አትሮኖስ
286K subscribers
118 photos
3 videos
41 files
567 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
“ምድር ከሰጠችኝ ገጸ በረከት እሷ ዋነኛዋ ነች። ምድር ላይ መቆየት ካማረኝ የሚያምረኝ በእሷ ምክንያት ነው። የሕይወት ተጋድሎዬን ያህል ነው ትርጉም የምትሰጠኝ፤ በዚህ በዝባዥ ስርዓት፣ በእዚህ አምባገነን ስርዓት፤ ሕዝብ ከቁጥር በቀር ትርጉም በማይሰጠው ይህን በዝባዥ አገዛዝ እታገለው ዘንድ እሷ የምትሰጠኝ ተስፋ እና ፍቅር ግዙፍ ነው።

'Socialism እና Karl Marx' እንደማይነጣጠሉ ሁሉ የኖረኝ ክብር እና ዝና ከእሷ ከሚስቴ ጋር ሊነጣጠል እና ካለ እሷ የሚቻል አልነበረም። አይኔን አይታ የምትታዘዘኝ እና የምታዝንልኝ የእኩለ ሌሊት ብርሃኔ እሷ ናት።

እሷ ጠይም የደስታ መግቢያ በሬ ናት። እሷ ሳትኖረኝ ምንስ ቢኖረኝ ምን ያደርግልኛል? ስንት ቀን እሱን ያየ፤ ከእሱ ጋ የቆመ እንደሎጥ ሚስት የጨው ሐውልት ይሆናል ተብሎ ታውጆ እንኳን ምን ቢመጣ ካላንተ ስሆን ከሚሰማኝ አይበልጥም ብላ አብራኝ ነበረች፤ ስንቴስ መቀመቅ ሲያወርዱኝ ከእሷ በቀር ማን አብሮኝ ቆመ?

እሷ የነፍስ ምግብ ጸዳሌ ናት። ምንም ብሆን፤ ምንም ባጣ የማይደንቀኝ ልበ ደንዳና እንደሆንኩ ያለፍኩበት ጨለማ ይመሰክራል፤ እሷ ብቻ ከእኔ ጋ ትሁንልኝ እንጂ።

እሷ ከቀደመችብኝ ያን ዕለት ነው ኩራባቸው መንፈሱ የሚታወከው፤ እሷ ካለችማ ኩራባቸው ልቡ ላይ ሐሴት እንደተመላለሰ የተሰፈረለትን ዘመን ይጨርሳል ..

እሷ የልቤ ብርሃን ናት። ግፍን እቋቋም ዘንድ የተቸረችኝ ጫንቃዬ ናት፤ በንፅሕና ከእውነት ጋ እንድቆም፤ አቋሜ እንዳይሸረሸር፤  መንገዴን፣ አቋሜን  በፍቅር  ከመንገዴ እንዳልሰናከል በትልቁ አቅም ሆናኛለች።

በጠላት፣ በአሰናካይ፣ በቀለብተኛ ተከብቤ : ሳለሁ እንዳላፈገፍግ የምታበረታኝ የደስታዬ ፍላጽ መዓዙን የዓላማዬ ያህል ነው የምወዳት... ይላል። .

ሌላ ገጽ ገለጥኩ

'I will not quit until I make my dreams come true. tius. ኣ"ደምን እንደምን ድምጽ ለመሆን መጥቼ ዝም እላለሁ?

በዜጎች መሀል ግጭትን የሚቸረችር አገዛዝ፤ የማንነታችንን ግንብ የሚሸረሸር ትርክት  የሚያንሸረሽሩ ቀለብተኞች ባሉበት፤ ግፍ ባራኪ፣ ሞራል አልባ አሸከር፣ ፈሪ፣ መርሕ አልባ አለቅላቂ ልሒቃን በተሰባሰቡበት ምድር ተገኝቼ  እስክሞት ዝም አልልም። ደግሞስ ላለመሞት አልመጣሁ፣ ይግደሉኝ እንጂ መቼም እንደማልደለል እኔም፣ መዓዙም፣ እነሱም ያውቃሉ።

እኔ ኩራባቸው ዓለሙ አገር እንድታብብ ከማለም በቀር፤ መነሻ አልባ ትርክት ከማጋለጥ በቀር አንድም ስውር ሕልም እና ግብ ኖሮኝ እንደማያውቅ የልቤን እውነት የምታውቀው መዓዚ እና ሕያው አምላኬ ምስክር ነው እንጂማ ስንቴ በስልጣን ሊደልሉኝ ታከውኝ የለ! እንጂማ በጉቦ ሊጥሉኝስ አላሴሩም? እኔ ኩራባቸው ሳንቲም ግድ የሚሰጠኝ መስሏቸው… ሃሃሃሃሃ የሚታገሉትን ኩራባቸውን አያውቁትም ::

ሌላ ገጽ ገለጥኩ

“አንቺ ግዙፍ ሕልሜን የምታክይ፤ አይበገሬው ልቤን የበገርሽ፣ ኮስታራ ግንባሬን ገንብረሽ ለፈገግታ የራቀውን ፊቴን የምታፈኪ ሚስቴ ሆይ የሕይወት ዘመን ንዑዴ ነሽ። በትንሽ ቀልድ፣ በትንሽ ጨዋታ የምትደሰችልኝ፤ በወደኩበት
በታመምኩበት በታሰርኩበት ሰው ሁሉ ፈርቶ ከእኔ ሲርቅ፣ ከእኔ ጋ ላለመተያየት ሲደበቀኝ በኩራት ፈቅደሽ መርጠሽ ከእኔ ጋ የሆንሽ የእኔ መዓዚ ሕልሜን ልቤ ውስጥ ካስቀመጠው በረከቴ እኩል ባንቺም ተባርኬያለሁ። ባንቺ ምክንያት የምድር ቆይታዬ ከሕልሜ ያላስበለጥኩት የእኔን ያህል መርሄን ስለምትወጅልኝ መስሎኝ...

ጽሑፎቹ እንኳን ለጉዳዩ ባለቤት ለማንም መንገደኛ ትርጉም ይሰጣሉ፤ አጀንዳውን ከተቀመጠበት አኖርኩት፡፡

ጋሼ ታዋቂ፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ፣ መንግሥት እንቅስቃሴውን የሚያጠናው፣ መንግሥትም ሆነ መንግሥት የሚቃወሙ አካላት በዛቻ እና በንዋይ ሊደልሉት እንደሚሞክሩ በርካታ ጸሐፊያን በማስረጃ ከትበው አንብቤያለሁ፡፡ እንዲህ እየወደዳት፣ እንዲህ እየተመካባት፣ እንዲህ እየተንሰፈሰፈላት ሲቀጭባት፣ ሜዳ ላይ ሲሞትባት የገዳዩን ማንነት ከመላምት በቀር ገላጭ ሲጠፋ አረቄ ውስጥ ባትደበቅ ከማዘን ውጪ ማጠንከሪያ አቅም እና ሞራል ከየት በኩል ይወለዳል?

