የኡስታዝ አቡ ሀይደር ትምህርቶች ስብስብ
17.3K subscribers
306 photos
106 videos
47 files
801 links
ኡስታዝ አቡ ሀይደር በፌስቡክ ያስተማራቸው የኦዲዮ የጹሁፍ እና የቪዲዮ ትምህርቶች ተሰባስበው የሚገኙበት ቻናል ነው።
Download Telegram
የኡስታዝ አቡ ሀይደር ትምህርቶች ስብስብ
"ሙሐመዱን ረሱሉሏህ" 7 በአቡ ሀይደር በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡ 2. ለነቢይነታቸው ከአላህ ዘንድ የተሰጣቸው ማስረጃ…
"ሙሐመዱን ረሱሉሏህ" 8
በአቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
3. የተላኩት ለመላው የዓለም ህዝብ ነው!!
በቁጥር አንድ ትምሕርታችን ላይ ስለ ነቢይነታቸው በቀደምት ነቢያት፣ መለኮታዊ መጽሐፍትና ሊቃውንት አንደበት የተነገረ ትንቢት በሚለው ስር፡ ለሶስት ተከታታይ ክፍሎች የተነገረላቸውን ትንቢት አይተናል፡፡
በቁጥር ሁለት ላይ ደግሞ፡- ለነቢይነታቸው ከአላህ ዘንድ የተሰጣቸው ማስረጃ (ሙዕጂዛ) የሚለውን፡ ለአራት ተከታታይ ክፍሎች ስንመለከት ቆይተናል፡፡ ዛሬ ደግሞ አላህ ፈቃዱ ከሆነ የተላኩት ለነማነው? የሚለውን እንመለከታለን ኢንሻአላህ፡፡
ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ከቀደምት ነቢያትና መልክተኞች ከሚለያቸው አንዱ ለሁሉም የሰው ዘር መልክተኛ ሆነው መላካቸው ነው፡፡ ከሳቸው በፊት የነበሩት በጠቅላላ የተላኩት ለህዝቦቻቸው ነው፡፡
አላህ በየጊዜው ነቢያትን በተከታታይ ያስነሳ ስለነበር፡ ነቢይ በሞተ ቁጥርም ሌላ ነቢይ ይተካው ስለነበር፡ ለሁሉም ህዝቦች መልክተኛ ከራሳቸው ህዝብ ተልኮላቸዋል (አን-ነሕል 36)፡፡ ከነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በኋላ ግን የሚላክ ነቢይም ሆነ መልክተኛ ባለመኖሩ አላህ የሳቸውን መልክተኝነት ለመላው ህዝብ በማድረግ ነቢይነትን በሳቸው ደመደመው (ሱረቱል አሕዛብ 40)፡፡
عَنْ جَابِرِ بْنِ عَبْدِ اللَّهِ قَالَ: قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ: " أُعْطِيتُ خَمْسًا لَمْ يُعْطَهُنَّ أَحَدٌ قَبْلِي: …، وَبُعِثْتُ إِلَى النَّاسِ كَافَّةً، وَكَانَ النَّبِيُّ يُبْعَثُ إِلَى قَوْمِهِ خَاصَّةً " رواه البخاري.
ጃቢር ኢብኒ ዐብዲላህ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- "ከኔ በፊት ለነበሩት (ነቢያት) ያልተሰጣቸው አምስት ነገር ተሰጠኝ፡፡….ለሰዎች ሁሉ መልክተኛ ሆኜ ተላክሁ፡፡ (ከኔ በፊት የነበረ) ነቢይ ግን ለህዝቦቹ ብቻ ይላክ ነበር" (ቡኻሪይ 335)፡፡
ከዚህ በመቀጠል የነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ተልእኮ ለመላው ህዝብ መሆኑን የሚያመላክቱ ማስረጃዎችን እናቀርባለን፡-
ሀ. በቀጥታ ለዓለማት እንደተላኩ መነገሩ፡-
ቅዱስ ቁርኣን ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ለዓለማት መላካቸውን በቀጥታ ቋንቋ እንዲህ በማለት ይገልጻል፡-
" وَمَا أَرْسَلْنَاكَ إِلَّا رَحْمَةً لِلْعَالَمِينَ * قُلْ إِنَّمَا يُوحَى إِلَيَّ أَنَّمَا إِلَهُكُمْ إِلَهٌ وَاحِدٌ فَهَلْ أَنْتُمْ مُسْلِمُونَ * فَإِنْ تَوَلَّوْا فَقُلْ آذَنْتُكُمْ عَلَى سَوَاءٍ وَإِنْ أَدْرِي أَقَرِيبٌ أَمْ بَعِيدٌ مَا تُوعَدُونَ " سورة الأنبياء 109-107
