ወሒድ የዕቅበተ ኢሥላም መጣጥፍት"Wahid Articles of Islamic Apologetics"
58.4K subscribers
68 photos
69 videos
19 files
1.72K links
ዳዒ ወሒድ በኢሥላም እና በክርስትና መካከል ያለውን ልዩነት እና አንድነት በንጽጽር የሚያስቀምጥ ወንድም ነው። ለዚህም የቋንቋ፣ የሰዋስው፣ የዐውድ፣ የተዛማች እና የሥነ አመክንዮ ሙግት በማቅረብ የሚታወቅ ተሟጋች እና ጦማሪ ነው። ለሙግቱ ነጥብ በዋነኝነት የሚጠቀምባቸው ቋንቋ ዐማርኛ፣ ግዕዝ፣ እንግሊዝኛ፣ ዐረቢኛ፣ ዕብራይስጥ እና ግሪክ ናቸው። መልካም የንባብ፣ የጥናት፣ የማነጻጸር ጊዜ ይሁንልዎ!
Download Telegram
ጌታ እና ባሪያ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፤

5፥117 በእርሱ ያዘዝከኝን ቃል *”ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን አምልኩ”* ማለትን እንጂ ለእነርሱ ሌላ አላልኩም፡፡ مَا قُلْتُ لَهُمْ إِلَّا مَآ أَمَرْتَنِى بِهِۦٓ أَنِ ٱعْبُدُوا۟ ٱللَّهَ رَبِّى وَرَبَّكُمْ

ዒሣ የትምህርቱ ጭብጥ፦ “አላህ ጌታዬና ጌታችሁ ነው፤ ስለዚህ አምልኩት” የሚል ነው፤ አምላካችን አላህም ኢየሱስን ተናገር! ብሎ ያዘዘው ቃል “ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን አምልኩ” ማለትን ነው፦
3፥51 *”አላህ ጌታዬና ጌታችሁ ነው፤ ስለዚህ አምልኩት”* ፤ ይህ ቀጥተኛ መንገድ ነው» አላቸው፡፡ إِنَّ ٱللَّهَ رَبِّى وَرَبُّكُمْ فَٱعْبُدُوهُ ۗ هَٰذَا صِرَٰطٌۭ مُّسْتَقِيمٌۭ
5፥117 በእርሱ ያዘዝከኝን ቃል *”ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን አምልኩ”* ማለትን እንጂ ለእነርሱ ሌላ አላልኩም፡፡ مَا قُلْتُ لَهُمْ إِلَّا مَآ أَمَرْتَنِى بِهِۦٓ أَنِ ٱعْبُدُوا۟ ٱللَّهَ رَبِّى وَرَبَّكُمْ

ጌታችን አላህ ላኪ ባሪያው ኢየሱስ መልእክተኛ ነው። ባሪያ ከጌታው አይበልጥም፥ መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም፦
ዮሐንስ 13፥16 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ *ባሪያ ከጌታው አይበልጥም። መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም*።

ፈጣሪ ኢየሱስን “አብዲ” עַבְדִּי֙ ማለትም “ባሪያዬ” በማለት ፈጣሪ ተመላኪ ኢየሱስ አምላኪ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፦
ኢሳይያስ 42፥1 እነሆ *ደግፌ የያዝሁት “ባሪያዬ” עַבְדִּי֙፤ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ምርጤ*፤ በእርሱ ላይ መንፈሴን አድርጌአለሁ፥ እርሱም ለአሕዛብ ፍርድን ያወጣል።

ይህንን በኢሳያያስ በኩል “ባሪያዬ” የሚለውን ትንቢት ወደ አዲስ ኪዳን ስንመጣ ተርጓሚዎች “ብላቴና” ማለትም “ልጄ” ብለው ለመለወጥ ቢዳዱም ግሪኩ ግን “ፔይስ ሞዩ” παῖς ማለትም “ባሪያዬ” ብሎ አስቀምጦታል፤ “ፔይስ” παῖς ማለት “ባሪያ” ማለት ነውና፦
ማቴዎስ 12፥17-18 በነቢዩ ለአሕዛብ በኢሳይያስ የተባለው ይፈጸም ዘንድ እንዲህ ሲል፦እነሆ *"የመረጥሁት “ባሪያዬ” παῖς μου ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ*፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፥ ፍርድንም ያወራል።

በትርጉም ኢየሱስን “ልጅ” ብለው ቢቀይሩትም ግሪኩ ግን “ባሪያ” ብሎ ያስቀመጠበት ጥቅስ በቁና ነው፣ በተጨማሪም የአማርኛው ትርጉም እና KJV ትርጉም “ልጅ” እያሉ ቢለውጡም NIV ትርጉም በትክክል የግሪኩን ትርጉም ይዞ “ባሪያ” ብሎ አስቀምጦታል፦
የሐዋርያት ሥራ 3፥13 የአብርሀምና የይስሐቅ የያዕቆብም አምላክ፥ የአባቶቻችን አምላክ፥ እናንተ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትንና ሊፈታው ቈርጦ ሳለ በጲላጦስ ፊት የካዳችሁትን *“ባሪያዬውን” παῖς ኢየሱስን አከበረው*።
የሐዋርያት ሥራ 3፥26 ለእናንተ አስቀድሞ *እግዚአብሔር “ባሪያዬውን” παῖς አስነሥቶ*፥ እያንዳንዳችሁን ከክፋታችሁ እየመለሰ ይባርካችሁ ዘንድ፥ ሰደደው።
የሐዋርያት ሥራ 4፥27-28 *"በቀባኸው በቅዱሱ “ባሪያህ” παῖς በኢየሱስ"* ላይ ሄሮድስና ጴንጤናዊው ጲላጦስ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር፥ እጅህና አሳብህ እንዲሆን አስቀድመው የወሰኑትን ሁሉ ሊፈጽሙ፥ በዚች ከተማ በእውነት ተሰበሰቡ።
የሐዋርያት ሥራ 4፥29-30 አሁንም፥ ጌታ ሆይ፥ ወደ ዛቻቸው ተመልከት፤ ለመፈወስም እጅህን ስትዘረጋ *በቅዱስ “ባሪያህም” παῖς በኢየሱስ"* ስም ምልክትና ድንቅ ሲደረግ፥ ባሪያዎችህ በፍጹም ግልጥነት ቃልህን እንዲናገሩ ስጣቸው ።
በተለይ ጴጥሮስ አብን፦ "ጌታ ሆይ" ካለ በኃላ ስለ ኢየሱስ ለአብ፦ "ባሪያህ" ማለቱ አብ ጌታ ወልድ ባሪያ መሆኑን አስምሮበታል። በእርግጥም አብ የሰማይና የምድር ጌታ ነው፦
ማቴዎስ 11፥25 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ፦ *"አባት ሆይ፥ የሰማይና የምድር ጌታ"*፥
የሐዋርያት ሥራ 17፥24 ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ *"እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና"* እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም።

"እርሱ" ተብሎ በነጠላ ተውላጠ-ስም የተቀመጠ አንድ ማንነት የሰማይና የምድር ጌታ ነው፥ ይህም አብ ነው። አብ በጌትነቱ ላይ ባርነት የለበትም። ማርያምና ዮሴፍ ይህንን የአብን ባሪያ ኢየሱስን በጌታ ፊት አቁመው ለጌታው መስዋዕት አቅርበዋል፤ ኢየሱስ በጌታ የተቀባና ለመፈወስ የጌታ ኃይል የሆነለት ባሪያ ነው፦
ሉቃስ 2፥24 እንደ ሙሴም ሕግ የመንጻታቸው ወራት በተፈጸመ ጊዜ፥ በጌታ ሕግ፡— የእናቱን ማኅፀን የሚከፍት ወንድ ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይባላል፡ ተብሎ እንደ ተጻፈ፡ *"በጌታ ፊት ሊያቆሙት"*፥ በጌታም ሕግ፡— ሁለት ዋሊያ ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች፡ እንደ ተባለ፥ መሥዋዕት ሊያቀርቡ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት።
ሉቃስ 2፥26 *"በጌታም የተቀባውን"* ሳያይ ሞትን እንዳያይ በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ነበር።
ሉቃስ 5፥17 እርሱም *"እንዲፈውስ የጌታ ኃይል ሆነለት"*።

አንድ ህላዌ ባሪያ ከሆነ ተመልሶ ጌታ አይሆንም። ጌታ ከተባለ ደግሞ ግን ስልጣንና ሹመትን አሊያም እልቅናና ክብርን ያመለክታል። ስለዚህ የኢየሱስ ጌትነት የፍጡር ማእረግ ብቻ ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ኢየሱስን ጌታ አደረገው ስለሚል፦
የሐዋርያት ሥራ 2፥36 አለ። እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን *ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው* የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።

መቼም አንድ ጤነኛ የሆነ ሰው ፈጣሪን ፈጣሪ ጌታ አደረገው ብሎ እንደማይቀበል እሙን ነው፤ ይስሐቅ ያዕቆብን ጌታ አደረግሁት ይላል፦
ዘፍጥረት 27፥37 ይስሐቅም መለሰ ዔሳውንም አለው። እነሆ፥ *ጌታህ አደረግሁት*፥ ወንድሞቹንም ሁሉ ለእርሱ ተገዦች ይሆኑ ዘንድ ሰጠሁት፥

ይህም ስልጣንና ሹመትን አሊያም እልቅናና ክብርን ያመለክታል፤ ዮሴፍ፦ "እግዚአብሔር ጌታ አደረገኝ” ይላል፦
ዘፍጥረት 45፥9 *እግዚአብሔር በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ጌታ አደረገኝ*፤ ወደ እኔ ና፥ አትዘግይ፤

ኢየሱስ ጌታ ተደረገ ሲባል ያዕቆብ ጌታ ተደረገ ዮሴፍ ጌታ ተደረገ በተባለበት ሒሳብ እንጂ የዓለማቱ ጌታ የሚለውን አያመለክትም፤ ይህም በራሡ የተብቃቃ አሊያም የባህርይ ገንዘቡ ሣይሆን በስጦታ ያገኘው ነው። ታዲያ ኢየሱስ ለምን "አንድ ጌታ" ተባለ? አዎ "አንድ ጌታ" ማለት "አንድ መምህር" ማለት ነው፦
1ኛ ቆሮንቶስ 8፥6 ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን *"አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን"*።
ማቴዎስ 23፥8 እናንተ ግን፡- *መምህር* Ῥαββί ተብላችሁ አትጠሩ፤ *መምህራችሁ አንድ* ስለ ሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ።

ቅድሚያ "ረቢ" Ῥαββί ማለት በአገናዛቢ ሙያ "መምህር" ማለት እንደሆነ ይሰመርበት፦
ዮሐንስ 1፥38 እርሱም፦ *"ረቢ" Ῥαββί ፥ ወዴት ትኖራለህ? አሉት፤ ትርጓሜው "መምህር ሆይ"* ማለት ነው።
ዮሐንስ 20፥16 ኢየሱስም፦ ማርያም አላት። እርስዋ ዘወር ብላ *በዐረማይክ፦ "ረቡኒ" Ραββουνι አለችው፤ ትርጓሜውም፦ "መምህር ሆይ" ማለት ነው*። NIV

"ረቢ" Ῥαββί በነጠላ "መምህሬ" ማለት ሲሆን "ረቡኒ" Ραββουνι በብዜት "መምህራችን" ማለት ነው። ማርቆስ ጴጥሮስ ኢየሱስን "ረቢ" ῥαββί አለው ሲል የማቴዎስ ጸሐፊ ደግሞ ጴጥሮስ ኢየሱስን "ኩሪዮስ" κύριος አለው ይለናል፦
ማርቆስ 9፥5 ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን። *"መምህር ሆይ"* ῥαββί ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ አለው።
ማቴዎስ 17፥4 ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን፡- *"ጌታ ሆይ"* κύριος ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ።

በግሪክ "ኩሪዮስ" κύριος የሚለው ቃል "ወንድ መምህር" ሲባል "ሴት መምህር" ደግሞ "ኩርያ" κυρία ትባላለች። ጥያቄአችን "ኩሪዮስ" ማለት "ረብ" ለሚለው ትርጉም ነው? አዎ! ከተባለ እንግዲያውስ ኢየሱስ፦ "ረብ አንድ ነው" ማለቱ እና ጳውሎስ፦ "አንድ ኩሪዮስ ነው" ማለቱ አንድ ትርጉም ካለው ኢየሱስ በአንድ አምላክ እና በሕዝቦቹ መካከል ያለ አንድ መምህር ነው፦
1ኛ ጢሞቴዎስ 2፥5 *አንድ አምላክ Θεὸς አለና፥ በአምላክ Θεὸς እና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ *አንድ* አለ፥ እርሱም ሰው ἄνθρωπος የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው"*።
ዮሐንስ 3፥2 *"መምህር ሆይ" Ῥαββί ፥ "አምላክ" Θεὸς ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና "መምህር" ሆነህ "ከአምላክ" Θεὸς ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው*።

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
አዶናይ እና አዶኒ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኛ በሆነው፡፡

6፥164 በላቸው *«እርሱ አላህ “የሁሉ ጌታ” ሲሆን ከአላህ በቀር ”ሌላን ጌታ” እፈልጋለሁን?"* ነፍስም ሁሉ በራሷ ላይ እንጅ ክፉን አትሠራም፡፡ قُلْ أَغَيْرَ ٱللَّهِ أَبْغِى رَبًّۭا وَهُوَ رَبُّ كُلِّ شَىْءٍۢ ۚ وَلَا تَكْسِبُ كُلُّ نَفْسٍ إِلَّا عَلَيْهَا

በአዲስ ኪዳን ግሪክ ኮይኔ "ኩሪዮስ" κύριος የሚለው ቃል በግርድፉ "ጌታ" የሚል ፍቺ አሊያም "መምህር" ለሚል ተለዋዋጭ ቃል ቢኖረውም በዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳን ግን "ጌታ" የሚለው የተለያየ ትርጉም አለው። "ያህዌህ አምላካችን አንድ ያህዌህ ነው" የሚለው "ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው" ብለው አስቀምጠውታል፦
ዘዳግም 6፥4 እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ *አምላካችን ያህዌህ አንድ ያህዌህ ነው*። שְׁמַע, יִשְׂרָאֵל: יְהוָה אֱלֹהֵינוּ, יְהוָה אֶחָד.
ማርቆስ 12፥29 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ። እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ *"ጌታ" κύριος አምላካችን አንድ "ጌታ" κύριος ነው"*።

መቼም ኢየሱስ ከዘዳግም 6፥4 ላይ ሲጠቅስ "ያህዌህ" የሚለውን ቴትራግራማተን እየመነቀረ መንግሎ "ኩሩዮስ" እያለ ተናገረ ማለት ዘበት ነው፥ የሚመነቅርበትና የሚመነግልበት አንዳች ቁብ የለውም፤ እርሱ የሙሴ ዚቅ የሚያቀነቅንና የሚወርብ ዚቀኛ እንጂ የሚቀናቀን ተቃራኒ በፍጹም አይደለም። ሲቀጥል ግሪከኛ ተናጋሪም አይደለም።
ደግሞም አንዱ ያህዌህ እና መሢሑ ሁለት ማንነት እና ምንነት ናቸው፦
መዝሙር 2፥2 የምድር ነገሥታት ተነሡ፥ አለቆችም *"በያህዌህ" יְהֹוָה እና በመሢሑ ላይ እንዲህ ሲሉ ተማከሩ"*።
የሐዋርያት ሥራ 4፥26 የምድር ነገሥታት ተነሡ አለቆችም *በጌታ" κύριος እና በተቀባው ላይ አብረው ተከማቹ"* ብለህ የተናገርህ አምላክ ነህ።

ያህዌህ እና መሢሑ "እና" በሚል መስተጻምር መለያየታቸው አንባቢ ልብ ይለዋል፤ ነገር ግን "ያህዌህ" የሚለው "ኩርዮስ" በሚል እንደተለወጠ ልብ በል።
አይሁዳውያን "ያህዌህ" יְהֹוָה በሚለው ፈንታ የሚጠቀሙበት "አዶናይ" אֲדֹנָ֥י የሚለውን ጌትነት ነው፥ "አዶናይ" ለአንድ አምላክ ብቻ የሚጠቀምበት ነው፤ ያህዌህ ብቻውን “አዶናይ” ተብሏል፤ አንድም ፍጡር “አዶናይ” ተብሎ የተጠራ የለም፤ እስቲ አንዱ አምላክ "አዶናይ" የተባለበትን አናቅፅ ለናሙና ያክል እንየው፦
መዝሙር 16፥2 ያህዌህን *"አንተ “ጌታዬ” אֲדֹנָ֥י ነህ አልሁ"*፤ ከአንተ በቀር በጎነት የለኝም።
መዝሙር 110፥5 “ጌታዬ” אֲדֹנָ֥י በቀኝህ ነገሥታትን በቍጣው ቀን ይቀጠቅጣቸዋል።

