አትሮኖስ
286K subscribers
120 photos
3 videos
41 files
567 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#ቋጠሮ_ሲፈታ


#ክፍል_አንድ


#ድርሰት_በዘሪሁን_ገመቹ
///

አለም የሆቴሉን የተወሰነ ክፍል አገልግሎት ዝርዝር የሚያሳየውን ካርድ አንስታ ተመለከተች። የአርብ ምሽት የአካባቢው ዘመናዊና ባህላዊ ባንድ በጥምረት ከምሽቱ አንድ ሰዓት እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ የሙዚቃ ድግስ እና ትርኢት ያሳያሉ።
ክፍል 125 ተከራይታ ጓዟን አሳረፈችና ልብሷን መቀያየርና እራሷን ማስዋብ ጀመረች፡፡ የመዋቢያ እቃዎቾን ከያዘው ሻንጣ ግርጌ ላይ የጥፍር መቁረጫ  አገኘች። ጥፍሯን ከሞረደች በኃላ አለባበሷን እና ጠቅላላ አቋሟን ለማየት መስታወት ፊት በመቆም ለመጨረሻ ጊዜ እራሷን ተመለከተች...።

በምትገናኛቸው ሰዎች ላይ የመጀመሪያ አስደናቂ የስሜት ትስስር ለመፍጠር ትፈልጋለች። ማንነቷን ስትነግራቸው በጣም እንደሚገረሙ እርግጠኛ ነች፣ ነገር ግን የበለጠ  ጠንካራ  ተጽእኖ  መፍጠር  ፈልጋለች።ከዚህ  ቀደም  ከሚያውቋት  ሴት ጋር እንደሚያነፃፅሯት ጥርጥር የለውም። እሷ ያንን መከላከል አትችልም፤አትፈልግምም፡፡. እሷን በትክክል መመዘንና መገምገም ከቻሉ እርግጠኛ ነች ሰሎሜ ጎይቶምን ለማስታወስ ይገደዳሉ ።የምትለብሰውን በጥንቃቄ መርጣለች። ሁሉም መዋቢያዎችና ጌጣጌጦች በተገቢው ልኬትና መጠን ተጠቅማለች፡፡በዛም የተነሳ በጣም ጥሩ የሚባል የተለየ እይታ እና ልዩ አይነት ውበት እንደተላበሰች ተሰምቷታል ። ሴትነቷን በጥበብ አጉልቶ የሚያሳይ ልዩ አይነት ብርሀን የሚንቦገቦግባት የውበት መቅረዝ ነው የምትመስለው፡፡

ግቧ መጀመሪያ እነሱን ማስደነቅ ነበር፣ እዚህ ወደ ሻሸመኔ በመምጣቷ እንዲገረሙ ብቻ ሳይሆን በዛው ልክም እንዲደነግጡ ነው የምትፈልገው።ከመጣችበት የሀገሪቱ ዋና ከተማ አዲስአበባ ጋር ሲነፃፀር ሻሸመኔ የአንድ ክፍለከተማን ያህል እንኳን ስፋት የሌላት ከተማ ነች፡፡ግን ደግሞ በሀገሪቱ ካሉ ማንኛውም ከተሞች የበለጠ ፤ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚደረግባት…በየቀኑ በሚሊዬን የሚቆጠሩ ሰዎች ገብተው የሚወጡባት በጣም ደማቅ ከተማ ነች፡፡እና አሁን ፊት ፊት የምትጋፈጣቸው ሰዎች የዚህ ከተማ የጡት አባት ተደርገው የሚታዩ….ናቸው፡፡

