ዐውደ ምሕረት
3.69K subscribers
930 photos
24 videos
271 files
193 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
#ሱባዔ ነቢያት

እግዚአብሔር ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ ቀደምት ነቢያት በተነሡበት ዘመን ቅደም ተከተል ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆንና ዳግም መምጣት ትንቢት ተናግረዋል፡፡ ሱባዔም ቆጥረዋል፡፡ ኢሳ.7.14፡፡ መዝ.49.3፡፡ ዘካ.13.6፤ ዘካ.14.1፡፡ የአንዱ ነቢይ ትንቢታዊ ንግግርና ሱባኤ በአነጋገርና በአቆጣጠር ከሌላኛው ነቢይ ጋር ይለያያል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ትንቢቱን ሲያናግር ምሳሌውን ሲያስመስል ጐዳናው ለየቅል በመሆኑ ነው፡፡ «ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ፡፡» እንዲል፡፡ ዕብ.1.1፡፡ የአቆጣጠር ስልታ ቸውና የሱባዔ መንገዳቸው ቢለያይም ዓላማና ግባቸው ግን አንድ ነው፡፡

#ሱባዔ አዳም

አዳም ትንቢት በመናገርና ሱባዔ በመቁጠር የመጀመሪያውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ምክንያቱም በገነት ሰባት ዓመት ከአንድ ወር ከዐሥራ ሰባት ቀን በተድላና በደስታ ከኖረ በኋላ ሕግ በማፍረሱና የፈጣሪውን ቃል በመጣሱ ያለምንም ትካዜና ጉስቁልና ከሚኖርበት ዔደን ገነት ተባርሯል፡፡ ዘፍ.3.24፡፡ እርሱም ፈጣሪው እንዲታረቀው፣ በዐይነ ምሕረት እንዲጐበኘው፣ ቅዝቃዜው ሰውነት ከሚቆራርጥ ባሕር ውስጥ በመቆም ለሠላሳ አምስት ቀን /አምስት ሱባዔ/ ሱባዔ ገብቷል፡፡ በባሕርዩ የሰውን ልጅ እንግልት የማይወድ ቸሩ ፈጣሪ የአዳምን ፈጽሞ መጸጸት ተመልክቶ «በኀሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ ወእድኅክ ውስተ መርህብከ ወእቤዝወከ በመስቀልየ ወበሞትየኸ በአምስት ቀን ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ» ብሎ ተስፋውን ሰጠው፡፡ አዳም የተሰጠውን ተስፋ ይዞ በዓለመ ሥጋ ለዘጠኝ መቶ ሠላሳ አመት ከኖረ በኋላ መከራና ችግር ከበዛበት ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡
በወንጀል ተከሶ በወኅኒ የተፈረደበት ሰው ከእስር የሚፈታበትን ዕለት በማውጣት በማውረድ ወራቱንና ዓመታቱን እንደሚቆጥር፣ አዳምም በሞት ቢለይም በሲኦል የነፍስ ቅጣት ካለበት ሥፍራ ይኖር ስለነበር የተሰጠውን ተስፋ በማሰብ ሱባዔውን እየቆጠረ የተናገረውን የማያስቀር የማያደርገውን የማይናገር ጌታየ «እነሆ አድንኀለሁ» ብሎ የገባልኝ ዘመን ተፈጸመ፤ ሰዓቱ አሁን ነው፤ እያለ ሲያወጣ ሲያወርድ ቸር አምላክ ሰው ኾኖ ሥጋ ለብሶ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ፡- «ተንሥኡ ለጸሎት ለጸሎት ተነሡ፤ ሰላም ለኩልክሙ፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን» በማለት አዳምን ከነልጅ ልጆቹ ነጻ አውጥቶታል፡፡ አዳምን በመከተል ልጆቹም አበው ቅዱሳን ነቢያት ሱባዔ በመግባት የተስፋን ዘመን በመቁጠር በመልካም ግብር ተከትለውታል፡፡ በዚህም መሠረት በርካታ ነቢያት በተለያየ ስልት ሱባዔ ቆጥረዋል፤ እኛም ሱባዔ ከቆጠሩ ነቢያት የተወሰኑትን በዚህ ጽሑፍ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡

#ሱባዔ ሔኖክ

ጻድቁ ሔኖክ፣ የያሬድ ልጅ ሲሆን፣ በትውልድ ከአዳም ሰባተኛ ነው፡፡ እርሱም በሕይወቱ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ቤት ንብረቱን በመተው በሱባዔና በትሕርምት እግዚአብሔርን አገልግሏል፡፡ ፍጹም አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ ሰው በመሆኑ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን መልካም ግብር ተመስክ ሮለታል፡፡ «ሔኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ፡፡» ዘፍ.5.22፡፡ ይህም በመሆኑ እግዚአብሔር የሱባዔውን ዋጋ ቅዱስ መንፈሱን በረድኤት ስለ አሳደረበት ትንቢት ተናግሯል፤ ሱባዔ ቆጥሯል፡፡ በሰማይ ተሰውሮ ሳለ ስለ ቅዱሳን መላእክት፣ ስለ መሲሕ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ስለ ፀሐይና ጨረቃ አመላለስ /ዑደት/ የሚተርክ በስሙ የተሰየመውን መጽሐፍ ጽፏል፡፡ ዘፍ.5 21-24፡፡ ይሁዳ ቁ.14፡፡ ሔኖክ 1.9፡፡
ሱባዔ ሔኖክ የሚባለው ነቢዩ ሔኖክ በመስፈርት የቆጠረው ሱባዔ ነው፡፡ መስፈርቱ /ማባዣ ቁጥር/ 35 ሲሆን 35'19 ሲበዛ በውጤቱ 685 ዓመት ይሆናል፡፡ 685'12 ስናባዛው 7980 ይሆናል፡፡ ይኸውም ሐሳብ የሚያስረዳው ስለክርስቶስ ምጽአት ነው፡፡
ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አሁን የደረስንበት ዘመን 7497 ይሆናል፡፡ ይህን ለማረጋገጥ በ5500 ዓመት ላይ 1997 ዓመትን መደመር ነው፡፡ በዚህን ጊዜ ከላይ ያስቀመጥነውን 7497 ዓመት ይሰጠናል፡፡ በነቢዩ ሔኖክ አቆጣጠር መሠረት ምጽአተ ክርስቶስ በ7980 ይሆናል፡፡ ከላይ ሔኖክ የቀመረውን ቁጥር ይዘን ከ7980 ዓመት ላይ አሁን ያለንበትን ዘመን /1997/ ስንቀንስ 483 ዓመት እናገኛለን፡፡ ስለዚህ በሔኖክ ሱባዔ መሠረት ምጽአተ ክርስቶስ ሊሆን 483 ዓመት ይቀራል፡፡

#ሱባዔ ዳዊት

ነቢዩ ዳዊት ከእስራኤል ነገሥታት ሁሉ ታላቅና ተወዳጅ ንጉሥ ነበር፡፡ ዘመነ መንግሥቱ 1011-971 ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደ ነበር ይታመናል፡፡ ነቢዩ ዳዊት ልበ አምላክ እንደ መሆኑ ትንቢት ተናግሯል፡፡ ሱባዔ ቆጥሯል፡፡ ይኽውም ቀመረ ዳዊት በመባል ይታወቃል፡፡ «እስመ ዐሠርቱ ምእት ዓመት በቅድሜከ፤ ከመ ዕለት እንተ ትማልም ኃለፈት፤ ሺ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትላንት ቀን»፡፡ /መዝ.89.4/ የሚለውን መምህራን ሲቆጥሩት 1140 ዓመት ይሆናል፡፡ ይኸውም በጌታ ዘንድ 1140 ዓመት እንደ አንድ ቀን እንደሆነ ነቢዩ ዳዊት ተናግሯል፡፡ ይህም ለዳዊት ሱባዔ መቁጠሪያ /መሥፈሪያ/ ሆኖ አገልግሏል፤ 1140’7= 7980 ዓመት ይሆናል፡፡ ይህም ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በ7980 ዓመት ክርስቶስ ዳግም እንደ ሚመጣ የሚያመለክት ነው፡፡

