አትሮኖስ
286K subscribers
121 photos
3 videos
41 files
568 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#ጠላፊዎቹ


#ክፍል_አንድ


#በኬንፎሌት


#ትርጉም_በወንዳየሁ_ንጉሴ


ጦርነቱ የፈነዳው በአንዱ ፀሐያማ እሁድ ቀን ነበር፡
አይሮፕላኑ እስካሁን ከተሰሩት ሁሉ የተለየ ነው፡፡ ጦርነቱ የታወጀ ቀን ስድስት ሰዓት ከሰላሳ ላይ አይሮፕላኑ ብቅ ይል ይሆን እያለ ቶም ሉተር ልቡ ተሰቅሎ ወደ ሰማይ አንጋጦ እየጠበቀ ነው።

ቶም ወሬ ለማየት ባሰፈሰፉ ሰዎች ተከቧል፡ የፓን አሜሪካን ኩባንያ ንብረት የሆነው ባህር ላይ ማረፍና መነሳት የሚችለው አይሮፕላን ሳውዝ ሃምፕተን ወደብ ላይ ሲያርፍ ይህ ዘጠነኛው ጊዜ ቢሆንም አሁንም ማራኪነቱ አልደበዘዘም፡፡ ይህ አይሮፕላን አስደናቂ በመሆኑ አገሪቱ ጦርነት
ባወጀችበት ቀን እንኳን ሰዎች እሱን ለማየት ወደሚያርፍበት ቦታ
እየተንጋጉ ነው፡፡ በዚሁ ወደብ ዳርቻ አንዳች የሚያካክሉ ሁለት መርከቦች መልህቃቸውን ጥለው ቢቆሙም እነሱን ነገሬ ያለ የለም፡፡

ታዲያ አይሮፕላኑን እየጠበቁም ቢሆን ሰዎች የሚያወሩት ስለጦርነቱ
ነው ወንዶቹ ስለታንክና መድፎች ሲያወሩ ሴቶቹ በአርምሞ ይመለከታሉ፤
ከፍቷቸዋል። ሉተር አሜሪካዊ እንደመሆኑ ፍላጎቱ ሀገሩ በጦርነቱ እጇን እንዳታስገባ ነው፡፡ ጦርነቱ የእሷ ጉዳይ አይደለም፡፡ ከዚህም በላይ ናዚዎች በኮሚኒስቶች መጨከናቸው ተገቢ ነው፡፡

ሉተር በንግድ ሥራ የሚተዳደር ሲሆን የልብስ ስፌት ፋብሪው ውስጥ የሚሰሩት ኮሚኒስቶች አንድ ወቅት ላይ ችግር ፈጥረውበት ሊያጠፉት ሁሉ ምንም አልቀራቸውም ነበር፡፡ ትዝ ሲለው በንዴት
ይንቀጠቀጣል፡፡ የአባቱ የልብስ መሸጫ መደብር በይሁዳውያን ተቀናቃኞች
አፈር ድሜ ሊበላ ነበር፡፡ ሉተር ሬይ ፓትሪያርካን በጡት አባትነት ሲይዝ
ግን ህይወቱ ባንድ ጊዜ ተለወጠ የፓትሪያርካ ሰዎች እዚህም እዚያም
አደጋ በመፍጠር ኮሚኒስቶችን ልክ ማስገባት ያውቃሉ አንዱ ከውካዋ
ኮሚኒስት እጁ በማዳወሪያ ማሽን ውስጥ ተወትፎ እንዲቀር ተደረገ፡፡ የሰራተኛ ማህበር ቀስቃሽ አባል በመኪና ተገጭቶ ህይወቱ አለፈ፡ በፋብሪካ ውስጥ ስላለው የደህንነት ደምብ መጣስ ቅሬታ ያቀረቡ ሁለት ሰዎች ቡና ቤት ውስጥ በተፈጠረ ጠብ ቆስለው የአልጋ ቁራኛ ሆኑ፡ አንዷ ችግር ፈጣሪ ቤቷ በእሳት እንዲጋይ በመደረጉ በኩባንያው ላይ ያቀረበችውን ክስ ለማንሳት
ተገደደች፡፡ ከዚህ በኋላ ሰላም ሰፈነ፡፡ ፓትሪያርካ ሂትለር የሚያውቀውን
ያውቃል፡፡ ኮሚኒስቶችን ልክ ለማስገባት እንደ በረሮ መንጋ መደምሰስ ነው::

