ግጥም ብቻ 📘
67.3K subscribers
1.53K photos
31 videos
61 files
175 links
በየቀኑ ምርጥ ምርጥ የጥበብ ስራዎችን ለማግኘት የቻነላችን ተከታይ ስለሆኑ እናመሰግናለን።

@getem @serenity13
@wegoch @Words19
@seiloch @shiyach_bicha
@zefenbicha

@leul_mekonnen1
Download Telegram
#አንቺን_ነው



ምድርን በጥፋት ውሃ
ዳግመኛ እንደሚያጠፋት
እግዜር ነግሮኝ ማሰቡን፤
እኔን ኖህ አርጎ መርጦኝ
ሥራ ቢለኝ መርከቡን፤
ከ አዕዋፍ ከ እንስሳቱ
ወደ መርከቡ ላስገባ
ሁለት ሁለቱን ስገልጠው፤
አንቺን ነው ከሴት ምመርጠው።

#ሄኖክ_ብርሃኑ (@yeneeyita)
@yeneeyita

@getem
@getem
@getem
👍3927😁9👎4🔥4
#እግዜአብሔርን_ፍሪ
:
:

አምናለው አልክድም እጅጉን ታምሪያለሽ፤
ስሜትን የሚጭር ብዙ ነገር አለሽ።
:
:
ፀዳልሽ ያስፈራል ግርማሽ ነው የንግስት፤
ባይኔ ዞሮ አያውቅም እንዳንቺ አይነት እንስት።
:
:
ግና በኔ መስፈርት፤
በአምላክ ቃል መሰረት፤
ውበትም ሀሰት ነው ደምግባትም ከንቱ፤
ጌታዋን ምትፈራ በፅኑ በብርቱ፤
በፈሪሀ እግዚአብሔር ሰርክ ምትተጋ፤
ከቀይ ዕንቁ በላይ ተመን አላት ዋጋ።
ትመሰገናለች፤
ለባሏም ዘውድ ነች።


ቃሉ ያልገባቸው፤
ቁንጅናሽ ሰልቧቸው፤
ቁመናሽ ተብትቦ፤
ቀልባቸውን ስቦ፤
ማማርሽ ድር ሰርቶ በመልክሽ ተጠልፈው፤
ወንዶች ሲከጅሉሽ አየሁ ተሰልፈው።


እኔስ አይጠፋኝም ...
ውበት ማገር ሆኖት ቁመናም ምሰሶ፤
ተገንብቶ እንደሆን መልክ ተቀይሶ፤
የደበዘዘለት ማማር ከበርቻቻው፤
ዘመም ይላል ጎጆ ይናዳል ጉልቻው።


እናልሽ አንቺ ሴት ...
ለብቻው ሞግቶ እኔን ስላልጣለኝ
የውበትሽ ወጥመድ፤
በርግጥ ካፈቀርሺኝ ከሰው የተለየ
ለኔ ካለሽ መውደድ፤
እንደወይን ፍሬ ከትናንቱ ዛሬ
በስሎ እየጎመራ፤
ፍቅራችን ተባርኮ ለምልሞ እንዲያፈራ፤
እንድሸነፍልሽ እንዶንሽ ከከጀልሽ
እውነተኛ አፍቃሪ፤
መሽቀርቀሩ እንዳለ እግዜአብሔርን ፍሪ።

#ሄኖክ_ብርሃኑ (@yeneeyita)
@yeneeyita

@getem
@getem
@getem
44👍34🔥1😱1
#ተይ



ያኔ ገና ከጅምሩ
ጥበብ ውስጤ ስትገባ፤
ደስ አይለኝም ሲያሞግሱኝ
በ አድናቆት ቃል በጭብጨባ።
ከርሞ እያደር ግዜው ሲነጉድ
ብዙ አድናቂ እንዳተረፍኩ፤
የፈራሁት ደረሰና
ጭብጨባቸው ገሎኝ አረፍኩ።


እንደ ጥበብ ልክ እንደዛ፤
ምስጢር ፍቅርሽ አሳስቆኝ
የደሜን ሥር እንደገዛ፤
እንደ አታሞ ስንዳለቅ
ፌሽታ አስክሮን ሆያሆዬ፤
በጭብጨባሽ እንደማልሞት
በምን ልመን እንዴት ብዬ?


