አትሮኖስ
279K subscribers
110 photos
3 videos
41 files
457 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#የወርቅ_በርጩማውን_ፍለጋ


#ክፍል_ሦስት(የመጨረሻ ክፍል)


#በእንዳለጌታ_ከበደ


...እናቷ ቀጠሉ፡፡ « . . . እንዴት እየኖርኩ እንደሆነ ብታይልኝ! የሰፈር ሰው ያሾፍብኛል ብጤዎቻችን ሊያሳብዱኝ ደርሰዋል . . .»

«አሁን ደግሞ ምን ሆናችሁ? ማለቂያ የለው የናንተ ጣጣ!»

ገንዘብ አይደለም የጎደለብን ልጄ! ከአፍሽ
ነጥቀሽ አይደል የምታጎርሽን? ዕድሜሽን ያርዝመው እንጂ ስራ ከጀመርሽ በኋላ ሰፈርተኛ የሚቀናብን ሆነናል
ተንቀባርረን ከሰው ጋር እንቀላቀላለን በፊት የአፈር ገንፎ ይመስላሉ እያሉ ይሳለቁብን የነበሩ ሁሉ አሁን
አፋቸውን ይዘዋል፡ ዕድሜ ላንቺ!»

ጆሮዬን ቀስሬ ማዳመጤን ቀጥያለሁ:: የእናትና የልጅ የሹክሹክታ ድምፅ፡፡

ከየጣሪያው ስር ስንት አይነት አቤቱታ አለ? ስንት አይነት የተከፋ ልብ? ስንት አይነት አፅናኝ ያጣ ልቅሶ? ልብን የሚያጨልም መልሶ መላልሶ፡፡

«አጥሩን ኣሳጠርኩት:: ቤቱን አሳደስኩት:: አሁን ደግሞ ታናሽሽ ሊያገባ ነው አግዢው አላችሁኝ።ስንቱን ቀዳዳ ልሽፍን? እኔስ እማ? እኔስ! ... ለእኔስ?! »

በእንባ ሳትታጠብ አልቀረችም፡፡ ድምፅዋ ነገረኝ፡፡

«ከወንድምሽ ጋር ተጣልተናል ... ተኮራርፈናል! ባንቺ ጉዳይም ተቀያይመናል»

__«በእኔ ጉዳይ? ለምን?!»

«እህትህን ለምን ታስቸግራታለህ? . . .
ለኛ በመጨነቅ ዕድሜዋን ልትገፋ ነወይ!
· . . ስለው
"እኔ ትዳር ልመሰርት ስል ነው ወይ እንደዚህ አይነት እንድታመነታና እንዳትረዳኝ የሚያደርጋት ሃሳብ
የምታመነጨው?' ብሎ ተቆጥቶ አኮረፈ .

ዘሪቱ «እሺ አሁን እኔ ምን እንዳደርግ ነው
የምትፈልጊው?» አለች።

«የሰርግህን መሉ ወጪ እሸፍንልሃለሁ ብለሽ ደብዳቤ ጻፈለት፡፡ ቁጥርና ፊደል ታውቂበት የለ? »

«እንዴ? የወንድሜን የሰርግ ወጪ ለመሸፈንኮ ቢያንስ ሁለት ሶስት ዓመት መስራት አለብኝ ያውም የደሞዝ ጭማሪ ካገኘሁ! .. .ከየት አመጣለሁ እማ? .
በእርግጥ ታሳዝኚኛለሽ ግን ... »

አሳዘነችኝ፡፡ ይህቺ ከተወለደች ሃያ አምስት ዓመት ያስቆጠረች የማትመስል ሴት ስንት መከራ ተሸክማለች?
ቆይ ደሞዟን ...

«ለሱ አታስቢ!» አሉ እናቷ

«ለምኑ?»

