አትሮኖስ
279K subscribers
110 photos
3 videos
41 files
459 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#ሁቱትሲ


#ምዕራፍ_ስድስት


#የወጣቷ_ልብ_አንጠልጣይ_ትውስታዎች

#ትርጉም_በመዝምር_ግርማ


#መመለስ_አይታሰብም

እናቴ፣ አባቴ፣ ዳማሲን፣ ቪያኒ፣ ኦገስቲንና እኔ ቀኑን ሙሉ በግቢያችን ውስጥ በፍርሃት ተቆራምደን ሬድዮ ስናዳምጥ ዋልን፡፡ ከሀገራችን ውጪ የሚተላለፉት ዘገባዎች ተራ ሁቱ ዜጎች የመንግሥቱን ሰራዊትና የኢንተርሃምዌ ታጣቂዎችን ያልታጠቁ ንጹሃን ቱትሲዎችን በመግደሉ ተግባር ላይ እየተቀላቀሏቸው እንደሚገኙ ዘገቡ፡፡ የሀገር ውስጥ ጣቢያዎች በበኩላቸው ሁቱዎች ገጀራ እያነሱ ቱትሲ ጎረቤቶቻቸውን እንዲያጠቁ ያበረታቱ ገቡ፡፡
እንደ ትንሽ ልጅ አደረገኝ - ወላጆቼ ምን እንደማደርግ እንዲመሩኝ ተመኘሁ፡፡ ከ1959 ጀምሮ ከፖለቲካ አለመረጋጋቶችና ከቱትሲ ጭፍጨፋዎች ስለተረፉ መቼም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ማወቃቸው አይቀርም ስል አሰብኩ፡፡ ብሔራዊው ሬድዮ ጣቢያ ሕዝቡ በየቤቱ እንዲቆይ አስጠነቀቀ፤ እኛም የወላጆቻቸውን ምክር እንደሚሰሙ ማለፊያ ልጆች ተቀበልነው፡፡ ከአጥራችን ውጪ ምን እየተከሰተ እንደነበር ለማወቅ በራችንን ለመክፈት እንኳን በጣም ፈራን፡፡ ከቅጥር-ግቢያችን ውጪ መንቀሳቀስ አደጋ ይኖረዋል ወይንም ሞት ያስከትላል ብለን እንደ እስረኛ እንቅስቃሴያችንን በቤት ውስጥ ገደብን፡፡
ስልክ አልነበረንም፤ ቢኖርም ኖሮ እንኳን አብዛኞቹ የሀገሪቱ የስልክ መስመሮች ዝግ ናቸው፡፡ ሬድዮናችን ከሚያደርሰን ወሬ በቀር ከማንም ጋር ግንኙነት የምናደርግበት መንገድ አልነበረም፡፡ ራሴን ልስት መሆኑ አስኪሰማኝ ድረስ ስለ አሰቃቂዎቹ ግድያዎች ስንሰማ ለሰዓታት ተቀመጥን፡፡ ጥላ በረድ ሲል መጻሕፍቴን ሳብ አድርጌ ለፈተናዎቼ መዘጋጀት ጀመርኩ፡፡
‹‹እንዴት ይሆንልሻል ኢማኪዩሌ?›› ሲል ዳማሲን ጠየቀኝ፡፡ ‹‹ለማጥናት የሚሆንሽን ጽናትስ ከየት አመጣሽው? ተመልሰሽ ትምህርት ቤት እንደምትገቢስ ለምን ታስቢያለሽ?››
ወንድሜ ከሰዓታት በፊት ተስፋ ስቆርጥ ሲያጽናናኝ እንዳልነበር አሁን ራሱም ተስፋ ቆረጠ፡፡ ለመበርታት ተራው የኔ ስለሆነ ‹‹መጨነቅህን ተው›› አልኩት፡፡ ‹‹ይህን እናልፈዋለን፤ ሁኔታዎች ከተባባሱ በድንበሩ በኩል እንሾልካለን፡፡ እማማና አባባ ካሁን በፊት ይህን ዓይነቱን ችግር አልፈውታል፡፡ እምነት ይኑርህ፡፡››