ልብ አድርግ ዳዊት አንድ ዐውድ ላይ ያህዌህን "አዶናይ" אֲדֹנָ֥י ሲል ኢየሱስ ግን "አዶኒ" אֲדֹנִ֖י ነው ያለው፦
መዝሙር 110፥1 *"ያህዌህ יְהֹוָה "ጌታዬን" אדֹנִ֗י ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው"*።
የሐዋርያት ሥራ 2፥34 ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና፥ ነገር ግን እርሱ። *"ጌታ κύριος "ጌታዬን" κύριος ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው"*።
ዘዳግም 6፥4 ላይ ያለው አንዱ ያህዌህ መሢሑን፦ "ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ" አለው። አንዱ ያህዌህ ባለቤት ሲሆን መሢሑ ተሳቢ ነው፥ በባለቤት እና በተሳቢ መካከል "አለው" የሚል ተሻጋሪ ግስ መኖሩ በራሱ አንዱ አምላክ ያህዌህ እና መሢሑ ሁለት የተለያዩ ማንነቶች እና ምንነቶች እንደሆኑ ቁልጭና ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ነገር ግን የአዲስ ኪዳን ተርጓሚዎች "ያህዌህ" የሚለውን "ኩርዮስ" በማለት "አዶኒ" የሚለውን "ኩርዮስ" በማለት የዳዊትን ንግግር አምታተውታል። አንደኛው ጌታ ሌላይኛውን ጌታ፦ "ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ" ያለው ይመስላል። ግን ዳዊት ያለው "አዶኒ" እንጂ "አዶናይ" አይደለም። ልክ እንደ ዳዊት የደማስቆ ሰው ኤሊዔዘር፦ "ያህዌህ ጌታዬን እጅግ ባረከው" አለ፦
ዘፍጥረት 24፥35 *"*"ያህዌህ יְהֹוָה "ጌታዬን" אדֹנִ֗י እጅግ ባረከው"*።

"አዶኒ" በተመሳሳይ ሳራ አብርሃምን ያለችበት ነው፦
ዘፍጥረት18፥12 ሣራም በልብዋ እንዲህ ስትል ሳቀች። ካረጀሁ በኋላ በውኑ ፍትወት ይሆንልኛልን? *"ጌታዬም אדֹנִ֗י ፈጽሞ ሸምግሎአል"*።
1 ጴጥሮስ 3፥6 እንዲሁም ሣራ ለአብርሃም፦ *"ጌታ" κύριος ብላ እየጠራችው ታዘዘችለት"*።

የዘፍጥረት አንቀጽ ላይ ሳራ አብርሃምን "አዶኒ" אדֹנִ֗י ያለችው ወደ ግሪኩ ኮይኔ ሲመጣ "ኩርዮስ" κύριος ብለው አስቀምጠዋል። ነገር ግን "አዶኒ" אֲדֹנִֽי ለፍጡራን ማለትም ለመላእክት እና ለሰዎች አገልግሎት ላይ ውሏል።

ለመላእክት፦
ኢያሱ 5፥14 እርሱም፦ አይደለሁም እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁን መጥቼአለሁ፡ አለ። ኢያሱም ወደ ምድር በግምባሩ ተደፍቶ ሰገደና፦ *"ጌታዬ"* אֲדֹנִֽי ለባሪያው የሚነግረው ምንድር ነው? አለው።
መሳፍንት 6፥13 ጌዴዎንም፦ *"ጌታዬ"* אֲדֹנִֽי ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረሰብን?... አለው።
ዘካርያስ 6፥4 ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረውም መልአክ መልሼ፦ *"ጌታዬ"* אֲדֹנִֽי ሆይ፥ እነዚህ ምንድር ናቸው? አልሁት።

ለሰዎች፦
ዘፍጥረት 32:4 እንዲህም ብሎ አዘዛቸው። *"ለጌታዬ"* אדֹנִ֗י ለዔሳው። ባሪያህ ያዕቆብ እንዲህ አለ፦ ብላችሁ ንገሩት።
ዘኊልቅ 11:28 ከልጅነቱ ጀምሮ የሙሴ አገልጋይ የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ። *"ጌታዬ"* אדֹנִ֗י ሙሴ ሆይ፥ ከልክላቸው አለው።
1ሳሙኤል 24:8፤ ከእርሱም በኋላ ዳዊት ደግሞ ተነሣ፥ ከዋሻውም ወጣ፥ ከሳኦልም በኋላ። *"ጌታዬ"* אדֹנִ֗י ንጉሥ ሆይ፥ ብሎ ጮኸ፤
ዳንኤል 4:24፤ *"በጌታዬ"* אדֹנִ֗י በንጉሥ ላይ የወረደው የልዑሉ ትእዛዝ ነው፤

አዲስ ኪዳን ላይ ኢየሱስ "ኩርዮስ" የተባለው "አዶኒ" የሚለውን ማዕረግ ለማሳየት እንጂ ያህዌህ ወይም አዶናይ የሚለውን ለማሳየት አይደለም፤ ስለዚህ የኢየሱስ ጌትነት የፍጡር ማእረግ ብቻ ነው። ምክንያቱም እዛው "ጌታ ጌታዬን" በተባለበት ዐውድ ላይ እግዚአብሔር ኢየሱስን ጌታ አደረገው ስለሚል፦
የሐዋርያት ሥራ 2፥36 አለ። እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን *ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው* የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።

መቼም አንድ ጤነኛ የሆነ ሰው ፈጣሪን ፈጣሪ ጌታ አደረገው ብሎ እንደማይቀበል እሙን ነው፤ ይስሐቅ ያዕቆብን ጌታ አደረግሁት ይላል፦
ዘፍጥረት 27፥37 ይስሐቅም መለሰ ዔሳውንም አለው። እነሆ፥ *ጌታህ አደረግሁት*፥ ወንድሞቹንም ሁሉ ለእርሱ ተገዦች ይሆኑ ዘንድ ሰጠሁት፥

ይህም ስልጣንና ሹመትን አሊያም እልቅናና ክብርን ያመለክታል፤ ዮሴፍ፦ "እግዚአብሔር ጌታ አደረገኝ” ይላል፦
ዘፍጥረት 45፥9 *እግዚአብሔር በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ጌታ አደረገኝ*፤ ወደ እኔ ና፥ አትዘግይ፤

ኢየሱስ ጌታ ተደረገ ሲባል ያዕቆብ ጌታ ተደረገ ዮሴፍ ጌታ ተደረገ በተባለበት ሒሳብ እንጂ የዓለማቱ ጌታ የሚለውን አያመለክትም፤ ይህም በራሡ የተብቃቃ አሊያም የባህርይ ገንዘቡ ሣይሆን በስጦታ ያገኘው ነው። አዶናይ የሁሉ ጌታ የሆነው አንድ አምላክ ነው። እርሱ አላህ “የሁሉ ጌታ” ሲሆን ከአላህ በቀር ”ሌላን ጌታ” እፈልጋለሁን? በፍጹም! ከዓለማቱ ጌታ ከአላህ በቀር ሌላ የዓለማት ጌታ የለም፦
6፥164 በላቸው *«እርሱ አላህ “የሁሉ ጌታ” ሲሆን ከአላህ በቀር ”ሌላን ጌታ” እፈልጋለሁን?"* ነፍስም ሁሉ በራሷ ላይ እንጅ ክፉን አትሠራም፡፡ قُلْ أَغَيْرَ ٱللَّهِ أَبْغِى رَبًّۭا وَهُوَ رَبُّ كُلِّ شَىْءٍۢ ۚ وَلَا تَكْسِبُ كُلُّ نَفْسٍ إِلَّا عَلَيْهَا

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
መስካሪ እና ተመስካሪ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

85፥3 *"በመስካሪ እና በተመስካሪ እምላለሁ"*፡፡ وَشَاهِدٍ وَمَشْهُودٍ

"ሻሂድ" شَاهِد ማለት የሚመሰክር "መስካሪ" ማለት ሲሆን "መሽሁድ" مَشْهُود ማለት ደግሞ የሚመሰከርበት "ተመስካሪ" ማለት ነው። በተቀጠረው ቀን መስካሪ በተመስካሪ ላይ ይመሰክራሉ፦
85፥2 *"በተቀጠረው ቀንም እምላለው"*። وَالْيَوْمِ الْمَوْعُودِ
85፥3 *"በመስካሪ እና በተመስካሪ እምላለሁ"*፡፡ وَشَاهِدٍ وَمَشْهُودٍ
And by the witness and the witnessed.

አላህ በቁርኣን የማለባቸው ነገሮችን ሁሉ ጉዳዩን አጽንዖትና አንክሮት መስጠቱን የሚያመላክት ነው። ያ የተቀጠረው ቀን ሙታን የሚቀሰቀሱበት የትንሳኤ ቀን ነው፦
34፥30 *«ለእናንተ ከእርሱ አንዲትንም ሰዓት የማትዘገዩበት የማትቀድሙበትም "የቀጠሮ ቀን" አላችሁ»* በላቸው፡፡ قُل لَّكُم مِّيعَادُ يَوْمٍ لَّا تَسْتَأْخِرُونَ عَنْهُ سَاعَةً وَلَا تَسْتَقْدِمُونَ
36፥52 *«ወይ ጥፋታችን! ከመኝታችን ማን ቀሰቀሰን? "ይህ ያ አዛኙ ጌታ በእርሱ የቀጠረን" እና መልክተኞቹም እውነትን የነገሩን ነው»* ይላሉ፡፡ قَالُوا يَا وَيْلَنَا مَن بَعَثَنَا مِن مَّرْقَدِنَا ۜ ۗ هَـٰذَا مَا وَعَدَ الرَّحْمَـٰنُ وَصَدَقَ الْمُرْسَلُونَ
11፥103 በዚህ ውስጥ የመጨረሻውን ቀን ቅጣት ለሚፈሩ ሁሉ መገሰጫ አለ፡፡ *"ይህ የትንሣኤ ቀን ሰዎች በእርሱ የሚሰበሰቡበት ቀን ነው፡፡ ይህም የሚጣዱት ቀን ነው"*፡፡ إِنَّ فِي ذَٰلِكَ لَآيَةً لِّمَنْ خَافَ عَذَابَ الْآخِرَةِ ۚ ذَٰلِكَ يَوْمٌ مَّجْمُوعٌ لَّهُ النَّاسُ وَذَٰلِكَ يَوْمٌ مَّشْهُودٌ

የተቀጠረው ቀን የመሽሁድ ቀን ነው። አላህ፦ "በመስካሪው እና በሚመሰከርባቸው እምላለው" ብሏል፤ "መስካሪ" የተባሉት "ነቢያት" ሲሆኑ "የሚመሰከርባቸው" ደግሞ "ኡማቸው" ናቸው፦
16፥84 *"ከየሕዝቡም ሁሉ መስካሪን የምንቀሰቅስበትን ቀን አስታውስ"*፡፡ وَيَوْمَ نَبْعَثُ مِن كُلِّ أُمَّةٍ شَهِيدًا
4፥41 *"ከሕዝቦችም ሁሉ መስካሪን ባመጣን ጊዜ አንተንም በእነዚህ ሕዝብ ላይ መስካሪ አድርገን በምናመጣህ ጊዜ የከሓዲዎች ኹኔታ እንዴት ይኾን?"* فَكَيْفَ إِذَا جِئْنَا مِن كُلِّ أُمَّةٍ بِشَهِيدٍ وَجِئْنَا بِكَ عَلَىٰ هَـٰؤُلَاءِ شَهِيدًا
16፥89 *"በየሕዝቡም ሁሉ ውስጥ ከራሳቸው በእነርሱ ላይ መስካሪን የምንቀሰቅስበትን አንተንም በእነዚህ ሕዝብ ላይ መስካሪ አድርገን የምናመጣህን ቀን አስታውስ"*፡፡ وَيَوْمَ نَبْعَثُ فِي كُلِّ أُمَّةٍ شَهِيدًا عَلَيْهِم مِّنْ أَنفُسِهِمْ ۖ وَجِئْنَا بِكَ شَهِيدًا عَلَىٰ هَـٰؤُلَاء
28፥75 *"ከሕዝቦችም ሁሉ መስካሪን እናወጣለን፡፡ ያን ጊዜ እውነተኛውም አምላክነት ለአላህ ብቻ መኾኑን ያውቃሉ፡፡ ይቀጣጥፉት የነበሩትም ከእነርሱ ይጠፋቸዋል"*፡፡ وَنَزَعْنَا مِن كُلِّ أُمَّةٍ شَهِيدًا فَقُلْنَا هَاتُوا بُرْهَانَكُمْ فَعَلِمُوا أَنَّ الْحَقَّ لِلَّهِ وَضَلَّ عَنْهُم مَّا كَانُوا يَفْتَرُونَ

“ኡማህ” أُمَّة ማለት “ሕዝብ” ማለት ሲሆን በአንድ ነቢይ ዘመነ-መግቦት"dispensation" የሚቆዩትን "ሰዎች" ያመለክታል። እያንዳንዱ ነቢይ በራሱ ኡማህ ላይ በትንሳኤ ቀን ይመሰክራሉ። ይህ ሙግት “የተዛማች ሙግትን”textual approach” ታሳቢና ዋቢ ያደረገ ሙግት ነው።

ነገር ግን "ተጣጅ" እና "ሚጣዱት" የሚለው እንደ ኢትዮጵያ ክርስትና አቆጣጠር በ 1961 ዓመተ-ልደት በተዘጋጀው የሐጅ ሣኒ ሐቢብ የዐማርኛ የቁርኣን ትርጉም ላይ ተቀምጧል። አንዳንዶች፦ "የወሎ አማርኛ ነው" ቢሉም ምን ለማስተላለፍ እንደፈለጉ እኔ በቅጡ አልገባኝም፥ አላህ ነው ሁሉን የሚያውቀው። ነገር ግን የኢንግሊሹ የቁርኣን ትርጉም እና እራሱ ኦርጅናሉ ቁርኣን "ሻሂድ" شَاهِد "መስካሪ" "the witness" እና "መሽሁድ" مَشْهُود "ተመስካሪ" "the witnessed" ብሎ ጥልልና ጥንፍፍ አርጎ አስቀምጦታል። የአገራችን ሚሽነሪዎች ጭረው ተፍጨርጭረው ስለ ድስት መጣድ ለማስመሰል ቢዳዱም ከላይ ባለው የቋንቋ ሙግት”linguistical approach” ድባቅ ይገባሉ።

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
ቅዱስ ቁርኣን

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

56፥77 እርሱ *የከበረ* ቁርኣን ነው። إِنَّهُۥ لَقُرْءَانٌۭ كَرِيمٌۭ

ቅዱስ ቁርኣን የምንልበት ምክንያት ቁርኣን "ከሪም" ስለተባለ ነው፤ "ከሪም" كَرِيم የሚለው ቃል "ቅዱስ" "ክቡር" "ብፁዕ" "ንኡድ" "ውዱስ" "ስቡህ" "እኩት" "እጹብ" የሚል ፍቺ አለው፦
56፥77 እርሱ *የከበረ* ቁርኣን ነው። إِنَّهُۥ لَقُرْءَانٌۭ كَرِيمٌۭ

"መጽሐፍ ቅዱስ" ማለት "ቅዱስ መጽሐፍ" ማለት ነው፤ የፈጣሪ ንግግር ብቻ ነው ቅዱስ እንጂ የሰው ንግግር ቅዱስ አይደለም። ባይብል የሰው ንግግር ስላለበት ቅዱስ መጽሐፍ አይባልም። ስለዚህ ባይብልን "መጽሐፍ ቅዱስ" በማለት ፋንታ "ባይብል" በሉት፤ "ባይብል" የሚለው የኢንግሊሹ ቃል "ቢብሊያ" βιβλία ከሚል የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙ "ጥቅሎች"scrolls" ማለት ነው፣ በነጠላ ደግሞ "ቢብሊኦን" βιβλίον ሲሆን "ጥቅል"scroll" ማለት ነው። ይህ ቃል ለማንኛውም መጽሐፍ ቃሉ ያገለግላል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ቁርኣን ብቻ ነው፤ ምክንያቱም የቁርኣን ተናጋሪ ፈጣሪ ብቻ ስለሆነ ማለት ነው፤ በእግጥም ቁርኣን "ቅዱስ" "ክቡር" "ብፁዕ" "ንኡድ" "ውዱስ" "ስቡህ" "እኩት" "እጹብ" ነው።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሰላሙ አለይኩም
እንስሳት እና ዕፅዋት

