አትሮኖስ
281K subscribers
111 photos
3 videos
41 files
486 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#ምንትዋብ


#ክፍል_አስራ_ሰባት


#ድርሰት_በሕይወት_ተፈራ

....ምንም እንኳን ልጇ ደሕና መሆኑንና ትምህርትና ዋናም እየተማረ እንደሆነ፣ ከፍ ሲል ደግሞ ቀስት ውርወራ፣ ጉግስና አደን እንደሚማር ብትሰማም፣ ጭንቀቷ እምብዛም ሊቀንስላት አልቻለም። ሳታስበው ግን ሁኔታዎች ተቀየሩ። ለንጉሠ ነገሥቱ ቅርብ የሆነው ዐቃቤ ሰዐቱ ዲዮስቆሮስ ንጉሠ ነገሥቱን፣ “ኢያሱ መጥቶ የቤተመንግሥት ወግ፣
አስተዳደርና ትምርት በአግባቡ ይማር፤ ባባትዎ አጥንት ይዤዎታለሁ”እያለ አላስቆም አላስቀምጥ አላቸው።

ምንትዋብ አጋዥ ያገኘች መሰላት

አንድ ቀን ያልታሰበ ነገር ተፈጠረ። የስድስት ዓመቱ ኢያሱ ሲጫወት ድንገት በቀስት የሰው ጊደር ወጋ። የጊደሩን ባለቤት ፈርቶ ከዐይን ተሰወረ። ሲፈለግ በመጥፋቱ ክርስትና አባቱ፣ የእህቱ ባል
ደጃዝማች ባስልዮስና የአካባቢው ነዋሪ በጭንቀት አካባቢውን አሰሱ::ሰፈርተኛው ሁሉ በደቦ ተከፋፍሎ ቀየውን፣ ወንዙንና ጫካውን ፈተሽ::ኢያሱ የውሃ ሽታ ሆነ። ሰዉ ተደናገጠ፣ የሚያደርገው ጠፋው። ብሎም
ኡኡታ፣ ለቅሶና ጩኸት በረከተ። ለንጉሠ ነገሥቱና ለምንትዋብ
እንዴት እንደሚነገራቸው ተመከረ።

ኢያሱ ከተደበቀበት ሲወጣ ዕልልታና ደስታ ጩኸትንና ለቅሶን
ተኩ። ማንነቱ ተደብቆ የኖረው ልጅ በዚህ አጋጣሚ ማንነቱ ታወቀ።

ደጃዝማች ባስልዮስ ግን የኢያሱ ማንነት መታወቁ አደገኛና አሳሳቢ
መሆኑን ተረድቶ በሐሳብ ማሰነ። አፄ በካፋ ጉዳዩን እንዲሰሙ አደረገ።ኢያሱም በፍጥነት ጐንደር እንዲመለስ ተደረገ። ምንትዋብ፣ እናቷና አያቷ የደስታና የእፎይታ እንባ አነቡ።

ምንትዋብ ሳትውል ሳታድር፣ ኢያሱ በተመረጡ አስተማሪዎች
ትምህርት እንዲማር አደረገች። የመንፈስ፣ የግብረገብ፣ የአካል ግንባታና የቤተመንግሥት ወግ ትምህርትም ላይ አተኮረች።
አፄ በካፋ ጠላቶቼ ይገድሉብኛል ብለው ስጋት ቢገባቸውም፣ ዝምታን ፈቀዱ። በሌላ በኩል ግን ከእሷ፣ ከእመቤት እንኰዬ፣ ከእመቤት ዮልያናና ከግራዝማች ኒቆላዎስ ጋር ብዙ ጊዜ ቆይታ መያዝ አዘወተሩ።

በተለይ ምንትዋብን፣ “አንቺ ብልህና አስተዋይ ስለ ሆንሽ እኔ ሳልኖር ኸልዤ ጋር ሁነሽ አገሬን ባግባቡ እንድትመሪ፣ እንድታስተዳድሪ።
የባሕር ማዶ አረመኔዎች አገሬ ገብተው እንዳይበጠብጡ፤ ሕዝቤንም በሃይማኖት ሆነ በሌላ እንዳይበክሉ ዐደራ” ይሏታል።

