አትሮኖስ
280K subscribers
109 photos
3 videos
41 files
460 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#ምንትዋብ


#ክፍል_አስራ_ስድስት


#ድርሰት_በሕይወት_ተፈራ


...“ቁስቋም ብዙ ነገር ሰጥታኛለች፣ ወንድ ልዥ ደሞ ብትሰጠኝ።”

“ትሰጥሻለች። ምን ይሳናታል? አሁን ስለሱ አታስቢ።”

ሆዷ እየገፋ ሲመጣ፣ ጭንቀቷ በረታ። ሴት በመውለዷ ባትከፋም፣ ወንድ አለመውለዷ ቤተመንግሥት ውስጥ ሊኖረኝ ይችላል ብላ ያሰበችውን ቦታ የሚያሳጣት መሰላት።
ይበልጡንም ደግሞ ወህኒ
አምባ ያሉ የነገሥታት ዘሮች የሚወለደው ወንድ ቢሆን ሐዘናቸውን፣ ሴት ብትሆን ደግሞ ደስታቸውንና የበካፋን ተስፋ መጨናገፍ እያሰበች መንፈሷ ተበጠበጠ። የጐንደርን ታቦታት ሁሉ ተማጸነች። የእሷ
ቋረኝነት ያብከነከናቸው መሣፍንትና መኳንንት ደግሞ በካፋ ሲሄዱ ቋረኛ አልጋው ላይ የመውጣቱ ጉዳይ ሲያሳስባቸው፣ ሲያነጋግራቸውና ልባቸውን ሲሰቅለው እሷ የበለጠ ጭንቀት ውስጥ ገባች።
የቤተመንግሥት ባለሟሉ፣ የበካፋ ደጋፊ መኳንንትና ሕዝቡ ግን
በእነሱ ዘንድ ተወዳጅነትን እያተረፈች ለመጣችው፣ ለእሷ... ለምንትዋብ ወንድ ልጅ እንድትወልድ ተመኙላት።

ለወራት ቤተመንግሥት ግቢ ውስጥ፣ በየቤቱና በየመንደሩ ወሬው ተጋጋለ፤ ሞኝ መቆሚያ ላይ ተሟሟቀ፤ ጃን ተከል ላይ ተፋፋመ።የጃን ተከል ደንበኞች ወደ ሞኝ መቆሚያ ተጨማሪ ወሬ ለማሳደድ አሽቆለቆሉ። የሞኝ መቆሚያዎቹ ወደ ጃን ተከል በጥድፊያ አሻቀቡ።

መጽሐፍ ገላጩና ኮከብ ቆጣሪው ገሚሱ ወንድ፣ ሌላው ሴት ነው
ሲል ተነበየ። ገበሬው በየእርሻው፣ ነጋዴው በገበያው ላይ፣ ሴቶች ወንዝ ዳር፣ ሽማግሌና ወጣት በየጎጡ እሰጥ አገባ ያዙ፤ ተወራረዱ። የንግርት
ዓይነቶች ተወሱ። የቆራጣ ገዳም እመምኔቷ፣ የወለተጴጥሮስ ትንቢት ተወራ፣ የሰማው ላልሰማው አስተላለፈ። ወሬው ጐንደርን ተሻግሮ በየግዛቱ ተናፈሰ። ቀድሞ ስለነገሥታት የተነገሩ ሌሎች ንግርቶች
ሁሉ ለማመሳከሪያነት ቀረቡ፣ ተመረመሩ፣ ተተነተኑ።
ሃገር በወሬ ታመሰች። ወንድ ነው ሲሏት ጮቤ ስትረግጥ፣ ሴት ናት
ሲሏት ስትተክዝ ከረመች።

ምንትዋብ በበኩሏ ቀናቱ ሲያዘግሙባት፣ ወራቱ እንደ ገመድ ሲጎተቱባት ቆይታ አንድ ሌሊት ምጥ ያዛት። እናቷና አያቷ የነገሥታቱ አዋላጅ የሆኑትን ሴት በፍጥነት አስመጡ። ምንትዋብ ሌሊቱን በሙሉ ስታምጥ፣ ሴቱ “ማርያም”፣ “ማርያም” ሲል፣ በካፋ በጭንቀት ቁጭ
ብድግ ሲሉ፣ ሲጸልዩ፣ ካህናት ምህላ ሲያወርዱና የቤተመንግሥት ባለሟሎች ሲንቆራጠጡ ቆይተው ንጋት ላይ የመጀመሪያው ዕልልታ ተሰማ። በሰላም የመገላገሏ ዜና በመኾኑ ለአፄው የአፍታ እፎይታ
ቢሰጣቸውም የሕጻኑን ጸታ ለመለየት ዕልልታውን መቁጠር ጀመሩ።