ስለ እውነት ለመናገር ግን እኔ ራሴ ያለኝ እምነት ተሟጧል - የማጠናው ከቤተሰቤ ጭንቀት ላይ ሐሳቤን ለማንሳት አስቤ እንጂ ለፈተና ለመዘጋጀት አልነበረም፡፡
በእለቱ የሰማነው ብቸኛው አበረታች ዜና መነሻቸውን በዩጋንዳ ያደረጉት የቱትሲ አማጽያኑን መሪ የሩአጉን የፖል ካጋሜን መልዕክት ነው፡፡ በቱትሲዎች ላይ የሚፈጸሙት ግድያዎች ካላቆሙ በስተቀረ እየተፋለሙ ሩዋንዳን ለመውረርና ቱትሲዎችን ለመታደግ እስከመጨረሻው እንደሚጸኑ ቃል ገቡ፡፡ ካጋሜ ያንን ሲሉ መስማቱ ያበረታታል፤ ሆኖም ግን ብቸኛው ‹‹መልካም›› ዜና የለየለት ጦርነት እንከፍታለን የሚል ማስፈራሪያ ብቻ በመሆኑ አዘንኩ፡፡ በዚያ ምሽት ማናችንም ከጥቂት ደቂቃዎች በላይ አልተኛንም፡፡ በሚቀጥለው ቀን በኪጋሊ ከሚኖሩት ከለዘብተኛ ሁቱዋ የሩዋንዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ከአጋቴ ጋር የተደረገ የቢቢሲን የስልክ ቃለ-መጠይቅ ሰማን፡፡ ምንም እንኳን የተ.መ.ድ ሰላም አስከባሪዎች እየጠበቋቸው ቢሆንም በቤታቸው ዙሪያ ሁሉ የጥይት እሩምታ ይሰማል፡፡ በዚህ ንግግራቸው ወቅት እርሳቸው፣ ባለቤታቸውና አምስት ልጆቻቸው ወለል ላይ መተኛታቸውንና የማምለጫ መንገድም እንደሌላቸው ገለጹ፡፡ ወዲውኑም ቃለ-መጠይቁ ሳያልቅ የስልክ መስመሩ ተቋረጠ፡፡ በኋላ እንደሰማነው ወታደሮች ወደ ቤታቸው ድንገት ገብተው እርሳቸውንና ባለቤታቸውን ገድለዋቸዋል፡፡ ትረፉ ሲላቸው ልጆቻቸው አልተገደሉም፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሯ ቃላት ስሜታችንን በእጅጉ ነኩት፤ በዚህ ወቅት ሁኔታዎች ይሻሻላሉ ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ገዳዮቹ ሁቱዋን ጠቅላይ ሚኒስትር ከገደሉ እኛንስ ከመግደል ምን ያቆማቸዋል?
በነዚያ 24 ሰዓታት የነበረው ረፍት-አልባ ውጥረት ቤተሰቤን ጎዳው፡፡ እናቴ በደመ-ነፍስ ከክፍል ክፍል እየተዘዋወረች የነበረንን ማንኛውንም ሻንጣ እጇ በገቡላት እቃዎች ትሞላለች፡፡ ‹‹በስንት ልፋት ያሟላኋቸውን እቃዎች ሰዎች እንዲዘርፏቸው ትቼ አልሄድም›› አለችን፡፡ ‹‹አርቄ እደብቃቸዋለሁ፡፡ እንድ ቀን ተመልሰን እናገኛቸዋለን፡፡››
ወዴት ለመሄድ እንዳቀደች አላወቅሁም፡፡ ብቸኛው ሊያስኬደን የሚችለው የማምለጫው መንገዳችን (የኪቩ ሐይቅን አቋርጦ) በኢንተርሃምዌ ታጣቂዎች እንደተዘጋ ሰምተናል፡፡ ወደ ሐይቁ የሚጠጋን ማናቸውንም ቱትሲም ሆነ ለዘብተኛ ሁቱ በመግደል ላይ ናቸው፡፡
አባቴ በግራ መጋባት ነባራዊውን ሁኔታ ሊያምን አልቻለም፡፡ ‹‹ግድያው ከቀጠለ ሩአግ ሊያቆመው ጣልቃ ይገባል፡፡ በጥቂት ቀናት ውስጥ እዚህ ይመጡና ያድኑናል›› ሲል ግምቱን ይነግረን ጀመር፡፡
