ግጥም ሲጥም - Gitem Sitem
1.85K subscribers
842 photos
55 videos
20 files
394 links
የዘመናችንን ቀለም ያሳያሉ ያልናቸውን የዚህ ትውልድ የስነ ግጥም ውጤቶችን እንጋራ - እናጋራ።
ለማካፈል የፈለጋችሁትን በGitem_Sitem ፣ gitemsitem@gmail.com የጸሃፊ ስም እና ርዕስ አክላችሁ ላኩልን።

We are all about sharing this generation's poetry. Please email us your pieces gitemsitem@gmail.com
Download Telegram
ስንል ጥቅም ጥቅም

ፍቅርን ጥርቅምቅም

ስንል ፍቅር ፍቅር

ጥቅማችን ላይ ቅርቅር

አቤቱ አድለነ

ጥቅማጥቅም ያለው

ፍቅር አዘግነነ

#ጥቅር #ሰይፈተማም
ላንቺ
#ሰይፈተማም #poeticsaturdays #ግጥምሲጥም

ከሰውነትሽ በላይ - ሰው ለመሆንሽ ክብር
ዘንባባ እንኳን ባልዘነጥፍ - ቄጤማ ፊትሽ ባልከምር
ከመንገድሽ ጋሬጣውን ባልመነጥር
እንቅፋት አልሆንብሽም - እንደው ሌላው ሌላው ቢቀር

ላንቺ

የሚገባሽ እንዲገባሽ - መስመሮቼን አነጻለሁ
በለከፈሽ እንዳይከፋሽ - መልካም አፎች እጣራለሁ
ባንቀመጥ በእኩል ሚዛን - የሰው ነገር ቢሆን ግራ
እስከማይሽ እተጋለሁ - ውጅንብሩ እንዲጠራ

ላንቺ

መሞቱን እየረሳ ሰው - ቀኑ ላይ ቀመር ሲያበዛ
የህይወት መስመር ተስታ- በጾታ ዳስ ስንገዛ
ዓለምሽ ተንቃ ሳይ - መከበርሽ ተወዛውዛ
ሳንካ አልባ ምድር ስዬ - ብራ ቀንሽን ላወዛ
ቀስቃሽ አለሁሽ ለፋፊ - እንዳትታዪ በዋዛ

ላንቺ

አቅሜን የማልለካብሽ - እንደሰው ላይሽ ሰው ሆኜ
እራሴን የማነጻልሽ - ከመንገድ ሳይሽ ሰክኜ
ለራሴ ስል የማግዝሽ - ከወንድ ጉራ መንኜ
የምነቃ በጥበብሽ - የነቁ ቃላት ሰንኜ

ላንቺ

እንደ ራስሽ ስትኖሪ - የምትችይውን ይውቁ
በሴትነት ምሽግ ከትተው - አቅምሽን እንዳይንቁ
ብርሃን ይሁን መንገድሽ
የሚመራሽም ልብሽ
የምትመሪውም እራስሽ
የልብሽ ብርሃን ፈክቶ - ድቅድቃችን ላይ ያብራ
ቀስቃሽ ነኝ ያለው ሁላ - ተቀስቅሶ ይጠራ
ተቀስቅሶ ይጣራ
ተቀስቅሶ እንዲበራ
የተፈጥሮ አካል ሆነሽ - እሱም ተፈጥሮን ይኑራ
ነጻ አውጥተሽው ደሞ - ነጻ ይሁን ከአጥሩ
ነጻ አውጥተሽው ደሞ- ባንቺው ይኩራ እንዳገሩ
ላንቺ እምር እንዳሉ - ላንቺ ይሁኑ ቀናት ሁሉ

ሰይፈ ተማም 2012
እዬዬ አልባ ሞቴ

ለራሴ አዝኜ ሳልጨርስ
ባዘንኩብሽ ቀን ሳልተክዝ
በሬን ሳልዘጋ ለእዬዬ
ሳልደበር ተበድዬ

አዬ. . .

በብርዳም ኮተታም ዓለም
ቁር ከውስጥሽ ሲፋለም
ጨለማ ጮሆ ሲንጫረር
ዝምታሽ ታሞ ሲጫፈር
ክፍተትሽ ከፍቶ ሲዛባ
ዛቢያሽ ከራሱ ሲቃባ
ማን ነበረ ያለበሰሽ - ያንን ጸዓዳ ጋቢ
እርምሽንም ባታወጪ - ከድንኳኑ እንድታድሪ
ብርዱን ችለሽ እንድትበሪ
ለቅሶኛውን እንድትመስዪ

አዪ. . .