ሉተር ይህን እያሰላሰለ እግሩን ወለሉ ላይ ይጠበጥባል፡፡ አንዲት ጀልባ
አይሮፕላኑ የሚያርፍበት የባህር ክፍል አካባቢ ለማረፍ ችግር የሚፈጥርበት
አንዳች የተንሳፈፈ ነገር እንዳለ ለማየት ወደ ቦታው በረረች፡፡ የተሰበሰበው
ሰው ይህን ሲያይ በጉጉት አጉተመተመ አይሮፕላኑ እየመጣ ነው ማለት
ነው፡፡

አይሮፕላኑን ቀድሞ ያየው አንድ ትንሽ ልጅ ነው፡፡ አጉልቶ የሚያሳይ
መነጽር ባይዝም ‹‹ያውላችሁ!›› ሲል ጮኸ፡፡ ‹‹ባህር ላይ የሚያርፈው
አይሮፕላን መጣ!›› በማለት ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ሲያመለክት ሁሉም
ዓይኑን ወደዚያው ወረወረ፡፡ ሉተር በመጀመሪያ አሞራ የመሰለ ነገር ደብዘዝ
ብሎ ታየው፡፡ በኋላ እየጎላ መጣ ‹‹ልጁ እውነቱን ነው! እውነቱን ነው!››በማለት የተሰበሰበው ህዝብ አውካካ፡፡

ፓን አሜሪካን አየር መንገድ ሰዎችን በምቾት አሳፍሮ አትላንቲክ ውቅያኖስን ማቋረጥ የሚችል ቦይንግ B 134 የተሰኘ አይሮፕላን በቦይንግ ኩባንያ አሰርቷል፤ ግዙፍ፣ ማራኪና ጉልበቱ ከፍተኛ የሆነ የአየር ላይ ቤተ መንግስት፡፡ አየር መንገዱ ስድስት አይሮፕላኖችን ያስመጣ ሲሆን ሌሎች ስድስት ደግሞ እንዲሰሩለት አዟል። በምቾትና በማራኪነት በወደቡ ላይ ከቆሙት የመንገደኛ መርከቦቹ አይተናነሱም፡፡ ነገር ግን መርከቦቹ አትላንቲክን ለማቋረጥ አራት ወይም አምስት ቀን ሲወስድባቸው ይህ ባህር ላይ ማረፍና ከባህር ላይ መነሳት የሚችል አይሮፕላን ግን ይህን ጉዞ በሃያ አራት ወይም በሰላሳ ሰዓት ያጠናቅቀዋል፡፡

ልክ ክንፍ ያለው ዓሳ ነባሪ ይመስላል› አለ ሉተር በሆዱ አይሮፕላኑ እየቀረበ ሲመጣ፡፡ ከወደ ፊቱ ሾል ያለ ግዙፍ ነው፡፡ ክንፎቹ ውስጥ ኃይለኛ
ሞተሮች ተሰክተዋል፡ አይሮፕላኑ ውሃ ላይ ሲያርፍ ሚዛኑን እንዲጠብቅ
የሚያስችሉት ከክንፎቹ በታች አጠር ወፈር ያሉ ትናንሽ ክንፎች
ተገጥመውለታል፡፡ የአይሮፕላኑ የታችኛው ክፍል እንደ ፈጣን ጀልባ
ውሃውን መሰንጠቅ እንዲያስችለው ጫፉ እንደ ቢላ የሰላ ነው፡፡

አይሮፕላኑ ፎቅና ምድር አለው፡ ሉተር ባለፈው ሳምንት ስለመጣበት
የአይሮፕላኑን ውስጣዊና ውጫዊ ገጽታ በሚገባ ያውቀዋል፡ የላይኛው ፎቅ
ፓይለቶቹንና የዕቃ ማስቀመጫ ክፍሎችን የያዘ ሲሆን የታችኛው ክፍል
ተሳፋሪዎች የሚቀመጡበት ነው፡፡ ተሳፋሪዎች የሚቀመጡባቸው ክፍሎች
በመደዳ በተደረደሩ የእንግዳ ማረፊያ ሶፋዎች የተሞሉ ናቸው፡፡ በመብል ጊዜ እነዚህ ክፍሎች ወደ መብል ቤትነት የሚለወጡ ሲሆን በመኝታ ጊዜ ደግሞ
ሶፋዎቹ እንደ አልጋ ይዘረጋሉ፡