አለም ያሰበችው ስራ በስኬት ካጠናቀቀች በሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሀን ዜናዎችን በዋናነት የሚቆጣጠር ርዕሰ አንቀፅ እንደሚሆን እርግጠኛ ነች።ለበርካታ ደቂቆች መኝታ ክፍሏ ባለው መስታወት ፊት እየተሸከረከረች መልኳን ሆነ ጠቅላላ ቁመናዋን ደጋግማ ካየች በኃላ ሁለ ነገሯ እንከን ሊወጣለት እንደማይችል በመደምደም የእጅ ቦርሳዋን ትከሻዋ ላይ አንጠልጥላ ፣ የፍይል መያዣ ፎልደሯን አነሳችና እና የክፍል ቁልፍ እንደያዘች እርግጠኛ ሆና  ወጣች፡፡  የክፍሉን  በር  ዘጋችው።  የሆቴሉን  ህንፃ  ለቃ  ወጣችና ቀጥታ ወደመኪናዋ በመግባት መሃል ከተማውን እየሰነጠቀች ወደቀጠሮ ቦታ መንዳት ጀመረች፡፡ይሄንን ስብሰባ ያዘጋጀላት የዞኑ ዋና አቃቢ ህግ ነው፣ያንንም ስላደረገላት ለእሱ ታላቅ ምስጋና አላት፡፡ የትምህርት ቤት መለቀቂያ ሰዓት ስለሆነና ..አስፓልቱን በሰዎችና በተማሪዎች ስለተጨናነቀ እንድልቧ በፈለገችው ፍጥነት ለመንዳት ከባድ ሆኗባት ነበር፡፡

አለም ወደእዚህች ውብ ከተማ የመጣችው ለጉብኝት አይደለም፡፡ወይንም ዓላማዋን ከግብ እስክታደርስ ድረስ በእንግድነት አይደለም፡፡የከተማዋ ምክትል አቃቢ ህግ ሆና በመመደቧ ምክንያት ነው የመጣችው፡፡የትምህርት ዝግጅቷን እና ብቃቷን በማየት ይህን ሹመት የተሰጣት የአካባቢውን ህብረተሰብ ፍትህ እንዲያገኝ እንድታግዝ ነው፡፡ የእሷ ተልእኮ ግን የተለየ ነው፡፡የራሷ የሆነ አላማ እና ፍላጎት ባይኖራት ኖሮ በሞያዋ ለመስራትና ለማገልገል ከአደገችበት እና እድሜዋን ሙሉ ካሳለፈችባት አዲስአበባ እግሯን አታነሳም ነበር፡፡ የእሷ ተልእኮ እና ዓላም ለህብረተሰቡ ምንም ረብ እንደሌለው ስታስብ ትፀፀታለች። እሷ ለምን ወደእዚህ እንደመጣች ባስታወሰች ጊዜ የሚሰማትን የጥፋተኝነት ስሜት ነው፤ግን ደግሞ ምርጫ የላትም፡፡
በህይወቷ ውስጥ ወደዚህ ደረጃ እንድትደርስ ገፊ ምክንያት የሆናትን ጉዳይ ለአንድ ሰከንድ እንኳን ከረሳች እና ችላ ካለች ራሷን መቼም ይቅር ለማለት አትችልም፡፡ አካባቢው ስትደርስ ወደቀኝ ታጠፈችና ወደመዘጋጃ የሚወስደውን ጠባብ የአስፓልት መንገድ ተያያዘችው፡፡መዘጋጃ ጽ/ቤት ከመድረሷ በፊት አሁንም ወደቀኝ ታጠፈችና ከቀበሌ ጽ/ቤት ጎን ካለው የፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ መኪናዋን አስገባችና ምቹ ቦታ ፈልጋ በማቆም
… ሞተሩን አጥፍታ ቦርሳዋንና የፋይል ፎልደሯና ይዛ ወረደች፡፡ በግቢው ውስጥ ያሉ የቢሮ ሰራተኞች ሆኑ የባለጉዳይ አይኖች ሁሉ እሷ ላይ ሲንከራተት ይታወቃታል…ብዙም ትኩረት ያልሰጠቻችው በማስመሰል ወደውስጥ ገባች፡፡

የፍርድ ቤቱን በር አልፋ ወደውስጥ ገባች፡፡ የተላላጠ ቀለምና የተፋፋቀ ግድግዳ እያየች ኮሪደሩን አቋርጣ ወደአንድ ክፍል ገባች፡፡
የፍርድ ቤቱ እንግዳ ተቀባይ የተለየ አይነት ሽቶ ስለሸተተው በደስታ ካቀረቀረበት ቀና አለ
…ቆንጆ መልክና ማራኪ አለባበስ የለበሰች ውብ ሴት ወደእሱ ስትመጣ ተመለከተ..ለሴቶች ስስ ልብ ያለው ወጣት ፀሀፊ በተቀመጠበት ተቁነጠነጠ፡፡