"(ሙሐመድ ሆይ!) #ለዓለማትም እዝነት አድርገን እንጅ አልላክንህም። ያ ወደኔ የሚወረደው፣ አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው ማለት ነው፤ ታዲያ እናንተ ፍጹም ታዛዦች ናችሁን? በላቸው። እምቢም ቢሉ (በማወቅ) በእኩልነት ላይ ሆነን (የታዘዝኩትን) አስታወቅኋችሁ፤ የምትስፈራሩበትም ነገር ቅርብ፣ ወይም ሩቅ፣ መሆኑን አላውቅም፤ በላቸው።" (ሱረቱል አንቢያእ 107-109)፡፡
ለ. ለሰዎች ሁሉ በማለት መናገሩ፡-
ሌላው ማስረጃችን፡- አላህ እሳቸውን የላከው ለሰዎች ሁሉ ነው በማለት መናገሩ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው፡- በየትኛውም ቦታ ሆነ በየትኛውም ጊዜ የሚኖር የሰው ዘር በጠቅላላ የሳቸው ነቢይነት ይመለከተዋል፡ ሊያምንባቸውም ግድ ይላል ማለት ነው፡፡ ቀጣዮቹ ቅዱስ ቁርኣናዊ አንቀጾች ይህን ይበልጥ ያስረዳሉ፡-
" مَا أَصَابَكَ مِنْ حَسَنَةٍ فَمِنَ اللَّهِ وَمَا أَصَابَكَ مِنْ سَيِّئَةٍ فَمِنْ نَفْسِكَ وَأَرْسَلْنَاكَ لِلنَّاسِ رَسُولًا وَكَفَى بِاللَّهِ شَهِيدًا " سورة النساء 79
"ከደግ ነገር የሚያገኝህ ከአላህ (ችሮታ) ነው፤ ከመከራም የሚደርስብህ ከራስህ (ጥፋት የተነሳ) ነው፤ #ለሰዎችም ሁሉ መልክተኛ ኾነህ ላክንህ መስካሪም በአላህ በቃ።" (ሱረቱ-ኒሳእ 79)፡፡
" قُلْ يَا أَيُّهَا النَّاسُ إِنِّي رَسُولُ اللَّهِ إِلَيْكُمْ جَمِيعًا الَّذِي لَهُ مُلْكُ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ لَا إِلَهَ إِلَّا هُوَ يُحْيِي وَيُمِيتُ فَآمِنُوا بِاللَّهِ وَرَسُولِهِ النَّبِيِّ الْأُمِّيِّ الَّذِي يُؤْمِنُ بِاللَّهِ وَكَلِمَاتِهِ وَاتَّبِعُوهُ لَعَلَّكُمْ تَهْتَدُونَ " سورة الأعراف 158
"(ሙሐመድ ሆይ!) በላቸው፦ እላንተ ሰዎች ሆይ! እኔ ወደ እናንተ #ወደሁላችሁም የአላህ መልክተኛ ነኝ፤(እርሱም) ያ የሰማይና የምድር ንግስና ለርሱ ብቻ የሆነ ነው፤ እርሱ እንጂ ሌላ አምላክ የለም፤ ሕያው ያደርጋል፤ ይገድላልም፤ በአላህና በዚያም በአላህና በቃላቶቹ በሚያምነው የማይጽፍ የማያነብ ነብይ በሆነው መልክተኛው እመኑ፤ ቅንንም መንገድ ትመሩ ዘንድ ተከተሉት።" (ሱረቱል አዕራፍ 158)፡፡
" وَمَا أَرْسَلْنَاكَ إِلَّا كَافَّةً لِلنَّاسِ بَشِيرًا وَنَذِيرًا وَلَكِنَّ أَكْثَرَ النَّاسِ لَا يَعْلَمُونَ " سورة سبأ 28
"አንተንም #ለሰዎች ሁሉ በመላ፣ አብሳሪና አስፈራሪ አድርገን ቢሆን እንጂ አልላክንህም፤ ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያውቁም።" (ሱረቱ ሰበእ 28)፡፡
ሐ. ከዐረቦች ውጪ ያሉትን መጣራታቸው፡-
የነቢዩ ሙሐመድ (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ሃይማኖታዊ ጥርሪ ዐረቦቹ ላይ ብቻ የተገደበ አልነበረም፡፡ የመጽሐፉ ሰዎችን (አይሁዶችንና ክርስቲያኖችንም) ያቀፈ ነበር፡፡ እነሱንም ወደ ኢስላም ጥርሪ እንዲያደርጉላቸው ታዘዋል፡፡ ይህም ተልእኮአቸው ለመላው የሰው ዘር ለመሆኑ ሌላ አስረጂ ነው፡፡