አትሮኖስ
279K subscribers
110 photos
3 videos
41 files
460 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#ሁቱትሲ


#ምዕራፍ_አስራ_አምስት


#የወጣቷ_ልብ_አንጠልጣይ_ትውስታዎች

#ትርጉም_በመዝምር_ግርማ


#ወደ_አማጽያኑ_የሚወስደው_መንገድ


በነሃሴ መጨረሻ በአንድ ሞቃት ከሰዓት በኋላ የፈረንሳዩ መኰንን ምሽጉን ለቀን ልንሄድ እንደሆነ ነገረኝ፡፡ ዘመቻ ቱርኮይዝ ተጠናቀቀ፣ ስለሆነም ፈረንሳውያኑ ከሩዋንዳ ለመውጣት ይዘገጃጃሉ፡፡ ‹‹ምሽጋችንን ዛሬ እንዘጋለን›› አለኝ፡፡ ‹‹በሁለት ሰዓታት ውስጥ ሁሉም ሰው ይህን ምሽግ ለቆ እንዲወጣ ይዘገጃጅ፡፡››
‹‹የት ነው የምንሄደው?›› ስል ጠየቅሁት፡፡ ‹‹እዚህ ሰላሳ ሰዎች አሉ… የት ሂዱ ልበላቸው? ቤት የለንም!›› በድንገተኛው ዜና ተገረምኩ፡፡
‹‹ሁላችሁንም ከቱትሲ ወታደሮች ጋር እንድትቆዩ ልንወስዳችሁ ነው፡፡ ሩአግ ወደ አካባቢው የተጠጋ ሲሆን ካለንበት ስፍራ የተወሰኑ ኪሎሜትሮች ራቅ ብሎም ምሽግ
አቋቁሟል፡፡ እዚያ ወስደን ለእነርሱ እንሰጣችኋለን፡፡ ከራሳችሁ ሰዎች ጋር መሆኑ ይሻላችኋል፡፡››
የቱትሲ ወታደሮቹ በመጨረሻ ወደኛ እየተዋጉ መምጣታቸውንና ኢንተርሃምዌዎችን ከሀገር እያስወጡ መሆናቸውን በመስማቴ ተደሰትኩ፡፡ ጀግናችን፣ የሩአጉ መሪ ፖል ካጋሜ፣ በኪጋሊ አዲስ መንግሥት ማቋቋሙን ሳይቀር ሰማሁ፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን በመጨረሻም ሰላም አገኘን - ያች ቀን ደረሰች፤ የዘር ጭፍጨፋው መቆሙ ነው!
መሄዳችን መሆኑን በምሽጉ እየተዘዋወርኩ ለእያንዳንዱ ሰው ተናገርኩ፡፡ በቅርቡ ከመጡት አንዳንዶቹ ተጠራጠሩ፤ ፈረንሳውያኑ የማይታመኑና የስደተኛ መጠለያውን ያዘጋጁትም የዘር ጭፍጨፋውን ያስተባበሩትን ሁቱዎች በኪቩ ሐይቅ የማሻገርና ከሩዋንዳ በደኅና የማስወጣት እውነተኛ ተልዕኳቸውን ለመሸፈን እንደ ሰብዓዊ መከላከያ አድርገው ለመጠቀም ነው ሲሉ ተናገሩ፡፡
‹‹ይህን እንኳን አላምንም›› አልኳቸው፡፡ ‹‹ፈረንሳውያኑ ለሳምንታት በደኅና ይዘውን ከርመዋል፤ ነጻ ሊያወጡንም ትንሽ ነው የቀራቸው! እናደርጋለን ያሉትን ሁሉ እያደረጉልን ነው፡፡››
በተጠንቀቅ ስለሆንን ለመዘገጃጀት ጊዜ አልወሰደብንም፡፡ ጓዝ ብሎ ነገር ያለው ስደተኛ የለም፡፡ በመሆኑም የምንሸክፈው ኮተት የለንም፡፡ ያሉኝን ጥቂት ንብረቶች ሰባሰብኩ - የቄስ ሙሪንዚ ልጅ የሰጠችኝን ሹራቤንና ፎጣዬን፣ ፒየር የሰጠኝን ሁለት መጻሕፍትና የተወሰኑ ወታደሮቹ የሰጡኝን ትርፍ ሳሙናዎችና ቲሸርቶችን በከረጢት አደረግሁ፡፡ ይህን ሳደርግ ግን እናቴ ገዳዮቹ በቤታችን አካባቢ እንደተሰበሰቡ እቃዎቿን በሻንጣዎች ስትከት የነበረው ትዝ አለኝና ካለፈው ሕይወቴ እቃዎችን ወደ አዲሱ ሕይወቴ ማንኳተት እንደሌለብኝ ወሰንኩ፡፡ በሁለቱ ሕይወቶቼ መካከል ንጹሕ መለያያ ለማድረግ ወሰንኩ፡፡ ከረጢቱን አንድ ሌላ ምስኪን ቤት-አልባ ቱትሲ ያገኘው ዘንድ በመመኘት ወደ መማሪያ ክፍሉ ወስጄ ጥጋት ላይ ተውኩት፡፡ ልሄድ ዘወር ስል በሩ ላይ ከቆመው ከፒየር ጋር ድንገት ግጥምጥም አልን፡፡ በሐዘኔታ አየኝና አንዲት ወረቀት ሰጠኝ፡፡ ‹‹እንዲያው ምናልባት ሐሳብሽን ከቀየርሽ ይህ የፈረንሳዩ አድራሻዬ ነው፡፡ በጣም እናፍቅሻለሁ፤ በልቤም አኖርሻለሁ፡፡ አምላክ በደኅና እንዲያቆይሽ እጸልያለሁ፡፡››
‹‹በል ደኅና ሁን ፒየር፡፡ እግዚአብሔር ይባርክህ›› ብልም እርሱ ግን ምላሼን እንኳን ሳይሰማ ሄዶ ኖሯል፡፡

