ዐውደ ምሕረት
3.68K subscribers
930 photos
24 videos
271 files
193 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

በስመ አብ፤ ወወልድ፤ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከጥር ፳፱ እስከ የካቲት ፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ለ ፫ ተከታታይ ቀናት በመላው ዓለም የታወጀው የነነዌ ፆም እና ምሕላ መጠናቀቅን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ::

#Ethiopia | በትንቢተ ዮናስ በሰፊው እንደተጠቀሰው የነነዌ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ላይ ስለአመጹ እና ግብራቸውም በእግዚአብሔር ፊት አጸያፊ በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር ዮናስን “ተነስተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ ክፋታቸውም ወደ ፊቴ ወጥቷልና በእርስዋ ላይ ስበክ” በማለት አዘዘው፡፡ ትንቢተ ዮናስ ምዕ ፩ ቁጥር ፪ ዮናስም ድምፁን ከፍ አድርጎ ለነነዌ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ሲሰብክ “የነነዌ ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ፤ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ፡፡ ወሬውም ወደ ነነዌ ንጉሥ ደረሰ፤ እርሱም ከዙፋኑ ተነስቶ መጎናጸፊያውን አወለቀ ማቅም ለበሰ፤ በአመድም ላይ ተቀመጠ፡፡ አዋጅም አስነገረ፤ በነነዌ ውስጥ የንጉሡንና የመኳንንቱን ትእዛዝ አሳወጀ፤ እንዲህም አለ ሰዎችና እንስሶች፤ ላሞችና በጎች አንዳችን አይቅመሱ፣ አይሰማሩ፣ ውኃንም አይጠጡ፤ ሰዎችና እንስሶችም በማቅ ይከደኑ፣ ወደ እግዚአብሔርም በብርቱ ጩኸት ይጩኹ፤ ሰዎችም ሁሉ ከክፉ መንገዳቸውና በእጃቸው ካለው ግፍ ይመለሱ፡፡ እኛ እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ተመልሶ ይጸጸት እንደሆነ ማን ያውቃል፡፡ እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውንም አየ፤ እግዚአብሔርም ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም” ትንቢተ ዮናስ ፫፡ ፭-፲

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ይህን የነነዌ ሰዎች ፆም መነሻ በማድረግ የነነዌ ሰዎችን በምሕረቱ የጎበኘ አምላክ እኛንም በምሕረቱ ይቅር ይለን ዘንድ በየዓመቱ በአዋጅ በመፆም አምላካችንን ስንማጸንበት ኖረናል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባዔ በጥር ፳፮ ቀን ፳፻፲፭ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በወሰነው መሠረት የካቲት ፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም የተጠናቀቀው የነነዌ ፆምና ምሕላ ልዩ በሆነ በመንፈሳዊ የንስሐ ጸሎት በሰላም ተጠናቋል፡፡

በምሕላውም ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ጀምሮ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ ካህናት፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ አገልጋዮች እና ምእመናን እንደነነዌ ሰዎች ጥቁር ለብሰን ጠዋትና ማታ በጸሎት ፤ በምሕላ፤ ቀን በቅዳሴ እንዲሁም በሰባቱ የጸሎት ጊዜያት ፈጣሪያችንን ስንለምን እና ስንማጸን የቆየንበት ምክንያት በቤተክርስቲያናችን ላይ የመጣው ፈተና እጅግ በጣም ከባድ በመሆኑ ነው፡፡

በዚህ የጾምና የንስሐ ወቅት ምእመናን ልጆቻችን የአባቶቻችሁን ጥሪ ሰምታችሁ፤ የሹመኞችን ማዋክብና እስር ሳትፈሩ ጥቁር ለብሳችሁ ጠዋትና ማታ በጾምና በምሕላ፣ ቀን በቅዳሴ በቤተክርስቲያን ቅጥር እየተገኛችሁ ለአምላካችን ያቀረባችሁትን ጸሎት እና ምሕላ እግዚአብሔር ሰምቶ ለችግራችን መፍትሄ፣ ለሀገራችን ሰላምን እንደሚሰጠን እምነታችን ጽኑ ነው፡፡ እናንተም ምእመናን የቤተ ክርስቲያንን ጥሪ ሰምታችሁ ለሃይማኖታችሁ፣ ለሀገራችሁ አንድነትና ሰላም ያላችሁን ጥልቅ ፍቅር ስለገለፃችሁም ያገኘነው መንፈሳዊ ብርታት ሳንገልፅላችሁ አናልፍም፡፡

በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም እና በቅዱሳን አማላጅነት፣ በመላእክት ተራዳኢነት በፍፁም ፍቅርና አንድነት የያዝነውን ጸሎት እና ምሕላ አጠናቀናል፡፡ ችግራችንን ለአምላካችን በለቅሶ እና በጩኸት ነግረናል፡፡ ከዚህ በኋላ መከራው ቢጸና፣ የመከራው ጊዜ እንኳን ቢረዝም እግዚአብሔር በመከራ ውስጥ ሊያፀናን እና ሊያበረታታን አስቦ በመሆኑ በፍፁም አንናወጽም፡፡ ከእነኚህ መከራዎች በኃላም ታሪክን ጽፈን ሃይማኖታችንን ጠብቀን እና አስጠብቀን በመንፈሳዊ ጽናት እና ተጋድሎ እንሻገራለን፡፡