ብዙ ጋዜጠኞች፣ ታዋቂ ሰዎች ስለ ኩራባቸው ዓለሙ ቃለ መጠይቅ እንድትሰጥ ይለምኗታል። አንድም ቀን ግን እሽ ብላ አታውቅም። አንድ ዕለት ስለ ሌላ የባጥ የቆጡን እያወራሁ ሳለ ...

እኔ የምልሽ አታቲ ለምንድን ነው ግን ስለ ጋሼ ምስክርነት፣ እውነት እና የሕይወት ዘመን እንቅስቃሴው የማትናገሪው? ካንቺ በቀርስ ስለሱ ሊያወራ የሚችል ማን ይኖራል? አልኳት...

አታቲ አይኗን ቦዘዝ አድርጋ ጠረጴዛው ላይ ከተቀመጠው ትልቅ ጉርድ ፎቶ ላይ በትካዜ ተክላ

“ይሄውልሽ ዕድሌ ኩራባቸው ምስክርነት አያስፈልገውም። የራሱን ሐውልት ገንብቶ ነው ያለፈው፤ ስለ እሱ ከሥራዎቹ በላይ መናገር የሚቻለው አንድም የለም። ሥራዎቹን መመርመር እና ሥራዎቹን መሞገት ይችላሉ፤ ሕልሙን ጽፎ
አቋሙን ተንትኖ ታግሎ የተሰዋ ሕያው ነው፡፡ ከጻፈው ውጭ የምናገረው፣ ማለት ፈልጎ ያላለው አንድም እውነት የለውም። ከእኔ ጋ ያሳለፍነውን በየሜዳው፣ በየስፍራው ለማንም አላወራም፤ ይነፍስበታል፣ ይቀልብኛል፤ ቀስ እያልኩ እየተረኩ እያዋዛው፣ እያስታወስኩ ራሴ ጋ የማስቀምጠው የሕይወት ዶሴዬ ነው..."

አታቲ ትንሽ ስትቀማምስ ጀግና እንዳላገባ የምትመክረኝ ምክሯ አልሠራም። ከቢልልኝ ጋ ተፋቀርን፤ ቢልልኝ እውነት፣ ከስሜትም፣  ከፍቅርም ይበልጣል የሚል የዘመኑ የማይናወጥ ጀግና ነው።

አታቲ ሞቅ ባላት ቁጥር “ጀግና እንዳትወጂ” ብትለኝም ልቤ ግን ጀግና፣ ባለ ራዕይ፣ ትጉህ እያየ ስላደገ ጀግና ከማፍቀር የታደገው የለም።

ቢልልኝ ኩራባቸው ዓለሙ አሳዳጊ አባቴ እንደሆነ ሲያውቅ የተሰማው ሐሴት ልዩ ነበር። የሰው ማንነት፣ እውነት የተወሸቀው እያየ ባደገው የተበጃጀ ፍጡር ነው ስለሚል የደስታው ምክንያት አልጠፋኝም።

ቢልልኝን አንድ አርብ ዕለት አመሻሽ ላይ ከአታቲ ጋር አስተዋወቅኳቸው። በጋራ እየተጫወትን ሳለ ጨዋታችን ሀገር፤ ትግል፤ እውነት፤ ታሪክ ሆነ። አታቲ የቢልልኝ ሐተታ ምቾት የሰጣት አልመሰለኝም። ስትሰማው ቆየች እና ተቆርቆሪነትህ እና አቋምህ ዋጋ እንደሚያስከፍል ታውቃለህ አይደል? አለችው በፍጹም እናትነት በስስት እያየችው።

ቢልልኝ ትንሽ ዝም ካለ በኋላ እኔ እንደምጠራት “አታቲ" አላት ፊቷ ሐዘን እንደተላበሰ በቀጥልልኝ ዓይነት አየችው
"ክብር አይደለምን ለሚያማኑበት ጉዳይ ዋጋ መክፈል?” ኣላት። ትክዝ ብላ እኔንም እሱንም አፈራርቃ ካየችን በኋላ አቅም አልባነት ፊት እያሳየችን መርዶ እንደሰማ ሰው በእንባ ታጅባ “አዬ መረገሜ” አለች፡፡

🔘አድኀኖም ምትኩ🔘

#Share #like and #subscribe እያደረጋቹ።

👇Sebscribe

YouTube link👇
https://www.youtube.com/@atronose
40
#እንባ_አዳሽ_ነፍሶች

አብረውኝ ከሚሰሩት ለየት ይልብኛል፤ ግሬይ፣ አመድማ፣ ሽሮ ከለር ልብሶች ያዘወትራል። አይዘንጥም፣ ጸጉሩን ስለማይንከባከብ የብርድልብስ ብናኝ በተለይ ጠዋት ላይ ከጸጉሩ አይጠፋም። ጺሙን በቶሎ አያነሳውም፣ ከሰው ጋ አይተራረብም፣ ሰው ሲተረብም አይስቅም። ፖለቲካ ይከታተላል፣ አንባቢ ነው፤ ቅዱስ ዮሃንስ አፈወርቅን ይወደዋል፤ ጆን ሎክን ይተነትናል፤ አረቄ ነፍሱ ነው።

አንዳንድ ጠዋት የተመሳቀለ ፊት ይዞ ይመጣል። ፊቱ አልኮል ያመሳቀለው ይመስለኛል። ስለ ራሱ አያብራራም፣ ሰው እሱ ላይ ሰለሚይዘው አቋም አይጨንቀውም።

የሚረዳው የለም ብዬ ዋስ ጠበቃ ለመሆን እጋጋጣለሁ፣ ግን ነገሮችን ስለሚመረምር ለራሱ አያንስም።

ሲያወራ፣ ሲሰማ፣ ሐሳብ ሲሰጥ ጥድፍ ጥድፍ አይልም። የዋዛ አንቅስቃሴዎቹ ላይ እንኳን እመለከታለሁ። አስተውሎትን

ሰኞ ዕለት ያሳደገው፣ ያስተማረው አንድ ወንድሙ በመኪና አደጋ ሞተበት። የቢሮ ሰዎች ተሰባስበን ቀብር ላይ ተገኘን። ብሩክ ፍልስፍናው፣ መጀናተሉ ቀሰስ ማለቱ ከእሱ በኖ ጠፋ። መሬት እየተንከባለለ ሲያለቅስ ሳየው አንጀቴ ተንሰፈሰፈ። እንባዬ አካላቴን ሳላወናጭፍ፣ ድምጽ ሳላወጣ ወለል እያለ ወረደ። ብሩክ አቅም አልባነት ሲያጥመለምለው፣ ለብዙ ሰው አለኝታ የነበረውም ወንድሙ ተጀቡኖ ወደ ጉድጎድ ሲወረወር ከንቱነት በላኝ።