ተሳፋሪዎቹን ከሙቀትና ከብርድ ለመጠበቅ አይሮፕላኑ ውስጡ
ተለብጧል፡ ወለሉ ወፋፍራም ምንጣፍ የተነጠፈበት ሲሆን ክፍሉ ዓይን የማይወጉ መብራቶች ተገጥመውለታል፡፡ በሃር ጨርቅ የተሸፈኑ ሶፋዎቹ
ድሎታቸው ልክ የለውም፡ የአይሮፕላኑ ግድግዳ ላይ የተገጠመው ድምጽ
ማፈኛ የሞተሮቹን ድምጽ ይውጣል፡ የአይሮፕላኑ ካፒቴን የአዛዥነት ባህሪ
የተላበሰ ሲሆን ባልደረቦቹ ደግሞ ጸዳ ያለና ማራኪ የፓን አሜሪካን አየር
መንገድ ዩኒፎርም ለብሰዋል፡፡ አስተናጋጆቹ የተሳፋሪዎቹን ፍላጎት ለማርካት ተፍ ተፍ ይላሉ፡ ምግብና መጠጥ ያለማቋረጥ ይጋዛል፡፡ ተሳፋሪዎች የጠየቁት ነገር በሙሉ ልክ በአስማት የሚመጣ እንደሆነ ሁሉ እፊታቸው ዱብ ይላል፡ እንዲህ አይነት ድሎት በቀላል ዋጋ አይገኝም፡ ተሳፋሪዎቹ አብዛኛውን ጊዜ የንጉሣውያን ቤተሰቦች፣ የፊልም ተዋናዮች፣ የትላልቅ ኮርፖሬሽኖች ኃላፊዎች እና የአገር መሪዎች ናቸው፡፡ ቶም ሉተር ከእንደነዚህ አይነት ሰዎች ጋር የሚመደብ አይደለም፡ ሀብታም ቢሆንም እዚህ ደረጃ ለመድረስ ብዙ የለፋ በመሆኑ ለድሎት ሲል ብቻ ገንዘቡን አይረጭም: ቢሆንም ራሱን ከአይሮፕላኑ ጋራ ለማለማመድ ፈልጓል፡፡
አንድ ኃያል ሰው በጣም ኃያል የሆነ አንድ አደገኛ ተግባር እንዲፈጽምለት
ውለታ ጠይቆታል፤ ለዚህ ስራው ሉተር የሚከፈለው ነገር የለም፡ ነገር ግን
ለዚህ ሰው ውለታ መዋል ከገንዘብ ይልቃል፡

ይሄ ዕቅድ ምናልባት ይሰረዝ ይሆናል፡ ሉተር ‹‹ስራውን ቀጥል››
የሚለውን የመጨረሻውን ትዕዛዝ እየጠበቀ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን አዕምሮው
ዕቅዱን ቶሎ ለመፈጸም በመጓጓትና ምነው ባልሰራሁት! ብሎ በመመኘት መካከል ይዋልልበታል፡

አይሮፕላኑ ከአፍንጫው ከፍ ከጭራው ዝቅ እያለ ወደ መሬት እየወረደ
ነው፡፡ አሁን ለማረፍ ተቃርቧል፡ ሉተር በአይሮፕላኑ እንደአዲስ ተደንቋል፡፡

ለአፍታ ያህል አይሮፕላኑ እየተንሳፈፈ ይሆን እየወደቀ ሳይለይ አንዳንዴ ደግሞ ወደ ላይ ከፍ እያለ በመጨረሻም ባህር ላይ እንደተወረወረ ዝይ እዚህም እዚያም እየነጠረና ውሃውን ሁለት ቦታ እየከፈለ ፍጥነቱን በመቀነስ ውሃው ላይ አረፈና እንደ ጀልባ ይሄድ ጀመር፡