ጥቃቱ የቤተ ክርስቲያንን እውነት በካዱና በእውነተኛዋ ቤተ ክርስቲያን መካከል ነው፡፡ ይህም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሃይማኖት፤ ቀኖና እና አስተዳደራዊ ሕግጋትን ጥሰው ሕገወጥ የጳጳሳት ሢመት በመደረጉ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ቅዱስ ሲኖዶስ በሕገ ቤተ ክርስቲያንና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት በጥር ፲፰ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ይህን ጥሰት የፈፀሙትን ግለሰቦች አውግዛ ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት የለየቻቸው ቢሆንም ጉዳዩ ከግለሰቦቹ በላይ በመንግሥት ስልጣን ላይ ባሉና ጽንፈኛ በሆኑ ፖለቲከኞች እንዲሁም የሌላ እምነት ተከታዮች ጭምር የሚደገፍ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያንን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል፡፡

እየተፈጸመ ያለው ድርጊት በሰማያዊ መንፈሳዊ ዓለምና በምድራዊ ሥጋዊ ዓለም መካከል ስለሆነ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥም የቤተ ክርስቲያን ክብርና ተቋማዊ ልዕልና ተደፍሯል፡፡ የቤተክርስቲያን ቅጥሮች መሣሪያ በያዙ አካላትና በመንግሥት የጸጥታ መዋቅር በኃይልና በጉልበት ተወሯል፡፡ ሊቃነ ጳጳሳት አባቶች ለብዙ ዓመታት ከኖሩበት አህጉረ ስብከት ያለአንዳች የሕግ መሠረት በጸጥታ መዋቅሮች ተባረዋል፡፡ በነጻነት የመንቀሳቀስ መብቶቻቸው ተገድቦም በግዞት ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ተደርገዋል፡፡ ወደ አህጉረ ስብከታቸውም ተመልሰው መግባት እንዳይችሉ እቀባ ተደርጎባቸዋል፡፡ ካህናት አባቶች እና ምእመናንም ያለአንዳች የሕግ መሠረት በየእስር ቤቱ ያለበቂ ምክንያት በሕገወጥ መንገድ ታጉረዋል፡፡ በጸጥታ ኃይል ከመጠን በላይ ከመደብደባቸው የተነሳ የሞት፣ የከባድ እና ቀላል አካል ጉዳት እንዲደርስባቸው ምክንያት ሆኗል፡፡ በአጠቃላይም በመንግሥት ኃይሎች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈፅሞባቸዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ይህ ሁሉ በደል ቢፈጸምባትም ናዛዜ ሕዙናን የሆነው አምላካችን ለቤተ ክርስቲያናችን እና ለሀገራችን መፍትሔ እንዲያመጣልን፣ መንግሥትም ወደ ልቡ ተመልሶ ቤተክርስቲያንን እንዲያከብርና እንዲጠብቅ በሚል ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ይህን ጾም የነነዌ ሰዎች እንዳደረጉት ጥቁር ለብሰን በፍፁም ኃዘን ወደ አምላካችን እንድንጮህ ቅዱስ ሲኖዶስ ትእዛዝ ባስተላለፈበት ማግስት በሻሸመኔ ደብረ ስብሐት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ሕገወጡን ቡድን በኃይል ለማስገባት በመንግሥት የጸጥታ መዋቅሮች በተወሰደ አሰቃቂ እርምጃ እስከ አሁን በደረሰን መረጃ ቁጥራቸው ከ፴ በላይ የሚሆኑ ካህናትን እና አገልጋዮችን ጨምሮ የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች ቅጥሯ አይደፈርም፣ ቤተክርስቲያን በተወገዙ ግለሰቦች አትረክስም በሚል ለሃይማኖታቸው ሰማእትነትን ተቀብለዋል፡፡ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ልጆቿም በደረሰባቸው ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት ምክንያት በሕክምና ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ በደል በኋላም እስከ አሁን ድረስ የሞቱትን በአግባቡ መቅበርና የተጎዱትን በበቂ ሁኔታ ማሳከም ሳንችል ቀርተናል፡፡ እነዚህ ሰማዕታት በዚህ ኃጢያት በበዛበት ዘመን ለቤተክርስቲያን እስከሞት ድረስ በመታመን ለቤተ ክርስቲያንና ለምእመናን የጽናት ተምሳሌት በመሆናቸው ቤተክርስቲያን ስትዘክራቸው ትኖራለች፡፡ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን በልጆቿ ላይ እየደረሰ ባለው ሞት፤ እርዛት፤ እስራት እና መልከ ብዙ በሆነው መከራ ብታዝንም ለክርስትና እውነተኛነት ምስክሮች የሆኑ አዳዲስ ቅዱሳን ሰማእታትን በማግኘቷም እጅግ ደስ ትሰኛለች፡፡
ጾሙ ከተጀመረም በኋላ ሕዝቡ ወደ አምላኩ እንዳይጮህ እና እንዳይጸልይ ለማወክ የሕዝብ አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙ የመንግሥት ሹማምንት ሊያገለግሉት ኃላፊነት የተቀበሉበትን የሀገሪቱን ሕግ ጥሰው ምእመናን ልጆቻችን ጥቁር ለብሰው ወደ መሥሪያ ቤት እንዳይገቡና በመንግሥት ቢሮዎችም አገልግሎት እንዳያገኙ በተለይም በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና አንዳንድ በፌዴራል እና በከተማ መስተዳድር ቢሮዎች ጥቁር የለበሱ እና በሀዘን ላይ ያሉ ልጆቻችንን በማሠር ሲያንገላቱ በዓይናቸው ያዩ ምስክሮች አረጋግጠውልናል፡፡ በዚህም ሹማምንት ስልጣናቸውን ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት እየተጠቀሙበት መሆኑን እና ለቤተ ክርስቲያናችንም ሆነ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ከፍተኛ ንቀት እና ጥላቻ ያላቸው መሆኑን ተረድተናል፡፡