….አለም ወደፀሀፊው እየተራመደች በጎሪጥ ቀጣዩን ቢሮ በጉጉት ተመለከተች።

ስሩ ደረሰችና ‹‹ጤና ይስጥልኝ››አለችው፡፡

‹‹አቤት የእኔ እመቤት ….እንዴት ነሽ….?ይሄንን የመሰለ ውበት ይዘሽ መቼስ ተከሰሽ አይሆንም ወደዚህ የመጣሽው?››አላት፡፡

‹‹አረ በፍፅም››ስትል መለሰችለት፡፡

‹‹እና ከሰሽ ነው?››

ስለመቅለብለብ እያሰበች ‹‹እንደዛም አይደለም››ስትል መለሰችለት፡፡

‹‹እና….እኔን ፈልገሽ ብቻ እንዳይሆን?››

ከንግግግሩ በላይ ጉንጭ ውስጥ እያላመጠ ያለው ማስቲካ ሲታኘክ የሚያሰማው ድምፅ ምቾት ነሳት።ቢሆንም ፈገግ አለችለትና ሌላ ነገር ለመናገር እየተቅለበለበ እያለ፡፡"እኔ ከዞኑ አቃቢ ህግ ቢሮ ነው የመጣሁት። ዋና አቃቢ ህጉ ክቡር ግርማ ጠያቂነት ክብሩ ዳኛው የጠሩት ስብሰባ ነበር ››

ፈጎ የነበረው ፊቱ ሲኮሳተር እና ልቅ የነበረው ንግግሩ ሲሰበሰብ ታወቃት….

"ከአቃቢ ህግ ቢሮ ሰው እንደሚልኩ ተነግሮኝ ነበር…ግን ተወክሎ የሚመጣው ሰው ወንድ ይሆናል ብለን ነበር የጠበቅነው"አላት፡፡

"እንደምታየው እኔ ነኝ የመጣሁት…ምነው የክብሩ ግርማ ምክትል መሆኔ አላሳመነህም?ነው ወይስ አላስደሰተህም?፡፡››ሰውዬው ሴት አውል ከመሆኑም በተጨማሪ የወንድ ትምክት እንዳለበት ተረዳች፡፡እናም አበሳጫት፡፡

ከተቀመጠበት  አሻግሮ  ጉልበቷ  ጋር  የቀረውን  አጭር  ቀሚሷን  እየተመለከተ…"ደህና
..በቀጠሮ ሰዓት ነው የተገኘሽው። "ስሜ ቶሌራ ይባላል። ቡና ትፈልጊያለሽ? ››አላት ፡ የእሱን ግብዣ ችላ ብላ "የተጠሩት ሁሉም እንግዶች መጥተዋል?"
ከእሱ መልስ ከመስማቷ በፊት ከተዘጋው በር የፈነዳ ተንከትካች የወንዷች ሳቅ ተሰማ ።

‹‹አዎ…ሁሉም ተገኝተዋል!!››

‹‹ለቡናው አመሰግናለው….መግባት አለብኝ ››አለችና ቦታውን ለቃ ወደክፍሉ ተራመደች…አለም በህይወቷ ውስጥ በጣም ወሳኝ ለሆነው ስብሰባ ራሷን አበርትታ ወደ ቢሮ ተጠጋች።በስሱ ስታንኳኳ ሳቁ ተቋረጠና ፀጥታ ሰፈነ፡፡ገፋ አድርጋ አንገቷን አስቀድማ ወደውስጥ ገባች ፡፡በክፍሉ ውስጥ ያሉት ወንዶች ሌላ ወንድ ሲጠብቁ እንደነበረ ከተረጋጋ መንፈሳቸው በግልፅ መረዳት ችላ ነበር። በራፉን ተሻግራ ወደውስጥ በገባች ቅጽበት በራፉ ከኃላዋ ሲዘጋ ተሰማት፡፡.የአራት ሰዎች ጥንድ ስምንት አይኖች እሷ ላይ ተተከሉ….በሁሉም ላይ ተመሳሳይ አይነት ግራ የመጋባት እና የመደነቅ ስሜት አነበበች…የፈለገችውም እንደዛ እንዲሆን ነው፡፡
57👍5