በነጋታው ጠዋት ከእነ ዱካኬ ከእንቅልፌ ነቃሁ። ተጣጥቤ፣ ቁርሴን በልቼ ከሥራ መልስ ብሩክ ጋ ለመሄድ ጥቁር ሻርፔን ቦርሳዬ ውስጥ ከትቼ ወደ ቢሮዬ ሄድኩ።

አይኔን አላመንኩትም፤ ብሩክ ወንበሩ ላይ ፋይል ከምሮ አንገቱን ደፍቶ ይሠራል። ሳየው ደነገጥኩ፤ በደመ ነፍሴ ብሩኬ ስለው ኮስተር እንዳለ በማያቀርብ አስተያየት እያየኝ "ሰላም ሊዲያ” አለኝ።

ሁላችንንም ፊት ነሳን። በሌሊት ሥራ ይገባል፣ አምሽቶ ይወጣል፣ ምሳ ብቻውን ይበላል። አይኑ አባብጦ እንባ ያሸበረው ፊት አይበታለሁ፤ ማንም እንዳያጽናናው መንገዱን ዘጋጋው። አለቃችን እንኳን በረታህ ብሎ ሲጀምር አዎ ይልና ከአጠገቡ እብስ ይላል፣ ወይ ደግሞ ወሬ ይቀይራል።

ወንድሙ ካለፈ በአስራ አራተኛው ቀን ላይ ብሩኬ ደህና ነህ? ግን ምነው እራቅከኝ? አልኩት።

"ትንሽ ቀን ነው የምፈልገው ደህና እሆናለሁ፤ ሁሉም ደህና ይሆናል" ብሎኝ ጭጭ አለ።

በቅጡ አንዳላጽናናህ እኮ መንገዱን ዘጋኸው፤ : ሰው በሚያስፈልግህ ጊዜ ነው ከሰው የራቅከው አልኩት። አየኝ፣ አጎነበሰ ቀስ ብሎ ቀና ብሎ እያየኝ ከትንሽ ዝምታ በኋላ...

“ይሄውልሽ ሊዱ ማጽናኛችን የጎደፈ ነው፤ አንዳንዱ ቤትሽ የሚመጣው ለወጉ ነው፤ አይኑ ላይ ምንም እንባ ሳይታይ ወንድሜ፣ ወንድሜ እያለ ድንኳን ውስጥ ይገባል። አጠገብሽ ይመጣና ምን አገኘው? ገጪው ተያዘን ወንድሜ፣ ሰላምተኛዬ፣ ጥሩ ሰው፣ መከታዬ ይላል። ሐኪም ቤት አልወሰዳችሁትም? ጥያቄ በጥያቄ። የሚያስቆጭ፣ ሐዘን የሚፈጥር ጥያቄ፣ የሚያጎላ ጥያቄ። እንዳልታዘበው፣ እንዳልቀየመው ሐዘንህን መጥቻለሁ ፊቶች፣ ፊታቸውን ለማሳየት የሚጋጋጡ ሰዎችን ጋቢ ለብሶ መታዘብ ሕመም ነው።

በጣም ከባድ ነው ሊዱ፤ ሁሉም የሚጽናናበት መንገድ ሊሆን ይችላል እኔ ግን አልቻልኩም፤ የአጽናኞቼን መንገድ የዘጋጋሁት ሆን ብዬ ነው። ለማጽናናት ስለጉዳዩ ማተት የግድ አይደለም እኮ፤ አብሮ መሆን በቂ ነው፤ ማቀፍ በቂ ነው። ጊዜ ኃያል ነው፤ የማያዶለዱመው ሕመም የለም።

ወንድሜ ጋሽዬ ለእኔ ብዙ ነበር። እሱ ነው ያሳደገኝ፤ የምምለው እንኳን በእሱ አይደል? ለቁም ነገር እንድደርሰ ያልሆነልኝ አልነበረም፤ ኃላፊነቱ ነበርኩ፤ የበኩር ልጄ ነው የሚለኝን ወንድሜን ነው ያጣሁት።

ጉዳዬ ከእግዜር ጋ ነው።

እሱ ነው የተመሳቀለውን እጦቴን በመልክ በመልኩ በእግዜርኛ የሚያበጃጅልኝ፤ እንጂማ በፍጡር ሊያውም ማብሸቅ በሚመስል ማጽናኛ አልድንም። ለዚህ ነው ከቀብር ጀምሮ ቤተክርስትያን የማድረው። ከአማኝ ጥቅማጥቅማችን አንደኛው ከአቅማችን በላይ የሆነ ሁነት ሲጋረጥብን እግዜርላይ ሙጥኝ ማለት አይደል? ከትናንት ዛሬ በደንብ እየበረታሁ ነው፤ የታመንኩት አምላክ እያጽናናኝ እያጸናኝም ነው።"

የብሩኬ አወራር፣ ሁኔታው፣ ሕመሙ አንጀቴን አላወሰው። አይኔ ላይ ያቀረረው እንባ አለመውረድ አልቻለም። አንድ ነገር ብቻ አልኩት

እግዜር ያበርታህ ወዳጄ።

🔘አድኀኖም ምትኩ🔘

#Share #like and #subscribe እያደረጋቹ።

👇Sebscribe

YouTube link👇
https://www.youtube.com/@atronose
👏1615😢3
#አርፋጅ

አንድ ሰፈር ነው ያደግነው፡፡ አንድ ዩኒቨርስቲ ተማርን። ብሩክ ፈታ ያለ ነው፣ ጨዋታ ያደምቃል፣ ጨዋታም ያውቃል። እሱ ካለ የሳቅ ድምጽ አይጠፋም። ስድስተኛ ክፍል አልፈልግህም ተብሎ የተላከለትን ደብዳቤ አባቱ አግቶበት
የመታውን ጠረባ፣ ለፍቺም ደርሰህልኛላ እያለ የሚጦልበውን ጡለባዎችን እየቀመመ ሲያጫውት አፉን ከፍቶ የማይስቅ አልነበረም።

ታላቅ ወንድሙ ላይ የሚሠራውን ተንኮል፣ የግድያ ሙከራ የሚመስሉ ድብደባዎችን ኮስተር ብሎ በፌዛም ፊቱ እያወጋ ያዝናናን ነበር። ግሬድ ሲሰቅልም፣ ሲሾቅም ማላገጡ የሚጠበቅ ነው። በዙሪያው የማንጠፋው ፍሬንዶቹ ላይ እንዳይደብረን አድርጎ ለጨዋታ ፐርፐዝ ብቻ ይቀልድብናል።