ዕልልታው ተደገመ፤ የበካፋ ጭንቀትም ናረ፤ ሦስተኛውና የመጨረሻው ዕልልታ ይሰማና ወሽመጤን ይቆርጠው ይኾን ወይስ ይቀጥላል? የሚለው ጭንቀት በእያንዳንዱ ዕልልታ መሃል ያለችዋን ቅጽበት ዝንተዓለም እስክትመስል ድረስ ለጠጣት። ሦስተኛው ዕልልታ
ተሰማ። እዚኸ ላይ የበካፋ የልብ ትርታ ፀጥ አለ፤ ሌላ ዕልልታ ካልተሰማ አልቦ አልጋ ወራሽ የሚለው ሥጋት ሰቅዞ ይዟቸዋል። የጠላቶቻቸውን መደሰት፣ የወዳጆቻቸውን መሳቀቅ እየቃኙ ሳለ፣ አራተኛው የዕልልታ
ድምጽ መጣ። ወንድ ልጅ! አምስተኛውን፣ ስድስተኛውንና ሰባተኛውን ዕልልታ መስማት አላስፈለጋቸውም፤ ወንድ ልጅ ተወልዶላቸዋል! ዜናውን በመላ ቤተመንግሥቱ ግቢ ውስጥ ሲያስተጋቡት፣ ግቢው
ትርምስምሱ ወጣ።

ምንትዋብ ድካም ላይ ብትሆንም ደስታዋ ወሰን አጣ፣ በጭንቀት
የተኮማተረው ግንባሯ ተፍታታ፤ ቁስቋም ማርያምን አመሰገነች።
አፄ በካፋ በጭንቀት የሙጥኝ ይዘውት የነበረውን የጸሎት
መጽሐፋቸውን አስቀምጠው ከመኝታ ክፍላቸው ወጡ።

ምንትዋብ ወዳለችበት ገሰገሱ። ምንትዋብ እስክትጸዳዳ ጠብቀው
ሲገቡ፣ እየደጋገሙ፣ “እንኳን ማርያም ማረችሽ” አሏት። እንኰዬ
ህጻኑን ኣቅፈው ሲያሳይዋቸው የደስታ እንባ ተናነቃቸው። አልጋ ወራሽ በማግኘታቸው ሩፋኤልንና ከአንገርብ ወንዝ በስቲያ ደፈጫ የተከሏትን ኪዳነ ምሕረትን አመሰገኑ፤ ውለታቸውን በወርቅ እንደሚከፍሉ ቃል ገቡ።

ቤተመንግሥቱ ውስጥ ታላቅ ፈንጠዝያ ሆነ። ወዲያው ስፍር ቁጥር የሌለው የግባት ነፍጥ ወደላይ ተተኮሰ። የአካባቢው ሰው “ወንድ ነው!
ወንድ ነው!” እያለ ጃን ተከል ግልብጥ ብሎ ወጣ። ሴቶች ዕልልታቸውን አቀለጡት። ጐንደር የምሥራቹ ደረሳት፤ ፈነደቀች። ራቅ ካሉ ቦታዎች ሳይቀር ጐንደሬዎች እየከነፉ ጃን ተከል ደረሱ።

እቴጌ ወንድ ልዥ ተገላገሉ! ሰባት ግዝየ ሲተኮስ ቆጥሬያለሁ።
ወንድ ነው። ንጉሡ አልጋ ወራሽ አገኙ!” ይላል አንዱ።

“ሦስት ቆጥሬ ሴት ትሆን? ስል ዐራት ሲደገም እንግዲያማ ሰባት
ነው ሚሆን። ወንድ ነው ብየ ስሮጥ መጣሁ” ይላል ሌላው።
የዕጣና የውርርድ አሸናፊዎች የድል ዋጋቸውን ጠየቁ።

ንግርቶች ሁሉ እንደገና ተነገሩ። የቅድስት ወለተጴጥርስ ትንቢት
ተነሣ። “የሷ ንግርት መሬት አይወድቅም” ተባለ። በየደብሩ ካህናት ደወል አሰሙ። ዘመሩ፣ አሸበሸቡ። መነኮሳት ሕልማቸውን ተለወዋጡ: ደስታ በደስታ ሆኑ።

