አትሮኖስ
279K subscribers
110 photos
3 videos
41 files
459 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#ሁቱትሲ


#ምዕራፍ_አስር


#የወጣቷ_ልብ_አንጠልጣይ_ትውስታዎች

#ትርጉም_በመዝምር_ግርማ


#በልሳን_ሲያናግረኝ


በመታጠቢያ ቤቱ ሰባት ሳምንታት መቆየታችን ሁላችንንም በሚያስደነግጥ ሁኔታ አክስቶናል — አጥንቶቻችን ገጠው ወጥተዋል፤ ቆዳችንም አሸበሸበ፡፡ በሰውነታችን ውስጥ የነበረው ስብና ጡንቻዎቻችን ጠፍተው፣ መቀመጫችንም አጥንቱ ብቻ ስለቀረ በጠጣሩ ወለል ላይ መቀመጡ አልስማማ ይለን ጀመር፡፡ ሁለት ሴቶች ቢጨመሩብንም መታጠቢያ ቤቱ ግን ከቀን ወደ ቀን እየሰፋ ሄደ፡፡ መነመንን፤ ተቆጥቦ የሚሰጠን ምግብም ብዙውን ጊዜ ያደካክመንና ራሳችንንም ያዞረን ገባ፡፡ በልብሶቼ መስፋት ቢያንስ 17 ኪሎግራም እንደቀነስኩ መናገር እችላለሁ (መጀመሪያ ላይ ወደ
50 ኪሎግራም እመዝን ነበር)፡፡
ቆዳችን ቀልቶ፣ ከንፈሮቻችን ተሰነጣጥቀው፣ ድዶቻችንም አባብጠውና ቆሳስለው እጅግ ተጎድተናል፡፡ በዚያ ላይ ከደረስንበት ጊዜ ጀምሮ ታጥበንም ሆነ ልብስ ቀይረን ስለማናውቅ በአሰቃቂ የተባይ ወረራ ተቸገርን፡፡ አንዳንዴ ትናንሾቹ ተባዮች ደማችንን መጠው ስለሚያብጡ በፊታችን ላይ ሲንፈላሰሱ እናያቸዋለን፡፡ ሲያዩን የምናማልል ላንሆን እንችላለን፡፡ ግን ከዚያ በላይ ቆንጆነት ተሰምቶኝ አያውቅም፡፡ በየቀኑ እነሳና እግዚአብሔርን ሕይወትን ስለሰጠኝ አመሰግነዋለሁ፡፡ አምላኬም በየጠዋቱ እንደምወደድና የብርቅዮ እንደምያዝ እንዲሰማኝ አደረገኝ፡፡ ይህን ያህል ጊዜ በሕይወት ያቆየኝና በብዙ ሥቃይ ውስጥ ያሳለፈኝ በደም በሰከረ ገዳይ ገጀራ እንድገደል እንዳልሆነ አውቃለሁ! በአንድ የማይረባ የዕለት ህመም እንድሞት እንደማያደርገኝም ይታወቀኛል፡፡ በመታጠቢያ ቤቱ ለሁለት ጊዜ ያክል በተወሰኑ ክኒኖች በአንድ ቀን ልቆጣጠራቸው በምችላቸው ህመሞች ተይዤ ነበር … ኪኒን ቢኖረን ኖሮ፡፡ የመጀመሪያው ህመሜ በመንዘፍዘፍና በራስ ምታት ባሰቃየኝ በ40.5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀት ታጅቦ ነበር የመጣው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አሳልፌ ከማውቃቸው በጣም አሰቃቂ ክስተቶች አንዱ የሆነው አስከፊ የሽንት ቧንቧ መመረዝ ነበር፡፡ ቄሱ ሊያቀርቡልኝ የቻሉት ብቸኛው ነገር የሙቀት መለኪያ መሣሪያና መልካም ምኞታቸውን ነበር - የቀረ ምንም መድኃኒት አልነበራቸውም፡፡
ማድረግ የምችለው ብቸኛው ነገር መጸለይ በመሆኑ ያንን ብቻ ነበር ያደረግሁት፡፡ ሕመሙና ትኩሳቱ ከምችለው በላይ ሲሆንብኝ አምላክ እንደተኛሁ ፈዋሽ እጆቹን እንዲያሣርፍብኝ ጠየቅሁት፡፡ በሁለቱም ጊዜያት ያለምንም ትኩሳትና ህመም
ተነቃቅቼና ደኅና ሆኜ ተነሣሁ፡፡ በፍቅሩ ኃይል ተፈወስኩ፡፡
ምንም ዓይነት ህመም ሕይወቴን እንደማይነጥቀኝ ተማምኛለሁ፡፡ አምላክ ለእኔ አንድ ታላቅ ዓላማ እንደነበረው እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ እናም በየቀኑ ያንን ይገልጽልኝ ዘንድ እጠይቀዋለሁ፡፡ መጀመሪያ ላይማ ሁሉንም የወደፊት ሕይወቴን ባንዴ እንዲያሳየኝ እጠብቃለሁ፡፡ ምናልባት ለጥሩ ዓላማ እንደተሰነዘሩ ሁሉ፤ ልክ እንደ መብረቅ ብልጭታና እንደ ድርቅርቅ ምች፡፡ ግን አምላክ ምንም ቢሆን አንድን ልንረዳው ያልተዘጋጀንለት ነገር እንድናይ እንደማያደርገን እየተማርኩ መጣሁ፡፡ ይልቁኑ ለማየት የሚያስፈልገንን ልናይ በሚገባን ጊዜ እንድናይ ያደርገናል፡፡ ዓይናችንና ልባችን ክፍት እስኪሆኑለትም ይጠብቃል፡፡ ዝግጁም ሲሆኑ እግሮቻችንን ለኛ አመቺ በሆነው መንገድ ላይ ያስቀምጣቸዋል…. መራመዱ ግን የኛ ድርሻ ይሆናል፡፡