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኛ በሆነው፡፡

50፥7 *ምድርንም ዘረጋናት፡፡ በእርሷም ውስጥ ጋራዎችን ጣልንባት፡፡ "በውስጧም ከሚያስደስት ጥንድን ሁሉ አበቀልን"*፡፡ وَالْأَرْضَ مَدَدْنَاهَا وَأَلْقَيْنَا فِيهَا رَوَاسِيَ وَأَنبَتْنَا فِيهَا مِن كُلِّ زَوْجٍ بَهِيجٍ

"ዘውጅ” زَوْج የሚለው ቃል “ጥንድ” “ባል” ወይም “ሚስት” ተብሎ ተቀምጧል፦
58:1 አላህ የዚያችን *በባልዋ* ነገር የምትከራከርህንና ወደአላህ የምታስሙተውን ቃል በእርግጥ ሰማ። قَدْ سَمِعَ ٱللَّهُ قَوْلَ ٱلَّتِى تُجَٰدِلُكَ فِى زَوْجِهَا وَتَشْتَكِىٓ إِلَى ٱللَّهِ وَٱللَّهُ يَسْمَعُ تَحَاوُرَكُمَآ ۚ إِنَّ ٱللَّهَ سَمِيعٌۢ بَصِيرٌ
7:19 አዳምም ሆይ! አንተም *ሚስትህም* ከገነት ተቀመጡ፤ وَيَٰٓـَٔادَمُ ٱسْكُنْ أَنتَ وَزَوْجُكَ ٱلْجَنَّةَ فَكُلَا مِنْ حَيْثُ شِئْتُمَا وَلَا تَقْرَبَا هَٰذِهِ ٱلشَّجَرَةَ فَتَكُونَا مِنَ ٱلظَّٰلِمِينَ
35:11 አላህም ከዐፈር፣ ከዚያም ከፍትወት ጠብታ ፈጠራችሁ፤ *ከዚያም ጥንዶች አደረጋችሁ*፤ وَٱللَّهُ خَلَقَكُم مِّن تُرَابٍۢ ثُمَّ مِن نُّطْفَةٍۢ ثُمَّ جَعَلَكُمْ أَزْوَٰجًۭا
53:45 እርሱም *ሁለቱን ዓይነቶችን ወንድ እና ሴትን ፈጠረ*። وَأَنَّهُۥ خَلَقَ ٱلزَّوْجَيْنِ ٱلذَّكَرَ وَٱلْأُنثَىٰ

“ዘውጀይኒ” زَّوْجَيْنِ ሙተና ሲሆን ሁለት የወንድ እና የሴት ዓይነቶች በሚል መጥቷል፤ “ባልዋ” ለሚለው ቃል የገባው “ዘውጂሃ” زَوْجِهَا መሆኑ እና “ሚስትህ” ለሚለው ቃል የገባው ደግሞ “ዘውጅከ” َزَوْجُكَ መሆኑ አንባቢ ልብ ይለዋል። እዚህ ድረስ ከተግባባን አምላካችን አላህ ለእኛ ከምድር ጥንድ ጥንድ የሆኑ ፍጥረታትን ፈጥሮልናል፦
50፥7 *ምድርንም ዘረጋናት፡፡ በእርሷም ውስጥ ጋራዎችን ጣልንባት፡፡ "በውስጧም ከሚያስደስት ጥንድን ሁሉ አበቀልን"*፡፡ وَالْأَرْضَ مَدَدْنَاهَا وَأَلْقَيْنَا فِيهَا رَوَاسِيَ وَأَنبَتْنَا فِيهَا مِن كُلِّ زَوْجٍ بَهِيجٍ

እዚህ አንቀጽ ላይ "ዓይነት" ተብሎ የተቀመጠው ቃል "ዘውጅ” زَوْج ሲሆን “ጥንድ” ማለት ነው። ለእኛ የተፈጠሩት እነዚህም ጥንድ ጥንድ የሆኑ ፍጥረታት እንስሳት እና ዕፅዋት ናቸው። እስቲ ይህንን እሳቤ ነጥብ በነጥብ እንመልከት፦

ነጥብ አንድ
"እንስሳት"
እንስሳት ከምድር የተፈጠሩ መነሻቸው ውኃ የሆኑ ፍጥረታት ናቸው፦
24፥45 *"አላህም ተንቀሳቃሽን ሁሉ ከውሃ ፈጠረ፡፡ ከእነርሱም በሆዱ ላይ የሚኼድ አለ፤ ከእነሱም በሁለት እግሮች ላይ የሚኼድ አለ፡፡ አላህ የሚሻውን ሁሉ ይፈጥራል"*፡፡ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነውና፡፡ وَاللَّهُ خَلَقَ كُلَّ دَابَّةٍ مِّن مَّاءٍ ۖ فَمِنْهُم مَّن يَمْشِي عَلَىٰ بَطْنِهِ وَمِنْهُم مَّن يَمْشِي عَلَىٰ رِجْلَيْنِ وَمِنْهُم مَّن يَمْشِي عَلَىٰ أَرْبَعٍ ۚ يَخْلُقُ اللَّهُ مَا يَشَاءُ ۚ إِنَّ اللَّهَ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ قَدِيرٌ
42፥11 ሰማያትንና ምድርን ፈጣሪ ነው፡፡ ከራሳችሁ ጥንዶችን፣ *ከቤት እንስሳዎችም ጥንዶችን ለእናንተ አደረገላችሁ*፡፡ በእርሱ ያበዛችኋል፡፡ የሚመስለው ምንም ነገር የለም፡፡ እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው፡፡ فَاطِرُ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ ۚ جَعَلَ لَكُم مِّنْ أَنفُسِكُمْ أَزْوَاجًا وَمِنَ الْأَنْعَامِ أَزْوَاجًا ۖ يَذْرَؤُكُمْ فِيهِ ۚ لَيْسَ كَمِثْلِهِ شَيْءٌ ۖ وَهُوَ السَّمِيعُ الْبَصِيرُ

"ከቤት እንስሳዎችም ጥንዶችን ለእናንተ አደረገላችሁ" የሚለው ሃይለ-ቃል ይሰመርበት። አሁንም “አዝዋጅ” أَزْوَاج ተብሎ የተቀመጠው ቃል ” ዘውጅ” زَوْج ለሚለው ቃል ብዜት ሲሆን “ጥንዶች” ማለት ነው፤ እንስሳት የጾታ ጥንዶች እንደሆኑም እሙንና ቅቡል ነው። በእነዚህ እንስሳ ላይ ሰው ባለቤት እና ንጉሥ ነው፦
36፥71 እኛ እጆቻችን ከሠሩት *"ለእነርሱ እንስሳዎችን መፍጠራችንን አያውቁምን? እነርሱም ለእርሷ ባለ መብቶች ናቸው"*፡፡ أَوَلَمْ يَرَوْا أَنَّا خَلَقْنَا لَهُم مِّمَّا عَمِلَتْ أَيْدِينَا أَنْعَامًا فَهُمْ لَهَا مَالِكُونَ

“ባለ መብት” ተብሎ የተቀመጠው ቃል “ማሊክ” مَٰلِك ማለትም “ባለቤት”owner” ማለት ሲሆን ሚምን በሁለት ሃረካት ሲሳብ ሚም ፈትሃ አሊፍ ስኩን “ማ” مَٰ ብሎ ሲቀራው “ባለቤት”owner” ይሆናል፤ እንዲሁ “መሊክ”مَلِيك ብሎ ሚምን ባለ አንድ ሃረካ ተስቦ ሚም ፈትሃ “መ” ብሎ مَ ሲቀራ “ንጉሥ”king” ይሆናል። ወደ ነጥቡ ስንገባ ሰው የእንስሳት "ንጉሥ" "ባለቤት" "ባለመብት" መሆኑን ነው።
ነጥብ ሁለት
"ዕፅዋት"
ዕፅዋትም ከምድር የተፈጠሩ መነሻቸው ውኃ የሆኑ ፍጥረታት ናቸው፦
50፥9 *"ከሰማይም ብሩክን ውሃ አወረድን፡፡ በእርሱም አትክልቶችንና የሚታጨድን ፍሬ አበቀልን"*፡፡ وَنَزَّلْنَا مِنَ السَّمَاءِ مَاءً مُّبَارَكًا فَأَنبَتْنَا بِهِ جَنَّاتٍ وَحَبَّ الْحَصِيدِ
15፥19 ምድርንም ዘረጋናት፡፡ በውስጧም ኮረብታዎችን ጣልናባት፡፡ *"በውስጧም የተለካን በቃይ ሁሉ አበቀልንባት"*፡፡ وَالْأَرْضَ مَدَدْنَاهَا وَأَلْقَيْنَا فِيهَا رَوَاسِيَ وَأَنبَتْنَا فِيهَا مِن كُلِّ شَيْءٍ مَّوْزُونٍ

ዕፅዋት ልክ እንደ እንስሳት የተባእት እና የእንስት ህዋስ"gamete" ያመነጫሉ። አላህ በዕፅዋት መካከል ጥንድ የሆኑ ተቃራኒ ጾታዎች እንዳሉ ለማመልከት “ዘውጀይኒ” زَوْجَيْنِ በማለት ይናገራል፦
13፥3 እርሱም ያ ምድርን የዘረጋ በእሷም ተራራዎችን እና ወንዞችን ያደረገ *በውስጧም ከፍሬዎች ሁሉ ሁለት ሁለት ጥንዶችን ያደረገ ነው*፡፡ ሌሊትን በቀን ይሸፍናል፡፡ *በዚህም ውስጥ ለሚያስተነትኑ ሕዝቦች ታምራቶች አሉ*፡፡ وَهُوَ الَّذِي مَدَّ الْأَرْضَ وَجَعَلَ فِيهَا رَوَاسِيَ وَأَنْهَارًا ۖ وَمِن كُلِّ الثَّمَرَاتِ جَعَلَ فِيهَا زَوْجَيْنِ اثْنَيْنِ ۖ يُغْشِي اللَّيْلَ النَّهَارَ ۚ إِنَّ فِي ذَٰلِكَ لَآيَاتٍ لِّقَوْمٍ يَتَفَكَّرُونَ

“ኩል” كُلٌّ ማለትም “ሁሉ” የሚለው ቃል ፍጹማዊ “Absolute" ሆኖ ሲመጣ “ሙጥለቅ” مطلق ሲባል በአንጻራዊ “Relative” ሆኖ ሲመጣ ደግሞ "ቀሪብ” قريب ይባላል። እዚህ አንቀጽ ላይ ቀሪብ ሆኖ የመጣ ነው። ነቢያችን"ﷺ" በተላኩበት ጊዜ ላይ ዕፅዋት ጾታ አላቸው ብሎ ማንም ሰው ዐያውቅም ነበር፥ በዚህ ጊዜ አምላካችን አላህ ሁሉን ዐዋቂ በመሆኑ “ዘውጀይኒ” በማለት ዕፅዋት ጥንዶች እንደሆኑ ነግሮናል። በተጨማሪም ይህንንም እሳቤ ቁርኣን በወረደበት ጊዜ ዐለማወቃችንንም ለማመልከት፦ "ከማያውቁትም ነገር ጥንዶችን ሁሏንም የፈጠረ ጥራት ይገባው" በማለት በሦስተኛ መደብ እራሱ ይናገራል፦
36፥36 ያ ምድር ከምታበቅለው ከራሶቻቸውም *ከማያውቁትም ነገር ጥንዶችን ሁሏንም የፈጠረ ጥራት ይገባው*፡፡ سُبْحَانَ الَّذِي خَلَقَ الْأَزْوَاجَ كُلَّهَا مِمَّا تُنبِتُ الْأَرْضُ وَمِنْ أَنفُسِهِمْ وَمِمَّا لَا يَعْلَمُونَ

አምላካችን አላህ ጊዜው ሲደርስ በ 19ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ለሚያስተነትኑ ሕዝቦች ታምራት ይሆን ዘንድ ዕፅዋት ጾታ እንዳላቸው ዐሳውቆናል። "ጋይኒ" γυνή ማለት "ሴቴ" ማለት ሲሆን ይህቺ የዕፅዋት እንቁላል ህዋስ"gynoecious" በሥነ-ሕይወት ጥናት "ካርፔልስ"carpels" ትባላለች፥ "አንድሮ" ἀνήρ ማለት "ወንዴ" ማለት ሲሆን የዕፅዋት የዘር ህዋስ"Androecium" በሥነ-ሕይወት ጥናት "ስቴመንስ"stamens" ይባላል።

እንግዲህ እንስሳት እና ዕፅዋት ከምድር የተፈጠሩ መነሻቸው ውኃ የሆኑ ፍጥረታት መሆናቸውን ካየን ዘንዳ የተፈጠሩበት አላማ ለሰው መደሰቻ ነው፦
2፥29 *"እርሱ ያ በምድር ያለውን ሁሉ ለእናንተ የፈጠረ ነው"*፡፡ هُوَ الَّذِي خَلَقَ لَكُم مَّا فِي الْأَرْضِ جَمِيعًا
50፥7 *ምድርንም ዘረጋናት፡፡ በእርሷም ውስጥ ጋራዎችን ጣልንባት፡፡ "በውስጧም ከሚያስደስት ጥንድን ሁሉ አበቀልን"*፡፡ وَالْأَرْضَ مَدَدْنَاهَا وَأَلْقَيْنَا فِيهَا رَوَاسِيَ وَأَنبَتْنَا فِيهَا مِن كُلِّ زَوْجٍ بَهِيجٍ

በባይብልም ከሄድን እንስሳት እና ዕፅዋት ከምድር የተፈጠሩ መነሻቸው ውኃ የሆኑ ፍጥረታት መሆናቸውን ይናገራል፦
ዘፍጥረት 1፥20 እግዚአብሔርም አለ፦ *"ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾች ታስገኝ፥ ወፎችም ከምድር በላይ ከሰማይ ጠፈር በታች ይብረሩ"*።
ዘፍጥረት 1፥24 እግዚአብሔርም አለ፦ *"ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን እንደ ወገኑ፥ እንስሳትንና ተንቀሳቃሾችን የምድር አራዊትንም እንደ ወገኑ፥ ታውጣ! እንዲሁም ሆነ"*።
መክብብ 3፥19-20 *"የሰው ልጆች እና የእንስሳ እድል ፈንታ አንድ ነው"*፤ ድርሻቸውም ትክክል ነው፤ አንዱ እንደሚሞት ሌላውም እንዲሁ ይሞታል፤ የሁሉም እስትንፋስ አንድ ነው፤ ሁሉም ከንቱ ነውና ሰው ከእንስሳ ብልጫ የለውም። ሁሉ ወደ አንድ ቦታ ይሄዳል፤ *"ሁሉ ከአፈር ነው ሁሉም ወደ አፈር ይመለሳል"*።
ዘፍጥረት 1፥11 እግዚአብሔርም፦ *"ምድር ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን በምድርም ላይ እንደ ወገኑ ዘሩ ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን ታብቅል! አለ፤ እንዲሁም ሆነ"*።

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
ቂሰቱል ገራኒቅ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

69፥44-46 በእኛ ላይም ከፊልን ቃላት ያላልነውን “በቀጠፈ” ኖሮ وَلَوْ تَقَوَّلَ عَلَيْنَا بَعْضَ ٱلْأَقَاوِيلِ ፤ በኀይል በያዝነው ነበር لَأَخَذْنَا مِنْهُ بِٱلْيَمِينِ ፡፡ ከዚያም ከእርሱ የልቡን ሥር በቆረጥን ነበር ثُمَّ لَقَطَعْنَا مِنْهُ ٱلْوَتِينَ ፡፡

ዊሊያም ሙኢር በ 1819 AD ተወልዶ በ 1905 AD ያለፈ “ሙስተሽሪቅ” مستشرق ማለትም “የመካከለኛው ምስራቅ ጥንተ-ነገር አጥኚ”Orientalist” ሲሆን እርሱ ለመጀመሪያ ጊዜ በ 1858 AD በመጽሐፉ ሽፋን ላይ “ሰይጣናዊ አንቀፅ”Satanic Verse” ብሎ ጻፈ፤ በመቀጠል የእርሱን ፈለግ የተከተለው ሳልማን ሩሽዲ 1988 AD በመጽሐፉ ሽፋን ላይ “ሰይጣናዊ አንቀፅ” ብሎ ጻፈ፤ ይህ መጽሐፍ በምዕራባዊያና በሚሽነሪዎች እገዛ በዓለማችን ላይ ትልቅ የህትመት ሽፋን ተሰቶት ተሰራጭቶ ነበር፤ ሳልማን ሩሽዲን ብዙዎች ከሊቅ እስከ ደቂቅ እጹብ ድንቅ በማለት አሞካሽተውት ነበር፤ ቂሰቱል ገራኒክ በቅጡ በማይታወቅበት በዚያ ጊዜ አለማወቅን ተገን አድርጎ የተነሣው ይህ ሰው ብዥታው አላንዳች ከልካይ እንደ ተዛማጅ በሽታ በዓለማችም ላይ ተዛምቶ ነበር፤ ከመነሻው የብዙዎችን ልብ የሳበው ይህ መጽሐፍ ከእርሱ በኋላ ለመጡት መሰል የሚሽነሪዎች ትችት ትልቅ የማደላደል ሥራ ሠርቷል። “ሰይጣናዊ አንቀፅ” ከትችት የመነጨ ሲሆን ይህ ስያሜ በኢስላም ጽሑፎች ውስጥ የለም። “ሰይጣናዊ አንቀፅ” በኢስላማዊ ጥናት ውስጥ ግን “ቂሰቱል ገራኒቅ” قصة الغرانيق ይባላል፤ “ገራኒቅ” غرانيق ማለት “የውሃ ወፍ”crane” ማለት ነው።
“ቂሰቱል ገራኒቅ” ማለት ይህ ነው፦
“ቲልከል ገራኒቁል ዑልያ፤ ወኢንነ ሸፋዐተሁንነ ለቱርጃ” تِلْكَ الْغَرَانِيقُ الْعُلْيَ وَ إِنَّ شَفاَعَتَهُنَّ لَتُرْجَى.
‹እነዚህ የተከበሩ ናቸው ምልጃቸው ተቀባይነት ያገኘው ናቸው›These are the high-flying ones, verily their intercession is to be hoped for!

