አትሮኖስ
280K subscribers
111 photos
3 videos
41 files
473 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#የቤተሰባችን_ፎቶ


#በሕይወት_እምሻው


አቤት የቤተሰብ ፎቶዋችን ማማሩ የጥርሳችን ንጣቱ የሣቃችን ድምቀቱ!

አባዬ እበርበት ይመስል እኔን ጥብቅ አድርጎ አቅፏል፡፡ እማዬ ይበርባት ይመስል ናሆምን ጥብቅ አድርጋ አቅፋለች፡፡ እኔና ናሆም ያለን ጥርስ ሁሉ እስኪታይ ሥቀን ከእናትና አባታችን ሥር
እንደጉልቻ ቁጭ ቁጭ ብለናል፡፡

የሚያስቀና አራት ጉልቻ፡፡ ዕዩት የእማዬን ሣቅ!

አባዬ ሚስቱን ከሚደብደብበት ቀናት በአንድ ቦክስ ሲነርታት ያወለቀው ጥርሷ የት እንደገባ እንጃ፡፡ የሚታየው እህል ነክተው የማያውቁ የሚመስሉት ነጫጭ ጥርሶቿ ብቻ ነው፡፡ ለወትሮው
ዐይኖችዋን እንደ አጥር የሚከበው ደማቅ ጥቁር ብልዝ፤ ፎቶው ላይ የለም፡፡

አባዬ ፣

“ደሞ ምን ለመሆን ነው ልጅ ከወለዱ እንዲህ ዓይነት ልብስ መልበሱ” እያለ ስለሚቆጣት፣ ብዙ ጊዜ የማትለብሰውን ፡ እጅጌው ጥሩምባ አበባን የሚመስል መዐት አበቦች የፈሰሱበት ቀሚስ ለብሳለች፡፡ ቀለሙ ዐይን የሚያደነቁር ቀይ ነው:: ከእድሜዋ ፈጥኖ
ለእርጅናና ማዲያት እጅ የሰጠው ፊትዋ በእጅ ሥራ ቆንጅቷል።

እማ ፍክት ብላለች፡፡ አበባ ነገር ሆናለች፡

አባዬን እዩትማ! ከእማዬ ጥርስ ድምቀት ጋር የሚፎካከር የወርቅ ቀለበቱ ብልጭታ፣ እጁ ላይ ትንሽ ፀሐይ ያለ አስመስሎታል። ይሄ አብረቅራቂ የጋብቻ ቀለበቱ ከማያልቀው ጭቅጨቃቸው ባንዱ ቀን፣እንዲያውም ያውልሽ! ካንቺ ጋር ያለኝ ትዳር በዚህ አብቅቷል”
ብሎ የሽንት ቤት ጉድጓድ የወረወረው ነው፡፡ እማዬ በምልጃና በልመና ጎትታ አወጣችው እንጂ!

የለበሰው ደማቅ ሮዝ ሸሚዝ፣ ከጥቁር በሮዝ መስመር መስመር
ከረቫቱ ጋር ፍጹም ተቀናጅቷል፡፡ ይሄን ከረቫት፣ ካንቺ የማያልቅ ጭቅጭቅ ለመገላገል በእዚህ ተንጠልጥዬ በሞትኩ!” እያለ እማዬን
የሚያስፈራራበትና አብዝቶ የሚለብሰው ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማታ ማታ፣ ያውም በተመሳሳይ ሰዐት ፤ ትልቅ
ስልኩን ይዞ እየተንሾካሾከ ወደ ሽንትቤት ሲሮጥ ሲሮጥ ብቻ የማውቀው ሣቁ ያምራል፡፡

ናሆምዬ፣

ቀኝ እጁ ፎቶው ከመነሳቱ ሰከንዶች በፊት የተቀማውን “ሎሊፖፕ”
ሰመያዝ እንደተስተካከለ ተንከርፍፎ ቀርቷል፡፡ የአባዬን ስልክ ነካክቶ
ለእማዬ መስጠት ከጀመረ ወዲህ፣ አባዬ ሊደልለው በየቀኑ የሚገዛለትን ሎሊፖፕ
ነበር የያዘው - እማዬ ፎቶ ውስጥ አይገባም ብላ እስክትነጥቀው

