የኡስታዝ አቡ ሀይደር ትምህርቶች ስብስብ
17.3K subscribers
306 photos
106 videos
47 files
801 links
ኡስታዝ አቡ ሀይደር በፌስቡክ ያስተማራቸው የኦዲዮ የጹሁፍ እና የቪዲዮ ትምህርቶች ተሰባስበው የሚገኙበት ቻናል ነው።
Download Telegram
ኢስላማዊ ሰላምታና ስርአቱ!

በአቡ ሀይደር

በአላህ ሥም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምሥጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን(አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

1ኛ/ ከጌታ አላህ መለኮታዊ ሥሞች ውስጥ አንዱ "አስ-ሰላም" የሚለው ነው፡፡ ትርጉሙም የሰላም ባለቤት እንዲሁም ከነውር (ከእንከን) የጸዳ ማለት ነው፡፡ ጌታ አላህ የሰላም ምንጭ በመኾኑ ‹‹አስ-ሰላም›› ይባላል፡፡ ለአማኝ ባሪያዎቹ ሰላምን የሚለግስ እሱ ብቻ ነውና፡፡ ጌታ አላህ የሰላም ባለቤት በመኾኑ ወደ ሰላም ሀገር (ጀነት) ይጣራል፡፡ ለአማኝ ባሪያዎቹም የሰላምን ሀገር አዘጋጅቶላቸዋል፡፡
"እርሱ አላህ ነው፡፡ ያ ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለ፣ ንጉሡ ከጉድለት ሁሉ የጠራው፣ #የሰላም ባለቤቱ፣ ጸጥታን ሰጪው፣ ባሮቹን ጠባቂው፣ አሸናፊው፣ ኀያሉ፣ ኩሩው ነው፡፡" (ሱረቱል ሐሽር 59፡23)፡፡
"አላህም ወደ #ሰላም አገር ይጠራል፡፡ የሚሻውንም ሰው ወደ ቀጥተኛው መንገድ ይመራል፡፡" (ሱረቱ ዩኑስ 10፡25)፡፡
"ለእነርሱ በጌታቸው ዘንድ #የሰላም አገር አላቸው፡፡ እርሱም (ጌታህ) ይሠሩት በነበሩት ምክንያት ረዳታቸው ነው፡፡" (ሱረቱል አንዓም 6፡127)፡፡
ሠውባን (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡- "የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሶላታቸውን ሲያጠናቅቁ፡ ሶስት ጊዜ ‹አስተግፊሩላህ› ከዛም ‹‹አልላሁመ አንተ-ስ-ሰላም፣ ወሚንከ-ስ-ሰላም፣ ተባረክተ ዘል-ጀላሊ ወል-ኢክራም›› ይሉ ነበር" (ሙስሊም 1362)፡፡ ትርጉሙም፡- አምላኬ ሆይ! አንተ ራስህ ሰላም ነህ! ሰላምም የሚገኘው ካንተው ዘንድ ነው፡፡ የእልቅናና የክብር ባለቤት የኾንከው ክብርህ ከፍ አለ (ላቀ) ማለት ነው፡፡

2ኛ/ ‹‹አሰላሙ ዐለይኩም ወራሕመቱላሂ ወበረካቱሁ›› ማለት፡- የአላህ ሰላም፣ እዝነቱና በረከቱ በናንተ ላይ ይስፈን ማለት ነው፡፡ በሰላምታ ወቅት አንዱ ለሌላው የአላህን ሰላምና እዝነት እንዲሁም በረከት እንዲሰፍንበት ከመመኘት የበለጠ ምንም አይነት ሰላምታ የለም፡፡ የሰላምታዎች ሁሉ ቁንጮ፣ ዓለም-አቀፋዊ የሰላምታ መግባቢያ የኾነ ነገር ቢኖር ይኸው ‹‹አሰላሙ-ዐለይኩም›› የሚለው ሰላምታ ብቻ ነው፡፡

