ስንክሳር
7.32K subscribers
825 photos
4 videos
37 files
237 links
በስንክሳር channal ስንክሳሩ ተገልጦ ቅዱሳን ይዘከራሉ፣ ወቅቱን የጠበቁ መረጃዎችን ያገኛሉ፡፡ ይከታተሉን!
Download Telegram
#ቅድስት_ኄራኒ_ሐዋርያዊት_ሰማዕት
ይህቺ ቅድስት ወጣት መልክ ከደም ግባት: ምግባር
ከሃይማኖት: ስም ከመልካምነት የተባበረላት ሰማዕት
ናት:: #ኄራኒ ማለት "ሰላማዊት: የተወደደች" ማለት
ነው:: አንድም በጥሬው "ሰላምና ፍቅር" ማለት ነው::
ቅድስት ኄራኒ በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን በታናሽ
እስያ የንጉሥ #ሉክያኖስ ልጅ ናት:: ከተወለደች ጀምሮ
ስለ ክርስትና ሰምታ አታውቅም:: ምክንያቱም አባቷ
ጣዖት አምላኪ ከመሆኑ ባለፈ ክርስቲያኖችን ይቀጣ ስለ
ነበር ነው::
ልጁን ማንም እንዳያገኛት ሲል ንጉሡ ለቅድስት ኄራኒ
ቤተ መንግስት ሠራላት:: ማንም እንዳይገባ በዙሪያው
12 አጥር አጠረበት:: ጣዖቶቹን እንድታጥን
አገልጋዮችንም ሾመላት::
ምናልባት አጥር ሰውን ሊከለክለው ይችላል::
#እግዚአብሔር ግን እግዚአብሔር ነውና ምንም
አይከለክለውም:: ጌታ ደግሞ ይህቺን ወጣት ለወንጌል
አገልግሎት ይፈልጋታል:: አንድ ቀን አባቷ: ልጁ ምሑር
እንድትሆንለት አለ የተባለ ሽማግሌ ፈላስፋ ቀጠረላት::
ጥበበ እግዚአብሔር ማለት ይሔ ነው:: አባቷ ይሕ
ሽማግሌ ማንን እንደሚያመልክ አልተረዳም:: አረጋዊው
እጅግ የተዋጣለት ክርስቲያን ነው:: ግን ማንም
አያውቅበትም:: አረጋዊው ቅድስት ኄራኒን ዝም ብሎ
ሊሰብካት አልወደደም::
መጀመሪያ በስነ ምግባር አነጻት:: ቀጥሎ ግን "ጌታ ሆይ! ጐዳናህን ምራት" እያለ ይጸልይላት ገባ:: ጌታችን ልመናውን ሰምቶታልና ቅድስቷ አንድ ቀን ግሩም ራዕይን
አየች::
እርሷ ለማዕድ ተቀምጣ ሳለ: የምሥራቅና የምዕራብ
መስኮቶቿም ተከፍተው ሳሉ: በምሥራቁ መስኮት ነጭ
ርግብ በአፏ የወይራ ዝንጣፊ (ቆጽለ ዘይት) ይዛ ገባችና
ማዕዷ ላይ አኑራው ሔደች:: እርሷን ተከትሎ ደግሞ
ንስር በአፉ አክሊል ይዞ ገብቶ ማዕዷ ላይ ጥሎት ሔደ::
በ3ኛው ግን ቁራ: እባብ በአፉ ይዞ በምዕራቡ መስኮት
ገብቶ ማዕዷ ላይ ጥሎት ወጣ:: ቅድስት ኄራኒ ያየችው
ራዕይ ቢጨንቃት ሽማግሌ መምሕሯን "ተርጉምልኝ"
አለችው::
እርሱም "ልጄ ሆይ! ለዘመናት ስጠብቀው የነበረ ምኞቴን ነው ጌታ ያሳየሽ:: የሕልምሽ ትርጉም እንዲህ ነው:- ነጭ ርግብ የመንፈስ ቀዱስ (የሃይማኖት) ምሳሌ
ናት:: የወይራ ዝንጣፊው ደግሞ #ማሕተመ_ጥምቀት
( #ሜሮን ) ነው:: ቁራ የክፉ ነገሥታት ምሳሌ ሲሆን
እባብ የመከራ ምሳሌ ነው::
ንስር ድል የመንሳት ምልክት ሲሆን አክሊል ደግሞ
የመንግስተ ሰማያት ምሳሌ ነው:: ልጄ! ክርስቲያን ሆነሽ
የሚደርስብሽን ሁሉ ጌታ አሳይቶሻል" ብሎ ተርጉሞላት
ተሰናበታት::
እርሷም ወደ ምሥራቅ ዙራ ጸለየች:- "የማላውቅህ
አምላክ ሆይ! ወደ እውነትህ ምራኝ" ስትል ለመነች::
በዚያች ሰዓት የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ አጽናናት::
የሚያጠምቃትም እንደሚልክላት ነገራት::
በዚያን ጊዜ አባቷ ገብቶ "ልጄ! ከመሣፍንቱ ላንዱ ልድርሽ ስለሆነ ምን ትያለሽ?" አላት:: "3 ቀን ስጠኝ" አለችውና ሰጣት:: ወደ ጣዖቶቹ ዕለቱኑ ወርዳ "ላግባ
ወይስ ይቅርብኝ?" አለቻቸው:: ከቀድሞም በወርቅ
የተለበጡ ድንጋዮች ናቸውና ዝም አሉ:: በሙሉ ቀጥቅጣ
ሰባብራቸው ተመለሰች::
በዘመኑ #ቅዱሳን_ሐዋርያት (በተለይ እነ
#ቅዱስ_ዻውሎስ ) በሕይወተ ሥጋ ነበሩና ከቅዱስ
ዻውሎስ ደቀ መዛሙርት አንዱ ቤቷ እንደ ተዘጋ ገባ::
ክርስትናን ከጥንቱ እስከ ተፍጻሜቱ አስተምሮ አጠመቃት::
በ3ኛው ቀን አባቷ "ምን መከርሽ?" ቢላት "የእኔ ምክር
#መርዓተ_ክርስቶስ (ሰማያዊ ሙሽራ) መሆን ነው"
አለችው:: አባቷ ደነገጠ:: እጅግ ስለ ተናደደ ወደ
አደባባይ አውጥቶ: አስሮ መሬት ላይ ጣላትና በመቶ
የሚቆጠሩ ፈረሶች እንዲረግጧት አደረገ::
በወቅቱ ሰው የሚጠብቀው የአካሏን ቁርጥራጭ ነበር::
ነገር ግን ጌታ ከእርሷ ጋር ነበርና ልብሷ እንኩዋ ጭቃ
አልነካም:: አባቷ ንጉሥ ሉክያኖስና ሠራዊቱ ያዩትን
ማመን አልቻሉም:: ሁሉም ድምጻቸውን ከፍ አድርገው
"ከክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም" አሉ:: ቅድስት
ኄራኒ ምንም ሳትናገር ይህንን ሁሉ ሰው ማረከች::
ወዲያውም ንጉሡ መልእክተኛ ልኮ: የቅዱስ ዻውሎስ
ደቀ መዝሙርን አስጠርቶ: ከነ ቤተሰቦቹ ተጠመቀ::
የዚህን ዓለም ክብር ንቆም ንግሥናውን ተወ:: የጸሎት
ሰውም ሆነ:: የቅድስት ኄራኒ ተጋድሎ ግን ቀጠለ::
በአካባቢው የነበረ ንጉሥ መጥቶ የአባቷን መንግስት
ቀማ:: እርሷንም እጅግ አሰቃያት:: እርሱ አልፎ
አርማንዮስ የሚባል ንጉሥ እንዲሁ አሰቃያት:: እርሱም
አለፈ:: ከእርሱ ቀጥሎ የመጣው ንጉሥ ብዙ
መከራዎችን በእርሷ ላይ አደረሰ:: በጦርም ጐኗን ወግቶ
ገደላት::
ከጥቂት ሰዓታት በሁዋላ ግን ልክ ከእንቅልፉ
እንደሚነቃ ሰው ተነስታ ጠራችው:: በጣም ደንግጦ
"አምላክሽ አምላኬ ነው" ሲል አመነ:: ከ30,000 በላይ
ሠራዊቱን ይዞም ተጠመቀ::
ቅድስት ኄራኒ በቀረ ሕይወቷ በስብከተ ወንጌል እስያን
አድርሳለች:: ጌታ አብርቶላት: እርሷም አብርታ: እልፍ
ፍሬን አፍርታ: በዚህች ቀን ዐርፋለች:: የሐዋርያትንም:
የሰማዕታትንም አክሊል ተቀዳጅታለች::
#ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ
ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነ ዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር
ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል:: #ቅዱስ_ሉቃስ
ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ
ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል:: "#ዘካርያስ ካህኑና
#ቅድስት_ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ
ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: (ሉቃ. 1:6)
የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ
መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል!
እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው
ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ
ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90
የዘካርያስ 100 ደግሞ ደርሶ ነበር::
ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ
እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ: ትንቢት ለብቻው
የተነገረለት (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) ታላቅ ነቢይን
ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን
ላከላቸው::
ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ
ድዳ ሆነ:: ቅድስቲቷ ግን መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው
ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች:: በ6ኛው ወር የፍጥረት
ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል
#እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች::
ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው::
የአምላክ እናቱ ስትደርስና "#ሰላም " ስትላቸው መንፈስ
ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና: ዮሐንስ
ደግሞ ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ):: ከዚህ
በሁዋላ ሰኔ 30 ተወልዶ: አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው
አንደበቱ
ተፈትቶለታል::
ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ 2 ዓመት ከ6 ወር በሆነው
ጊዜ #ሰብአ_ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር
የሚገኙ ሕጻናትን ሔሮድስ ቁዝ አስፈጀ:: ትንሽ ቆይቶም
አይሁድ ለሔሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕጻን ነገሩት:: "ሲጸነስ
የአባቱን አንደበት የዘጋ: ሲወለድ ደግሞ የከፈተ
'ዮሐንስ' የሚባል ሕጻን አለና እሱንም ግደል" አሉ::
እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን
ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል::
አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕጻኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ
ለ3 (5) ዓመታት ቆይታለች:: ቅዱስ ዮሐንስ 5 (7)
ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች::
ከሰማይ ዘካርያስና # ስምዖን ወርደው ቀበሯት::
ሕጻኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ #ድንግል_ማርያም ስንት አገር
አልፋ ሰማችው:: እርሷም ስደት ላይ ነበረችና:: ከጌታ
ጋር በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው:: ጌታንም
"እንውሰደው ይሆን?" አለችው:: ጌታችን ግን
"ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ" አላት::
ባርካው: አጽናንታውም ተለያዩ::
ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በሁዋላ በዚያ ቆላ የግመል
ጠጉር ለብሶ: ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ:: ለ25
(23) ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና
ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም:: ይሕችን
ዐመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም::
ከዚህ በሁዋላ 30 ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር
ከሰማይ ተናገረው:: "ሒድ! የልጀን ጐዳና ጥረግ"
አለው:: ነቢያት ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና:: (ኢሳ.