ይህ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየደረሰ ያለው መከራና በደል በዚህ ዘመን በጉልህ የሚጠቀስ የቤተ ክርስቲያን የስደትና የመከራ ጊዜ ነው፡፡ ይህ የቤተ ክርስቲያን የስደትና የመከራ ጊዜ በቤተ ክርስቲያኒቱ የታሪክ መዝገብ እና በመጽሐፈ ስንክሳር ተመዝግቦ ይቀመጣል፡፡ ለትውልድም ይተላለፋል፡፡ ይህ የፈተና ዘመን ያልፋል፤ ነገር ግን በዚህ ታሪክ ውስጥ ከእውነት ጎን የቆማችሁ ስማችሁ በታሪክ እና በወርቅ ቀለም ሲፃፍ በቤተክርስቲያን ላይ መከራ ያበዛችሁ ክፉ ታሪካችሁን ዛሬ በእጃችሁ ጽፋችሁ አልፋችኋል፡፡

በዚህ አጋጣሚ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውጭ ሌሎች የክልል ርዕሳን መስተዳድሮችና ከተሞች በተለይም

* የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፤ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት፤

* የሲዳማ ክልላዊ መንግስት፣

* የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት፤

* የሱማሌ ክልላዊ መንግሥት፤

* የቤንሻንጉል ክልላዊ መንግሥት፣ የሐረሪ ክልላዊ መንግሥት፣

* የአፋርና ጋምቤላ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት፤

* በጎፋ ዞን የሳውላ ከተማ እና ሌሎች ስማቸውን ያልጠቀስናቸው መንግሥታዊ ተቋማት የቤተ ክርስቲያናችንን ጥሪ በመከተል በአግባቡ ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር የወሰዳችሁ ፍትሐዊ እና ሕጋዊ መፍትሔዎችን እናደንቃለን፣ በቤተ ክርስቲያንም ስም እናመሰግናለን፡፡

እንዲሁም ሀዘናችሁ ሀዘናችን ነው ብላችሁ ከጎናችን የተሰለፋችሁ አኃት አብያተ ክርስቲያናት፤ የሃይማኖት ተቋማት፣ ድርጅቶች እና ጉባኤያት፤ የእስልምና እምነት ተከታዮች፤ በእምነት የማትመስሉን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ስላደረጋችሁልንና ስለምታደርጉልን እርዳታና ትብብር በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም እናመሰግናለን፡፡

ጸሎተ ምሕላውን ስናውጅ መንግሥት ሕግ አክብሮ እንዲያስከብር፣ የቤተክርስቲያኒቱን ክብር እና ልዕልና እንዲያከብር፣ በሃይማኖታችን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን እንዲያቆምና ወደ ውስጡ ማየት እንዲችል ነበር:: ይህ ድርጊት እስከ አሁን ድረስ ግን መንግሥት ለዘመናት ሕጋዊ ተቋም እና የሀገር ባለውለታ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን ከመስማት እና ችግሯን ከመቅረፍ ይልቅ የማዋከቡን ሥራ አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡ በዚህም መንግሥት ችግሮችን ኃላፊነት ተሰምቶት እንዲፈታ ያደርገዋል የሚል እምነት ቢኖረንም አገዛዙ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ልቡ መደንደኑን መመልከታችን በእጅጉ ልባችንን ሰብሮታል፡፡

በተለይም ቤተ ክርስቲያናችን ያወጀችው የ፫ ቀናት ጸሎትና ምህላ በአግባቡ እንኳን ሳይጠናቀቅ ከመንግሥት ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ወቅታዊ የፀጥታ ጉዳይን አስመልክቶ በየካቲት ፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም የተሰጠው የሰልፍ ክልከላ መግለጫ መንግሥት አሁንም ችግሩን ለመፍታት ሳይሆን ቤተክርስቲያኒቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ለማውደምና ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማጥፋት የታወጀ አዋጅ መሆኑን በጽኑ እንድናምን አድርጎናል፡፡

