ስንክሳር
7.32K subscribers
825 photos
4 videos
37 files
237 links
በስንክሳር channal ስንክሳሩ ተገልጦ ቅዱሳን ይዘከራሉ፣ ወቅቱን የጠበቁ መረጃዎችን ያገኛሉ፡፡ ይከታተሉን!
Download Telegram
#ቅዱስ_ዲዮስቆሮስ_ሊቅ
ይህ አባት የተዋሕዶ ሃይማኖታችን ምሰሶ ነው:: በ5ኛው መቶ ክ/ዘ በግብጽ ተወልዶ አድጐ: በልጅነቱ
መጻሕፍትን ተምሮ: የምናኔ ሕይወትን መርጧል::
ቆይቶም የታላቁ ሊቅ #ቅዱስ_ቄርሎስ ረድእ ሆኖ
ተምሯል: አገልግሎታል::
+በጉባኤ #ኤፌሶን ጊዜም ቅዱስ ቄርሎስን ተከትሎ
ሒዶ ተሳትፏል:: በ444 ዓ/ም ታላቁን ሊቅ ተክቶ
የእስክንድርያ 25ኛ ፓትርያርክ ሆኖ ተሹሟል:: ለ7
ዓመታትም መጽሐፈ ቅዳሴውን (እምቅድመ ዓለምን)
ጨምሮ ብዙ ድርሰቶችን ደርሷል:: በመልካም እረኝነትም
ሕዝቡን ጠብቋል::
ዘመነ ሰማዕታትን ተከትሎ የመጣው የመናፍቃን ዘመን
ሲሆን ለ150 ዓመታት ያህል መናፍቃን እንደ አሸን
ፈልተዋል:: በዚያው ልክ ከዋክብት ቅዱሳን ሊቃውንት
ነበሩና በየጊዜው ጉባኤያትን እየሠሩ: መናፍቃንን
አሳፍረዋል:: ምዕመናንንም አጽንተዋል::
በ451 ዓ/ም የተፈጸመው ድርጊት ግን ዛሬም ድረስ
ጠባሳው የሚለቅ አልሆነም:: ንጉሡ መርቅያንና ዻዻሱ
ልዮን የንስጥሮስን ትምሕርት አለባብሰው ሊያስተምሩ
ሲሞክሩ ግጭት በመፈጠሩ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ
ጊዜ ወደ 2 ተከፈለች::
በጉባኤው የነበሩ 636 ዻዻሳት ስቃይና ሞትን ፈርተው
በኑፋቄ መጽሐፍ ላይ በመፈረማቸው
"መለካውያን" (ከእግዚአብሔር ይልቅ ለንጉሥ
የሚታዘዙ) ተባሉ:: ጉባኤውም "ጉባኤ
ከለባት" (የውሾች ስብሰባ): "ጉባኤ አብዳን" (የሰነፎች
ጉባኤ) ተብሏል::
ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ግን "በኑፋቄው ላይ አልፈርምም"
ከማለቱ አልፎ መናፍቃኑን አወገዛቸው:: በዚህ ምክንያት
ወደ ጋግራ ደሴት ከ7 ደቀ መዛሙርቱ ጋር አሳደዱት::
በዚያም ለ3 ዓመታት ቆይቶ በ454 ዓ/ም ዐረፈ::
ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ከማረፉ በፊት በተሰደደባት ደሴተ
#ጋግራ ለ3 ዓመታት ብዙ መከራ ከመናፍቃን ደርሶበታል:: እርሱ ግን በትእግስቱና በትምሕርቱ
ብዙዎችን ወደ ሃይማኖት መልሷል:: ቤተ ክርስቲያን እርሱን 'አበ ተዋሕዶ' (የተዋሕዶ
እምነት አባትና አርበኛ) ትለዋለች:: የተነጨ ጺሙ:
የረገፉ ጥርሶቹና የፈሰሰ ደሙ ዛሬም ድረስ ትልቅ ምስክርና የሃይማኖት ፍሬ ነውና::
"ያስተጻንዕ ህየ እለ ኀለዉ ደቂቀ:
ዘተነጽየ እምነ ጽሕሙ ወእም አስናኒሁ ዘወድቀ: ፍሬ ሃይማኖቱ ፈነወ ብሔረ ርሑቀ" እንዲል::
💚💛ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ 💛❤️
ቅዱስ ቄርሎስን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን " #ዓምደ_ሃይማኖት- የሃይማኖት ምሰሶ" ይሉታል:: ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

