YeneTube
116K subscribers
31.6K photos
485 videos
79 files
3.91K links
መረጃዎችን ለመላክ @Fikerassefa
Download Telegram
የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ የወጣላቸው እድለኞችን ውል የማስገባትና ቁልፍ የማስረከቡ ስራ በአፋጣኝ እንዲፈፀም ማሳሰቢያ ተሰጠ!

በአዲስ አበባ በየካቲት 27-2011 ዓ.ም በተደረገው ዕጣ ማውጣት ስነ-ስርአት ዕጣ ወጥቶላቸው ውል ላልገቡ እና ቁልፍ ላልተረከቡ ባለ ዕጣዎች ውል ማስገባትና ቁልፍ ማስረከቡ በአፋጣኝ እንዲፈፀም  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሳሰበ።የከተማ አስተዳደሩ በየወቅቱ የሚነሱ የነዋሪዎቹን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ከእነዚህም ውስጥ የጋራ መኖርያ ቤቶች ጉዳይ አንዱና የህዝብ ቅሬታና አቤቱታ የበዛበት ሆኖ ቆይቷል፡፡በተደረገው ማጣራት እና የስራ  ሪፖርት መሰረት ዕጣ ወጥቶላቸው ለባለ  ዕጣዎች እጅ ያልደረሱ ቤቶች መኖራቸውን ማወቅ ተችሎአል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ40/60 እና 20/80 ፕሮግራሞች የተገነቡ ቤቶችን የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም ዕጣ ማውጣቱ  የተገለፀ ሲሆን ሆኖም ቤቶቹ በቂ የመሠረተ ልማት በሌለባቸው የማስፋፊያ አካባቢዎች በመገንባታቸው እና በሚፈለገው ልክ አጠቃላይ የሳይት ስራው በወቅቱ ባለመጠናቀቁ ለባለ እድለኞች ሳይተላለፉ መቆየታቸውን የከተማው አስተዳደር በመረዳቱ እጣ ወቶላቸው ውል ላልገቡ እና ቁልፍ ላልተረከቡ ባለ ዕጣዎች ውል ማስገባትና ቁልፍ ማስረከቡ በአፋጣኝ እንዲፈፀም አሣስበዋል።በመሆኑም በ20/80 ፕሮግራም የዕጣው አሸናፊ ሆነው ውል ላልፈጸሙ 32 ሺህ 653 ባለ እድለኞች ውል ማዋዋሉ የተጀመረ ሲሆን በቅርቡ ቁልፍ የሚረከቡ መሆኑን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ  ያመለክታል፡፡በ40/60 ፕሮግራም ከዚህ ቀደም ውል ለፈጸሙ 18 ሺህ 576 እድለኞች ቁልፍ የማስረከብ ስራ መጀመሩንም የከተማ አስተዳደሩ ለመግለጽ ይወዳል፡፡

[FBC]
@YeneTube @FikerAssefa
በኢትዮጵያ 889 ተጨማሪ ሰዎች ኮሮናቫይረስ ሲገኝባቸው፤ የ12 ሰዎች ህይወት ደግሞ አልፏል።

ባለፉት 24 ሰዓታት በተደረገ 8,115 የላቦራቶሪ ምርመራ ተጨማሪ 899 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡301 ሰዎች ሲያገግሙ 12 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።እስካሁን 1,210,933 ምርመራ ተደርጎ በአጠቃላይ 69 ሺ 709 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 28 ሺ 634 ሰዎች ያገገሙ ሲሆን የ 1,108 ሰዎች ህይወት ማለፉን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።

@YeneTube @FikerAssefa
'የሀገር መድህን ሸንጎ' እንዲመሰረት ጥሪ አቀረበ!