40:3, ሚል. 3:1) አባቱ ዘካርያስም "ወአንተኒ ሕጻን
ነቢየ ልዑል ትሰመይ: እስመ ተሐውር ቅድመ
እግዚአብሔር ከመ ትጺሕ ፍኖቶ" (ሉቃ. 1:76) ብሎ
መንገድ ጠራጊነቱን ተናግሮ ነበርና::
ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ #መንፈስ_ቅዱስ
እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ:: ያዩት ሁሉ ፈሩት:
አከበሩት:: ቁመቱ ቀጥ ያለ: ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር
የወረደ: ጸጉሩ የቁራ ያህል የጠቆረ: መልኩ የተሟላ:
ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ነውና::
ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሃ ሰበከ:: ለንስሃም በርካቶችን
አጠመቃቸው:: በዚህ አገልግሎት ለ6 ወራት ቆይቶ
ጌታችን ወደ እርሱ ዘንድ መጣ:: ዮሐንስ ሰማይን
ከነግሱ: ምድርን ከነ ልብሱ የያዘ ፈጣሪ 'አጥምቀኝ'
ብሎ ሲመጣ ደነገጠ:: የሚገባበትም ጠፋው::
"እንቢ ጌታየ! አንተ አጥምቀኝ" አለው:: ጌታ ግን
"ፈቅጄልሃለሁ" አለው:: አጠመቀው:: በዚህ ምክንያት
ይሔው እስከ ዛሬም "#መጥምቀ_መለኮት " ሲባል
ይኖራል:: ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻ ሔሮድስን ገሰጸው::
ንጉሡም ተቀይሞ ለ7 ቀናት አሠረው::
በዚህች ቀንም ልደቱን ባከበረ ጊዜ ወለተ ሔሮድያዳ
በዘፈን አጥምዳ አስማለችው:: እርሱም የታላቁን ነቢይ
ራስ አስቆርጦ በወጪት አድርጐ ሰጣት:: አበው
"እምሔሶ ለሔሮድስ ይብላዕ መሐላሁ - ሔሮድስ
መሐላውን በበላ በተሻለው ነበር" ይላሉ:: የቅዱስ
ዮሐንስ ራሱ በርራ ስትሔድ አካሉን ግን ደቀ መዛሙርቱ
ቀብረውታል:: (ማቴ. 3:1, ማር. 6:14, ሉቃ. 3:1, ዮሐ.
1:6)
ርጉም ሔሮድስ አንገቱን ካስቆረጠው በሁዋላ
የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራሱ የጸጋ ክንፍ ተሰጥቷት
ጌታችን ወዳለበት #ደብረ_ዘይት ሔዳ በፊቱ ሰገደች::
#ቅዱሳን_ሐዋርያት በአዩት ነገር ተገርመው ራሱን እጅ
ነሷት::
ከዚሕ በሁዋላ ጌታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ ለቅዱስ
ዮሐንስ ራስ የማስተማር ስልጣን ሰጥቶ አሰናበታት::
በመላው ዓለም ለ15 ዓመታት ስትሰብክ ኑራ በዚህች
ቀን ዓረቢያ ውስጥ ዓርፋለች::
#ቅዱሳን_ሐዋርያት (12 ናቸው)
-----------------------------
ሊቀ ሐዋርያት ጴጥሮስ (ስምዖን)
ቅዱስ እንድርያስ (የጴጥሮስ ወንድም)
ቅዱስ ያዕቆብ ወልደ ዘብዴዎስ
ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ዘብዴዎስ
ቅዱስ ፊሊጶስ
ቅዱስ በርተሎሜዎስ
ቅዱስ ቶማስ ዘህንደኬ (ዲዲሞስ)
ቅዱስ ማቴዎስ (ቀራጭ)
ቅዱስ ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ
ቅዱስ ታዴዎስ (ልብድዮስ)
ቅዱስ ናትናኤል (ስምዖን ቀነናዊ)
ቅዱስ ማትያስ
#ቅዱሳን_ሐዋርያት (12 ናቸው)
-----------------------------