ብሩክ እንደ ጃካራንዳ ዛፍ በዙሪያው ሚያጅበው አይጠፋም፣ ሰው ይወደዋል። ከሰው ጋ እይጋጭም፣ መከባበር የማይደራደርበት ዋነኛ ፖሊሲው እንደሆነ በደንብ የሚቀርበው ሁሉ ያውቃል፣ የጠበቀ ወዳጅነት ያለን ደግሞ በይበልጥ እናውቃለን።

ብሩክ ለእኔ ወንድሜ ነው የማልለው ባልጀራነትን ማሳነስ ስለሚመስለኝ ነው። ብዙ ሳቅ እና ጭንቀቶችን ተጋርተናል። በድዬ ሳለሁ ለእኔ አግዞልኛል፣ እስከ ድክመቱ ተቀብየዋለሁ፤ ጓደኛዬ ነው፣ ምንም ሳይኖረን ጊዜ ብቻ እያለን ነው ነፍሳችን የተናበበው፤ የጓደኝነት ትርጉም መተንተን ሳንጀምር ነው የተወዳጀነው።

እኔ ታላቅ ወንድሜ የጀመረውን ቢዚነስ ተቀላቅዬ በሂደት ብዙ ሳንቲም ማግበስበስ ጀመርኩ። ብዙ ሀብት ባገኘሁ ቁጥር መፍጨርጨሬ ጠነከረ፣ ነገሮችን በውሎዬ ስለምመዝን እነጫነጫለሁ፣ ብሩክ ነገሮችን ከእሱ አንጻር ስለሚያይ መነጫነጬ አይገባውም።

ብሩክ ቀልደኝነቱ መፍዘዝ ጀመረና መገለጫው ያልሆነ ጨለምተኝነት ወረሰው። ምሬቱን ቀልቤን ሰብስቤ አሰላስዬ አላውቅም፣ መንገዱን ለመደልደል አልጣርኩም። ከእጮኛው ጋ የሚያጋጥመውን ግጭት በምሬት ሲነግረኝ ቀልቤን ሰብስቤ ከጊዜያዊ ስሜት የገዘፈ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም።

የድሃ ልጅ መሆኑ፣ አይዞህ የሚለው አለመኖሩን ሲጠቅስ አብሬው ከማሸብሸብ የዘለለ ጊዜ ሰጥቸው ምን ላግዘው? ከእኔ ምን ይጠበቃል? ብዬ ለአፍታ አሰላስዬ አላውቅም።

እድገት ላይ በመመሰጤ ያሉኝን በረከቶች ለማስተዋል አልተቻለኝም ነበር። ያሉንን እየጣልን የምናመጣው አዲስ ስኬት እንደምን የምንፈልገውን ደስታ ሊያመጣልን ይቻለው ይሆን??

ለሥራ ኔትወርክ የማይሰራበት ቦታ ከርሜ ስመጣ እንድንጠጣ፣ እንድንስቅ ደወልኩለት ግን ስልኩ ዝግ ነው። ደጋግሜ ደወልኩ፤ አሁንም ስልኩ ዝግ ነው። ስልክ ማጥፋት፣ ስልክ አለማንሳት፣ ለብቻው መሆን አዲስ ያመጣው ፋሽኑ መሆን ጀምሯል። ቤቱ ልሄድ ተነሳሁ።

ፀሐዩ ሀሩር ነው፤ ዘንድሮ ፀሐዩን ለማምለጥ እንደዝናብ መጠለል እና መሮጥ መጀመራችን አይቀርም። የድሮ ሰፈሬ ደረስኩ፣ የነ ብሩኬ ደጅ ላይ ድንኳን ተደኩኗል፤ ብሩኬ አያቱ ጠንካራ ሕመም እያንገላታቸው እንደሆነ ነገሮኝ ነበር።

አያቱ በሕይወቱ ደማቅ ስፍራ አላቸው፤ ይወዳቸዋል፡፡ እንደ ወንድሙ ነበር የሚያዋራቸው፣ እንደ ጓደኛቸው ነበር የሚያጫውቱት። ከልጅነት ጀምሮ የምናቀውን ሰው ማጣት ሕመሙ ብርቱ ነው። ድብርት እና ምሬት ሳይጣባው አያቱ ሳይተኙ ለመድረስ ነበር የሚሮጠው።

እርምጃዬን ቀስ እያደረኩ ወደ ድንኳኑ ስሄድ የሰፈራችን ለቀስተኞች አይን እኔ ላይ አረፈ፣ አጎነበስኩ። ቀስ ብዬ የድንኳኑ መግቢያ በር ላይ ያገኘሁት ወንበር ላይ ቁጭ አልኩ፣ በቀስታ ቀና ብዬ ብሩኬን በአይኔ ሳስሰው ወንበርተደርድሮ በተቀመጠ ፍራሽ ላይ የደከሙ አያቱን አየኋቸው፤ ፍጥጥ ብዬ እንዳየኋቸው አስታውሳለሁ።

ከአጠገባቸው እናቱን አየኋት፣ በጥሩ መንፈስ አላየችኝም፤ አይኔ ወደ ተሰቀለው ፎቶ ተምዘገዘገ። ከዛ ሰዓት በኋላ የሆነውን ብዙ አላስታውስም። ለቀበሌ መታወቂያ ብሎ አብረን ሄደን የተነሳነው የብሩኬ ፎቶ ተሰቅሏል። በጣም እንደጮህኩ አስታውሳለሁ፤ እናቱን ሂሩቴን እየወደቅኩ፣ እየተነሳሁ የሆነውን ለመጠየቅ ፍራሹ ጋ ለመሄድ መሞከሬንም አልረሳሁትም። የሆነውን ሁሉ ፡ አለማወቄ ተገለጸላቸው፡፡ ረጭ ያለው ለቅሶ ቤት ታወከ፤ ሁኔታዬ ያሳዘናቸው ሰዎች አብረውኝ ያለቀሱ ይመስለኛል።

አያቱን አንቄ ጋሽ በላይ ጓደኛዎት የት ሄደ፣ ብሩኬ የት ሄደ? አልኳቸው። በዛለ እጃቸው አቅፈውኝ በትኩስ እንባ ታጅበው እጁን በእጁ በላ አሉኝ። እግሬ አልጸና ያለ ይመስለኛል፤ ብዙ ሰዎች ያዙኝ፤ ክንዴን ክንዴን ብዬ ጮህኩኝ፤ ሰው ለካ እንዲህ ደካማ ነው፤ የቻልኩት መጮህ እና የሆነውን መካድ ነበር።

