ስንክሳር
7.32K subscribers
825 photos
4 videos
37 files
237 links
በስንክሳር channal ስንክሳሩ ተገልጦ ቅዱሳን ይዘከራሉ፣ ወቅቱን የጠበቁ መረጃዎችን ያገኛሉ፡፡ ይከታተሉን!
Download Telegram
እንኩዋን ለጌታችን ቅዱስ #ዕፀ_መስቀል የተአምር በዓል በሰላም አደረሳችሁ
#ቅዱስ_ዕፀ_መስቀል +"+
የዕፀዋት ሁሉ ንጉሣቸው የሚሆን ቅዱስ ዕፀ መስቀል
ለእኛም #ኃይላችን: #ቤዛችን: #መዳኛችን: #የድል_
ምልክታችን ነው:: መስቀል #በደመ_ክርስቶስ ተቀድሷልና
አንክሮ: ስግደት ክብርና ምስጋና በፀጋ ይገባዋል::
#ቅዱስ_መስቀለ_ክርስቶስ ላለፉት 2,000 ዓመታት ብዙ
ተአምራትን ሠርቷል:: ከእነዚህ መካከልም አንዱን በዚህ
ዕለት እናዘክራለን:: ታሪኩ: ምሥጢሩስ እንደ ምን ነው
ቢሉ:- በ400 ዓ/ም አካባቢ በግብፅ #አባ_ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ
ሳለ: #ቅዱስ_ቄርሎስም በሊቀ ዲቁና ሲያገለግል ሳለ
በእስክንድርያ ከተማ 2 ደሃ ክርስቲያኖች ይኖሩ ነበር:: የቀን
ሠራተኞች በመሆናቸው ከዕለት ምግብ አይተርፋቸውም
ነበር::
ከ2ቱ አንዱ ፍጹም አማኝ ሲሆን ሌላኛው ግን ተጠራጣሪ
ነበር:: ስለ ምን ነው ቢሉ:- በከተማዋ ብዙ ሃብታም አይሁድ
ነበሩና እነሱን እየተመለከተ ነው:: ለእርሱ #ክርስትና ማለት
ገንዘብ መስሎታልና ዘወትር "ለምን ክርስቶስን እያመለክን ድሃ
እንሆናለን?" እያለ ያማርር ነበር::
"ያዛቆነ ሰይጣን . . . " እንደሚባለው አንድ ቀን ባልጀራውን "ለምን ክርስቶስን አንክደውም? (ሎቱ ስብሐት!) እርሱን ከማምለክ የተረፈን ድህነት ብቻ ነው" አለው:: ባልንጀራው ሊመክረው ሞከረ:-
"እግዚአብሔር አምላከ-ነዳያን ነው:: ቅዱሳን #ነቢያት :
#ሐዋርያት : #ጻድቃን: #ሰማዕታትም በሥጋዊ ሃብት ነዳያን
ነበሩ" ብሎ ቢለውም ሰይጣን ሠልጥኖበታልና
አልሰማውም:: ያ ስሑት ደሃ ወዲያው ወጥቶ ወደ ማሕበረ አይሁድ ሔደ::
እነርሱ በቁጥር ብዙ ሁነው በአንድነት ይኖሩ ነበር::
"ሥራ ቅጠሩኝ" አላቸው:: "በእምነት አትመስለንምና
አይሆንም" አሉት:: ያን ጊዜ ለአለቃቸው ( #ፈለስኪኖስ)
"አንተ ሥራ ቅጠረኝ እንጂ እኔ ክርስቶስን እክዳለሁ" (ሎቱ
ስብሐት!) አለው::
ወዲያው የከተማው ሕዝብ ተጠርቶ: በጉባኤ መካከል
ሊያስክዱት ተዘጋጁ:: በፍጥነትም #መስቀል: ጦር: ሐሞት
አዘጋጁ:: ስዕለ ስቅለቱንም አመጡ:: ያን ደሃ ከሃዲም
"በል-ክርስቶስ ሆይ! ካድኩህ ብለህ ምራቅህን ትፋበት:
ሐሞቱን አፍስበት: በጦርም ውጋው" (ሎቱ ስብሐት!)