የኔም ተራ ደረሰና
ስወድቅልሽ ከወና
ስንከባለል ዝምታ ጋር
እነጋንጩርን ሳናግር
እነጽልመትን ስጋግር
ከነ ጋኔንም ስበደር
ማን ነበረ ያሰከረኝ - በዚህ የሃቅ አረቄ
በወጉ እንኳ ሳላዝን - ከለቅሶ ቀድሞ ሳቄ
ድሮስ መቼ ለ'ኔ አውቄ

ብርቄ. . .

ለራሴ አዝኜ ሳልጨርስ
ባዘንኩብሽ ቀን ሳልተክዝ
በሬን ሳልዘጋ ለእዬዬ
ሳልደበር ተበድዬ
አዬ አዬ . . .
ይኸው ክፉ ቀን መጥቶ
ደጄም አደረ ተዘግቶ
ሞት ቢሞላው መንገዱን
እኔስ ሞትኩኝ የምለው
አንቺ ውስጥ ሞቼ እንደሆን

ድብን. . .

#ሰይፈተማም #ግጥምሲጥም #ግጥማዊቅዳሜ @poeticsaturdays @artsmailinglist
አዲስ ቅርበት

እንደ አዲስ ተዋውቀንበት
አዲስ ሰው የምናውቅበት
በቅርበት የምንረቅበት
ረቅቀን የምንኖርበት
አዲስ መርገም አዲስ በረከት

በእጅ ማንጫው ስንነጣ
ተጣጥበነው የ'ጅን ዕጣ
ቤት ከትመን ሳንወጣ
አዲስ ውረድ አዲስ ውጣ
ዛሬን ኖረን ነገም ይምጣ

እሲቲህ ባንድነት እንስከን
እሲቲ ላንድነት እንዝፈን
እሲቲህ እንግዘፍ በአዲስ ቀን
አዲስ ቅርበት ነው ያደለን
እጅ ከሚያስጥል አስጥሎን
አስተባብሮ 'ሚያረዳዳን

ቅርበት ተው ከቻልክ ቅር እቤት
ታጠቢው እጅሽ ይንጻበት
እንንጻ እንድንጸናበት
እንጽና እንድንጸናበት

ይኸው እጄን ፊት ነሳሁት
ይኸው ፊቴም እጅ ነሳ
የራቁኝን ቀረብኳቸው
የቀበርኩት ፊት ተረሳ
ምን ጉድ ነው አትበሉ ለዚህ
አዲስ መልክ ነው ጭምብሉም
ፈተና መች ችግር ሆኖ
ያው በረከት ነው መርገሙም

#ሰይፈተማም #ግጥምሲጥም #ግጥማዊቅዳሜ
እሰይ ሰውነት ገነነ
(ከሰይፈ ተማም)

ምስጋና፣ ውዳሴ፣ አርምሞ
ነፍስ በስጋ ተስሞ
ዓለም ምድሩ ቀሊል ሆነ
እሰይ ሰውነት ገነነ

ቅድስና ውስጡ እንዳለ
የሰው አይምሮ ባነነ
በአንዲት ቅጽበት እልፍ ሃሳብን
እንደጭስ እያቦነነ

መከልከልን እንኳን ለሰው
ለ'ግዜር እምቢ ያልን አመጸኛ
በቅጠል ሳንጽፍ አንሞትም
የአለም ምድሩን መዳኛ
የሳር ቅጠሉን አዱኛ

የዳመናውን ጥጥ ዳመጥን
ሰማይ አልጋችን ሆነ
ምድርን እደጊ ብለን
እንትፍ ያልንባት ዘነበ
በነጠላ ቆመን እንኳ
እኛ ብሎ ለማለት ልባችን መቼ ቦዘነ
እሰይ ሰውነት ገነነ

የዳመጥነው ተፈተለ
በውብ ተሸመነ
አማረ
በጠላት ያልወደቀ ገላ
ይኸው በጥለት ዘመነ
እሰይ ሰውነት ገነነ

እሰይ ሰውነት ገነነ
ነፍሱን ተግባባት ስጋ
'ራሱን መጠየፍ ሰጋ
ማብቀል ሆነ ያሁን ጸጋ
በጸደቀው ደምቆ ረካ
ባጸደቀው ጸድቆ ፈካ
ሰውም ከሰው ተሰካካ