ቄስ ሙሪንዚ አንድ ቀን ስለ ጦርነቱ ሲያወሩ ጌታ ትክክለኛውን ነገር አስመለከተኝ፡፡ የተመድ የሰላም አስከባሪ ወታደሮቹን ወደ ሩዋንዳ ሊልክ ስላቀደ ለጦርነቱ ፍጻሜ ያበጅለታል ብለው በማሰብ ቄሱ በጣም ተደሰቱ፡፡ የተመድ አሥር ቤልጅዬማውያን ሰላም አስከባሪዎች በዘር ፍጅቱ የመጀመሪያ ቀን በሁቱ ወታደሮች ከተገደሉበት በኋላ አብዛኞቹን ወታደሮቹን አስወጥቷል፡፡ በእርግጥ ሁሉም ምዕራባዊ ሀገር ቱትሲዎችን ዕጣ ፈንታቸውን ብቻቸውን ይጋፈጧት ዘንድ በመተው ዜጎቹን ከሀገሪቱ አስወጥቷል፡፡ የዘር ፍጅቱ ከጀመረ ወዲህ ምንም የውጪ ዜጎች አልነበሩም ማለት ይቻላል - ያም ለኛ መንግሥት የዘር ፍጅትም ቢያካሂድ ዓለም ግድ እንደማይሰጠውና የቱትሲዎች ሕይወት ዋጋ እንደሌለው መልዕክት አስተላልፎለታል፡፡ ስለሆነም ግድያው ቀጠለ፡፡
የተመድ አዲስ ጦር መላኩ ትልቅ ነገር ነው… የዘር ፍጅቱን ሳይቀር ሊያስቆመው ይችላል! ቄሱ ግን ችግር እንዳለ ይናገራሉ፡፡ ‹‹በሩአግ ውስጥ ያሉት ቱትሲዎች የተመድ ወታደሮቹን እንዲልክ አይፈልጉም፡፡ ምክንያቱም ጦርነቱ እንዲቀጥል ስለሚፈልጉ ነው፡፡ ጦርነቱን እንደሚያሸንፉና ሥልጣን እንደሚይዙ ያስባሉ!›› ሲሉ ጮሁብን፡፡ ‹‹ወግ ወጉ ተይዞልኛል፡፡ የተመድ ወታደሮችን ከላከ እንግሊዝኛ ተናጋሪ መሆን እንዳለባቸው እየጠየቁ ነው … ይህን ያህል ድፍረት!››
ቄሱ አብዛኞቹ የሩአግ ወታደሮች በብሪታንያ ቅኝ በተገዛችው በዩጋንዳ ያደጉ ስለሆኑ እንግሊዝኛ እንደሚናገሩ ነገሩን፡፡ ይህም ፈረንሳይኛ በሚነገርባት በቤልጅዬም ከተገዛችው ከሩዋንዳ ጋር ይቃረናል፡፡ አብዛኞቻችን በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ፈረንሳይኛን እንደ ሁለተኛ ቋንቋችን ተምረናል፡፡
‹‹የራሱ ወታደሮች ፈረንሳይኛ ቢችሉም እንኳን ሩአግ አንናገርም ብሎ ይቃወማል›› ቄስ ሙሪንዚ ጨመሩልን፡፡ ‹‹የፈረንሳይ ጦር ሠራዊት የኢንተርሃምዌን ገዳዮች አሰልጥኗል ብለው ይወነጅላሉ፡፡ ፈረንሳውያንን ይጠሏቸዋል… ሩአግ ጦርነቱን የሚያሸንፍ ከሆነ ሁላችንንም እንግሊዝኛ እንድንናገር ያደርጉናል!›› አምላክ በአእምሮዬ አንዳች ብርሃን አበራልኝ፡፡