በነገሡ በዘጠነኛው ዓመት መጀመሪያ ላይ ጥቅምት ወር ውስጥ ግን፣
“ወዳጅ ዘመዴን እለያለሁ” በሚል ታመምኩ ብለው ሲደበቁ ምንትዋብ
ምሥጢር ጠበቀች። ወዲያው፣ “ንጉሡ ሊሞቱ ነው”፣ “ንጉሡ ሙተዋል” የሚል ወሬ ጐንደርን አወዛገባት። የጐንደር ከንቲባ ብላቴን ጌታ ኩቾ ከወህኒ አምባ ንጋሢ አመጣለሁ' ብሎ ሠራዊት አዘጋጀ። ወህኒ አምባዎች በበኩላቸው ወሬውን ሲሰሙ እኔ ልንገሥ፣ አንተ ንገሥ፣ የለም እሱ ይንገሥ ተባባሉ፤ ተመራረጡ፤ ተፎካከሩ።

ጐንደር እንደ ልማዷ ልትታመስ ሆነ።

በካፋ ይህን ሲሰሙ አለመታመማቸውን ለማሳየት ሐሙስ ቀን ደብረብርሃን ሥላሤ ሲሄዱ፣ መኳንንቱ በርቀት ከጋሻ ጃግሬዎች ኋላ በፈረስ ተከተሏቸው። ሕዝቡም ከየቤቱ እንደ ጎርፍ ፍንቅል ብሎ
ወጣ፡፡

በካፋ፣ ሕዝቡን፣ “ታዩኛላችሁና ወደየቤታችሁ ግቡ” ብለው አሰናበቱ።ሊቃውንት ንጉሠ ነገሥቱን በሕይወት በማየታቸው መሬት ሳሙ፤ካህናት ዘመሩ፤ ሕዝቡ ተደሰተ። ከረብሻ ዳነ። በካፋ ግን ብዙ ታዘቡ።
ወዳጅ መሳይ ሁሉ ከበስተጀርባቸው ምን እንደሚያስብ ተረዱ።

መኳንንቱን ወርቅ ሰቀላ ጠርተው፣ በአፈ ንጉሥ በኩል፣ “ምነው
ባካችሁ እንዳው ጥቂት ቀን ታምሜ ብተኛ ሽብር ማስነሳታችሁ? ስለምን ከተማዬን አስደነገጣችኋት? ሞተ ብላችሁ እንደዝኸ መሆናችሁ ተገቢ ነውን?” ሲሉ ጠየቋቸው። እንደማይተኙላቸውም ተረዱ። ሆኖም፣“እነዝኸ በልባቸው ክፋት የለም” ብለው ይቅርታ አደረጉላቸው።መሣሪያ ያነሳው ኩቾ ግን ከነተከታዮቹ ተይዞ ጊዜያዊ እስር ቤት ገብቶ ለፍርድ እንዲቀርብ ተወስኖበት ፍርድ ሸንጎ ቀረበ።

የሃገር ክህደት ወይም ሌላ ከፍተኛ ወንጀል ካልሆነ በስተቀር የዙፋን
ችሎት የማይዙት ንጉሠ ነገሥት፡ ጃን ተከል ተገኝተው ከምንትዋብ ጋር እንደወትሯቸው ቀይ ድባብ ተይዞላቸው፣ ከፍ ያለ ቦታ ላይ ተቀመጡ።መሣፍንቱ፣ መኳንንቱና ሊቃውንቱ እንደየደረጃቸው ተሰየሙ። ፍትሐ ነገሥት ተርጓሚዎቹ፣ ፍርድ ሰጭዎቹና አዛዦቹ፣ ግራ ቀኝ ተችዎቹ
ሁሉ ተገኝተዋል። ዐራቱ ሊቃውንት ፍትሐ ነገሥት ይዘው ቦታቸው
ላይ ተቀመጡ። አቡኑ፣ ዐቃቤ ሰዐቱና መኳንንቱ የተለመደ ቦታቸው ላይ ሆኑ።

ኩቾና ተከታዮቹ እግራቸው በእግረ ሙቅ ታስሮ፣ ጋሻ ጃግሬዎች
ግራና ቀኝ እየጠበቋቸው በንጉሠ ነገሥቱ ትይዩ ቆሙ።ከአዛዦቹ አንደኛው፣ “ጠበቃ ኸፈለግህ ይፈቀድልኻል” አለው፣
ኩቾን።

“አያሻኝም።”

“እንግዲያማ ተጠየቅ።”

“ልጠየቅ!”

