አትሮኖስ
280K subscribers
109 photos
3 videos
41 files
459 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#ድንቡጮ_ለምን_ለምን_ሞተ?


#አንድ


#በአሌክስ_አብርሃም

ሰፈራችን ውስጥ መክብብ ግሮሰሪ የምትባል አለች። ማታ ማታ ፀሐይ ሲያዘቀዝቅ ትልልቅ ሰዎች በረንዳዋ ላይ ተሰባስበው እያወሩ ጅን የሚባል መጠጥ ድርፍጭ ባሉ ብርጭቆዎች የሚጠጡባት።በግሮሰሪዋ ሁሉም ዓይነት መጠጥ ቢኖርም በረንዳ ላይ የሚቀመጡት ሽማግሌና ጎልማሶች ግን ልክ ዕድሜ ይቀጥል ይመስል ጅን ብቻ ነበር የሚጠጡት። በሯ ላይ በግራ በኩል እንደ ኤሊ ፍርግርግ
ድንጋይ የለበሰ የሚመስል ግንድ ያለው የዘንባባ ዛፍ የግሮሰሪዋ ግርማ ሞገስ ነው። ይህች የዘንባባ ዛፍ ለጥምቀት ሰፈራችንን አቋርጠዉ የሚያልፉት ሁለት ታቦታት ከመለያየታቸው በፊት የሚቆሙባት የታቦት መቆሚያ ነበረች። ባለቤቱ አባባ መክብብ ይባላሉ።አጭር፣ ሙሉ ፀጉራቸውን ነጭ ሽበት
የወረሰው፣ ከባድ ሌንስ ያለው መነፅር የሚያደርጉ ሰውዬ ናቸው።

አባባ መክብብን ባየኋቸው ቁጥር የሚገርሙኝ ሁለት ነገሮች አሉ። የመጀመሪያው ግርምቴ አፋቸው
ውስጥ ምግብ ኖረም አልኖረም በባዶው ያላምጣሉ። አፋቸው አያርፍም፤ ዝም ብሎ ያላምጣል። በፊት በፊት ማስቲካ የሚያላምጡ ይመስለኝ ነበር። ታዲያ ትልልቅ ሰዎች ማስቲካ ብዙም ስለማያላምጡ አባባ መክብብ ዘመናዊ ሽማግሌ ይመስሉኝ ነበር። በኋላ ከፍ ስል ግን እንደው ልማድ ኾኖባቸው ነው…. ሲባል ሰማሁ። ሲያወሩ ሁሉ በየመሀሉ ባዶ አፋቸውን እንደሚያላምጥ ሰው እያንቀሳቀሱ አየር ያኝካሉ። ሁልጊዜ ሙልጭ ተደርጋ የምትላጭ ትንሽ አገጫቸው ላይና ታች ከፍ ዝቅ ስትል ነው
የምትውለው። ታዲያ አንዳንዴ ሊልኩኝ ፈልገው ወይም ለሆነ ጉዳይ በባዶው በሚያኝኩት አፋቸው “አብራም” ሲሉኝ ስሜን አላምጠው የተፉት ይመስለኛል። በዛ እድሜዬ የሚመስለኝ ነገር ይበዛ ነበር።

ሁለተኛው ከአባባ መክብብ የሚገርመኝ ሱሪያቸው ነው። ሱሪያቸው ከታች እስከላይ ይገርመኛል።ከግርጌው እንደዣንጥላ ጨርቅ ወደ አንድ በኩል ተጠምዝዞ ይጠቀለልና ካልሲያቸው ውስጥ ይጠቀጠቃል። በእርግጥ የእኔም አባት እንደዛ ያደርጋል። ግን አባባ እንደዛ የሚያደርገው ዝናብ ጥሎ
መሬቱ ሲጨቀይ ብቻ ነው። አባባ መክብብ ግን ሁልጊዜም ነው የሚያጭቁት። ከላይ ደግሞ ጥቁር የቆዳ ቀበቷቸው ወገባቸው ላይ ሳይሆን ከእንብርታቸው ከፍ ብሎ ከልባቸው ሥር ... እዛ ላይ ነው ቅብትር ተደርጎ የሚታሰረው። ከነተረቱ ሰፈራችን ውስጥ የሆነ ሰው ሱሪውን ከፍ አድርጎ ከታጠቀ
“ምነው እንደአባባ መክብብ ሱሪህን ደረትህ ላይ ሰቀልከው ?” ይባላል።