በመግለጫውም፡-
፩ኛ. በእምነቱ አባቶች በተመሳሳይ መልኩ ሰልፍ ተጠርቷል በማለት መጥቀሱ የቤተክርስቲያን የመጨረሻው አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞ የለያቸውን አካላት የእምነቱ ተከታይ ማድረግ ብቻ ሳይሆን መብት ያላቸው ሕጋዊ አካላትና የቤተ ክርስቲያን አባቶች አድርጎ መጥራቱ አሁንም ላይ ማብራርያ ለመስጠት መሞከሩ የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር የሚነካ እና የሚያጠለሽ እንዲሁም ሕግና ሥርዓትን ከማስከበር ይልቅ ለሕገ ወጦች ጠበቃ ሆኖ የሚከራከረው መንግሥት መሆኑን ጭምር ለመረዳት ችለናል፡፡ በመሆኑም ቤተክርስቲያን በመንግሥት የደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ተሰጠ የተባለው መግለጫ የቤተ ክርስቲያናችንን ሕጋዊ መብት የገፈፈ እና ሕገ ወጥ መግለጫ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን አትቀበለውም፡፡
፪ኛ. ጉዳዩን የውጪ እና የውስጥ ጠላቶች የፈጠሩት ነው በማለት የተለመደውን ፖለቲካዊ ቅርፅ ለማስያዝ መሞከርም ቤተክርስቲንያንም ሆነ ሕዝብን መናቅ በመሆኑ የምንቀበለው አይሆንም፡፡ ቤተ ክርስቲያን በተለይ ላለፉት ፬ ዓመታት በሀሰተኛ ትርክት ልጆቿ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል መከራን ሲቀበሉ ችግሮችን በሆደ ሰፊነት ችላ ያለፈችው የሀገር መሠረት እንዳይናጋ፣ ቅጥሯ እንዳይደፈር በማሰብና በሀገር አንድነት ላይ ባላት የማይናወጽ ጽኑ አቋም ምክንያት መሆኑን መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡ ጉዳዩ ግልፅ የሆነ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ሆኖ እያለና መፍትሄውም በመንግሥት እጅ የሚገኝ ብቻ መሆኑ እየታወቀ የፖለቲካ ቅርፅ ለማስያዝ መሞከር ችግሩን ያባብሰው እንደሆን እንጂ አይፈታውም፡፡

በሰሞኑም ቤተ ክርስቲያናችን በመዋቅር የምትመራ እና ልጆቿም ድምጽዋን አውቀው በአግባቡ የሚሰሟት መሆኑ እየታወቀ ሆነ ተብሎ ቃላት አጠቃቀሙ እንኳን ኦርቶዶክሳዊ ያልሆነ የሀሰት እና ጸብ አጫሪ የሆኑ መልእክቶችን በአደባባይ የተለጠፉ መሆናቸውን ሲታይ ምን ያህል ጉዳዩን ላልተገባ ፖለቲካዊ ጥቅም እንደተፈለገ ለመረዳት ችለናል፡፡ ይህ ተለጠፈ የተባለውም ሕገ ወጥ ጽሑፍ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ያልሆነና ፈጽሞም ሊሆን የማይችል መሆኑን ጭምር ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡

፫ኛ. የትኛውም ሰልፍ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ማድረግ አይቻልም በማለት የተደረገው ክልከላን በተመለከተም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ውስጥ መሠረታዊ መብት ሆኖ የተጠቀሰ እና በሕገ መንግሥቱም አንቀፅ ፴ ላይ በግልጽ የተደነገገ በመሆኑ መንግሥት ራሱ የሚመራበትን ሕገ መንግሥት ማክበርና ማስከበር ይኖርበታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ላይ ከላይ የተጠቀሰው ከፍተኛ መከራና በደል ምክንያት ከብዙ ሺህ ዓመታት በላይ ጸንታ የመጣችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በእኛ በልጆቿ ዘመን ስትፈርስ ዝም ብሎ መመልከት በጭራሽ የሚታሰብ አይሆንም፡፡

ይህን በደላችንን ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ለማሳወቅ እና መንግሥትም ከሚያደርገው ጣልቃ ገብነትና አፈና ወጥቶ ሕግ እንዲያከብር እና እንዲያስከብር የጠራነው የየካቲት ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ሰላማዊ ሰልፍም መንግሥት ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ እንድናከናውን መፍቀድ አሊያም የጠየቅናቸውን ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎቻችንን በአግባቡ እና አንድ በአንድ መመለስ አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ደግመን ደጋግመን ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥም የሚደርስብንን ሞት፣ መከራና ስደት እኛ አባቶች ከመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ጋር ደስ ብሎን የምንቀበለው እንጂ ቤተ ክርስቲያናችን እና ሀገራችን ስትፈርስ ቆመን የምንመለከት፣ ዝም የሚል አንደበትና የሚሸከም ኀሊና የማይኖረን መሆኑን በአጽንዖት እናሳስባለን፡፡

መንግስት ከአጉል እልከኝነቱ ወጥቶ ከሕገ ወጦቹ ግለሰቦች ጋር በመተባበር በአደባባይ እየፈጸመ ያለውን የሕግ ጥሰት ዛሬን ጨምሮ በቀጣዮቹ ፪/ሁለት/ ቀናት ውስጥ እንዲያቆም እና ሕግ እና ሥርዓትን እንዲያስከብር፣ በኃይል የወረራቸውን መንበረ ጵጵስና እና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ለቆ ለቤተክርስቲያኒቱ ሕጋዊ መዋቅር እንዲያስረክብ፣ ያለአግባብ ያሠራቸውን ካህናት እና ምእመናን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቅ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ለፈፀመው በደል በአደባባይ ይቅርታ እንዲጠይቅ፤ በካህናት እና ምእመናን ላይ ለደረሰው ሞት እና የአካል ጉዳት ተገቢውን ካሳ እንዲክስ እና የወደሙ ንብረቶቿን እንዲጠግን በጥብቅ እንጠይቃለን ፡፡