ከፍቅር አምላክ የተቸርሺኝ
ጥበቤ ነሽ ብዬሽ ሳለው፤
ፈር የሌለው ያንቺ አድናቆት
ተይ ይቅርብኝ እሞታለው።

#ሄኖክ_ብርሃኑ (@yeneeyita)
@yeneeyita

@getem
@getem
@getem
👍2316😱3🎉1
#አበስ_ገበርኩ
:
:
እንደተለያየን ...
ንቃቃቷ ሞላ ጣለች ገፋ ከሏን፤
ነዶ ሰበሰበች ጠል ወርሶት አካሏን።
እግሯ ባ'ለት ፀና ሻረች መወላገድ፤
ተደላደለላት ስርጓጎጡ መንገድ።


እንደተለያየን ...
ዕድል ተከተላት፤
ንዋይ ሲሳይ ምንዳ ባንድነት ነደላት።
ራስ ሆነች ቁንጮ ፈላጊዋ ጋመ፤
የማይደገመው እየደጋገመ፤
መዳፏ ላይ ታየ፤
የሚያያት ፈዘዘ የነካት በረየ።


እንደተለያየን...
ገዛት ህያው ቃሉ፤
ሰላም ሰፈነለት ሰላም ያላት ሁሉ።
የአፏም ቃል ፀና ይሁን ስትል ሆነ፤
ፈሪው ድፍረት በዛው አንጋሴው ጀገነ።


እንደተለያየን...
ተገለጠ ጥርሷ፤
ይስረቀረቅ ጀመር ቱማታው የልብሷ።
እንደ ጀምበር ፈካች፤
በሳቋ ካካት ሰማይ ጫፉን ነካች።


እግዚኦ ምህረት ለኔ አበሳ ለገበርኩ፤
በደል ሀጥያቷ ለካስ እኔ ነበርኩ።

#ሄኖክ_ብርሃኑ(@yeneeyita)
@yeneeyita

@getem
@getem
@getem
29👍14🔥1😱1
#ምኗ_ነው?
:
:
:
ምኗን ነው ግን የወደድከው
አልፎ አልፎ ይለኛል ሰው፤
እንዲ ብሎ ሚጠይቀኝ
የሆነ ብቃት እንዳነሰው፤
መጠይቁ ያሳብቃል፤
የልቡ ዓይን ያልበራለት
ወትሮስ ፍቅርን እንዴት ያውቃል።
:
:
ብዙ ማዕረግ ብዙ ገድል
የቀለም ቀንድ ጥልቅ ሀሳቡ፤
እስካልበራ እውር ልቡ፤
ፍቅር ወርሶ እስካልቋጨው፤
ሰው አይሆንም የምድር ጨው።
:
:
ሆነሽልኝ ዝርግፍ ጌጤ
ወርቀዘቦ ተክህኖ፤
አዋቂው ሰው ለጋ ሆኖ፤
እንዲያ ብሎ ሲጠይቀኝ
ያደርገኛል ደርሶ ብግን፤
የሚጠላው ምኗ ነው ግን?

#ሄኖክ_ብርሃኑ (@yeneeyita)
(@yeneeyita)