ይህንን ከማየታችን በፊት ሙሉ ታሪካዊ ዳራውን እንመልከት፤ የረመዷን ወር ነብያችን”ﷺ” ወደ ተከበረው የሐረም መስጊድ ሄዱ፤ ቁረይሾች ተሰባስበው ባሉበት በድንገት ከመካከላቸው ቆሙና ሱረቱል ነጅም የተሰኘውን የቁርዓን ክፍል አነበቡ፤ ይህንን ሱራ አንብበው ሲጨርሱ “ለአላህም ስገዱ አምልኩትም” አንቀፅ ስለነበር ሁሉም ሙስሊሞች ሰገዱ፤ ከኃላ ሲሰሙ የነበሩት ቁረይሾች አብረው ሰገዱ፦
53፥62 ለአላህም ስገዱ አምልኩትም فَٱسْجُدُوا۟ لِلَّهِ وَٱعْبُدُوا۟ ۩ ፡፡
ኢማም ቡኻሪይ መጽሐፍ 17 , ሐዲስ 5:
ኢብኑ ዐባስ”ረ.ዓ.” እንደተረከው፦ ነቢዩ”ﷺ” ሱረቱል ነጅምን በቀሩ ጊዜ ሰገድኩ፣ ከእርሳቸው ጋር ሙስሊሞች፣ ሙሽሪኮች፣ ጂኒዎችና ሰዎችም ሰገዱ عَنِ ابْنِ عَبَّاسٍ ـ رضى الله عنهما أَنَّ النَّبِيَّ صلى الله عليه وسلم سَجَدَ بِالنَّجْمِ وَسَجَدَ مَعَهُ الْمُسْلِمُونَ وَالْمُشْرِكُونَ وَالْجِنُّ وَالإِنْسُ‏.‏ ።

አረብ ሙሽሪኮች የሰገዱበት ምክንያት “”አል-ላትንና አል-ዑዛን አያችሁን? ሦስተኛይቱንም አነስተኛዋን መናትን?”” የሚለውን አንቀጽ ነብያችን”ﷺ” ስላነበቡ እንደሆነ ሰሒህ የሆነው ሐዲስ ላይ ከላይ ተቀምጧል።
ይህ የመጀመሪያው እይታ ሲሆን ነገር ግን ሁለተኛው እይታ ከዚህ በኃላ ያለው ታሪክ ኢብኑ ሃጅር አል አስቃላኒ እና ሼኽ አልባኒ ደኢፍ ነው ብለው አስቀምጠውታል፤ ራዚም፦ “በሙናፊቃን የተቀጠፈ መውዱዕ ነው” ብሏል(ተፍሲሩል ራዚ 11/134)። በተጨማሪም ኢብኑ ከሲር ሲናገር ይህ ታሪክ ደኢፍ ነው ብሎ ከደኢፍ ሁለተኛውን ክፍል ሙርሰል እንደሆነና በእርሱ አስተሳሰብ ሳሒህ እንዳልሆነ ተናግሯል። ይህንን ደኢፍ ታሪክ ኢብኑ ሂሻም፣ አል-ፈይሩዝ አባዲ፣ ተፍሲሩል ጀላለይን እና ኢብኑ ጀሪር አጥ-ጣባሪ ዘግበውታል፤ እንደውም ኢብኑ ጀሪር አጥ-ጣባሪ መግቢያው ላይ እንዲህ ይላል፦
“በዚህ መጽሐፍ ትረካ አንባቢ ተቃራኒ ወይም ተገቢ ሆኖ በሚያገኝበት ጊዜ ይህ የእኛ ባህርይ እንዳልሆነ ማወቅ አለበት፤ ነገር ግን ካለፉት ሰዎች ወደ እኛ የተላለፈ ትረካ ነው” (ታሪኩር ረሱል ወል ሙልክ ቅፅ 1, ገፅ 3)
ስለዚህ ከዚህ በታች ያለው የኢብኑ ጀሪር አጥ-ጣባሪ ትረካ ደኢፍ የሆሃንበት አጋጣሚ አለ ማለት ነው፤ አንዳንድ ሙፈሲሪን መሰረት ያደረጉበትን የኢብኑ ጀሪር አጥ-ጣባሪ ትረካ እስቲ እንየው፦
“አላህ፦ “በኮከብ እምላለሁ በገባ ጊዜ፡፡ ባልደረባችሁ አልተሳሳተም፤ አልጠመመምም፡፡ ከልብ ወለድም አይናገርም፡” የሚለውን አንቀጽ አወረደ፤ በመቀጠል፦
“አል-ላትንና አል-ዑዛን አያችሁን? ሦስተኛይቱንም አነስተኛዋን መናትን?”
ይህንን በአነበቡ ጊዜ ሸይጣን “”በንባቡ ላይ””፦
“ቲልከል ገራኒቁል ዑልያ፤ ወኢንነ ሸፋዐተሁንነ ለቱርጃ” تِلْكَ الْغَرَانِيقُ الْعُلْيَ وَ إِنَّ شَفاَعَتَهُنَّ لَتُرْجَى.
‹እነዚህ የተከበሩ ናቸው ምልጃቸው ተቀባይነት ያገኘው ናቸው› የሚለውን ቃል ጣለ።
አላህም፦ “ከመልክተኛና ከነቢይም ከአንተ በፊት አንድንም አላክንም ባነበበ ጊዜ ሰይጣን በንባቡ ላይ የሚጥል ቢሆን እንጅ፡፡ ወዲያውም አላህ ሰይጣን የሚጥለውን ያስወግዳል” የሚለውን አንቀፅ አወረደ።
(ታሪኩር ረሱል ወል ሙልክ ቅፅ 1, ገፅ 108)

“በንባቡ ላይ” ተብሎ የተቀመጠው ቃል “ፊ ዑምኒይየቲሂ” فِي أُمْنِيَّتِهِ ሲሆን በነብያችን”ﷺ” ንባብ ማለትም “አል-ላትንና አል-ዑዛን አያችሁን? ሦስተኛይቱንም አነስተኛዋን መናትን?” ብለው ባሉ ጊዜ ጎን ለጎን ሸይጣን፦ ‹እነዚህ የተከበሩ ናቸው ምልጃቸው ተቀባይነት ያገኘው ናቸው› የሚለውን ቃል ጣለ። እንግዲህ ይህ ነው “ቂሰቱል ገራኒቅ” የሚባለው፤ ሙሽሪክ ከሃድያን ይህ ሱራ ሲነበብ «ይህንን ቁርኣን አታዳምጡ፡፡ ታሸንፉም ዘንድ ሲነበብ በእርሱ ውሰጥ ተንጫጩ» አሉ፦
41፥26 እነዚያም የካዱት «ይህንን ቁርኣን አታዳምጡ፡፡ ታሸንፉም ዘንድ “ሲነበብ” በእርሱ ውሰጥ ተንጫጩ» አሉ وَقَالَ ٱلَّذِينَ كَفَرُوا۟ لَا تَسْمَعُوا۟ لِهَٰذَا ٱلْقُرْءَانِ وَٱلْغَوْا۟ فِيهِ لَعَلَّكُمْ تَغْلِبُونَ ፡፡

በዚህ ሰአት ከእውነት “በራቀ ጭቅጭቅ ውስጥ” ሆነው “አል-ላትንና አል-ዑዛን አያችሁን? ሦስተኛይቱንም አነስተኛዋን መናትን?” የሚለው አንቀፅ ሲነበብ በሚንጫጩት ልብ ውስጥ ፈተና ሊያደርግ ሸይጣን ልብስብስን ቃልን ጣለ፤ ሁልጊዜ በእያንዳንዱ ነብይ ዘመን ነብዩ ባነበበ ጊዜ ሰይጣን ልቦቻቸውም ደረቆች በሆኑት ውስጥ ልብስብስን ቃልን ይጥላል፤ ይህን የሚያደርገው የቀጠፈውን እንዲቀጣጥፉ ነው፦
22፥53 ሰይጣን የሚጥለውን ነገር ለእነዚያ በልቦቻቸው ውስጥ በሽታ ላለባቸው ልቦቻቸውም ደረቆች ለሆኑት ፈተና ሊያደርግ ይጥላል፡፡ በዳዮችም ከእውነት “በራቀ ጭቅጭቅ ውስጥ” ናቸው لِّيَجْعَلَ مَا يُلْقِى ٱلشَّيْطَٰنُ فِتْنَةًۭ لِّلَّذِينَ فِى قُلُوبِهِم مَّرَضٌۭ وَٱلْقَاسِيَةِ قُلُوبُهُمْ ۗ وَإِنَّ ٱلظَّٰلِمِينَ لَفِى شِقَاقٍۭ بَعِيدٍۢ ፡፡
6:112-113 እንደዚሁም *ለነቢያት ሁሉ ከሰውና ከጋኔን የኾኑን ሰይጣናት ጠላት አደረግን*፡፡ ከፊላቸው ወደ ከፊሉ ለማታለል *ልብስብስን ቃል ይጥላሉ*፡፡ ጌታህም በሻ ኖሮ ባልሠሩት ነበር፡፡ *ከቅጥፈታቸውም ጋር ተዋቸው*፡፡ *የሚጥሉትም ሊያታልሉ* እና የእነዚያም በመጨረሻይቱ ሕይወት የማያምኑት ሰዎች ልቦች ወደእርሱ እንዲያዘነብሉ እንዲወዱትም እነርሱ *ይቀጥፉ የነበሩትንም እንዲቀጣጥፉ* ነው፡፡
22፥52 ከመልክተኛና ከነቢይም ከአንተ በፊት አንድንም አላክንም ባነበበ ጊዜ ሰይጣን በንባቡ ላይ የሚጥል ቢሆን እንጅ፡፡ ወዲያውም አላህ ሰይጣን የሚጥለውን ያስወግዳል፡፡ ከዚያም አላህ አንቀጾቹን ያጠነክራል፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው وَمَآ أَرْسَلْنَا مِن قَبْلِكَ مِن رَّسُولٍۢ وَلَا نَبِىٍّ إِلَّآ إِذَا تَمَنَّىٰٓ أَلْقَى ٱلشَّيْطَٰنُ فِىٓ أُمْنِيَّتِهِۦ فَيَنسَخُ ٱللَّهُ مَا يُلْقِى ٱلشَّيْطَٰنُ ثُمَّ يُحْكِمُ ٱللَّهُ ءَايَٰتِهِۦ ۗ وَٱللَّهُ عَلِيمٌ حَكِيمٌۭ ፡፡
ይህ አንቀፅ ሙጅመል ማለትም ጥቅላዊ ነው፤ ምክንያቱም *”ከአንተ በፊት”* የሚለው ገለጻ ከነብያችን በፊት በነበሩት ነብያትና መልእክተኞችም ላይም ከሰውና ከጋኔን የኾኑን ሰይጣናት ለማታለል *ልብስብስን ቃል* ይጥላሉ፤ ወዲያውም አላህ ሰይጣን የሚጥለውን ያስወግዳል፡፡ ከዚያም አላህ አንቀጾቹን ያጠነክራል፤ ሸኹል ኢስላም ኢብኑ ተምያህ ይህንን እይታ ይጋራሉ። ነገር ግን በወቅቱ ነብያችን”ﷺ” “አል-ላትንና አል-ዑዛን አያችሁን? ሦስተኛይቱንም አነስተኛዋን መናትን?” የሚለው አንቀጽ በአሉታዊ መልኩ አንብበው ሲጨርሱ በንባቡ ላይ ሸይጣን፦ “እነዚህ የተከበሩ ናቸው ምልጃቸው ተቀባይነት ያገኘው ናቸው” የሚለውን ለሙሽሪኮች ሲያነብ ሙሽሪኮች ይህን ቃል ሲሰሙ፦ “ነቢዩ”ﷺ” አማልክቶቻችንን አወድሷል” ሲሉ ዋሹ፤ የዚህ ቅጥፈት ዜና ወደ ሐበሻ ከተሰደዱ ሰሐቦች ዘንድ ከእውነታው እጅግ በተለየና በራቀ መልኩ ተሰማ፤ አላህም ነብያችንን”ﷺ” “ከዚያም ወደ አንተ ካወረድነው ሌላን በእኛ ላይ ትዋሽ ዘንድ ሊፈትኑህ በእርግጥ ተቃረቡ፡፡ ያን ጊዜም ወዳጅ አድርገው በያዙህ ነበር” በማለት ይህ ቅጥፈት ለማስዋሸት ፈተና መሆኑን እና ቢዋሹ ወዳጆች አድርገው ይይዧቸው እንደነበር ተናገረ፦
17፥73 እነሆ ከዚያም ወደ አንተ ካወረድነው ሌላን በእኛ ላይ ትዋሽ ዘንድ ሊፈትኑህ በእርግጥ ተቃረቡ፡፡ ያን ጊዜም ወዳጅ አድርገው በያዙህ ነበር وَإِن كَادُوا۟ لَيَفْتِنُونَكَ عَنِ ٱلَّذِىٓ أَوْحَيْنَآ إِلَيْكَ لِتَفْتَرِىَ عَلَيْنَا غَيْرَهُۥ ۖ وَإِذًۭا لَّٱتَّخَذُوكَ خَلِيلًۭا ፡፡

ሙሽሪኮች ጠላት መሆናቸው በራሱ ከአላህ ቃል ሌላ ቃልን እንዳልተናገሩ በቂ ማስረጃ ነው፤ ምክንያቱም ነብያችንን”ﷺ” ወዳጅ አድርገው አለመያዛቸው ነው፤ በተጨማሪም በመቀጠል ከአላህ ውጪ ከሌላ ማንነት ሆነ ምንነት ከፊል ቃልን አምጥቶ ቢቀጥፉ የልብ ስራቸውን እንደሚቆርጥ በመናገር ከሌላ ህልውና ምንም እንዳላሉ መስክሮላቸዋል፤ ፦
69፥44-46 በእኛ ላይም ከፊልን ቃላት ያላልነውን “በቀጠፈ” ኖሮ وَلَوْ تَقَوَّلَ عَلَيْنَا بَعْضَ ٱلْأَقَاوِيلِ ፤ በኀይል በያዝነው ነበር لَأَخَذْنَا مِنْهُ بِٱلْيَمِينِ ፡፡ ከዚያም ከእርሱ የልቡን ሥር በቆረጥን ነበር ثُمَّ لَقَطَعْنَا مِنْهُ ٱلْوَتِينَ ፡፡

“”የልቡን ሥር በቆረጥን ነበር “”ብሎ ማለት የቱን ያህል በግህደተ-መለኮት ቀልድ እንደሌለ የሚያሳይ ሃይለ-ቃል ነው። ከአላህ ወዲህ የትኛው ንግግር ማስረጃ ሊሆን ይችላል? ቁርአንን አላህ ነው ያወረደው፤ አላህ ከሰው ሆነ ከሸይጣን ቃላት ጠብቆታል፣ ከኋላውም ከፊቱም ውሸት አይመጣበትም፦
15:9 እኛ ቁርኣንን እኛው አወረድነው፡፡ እኛም ለእርሱ ጠባቂዎቹ ነን፡፡
41:42 ከኋላውም ከፊቱም ውሸት አይመጣበትም፤ ጥበበኛ ምስጉን ከሆነውጌታ የተወረደ ነው።