መንግሥት በዚሁ አካሄድ ሕግ እየጣሰ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር እና ልእልና እያዋረደ የሚቀጥል ከሆነ ቤተ ክርስቲያን መንግሥት የጣሰውን ሕግ መሠረት በማድረግ መብቷን ለማስከበር እስከአሁን ድረስ ፍጹም ሰላማዊ የሆነውን እንቅስቃሴዋን አድማሱን በማስፋት በየካቲት ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ለማድረግ ያቀደችውንና ያሳወቀችውን ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ ያለማንም ከልካይነት በራሷ አደባባይ የምታከናውን መሆኑን እያሳወቅን መንግሥትም ድርሻው ሰልፉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ብቻ መሆኑን እያሳሰብን ዛሬም ቢሆን መንግሥት ቆም ብሎ በማሰብ ከእኛ ከአባቶች ጋር ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና መንፈሳዊ የአስተዳደር ሥርዓታችንን ባልጣሰ መልኩ ለመነጋገር እና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት ካደረገ በውይይት ለመፍታት መንፈሳዊ በራችን ክፍት መሆኑንም እናሳውቃለን፡፡

ከዚህ ውጭ ግን በሁለቱ አባቶች መካከል የተፈጠረ ችግር እየተባለ የሚነገረው ፖለቲካዊ ጨዋታ የመንግሥት እንጂ በሀገሪቱ ሕጋዊ ሰውነት የሌላቸውና ከቤተ ክርስቲያን የተለዩ ግለሰቦች ጋር ማነጻጸር ሕገ መንግሥታዊም ሆነ ሞራላዊ የሕግ መሠረት የለውም፡፡

ስለዚህ ቤተ ክርስቲያናችን የጠራችውን ሰላማዊ እና ሕጋዊ የሆነ የመብት ጥያቄ የማፈን ሂደትን በጥብቅ እንቃወማለን፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን እስከአሁን ባደረጋችሁት ጽናትና ተጋድሎ ሃይማኖታችሁንና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንችሁን እንዳላሳፈራችሁ ሁሉ አሁንም ከስሜታዊነት በወጣ ሁኔታ በከፍተኛ ጽናት እና ጥንካሬ የአባቶቻችሁን ድምጽ ብቻ እንድትሰሙ፣ ቤተ ክርስቲያንን በየአጥቢያችሁ ተደራጅታችሁ እንድትጠብቁ፤ ለአባቶቻችሁ መንፈሳዊ ጥሪ ፈጣን ምላሽ እንድትሰጡ፣ እየመጣው ላለ መከራና ስደት ለመንፈሳዊ ተጋድሎ እንድትዘጋጁና በፍፁም መንፈሳዊ ጨዋነት በአንድነት የመጣብንን ፈተና እንድትወጡ አደራ እያልን አባታዊ መልእክታችንን እያስተላለፍን ሰላማዊ ሰልፉን በተመለከተም በአጭር ጊዜ ውስጥ ዝርዝር መግለጫ የምንሰጥ መሆኑን እያሳውቅን በዚህ ጥቃት መስዋእትነት የከፈሉ እና ያረፉ ልጆቻችንን ነፍሳቸውን በአጸደ ገነት በክብር ያሳርፍልን እያልን ጸሎተ ፍትሐትም በየደረጃው የሚከናወን መሆኑን እያሳወቅን በተለያዬ ጊዜ ዛሬን ጨምሮ በወለቴ እና በሰበታ ከተሞች የደረሰውን የአካል ጉዳት እና ሞት እግዚአብሔር ምህረት እና መጽናናቱን ያድልልን፡፡ እግዚአብሔርም ገድላችሁን፣ ጽናታችሁንና ጸሎታችሁን ይቀበል፤ የቅዱሳን አምላክ ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

“እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክ”
የካቲት ፪ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
የማይቀርበት ጉባዔ ተጋብዘዋል !!!!!!
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
እንኳን ለበዓለ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ለአድዋ በዓል በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን !!!!
Channel photo updated
Audio
Forwarded from ዐውደ ምሕረት (😷ተርቢኖስ ሰብስቤ😷)
Forwarded from ዐውደ ምሕረት (😷ተርቢኖስ ሰብስቤ😷)
#በሌላ_ሰው ገንዘብ ካልታመናችሁ፥
#የእናንተን ማን ይሰጣችኋል? ”
#ሉቃስ ፲ ፮ ፥፲ ፪


ወደ ሌላ ሀገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፤
ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ።
አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ። ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው።
#አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ፦ ጌታ ሆይ፥ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ።
#ጌታውም፦ መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። ሁለት መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት አለ።
#ጌታውም፦ መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፥ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው።
#አንድ_መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ።
#ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው፦ አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ፥ ካልዘራሁባት እንዳጭድ ካልበተንሁባትም እንድሰበስብ ታውቃለህን?
ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር፥ እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር። ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት አሥር መክሊትም ላለው ስጡት፤ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።
የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።


የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል ቅዱስ ማቴዎስ እንደጻፈው የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፳ ፭ ÷፲ ፬ - ፴
#መድኃኔ_ዓለም
እንኳን  አደረሳችሁ!