@getem
@getem
@getem
67👍37🔥2👎1
#አለማማር_ማማር
:
:
ገጣሚው በግጥሙ ገና ከምርጊቱ
ውበትን ያደንቃል፣
ወረቀት ብዕሩም የቆንጆን ሴት ፀዳል
እልፍ ያንፀባርቃል።
:
:
አንደኛው ገጣሚ፦
:
:
ዐይኖችሽን አይተው ኮከቦች አፈሩ፣
ድንቄም ብርሃን ሆንን ብለው ተናገሩ።
ፀሀይዋም ጠለቀች ባለችበት ቦታ፣
አንቺን ብታይ ጊዜ ተደናግራ ፈርታ።
እውነት እልሻለው ምዬ በዚ ሰማይ፣
ጨረቃም ሻማ ናት ካንቺ አንፃር ስትታይ።
እያለ ይገጥማል እያለ ይፅፋል፣
ቃላትን አዝንቦ ውበትን ያጎርፋል፣
ሰማይ ጠቀስ ግጥሙን በቀለም ይነድፋል።
:
:
ሌላኛው ገጣሚም፦
:
:
ገና ከሩቅ ሳይሽ ይድናል ህመሜ፣
ብሞትም አይቆጨኝ ከንፈርሽን ስሜ።
ባለንጋ ጣቶችሽ የዳበስሺኝ እንደው፣
እንደ እቶን እሳት ነው ውስጠቴ ሚነደው።
ዳሌሽ እየኮራ ባትሽ ላይ ሲሳለቅ፣
እኮሰምናለው እንደመታው መብረቅ።
ወገብሽ ሲል ዘመም ጥርስሽ ሲገለጥህ፣
ነግቶ ይመሽብኛል ምራቄን ስውጥህ።
እያለ ይገጥማል እያለ ይፅፋል፣
መልዕቁን ተማምኖ ቁንጅናን ይቀዝፋል፣
ዘንድሮስ ገጣሚው በውበት ተለክፏል።
:
:
አቤት ጊዜው ከፋ አቤት ጥበብ ከፋ፣
ለመልከ ጥፉ ሴት የሚገጥም ጠፋ።
ከሊቅ እስከ ደቂቅ ባንድ ሀሳብ ታጠረ፣
መልከ ጥፉነትም ግጥም ሳይሆን ቀረ።
:
:
ለመልከ ጥፉ ሴት ግጥምን በማስፈር፤
እስኪ እኔው ልቅደድ ፈር።
:
:
ያ ገጣጣው ጥርስሽ የኔ ጥርስ ቢሆን
ምነኛ ታደልኩኝ፣
ስለሚያስመስለኝ ሳልስቅ እየሳኩኝ።
ጉንጭና ለንቦጭሽ ሳይ ሲንዘፈዘፉ፣
ሞት ነው ሚሆንብኝ ሳልስምሽ ማለፉ።
ብይ ሚያክሉትን እነዚያን ዐይኖችሽ
ያየዋቸው እንደው፣
ምን እንዶን ባላውቅም አንድ ስሜት አለ
ልቤን የሚርደው።
ያ ሽቦው ፀጉርሽ አልያዝም ብሎሽ
አስሬ ሲፈታ፣
አቤት በዚያ ጊዜ ከቃላት በላይ ነው
የሚሰማኝ ደስታ።
የከናፍሮችሽ ትልቅ ዳቦ ማከል
በውነት ይገርመኛል፣
የራበኝ እንደሆን ሄደ ግመጣቸው
ብሎም ያሰኘኛል።
ደም ግባት የሌለው የመልክሽ ገፅታ፤
ሲናፍቀኝ ያድራል ላ'ሳብ ድሮኝ ማታ።


እያልኩኝ ገጥማለው እያልኩኝ ፅፋለው፣
የመልከ ጥፉን ሴት ውበት አገዝፋለው፣
አለማማር ማማር እንደሆነም ነድፋለው።

#ሄኖክ_ብርሃኑ (@yeneeyita)
(@yeneeyita)

