርሱንም ባየ ጊዜ ያ መንፈስ ወዲያው አንፈራገጠው፤ ወደ ምድርም ወድቆ አረፋ እየደፈቀ ተንፈራፈረ። ብዙ ጊዜም ሊያጠፋው ወደ እሳትም ወደ ውኃም ጣለው፤ ቢቻልህ ግን እዘንልን እርዳንም አለው። ኢየሱስም። ቢቻልህ ትላለህ፤ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል አለው። ወዲያውም የብላቴናው አባት ጮኾ። አምናለሁ፤ አለማመኔን እርዳው አለ። ይህ ሰው በችኮላ መድኃኒት የሆነውን ክርስቶስን " ቢቻልህ እዘንልን" ብሎ በአንደበቱ ችኩልነት የፍጥረትን ጌታ ባለማስተዋሉ ተሳሳተ። አንተ ሰው አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ እንደው ሠማይና ምድርን የፈጠረ ጌታን ይህን ፈውሰ አያደርግም ብለህ እንዴት አሰብክ? ኋላ ግን ማመንህ በጀህ ጥፋትህን አምነህ አለማመኔን እርዳው ብለህ ታረምህ ። እንዲሁም ጌታችንን አንዲት ከነናዊት ሴት ልጄን ማርልኝ ብላ ብትጠይቀው (የማቴዎስ ወንጌል 15 ) እርሱ ግን መልሶ። የልጆችን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባም አለ።እርስዋም አዎን ጌታ ሆይ፤ ''ቡችሎችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ'' አለች። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ አንቺ ሴት እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደወደድሽ ይሁንልሽ አላት። ልጅዋም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነች። ይህ አይነት አንደበት ሲኖረን ጥበብ ከእውቀት ጋር ከእኛ ትሆናለች ሐስት ቦታ አጥታ ከእኛ ትሸሻለች ለሐሰት ሞተን ለእውነት መኖር እንጀምራለን " የእውነት ከንፈር ለዘላለም ትቆማለች ፤ ውሸተኛ ከንፈር ግን ለቅጽበት ነው " እንደተባለ ከዚያም ንግግራችን በጨው እንደተቀመመ በጸጋ ይሆናል ትህትናን ገንዘብ እናደርጋለን "፤ ሞትና ሕይወት በምላስ እጅ ናቸው፤ የሚወድዱአትም ፍሬዋን ይበላሉ። " እንደተባለ መልካሙን የሕይወት ፍሬ ለመብላት እንበቃለን ማለት ነው ..... ይህን እንፈጽም ዘንድ እመብርሃን ድንግል ማርያም ትርዳን...አሜን!!!
* ማውራት ከመጀመርህ በፊት ሁለቱን ማገናኘት አትርሳ *
.....ቡሩክ መልሣቸው ...
.....ጥር 14/ 2013....
.....አ.አ ኢትዮጵያ
@BarokZamin
ውድ ታዳሚዎቻችን እንደምን ዋላችሁ (አደራችሁ) ...አሜን ስለ ቸርነቱ እግዚአብሔር አምላክ የተመሰገነ ይሁን አትለይምና እመ አምላክ ወላዲተ አምላክ #ቅድስት_ድንግል_ማርያምም እንደተሰጣት ከፍ ያለ ጸጋ የተመሠገነች ትሁንልን አሜን..!::
እነሆ ተወዳጁ የምን እንጠይቅልዎ መርኃ ግብር አሁን ጀምሯል ጥያቄዎን በሚከተሉት አድራሻዎች ይስደዱልን ሊቃውንትን ጠይቀን መጻሕፍትን አገላብጠን ቤተ ክርስቲያናዊ ምላሽ እንሰጥበታለን።
👇👇👇👇👇
@Abenma
@YEAWEDIMERITE
👇👇👇👇👇👇
ዓውደ ምሕረት የእናንተ
@AwediMeherit
@AwediMeherit
✞ኀዘናችንን ወደ ደስታ ለውጦታል✞