«ለወንድምሽ ሰርግ ወጪ»

«ምን አዲስ ነገር ተገኝቶ ነው የማላስበው? እናንተ ሃሳባችሁን ሁሉ እኔ ጫንቃ ላይ ጥላችሁ አይደል በሰላም
ዕንቅልፋችሁን የምትለጥጡት?! መስራት
የሚገባችሁን ያህል ለመስራት ሰንፋችሁ በኔ ገንዘብ የከርሞ እቅድ ትነድፋላችሁ! ...››

« ይኸውልሽ ዘሪቱ፣ ጅማ ያሉት የቀርከሃ ሶፋ የሚሠሩ ወንድሞቼ ተደራጂበት፣ ነግጂበት ብለው የላኩልኝ ሁለት መቶ ብር አለ፡፡ ለወንድምሽ ' ለአንዳንድ
ጉዳይ ማሟያ' ብለሽ ትልኪለታለሽ፡፡ ከማግባትህ በፊት ስራ መያዝ አለብህ' ብለሽ - ገንዘቡን 'ተሳፈርበት ወደኔ
ናበት' ትይዋለሽ፡፡ ከኪስሽ እንዳወጣሽው እንጂ እኔ እንደሰጠሁሽ ወፍ እንዳይሰማ!»

አንዳንዴ የምታመነጨው ሃሳብኮ
«አይ እማዬ . . .

«ምን ላድርግ? ብቻሽን ስትለፊ እያየሁ እጄን አጣጥፌ አልቀመጥ! ... የምሰጥሽን ብር ከላክሽለት
ከተማ ገብቶ መስራት ብዙ ገንዘብ የማያስገኝ ይመስለዋል»

የተስማሙ መሰለኝ።

እኔም እፎይ ብዬ ዘሪቱ እንደማትሄድብኝ እርግጠኛ ሆኜ በባለቤቴ ሞት ምክንያት ያገኘሁትን ብር ምን መስራት እንዳለብኝ እያውጠነጠንኩ፣ የለውጥ ቀን ቅርብ
እንደሆነ አስተውዬ . . . ወደ መኝታ ቤቴ ልሄድ ስል ስልኩ ጮኸ።

ደነገጥኩ፡፡

በዚህ ሰዓት የሚደወልልኝ ከአስቴር ነው::
አስቴር ምን ሆና ይሆን? ስፈራ ስቸር ስልኩን አነሳሁት። ልክ ነኝ።

ረጅም የሆነ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ፡
«እቴትዬ!» አለችኝ:: አቤት ድምዕዋ ውስጥ ያለው ፍቅር! በናፍቆት የተሞላ ዜማ! እንደዚህች ያለችዋን እህቴን በባዕድ አገር እንድትጎሳቆል መፍቀዱ ምን ሆኜ ነው?

«ወዬ!»

‹ደወለልኝ!! »

«ጓደኛሽ?››

«አዎ! ከደቡብ አፍሪካ! ... አሳዘነኝ:: ተላቀስን፡፡

እንዳያሳስበኝ ብለ አጽናናኝ:: የተባባልነወን እፅፍልሻለሁ ... እሺ እቴትዬ!»
«አይዟችሁ ይነጋል . . .»

«እንዴት ነው እቴት ቤተሰብ አቤቱታ ማሰማት አልጀመረም? . . ባለፈው የሰራሁበትን ብር ሁሉ ለጓደኛዬ ላክሁለት፡፡ ከወላጆቹ የወረሰውን ቤት አሳድሶ በኮንትራት ለሆቴል አከራይቶት እኮ ነው፤ በደቡብ አፍሪካ አድርጎ አሜሪካ ለመግባት ስንቁን የቋጠረው! .
ስንደራጅ ቤቱን እኛ እንስራበታለን!»
:
«ይሁን እስኪ እንግዲህ . . .»

«እቴትዬ! . . . ሁልጊዜ እጠይቅሻለሁ ብዬ እየረሳሁ!»

«ምን?››

«ሰራተኛሽ ዘሪቱ አጫውታሽ ያዝናናሽኝ ያ
የወርቅ በርጩማ ነገር የት ደረሰ? ለወንድሜ ተበረከተለት?»