ራሱን የኢትዮጵያ ፌደራሊት ሐይሎች ጥምረት ብሎ የሚጠራው የሀያ ገደማ ፓርቲዎች ስብስብ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግሮች ለመፍታት ሁሉም ሐይሎች ያሳተፈ «የሀገር መድህን ሸንጎ» እንዲመሰረት ጥሪ አቀረበ፡፡ ባለፈው ዓመት በመቐለ የተመሰረተውና አሁን ላይ ለሁለት ተከፍሎ ውዝግብ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ፌደራሊስት ሐይሎች ጥምረት ሀገራዊ ምርጫ አለመካሄድና ጨምሮ በኢትዮጵያ በርካታ ዴሞክራስያዊና ሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመ ነው የሚል ሲሆን በሀገሪቱ መፃኢ ላይ አደጋ ከደቀኑ ችግሮች ለመዳን 'የፖለቲካ እስረኞች'  ተፈተው፣ ሁሉም ሀይሎች ያካተተ ንግግር እንዲጀመር ጠይቋል፡፡ በተጨማሪም የውጭ የፀጥታ ሐይሎች በኢትዮጵያ መኖራቸው ጠቅሶ በተለይም የኤርትራ መንግስት የፀጥታ ሐይሎች ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ሲል የኢትዮጵያ ፌደራሊስት ሐይሎች ጥምረት ጥሪ አቅርቧል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የጥምረቱ ሊቀ መንበር ጨምሮ ሌሎች ፓርቲዎች ያሉበት የፌደራሊት ሐይሎች ጥምረት መግለጫ ጥምረቱ አይወክልም ሲል ተቃውሞው ይገልፃል፡፡

[DW]
@YeneTube @FikerAssefa
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነገው ዕለት ለዕጩ ዳኞች ሹመት እንደሚሰጥ ይጠበቃል!

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና ለፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተመለመሉ ዕጩ ዳኞችን ነገ መስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም በሚያካሒደው ስብሰባ ይሾማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡በፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ተመልምለው በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ለሹመት ለምክር ቤቱ የሚቀርቡት ዕጩ ዳኞች ቁጥር 90 ሲሆን ከዚህ ውስጥ 40 ዕጩ ዳኞች ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት፣ 50 ዕጩ ዳኞች ደግሞ ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት እንደሚሾሙ ከፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ዕጩ ዳኞቹ የተመለመሉት ከበርካታ ተወዳዳሪዎች መካከል በጽሑፍ እና በቃለ-መጠይቅ ፈተና ተፈላጊውን የመመዘኛ መስፈርት በማሟላታቸውና የሕዝብ አስተያየትን መሠረት በማድረግ መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል፡፡

@YeneTube @FikerAssefa
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመክፈት የሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ በጅማ ዩኒቨርስቲ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ መጀመሪያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሙሉ ነጋ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመከላከል የትምህርትና ስልጠና ተቋማት መልሶ የመክፈት ሂደትና ዝግጅት በሚል ርዕስ ምክረኃሳብ አቅርበዋል፡፡በ2012 ዓ.ም የተቋረጠዉን ትምህርት በልዩ ዕቅድ ለማጠናቀቅ በሚሰሩ ስራዎችና ትምህርት ሲጀመር ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች እንዲሁም ቀደም ተብለው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የሚደረጉ ጥንቃቄዎች ምን መምሰል እንዳለባቸው በምክረሃሳባቸው ቀርቦ ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡በጉባኤው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው መች እንክፈት  ለሚለው ትክክለኛ መልስ እያንዳንዱ ዩኒቨርስቲ በዓለም የጤና ድርጅት መለኪያ መስፈርት መሰረት ደረጃውን ጠብቆ በተዘጋጀ ዝርዝር በጥልቀት የዝግጅት መጠኑ ተፈትሾ ዝግጁ ሲሆን ብቻ ነው ብለዋል፡፡  በዚያ መሰረት የተቋማት ዝግጅት ይፈተሻል።

በዳሰሳውም መሰረት መቀበል እንደሚችሉ ፍቃድ ይሰጣል ሲሉ አብራርተዋል፡፡ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ እንደገለፁት ቅድሚያ ለተመራቂዎች በመስጠት ተማሪዎችን በመከፋፈል በትንሽ ቁጥር ይጀመራል፡፡ ይህም ከሚታዩ ነገሮች እየተማርን የተማሪ ቁጥር ለመጨመር እድል ይሰጠናል ብለዋል፡፡ ዝርዝር አፈጻጸሙ በምን እንደሚመራ ከጤና ሚኒስቴር  ጋር በመሆን ፕሮቶኮል ይዘጋጃልም ብለዋል፡፡

ዩኒቨርስቲዎች የለይቶ ማቆያ ማዕከላት እንደመሆናቸው የክልል መንግስታት ስራ ይጠበቅባቸዋል። አማራጭ የኳረንቲን ቦታዎችን ማዘጋጀትም ግድ ስለሚላቸው እዚያ ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል፡፡ተማሪዎችን በማጓጓዝ ሂደት ችግር እንዳያጋጥም ከትራንስፖርት ሚኒስቴርና ጤና ሚኒስቴር  ጋር በትብብር እንሰራበታለን ብለዋል፡፡

ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎችን መልሶ ለመቀበል የሚያስችል እቅድ ካሁኑ አዘጋጅተው ከአስተዳደር ሰራተኞችና መምህራን ጋር በመወያየት የጋራ ሊያደርጉ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ የበፊቱን አሰራር ይዘን መቀጠል አንችልም፡፡ ዝግጅታችንን ተጋላጭነታችንን አውቀን ተማሪ እንቀበላለን።  አንድ ብሎክ ወይም አንድ ካምፓስ ኮቪድ 19 ቢያጋጥም ምን እናደርጋለን ከሚለው ጀምሮ በዝርዝር መስራት እና እያንዳንዱ እቅድ ያለተማሪዎች እገዛ ተፈፃሚ ስለማይሆን ወደነሱ ለማስረፅ መስራት የግድ ይለናል ብለዋል፡፡

ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ እንዳሉት ጊዜው የተማሪዎች ህብረት ኃላፊነት የሚፈተንበት  ነው። የተማሪዎች ህብረት አባላት የመፍትሄ ኃሳብ ሆናችሁ ለተፈፃሚነቱ ከዩኒቨርስቲያችሁ ጋር በትብብር እንድትሰሩ ከእናንተ ይጠበቃል፡፡ ሰላማችሁን ማስጠበቅና ለደህንነታችሁ ዘብ መቆም ለትምህርታችሁ ቀጣይነት ዋስትና ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡ ዩኒቨርስቲዎች መከፈታቸው ላይ ብቻ ሳይሆን ተመልሰው እንዳይዘጉም ጭምር የተማሪዎች ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

የጥንቃቄ ቁሳቁሶችን አስመልክቶም የትኞቹ በዩኒቨርስቲዎች ይቅረቡ የትኞቹ በተማሪዎች ይሟሉ የሚለውን ከተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ለይቶ መወሰን አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በውይይቱ ማጠቃለያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ ውይይቱ ተቋማት የት ላይ እንደሆኑ ለይተን ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ግንዛቤ ለመያዝ ታስቦ የተካሄደ ነው ብለዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሪዎች በአሁኑ ጊዜ ቁርጠኝነት የሚፈልግ የለውጥ ስራ እየሰራን እንደሆነ መገንዘብ እና በዛው መጠን መፍጠን ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡ ተማሪዎችን ወደትምህርት የመመለስ ሂደት ባለድርሻ አካላትን በተገቢው መንገድ የማቀናጀት ኃላፊነት ተወስዶ መሰራት ያለበት ጉዳይ ነውም ብለዋል፡፡

ተማሪዎችን ከመመለስና የኮቪድ 19 ለይቶ ማቆያ ቦታዎችን ከማዘጋጀት አንፃር የፌደራልም ሆነ የክልል መንግስታት እያንዳንዱ የራሱን ኃላፊነት ወስዶ እንዲሰራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ ገልፀዋል፡፡ እንደከፍተኛ ትምህርት ዓለም አቀፋዊና አገራዊ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት እናደርጋለን፡፡ ምርምር ላይ የተገኘውን እውቀት ተጠቅመን ለአገር የሚውል አድርገን መጠቀምም ይገባናል ብለዋል።ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ ስራውን በማስፈፀም ሂደት ኃላፊዎች የኮሙኒኬሽን ክፍተት እንዳይኖር በመነጋገር ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመው አመራር የሁሉ ነገር ቁልፍ እንደመሆኑ በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ነገ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ እንደሚወያይና ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል የተባለ ሲሆን ከዚያም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተቋማቱን ለመክፈት ያበቃሉ ተብለው የተቀመጡ ዝርዝሮችን በመያዝ በዩቨርስቲዎች በመገኘት ብቁ መሆን አለመሆናቸው ታይቶ አስፈላጊውን መስፈርት ካሟሉ ብቻ እንዲከፍቱ ይደረጋል ብለዋል፡፡ተማሪዎችን መልሶ ለመቀበል በሚደረግ ቅድመ ዝግጅት ወደኃላ የቀራችሁ ዩኒቨርስቲዎች ካላችሁ ፈጥናችሁ ዝግጅታችሁን አጠናቅቁ ብለው መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ጉዳዩንም እንደፕሮጀክት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለባቸው አስበዋል፡፡ከተሳታፊዎች የተለያዩ ስጋት ናቸው ተብለው የተነሱ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን በሂደት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆኖ ለመፍታት እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡

[MoSHE]
@YeneTube @FikerAssefa
ለህዳሴ ግድብ በነሐሴ ወር ከ152 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ!