ዛሬ ወደ አስቴር ህይወት እናቅና መጽሐፍ ቅዱሱ " የተዋበች መልከመልካም ነበረች" ብሎ ስለ አካላዊ ውበቷ ተናግሮ አድንቆ ይጀምራል። የገጽዋ ውበት እንዲ ከተገለጸ ውሳጣዊ ውበቷን ማወቅ ምን ያክል እንደሚያጓጓ መገመት አያቅትም። ንጉሱ አርጤክስ ቀዳማዊ ሚስቱ አስጢን በድላው ፊቱን አዙሮባት ነበርና የእርሱ አገልጋዮች ሁለተኛ ድንግል ልጃገረድ እንደሚያስፈልገው ያወጉት። መቼስ ንጉስ አልጋ ወራሽ ያስፈልገው ብቻውንም ይሆን ዘንድ አይገባምና ሀሳባቸውን ተቀብሎ ከድንግልናዋ ውጪ የእርሱን መስፈርት ልታሟላ የምትችል ሴት መጥታ ፈተናውን መፈተን እንደምትችል አዋጅ ያስነገረው።ያን ጊዜ ነበር መልከ መልካሟ አመለ ሸጋዋ አስቴር በንጉሱ ቅጽር የተገኘችው። የፈተናው ጊዜ ተጀመረ! ሁሉም ንግስት የመሆን ፍላጓታቸውን አንግበው በተስፋ ወደ ንጉሱ እልፍኝ ገቡ ፈተናቸውን አጠናቀው እየወጡ የአስቴር ተራ ደርሶ ወደ ፈተናው አዳራሽ ያለፍርሃት እግዚአብሔርን ይዛ ገባች። ወዲያውኑ ንጉሱ ፊት ክብርና ሞገስ አግኝታ ንጉሱም በእርሷ ተማርኳ ድል ተነሳ። ያኔ በዚያ የተሰበሰቡ በንጉሱ ዘንድ ተቀባይነት ያጡ ሴቶች ምነኛ አዘኑ ይሆን? የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ ተብሎ እንደተጻፈ አስቴር በእግዚአብሔር ተመክታ እርሱን ይዛ የንጉሱን ልብ ተቆጣጠረች ውጫዊ ብቻ ሳይሆን የውስጧ ውበት ልዩ ነበር ። ነገር ግን የውስጥ ውበት ምንድር ነው ? በአጭሩ ስንገልጸው ትሁትነት ነው። ትሁት ልብ ቅን ነው ደግነትን ያበዛል፤ ትሁት ልብ የዋህ ነው ይራራል፤ ትሁት ልብ እውነተኛ ፍቅር አለው ሁሉንም በእኩል ያያል አይጨክንም ምክንያቱም ፍቅር ይታገሣል፥ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፥ አይታበይም፤ የማይገባውን አያደርግም፥ የራሱንም አይፈልግም፥ አይበሳጭም፥ በደልን አይቆጥርም። ይህን ያሟላ በምድራውያን ሰዎች በሰማያውያን መላእክት ብሎም በእግዚአብሔር ዘንድ ክብርን ይጎናጸፋል።
ወደ አስቴር ስንመለስ በንግስናዋ ወራት ክፋውን እና ደጉንም በእግዚአብሔር አጋዥነት ለንጉሱ እየገለጠች ተአማኒነትን ፍቅርን በንጉሱም በሐዝቡ ዘንድ አተረፈች። ክፋውንም ድግስ ሲያሰናዳ የነበረውን በአሳዳጊዋ በመርዶክዮስ እና በሕዝቦቿ ላይ ሲያሴር የነበረውን የሐማን ግብር በልዩ ጥበብ አጋለጠች። የሐማ ዘውድ የሐማ ቀለበት የሐማ ክብር እና ሥልጣን ለመርዶክዮስ ተሠጠ።ሐማ ለመርዶክዮስ ባዘጋጀው መስቀል ላይ እራሱ ተሰቀለ ፤ አዳም ከእስራቱ ተፈቶ ነፃ ወጥቶ የሐሰት አባት ዲያቢሎስ በንፋስ አውታር በእሳት ዣንዥርታ እንደታሰረ ሁሉ፤ የአስቴር ሕዝብ አይሁዶች በአስቴር ድንቅ ስራ ነፃ ወጡ ከሞት ዳኑ የአዳም ልጆች እኛም በክርስቶስ የማዳን ስራ በደሙ ቤዛነት ከሞት አመለጥን ከውርደት ድነን ክብርን አገኘን።
በዚያችም ቀን ለአይሁድም ብርሃንና ደስታ ተድላና ክብርም ሆነ። ኀዘናቸው ወደ ደስታ ተለውጧልና ፤ እኛም ከጨለማ ወደ ብርሃን ገብተናልና ከዲያቢሎስ ቁራኝነት ነጻ ወጥተናልና እንደ አስቴር ከርስቶስን ይዘናልና እርሱ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ኀዘናችንን ወደ ደስታ ለውጦልናል ለማይከፈል ውለታው ለመድኃኒታችን ክብር እና ምስጋና አምልኮ እና ውዳሴ ለእርሱ ይሁን አሜን!!!።
........ቡሩክ መልሳቸው......
......ጥር 15/2013......
.......አ.አ ኢትዮጵያ .......
@BarokZamin
+ #እመ_ዕረፍት +
ዛሬ እመ ዕረፍት ዐረፈች፤እመ ሕይወት ዛሬ ሞትን ቀመሰች፤ዛሬ አማናዊት ዕፀ ሕይወት
ከዕፀ ሕይወት ሥር ዐረፈች።ዲያቢሎስ በክፋት ግብሩ ጥል ፣ሞት እየተባለ እንደሚጠራ
(ኤፌ 2፥16፤1ኛ ቆሮ 15፥26) እንዲሁ እግዚአብሔርም በጽድቁ ንጹህ ብቻ ሳይሆን