የበካፋ የሥልጣን ተቀናቃኞች ወሬውን ሲሰሙ ደነገጡ፤ ተስፋቸው እንደ እንፋሎት ተነነ። የማስመሰል ካባ የደረቡ አንጀታቸው ያረረ፣ወንድ ልጅ በመወለዱ ከልብ የተደሰቱ መኳንንት፣ ካህናትና ሊቃውንት
ከቅርብና ከሩቅ ደስታቸውን ለመግለፅ ወደ ቤተመንግሥት ጎረፉ።

ለሕጻኑም መልካም ምኞታቸውን አዥጎደጎዱ። ሕጻኑ በአያቱ፣ በአፄ ኣድያም ሰገድ ኢያሱ ስም ተጠራ። ግብር በየቀኑ ገባ። ኢያሱ፣ በወጉ መሠረት በአርባ ቀኑ ክርስትና ተነሣ።

ኢያሱ ከተወለደ በኋላ፣ የመጀመሪያው መስቀል ነው። ለአፄ በካፋ ዓመታዊ ሠራዊት ግባት ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ ነው። እንደ ጎጃምና ትግራይ ካሉ ራቅ ካሉ ግዛቶች የሚመጡ አስተዳዳሪ መኳንንት
ክረምቱ ሳይገባ ግንቦት ወር ላይ እያንዳንዳቸው ሠራዊታቸውን
ይዘው ጐንደር ሲገቡ፣ እንደ ስሜንና ቤገምድር ካሉ ቅርብ ቦታዎች የሚመጡት ደግሞ ዐዲስ ዓመትን ቤታቸው ውለው ሠራዊታቸውን ይዘው ጐንደር ገብተዋል። ቤተመንግሥት ዙርያ ለየግላቸውና ይዘውት
ለመጡት ሠራዊት ድንኳን ተተክሎላቸው እዚያው አርፈዋል።

ምንትዋብና አያቷ ስለ ሠራዊት ግባቱ አስፈላጊነት ሲነጋገሩ
አያትየው፣ ነገሥታቱ እኼን በዓል ሚያደርጉት አንድም እንግዲህ
ወታደራዊ ጉልበታቸውን ለማሳየት...” ብለው ሲጀምሩ አቋረጠቻቸው።

“ለማን ነው ሚያሳዩት?”

“ለሁሉም። እሱ ብቻ ማዶል። የመኳንንቱን ታማኝነት ለማረጋገጥም ሲሉ ነው። ሌላ ደሞ... ደንብ ሲያወጡ ወይም አዋጅ ሲነግሩ መኳንንቱ
በየግዛታቸው ያነን ደንብና አዋጅ በተመሳሳይ መንገድ እንዲያስከብሩ ጭምር ነው። ሌላው ደሞ መቸም ንጉሡ መኳንንቱ እንዳያምጹባቸው...
ተቀይመዋቸው ከሆነ ደሞ ለማረጋጋትና ሰላም ለመፍጠር በጋብቻ ሚተሳሰሩበትም ግዝየ ነው። በዝኸ ግዝየ አንድ የተቀየመ መኰንን አሞኛል ብሎ ሊቀር ይችላል። እናም እኼ ግዝየ ጃንሆይ አለ ነገር ሚሉበት፣ ብዙ ነገር ሚያውቁበትና ሚስተካከል ኻለም ተሎ ብለው ሚያስተካክሉበትም ግዝየ ነው” አሏት።

የበዓሉ ዕለት፣ ምንትዋብ ከአፄ በካፋ ጎን ድባብ ተይዞላት አደባባይ ወጣች። ሥርዐቱን ለማየት እጅግ ጓግታለች። ከንጉሠ ነገሥቱ ጎን ተቀመች። ጐንደሬዎችም ይህን ታላቅ በዓል ለመታደም ሥራቸውን
ነቅለው ወጥተዋል። ፎካሪዎች በየተራ እየወጡ ወደላይ ወደታች እያሉ ፎከሩ፣ ሽለሉ። ንጉሠ ነገሥቱን አወደሱ፤ አመሰገኑ።ሽለላውና ፉከራው ሲቆም፣ በአጋፋሪ መሪነት ታላቁ ስልፍ ተጀመረ።
👍13
#ምንትዋብ


