የኡስታዝ አቡ ሀይደር ትምህርቶች ስብስብ
17.3K subscribers
306 photos
106 videos
47 files
801 links
ኡስታዝ አቡ ሀይደር በፌስቡክ ያስተማራቸው የኦዲዮ የጹሁፍ እና የቪዲዮ ትምህርቶች ተሰባስበው የሚገኙበት ቻናል ነው።
Download Telegram
ንጉሡና 4ቱ ሚስቶቹ!
በድጋሚ የቀረበ
በአቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
በድሮ ዘመን የነበረ አንድ ንጉሥ ነበር፡፡ ይህ ንጉሥ በስሩ አራት ሚስቶች ነበሩት፡፡ አራተኛዋን ሚስቱን ከሌሎቹ በተለየ መልኩ ይወዳታል፡፡ ያበደ ፍቅር እስኪባል ድረስ፡፡ እሷን ለማስደሰት አቅሙ የቻለውን ሁሉ ይጥራል፡፡
ሶስተኛዋን ሚስቱንም ይወዳታል፡፡ ግን በልቡ እሱን ትታ የሌላ ሰው ለመሆን እንዳሰበች ይሰማዋል፡፡
ሁለተኛዋ ደግሞ በችግርና በመከራ ጊዜ የሚጠጋባት ነች፡፡ ችግሩን ሁሌም ታዳምጣለች፡፡ አብራውም ትካፈለዋለች፡፡
የመጀመሪያዋን ሚስት ግን ብዙም ትኩረት አይሰጣትም፡፡ አይንከባከባትም፡፡ ሐቋንም አያሟላላትም፡፡ እሷ ግን ከሁሉም ሚስቶቹ አብልጣ ትወደው ነበር፡፡ ንግስናውም እንዲቆይ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጋለች፡፡
የአላህ ቀደር ይሆንና ንጉሡ ይታመማል፡፡ አጀሉም (የሞት ጊዜው) እንደተቃረበ ተሰማው፡፡ እንዲህ ሲልም አሰበ፡- ‹‹እኔ በስሬ አራት ሚስቶች አሉኝ፡፡ ስለዚህ ብቻዬን ወደ ቀብር መሄድ አልፈልግም!›› ይህንን ይልና፡- የሚወዳትን አራተኛ ሚስቱን፡- ከሚስቶቼ የበለጠ ወድጄሻለሁ፡፡ ፍላጎቶችሽንና ምኞትሽን ሁሉ አሟልቼልሻለሁ፡፡ ታዲያ ቀብር ከኔ ጋር በመግባት ታጽናኚኛለሽ? ይላታል፡፡ እሷም፡- ‹‹የማይታሰብ ነው!›› ትለውና በፍጥነት ያለምንም ርኅራሄ ጥላው ትሄዳለች፡፡
ሶስተኛ ሚስቱን ያስጠራና፡- በህይወት ዘመኔ ሁሉ ወድጄሻለሁ፡፡ ታዲያ ቀብር ከኔ ጋር በመግባት ታጽናኚኛለሽ? ይላታል፡፡ እሷም፡- በፍጹም አላደርገውም! ህይወት በጣም ጣፋጭ ነች፡፡ አንተ በምትሞት ጊዜ እኔ ሌላ ባል ፍለጋ እሄዳለሁ! ብላ መለሰችለት፡፡
ሁለተኛ ሚስቱን ያስጠራና፡- በችግር ጊዜ ሁሌም የምጠጋው ወዳንቺ ነበር፡፡ ለኔ ብለሽ ብዙ መስዋእትነት ከፍለሻል፡፡ ታዲያ ቀብር ከኔ ጋር በመግባት ታጽናኚኛለሽ? ይላታል፡፡ እሷም፡- ይቅርታ አድርግልኝና ፍላጎትህን ላሟላልህ አልችልም! ላንተ ማድረግ የምችለው ነገር ቢኖር እስከ ቀብርህ ድረስ አንተን መሸኘት ብቻ ነው! ትለዋለች፡፡
ንጉሡም በሚስቶቹ ክህደት በጣም አዘነ ተጸጸተም፡፡ ወዲያውኑ ከሩቅ እንዲህ የሚል ድምጽ መጣ፡- እኔ እስከ ቀብርህ አብሬህ እሆናለሁ! የትም ብትሄድ እኔ ካንተ ጋር ነኝ! ንጉሡም ቀና ብሎ ሲያይ፡ ያቺ የመጀመሪያ ሚስቱ ነበረች፡፡ በተጎሳቆለ፡ በደከመና በታመመ ሁኔታ ላይ ነበረች፡፡ እሱ ችላ ብሏት በነበረው ሁኔታ ሰበብ ማለት ነው፡፡ በህይወት ዘመኑ ለሷ ጥሩ እንክብካቤ ባለማድረጉ ንጉሱም በጣም ተጸጸተ፡፡ እንዲህም አለ፡- ከተቀሩት ሚስቶቼ በላይ ልንከባከብሽ የሚገባው አንቺን ነበር፡፡ ጊዜው ቢመለስልኝ ኖሮ ከአራቱ ሚስቶቼ ላንቺ ነበር የበለጠ እንክብካቤና ትኩረት የሚኖረኝ፡፡
መልእክቱ፡- እንደ እውነቱ ሁላችንም አራት ሚስት አለን፡፡ እንዴት የሚሉ ከሆነ፡-
4. ሰውነታችን፡- በአራተኛዋ ሚስት የተመሰለው ነው፡፡ ስለ ሰውነታችን የቱንም ያህል ብንጨነቅ፡ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ብናሟላለትም፡ የሞትን ጊዜ ግን በፍጥነት ይከዳናል፡፡ አራተኛዋ ሚስት ጥላው እንደጠፋች፡፡
3. ገንዘብና ንብረት፡- በሶስተኛዋ ሚስት የተመሰለው ነው፡፡ ምንም ብናከማቸውና ብንሰበስበው፡ የሞትን ጊዜ ቀብር አብሮን አይገባም፡፡ ይልቁኑ የሌላ ሰው (የወራሾች) ንብረት በመሆን ይከዳናል፡፡ ሶስተኛዋ ሚስት፡- እንደሞትክ ሌላ አገባለሁ እንዳለችው፡፡
2. ቤተሰብና ወዳጆች፡- በሁለተኛዋ ሚስት የተመሰሉት ናቸው፡፡ በምድራዊ ህይወታችን ከጎናችን በመቆም ከአላህ ቀጥሎ የሚያስፈልገንን ቢረዱንና ቢተባበሩንም፡ የሞትን ጊዜ ግን ወደ መቃብር ከመሸኘት ውጪ ምንም ሊያደርጉልን አይችሉም፡፡ ሁለተኛዋ ሚስት፡- አንተን ከመሸኘት ውጪ ምንም ማድረግ አልችልም እንዳለችው፡፡
1. ስራችን፡- በመጀመሪያዋ ሚስት የተመሰለው ነው፡፡ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተን፡ በኢማንና በተጨማሪ መልካም ተግባራት ልናጠናክረውና ልናጸናው ሲገባ፡ በቤተሰብ፣ በገንዘብና በጤና ፍቅር ተጠምደን፡ እሱን በመዘንጋት አዳከምነው፡፡ ቀብር አብሮን የሚገባው ግን እሱ ሆኖ ሳለ፡፡ ልክ 1ኛዋን ሚስት በ2ኛዋ፡ በ3ኛዋና በ4ኛዋ በመጠመድ ሐቋን እንዳጎደለባት አይነት ማለት ነው፡፡ እሷ ግን በጣም እየወደደችው፡፡ እናም ወንድሞችና እህቶች! ለአኼራው ዘለቄታዊ ህይወታችን የሚበጀንን መልካም ስራ ላይ ትኩረት በመስጠት እንጠናከር፡፡
"يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا اتَّقُوا اللَّهَ وَلْتَنْظُرْ نَفْسٌ مَا قَدَّمَتْ لِغَدٍ وَاتَّقُوا اللَّهَ إِنَّ اللَّهَ خَبِيرٌ بِمَا تَعْمَلُونَ" سورة الحشر 18
"እላንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ፍሩ፤ ማንኛይቱም ነፍስ ለነገ ያስቀደመችውን ትመልከት፤ አላህንም ፍሩ፤ አላህ በምትሠሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው።" (ሱረቱል ሐሽር 18)፡፡
ምንጭ፡- الثقافة لكم ከሚለው የፌስ ቡክ ገጽ የተተረጎመ
Click and Like ➤➤ https://www.facebook.com/Ustaz.Abuhyder
Join us➤ t.me/abuhyder
በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ
በአቡ ሀይደር
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
عن أبي هريرة ، عن رسول الله صلى الله عليه وسلم قال: «من كان يؤمن بالله واليوم الآخر فليقل خيرا أو ليصمت، ومن كان يؤمن بالله واليوم الآخر فليكرم جاره، ومن كان يؤمن بالله واليوم الآخر فليكرم ضيفه» أخرجه البخاري ومسلم.
ከአቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደተላለፈው የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- "በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ ሰው መልካም ነገርን ይናገር ወይም ዝም ይበል፣ በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ ሰው ጎረቤቱን ያክብር፣ በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ ሰው እንግዳውን ያክብር" (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡
ይህ ነቢያዊ ምክር የተሰጠው፡- በአላህና በመጨረሻው ቀን ላመኑት ሙስሊሞች ነው፡፡ ምክሮቹን ሰፋ አርገን ከመመልከታችን በፊት ‹‹በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ›› የሚለውን በጨረፍታ እንየው፡-
በአላህ ማመን ማለት፡- ይህንን ግዙፉን አጽናፈ ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር፡ ያለ ማንም ረዳት ብቻውን ያመጣና ያስገኘ አንድ ጌታ መሆኑን፣ በአንድነቱ ሁለትነት ወይም ሶስትነት ወይም ብዜት የሌለበት ጌታ መሆኑን፣ በስሞቹም ሆነ በባሕሪያቱ ፍጹም አምሳያ የሌለው የምሉዕ ባሕሪያት ባለቤት መሆኑን፣ ከርሱ ጋርም አብሮ ሊመለክ የሚችል ተጋሪ የሌለው አምላክ መሆኑን አምኖ መቀበል ማለት ነው፡፡ "ተውሒድ" ማለት የአላህን ፍጹማዊ አንድነት አምኖ መቀበል ማለት ነውና፡፡
አላህ በዛቱ (በህልውናው) አንድ ነው፡፡ ሁለትነት የለበትም፣ ሶስትነት የለበትም፣ ከዛም በላይ አይደለም፡፡ እሱ አንድና አንድ ብቻ ነው፡- "አምላካችሁም አንድ አምላክ ብቻ ነው፤ ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ (እርሱ) እጅግ በጣም ርኅሩህ አዛኝ ነው፡፡" (ሱረቱል በቀራህ 163)፡፡ "አላህም አለ፦ ሁለት አማልክትን አትያዙ፤ እርሱ አምላክ ብቻ ነው፤ እኔንም ብቻ ፍሩ።" (ሱረቱ-ነሕል 51)፡፡ "…በአላህና በመልክተኞቹም እመኑ (አማልክት) ሦስት ናቸው አትበሉም፤ ተከልከሉ ለናንተ የተሻለ ይሆናልና፤ አላህ አንድ አምላክ ብቻ ነው። ለርሱ ልጅ ያለው ከመሆን የጠራ ነው። በሰማያትና በምድር ያለ ሁሉ የርሱ ነው። መመኪያም በአላህ በቃ።" (ሱረቱ-ኒሳእ 171)፡፡ "አላህ ምንም ልጅን አልያዘም (አልወለደም)፡፡ ከእርሱም ጋር አንድም አምላክ የለም፡፡ ያን ጊዜ (ሌላ አምላክ በነበረ) አምላክ ሁሉ በፈጠረው ነገር በተለየ ነበር፡፡ ከፊላቸውም በከፊሉ ለይ በላቀ ነበር፡፡ አላህ ከሚመጥኑት ሁሉ ጠራ፡"ቨ(ሱረቱል ሙእሚኑን 91)፡፡
*አላህ በስራው ፍጹም አንድ ነው፡፡ ምንም አይነት ተጋሪ ወይም አጋዥ የለውም፡፡ ሁሉንም ነገር የፈጠረውና ያስገኘው ብቻውን ነው፡- "ምስጋና ለአላህ ለዚያ ልጅን ላልያዝነው ለርሱም በንግሥናው ተጋሪ ለሌለው ለርሱም ከውርደት ረዳት ለሌለው ይግገባው፣ በልም ማክበርን አክብረው።" (ሱረቱል ኢስራእ 111)፡፡ "እርሱ ያ የሰማያትና የምድር ንግሥና የርሱ ብቻ የሆነ ልጅንም ያልያዘ፣ በንግሥናውም ተጋሪ የሌለው፣ ነገሩንም ሁሉ የፈጠረና፣ በትክክልም ያዘጋጀው ነው።" (ሱረቱል ፉርቃን 2)፡፡ "ይሃችሁ፣ ጌታችሁ አላህ ነው፤ የነገር ሁሉ ፈጣሪ ነው፤ ከርሱ ሌላ አምላክ የለም፤ ታዲያ (ከእምነት) ወዴት ትመለሳላችሁ።" (ሱረቱ ጋፊር 62)::
*አላህ በባሕሪያቱ ፍጹም አምሳያና ብጤ እንዲሁም ሞክሼ የሌለው አንድ ጌታ ነው፡፡ እሱ ፈጣሪ ነውና ከፍጡሩ እሱን የሚመስል አንዳችም የለም፡- "ለአላህም አምሳያዎችን አታድርጉ፤ አላህ (መሳይ እንደሌለው) ያውቃል፤ እናንተ ግን አታውቁም።" (ሱረቱ-ነሕል 74)፡፡ "(እርሱ) የሰማያትና የምድር፣ በሁለቱም መካካል ላለዉ ሁሉ ጌታ ነዉና ተገዛዉ፤ እርሱን በመግገዛትም ላይ ታገሥ፤ ለርሱ ሞክሼን ታዉቃለህን ?" (ሱረቱ መርየም 65)፡፡ "ሰማያትንና ምድርን ፈጣሪ ነው፤ ከነፍሶቻችሁ ሴቶችን፣ ከቤት እንሰሳዎችም ዓይነቶችን (ወንዶችና ሴቶችን) ለእናንተ አደረገላችሁ፤ በርሱ (በማድረጉ) ያበዛችኋል፤ የሚመስለው ምንም ነገር የለም፤ እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው።" (ሱረቱ-ሹራ 11)፡፡ "ለርሱም አንድም ብጤ የለውም።" (ሱረቱል ኢኽላስ 4)፡፡
*አላህ በባሮቹ ተግባር ብቻውን የሚመለክ ማንም የማይጋራው አንድ አምላክ ብቻ ነው፡፡ ከርሱ ጋር አብሮ ሊመለክ የሚችል የለም፡- "አላህን ተገዙ፤ በርሱም ምንንም አታጋሩ…" (ሱረቱ-ኒሳእ 36)፡፡ "«ኑ፤ ጌታችሁ በእናንተ ላይ እርም ያደርገውን ነገር (በእርሱም ያዘዛችሁን) ላንብብላችሁ» በላቸው፡፡ «በእርሱ (በአላህ) ምንንም ነገር አታጋሩ…" (ሱረቱል አንዓም 151)፡፡ "ጌታዬ እርም ያደረገው መጥፎ ሥራዎችን፣ ከርሷ የተገለጸውንና የተደበቀውን ኃጢአትንም ያላግባብ መበደልንም፣ በርሱም ማስረጃ ያላወረደበትን (ጣዖት) በአላህ ማጋራታችሁን፣ በአላህም ላይ የማታውቁትን መናገራችሁን ብቻ ነው በላቸው።" (ሱረቱል አዕራፍ 33)፡፡