እሰይ ሰውነት ሰላ
ገዘፈ ከአካል ከገላ
ተኖረ በቅጡ ሞልቶ
ተሰማ ኦባንግ ሜቶ
ተተነፈሰ ጻድቅ ቃል
እሰይ ሰው መግደል ሞቷል
እሰይ ሰውነት ገኗል

በአንዲት ቅጽበት እልፍ ሃሳብን
እንደጭስ እያቦነነ
የሰው አይምሮ ባነነ
ቅድስና ውስጡ እንዳለ

ምስጋና፣ ውዳሴ፣ አርምሞ
ነፍስ በስጋ ተስሞ
ዓለም ምድሩ ቀሊል ሆነ
እሰይ ሰውነት ገነነ

#ሰይፈተማም #ግጥምሲጥም #ግጥማዊቅዳሜ 2012

@seifetemam
በምን ሃሳብ?
በሚሞናደለው በሚሞዳሞደው
ጎረምሳውን ሁሉ አንገቱን ባስቀጨው
መዳፌን ቸብ አርገሽ ልቤን የሰቀልሽው
ምን ልሁን ብለሽነው?

ደሞ ሲያወሩብሽ የሰፈር ሰው ሁሉ
ተነኳኮሰቸው ለከፈችው አሉ
በአንዱ እያየሽኝ አንዱ መራገቡ😉
ምን ማለትሽ እንደው አይኖችሽ ያውቃሉ

. . . ምን አስበሽ ነው ግን?

ቆነጀሁኝ ብሎ እግር ማደናበር
ተኩያለሁ ብሎ አይን ማቀዣበር
ወገብ አለኝ ብሎ ቅስሞች መሰባበር
አለንጋ አለኝ ብሎ ሰው በጣት ማባረር

ምን አስበሽ ነው ግን ምን አስበሽ ነበር?

በፈገግታሽ ግለት ወደ አፍሽ መጣራት
በከንፈርሽ ቅንጦት መሳምን ማስመኘት
ጀላቲ ባረገኝ ምላስሽን ብበርዳት
ጥርስሽን ታክኬ ጣዕሜን ብትመጫት
ምን አስቤ ነው ግን?🤔

ተራራሽን አየሁ አካል ማንቀጥቀጫ
ለፓርቲ 🕺 ይመቻል ያወጡት መግለጫ
ወዮ ከምን ገባሁ🙆🙆 እንጃልኝ እኔንጃ
ይኸው ስቆም አለሁ ላንቺ መቀመጫ

ምን አስቤ ነው ግን?

ከገላሽ የጣፍሽው ጎትተሽ አይኖቼን
መዳፌን ቸብ አርገሽ የሰቀልሽው ልቤን
የምትነካኪው በጸጉርሽ ታጦቼን
በአምስተኛው አፍሽ የምትበዪው አፌን

ምን አስበሽ ነው ግን?🤔

የምታቃስችው በርሜል 🛢 እንደገፋ
የምተነፍሰው ባሉን 🎈 እንደነፋ
ላብ አደሮች ሆነን ሰርክ የምንለፋ😥
ለምንረሳሳው ለምንጠፋፋ
ምን አስበን ነው ግን?🤷

#ሰይፈተማም #ግጥምሲጥም
የፀባዖት ጣሪያ
(ከ ሰይፈ ተማም)

ከደሜ ደም ተጣብቆ
የልቤን ልብ አርቆ
ከ ́እኔ ́ በላይ ዘልቆ
በመምጠቅ ህዋ ላይ
ከዛ በላይ
መጥቆ
ሲፍለቀለቅ
ሲንዠቀዠቅ
ሲያብረቀርቅ
ሲርቅ
ሲመጥቅ
... ሲደባለቅ
አዩትና ይህን ልዩ
አዩትና ́ከኔ ́በላይ
ካለው በላይ ከበላዩ
አዩትና በእንቅልፍልብ
አዩትና ባሳብ ክልብ
አዩትና . . .
(አይ ሰው ሞኙ
ስም ወዳጁ ርዕስ ቀኙ)
. . .
ከደሜ አንጓ ተፈልቅቆ
ከ ́እኔ ́ በላይ ካጥናፍ ዘልቆ
በመምጠቅ ህዋ ላይ
ከዛ በላይ መጥቆ

ዘመን አልባ
ቅጽበት አልባ
የማይነጋ የማይጠባ
የማይተጋ የማይገባ
የማይለማ የማይሰባ
የጸጋ ለምድ የክብር ካባ
የንቁ አጸድ የፍቅር አምባ
መሻትን የማይሻ
ምሉዕ የሁሉ ድርሻ
ሰቶም እማይጎድል
ነዶም እማይከስል . . .