ሌላም የረሳሁት ሦስተኛ አስገራሚ ነገር አለ። አባባ መክብብ ደንበኞቻቸውን እያስተናገዱ (ሁሉም ደንበኞቻቸው በርሳቸው ዕድሜ ስለሆኑ ከደንበኛ ይልቅ ጓደኞቻቸው ይመስሉኛል) ከመኪና ላይ ቢራ እያስወረዱ ወይም ግሮሰሪው በር ላይ በጉርድ የብረት በርሚል የተሞላ ፉርሽካ ተዘርግፎላቸው የሚበሉትን ሦስት ሙክት በጎቻቸውን እየተመለከቱ የሚሠሯት አንዲት ነገር አለች፤ ከእጃቸው በማትለየውና የቀንድ እጀታ ባላት የጢም መላጫቸው በደረቁ ጉንጫቸውን፣ አገጫቸውንና የአገጫቸውን ሥር ይፈገፍጋሉ ሁልጊዜ። እንደውም ሰው ሰላም ሲሉ የጢም መላጫቸውን በቀኝ እጃቸው ስለሚይዙ ለመጨበጥ አይመቻቸውም። እናም እንደጨበጧት አይበሉባቸውን
አዙረው ሰላም ወደሚሉት ሰው እጅ ይዘረጉና ነካ አድርገውት እጃቸውን ይመልሳሉ። ታዲያ የጢም መላጫቸውን የበረንዳዋ መከለያ ብረት ላይ ኳ ኳ አድርገው ያራግፏታል ! ድምፁ እስካሁን ጆሮዬ ላይ አለ።

አባባ መክብብ በመንደሩ ሰው በሙሉ “ደግ ሰው ናቸው…” ነው የሚባሉት። ግሮሰሪው በር ላይ
ለበጎቻቸው ፉርሽካ ከሚቀመጥበት ጎራዳ በርሚል ራቅ ብሎ ሰማያዊ የፕላስቲክ በርሚል በውኃ ተሞልቶ ይቀመጣል። በርሚሉ ጋር በረዶ በመሰለች የኤሌክትሪክ ገመድ ጫፏ ተበስቶ የታሰረ ቢጫ
የቲማቲም ሥዕል ያለባት የመርቲ ጣሳ አለች ... በርሚሉና ጣሳው ከድሮ ጀምሮ ስለማይነጣጠሉ
በኤሌክትሪክ ገመድ እትብት የተያያዙ እናትና ልጅ ይመስሉ ነበር። እንግዲህ አላፊ አግዳሚ የኔ ቢጤ ውኃ ከጠማው ከዛ በርሚል በጣሳዋ እየጠለቀ ይጠጣል። ትንሽ ልጆች እንደነበርን ውኃው የተለየ
ነገር ስለሚመስለን እኛም እየተደበቅን እንጠጣ ነበር። በኋላ ግን ወላጆቻችን “ማንም በሚጠጣበት እየጠጡ ኮሌራ ሊያመጡብን…” እያሉ ሲቆጡን አቆምን !

ምንጊዜም የቡሄ በዓል ሲሆን የሰፈር ልጆች ተሰባስበን አንደኛ የምንሄደው አባባ መክብብ ግሮሰሪ ነበር። ፈንታው ድንቡጮ የሚባል ጓደኛችን አውራጅ ይሆናል። አባባ መክብብ ፈንታውን በጣም ነው የሚወዱት። ጉንጩ ድንቡጭ ያለ ስለሆነ ነው መሰል 'ድንቡጮ' እያሉ ነው የሚጠሩት። በዚሁ ሰበብ ጓደኛችን ፈንታው ፈንታው ድንቡጮ ተብሎ ቀረ። ግሮሰሪዋ በር የዘንባባውን ግንድ ተገን አድርጎ
የተቀመጠ ትልቅ ድንጋይ ላይ ካርቶን ጣል አድርጎ እንደ ወንበር በመጠቀም ሊስትሮ ይሠራል።
ጫማውን የሚያስጠርገው ደንበኛ ድንጋዩ ላይ ተቀምጦ የዘንባባውን ግንድ ደገፍ ይልና ከድንጋዩ ሥር
ብሩሹን ይዞ ለሚጠብቀው ፈንታው እግሩን ያቀብለዋል። ታዲያ ያች ድንጋይ የፈንታው ድንቡጮ ድንጋይ' ነው የምትባለው። የእኛ ሰፈር አክሱም ናት. የእኛ ሰፈር ላሊበላ ናት... የእኛ ሰፈር ውቅር የሊስትሮ ወንበር ናት ... የእኛ ሰፈር አፈ ታሪክም ናት!