በመጨረሻው ቀን ማመን ማለት ደግሞ፡- ከሞት በኋላ ዳግም ህይወት እንዳለ ማመን፣ ተቀስቅሰንም በአንድ ሜዳ እንደምንሰበሰብ፣ ተሰብስበንም በጌታችን ፊት ለፍርድ ውሳኔ እንደምንቀርብ፣ ቀርበንም ስራችን ተመዝኖ ውጤቱን እንደምንቀበል፣ ተቀብለንም አማኞች ወደ ጀነት፡ ከሀዲያን ደግሞ ወደ ጀሐነም እንደሚገቡ አምኖ መቀበል ማለት ነው፡-
"ከርሷ (ከምድር) ፈጠርናቸሁ፤ በርሷም ውስጥ እንመልሳችኋለን፤ ከርሷም በሌላ ጊዜ እናወጣችኋለን።" (ሱረቱ ጣሀ 55)፡፡ "አላህም ከምድር ማብቃልን አበቀላችሁ። ከዚያም በውስጧ ይመልሳችኋል። ማውጣትንም ያወጣችኋል።" (ሱረቱ ኑሕ 17-18)፡፡ "ተራራዎችንም የምናስኼድበትን ቀን፥ (አስታውስ)፤ ምድርንም ግልጽ ሆና ታያታለህ፤ እንሰበስባቸዋለንም፤ ከነሱም አንድንም አንተውም። የተሰለፉም ሆነው በጌታህ ላይ ይቀረባሉ፤ (ይባላሉም)፦ በመጀመሪያ ጊዜ እንደ ፈጠርናችሁ፣ (ራቁታችሁን) በእርግጥ መጣችሁን፤ በውነቱ ለናንተ (ለመቀስቀሻ) ጊዜን አናደርግም መሰሏችሁ ነበር።" (አል ከህፍ 47-48):: "በትንሣኤም ቀን፣ ትክክለኛ ሚዛኖችን እናቆማለን፣ ማንኛይቱም ነፍስ ምንንም አትበደልም፤ (ሥራው) የሰናፍጭ ቅንጣት ያክል ቢሆንም እርሷን እናመጣታለን፤ ተቆጣጣሪዎችም በኛ በቃ።" (ሱረቱል አንቢያእ 47)፡፡ "እነዚያ ከመጽሐፉ ሰዎች የካዱት፣ አጋሪዎቹም በገሃነም እሳት ውስጥ ናቸው፤ በውስጧ ዘውታሪዎች ሲኾኑ፤ እነዚያ እነሱ ከፍጥረት ሁሉ ክፉ ናቸው። እነዚያ ያመኑትና መልካሞችንም የሠሩት፣ እነዚያ እነሱ ከፍጥረት ሁሉ በላጭ ናቸው።" (ሱረቱል በይነህ 6-7)፡፡
በጥቅሉ በዚህ ምድር ላይ ለምንፈጽማቸው ማንኛውም ተግባራት የሚመለከተንና የሚቆጣጠረን እምላክ አላህ አለ ብለን ካመንን፡ በመጨረሻው ዓለምም ይተሳሰበናል እንደ-ስራችን መጠን ዋጋም ይከፍለናል ብለን በአኼራ ካመንን ቀጥሎ ያሉትን ነገራት እንፈጽማቸው፡-
ሀ. መልካም እንናገር ወይንም ዝም እንበል፡-
ኢማሙ-ሻፊዒይ (ረሒመሁላህ) የሐዲሡን መልክት ሲናገሩ እንዲህ አሉ፡- "መናገር የፈለገ እንደሆን ቀድሞ ያስብበት፡፡ ጉዳት እንደሌለው ከታየው ይናገረው፡፡ ጉዳት እንዳለው ካወቀ ወይም ከተጠራጠረ ይተወው" ከሰዎች አንደበት የሚወጡ ቃላት በጠቅላላ ይጻፋል (በዕብደት፣በልጅነት፣በዕንቅልፍ ምክንያት የሆኑት ብቻ ሲቀሩ)፡- "ከቃል አንድንም አይናገርም ከርሱ ዘንድ(ቃሉን ለመመዝገብ)ዝግጁ የሆኑ መላእክት ያሉ ቢሆን እንጅ።" (ሱረቱ ቃፍ 18)፡፡ "የእነዚያን አላህ ድኻ ነዉ፥ እኛ ግን ከበርቴዎች ነን ያሉትን ሰዎች ቃል አላህ በእርግጥ ሰማ፤ ያንን ያሉትንና ነቢያትን ያለ ሕግ መግደላቸዉን በእርግጥ እንጽፋለን፤ የእሳትንም ስቃይ ቅመሱ እንላቸዋለን።" (ሱረቱ አለ-ዒምራን 181)፡፡ "በናንተ ላይ ተጠባባቂዎች ያሉባችሁ፤ ስትሆኑ፤ የተከበሩ ጸሐፊዎች የሆኑ፤ (ተጠባባቂዎች)" (ሱረቱል ኢንፊጣር 10-11)፡፡
ስለሆነም የምናነገረውን እንጠንቀቅ፡፡ ወይ ሊጠቅመን ወይም ሊጎዳን መሆኑ እስካልቀረ የሚበጀንን መምረጥ ብልኅነት ነው፡፡ ከተናገርን ጌታችንን የሚያስደስት፣ ሰዎችን የሚጠቅምና በሚዛናችን ላይ የሚቀርልንን እንምረጥ፡፡ መልካም ንግግር አስተዋይ ስብዕናን እንጂ ወጪን አይጠይቅምና፡-
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- "ጸሐይ በምትወጣበት ቀን ሁሉ እያንዳንዱ የሰውነት መገጣጠሚያ ሶደቃ አለበት፡፡ በሁለት ሰዎች መሐል በትክክል መፍረድ ሶደቃ ነው፣ ሰውየውን በመጓጓዣው ላይ እቃውን እንዲጭን ብታግዘው ሶደቃ ነው፣ #መልካም_ንግግር ሶደቃ ነው፣ ወደ ሶላት የምታደርገውው እንቅስቃሴም ሶደቃ ነው፣ የሚያስቸግር ነገር ከመንገድ ማንሳትህም ሶደቃ ነው" (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡
አቢ-ሙሳ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ አለ፡- "የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሆይ! ከሙስሊሞች መሐል በላጩ ማነው? ስላቸው፡ እሳቸውም፡- ‹‹ሙስሊሞች ከምላሱና ከእጁ የተረፉበት ሰው ነው›› ብለው መለሱልኝ" (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡
ሰህል ኢብኑ-ሰዕድ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደተናገረው የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- "በሁለቱ አጥንቶቹ መሐል ያለውን (ምላሱን) እና በእግሮቹ መሐል ያለውን (ብልቱን) ለመጠበቅ ቃል ለሚገባልኝ ሰው ጀነትን ዋስ እሆነዋለሁ" (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡
አላህ ካልወፈቀንና መልካም ነገርን መናገር ካልቻልን ዝም እንበል፡፡ ዝምታም በራሱ ኸይር ነውና!! ዐብዱላህ ኢብኑ-ዑመር (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንደተናገሩት የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- " ‹‹ዝም ያለ ሰው ነጃ ወጣ (ዳነ)›› እሳቸውም በጣም ዝምተኛና ሳቃቸውም መጠነኛ ነበር" (አሕመድ 9/196)፡፡ የምንናገረውን ነገር ቀድመን ሳናውቅ ከተናገርን አደጋው የከፋ ይሆናልና ቆጠብ እንበል፡-
