ግጥም ብቻ 📘
67.6K subscribers
1.53K photos
31 videos
61 files
174 links
በየቀኑ ምርጥ ምርጥ የጥበብ ስራዎችን ለማግኘት የቻነላችን ተከታይ ስለሆኑ እናመሰግናለን።

@getem @serenity13
@wegoch @Words19
@seiloch @shiyach_bicha
@zefenbicha

@leul_mekonnen1
Download Telegram
#የማታ_ቀጠሮ 🕊

እና .....እንደነገርኩሽ !!
አዲስ ቀን ተስፋ ጥሎ .....ከሚሰነቅ ስንቅ
የራእይ ወቅቱ ፥ በበነጋ ሲርቅ
እስትንፋሰ እድሜ ተኮላሽቶ
ሬሳ ለቃሚ ፥ ከየ ስርፋው በዝቶ
እምነታችን መንገድ ሳተ ....አካሄዱ ተሸረፈ
መኖር መሰንበቱ ፥ ፍርሀት ሸከፈ
ሰው እንደ ባህር ዛፍ ፥ በምሳር ታጠፈ
ሀሳባችን ታጥሮ
የተስፋችን ፋኖስ አይሆኑ ተሰብሮ
በኔና ባንቺ አገር ፥ መሞት ዋዛ ቀረ
የለትተለት ዜና
ልጅ አሞራ በላው ፥ ወላጅ ተሸበረ
የተማረው ብሶ
ወደ እናት አባት ቤት ፥ ሳጥን ተሳፈረ።

አየሽ !!
በግብሬ ፣ በክፍሌ ፥ በስጋ ላደረ
ሰብነት ሸክፎ
በህላዌ ተስፋ ፥ ኑሮ ለመተረ
ከሊቅ እስከ ደቂቅ ፥ ለትልቅ ትንሹ
ለነ ንዋይ ዘገን !!
ለነ አመድ አፋሹ !!
እኩል እንደ አቅሙ ፥ ብስራተ ጥሞና
የመኝታ ደወል ፥ የህልም መዲና
ከምሽቱ በላይ ፥ ፅልመታም ጀበርና
ከሚታወጅበት...
የውድቅት ጀምበር ፥ የጨለማ ጋራ
ገላጣና ግልፁን ፥ ቀኑን ነው ምፈራ !!

ቀኑን ነው ምፈራ !!

አለሰአት ስንጦሎጦል.... ከሚያገኘኝ አውሬ
በለሊት ከሚያፍን ፥ ከቅጥረኛ ካድሬ
ሌት ከሾመው ፥ ኪስ አውላቂ ፥ ንብረተ ወዝ ከሚጋራ
ድንቡሎ ላየገኝ ፥ ደሜን የሚዘራ
ማጅራት ከሚመታ
በድቡልቡል ድንጋይ ፥ በሰላ ቆንጨራ
ከውድቅት ልክፍት ፥ ከቄሳር አሞራ
ከዚህ ....ከዚህ በላይ
ባማረበት ጀምበር ፥ በገላጣው ፀሀይ
በኔና አንቺ ሰማይ
ክልክል ባረጉብኝ ፥ በጋረዱኝ ቦታ
ነቃይ
አስነቃዩ
ባለ መሬት ጋንታ
በጠራራ ፀሀይ ፥ የሰየመው ሽፍታ
ቀለሀውን ዘግኖ
እርሳስ በሰው ገላ ፥ ቃታውን ሲፈታ
የሰፈር ተጠሪ ፥ ቀን የሰጠው ጌታ
ሮንድ የሚቃርም ፥ አለሁ ባይ ኮማንዶ
በዘረኛ ምላስ ፥ መቃቃር ሞርዶ
እንደ መብረቅ መአት ፥ ደቦ ጎኔ ወርዶ
መታወቂያ አውጣ !!
የሚለኝ ኮበሌ
በብሄር መታደን
የፈቀደ ገዢ፥ ያወጀ ቀበሌ
ደፍቶ መጣያውን ፥
አቅም አደርጅቶ ፥ ቀብር አስተካክሎ
በስመኔ ...ለኔ
በገዛ ፈቃዱ ፥ ራሱን ወክሎ
የናቴን ልጅ....... እቴን
በነገር ጥላሸት
በበቀል ስንደዶ ፥ አይነስቧን ኩሎ
ለወንድሜ ባዳ
ለህቴ ባይተዋር ፥ አዲስ ችካል ተክሎ
ባላንጣ !!
ደመኛ !!
ቀበኛ !! ያረገኝ
ጥማዴን ሻሽጬ ፥ ክላሽ ያስታጠቀኝ
ሰላም ሰልፍ ጠርቶ ፥ ሰላሜን የነሳ
ዝጋ !!
ክፈት !! ብሎ ፥ አርጩሜ ያነሳ
መንግስትለይ የሚሸፍት.... አለቃላይ የሚነሳ
እረ'ፍ... የሚል ብርቱ !!
ማስታረቂያ ገመድ ፥ ከስጋንት ያጣ
አሻግሮ ከማየት
በደንጋዛ ግዜ ፥ መነፀር ደርቦ ፥ እራሱን የቀጣ
ፅድቅ ያላጀገነው ፥ ኩነኔ ያልፈራ
የዘመን ውልክፍክፍ ፥ ከንቱ የሰው ተራ
ይህንን ያቀፈ ፥ ቀን ነው የምፈራ !!