በቂሰቱል ገራኒቅ ዋቢ ደርስ የዶክተር ሸኽ ያሲር ”ሀፊዘሁላህ” ሌክቸር እዚህ ይመልከቱ፦
https://youtu.be/wFq5ZnD6pFQ
መደምደሚያ
ይህንን የተመታ እና የተመምታታ ውሃ የማያነሳ ሙግት ሳልማን ሩሽዲ በ 1988 AD “ሰይጣናዊ አንቀፅ” የሚል መጽሐፉን ሲያራግቡ ከነበሩት መካከል ሚሽነሪዎች አንዶቹ ናቸው፤ እስቲ በዚህ ሂስ ባይብል ላይ ያለውን ዳዊት እንመልከተው፤ ይህን ሙግት የዳዊትን ነብይነት ለማስተባበል ሳይሆን እሾህክን በእሾክ እንዴት እንደሆነ ለማሳየት ነው፤ ዳዊት እስራኤልን ቁጠር ሳይባል ቆጥሮ ዳዊት በሰራው ስህተት እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ቸነፈርን ልኮ ከእስራኤልም ሰባ ሺህ ሰዎች በመቅሰፍት ገደለ፦
2ኛ ሳሙኤል 24.14 እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ቸነፈርን ሰደደ፤ ከእስራኤልም ሰባ ሺህ ሰዎች ወደቁ።

ይህ ስህተት የራሱ የዳዊት እንደሆነ አምኗል፣ ይቅርታም ጠይቋል፣ ከዚያም ባሻገር ይህ የእኔ ስህተት ነው ህዝቡን አትንካ ብሎ ጸለየ፣ ነገር ግን የዳዊት ልመናም አልሰራም፦
1ኛ ዜና መዋዕል 21፥8 ዳዊትም እግዚአብሔርን፦ ይህን በማድረግ እጅግ በድያለሁ፤ አሁን ግን ታላቅ ስንፍና አድርጌአለሁና የባሪያህን ኃጢአት ታስወግድ ዘንድ እለምንሃለሁ አለው።
1ኛ ዜና መዋዕል 21፥17 ዳዊትም እግዚአብሔርን፦ ሕዝቡ ይቈጠር ዘንድ ያዘዝሁ እኔ አይደለሁምን? የበደልሁና ክፉ የሠራሁ እኔ ነኝ፤ እነዚህ በጎች ግን ምን አድርገዋል? አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ትሁን፥ ነገር ግን ይቀሠፍ ዘንድ በሕዝብህ ላይ አትሁን አለው።

ታዲያ ዳዊት ማን ቁጠር ብሎት ነው የቆጠረው? ስንል! ዳዊት እስራኤልን የቆጠረው ሰይጣን “ቁጠር” ብሎት ነው ይለናል፦
2ኛ ሳሙኤል 24.1 ደግሞም የእግዚአብሔር ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ ዳዊትንም፦ *ሂድ፥ እስራኤልንና ይሁዳን ቍጠር* ብሎ በላያቸው አስነሣው።

ሂድ፥ እስራኤልንና ይሁዳን ቍጠር ያለው ሰይጣን ነው፥ እርሱ የተባለው ህቡዕ ተውላጠ-ስም ሰይጣን መሆኑን ሌላ ጥቅስ ይነግረናል፦
1ኛ ዜና መዋዕል 21፥1 ሰይጣንም በእስራኤል ላይ ተነሣ፥ እስራኤልንም ይቈጥር ዘንድ ዳዊትን “አንቀሳቀሰው”።

“አንቀሳቀሰው” ብለው ያስቀመጡት የዕብራይስጡ ቃል “የሰት” תְּסִיתֵ֥נִי ሲሆን “ሱት” סוּת ማለትም “አሳሳተ” ከሚል ግስ የመጣ ነው ፣ ለሃሰተኛ ነብይ ማሳሳት “የስቲአከ” יְסִֽיתְךָ֡ ማለትም “ቢያስትህ” በሚል መጥቷል፦
ዘዳግም 13.6 አንተም አባቶችህም የማታውቋቸውን ሌሎች አማልክት እናምልክ ብሎ ቢያስትህ יְסִֽיתְךָ֡፥

ዳዊትም ከሰይጣን መልዕክት የተቀበለውን ለኢዮአብንና ለሕዝቡ አለቆች ቍጠሩ ብሎ አስተላልፏል፦
ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 21.8 ዳዊትም ኢዮአብንና የሕዝቡን አለቆች፦ ሂዱ፥ ከቤርሳቤህ ጀምሮ እስከ ዳን ድረስ እስራኤልን ቍጠሩ፥ ድምራቸውንም አውቅ ዘንድ አስታውቁኝ አላቸው።

አንዱ ይህንን ሙግት ሳቀርብለት ዳዊት ነብይ አይደለም ብሎ ሽምጥጥ አድርጎ ሊክደኝ ሞክሯል፤ በባይብል የተገለጸው ዳዊት የፈጣሪ ነብይ እንደሆነ ይናገራል፦
የሐዋርያት ስራ 2፡29-30 ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም ለእናንተ በግልጥ እናገር ዘንድ ፍቀዱልኝ፤ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ ነው። *ነቢይ ስለ ሆነ*፥

አዎ ዳዊት ነብይ ነበረ ከተባለ፤ የነብይ መስፈርቱ ከፈጣሪ መልዕክት መቀበል ወይስ ከሰይጣን መልዕክት መቀበል ? ፍርዱን ለኅሊና።

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሰላሙ አለይኩም
ጨውን ሺ ጊዜ "እሬት ነው" ብትለው ስሙን እንጂ ጣዕሙን መቀየር አችልም። እንዲሁ ቁርኣንን ሺ ጊዜ "ውሸት ነው" ብትለው ስሙን እንጂ የምታጠለሸው መለኮታዊ እውነትነቱን መቀየር አትችልም
ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://tttttt.me/Wahidcom
ጥንቧ ዘረኝነት

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

49፥13 *እናንተ ሰዎች ሆይ! እኛ ከወንድና ከሴት ፈጠርናችሁ፡፡ እንድትተዋወቁም ጎሳዎችና ነገዶች አደረግናችሁ፡፡ አላህ ዘንድ በላጫችሁ በጣም አላህን ፈሪያችሁ ነው፡፡ አላህ ግልጽን ዐዋቂ ውስጥንም ዐዋቂ ነው*፡፡ يَا أَيُّهَا النَّاسُ إِنَّا خَلَقْنَاكُم مِّن ذَكَرٍ وَأُنثَىٰ وَجَعَلْنَاكُمْ شُعُوبًا وَقَبَائِلَ لِتَعَارَفُوا ۚ إِنَّ أَكْرَمَكُمْ عِندَ اللَّهِ أَتْقَاكُمْ ۚ إِنَّ اللَّهَ عَلِيمٌ خَبِيرٌ

“ዘረኝነት”racism” ማለት የራስን ቋንቋና ዘውግ አተልቆ የሌላውን ማሳነስ፣ ማግለል፣ መቃረን እና ማራከስ ነው። ዘረኝነት ትዳርን፣ ቤተሰብን፣ ጉርብትናን፣ ማህበረሰብን፣ ሃይማኖት፣ መንግሥትን፣ አገርን የሚበትን ክፉ በሽታ ነው። ዘረኝነት፣ ጎጠኝነት፣ ጠርዘኝነት፣ ቡድንተኝነት ምንጫቸው “አህዋ” أَهْوَآء ማለትም “ዝንባሌ”inclination” ነው፤ አንድ ሙስሊም ነፍሱንም ከዝንባሌዋ የከለከለ ገነት እርሷ በእርግጥ መኖሪያው ናት፦
79፥40-41 በጌታው ፊት መቆምን የፈራ ሰውማ *ነፍሱንም ከዝንባሌዋ የከለከለ ገነት እርሷ በእርግጥ መኖሪያው ናት*፡፡ وَأَمَّا مَنْ خَافَ مَقَامَ رَبِّهِ وَنَهَى النَّفْسَ عَنِ الْهَوَىٰ فَإِنَّ الْجَنَّةَ هِيَ الْمَأْوَىٰ

ዝንባሌ ደግሞ ከተከተሉት ሊመለክ የሚችል አደገኛ ጣዖት ነው፦
25:43 *ዝንባሌውን አምላኩ አድርጎ የያዘውን ሰው አየህን? አንተ በእርሱ ላይ ጠባቂ ትሆናለህን?* أَرَأَيْتَ مَنِ اتَّخَذَ إِلَـٰهَهُ هَوَاهُ أَفَأَنتَ تَكُونُ عَلَيْهِ وَكِيلًا

ዘረኝነት ምንጯ ዝንባሌ ከሆነ ታዲያ ከዘረኝነት በሽታ ለመገላገል መፍትሔው ምንድን ነው? አዎ አምላካችን አላህ በቅዱስ ቃሉ የሚናገረውን እና ነብያችን”ﷺ” በሐዲሳቸው የተናገሩትን በጥሞና ሰምቶ መተግበር ነው፤ እስቲ ከቁርኣን እንጀምር፦
4፥1 *እናንተ ሰዎች ሆይ! ያንን ከአንዲት ነፍስ የፈጠራችሁን ከእርስዋም መቀናጆዋን የፈጠረውን ከእነርሱም ብዙ ወንዶችንና ሴቶች የበተነውን ጌታችሁን ፍሩ*፡፡ يَا أَيُّهَا النَّاسُ اتَّقُوا رَبَّكُمُ الَّذِي خَلَقَكُم مِّن نَّفْسٍ وَاحِدَةٍ وَخَلَقَ مِنْهَا زَوْجَهَا وَبَثَّ مِنْهُمَا رِجَالًا كَثِيرًا وَنِسَاءً

“ነፍሥ” نَفْس የሚለው ቃል አደምን ያሳያል፤ “መቀናጃዋ” ተብሎ የተቀመጠው ቃል ”ዘውጀሃ” زَوْجَهَا ሲሆን የአደም ጥንድን ያሳያል፤ ይህቺም ጥንድ ሐዋ ናት፤ “ነፍሥ” በሚለው መነሻ ቅጥያ ላይ “ከ” የሚል መስተዋድድ አለ፤ ይህም ከአደም መፈጠራችንን ያሳያል፤ “ከእነርሱም” ተብሎ የተቀመጠው ቃል “ሚንሁማ” مِنْهُمَا ሲሆን ሙተና ማለትም ሁለትዮሽ”dual” የሚያሳይ ነው፤ እነዚህ ሁለቱ አደምና ሐዋ ናቸው፤ “እነርሱም” በሚለው መነሻ ቅጥያ ላይ “ከ” የሚል መስተዋድድ አለ፤ ይህም ከአደምና ከሐዋ መፈጠራችንን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ታዲያ የአንድ እናት እና አባት ልጆች ከሆንን አንዱን ዘር ማብለጥ ሌላውን ማሳነስ ጠባብነት አይደለምን? አንድ ሙስሊምስ እንዲህ አይነት ውዝግብ ውስጥ መግባት የእምነትን ገመድ የሚበጥስ አይደለምን? አላህ ሁላችንንም የፈጠረን ከአንድ አባትና እናት ነው፦
49፥13 *እናንተ ሰዎች ሆይ! እኛ ከወንድና ከሴት ፈጠርናችሁ፡፡ እንድትተዋወቁም ጎሳዎችና ነገዶች አደረግናችሁ፡፡ አላህ ዘንድ በላጫችሁ በጣም አላህን ፈሪያችሁ ነው፡፡ አላህ ግልጽን ዐዋቂ ውስጥንም ዐዋቂ ነው*፡፡ يَا أَيُّهَا النَّاسُ إِنَّا خَلَقْنَاكُم مِّن ذَكَرٍ وَأُنثَىٰ وَجَعَلْنَاكُمْ شُعُوبًا وَقَبَائِلَ لِتَعَارَفُوا ۚ إِنَّ أَكْرَمَكُمْ عِندَ اللَّهِ أَتْقَاكُمْ ۚ إِنَّ اللَّهَ عَلِيمٌ خَبِيرٌ

“ወንድ” እና “ሴት” በሚለው መነሻ ቅጥያ ላይ “ከ” የሚል መስተዋድድ አለ፤ ይህም ሰዎች ከወንድና ከሴት መፈጠራቸውን ያሳያል፤ አላህ ነገድ እና ጎሳ ያደረገን ብዙ ስለሆንን ለትውውቅ የትውልድ መዝገብ እንጂ አላህ ዘንድ ማነስ እና መተለቅ አላህ በመፍራት ብቻ ነው።
አማራ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ፣ ትግሬ ወዘተ ቋንቋ ነው፤ የቋንቋዎቻችን መለያየት ከአስደናቂ ታምራቶቹ ነው፤ በዚህ ውስጥ ለዐዋቂዎች ተዓምራቶች አሉበት፦
30፥22 ሰማያትንና ምድርንም መፍጠሩ፣ *የቋንቋዎቻችሁ እና የመልኮቻችሁም መለያየት ከአስደናቂ ታምራቶቹ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ለዐዋቂዎች ተዓምራቶች አሉበት*፡፡ وَمِنْ آيَاتِهِ خَلْقُ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ وَاخْتِلَافُ أَلْسِنَتِكُمْ وَأَلْوَانِكُمْ ۚ إِنَّ فِي ذَٰلِكَ لَآيَاتٍ لِّلْعَالِمِينَ

ቋንቋዎች ይዘውት የመጡት ታሪክ፣ ባህል፣ ልማድ፣ ትውፊት፣ ወግ፣ ክህሎት እና ሙዳየ-ቃላት “ዘውግ” ethnic” ሆኗል፤ ይህ እራሱ የቻለ ውበት ነው። ነገድ እና ጎሳ ለዐዋቂዎች ተዓምራቶችና መተዋወቂያ ነው። ዘረኝነት ግን ከቋንቋ አሊያም ከቀለም የሚመጣ ሳይሆን የልብና የአስተሳሰብ በሽታ ነው። በኢስላም ደሃ ሃብታም ሳንል፤ ዘመድ ባዕድ ሳንል፣ ዝንባሌ ተከትለን ሳናዳላ ለአላህ ብለን ለሰው ሁሉ በትክክል ፍትሕ ቀዋሚዎች መሆን አለብን፦
4፥135 እናንተ ያመናችሁ ሆይ! *በትክክል ፍትሕ ቀዋሚዎች በራሳችሁ ወይም በወላጆችና በቅርብ ዘመዶች ላይ ቢኾንም እንኳ ለአላህ መስካሪዎች ኹኑ፡፡ ሀብታም ወይም ድኻ ቢኾን አላህ በእነርሱ ከእናንተ ይበልጥ ተገቢ ነው፡፡ እንዳታደሉም ዝንባሌን አትከተሉ፡፡ ብታጠምሙም ወይም መመስከርን ብትተው አላህ በምትሠሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው*፡፡ يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا كُونُوا قَوَّامِينَ بِالْقِسْطِ شُهَدَاءَ لِلَّهِ وَلَوْ عَلَىٰ أَنفُسِكُمْ أَوِ الْوَالِدَيْنِ وَالْأَقْرَبِينَ ۚ إِن يَكُنْ غَنِيًّا أَوْ فَقِيرًا فَاللَّهُ أَوْلَىٰ بِهِمَا ۖ فَلَا تَتَّبِعُوا الْهَوَىٰ أَن تَعْدِلُوا ۚ وَإِن تَلْوُوا أَوْ تُعْرِضُوا فَإِنَّ اللَّهَ كَانَ بِمَا تَعْمَلُونَ خَبِيرًا
6፥152 *”በተናገራችሁም ጊዜ በዘመዶቻችሁ ላይ ቢኾንም እንኳ እውነትን በመናገር አስተካክሉ”*፡፡ በአላህም ቃል ኪዳን ሙሉ፡፡ እነሆ ትገሰጹ ዘንድ በርሱ አዘዛችሁ፡፡ وَإِذَا قُلْتُمْ فَاعْدِلُوا وَلَوْ كَانَ ذَا قُرْبَىٰ ۖ وَبِعَهْدِ اللَّهِ أَوْفُوا ۚ ذَٰلِكُمْ وَصَّاكُم بِهِ لَعَلَّكُمْ تَذَكَّرُونَ
ስለዚህ የቋንቋዎቻችሁ እና የመልኮቻችሁም መለያየት ከአስደናቂ ታምራቶቹ እንጂ መኩሪያ ወይም ማብጠልጠሊያ አይደለም፤ ዘረኝነት በዲንያ በአላህ ዘንድ ዋጋ የሚያሳጣ ሲሆን በአኺራም ደግሞ ለጀሃነም ይዳርጋል፦
ሱነን አቢ ዳውድ መጽሐፍ 43, ሐዲስ 344
አቢ ሁረይራህ”ረ.ዐ” እንደተረከው፤ የአላህ መልእክተኛም”ﷺ” አሉ፦ *”አላህ ዐዘ ወጀል ከእናንተ የዘመነ-ጃሂሊያን ኩራት አስወግዷል፤ ይህም በዘር መኩራት ነው። ይህ ለጥንቁቁ አማኝም ወይም ለአደገኛው ካሃዲ አንድ ብቻ ነው። እናንተ የአደም ልጆች ናችሁ፤ አደም ከአፈር ነው የመጣው፤ ሰዎች በዘራቸው የሚኮሩ ከሆነ ጀሃነምን ይሞሏታል፤ ወይም አላህ ዘንድ ዋጋቸው ጥንዚዛ በአፍንጫው ከሚሽከረከር ጉድፍ ያነሰ ከሆኑት ይሆናል*። عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم ‏ “‏ إِنَّ اللَّهَ عَزَّ وَجَلَّ قَدْ أَذْهَبَ عَنْكُمْ عُبِّيَّةَ الْجَاهِلِيَّةِ وَفَخْرَهَا بِالآبَاءِ مُؤْمِنٌ تَقِيٌّ وَفَاجِرٌ شَقِيٌّ أَنْتُمْ بَنُو آدَمَ وَآدَمُ مِنْ تُرَابٍ لَيَدَعَنَّ رِجَالٌ فَخْرَهُمْ بِأَقْوَامٍ إِنَّمَا هُمْ فَحْمٌ مِنْ فَحْمِ جَهَنَّمَ أَوْ لَيَكُونُنَّ أَهْوَنَ عَلَى اللَّهِ مِنَ الْجِعْلاَنِ الَّتِي تَدْفَعُ بِأَنْفِهَا النَّتْنَ ‏”‏