ለማመን ተቸግሬ ‹‹አባባ ምን እያሰብክ ነው›› ስል ጠየኩት፡፡ ‹‹የሩአግ ወታደሮች ገና በስተሰሜን በዩጋንዳ ድንበር አቅራቢያ ናቸው፡፡ ተሽከርካሪ ስለሌላቸው በእግራቸው እየተጓዙ ጦሩንና ኢተርሃምዌን መዋጋት ግድ ይላቸዋል፡፡ እዚህ ለመድረስ ሳምንታት ይፈጅባቸዋል … ከነጭራሹ እዚህ መድረስ መቻላቸውንስ ማን ያውቃል!››
ከአባቴ ጋር የተከራከርኩባቸውን ውሱን ጊዜያት መጥቀስ እችላለሁ፤ ያለወትሮዬ መሟገቴ ሁሉም ነገር በመቀያየር ላይ በመሆኑ ነው፡፡ ወላጆቼ በትክክል እያሰቡ አይደለም፤ ኦገስቲንና ቪያኒም ልጆች ስለሆኑና ስለተደናገጡ ሊታመንባቸው አይችልም፡፡ በሕይወቴ ሙሉ የዳማሲንን መርህ እከተላለሁ፤ አሁን ግን ወደ ክፍሉ አፈግፍጎ ግድግዳ ላይ አፍጥጧል፡፡
ፈልጌው ወደ ክፍሉ እንደገባሁ ‹‹እስኪ እንዲያው የምታስቢውን ሳትደብቂ ንገሪኝ፤ ይችን ቀን የምናልፋት ይመስልሻል?›› ሲል ጠየቀኝ፡፡ ‹‹ይኸውልሽ በመጪው ዓመት የማደርገውን ነገር ተኝቼ ለማለም እየሞከርኩ ነው፤ ግን አልሆነልኝም፡፡ በሕይወት የምኖር አይመስለኝም፡፡ የወደፊት ሕይወት የለኝም፡፡››
‹‹ዳማሲን ከዚህ ነገር ውስጥ እንደምንም መውጣት አለብህ!›› ስል ጮህኩበት፡፡‹‹ትግሉን ገና ሳትጀምር ተስፋ መቁረጥ የለብህም!›› አንተ በመጭው ዓመት ምን እንደምትሠራ ማየት ካልቻልክ እኔ እችላለሁ! ከዩኒቨርሲቲ ስመረቅ ቡታሬ እኔ ጋ ትመጣለህ፡፡ ዲፕሎማዬን ስቀበል በፊት ወንበር ተቀምጠህ እያጨበጨብክ በደስታ ትጮሃለህ፡፡ ስለዚህ አሁን ተነሥና እነእማማን አግዛቸው!››
‹‹ምናለ ያንቺ እምነትና ጽናት ቢኖረኝ›› ብሎ ተነፈሰና መልሶ ግድግዳውን አተኩሮ ያይ ገባ፡፡
እኔ ብርታቱ ባይኖረኝም አንድ ሰው መልሶ ቤተሰቤን ማረጋጋት አለበት፡፡ ቤተሰቡ በለየለት ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንዳይገባ ለመበርታትና ቢያንስ ጠንክሬ ለመሥራት ሞከርኩ፡፡
ለጠቅላይ ሚኒስትሯ ጥበቃ ያደርጉ የነበሩ አሥር ቤልጅየማውያን የተመድ ሰላም አስካባሪዎች በመንግሥት ወታደሮች እንደተገደሉና በሩዋንዳ የሚኖሩ የቤልጅዬም ዜጎች ሁሉ ሕይወታቸው አደጋ ላይ እንደወደቀ ምሽት ላይ ሰማን፡፡ ቤልጅዬማውያኑና የሌሎች ሀገር ዜጎች አገሪቱን ለቀው ከወጡ ይህን የለየለትን ጭፍጨፋ ለማስቆም ዐቅሙ ያለው ሌላ ማንም ሊኖር እንደማይችል እናውቃለን፡፡ በዚህ ምሽትም ስላልተኛን ለተከታታይ ሁለት ቀናት ሁላችንም እንቅልፍ አጣን ማለት ነው፡፡

ንጋት ላይ ጩኸት ይሰማን ጀመር፡፡
👍1