@getem
@getem
@getem
👍62🤩1813😁7🔥4😱2👎1
#ዓይኔን_ያርገው_ግንባር



ቁመቴ ሎጋ ነው አንገቴ ጠንበለል፤
ስንቷን ሴት ጥያለሁ ዓይኔ ሲንከባለል።
ይመስላል አውቃለሁ
የጥርሴ ድርድሩ እንደ ወቶአደር ሰልፍ፤
ከንፈሬን ሳሸሸው እኔን አይተው ማለፍ፤
እንዴት ይታሰባል፤
ጥርሴ እንደው ማግኔት ነው
አንዴ ፈገግ ብሎ ብዙ ሴት ይስባል።
የደረቴን ስፋት ተክለሰውነቴን ያየች ቀና ብላ፤
ምራቋን ነው እንጂ እህሏን አትበላ።
ከትከሻዬ ላይ እጇን ጣል አድርጋ
ለመሄድ ማትመኝ፤
ቢታሰስ ባገሩ አንድም ሴት አትገኝ።
አሳ መሳይ መልኬን
በጣታቸው ዳብሰው ጉንጮቼን ለመሳም፤
የሚያዩት አበሳ አይጣል አይረሳም።
ወንዳወንድነቴ ያረማመድ ልኬ
ባለበሰኝ ግርማ፤
እጇን ባፏ ጭና ስንቷን ታዝቤያለሁ
እመንገድ ዳር ቆማ።
ጠረኑ ጠርቷቸው የፀጉሬ ክምክሞ፤
ስንቴ ብዬ አውቃለሁ ጀመራቸው ደግሞ።



ሰው እንዴት ያደንቃል እራሱን በራሱ
አይጠፋም የሚል ሰው፤
በሴት መሞካሸት እያማረኝ ቀርቶ
እድሜዬን ቢገምሰው፤
አድናቂ ሴት ባጣ የወጠንኩት ተግባር፤
ብሎ መለፈፍ ነው ዓይኔን ያርገው ግንባር።

#ሄኖክ_ብርሃኑ (@yeneeyita)
(@yeneeyita)

@getem
@getem
@getem
😁3721👍21🎉1🤩1
#አወይ_ጥርሷ



ዓይኖቿ ጥለውኝ ገና ሳልነሳ፤
ከንፈሯ ደገመኝ አቤት የኔ አበሳ።


እኔን ማለት ትታ፤
ጭራሽ በሱ ፈንታ፤
ከንፈሯን አሽሽታ፤
ሳቀችብኝ ልጅት መሬት ስወድቅ አይታ።


እኔስ...
ካ'ይኗ ከከንፈሯ እመሬት ከጣለኝ፤
የጥርሷ ድርድር ነው ይበልጥ ያቃጠለኝ።

#ሄኖክ_ብርሃኑ (@yeneeyita)
@yeneeyita

@getem
@getem
@getem
48👍20😁17
#እንደው
:
:
አብሬሽ መኖር ይከብደኛል፣
የበደልሺኝ ትዝ እያለኝ ሰርክ እንዳዲስ ያነደኛል።
ተለይቼሽም አልችል አይቆርጥልኝ ስንጣላ፣
እንደው ፍቅር ሚሉት ጉድ አሁንስ አፈር በበላ!

#ሄኖክ_ብርሃኑ(@yeneeyita)
(@yeneeyita)
@getem
@getem
@getem
😁53👍2220🤩7😢5👎3
#በዋልክበት_ፍሰስ
:
:
:
እውነትን ሰንቄ ብታትር ብለፋ፤
ሲበሉ እንጂ ማየው የምጎርሰው ጠፋ፤
መልካም የዋልኩለት ዞሮ በኔው ከፋ።
:
:
ድጡን አለፍኩ ስል ማጡ ተከተለ፤
ስንዴ እየተመኘው እንክርዳድ በቀለ።
የ ህሊናዬ ሰላም የክንዴም መፈርጠም፤
ከገዛ ጠላቴ ከሆዴ አልበለጠም።
:
:
ያ ቀናው ጎዳናም ትክክሉ መንገድ፤
አመላላሽ ሆኗል ሀረግ እና ዘመድ።
ትዝብት ዓይኔን ገልጦት ዞሬ ብመረምር፤
ያንዱ ቤቱ ሰማይ ያንዱ ቤቱ ምድር።
:
:
የባለሳምንቱ ወጥመዱ እንዲሰበር፤
ሀቅ አንግቡ እያልኩኝ ስለፈልፍ ነበር።
ለካስ እንዲ ኖሯል ...
ሆድ ሰላም እንዲያድር ልቦናህን መተው፤
በዋሉበት መፍሰስ በዋሉበት ሞልተው።