በቀን ብዛት ተበረታታሁ ያወራነውን ሳሰላስለው ኋላ መቅረት ሲንጠው እንደነበር ገባኝ። ጨለምተኝነቱ ለመኖር ያለውን ፍላጎት ቀድሞ እንደገደለበት ገባኝ። ለካስ ማስተዋል አቅቶኝ ነው እንጂ ሁሉም ነገሩ ይገባ ነበር። አብረን ብንሆንም ለካ ተለያይተን ነበር፤ ለካ እሱ ነበር ጓደኛዬ እንጂ እኔ ጓደኛው አልነበርኩም። አናቱ ላይ በፍጥነት የወረረውን ሽበት ከ"stress"፤ ከመብሰልሰል የተፈጠረ መሆኑን አልጠረጠርኩም ነበር።

ተሳክቶለታል የምባለው እኔ ነገሮች ሲጠሙብኝ፣ አንዳንድ ነገሮች ሲከፉብኝ ይቺ ዓለም እንደምትሰለቸኝ አውርቼው አላውቅም።

ራሴን ልገድለው እንደነበር ነግሬው አላውቅም። ሽራፊ ፈገግታ በሀሩር ፀሐይ ጤዛ እንደመፈለግ ሆኖብኝ ሳለ፣ የሞከርኩት ሙከራዎች ሲከሽፉ፣ ከሰው ሁሉ አነስኩኝ ስሜቴ ሲበላኝ፣ ብቻ መሆን ሲጨፍርብኝ፣ አለመፈለግ ስሜት ሲወዘውዘኝ፣ ያለኝን ነገር ሁሉ ያፈሰስኩበት ተስፋዬ ሲጠፋ፣ ሕልሜ ሰፍቶኝ ስንከላወስ፣ የምሸሸግበት ጥግ ሳጣ፣ በማምነው ሰው ስካድ፣ ዕድለቢስነት እንዳልጠራጠር አድርጎ ሲመሰክርብኝ ራሴን ልገለው ዳድቶኝ ነበር። መዳዳቴን እንዴት ድል እነደነሳሁት ሳልነግረው!

አምላኬ ጋር ሙጥኝ እያልኩ፤

አንዳንዴ በረከቶቼን ፈልፍዬ ለራሴ እየተረኩ፣

አንዳንደ ጭላንጭል ብርሃኔ ላይ ተመስጬ፣

ብሞት የምሰብራቸውን ሰዎች አዝኜላቸው።

አንዳንዴ ክችች ያልኩበትን ጉዳይ እያላላሁ፣ አንዳንዴ ግትርነቱን እየገሰጽኩ፣ አንዳንዴ ሆስፒታል ያሉ አካላቸው የማይታዘዝላቸው ነፍሶችን እየረዳሁ፣ አንዳንዴ እስረኞችን እየጠየቅኩ ነው ራሴ ላይ የራራሁት ሳልለው
ይሄ ትግሌ ለብሩኬ ትርጉም ሊሰጠው እንደሚችል ማሰብ አልተቻለኝም ነበር። የምንወዳቸውን ሰዎች ምን ያህል እንደምንወዳቸው ካለ እጦት እንዴት መረዳት ያቅተናል? ለራስ ሰው አለመድረስን ያህል አርፋጅነት የለም።

🔘አድኀኖም ምትኩ🔘

#Share #like and #subscribe እያደረጋቹ።

👇Sebscribe

YouTube link👇
https://www.youtube.com/@atronose
34👍11😢9
#እግዜር_አደራውን_ሲበላ

ግርግር ከማይወዱ ጓደኞቼ ዛብሎን አንደኛው "ነው። እይታዎቹ በወፍ በረር የተኮረጁ አይደሉም፤ ስለማያውቀው ነገር ከተወራ ይሰማል ረጋ ብሎ ስለሚያወራ፣ ስለሚያውቀው ነገር ብቻ ስለሚያወራ እያዳመጠ ስለሚያወራ፣ መናገር .. ሲጀምር የማይሰማው የለም።

ጨዋታው ብዙ ሰው ላይ ያለው እመነኝ፣ ቅዱስ ነኝ ዓይነት ስብከት የለበትም።

ክላስ አለው!!

አጠገቡ ያለ ሰው ስለማያውቀው ነገር ሲቀባጥር፣ ዛብሎን ደግሞ ስለጉዳዩ በደንብ እውቀት ካለው ለስለስ አድርጎ ቀባጣሪው የቀባጣሪነት ስሜትን ሳያሳድርበት ደርበብ ባለ መልኩ ሐሳቡ ላይ ብቻ አተኩሮ ሙግት ውስጥ ሳይገባ ስለሚያውቀው ነገር ይናገራል። እንደዚህ ዓይነት ግለሰብ ሰውዬው የበታችነት ሳይሰማው፣ አላዋቂነት ሳይታገለው የያዘውን መረጃ አልያም አቋም እንዲመረምር ያስችላል።

ዛብሎን ጺሜ አደገ፣ ጸጉሬ ተንጨባረረ ብሎ ጸጉር ቤት እንደማይሄድ የጸጉሩ መንጨባረር እና የጺሙ መንዥርገግ ምስክር ናቸው። ዘናጭ አይደለም ግን ንፁሕ ነው። ከሁሉ የሚገርመኝ ካላሳቀው አይስቅም። በጋራ ተሰብስበን ሁላችንም እየሳቅን በእርጋታ ሳቃችን እስክንጨርስ ጠብቆ በትንሽ ፈገገግታ አልገባኝም ብሎ ስለሳቅንበት ነገር ማብራሪያ ይጠይቃል፤ ተጨብጭቦለታል ብለን ለምናጨበጭብ ሰዎች አጀብ ነው ይሄ፡፡

ካፌ ውስጥ እንደተቀመጥን ዛብሎን አስተናጋጇን በምልክት ጠራትና መጥታ

'ምን ልታዘዝ'

"ተቆራጭ አምጭልኝ" አስናጋጇ ስትሄድ ጠብቄ

የገና ጾም አትጾምም እንዴ?

“አልጾምም!“

ለምን?