ንጽሕና ሕያው ብቻ ሳይሆን ሕይወት እየተባለ ይጠራል።ዛሬ "የአሸናፊ እግዚአብሔር እናቱ"
ድንግል ማርያም ዐረፈች።አራቱ ባሕርያተ ሥጋን አምስተኛ ባሕርየ ነፍስን አዋሕዶ የፈጠረ
(ዘፍ 2፥7) የጌታችን እናቱ ዛሬ ቅድስት ነፍሷ ከክቡር ሥጋዋ ተለየ።"እንደ እመቤታችን
እንደ ማርያም የአብ ማረፊያ የሆነ ማን ነው?እንደ እመቤታችን እንደ ማርያም የወልድ
ማደሪያ የሆነ ማን ነው?እንደ እመቤታችን እንደ ማርያም የመንፈስቅዱስ ንጹሕ አዳራሽ
የሆነ ማን ነው?"(ተአምረ ማርያም)።እኛም በአንክሮ በተደሞ "እንደ እመቤታችን እንደ
ማርያም ሞት እንግዳ ነገር ምንድን ነው?" ስንል እንጠይቃለን።"ሞት የኃጢአት ደሞዝ
ነዋ"(ዘፍ 2፥17፤ሮሜ6፥23)።በክብር ሁሉ ጌጥ ያጌጠ እርሱ ያደረባት ንጽሕት የሰርግ ቤት
ታዲያ ለምን ታርፋለች?ይህስ መርምረን የማንዘልቀው ድንቅ የመለኮት ሥራ ነው።አዳምና
ሔዋን የእግዚአብሔርን ቃል አቃልለው ምክረ ሰይጣንን ሰምተው ሞትን ወደ ዓለም
አገቡ።ድንግል ማርያም ግን በመልአከ ብሥራት በቅዱስ ገብርኤል አማካኝነት ቃለ
እግዚአብሔርን ሰምታ ሕይወትን ለዓለም ሰጠች።(ሮሜ 5፥12-17)።ታዲያ እመቤታችን
እንዴት ዐረፈች?ይህንን ነገር ፈጽመን መናገር አይቻለንምና ዝም እንበል።
ሰንበተ ክርሰቲያን ድንግል ማርያም በሰንበተ ክርስቲያን እሑድ ዐረፈች።ዕለተ እሑድ
የድንግል ማርያም ምሳሌ ነው።በዕለተ እሑድ የፍጥረታት መሠረት የሆኑ አራቱ ባሕርያተ
ሥጋ(አሥራወ ፍጥረታት) ተገኝተዋል።ከድንግል ማርያምም የፍጥረታት ሁሉ አስገኚ ጌታ
ተገኝቷል።ዕለተ እሑድ የፍጥረታት መጀመሪያ ነው ድንግል ማርያም ግን ለጠፋው ፍጥረት
ሁሉ "የደኅንነት መጀመሪያ" ናት።በዕለተ እሑድ ገነት ተፈጠረልን "ስለ ሔዋን የተዘጋብን
የገነት ደጅ" "በምትናገር ገነት" በድንግል ማርያም "ዳግመኛ ተከፈተልን"
በዕለተ እሑድ መንግሥተ ሰማያት ተፈጠርልን በድንግል ማርያም ግን ዕለት ተዕለት
"መንግሥትህ ትምጣ" "መንግሥት የአንተ ናትና" እያልን የምንማጸነው መንግሥቱን
የሚያወርሰን አምላካችን አማኑኤል ተገኘልን።በዕለተ እሑድ እግዚአብሔር አምላክ ውኃን
ፈጠረ በፈጠረው ውኃም ላይ መንፈሱን አሰፈረ።መንፈስ ቅዱስ የጠበቃት ኃይለ ልዑል
የጋረዳት ድንግል ማርያም ግን "ማንም የተጠማ" ከእርሱ የሚጠጣ ጠጥተውት ዳግመኛ
የማያስጠማ ማየ ሕይወት ክርስቶስን ወለደችልን።በዕለተ እሑድ መላእክት ተፈጠሩ
በአማናዊት እሑድ በድንግል ማርያም ግን"ኪሩቤል በፍርሃት የሚሰግዱለት ሱራፌልም
የሚያመሰግኑት" "የመላእክት ደስታቸው"መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገኘ።በዕለተ
እሑድ "እግዚአብሔር ብርሃን ይሁን አለ ብርሃንም ሆነ።"(ዘፍ 1፥3)በድንግል ማርያም ግን
"በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ" ለምንኖር ለእኛ "ታላቅ ብርሃን ወጣልን።"በዕለተ እሑድ
መንግሥተ ሰማያት ለጻድቃን ትሰጣለች ጌታችን ከድንግል ማርያም የነሣውን ሥጋ ግን
ወርሰውት ለዘላለም ይኖራሉ።እመቤታችን ሆይ በማንና በምን እንመስልሻለን?ሰንበት
ድንግል ማርያም ሆይ ሰንበት ከሚባል የሰንበታት ጌታ ከሆነ ልጅሽ ጸጋውን ክብሩን
እንዳይነሣን ለምኚልን።
እመቤታችን ካረፈች በኋላ ለምቀኝነት የማያርፉ አይሁድ በፊት ልጇ ከሞተ በኋላ ተነሥቷል
ዐርጓል እያሉ አወኩን።አሁን ደግሞ እሷን ተነሣች ዐረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለምን?
ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ ሥጋዋን እናቃለጥለው ተባባሉ።ምቀኝነት ትርፉ ይህ
ነው።መታወክ።"ዓለም እንደሚሰጠው ሰላም ያይደለ እውነተኛ ሰላም የሚሰጠን የሰላም
አለቃ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ" ግን ዕረፍተ ኅሊናን እናገኝ ዘንድ "ጠላቶቻችሁን
ውደዱ" ብሎ አስተማረን።ማኅደረ ሰይጣን የሆነ ታዖፋንያ የሚባል ከእነርሱ አንዱ ክቡር
ሥጋዋን አቃጥላለሁ ብሎ የአልጋዋን አጎበር ቢይዝ መልአከ እግዚአብሔር እጆቹን በሰይፍ
ቆርጧቸዋል።አላወቃትማ "ቢያውቃትስ ኖሮ የክብርን እናት ሥጋ ለማቃጠል ባልደፈረ
ነበር።" በመስቀል ላይ"አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያዉቁምና ይቅር በላቸው"ብሎ የለመነ
የፍቅር እናቱ የምትሆን ድንግል ማርያም ግን በከበረ ምልጃዋ እጆቹን አሰጠችው።እሱ
ቅዱስ ሥጋዋን ለማቃጠል እጆቹን ዘረጋ እመቤታችን ግን በሥጋዉም ሆነ በነፍሱ ታድነው
ዘንድ የምህረት እጆቿን ዘረጋችለት።ወንጌልን ያስተማርሽን ንጽሕት ፊደላችን ሆይ
እናመሰግንሻለን።የድንግል ማርያም ትንሣኤ ያውካልን?አዎን፤ በእኛ በክርስቲያኖች ዘንድ
"ከኪሩቤልና ከሱራፌል የሚበልጥ የመወደድ ግርማ" ያላት ድንግል ማርያም
በአጋጋንት፣በአይሁድና በመናፍቃን ዘንድ ግን "ከቅዱስ ሚካኤልና ከቅዱስ ገብርኤል
የሚበልጥ የማስፈራት" ግርማ አላት።
ከከበረ ዮሐንስ ጋር ወደ ዕፀ ሕይወት ተነጠቀች።"ዓለም አልተገባቸውምና።"(ዕብ
11፥38)ጌታን ከሁሉ አብልጦ ለወደደ ዮሐንስ ከሁሉ አብልጦ የሚወዳት ድንግል
ማርያምን በዕለተ ዓርብ ሰጠው።ከወንድሞቹ ሐዋርያት ተለይቶ ከእመቤታችን ጋር ከእግረ
መስቀሉ ሥር የተገኘ ዮሐንስ አሁን ደግሞ ከእነርሱ ተለይቶ ከእመቤታችን ጋር ከዕፀ
ሕይወት ሥር ተገኘ።ቅዱስ ዮሐንስ ከሕይወት ከክርስቶስ ደረት እየተጠጋ ጌታውን ያነጋግር
እንደነበረም ቅዱስ ወንጌል ነግሮናል።የቅዱስ ዮሐንስ እናት ማርያም ጌታ ሆይ በዙፋንህ
በተቀመጥህ ጊዜ አንዱ ልጄን በቀኝህ አንዱን በግራ አስቀምጥልኝ ብላ ለምናው
ነበር።በዙፋኑ "በአባቱ ቀኝ"የተቀመጠውም ቅዱስ "በቀኙ በምትቆመው" በአማናዊቱ ዙፋን
በድንግል ማርያም አጠገብ ከዕፀ ሕይወት ሥር አኖረው።ቅዱስ ዮሐንስ እመቤታችንን
በዕለተ ዓርብ ከጌታችን ከተቀበለ በኋላ "ወደ ቤቱ ወሰዳት"(ዮሐ19፥27) እሷ ደግሞ አሁን
በዕለተ እሑድ "ወደ ቤቷ ወሰደችው"። የዓርብ መከራ ተካፋይ ቅዱስ ዮሐንስ የእሑድ ደስታ
ተካፋይም ነበር።ዕፀ ሕይወት አዳምን ከእርጅናው(ከኃጢአቱ) ልታድሰው አልቻለችም።ዕፀ
ሕይወት ድንግል ማርያም ግን "በአዲስ ተፈጥሮ" ዳግመኛ የሚፈጥረዉን ሕይወቱ
ክርስቶስን ወለደችለት።ቅዱስ ኤፍሬም እንዲህ ይላል "ከዕፀ ሕይወት እንበላ ዘንድ አደለን
ይኸውም... የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋው ክቡር ደሙ ነው።"
ሞቷ እንደ ልጇ ሞት ነው።እሱ መላ ዘመኑን አዝኖ "ነፍሱ እስከሞት ድረስ ያዘነች" ሆና
ሞተ።(ማቴ 26፥38)
እሷም ከእሱ ጋር ተንከራታ "በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል"እንዳላት ቅዱስ ስምዖን አረጋዊ(ሉቃ
2፥34-35) እንደ ሰይፍ ነፍስን ከሥጋ ሊለይ የሚችል ጽኑ ኀዘንና መከራ ገጥሟት
ሞተች።የጌታችን ሞት ቅዱሳን መላእክትንና ሰዎችን አንድ አደረገ።የእመቤታችንም ሞት
እንዲሁ ነው።
ትንሣኤዋም እንደ ልጇ ትንሣኤ ነው። እንደ ልጇ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር
ቆይታ ተነሥታለችና።"ከመ ትንሣኤ ወልዳ" "እንደ ልጇ ትንሣኤ" ያሰኘውም ይህ
ነው።"ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር የተባበረች ድንግል ማርያም ትንሣኤውን
በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከልጇ ጋር ተባበረች።"(ሮሜ 6፥5)
ዕርገቷም እንደ ልጇ ዕርገት ነው።ልጇ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስፍራ ሊያዘጋጅልን ወደ
ሰማይ ዐረገ።(ዮሐ 14፥2-3)እርሷም በቃልኪዳኗ መንግሥተ ሰማያትን ልታዘጋጅልን ወደ
ሰማይ ዐረገች።ጌታችን ሲያርግ "ምርኮን ማረከ"።(መዝ 67፥18)እመቤታችንም በዕርገቷ
ብዙ ነፍሳትን ማረከች።ቅዱስ ኤፍሬም እንዲህ አለ "ከምድር ወደ ሰማይ ለማረግ መሰላል
ሆንሽ።"እንዲህ ነው እግዚአብሔርን መምሰል ማለት።
"ነገረ ማርያምን ማወቅ ነገረ ክርስቶስን ማወቅ ነው።"
"ቅድስት ሆይ ለምኚልን"
#አዘጋጅ መ/ር ኢዮብ ክንፈ
ጥር 2012 ዓ.ም
ጎልያድን የገደለ #ሐዲስ ዳዊት #ሊቀ_ሰማዕቱ_ቅዱስ_ጊዮርጊስ
#በተኵላና_በእባብ ላይ ትጫማለህ፤ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ።
#በእኔ_ተማምኖአልና አስጥለዋለሁ፤ ስሜንም አውቆአልና እጋርደዋለሁ።
#ይጠራኛል እመልስለትማለሁ፥ በመከራውም ጊዜ ከእርሱ ጋራ እሆናለሁ፤አድነዋለሁ አከብረውማለሁ። " #መዝ 90(91)÷13-15
ይህ #የእግዚአብሔር_ቃል ነው ፤ እንግዲህ #እግዚአብሔር_ያከበረውን ማን ያቀልዋል ? #ማንም!