#ሄኖክ_ብርሃኑ (@yeneeyita)
(@yeneeyita)

@getem
@getem
@getem
36👍19🔥3😱2😢1
#ታምር
:
:
:
ቅንነቷ ጩኸታም ነው
ይዳረሳል ለመንደሩ፤
ፈሊጥ ቅኔ መደርደሩ፤
ለቀባሪው እንደማርዳት፤
ጆሮው ዳባ ያልለበሰ
ሁሉም ሰው ነው የሚወዳት።


መልኳ ደሞ ዝም ያለ ነው
እርግት ጭጭ የረበባት፤
በአርምሞ ላነበባት፤
ውበት እፍስ ስክነት ልቅም፤
አራት ነጥብ ገጿ አያውቅም።


ምትሰማ ዝግ ብላ፤
ምጥን ያለች የምትጎላ፤
ሳትናወዝ የምታምር፤
እኔ ግርም እሷ ታምር።
እወድሻለሁ!

#ሄኖክ_ብርሃኑ (@yeneeyita)
@yeneeyita

@getem
@getem
@getem
31👍14🤩3😁2👎1
#አልገባሽም
:
:
:
ስንለያይ ጊዜ
የየብቻው ጉዞ ገና ሲጠነሰስ፤
አብረን የገራነው የጋራችን ፈረስ፤
ትዝታን ሸክፎ ቤትሽ እንደመጣ፤
ከዛም ከደጃፍሽ አራግፎ እንደወጣ፤
የኋሊት ጎትቶ ሆዴን ሊያላውሰው፤
በሰመመን ስትሄጅ ነግሮኛል ያየሽ ሰው።
:
:
ስንለያይ ጊዜ
ህይወት በኛ ስትከር፤
እንዲው እንደ ዘበት ፍቅራችን ሲሰበር፤
የሀዘን ድንኳን ጥለሽ፤
እንዴት ሆነ ብለሽ፤
እንባሽን ስትዘሪ፤
ደግሞም ከራስሽ ጋር ስትከራከሪ፤
ባላይ እንኳን ባይኔ፤
ያየሽ አርድቶኛል ሁሉን ክንዋኔ።
:
:
ስንለያይ ጊዜ
ያቆራኘን ገመድ እንደተበጠሰ፤
የትካዜው ሾተል ስለቱን አስሎ ካንቺ እንደደረሰ፤
ከዚያም አልፎ ተርፎ እንዶነብሽ እዳ፤
ሁሉን ሰምቻለው ያንቺን ሳሎን ጓዳ።
:
:
ስንለያይ ጊዜ
ደስታ ሚባል ነገር ጥሎሽ እንደሄደ፤
የቀለለሽ ሁሉ ደርሶ እንደከበደ፤
እንኳን እኔን ቀርቶ ዘር አዳም ሚረታ፤
የተከዘን ሚያስቅ ያ ምጥን ፈገግታ፤
ፅልመት መደረቡን፤
ድንገት መለዘቡን፤
አንቺ ባታወሪኝ ያየሽ ሰው ነግሮኛል፤
በሰማውኝ ጊዜም በጣሙን ከፍቶኛል፤
ደግሞም አስቆኛል።
:
:
እውነት ነው አንቺ ሴት፤
እየው ተሰምቶኛል ሁለት አይነት ስሜት።
እያዘኑ መሳቅ እየሳቁ ማዘን፤
ከራሴ ጋር ማውጋት እራሴን መመዘን።
:
:
እያዘንኩኝ ስቄ እየሳቅኩኝ ሳዝን፤
በህሊና ሚዛን ላይ እራሴን ስመዝን፤
የሳቅኩት ባንቺ ነው
እውነቱን መርምረሽ ገልጠሽ ላላወቅሽው፤
መቦረቅ ሲገባሽ በእምባ ለታጠብሽው፤
ገራገር ለሆንሽው።
ያዘንኩት ለራሴ ይብላኝ ያልኩት ለኔው፤
ወርቁ ላልበራልኝ የመዋደድ ቅኔው፤
ለሰጠሺኝ ፍቅር ለጠፋኝ ምጣኔው።
:
:
ሀቅ ነው አንቺ ሴት ...
ያንቺ አይነት ነው እንጂ
ሚገኝ ከስንት አንዴ እሱም ለታደለ፤
የኔ አይነት ሰውማ
የትም በሄድሽበት በየቦታው አለ።
:
:
አልገባሽም እንጂ
የእኔ 'ና አንቺ ቅኔ ወርቁ ቢበረበር፤
ፍቅርን ከቃል በስቲያ ሆኖት ማያቅን ሰው
አጥቻለው ብለሽ አታለቅሺም ነበር።
አልተረዳሽ እንጂ እውነቱን ብታውቂ፤
እንኳን ልተክዢ
ካንጀትሽ ነበር ሰርክ ምትስቂ።
ሽፍንፍኑን ገልጠሽ ብትረጂ ኖሮ፤
በደስታ ነበረ
ጥለሺኝ ምትሄጂው ገና ያኔ ድሮ።
:
:
እናልሽ አንቺ ሴት...
ዋጋሽ የከበረ ገራገር ቀይ ዕንቁ፤
የተለባበሰው ሲገለጥ ድብቁ፤
የኔ ፋንታ ማልቀስ ያንቺም ነው መሳቁ።