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝቡ በነሐሴ ወር ብቻ ከ152 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት አስታወቀ።የፅህፈት ቤቱ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ለግድቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ቀጥሏል።በተለይ ከመጀመሪያው ውሃ ሙሌት በኋላ በየወሩ የሚደረገው ድጋፍ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው።

በነሐሴ ወር ብቻ ከ152 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን ያመለከቱት ዳይሬክተሩ ፣የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሶስተኛው ዙር ለስድስት ወር ከተሰበሰበው የ8100 ኤ ደግሞ ነሐሴን ጨምሮ ከ52 ሚሊዮን ብር በላይ ነው።ወደ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ህዝብ ደግሞ ሰብስክራይብ አድርጓል። ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ውስጥ ሐምሌ ወር ላይ የተዋጣው 119 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር እንደነበረ ጠቁመው ፣ ነሐሴ ላይ ከ152 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉ በግድቡ ዙሪያ የተፈጠረ መነቃቃት መኖሩን አመላካች ነው ብለዋል።አጠቃላይ ያለው የሕዝብ ድጋፍም በገንዘብ ሲታይ በቦንድም በስጦታም እየጨመረ መምጣቱን አመልክተዋል።

Via EPA
@YeneTube @FikerAssefa
ተማሪዎቿን ወደ ትምህርት ገበታ የመለሰችው ደቡብ አፍሪካ 500 ተማሪዎች ወደ ኳራንቲን አስገባች።

በደቡብ አፍሪካ አንድ ትምህርት ቤት የኮሮና ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ ወደ አምስት መቶ የሚጠጉ ተማሪዎች ኳረንቲን እንዲገቡ መደረጉ ተሰምቷል፡፡ በደቡብ አፍሪካ በርገርስድሮፕ በተባለች ከተማ ውስጥ በሚገኝ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡን ተከትሎ ነው አምስት መቶ የሚጠጉ ተማሪዎች ኳረንቲን እንዲገቡ የተደረጉት፡፡

የከተማዋ ባለስልጣናት እንደሚሉት ቫይረሱ ወደ ማህበረሰቡም በስፋት ሳይዛመት አልቀረም ተብሏል። ባለስልጣናቱ አክለውም ወረርሽኙ በትምህርት ቤቱ በዚህን ያህል እንዲዛመት ምክንያት የሆነው ሁለት ተማሪዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ካረጋገጡ በኋላ ለትምህርት ቤቱ ባለማሳወቃቸው ነው፡፡እንደውም በትምህርት ቤቱ ማስክ አይደረግም ፣አካላዊ እርቀትም አይጠበቅም ዋነኛው መንስኤ መሆን ያለበትም ይህ ነው በማለት ትምህርት ቤቱን ወቅሰዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

@YeneTube @FikerAssefa
የኤ.ቲ.ኤም ማሽኖቹ አዲሱን የብር ኖት እንዲያነቡ መደረጋቸውን ንግድ ባንክ አስታወቀ!

ነባሩን የብር ኖት ሲያነቡ የነበሩ የኤቲኤም ማሽኖች አዲሱን የብር ኖት ማንበብ እንዲያስችላቸው የሚያደርግ ስራ መሰራቱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ የአብስራ ከበደ ገለጹ። አዲሱ የብር ኖት በየቅርንጫፎቹ በመዳረስ ላይ እንደሆነም ተናገሩ።

ተጠባባቂ ዳይሬክተሩ አቶ የአብስራ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ አዲሱን የብር ኖት መለወጥ ከተጀመረበት ቀን አንስቶ ደንበኞች ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመምጣት እየለወጡ ይገኛሉ።አዲሱን የብር ኖት የኤ.ቲ.ኤም ማሽኖች ማንበብ እንዲችሉ ማድረግ የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ስራ በመሆኑ ነባሩን የብር ኖት ሲያነቡ የነበሩ ማሽኖች አዲሱን የብር ኖት ማንበብ እንዲችሉ የሚያስችል ስራ ተሰርቷል።በዚህም መሰረት በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ባሉት ኤ.ቲኤ.ም ማሽኖች አዲሱን ኖት መክፈል ተጀምሯል።እንደዚያም ሆኖ ነባሩን የብር ኖት መክፈል ባለማቆማችን ስራውን ጎን ለጎን በመስራት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