#ክፍል_አስራ_ሰባት


#ድርሰት_በሕይወት_ተፈራ

....ምንም እንኳን ልጇ ደሕና መሆኑንና ትምህርትና ዋናም እየተማረ እንደሆነ፣ ከፍ ሲል ደግሞ ቀስት ውርወራ፣ ጉግስና አደን እንደሚማር ብትሰማም፣ ጭንቀቷ እምብዛም ሊቀንስላት አልቻለም። ሳታስበው ግን ሁኔታዎች ተቀየሩ። ለንጉሠ ነገሥቱ ቅርብ የሆነው ዐቃቤ ሰዐቱ ዲዮስቆሮስ ንጉሠ ነገሥቱን፣ “ኢያሱ መጥቶ የቤተመንግሥት ወግ፣
አስተዳደርና ትምርት በአግባቡ ይማር፤ ባባትዎ አጥንት ይዤዎታለሁ”እያለ አላስቆም አላስቀምጥ አላቸው።

ምንትዋብ አጋዥ ያገኘች መሰላት

አንድ ቀን ያልታሰበ ነገር ተፈጠረ። የስድስት ዓመቱ ኢያሱ ሲጫወት ድንገት በቀስት የሰው ጊደር ወጋ። የጊደሩን ባለቤት ፈርቶ ከዐይን ተሰወረ። ሲፈለግ በመጥፋቱ ክርስትና አባቱ፣ የእህቱ ባል
ደጃዝማች ባስልዮስና የአካባቢው ነዋሪ በጭንቀት አካባቢውን አሰሱ::ሰፈርተኛው ሁሉ በደቦ ተከፋፍሎ ቀየውን፣ ወንዙንና ጫካውን ፈተሽ::ኢያሱ የውሃ ሽታ ሆነ። ሰዉ ተደናገጠ፣ የሚያደርገው ጠፋው። ብሎም
ኡኡታ፣ ለቅሶና ጩኸት በረከተ። ለንጉሠ ነገሥቱና ለምንትዋብ
እንዴት እንደሚነገራቸው ተመከረ።

ኢያሱ ከተደበቀበት ሲወጣ ዕልልታና ደስታ ጩኸትንና ለቅሶን
ተኩ። ማንነቱ ተደብቆ የኖረው ልጅ በዚህ አጋጣሚ ማንነቱ ታወቀ።

ደጃዝማች ባስልዮስ ግን የኢያሱ ማንነት መታወቁ አደገኛና አሳሳቢ
መሆኑን ተረድቶ በሐሳብ ማሰነ። አፄ በካፋ ጉዳዩን እንዲሰሙ አደረገ።ኢያሱም በፍጥነት ጐንደር እንዲመለስ ተደረገ። ምንትዋብ፣ እናቷና አያቷ የደስታና የእፎይታ እንባ አነቡ።

ምንትዋብ ሳትውል ሳታድር፣ ኢያሱ በተመረጡ አስተማሪዎች
ትምህርት እንዲማር አደረገች። የመንፈስ፣ የግብረገብ፣ የአካል ግንባታና የቤተመንግሥት ወግ ትምህርትም ላይ አተኮረች።
አፄ በካፋ ጠላቶቼ ይገድሉብኛል ብለው ስጋት ቢገባቸውም፣ ዝምታን ፈቀዱ። በሌላ በኩል ግን ከእሷ፣ ከእመቤት እንኰዬ፣ ከእመቤት ዮልያናና ከግራዝማች ኒቆላዎስ ጋር ብዙ ጊዜ ቆይታ መያዝ አዘወተሩ።

በተለይ ምንትዋብን፣ “አንቺ ብልህና አስተዋይ ስለ ሆንሽ እኔ ሳልኖር ኸልዤ ጋር ሁነሽ አገሬን ባግባቡ እንድትመሪ፣ እንድታስተዳድሪ።
የባሕር ማዶ አረመኔዎች አገሬ ገብተው እንዳይበጠብጡ፤ ሕዝቤንም በሃይማኖት ሆነ በሌላ እንዳይበክሉ ዐደራ” ይሏታል።

በነገሡ በዘጠነኛው ዓመት መጀመሪያ ላይ ጥቅምት ወር ውስጥ ግን፣
“ወዳጅ ዘመዴን እለያለሁ” በሚል ታመምኩ ብለው ሲደበቁ ምንትዋብ
ምሥጢር ጠበቀች። ወዲያው፣ “ንጉሡ ሊሞቱ ነው”፣ “ንጉሡ ሙተዋል” የሚል ወሬ ጐንደርን አወዛገባት። የጐንደር ከንቲባ ብላቴን ጌታ ኩቾ ከወህኒ አምባ ንጋሢ አመጣለሁ' ብሎ ሠራዊት አዘጋጀ። ወህኒ አምባዎች በበኩላቸው ወሬውን ሲሰሙ እኔ ልንገሥ፣ አንተ ንገሥ፣ የለም እሱ ይንገሥ ተባባሉ፤ ተመራረጡ፤ ተፎካከሩ።