ያዩትን ብቻ ́'ሚያዩ
ከትውስታ ሳይለዩ
አዩትና ይሄን ልዩ
አዩትና ካ ́ለምጋራ የዘገዩ
አይተው መስሏቸው ያዩ
ጻፍልን አሉኝ ስሙን
ጻፍልን አሉ ማሰሪያ
ጻፍልን አሉ ማጠሪያ
ጻፍልን አሉ መጠሪያ
ስም ያለው ይመስል
የፀባዖት ጣሪያ

#ሰይፈተማም #ግጥምሲጥም #ግጥማዊቅዳሜ #ስነ_ግጥም
በድጋሚ የቀረበ
መንገደኛ
(ሰይፈ ተማም)

ከደመናት ቅድስናን የምቀዳ
በጉንዳን መስመር ‘ምቀና
በልቤም በ’ግሬም ‘ማቀና
ረቂቅ የመንገድ ጀግና

ከየትም ወዴት ያልመጣሁ
ካለመኖር ውስጥ ኖሬ - ከመኖር መዝገብ የታጣሁ
መጣህብኝ ባይ የሌለኝ
መንገድ ነኝ - መንገደኛ ነኝ

ካልነበረውም ወደ ነበረው መጥቼ
ያልነበረውም ሲነብር አይቼ
እርጥበት ላይ ትኩሳትን
እርኩሰት ላይ ምርቃትን
እርግበት ላይ ክርራትን
እየበተንኩ የማቀና
በጉንዳን መስመር ‘ምቀና
ረቂቅ የመንገድ ጀግና
መ ን ገ ደ ኛ

በቅድስናም ሆነ በፍልስፍና ‘ምነጉድ
‘ሚያመጣ ‘ሚወስደኝ መንገድ
የሆንኩት ሁሉ ቢሰፈር
ቢመጣ ቢሄድ ቢቀመር
ቢለካ በሰፈር ባገር
ቢመተር በቀለም በዘር
ስዘረፍ ቅኔ ወርቅ አሰር
ስታሰር ስንኝ ምቋጠር
ስቋጠርም ስንቅ ‘ምካፈል
ስካፈል አሸዋ ‘ምገረፍ
ስገረፍ ቅኝት ‘ምካረር
ንዝረት ነኝ ያውታር በገና
በጉንዳን መስመር ‘ምቀና
በልቤም በ'ግሬም 'ማቀና
ረቂቅ የመንገድ ጀግና
መ ን ገ ደ ኛ

#ሰይፈተማም #ግጥምሲጥም #ጥበብበአደባባይ #ግጥማዊቅዳሜ
#seifetemam #gitemsitem #poeticsaturdays #tba #tibeb2020 #tibebbeadebabay #digitalartfestival #artinaddis
እኔና መስከረም

ጉድን አስቀድሞ በጠባው መስከረም
መልሶ ሊሰለች ያልናፈቀ የለም
እንደ ዘማች ፋኖ ሜዳው አጎፍሮ
በአደይ ጥርሱ ሲስቅ በመላጣው አፍሮ
በዛ ባዶ ደብተር ስም እንኳን በሌለው
ስምሽን አየሸጎጥኩ ሜዳውን ስስለው
የእፉዬዋን ገላ ጆሮሽ ላይ ስሽጠው
የአምናው ትዝ እያኝ
መስከረም ናፈቀኝ

ሸተተኝ ጠረኑ የምሳቃው አይነት
ዶሮና አጥንቱ ተባብረው የሞሉት
ታየኝ ሌላ ክፍል ወስደው ሊለጥፉት
ታወቀኝ ከዴስኬ ስምሽን እንዳጠፉት

ምን ያረጋል ክረምት ምንያረጋል ብርዱ
ፈገግታሽ የላቸው ካርታና ገመዱ
ሽልጦና አርጩሜ
ታላቅ ፊልም ድጋሚ
ድጋሚው ድጋሚ

አንቺን ናፍቋል መሰል ሰማዩም ያለቅሳል
ቀኑ ረጃጅም ነው ለጨዋታ ያንሳል
አሁን የዝናብ ነው ጭቃ የነገሰበት
አንቺ ከቤት ስትውይ እኔ ትምርት ቤት
ከበጋው ግፋችን የምንማርበት

... የክረምት ትምህርት...