#ኢትዮጵያዊው_ኤልሳዕ
በአጽሙ ሙት ያስነሳ
፪ኛ ነገሥት ፲ ፫÷፳ -፳ ፩
ገ/ተ ሃይማኖት ም/፶ ፫

አጥንት በመጻሕፍ ቅዱስ ውስጥ በምሳሌነት ሲጠቀስ ሦስት ነገሮችን ያመለክታል።
፩ የሰው ኃይልን ያመላክታል መዝ፶ ፫፥፭ ኢሳ፴፰፥፲፫
፪ የቅርብ ዝምድና መግለጫ ዘፍ ፳፱÷፲፬ ሳሙ ፱÷፪
፫ የሞተ ሰውን ክብር ያስረዳል ዘፍ ፶÷፳፭ ዕብ ፲፩÷፳፪
#ይበልጡኑ_የቅዱሳን_ሰዎች ሞት /አጥንት (አጽም)/ እጅግ የከበረ ነው ። መዝ ፻፲፭ (፻፲፮) ÷፲፭ ለአብነትም ተቀብሮ የነበረው የኤልሳዕ አጥንት /አጽም/ ሌላ የሞተ ሰው ከሞት እንዳስነሳ መመልከት በቂ ነው። ከሞዓብም አደጋ ጣዮች በየዓመቱ ወደ አገሩ ይገቡ ነበር።ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዮችን አዩ፥ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ጣሉት፤ የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውዮው ድኖ በእግሩ ቆመ። ፪ኛ ነገሥት ፲፫÷፳ -፳፩
በተመሳሳይ ኢትዮጵያዊው ኤልሳዕ ጻድቁ አባታችን ተክለ ሃይማኖትም የሥጋ ድካም ከትጋቱ እንዳያስታጉለው በስምንት ሰለታም ጦር እራሱን ከቦ ከደብረ አስቦ ዋሻ ከቆመ ሳይቀመጥ ከዘረጋ ሳያጥፍ ፳፪ ዓመት ሲጋደል ሳለ ከመቆም ብዛት አንዲቷ የእግሯ አገዳ ተሰበረችና ከሰውነቱ ተለይታ ወደቀች።
#ደቀ_መዛሙርቱም እንደ ማንም መስሏቸው ስባረ እግሩን ከመቃብር ሥፍራ ወረወሯት የኤልሳዕን አጽም ሲነካው ከሞት ድኖ እንደተነሳው ሰው የአባታችን የእግራቸው አጥንት የነካው በመቃብሩ ሥፍራ ተቀብሮ የነበረ አንድ ሰው አፈፍ ብሎ ድኖ በእግሩ ቆመ ። ገ/ተ ሃይማኖት ፶ ፫
የአባታችንንም ስባረ አጽም (ስባረ እግር) እያመሰገነ ሰላምታ ሰጠ " ይህን ያዮ ደቀ መዛሙርቶቻቸውም የጻድቁ ስባረ አጽም ገባሬ ተአምራት መሆኗን አውቀው ከመንበሩ እግር በታች አክብረው በሰበን ጠቅልለው ቀብረዋታል::
" #የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፥ እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል። እግዚአብሔር አጥንቶቻቸውን ሁሉ ይጠብቃል፥ ከእነርሱም አንድ አይሰበርም። " መዝ ፴፫{፴፬}÷፲፱-፳ ይህ የቅዱሳን አጥንት (አጽም) እግዚአብሔር የማይለየውና ሌት ተቀን የሚጠብቀው ነውና ቅዱሳን ጻድቃን ካረፉበት ሄዶ መሳለም በረከትን ያሰጣል ከሥጋም ከነፍስም ህመም አድኖ በጤና ያቆማልና የአጽማቸውን በዓል ማክበር እጅግ የሚገባ ነው ::
ቅዱስ ጳውሎስ በልብሱ ጨርቅ " (ሐዋ፲፱÷፲፩-፲፪) ቅዱስ ጴጥሮስ በሰውነቱ ጥላ ድውያንን ሁሉ ይፈውሳቸው ነበር ። ( ሐዋ ፭÷፲፭ ) ቅዱሳን የነፍሳቸው ቅድስና ለሥጋቸው፣ የሥጋቸው ቅድስና ለለበሱት ልብስና ለአካላቸው ጥላ ተርፎ ድንቅ ተአምራትን የሚሰራ ከሆነ እግዚአብሔር የሚጠብቀው አጽማቸውማ እንዴት አብልጦ ድንቆችን አይሳ?!::
#አጥንት_ለሰዉ ልጅ ተክለ ሰውነት ወሳኝ ድርሻ አለው። ከሚሰጣቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች መካከል የተወሰኑት ብንዳስስ፤ ለሰዉነታችን ቅርፅ ለመስጠት፣ የሰዉነት የውስጥ አካላት (Organs) ከአደጋ ለመከላከል #ለምሳሌ ደረት የሚያርፍበት ክፍለ አጥንት ለሳንባና ለልብ ከለላ(covering) ይሰጣል፤ የራስ ቅል አጥንት አንጎል ምንም አይነት ጉዳት እንዳይገጥመው ጠንካራ ልባስ ሆኖ ይከላከላል ፣ ሥጋና ጡነቻዎቻችንን አጣብቆ ለመያዝና የካልስየም ንጥረ ነገርን ለማጠራቀም ይረዳል፡፡
ክቡር የሆነ አባታችን ቅዱስ ተክለ ሃይማኖትም ለቀናች ሃይማኖቱ አጥንት ነው። አጥንት የሌለው አካል ጤፍ እንደሌለው ማዳበሪያ መቆም አይቻለሁም:: ሀገሪቱና ቤተክርስቲያኒቱ ዶግማ ቀኖናና ትውፊቷን ይዛ ቅርጻን ሳትለቅ ቀጥ ብላ እንድትቆም አድርጓታልና።