ጐንደር እንደ ልማዷ ልትታመስ ሆነ።

በካፋ ይህን ሲሰሙ አለመታመማቸውን ለማሳየት ሐሙስ ቀን ደብረብርሃን ሥላሤ ሲሄዱ፣ መኳንንቱ በርቀት ከጋሻ ጃግሬዎች ኋላ በፈረስ ተከተሏቸው። ሕዝቡም ከየቤቱ እንደ ጎርፍ ፍንቅል ብሎ
ወጣ፡፡

በካፋ፣ ሕዝቡን፣ “ታዩኛላችሁና ወደየቤታችሁ ግቡ” ብለው አሰናበቱ።ሊቃውንት ንጉሠ ነገሥቱን በሕይወት በማየታቸው መሬት ሳሙ፤ካህናት ዘመሩ፤ ሕዝቡ ተደሰተ። ከረብሻ ዳነ። በካፋ ግን ብዙ ታዘቡ።
ወዳጅ መሳይ ሁሉ ከበስተጀርባቸው ምን እንደሚያስብ ተረዱ።

መኳንንቱን ወርቅ ሰቀላ ጠርተው፣ በአፈ ንጉሥ በኩል፣ “ምነው
ባካችሁ እንዳው ጥቂት ቀን ታምሜ ብተኛ ሽብር ማስነሳታችሁ? ስለምን ከተማዬን አስደነገጣችኋት? ሞተ ብላችሁ እንደዝኸ መሆናችሁ ተገቢ ነውን?” ሲሉ ጠየቋቸው። እንደማይተኙላቸውም ተረዱ። ሆኖም፣“እነዝኸ በልባቸው ክፋት የለም” ብለው ይቅርታ አደረጉላቸው።መሣሪያ ያነሳው ኩቾ ግን ከነተከታዮቹ ተይዞ ጊዜያዊ እስር ቤት ገብቶ ለፍርድ እንዲቀርብ ተወስኖበት ፍርድ ሸንጎ ቀረበ።

የሃገር ክህደት ወይም ሌላ ከፍተኛ ወንጀል ካልሆነ በስተቀር የዙፋን
ችሎት የማይዙት ንጉሠ ነገሥት፡ ጃን ተከል ተገኝተው ከምንትዋብ ጋር እንደወትሯቸው ቀይ ድባብ ተይዞላቸው፣ ከፍ ያለ ቦታ ላይ ተቀመጡ።መሣፍንቱ፣ መኳንንቱና ሊቃውንቱ እንደየደረጃቸው ተሰየሙ። ፍትሐ ነገሥት ተርጓሚዎቹ፣ ፍርድ ሰጭዎቹና አዛዦቹ፣ ግራ ቀኝ ተችዎቹ
ሁሉ ተገኝተዋል። ዐራቱ ሊቃውንት ፍትሐ ነገሥት ይዘው ቦታቸው
ላይ ተቀመጡ። አቡኑ፣ ዐቃቤ ሰዐቱና መኳንንቱ የተለመደ ቦታቸው ላይ ሆኑ።

ኩቾና ተከታዮቹ እግራቸው በእግረ ሙቅ ታስሮ፣ ጋሻ ጃግሬዎች
ግራና ቀኝ እየጠበቋቸው በንጉሠ ነገሥቱ ትይዩ ቆሙ።ከአዛዦቹ አንደኛው፣ “ጠበቃ ኸፈለግህ ይፈቀድልኻል” አለው፣
ኩቾን።

“አያሻኝም።”

“እንግዲያማ ተጠየቅ።”

“ልጠየቅ!”

“አንድ ስጠይቅህ አንድ፣ ሁለት ስሰጥህ ሁለት መልስልኝ። ኸዝኽ
እንዳትዛነፍ በቅሎ ያግድህ። ጃንሆይ ትንሽ አሟቸው ሰንብተው
እንደነበር አልሰማህም?”

“ሰምቻለሁ።”

“ተጠየቅ!”

“ልጠየቅ!”