በአይኔ ለወደድኩሽ ሌላ ደርቤበት
ላንቺ የቀለድኩት ቲቲን እያሳቃት
ሳሩም አደገብን ሊደብቀን ሻተ
ጭቃው አዳለጠን ዋንጫችን ወለቀ
ይህ አሮጌ ደብተር ገጹ መጀመሪያ
ስምሽ ተስሎበት ከሜዳው ሳር ጉያ
የክረምቱን ሳልስል የክረምቱን ሳልፅፍ
ነሐሴ መጣና ጿሚ ሆኜው እርፍ

አንቺን ናፍቋል መሰል ሰማዩም ያለቅሳል
ቀኑ ረጃጅም ነው ለጨዋታ ያንሳል
አሁን የዝናብ ነው ጭቃ የነገሰበት
አንቺ ከቤት ስትውይ እኔ ትምርት ቤት
ከአዘቦት ግፋችን የምንማርበት

... የሰንበት ትምህርት...

ነጠላ አጣፍቼ ሳንቲም እያጋኘሁ
120ን ትቼ ቤተስኪያን ተገኘሁ
ይቺ ህይወት ናታ ወስዳ ያሳለመችኝ
ደጀ ሰላም ጠርታ ደሞ እያሳመችኝ
ደሞ የቆረበች ለት አፏን ነጠላ አምቆ
ያለችኝንም አልሰማሁ ከንፈሯ ካይኔ እርቆ
ደብተሬም የመዝሙር እንጂ የውዳሴያት ማህደር
በራጅ ላስቲክ ያሸኳት ቢሳልም ሰማዕት ነበር

መስከረም አትምጣ አትጥባ ግዴለም
ደብተሬ በላስቲክ ገና አልተሸፈነም
አይኔ አይኖቿን ሊያይ ድፍረት አላገኘም
ቀለም ጨርሻለሁ አበባ መሳያ
ቀለም ጨርሻለሁ ግጥም ማሳመሪያ
በቀረች ብያለሁ አበባ አየሽ ባዯ
🎤
አበባ አየሽ ወይ - የወር
አበባ አየሽ ወይ - የወር

የሷን አበባ ለወር የኔን ለዓመት አርገህ
ወዲያው ለሚያረጅ ነገር አታምጣ ቀኑን አድሰህ
... ክፍላችንን ለይተህ

አንተም ቀንህ አልፎ
ጊዜህ ተንጠፍጥፎ
እንዳልነበር ውሉ የሚለየን የለም
ዘመን ሲወነጨፍ ሌላ ሚሊኒየም
ብዙ ጉድ ሰምተናል ና ጥባ ግዴለም
ና ግባ መስከረም

አንቺን ናፍቋል መሰል ሰማዩም ያለቅሳል
ቀኑ ረጃጅም ነው ለጨዋታ ያንሳል
ለፀሀይ ቀርቤ ማውጋቱም ናፍቆኛል
ልቃጠል ልንደደው የጉድ ቀን ባይነጋም
ብርድ እያሳበቡ ሰለቸኝ መስከርም
ናፈቀኝ መስከረም
ምንቸቱን ቀይረው
መቼቱን ቀይረው
ለአዲስ ቀን አልሰጋም
ለአዲስ ቀን አልሰጋም

ሰይፈ ተማም 2010

#ሰይፈተማም #ግጥምሲጥም #ግጥማዊቅዳሜ
ለአቃጣይ ከመንደድ

...ቢወቅሱት ላይሰላ
የማይቆርጥ ቢላ
ማሸት ነው መሞረድ
የማቅኛም መንገድ ነው
አንዳንዴም ማንጋደድ

ሰይፈ ተማም 2009

#ሰይፈተማም #ግጥምሲጥም #ግጥማዊቅዳሜ
ምህረት
--------
(ለ ኒኪ ጂዮቫኒ)
ሸረሪቷን ግደላት እንጂ አለችኝ
ግና መግደል ቢሰቅቀኝ
የሰላም መንጃ ተቸረኝ