የአደም ልጆች የአንድ አባት እና እናት ልጆች ነን ብሎ ማስተንተን መጠበብ ሲሆን በዘረኝነት አራንቋ መለከፍ መጥበብ ነው፦
ሱነን ነሳኢ መጽሐፍ 37 , ሐዲስ 150
ጁንደብ ኢብኑ ዐብደላህ እንደተረከው፦ “የአላህ መልእክተኛም”ﷺ” አሉ፦ *”ማንም ሰው ግልጽ ባልሆነ ነገር፣ በዘረኝነት ጥብቅና፣ በዘረኝነት መንገድ የተጋደለ ግድያው የጃህሊያ ነው*። عَنْ جُنْدُبِ بْنِ عَبْدِ اللَّهِ، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم ‏ “‏ مَنْ قَاتَلَ تَحْتَ رَايَةٍ عُمِّيَّةٍ يُقَاتِلُ عَصَبِيَّةً وَيَغْضَبُ لِعَصَبِيَّةٍ فَقِتْلَتُهُ جَاهِلِيَّةٌ ‏”‏

“ጃህሊያህ” جَاهِلِيَّةٌ ማለት “መሃይምነት” ማለት ነው፤ ቅድመ-ቁርኣን ያለው ጊዜ ዘመነ-ጃህሊያህ ይባላል፤ በእርግጥም በዘመነ-ጃህሊያህ ጊዜ የነበረችው ዘረኝነት ጥንብ ናት፦
ኢማም ሙስሊም መጽሐፍ 45, ሐዲስ 81
ጃቢር ኢብኑ ዐብደላህ እንዳስተላለፈው፦ “በጉዞ ከነቢዩ”ﷺ” ጋር ነበርን፤ አንድ ሰው ከሙሃጅር ከአንሷር የሆነውን አንድ ሰው ጀርባውን መታው፤ አንሷሩም፦ “አንሷሪ ሆይ! አለ፤ ሙሃጅሩም፦ “ሙሃጅር ሆይ! አለ። ከዚያም የአላህ መልእክተኛም”ﷺ” *”ይህ የጃህሊያህ አጠራር አይደለምን? አሉ፤ እነርሱም፦ “የአላህ መልእክተኛ ሆይ! አንድ ሰው ከሙሃጅር ከአንሷር የሆነውን አንድ ሰው ጀርባውን መታው” አሉ፤ እርሳቸው፦ “እርሷን(ዘረኝነትን) ተዋት ጥንብ ናት” አሉ*። جَابِرَ بْنَ عَبْدِ اللَّهِ يَقُولُ كُنَّا مَعَ النَّبِيِّ صلى الله عليه وسلم فِي غَزَاةٍ فَكَسَعَ رَجُلٌ مِنَ الْمُهَاجِرِينَ رَجُلاً مِنَ الأَنْصَارِ فَقَالَ الأَنْصَارِيُّ يَا لَلأَنْصَارِ وَقَالَ الْمُهَاجِرِيُّ يَا لَلْمُهَاجِرِينَ ‏.‏ فَقَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم ‏”‏ مَا بَالُ دَعْوَى الْجَاهِلِيَّةِ ‏”‏ ‏.‏ قَالُوا يَا رَسُولَ اللَّهِ كَسَعَ رَجُلٌ مِنَ الْمُهَاجِرِينَ رَجُلاً مِنَ الأَنْصَارِ ‏.‏ فَقَالَ ‏”‏ دَعُوهَا فَإِنَّهَا مُنْتِنَةٌ ‏
‏ ‏
“ሙሃጅር” مُهَاجِر ማለት “ስደተኛ” ማለት ሲሆን ከመካ የተሰደዱትን ሶሓብይን ያመለክታል፤ “አንሷር” أَنْصَارٍ ማለት “ረዳት” ማለት ሲሆን ከመካ የተሰደዱት የተቀበሉ የመዲና ሶሓብይን ያመለክታል።
አንዱ ዘር ተነስቶ ሌላውን ዘር ሲበድል የተበደለው ያልበደለውን በዘሩ ብቻ በቁርሾ ለመበቀል መነሳት ጠባብነት ነው፤ በኢስላም የቀደሙት ትውልድ በሰሩት ወንጀል የአሁኑን ትውልድ መጠየቅ ወይም መቅጣት እራሱ ሕግ መተላለፍ ነው፦
ሱነን ነሳኢ መጽሐፍ 37 , ሐዲስ 162
ዐብደላህ እንደተረከው ነብዩም”ﷺ” አሉ፦.. *ሰው በአባቱ ወይም በወንድሙ ወንጀል አይቀጣም*። وَلاَ يُؤْخَذُ الرَّجُلُ بِجَرِيرَةِ أَبِيهِ وَلاَ بِجَرِيرَةِ أَخِيهِ ‏”

በተጨማሪም አንድ ሰው ባጠፋው ብዙኃኑን ዘር ማንቋሸሽ ወይም ማዋረድ ሐራም ነው፦
ሱነን ኢብኑ ማጃህ መጽሐፍ 33, ሐዲስ 106
ዓኢሻህ”ረ.ዐ.” እንደተረከችው፦ “የአላህ መልእክተኛ”ﷺ” እንዲህ አሉ፦ *”ከሰዎች መካከል ትልቁ ውሸታም ሌላው ሰው ማንቋሸሽ እና መላውን ዘር ማዋረድ ነው*። عَنْ عَائِشَةَ، قَالَتْ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ ـ صلى الله عليه وسلم ـ ‏ “‏ إِنَّ أَعْظَمَ النَّاسِ فِرْيَةً لَرَجُلٌ هَاجَى رَجُلاً فَهَجَا الْقَبِيلَةَ بِأَسْرِهَا

እረ እሩቅ ሳንሄድ ወደ ዘረኝነት የሚጣራ፣ በዘረኝነት መንገድ የሚታገል፣ በዘረኝነት መንገድ ሲከተል የሞተ ሰው ከነብያችን”ﷺ” ሱናህ ውጪ ነው፦
ሱነን አቢ ዳውድ መጽሐፍ 43, ሐዲስ 349
ጁበይር እንደተረከው፦ “የአላህ መልእክተኛ”ﷺ” እንዲህ አሉ፦ *”ወደ ዘረኝነት የሚጣራ ከእኛ አይደለም። በዘረኝነት መንገድ የሚታገኝ ከእኛ አይደለም። በዘረኝነት መንገድ ሲከተል የሞተ ከእኛ አይደለም*። عَنْ جُبَيْرِ بْنِ مُطْعِمٍ، أَنَّ رَسُولَ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم قَالَ ‏ “‏ لَيْسَ مِنَّا مَنْ دَعَا إِلَى عَصَبِيَّةٍ وَلَيْسَ مِنَّا مَنْ قَاتَلَ عَلَى عَصَبِيَّةٍ وَلَيْسَ مِنَّا مَنْ مَاتَ عَلَى عَصَبِيَّةٍ ‏”‏

በድንበር፣ በክልል፣ በወሰን የከፋፈሉን ሰዎች ናቸው። ምድር እኮ የአላህ ናት፤ ተቸግረን ብንሰደድ ሰፊ ናት፤ ዋናው ይህቺ አንድ የተውሒድ መንገድ ሃይማኖታችን ናትና አላህን በብቸኝነት ማምለክ ነው፦
29፥56 እናንተ ያመናችሁ ባሮቼ ሆይ! *ምድሬ በእርግጥ ሰፊ ናት፤ ብትቸገሩ ተሰደዱ፡፡ እኔንም ብቻ አምልኩኝ*፡፡ يَا عِبَادِيَ الَّذِينَ آمَنُوا إِنَّ أَرْضِي وَاسِعَةٌ فَإِيَّايَ فَاعْبُدُونِ
21፥91 *ይህች አንዲት መንገድ ስትሆን በእርግጥ ሃይማኖታችሁ ናት፡፡ እኔም ጌታችሁ ነኝና አምልኩኝ*፡፡ إِنَّ هَـٰذِهِ أُمَّتُكُمْ أُمَّةً وَاحِدَةً وَأَنَا رَبُّكُمْ فَاعْبُدُونِ
እንግዲህ ዲነል ኢስላምን የመሰለ ሰውን የሚያስተሳስር የአላህ ገመድ እያለ በዘረኝነት፣ በጎጠኝነት፣ በጠርዘኝነት፣ በቡድንተኝነት መለያየት “አትለያዩ” ያለን አላህ አለመታዘዝ ነው። በዘመነ-ጃህሊያህ ጊዜ ጠበኞችም በነበርን ጊዜ በእኛ ላይ የዋለውን የአላህን ጸጋ እናስታውስ፤ በልቦቻችሁም መካከል አስማማን፤ በጸጋውም ወንድማማቾች ሆንን፥ በእሳት ጉድጓድ አፋፍም ላይ በነበር ጊዜ አዳነን፦
3፥103 *የአላህንም የማመን ገመድ ሁላችሁም ያዙ፡፡ አትለያዩም፡፡ ጠበኞችም በነበራችሁ ጊዜ በእናንተ ላይ የዋለውን የአላህን ጸጋ አስታውሱ፡፡ በልቦቻችሁም መካከል አስማማ፡፡ በጸጋውም ወንድማማቾች ኾናችሁ፡፡ በእሳት ጉድጓድ አፋፍም ላይ ነበራችሁ፡፡ ከእርስዋም አዳናችሁ*፡፡ እንደዚሁ ትመሩ ዘንድ አላህ ለእናንተ አንቀጾቹን ያብራራል፡፡ وَاعْتَصِمُوا بِحَبْلِ اللَّهِ جَمِيعًا وَلَا تَفَرَّقُوا ۚ وَاذْكُرُوا نِعْمَتَ اللَّهِ عَلَيْكُمْ إِذْ كُنتُمْ أَعْدَاءً فَأَلَّفَ بَيْنَ قُلُوبِكُمْ فَأَصْبَحْتُم بِنِعْمَتِهِ إِخْوَانًا وَكُنتُمْ عَلَىٰ شَفَا حُفْرَةٍ مِّنَ النَّارِ فَأَنقَذَكُم مِّنْهَا ۗ كَذَٰلِكَ يُبَيِّنُ اللَّهُ لَكُمْ آيَاتِهِ لَعَلَّكُمْ تَهْتَدُونَ

በተሰጠን ጸጋ ልክ ወንድማማች መሆን ሲገባን ዛሬ በመሃይምነት አራንቋ ተጠቅተን በማህበራዊ ሚድያ ዘረኝነትን ስናራግብ እንውላለን፤ ኢስላም ዓለም-ዐቀፍ ሆኖ ሳለ ምነው ጠበብንሳ? ምነው ይህ ያህል ኢማናችን ወረደሳ? የኢሥላም ልዕልና ከዘር፣ ከብሔር፣ ከቋንቋ፣ ከቀለም፣ ከፓለቲካ በላይ ነው። አላህ ሁላችንም ያስተካክለን፥ ሂዳያ ይስጠን፣ ከጥንቧ ዘረኝነት ይጠብቀን! አሚን።

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሰላሙ አለይኩም
ኸምር

ገቢር አንድ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

2፥219 *አእምሮን ከሚቃወም መጠጥና ከቁማር ይጠይቁሃል፡፡ «በሁለቱም ውስጥ ታላቅ ኃጢኣትና ለሰዎች ጥቅሞች አሉባቸው፡፡ ግን ኃጢኣታቸው ከጥቅማቸው በጣም ትልቅ ነው» በላቸው*፡፡ يَسْأَلُونَكَ عَنِ الْخَمْرِ وَالْمَيْسِرِ ۖ قُلْ فِيهِمَا إِثْمٌ كَبِيرٌ وَمَنَافِعُ لِلنَّاسِ وَإِثْمُهُمَا أَكْبَرُ مِن نَّفْعِهِمَا

ከሚሽነሪዎች የሚሰነዘሩ ጥያቄዎች አብዛኛውን አርቲ ቡርቲና ቶራ ቦራ ናቸው፤ “አስካሪ መጠጥ በኢስላም ይፈቀዳል” የሚል ጥራዝ ነጠቅ መረጃ ይነዛሉ። ጠይቆ ከስሩ በአጽንኦትና በአንክሮት መረዳት የእናት ነው፤ “ነገርን ከስሩ ውሃን ከጡሩ” ይላል ያገሬ ሰው።
እስቲ ስለ ኸምር ጥልልና ጥንፍፍ ባለ መልኩ እናስተንትን፤ “ኸምር” خَمْر ማለት “ወይን ጠጅ” ማለት ሲሆን ከዘምባባ እና ከወይን ፍሬ የሚሰራ ጠጅ ነው፦
16፥67 *ከዘምባባዎች እና ከወይኖችም ፍሬዎች እንመግባችኋለን፡፡ ከእርሱ ጠጅን እና መልካም ምግብንም ትሠራላችሁ፡፡ በዚህም ውስጥ ለሚያስቡ ሕዝቦች በእርግጥ ተዓምር አለ*፡፡ وَمِن ثَمَرَاتِ النَّخِيلِ وَالْأَعْنَابِ تَتَّخِذُونَ مِنْهُ سَكَرًا وَرِزْقًا حَسَنًا ۗ إِنَّ فِي ذَٰلِكَ لَآيَةً لِّقَوْمٍ يَعْقِلُونَ

አላህ ከዘንባባ እና ከወይን ፍሬ ማብቀሉ በእርግጥ ታምር አለበት፤ ከዚህም ሰው በሰናይ መልካም ምግብ ማለትም ጭማቂ ሲሰራ በተቃራኒው እኩይ የሆነውን አስካሪ ጠጅን ይሰራል፤ “ዛሊከ” ذَٰلِكَ ማለትም “በዚህም” የተባለው አመልካች ተውላጠ-ስም”demonstrative pronoun ከበፊቱ ያለው “ሁ” هُ ማለትም “እርሱ” የተባለው ተሳቢ ተውላጠ-ስም”objective pronoun” የሚያመለክት ነው፤ ይህም “እርሱ” የተባለው ፍራፍሬው ነው፦
16፥11 *በእርሱ ለእናንተ አዝመራን፣ ወይራንም፣ ዘምባባዎችንም፣ ወይኖችንም፣ ከፍሬዎችም ሁሉ ያበቅልላችኋል፤ በዚህ ውስጥ ለሚያስተነትኑ ሕዝቦች በእርግጥ ታምር አለ*። يُنبِتُ لَكُم بِهِ الزَّرْعَ وَالزَّيْتُونَ وَالنَّخِيلَ وَالْأَعْنَابَ وَمِن كُلِّ الثَّمَرَاتِ ۗ إِنَّ فِي ذَٰلِكَ لَآيَةً لِّقَوْمٍ يَتَفَكَّرُونَ

