ዐውደ ምሕረት
3.69K subscribers
930 photos
24 videos
271 files
193 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
"ዕርገተ ክርስቶስ"

#ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት "አምላክ በእልልታ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ፤ዘምሩ ለአምላካችን ዘምሩ፤ዘምሩ ለንጉሣችን ዘምሩ"(መዝ46:5) በማለት ጌታው ሲሆን ልጁ ልጁ ሲሆን ጌታው ስለሚሆን ስለ ኢየሱስ ክርሰቶስ ትንቢት ተናግሯል።

#በዚህ ኃይለ ቃል ያለው ምሥጢረ ተዋሕዶ ምንድን ነው? ቢሉ "አምላክ" ብሎ አምላክነቱን "ዐረገ" ብሎ ሰውነቱን ያስረዳል።ማረግ (ከፍ ከፍ ማለት፣ወደ ሰማይ መውጣት) የሚስማማው ሥጋ ነውና በተዋሕደው "ሥጋ ማርያም" በሁሉ ላለ "ቃል ለሚባል እግዚአብሔር" ዕርገት ተነገረለት።

#ነገሩን ትንሽ ለመግለጥ ያህል፦አምላክ በሁሉ ቦታ (በምልዐት) የሚገኝ ስለሆነ ከዚህ ተነሥቶ እዚያ ደረሰ አይባልም።አምላክ በተዋሕዶ ሰው ሲሆን ግን ከብቻዋ ከኃጢአት በቀር ለእኛ የሚነገረው ሁሉ ለእርሱም ተነገረለት።ተፀነሰ፣ተወለደ፣ተሰደደ፣ተጠመቀ፣ተሰቀለ፣ሞተ፣ተቀበረ፣ተነሣ፣ዐረገ ተባለለት።ይህ ሁሉ ግን በበጎ ፈቃዱ የተከናወነ ነው ፤ እንደኛ ግዳጅ ያለበት አይደለም።

#ክርስትና የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስን የእግር አሻራ የመከተል ሕይወት ነውና እርሱ ስለኛ የፈጸማቸውን ሁሉ እንፈጽማለን።ኋላም እርሱ በኃይሉና በሥልጣኑ ተነሥቶ እንዳረገ እንዲሁ እኛንም አስነሥቶ ያሳርገናል።ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ "እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ" ማለቱም ለዚህ ነው።

#ወደ እኔ እወስዳችኋለሁ ብሎ ጌታችን የነገረን ቃል እኔን በመመሰል እንድታድጉ (Theosis:ሱታፌ አምላክ) አደርጋችኋለሁ ሲል ነው።ይኸውም በመንግሥተ ሰማያት የምንኖረው ኑሮ "ዕርገታዊ" (ከፍ ከፍ የማለት) እንደሆነ ያስረዳል።ከቅዱሳን መላእክቱ ጋር "ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ" በማለት ውስጥ እየተቀደስን በጸጋ ላይ ጸጋ በክብር ላይ ክብር በጣዕም ላይ ጣዕም እየተጨመረልን እግዚአብሔርን እየመሰልን ከፍ እንላለን።

ከበዓለ ዕርገቱ ረድኤት በረከት ያሳትፈን አሜን!!!