“ጃንሆይን አደባባይ ባታያቸው ሊሞቱ ነው ብለህ አላወራህም?”

“አላወራሁም።”

“ተጠየቅ!”

“ልጠየቅ!”

“ያለ ጃንሆይ ፈቃድ ሠራዊትህን ማንቀሳቀስ እንደማትችል
ታውቃለህ አታውቅም?”

“አውቃለሁ ።"

“ተጠየቅ!"

“ልጠየቅ!”

“ዛዲያ ስለምን ሠራዊትህን አንቀሳቅሰህ ለአመጥ ተነሳህ?”

“ለአመጥ አልተነሳሁም።”

“ምስክር ይጠራብህ?”

“ሠራዊት...”

"አንድ ስጠይቅህ አንድ፣ ሁለት ስሰጥህ ሁለት መልስልኝ ያልኩህን አጣርሰኻል። ለበቅሎ ዋስ ጥራ።”

“አላጣረስሁም።”

“አጣርሰኻል። ምስክር ይጠራብኝ ወይንም አይጠራብኝ ነበር
መልሱ።”

“ኸጥያቄህ አልወጣሁም። እማኞች ይጠሩልኝ” እያለ ወደ ሰዉ ተመለከተ ኩቾ።

“አጣርሷል! አጣርሷል! በቅሎዋን ይክፈል!” አለ፣ ሰዉ።

“ተጠየቅ!”

“ልጠየቅ!”

“ለአመጥ መሣሪያ አላነሳህም?”

“ራስ ተስፋ ኢየሱስና ቢትወደድ ስኩት ጃንሆይ ያስሩኻል ቢሉኝ
መሣሪያ አነሳሁ።”

“ተጠየቅ!”

“ልጠየቅ!”

“ምንም ሳታደርግ ጃንሆይ ስለምን ያስሩኻል? ሞተዋል ብለህ
ስላስወራህና ኸወህኒ ነጋሢ ልታመጣ ስለፈለግህ ነው እነራስ ተስፋ ኢየሱስ ያስሩኻል ያሉህ።”

ኩቾ ወደ እፄ በካፋ ተመለከተ። ሁለት እጆቹን ዘርግቶ፣ “ጃንሆይ
ይማሩኝ” ብሎ አጎነበሰ።

“ምትጠይቀው ጥያቄ አለ?” ሲል ጠየቀው አንደኛው አዛዥ ።

“የለኝም። ምሕረት ያርጉልኝ ጃንሆይ!” አለ፣ ኩቾ፣ አጎንብሶ።

ከአዛዦቹ አንደኛው ጋቢውን አስተካከለና ወደ ንጉሠ ነገሥቱ
ተመለከተ፣ “ጃንሆይ ኩቾ የቀረበበት ክስ ክህደት ነው። ክህደት ደሞ በሞት ያስቀጣል” አለ፣ ፍትሐ ነገሥቱን እያገላበጠ። “ፍታ ነገሥቱ ሚለው በንጉሥ ላይ ያመጠና ያሳመጠ በሞት ይቀጣ ነው።”

ይህን ዓይነቱ የሞት ብይን ይገባዋል አይገባውም፤ ወይንም ደግሞ ሌላ ቅጣት ይቀጣ ብለው ለመወሰን መኳንንት እንደየማዕረጋቸው እየቆሙ ከዝቅተኛው ጀምሮ እስከ ከፍተኛው ድረስ አስተያየት ሰጡ።

“ክህደት ነውና ሞት ይገባዋል!” አሉ፣ አንደኛው መኰንን።

“ግዞት ይላክ!” አሉ፣ ሌላው።

“በግርፋት ይቀየርለት!” ብለው ተቀመጡ፣ አንደኛው
“ጃንሆይ መሐሪ ናቸውና ምህረት ይደረግለትና ሹመቱን ይገፈፍ”
አሉ፣ ሌላኛው።

እንደዚህ እያለ ሁሉም ተናግረው ከጨረሱ በኋላ፣ የማሳረጊያው
ንግግር የንጉሠ ነገሥቱ በመሆኑ፣ አፈ ንጉሡ አጎንብሶ ጆሮውን
ሲሰጣቸው ሁሉም ለመስማት ጆሯቸውን ሲያቀኑ ኩቾና ተከታዮቹ
ትንፋሻቸውን ውጠው ተጠባበቁ። ይህን ሁሉ በአንክሮ የምትመለከተው ምንትዋብም ተጠባበቀች።
👍20🤩1