“አንድ ስጠይቅህ አንድ፣ ሁለት ስሰጥህ ሁለት መልስልኝ። ኸዝኽ
እንዳትዛነፍ በቅሎ ያግድህ። ጃንሆይ ትንሽ አሟቸው ሰንብተው
እንደነበር አልሰማህም?”

“ሰምቻለሁ።”

“ተጠየቅ!”

“ልጠየቅ!”

“ጃንሆይን አደባባይ ባታያቸው ሊሞቱ ነው ብለህ አላወራህም?”

“አላወራሁም።”

“ተጠየቅ!”

“ልጠየቅ!”

“ያለ ጃንሆይ ፈቃድ ሠራዊትህን ማንቀሳቀስ እንደማትችል
ታውቃለህ አታውቅም?”

“አውቃለሁ ።"

“ተጠየቅ!"

“ልጠየቅ!”

“ዛዲያ ስለምን ሠራዊትህን አንቀሳቅሰህ ለአመጥ ተነሳህ?”

“ለአመጥ አልተነሳሁም።”

“ምስክር ይጠራብህ?”

“ሠራዊት...”

"አንድ ስጠይቅህ አንድ፣ ሁለት ስሰጥህ ሁለት መልስልኝ ያልኩህን አጣርሰኻል። ለበቅሎ ዋስ ጥራ።”

“አላጣረስሁም።”

“አጣርሰኻል። ምስክር ይጠራብኝ ወይንም አይጠራብኝ ነበር
መልሱ።”

“ኸጥያቄህ አልወጣሁም። እማኞች ይጠሩልኝ” እያለ ወደ ሰዉ ተመለከተ ኩቾ።

“አጣርሷል! አጣርሷል! በቅሎዋን ይክፈል!” አለ፣ ሰዉ።

“ተጠየቅ!”

“ልጠየቅ!”

“ለአመጥ መሣሪያ አላነሳህም?”

“ራስ ተስፋ ኢየሱስና ቢትወደድ ስኩት ጃንሆይ ያስሩኻል ቢሉኝ
መሣሪያ አነሳሁ።”

“ተጠየቅ!”

“ልጠየቅ!”

“ምንም ሳታደርግ ጃንሆይ ስለምን ያስሩኻል? ሞተዋል ብለህ
ስላስወራህና ኸወህኒ ነጋሢ ልታመጣ ስለፈለግህ ነው እነራስ ተስፋ ኢየሱስ ያስሩኻል ያሉህ።”

ኩቾ ወደ እፄ በካፋ ተመለከተ። ሁለት እጆቹን ዘርግቶ፣ “ጃንሆይ
ይማሩኝ” ብሎ አጎነበሰ።

“ምትጠይቀው ጥያቄ አለ?” ሲል ጠየቀው አንደኛው አዛዥ ።

“የለኝም። ምሕረት ያርጉልኝ ጃንሆይ!” አለ፣ ኩቾ፣ አጎንብሶ።

ከአዛዦቹ አንደኛው ጋቢውን አስተካከለና ወደ ንጉሠ ነገሥቱ
ተመለከተ፣ “ጃንሆይ ኩቾ የቀረበበት ክስ ክህደት ነው። ክህደት ደሞ በሞት ያስቀጣል” አለ፣ ፍትሐ ነገሥቱን እያገላበጠ። “ፍታ ነገሥቱ ሚለው በንጉሥ ላይ ያመጠና ያሳመጠ በሞት ይቀጣ ነው።”

ይህን ዓይነቱ የሞት ብይን ይገባዋል አይገባውም፤ ወይንም ደግሞ ሌላ ቅጣት ይቀጣ ብለው ለመወሰን መኳንንት እንደየማዕረጋቸው እየቆሙ ከዝቅተኛው ጀምሮ እስከ ከፍተኛው ድረስ አስተያየት ሰጡ።

“ክህደት ነውና ሞት ይገባዋል!” አሉ፣ አንደኛው መኰንን።

“ግዞት ይላክ!” አሉ፣ ሌላው።

“በግርፋት ይቀየርለት!” ብለው ተቀመጡ፣ አንደኛው
“ጃንሆይ መሐሪ ናቸውና ምህረት ይደረግለትና ሹመቱን ይገፈፍ”
አሉ፣ ሌላኛው።

እንደዚህ እያለ ሁሉም ተናግረው ከጨረሱ በኋላ፣ የማሳረጊያው
ንግግር የንጉሠ ነገሥቱ በመሆኑ፣ አፈ ንጉሡ አጎንብሶ ጆሮውን
ሲሰጣቸው ሁሉም ለመስማት ጆሯቸውን ሲያቀኑ ኩቾና ተከታዮቹ
ትንፋሻቸውን ውጠው ተጠባበቁ። ይህን ሁሉ በአንክሮ የምትመለከተው ምንትዋብም ተጠባበቀች።
👍20🤩1
#ምንትዋብ