አሉት::
ያ ልቡ የደነቆረ መስቀለ ክርስቶስ ላይ ተፋ:: ሐሞትም
አፈሰሰበት:: በመጨረሻ በጦር ሲወጋው ግን ድንቅ ተአምር
ተገለጠ:: በጦር ከተወጋው ከመስቀሉ ጐን ብዙ ደም
ፈሰሰ:: ለረዥም ሰዓትም አላቁዋረጠም:: በዚህች ሰዓት
በአካባቢው የነበሩ ሁሉም አይሁድ በግንባራቸው ተደፍተው
ለክርስቶስና ቅዱስ መስቀሉ ሰገዱ::
ሁሉም በአንድነት "#ክርስቶስ_የአብርሃም_አምላክ_ነው
:: #መድኃኒትም_ነው " ሲሉ እየጮሁ ተናገሩ:: ባለማወቅ
ስላደረጉት እነርሱ ምሕረትን ሲያገኙ ያ አዕምሮ የጐደለውን
ደሃ ግን ዘወር ብለው ሲያዩት ወደ ድንጋይነት ተቀይሮ ነበር::
ነፍሱንም: ሥጋውንም በፈቃዱ አጠፋ::
የአይሁድ አለቃም ዐይነ ሥውር ዘመድ ነበረውና ወዲያው
አምጥቶ ከደሙ ቢቀባው ዐይኑ በራ:: ታላቅ ደስታም በዚያ
ሥፍራ ተደረገ:: ነገሩን የሰሙት #ቅዱሳን #ቴዎፍሎስ እና
#ቄርሎስ ሲመጡ ደሙ ከመፍሰስ አላቆመም ነበር::
በተአምሩ ደስ ተሰኝተው: ከደመ ክርስቶስ ለበረከት ተቀቡ::
የፈሰሰውን #ቅዱስ_ደም ከነ አፈሩ አንስተው: መስቀሉን
በትከሻ ተሸክመው: በፍፁም እልልታና ዝማሬ ወስደው በቤተ
መቅደስ አኑረውታል:: የከተማዋ ሁሉም አይሁድም
በክርስቶስ አምነው ተጠምቀዋል::
#ቅዱሳን_ስምዖንና_ዮሐንስ
በቤተ ክርስቲያን ታሪክ አስደናቂ ታሪክ ካላቸው #ጻድቃን
እነዚህ 2ቱ ቅድሚያውን ይይዛሉ:: እርሱስ እንደ ምን ነው
ቢሉ:-
ቅዱሳኑ በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን ሶርያ አካባቢ ተወልደው
ያደጉ ክርስቲያኖች ናቸው::
ዘመዳሞች ከመሆናቸው ባሻገር አብረው ስላደጉ እጅጉን
ይፋቀሩ ነበር:: የዋሃንም ነበሩ:: ወጣት በሆኑ ጊዜ ትልቁ
#ዮሐንስ ሚስት አገባ:: ታዲያ አንድ ቀን ከጌታችን መቃብር
#ኢየሩሳሌም ደርሰው ሲመለሱ #ገዳመ_ዮርዳኖስ አካባቢ
ደረሱ:: እርስ በርሳቸውም "ይህ ገዳምኮ የመላእክት ማደሪያ
ነው" ተባባሉ::
በዚያውም መንነው ለመቅረት አሰቡ:: ፈረስና ንብረታቸውን
ለዘመዶቻቸው ልከው ጸሎት አደረሱ:: ፈቃደ እግዚአብሔርን
ሊረዱም ዕጣ ተጣጣሉ:: ዕጣውም "ወደ ገዳም ሒዱ"
የሚል ስለሆነ ተቃቅፈው ደስ አላቸው::
ወደ ገዳሙ ሲደርሱም አበ ምኔቱ #አባ_ኒቅዮስ ፈጣሪ
አዞት የገዳሙን በር ከፍቶ ጠበቃቸው:: ተቀብሎ
ሲያስገባቸውም አንድ ደግ መነኮስ ሲያልፍ: ቆቡ ቦግ ቦግ
እያለ እንደ ፋና ሲያበራ እና #መላእክት ከበውት አዩ::
ወዲያውም አበ ምኔቱን "እባክህ አመንኩሰን" አሉት::
እርሱም የአምላክ ፈቃድ ነውና በማግስቱ አመነኮሳቸው::
ፍቅረ ክርስቶስ ገዝቷቸዋልና በጥቂት ዓመታት ተጋድሎ
ከብቃት (ከጸጋ) ደረሱ:: 2ቱም ቆመው በፍቅር ሲጸልዩ
የብርሃን አክሊል በራሳቸው ላይ ይወርድ ነበር:: አካላቸውም