#ሱባዔ ዳንኤል

ነቢዩ ዳንኤል ምድቡ ከዐበይት ነቢያት ነው፡፡ እስራኤል ወደ ባቢሎን ሲማረኩ ተማርኮ ወደ ባቢሎን ወርዷል፡፡ እርሱም ስለ ክርስቶስ መምጣት ትንቢት ተናግሯል፤ ሱባዔም ቆጥሯል፡፡ «ሰብአ ሰንበታተ አድሞሙ ለሕዝብከ፤ ሰባ ሰንበት ወገኖችህን ቅጠራቸው፡፡» ይኸውም ክርስቶስ ከ490 ዓመት በኋላ ሰው መሆኑን የሚያመለክት ትንቢት ነው፡፡ እንዲሁም «እስከ ክርስቶስ ንጉሥ ትትሐነፅ መቅደስ ወእምዝ ትትመዘበር፤ እስከ ንጉሥ ክርስቶስ ድረስ መቅደስ ትታነፃለች በኋላም ትፈርሳለች» ሲል ተናግሯል፡፡
የአቆጣጠር ስልቱም በዓመት ሲሆን ይኸውም ሰባቱን ዓመት አንድ እያሉ መቁጠር ነው፡፡ ይኽውም ሱባዔ ሰንበት ይባላል፡፡ ዳንኤል ሱባዔ ከቆጠረበትና ትንቢት ከተናገረበት ጀምሮ ክርስቶስ እስከ ሚወለድ 490 ይሆናል፡፡ መስፈርቱ /ማባዣው/ ሰባት ስለሆነ 7’70 ስናባዛው 490 እናገኛለን፡፡ ይኸውም ነቢዩ ሱባዔ ከቆጠረና ትንቢት ከተናገረ ከ490 ዓመት በኋላ የክርስቶስን መወለድ ያመለክታል፡፡
በአጠቃላይ ከላይ የተመለከትናቸው ቅዱሳን ነቢያት አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር በማድረግ ሱባዔ ገብተው በትሕርምት በመኖራቸው ድንቅ የሆነውን የክርስቶስን ልደትና ዳግም ምጽአት ለመተንበይ ችለዋል፡፡ ሱባዔ መግባት የራቀን ለማቅረብ የረቀቀን ለማጉላት ብቃትን ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስገኝ መንፈሳዊ ጥበብ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

**** ይቀጥላል*****
ስለ ታቦቲቱ የባዕዳኑ መልከታ
...... #ካለፈው የቀጠለ.....
#ጀምስ_ብሩስ /james bruce/
____________________________
#የዓባይን ምንጭ ወይስ #ታቦቲቱን ፍለጋ ???
_________________________________