“እናቴ ስትሞት ነው ከመንፈሳዊ ሕይወት ጋር ያለኝ ቁርኝት የተፋታሁ፤ ተስፋ ቆረጥኩ፣ የምለፋበት ምክንያት አጣሁኝ። ድሮ ቤተክርስትያን ስሄድ ነጭ ሐበሻ ቀሚስ የለበሱ፣ ሹርባ የተሠሩ እናቶች ሳይ፣ ሥራ ስይዝ ለእናቴ እንዲህ እገዛለሁ እለው ነበር እግዚአብሔርን። ቆርበው ከቤተክርስትያን በር ላይ መኪና የሚጠብቃቸው እናቶችን ሳይ እኔ ለእናቴ እንዲህ እንደምንሆን ለእግዚአብሔር ፈገግ እያልኩ አጫውተው ነበር። ስማር እንቅልፌ እየመጣ እግሬን ውሃ ውስጥ ዘፍዝፌ የማጠናው ከእግዜር ጋር የተጨዋወትነውን ምኞቴን ለማሳካት ነበር። እሱ እኮ እሹ ታገኛላችሁ፣ አንኳኩ ይከፈትላችኋል ነው የሚለው እያልኩ።

ሱሰኛ ያልነበርኩት እናቴ ልጄ እኮ እንደዚህ ዓይነት ነገር አይወድም፤ የእኔ ልጅ እኮ ብላ እንድትጎርር ነበር። ሕልሜን ከእናቴ ጋ ብቻ ማቆራኘት አልነበረብኝም። ግን እኮ ወድጄ አይደለም፤ ቤተሰቦቿ አረገዝሽ ብለው ሲያባርሯት፣ አባትየው ሲክዳት፣ ምድረ በዳ ላይ ተነጥሎ እንደቀረ ሰው እኔን አገሯ፣ ዓለሟ አድርጋ የተዋደቀችልኝ ናት"

ፊቱ ቅዝቅዝ አለ... ትኩስ እንባ አይኑ ላይ ቅርርር ሲል አየሁ። ከዚህ በፊት አስተውየዋለሁ፤ ስለ አምላክ ሲወራ አስተያየት አይጎጥም። በቤተክርስቲያን ስናልፍ በእጃችን እያማተብን ከጉልበታችን ሸብረክ ስንል እሱ ግን ልክ መንገድ ላይ የምናውቀውን ሰው አግኝተን ሰላም ስንል ስለማያውቀው ብቻ እልፍ ብሎ እንደሚሄደው ልክ እንደሱ አልፎ ይሄዳል።

ውለታ የዋለለትን ሰው የእግዜር ስምን እያጠቀሰ ሲመርቀው አሜን አይልም። ተመጽዋች ምጽዋት ሲጠይቀን ከሌለን እኛ እግዜር ይስጥልን እንላለን ወደ እሱ ዞሮ ሲለምነው የለኝም ይላል።

እግዚአብሄሩን አኩርፎት እንደሆነ ካስተዋልኩ ቆየሁ። በዙሪያው የሚያፈቅረው የለም፤ አለማፍቀሩ ከፍቅር ሾልከው የሚመጡ ስጋት፣ ተስፋ እና ስስት የሚባሉትን ከውስጡ አሽሽቶለታል። አንድ ቀንም ለእግዜር ስሞታም፣ ውዳሴም ሲያቀርብ አይቼው አላውቅም። ዝም ብዬ ሳየው በለሆሳስ ብቻውን ከእግዚአብሄሩ ጋር የሚዋቀስ ነው የሚመስለኝ።

ሳየው በዝምታ እግዜሩን ለምን አደራኽን በላህ የሚለው ነው የሚመስለኝ!!!

🔘አድኀኖም ምትኩ🔘

#Share #like and #subscribe እያደረጋቹ።

👇Sebscribe

YouTube link👇
https://www.youtube.com/@atronose
21🤔7👍1
#ኀሰሳችን_ከሽፎ_እንጂ

ጥዑም ጊዜ ላይ ነበርን። ወይን እየተጎነጨን፣ እየተሳሳምን፣ ድንገት ሳላቅድ፣ ሳልቀምር፣ ሳላስብበት ከአንደበቴ የውስጤ እውነት አመለጠኝ፡፡

ትክ ብዬ ሳያት ፈገግ ብላ “እችን የመሰለች ልጅ ጠበስክኣ?" አለችኝ ወደ ራሷ እያመለከተች፤ በትንሹ ፈገግ አልኩ። ፈገግታዬን እንደ መስማማት ቆጥራ በሚያምር ፈገግታዋ እያየችኝ "እናትህማ መርቀውሃል" ስትለኝ ይሄኔ ነበር የልቤ እውነት ያመለጠኝ።

ታውቂያለሽ ግን አንቺ ሕልሜ እንዳልሆንሽ፤ የመጣሽበት መንገድ፣ ዕቅድሽ፣ መርሕሽ ከእኔ ጋ መች ይሄዳል? አልኳት።

ሽማግሌ ከላክሁኝ በኋላ፣ በጋራ ስለምንወልዳቸው ልጆቻች ስናወራ ከርመን እንዴት እንዲህ ይባላል? ሁሉ እውነት እንዴት ይወራል? የልብ እውነት ሁሉ ይዘረዘራል?! ትበሳጫለች ብዬ ነበር ግን ደግሞ የጠበኩትን የፊት መለዋወጥ አላየሁም። ረጋ እንዳለች፣ ፊቷ ሳይለዋወጥ ትክ ብላ አየችኝ፤ ቅፍፍፍ የሚል  ስሜት ዋጠኝ፤ ምን አለ አስማተኛ በሆንኩ እና እንዳልሰማች ማድረግ አልያም እንዳልተናገርኩ መሆን ብችል።

ቃላቱን እርግጥ አድርጋ

“ትክክል!! ጊዜው አሳዝኖን ነው አብረን የሆነው፤ አብረን ሆነን በስሱ ሌላ የፍለጋ ሙከራ ስላልተሳካልን ነው የምንጋባው። አንዲት ቀን 'Messenger ህን ከፍቼ አይቻለሁ፡፡ የምታወራቸውን እንስቶች ቀልብ ለመግዛት የምትሄድባቸውን መንገዶች፣ መሻፈዶች፣ ላጤ ነኝ ጨዋታዎች፣ ብልግናዎች ተመልክቻለሁ፤ ሁሉም ከእኔ ጋ አንድ ዓይነት ነበሩ። የማደርገውን ነበር የምታደርገው፤ ከፍቶኝ ነበር እንዳላኮርፍ፣ እንዳልጨቀጭቅህ፣ እንዳልጣላህ ካንተ አለመሻሌ አሸማቀቀኝ። የብዙ ሰዎች ትዳር እንዲህ እንደሆነ አይቻለሁ፤ ከገቡ በኋላ በልጆቻቸው ይጽናናሉ፤ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሚስትና እና ባላቸውን እየከሰሱ ኑሮን ይገፉታል።

ለዛ ነው እንከን የለሽ ትዳር የሚያስሱት ቆመው የሚቀሩት! በቆዩ ቁጥር መለኪያቸውን እየቀየሩ ካጣጣሉት፣ ከተጠየፉት የኑሮ ቀንበር ላይ ራሳቸውን ያገኙታል። ለዛ ነው እንደሚታረድ በግ ሁሉን እያወቅኩ ሽማግሌ ስትልክ፣ ቀለበት ስታጠልቅልኝ፣ የልቤን እውነት አፍኜ የምከተልህ።"

ሲዘበራረቅብኝ ይታወቅኛል። ግራ ገባኝ፤ የሕይወት አጋርን በዚህ ደረጃ አለማወቅ ምን ይባላል? እችን ልጅ ነገሮች በዚህ ደረጃ ይገባታል ብዬ አላሰብኩም። ሴት ልጅ ትታልልህልሀለች እንጂ አታታልላትም እኔ እንዲህ እንደሚሰማኝ እንጂ እሷ እንደዚህ እንደሚሰማት አላውቅም ነበር።

ለምን ታድያ አብረን እንሆናለን ሁለታችንም እንዲህ
ከተሰማን?