ክንፍ እስከሚያካክሉት ትልልቅ ጆሮዎቹ በተዘረጋው ሰፊ ፈገግታው መሀል በቀርብ የወለቀው ጥርሱ ትቶት የሄደው ክፍተት ይታየኛል፡፡ የእማዬን ወላቃ ጥርስ በጥበቡ የደፈነው ፎቶ አንሺያችን የናሆምን መርጦ መተዉ ገረመኝ፡፡

“ይሄን ሳተላይት ጆሮ የወረስከው ከአባትህ ነው... እሱን ጠይቀው
ትለዋለች እማዬ ፤ ትምህርት ቤት በጆሮዬ ትልቅነት ሳቁብኝ ብሎ እያለቀሰ ሲነግራት፡፡ ያለችውን አምኖ አባዬን ሲጠይቅ፣ የናሆም ጆሮ የዘር ግንድ፣ አዲስ የጭቅጭቅ ማገዶ ይሆናል፡፡ እነሱ
በጩኸት ሲጨቃጨቁ የሳሎኑን ጥግ ይዞ ሲያለቅስ የማየው ልብ ሰባሪ ፊቱ እዚህ የለም፡፡

እኔ፣

አርቴፊሻል ፈገግታዬ ለፊቴ እንግዳ የሆነበት አይመስልም፡፡ ጥርሴ
እንኳን፣ ከዓመት ጀምሮ ከትምህርት ቤታችን ሦስት አጥር ዘልሎ
ካለው መርኬ ጫት ቤት እየሄድኩ፤ ከብዙ ጎረምሶች ጋር ታጅዬ ጫት ሳሻምድና ሺሻ ሳጨስ እንደምውል አያሳብቅም፡፡

አገጬን ሊነካ ምንም ያልቀረው ቢትልስ ሹራቤ ትላንት መርኬ ጓዳ፣ ጥግ ካለው ፍራሽ ላይ፣ የሰሞኑ ጓደኛዬ መሳይ በአንገቱ ላይ የሰራውን የገድል ማስታወሻ ሸፍኖታል፡፡

አቀማመጤ እንደጨዋ ልጃገረድ ሰብሰብ፣ ቆጠብ ! ከረጅም ቀሚሴ ጋር የሚሄድ ነው፡፡ አባዬ፣ ድሮ ሁሉ ነገር እነግረው በነበረ ጊዜ ያቅፈኝ እንደነበረው ስላቀፈኝ፤ ከአስተቃቀፉ ጋር የድሮን
ንጽሕናዬን ለማምጣት ባደረግኩት ከፍተኛ ጥረት ያመጣሁት
አቀማመጥ አይመስልም፡፡

ያቀፈኝ እጁን አያያዜ፣ ጥብቅ ያለና አትልቀቀኝ የሚል ይመስላል፡፡
“አባዬ መልሰኝ... አባዬ ልጠፋ ነው መልሰኝ” የሚል፡፡ ከቤታችን
ሰላም ጋር አብሮ የጠፋው ጨዋነቴን በአባቴ እቅፍ ውስጥ እፈልግ
ይመስል የምለምነው ይመስላል፡፡

...አቤት የቤተሰብ ፎቶዋችን ማማሩ! የጥርሳችን ንጣቱ! የሣቃችን ድምቀቱ!
.
የምፈልገው ቤተሰብ ፎቶዋችን ላይ ያለውን ነው፡፡

የምመኘው ቤተሰብ ፎቶዋችን ላይ ያለውን ነው፡፡

አሁን አሁን የምጸልየው፤ ፎቶው ላይ እንዳለው ያለ ቤተሰብ
እንዲሰጠኝ ብቻ ነው፡፡

💫አለቀ💫

ለአስተያየቶ @atronosebot ን ይጠቀሙ መልካም ቀን። 🙏
🥰1