ሉተር ትንፋሹን ውጦ ቆይቶ ስለነበር በእፎይታ ለቀቀው፡ አይሮፕላኑ ወደ መቆሚያው ተጠግቶ ቆመ፡ ሉተር ከሳምንት በፊት እዚህ ቦታ ላይ ነው ከአይሮፕላኑ የወረደው:፡ ከአፍታ በኋላ አይሮፕላኑ ከፊትና ከኋላ
በገመድ ከወደቡ ምሰሶ ጋር ይታሰራል፡
👍593👎1🔥1
#ጠላፊዎቹ


#ክፍል_ሁለት


#በኬንፎሌት


#ትርጉም_በወንዳየሁ_ንጉሴ

ጦርነቱ የታወጀው የበጋው ወቅት ማብቂያ አካባቢ በአንድ ፀሃያማና ቀለል ያለ እሁድ ነበር፡፡

የጦርነቱ ዜና ሲታወጅ ማርጋሬት ኦክሰንፎርድ ቤት ውስጥ ነበረች፡፡ወደ ቤተክርስቲያን ለመሄድ ተዘጋጂ በመባሏ ጨሳለች፡፡ ከርቀት ያለማቋረጥ
የሚሰማት የቤተክርስቲያን ደወል አሰልቺ ሆኖባታል፡ የ19 ዓመት ልጅ በመሆኗ ስለሃይማኖት የራሷን ውሳኔ መወሰን ብትችልም አባቷ ከቤተክርስቲያን እንድትቀር አይፈቅዱላትም፡፡ ከዓመት በፊት ቤተክርስቲያን መሄድ
እንደማትፈልግ ነግራቸው ነበር፡፡ እሳቸው ግን ጆሮ ዳባ ልበስ ብለዋል።

‹‹በእግዚአብሔር የማላምን መሆኔን እያወቅሁ ቤተክርስቲያን መሄድ
ማስመሰል አይመስልም ወይ?›› አለቻቸው አንድ ቀን፡፡

‹‹ጅል አትሁኚ›› አሏት አባቷ ሎርድ ኦክሰንፎርድ፡
ትልቅ ስትሆን እንደማትሄድ ለእናቷ ነገረቻቸው፡፡
‹‹ባልሽ ይጨነቅበት የኔ ማር›› አሏት እናቷ፡፡ ከዚያ ቀን በኋላ ስለዚሁ ጉዳይ ተነጋግረው ባያውቁም እሁድ በመጣ ቁጥር ማርጋሬት ጥላቻዋ
ይጠነክራል፡

እህቷና ወንድሟ ከቤት ሲወጡ ሰማች። ኤልሳቤት 21 ዓመቷ ነው፡፡ ቁመቷ የብቅል አውራጅ ሲሆን መልክ አልፈጠረባትም፡፡ በልጅነታቸው እህትማማቾቹ ምስጢረኞች ስለነበሩ አይለያዩም፡፡ ካደጉ በኋላ ግን ተራራቁ፡፡
ትምህርት የተማሩት እንደሌሎች እኩዮቻቸው ትምህርት ቤት ሄደው
ሳይሆን አስተማሪ ተቀጥሮላቸው ቤት ውስጥ ነው፡ ኤልሳቤት በጉርምስና
ጊዜ የምታራምደው የወላጆቿን ግትር ልማዳዊ አስተሳሰብ ነበር፡፡
አመለካከቷ አክራሪ ሲሆን ከመኳንንት ዘር በመገኘቷ በእጅጉ ትመካለች፡
አዳዲስ ሃሳቦችና ለውጥ ጠላቶቿ ናቸው፡፡ በአንጻሩ ማርጋሬት የእሷ ተቃራኒ ናት፡ የሴቶች መብት ተሟጋችና የሶሻሊስት ፖለቲካ አቀንቃኝ
ስትሆን ጃዝ ሙዚቃ ትወዳለች፡ ኤልሳቤት ማርጋሬት ተራማጅ አስተሳሰብ በማፍቀሯ ለወላጆቿ ታማኝ አይደለችም ብላ ታምናለች፡፡ ማርጋሬት ደግሞ በእህቷ ጅልነት ትናደዳለች፡፡ በዚህ ምክንያት የልብ ወዳጆች ባለመሆናቸው ታዝናለች፡፡ የልብ ጓደኞች ደግሞ የሏትም፡፡