"እንሂድ"

ምን አልባት ጊዜያችን፤

ምን አልባት ዕድሜያችን አሳዝኖን?

ምን አልባትም በዙሪያችን ያለ ውትወታ?

ምን አልባት ዘራችንን ለመተካት ካለን ፍላጎት?

ምን አልባት መላመዳችን እንዳንለያይ አግቶን ይሆን?

ምን አልባት አንዳችን ለአንዳችን ካለን ውስጣዊ ስሜት ይሆን?

ምን አልባት በዙሪያችን ካሉት ሰዎች የበለጠ ስለምንዋደድ??

ምን አልባት በስሱ ሌላ ለማግኘት ያሰስነው ኀሰሳ ስላልተሳካ??

ሰው የልቡን ሁሉ አለማውጣቱ ይሆን ቁርኝታችንን
ያላሳደፈው? ባለጋራችንን አለማወቅ ጠቀሜታ ይኖረው ይሆን? አንዳንድ ዕውቀት ምቾት አይሰጥም። ዕውቀት ትካዜን ታበዛለች እንዲል መጽሐፉ፤ አንዳንድ ውይይቶች ሽንቁር ያበጃሉ። የጀመርኩትን ወይኔን በአንድ ትንፋሽ ወደ ጉሮሮዬ አንቆረቆርኩት።

እንደዚህ ዓይነት ሎጂክ ተዘባዝቦ ግንኙነት፣ ትዳር መመሥረት ይቻል ይሆን? እንዳለችው ፍርሀት ነው? እጦት ነው? መላመድ ነው? ምንድን ይሆን በትክክል ያጋመደን?

ምን አስቸኮለን? ምን አሸበረን? ይሄን እውነታ ከተዘራዘሩ በኋላ እንዴት ጎጆ ይቀለሳል? ልጅ ሳይመጣ፣ ንብረት ሳናፈራ፣ ኑሮ ሳይንጠን የግንኙነታችንን መዓዘን መገምገም እንዳለብን ነው የገባኝ። አሁን የምጎዳት ነገ ከምሰብራት አይበልጥም፤ ዛሬ የሚሰማኝ ሕመም ነገ ከሚጋረጥብኝ መከራ አይበልጥም።

ማሬዋ ሰው ውድ ፍጡር ነው። ችኮላችን ብልጣብልጥነታችን፣ በራሳችን ማስተዋል መንጠልጠላችን የእኛ የራሳችን የሆኑት ሰዎች ጋ አንድንሸዋወድ ያደርገናል። ጊዜ እንውሰድ፣ ተነጣጥለን ዙሪያችንን፣ መንገዳችንን እንመርምር፤ ብልግናችንን ይቅር እንበለው። የቆምንባቸውን ስፍራዎች እንቃኛቸው፣ ከፈጸምናቸው ጥፋቶች ጋ እንፋጠጥ፣ እናርማቸው፣ እናበጃጃቸው። ብቸኝነት አባብቶን፣ አቻ ግፊት ወትውቶን፣ መላመድ አሳስሮን፣ የቤተሰብ ግፊት ገፈታትሮን ኑሮ አይመሰረትም። የሁሉም ጓዳ እንዲህ ነው ተብሎ አዲስ ጎጆ አይበጅም፤ ሁሉም ሄዷል ተብሎ እንኳን በስሕተት መንገድ በትክክለኛ መንገድ መሄድ ተገቢ አይደለም።

ከመጣንበት መንገድ የምንሄድበት ሩቅ ነው። ራሳችንን ከእርስ በእርሳችን ነጣጥለን እናጢነው። የአሰተውሎት መንገድ ደግሞ አሜን ካልነው ባሻገር ያለውን እውነታ መጋፈጥን ይጨምራል።

ያኔ የውስጣችን እውነት ፍንትው ብሎ ይታየናል፤ ለውሳኔም ይረዳናል። ስሕተታችንን ለማረም ከፍርሀት ጋ መጋፈጥ የመጀመሪያው እርምጃ ነው።

ከዚህ ሁሉ መንገድ በኋላ መመለስ እንዳስፈራት ታስታውቃለች። እኔም የወጠንኩትን፣ የለመድኩትን፣ የወሰንኩትን ዳግም ለመመርመር እና ለመከለስ ሳስብ ደስስ የማይል የሚቀረዝዝ ስሜት ሲወረኝ እየተሰማኝ ነው።

🔘አድኀኖም ምትኩ🔘

#Share #like and #subscribe እያደረጋቹ።

👇Sebscribe

YouTube link👇
https://www.youtube.com/@atronose
23👍2
በየደቂቃው ከጭንቅላቴ የሚፈልቀውን ዝባዝንኬ ሳላስቀር፣ በአጠገቤ ውል ያለውን ሳይቀር ነበር የምተነፍስለት። እንዳልቆም አድርጎ ያፍረከረከኝ፤ ያሳለፍነውን፣ ያገዘፍኩትን ነገር አንድ ሳይቀር ነው አሳንሷት የሄደው፡፡ ትረካ የሌለው መለያየት፣ ውጣ ውረድ የሌለው ፍቺ፣ የማይተነፈስ ሕመም ለማይታይ ጠባሳ ይዳርጋል፡፡ እንዴት በዚህ መጠን ተራ ይሆናል? እንዴት እየተፍለቀለቅሁ የምተርከውን ትዝታዬን እንደዚህ ያባክነዋል?

እንዴት ጥሩ ምክንያት አይፈበርክም?

እንዴት አካሄዱን ወዝ አያላብሰውም?

በዚህ መጠን ተራ አድርጎኝ እንዴት ይሄዳል? ያውቅ የለ ማን እንዳሳደገኝ፤ ለክብሬ ለግንኙነታችን ያለኝን ቦታ እያወቀ።

እችን ብቻ ነበር የምናክለው?