ሁሉም ነገር የሆነው በቅጽበት ነው፡፡ በዚያን አፍታ ሩአግ ጦርነቱን እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ ሆንኩ፡፡ ይህም ማለት እኔ እንግሊዝኛ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎችን ከዘር ፍጅቱ በኋላ አገኝና የደረሰብንን ሁሉ የተከሰተውን እነግራቸዋለሁ ማለት ነው፡፡ ሀሉም ሰው እንግሊዝኛ ብቻ በሚናገርበት በተመድ ውስጥ እንደምሠራም ራእይ ታየኝ፡፡ ድንገት በመታጠቢያ ቤቱ ውስጥ ያለውን ቀሪውን ጊዜዬን እንግሊዝኛ ቋንቋን ስናገር አንደማሳልፍ በግልጽ ታወቀኝ፡፡ አምላክ የአንድን ትልቅ ሕጋዊ ቁማር አሸናፊ ቁጥሮች እንደሰጠኝ ተሰማኝ… ማድረግ የነበረብኝ ብቸኛው ነገር ቢኖር ዕጣው ሲወጣ ዝግጁ መሆኔን ማረጋገጥ ይሆናል፡፡ ዕጣ ፈንታዬን ለመጋፈጥ መዘጋጀት ነበረብኝ!
ፍጹም እንግዳ የሆነን ቋንቋ መማር የብዙ ሰዓታት ጥናት እንደሚጠይቅ አውቃለሁ፤ ይህም ጸሎቴን እንድቀንስ ያስገድደኛል፡፡ ይህም መሆኑ ለዲያብሎስ የሚጠብቀውን ዕድል ይሰጠዋል ብዬ ሠጋሁ፡፡ ወደ አእምሮዬ ተመልሶ ዘሎ ገብቶ በፍርሃትና በጥርጣሬ ሞልቶኝ ወደ ጨለማና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ይከተኛል፡፡ ማድረግ የምችለውን ብቸኛውን ነገር አደረግሁ፡፡ አምላክን ምን እንደማደርግ ጠየኩት፡፡ ውድ እግዚአብሔር - ይህን እንግሊዝኛ ተማሪ የሚለውን ሐሳብ አንተ ወደ ራሴ ከተኸዋል፤ ስለዚህ በማጠናበት ጊዜ ዲያብሎስን አርቅልኝ! እባክህ እዚህ መታጠቢያ ቤት ውስጥ ተቀርቅሬ አዲስ ቋንቋ እንዴት አንደምማር አሳየኝ፡፡ ለሌሎቹ ሴቶች ስለ ዕቅዴ ለመንገር ግድም አልሰጠኝ - በዚያ በምጸልይበት መንገድ ስጸልይ ሲያዩ ነገሩን ቀለል አድርጌ እንዳየሁት አስበዋል፡፡ ሕይወታችንን ለማትረፍ ስንጣጣር የውጪ ቋንቋ ለመቻል እንደፈለግሁ ብነግራቸው ቄሱን ለአንድ አባሺ ጎሳ አባል ወዲያውኑ አሳልፈው እንዲሰጡኝ ሊጠይቋቸው ይችላሉ፡፡ ስለሆነም ህልሞቼን ለራሴ ይዤ ቆየሁ፡፡
👍1