“በድሮ ጊዜ እግዜር ለቅዱስ ድንቡጮ ተገለጠለትና እንዲህ አለው፣ 'ልጄ ድንቡጮ ሆይ፣ ምድር የእግሬ መርገጫ መሆኑን ሰምተሃል.. እንግዲህ እግሬ ምድር ላይ ሲያርፍ የወርቅ ጫማዬን ትቦርሽ ዘንድ የእግሬን ማረፊያ ድንጋይ በዚህ አስቀምጥ .. የሚል ራዕይ ተገልጦለት ከእንጦጦ ድረስ ይቺን ድንጋይ በኤኔትሬ መኪና አስጭኖ ወደዚህ ሰፈር አመጣት .…”

ታዲያ የሰፈሩ ልጆች ለቡሄ አባባ መክብብ ግሮሰሪ በር ላይ እንሄድና ጭፈራውን እናወርደዋለን።እሳቸውም በጢም መላጫቸው ግራ ቀኝ ጉንጫቸውን በደረቁ እየፈገፈጉና ብረቱ ላይ
ኳኳ አድርገው እያራገፉ ግጥማችንን በጥሞና ያዳምጣሉ፤

“እዛ ማዶ…
ሆ!
አንድ ሞተር
ሆ!
እዚህ ማዶ!
ሆ!
አንድ ሞተር!
ሆ!
የኔ አባባ መከብብ!
ሆ!
ባለ ዲሞፍተር!
"ሂዱ ወዲያ ! የምን ዲሞፍተር ነው …” ይሉና ይቆጣሉ። ረስተነው ነው እንጂ አባባ መክብብ የጦር
መሣሪያ አይወዱም። እንደውም መሣሪያ ታጥቆ ወደ ግሮሰሪያቸው የሚሄድ ደንበኛ ያስወጣሉ
እየተባለ ይወራ ነበር። ታዲያ ይችን አመላቸውን ስለምናውቅ በቁጣቸው አንደነግጥም። ፈንታው ድንቡጮ ወዲያው ግጥሙን ይቀይረዋል … እሳቸውም ወዳቋረጡት ጢም መላጨታቸው ተመልሰው
አንጋጥጠው የአገጫቸውን ሥር እየፈገፈጉ ዓይኖቻቸውን ጨረር እንዳይወጋቸው ጨፍነው
ይሰሙናል ...

“እዛ ማዶ!አንድ አፍንጮ፣
የኔ አባባ መክብብ ባለ ወፍጮ…!
እዛ ማዶ!አንድ በሬ፣
የኔ አባባ መክብብ ጀግና ገበሬ..”

ሃሃሃሃ እንደሱ ነው የሚባለው እደጉ! እደጉ! ድንቡጮ! ... ና ወዲህ …” ይሉና የጢም
መላጫቸውን ወደ ግራ እጃቸው አዘዋውረው በቀኝ እጃቸው አጭሯን የሥራ ገዋን ወደ ቀኝ ገልበው ሱሪያቸው ኪስ ውስጥ እጃቸውን ካስገቡ በኋላ በጣም ብዙ ተዘበራርቆ የተቀመጠ ብር (ድፍን የመቶና የሃምሳ ብር ኖቶች የሚበዙበት) ዘግነው ያወጣሉ። ከዝግኑ መሃል መርጠው ድፍን አምስት ብር ከለዩ
በኋላ (ይሄ ድርጊታቸው ቀልባችንን ስለሚወስደው ጭፈራችን ቀዝቀዝ ይላል…) ሌላውን ብር ወደ ኪሳቸው መልሰው ሲያበቁ ብሩ ላይ ትፍ ትፍ ብለው ድንቡጮ ግንባር ላይ ይለጥፉታል (እንደውም
ግንባሩ ለሽልማት ይመቻል) ..እኛም ሞቅ ይለናል ፤ ጭፈራውን በአዲስ ጉልበት ምርቃቱንም ለየት ባለ ፍቅር እናዥጎደጉደዋለን።
👍25🔥31
#ድንቡጮ_ለምን_ለምን_ሞተ