#ሄኖክ_ብርሃኑ (@yeneeyita)
@yeneeyita

@getem
@getem
@getem
55👍55🤩4😱3😢2🔥1
#ሁለት_ማዶ
:
:
:
ማዶ ቆማ ታየኛለች
ማዶ ቆሜ አያታለሁ፤
እንዳየችኝ ትስቃለች
እኔም ሳያት እስቃለሁ።
ወዳኛለች ያሳብቃል
እርግጥ እኔም ወዳታለሁ።
:
:
ረግረጉን ልቤ ችሎ ቀስ እያለ አዘገመ፤
እፎይ ልል ስል ክምር ቋጥኝ
በተጠንቀቅ ፊቴ ቆመ።
:
:
ልቤ ሳይዝል አጠረኝ እጅ፤
ወዲያ ማዶ ያለችው ልጅ፤
አሁንም አለች፤
ተራራውን ታውቀዋለች፤
አያታለው ታየኛለች፤
እስቃለሁ ትስቃለች።
:
:
ልንያያዝ ተንጠራራን፤
በእምነቷ በእምነቴ
እንዲረዳን ፍቅርን ጠራን።
:
:
ሁለት ማዶ ሁለት እምነት
ድልድይ አልባ ማያስቀጥል፤
ብቻ ...
ብቻ ...
ብቻ ...
ስቃ ድብን ስቄ ቅጥል።

#ሄኖክ_ብርሃኑ (@yeneeyita)
@yeneeyita

@getem
@getem
@getem
31👍24🎉3😱2🤩1
#ፈር_ቀደደች
:
:
:
እሾ ብትሆን አሜኬላ፤
አካል ብትሆን የ'ፃን ገላ።
ብዛት ብትሆን ለናሙና፤
ከንፈር ብትሆን ያንጀሊና።
ድንጋይ ብትሆን የማዕዘን፤
ልቅሶ ብትሆን መሪር ሀዘን።
አንገት ብትሆን እንደ መቃ፤
ድቅድቅ ብትሆን ጠፍ ጨረቃ፤
ህመም ብትሆን የምጥ ሲቃ።
ሀሳብ ብትሆን ተመስጦ፤
ሰብል ብትሆን እንደ ግብጦ።
ፀዳል ብትሆን እንደ ንጋት፤
ፍርሃት ብትሆን ክምር ስጋት፣
ትጋት ብትሆን እንደ ጉንዳን፤
መዕላ ብትሆን አዲስ ኪዳን፣
ጥልቅ ብትሆን እንጦሮጦስ፤
ጥበብ ብትሆን የጲላጦስ።
ተንኮል ብትሆን እንደ ጋኔን፤
ወንድ ብትሆን ቁርጥ እኔን።
ፍቅር ብትሆን እንደ እየሱስ፤
ልማድ ብትሆን የ እንጋዳ ሱስ።