#ክፍል_አስራ_ስምንት


#ድርሰት_በሕይወት_ተፈራ

“ሺሕ ዓመት ንገሥ።"

ምንትዋብ፣ አፄ በካፋ ወደ መሠሪ እንድትመጣ ሲልኩባት፣ ሕይወቷ
ዳግም ተለወጠ። ለጥቂት ቀናት መሠሪ ሱባዔ ገብተው ስለነበር
ጨርሰው ነው ብላ አስባለች። ከእናቷና ከአያቷ ጋር መሠሪ ስትደርስ፣የበካፋ ታማኝ እልፍኝ አስከልካዮች ቴዎድሮስ፣ ገላስዮስና ድንጉዜ ዐይኖቻቸው ደም መስለዋል። እጅ ነስተዋት ስትገባ መሠሪ ከብዶታል፤
ጨላልሟል። ከወትሮው ጠባብ ሆኖባታል።

አፄ በካፋ ከተኙበት ኣልጋ ራስጌ የነፍስ አባታቸው አባ ዐደራ
መስቀላቸውን ይዘው ቆመዋል። ኒቆላዎስ ከንጉሠ ነገሥቱ ግርጌ
አቀርቅሮ ቆሟል። ምንትዋብ ርምጃዋን ገታ አድርጋ ክፍሉንም
ሰዎቹንም ቃኘች።

ነገሩ አላምር አላት። መንፈሷ ተረበሸ። ሱባዔ ላይ የነበሩት ባሏ ምን እንደደረሰባቸው መገመት አቃታት። ወደ አልጋቸው መራመድ ፈልጋ እግሮቿ አልታዘዝ አሏት፤ ትንፋሽ አጠራት። ልቧ ደረቷን ሲደልቅ እንደ ማጥወልወል አላት። ሐውልት ይመስል ደርቃ ቀረች። ዐይኗ ኒቆላዎስን ኣልፎ ንጉሠ ነገሥቱ ላይ ሲያርፍ፣ ፊታቸው ተሸፍኗል።

ዕለቱ ማክሰኞ፣ ቀኑ መስከረም አስራ ስድስት ዓመተ ምህረቱ 1723 ነው። እኒያ ቅኔ የሚቀኙት፣ መንፈሳዊ መጻሕፍትን የሚፈትሹት፣ አደን የሚወዱት፣ ለሃገራቸው ፊደላት ጥብቅና ቆመው፣ “ፊደል አሳስቶ የጻፈ
እጁ ይቆረጣል” ብለው አዋጅ የጣሉት፣ ሥነ-ጥበብ እንዲዳብር፣ ቃላት እንዲበለፅጉ የጣሩት፣ በወባ ንዳድ ርደው እንደተራ ሰው ባላባት ቤት መደብ ላይ የተኙት፣ ላይ ታች እያሉ ያመጸውን ያስገበሩት፣ ያጠፋውን አይቀጡ ቅጣት የቀጡት፣ እንደ ቀደምት ነገሥታት የሃይማኖት ክርክር
ያከራከሩትና አሻራቸውን ለመተው የራሳቸውን ግንብ የገነቡት አፄ
በካፋ በነገሠ በዘጠኝ ዓመት ከዐራት ወራቸው፣ ምንትዋብን ባገቡ በሰባት ዓመታቸውና በተወለዱ በሰላሳ ሰባት ዓመታቸው ሕይወታቸው
አልፏል።

“ምንድርነው? ጃንሆይ ምን ሁነዋል?” አለች፣ ምንትዋብ፣ ድምጾ ይርበተበታል ።
ተጠጋቻቸውና ቡሉኮውን ከፊታቸው ላይ ገለጥ አደረገችው።አፍንጫቸው ጫፍ ላይ ደም አየች፤ መላ ሰውነቷ ራደ። ኒቆላዎስ ላይ አፈጠጠች።