3ኛ/ ‹‹አሰላሙ ዐለይኩም ወራሕመቱላሂ ወበረካቱሁ›› የሚለው ኢስላማዊ ሰላምታ፡ ከመጀመሪያው አባታችን ከአደም (ዐለይሂ-ሰላም) ዘመን ጀምሮ የነበረ ሰላምታ ነው፡፡ ጌታ አላህ አደምን (ዐለይሂ-ሰላም) ከፈጠረው በኋላ መላእክት ዘንድ በመሄድ ሰላምታን ያቀርብላቸው ዘንድ፡ እነሱም የሚመልሱለትን ምላሽ እንዲሰማና ይህም የሱና የዘሮቹ የመከባበሪያ ሰላምታ እንደሚኾን በመንገር አዘዘው፡፡ እሱም ‹‹አሰላሙ-ዐለይኩም›› በማለት ሰላምታን አቀረበላቸው፡፡ እነሱም ‹‹አስ-ሰላሙ ዐለይከ ወራሕመቱላህ›› በማለት ጨምረው መለሱለት፡፡ (ቡኻሪይ 6227፣ ሙስሊም 7342)፡፡
ይህ ኢስላማዊ የመከባበሪያ ሰላምታ በዚህ ምድር ብቻ ሳይኾን፡ በመጪው ዓለም በአኼራ የጀነት ሰዎች የመከባበሪያ ሰላምታ ነው፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
"በእርሷም ውስጥ ጸሎታቸው ጌታችን ሆይ! ጥራት ይገባህ (ማለት) ነው፡፡ በእርሷ ውስጥ መከባበሪያቸውም ሰላም መባባል ነው፤ የመጨረሻ ጸሎታቸውም ምስጋና ለዓለማት ጌታ ይሁን (ማለት) ነው፡፡" (ሱረቱ ዩኑስ 10፡10)፡፡
"እነዚያም ያመኑና መልካም ሥራዎችን የሠሩ ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲኾኑ በጌታቸው ፈቃድ እንዲገቡ ይደረጋሉ፡፡ በውስጣቸው መከባበሪያቸው ሰላም (ለእናንተ ይኹን መባባል) ነው፡፡" (ሱረቱ ኢብራሂም 14፡23)፡፡