#ሁለት(መጨረሻ)


#በአሌክስ_አብርሃም


...“እደጉ ልጆቸ እድግ በሉ !! ወርቅ ይፍሶስቦት ሟለት ትልቅ በረከት ነውኮ…፤ ከወርቅ በሏይ ሙን አለ…? ቡዙ ተብዛዙ ቁም ነገር ያቡቋችሁ..! አቡነ አረጋዊ ጭንቅላታቹሁን ይከፋፍተውና ትሙሩቱ ይግባዓባችሁ…” ብለው ይመርቁናል። አፋቸው ይጣፍጣል። እማማ ንግሥት ኤርትራዊት ናቸው። ታዲያ በአማርኛ ሲያወሩ አንደበታቸው አይጠገብም። ጥርስ የማያስከድኑ ተጨዋች ናቸው። ሲቆጡም በዚያው ልክ ነው ይባላል ሲቆጡ አይተናቸው አናውቅም እንጂ…!! አባባ መክብብ ታዲያ ሚስታቸውን ሲወዷቸው ልክ የላቸውም። አንድ ቀን እትየ ንግሥት ታመው (የደም ግፊት የሚባል ነገር ነው አሉ) አንቡላንስ ተጠርቶ ጎረቤቱ ሁሉ ሲሯሯጥ አባባ መክብብ እንደ ሕፃን ልጅ በሁለት እጆቻቸው ጭንቅላታቸውን ይዘው ስቅስቅ ብለው ሲያለቅሱ እና ሲጮሁ አይቻቸዋለሁ ! ሰው ሁሉ እያባበላቸው!

“እትየ ንግሥት ... እናቴ፣ እህቴ፣ ጓደኛዬ ሜዳ ላይ እኔን ጥለሽ ..” እያሉ…

ባልና ሚስቱ አንዲት ልጅ አለቻቸው፤ ህደጋ የምትባል፣ ፈረንጅ አግብታ ውጭ አገር የምትኖር።በየሦስት ዓመቱ እናትና አባቷን ልትጠይቅ ስትመጣ ከታች ሰፈር ጀምሮ እስከላይ ሰፈር ድረስ
ሁሉም ቤት እየገባች ጎረቤቱን ሁሉ ትስምና ሃምሳ ሃምሳ ብር ትሰጣለች። ለትልልቅ ሰዎች ብቻ
ነው የምትሰጠው። ከእኛ መካከል የሃምሳ ብር እጣ የሚወደቅለት ፈንታው ድንቡጮ ብቻ ነበር።
የፈንታው እናት ሚስኪን ናት፤ በሽተኛ ስለሆነች ከአልጋ ላይ አትነሳም። ፈንታው አባባ መክብብ
ግሮሰሪ በረንዳ ሥር ጫማ እየጠረገ እና እየተላላከ ነው እናቱን የሚያስታምመው። አባቱ በደርግ ጊዜ ዘምቶ ይሙት ይትረፍ ሳይታወቅ በዛው ቀልጦ ቀርቷል። ያው የህደጋ ሃምሳ ብር ፈንታው ድንቡጮን የሚያካትተው ለዚህ ሳይሆን አይቀርም !

አንድ ቀን ታዲያ የስፖርት ትጥቅ ለመግዛት ከመንደርተኛው ሳንቲም እንለምናለን። በአጋጣሚ ፊት
ለፊታችን ህደጋ አሻንጉሊት የመሰለ ልጇን በደረቷ አቅፋ ስትመጣ ተገጣጠምን። ሌላውን መንደርተኛ ሳንቲም ውለድ እያልን ምናስቆም እኛ፣ ህደጋን ለምን እንደፈራናት እንጃ፤ ብቻ ገለል ብለን አሳለፍናት።
በቀጣዩ ቀን ታዲያ አስጠራችንና እንኳን በእውናችን በህልማችንም አስበነው የማናውቀውን የስፖርት
ትጥቅ ከነኳሱ ገዛችልን።