“ድንገት ነው የሆነው። ባፍ ባፍንጫቸው ደም ፈሰሰ... ምንም ያህል አልቆዩ ዐረፉ” አላት።

ራሷን በሁለት እጆቿ ይዛ “ኡኡኡኡ...” አለች። እናቷና አያቷ
ፈጠን ብለው ግራና ቀኝ ደገፏት።

“ምነው ሳትነግሩኝ? ስለምንስ ከፋችሁብኝ?” እያለች ጮኸች።
መሬት ላይ ተንከባለለች።

ያን ጊዜ እናቷና አያቷ አብረዋት ጮሁ። እንደ እሷ መሬት
ላይ ተንከባለሉ። መሠሪ ጩኸት በጩኸት ሆነ። ዋይታ በረከተ።
ምንትዋብ ለያዥ አስቸገረች። እነግራዝማች ኒቆላዎስ ተጨነቁ፡
ለቅሶው እንዳይሰማ። የቤተመንግሥት ባለሟሎች እንኳን እንዲሰሙ አልተፈለገም።

ምንትዋብ የምትሆነው ጠፋት። ከቶውንም የደረሰውን ማመን
አቃታት። አጎንብሳ፣ “ወዮ እኔ! ይብላኝ ለኔ” እያለች እንባዋን አዘራች።ኒቆላዎስና አባ ዐደራ ግራና ቀኝ እጆቿን ይዘው እንድትቀመጥ ግድግዳ ተጠግቶ ወደ ተቀመጠ ወንበር ሊወስዷት ሞከሩ።

“ተዉኝ... ተዉኝ! ለባሌ ላልቅስ።
ተዉኝ!” እያለች እሪ አለች።

“እቴጌ ባክዎ ለቅሶዎ እንዳይሰማ” አሏት፣ አባ ዐደራ።

“ይሰማ ይሰማ! አገር ይስማ! እኔ አለባል ልዤ አላባት መቅረታችንን...አገር ይስማ... ወዮ እኔ...ወዮ ልዢ ።”

እነኒቆላዎስ እንደ ምንም አባብለው አስቀመጧት። አንዴ ንጉሠ ነገሥቱ የተኙበትን አልጋ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጣራውን ደግሞም ወለሉን እያየች እንባዋ ረገፈ። ሐዘኗ መሪር ሆነ። የደረሰባትን ድንገተኛ ሐዘን
ጫንቃዋ መቋቋም የሚችል አልመስል አላት። ዓለም አስፈሪ ቦታ ሆነችባት። ሕይወቷ ላይ የሐዘን ጥላ አጠላችበት። የመኖር ተስፋዋን ሸረሽረችው። ትናንት ማሾ እያበራች ፈለጓን የተከተለችው መሬትም
ድንገት ጨለመችባት።

አልጋ ባልጋ የመጣው የሕይወቷ መንገድ ፍጻሜው የተቃረበ
መሰላት።

እንደገና ጩኸት ጀመረች። እነኒቆላዎስ ተደናገጡ። የእሷም
ሆነ የእናቷና የአያቷ ጩኸት እንዳይሰማ ፈሩ፤ ለማባበል ሞከሩ፤ አልሆነላቸውም። ምንትዋብን ብዙ ኃላፊነት እንደሚጠብቃት ኒቆላዎስ
ለማስረዳት ቢሞክር አልሰማ አለችው።

“ባሌ ኸሞቱ ገዳም ገብቸ መመንኮስ አለብኝ” አለችው።
እንባዋ ደረቷ ላይ ይወርዳል። ያቺ ፀዳል የመሰለች ሴት ፊቷ ድንገት
ጨለማ ለብሷል። ከመቅጽበት ዕድሜዋ ላይ ዓመታት የተጨመሩ
መስለዋል። ከዐይኗም ከአፍንጫዋም የሚወርደው ፈሳሽ አልቃሻ ሕፃን ልጅ አስመስሏታል።

ኒቆላዎስና አባ ዐደራ ተረበሹ። እናቷና አያቷ ለቅሷቸውን አቋርጠው በድንጋጤ ተመለከቷት።

“አዎ... ኸዝኸ በኋላ ምን ዓለም አለኝ? እኔም እንደ ባለቤቴ መሬት
እስትገባ ዓለሜ ምናኔ ነው። እሳቸው ሙተው እኔ እንዴት ባለም
ኖራለሁ? ልዤን ይዤ ኸዳለሁ” እያለች ጮኸች።