አብረን ስንሆን የእኔ ነው ብዬ አይደል እርቃኔን የተንጎማለልኩት?

የነበረን ነገር ቢያይል አይደለ ድክመት እና ስጋቴን መግለጼ?

ያሳለፍነውን ውብ ጊዜያት ካለጥንቃቄ በአካሄዱ ተረማምዶበት ነው ያናወዘኝ፣ እንጂ'ማ መለያየት ተፈጥሯዊም አይደል? ነፍስስ ኵስጋ ይለይ የለ? መሄዱ አይደለም፣ አካሄዱ ነው መላቅጡ የጠፋ ዱካክ ውስጥ የዘፈቀኝ።

አወዳደቃችን ውስጥ የጠያችን ግዝፈት እና ተራነት አሻራ በጉልህ አለ፡፡ ምን አለ አለሳልሶ ቢጥለኝ? ምን አለ ሲተወኝ ይሉኝታ ቢስ ባይሆን፡፡ አብረን በነበረን ጊዜ እንደምወደው እያንዳንዱ ዳናዬ ምስክር ነበር። ሰው ለሚወደው አይደለም ላሸነፈው ጠላቱ እንኳ ይራራ የለ?

ምን አለ ራርቶልኝ ቢሆን...

ምን አልባት እኮ የእኔ ብቻዬን የመሆን ፍርሀት ሲያርደኝ መለማመጤን አይቶ ነው ለእኔ ያለው ስሜቱ የተከለለበት፤ ምን አልባት ከእኔ የተሻለ ሰው አግኝቶ በእጁ እስኪያረጋት ወረት አውሮት ነው።

ምን አልባት እንዲህ መሙለጭለጭ ማንነቱ ይሆን ይሆናል። እሱ እንዳልሄድበት ከመጣው መንገድ በላይ እኔስ አልሄድኩም? ለእናቴስ የጀመርኩትን የደበቅኋት፣ የማትወደውን የሆንኩት ነገ ስነግራት አታፍርብኝም ብዬ አይደል? ከራስ ሰው ጋ መንዘላዘል ትዝታውም ሁኔታውም ይጣፍጣል ብዬ አይደል ከእናቴ የዘወትር ስጋት ራሴን ጥዬ ያገኘሁት?

ይሂድ! መሄዱ አይደለም ያጎሳቆለኝ!

ይሄ ማለቂያ የሌለው የምን አልባት ጉዞ ነው ከሰውነት ተራ ያወጣኝ። ምን አልባት ቃል ገድፌ የማይወደውን ብዬ፣ ወይ ምን አልባት ያልዋልኩበትን ነግረውት ይሆን? ወይ የሆንኩትን አገዛዝፈው አሻክረውት ይሆን? ይሄ እና ሌሎች የምን አልባት መላምቴ ነው ጭንቅላቴን ያጣበበው፤ እንዲህ እንደባተልኩ አልቀርም፤ እረሳዋለሁ። ያኔ እዚህ የዘራውን እዛ ሲያጭድ መሰስ እያለ ይመጣል፤ ያኔ የእኔን የምን አልባት የመላምት ችንካርን ይቀምሰዋል።"

ተሾመ ረጋ ብሎ ነበር የሚመለከተኝ። ሶልያና ያለችውን ሳነብ አንዱም ቃል አልለሰለሰኝም። ልቤን የጥፋተኝነት ስሜት ሸቀሸቀኝ። እያነበብኩ እንባዬ ሲንከባለል ተሾመ ተረጋግቶ ከመቀመጥ በቀር ምንም አላደረገም። ስቃይህ ከስቃይዋ አይበልጥም ብሎ ይሆናል።

ሶልያና ሕመሟን ከመቼ ጀምሮ ነው እንዲህ ለሰው ማጋራት የጀመረችው? አንዳንድ በደል የሌለንን ማንነት እና ባሕሪ ይወልዳል ማለት ነው።

አለሌ ብሆንም ስንቴ እየወደድኩ ተትቻለሁ፤ እየለመንኩ ተረግጫለሁ፤ ከእኔ የተሻለ ጋ ሄዳለች ብዬ ናፍቆቴን ፊት ነስቻለሁ። ጭር ያለ ስፍራ ተሸጉጬ አልቅሻለሁ። በሌላ አሳብቤ ተነጫንጫለሁ። ስንት ጓደኛ ሽምግልና ልኬያለሁ፤ የኔ ያድርጋት ብዬ ጸልያለሁ፤ አለመፈለጌን ለመርታት አነቃቂ ንግግር ሰምቻለሁ፤ ሴት እንዲህ ነች ብዬ ተቦትርፌያለሁ። ጥላኝ ማን ጋ እንደሄደች እያሰብኩ አርሬያለሁ።

ቃሏን እያጣቀስኩ ከስሻለሁ፤ ናፍቄ ረግሜያታለሁ። ይሄ እንዲህ ሆኖ ሳለ የሚወዱትን በገዛ ፍቃድ እንደመተው ያለ ሕመም ግን የትም የለም!

🔘አድኀኖም ምትኩ🔘

#Share #like and #subscribe እያደረጋቹ።

👇Sebscribe

YouTube link👇
https://www.youtube.com/@atronose
😢135
#አንዲት_ዕድሜ_ለስንት_ትሆናለች

በጨዋታችን መሀል "ባል ፈልግልኝ" አለችኝ ምን ዓይነት? አልኳት።

“ጥሩ ፀባይ ካለው ይበቃኛል።" የምሯን እንደሆነ ሁለ ነገሯ ይናገራል። ጉጉቷ አንጀቴን በላው።

ፍቅረኛ ኖሮሽ ያውቃል? አልኳት።

ጥያቄውን ለማለስለስ ስታገል በደረቁ ወጣብኝ።

“ዛሬ ነገ እያለ ሕልሙ ላይ ተመስጦ ድክመቴን እያጎላ፣ እያሳጣ ከዛሬ ነገ እንጋባለን እያለ ቀኔን ዕድሜዬን በልቶ ተልካሻ ምክንያቶችን ጠቃቅሶ ተለየኝ። አሁን ሌላ ከእኔ በአስር ዓመት የምታንስ ጉብል አግብቶ ወልዶ ይኖራል"

ምናለ ...

ካልወደድካት፣ ካላገባሃት ብትተዋት፤ ቀኗን ባታኝከው! ውበቷ ሳይደበዝዝ፣ የከጀለችውን አማርጣ በጊዜዋ ታግባ፡፡ ጊዜ ለሴት ልጅ ከወንድ ልጅ የበለጠ ትርጉም አለው።

🔘አድኀኖም ምትኩ🔘

#Share #like and #subscribe እያደረጋቹ።

👇Sebscribe

YouTube link👇
https://www.youtube.com/@atronose
👍103🥰1