በየመስኩ ፊት ወረረች፤
ፋና ወጋች ቀደደች ፈር፤
አልሰራትም እንዴ ካ'ፈር?
አስመሰለባት🤔🤔🤔

#ሄኖክ_ብርሃኑ (@yeneeyita)
@yeneeyita

@getem
@getem
@getem
40👍36
#ባሰ
:
:
ልቤን መደብ አርጋ አንድ ሆዴን ትራሷ፤
ፆሜን ልፁምበት ትለኛለች እሷ።


አምላክ ሰው አይደለም...
አይሸነገልም በሰው ምላስ ምላሽ፤
ፆመኛ ነኝ አትበይ አንጀት እየበላሽ።
ያንቺስ ባሰ!

#ሄኖክ_ብርሃኑ (@yeneeyita)
@yeneeyita

@getem
@getem
@getem
34👍18😁15🤩2🎉1
#ወይኔ!
:
:
አንዱን ፍቅርሽን ምቋቋምበት፤
ምሱ ቢጠፋኝ ደህና መሰንበት፤
ይበጃል ብዬ፤
ካንቺነትሽ ላይ እኔን ነጥዬ፤
ላላይሽ ምዬ፤
ሰግቶ እንዳልሰጋው፤
በራፉን ዘጋው።


አንቺ ግን...
ቀኑ ሲመሻሽ፤
ከነ ትዝታሽ፤
ሺህ ሆነሽ መጣሽ።


ወይኔ!
መጥኔ ለኔ!

#ሄኖክ_ብርሃኑ (@yeneeyita)
@yeneeyita

@getem
@getem
@getem
33👍16🔥3😁1
#ተነድፈሽ_ክበሪ
:
:
እኔ አልነደፍም የሚለው ፉከራ፤
በገዛ አንደበትሽ በኩራት ሲወራ፤
ካንዴም አስር ጊዜ ደርሶ ሰምቻለው፤
ትክክል ነው ብሎም የሚያጎበጉብ ሰው በቅርብ አይቻለው።
:
:
እውነት ነው ወይ ብዬም በዙሪያሽ ያሉትን ዞሬ ሳጤናቸው፤
መላከፍ ነው እንጂ መንደፍ የማይችሉ ተራ ዝንቦች ናቸው።
:
:
አፍኜው ነው እንጂ ድሮም ያንቺ ነገር ያንገበግበኛል፤
ከንቱ ፉጨት ከቦሽ መኩራትሽ ገርሞኛል።
:
:
ከ ዐጀቦችሽ አንፃር መደምደምሽን ሳይ አናገረኝ እንጂ የሆዴ መከፋት፤
ባንቺ አልተጀመረም አደባባይ ቆሞ በጀሌ ተከቦ አጉል ጉራ መንፋት።
:
:
እውነት እውነት ስልሽ ያለመነደፍሽን ሚስጥሩን ላወቀው፤
ልክ እንደኔ ሁሉ ሆድ ቢብሰው እንጂ ቅንጣትም አይደንቀው።
:
:
ይልቁን አንቺ ሴት አንዣባቢሽ በዝቶ እንዳትዘናጊ፤
የማሩን እንጀራም ያንቺ እንድታደርጊ፤
ተነድፎ ለመክበር በይ ከንብ ተጠጊ።