እንደ አቶ የአብስራ ገለጻ፤ ደንበኞች ነባሩን የብር ኖት በመመለስ ላይ ሲሆኑ፣ በተለይ ከአምስት ሺህ ብር በላይ ከሆነ አዲስ ሒሳብ ከፍተው እያስቀመጡ ይገኛሉ።የብር ኖቱ ለውጥ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ አዲስ አበባ እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ ብቻ ባሉት 320 ቅርንጫፎች ላይ አዲሱ የብር ኖት እንዲዳረስ ተደርጓል።ከዚህ ባሻገር ደግሞ በተመረጡ ስድስት የክልል ከተሞች ላይ ከብሄራዊ ባንክ ጋር በትብብር አዲሱን ኖት የማድረስና የማሰራጨት ስራ ተጀምሯል።የገንዘብ ኖቱ በበርካታ ቦታ ማለትም ገንዘብ የሚከፋፈልባቸው ቦታዎች ደርሷል ያሉት ተጠባባቂ ዳይሬክተሩ፣ ለአብነትም ጅግጂጋ፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ ባህርዳር፣ ጅማ፣ መቀሌ፣ አዳማና ሌሎችም ከተሞች ላይ በመዳረስ ላይ ይገኛል ብለዋል።በተጨማሪም ሌሎች ገጠራማ የሆኑ ስፍራዎችም በመጓጓዝ ላይ እንደሆነ አመልክተዋል።

[EPA]
@YeneTube @FikerAssefa
ምርጫውን በተመለከተ ጤና ሚኒስቴር ያቀረበውን ምክረ ሃሳብ የመረመረው ቋሚ ኮሚቴ ምርጫው በ2013 እንዲካሄድ የውሳኔ ሀሳብ አቀረበ።

የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች እና የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴዎች በጋራ የውሳኔ ሃሳቡን አቅርበዋል።ምክር ቤቱ በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ መክሮ ውሳኔው ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

Via ESAT
@YeneTube @FikerAssefa
#NewsAlert

በሀገር አቀፍ ደረጃ ትምህርት የሚጀመርበት ቀን ነገ ከቀኑ 9 ሰአት ላይ ይፋ ይደረጋል ተባለ!

የትምህርት ሚኒስቴር አመራሮች እና የክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊዎች በቀጣይ የትምህርት ሁኔታ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ ውይይት እያካሄዱ ነው።ውይይት እየተካኔደባቸው እና ውሳኔ ከሚያገኙ ጉዳዮች መካከል የመደበኛ ትምሀርት የሚጀመርበት ቀን፣የ8ኛና 12ኛ ክፍል ክልላዊ እና ሀገራዊ ፈተና የሚሰጥበት ቀን እንዲሁም በግል ትምህርት ቤቶች ላይ እየቀረቡ ባሉ ቅሬታ ላይ ውሳኔ የሚሰጥ ሲሆን።ከዚህ በተጨማሪም አዲሱ የትምህርት ስርዓት ዝግጅት አካሄድ እና ሁኔታ በውይይቱ ላይ የሚገመገም እና ውሳኔ የሚሰጠው ይሆናል። የጎልማሶች ትምህርት አሰጣጥና አፈፃፀምም በውይይቱ ውሳኔ ከሚያገኙ ጉዳዬች መካከል ነው።በውይይቱ ላይ የተደረሰውን ውሳኔም ነገ በ 9:00 ለህዝብ ይፋ የሚደረግ ይሆናል።

[MoE]
@YeneTube @FikerAssefa
ቻይና አማርኛ ቋንቋን በመጀመሪያ ዲግሪ ልታስተምር ነው!

ቻይና አማርኛ ቋንቋን በመጀመሪያ ዲግሪ ልታስተምር እንደሆነ በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ፡፡ትምህርቱ መሰጠት የጀመረበትን ይፋዊ የመክፈቻ ስነ ስርዓት የተመለከተ መረጃን በማህበራዊ ገጹ ያጋራው ኤምባሲው ትምህርቱ በቤጂንግ የውጭ ጥናት ዩኒቨርስቲ (BFSU) መሰጠት እንደጀመረ ገልጿል፡፡በስነ ስርዓቱ የኤምባሲው የሚኒስትር አማካሪ አቶ ሳሙዔል ፍጹም ብርሃን እና የዩኒቨርስቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ጂያን ውንጂን ንግግር አድርገዋል፡፡

[Alain]
@YeneTube @FikerAssefa
ምክር ቤቱ እያካሄደው ባለው በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በጠቅለይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የቀረቡትን የሚኒስትሮች ሹመት አጽድቋል፡፡