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ሲሉ ሰማ፡- "አንድ አላህ ባሪያ አንዲትን ቃል ጥሩ ይሁን መጥፎ ሳያስተውል ይናገርና በሷ ሰበብ ወደ እሳት ምስራቁና ምእራቡ ከሚራራቀው የበለጠ ይጣላል" (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡
ዐብዱላህ ኢብኑ-ዑመር (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንደተናገሩት የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- "አላህን ከማውሳት ውጭ በሆነ ነገር ላይ ንግግር አታብዙ፡፡ አላህን ከማውሳት ውጭ የሆነ ንግግር ማብዛት የልብ ድርቀት ነው፡፡ ልበ ደረቅ ሰው ደግሞ ከአላህ (ራሕመት) የራቀ ነው" (ቲርሚዚይ)፡፡
ዑቅበተ ኢብኑ-ዓሚር (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ አለ፡- "የአላህ መልክተኛ ሆይ! መዳን እንዴት ነው? ስላቸው፡ እሳቸውም፡- ‹‹ምላስህን ተቆጣጠር፣ ቤትህ ይስፋህ፣ ለኃጢአትህ አልቅስ›› አሉኝ" (ቲርሚዚይ)፡፡
ለ. ጎረቤት እናክብር፡-
ጎረቤት የሚባለው ማነው ማነው? የሚለውን ጉዳይ የኢስላም ሊቃውንቶች የገለጹበት መንገድ ያስደነግጣል፡፡ እኛ ጎረቤት ብለን የምንገምተው ከቤታችን ቀጥሎ ያሉት ከ1-4 ቤቶች ላይ ብቻ የተገደበ አድርገን ነበር፡፡ ሐሰኑል በስሪ ረሒመሁላህ) ስለ ጎረቤት ተጠይቀው ሲመልሱ ግን እንዲህ ነበር ያሉት፡- ‹‹ከፊት ለፊቱ እስከ አርባ ቤት ድረስ፣ ከኋላው እስከ አርባ ቤት ድረስ፣ ከቀኝ ጎኑ እስከ አርባ ቤት ድረስ፣ ከግራ ጎኑ እስከ አርባ ቤት ድረስ ያለው ነው›› ብለው መለሱ (ቡኻሪይ አደቡል-ሙፍረድ 109)፡፡ ወይንም ደግሞ እንደ አካባቢው ባሕል መታየት ስላለበት ያ አካባቢ ጎረቤት ብሎ የሚጠራውን ሁሉ ያካተተ በሚለው መጓዙም መልካም ነው፡ ወላሁ አዕለም፡፡ ጎረቤት ሶስት አይነት ነው፡- 1. በኛ ላይ ሶስት ሐቅ (መብት) ያለው፡- 2. በኛ ላይ ሁለት ሐቅ ያለው፡- 3. በኛ ላይ አንድ ሐቅ ያለው፡-
የመጀመሪያው አይነት ጎረቤት፡- ሙስሊምና የስጋ ዘመዳችን የሆነ ነው፡፡ እሱ ከጉርብትናም በተጨማሪ የዝምድና ሐቅ እንዲሁም የእስልምና ሐቅ አለው፡፡
ሁለተኛው ጎረቤት ደግሞ የስጋ ዝምድና የሌለን ሙስሊም ጎረቤት ነው፡፡ እሱ ደግሞ ከጉርብትናው ጋር የኢስላም ሐቅ አለው፡፡
ሶስተኛው ጎረቤት ደግሞ ሙስሊም ያልሆነና የስጋ ዝምድናም የሌለን ሲሆን፡ እሱም የጉርብትና ሐቅ አለው፡፡ ለጎረቤታችን መጥፎ ከመስራት መቆጠብ ጀምሮ መልካም ነገር እስከ-ማድረግ ያለው አላህ የሚደው ነገር ነው፡፡ ጌታ አላህም በቅዱስ ቃሉ እንዲህ ያዘናል፡-
"አላህን ተገዙ፤ በርሱም ምንንም አታጋሩ በወላጆችና በቅርብ ዝምድና ባለቤትም፣ በየቲሞች፣ በምስኪኖችም፣ በቅርብ ጎረቤትም፣ በጎን ባልደረባም፣ በመንገደኛም፣ እጆቻችሁም ንብረት ባደረጓቸው (ባሮች)፣ መልካምን (ሥሩ)፤ አላህ ኩራተኛ ጉረኛ የኾነን ሰው አይወድም።" (ሱረቱ-ኒሳእ 36)፡፡
"የቅርብ ጎረቤት" የተባለው ዝምድናም ያለውን ሲሆን "የጎን ባልደረባ" የተባለው ደግሞ ዝምድና የሌለውን ነው፡፡ ዐብዱላህ ኢብኑ-ዑመር (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንደተናገሩት የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- "ጂብሪል (ዐለይሂ ሰላም) በጎረቤት ሐቅ እኔን አደራ! እያለ ከማስታወስ አልተወገደም፡ ምናልባትም ጎረቤት ይወርሳል ብዬ እስካስብ ድረስ" (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡
ዐብዱላህ ኢብኑ-ዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንደተናገሩት የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- "ጎረቤቱ ተርቦ እያደረ እሱ የሚጠግብ ከሆነ ሙእሚን አይደለም" (ሲልሲለቱ-ሶሒሐህ 149)፡፡
የምእመናን እናት አዒሻህ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንዲህ አለች፡- "የአላህ መልክተኛን፡- እኔ ሁለት ጎረቤቶች አሉኝና ወደማንኛቸው ስጦታ ልጀምር? ስላቸው፡ እሳቸውም፡- ‹‹ላንቺ ቤት ቅርብ ከሆነው›› አሉኝ" (ቡኻሪይ)፡፡
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዳስተላለፉት የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- "ሙስሊም ሴቶች ሆይ! ጎረቤት ጎረቤቷን ትንሽ ስጋ ባዘለ አጥንትም ቢሆን እንኳ እንዳትንቅ!" (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡
አቢ-ሹረይሕ (ረዲየላሁ ዐንሁ) የአላህ መልክተኛ እንዲህ ተናገሩ አለ፡- "‹‹በአላህ ይሁንብኝ አላመነም! በአላህ ይሁንብኝ አላመነም! በአላህ ይሁንብኝ አላመነም!›› የአላህ መልክተኛ ሆይ! ማነው ያላመነው? ሲባሉ፡ እሳቸውም፡- ‹‹ጎረቤቱ በንብረታቸው የማያምኑት ሰው›› ብለው መለሱ" (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡
👍2
ሐ. እንግዳውን ያክብር፡-
በእንግድነት ቤታችን የመጣና ያረፈ ሰው ክብርና መስተንግዶ እንደሚገባው ነቢያችን (ዐለይሂ ሶላቱ ወስ-ሰላም) አስተምረውናል፡- አቢ-ሹረይሕ (ረዲየላሁ ዐንሁ) የአላህ መልክተኛ እንዲህ ተናገሩ አለ፡- "እንግድነት ሶስት ቀን ድረስ ነው፡፡ (ልዩ መስተንግዶው) አንድ ቀን ከነ-ሌሊቱ ነው፡፡ ከዛ ውጭ ያለው ቀን ለተቀባዩ እንደ ሶደቃ ነው" (ቡኻሪይ)፡፡ አላህ በሰማነውና ባወቅነው የምንሰራ ያድርገን፡፡
Click and Like ➤➤ https://www.facebook.com/Ustaz.Abuhyder
Join us➤ t.me/abuhyder
በ_ፈጣሪ_ማመን_ክፍል_1_By_Dai_Sadiq_Moh.m4a
12.7 MB
በፈጣሪ ማመን
"የፈጣሪ ፅንስ ሀሳብ በቁርአን እና በቀመደምት መፅሐፍት" ክፍል 1
☞በኡስታዝ አቡ ሀይደር

Mp3 ዳውሎድ ለማድረግ
https://goo.gl/DjpZvN

Join us➤ t.me/abuhyder
የኡስታዝ አቡ ሀይደር ትምህርቶች ስብስብ
በ_ፈጣሪ_ማመን_ክፍል_1_By_Dai_Sadiq_Moh.m4a
በ_ፈጣሪ_ማመን_ክፍል_2_By_Dai_Sadiq_Moh.m4a
6 MB
በፈጣሪ ማመን
"የፈጣሪ ፅንስ ሀሳብ በቁርአን እና በቀመደምት መፅሐፍት" ክፍል 2
☞በኡስታዝ አቡ ሀይደር

Mp3 ዳውሎድ ለማድረግ
https://goo.gl/17EDoz

Join us➤ t.me/abuhyder
ህመምተኛን መጎብኘት በኢስላም
በአቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
عن أبي هريرة قال: قال رسول الله صلى الله عليه وسلم: «ثلاث كلهن حق على كل مسلم: عيادة المريض، واتباع الجنائز، وتشميت العاطس إذا حمد الله عز و جل» رواه الإمام أحمد.
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- "ሶስት ነገሮች በያንዳንዱ ሙስሊም ላይ የተገቡ ተግባራት ናቸው፡ በሽተኛን መጎብኘት፣ የሞተን (ጀናዛ) መሸኘት፣ ላስነጠሰ ሰው አልሐምዱ ሊላህ ካለ በመልካም ዱዓ ማድረግ " (አሕመድ የዘገቡት)፡፡
የአላህ ነቢይ (ዐለይሂ ሶላቱ ወስ-ሰላም) በዚህ ቦታ ማስተላለፍ የፈለጉት ሶስቱን ትምሕርቶች ስለሆነ ነው እንጂ፡ ሙስሊም በሌላው ሙስሊም ላይ ያለው ሐቅ ሶስት ብቻ ስለሆነ አይደለም፡፡ በሌሎች ሐዲሦች እንደተረጋገጠው አምስትና ስድስት የሚሆኑ ሐቆችም ተዘርዝረዋል፡፡
‹‹የሙስሊም ሐቅ›› ሲባል፡- አንዱ ሙስሊም ለሌላው ወንድሙ (እህቱ) በነፍስ-ወከፍ ሊፈጽመው የሚገባ ግዴታው፣ ወይንም የተወሰኑት ላይ ብቻ የሚጣል ግዴታ፣ ካልሆነም ሊተገበር የሚገባው ጠንካራ ሱና ማለት ነው፡፡
ህመምተኛን መጠየቅ፡-
ይህ ሙስሊም ህመምተኛ በጤነኛው ላይ ያለው መብቱ ነው፡፡ ወንድሞችና እህቶች ከታመሙ ልንጎበኛቸው ይገባል፡፡ ምንም ልናደርግላቸው ባንችል እንኳ፡ እነሱን ለመጎብኘት መገኘታችን ለነሱ ግማሽ ጤና ነው፡፡ በሙስሊም ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው እንዳልተረሱ ማወቃቸው ብቻ ያስደስታቸዋል፡፡ መተባበርንና መተዛዘንን የደነገገው ኢስላም ያኮራቸዋል፡፡ የአክፍሮት ኃይላት በየሆስፒታሉ እየዞሩ ወንድምና እህቶቻችን በኛ ቦታ ከጎበኙብን ውጤቱ አደጋ ነው፡፡ የነሱ ጉብኝት ለስጋዊ ጤንነት ቢሆንም ዘላለማዊ ክስረትንም ተሸክመው ነው የሚሄዱት፡፡ ነጌ ከሆስፒታሉ ሲወጣ ከበፊት ወንድሞችና እህቶች ጋር የነበረው ወዳጅነት ይሻክራል፡፡ መራራቅና ለጠላት ተንኮል ሰለባ መሆንን ያስከትላል፡፡ በመሆኑም ህመምተኛን በመጎብኘት ላይ ልንጠናከርበት ይገባል፡፡ እኛ እንኳ ህመምተኛው ወዳለበት ስፍራ መገኘት ባንችል፡ ሌሎች እንዲገኙና ቦታው እንዲሸፈን ያድርጉ፡፡ በስልክም ሆነ በሌላ መንገድ ህመምተኛውን በማግኘት እናጽናናው፡፡ ህመምተኛን መጎብኘት የፈለገ ሰው ከቻለ ቀጥሎ ያሉትን አዳቦች ቢያሟላ ተወዳጅ ነው፡-
1. በር አይደብድብ፡- ወደ ህመምተኛው ሰው ቤት ስትሄዱ ውስጥ ያለውን ሰው በሚያስደነግጥ መልኩ በሩን በኃይል አይደብድቡ፡፡ ከውስጥ ማነው? ተብለው ሲጠየቁም ማንነትዎን አይደብቁ፡፡ ሳይፈቀድልዎት አይግቡ፡፡ ተፈቅዶልዎት ከገቡም አይንዎትን ሰበር ያድርጉ፡፡
2. ህመምተኛውን ለመጠየቅ አመቺ ሰዓታትን ይምረጡ፡፡ እነሱ ተሰብስበው በሚመገቡበት ወይም የውጭ ሰው በማይጠበቅበት ሰዓት አይሂዱ፡፡
3. ህመምተኛውን ሊጎበኙ ከመጡ ከወደ ጎኑ በመጠጋት አመቺ በሆነ መልኩ ይቀመጡ፡፡ እጆትንም ግንባሩ ላይ በማሳረፍ ስለ-ህመሙ ሁኔታና አሁን ምን እንደሚያስፈልገው ይጠይቁት፡፡ መልካም አክብሮት የፈውስ አንድ አካል ነውና፡፡ ከቤት ሰው ተሸክሟቸው ሆስፒታል የሚወሰዱ ህመምተኞች በሐኪሙ ፊት እራሳቸውን ችለው ሲቆሙ አልገጠማችሁንም? መፍትሄ የሚሰጥ ባለሙያ ዘንድ መጥቻለሁ ብለው ስለሚያስቡ ህመሙ በተወሰነ መልኩ ጋብ ይላል፡፡
4. ከተመቾት ህመምተኛውን መጎብኘት ይደጋግሙ፡፡ ገና በመጀመሪያው ጉብኝትዎት ብቻ ‹‹አላህ ያሽርህ›› ብለው አይጥፉበት፡፡ ህመም እየባሰ ወይም እየሻረ ሊሄድ የሚችል ነገር ነውና፡፡
5. የርሶ በህመምተኛው ቤት መቆየት ታማሚውን ወይም ቤተሰቦቹን ያስቸግራል ብለው ከገመቱ ብዙም አይቆዩ፡፡ የርሶ በቦታው መኖር ግን ጠቀሜታ ካለው ይቆዩ፡፡