በሌሊት ያበራ ነበር::
እንዲህ ባለ ቅድስና ለዓመታት ቆይተው ከገዳሙ ወደ ጽኑ
በርሃ ሊሔዱ ስለ ፈለጉ የገዳሙ በር በራሱ ተከፈተ:: አበ
ምኔቱ አባ ኒቆን (ኒቅዮስ) እያነባ በጸሎት ሸኛቸው::
በበርሃም በጠባቡ መንገድ: በቅድስና ተጠምደው ለ29
ዓመታት ተጋደሉ:: በዚህ ሰዓት ግን 2ቱን የሚለያይ ምክንያት
ተፈጠረ::
#እግዚአብሔር ቅዱስ ስምዖን ወደ ከተማ እንዲገባ: ቅዱስ
ዮሐንስ ግን በዚያው እንዲቆይ አዘዘ:: 2ቱ ለረዥም ሰዓት
ተቃቅፈው ተላቅሰው ተለያዩ:: ከ50 ዓመታት በላይ
ተለያይተው አያውቁም ነበርና::
#ቅዱስ_ስምዖን ወደ ከተማ ሲገባ ክብሩን ይደብቅ ዘንድ
እንደ እብድ ሆነ:: በዚህ ምክንያትም የወቅቱ ከተሜዎች
ይንቁት: በጥፊም ይመቱት ነበር:: (እባካችሁ ብዙ
በየመንገዱ የወደቁ አባቶች አሉና እንጠንቀቅ!) ቅዱሱ ግን
ስለ እነርሱ ይጸልይ ነበር::
በከተማዋ የነበሩ እብዶችን ሁሉንም በተአምራት
ፈወሳቸው:: አንድ ቀን ግን ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች
ደብድበውት ደከመ:: የእግዚእብሔር መልአክ ወርዶ "ና
ልውሰድህ" ብሎ ዮሐንስን ከበርሃ: ስምዖንን ከከተማ
በዚህች ቀን ወሰዳቸው:: እነሆ ብርሃናቸው ዛሬም ድረስ
ለሚያምንበት ሁሉ ያበራል::
💚💛ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ 💛❤️
ለቤተ ክርስቲያን በንጹሕ ሕይወታቸው ካበሩላት ዐበይት ቅዱሳን አንዱ #ቅዱስ_ዱማድዮስ ነው:: እርሱ ወደ ክርስትና የመጣው ከባዕድ አምልኮ ሲሆን መሪው #መንፈስ_ቅዱስ ነው:: ጣዕመ ሕይወቱን ሲሰሙት ዕዝነ ልቡናን ደስ ያሰኛል::

ገና በወጣትነቱ እንደ #ሐዋርያት ሰብኮ አሕዛብን አሳምኗል:: እንደ #ጻድቃን አካሉ አልቆ አጥንቶቹ እስኪታዩ ተጋድሏል:: እርሱ #ድንግል: #ንጹሕ: #መነኮስ: #ባሕታዊና #ካህን ነው:: ግን ውዳሴ ከንቱን አምርሮ ይጠላል:: በዚህ ምክንያት ካደረበት አይውልም: ከዋለበትም አያድርም::
እርሱ በጸሎቱ የተዘጉ ማሕጸኖችን ከፍቷል:: ዕውራንን አብርቷል:: ለምጻሞችን አንጽቷል:: አንካሶችን አርትቷል:: በፈጣሪው ኃይል ፈሳሽ ወንዝን አቁሟል:: እንደ ገናም እንደ ነበረው መልሶታል::

የቅዱስ ዱማድዮስ መጨረሻው ደግሞ #ሰማዕትነት ነው:: በበዓቱ ውስጥ ሳለ ከደቀ መዝሙሩ ጋር ክፉዎች በድንጋይ ወግረው ገድለውታል:: ድንጋዩም የኮረብታ ያህል ነበር:: ልክ በዓመቱ በዚህች ዕለት ምዕመናን ሥጋውን አፍልሠዋል::
🌿🌿🌿🌿🌿🌿🌿🌿🌿🌿🌿🌿
ቸር አምላክ ከነቢያት: ሐዋርያት: ጻድቃንና ሰማዕታት ክብርን ያሳትፈን::
From:- dn yordanos abebe
@senkesar @senkesar