1. ዶ/ር ቀነዓ ያዴታ የኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር
2. ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ
3. ዶ/ር ሳሙኤል ሁርቃቶ የኢፌዴሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር
4. ኢንጅነር ታከለ ኡማ የኢፌደሪ ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሚኒስትር

በዚህ መሠረትም ምክር ቤቱ የቀረበውን ሹመት በአምስት ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡በተጨማሪም ምክር ቤቱ የ40 የከፍተኛ ፍርድ ቤት እጩ ዳኞችን ሹመት በ5 ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ እንዲሁም የ50 የመጀመሪያ ፍርድ ቤት እጩ ዳኞችን ሹማት ደግሞ በ3 ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ያጸደቀ ሲሆን እጩ ዳኞቹም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ አማካኝነት በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለመሃላ ፈጽመዋል፡፡

[HoPR]
@YeneTube @FikerAssefa
የበርሃ አንበጣ መንጋ በ166 ሄክታር መሬት በተዘራ ሰብል ላይ ጉዳት ማድርሱን የራያ ቆቦ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለጸ፡፡የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በበኩሉ በሰው ጉልበት እና በኬሚካል ርጭት የመከላከል ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጧል፡፡

[AMMA]
@YeneTube @FikerAssefa
በሊቦ ከምከም ወረዳ በጎርፍ መጥለቅለቅ ለተጎዱ ቀበሌዎች ድጋፍ ተደረገ!

የአማራ ክልል ቅ/አደ/መከ/ምላሽ መስጠት ከክልሉ ምግብ ዋስትና ጋር በመተባበር፤በሊቦ ከምከም ወረዳ በውሀ መጥለቅለቅ ለተጎዱ ወደኖች የሚሆን የተለያዩ ነገሮችን ማለትም 350 ኩንታል ስንዴ ፣ 1000 ሊትር የምግብ ዘይት እንዲሁም 397 ብርድ ልብሶችንና 100 የፕላስቲክ ሽቶችን ለወዳው ያበረከተ ሲሆን ይህም የወረዳው ቅ/አደ/መከ/ ምላሽ መስጠት ባለሙያዎች ባሉበት የተፈጸመ ነው፡፡

[የሊቦ ከምከም ወረዳ ኮሙኒኬሽን]
@YeneTube @FikerAssefa
ፍርድ ቤቱ አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ በ7 ግለሰቦች ላይ አቃቤ ህግ ያቀረበውን ክስ እንዲያሻሽል ትእዛዝ ሰጥቷል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የሕገ መንግስት እና የፀረ ሽብር ወንጀል ችሎት አቃቤ ህግ ከዚህ በፊት የመሰረተው ክስ አጠቃላይ ዋስትና ላይ ዝርዝር ክሱን ተመልክቶ ውሳኔ ለማሳረፍ ክሱ ሊሻሻል ይገባል ሲል አዟል።በዚህም አቃቤ ህግ የሚያሻሽለው በሰኔ 23 እና ሰኔ 24 2012 ዓ.ም በሰው ላይም በንብረት ላይም ደረሰ የተባለው ጉዳት ተለይቶ እንዲቀርብ፣ የደረሰው ጉዳት ቦታው የት እንደሆነ፣ በየት ክፍለ ከተማ እና ወረዳ፣ በስንት ሰዓት የሚለው መገለፅ አለበት ያለው ፍርድ ቤቱ፤ ቦታው ከታወቀ በኋላም የተከሳሾቹ የወንጀል ተሳትፎ በዝርዝር ተለይቶ እንዲቀርብ አዟል።

በዚህ መሰረት አቃቤ ህግ በሳምንት ውስጥ ክሱን አሻሽሎ እንዲቀርብ ለመስከረም 19 2013 ዓ.ም ጠዋት በችሎት እንዲያቀርብ አዟል።በችሎቱ የተገኙት የእነ አቶ እስክንድር 4 ጠበቆች ማረሚያ ቤት ከቤተሰብ ጋር እያገናኛቸው እንዳልሆነ፣ ምግብና ልብስም እየገባላቸው አይደለም ሲሉ አቤቱታ አቅርበዋል።ሌሎች አቤቱታዎችንም እናቅርብ ያሉት ጠበቆቹ፤ ፍርድ ቤቱ ጥያቄያችሁ በችሎት ተመዝግቦ የሚሄድ አይደለም፤ ክርክር አንዳይነሳበት ሲል ጊዜ የማይሰጡ የህክምና እና በቤተሰብ መጎብኘት ያለባቸውን ማረሚያ ቤቱ እንዲፈፅም ትእዛዝ ሰጥቷል።በተከሳሾች በኩልም የተለያዩ የመብት አቤቱታዎች ለችሎቱ አቅርበዋል።