አሮጌ ጣሳ ደፍቼ
ብጣሽ ጨርቅ ላይ ዘግቼ
የያዝኳትን የነፍሳት ነፍስ
ወደ ውጪ ለቀኳት
በነጻነት እንድትነፍስ
አለም ምድሯን እንድታስስ

ማንም ላይ ባልደርስም እንኳን
ድንገት ከተገኘሁኝ በማይገባኝ ድንኳን
ሩሄን እያሰነበትኩ ያለቦታዬ ብከሰት
ባልታሰብኩበት ቦታ በማይገባኝ ሰዓት

እላለሁ 'አቤቱ ምኞቴን አደራ'
ሸረሪቷን እንዳዳንኳት
ለእኔም ቀን ም’ረትን ስራ

ሩዲ ፍራንሲስኮ (ትርጉም፦ ሰይፈ ተማም)
ሂሊየም

#ሩዲ #ሰይፈተማም #ግጥምሲጥም #ግጥማዊቅዳሜ
አይ ባልና ሚስት!

ጥንትማ ከአንድ ወንዝ ይቀዱ ነበረ
የኔና ያንቺ ግን መልኩ ተቀየረ
የትዳራችን ቅል ይዞት ክፉ አባዜ
አንቺን ከዓባይ ቀዳሽ እኔን ከተከዜ

ሰይፈ ተማም 1999
#ሰይፈተማም #ግጥማዊቅዳሜ #ግጥምሲጥም
እንዴትም
----------
እንዴት ናችሁ ላላችሁን
አለን አንደምጥ ስቀን
በማይለቅ ጉንፋን ታፍነን
የማያልቅ ንፍጥ ተናፍጠን
የማያልቅ ነፍጥ ተናፍጠን
ወደራሳችን ደግነን
...
እንዴት ናችሁ ላላችሁ
እንዴት እንመልስላችሁ
'አለን' ለማለት ፈርተን
ያለን መስሎን የሌለን
የሌለን መስሎን አለን
አይባል ነገር ለሰው
አንዴት ናችሁም ያሉን
መቼም ያለን መስለን ነው
...ምን ሊውጠን ልንል ስንል
ምን ልንውጥ ነው 'ምንል
ምኑን እንዴት ነህ ይባላል
ሊጥ መጥለቂያ የራስ ቅል

ሰይፈ ተማም 2009
#ሰይፈተማም #ግጥምሲጥም #ግጥማዊቅዳሜ
የመኖር ልክሽ አዙሪት

የታል አምሳያሽ
ምትክ እና ልክ የሚሆንሽ
ምንስ ብለው ሲጠሩሽ
አንቺን
እራስሽን
ነሽ?

በምን ይለካል መኖር በድህነት ከብሮ ከብዶ
በምን ይጸድቃል ካህን በሼኪው ልጅ ፍቅር አብዶ
እንዴት ይመቸው ሴጣን ብርሃንሽ ላይ ጸዳል በዝቶ
እንዴት ይዝለቀው ብርሃን ጽልመትሽ ላይ ሞት በርክቶ

ቢሸፍን ቢከልል አንቺን ችሎ የሚደብቅ
የትኛው ጋራ ነው የትኛው መቀመቅ
ደሞስ ያልታየ ሁሉ እንደሌለ ተቆጥሮ
ስለታየም ደሞ ብቻ የሌለው አለ ተብሎ
መኖርና ማኖር በተምታቱባት ኗሪ ዓለም
ከኖሩስ እንዳንቺ ነው እንዳንቺው ደሞ ካልኖሩም

ሰይፈተማም
#ሰይፈተማም #ግጥምሲጥም #ግጥማዊቅዳሜ
ከወደድኩኝ ቆየሁ

አብዝቶ ከመታ ልቤ ተደናግጦ ከተደናበረ
ስንቱ ልብ ተስሞ
ስንቱ ተስለምልሞ
ስንቱ ድኖ ታሞ
ስንቱ ተሰበረ

ጊዜ ጥሎኝ መጣ ወዳለሁበት ቀን ባዶ እጁን አንግቦ
ከወደድኩኝ ቆየሁ የሚለውን ልቤን ሊጎበኝ አስቦ

በመኖር ዛላ ውስጥ በቀናት ስንጥር ላይ
ከመንጋጋ መሃል የተሰነቀረች የስጋ ፍንቃይ
ጎርጉሮ እያወጣ ጨጓራዬ እንዲድን ከአንጀቴ እንዳትገባ
ለዓይኖቼ ይልካል ውበትን ዘጋግኖ ለልቤ አበባ
ያማረ በሙሉ የተንቆጠቆጠ እንዴት ይወደዳል
የተወደደ እንጂ ቢዝረከረክ ሁላ ሁል ጊዜ ያምራል