በተሸከርካሪው ኋላ ላይ ለመውጣት የመጨረሻዋ ነኝ፡፡ የኋላ መዝጊያው ገጭ ብሎ ሲዘጋ የሸራ ከለላው እኛን ለመደበቅ ቁልቁል ተጋረደ፤ ተሽከርካሪውም ወደፊት ተንቀሳቀሰ፡፡ መቼም አሳልፌ የማልሰጠው ንብረቴን፣ አባቴ የሰጠኝን መቁጠሪያዬን፣ አወጣሁና ጸሎቴን አደረስኩበት፡፡ እግዚአብሔርን በአዲሱ መንገዳችን እንዲባርከንና ወደ ቱትሲ ወታደሮቹ በደኅና እንዲያደርሰን ጠየቅሁት፡፡
ተሸከርካሪው በግማሽ ክብ ቅርጽ የተደረደሩትን ብረት-ለበስ ተሸከርካሪዎችና ቁልቁል ጥርጊያ መንገዱን አልፎ ወደ ገዳዮች ባሕር ሰጠመ! ሸራው ላይ ባለች ትንሽ ቀዳዳ አጮልቄ በሺዎች የሚቆጠሩ ሁቱዎች በዋናው መንገድ ወደ ኪቩ ሐይቅ ሲተሙ አየሁ - ከመካከላቸው በመቶዎች የሚቆጠሩት የኢንተርሃምዌን የደንብ ልብስ ለብሰው ገጀራ ይዘዋል፡፡
‹‹ወይ አምላኬ›› አልኩ ተሸከርካሪው ላይ እንደገና ወድቄ፡፡ ‹‹ድጋሚ አያምጣው!›› ሁቱዎቹ መንገድ እንዲለቁና እንዲያሳልፉን የተሸከርካሪውን ጡሩንባ እየነፋን በተጨናነቀው መንገድ እናዘግም ገባን፡፡ ኢንተርሃምዌዎቹ ካስቆሙን ወይም ተሸከርካሪያችን ከተበላሸ በደቂቃዎች ውስጥ ይረባረቡብናል፡፡ መታጠቢያ ቤቱን ለቅቄ ከወጣሁ ወዲህ ይህን ያህል ፈርቼ አላውቅም፡፡
‹‹እባክህ አምላኬ›› ስል ጸለይኩ፡፡ ‹‹ይህን ያህል አምጥተኸናል - አሁን ቀሪውንም ጎዳና ውሰደን! እነዚህን ገዳዮችም አሳውርልን … እዚህ ተሸከርካሪ ጀርባ ላይ እንዲያዩ አታድርጋቸው፡፡ መሐሪው ጌታ ሆይ! ከነዚህ ጥላቻ ከተሞላባቸው ዓይኖቻቸው ሰውረን!››
ወደ ሩአግ ምሽግ ከሚወስደን መንገዳችን ከግማሽ በላይ እንደሄድን ተሸከርካሪው ቆመ፡፡ ፈረንሳዊው መኰንን ወደ ኋላ መጥቶ ሸራውን ገለጠና ‹‹በአካባቢው ተኩስ አለ የሚል ወሬ ደርሶናል፤ ስለሆነም በማናቸውም ሁኔታ ቢሆን ተኩስን የማስቆም ግዴታ አለብን፡፡ ስለዚህ ልንመለስ ስለሆነ የግድ እዚህ መውረድ አለባችሁ፡፡›› አሳስቼ የሰማሁት መሰለኝ፡፡ ‹‹መልሰህ ትወስደናለህ ማለት ነው፣ አይደል?››