የእሷ ተከታይ ፔርሲ 14 ዓመቱ ነው፡፡ ተራማጅ ሃሳቦችን ወይ አይወድ ወይ አይቃወም፡፡ በተፈጥሮው ሸረኛ ነው፡፡ የማርጋሬት አመጸኝነት ባህሪ ግን ደስ ይለዋል፡፡ በአባታቸው አምባገነንነት ሁለቱም ተጎጂዎች በመሆናቸው ይተዛዘናሉ፣ ይደጋገፋሉ፡ ማርጋሬትም ለእሱ ልዩ ፍቅር አላት፡

ሎርድና ሌዲ ኦክሰንፎርድ ቀድመው ከቤት ወጥተዋል፡፡ ሎርድ
ዥንጉርጉር ክራቫት አስረዋል፡፡ እመቤቲቱ ጸጉራቸው ቀይ፣ ዓይኖቻቸው አረንጓዴ ሲሆን ፊታቸው የገረጣ ነው፡፡ ጌቶች ጥቁር ጸጉራቸው ላይ ሽበት ጣል ጣል አድርጎባቸዋል፡ ፊታቸው ደግሞ እንደ ቲማቲም የቀላ ነው።

ኤልሳቤት የአባቷን ጥቁር ጸጉርና ቅርጸ ቢስ መልክ የያዘች ስትሆን ማርጋሬት ደግሞ የእናቷን ግርጣት ወርሳለች፡ ፔርሲ መልኩ በየጊዜው ስለሚለዋወጥ የማንን መልክ እንደሚይዝ በውል አይታወቅም:

መላው ቤተሰቡ ከግቢው ወጣና በእግር ጉዞ ጀመረ፡፡ ከቤታቸው በአንድ
ኪሎ ሜትር ርቀት ከሚገኙት አብዛኛዎቹ ቤቶችና መሬቱ በሙሉ
የአባትየው ሀብት ሲሆን ይህንን ሀብት ያገኙት ያለምንም ድካም ነው፡
በአገሪቱ ያሉት ባለመሬት ቤተሰቦች በጋብቻ በመተሳሰራቸው የፈጠሩት
ርስት ይኸው ከዘር ወደ ዘር ተላልፎ በአባትየው እጅ ገብቷል፡

በመንደሩ ውስጥ ለውስጥ ተጉዘው ከድንጋይ ጥርብ የተሰራው ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ደረሱ።
ከዚያም አባትና እናት ከፊት፣ማርጋሬትና ኤልሳቤት በመከተል ፔርሲ ደግሞ ከእነሱ ኋላ ተከታትለው
ገቡ፡ የኦክሰንፎርድን መሬት የተከራዩ ገበሬዎች በአክብሮት እጅ ነሷቸው፡
ማርጋሬት ይሄ ኋላቀር ልማድ ሲፈጸም ስታይ በእፍረት ትሽማቀቃለች፡
‹‹ሁሉም ሰው በእግዜር ፊት እኩል ነው! በይ በይ ይላታል፡፡ አንድ ቀን
ድፍረቱ ይኖራትና እዚያ ሁሉ ሰው ፊት ትናገር ይሆናል፡፡ ነገር ግን አባቷ
የሚያደርሱትን ነገር ስታስብ አስፈራት፡፡

የሰው ሁሉ አይን እየተከተላቸው ቤተክርስቲያኑ ውስጥ የቤተሰቡ መቀመጫ ጋ እንደደረሱ ፔርሲ አባቱን ‹‹ክራቫትህ ታምራለች አ
አላቸው፡፡ ማርጋሬት ይህን ስትሰማ ሳቅ አፈናት፡፡ እሷና ፔርሲ ቶሎ ቁጭ አሉና ሳቃቸው እስኪጠፋ የሚጸልዩ ለመምሰል ራሳቸውን አጎነበሱ፡
ሰባኪ ወንጌሉ ገንዘቡን በዋዛ ፈዛዛ ስላባከነውና በመጨረሻም ወደ
ቤተሰቡ ስለተመለሰው ልጅ ታሪክ አስተማሩ፡፡ ማርጋሬት ጨርጫሳው ቄስ!
በእያንዳንዱ ሰው ጭንቅላት ውስጥ ስለሚጉላላው ጦርነት ቢሰብኩ ምናለ
ስትል አሰበች፡፡