እናልሽ ውዴዋ....
ከገነተ ምድር ፥ የፍቅራችን ጠበል
በሰማዩ ጎማ ፥ በእግዜሩ ተጠልፎ
በድንግል መቀነት
በራማ ወገብ ላይ ፥ ቁልቁል ተሰልፎ
ለፍቅራችን አፈር
የሰላም እርጥበት ፥ ከላይ እስኪደፋ
ቀን ከሚሮጡት ጋራ
አብረን ተሯሩጠን ፥ ሞሰብ እንዳንደፋ
ወድቀን እንዳንጋጥ ፥ በርግጫ እንዳንጠፋ
ለዚህ ነው...
ቀን ቀን ላይ ፥ ስልኬን የምዘጋ ፥ ድምጤን የማጠፋ።

እኔ ያንቺ አፍቃሪ
ጭን ፍለጋ መስሎሽ ፥ነይ ማታ ማለቴ
ዋልጌ ነው አትበይ ሳይገባሽ ስጋቴ
የአራዊቶቹን ቀን ፥ ጨለማን አውቄ
እለቱን ጠልቼ ፥ ፅልመቱን ታርቄ
ቢጨንቀኝ ነው እንጂ እኔስ ማስጨነቄ
ጥንታዊ አዋዋል
ኢትዮጵያዊ ቀኔን ፥ ዛሬ መናፈቄ
አንቺም ታውቂዋለሽ ፥ የቀደመውን ቀን
ጨቅላነት ሲጥመን ፥ ጉዲፈቻ ሲያቅፈን
ድክ ድክ ስንል
እስላም ክርስቲያኑ ፥ አዝሎ ሲታቀፈን
በልጅ ቡረቃችን ፥ ዝምድና ሳንፈራ
ጎረቤት በሙሉ
ጡት እያጎረሰን ፥ በለት እለት ተራ
እንኳን ሰው ሊገደል ፥ አይናችን እያየ
ምንኛ በዳዩ ፥ አፈሩን ሲቀምሰው
ነብስ ይማር !! ብለን ነው ፥ ደጁን የምናልፈው
ደስታችን ሰው አይመርጥ ሀዘኑ የጋራ
ልእለ ሰውነት ነው !! ኢትዮጵያዊ ዳራ
ለማያውቁት ማዘን
ለእግዚሀር እንግዳ ፥ ላይ እታች መባዘን
ፀዲቅ እና ዘካ ፥ ወንጌል ቁርአኑ ፥ ከቀዲም ያዘዘን።
እኔ ብቻ አይደለሁ
እንቺም ታውቂዋለሽ ፥ እንዴት እንደነበር
ወረንጦ ፍቅራችን
ከጥላቻ እሾህ ፥ ፈውሶ ያስታርቀን።

እስከዛው ድረስ ግን.....
ለምንመኘው ቀን ፥ ፍቅርን ዘውሪ
አቅምሽ እስከቻለ
ትንፋሽሽ እስካለ ፥ ሰላምን ዘምሪ
ገራ ገር ማንነት
ጥቂት ፀበል ቢያጣ ፥ ተለከፈ ብለሽ አትደናገሪ
ወዶ ማን ሰው ያብዳል ፥ በዲያቢሎስ ጋሪ ??

እኔም በፈቀደ ፥ እድሌ በሰጠኝ
እምነቴን የበላ ፥ ፍርሀቴ እስኪለቀኝ
ከወራት ግርግር ፥ እራሴን መንጭቄ
ያቻዬን አብሮነት ፥ ፍስሀ ናፍቄ
ፈረሰች ለሚለኝ !!
ወደቀች ለሚለኝ !!
የሀገር ሟርተኛ ፥ እሬት እየጋትኩኝ
ማዕልት ሳላጎል ፥ ፍቅር እየዳርኩኝ
ሰርክ ማታ ማታ እጠብቅሻለው
አንቺም መውደድ አለሽ ፥ ሀበሻም ቀልብ አለው።

እስከዛው ድረስ ግን....ሲመሽ እንገናኝ !!

#ያንቺው_አፍቃሪ !!

❤️❤️❤️❤️❤️❤️❤️❤️❤️❤️❤️❤️
#አብርሀም_ተክሉ
contact ፦ @Abr_sh

@getem
@getem
@getem
👍1