ሊቁ የተወለደው በእስክንድርያ (ግብጽ) በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: እናቱ የወቅቱ ፓትርያርክ #ቅዱስ_ቴዎፍሎስ እህቱ ነበረችና አጎቱ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ወስዶ አሳድጐታል:: ገና በልጅነቱ ወደ #አባ_ሰራብዮን ገዳም ገብቶ ቅዱሳት መጻሕፍትንና ገዳማዊ ሕይወትን ተምሯል:: በጾም: በጸሎትና በትሕትና የታሸ ነውና ሲማር አንድ ጊዜ ካነበበው በሕሊናው ተስሎ ይቀር ነበር::
ቅዱስ ቴዎፍሎስ "ምዕመናንን አስተምርልኝ" ብሎ ወደ ከተማ አመጣው:: #መንፈስ_ቅዱስ አድሮበታልና ሲያስተምር ወይ ደግሞ መጻሕፍትን ሲያነብ ከምዕመናን ወገን ስንኩዋን የሚያወራና የሚንቀሳቀስ ቀርቶ የሚቀመጥም አልነበረም:: ጣዕመ ስብከቱም ብዙዎችን ለወጠ::
ከዚያም በ412 ዓ/ም አጎቱ የነበረው ፓትርያርክ አባ ቴዎፍሎስ ሲያርፍ ዻዻሳትና ሊቃውንት በአንድነት ቅዱስ ቄርሎስን መረጡ:: የእስክንድርያም 24ኛ ሊቀ ዻዻሳት ሆኖ ተሾመ:: በዘመኑ #ቤተ_ክርስቲያን አበራች:: በቅድስናው: በሊቅነቱ: በስብከቱ: በድርሰቶቹና በትጋቱ በፍጹም አገለገላት::

በወቅቱ ስመ ክፉ መናፍቅ ንስጥሮስ ተነስቶ የእስያ አብያተ ክርስቲያናትን አወካቸው:: ትምሕርቱ ክርስቶስን "2 አካል: ባሕርይ ነው" (ሎቱ ስብሐት!) የሚል ነበር:: በእውነት እንየው ከተባለ ግን ጠቡና ጥላቻው ከድንግል ማርያም ጋር ነበር:: ምክንያቱም ጌታችንን ወደ 2 የከፈለው #እመቤታችንንየአምላክ እናት አይደለሽም ለማለት ነው:: (ላቲ ስብሐት!)
ነገሩን #ቅዱስ_ቄርሎስ በሰማ ጊዜ ወዳለበት ሒዶ ቢመክረውም ንስጥሮስ ሊሰማ አልፈለገም:: በዚህ ምክንያት በትንሹ ቴዎዶስዮስ (የቁስጥንጥንያ ንጉሥ) ትዕዛዝ በኤፌሶን ታላቅ ጉባኤ እንዲሰበሰብ ሆነ:: ይህ ጉባዔ በቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻው የተቀደሰ ጉባዔ ነው:: በ431 ዓ/ም #በኤፌሶን ከተማ የመናፍቃኑን ጥርቅም ሳንቆጥር ሃይማኖታቸው የቀና 200 #ቅዱሳን_ሊቃውንት ተገኙ::

የሚገባው ጸሎትና ሱባዔ ከተፈጸመ በሁዋላ ጉባዔው ተጀመረ:: አፈ ጉባዔው ሊቀ ማሕበር ማር (ቅዱስ) ቄርሎስ ነበርና በጉባዔ ፊት ንስጥሮስን ተከራክሮ ረታው:: ምላሽም አሳጣው:: ከቅዱሳት መጻሕፍት #ክርስቶስ አንድ ባሕርይ መሆኑን: #ድንግል_ማርያምም #ወላዲተ_አምላክ መሆኗን እየጠቀሰ: በምሳሌም እያሳየ አስረዳ::
የሰይጣን ማደሪያ ንስጥሮስ ግን እንቢ: አላምንም በማለቱ ተወግዞ ተለየ:: ቅዱሳን ሊቃውንቱም በቅዱስ ቄርሎስ አርቃቂነት 12 አንቀጾችን አዘጋጅተው ወደ ዓለም ሁሉ ላኩ:: እሊህ አንቀጾች ዛሬም በሊቃውንቱ እጅ አሉ:: ይነበባሉ: ይተረጎማሉ::

ከእነዚህም አንዱ ድንግል ማርያም " #ታኦዶኮስ(የእግዚአብሔር እናቱ) ናት" የሚል ነው:: እመቤታችንን:-
¤የአምላክ እናት:
¤ዘላለማዊት ድንግል:
¤ፍጽምት:
¤ንጽሕትና አማላጅ ብሎ ማመን ለሰማያዊ ርስት የሚያበቃ በጐ ሃይማኖት ነውና::
ጉባዔው ከተጠናቀቀ በሁዋላ ቅዱስ ቄርሎስ ንስጥሮስን ጠርቶ "በድንግል ማርያም እመን:: እርሷ ከልጇ ታስታርቅሃለች" ቢለው በድጋሚ "እንቢ" አለው:: ያን ጊዜ ሊቁ "ለአምላክ እናት ያልታዘዘ ምላስህ ላንተም አይታዘዝህ" ብሎ ረገመው:: ወዲያው ምላሱ ተጐልጉሎ ወጥቶ ደረቱ ላይ ወደቀ::
እንደ ውሻ እየተዝረከረከ ሒዶ ከወዳጆቹ ጋር ቁሞ ሳለ መሬት ተከፍታ ውጣዋለች::
ቅዱስ ቄርሎስ ግን ለ32 ዘመናት በመንበሩ ላይ አገልግሎ: ፍሬ ትሩፋት አፍርቶ: ብዙ ድርሰቶችንም ደርሶ በ444 ዓ/ም በዚህች ቀን ዐርፏል:: ከድርሰቶቹም ቅዳሴው: ድርሳነ ቄርሎስና ተረፈ ቄርሎስ ይጠቀሳሉ::

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአባቶቻችን ጸሎት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቅልን:: ከሊቁም በረከቱን ይክፈለን::
From:- d/n yordanos abebe

@senkesar @senkesar