"እርሱ በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደሆነ እናውቃለን" (ዮሐ 4÷42)

ኢየሱስ ማለት መድኃኒት ማለት ነው መድኃኒትነቱ በጥቂት ሰዎች ብቻ የተገደበ፤እንደነ ኢያሱ በእስራኤል ዘሥጋ ማዳን ብቻ የተገለጠ ሳይሆን፤በሥጋ፣ በመንፈስና በነፍስ ማዳን ላይ የተመሠረተ ለሰው ልጆች ሁሉ የተሰጠ፤ ያውም ከአዳም ጀምሮ እስከ ዓለም መጨረሻ ድረስ ለሚነሳው ትውልድ ሁሉ የሆነ ማዳን ነው፡፡

ስለዚህም መድኃኒትነቱ ውሱን እንዳልሆነ ለማጠየቅ ˝ኢየሱስ˝ የሚለው በምልኣት ሲገለጥ ˝የዓለም-መድኃኒት˝ ብለን እንጠራዋለን፡፡

ዓለም ማለት ዘመድ፤ ዘመደ ፍጥረት ፤ሰማይ ከነግሡ ምድር ከነልብሱ፤ሰማይ ከነደመናው ምድር ከነጉተናው ማለት ሲሆን ሁሉን የጠቀለለ ስም ነው፡፡
በሊቃውንቱ ሃያ ዓለማት እና ሃያ አየራት እንዳሉ ይገለጣል፤ሃያ ዓለማት የሚባሉትም ዘጠኝ ዓለመ እሳት፤አምስት ዓለመ ምድር፤አራት ዓለመ ማይ እና ሁለት ዓለመ ነፋስ ናቸው፤(9+5+4+2=20)፤አየራቱም በዚህ ልክ ናቸው ይላሉ (ቅዳሴ.ማር አንድምታ)፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሰቀል ዓለሙን ሁሉ ለማዳን ነው ሲባል ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን በአዳም ምክንያት ተረግሞ የነበረውን ዓለም ለሰው ልጆች በግዛት መልክ ተስጥቶ የነበረውን ሁሉ ዓለም ለመባረክ መሆኑንም ማወቅ ያስፈልጋል፤ለአዳም "ከሰማይ በታች ከምድር በላይ ያለውን ሁሉ ብላ ጠጣ ግዛ ንዳ" (ዘፍ 1÷29-31) ተብሎ መሰጠቱ ይታወቃል፤ይህም በረከት ነው፡፡
አዳም ያልታዘዘውን ዕፀ በለስ በልቶ ሲረገም ደግሞ የእርሱ የሆነው ሁሉ አብሮ ተረግሟል፤
ለዚህም "ካንተ የተነሣ ምድር የተረገመች ትሁን" (ዘፍ 3÷17) የሚለው ቃል ማረጋገጫችን ነው፡፡

ነቢዩ ኢሳይያስም፡-
"ምድርም አለቀሰች ረገፈችም ፤ዓለም ደከመች ረገፈችም፤የምድርም ሕዝብ ታላላቆች ደከሙ" በማለት በኢየሩሳሌም ምርኮ አንፃር የነበረውን የዓለምን ስቃይ አመልክቶናል (ኢሳ 24÷4)፡፡

ነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤልም፡-
"ወሶበ ዐለወ አቡነ አዳም ኮነ ፍናዊሁ ለዓለም መብእሰ ወጐጻጒጸ" "አዳም ትእዛዙን ባፈረሰ ጊዜ የዚህ ዓለም ጎዳናው ጒድጓድ ሆነ፤ጠባብ ያነሰ የከፋ መከራው የበዛ፤ ፃር ጋር የተመላ ሆነ" (ዕዝ.ሱቱ 5÷2)፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፡-
"ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ" (ሮሜ 5÷12)፡፡

ጌታችንም ለሐዋርያት ሲያስተምር፡-
"ርእዮ ለዓለም በማእሰረ ኃጢአት እንዘ ይትኀጐል፤ፈቂዶ ይፈውስ ትዝምደ ሰብእ…." "ዓለም በኃጢአት ማሰሪያ ተይዞ ሲጎዳ አይቶ የሰውን ባህርይ የሰውን ነገድ ይፈውስ ዘንድ …" ብሏል (ትምሕርተ ኅቡአት)፡፡

ስለዚህ ለአዳም የተሰጠ ዓለም በአዳም ምክንያት የተረገመ ሆኖ ነበር፤ ዓለማችን በአዳም ምክንያት መከራንና ሞትን ተቀብላ አስተናገደች፤ይህ መርገም ለዓለም አንዲወገድላት ሌላ ሁለተኛ አዳም ያስፈልግ ነበር፤ እሱም "የዓለም መድኃኒት" መሆን አለበት፤ሁለተኛው አዳም ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጣ፤ ዓለምን በደሙ ፈሳሽነት አጠባት፤ በሰው ውስጥ የሚገኙትን አራቱን ባህርያት አደሳቸው፤ ተረግማ የነበረችው ምድር በጌታ ደም ታጥባ ፋሲካን አደረገች ("ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተኀፂባ በደመ ክርስቶስ" እንዲል ቅ.ያሬድ)፤ ክርስቶስ መርገማችንን ቀበረልን፤ ልጅነታችንን መለሰልን!!!