እዚህ አንቀጽ ላይ “ዛሊከ” ذَٰلِكَ የተባለው የአዝመራን፣ የወይራንም፣ የዘምባባዎችንም፣ የወይኖችንም ፍራፍሬ ነው፤ ተጨማሪ አናቅጽ፦ 6፥99 13፥3 ይመልከቱ። ፍራፍሬ ሲቆይ ስኳርነቱ ወደ አሲድ ይቀየርና ያሰክራል፤ ይህ ሂደት በሥነ-ምርምር ጥናት ቆምጣጣነት”Fermentation” ይባላል፤ አሊያም ጌሾና ብቅል ሲቀላቀልበት ያሰክራል። ይህ ሂደት በሥነ-ምርምር ጥናት ፓስቸራዜሽን”Pasteurization” እና ኒዩትራላይዜሽን”Neutralization” ይባላል፤ ቢራ ፣ ቮድካ፣ ውስኪ የመሳሰሉት የዛ ውጤት ናቸው። ይህ ኣስካሪ መጠጥ አልኮልነት ሲኖረው የሰውን ህይወት በእጅጉ ይጎዳል፤ ነገር ግን በተፈጥሮ ሰውነታችን ውስጥ አልኮል ስላለ አልኮል ለጎደለው ሰውነት ጥቅም አለው፣ ከዚያም ባሻገር ጊዜአዊ ደስታ አለው። ነገር ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። አምላካችን አላህ ስለዚህ ጉዳይ እንዲህ ይለናል፦
2፥219 *አዕምሮን ከሚቃወም መጠጥ እና ከቁማር ይጠይቁሃል፡፡ «በሁለቱም ውስጥ ታላቅ ኃጢኣት እና ለሰዎች ጥቅሞች አሉባቸው፡፡ ግን ኃጢኣታቸው ከጥቅማቸው በጣም ትልቅ ነው» በላቸው*፡፡ يَسْأَلُونَكَ عَنِ الْخَمْرِ وَالْمَيْسِرِ ۖ قُلْ فِيهِمَا إِثْمٌ كَبِيرٌ وَمَنَافِعُ لِلنَّاسِ وَإِثْمُهُمَا أَكْبَرُ مِن نَّفْعِهِمَا

ቁማር ጥቅሙ ገንዘብ ቢሆንም የሰው ሃቅ ነውና ታላቅ ኃጢኣት ነው። አስካሪ መጠጥ ጥቅሙ ጊዚያዊ ደስታ ቢሆንም አዕምሮን የሚያደንዝና ለጥል፣ ለጥላቻ፣ ለዝሙት፣ ለጣዖት አምልኮ የሚዳርግ፤ ከሰላትና አላህ ከማውሳት የሚያዘናጋ እኩይ ነገር ስለሆነ ከሸይጧን ነው፦
5፥90 *እናንተ ያመናችሁ ሆይ! የሚያሰክር መጠጥ ቁማርም ጣዖታትም አዝላምም ከሰይጣን ሥራ የኾኑ እርኩስ ብቻ ናቸው፡፡ እርኩስን ራቁትም ልትድኑ ይከጀላልና*፡፡ يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا إِنَّمَا الْخَمْرُ وَالْمَيْسِرُ وَالْأَنصَابُ وَالْأَزْلَامُ رِجْسٌ مِّنْ عَمَلِ الشَّيْطَانِ فَاجْتَنِبُوهُ لَعَلَّكُمْ تُفْلِحُونَ
5፥91 *ሰይጣን የሚፈልገው በሚያሰክር መጠጥና በቁማር በመካከላችሁ ጠብንና ጥላቻን ሊጥል፤ አላህን ከማውሳት እና ከስግደትም ሊያግዳችሁ ብቻ ነው፡፡ ታዲያ እናንተ ከእነዚህ ተከልካዮች ናችሁን ተከልከሉ*፡፡ إِنَّمَا يُرِيدُ الشَّيْطَانُ أَن يُوقِعَ بَيْنَكُمُ الْعَدَاوَةَ وَالْبَغْضَاءَ فِي الْخَمْرِ وَالْمَيْسِرِ وَيَصُدَّكُمْ عَن ذِكْرِ اللَّهِ وَعَنِ الصَّلَاةِ ۖ فَهَلْ أَنتُم مُّنتَهُونَ

ነብያችንም”ﷺ” በሐዲስ ላይ አስካሪ መጠጥ መጠጣት ከልክለዋል፦
ኢማም ሙስሊም መጽሐፍ 36, ሐዲስ 81
ዐብደላህ ኢብኑ ቡረይዳህ አባቱ እንዳለው የአላህ መልእክተኛ”ﷺ” አሉ፦ *በኮዳ በስተቀር ከነቢድ የሚዘጋጅ ነገር እንዳትጠጡ ከልክያችሁ ነበር፤ ግን አሁን በሁሉም ሰፍነግ መጠጣት ትችላላችሁ። ነገር ግን አስካሪ መጠጥ እንዳትጠጡ*። عَنْ عَبْدِ اللَّهِ بْنِ بُرَيْدَةَ، عَنْ أَبِيهِ، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم ‏ “‏ نَهَيْتُكُمْ عَنِ النَّبِيذِ إِلاَّ فِي سِقَاءٍ فَاشْرَبُوا فِي الأَسْقِيَةِ كُلِّهَا وَلاَ تَشْرَبُوا مُسْكِرًا ‏”‏

“ነቢድ” نَّبِيذ ማለት ከዘምባባ እና ከወይን ፍሬ የሚጠጣ ጭማቂ ነው፤ ይህ ሃላል ሲሆን ይህ ጭማቂ ከሁለት ቀናት አሊያም ከሦስት ቀናት በኃላ “ሙሥኪር” مُسْكِر ወይም “ሠከር” سَكَر ማለትም “አስካሪ”intoxicant” ይሆናል፤ ይህንን መጠጣት ሃራም ነው፤ አይደለም ኸምር ጠጪው ይቅርና ቀጂውን፣ ሻጩንም፣ ገዢውንም፣ ጨማቂውን፣ አስጨማቂውን፣ ተሸካሚውን እና የሚሸከሙለትንም ሁሉ ተጠያቂዎች ናቸው፦
ሱነን አቢ ዳውድ መጽሐፍ 27, ሐዲስ 6: 
ዐብደላህ ኢብኑ ዑመር”ረ.ዐ.” እንዳስተላለፈው የአላህ መልክተኛም”ﷺ” አሉ፦ “አላህ ኸምርን ጠጪውን፣ ቀጂውን፣ ሻጩንም፣ ገዢውንም፣ ጨማቂውን፣ አስጨማቂውን፣ ተሸካሚውን እና የሚሸከሙለትንም ሁሉ ረግሟቸዋል” أَنَّهُمَا سَمِعَا ابْنَ عُمَرَ، يَقُولُ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم ‏ “‏ لَعَنَ اللَّهُ الْخَمْرَ وَشَارِبَهَا وَسَاقِيَهَا وَبَائِعَهَا وَمُبْتَاعَهَا وَعَاصِرَهَا وَمُعْتَصِرَهَا وَحَامِلَهَا وَالْمَحْمُولَةَ إِلَيْهِ ‏”‏

በዱኒያህ ያለው ኸምር አስካሪ እና ሃምራ ከሆነ ታዲያ በጀነት ያለው ኸምር ምንድን ነው? ኢንሻላህ ይህንን ነጥብ በክፍል ሁለት እንዳስሳለን።

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሰላሙ አለይኩም
ኸምር

ገቢር ሁለት

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

32፥17 ይሠሩትም በነበሩት ለመመንዳት ከዓይኖች መርጊያ ለእነርሱ *”የተደበቀላቸውን ጸጋ ማንኛይቱም ነፍስ አታውቅም”*፡፡ فَلَا تَعْلَمُ نَفْسٌ مَّا أُخْفِيَ لَهُم مِّن قُرَّةِ أَعْيُنٍ جَزَاءً بِمَا كَانُوا يَعْمَلُونَ

“ጀነት” جَنَّة የሚለው ቃል እራሱ “ጀነ” جَنَّ ማለትም “ተሰወረ” ወይም “ተደበቀ” ከሚል ግስ የመጣ ሲሆን “ድብቅ” ወይም “ስውር” ማለት ነው፤ በጀነት ውስጥ ያለው ለሙስሊሞች የተደበቀላቸውን ፀጋ ደግሞ ማንኛይቱም ነፍስ አታውቅም፦
32፥17 *"ይሠሩትም በነበሩት ለመመንዳት ከዓይኖች መርጊያ ለእነርሱ የተደበቀላቸውን ጸጋ ማንኛይቱም ነፍስ አታውቅም”*፡፡ فَلَا تَعْلَمُ نَفْسٌ مَّا أُخْفِيَ لَهُم مِّن قُرَّةِ أَعْيُنٍ جَزَاءً بِمَا كَانُوا يَعْمَلُونَ

አላህ በሐዲሰል ቁድሲይ ላይ የጀነት ፀጋ አይን አይቶት፣ ጆሮ፣ ሰምቶት፣ ልብ አስቦት የማያውቅ ለባሮቹ ያዘጋጃት እንደሆነች ነግሮናል፦
ኢማም ቡኻሪይ መጽሐፍ 97, ሐዲስ 123:
አቢ ሁረይራህ”ረ.ዐ.” እንደተረከው፦ ነብዩ”ﷺ” እንዲህ ብለው አሉ፦ *"አላህም እንዲህ አለ፦ እኔ ለደጋግ ባሮቼ አይን አይቶት የማያውቅ፣ ጆሮ ሰምቶት የማያውቅና በሰው ልቦና ውል ብሎ የማያውቅ ጸጋን አዘጋጅቻለው"*። عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ ـ رضى الله عنه ـ عَنِ النَّبِيِّ صلى الله عليه وسلم قَالَ ‏ “‏ قَالَ اللَّهُ أَعْدَدْتُ لِعِبَادِي الصَّالِحِينَ مَا لاَ عَيْنٌ رَأَتْ، وَلاَ أُذُنٌ سَمِعَتْ، وَلاَ خَطَرَ عَلَى قَلْبِ بَشَرٍ ‏”

ታላቁ ሰሓቢይ ዐብደሏህ ኢብኑ ዐባሥ”ረ.ዐ” እንዲህ ይላሉ፦ *"በጀነት ውስጥ ካሉ ነገሮች ዱንያ ውስጥ ምንም የለም ግን ከስሞች መመሳሰል በስተቀር”* (ተፍሲሩ አጥ-ጦበሪይ)

ስለዚህ በጀነት ውስጥ ያሉትን አላህ ለባሮቹ ያዘጋጃቸው ፀጋዎች አይን አይቶት፣ ጆሮ፣ ሰምቶት፣ ልብ አስቦት የማያውቅ ነገር ከሆነ ሙዝ፣ ዘንባባ፣ ወይን፣ ተምር የመሳሰሉት የስም መመሳሰል እንጂ ቅርጽና ይዘቱ፣ ጥፍጥናውና ጣእሙ ከዚህ ዓለም ጋር አንድ አይደለም፤ ይህን አምላካችን አላህ ሲናገር፦
47፥15 *የዚያች ጥንቁቆች ተስፋ የተሰጧት ገነት "ምሳሌ" በውስጧ ሺታው ከማይለወጥ ውሃ ወንዞች ጣዕሙ ከማይለውጥ ወተትም ወንዞች ለጠጪዎች ሁሉ ጣፋጭ ከኾነች የወይን ጠጅም ወንዞች፤ ከተነጠረ ማርም ወንዞች አሉባት፤ ለእነሱም በውስጧ ከፍሬዎች ሁሉ በያይነቱ ከጌታቸው ምሕረትም አላቸው*። مَّثَلُ الْجَنَّةِ الَّتِي وُعِدَ الْمُتَّقُونَ ۖ فِيهَا أَنْهَارٌ مِّن مَّاءٍ غَيْرِ آسِنٍ وَأَنْهَارٌ مِّن لَّبَنٍ لَّمْ يَتَغَيَّرْ طَعْمُهُ وَأَنْهَارٌ مِّنْ خَمْرٍ لَّذَّةٍ لِّلشَّارِبِينَ وَأَنْهَارٌ مِّنْ عَسَلٍ مُّصَفًّى ۖ وَلَهُمْ فِيهَا مِن كُلِّ الثَّمَرَاتِ وَمَغْفِرَةٌ مِّن رَّبِّهِمْ ۖ كَمَنْ هُوَ خَالِدٌ فِي النَّارِ وَسُقُوا مَاءً حَمِيمًا فَقَطَّعَ أَمْعَاءَهُمْ
2፥25 *ከእርሷ ከፍሬ ዓይነት ሲሳይን በተመገቡ ቁጥር ፍሬዎችዋ ስለሚመሳሰሉ «ይህ ያ ከአሁን በፊት የተገመብነው ነው» ይላሉ፡፡ እርሱንም ተመሳሳይ ኾኖ ተሰጣቸው*፡፡ ۖ كُلَّمَا رُزِقُوا مِنْهَا مِن ثَمَرَةٍ رِّزْقًا ۙ قَالُوا هَـٰذَا الَّذِي رُزِقْنَا مِن قَبْلُ ۖ وَأُتُوا بِهِ مُتَشَابِهًا ۖ وَلَهُمْ فِيهَا أَزْوَاجٌ مُّطَهَّرَةٌ ۖ وَهُمْ فِيهَا خَالِدُونَ

"መሰል" مَثَل ማለት "ምሳሌ" ማለት ሲሆን እዚህ ላይ የተዘረዘሩት ውሃ፣ ወተት፣ የወይን ጠጅም፣ ማር፣ ፍሬዎች "ምሳሌ" ናቸው፤ ምክንያቱም የዚህ ዓለም ውሃ ሲቆይ ይሸታል፣ ወተት ሲቆይ ረግቶ ይቀየራል፣ ማርና ወይንም ጥፍጥናው ይሰለቻል፤ ነገር ግን የጀነት ውሃ፣ ወተት፣ የወይን ጠጅም፣ ማር፣ፍሬዎች ግን የተለየ ነው፤ የዚህ ዓለም ወይን ከቆየ ይቆመጥጥና ያሰክራል፤ እራስምታት ያመጣል፤ ከዚያም መጥፎ ንግግር ሰው እንዲናገር ያደርጋል፣ በመቀጠልም ወንጀልም ያሰራል። ነገር ግን የጀነት ወይን ጠጅ አያሰክርም፣ ራስምታት የለውም፣ ውድቅ ንግግር እና ወንጀልም አያሰራም፤ ምክንያቱም ምንም አልኮል የሌለበት "ንጹህ" የሆነ ነው፦
56፥19 *ከእርሷ የራስ ምታት አያገኛቸውም፤ አይሰክሩምም*። لَّا يُصَدَّعُونَ عَنْهَا وَلَا يُنزِفُونَ
37፥47 *በእርሷ ዉስጥም ራስ ምታት የለባትም። እነርሱም ከእርሷ የሚሰክሩ አይደሉም*። لَا فِيهَا غَوْلٌ وَلَا هُمْ عَنْهَا يُنزَفُونَ
52፥23 *በውስጧ መጠጥን ይሰጣጣሉ፤ በውስጧ ውድቅ ንግግር እና ወንጀልም የለም*። يَتَنَازَعُونَ فِيهَا كَأْسًا لَّا لَغْوٌ فِيهَا وَلَا تَأْثِيمٌ
76፥21 *ጌታቸውም ንጹህ የሆኑን መጠጥ ያጠጣቸዋል*። رَبُّهُمْ شَرَابًا طَهُورًا

"ንጹህ" የሚለው ቃል "ጠሁር" طَهُور ሲሆን ይህም ከአልኮልነት ነጻ የሆነ የተጣራ ወይን ነው፦
83:25 *ተጣርቶ ከታተመ ጠጅ ይጥጠጣሉ*። يُسْقَوْنَ مِن رَّحِيقٍ مَّخْتُومٍ

ይህም ንጹህ ወይን መበረጃው "ካፉር" كَافُور "ዘንጀቢል" زَنجَبِيل "ተሥኒም" تَسْنِيم ነው፦
76፥5 በጎ አድራጊዎች፥ *መበረዣዋ ካፉርው ከሆነች ጠጅ ይጠጣሉ*። إِنَّ الْأَبْرَارَ يَشْرَبُونَ مِن كَأْسٍ كَانَ مِزَاجُهَا كَافُورًا
76፥17 በእርሷም *መበረዣዋ ዘንጀቢል የሆነችን ጠጅ ይጠጣሉ*። وَيُسْقَوْنَ فِيهَا كَأْسًا كَانَ مِزَاجُهَا زَنجَبِيلًا
83፥27 *መበረዣውም ከተሥኒም ነው*። وَمِزَاجُهُ مِن تَسْنِيمٍ