#ምዕመኗ ልዮ ልዮ በሆነ በእግዳ ትምህርት ከበረትቷ እንዳይኮበልሉ ኖላዊ ትጉሁ ሆኖ በጻም በጸሎቱ የሀገር ዋልታ ጥላ ከለለ በመሆንም አካል የምትባል ቤተክርስቲያንን እንደ አጥንት ጋሻ፣ መከታ፣ ጥላ ፣ከለላ ሆነላት።
የሃይማኖት ማነስ የምግባር ጉድለት እንዳያጋጥማትም እንደ አጥንት እያለ በቃሉ ትምህር በእጁ ተአምራት በበረከቱና ሞላት በረድኤቱ ጋረዳት የሃይማኖት መፍሰሻ ነቅ የወንጌል መፍለቂያ ምንጭም አደረጋት።
#ዞሮ_ማስተማሩ ሳይሰለቸው ፳፪ዓመት በጾም፣ በጸሎት መቆሙ ሳይታየው ፤የእግሩም መሰበር ግድ ሳይሰጠው በአንዲት እግሩ ሰባት ዓመት በትእግስት ቆሞ በትግኃ ጸሎት ጽሙድ ሆኖ ፳፱ ዓመት አስቆጠረ። “እነሆ፥ በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን እንላቸዋለን፤ ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል፥ ጌታም እንደ ፈጸመለት አይታችኋል፤ ” የሚለውም ቃል በዳግማዊ ኢዮብ በጻድቁ ተክለ ሃይማኖት ደግሞ ተገለጠ ስለዚህ ብጹህ ይባል ዘንድ የተገባው ነው #ያዕቆብ ፭÷፲፩
"በጻድቅ ሰው ጸሎት ሀገር ትለማለች እንጂ አትጠፋም" እዳለው ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የመቆም ምክንያት እርሱ ብጹዊው አባታችን የጀርባ አጥንቷ ነው ። “የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች።” ያዕ ፭ ፥፲፮
#በአጽሙ_ሙት ያስነሳ የኢትዮጵያዊው ኤልሳዕ የዳግማዊው ኢዮብ #የብጹዕ_አባታችን_የቅዱስ_ተክለ_ሃይማኖት በረከት በሁላችን ሕዝበ ክርስቲያኖች ላይ ጸንታ ትኑር!
.......ይቆየን.........
ኃ/ማርያም አ.አ ኢትዮጵያ
ጥር ፳ ፬\፳ ፻ ፲ ፫ዓ.ም
👇👇👇👇👇👇
@YEAWEDIMERITE

#ዓውደ_ምሕረት_የእናንተ
👇👇👇👇👇👇
@AwediMeherit
@AwediMeherit
@AwediMeherit
#አማኑኤል:- #እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ!

"ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።” #ዮሐ ፩ ፥ ፲ ፬
#ቸሩ ሆይ ቸሩ ሆይ ናና
#ቸሩ ሆይ አማኑኤል ናና
#የእስራኤል መና ቸሩ ሆይ ናና
#ቸሩ ሆይ መድኃኔዓለም ናና
#ሊቀ_መዘምራን_ቀሲስ_ምንዳዬ_ብርሃኑ
" የታላቂቱ ከተማ ጾም"
የታላቂቱ ከተማ የነነዌ ኃጢያት ከመብዛቷ የተነሳ እግዚአብሔር ፊት ደረሰች ።ት.ዮና ፩÷፪ ነቢዮ ዮናስ ሄዶ በዛች በታላቂቁ ከተማ በነነዌ እንዲሰብክ #እግዚአብሔር ላከው የዋህው ዮናስም #እግዚአብሔር መሐሪ ነው በኃላ ሄጄ ካልተመለሳችሁ ከሰማይ እሳት ወርዳ ትበላችዋለች ብዬ ከሰበኩ በኃላ ቢምራቸው እኔ ሐሰተኛ ነቢይ እባላለው ብሎ ወደ ነነዌ መሄድ ትቶ ወደ ተርሴስ በመርከብ ተሳፍሮ ኮበለለ።
አዳም እጸ በለስን ከበላ በኃላ ከእግዚአብሔር ፊት ለመደበቅ ሞክሮ ነበር እግዚአብሔር አምላክም እንደ አባት ነውና እንዳይሳቀቅበት አንድም በኃላ ዘመን አላዋቂ የሰው ሥጋን ተዋህጄ አድንሃለው ሲለው ባላዋቂ ልማድ ከፊቱ የተሰወረበት ይመስል " አዳም አዳም ሆይ ወዴት አለህ " ሲል በፍቅር ጠይቆት ነበር።
አበው " #እግዚአብሔር አምላክ ሞኝ ነጋዴን ይመስላል መንግስተ ሰማያትን የምታክል ውድ ነገር በጥርኝ ውኃ ልስጣችሁ ብሏልና" ይላሉ ማቴ ፲ ÷ ፴ ፱ የዋህው ዮናስ ይህን ብሒለ አበው ሳይሰማ የቀረ አይመስልም እግዚአብሔር እንደ ሞኝ ቆጥሮ አካሄዱንም እንደማያውቅበት አስቦ ከፊቱ ኮበለለ ።

የዳዊትን መዝሙር ያልሰማህ ይህ አይሁዳዊ ሰው ምነኛ የዋህ ነው።
"ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ?
ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ?
ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ ነህ፤
ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ።
እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥ በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች።በውኑ ጨለማ ትሸፍነኛለች ብል፥ ሌሊት በዙሪያዬ ብርሃን ትሆናለች፤ ጨለማ በአንተ ዘንድ አይጨልምምና " #መዝ ፻ ፴ ፰(፻ ፴ ፱) ÷ ፯-፲ ፩


እግዚአብሔር ግን የተሳፈረበትን ታንኳ በማዕበልና በሞገድ አስጨነቃት ይህም ሁሉ በእርሱ ምክንያት እንደሆነ ለመረከበኞቹ ነግሮ እርሱን ወደ ባሕር ቢጥሎት በጸጥታ መጓዝ እንደሚችሉ ገለጠላቸው ። ባንተ በእግዚአብሔር ሰው ላይማ ይህን አናደርግም ባይሆን ዕጣ እናውጣ ተባባሉ ዕጣውም ሲወጣ ለሦስት ጊዜ ያክል በዮናስ ላይ ደረሰበት ወደ ባሕሩም ጨመሩት ወዲያውም ታላቅ ዓሳ አንበሪ ከእግዚአብሔር ታዞ ዮናስን ዋጠው መንገዱንም ከተርሴት ወደ ነነዌ ሀገር ቀየረው ነነዌም ሲደርስ ከደረቅ የብስ ላይ አውጥቶ ተፋው “ከሰው ይልቅ #የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፥ ” ፩ኛ ቆሮ ፩፥፳ ፭

ዮናስም የእግዚአብሔር ሥራ እያደነቀ ወደ ነነዌ ከተማ ገብቶ ንስሐን ፣ጾምን፣ ጸሎትን ሰበከላቸው ካልተመለሱ ግን የእሳት ዲን እንደሚበላቸውም አስጠነቀቃቸው ነነዌም ሰማች ወደ ልቧም ተመለሰች ንጉሱም ህጻናትና የሚጠቡ ልጆች ሳይቀሩ የእናታቸውን ጦት እንዳይጠቡ እንሰሳትም ቢሆኑ እስከ ሦስት ቀን ድረስ አፋቸው ታስሮ ከምግብ ተከልክለው እንዲቆዮ የጾም አዋጅ አወጀ። ከሦስት ጾም ቀናት በኃላ እግዚአብሔር ለነነዌ ምሕረትና ይቅርታ አደረገላት።
በዚህም ከሰማይ ይመጣባቸው የነበረ የእሳት ዲን ቀረላቸው ነቢዮ ዮናስም ይህው እግዚአብሔር ማራቸው እሳቱም ቀረላቸው። ስለዚህ እኔ የታለ እሳቱ ?ውሸታም እባላለው ብሎ ሰጋ እግዚአብሔር አምላክ ግን ቅዱሳኑ ዝቅ ብለው እሱ ይከብር ዘንድ ሰው አይደለምና ዮናስም አልዋሸም ባትመለሱ ይበላችሁ ዘንድ ያለው እሳት ይህቺ ነበረች ሲል ለምልክት እሳት ከሰማይ አውርዶ የነነዌን ከተማ እረጃጅም ዛፎች ጫፎቻቸውን አቃጥላ ተመልሳ እንድትሄድ አድርጓል ።


ባትመለሱ ኖሮ ወርዳ ትበላችሁ ነበር ሲል ነው። ዛሬ ዳግማዊቷ ነነዌ ኢትዮጵያ እሳቱ ወርዶ እየለበለባት ነው። ዘረኝነቱ እሳት ነው፣ የሥልጣን ሽኩቻው እሳት ነው፣ እምነት የለሽነቱ እሳት ነው... ግን ዛሬም አልተመለሰችም ዮናሶቿም ስደት፣ ሽሽትን መርጠው ከሩቁም ሆነው የወደፊቷን ይተነቢዮላት ዘንድ ወደዋል። መቆስቆስ ቀላል ነው መማገድ ግን መንደድን በኃላም አመድ መሆንን ያስከፍላል።
ተክለ ኤል ኃ/ማርያም
አ.አ ኢትዮጵያ
የካቲት፲ ፬/፳ ፲ ፫ዓ.ም
@YEAWEDIMERITE

#ዓውደ_ምሕረት የእናንተ
👇👇👇👇👇👇
👉@AwediMeherit
👉@AwediMeherit
👆👆👆👆👆👆
#በላኢ_ሰብ_እና_እሥራኤል_ዘሥጋ

በታሪክ እንደሚታወቀው እሥራኤል ዘሥጋ በግብጽ ባርነት ለ430 ዓመት ተገዝተው ነበር፡፡ እግዚአብሔርም የሲዖል ምሳሌ ከምትሆን ግብጽ በዘጠኝ ታላላቅ ተዓምራት በአሥረኛ ሞተ በኵር በአሥራ አንደኛ ስጥመተ ባሕር ግብጽን በመቅሰፍ ነጻ አውጥቷቸዋል፡፡
እስራኤል ዘሥጋ ግን ይህንን ታላቅ ውለታ በማሰብ ፈንታ አምላካቸው እግዚብሔርን አሳዘኑ ቀልጦ ለተሠራ ጣዖት ሰገዱ ሰዉለትም፡፡ ‹‹እስራኤል ሆይ ስማ እነዚህ ከግብጽ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው አሉ፡፡›› ዘጸ 32፡1-14 መዝ 105፡23