ዛሬ በዚህ ደም ታጥበን ነጽተን መንግሥቱን እንጠባበቃለን

ፍቅሩንና መከራውን እያሰብን
ቁስሉንና ሞቱን እያስታወስን እንማፀናለን

ለዓለም ቤዛነት መስቀል ላይ የተፈተተው ጌታ ዛሬም እንደማይተወን እናምናለን

ስለዚህም እንዲህ እያልን እንለምነዋለን፦

መድኃኔ ዓለም ሆይ!
• 6,666 ጊዜ ስለተገረፈው ጀርባህ
• ስለተቸነከሩት እጆችህና እግሮችህ
• ስለተወጋው ጎንህ
• ስለ ቅዱስ ሥጋህና ስለ ክቡር ደምህ
• በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ስለወለደችህ ስለ እናትህ ስለ ማርያም ብለህ
ይቅር በለን!!!

አሜን!!!
+ እንኳን አደረሳችሁ [መጋቢት ፳፱/29]

በቅድስት ቤተክርስቲያን አስተምህሮ መሰረት ታላቂቱ ቀን በመባል ትታወቃለች።

ይህችን ዕለት ታላቅ ያሰኟት ምክንያቶች:-
1. አስቀድሞ ዓለም የተፈጠረችበት (መዝ ፻፩:፳፭)
2. መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ያበሠረባት፣ (ሉቃ ፩:፴፩)
3. ክብር ይግባትና እመቤታችን ድንግል ማርያም መድኅን ክርስቶስን የፀነሰችበት፣ (ሉቃ ፩:፴፩ ማቴ ፩:፳፫)
4. በዕለተ ዓርብ በዕፀ መስቀል ነፍሱን በፈቃዱ ስለእኛ አሳልፎ ከሰጠ በኋላ በዕለተ እሑድ ከሙታን ተለይቶ የተነሣባት (መዝ ፻፲፯:፳፬፣ መዝ ፸፯:፷፭-፷፮፣ ዮሐ ፲፱:፩፣ ፩ኛ ቆሮ ፲፭:፳)
5. ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ የሚመጣባት ቅድስት ዕለት ናት። (ራእ ፳፪:፲፪ ፣ መዝ ፵፱:፪ ፣ ማቴ ፳፬:፵፬)
#ሰሙነ ሕማማት

ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ሰሙነ ሕማማት የጾመ ሁዳዴ የመጨረሻው ሳምንት፤ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም የሚታሰብበት፤ ካህናትና ምእመናን በአጸደ ቤተክርስቲያን ተሰብስበው የሕማሙን ነገር የሚያወሳውን ዜማ የሚያዜሙበት፤ ግብረ ሕማም በመባል የሚታወቀውን መጽፍ የሚያነቡበትና የሚሰሙበት፤ በነግህ፣ በሠልስት፣ በስድስት፣ በተሰዓት /ዘጠኝ /ሰዓት፣ በሰርክ /በዐስራ አንድ/ ሰዓት እየመላለሱ የሚሰግዱበትና የሚጸለዩበት ልዩ ሳምንት ነው ከሆሳዕና ማግስት እስከ ትንሳኤ።

በዚህ ሳምንት በተለይ ካህናት ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ ምክንያቱም ጌታችን የደረሰበትን መከራና ስቃይ እንዲሁም የሰው ልጅ ፭ ሺ ፭ መቶ ዘመን በጨለማ ግዞት ይኖር እንደነበር ለማዘከርም ጭምር ነው።
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መከራና ሕማም በጽኑ እንድናስበው ያስተማሩን ሐዋርያት ናቸው። ለእነርሱም የነገራቸው ደግሞ ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
ሰሙነ ሕማማት የጌታችንን ሕማማት ከማሰብ ጋር በየዕለቱ በርካታ ድርጊቶች መፈጸማቸውን የምናስታውስበት ሳምንት ነው፦

📖ሰኞ

መርገመ በለስ የተፈጸመበት ሰኞ ይባላል፦
በዚህ ዕለት ጌታችን ከቢታኒያ ሲወጣ ተራበ ቅጠል ያለባትን በለስ ተመልክቶ ወደ በለሲቱ ቢቀርብ ከቅጠል በቀር ምንም ነገር ባለማግኘቱ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ምንም ካንቺ ፍሬ አይበላ” ማር ፲፩፥፲፬ በማለት ስለረገማት መርገመ በለስ የተፈጸመበት ሰኞ ይባላል።

አንጽሖተ ቤተመቅደስ ይባላል፡-
ጌታ ወደ ቤተመቅደስ ሄዶ በቤተመቅደሱ የሚሸጡትን እና የሚለውጡትን “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች” ማቴ ፳፩፥፲፫ በማለት ከቤተመቅደስ ገርፎ አስወጥቷቸዋልና።