#ሄኖክ_ብርሃኑ (@yeneeyita)
@yeneeyita

@getem
@getem
@getem
👍4932🤩3🔥2
#ፈር_ቀደደች
:
:
:
እሾ ብትሆን አሜኬላ፤
አካል ብትሆን የ'ፃን ገላ።
ብዛት ብትሆን ለናሙና፤
ከንፈር ብትሆን ያንጀሊና።
ድንጋይ ብትሆን የማዕዘን፤
ልቅሶ ብትሆን መሪር ሀዘን።
አንገት ብትሆን እንደ መቃ፤
ድቅድቅ ብትሆን ጠፍ ጨረቃ፤
ህመም ብትሆን የምጥ ሲቃ።
ሀሳብ ብትሆን ተመስጦ፤
ሰብል ብትሆን እንደ ግብጦ።
ፀዳል ብትሆን እንደ ንጋት፤
ፍርሃት ብትሆን ክምር ስጋት፣
ትጋት ብትሆን እንደ ጉንዳን፤
መዕላ ብትሆን አዲስ ኪዳን፣
ጥልቅ ብትሆን እንጦሮጦስ፤
ጥበብ ብትሆን የጲላጦስ።
ተንኮል ብትሆን እንደ ጋኔን፤
ወንድ ብትሆን ቁርጥ እኔን።
ፍቅር ብትሆን እንደ እየሱስ፤
ልማድ ብትሆን የ'ንጋዳ ሱስ።


በየመስኩ ፊት ወረረች፤
ፋና ወጋች ቀደደች ፈር፤
አልሰራትም እንዴ ካ'ፈር?
አስመሰለባት🤔🤔🤔

#ሄኖክ_ብርሃኑ
(ለአስተያየቶ @yeneeyita)
@getem
@getem
@getem
👍6324🔥4🤩3😱2
#ያልፋል_አይደል?
:
:
:
እየደለብኩ እየሰባው፤
መሸ ነጋ ወጣው ገባው።
እንደዘበት እንደኑረት፤
ሽቅብ ፍስስ የዕድሜ ጅረት።
ያለ ቁዝም ያለ ስጋት፤
አሁን ምሽት አሁን ንጋት።
ልብ ሳይለኝ ሰቀቀኑ፤
እንደወትሮ ጋመ ቀኑ።


ኖርኩኝ፤
ሄድኩኝ፤
የት እንዳለው ሳላስታውስ፤
እንዲው ንጉድ እንዲው ፍስስ።


መጓዜንም አላበቃው፤
እግር ሲያጥረኝ ድንገት ነቃው።
ልቤ ቢናኝ፤
ዞሬ ስቃኝ፤
ተንደረደርኩ ልደላደል፤
ከቦኝ ኖሯል ለካስ ገደል።


እንዴት ገባው እንዴት ልውጣስ፣
ማን ያድነኝ ምን አውቄ፤
የሚያኖረኝ አንዱ ተስፋ፣
« ያልፋል አይደል ? » ሚል ጥያቄ።

#ሄኖክ_ብርሃኑ (@yeneeyita)
@yeneeyita

@getem
@getem
@getem
56👍23🎉3🔥2
#ገባኝ
:
:
:
ውበት ግርማሽ እንደ ቀላይ
ቢኬድ ቢታይ አይጨረስም፤
እጅን በአፍ ማስጫን እንጂ
መገለጫ የለሽም ስም።


ዓይቶሽ ዓይኑን ለመለሰው፤
ወቸው ጉድ ነው
ሚተርፈው ሰው።
ጠልቆት ሀሳብ
ዳምኖት ድማም፤
ወይ አይሰማም
ወይ አይለማም።


ሀረግ ስንኝ ለመቋጠር፤
ይደገፋል ጋን በጠጠር፤
ብዬ ባይሽ እኔው ለኔው፤
ልምሻ ዳዳው ፈሊጥ ቅኔው።


ቃል ቃል አጣ
ሆሄም ሞተ፤
አንገት ደፋ ተማረከ
ስነጥበብ ተገመተ።


አፈቀርኩሽ እጅ አልሰጥም
« ሞት አይቀርም » እያባባኝ፤
አንቺን ባጣም ውበት ገባኝ።
አይቆጨኝም!

#ሄኖክ_ብርሃኑ (@yeneeyita)

@yeneeyita
@getem
@getem
@getem
👍5226😱1