ኒቆላዎስ፣ “የለም የለም፤ እኼማ አይሆንም” አላት፣ ተጠግቷት።
“ደሞስ ምናኔ ማን ያደርስሻል? የጃንሆይ ጠላቶች ወይም ወህኒ
አምባ ያሉ ደጋፊዎች ምንገድ ላይ ጠብቀው አንቺንም ልዥሽንም
ይገድሏችኋል። ባይገድሏችሁ ስንኳ መውጫና መውረጃ የሌለው ወህኒ አምባ ወስደው ያስሯችኋል። ገዳም ብትገቢም ጃንሆይ ቅባት ሃይማኖት
ተከታይ ነበሩ ተብለው ስለሚጠረጠሩ እዚያ ብዙ የተዋሕዶ መነኩሴ ጠላቶች አሏቸው፤ ይጣሉሻል” አላት።

እሷ ግን፣ “በቁስቋሟ ተዉኝ! ተዉኝ” እያለች እጆቿን እያርገበገበች ተማጸነቻቸው።

ያን ጊዜ አባ ዐደራ፣ “እቴጌ መቸም መቀበል እንጂ ምን ማረግ ይቻላል? ኸሞት ሚቀር የለ። አሁን እርስዎ እንደዝኸ ሲሆኑ ሳንዘጋጅ የጃንሆይ መሞት የተሰማ እንደሁ ሁከት ይነሳል። ወህኒ ያሉትም እግረ ሙቃቸውን ፈተው ይመጣሉ። ንጉሥ ሞተ ሲባል ሚሆነውን እናውቃለን። ባክዎ ይጠንክሩልን” እያሉ ተለማመኗት።

ዮልያናም፣ “የኔ ልዥ! ባክሽ ጠንክሪ። እንደዝህ መሆን ደግ ማዶል” እያሉ እንባዋን በነጠላቸው ጠራረጉላት፣ የራሳቸውን ለመግታት
እየታገሉ።

“ልጄ በጡቴ ይዤሻለሁ! በኢያሱ ይዠሻለሁ! በምትወጃት በቁስቋም ማርያም ይዠሻለሁ! በምትወጃቸው ባባትሽ አጥንት ይሻለሁ በርቺልኝ” እያሉ እንኰዬም ሙሾ እንደሚያወርዱ ሁሉ እጃቸውን ወደ ኋላ አድርገው እንባቸውን እያዘሩ ለመኗት።

እሷ ግን እንባዋን መግታት አቃታት፤ አልጽናና አለች።

ኒቆላዎስ አንዴ እንድታዳምጠው ለምኗት የንጉሠ ነገሥቱን ኑዛዜ
ቃል በቃል ነገራት።

“ምን እንደተሰማቸው አላወቅሁም ብቻ እኔን አስጠሩኝ። ኒቆላዎስ...
ዐደራ ምልህ ልዤን... አሉኝ፣ ድምጣቸው እየተቆራረጠ። ልዤን
ኢያሱን እንድታነግሥልኝ። ለነገሥታት ሚደረገውን ሥርዐት ሁሉ... ቅባዓ ንጉሡንም ዘውዱንም... አርገህ እንዲነግሥልኝ። እናቱ ምንትዋብ
ብልህ ናት ትርዳው፤ ኸጎኑ ትሁን። እሷ አገር መምራትና... ማስተዳደር
ትችላለች። አርቆ አስተዋይና እዝጊሃር የባረካት ሰው ናት። አገሬን... አገሬን ኸልዣችን ጋር ሁና፣ ተባህር እስተ ባህር ታስተዳድር። አገሬ.. ምንም ዓይነት በደል እንዳይፈጠምባት። እኔ የዠመርሁትን ሁሉ. አጠናክረሽ ቀጥይ፤ በዐጸደ ነፍስ ኹኜም አልለይሽም በልልኝ። ሁላችሁም ቃሌን ንገሩልኝ…. ዐደራ” ብለው አንቺን እንድንጠራላቸው
ሲጠይቁ፤ ደም ባፍ ባፍንጫቸው ያለማቋረጥ ወረደ። ግዝየም አላገኙ ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለየች።”

ምንትዋብ፣ ተናግሮ ሲጨርስ ሳግ እየተናነቃት ጣሪያውን፣
ግድግዳውን፣ ወለሉን፣ ሁሉንም በየተራ ተመለከተች። እነሱ ምን
እያሰበች እንደሆነ መገመት አቃታቸው። አንዴ እርስ በእርስ እየተያዩ ሌላ ጊዜ እሷን እያዩ ከአፉ የሚወጣውን ለመስማት ተጠባበቁ።
👍111