አቤ…ት! እንዴት እንደተደሰትን…! ለስንት ዓመት ታሪክ ሆኖ በመንደራችን ተወራ ! “ኳሱ የት
ይቀመጥ” በሚል በመካከላችን ከባድ ክርክር ተደርጎ እኔጋ እንዲቀመጥ ተወሰነ። የተሰማኝ ደስታ ወደር አልነበረውም። ግን ምን ያደርጋል አንድ ቀን ያ ለብዙ ሕፃናት ህልም የነበረ ኳስ ምጥ ይግባ ስምጥ ሳይታወቅ ጠፋ። የጠፋው ከእኛ ቤት ስለነበር በቡድኑ አባላት ዘንድ ክፉኛ አስተችቶኛል።ለረዥም ጊዜ ያኮረፉኝ የሰፈር ልጆችም ነበሩ። በእግር በፈረስ በሰፈራችን ስርቻ ሁሉ ኳሱን ፈልገን ስናጣው በቃ ወደ ጨርቅ ኳሳችን ተመለስን። አሁን ካደግን በኋላ ሳይቀር የኳሱ ነገር ሲነሳ እወቀሳለሁ።
እንደውም አሁን ካደግን በኋላ እድሜያችን ሃያዎቹ ውስጥ ገብቶ ተፈሪ የሚባለው የሰፈራችን ልጅ
(አሁን አዉስትራሊያ የሚኖር) ኢ-ሜይል ሲያደርግልኝ ስለ ኳሱ ጉዳይ አንስቶ እንዲህ ብሎኛል፣
“አቡቹ እዚህ የፈረንጅ ሕፃናት ኳሶች ይዘው ሲጫወቱ ሳይ ያች ህደጋ የገዛችልን የጣልክብን ኳስ ትዘ እያለችኝ ይቆጨኛል ሃሃሃ” አንረሳም እኮ አንዳንዴ !
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
ድንገት ነበር ነገሮች የተገለባበጡት፤ ልክ እንደ መሬት መንቀጥቀጥ፣ እንደጎርፍ መጥለቅለቅ ሰፈራችን ውስጥ በአብሮ መኖር የፍቅር ቆሌ የሆኑ ነዋሪዎችን ከሥራቸው እየመነገለ ድራሻቸውን ያጠፋ ድንገቴ
ነውጥ። እንዴት ነው ሰው ድንገት ተነስቶ ትላንት አለፍኩት ወዳለው አረንቋ መልሶ የሚዘፈቀው…?
“ሲደርሱብን ምን እናድርግ” ብሎ ነገር ...

“ኤርትራ ወረረችን…” ተባለ።
“ምናባቷ ቆርጧት ይች የእናት ጡት ነካሽ!” የሚሉ ደምፍላታም ሰዎች ሰፈሩን ሞሉት። ከየት አመጡት አማርኛውን…? መቸስ ታንክ ቢሆን፣ መትረየስ፣ ቦንብ ምናምን ገዙት ይባላል፣ ወይ በእርዳታ አገኙት፤ ስድብ ከየት ተፈበረከ ... ዛቻ መቼ ተረግዞ ነው በዜማ የተወለደው…? ትላንት እንደ ቦብ ማርሌ “ፀበኞች ካልታረቁ!” እያለ ሲያቀነቅን የነበረ ድምፃዊ “ፍለጠው ቁረጠው!” ዘፈኑን ከየት መዝርጦ ቴሌቪዥኑን ሞላው፤ ወይስ ሁሉም ዘፋኝ ለክፉ ጊዜ ያስቀመጠው ዘፈን አለው? ለጦርነት ግጥምና ዜማ መፍጠር ከፍቅር ዘፈን ይቀላል? ከቀበሌ ኪነት ቡድን እስከ አገር አቀፍ ታላላቅ ዘፋኞች ዘፈናቸው አይሄድ አይመጣ አንድ - “በለው ፍለጠው ቁረጠው !!”

