TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
63K photos
1.61K videos
217 files
4.38K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

መረጃ እና መልዕክት ፦ 0919743630

ማርኬቲንግ ፦ 0979222111 ወይም
0979333111

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#እናትፓርቲ #ምርጫቦርድ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ " እናት ፓርቲ በአዋጅ እና በመመሪያ ከተደነገገው ውጭ የፋይናንስ አስተዳደሩን እየመራ እና እያስተዳደረ ይገኛል " በማለት በዚህ አመት የሚሰጠውን የመንግስት የፋይናንስ ድጋፍ ሊያገኝ አይገባውም ሲል ውሳኔ አሳልፏል።

ከዚህ በተጨማሪ የፖርቲውን የባንክ ሒሳብ ወጪ ሆኖ ከታለመለት አላማ ውጪ የመንግስት ድጋፍ ገንዘብ እንዲውል አድርገዋል ባላቸው ሒሳቡን በጣምራ የሚያንቀሳቅሱት የፓርቲው አመራሮች ፦
- ዶ/ር ሰይፈሥሰላሴ አያሌው የፓርቲው ፕሬዚደንት፤
- ወ/ሪት ሜሮን ታደለ የፓርቲው ዋና ፀሐፊ
- ወ/ሪት ኩሪ አሠፋ የፓርቲው የሂሳብ ክፍል ኃላፊ ላይ የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ተገቢውን ምርመራ እንዲያደርግ የወሰነ መሆኑን ቦርዱ አሳውቋል።

ቦርዱ ተገኙ ያላቸው የፋይናንስ ግኝቶች ምንድናቸው ?

እናት ፖርቲ ከመንግስት ስለአገኘው የ2016 የበጀት ድጋፍ ሂሳቡን በራሱ የውጭ ኦዲተር አሰርቶ ሪፖርት ለቦርዱ ማቅረቡን አመልክቷል።

በፖርቲው የተሰየመው የውጭ ኦዲተር በኦዲት ሪፖርቱ ላይ ፦

ፓርቲው ከአባላት ለሰበሰበው መዋጮ የገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ ያለመስጠቱን በዚህ ምክንያት በሶስት ባንኮች ላይ የሚገኘውን 65,315ብር ትክክለኛነት ማረጋገጥ አለመቻሉን፤

ለቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ወጪ የሆኑ ገንዘቦች ህጋዊ በሆኑ የወጪ ደረሰኞች አለማስደገፉን ፤

ፓርቲው ለዕርዳታ በሚል ወጪ አድርጎ ብር 158,425 መክፈሉን ይገልጻል።

ቦርዱ ከላይ የተገለፁት ግኝቶች ከውጭ ኦዲተሩ ሲቀርብለት እንዲሁም የፓርቲው አባላት ጥቅምት 3/2017 ዓ/ም በተጻፈ አቤቱታ የፓርቲው ፋይናንስ አስተዳደር ችግር ላይመሆኑን ጠቅሰው ተገቢው ማጣራት በቦርዱ እንዲደረግ በመጠየቃቸው ጉዳዩን የፌደራል ዋና አዲተር መ/ቤት እንዲያየው ማድረጉን አስረድቷል።

የፓርቲው አባላት ያቀረቧቸውን ቅሬታዎች እና የፓርቲው የውጭ ኦዲተር የዘረዘሯቸውን ግኝቶች የያዘውን የኦዲት ሪፖርት ለፌደራል ዋና ኦዲተር በመላክ ፓርቲው ከመንግስት ያገኘውን ድጋፍ ለታለመለት ዓላማ መዋል /አለመዋሉን አጣርቶ እንዲገልጽ መጠየቁን አመልክቷል።

የፌደራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትም የፓርቲውን የመንግስት በጀት ድጋፍ ኦዲት አድርጎ ውጤቱ እንዳሳወቀው ገልጿል።

በዋና ኦዲተር የኦዲት ሪፖርቱ ላይ የታዩት ግኝቶች በዋናነት ምንድናቸው ?

🔴 ፓርቲው በአዋጅ እና በመመሪያ ከመንግስት የተሰጠውን የበጀት ድጋፍ በተለየ የሒሳብ መዝገብ በየወጪ አርእስቱ ዘርዝሮ መያዝ እንዳለበት ቢደነግግም የሒሳብ መዝገብ እንደሌለው፤ የሒሳብ ማመዛዘኛ ሪፖርት እና የባንክ ሂሳብ ማስታረቂያ እንዳላዘጋጀ እንዲሁም ከቦርዱ የተሰጠውን ድጋፍ ወጪ ሲያደርግ በተለየ የሂሳብ መዝገብ በየወጪ አርእስቱ ዘርዝሮ ሳይዝ የተፈፀመ መሆኑን ይገልጻል።

🔴 ለማህበራዊ አገልግሎት በሚል ፖርቲው ከመንግስት ያገኘውን የበጀት ድጋፍን ከታለመለት ተግባር ውጪ አውሎ እንደተገኘ ይኸውም፦
• በጎፋ ዞን ለተከሰተው የመሬት መንሸራተት እርዳታ እንዲውል ሐምሌ 25/2016ዓ/ም በወጪ ማዘዣ 000098 ብር 20ሺ ማውጣቱን፤
• ለአቶ ዳዊት ብርሀኑ መሸኛ የሚውል መስከረም 18/2017ዓ/ም በወጪ ማዘዣ 000121 15 ሺ ወጪ ማድረጉን፤
• ለአቶ ተመስገን ሹመት የሐዘን በሚል ሐምሌ 25/2016ዓ/ም በወጪ ማዘዣ 000044 3,500ብር ወጪ ማድረጉን በድምሩ 38,500 ብር ከታለመለት አላማ እና ተግባር ውጪ ያወጣ መሆኑን ይገልጻል።

🔴 በተለያዩ ጊዜያት ለ13 ቅ/ጽ/ቤቶች በባንክ ቤት በኩል በዝውውር የላከው ብር 438,500ብር ለምን ተግባር እንደዋለ የወጪ ደጋፊ ሰነድ ተያይዞ ያልቀረበ መሆኑን ይህንንም ግኝት በተመለከተ የፖርቲው ፕሬዚደንት ሲጠየቁ የሰጡት መልስ አሳማኝ ያለመሆኑን ገልጿል።

በዚህም ምርጫ ቦርድ ፓርቲው ከመንግስት የተመደበለትን ድጋፍ ከታለመለት አላማ ውጭ እንዳዋለው መገንዘቡን አሳውቋል።

በዚሀ አመት የሚሰጠውን የመንግስት ድጋፍ ሊያገኝ አይገባውም ሲልም ወስኗል።

የፓርቲውን ባንክ ሒሳብ በጣምራ ሚያንቀሳቅሱት የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ላይ የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ምርመራ እንዲያደርግ የወሰነ መሆኑን ይፋ አድርጓል።

(የእናት ፓርቲ ምላሽ በቀጣይ ይቀርባል)

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
😡393110🤔24👏19😭13🙏10🕊7😱6😢6🥰1