።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ለሂትለር ማስጠንቀቂያ ቢልኩለትም
ሂትለር ማስጠንቀቂያውን ከምንም ባለመቁጠሩ የጦርነቱ እወጃ የማይቀር
ሆነ፡

ማርጋሬት እንደ ጦርነት የምትፈራው ነገር የለም፡፡ የእስፓኒሽ እር በእርስ ጦርነት ፍቅረኛዋን ነጥቋታል ዓመት ያለፈው ቢሆንም ትዝ ሲላት
ትሳቀቃለች፡፡ ጦርነት ለሷ አስጨናቂ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ጦርነትን ትሻለች፡፡ ለብዙ ዓመታት በእስፓኒሽ
ጦርነት እንግሊዝ ያሳየችው ቦቅቧቃነት ያሳፍራታል
በሂትለርና በሙሶሊኒ
የታጠቁ ወሮበሎች የተመረጠውን ሶሻሊስት መንግስት ሲገለብጡ አገሯ ዳር ቆማ ተመልክታለች፡፡ በሺህ የሚቆጠሩ ሶሻሊስት ወጣቶች ከመላው አውሮፓ
ዲሞክራሲን ለመታገል ወደ ስፔን ዘምተዋል፡፡ ነገር ግን በቂ መሳሪያ አልነበራቸውም፡፡ በመላው ዓለም ያሉ ዲሞክራቲክ መንግሥታት ፊታቸውን ቢያዞሩባቸውም ወጣቶቹ ግን ህይወታቸውን ሰዉ፡፡ እንደማርጋሬት ያሉ ሴቶችም
አንገታቸውን በሃዘን ደፉ፤ እፍረትንም ተከናነቡ፡፡ ብሪታንያ ፋሺስቶችን
ተቃውማ ብትነሳ ማርጋሬት በአገሯ እንደገና እንደምትኮራ ተማመነች፡፡

የጦርነቱ አይቀሬነት ልቧ ውስጥ ሌላም ደስታ አጫረባት፡፡ የዚህ ነፃነት
የሌለውና የተጨናነቀው የቤተሰብ ህይወቷ ማብቂያ ይሆናል ስትል አሰበች፡
ይሄ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ የማይታይበት ልማዳዊና ትርጉም የለሽ አኗኗሯ
አንገቷ ጋ ደርሷል፡ ከዚህ አሰልቺና ተስፋ አስቆራጭ ማህበራዊ ሕይወት
አምልጣ ወጥታ የራሷን ህይወት ለመኖር ፈልጋለች። ነገር ግን የሚሆን
የሚሆን አልመስልሽ ብሏታል፡፡ ዕድሜዋ ገና ነው ቤተሰቧን ለቃ ለመውጣት አይፈቀደላትም፡፡ ገንዘብም የላትም፡፡ ለየትኛውም የስራ ዓይነት ደግሞ ብቁ አይደለችም፡፡ ነገር ግን በጦርነት ጊዜ ሁሉ ነገር የተለየ ይሆናል ስትል አሰበች፡፡

ባለፈው ጦርነት ወቅት ሴቶች ሱሪ ታጥቀው ፋብሪካ ውስጥ እንዴት
ይሰሩ እንደነበር በአድናቆት አንብባለች፡፡ ባሁኑ ጊዜ ምድር ጦር፣ ባህር ኃይልና አየር ኃይል የሴቶች ቅርንጫፍ አላቸው፡ ማርጋሬት ምድር ጦርን
መቀላቀል ፈልጋለች፡ አንድ የምታውቀው ስራ መኪና መንዳት ብቻ ነው፡
የአባቷ ሾፌር መኪና መንዳት አስተምሯታል፡ የሞተው ፍቅረኛዋ ሞተር
ሳይክል አስነድቷታል፡ የሞተር ጀልባ መንዳት አያቅታትም፡ የምድር ጦር
መምሪያ የአምቡላንስ ሾፌሮችንና ፖስታ አመላላሽ ሞተር ሳይክል ነጂዎችን
ይፈልጋሉ፡ ዩኒፎርም ለብሳ ብረት ቆብ አድርጋ በሞተር ሳይክል ከጦር ሜዳ ወደ ጦር ሜዳ እየበረረች አገልግሎት መስጠት እንደምትችል እርግጠኛ ሆናለች፡
👍24👎1🔥1