በሌላ ዜና በእነ አቶ ጌታቸው አሰፋ የክስ መዝገብ የቀድሞ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሰራተኞች በተከሰሱበት በአዋጅ ከተሰጣቸው ስልጣን ውጪ ሰዎችን በመያዝና በማሰር ስልጣንን ያለ አግባብ መገልግል ወንጀል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ጀምሮ የነበረው ከመጋረጃ በስተ ጀርባ ምስክር የማሰማት ሂደት ቀጥሏል።

[ፋና]
@YeneTube @FikerAssefa
እምቦጭን ከነአካቴው የሚያጠፋ መድሐኒት መገኘቱ ተገለፀ።

የእምቦጭን አረም በሀገር በቀል እውቀት በመታገዝ ከነአካቴው ለማጥፋት የሚያስችል ፀረ-እምቦጭ መድሐኒት መገኘቱን የኢትዮጵያ ሊቃውንትና ምሁራን ማህበር ዛሬ በሰጠው መግለጫ አብስሯል።ይሄ በፈሳሽ መልክ የተዘጋጀ ፀረ እምቦጭ መድሐኒት በተረጨ በ24 ሰአታት ውስጥ የአምቦጭ አረምን ለማክሰም ይችላል የተባለ ሲሆን በ 30 ቀናት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ያስወግደዋል ተብሏል።መድሐኒቱ የተገኘው ስለ ዕፅዋት ከሚመራመረው ዕፀ ሕይወት የዕፅዋት ጥናትና ምርምር ማዕከል መሆኑን መግለጫውን የሰጠው የኢትዮጵያ ሊቃውንትና ምሁራን ማህበር ያስታወቀ ሲሆን መድሐኒቱን ወደ ተግባር አስገብቶ እምቦጭን በቀጣይ 3 አመታት ለማስወገድ ሕጋዊ ስምምነት ማድረጉን ገልጿል።ፀረ እምቦጭ ዕፅዋቱን ያገኘው ማዕከል መስራች መሪ ጌታ በላይ አዳሙ ዕውቀቱን የቀሰሙት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ስር ከሚገኙ ጠበብት ሊቃውንት መሆኑን በዕለቱ ተናግረዋል።

ፀረ እምቦጭ መድሐኒቱ ኦርጋኒክ በመሆኑ በሰው ላይም በስነ ፍጥረት ላይም ምንም አይነት የቀጥታም ሆነ የጎንዮሽ ጉዳት አያስከትልም ብለዋል።አረሙ ከዚህ በላይ ሳይስፋፋ በተፈለገው ፍጥነት ወደ ትግበራ ለመግባት ይረዳን ዘንድ ለምናደርጋቸው አውደ ጥናቶችና ተያያዥ ተግባራት በተለይ የመንግስት አካላትና የግል ባላሀብቶች እንዲሁም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የራሱን አስተዋፅኦ በማድረግ ከጎናችን እንዲቆም ጥሪ እናስተላልፋለን ሲል ማህበሩ መልዕክቱን አስተላልፏል።ጣና ሀይቅ 3 ሺህ 672 ኪሎ ሜትር ስፋት የነበረው ሲሆን ወደ 3 ሺህ ኪ.ሜ ወርዷል።በእምቦጭ ምክንያት፤ የሀዋሳና የዝዋይ ሀይቅ ተደምሮ የሚያክለው የሀይቁ ክፍል ወይም 125 ሺህ 579 የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳዎችን የሚያክል የቦታ ስፋት ወደ የብስነት መቀየሩን መረጃዎች ያሳያሉ።

[Ethio FM]
@YeneTube @FikerAssefa
ምክር ቤቱ 6ኛ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ ወሰነ፡፡

ምክር ቤቱ እያካሄደው ባለው 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛው አስቸኳይ ስብሰባው 6ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ የዓለም ጤና ድርጅትና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባስቀመጡት ምክረ ሀሳብ መሠረት ቫይረሱን በመከላከል ምርጫውን ማከናወን እንደሚቻል የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አበባ ዮሴፍ የውሳኔ ሃሳብ እና ሪፖርት አቅራቢ አቅርበዋል፡፡

የውሰኔ ሃሳቡም የውሳኔ ሃሳብ ቁጥር 16/2013 ሆኖ በአንድ ተቃውሞ በ8 ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡ምክር ቤቱ መስከረም 8/2013 ባካሄድው 5ኛ ዙር 3ኛ አስቸኳይ ስብሰባ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምላሽ አሰጣጥና ቀጣይ እርምጃዎች የቀረበውን ሪፖርትና ምክር ሃሳብ በዋናነት ለሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተባባሪነት ለህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መመራቱ ይታወሳል፡፡

[AMN]
@YeneTube @FikerAssefa
በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሕግ መዝገበ ቃላት ለማዘጋጀት የሚያስችል ሥምምነት ተፈረመ!

በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሕግ መዝገበ ቃላት ለማዘጋጀት የሚያስችል ሥምምነት ዛሬ ተፈረመ። ሥምምነቱን የተፈራረሙት የፌዴራል የፍትሕና የሕግ ምርምርና ሥልጠና ኢንስቲትዩት፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ጀስቲስ ፎር ኦል የተባለው ግብረ ሠናይ ድርጅት ናቸው። መዝገበ ቃላቱን ለማዘጋጀት አራት ሚሊዮን ብር በጀት የተያዘለት ሲሆን በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል። የሚዘጋጀው መዝገበ ቃላት በአማርኛ ቋንቋ ሲሆን በቀጣይ በሌሎች የአገሪቱ ቋንቋዎች የሚዘጋጅ መሆኑም ተጠቁሟል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

@YeneTube @FikerAssefa
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላኩ የቡና፣ ሻይና የቅመማ ቅመም ምርቶች 870 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ገለጸ፡፡

500 አርሶ አደሮች የቡና ምርታቸውን በቀጥታ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ፈቃድ መውሰዳቸውንም አስታውቋል።በተጠናቀቀው የ2012 በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበ 270 ሺህ 835 ቶን ቡና 854 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተርና የግብይት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሻፊ ዑመር ለኢዜአ ገልጸዋል።ከ2011 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻፀርም በመጠን ከ40 ሺህ ቶን በላይ፤ በገቢ ከ91 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብልጫ እንዳለውም ተናግረዋል።የኢትዮጵያን ቡና በመግዛት ጀርመን፣ ሳዑዲ አረቢያና አሜሪካ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

[ENA]
@YeneTube @FikerAssefa
የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ የቀድሞ የወላይታ ዞን አመራሮች የነበሩ ግለሰቦችን ጨምሮ ለ20 ተጠርጣሪዎች የተፈቀደው “ዋስትና ታግዶ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ሊሰጠኝ ይገባል” በሚል የክልሉ ፖሊስ ባቀረበው ይግባኝ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለዛሬ ከሰዓት ቀጠረ።

ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ ዛሬ ጠዋት በነበረው ውሎው በጉዳዩ ላይ ፖሊስ እና ጠበቆች ያቀረቡትን ክርክር አዳምጧል። በጠዋቱ ችሎት ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ዘጠኙ መገኘታቸውን የስድስት ተጠርጣሪዎች ጠበቃ የሆኑት አቶ ተመስገን ዋጃና ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል በመናድ ወንጀል ከተጠረጠሩት ግለሰቦች ውስጥ ባለፈው ነሐሴ ወር አጋማሽ ከስልጣናቸው የተነሱት የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ እና የዞኑ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥበቡ ዩሃንስ ይገኙበታል። ሁለቱ የቀድሞ የመንግስት ባለስልጣናት በሐዋሳ ከተማ በተካሄደው በዛሬው ችሎት አለመገኘታቸውን ለማወቅ ተችሏል።

የዛሬውን የፍርድ ቤት ሂደት በስፍራው ተገኝተው ከተከታተሉት ተጠርጣሪዎች መካከል የወላይታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሙሉነህ ወልደጻዲቅ፣ የዞኑ የፍትህ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ምህረት ቡኬ እና የወላይታ ዩኒቨርስቲ የህግ ትምህርት ክፍል ዲን አቶ ተከተል ላቤና ይጠቀሳሉ። በጠዋቱ የችሎት ውሎ ከተጠርጣሪዎች እና ጠበቆች ባሻገር የሀገር ሽማግሌዎችም ተገኝተው እንደነበር ጠበቃ ተመስገን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የሀገር ሽማግሌዎቹ ጉዳዩን በሽምግልና ለመፍታት ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ ማቅረባቸውንም አስረድተዋል።

[ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]
@YeneTube @FikerAssefa