ዐውደ ምሕረት
3.69K subscribers
929 photos
24 videos
271 files
192 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
#የቅዱስ_ገብርኤል ጸሎትና ምኞት !
___________________________
ጸሎት ና ምኞት እንዲሁም ተስፋ ማድረግ የሰው ልጆች ብቻ ጠባይ አይደለም በቅዱሳን መላእክት ዘንድ ያለ የፍጡር ሁሉ ጠባይ ጭምር ነው። ታድያ ጸሎት፣ምኞት፣ተስፋን መልካም ካልሆነ ውጤቱም መልካም አይሆንም ለምሳሌ ለእግዚአብሔር የቀረበ ቅሩበ #እግዚአብሔር የሚባል የነበረ ሳጥናኤል ከዚያ ሁሉ ክብሩ የተሻረው ባልተገባ ፈጣሪ የመሆን ምኞትና ተስፋ ነው።

ቅዱሳን መላእክት 24 ሰዓት ያለ ማቆረጥ ያለ መሰልቸት እረፍታቸው ምስጋናቸው ምስጋናቸው እረፍታቸው ሆኖላቸው ሥሉስ ቅዱስ እያሉ ያመሰግናሉ ይዘምራሉ። በምስጋናና በመዝሙር ውስጥ ደግሞ ጸሎትና ልመና አለ። የሰው ልጆችን ጸሎትና ልመና ወደ እግዚአብሔር እንደሚያደርሱ ሁሉ ማር ይቅር በል እያሉ የራሳቸውንም ጸሎትና ልመና ያቀርባሉ ለዚህም ነው ቅዱሳን መላእክት ያማልዱናል የምንለው።ዛሬ ግን ልዮ ጸሎትና ልመና ወደለመነው ወደ ቅዱስ ገብርኤል ምኞትና ጸሎት እናምራ።
#እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ለማብሰር የተመረጠው መላእክ ቅዱስ ገብርኤል ነው። ቢሆን ግን ይህን ዕድል ዝም ብሎ አላገኘውም ዕድል ፈንታ ጽዋ ተርታ ዝም ተብሎ የሚገኝ ነገር አይደለምና :: ይህን ዕድል ያገኘውን ቅዱስ ገብርኤልን አነሳን እንጂ ድንግል ማርያም ማብሰር የማኅበረ መላክት ሁሉ ምኞትና ጸሎት ነበር ማለት ይቻላል።
#እመቤታችንን ትጸንሲ ብሎ ለማብሰር መላእክ በሙሉ እኔ ብሆን እያሉ በእጅጉ ይመኑ፣ ይጓጉ ነበር :: ለምን ቢሉ ድንግል ፊት ቆሞ የሰማይና የምድር የሰውና የመላእክት የነፍስና የሥጋ መታረቂያ የጠቡ ግድግዳ መፍረሻ የሥግው ቃል የኢየሱስ ክርስቶስ ማደሪያ የሆንሽ አንቺ ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ አዳም ከነ ልጆቹ ነፃ የሚወጣበት ጊዜው ደረሰ አንባው ፈረሰ ብሎ ከማብሰር የበለጠ ሌላ የምሥራች በዓለም ላይ የለምና ነው ፡፡
#ቅዱስ_ገብርኤል የዚህ ምሥራች ነጋሪ ሆኖ የተመረጠው አስቀድሞ በዓለመ መላእክ በተፈጠረው የነገደ መላእክት መለያየትን በማረጋጋቱ ነው ፡፡ መላዕክት በተፈጠሩበት በዕለተ እሁድ ቅድሥት ሥላሴ በፈጠርኩላቸው አህምሮ ተጠቅመው አምላክነቴን መርምረው ይወቁ ሲል በዚያው በተፈጠሩበት ቀን ከመንበሩ ተሰወራቸው መላእክትም ከዙፋኑ ቀና ብለው ሲያ አጡት እርስ በእርሳቸውም "መኑ ፈጠረነ?"የፈጠረን ማነው? ሲሉ ተጠያየቁ ሳጥናኤል በክብር ይበልጣቸው ነበርና ቀና ቡሎ ቢመለከት ሥላሴን ከመንበር አጣ ዝቅ ብሎም ቢያይ መላእክ እርስ በእርስ ሲጠያየቁ ተመለከተ ሐሰት የሐሰትም አባቷ እርሱ ነውና "አነ ፈጠረክሙ" እኔ ፈጠርኳችሁ አላቸው ::
ገሚሱ አዎ የበላያችን ስለሆንክ ፈጠርከን ሲሉ ተገዙለት የቀሩት እርሱ ይሆን እያሉ ተጠራጠሩ በዚህ ጊዜ መላእኩ ቅዱስ ገብርኤል ተነስቶ ሳጥናኤል የበላያችን በመሆኑ ወይም በሥልጣን ሰለበለጠን የፈጠረን ከሆነ እኛም የበታቹቻችንን ፈጠርን እንደ ማለት ነው ፈጣሪስ ከሆነ አሁንም ደግሞ ፈጥሮ ያሳየን አለ ሳጥናኤልም እፈጥር ብሎ እጁን ወደ እሳት ቢከት ተቃጥሏል ገብርኤልም እርሱ ፈጣሪ አለመሆኑን ካሳወቀ በኋላ " እንቁም በዕበ ሕላዊከ " የፈጠረንን እስከምናውቅ ባለንበት (በቀደመ እምነታችን) ጸንተን እንቁም ብሎ አረጋጋቸው ::