6. ከቻሉም ተከታዩን ዱዓእ ሰባት ጊዜ በመደጋገም ያድርጉለት፡- ‹‹አስአሉላሀ-አል ዐዚም፣ ረበል-ዐርሺል ዐዚም፣ አን-የሽፊየክ/ኪ››፡፡ እንዲሁም ሱረቱል ፋቲሐህ፣ አል-ፈለቅ እና አን-ናስን ይቅሩበት፡፡ ይህንን ዱዓእ ህመምተኛን ጎብኝቶ ከልቡ አምኖ ያደረገ ሰው አላህ ህመምተኛውን ያሽረዋል በማለት ተወዳጁ ነቢያችን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ነግረውናል፡፡ (አቡ ዳዉድ 3108፣ ቲርሚዚይ 2227፣ ነሳኢይ ሱነኑል-ኩብራ 10883፣ ሶሒሕ ኢብኑ-ሒባን 2975)፡፡
7. ህመምተኛውን ልቡን በተስፋ ይምሉት፡፡ አላህ እንደሚያሽረው በመንገር ያጽናኑት፡፡ እስከዛም ሶብር ካደረገ ታላቅ ምንዳ እንዳለው ያበስሩት፡፡ ተስፋ መቁረጥ የሙስሊም ባሕሪ እንዳልሆነ በመንገር ተስፋውን ያድሱለት፡፡
8. ህመምተኛውን ለመጎብኘት የመጡ ሰዎች በዛ ካሉ በመሐል ለጭቅጭቅ መንስኤ የሚሆኑ ነገሮችን ይራቁ፡፡ በናንተ ጭቅጭቅ ለህመምተኛው ሌላ በሽታን እንጂ ማጽናናትን አይጨምርለትምና፡፡
እስካሁን ያየናቸው የህመምተኛውን ሙስሊም ሐቅ ሲሆን፡ ጎብኚዎች ደግሞ በዚህ ስራቸው አላህ ዘንድ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የሚያመላክቱ ነቢያዊ ሐዲሦችን በመጠኑ እንመለከታለን፡-
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- "ነጌ የውሙል ቂያም አላህ እንዲህ ይላል፡- ‹‹የአደም ልጅ ሆይ! ታምሄ ሳለሁ አልጎበኘኸኝምሳ?›› ባርያውም፡- ‹‹ጌታዬ ሆይ! አንተ የዓለማቱ ጌታ ሆነህ እንዴት ነው ታመህ የምጎበኝህ?›› ይላል፡፡ አላህም፡- ‹‹እንትና ባሪያዬ ታሞ ሳለ አንተ አለመጎብኘትህን አታውቅምን? እሱን ብትጎበኘው እኔን እሱ ዘንድ እንደምታገኘኝ አታውቅምን?›› ይለዋል፡፡" (ሙስሊም የዘገበው)፡፡
በዚህ ሐዲሥ መሰረት በሽተኛን መጎብኘት አላህ ዘንድ ታላቅ ጥቅም እንዳለው እንረዳለን፡፡ ኢማሙ ነወዊይ (ረሒመሁላህ) እንዳብራሩት፡ አላህን እዛ ማግኘት ማለት፡- የዚያራን አጅርና ክብር መጎናጸፍ ማለት ነው፡፡
ሠውባን (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- "ህመምተኛን የጎበኘ ሰው በጀነት የበሰሉ ፍሬዎች ጥላ ስር ከመሆን አይወገድም" (ሙስሊም)፡፡
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- "ዛሬ ከመሐከላችሁ የጾመ ማነው? ሲሉ ፡ አቡ በከር-ሲዲቅ(ረዲየላሁ ዐንሁ) ‹‹እኔ›› አለ፡፡ ዛሬ ህመምተኛን የጎበኘ ማነው? ሲሉ፡ አቡ በከር-ሲዲቅ(ረዲየላሁ ዐንሁ) ‹‹እኔ›› አለ፡፡ ዛሬ ጀናዛን(አስከሬን) የሸኘ ማነው? ሲሉ ፡ አቡ በከር-ሲዲቅ(ረዲየላሁ ዐንሁ) ‹‹እኔ›› አለ፡፡ ዛሬስ ምስኪንን የመገበ ማነው? ሲሉ ፡ አቡ በከር-ሲዲቅ(ረዲየላሁ ዐንሁ) ‹‹እኔ›› አለ፡፡ ከዛም እሳቸው፡- ‹‹እነዚህ ተግባራት በአንድ ሰው ላይ አይሰባሰቡም ሰውየው ጀነት የገባ ቢሆን እንጂ›› አሉ" (ሙስሊም)፡፡
ዐሊይ ኢብኑ አቢ-ጧሊብ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ አሉ፡- "የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ሲሉ ሰማኋቸው፡- ‹‹አንድ ሙስሊም ሌላውን ሙስሊም በንጋቱ ሰዓት አይጎበኘውም፡ እስኪያመሽ ድረስ ሰባ ሺህ መላእክት ዱዓእ የሚያደርጉለት ቢሆን እንጂ፣ በምሽቱ ወቅትም ከጎበኘው እስኪያነጋ ድረስ ሰባ ሺህ መላእክት ዱዓእ የሚያደርጉለትና ከጀነት የሆነ የበሰሉ ፍሬዎች ቢኖሩት እንጂ››" (ቲርሚዚይ 969)፡፡ አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- "ህመምተኛን የጎበኘ ሰው፡ ከሰማይ ተጣሪ እንዲህ ብሎ ይጣራል፡- ‹‹ኑሮህ ያማረ፣ መንገድህ የተስተካከለ፣ ለጀነት ክቡር ስፍራ የታጨህ ሁን›› ይለዋል" (ቲርሚዚይ 2008)፡፡
ሀሩን ኢብኑ አቢ-ዳዉድ (ረሒመሁላህ) እንዲህ አለ፡- "አነስ ኢብኑ ማሊክ ዘንድ መጣሁና እንዲህ አልኩት ‹‹አባ ሐምዛ ሆይ! አንተን መጎብኘት እየፈለግን ቦታው ግን ራቀብን›› እሱም ራሱን ቀና አድርጎ፡- የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ሲሉ ሰማሁ ‹‹ማንኛውም ሰው ህመምተኛን የሚጎበኝ ከሆነ የሚመላለሰው በራሕመት ውስጥ ነው፣ ህመምተኛው ጎን ከተቀመጠ ራሕመት ይሸፍነዋል›› እኔም፡- ‹‹የአላህ መልክተኛ ሆይ! ይህ ሁሉ ለጤነኛው ነው፡ ለህመምተኛውስ ምን አለው?›› ስላቸው፡ ‹‹ኃጢአቱ ይሰረዝለታል›› ብለው መለሱልኝ በማለት ነገረኝ" (አሕመድ 12782)፡፡
Click and Like ➤➤ https://www.facebook.com/Ustaz.Abuhyder
Join us➤ t.me/abuhyder
የኡስታዝ አቡ ሀይደር ትምህርቶች ስብስብ
በ_ፈጣሪ_ማመን_ክፍል_2_By_Dai_Sadiq_Moh.m4a
በፈጣሪ_ማመን_ክፍል_3_By_Dai_Sadiq_Moha.m4a
41.3 MB
በፈጣሪ ማመን
"የፈጣሪ ፅንስ ሀሳብ በቁርአን እና በቀመደምት መፅሐፍት" ክፍል 3
☞በኡስታዝ አቡ ሀይደር

Mp3 ዳውሎድ ለማድረግ
https://goo.gl/17EDoz