በልጅነት መንገድ ከመንጻት ነጽቼ መጓዝ ከዘነጋሁ
ድፍን ነፍፍፍ ዓመቴ እንደ ልቤ ደጃፍ እኔም ከተዘጋሁ
ከተፍለቀለኩኝ ካማረብኝ በጣም ኮርኩሬ ዘልዬ
ከተሽሞነሞንኩኝ ዓለምን ‘ረስቼ ዕቃ ዕቃ ነው ብዬ
ህጻናት አቅፌ ‘ባፋቸው አውርቼ ከተኮለታተፍኩ
‘አዋቂነት’ ንቄ እልፍ ሳቅ ካደመ’ኩ ቆየሁኝ ከወደድኩ

ብዙ ጊዜ ሆነኝ ከተንተፋተፍኩኝ ሌቱ እስከሚነጋ
መቀነት ፈትቼ ወኔ ከታጠኩኝ አልጋ እስከሚናጋ
ኮረዳ ኮርጄ ውቤ ውዴ ብዬ ለምኜ አባብዬ
ፎግሬ አፏግሬ ከደረቷ መሃል እንባ አቀባብዬ
ያላትን ሰልቤ የኔን አስረክቤ ከተሞዳሞድኩኝ
እንዲሆኑ ሆኜ አይሆኑ ሳልሆነው ቆየሁ ከወደድኩኝ

ሰይፈተማም

#ሰይፈተማም #ግጥምሲጥም #ግጥማዊቅዳሜ
ብርድ አሟሟቅ

ውርጭ ነበር
ቀዝቃዛ ዓየር
ንፋስ ነገር
ብርዳም ዘገር
ቁርፍድ ቆዳዬን ተርትሮ
ስንጥር አካሌን ገፍትሮ
እኔን ከላዬ አባርሮ

ልብ የሚያፍን ምትሃት ሰውነቴን ሲነዝራት
የሚያጀግን ፍርሃት ከንፈሬን ቃል ሲነጥቃት

መድረሻ ያጣ እጄ ጣዕም ሲለቅም ተግቶ
የኦርዮን መቀነት ንጹህ ሰማይ ላይ ጎልቶ
ያገኘኋትን ሜሮፒ ይዣት ልጠፋ ስዳረስ
ክንፌ አልታዘዝ ብሎ ጨረቃ አድርሻት ስመለስ

. . . ውርጭ ነበር
ብርድ ነገር

አገላብጦ እየገረፈ ሙቀቷ ላይ ሲያምሰኝ
ቁሩን ዓየር እየሳበች ግለት ትንፋሿን ሲያምገኝ
አንዴ ተሳምኩኝ ብሎ የእጇ ቀጭ ሲወረዛ
ካይን ገባሁኝ ብሎ ልቧ ምቱን ሲያባዛ
አይኗን በቅጡ ሳላየው ጠረኗ ውስጤ ተደፋ
እሷን ካላየሁበት አይኔም ቢጠፋ ይጥፋ
ብዬ ባቀፍኳት ሰዓት
ቀዝቃዛ ዓየር ያዘለ ውርጫም ንፋስ የበዛበት
ብርዳም ነበረ ቀኑ ጥቅምት የጠቀመበት

እያነቀኝ ሲወጣ ከልቤ ውስጥ ሾላልኮ
ቀልቤ እትት ሲላት ከአቅሏ ጋር ተንሾካሽኮ
የይለፍ ቃሉን ስነግራት ጣቶቿን ቆልፌ ይዤ
ግማሽ አካሏን አንቅቼ ግማሽ አካሌን ደንዝዤ
ስትለምነኝ ስለምናት
‘ተው እንኑር’ ‘ተይ እንሙት’
‘ተው እንኑር’ ‘ተይ እንሙት’
‘ከመኖር ብዙ አለ ካለመኖር እረፍት’
‘ከመኖር ነውር አለ ካለ መኖር እፍረት’
. . . ሁሉን ቋሚ ፍጡር
በቀስት የምቀውር
ተገኘሁኝ ዛሬ አይኔን እስክታወር
ዳስሼ ስሳከር
. . . ብርድ ነበር
ውርጭ ነገር
በራድ ንፋስ ቀዝቃዛ ዓየር . . .