‹‹አይ፣ መጠለያውን ልንዘጋው ስለሆነ ብትመለሱም የምታርፉበት ስፍራ የለም፡፡ እዚህ መውረድ አለባችሁ… አሁኑኑ፡፡ ይቅርታ እንግዲህ ኢማኪዩሌ፡፡›› ባለፉት ጥቂት ሳምንታት መኰንኑን በደንብ አውቄዋለሁ፡፡ ሁቱ ገዳዮችን ስለሚጠላ ቱትሲዎችን በተቻለው መጠን ለመርዳት እንደሚፈልግ ተናግሯል፤ ስለሆነም በታጠቁ ኢንተርሃምዌዎች እጅ ሊጥለን ነው ብዬ ላምን አልቻልኩም፡፡ እርሱን ለማሳመን ከተሽከርካሪው ወረድኩ፡፡ ‹‹እባክህ፣ መኰንን ሆይ፣ እዚህ ከተውከን ምን እንደሚከሰትብን ከማንም በላይ ታውቃለህ፡፡ በዙሪያችን ገዳዮቹ እያንዣበቡ ነው! እባክህ ተለመነኝ … የሩአግ ምሽግ ከዚህ በኋላ ግፋ ቢል አንድ ኪሎሜትር ስለሚርቅ እባክህ እዚያ አድርሰን፤ አሊያም መልሰህ ውሰደን … እዚህ ለእርድ አትተወን!››
‹‹ይቅርታ ኢማኪዩሌ፡፡ ትዕዛዝ አለብኝ፡፡››
‹‹እባክህ መኰንን ብትወስደን ምናለ!››
‹‹አይ! ሰዎችሽን አውርጅልኝ፡፡ መሄድ አለብን፡፡››
አንድ ደርዘን ገደማ ኢንተርሃምዌዎች አሥር ጫማ በሚሆን ርቀት እየተከታተሉን፣ የምንነጋገረውን እየሰሙና ፍላጎታቸው በጣም አይሎ ስለቆሙ እየተከሰተ ያለውን ነገር ልናምን አልቻልንም፡፡ ጨነቀኝ፤ መሬቷም ዞረችብኝ፣ ለአንድ አፍታ እንኳን የማየው ነገር የቁጡ ፊቶችን ብዥታ ሆነ፡፡ ራሴን በተሸከርካሪው አንድ ጎን ላይ አረጋግቼ ቆሜ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሬት ላይ ያሉትን አስከሬኖች ምንነት አወቅሁ - መንገዱን ተከትሎ ዓይኔ እስከሚያየው ድረስ ሳማትር አስከሬኖች በየቦታው ወድቀዋል፡፡
መኰንኑን ቀና ብዬ አይቼ በዓይኖቼ ለመጨረሻ ጊዜ ተለማመጥኩት፡፡ ረብ-አልባ ነው - ወይ ፍንክች አለ፡፡ ምናልባት ቄሱና ሌሎቹ ስለ ፈረንሳውያኑ የተናገሩት ልክ ነው ማለት ነው፡፡ እውነት እዚህ የመጡት ገዳዮቹን ለመርዳት ይሆን? ይኸው በእርግጠኝነት ለሞት ሊተዉን ነው፡፡
ለጓደኞቼ ‹‹ኑ ውረዱ›› አልኳቸው፡፡ ‹‹ሁላችሁም ውረዱ … ፈረንጆቹ እዚህ ትተውን ሊሄዱ ነው፡፡››