በዓይን ርግብግቢት ፍጥነት 'ለደኅንነታችሁ' ብለው ደህና ሰዎች ብለን ያመንናቸውን፣ ስንጣላ አስታራቂ፣ ስንቸገር ደራሽ የነበሩት ጎረቤቶቻችንን ሁሉ በአውቶብስ እየጫኑ አባረሯቸው። እማማ ንግሥትን ጨምሮ። ከመወለዳችን በፊት ኤርትራ የሄዱ የማናውቃቸው ብዙ እማማዎች ከዛም ተባርረው መጡ። ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ። ለካስ የመንግሥታት ፍርሃት እንደጅብ ያነክሳል አገርንም ያስነክሳል። አሁን እማማንግሥት ምናቸው ነው ለደህንነት የሚያሰጋው? በሹሩባቸው ውስጥ ቦምብ
እንዳይቀብሩ ነው? ወይስ በድፏቸው ውስጥ ጥይት እንዳይደብቁ ...። እማማ ንግሥት (ለደህንነት ስጋት ናቸው ተብለው የተባረሩ ቀን ማታ ህልም አለምኩ….

ቀኑ ቡሄ ይመስለኛል። የሰፈር ልጆች እንደልማዳችን ተሰባስበን እማማ ንግሥት በር ላይ ቆመን
እንጨፍራለን።

“እዛ ማዶ አንድ በረዶ!

እዚህ ማዶ አንድ በረዶ!

የኔ እማማ ንግሥት!
ፓራ ኮማንዶ ….”

የእማማ ንግሥት በር ድንገት ብርግድ ብሎ ተከፈተና፣ በወርቅና በሐገር ባህል ቀሚስ የምናውቃቸው እማማ ንግሥት፣ የወታደር ልብስና ከስክስ ጫማ ለብሰው አናታቸውም ላይ የብረት ቆብ ደፍተው ድፎ ሳይሆን ዝናሩ የተንዠረገገ መትረየስ ጠመንጃ ደግነው፣ “ አንች ዲቃላ ሁሉ … በሬ ላይ ሙናባሽ ትናጫጫለሽ አቡነ አረጋዊ ድራሽ አባትሽን ያጥፉት!” ብለው ታታታታታታታታታታታታታ
ሲያደርጉብን በተለይ እኔ ሰውነቴ ተበሳስቶ ወንፊት የሆነ ይመስለኛል…፤ እየጮህኩ ከህልሜ ባነንኩ…፤ እናቴ ከትራስጌ በኩል ቆማ “አቡቹ በስማም በል ቅዠት ነው…” ትላለች።

ያየሁትን ህልም ለማሚ ስነግራት ግን ተቆጣች…

“ምን እንደው የዛሬ ልጅ የነገሯችሁን ይዛችሁ ትጋደማላችሁ፣ ቅዠት ይተርፋችኋል ፤ በል አርፈህ
ተኛ”

አባባ መክብብ እትዬ ንግሥት ወደ ኤርትራ ከተባረሩበት ጊዜ ጀምሮ ግራ እግራቸውን ሰብስቦ
ያዛቸው፤ በከዘራ ድጋፍ ሆነ የሚራመዱት። የጢም መላጫቸውም ከእጃቸው ጠፋች። ነጭና ጥቁር ቡራቡሬ ፂም ትንሽ አገጫቸውን ሸፈነው…፤ ተዘናጉ፤ ሰፈሩ ተዘናጋ …። አንድ ቀን በግሮሰሪዋ በኩል ሳልፍ አባባ መክብብ ከዘራው እጀታ ላይ የተነባበረ እጃቸው ላይ አገጫቸውን አሳርፈው አፋቸው
ባዶ ነገር እያኘከ ትክዝ ብለው ተቀምጠዋል በቀስታ ወደ ፊትና ኋላ እየተወዛወዙ። ላልፍ ስል የውሃ ማጠራቀሚያው በርሚል ላይ ዓይኔ አረፈ፤ የሆነ ነገር ቅር አለኝ …፤ በትኩረት በርሚሉን አየሁት፤ ነፍስ ካወቅኩ ጀምሮ ከበርሚሉ ተነጥላ የማታውቀው የመርቲ ጣሳ በቦታዋ የለችም። ጣሳዋ ትታሰርባት የነበረችው የኤሌክትሪክ ገመድ ባዶዋን ተንጠልጥላ ነፋስ በቀስታ ያወዘውዛታል !
👍21🔥1