‘አሁን’ ከየት ተከሰተች ይሄ ሙቀት የት ነበረ
ልቦች ተጠራሩ እንጂ የታል አንዳች የደረበ?
ከቁሩ እና ከውርጩ ከስንቱ ጉድ አውጥታኝ
የተሰጠኝን ሳልጠግበው ባልተሰጠኝ ሲከፋኝ
እጄ እንደተሸለመ ለነካበት ተባርኮ
በከንፈሬ የዳበስኩት መውደጃዋን ነበር’ኮ
ምኑ ጋር ፎረሽኩና ዘልቄ ከሷ ያልገባሁ
አንዱን ሳንጨርሰው ስለ ድጋሚው ሰጋሁ

በሆነው፣ በሚሆነው እና ሊሆን ባለው መሃል ተጥጄ
ከነበልባል ነዳድ ትኩሳት ግለቷ በርጄ
እሷን ሸኝቼ ስመለስ ወደ በረዶ ቤቷ
እኔ ቤቴን አጣሁት የት አባቴ የት አባቷ

ምን ሊቆጨኝ ምን ሊቆጫት ታሪክ ጽፈን ነፍሳችን ላይ
ብርዱን ስንሞቅ ቀንቶ ሰማይ

ሰይፈ ተማም 2013

#ሰይፈተማም #ግጥምሲጥም #ግጥማዊቅዳሜ
እወቂብኝ

ከማላቃቸው መልኮች ላይ ሳቆችሽን ዘግኛለሁ
ለራሴ
በልቤ መንገዶች ላይ በእግሬ ብዙ ተጉዣለሁ
ለነፍሴ
'ምናለውና አይኗ!'
'ትቅራ!'
ብዬም ፍቅር ስቀራ. . .
ብርሃን ተምታቶብኛል
. . .
ብራ ቀኔን ብገብር ምን ይረባታል ማለቴስ
ሰማይ ልቧ ላይ ብበራ ምኗ ነዶ ምኔ ሊጤስ...?
. . .
እኔ ተወርዋሪ ነኝ
ምኔ ጋር እንደጨላለምኩ ምኑ ታወቀኝ ገና
ዥው ብዬ እስከማልፍሽ ይጎበኘኛል ወና
አንቺ ቅጽበት የምትይዢ
ቦግ ብዬ ሳልፍብሽ በብርሃኔ የምትፈዢ
ምኞት 'ምትናዘዢ
ፍቅር የምታፍዢ
እኔ ምኑ ጋር በርቼ ምኔን ጽልመት እንደወጋኝ
ምኑም ምኑም የማይገባኝ
ተወርዋሪ
በሪ
ሰይፍ ነኝ
እወቂብኝ!
እወቂብኝ!

ሰይፈ ተማም

#ሰይፈተማም #ግጥምሲጥም #ግጥማዊቅዳሜ
ሰው በሞላው ሃገር
ሰው ባረፈ ቁጥር ትንሽ እሞታለሁ
አገር 'ሚያሰድብ ያገር ሰው እያየሁ
በከሰሩ ቁጥር ትንሽ እረክሳለሁ
በሰከሩ ቁጥር ትንሽ አከስራለሁ
በረከሱ ቁጥር ትንሽ እሰክራለሁ
በከሰሱ ቁጥር ዶሴ አቀብላለሁ
ሰው በሞላው ሃገር
የሰው ያለህ እላለው

ሲመርቁኝ አሜን አልል
ሲነጅሱኝ የምነቅል
ስንቀለቀል የማልነድድ
ሳልለኮስ የምከስል

ሰው በሞላው ሃገር ያውም የረገፈ
አፈር ነካው ዘሬን ጸድቆም ተገዘፈ
ሃሳቤም ተምቧችሮ እልፍ ረፈረፈ
ሆዴም ልብ የባሰው
ልቤም ሆድ የባሰው
ሆኖት እያረፈ

ሰይፈ ተማም

#ሰይፈተማም #ግጥምሲጥም #ግጥማዊቅዳሜ