ከዚህ በኋላ ሥላሴ እራሱን ገለጠላቸው ለሳጥናኤል የተገዙትና የተጠራጠሩትም ከማህበረ ከመላክት ተለይተው ወደ ምድር ተጣሉ በቅዱስ ሳጥናኤል ፈንታ ቅዱስ ሚካኤል ተሾመ መቶ ነገደ መላእክትም ዘጠና ዘጠኝ ነገድ ሆነ በኃላም የሰው ልጅ ተተክቶበተ ነገዱ እንደ ቀድሞ መቶ መሆን ችሏል ::
ቅዱስ ገብርኤልም በዚህ ትልቅ የዕቅበተ እምነት ሥራውና በማረጋጋቱ ቅዱስት ድንግል ማርያምን ለማብሰር ተመረጠ ዕድለኛ መላእክ መሆን ቻለ። ከአዳም ውድቀት በኋላም 5500.ዘመን ሲፈጸም እንደ ተስፈው ቃል ዕድለኛው ቅዱስ ገብርኤል ድንግልን ለማብሰር ሊላክ ከሌሎቱ መላእክት ተለይቶ ወደ አምላኩ ተጠራ ናዝሪት ገሊላ ወደ ምትባለው ቦታ ሂድ ዮሴፍ ለተባለ ሰው የታጨች ድንግልም ታገኛለህ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነው።
ከሷ ደርሰህ የምሥራቹን ነገር ንገራት ስትነግራት ግን ቃልህን ባትቀበልህ በቀስታ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር እንደሌለ አስረዳት እንጂ እንደ ካህኑ ዘካሪያስ እንዳታሳዝናት አለው መላእኩም ክንፉን እያማታ ወደ ገሊላ መንደር ወረደ የክንፉም ድምጽ በገሊላ አውራጃ ሁሉ ይሰማ ነበር:: እመቤታችንም ከእስራኤል ሴቶች ጋር ውኃ ልትቀዳ ወደ ወንዝ ወርዳ ነበር ስተመለስም መላዕኩ እየተከተለ "ትፀንሲ"ትንሻለሽ "ይላት ጀመር
#እመቤታችንም አግብቶ ጸንሶ የመውለድ ሀሳቡ እንኳን አልነበራትምና ይህስ የቀደሙ እናትና አባቶቼን አዳምና ሔዋንን ያሳተ ከይሲ ሳይሆን አይቀርም አለች ወደ ቤተ ዮሴፍም ሄዳ የቀዳችሁን ውኃ ከጀርባዋ ስታወርድ በድጋሚ መላእኩ "ትጸንሲ" (ትጸንሻለሽ) አላት ይህ ነገር ተደጋገመሳ እንዲ ያለውን ነገር እውነት ከሆነ በቤተ መቅደስ መቶ ይነግረኛል ካሎነ ይቀራል ብላ ከእስራኤል ሴቶች የተካፈለችሁን ሐርና ወርቅ ይዛ ወደ ቤተ መቅደስ ሄደች::
ቤተ መቅደስም ሆና ሐርና ወርቁ እያስማማች ስተፈት ለሦስተኛ ጊዜ መላእኩ ተገልጾ ደስ በሚያሰኝ ንግግር እያረጋጋ ትጸንሲ (ትጸንሻላሽ )አላት እመቤታችንም ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው " ምድር ያለ ዘር ሴት ያለ ወንድ እንዴት ሊያፈሩ ይቻላቸዋል "ይህ ነገር አይሆንም አለችሁ መላእኩም ዘመድሽ ኤልሳቤጥ የመውለጃዋ ወራት ካለፈ በኃላ ፣ሙቀት ልምላሜ ከተለያት በኃላ ለመውለድ ጸንሳለች ከጸነሰችም ስድስት ወር አልፎታል አላት።
ኤልሳቤጥስ ብትጸንስ ምክንያት ሚሆን ዘካሪያስ አላት እኔ ማን አለኝ አለችሁ መላእኩም ኤልሳቤጥን የመውለጃዋ ጊዜ ካለፈ በኋላ እንድ ትጸንስ ያደረገ አምላክ አንችንም ያለ ወንድ ዘር እንድትጸንሽ ማድረግ ይቻለዋል #ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም ::
#እመቤታችንም እውነተኛ መላእክ መሆኑን መርምራ ከተረዳች በኋላ እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ ስትል ምሥራቹን በደስታ ተቀበለች ከዚህች ሰዓት ጀምሮ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ በማህፀኟ ተቀረፀ:: መላእኩም የዚህ ድንቅ ምሥራች አብሳሪ በመሆኑ እየተደሰተ ወደ መጣበት ተመለሰ:: #ሉቃ 1÷26-

..........ይቆየን........
እግዚአብሔር አምላክ ከእመቤታችን እና እርሷን ለማብሰር ከተመረጠው ከዕድለኛው መላእክ ረድኤትና በረከት ይክፈለን !

ተክለ ኤል ኃ/ ማርያም
ታህሳስ ፳ ፪ ቀን ፳ ፻ ፲ ፪ ዓ.ም
ዕድለኛው መላእክ በሚል ርዕስ
ተለጥፎ የነበረ