ተሳሳቅን::

«ለምን ጠየቅሽኝ?»

«ወደሃገር ቤት ስገባ የራሴን የወርቅ በርጩማ ለመስራት ላቤን ማፍሰስ እንዳለብኝ ይሰማኛል፡፡ በከንቱ
ምኞት የሚገኝ ሳይሆን ጠንክሮ የመስራት ውጤት ነው ያ የወርቅ በርጩማ!»

ያለችበት ሃገር ስራን አለመናቅን አስተምሯታል፡፡ ሰው ትልቅ የሚባለው ጊዜውን በተግባር መተርጎም የቻለ እንደሆነ መሆኑን ዕውቀትና ልምድ ቀስማለች።ይሄ ነው ብላ ልታሳየኝ የማትችለው ዲግሪ እንደተበረከተላትም ተረዳሁ:: ከመሪር ሕይወት የተገኘ
ዲግሪ!

«አሪፍ ሃሳብ ነው!» አልኳት!

ትንሽ ቆይታ «እቴትዬ! መርሮኛል! ትንሽ
ሰራርቼ እመጣለሁ ላብድ ጥቂት ነው የቀረኝ ..በየጊዜው የጓደኞቼ ቁጥር ሲቀንስ፣በሙቅ ውሃ ሲነፍሩ፣
ከፎቅ ሲወረወሩ አሟሟታቸው ሲከፋ እያየሁ እንዴት እንዴት ሆኜ ነው እዚህ በሰው አገር የምኖረው »
አለችኝ።

« ለምን አትመጪም? ነይ እዚህ! ዛሬ ነገ አትበይ! እኛም በስጋት አለቅንኮ! የግድ ቤተሰቦችሽ እንዲያልፍላቸው ያንቺ ህይወት ማለፍ አለበት?»

«አይ እቴትዬ! ...ዛሬ ነገ ሳትይ ነይ' አልሺኝ?
ምን ይዤ? መጥቼስ ምን ሰርቼ ልበላ?!»
«አንድ የመጣልኝን ሃሳብ ልንገርሽ?» አልኳት ለጥቂት ደቂቃ ሳሰላስል ቆይቼ።

«ምንድነው?»

«ላበድርሽ ነው! መለስተኛ ንግድ ሊያስጀምርሽ የሚችል ብር! .. ጓደኛሽ በውርስ ያገኘውን ቤት ወደ
ንግድ ተቋም የመለወጥ ዕቅድ አላችሁ አይደል? እረዳችኋለሁ!»

«ከየት አምጥተሽ?» እንደተገረመች ያስታውቃል::

«ለማንም እንዳትነግሪ! . . . ቤተሰብም ቢሆን እንዳያውቀው! ባለቤቴ ይሰራበት የነበረው ድርጅት ኢንሹራንስ ከፍሎኛል፡፡ ስለዚህ እሰጥሽና - ገንዘቡን
ትሰሪበትና - ዕቁብ ገብተሽ ትከፍይኛለሽ .. .»

«አይ እቴትዬ!» ከድምፅዋ ሃሳቤን እንደወደደችው ያስታውቃል፡፡

ስልኩን ከዘጋሁት በኋላ ነው፣ መፍትሄውን
የኮረጅኩት ከዘሪቱና ከእናቷ እንደሆነ የታወሰኝ!

በተገማሸረ መስክ ውስጥ እንደሚብሰከሰክ ውሃ
. . እፎይ ብላ የተረጋጋች የምትመስለዋ
ህይወታችን መንቀሳቀስ የምትጀምርበት ቀን ሩቅ እንደማይሆን ተሰማኝ፡፡
የዛሬዋን ማታ ወደድኳት፡፡

💫አለቀ💫

ለአስተያየቶ @atronosebot ን ይጠቀሙ መልካም ምሽት። 🙏
👍2