"እሺ የማያሳክር ወይን ከሆነ እንዴት ጀነት ውስጥ ወይን ይኖራል?" ብለው ሚሽነሪዎች ይሞግታሉ፤ ምነው በእናንተ መንግሥተ-ሰማይ ውስጥ የሚበላ ዛፍ እና የሚጠጣ ወይን የለም እንዴ? አንብቡት፦
ማቴዎስ 26፥29 *ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር አዲሱን ወይን ፍሬ እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ ከዚህ ከወይን ፍሬ አልጠጣም*። But I say unto you, I will not drink henceforth of this fruit of the vine, until that day when I drink it new vine with you in my Father's kingdom.
ራእይ 2፥7 *ድል ለነሣው በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ*።

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሰላሙ አለይኩም
ሙት ማስነሳት

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

46፥33 ያ ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ፥ እነርሱንም በመፍጠሩ ያልደከመው አላህ ሙታንን ሕያው በማድረግ ላይ ቻይ መኾኑን አላስተዋሉምን? በማስነሳት ቻይ ነው፡፡ እርሱ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነውና፡፡ أَوَلَمْ يَرَوْا أَنَّ اللَّهَ الَّذِي خَلَقَ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ وَلَمْ يَعْيَ بِخَلْقِهِنَّ بِقَادِرٍ عَلَىٰ أَن يُحْيِيَ الْمَوْتَىٰ ۚ بَلَىٰ إِنَّهُ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ قَدِيرٌ

ሚሽነሪዎች ሁልጊዜ ቋ ያለ ጉፋያ ሃሳብ እንደ በቀቀን መደጋገም ይወዳሉ፤ የማይመክን ሃሳብ ይዞ ከመሞገት ይልቅ መንፈቅፈቁንና መነፋረቁን፥ መንሰክሰኩንና መንከንከኑን ተያይዘውታል፤ ጭራሽ ኢየሱስ ሙት ማስነሳቱ ለአምላክነቱ ማስረጃ አድርገው አርፈውታል።
አምላካችን እና ጌታችን አላህ ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ፤ እነርሱንም በመፍጠሩ ያልደከመው፤ ሙታንን ሕያው በማድረግ ላይ ቻይ ነው፤ እርሱም በመጀመሪያ መደብ፦ “እኛ ሙታንን በእርግጥ ሕያው እናደርጋለን” ይለናል፦
46፥33 ያ ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ፤ እነርሱንም በመፍጠሩ ያልደከመው አላህ ሙታንን ሕያው በማድረግ ላይ ቻይ መኾኑን አላስተዋሉምን? በማስነሳት ቻይ ነው፡፡ እርሱ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነውና፡፡ أَوَلَمْ يَرَوْا أَنَّ اللَّهَ الَّذِي خَلَقَ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ وَلَمْ يَعْيَ بِخَلْقِهِنَّ بِقَادِرٍ عَلَىٰ أَن يُحْيِيَ الْمَوْتَىٰ ۚ بَلَىٰ إِنَّهُ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ قَدِيرٌ
36፥12 *”እኛ ሙታንን በእርግጥ ሕያው እናደርጋለን”*፡፡ ያስቀደሙትንም ሥራ ፈለጎቻቸውንም እንጽፋለን፡፡ ነገሩንም ሁሉ ገላጭ መሪ በኾነ መጽሐፍ ውስጥ አጠቃለልነው፡፡ إِنَّا نَحْنُ نُحْيِي الْمَوْتَىٰ وَنَكْتُبُ مَا قَدَّمُوا وَآثَارَهُمْ ۚ وَكُلَّ شَيْءٍ أَحْصَيْنَاهُ فِي إِمَامٍ مُّبِينٍ

አላህ “ማኅየዊ” ማለትም “አስነሺ” “ሕይወት ሰጪ” ነው። “ትንሳኤ” ለሚለው የግስ መደብ የገባው ቃል “አቃመ” أَقَامَ “አሕያ” أَحْيَا “በዐሰ” بَعَثَ ነው። ይህንን ቃል ይዘን ወደ ባይብል ከገባን በባይብል ሙት አስነሺ የተባለው ኢየሱስ ብቻ ሳይሆን ሐዋርያት እና ነቢያትም ጭምር ናቸው፦
ማቴዎስ 10፥8 ድውዮችን ፈውሱ፤ *”ሙታንን አስነሡ”*፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አውጡ፤ በከንቱ ተቀበላችሁ፥ በከንቱ ስጡ። اشفُوا المَرضَى، أقِيمُوا المَوتَى، اشفُوا البُرصَ، أخرِجُوا الأرواحَ الشِّرِّيرَةَ. أخَذْتُمُ السُّلطانَ لِعَمَلِ ذَلِكَ مَجّاناً، فَأعطُوا الآخَرِينَ مَجّاناً أيضاً.

“አስነሱ” ለሚለው ቃል “አቂሙ” أقِيمُوا በሚል መጥቷል፤ ታዲያ ሐዋርያቱ አምላክ ነበሩን? ኢየሱስ የሠራውን ሥራ በእርሱ መልእክተኝነት ያመኑ ሰዎችም እርሱ ከሠራው ሥራ ይበልጥ ሊሠሩ እንደሚችሉ እራሱ ተናግሯል፦
ዮሐንስ 14፥13 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን *”እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል”*፥

በዚህ መሰረት በኢየሱስ ነብይነት ያመኑት ሃዋርያትም ኢየሱስ የሠራውን ሥራ ማለትም ሰው ከሞት ማስነሳት ሠርተውቷል፦
የሐዋርያት ሥራ 9:40 ጴጥሮስም ሁሉን ወደ ውጭ አስወጥቶ ተንበርክኮም ጸለየ፥ *”ወደ ”ሬሳውም ዘወር ብሎ። ጣቢታ ሆይ፥ ”ተነሺ” አላት። እርስዋም ዓይኖችዋን ከፈተች ጴጥሮስንም ባየች ጊዜ ተቀመጠች”*።

ብሉይ ኪዳን ላይ የነበሩት ሁለት ነቢያት ኤልያስ እና ኤልሳዕ የሁለት ሴቶችን ልጆች አስነስተዋል፦
1. ኤልያስ፦
1ኛ ነገሥት 17፥21-23 *በብላቴናውም ላይ ሦስት ጊዜ ተዘረጋበት፥ ወደ እግዚአብሔርም። አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ የዚህ ብላቴና ነፍስ ወደ እርሱ ትመለስ ዘንድ እለምንሃለሁ ብሎ ጮኸ፤ እግዚአብሔርም “የኤልያስን ቃል ሰማ፤ የብላቴናው ነፍስ ወደ እርሱ ተመለሰች”፥ እርሱም ዳነ፤ ኤልያስም ብላቴናውን ይዞ ከሰገነቱ ወደ ቤት አወረደው፥ ኤልያስም። እነሆ፥ “ልጅሽ በሕይወት ይኖራል” ብሎ ለእናቱ ሰጣት*።

2. ኤልሳዕ፦
1ኛ ነገሥት 4፥32-34 *ኤልሳዕም ወደ ቤት በገባ ጊዜ እነሆ፥ “ሕፃኑ ሞቶ” በአልጋው ላይ ተጋድሞ ነበር። ገብቶም በሩን ከሁለቱ በኋላ ዘጋ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ፤ መጥቶም በሕፃኑ ላይ ተኛ፤ “አፉንም በአፉ፥ ዓይኑንም በዓይኑ፥ እጁንም በእጁ ላይ አድርጎ ተጋደመበት፤ የሕፃኑም ገላ ሞቀ”፤ ተመልሶም በቤቱ ውስጥ አንድ ጊዜ ወዲህና ወዲያ ተመላለሰ፤ ደግሞም ወጥቶ ሰባት ጊዜ በሕፃኑ ላይ ተጋደመ፤ ሕፃኑም ዓይኖቹን ከፈተ*።

የዕብራውያን ጸሐፊ ይህንን ጉዳይ በማስታወስ በኤልያስ እና በኤልሳዕ ዘመን የነበሩት ሁለት ሴቶሽ ሙታን ልጆቻቸውን በትንሳኤ ተቀበሉ ይለናል፦
11፥35 *ሴቶች ሙታናቸውን “በትንሣኤ” ተቀበሉ*፤

ልብ በል “ትንሳኤ” የተባለው በብሉይ ኪዳን ሁለት ነብያት የሞቱ ሰዎችን ያስነሱትን የሴቶችን ህፃናት እንደሆነ እሙንና ቅቡል ነው፤ ታዲያ ሁለት ነቢያት ኤልያስ እና ኤልሳዕ የሁለት ሴቶችን ልጆች ስላስነሱ አምላክ ናቸውን? አይ፦ “ሐዋርያቱ እና ነቢያቱ ሙት ያስነሱት በጸሎት ነው” ይሉናል፤ ኢየሱስስ ጸልዮ እኮ ነው ሙት ያስነሳው፤ ኢየሱስ እግዚአብሔርን ለምኖ ሰዎች እግዚአብሔር እንዳላከው እንዲያምኑበት የተሰጠው ስራ እንደሆነ ተናግሯል፦
ዮሐንስ 11፥41-44 ድንጋዩንም አነሡት። *ኢየሱስም ዓይኖቹን ወደ ላይ አንሥቶ። “አባት ሆይ፥ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ፤ ሁልጊዜም እንድትሰማኝ” አወቅሁ፤ ነገር ግን “አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ” በዚህ ዙሪያ ስለ ቆሙት ሕዝብ ተናገርሁ አለ። ይህንም ብሎ በታላቅ ድምፅ። አልዓዛር ሆይ፥ ወደ ውጭ ና ብሎ ጮኸ። የሞተውም እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደ ተገነዙ ወጣ፤ ፈቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበር። ኢየሱስም። ፍቱትና ይሂድ ተዉት አላቸው*።
ኢየሱስ የሚያደርጋቸው ታምራት ሁሉ በፈጣሪ ስም እንጂ ከራሱ ምንም ማድረግ አይችልም፦
ዮሐንስ 10፥25 ኢየሱስም መለሰላቸው፥ እንዲህ ሲል። ነገርኋችሁ አታምኑምም *”እኔ በአባቴ ስም የማደርገው ሥራ ስለ እኔ ይመሰክራል”*።
ዮሐንስ 5:30 *”እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም”*፤

እንዴት አምላክ የሆነ ህላዌ “ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም” ይላል? እንዴትስ አምላክ የሆነ ህላዌ በሌላ ማንነትና ምንነት ስም ታምር ያደርጋል? ጭራሽኑ የሚያደርጋቸው ሥራዎች ከፈጣሪ በጸጋ ያገኛቸው እንደሆኑ እና ለእርሱ መእክተኛነት ማስረጃ እንደሆኑ አበክሮ እና አዘክሮ ይናገራል፦
ዮሐንስ 17፥4 እኔ ላደርገው *የሰጠኸኝን* ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ፤
ዮሐንስ 5፥36 አብ ልፈጽመው *የሰጠኝ* ሥራ” ይህ የማደርገው ሥራ፥ አብ እንደ ”ላከኝ” ስለ እኔ ይመሰክራልና።
ዮሐንስ 11፥42 ሁልጊዜም እንድትሰማኝ አወቅሁ፤ ነገር ግን *”አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ”* በዚህ ዙሪያ ስለ ቆሙት ሕዝብ ተናገርሁ አለ።

የየናዝሬቱ ኢየሱስ ያደረጋቸው ተአምራት፣ ድንቆች እና ምልክቶችም እግዚአብሔር በኢየሱስ በኩል ያደረገው ነው፤ በተጨማሪም ከእግዚአብሔር ለእስራኤል ሰዎች የተላከ ሰው መሆኑን በአጽንዖትና በአንክሮት የሚያሳይ ነው፦
የሐዋርያት ሥራ 2፥22 የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ይህን ቃል ስሙ፤ ራሳችሁ እንደምታውቁ፥ *የናዝሬቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር በመካከላችሁ “በእርሱ”” በኩል ባደረገው “”ተአምራትና በድንቆች በምልክቶችም” ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእስራኤል ሰዎች የተላከ ሰው ነበረ፤ ይህ ሰው በራሱ ፈቃድ ሳይሆን በላከውን ፈቃድ ሙት ሲያስነሳ የነበረ ሰው ነው፦
ዮሐንስ 5፥30 *እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም”*፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፥ *”የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና”*።

አምላካችን እና ጌታችን አላህም ዒሣ ምን አስተምሮ እንደነበር በተናገረበት አንቀጽ ላይ ዒሣ ሙት ማስነሳቱ ለመልእክተኛነቱ ማስረጃ እንደሆነ ነግሮናል፦
3፥49 ወደ እስራኤልም ልጆች መልክተኛ ያደርገዋል፡፡ ይላልም፡- «እኔ ከጌታዬ ዘንድ በተዓምር ወደ እናንተ መጣሁ፡፡ እኔ ለናንተ ከጭቃ እንደ ወፍ ቅርፅ እፈጥራለሁ፡፡ በርሱም እተነፍስበታለሁ፡፡ በአላህም ፈቃድ ወፍ ይኾናል፡፡ በአላህም ፈቃድ ዕውር ኾኖ የተወለደን፣ ለምጸኛንም አድናለሁ፡፡ ሙታንንም *”አስነሳለሁ”*፡፡ የምትበሉትንና በቤታችሁ የምታደልቡትንም ሁሉ እነግራችኋለሁ፡፡ የምታምኑ እንደኾናችሁ ለእናንተ በዚህ ውስጥ በእርግጥ ተዓምር አለበት፡፡» وَرَسُولًا إِلَىٰ بَنِي إِسْرَائِيلَ أَنِّي قَدْ جِئْتُكُم بِآيَةٍ مِّن رَّبِّكُمْ ۖ أَنِّي أَخْلُقُ لَكُم مِّنَ الطِّينِ كَهَيْئَةِ الطَّيْرِ فَأَنفُخُ فِيهِ فَيَكُونُ طَيْرًا بِإِذْنِ اللَّهِ ۖ وَأُبْرِئُ الْأَكْمَهَ وَالْأَبْرَصَ وَأُحْيِي الْمَوْتَىٰ بِإِذْنِ اللَّهِ ۖ وَأُنَبِّئُكُم بِمَا تَأْكُلُونَ وَمَا تَدَّخِرُونَ فِي بُيُوتِكُمْ ۚ إِنَّ فِي ذَٰلِكَ لَآيَةً لَّكُمْ إِن كُنتُم مُّؤْمِنِينَ

ይህም ታምር ከአላህ ለእርሱ ነቢይነት የተሰጠው ስጦታ ነው፦
2፥87 ሙሳንም መጽሐፍን በእርግጥ ሰጠነው፡፡ ከበኋላውም መልክተኞችን አስከታተልን፡፡ *የመርየምን ልጅ ዒሳንም ግልጽ ታምራቶችን ሰጠነው*፡፡ በቅዱሱ መንፈስም አበረታነው፡፡ وَلَقَدْ آتَيْنَا مُوسَى الْكِتَابَ وَقَفَّيْنَا مِن بَعْدِهِ بِالرُّسُلِ ۖ وَآتَيْنَا عِيسَى ابْنَ مَرْيَمَ الْبَيِّنَاتِ وَأَيَّدْنَاهُ بِرُوحِ الْقُدُسِ
2፥253 እነዚህን መልክተኞች ከፊላቸውን በከፊሉ ላይ አበለጥን፡፡ ከእነርሱ ውስጥ አላህ ያነጋገረው አልለ፡፡ ከፊሎቻቸውንም በደረጃዎች ከፍ አደረገ፡፡ *የመርየምን ልጅ ዒሳንም ግልጽ ታምራቶችን ሰጠነው*፡፡ በቅዱሱ መንፈስም አበረታነው፡፡ تِلْكَ الرُّسُلُ فَضَّلْنَا بَعْضَهُمْ عَلَىٰ بَعْضٍ ۘ مِّنْهُم مَّن كَلَّمَ اللَّهُ ۖ وَرَفَعَ بَعْضَهُمْ دَرَجَاتٍ ۚ وَآتَيْنَا عِيسَى ابْنَ مَرْيَمَ الْبَيِّنَاتِ وَأَيَّدْنَاهُ بِرُوحِ الْقُدُسِ

ስለዚህ ኢየሱስ በአላህ ፈቃድ ሙት ማስነሳቱ ፈጣሪ ሙት አስነሺ በተባለበት መልክ እና ልክ በፍጹም አይደለም። ከዛ ይልቅ ለእርሱ መልእክተኛነት ማስረጃ መሆኑን እንረዳለን እንጂ ጭራሽ ለአምላክነት ሸርጥ ነው ብሎ እንደ ደሊል መረጃ ማቅረብ እጅግ በጣም ሲበዛ ቂልነት ነው።

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሰላሙ አለይኩም