የእግዚአብሔርም ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፡፡ ያጠፋቸውም ዘንድ ከተመረጠው መስፍን ከሊቀ ነቢያት ሙሴ ጋር መከረ፡፡
‹‹ይህንን ህዝብ አየሁት እነሆ አንገተ ደንዳና ነው፡፡ አሁንም ቁጣዬ እንዲቃጠልባቸው እንዳጠፋቸውም ተወኝ፡፡ አንተ ግን ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለው፡፡›› አለው፡፡ ዘጸ 32፡9-10
ሙሴም ሕዝቡን እንዳያጠፋቸውና ከቁጣው ይመለስ ዘንድ ስለ ሕዝቡ ያማልድ ጀመር፡፡ በተለይም እግዚአብሔር ከቅዱሳኑ ከአብርሃም ከይስሐቅ እና ከያዕቆብ ጋር የገባውን ቃልኪዳን ያስብ ዘንድ ለመነ፡፡
‹‹ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደ ምድር አሸዋ አበዛዋለው፡፡ ይህችንም የተናገርኳትን ምድር ለዘራችሁ ሁሉ እሰጣለው፡፡ ለዘላለምም ይወርሷታል ብለህ በራስህ የማልክላቸውን አብርሃምንና ይስሐቅን እስራኤልንም አስብ፡፡›› አለው፡፡ ዘጸ 32፡13
እግዚአብሔርም የቅዱሳኑ ስም ተጠርቶ ሲሰማ የገባላቸውን ቃል ኪዳን አሰበ፡፡ በሕዝቡ ላይ ሊያደርገው ስለነበረው መቅሰፍት ፈጽሞ ራራላቸው፡፡ ይቅርም አላቸው፡፡
‹‹ከመረጥኳቸው ጋር ቃልኪዳኔን አደረግሁ፡፡›› ያለ አምላክ ከተመረጡት ቅዱሳን ከአብርሃም ከይስሐቅ ከያዕቆብና ከሌሎችም ቅዱሳን ጋር ቃልኪዳኑን እንዳደረገ እንዲሁ ከተመረጡ የተመረጠች ከተለዩ የተለየች ከእናታችን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያምም ጋር እንዲሁ ቃልኪዳኑን በየካቲት 16 ቀን አድርጓል፡፡
እመቤታችንም ‹‹መታሰቢያዬን የሚያደርገውን፣ በስሜ ቤተ ክርስቲያን የሚያንጸውን ፣ የተራቆተ የሚያለብሰውን፣ በሽተኛ የሚጎበኘውን፣ የተራበ የሚያበላውን፣ የተጠማ የሚያጠጣውን፣ ያዘነን የሚያረጋጋውን የተበሳጨ የሚያስደስተውን፣ መመስገኛየን የጻፈና ያጻፈ ፣ ወንድ ወይም ሴት ልጁን በስሜ የሰየመውን፣ በምመሰገንበት ቀን ዝማሬ ያቀረበውን ዓይን ያላየውን ጆሮ ያልሰማውን የሰው ኅሊና ተመራምሮ ያልደረሰበትን መልካም ዋጋ ትሰጥልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ፡፡›› ብትለው፡
ጌታም ‹‹መሃልኩ ለኪ በርዕስየ በከመ ኢይሔሱ ኪዳንየ›› ያልሽውን ሁሉ ላደርግልሽ ቃል ኪዳኔንም ልጠብቅልሽ በራሴ ማልሁልሽ በማለት የምህረት ቃል ኪዳን ገብቶላታል፡፡
የአብርሃም የይስሐቅ እና የያዕቆብ ቃልኪዳን የእግዚአብሔርን ሕልውና ለካዱ ቀልጦ ለተሠራ ጣዖት ለሠገዱ ለእስራኤል ዘሥጋ መትረፉን መጽሐፍ ቅዱስ ከነገረን በተዓምረ ማርያም ላይ ደግሞ ስምዖን በግብር ስሙ በላኢ ሰብ 70 ሰዎችን በልቶ በቃልኪዳኗ ተጠቅሞ መዳኑን ይነግረናል፡፡
እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ቃልኪዳን የማይሆነውን እንዲሆን የሚሆነን ደግሞ እንዳይሆን ያደርጋል፡፡ ያጠረውን ያስረዝማል፡፡ የረዘመውን ያሳጥራል፡፡ ኃጥኡን ያጸድቃል፡፡
ዛሬም እስራኤል ዘነፍስ የምንሆን እኛ ክርስቲያኖች በእመቤታችን ቃልኪዳን በመታመን ሀገራችን ላይ እና ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ የተቃጣውንና እየደረሰ ያለውን መከራ እርሱ በቸርነቱ ያርቅልን ዘንድ ስለ እናትህ ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ብለህ ማረን ይቅር በለን እያልን ተግተን ልንለምነው ይገባል፡፡
የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ ስም ሲነሳ በእስራኤል ዘሥጋ ላይ ያልጨከነ ለድካማቸውም የራራ አምላካችን የእናቱን ስም ጠርተን በቃልኪዳኗ ብናምለው እንደምን አይራራልንም?

(አቤኔዘር ወልደ ተክለ ሃይማኖት)

👉@AwediMeherit
👉@AwediMeherit
👉@AwediMeherit