Join us➤ t.me/abuhyder
"ሙሐመዱን ረሱሉሏህ" 1
በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
የተከበራችሁ ሙስሊም ወንድሞቼና እህቶቼ! ባለፈው ፕሮግራማችን ላይ በአላህ ፈቃድ በ 29 ክፍል በተከታታይ ስለ "ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ" ስንማር ቆይተን ነበር አልሐምዱ ሊላህ፡፡ አሁን ደግሞ የዛው ክፍል አካል የሆነውን ሁለተኛውን ምስክርነት "ሙሐመዱን ረሱሉሏህ" እንጀምራለን ኢንሻአላህ፡፡
1. ስለ ነቢይነታቸው የተነገረ ትንቢት፡-
ይህ ዋናው ጥያቄ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ከተቃራኒ እምነት ተከታዮች የምንሰማው ጥያቄ፡፡ እውነት የእናንተ ነቢይ እውነተኛ ነቢይ ከሆኑ ስለሳቸው ነቢይነት ቀደምት ነቢያቶችና መለኮታዊ መጽሐፍቶች ለምን ትንቢትን አልተናገሩላቸውም? የመጽሐፉ ሊቃውንቶችስ ለምን አልተናገሩም? የሚል፡፡
ታዲያ እኛ ሙስሊሞች ለዚህ ጥያቄ ምን መልስ አለን? ቅዱስ ቁርኣንስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላል? ሙስሊሞች እንደሚያምኑትና ቅዱስ ቁርኣን እንደሚያስተምረው ስለ ነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ነቢይነት ትንቢትን ያልተናገረ አንድም ነቢይ የለም፡፡ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በአጋጣሚዎች ክስተት፡ በሁኔታዎች መመቻቸት ነቢይ ነኝ ብለው የተነሱ ሰው አይደሉም፡፡ ገና ነቢይ ከመሆናቸውና ከመፈጠራቸው በፊት አስቀድሞ በነቢያት አንደበት ሁሉ ትንቢት የተነገረላቸው፡ ከቅዱስ ቁርኣን በፊት የነበሩ ቀደምት መለኮታዊ መጽሀፍት የተነበዩላቸው፡ የመጽሀፍቶቹ ሊቃውንት የነበሩትም በሚገባ የሚያውቋቸው የነበሩ ነቢይ ናቸው፡፡ ዝርዝሩንም እነሆ፡- ሀ. በነቢያት በኩል፡-
አላህ የላካቸው 124.000 የሚጠጉ ነቢያት በጠቅላላ ስለሳቸው ነቢይነት ተናግረዋል፡፡ ከጀመሪያው ሰው ከአደም አንስቶ እስከ መጨረሻው የእስራኤል መልክተኛ እስከሆነው እስከ ዒሳ ድረስ ያሉት ነቢያቶች ሁሉ (ዐለይሂሙ-ሰላም) ሲናገሩ የነበሩት ስለ ነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ነው፡፡ የሳቸውን ነቢይነት ሳይናገሩ፡ ለህዝቦቻቸውም ፡- በህይወት ከደረሳችሁባቸው አደራ ተከተሏቸው! ሳይሉና ሳያስጠነቅቁ የነቢይነት ማዕረግ የተሰጣቸው ነቢያት የሉም፡፡ ለዚህ እምነታችንም ቀጣዩን የቅዱስ ቁርኣን አንቀጽ እንደማስረጃ እናቀርባለን፡-
"وَإِذْ أَخَذَ اللَّهُ مِيثَاقَ النَّبِيِّينَ لَمَا آتَيْتُكُمْ مِنْ كِتَابٍ وَحِكْمَةٍ ثُمَّ جَاءَكُمْ رَسُولٌ مُصَدِّقٌ لِمَا مَعَكُمْ لَتُؤْمِنُنَّ بِهِ وَلَتَنْصُرُنَّهُ قَالَ أَأَقْرَرْتُمْ وَأَخَذْتُمْ عَلَى ذَلِكُمْ إِصْرِي قَالُوا أَقْرَرْنَا قَالَ فَاشْهَدُوا وَأَنَا مَعَكُمْ مِنَ الشَّاهِدِينَ " سورة آل عمران 81
"አላህ የነቢያትን ቃል ኪዳን፣ ከመጽሐፍና ከጥበብ ሰጥቻችሁ ከዚያም ከእናንተ ጋር ላለዉ (መጽሐፍ) የሚያረጋግጥ መልክተኛ ቢመጣላቸዉ፣ በርሱ በእርግጥ እንደምታምኑበት በእርግጥም እንድትረዱት ሲል በያዘ ጊዜ (አስታዉስ)፤ አረጋገጣችሁን? በይሃችሁ ላይ ኪዳኔን ያዛችሁምን? አላቸዉ፤ አረጋገጥን አሉ እንግዲያስ መስክሩ፤ እኔም ከእናንተ ጋር ከመስካሪዎቹ ነኝ አላቸዉ።" (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 81)፡፡
ይህ ጥቅስ በግልጽ እንደሚያስረዳው አላህ የላካቸውን ነቢያቶች በጠቅላላ መጽሐፍና ጥበብ እንደሰጣቸው ከገለፀ በኋላ አንድ በመሐላ የጠበቀ ቃል ኪዳን አስገብቶዋቸዋል፡፡ እሱም፡- ወደፊት አንድ መልክተኛ ይመጣል:: እሱም እናንተ ዘንድ ያለውን መጽሀፍ አረጋጋጭ (እውነት መሆኑን መስካሪ) ነው፡፡ ታዲያ ይህ መልክተኛ በሚመጣበት ጊዜ እናንተ በህይወት ሆናችሁ ብታገኙት በዚህ መልክተኛ አምናችሁ ከኋላው ተከትላችሁ ትረዱታላችሁ? በማለት፡፡
እነሱም፡- አዎ ጌታችን ሆይ! በቃል ኪዳኑ ገብተናል አረጋግጠንማል በማለት መለሱ፡፡ ዋናው የሚነሳው ጥያቄ፡- ይህ ይመጣል የተባለው መልክተኛ ማን ነው? የሚለው ነው፡፡ ለዚህም ጥያቄ ምንም ሳንጠራጠር የምንመልሰው መልስ ነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ናቸው የሚል ነው፡፡ ማረጋገጫችንም ቀጣዩ አሠር (ከሶሐቦች የተገኘ ንግግርና ተግባር) ነው፡-
عن علي قال: "لم يبعث الله له نبيا آدم فمن بعده إلا أخذ عليه العهد في محمد صلى الله عليه وسلم، لئن بعث وهو حي ليؤمنن به ولينصرنه ويأمره فيأخذ العهد على قومه ثم تلا: {وَإِذْ أَخَذَ اللَّهُ مِيثَاقَ النَّبِيِّينَ لَمَا آتَيْتُكُمْ مِنْ كِتَابٍ وَحِكْمَةٍ} الآية، كنز العمال في سنن الأقوال والأفعال 4296