4ኛ/ አንድ ሙስሊም በሌላው ሙስሊም ላይ ካለው ኢስላማዊ መብት አንዱ ‹ሰላምታ› ነው፡፡ ሙስሊሞች በተገናኙ ቁጥር ‹አሰላሙ ዐለይኩም› የሚለውን ኢስላማዊ ሰላምታ መለዋወጥ አለባቸው፡፡ ቅድሚያ ሰላምታውን መጀመሩ ሱንና ቢኾንም፡ ሰላምታ የቀረበለት ሰው ግን ምላሽ መስጠቱ ግዳጅ ነው፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
"#በሰላምታ በተከበራችሁም ጊዜ ከእርሷ ይበልጥ ባማረ (ሰላምታ) አክብሩ፡፡ ወይም (እርሷኑ) መልሷት፡፡ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ተቆጣጣሪ ነውና፡፡" (ሱረቱ-ኒሳእ 4፡86)፡፡
ከአቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደተላለፈው የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- "ሙስሊም በሌላው ሙስሊም ላይ ስድስት መብቶች አሉት፡፡ ሶሓቦችም (ረዲየላሁ ዐንሁም) ‹‹ምንድናቸው እነዚህ መብቶች?›› ሲሉ፡ እሳቸውም፡- ‹‹ስታገኘው #ሰላምታን ልታቀርብለት፣ ሲጠራህ ጥርሪውን አክብረህ ልትገኝ፣ ምክርን ከፈለገ ልትመክረው፣ አስነጥሶ ጌታውን ካመሰገነ፡ የርሐሙከላህ ልትለው፣ ከታመመ ልትጎበኘው፣ ከሞተ ደግሞ ልትቀብረው›› በማለት መለሱላቸው" (ሙስሊም 5778)፡፡
ከዐብዱላህ ኢብኑ መስዑድ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደተላለፈው የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ አለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- "‹አስ-ሰላም› ከአላህ ሥሞች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ በምድር ላይ ሰዎች ይከባበሩበት ዘንድ አኖረው፡፡ እናንተም በመሀከላችሁ #ሰላም! በመባባል አሰራጩት፡፡ አንድ ሙስሊም በሰዎች በኩል ሲያልፍ፡ ኢስላማዊ ሰላምታን አቅርቦላቸው እነሱም ምላሽን ከሰጡት፡ እሱ ሰላምታውን ጀማሪ በመኾን ስላስታወሳቸው፡ በነሱ ላይ አንድ ብልጫ ይኖረዋል፡፡ እነሱ ምላሹን ባይሰጡት ደግሞ ከነሱ የተሸሉ ንጹሀን መላእክት ይመልሱለታልና" (ሙስነድ አል-በዝዛር 1771፣ ሶሒሑል-ጃሚዕ 3697፣ ሶሒሑ-ተርጊብ ወት-ተርሂብ 2705)፡፡
ከአቢ ሰዒድ አል-ኹድሪይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደተላለፈው የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- "በመንገድ ላይ መቀመጥን አደራችሁ ተጠንቀቁ!፡፡ ሶሓቦችም (ረዲየላሁ ዐንሁም) ‹‹የምንጨዋወትበት መሰባሰቢያችን ነውና ከመቀመጥማ ምንም ቅሮት የለንም›› አሉ፡፡ መልክተኛውም፡- ‹‹መሰባሰብን እንጂ እምቢ ካላችሁማ፡ እንግዲያውስ የመንገድን ሐቅ ጠብቁ!›› አሏቸው፡፡ እነሱም ‹‹የመንገድ ሐቅ ምንድነው?›› ብለው ሲጠይቁ፡ የአላህ መልክተኛም፡- ‹‹አይናችሁን መስበር፣ ሰውን አለማስቸገር፣ #ሰላምታን መመለስ፣ እንቅፋት ነገርን ከመንገዱ ማስወገድ፣ ሰዎችን በመልካም ማዘዝና ከመጥፎ መከልከል ነው›› በማለት መለሱላቸው" (ቡኻሪይ 2465)፡፡

5ኛ/ ኢስላማዊ ሰላምታን መለዋወጥ፡ ለጀማሪውም ኾነ ለመላሹ ከአሥር ጀምሮ እስከ ሰላሳ ሐሰናት (አጅርን) ያስገኛል፡፡ በአላህ ቸርነት ጀነት ለመግባትም ሰበብ ይኾናል፡፡ በምቀኝነትና በጥላቻ በሽታ ለተጠቃ ሰውም ፍቱን መድኃኒት ይኾነዋል፡፡
ከአቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደተላለፈው የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡-"ነፍሴ በእጁ በኾነችው ጌታ ይሁንብኝ! ጀነትን እስክታምኑ ድረስ አትገቡም!፣ እስካልተዋደዳችሁ ድረስም አታምኑም!፡፡ ከተገበራችሁት ሊያዋድዳችሁ የሚችል ነገርን አላመላክታችሁምን? በመሐከላችሁ #ሰላምታን አብዙ" (ሙስሊም 203፣ አቡ ዳዉድ 5195፣ ኢብኑ ማጀህ 71፣ ቲርሚዚይ 2699፣ ሶሒሕ ኢብኑ-ሒብባን 236)፡፡
ከዐብዱላህ ኢብኑ-ሰላም (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደተላለፈው እንዲህ አለ፡- "የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) መዲና እንደገቡ መጀመሪያ የተናገሩት ‹‹እናንተ ሰዎች ሆይ! #ሰላምታን አብዙ፣ ምግብንም አብሉ፣ ዝምድናን ቀጥሉ፣ ሰዎች በተኙበት ተነስታችሁ ስገዱ፣ ጀነትን በ