📖ማክሰኞ

የጥያቄ ቀን ይባላል፦
ሰኞ ዕለት በቤተመቅደስ ሲሸጡ እና ሲለውጡ የነበሩትን ሁሉ እየገረፈ በማባረሩ ምክንያት ለሰው ልጅ ሹመትንና ስልጣንን የሰጠ ጌታ “በምን ስልጣን ይህንን ታደርጋለህ?” ማቴ ፳፩፥ ፳፫ ተብሎ በፈሪሳውያን ተጠይቋልና የጥያቄ ቀን ይባላል።

የትምህርት ቀን ይባላል፡-
በዚህ ዕለት በቤተመቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረም የትምህርት ቀን ይባላል። ሉቃ ፳፩ ፥፳፰ ፣ ማር ፲፪፥፪።

📖ረቡዕ

ምክረ አይሁድ ይባላል፦
ረቡዕ እለት የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የመከሩበትና ውሳኔ ያሳለፉበት ቀን በመሆኑ ምክረ አይሁድ ይባላል። ወቅቱ የፋሲካን በዓል የሚያከብሩበት ቀን በመሆኑ እና ብዙ ህዝብም ጌታን ይከተለው ስለነበር ሁከት እንዳይነሳ ስጋት ነበራቸው ። ነገር ግን ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ስለነገራቸው ሉቃ ፳፪፥፩-፮ ጭንቀታቸው ተወግዶ በጌታ መያዝ ተስማምተዋል።

የመልካም መዓዛ ቀንም ይባላል፡-
ጌታችን በዚህ ዕለት በለምጻሙ በሰምዖን ቤት ተቀምጦ ሳለ መላ ሕይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት/ባለሽቶዋ ማርያም/ ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ የአልባጥሮስ ሽቱ አምጥታ በራሱ ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባቸው ማቴ ፳፮፥፮-፯ የመዓዛ ቀን ይባላል።

የእንባ ቀን ይባላል፡-
ባለሽቱዋ ሴት (ማርያም እንተ እፍረት) ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት እየለመነች በእግሩ ስር ተደፍታ በእንባዋ እግሩን አርሳለችና ማር ፲፬፥፱ የእንባ ቀን ይባላል።

📖ሐሙስ

ጸሎተ ሐሙስ ይባላል፦
ጌታችን ለአይሁድ ተላልፎ ከመሰጠቱ በፊት በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ሲጸልይ በማደሩ ማቴ ፳፮፥፴፮ ጸሎተ ሐሙስ ይባላል።ጌታችን የደቀመዛሙርቱን እግር በፍጹም ትህትና ዝቅ ብሎ ያጠበበት ዕለት በመሆኑም ዮሐ ፲፫፥፫-፲፩ ሕጽበተ ሐሙስ ይባላል።

የምስጢር ቀን ይባላል፡-
ከሰባቱ ምስጢራት አንዱ የቅዱስ ቁርባን ምስጢር ማቴ፳፮፥፳፮-፳፱ በዚህ ዕለት ተፈጽሟልና የምስጢር ቀን ይባላል።

የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል፡-
መሥዋዕተ ኦሪት /በእንስሳት ደም የሚቀርብ መሥዋዕት/ቀርቶ ለአለም ድህነት ራሱን ያቀረበበት ቀን በመሆኑ ሉቃ ፳፪፥፳ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል።

የነጻነት ሐሙስ ይባላል፡-
ለኃጢአትና ለዲያቢሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱን እንዲሁም የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነም ዮሐ ፲፭፥ ፲፭ የነጻነት ሐሙስ ይባላል።

📖ዓርብ

የስቅለት ዓርብ ይባላል፦
ጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ የዋለበት ዕለት ነውና ማቴ ፳፯፥፴፭ የስቅለት ዓርብ ይባላል።

መልካሙ ዓርብ ይባላል፡-
ከጌታ ስቅለት በፊት በተለይም በሮማውያን ህግ የወንጀለኛ መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል ጌታችን በደሙ ቀድሶ የምህረት፣ የሕይወት አርማ፣ የዲያቢሎስ ድል መንሻ ስላደረገው፤ በሞቱ መልካሙን ሕይወት ስላገኘን መልካሙ ዓርብ ይባላል።

📖ቅዳሜ

ቀዳም ስዑር ትባላለች ፦
ይህች እለት ከድሮ በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል የተሻረች ቅዳሜ ይባላል።
ለምለም ቅዳሜ ይባላል፡-
ካህናቱ ለምእመናን ለምለም ቀጤማ የሚያድሉበት ዕለት በመሆኑም ለምለም ቅዳሜ ይባላል። ምዕመናንም ይህንን ለምለም ቀጤማ እስከ ትንሣኤ ለሊት በራሳቸው ላይ ያስሩታል።

ቅዱስ ቅዳሜ ይባላል፡-
ቅዱስ የሆነው እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ያረፈበት ቀን ሲሆን በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ስራውን ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ በነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዶ ሲኦልን በርብሮ ባዶዋን ሲያስቀራት በዚያ የነበሩትን ነፍሳት የዘላለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ቅዱስ ቅዳሜ ይባላል