ዐሊይ ኢብኑ አቡ-ጧሊብ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላሉ፡- "አላህ አደምንም ሆነ ከሱ በኋላ ያሉትን ነቢያትን በሙሐመድ (ዐለይሂ ሶላቱ ወሰላም) ላይ ቃል ቢያስገባቸው እንጂ እንዲሁ አልላካቸውም፡፡ እሱም፡- እሳቸው ነቢይ ሆነው ሲላኩ ያ የቀደመው ነቢይ በህይወት ቢያገኛቸው ሊያምንባቸውና ከኋላቸው ሆኖ ሊረዳቸው፡ እንዲሁም ህዝቦቹን፡ እሳቸው ላይ በህይወት ከደረሱባቸው አምነው እንዲከተሏቸው እንዲያዛቸው ነው፡፡ ከዛም ዐሊይ ለማረጋገጫነት የቁርኣኑን አንቀጽ አነበቡ" (ከንዙል-ዑምማል ፊ-ሱነኒል አቅዋል 4296)፡፡
አንዳንድ ነቢያትን በስም ጠቅሰን ስለ ነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) የተናገሩትንም እንመልከት ከተባለ፡ ሶስት ነቢያትን እንመልከት፡-
-ኢብራሂምና ልጁ ኢስማዒል (ዐለይሂማ-ሰላም)፡-
"رَبَّنَا وَابْعَثْ فِيهِمْ رَسُولًا مِنْهُمْ يَتْلُو عَلَيْهِمْ آيَاتِكَ وَيُعَلِّمُهُمُ الْكِتَابَ وَالْحِكْمَةَ وَيُزَكِّيهِمْ إِنَّكَ أَنْتَ الْعَزِيزُ الْحَكِيمُ " سورة البقرة 129
"ጌታችን ሆይ! በውስጣቸውም ከነሱው የኾነን መልክተኛ በነርሱ ላይ አንቀጾችህን የሚያነብላቸውን መጽሐፍንና ጥበብንም የሚያስተምራቸውን (ከክህደት) የሚያጠራቸውንም ላክ፤ አንተ አሸናፊው ጥበበኛው አንተ ብቻ ነህና» (የሚሉም ሲኾኑ)፡፡" (ሱረቱል በቀራህ 129)፡፡
ከዚህ የቁርኣን ጥቅስ የምንረዳው ኢብራሂምና ልጁ ኢስማዒል (ሰላም በሁለቱም ላይ ይሁን) የአላህን ቤት ካዕባን ከገነቡ በኋላ ወደ ጌታቸው ዱዓእ አድርገዋል፡፡ ከነሱ ጎሳ የሆነ አንድ መልክተኛ እንዲያስነሳላቸው የጸለዩት ነው፡፡ ያም መልክተኛ ነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ሆኑና የኢብራሂምና የልጁም ዱዓእ ተቀባይነትን አገኘ፡፡
عَنِ الْعِرْبَاضِ بْنِ سَارِيَةَ الْفَزَارِيِّ، قَالَ: سَمِعْتُ رَسُولَ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ يَقُولُ: " إِنِّي عِنْدَ اللَّهِ مَكْتُوبٌ بِخَاتَمِ النَّبِيِّينَ، وَإِنَّ آدَمَ لَمُنْجَدِلٌ فِي طِينَتِهِ، وَسَأُخْبِرُكُمْ بِأَوَّلِ ذَلِكَ: دَعْوَةُ أَبِي إِبْرَاهِيمَ، وَبِشَارَةُ عِيسَى، وَرُؤْيَا أُمِّيَ الَّتِي رَأَتْ..."صحيح ابن حبان 6404
ዒርባድ ኢብኑ ሳሪያህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ባስተላለፈው ሐዲሥ ውስጥ ነብያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) እንዲህ አሉ፡- “እኔ አላህ ዘንድ የነቢያት መደምደሚያ ሆኜ ተጽፌአለሁ፡፡ አደም ጭቃ ሁኖ ሳለ እንኳ (ነብይነቴ ተወስኖ ነበር) ስለዚህ ጉዳይ እነግራችኋለሁ፡፡ እኔ የኢብራሂም ልመና፡ የዒሳ ብስራት፡ የእናቴም ህልም ነበርኩ፡፡” (ሶሒሕ ኢብኑ ሒባን 6404)፡፡
ከላይ የተጠቀሰውን ቁርኣን ነቢዩ ራሳቸው ተርጉመውታል፡፡ ከእሳቸው በላይ ቁርኣንን ለመተርጎም ስልጣን ያለው ማንም የለም፡፡ የዒሳ ብስራት ነኝ ያሉት ደግሞ ተከታዩን የቁርአን አንቀጽ በማመላከት ነበር፡-
" وَإِذْ قَالَ عِيسَى ابْنُ مَرْيَمَ يَا بَنِي إِسْرَائِيلَ إِنِّي رَسُولُ اللَّهِ إِلَيْكُمْ مُصَدِّقًا لِمَا بَيْنَ يَدَيَّ مِنَ التَّوْرَاةِ وَمُبَشِّرًا بِرَسُولٍ يَأْتِي مِنْ بَعْدِي اسْمُهُ أَحْمَدُ فَلَمَّا جَاءَهُمْ بِالْبَيِّنَاتِ قَالُوا هَذَا سِحْرٌ مُبِينٌ " سورة الصف 6
“የመርየም ልጅ ኢሳ፡- የእስራኤል ልጆች ሆይ እኔ ከተውራት በፊት ያለውን የማረጋግጥና ከእኔ በኋላ በሚመጣው መልክተኛ ስሙ አሕመድ በሆነው የማበስር ስሆን ወደ እናንተ (የተላክሁ) የአላህ መልክተኛ ነኝ ባለ ጊዜ(አስተውስ)…” (ሱረቱ-ሶፍ 6)፡፡
Click and Like ➤➤ https://www.facebook.com/Ustaz.Abuhyder
Join us➤ t.me/abuhyder
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
ኡስታዝ አቡ ሀይደር ተገኝቶ ዳእዋ ባደረገበት በሀዋሳው መድረክ 12 ሰዎች ሸሀዳ ተቀብለዋል አላሁ አክበር!
https://youtu.be/rbJvnEf_hMI
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
ኢስላም ብቸኛው መለኮታዊ ሀይማኖት በኡስታዝ አቡ ሐይደር በ ዲላ ከተማ
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
ኢሳ የአላህ ቃል ነው?

ምላሽ ድንቅ ምላሽ በኡስታዝ አቡ ሐይደር
ለተጨማሪ ትምህርቶች
http://tttttt.me/abuhyder