ባለፈው ጽሑፋችን ግራሃም ሐንኰክ የጠፋው ታቦት ዘራፊዎች/#Raiders_of_the_Lost_Ark/ በሚል ርእስ የተሠራውን የሆሊውድ ፊልም በ 1983 ናይሮቢ ውስጥ ካየ በኋላ ታቦቲቱን ለማግኘት እንደተነሳሳ ዓይተን ነበር። አሁን ደግሞ ጀምስ ብሩስን በሽፋን ስም ታቦቲቱንና መገኛዋን ለማግኘት ያደረገውን ምሥጢራዊ ጥረት እንመለከታለን።
#ከክርስቶፈር ደጋማ ሞት በኋላ "የክርስቶስ ሠራዊት" ስለ ኢትዮጵያ ለማወቅ የነበረው ጉጉት እየቀዘቀዘ ሲመጣ የስኮትላንዱ "ምሥጢራዊ የወንድማማቶች ማህበርም " ስለ ሰሎሞን ቤተ መቅደስና የቃል ኪዳኑ ታቦት የወረሳቸው አንዳንድ ምሥጢራዊ የሃይማኖት ሥርዓቶች ሲኖሩ በነዚህም ውስጥ ታቦቱ ጉልህ ሚና አለው።
በመሆኑም በዚህ ረገድ በድፍረቱና በቆራጥነቱ ስለሚታወቀውና ቴምፕላሮችን ካዳነው ከንጉስ ብሩስ ጋር የዘር ግንዱን ስለሚቆጠረውና ኢትዮጵያ በስፋት ስለጎበኘው የእስኮትላንዱ ተወላጅ ጀምስ ብሩስ መለመለ።
#ረጅሙና ግዙፉ ጀምስ ብሩስ ስኮትላንድ ውስጥ 1730 ተወለዶ ከፍተኛ ትምህርቱን በኤደን ብራ ዩኒቨርሲቲ ያጠናቀቀ ምሁር ነው። በትምህርቱ በኋላ ኢስት ኢንድያ በተባለ ድርጅት ተቀጥሮ ሠርቷል። ይሁንና በ1754 ባለ ቤቱ ስለሞተች በደረሰበት ብስጭት የተነሣ ከሀገር ወደ ሀገር መዘዋወር የጀመረ ሰው ነው።
የነበረው የቋንቋ ችሎታው በማጤንም በሰሜን አፍሪካ አልጀርስ ውስጥ የብሪቲሽ ቆንጽላ በመሆን እንዲሰራ ከመደረጉም ባሻገር ወደ ቅድስቲቱ ሀገር ወደ ኢየሩሳሌምም ተጉዟል። በቋንቋ ረገድ አረብኛ፣ፖርቱጋልኛ እንዲሁም ጥንታዊ የሆነውን የኢትዮጵያ ቋንቋ (ግእዝን) ያውቅ ነበር።
#ጀምስ_ብሩስ በ1759 የግእዝ ቋንቋ ያጠናበት ዋነኛ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ለመዝለቅ ላሰበው ጉዞ ዝግጅት ለማድረግ ሲሆን ከእርሱ በፊት ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው የነበሩ ሰዎችን የጻፏቸውንም በማንበብ በማጥናት ስለ ሀገሪቱ በቂ ዕውቀት ጨብጦ ነበር ዘዚያም 1768ወደ ካይሮ በመሄድ ታሪካዊ ጉዞዎን ለመጀመር ዝግጅቱን አጠናቀቀ።
ብሩስ ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ ምን አነሳሳው? እርሱ እንደሚለው የዓባይን ወንዝ ምንጭ ለማግኘትከ1768-1773በተከታታይ የተደረጉ ጉዞዎች( Travels to Discover The Source of Nile in The Years 1768-1773 የሚል ባለ 3ሺህ ገጽ መጻሕፍ በ5 ተከታታይ ጥራዝ ጽፎል። ቢሆንም ግን ቅሉ የዓባይን ወንዝ ምንጭ በትክክል እንኳ አላወቀውም፤አልደረሰበትም የዓባይ ወንዝ ጣና እንደሆነ አስፎሯልና
#ኢትዮጵያዊያን ሊቃውንት ግን የዓባይ ምንጭ ግሽ ዓባይ ሰከላ እንደሆነ እና ዋነኛ ምንጩም ገነት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስን ዋቢ አድርገው ይገልጻሉ ፤ያምናሉ #ዘፍ 2÷10 -13 የሱ ዓላማ ታቦቲቱን ማግኘት እንጂ የዓባይን ምንጭ ማግኘት ስላልነበረ ነው ያን የሚያክል ባለ ብዙ ገጽ መጽሐፍ ጽፎ ከስተት የደረሰው ። በኢትዮጵያም ሁለት ዓመት ከቆየ በኋላ ሦስት የመጽሐፈ ሄኖክ ቅጂዎችን ሰርቆ ኮብልሏል።

ኢትዮጵያ አ.አ
ተክለ ኤል ኃ/ማርያም
ነሐሴ ፯ / ፳ ፻ ፲ ፫